የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w26 የካቲት ገጽ 20-25
  • ከተጠመቅክ በኋላ ሊያጋጥሙህ ለሚችሉ ፈተናዎች ተዘጋጅተሃል?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ከተጠመቅክ በኋላ ሊያጋጥሙህ ለሚችሉ ፈተናዎች ተዘጋጅተሃል?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2026
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት ቅር ቢያሰኙህ
  • ትተህ የመጣሃቸውን ነገሮች መናፈቅ ብትጀምር
  • ሌሎች ይሖዋን ቢተዉ
  • ይሖዋ “የተሰበረ ልብ ያላቸውን ይጠግናል”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2024
  • የማታውቋቸው ነገሮች እንዳሉ አምናችሁ በመቀበል ልካችሁን እንደምታውቁ አሳዩ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • ይሖዋ “ሕያው አምላክ” እንደሆነ አስታውስ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2024
  • እርስ በርስ መቀራረባችን ይበጀናል!
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2026
w26 የካቲት ገጽ 20-25

ከሚያዝያ 27–ግንቦት 3, 2026

መዝሙር 99 እልፍ አእላፋት ወንድሞች

ከተጠመቅክ በኋላ ሊያጋጥሙህ ለሚችሉ ፈተናዎች ተዘጋጅተሃል?

“አረማመዴ በመንገድህ ላይ ይጽና።”—መዝ. 17:5

ዓላማ

በቅርቡ የተጠመቁ ክርስቲያኖች በእውነት ቤት ውስጥ ሊያጋጥሟቸው ለሚችሉ ፈተናዎች መዘጋጀት የሚችሉት እንዴት ነው?

1-2. በእውነት ቤት ውስጥ ሊያጋጥሙን ለሚችሉ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለመዘጋጀት ምን ማድረግ እንችላለን? በምሳሌ አስረዳ።

በሰይጣን ዓለም ውስጥ ስንኖር ፈተናዎች እንደሚያጋጥሙን እንጠብቃለን። ኢየሱስም ቢሆን “ማሰናከያ መምጣቱ የማይቀር ነው” ሲል ለደቀ መዛሙርቱ በግልጽ ነግሯቸዋል። (ማቴ. 18:7) ይህን በአእምሯችን በመያዝ ለሚያጋጥሙን ፈተናዎች መዘጋጀት ይኖርብናል። ከእነዚህም መካከል በጉባኤ ውስጥ የሚያጋጥሙን ፈተናዎች ይገኙበታል።

2 ሁኔታውን ለማስረዳት አንድ ምሳሌ እንመልከት። እኛ የይሖዋ ሕዝቦች ለተፈጥሮ አደጋዎች እንድንዘጋጅ እንበረታታለን። እንዲህ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ፣ እኛ በምንኖርበት አካባቢ ምን ዓይነት አደጋ ሊከሰት እንደሚችል ለማወቅ ጥረት እናደርጋለን። በተለይ ደግሞ ለአካባቢው አዲስ ከሆንን እንዲህ ማድረጋችን በጣም አስፈላጊ ነው። ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎችን ካወቅን በኋላ እያንዳንዱ አደጋ ቢደርስ ምን እንደምናደርግ ዕቅድ በማውጣት እንዘጋጃለን። (ምሳሌ 21:5) በተመሳሳይም በእውነት ቤት ውስጥ ሊያጋጥሙን የሚችሉ ተፈታታኝ ሁኔታዎችን ማወቅ ይኖርብናል፤ ከዚያም እነዚህ ፈተናዎች ሲያጋጥሙን ምን እንደምናደርግ ከአሁኑ መዘጋጀት እንችላለን። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ እነዚህን ፈተናዎች በተሻለ ሁኔታ መቋቋምና ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና ጠብቀን መኖር እንችላለን። (መዝ. 17:5) በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ ሊያጋጥሙን የሚችሉ ሦስት ተፈታታኝ ሁኔታዎችንና ለእነዚህ ፈተናዎች መዘጋጀት የምንችልበትን መንገድ እንመለከታለን።a

አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት ቅር ቢያሰኙህ

3. በጉባኤ ውስጥ ምን ተፈታታኝ ሁኔታ ሊያጋጥመን ይችላል?

3 ለመጀመሪያ ጊዜ በጉባኤ ስብሰባ ላይ ተገኝተህ በይሖዋ ሕዝቦች መካከል ያለውን ፍቅር ስትመለከት ምን እንደተሰማህ ታስታውሳለህ? እውነትን እንዳገኘህ ያሳመነህ እሱ ሊሆን ይችላል። (ዮሐ. 13:35፤ ቆላ. 3:12) ብላንካምb እንዲህ ተሰምቷት ነበር። ሆኖም ከተጠመቀች በኋላ ያልጠበቀችው ነገር አጋጠማት። እንዲህ ብላለች፦ “አንዲት እህት ደግነት የጎደለው ነገር አደረገችብኝ። ይህችው እህት ስለ ሌሎች አሉታዊ ነገር እንደምታወራም አስተዋልኩ። እንዲህ ያለ ነገር ይገጥመኛል ብዬ አልጠበቅኩም ነበር። ምክንያቱም በጥናቴ ላይ የተማርኩት የይሖዋ ሕዝቦች ሰላማዊና አፍቃሪ ለመሆን ጥረት እንደሚያደርጉ ነው።” እርግጥ ነው፣ ወንድሞችህና እህቶችህ ክርስቲያናዊ ባሕርያቸውን ለማሻሻል ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ። ሆኖም የይሖዋ ሕዝቦች ፍጹማን አይደሉም። (ኤፌ. 4:23, 24፤ 1 ዮሐ. 1:8) በመሆኑም የሆነ ወቅት ላይ ስሜትህን የሚጎዳ ነገር መናገራቸው ወይም ማድረጋቸው አይቀርም። (ያዕ. 3:8) የሚያሳዝነው፣ አንዳንዶች እንዲህ ባለው ሁኔታ ተሰናክለው ይሖዋን ማገልገላቸውን አቁመዋል።

4. አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት ቅር ቢያሰኙን ሁኔታውን በጥሩ መንገድ ለመያዝ ከወዲሁ መዘጋጀት የምንችለው እንዴት ነው? (ኤፌሶን 4:32)

4 አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት ስሜትህን የሚጎዳ ወይም ቅር የሚያሰኝ ነገር ቢያደርጉብህ ሁኔታውን በጥሩ መንገድ ለመያዝ ከአሁኑ መዘጋጀት የምትችለው እንዴት ነው? በኤፌሶን 4:32 ላይ የሚገኘውን ምክር ሁሌም ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት አድርግ። (ጥቅሱን አንብብ።) ደግና ሩኅሩኅ ለመሆን አቅምህ የፈቀደውን ሁሉ የምታደርግ ከሆነ ከሌሎች ጋር አላስፈላጊ ግጭት ውስጥ የመግባትህ አጋጣሚ ይቀንሳል። ሌሎች የሚሠሯቸውን ስህተቶች በነፃ ይቅር ለማለት አስቀድመህ ወስን። እንዲህ ለማድረግ ምን ይረዳሃል? ይሖዋ ይቅር እንዲልህ ስንት ጊዜ እንደምትጠይቀውና እሱም ምን ያህል ጊዜ በነፃ ይቅር እንዳለህ አስብ። (ማቴ. 6:12) ይሖዋ ባሳየህ ሰፊ ይቅርታ ላይ ካሰላሰልክ ሌሎችን ይቅር ማለት ቀላል ይሆንልሃል።

5. አንድ ሰው ቅር የሚያሰኝ ነገር ሲያደርግብን የትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት ይረዳናል? (ምሳሌ 19:11) (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)

5 ምሳሌ 19:11ን አንብብ። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው፣ ጥልቅ ማስተዋልc ሌሎች ቅር የሚያሰኝ ነገር ሲያደርጉብን ቶሎ እንዳንቆጣ ይረዳናል። ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት ሪማን ረድቷታል፤ ሪማ የተጠመቀችው ከጥቂት ዓመታት በፊት ነው። እንዲህ ብላለች፦ “ወንድሞችና እህቶች ስሜትን የሚጎዳ ወይም ቅር የሚያሰኝ ነገር ሲያደርጉ ምሳሌ 19:11ን ቶሎ ለማስታወስ ጥረት አደርጋለሁ። ያሉበትን ሁኔታና ያሳለፉትን ሕይወት ከግምት በማስገባት እንዲህ ያለ ነገር ያደረጉት ለምን እንደሆነ ለማሰብ እሞክራለሁ። በአገልግሎት አብሬያቸው ለመካፈልም ጥረት አደርጋለሁ። እንዲህ ማድረጌ የበለጠ እንዳውቃቸው ይረዳኛል።” እኛም እንዲህ ማድረግ እንችላለን። ከአሁኑ ወንድሞችህንና እህቶችህን የበለጠ ለማወቅ ጥረት ማድረግ ትችላለህ። ይበልጥ በተረዳሃቸው መጠን፣ ስሜትህን የሚጎዳ ነገር ቢያደርጉብህ እንኳ እነሱን ይቅር ማለት ይበልጥ ቀላል ይሆንልሃል።

ሥዕሎች፦ 1. አንድ ወንድም በስብሰባ አዳራሽ የጥገና ሥራ ሲካፈል አብሮት የሚሠራው ወንድም በተናገረው ነገር ቅር ይሰኛል። 2. ቅር የተሰኘው ወንድም በኋላ ላይ ከዚያ ወንድም ጋር ከቤት ወደ ቤት ያገለግላል።

ከአንድ ክርስቲያን ጋር አለመግባባት ካጋጠመህ አብረኸው ለማገልገል ጥረት አድርግ (አንቀጽ 5ን ተመልከት)


6. ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረን ምን ይረዳናል?

6 በጉባኤ ውስጥ ካሉ ክርስቲያኖች ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖርህ ምን ማድረግ ትችላለህ? ወንድሞችህንና እህቶችህን ይበልጥ እያወቅካቸው ስትሄድ በመልካም ባሕርያቸው ላይ ለማተኮር ጥረት አድርግ። (ከምሳሌ 10:12 ጋር አወዳድር፤ ሮም 12:10፤ ፊልጵ. 2:2, 3) ማርክ የተባለ በቅርቡ የተጠመቀ ወንድም እንዲህ ማድረጉ የረዳው እንዴት እንደሆነ እንመልከት። በጉባኤው ውስጥ ካሉ ወንድሞችና እህቶች ጋር ብዙ ጊዜ ሲያሳልፍ እንከኖቻቸውን ማስተዋል ጀመረ። ታዲያ ማርክ በዚህ እንዳይሰናከል የረዳው ምንድን ነው? እንዲህ ብሏል፦ “ትኩረት እያደረግኩ ያለሁት በትናንሽ ስህተቶች ላይ እንደሆነ አስተዋልኩ። በዓለም ያሉ ሰዎች ከሚፈጽሟቸው ኃጢአቶች አንጻር ደግሞ እነዚህ ስህተቶች እዚህ ግቡ የማይባሉ ናቸው። የእምነት አጋሮቼ ባሉባቸው እንከኖች ላይ መብሰልሰል እንደሌለብኝ ግልጽ ሆነልኝ። በመሆኑም በመልካም ባሕርያቸው ላይ ትኩረት ማድረግ ጀመርኩ።” አንተም እንዲህ የምታደርግ ከሆነ ከወንድሞችህና ከእህቶችህ ጋር ጥሩ ግንኙነት ይኖርሃል።

ትተህ የመጣሃቸውን ነገሮች መናፈቅ ብትጀምር

7. ትተን የመጣነውን ነገር እንድንናፍቅ የሚያደርገን ምን ሊሆን ይችላል?

7 እውነትን በሰማህበት ወቅት ክፉ ከሆነው የሰይጣን ዓለም በመላቀቅህ በጣም ተደስተህ እንደሚሆን ምንም ጥያቄ የለውም። ምናልባትም ‘ሰው እንዴት ይህን ሊናፍቅ ይችላል?’ ብለህ አስበህ ይሆናል። ሆኖም ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙህ ይሖዋን ለማገልገል ብለህ የተውካቸውን ነገሮች ማስታወስ አልፎ ተርፎም መናፈቅ ልትጀምር ትችላለህ። (ከዘኁልቁ 11:4-6 ጋር አወዳድር።) ለምሳሌ አንዳንድ ወንድሞች የቀድሞ ሥራቸው በማኅበረሰቡ ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ቢሆንም አብዛኛውን ጊዜያቸውን ስለሚይዝባቸው ትተውታል። ሌሎች ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ሲጀምሩ የቅርብ ጓደኞቻቸው ርቀዋቸዋል። ወደ እውነት ሲመጡ አንዳንድ ሱሶችን መተው ያስፈለጋቸውም አሉ፤ እነዚህ ሱሶች ርኩስ ቢሆኑም በተወሰነ መጠን ደስታ ያስገኙላቸው ነበር። አንድ ክርስቲያን ትቶት የመጣው ማንኛውም ነገር ከይሖዋ እንዲያርቀው ቢፈቅድ ምንኛ የሚያሳዝን ይሆናል! ታዲያ ወደፊት ምንም ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥምህ ትተህ ወደመጣኸው ነገር እንዳትመለስ ከአሁኑ ምን ማድረግ ትችላለህ?

8. አብርሃምና ሣራ ከተዉት ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን?

8 መጽሐፍ ቅዱስ ትተውት የመጡትን ነገር ሊናፍቁ ይችሉ የነበሩ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮችን ምሳሌ ይዟል። ለምሳሌ አብርሃምና ሣራ የይሖዋን ትእዛዝ በመከተል በቅጥር የተከበበች ከተማ ከነበረችው ከዑር ወጥተው በድንኳን መኖር ጀምረዋል። (ዕብ. 11:8, 9) በዑር የነበራቸውን የተመቻቸ ሕይወት አልፎ አልፎ አስታውሰው ሊሆን እንደሚችል ምንም ጥያቄ የለውም። ሆኖም ትተው የመጡትን ነገር “ሁልጊዜ ቢያስቡ” ወይም ቢናፍቁ ኖሮ ወደዚያ ሕይወት ለመመለስ ሊፈተኑ ይችሉ ነበር። እነሱ ግን በወደፊቱ ጊዜ ላይ አተኩረዋል።—ዕብ. 11:15, 16

9. ሐዋርያው ጳውሎስ ለተዋቸው ነገሮች ምን አመለካከት ነበረው? (ፊልጵስዩስ 3:7, 8, 13)

9 ሐዋርያው ጳውሎስ ይሖዋን ለማገልገል ሲል የሕይወት ጎዳናውን ቀይሯል። ጳውሎስ ክርስቲያን ከመሆኑ በፊት በጣም የተከበረ የሕጉ አስተማሪ ከነበረው ከገማልያል ተምሯል። (ሥራ 22:3) ጳውሎስ በአይሁዳውያን ሃይማኖት የላቀ ቦታ ላይ የመድረስ አጋጣሚ ነበረው። (ገላ. 1:13, 14) ሆኖም ምሥራቹን ሲቀበል ይህን ሁሉ ነገር ተወ። ታዲያ ጳውሎስ ክርስቲያን ከሆነ በኋላ ሕይወቱ አልጋ በአልጋ ነበር? በፍጹም! ተደብድቧል፤ ታስሯል፤ እንዲሁም የገዛ ወገኖቹ ጠልተውታል። (2 ቆሮ. 11:23-26) በእነዚህ ፈተናዎች ላይ ብቻ ቢያተኩርና የአሁኑን ሕይወቱን ከቀድሞ ሕይወቱ ጋር ቢያነጻጽር ኖሮ ‘ክርስቲያን ባልሆን ይሻለኝ ነበር’ ብሎ ሊያስብ ይችል ነበር። ነገር ግን ጳውሎስ ያተኮረው ክርስቶስ ኢየሱስን የማገልገል መብቱ ባለው ውድ ዋጋ እንዲሁም ወደፊት በሚጠብቀው ክብራማ ሕይወት ላይ ነው። ጳውሎስ እነዚህ በረከቶች ከከፈላቸው መሥዋዕቶች በእጅጉ እንደሚበልጡ እርግጠኛ ነበር።—ፊልጵስዩስ 3:7, 8, 13ን አንብብ።

10. በምን ላይ አዘውትረን ማሰላሰል ይኖርብናል? (ማርቆስ 10:29, 30) (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)

10 ከዚህ ምን ትምህርት ማግኘት ትችላለህ? ክርስቲያን ለመሆን ስትል የተውካቸው ነገሮች ወደ አእምሮህ ሲመጡ እነዚህን ነገሮች የተውካቸው ለምን እንደሆነም ለማስታወስ ሞክር። (መክ. 7:10) የተውካቸውን ነገሮች ወደ እውነት በመምጣትህ ካገኘሃቸው በረከቶች ጋር አወዳድራቸው። ከጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ጌታ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረት ችለሃል። (ምሳሌ 3:32) አፍቃሪ በሆነ መንፈሳዊ ቤተሰብ ተከበሃል። (ማርቆስ 10:29, 30ን አንብብ።) እንዲሁም ከፊትህ አስደናቂ የሆነ ተስፋ ይጠብቅሃል! (ኢሳ. 65:21-23) ይሖዋን ማገልገል በሚያስገኛቸው በረከቶች ላይ አዘውትረህ ካሰላሰልክ ትተህ የመጣሃቸውን ነገሮች የመናፈቅህ አጋጣሚ ይቀንሳል።

ትተህ የመጣሃቸውን ነገሮች ከመናፈቅ ይልቅ አምላክ በሰጠህ ውድ የአገልግሎት መብት ተደሰት (አንቀጽ 10ን ተመልከት)e


11. ከሮዝሜሪ ተሞክሮ ምን ትምህርት አግኝተሃል?

11 ሮዝሜሪ የተባለች እህት የተጠመቀችው በ50ዎቹ ዕድሜ ውስጥ እያለች ነው። ትታ የመጣቻቸውን ነገሮች ላለመናፈቅ ምን እንዳደረገች እንመልከት። እንዲህ ብላለች፦ “መጀመሪያ ላይ የገና በዓል ይናፍቀኝ ነበር፤ ምክንያቱም ከቤተሰቤ ጋር አስደሳች ጊዜ የማሳልፍበት ወቅት ነው። ለቤተሰቦቼ ስጦታ መስጠት በጣም ያስደስተኛል። ልጆቹ በገና ዛፍ ዙሪያ ተሰብስበው ስጦታቸውን ሲከፍቱ የሚሰማቸውን ደስታ ማየት ልዩ ስሜት ይፈጥርብኝ ነበር።” ታዲያ የረዳት ምንድን ነው? ሮዝሜሪ እንዲህ ብላለች፦ “የገና በዓልን የሚተካልኝ ነገር አግኝቻለሁ። በየዓመቱ ሌላ ቀን ላይ ቤተሰቦቼን ጠርቼ ስጦታ እሰጣቸዋለሁ፤ እንዲሁም የምወድላቸውን ነገር እነግራቸዋለሁ።” ሮዝሜሪ ሌላ ተፈታታኝ ሁኔታም አጋጥሟታል። እንዲህ ብላለች፦ “እውነትን ስማር የቀድሞ ጓደኞቼ ራቁኝ። አንዳንድ ጊዜ ስለሚናፍቁኝ ብቸኝነት ይሰማኝ ነበር።”d ታዲያ የረዳት ምንድን ነው? ከተለያዩ እህቶች ጋር ተቀጣጥራ ማገልገል ጀመረች። “እንዲህ ማድረጌ የምወዳቸውና የማደንቃቸው አዳዲስ ጓደኞች እንዳፈራ ረድቶኛል” ብላለች። አንተስ ከእሷ ተሞክሮ ምን ትምህርት ማግኘት ትችላለህ? እውነትን ከመስማትህ በፊት ያስደስትህ የነበረ አንድ ነገር ሊናፍቅህ ይችላል። ሆኖም የሚናፍቅህን ነገር ይሖዋን በሚያስደስት ሌላ ነገር መተካት እንደምትችል ምንም ጥያቄ የለውም። (ፊልጵ. 4:8, 9) ደግሞም ይህን አስታውስ፦ ይሖዋ ምንጊዜም ቢሆን ካጣነው ነገር የበለጠ ነገር ይሰጠናል።

ሌሎች ይሖዋን ቢተዉ

12. በጉባኤ ውስጥ በጣም ፈታኝ የሆነ ምን ችግር ሊከሰት ይችላል?

12 የይሖዋ ምሥክር በሆንክበት ወቅት፣ ብልሹ ከሆነው ዓለም ወጥተህ መንፈሳዊና ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናቸውን ለመጠበቅ ጥረት ከሚያደርጉ ሰዎች ጋር በመቀላቀልህ ተደስተህ መሆን አለበት። (ኢሳ. 65:14) ይሁንና አንዳንድ ጊዜ በጉባኤው ውስጥ ኃጢአት እንደተፈጸመ ትሰማ ይሆናል። እንዲያውም አንዳንዶች ከጉባኤው ሊወገዱ ይችላሉ። (1 ቆሮ. 5:13) ሳማር የተባለች እህት እንዲህ ያለው ሁኔታ ምን ስሜት እንደፈጠረባት ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “ከተጠመቅኩ ብዙም ሳይቆይ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ ከባድ ኃጢአት ፈጽሞ ከጉባኤው ተወገደ። አንድ ሽማግሌ በይሖዋና በጉባኤው ላይ ኃጢአት ሊፈጽም ይችላል ብዬ ፈጽሞ ስላልጠበቅኩ ልሰናከል ተቃርቤ ነበር።” እርግጥ ነው፣ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ይሖዋን እንደሚወዱና ለእሱ ታማኝ መሆን እንደሚፈልጉ ምንጊዜም ልንተማመን ይገባል። (1 ቆሮ. 13:4, 7) ያም ቢሆን እውነታውን አምነን መቀበል ይኖርብናል፤ በየዓመቱ አንዳንድ ክርስቲያኖች ከጉባኤው ይወገዳሉ። በተለይ መጥፎ አካሄድ ለመከተል የመረጠው የምትቀርበው ወይም የምታከብረው ሰው ከሆነ ሁኔታው ይበልጥ ሊከብድህ ይችላል።

13. አንድ የምንቀርበው ሰው ይሖዋን ቢተው እንዳንሰናከል ከወዲሁ ራሳችንን ማጠናከር የምንችለው እንዴት ነው?

13 አንድ የምትቀርበው ሰው ይሖዋን ቢተው እንዳትሰናከል ከወዲሁ መዘጋጀት የምትችለው እንዴት ነው? ከይሖዋ ጋር ያለህን የግል ዝምድና ማጠናከርህን ቀጥል። (ያዕ. 4:8) ከአምላክ ጋር ያለህ ወዳጅነት በሌላ ሰው ታማኝነት ላይ የተመካ እንዲሆን አትፍቀድ። ለምሳሌ በቤተሰብና በጉባኤ ሆነን አምልኮ የምናቀርብባቸው ብዙ አጋጣሚዎች ቢኖሩም በግላችን የምንጸልይበትና መጽሐፍ ቅዱስ የምናነብበት ፕሮግራም ሊኖረን ይገባል።—መዝ. 1:2፤ 62:8

14. ሐዋርያው ጴጥሮስ ከተወው ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን? (ዮሐንስ 6:66-68)

14 በርካታ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስን መከተላቸውን ባቆሙበት ወቅት ሐዋርያው ጴጥሮስ ከሰጠው ምላሽ ትምህርት ማግኘት እንችላለን። በወቅቱ ጴጥሮስም በተወሰነ መጠን ግራ ተጋብቶ ሊሆን ይችላል። ሆኖም በዮሐንስ 6:66-68 ላይ ምን እንዳለ ልብ በል። (ጥቅሱን አንብብ።) ጴጥሮስ ሌሎች ሰዎች ባደረጉት ነገር ላይ ከማተኮር ይልቅ ከኢየሱስ በተማረው የእውነት ቃል ላይ አተኩሯል። ይህም ጴጥሮስን እንዳይሰናከል ረድቶታል። ዛሬም በተመሳሳይ የሌሎች ሰዎች ድርጊት በአምላክ ድርጅት እርዳታ ያገኘኸው እውነት ያለውን ዋጋ አይቀንሰውም። ይህን እውነት አጥብቀህ ያዝ! ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ሳማር እንዲህ ብላለች፦ “አንድ ሰው የፈጸመው ስህተት መላውን ጉባኤ፣ ድርጅቱንም ሆነ የይሖዋን ባሕርያት እንደማይወክል ሁልጊዜ ለማስታወስ እሞክራለሁ።”

15. ከኤሚሊ ተሞክሮ ምን ትምህርት አግኝተሃል?

15 የኤሚሊን ተሞክሮ እንመልከት። ኤሚሊ ከተጠመቀች ከአንድ ሳምንት በኋላ እናቷ ቤተሰቧን ጥላ የሄደች ከመሆኑም ሌላ ከጉባኤው ተወገደች። ኤሚሊ እንዲህ ብላለች፦ “እንዲህ ዓይነት ነገር ሊፈጠር ይችላል ብዬ ፈጽሞ አልጠበቅኩም ነበር። እስካሁን ካጋጠሙኝ ፈተናዎች ሁሉ ከባዱ ይሄ ነው። እናቴ በጣም ትናፍቀኛለች።” ታዲያ ኤሚሊን የረዳት ምንድን ነው? እንዲህ ብላለች፦ “ብቻዬን አይደለሁም። አባቴ እንዲሁም በጉባኤ ውስጥ ያሉ ሌሎች ወንድሞችና እህቶች ይደግፉኛል። እነዚህ ወንድሞችና እህቶች ቤተሰብ ሆነውልኛል። ከችግር ነፃ የሆነ ሕይወት የሚመራ ማንም የለም። እርስ በርስ መቀራረባችንና አንዳችን ሌላውን ማበረታታታችን አስፈላጊ የሆነው ለዚህ ነው።” (1 ጴጥ. 5:9) አንተም ከወንድሞችህና ከእህቶችህ ጋር ለመቀራረብ ፈተና እስኪያጋጥምህ መጠበቅ አያስፈልግህም። ይህን ማድረግ ያለብህ አሁን ነው። እንዲህ ካደረግክ ማንኛውም ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥምህ የሚደግፉህና የሚያጽናኑህ ወዳጆች ይኖሩሃል።

16. ምን ማስታወስ ይኖርብናል? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

16 በተጨማሪም ይሖዋ የሚወዳቸውን እንደሚገሥጽ አስታውስ። (ዕብ. 12:6) ከጉባኤው የተወገዱ ሰዎች በሙሉ እንዲመለሱ ይፈልጋል። (2 ጴጥ. 3:9) ስለዚህ አንድ የምትቀርበው ሰው ከጉባኤው ከተወገደ ሽማግሌዎች ግለሰቡ ወደ ይሖዋ እንዲመለስ ለመርዳት አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ እንደሚያደርጉ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ።—2 ጢሞ. 2:24, 25

ሁለት ሽማግሌዎች ከጉባኤ የተወገደን አንድ ሰው ሄደው ሲያነጋግሩ። አንደኛው ሽማግሌ የተገለጠ መጽሐፍ ቅዱስ ይዟል፤ ሌላኛው ሽማግሌ ደግሞ ለሰውየው “ወደ ይሖዋ ተመለስ” ከተባለው ብሮሹር ላይ አንድ ምዕራፍ ገልጦ ያሳየዋል።

አንድ የምትቀርበው ሰው ከጉባኤው ከተወገደ ሽማግሌዎች ወደ ይሖዋ እንዲመለስ ሊረዱት እንደሚፈልጉ አስታውስ (አንቀጽ 16ን ተመልከት)f


17. ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን?

17 እስካሁን የተመለከትነው ከተጠመቅክ በኋላ ሊያጋጥሙህ ከሚችሉት ፈተናዎች ጥቂቶቹን ብቻ ነው። እርግጥ ነው፣ አንዳንዶቹ ፈተናዎች ለመቋቋም የሚያዳግቱ ሊመስሉ ይችላሉ። ሆኖም ልትፈራ አይገባም። ከወዲሁ ራስህን ማዘጋጀት የምትችልባቸው ብዙ መንገዶች አሉ። ደግሞም ከሁሉ የላቀ ረዳት እንዳለህ ምንጊዜም አትርሳ፤ እሱም ይሖዋ አምላክ ነው። እስካሁንም ሲረዳህ ቆይቷል፤ ለዘላለም ሊረዳህም ይፈልጋል! (1 ጴጥ. 5:10) ማንኛውንም ፈተና ለመቋቋም የሚያስፈልግህን ብርታትና ጽናት ሁልጊዜ ይሰጥሃል። የእሱን እርዳታ መቀበልህን እስከቀጠልክ ድረስ ከእሱ ሊያርቅህ የሚችል አንድም ፈተና አይኖርም!—መዝ. 119:165፤ ሮም 8:38, 39

ለሚከተሉት ፈተናዎች መዘጋጀት የምንችለው እንዴት ነው?

  • አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት ቅር ቢያሰኙን

  • ትተን የመጣናቸውን ነገሮች መናፈቅ ብንጀምር

  • አንድ ሰው ከጉባኤው ቢወገድ

መዝሙር 154 ፍቅር ለዘላለም ይኖራል

a ይህ ርዕስ በዋነኝነት የተዘጋጀው በቅርቡ ለተጠመቁ ክርስቲያኖች ቢሆንም ሁላችንም ከተጠቀሱት ሐሳቦች ጥቅም ማግኘት እንችላለን።

b ስሞቹ ተቀይረዋል።

c ጥልቅ ማስተዋል ፊት ለፊት ከሚታየው ነገር አልፎ የማየት ችሎታን ያመለክታል። ይህ ባሕርይ አንድ ሰው የሆነ ነገር የተናገረበትን ወይም ያደረገበትን ምክንያት ለመረዳት ያግዘናል።

d የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችና በቅርቡ የተጠመቁ ክርስቲያኖች በጉባኤ ውስጥ ባይተዋርነት እንዳይሰማቸው ማድረግ የአስጠኚዎቻቸው ብቻ ሳይሆን የሁላችንም ኃላፊነት ነው። በመጋቢት 2021 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች እድገት አድርገው እንዲጠመቁ በጉባኤ ደረጃ መርዳት” የሚለውን ርዕስ አንቀጽ 15ን እና 16ን ተመልከት።

e የሥዕሉ መግለጫ፦ አንዲት እህት አገልግሎት ላይ ሳለች ስፖርተኞች ኳስ ሲጫወቱ ታያለች፤ ከዚያም እሷ ኳስ ተጫዋች የነበረችበትን ጊዜ ታስታውሳለች። በኋላ ላይ እህት ለአንዲት ስፖርተኛ ትመሠክርላታለች፤ ምናልባትም ይህች ሴት ቀደም ሲል አንድ ቡድን ውስጥ አብራት ትጫወት የነበረች ስፖርተኛ ልትሆን ትችላለች።

f የሥዕሉ መግለጫ፦ ሁለት ሽማግሌዎች ከጉባኤ የተወገደን አንድ ሰው ሄደው በመጠየቅ ወደ ይሖዋ እንዲመለስ ያበረታቱታል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2026)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2026 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ