የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w26 የካቲት ገጽ 14-19
  • ወደ ጥምቀት የሚያደርሱህን እርምጃዎች ውሰድ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ወደ ጥምቀት የሚያደርሱህን እርምጃዎች ውሰድ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2026
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • አንዳንዶች ለመጠመቅ የሚያመነቱት ለምንድን ነው?
  • መጨረሻው ቅርብ እንደሆነ አስታውስ
  • አሁኑኑ እርምጃ ውሰድ
  • የጥምቀት ትርጉም ምንድን ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2026
  • ራስህን ለይሖዋ ለመወሰን ዝግጁ ነህ?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2024
  • ከተጠመቅክ በኋላ ኢየሱስን ‘ያለማቋረጥ ተከተል’
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2024
  • ለመጠመቅ አሁኑኑ እርምጃ ውሰድ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2026
w26 የካቲት ገጽ 14-19

ከሚያዝያ 20-26, 2026

መዝሙር 49 የይሖዋን ልብ ማስደሰት

ወደ ጥምቀት የሚያደርሱህን እርምጃዎች ውሰድ

“አምላክ ሞገስ የሚያሳይበት ልዩ ጊዜ አሁን ነው።”—2 ቆሮ. 6:2

ዓላማ

ከይሖዋ ጋር የቅርብ ወዳጅነት ለመመሥረትና ለመጠመቅ ጊዜው አሁን ነው።

1. (ሀ) መጠመቃችን የትኞቹን ጥቅሞች ያስገኝልናል? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን?

ራስህን ለይሖዋ ወስነህ ተጠምቀሃል? ከሆነ፣ ጥሩ ሕሊና ለማግኘት ለአምላክ ልመና አቅርበሃል። (1 ጴጥ. 3:21) በመጠመቅህ በጉባኤ ውስጥ ላሉ ያልተጠመቁ ልጆችና አዲሶች ጥሩ ምሳሌ ሆነሃል። ራስህን ለይሖዋ መስጠት ከሁሉ የተሻለ ውሳኔ ነው! ሆኖም እስካሁን ካልተጠመቅክስ? ይሖዋን እንደምትወደውና ፈቃዱን ለመፈጸም እንደምትፈልግ ጥያቄ የለውም። ኃጢአትህ ይቅር እንዲባልልህና የይሖዋን ሞገስ እንድታገኝ መጠመቅህ አስፈላጊ እንደሆነ ታውቃለህ። (ሥራ 2:38-40) ይሁንና ይህን ውሳኔ ለማድረግ እያመነታህ ይሆናል። ታዲያ ምን ሊረዳህ ይችላል? በዚህ ርዕስ ውስጥ የሚከተሉትን ነጥቦች እንመረምራለን፦ (1) አንዳንዶች ለመጠመቅ የሚያመነቱት ለምንድን ነው? (2) መጨረሻው ቅርብ እንደሆነ ማስታወስህ ጥበብ የሆነው ለምንድን ነው? እንዲሁም (3) ወደ ጥምቀት የሚያደርሱህን እርምጃዎች አሁኑኑ መውሰድህ ምን ጥቅም ያስገኝልሃል?

አንዳንዶች ለመጠመቅ የሚያመነቱት ለምንድን ነው?

2. አንዳንዶች ለመጠመቅ የሚያመነቱት ለምንድን ነው?

2 አንዳንዶች ለመጠመቅ የሚያመነቱት ፍርሃት ስለሚሰማቸው ነው። ለምሳሌ ይሖዋን ለማገልገል ቢፈልጉም ‘መቼም ቢሆን እሱን ማስደሰት አልችልም’ ብለው ይፈራሉ። አንተም እንዲህ የሚሰማህ ከሆነ ይሖዋ ከሰዎች ፍጽምና እንደማይጠብቅና ምርጥህን እስከሰጠኸው ድረስ አምልኮህን በደስታ እንደሚቀበል የሚያረጋግጡ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን አንብብ። (መዝ. 103:13, 14፤ ቆላ. 3:23) ተቃውሞን የምትፈራ ከሆነ ደግሞ የሚከተለውን ሐሳብ የጻፈው መዝሙራዊ የነበረውን ዓይነት ድፍረት እንዲሰጥህ ይሖዋን ጠይቀው፤ መዝሙራዊው እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ይሖዋ ከጎኔ ነው፤ አልፈራም። ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል?”—መዝ. 118:6

3. አንዳንዶች ለመጠመቅ የሚያመነቱት ምን ስለሚሰማቸው ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

3 አንዳንዶች ይሖዋን ቢወዱትም ከመጠመቅ ወደኋላ የሚሉት በቂ እውቀት እንደሌላቸው ስለሚሰማቸው ነው። ይሁንና በቂ እውቀት የሚባለው ምን ያህል ነው? አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ እንመልከት። ሐዋርያው ጳውሎስና ሲላስ ታስረው የነበረበት እስር ቤት በመሬት መንቀጥቀጥ ከተናወጠ በኋላ ለእስር ቤቱ ጠባቂና ለቤተሰቦቹ መሠከሩላቸው። ይህ ሰውና ቤተሰቡ የተከሰተው ነገር ተአምር እንደሆነ ሳይገነዘቡ አይቀሩም። በተጨማሪም በዚያ ምሽት ስለ ይሖዋና ስለ ኢየሱስ ብዙ ነገር ተምረዋል። የተማሩት ነገር ‘ወዲያውኑ እንዲጠመቁ’ አነሳስቷቸዋል። (ሥራ 16:25-33) አንተም ይሖዋን የምታውቀውና በሙሉ ልብህ የምትወደው ከሆነ፣ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች መሠረታዊ እውቀት ካለህ፣ ለኃጢአትህ ንስሐ ከገባህ እንዲሁም በይሖዋ መሥፈርቶች ለመመራት ቁርጥ ውሳኔ ካደረግክ ለመጠመቅ ዝግጁ ነህ።—ማር. 12:30

ጳውሎስና ሲላስ ምሽት ላይ ለእስር ቤቱ ጠባቂና ለቤተሰቡ ሲመሠክሩላቸው። ሁሉም በጥሞና እያዳመጧቸው ነው።

ጳውሎስና ሲላስ ለእስር ቤቱ ጠባቂና ለቤተሰቡ መሥክረውላቸዋል፤ ይህም ‘ወዲያውኑ እንዲጠመቁ’ አነሳስቷቸዋል (አንቀጽ 3ን ተመልከት)


4. አንዳንዶች ከመጠመቅ ወደኋላ እንዲሉ የሚያደርጋቸው ሌላው ምክንያት ምንድን ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

4 አንዳንዶች ይሖዋን ማስደሰት ቢፈልጉም ይህን ማድረግ የሚያስከፍላቸው መሥዋዕት ያሳስባቸዋል። እርግጥ ምንም ዓይነት ውሳኔ ከማድረጋችን በፊት ወጪያችንን ማስላታችን የጥበብ እርምጃ ነው። (ሉቃስ 14:27-30) ሆኖም አንዳንዶች አምላክን ማገልገል በሚጠይቅባቸው መሥዋዕት ላይ ከመጠን በላይ ያተኩራሉ። የካንደስን ምሳሌ እንመልከት። ካንደስ በልጅነቷ እውነትን ብታውቅም እርምጃ አልወሰደችም ነበር። አዋቂ ከሆነች በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን እንድታጠና ግብዣ ሲቀርብላት ምን እንደተሰማት ስትገልጽ እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋን ለማስደሰት ምን ማድረግ እንዳለብኝ አውቅ ነበር። ሆኖም የአሁኑን ሕይወቴን ስለምወደው ለመወሰን ተቸገርኩ። የምወዳቸውን ነገሮች መተው እንደሚከብደኝ ተሰምቶኝ ነበር።” ሌሎች ደግሞ ከተጠመቁ ሰዎች የሚጠበቀውን ላቅ ያለ መሥፈርት ማሟላት ከባድ እንደሚሆን ይሰማቸዋል። ‘ከተጠመቅኩ በኋላ ከባድ ኃጢአት ሠርቼ ከጉባኤው ብወገድስ?’ ብለው ይፈራሉ። አንተም እነዚህ ነገሮች የሚያሳስቡህ ከሆነ ምን ማድረግ ትችላለህ?

አንዲት እህት አንዲትን ሴት መጽሐፍ ቅዱስ ስታስጠና። እህት እየተናገረች ሳለ ጥናቷ ጭፈራ ቤት ውስጥ ከጓደኞቿ ጋር መጠጥ ስትጠጣና ስትደንስ በምናቧ ይታያታል።

አንዳንዶች አምላክን ማስደሰት ቢፈልጉም እሱን ማገልገል የሚጠይቀው መሥዋዕት ያሳስባቸዋል (አንቀጽ 4ን ተመልከት)


5. ለመጠመቅ እያመነታን ከሆነ በምን ላይ ትኩረት ማድረጋችን ይጠቅመናል? (ማቴዎስ 13:44-46)

5 አንድን ዕቃ ለመግዛት ስናስብ የሚያስከፍለንን ወጪ ብቻ ሳይሆን የሚሰጠንን ጥቅምም እናስባለን። ዕቃው የሚሰጠን ጥቅም ከሚያስወጣን ወጪ እጅግ የላቀ ከሆነ ወዲያውኑ ለመግዛት እንደምንነሳሳ ምንም ጥያቄ የለውም። በተመሳሳይም ለመጠመቅ እያመነታን ከሆነ በዋነኝነት ትኩረት ማድረግ ያለብን አስፈላጊዎቹን ለውጦች ማድረግ በሚያስከፍለን መሥዋዕት ላይ ሳይሆን ከይሖዋ ጋር የምንመሠርተው ወዳጅነት ባለው የላቀ ዋጋ ላይ ነው። ኢየሱስ ይህን ነጥብ ለማስተማር ሁለት ምሳሌዎችን ተጠቅሟል። (ማቴዎስ 13:44-46ን አንብብ።) በሁለቱም ምሳሌዎች ላይ የተጠቀሱት ሰዎች ያገኙትን ውድ ዋጋ ያለው ነገር ለመግዛት ሲሉ ንብረታቸውን በሙሉ ሸጠዋል። አንተም ውድ ዋጋ ያለው ነገር አግኝተሃል፤ ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጸውን እውነት አውቀሃል። ከአምላክ መሥፈርቶች ጋር ተስማምቶ መኖር የሚጠይቀውን መሥዋዕት ለመክፈል እያመነታህ ከሆነ ኢየሱስ የተናገራቸውን ምሳሌዎች በጥሞና አስብባቸው። ራስህን እንዲህ ብለህ መጠየቅ ትችላለህ፦ ‘የመንግሥቱ ምሥራች እጅግ ውድ ዋጋ እንዳለው አምናለሁ? ከይሖዋ ጋር ያለኝን ወዳጅነት፣ እሱ የሰጠኝን ተስፋ እንዲሁም ፍቅር የሰፈነበትን የወንድማማች ማኅበር ከፍ አድርጌ እመለከታለሁ?’ ለእነዚህ ጥያቄዎች የምትሰጠው መልስ እንዳትጠመቅ ያገደህ ምን እንደሆነ ለማስተዋልና ምን ዓይነት እርምጃ መውሰድ እንዳለብህ ለማወቅ ሊረዳህ ይችላል። ምናልባት ለእውነት ያለህን አድናቆት ማሳደግ ያስፈልግህ ይሆናል።

6. ጥሩ ልብ እንዲኖረን ምን ማድረግ እንችላለን?

6 ኢየሱስ ስለ ዘሪው በተናገረው ምሳሌ ላይ አንዳንድ ሰዎች የልባቸው ሁኔታ መንፈሳዊ እድገት እንዳያደርጉ እንቅፋት ሊሆንባቸው እንደሚችል ገልጿል። በሌላ በኩል ደግሞ ኢየሱስ አንዳንዶች “በመልካምና በጥሩ ልብ” የመንግሥቱን መልእክት ሰምተው ምላሽ እንደሚሰጡ ተናግሯል። (ሉቃስ 8:5-15) ልብህ እንደተከፈለ ከተሰማህ ተስፋ አትቁረጥ። በአምላክ እርዳታ፣ እሱን ለመታዘዝ ዝግጁ የሆነ “አዲስ ልብ” ማግኘት ትችላለህ። የተማርከውን ነገር ለመውደድና ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ጥሩ ልብ እንዲሰጥህ ይሖዋን በጸሎት ጠይቀው።—ሕዝ. 18:31፤ 36:26

7-8. አንዳንድ ልጆች እድገት አድርገው እንዳይጠመቁ እንቅፋት የሚሆንባቸው ምንድን ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

7 ይሖዋን የሚወዱ አንዳንድ ልጆች እድገት አድርገው እንዳይጠመቁ እንቅፋት የሚሆንባቸው ሌሎች የሚያሳድሩባቸው ተጽዕኖ ነው። ለምሳሌ አንዳንድ አስተማሪዎች ተማሪዎቻቸውን ከሥነ ምግባር መሥፈርቶች ጋር በተያያዘ “ጠባብ አስተሳሰብ እንዳይኖራቸው” ይመክራሉ። አምላክ ካወጣቸው የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ጋር የሚጋጩ ድርጊቶችም እንኳ ተቀባይነት እንዳላቸው ይናገራሉ። ሆኖም ይህ ምክር አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል። (መዝ. 1:1, 2፤ ምሳሌ 7:1-5) እንዲህ ያለው አደጋ እንዳይደርስብህ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? አንድ መዝሙራዊ እንዲህ ብሏል፦ “በማሳሰቢያዎችህ ላይ ስለማሰላስል፣ ከአስተማሪዎቼ ሁሉ የበለጠ ጥልቅ ማስተዋል አለኝ”፤ አንተም የእሱን ምሳሌ መከተል ትችላለህ።—መዝ. 119:99

8 አንዳንድ የይሖዋ ምሥክር ወላጆች ልጆቻቸው ከመጠመቅ ወደኋላ እንዲሉ ሊያደርጓቸው ይችላሉ። ልጆቻቸው ለትምህርታቸውና ወደፊት ለሚያገኙት ሥራ ከልክ በላይ ትኩረት እንዲሰጡ ያበረታቱ ይሆናል፤ ወይም ደግሞ ልጆቻቸው መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ በበቂ መጠን አልረዷቸው ይሆናል። አንተስ ወላጆችህ እድገት አድርገህ እንድትጠመቅ እንዲረዱህ ትፈልጋለህ? ከሆነ ስለ ጉዳዩ አንስተህ ለምን አታማክራቸውም? ዕድሜህ ከይሖዋ ጋር ወዳጅነት ለመመሥረት እንቅፋት እንደማይሆን አስታውስ።—ምሳሌ 20:11

በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኝ አንድ ልጅ “ለዘላለም በደስታ ኑር!” የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 23ን እየጠቆመ ወላጆቹን ሲያነጋግር።

ወላጆችህን ስለ ጥምቀት አንስተህ ለምን አታነጋግራቸውም? (አንቀጽ 8ን ተመልከት)


9. አንዳንዶች ለመጠመቅ የሚዘገዩት ለምንድን ነው?

9 አንዳንዶች ለመጠመቅ ብቃቱን ቢያሟሉም ይህን እርምጃ ለመውሰድ ይዘገያሉ። ይህን የሚያደርጉት ከአንድ ጓደኛቸው ወይም የቤተሰባቸው አባል ጋር አብረው መጠመቅ ስለፈለጉ ሊሆን ይችላል። እርግጥ ከምትወዳቸው ሰዎች ጋር አብረህ መጠመቅህ ስህተት የለውም። ግን በዚህ ምክንያት የምትጠመቅበትን ጊዜ ማዘግየት ተገቢ ነው? ራስህን ስትወስን የምትገባው ቃል በአንተና በአምላክ መካከል ብቻ ያለ ጉዳይ እንደሆነ አስታውስ። የምትጠመቅበት ጊዜ በሌሎች ላይ የተመካ መሆን የለበትም።—ሮም 14:12

መጨረሻው ቅርብ እንደሆነ አስታውስ

10. አንዳንዶች መንፈሳዊ እድገት ለማድረግ የሚዘገዩት ለምን ሊሆን ይችላል?

10 ከላይ ከተጠቀሱት ምክንያቶች በተጨማሪ አንዳንዶች መንፈሳዊ እድገት ለማድረግ የሚዘገዩት መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት ገና ብዙ ጊዜ እንዳላቸው ስለሚሰማቸው ሊሆን ይችላል። ግን እንዲህ ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ነው? ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “የሰው ልጅ ይመጣል ብላችሁ ባላሰባችሁት ሰዓት ስለሚመጣ ዝግጁ ሆናችሁ ጠብቁ” ሲል አሳስቧቸዋል።—ሉቃስ 12:40

11. በመዝሙር 119:60 መሠረት ይሖዋን ይበልጥ እያወቅነው ስንሄድ ስለ ትእዛዛቱ ምን ይሰማናል?

11 ራሳችንን ለይሖዋ እንድንወስን የሚያነሳሳን ፍቅር መሆን ይኖርበታል። አፍቃሪውን አምላካችንን ይበልጥ እያወቅነው ስንሄድ ትእዛዛቱን ይበልጥ እንወዳቸዋለን፤ እንዲሁም ለመታዘዝ ፈጣኖች እንሆናለን። (መዝሙር 119:60ን አንብብ።) ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ የይሖዋን ትእዛዛት በፍጥነት ለመታዘዝ የሚያነሳሳንን ሌላ ወሳኝ ምክንያት ጠቅሷል፦ ማናችንም ሕይወታችን ነገ ምን እንደሚሆን አናውቅም። “ትክክል የሆነውን ነገር” ማድረግ የምንችልበት አንድ ተጨማሪ ቀን እንኳ ላይኖረን ይችላል፤ ስለዚህ ማድረግ እንዳለብን የምናውቀውን ነገር አሁኑኑ ማድረግ ይኖርብናል።—ያዕ. 4:13-17

12. ኢየሱስ ስለ ወይን እርሻው ከተናገረው ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን?

12 ታዲያ ኢየሱስ ስለ ወይን እርሻው የተናገረውን ምሳሌ እንዴት ልንረዳው ይገባል? ኢየሱስ አንዳንዶቹ ሠራተኞች ለአንድ ሰዓት ብቻ ቢሠሩም ሙሉ ቀን ከሠሩት ጋር እኩል ደሞዝ እንደተከፈላቸው ተናግሯል። ሆኖም አንድ ሰዓት ብቻ የሠሩት ሠራተኞች ቀደም ብለው ሥራቸውን ያልጀመሩት ለምንድን ነው? ምክንያቱን ሲናገሩ “የሚቀጥረን ሰው ስላጣን ነው” ብለዋል። እነዚህ ሠራተኞች ቀኑን ሙሉ ያልሠሩት መሥራት ስላልፈለጉ አይደለም፤ የሚቀጥራቸው ሰው ስላጡ ነው። ልክ ጥሪው እንደቀረበላቸው ግን ወደ ሥራ ገብተዋል። (ማቴ. 20:1-16) ዛሬም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ እንድንሆንና በመንግሥቱ ሥራ እንድንካፈል ጥሪ አቅርቦልናል። ጥሪውን እንደሰማን ወዲያውኑ ምላሽ መስጠት ይኖርብናል።

13. ከሎጥ ሚስት ታሪክ ምን ትምህርት እናገኛለን?

13 አንዳንዶች መንፈሳዊ እድገት ለማድረግ የሚዘገዩት ልክ መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት አስፈላጊዎቹን ለውጦች ማድረግ እንደሚችሉ ስለሚሰማቸው ሊሆን ይችላል። ግን ባለቀ ሰዓት እነዚህን ለውጦች ማድረግ እንደሚያስቡት ቀላል ላይሆን ይችላል። ኢየሱስ ይህን ስለሚያውቅ ደቀ መዛሙርቱን “የሎጥን ሚስት አስታውሱ” ሲል አስጠንቅቋቸዋል። (ሉቃስ 17:31-35) የሎጥ ሚስት አምላክ ሰዶምንና ገሞራን የሚያጠፋበት ጊዜ እንደደረሰ ጠንቅቃ ብታውቅም ትታ ከወጣቻቸው ነገሮች ጋር ያላትን ትስስር እርግፍ አድርጋ መተው አልቻለችም። (ዘፍ. 19:23-26) በተጨማሪም የሎጥ ሚስት ታሪክ የመዳን በር ለዘለቄታው ክፍት ሆኖ እንደማይኖር ያስታውሰናል። አምላክ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ ይህ በር ይዘጋል፤ እስከ ወዲያኛውም ይቆለፋል።—ሉቃስ 13:24, 25

14. የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን ፍጻሜ በትኩረት መከታተል ያለብህ ለምንድን ነው?

14 በዓለም ላይ በየዕለቱ የሚፈጸሙት ክንውኖች ስለዚህ ሥርዓት መጨረሻ የሚናገሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች እየተፈጸሙ እንዳሉ የሚያሳዩ ናቸው። ከእነዚህ ክንውኖች አንዳንዶቹ አንተን በቀጥታ ባይነኩህም በተለያየ ስፍራ እየተከናወነ ያለውን ነገር ማየትህ በተቻለ ፍጥነት እድገት አድርገህ ለመጠመቅ ሊያነሳሳህ ይገባል። ሐዋርያው ጴጥሮስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖችን “የሁሉም ነገር መጨረሻ [ስለቀረበ]” “ንቁዎች” እንዲሆኑ አሳስቧቸዋል። (1 ጴጥ. 4:7) እዚህ ላይ “መጨረሻ” የሚለው አገላለጽ ኢየሩሳሌምና ቤተ መቅደሱ የሚጠፉበትን ጊዜ እንደሚያመለክት ከሁኔታዎች መረዳት ይቻላል። ጴጥሮስ የጻፈላቸው ክርስቲያኖች የሚኖሩት ከኢየሩሳሌም ርቀው ነው፤ በመሆኑም የኢየሩሳሌም መጥፋት በቀጥታ አይነካቸውም። (1 ጴጥ. 1:1) ይሁን እንጂ ይህ ትንቢት ሲፈጸም ማየታቸው ይሖዋ ቃል የገባቸው ሌሎች ነገሮችም እንደሚፈጸሙ ያላቸውን እምነት ያጠናክርላቸዋል። አንተም በአሁኑ ጊዜ እየተፈጸሙ ላሉት ትንቢቶች ትኩረት መስጠትህ አስፈላጊ ነው። መጨረሻው መቅረቡን ስትመለከት ንቁ በመሆን ወደ ጥምቀት የሚያደርሱህን እርምጃዎች ለመውሰድ ትነሳሳለህ።

15. ለይሖዋ ቀን መዘጋጀት የምንችለው እንዴት ነው? (2 ጴጥሮስ 3:10-13)

15 ጴጥሮስ በመንፈስ መሪነት በጻፈው ሁለተኛ ደብዳቤ ላይ ለይሖዋ የፍርድ ቀን መዘጋጀት የምንችለው እንዴት እንደሆነ ገልጿል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩት ክርስቲያኖች የይሖዋ ቀን ገና ሩቅ ነበር፤ ሆኖም ጴጥሮስ ያንን ቀን ‘በአእምሯቸው አቅርበው እንዲመለከቱ’ ወይም ‘እንዲናፍቁ’ ነግሯቸዋል። (2 ጴጥሮስ 3:10-13ን አንብብ፤ ግርጌ) እኛም ይህን ቀን በአእምሯችን አቅርበን መመልከት የምንችለው ዝግጁ በመሆንና ያ ቀን እንዲመጣ በመናፈቅ ነው። “ቅዱስ ሥነ ምግባር በመከተልና ለአምላክ [ያደርን መሆናችንን] የሚያሳዩ ተግባሮች በመፈጸም” ይህን ቀን እንደምንናፍቅ ማሳየት እንችላለን። ይሖዋ ‘ለአምላክ ያደርክ መሆንህን የሚያሳዩ ተግባሮችን ስትፈጽም’ ሲመለከት ምን ያህል እንደሚደሰት ለማሰብ ሞክር! በእርግጥም ራስህን ለእሱ ስትወስንና ስትጠመቅ ሲመለከት በጣም ይደሰታል።

አሁኑኑ እርምጃ ውሰድ

16. ወደ ጥምቀት የሚያደርሱህን እርምጃዎች ለመውሰድ ከሁሉ የተሻለው ጊዜ መቼ ነው? (2 ቆሮንቶስ 6:1, 2) (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)

16 ወደ ጥምቀት የሚያደርሱትን እርምጃዎች ለመውሰድ ከሁሉ የተሻለው ጊዜ አሁን ነው። (2 ቆሮንቶስ 6:1, 2ን አንብብ።) ፊልጶስ ያነጋገረው ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ያለውን አስፈላጊነት ተገንዝቦ ነበር። ስለ ምሥራቹ ከተማረና መጠመቅ የሚችልበት ቦታ ካገኘ በኋላ እንዲህ ብሎ አላሰበም፦ ‘በቅድሚያ ስለ ምሥራቹ ይበልጥ መማር እፈልጋለሁ። መንገዳችንን ስንቀጥል ውኃ ያለበት ሌላ ቦታ ማግኘታችን አይቀርም።’ ከዚህ ይልቅ “እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምን ነገር አለ?” ሲል ፊልጶስን ጠይቆታል። (ሥራ 8:26, 27, 35-39) እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው! ጃንደረባው ከተጠመቀ በኋላ “ደስ ብሎት ጉዞውን ቀጠለ።”

ሥዕሎች፦ 1. ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ለመጠመቅ ወደ ውኃ ሲገባ፤ ፊልጶስም ውኃው ውስጥ ቆሟል። 2. ቀደም ባለው ሥዕል ላይ የነበረችው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና አስጠኚዋ በስብሰባ አዳራሽ ውስጥ ፈገግ ብለው ሁለት ሽማግሌዎችን ሲያነጋግሩ።

ከኢትዮጵያዊው ጃንደረባ አንድ ወሳኝ ትምህርት እናገኛለን፦ ወደ ጥምቀት የሚያደርሱንን እርምጃዎች ለመውሰድ ከሁሉ የተሻለው ጊዜ አሁን ነው (አንቀጽ 16ን ተመልከት)a


17. ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን?

17 ለመጠመቅ እያመነታህ ከሆነ ይሖዋ የቅርብ ወዳጁ እንድትሆን ሊረዳህ እንደሚፈልግ እርግጠኛ ሁን። (ሮም 2:4) ለእድገትህ እንቅፋት የሆነን ማንኛውንም ፍርሃት፣ ስጋት ወይም ከሌሎች የሚመጣ ተጽዕኖ እንድታሸንፍ ሊረዳህ ይችላል። በጥምቀት አማካኝነት በአምላክ ፊት ጥሩ ሕሊና ስታገኝ ‘ከኋላህ ያሉት ነገሮች’ እዚህ ግቡ የሚባሉ እንዳልሆኑ ትገነዘባለህ። (ፊልጵ. 3:8, 13) ከዚያም ‘ከፊት ያሉትን ነገሮች’ ማለትም ይሖዋ ራሳቸውን ለእሱ ወስነው ለሚጠመቁ ሰዎች ያዘጋጃቸውን በረከቶች በጉጉት መጠባበቅ ትችላለህ።—ሥራ 3:19

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

  • አንዳንዶች ለመጠመቅ የሚያመነቱት ለምን ሊሆን ይችላል?

  • ለመጠመቅ መዘግየት የጥበብ አካሄድ ያልሆነው ለምንድን ነው?

  • ወደ ጥምቀት የሚያደርሱንን እርምጃዎች ለመውሰድ ከሁሉ የተሻለው ጊዜ መቼ ነው?

መዝሙር 38 ጠንካራ ያደርግሃል

a የሥዕሉ መግለጫ፦ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ መጠመቅ እንደሚፈልግ ለፊልጶስ እንደነገረው ሁሉ አንዲት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መጠመቅ እንደምትፈልግ ለሽማግሌዎች ስትናገር።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2026)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2026 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ