“ልጆች ከይሖዋ የተገኙ ውርሻ ናቸው”
“ውርሻ” የሚለውን ቃል ስትሰማ ወደ አእምሮህ የሚመጣው ምንድን ነው? አንድ የቤተሰብህ አባል ያወረሰህን ገንዘብ፣ ንብረት ወይም ውድ ቅርስ ታስብ ይሆናል። ያገኘኸው ውርስ ምንም ይሁን ምን፣ ውድ አድርገህ እንደምትመለከተውና በጥንቃቄ ለመያዝ ጥረት እንደምታደርግ ምንም ጥያቄ የለውም።
መጽሐፍ ቅዱስ “ልጆች ከይሖዋ የተገኙ ውርሻ ናቸው” ይላል። (መዝ. 127:3) ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸውን ከሰማዩ አባታቸው ያገኟቸው ውድ ስጦታዎች እንደሆኑ አድርገው ይመለከቷቸዋል። በመሆኑም እነሱን ከጉዳት ለመጠበቅ እንዲሁም አካላዊ፣ ስሜታዊና መንፈሳዊ ፍላጎታቸውን ለማሟላት የተቻላቸውን ሁሉ ጥረት ያደርጋሉ።
የሚያሳዝነው ግን፣ በዛሬው ጊዜ ያሉ አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸውን ከአምላክ እንደተገኙ ስጦታዎች አድርገው አይመለከቷቸውም። (ኢሳ. 49:15፤ 2 ጢሞ. 3:1-3) ሌሎች ደግሞ ልጆቻቸውን የመንከባከብ ልባዊ ፍላጎት ቢኖራቸውም ብዙ ልጆች ስላሏቸው እንዲህ ለማድረግ ይቸገራሉ። ወላጆች ተንከባክበው ሊያሳድጉ ከሚችሉት በላይ ብዙ ልጆችን እንዲወልዱ የሚያደርጋቸው ምን ሊሆን ይችላል? ይሖዋ ወላጆች ምን እንዲያደርጉ ይጠብቅባቸዋል? ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸውን ጥሩ አድርገው ማሳደግ የሚችሉትስ እንዴት ነው?
አንዳንድ ወላጆች ብዙ ልጆች የሚወልዱት ለምንድን ነው?
ቤተሰብና ማኅበረሰቡ የሚያሳድረው ተጽዕኖ። በአንዳንድ አገሮች፣ ብዙ ልጆች ያሏቸው ወላጆች በማኅበረሰቡ ዘንድ ከፍ ያለ ክብር ያገኛሉ። በመሆኑም ባለትዳሮች ማሳደግ ከሚችሉት በላይ ብዙ ልጅ እንዲወልዱ በዘመዶቻቸው ወይም በጎረቤቶቻቸው ጫና ይደረግባቸዋል።
ስለ ወደፊቱ ጊዜ መጨነቅ። በአንዳንድ አገሮች በምግብ እጥረት፣ በበሽታና በጤና አገልግሎት ውስንነት የተነሳ በርካታ ልጆች በጨቅላነታቸው ይሞታሉ። በእነዚህ አገሮች የሚኖሩ ወላጆች ‘ቢያንስ የተወሰኑት ያድጉልኝ ይሆናል’ ብለው በማሰብ በርካታ ልጆችን ይወልዳሉ። ሌሎች ባለትዳሮች ደግሞ ዕድሜያቸው ሲገፋ የሚጦራቸው እንዳያጡ በመስጋት ብዙ ልጆችን ለመውለድ ይወስኑ ይሆናል። በተለይ መንግሥት ለአረጋውያን ምንም ዓይነት ድጋፍ በማያደርግባቸው አገሮች ውስጥ እንዲህ ማድረግ የተለመደ ነው።
የቤተሰብ ምጣኔ። በአንዳንድ አካባቢዎች የሚኖሩ ባለትዳሮች የወሊድ መቆጣጠሪያ ለማግኘት ይቸገራሉ። ሌሎች ደግሞ ማግኘት የሚችሉት ዝቅተኛ የጥራት ደረጃ ያለውን የወሊድ መቆጣጠሪያ ብቻ ስለሆነ የጎንዮሽ ጉዳቱን ይፈራሉ። የወሊድ መቆጣጠሪያ ለመጠቀም የገንዘብ አቅማቸው የማይፈቅድላቸውም አሉ።a
ይሖዋ ወላጆች ምን እንዲያደርጉ ይጠብቅባቸዋል?
ከእያንዳንዱ ልጅ ጋር ጊዜ አሳልፉ
ልጆቻቸው የሚያስፈልጋቸውን ቁሳዊ ነገር እንዲያሟሉ። ይሖዋ ወላጆች ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆቻቸውን ቁሳዊ ፍላጎት እንዲያሟሉ ኃላፊነት ሰጥቷቸዋል። ይሖዋ ወላጆች ለእያንዳንዱ ልጃቸው ምግብ፣ ልብስና መጠለያ ለማቅረብ ጠንክረው እንዲሠሩ ይጠብቅባቸዋል። በተጨማሪም ይሖዋ፣ ወላጆች ልጆቻቸውን እንዲያስተምሯቸው ይፈልጋል። በመሆኑም ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ አዳሪ ትምህርት ቤት ልከው ከዚህ ኃላፊነት ነፃ ለመውጣት አይሞክሩም። ከዚህ ይልቅ ልጆቻቸው እስኪያድጉ ድረስ አብረዋቸው እንዲኖሩና አስፈላጊውን የቀለም ትምህርት እንዲያገኙ ያደርጋሉ፤ በተጨማሪም ለልጆቻቸው በግለሰብ ደረጃ ትኩረት ይሰጧቸዋል። ይህም ልጆቹ የሚያስፈልጋቸውን ፍቅርና እንክብካቤ አግኝተው እንዲያድጉ ያስችላል። ያም ሆኖ ይሖዋ ምክንያታዊ ነው፤ ወላጆች ሀብታም እንዲሆኑ አይጠብቅባቸውም። እንዲያውም ይሖዋ የሚወደውን ልጁን እንዲያሳድጉ የመረጣቸው ሰዎች ታታሪ ሆኖም ድሃ ነበሩ።—ማቴ. 13:55, 56፤ ሉቃስ 2:24
የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት፦ “በእርግጥም አንድ ሰው የራሱ ለሆኑት በተለይ ደግሞ ለቤተሰቡ አባላት የሚያስፈልጋቸውን ነገር የማያቀርብ ከሆነ እምነትን የካደ ከመሆኑም በላይ እምነት የለሽ ከሆነ ሰው የከፋ ነው።”—1 ጢሞ. 5:8
ይሖዋ ወላጆች በዕድሜ ሲገፉ እርዳታ ሊያስፈልጋቸው እንደሚችል ያውቃል። እንዲያውም ልጆች ወላጆቻቸውን እንደሚያከብሩ የሚያሳዩበት አንዱ መንገድ ወላጆቻቸው በዕድሜ ሲገፉ እንክብካቤ የሚያገኙበትን መንገድ በማመቻቸት ነው። (ዘፀ. 20:12፤ 1 ጢሞ. 5:4) ሆኖም ወላጆች ‘ልጆቼ ወደፊት እኔን እንዴት ይንከባከቡኛል?’ ከሚለው ጉዳይ ይልቅ ‘እኔ ልጆቼን መንከባከብ የምችለው እንዴት ነው?’ በሚለው ላይ ትኩረት ሲያደርጉ ይሖዋ ይደሰታል።—2 ቆሮ. 12:14
የልጆቻቸውን መንፈሳዊ ፍላጎት እንዲያሟሉ። ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸው ይሖዋን እንዲወዱና እንዲያመልኩት የማሠልጠን ኃላፊነትም አለባቸው። እንዲያውም በይሖዋ አመለካከት፣ ወላጆች ለልጆቻቸው ሊሰጡ የሚችሉት ትልቁ ነገር እንዲህ ያለው መንፈሳዊ ሥልጠና ነው።—ዘዳ. 6:6, 7
የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት፦ “ልጆቻችሁን . . . በይሖዋ ተግሣጽና ምክር አሳድጓቸው።”—ኤፌ. 6:4
ይሖዋ እንዲሳካላችሁ ይፈልጋል
ስንት ልጆች መውለድ እንደምትፈልጉ አስቀድማችሁ ተወያዩ
አስቀድማችሁ ዕቅድ አውጡ። ልጆች ለመውለድ እያሰባችሁ ከሆነ ሁኔታችሁን በጥንቃቄ ገምግሙ። ለምሳሌ ብዙ ልጆችን ለመመገብ፣ ለማልበስና ለማስተማር የገንዘብ አቅማችሁ ይፈቅድላችኋል? ካልሆነ፣ ከትዳር አጋራችሁ ጋር በመመካከር ይሖዋ በሚጠብቅባችሁ መጠን ተንከባክባችሁ ማሳደግ የምትችሉት ስንት ልጅ እንደሆነ ወስኑ። እርግጥ ይሖዋ ሁሉም ነገር ባቀድነው መሠረት እንደማይሄድ ያውቃል። (መክ. 9:11) ሆኖም ልጆቻችሁን ጥሩ አድርጋችሁ ለማሳደግ የምታደርጉትን ልባዊ ጥረት ይባርክላችኋል።
የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች፦ “የትጉ ሰው ዕቅድ ለስኬት ያበቃዋል፤ ችኩሎች ሁሉ ግን ለድህነት ይዳረጋሉ።”—ምሳሌ 21:5
“ከእናንተ መካከል፣ ግንብ ለመገንባት ፈልጎ ለመጨረስ የሚያስችል በቂ ገንዘብ እንዳለው ለማወቅ በመጀመሪያ ተቀምጦ ወጪውን የማያሰላ ማን ነው?”—ሉቃስ 14:28
በቤተሰባችሁ ውስጥ ይሖዋን አስቀድሙ። ቤተሰባችሁ ለይሖዋ አምልኮ ቅድሚያ እንዲሰጥ አድርጉ። ልጆች ካሏችሁ ለእያንዳንዱ ልጃችሁ ጊዜ ሰጥታችሁ ይሖዋን እንዲወድ ለማስተማር ጥረት አድርጉ። ልጆቻችሁ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ በትኩረት እንዲከታተሉና እንዲማሩ እርዷቸው። ቋሚ የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራም ይኑራችሁ። ልጆቻችሁን በአገልግሎት ረገድ አሠልጥኗቸው። ወላጅ እንደመሆናችሁ መጠን፣ እነዚህን ነገሮች ማድረግ የእናንተ ኃላፊነት ነው፤ ትላልቆቹ ልጆቻችሁ ወይም ሌሎች ዘመዶቻችሁ በእናንተ ፋንታ እነዚህን ነገሮች እንዲያደርጉላችሁ አትጠብቁ። ልጆች ይሖዋን እንዲወዱ አድርጎ ማሳደግ ጊዜና ጥረት ቢጠይቅም በእጅጉ የሚክስ ነው።
የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት፦ “ልጆቼ በእውነት ውስጥ እየተመላለሱ መሆናቸውን ከመስማት የበለጠ ደስታ የለኝም።”—3 ዮሐ. 4b
በይሖዋ ታመኑ። ልጆች ለመውለድ እያሰባችሁ ከሆነ ወይም ልጆች ካሏችሁ ከአካባቢያችሁ ባሕል ወይም ልማድ ይልቅ የይሖዋ መሥፈርቶች ቅድሚያ ሊሰጣቸው እንደሚገባ አስታውሱ።
የልጆችን መንፈሳዊ ፍላጎት ማሟላት ጊዜና ጥረት ይጠይቃል
ብዙ ልጆችን ላለመውለድ ብትወስኑም እንኳ ይሖዋ ዕድሜያችሁ ሲገፋ እንደሚደግፋችሁ ተማመኑ። አንዳንዶች እንደሚያደርጉት፣ ልጆችን እንደ “ጡረታ ዋስትና” አድርጋችሁ ከመመልከት ተቆጠቡ። ዕድሜያችሁ ሲገፋ የሚንከባከባችሁ እንደማይኖር በማሰብ ፈጽሞ ልትጨነቁ አይገባም። ይሖዋ እንደሚንከባከባችሁ ቃል ገብቷል፤ እሱ ደግሞ መቼም ቢሆን ቃሉን አያጥፍም።—ኢያሱ 23:14
የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች፦ “በሙሉ ልብህ በይሖዋ ታመን፤ ደግሞም በገዛ ራስህ ማስተዋል አትመካ። በመንገድህ ሁሉ እሱን ግምት ውስጥ አስገባ፤ እሱም ጎዳናህን ቀና ያደርገዋል።”—ምሳሌ 3:5, 6
“በአንድ ወቅት ወጣት ነበርኩ፤ አሁን ግን አርጅቻለሁ፤ ይሁንና ጻድቅ ሰው ሲጣል፣ ልጆቹም ምግብ ሲለምኑ አላየሁም።”—መዝ. 37:25
“እንግዲያው ከሁሉ አስቀድማችሁ የአምላክን መንግሥትና ጽድቅ ፈልጉ፤ እነዚህም ነገሮች ሁሉ ይሰጧችኋል።”—ማቴ. 6:33
ልጆች ይሖዋ ለወላጆች በአደራ የሰጣቸው ውድ ስጦታዎች ናቸው። ክርስቲያን ባለትዳሮች ይህን አደራ ሲወጡ ይሖዋ ምንኛ ይደሰት ይሆን! ከአካባቢያቸው ባሕል ወይም ልማድ ይልቅ ይሖዋ ለሚጠብቅባቸው ነገር ቅድሚያ ይሰጣሉ። በመሆኑም ስንት ልጆች እንደሚወልዱ በጥንቃቄ ይወስናሉ። እንዲሁም የልጆቻቸውን አካላዊ፣ ስሜታዊና መንፈሳዊ ፍላጎቶች ለማሟላት ልባዊ ጥረት ያደርጋሉ። ክርስቲያን ወላጆች እንዲህ በማድረግ ልጆቻቸውን ‘ከይሖዋ የተገኙ ውርሻ’ አድርገው እንደሚመለከቷቸው ያሳያሉ።
a ባለትዳሮች ስንት ልጆች እንደሚወልዱ፣ መቼ እንደሚወልዱ እንዲሁም የወሊድ መቆጣጠሪያ መጠቀም ይኖርባቸው እንደሆነና እንዳልሆነ በራሳቸው መወሰን ይኖርባቸዋል። በሚያደርጉት የግል ውሳኔ የተነሳ ማንም ሰው በእነሱ ላይ ሊፈርድ አይገባም። (ሮም 14:4, 10-13) እርግጥ የሚጠቀሙበት የወሊድ መቆጣጠሪያ ዘዴ ፅንስ የሚያቋርጥ ሊሆን አይገባም። በተጨማሪም ያገቡ ክርስቲያኖች በ1 ቆሮንቶስ 7:3-5 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን ምክር ማስታወስ ይኖርባቸዋል።
b ዮሐንስ እዚህ ላይ “ልጆቼ” ያለው እውነትን ያስተማራቸውን ደቀ መዛሙርት ቢሆንም ወላጆች ልጆቻቸው ይሖዋን ሲያገለግሉ ሲያዩ የእሱ ዓይነት ስሜት ይሰማቸዋል።