Courtesy Jamie Christiani/Bulletin of the Atomic Scientists
ነቅታችሁ ጠብቁ!
የመዓት ቀን ሰዓት ወደ እኩለ ሌሊት ይበልጥ ተጠጋ
ጥር 27, 2026 ሳይንቲስቶች የመዓት ቀን ሰዓትንa የደቂቃ መቁጠሪያ ወደ እኩለ ሌሊት ይበልጥ አስጠግተውታል። በዚህ ሰዓት አቆጣጠር እኩለ ሌሊት የሚያመለክተው ዓለማችን በሰው ልጆች ድርጊት ምክንያት የምትጠፋበትን ጊዜ ነው።
“ቡለቲን ኦቭ ዚ አቶሚክ ሳይንቲስትስ የተባለው ድርጅት የሳይንስ እና የደህንነት ቦርድ፣ የመዓት ቀን ሰዓት ለእኩለ ሌሊት 85 ሴኮንድ ብቻ እንዲቀረው በዛሬው ዕለት ወስኗል፤ ለጥፋት የዚህን ያህል ቀርበን አናውቅም።”—ቡለቲን ኦቭ ዚ አቶሚክ ሳይንቲስትስ
“የመዓት ቀን ሰዓት የሚያስተላልፈው መልእክት የሚያሻማ አይደለም። ጥፋት የሚያስከትሉ ስጋቶች እየጨመሩ ነው፤ ዓለም አቀፍ ትብብር እየቀነሰ ነው፤ እንዲሁም ጊዜው እያለቀብን ነው። ለውጥ የግድ አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን የሚቻል ነገርም ነው፤ ሆኖም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ፣ አፋጣኝ እርምጃ እንዲወሰድ በመሪዎቹ ላይ ጫና ማድረግ አለበት።”—አሌክሳንድራ ቤል፣ የቡለቲን ኦቭ ዚ አቶሚክ ሳይንቲስትስ ፕሬዚዳንት እና ዋና ሥራ አስፈጻሚ
ታዲያ የሰው ልጅ ከሕልውና ውጭ የሚሆንበትና ምድራችን የምትጠፋበት ጊዜ እየቀረበ ነው ማለት ነው? ከፊታችን ስላለው ጊዜ ልንሰጋ ይገባል? መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
መጪው ጊዜ ምን ይዞ ይመጣል?
መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው “ምድር . . . ለዘላለም ጸንታ ትኖራለች”፤ እንዲሁም ሰዎች በምድር ላይ “ለዘላለም ይኖራሉ።” (መክብብ 1:4፤ መዝሙር 37:29) ስለዚህ በሰው ልጆች ድርጊት ምክንያት ምድር አትጠፋም፤ እንዲሁም ለሰው ልጆች መኖሪያነት የማትስማማ ቦታ ልትሆን አትችልም።
ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ጥፋት እንደሚመጣ ይናገራል። ለምሳሌ ያህል፣ ‘ዓለም እንደሚያልፍ’ ይገልጻል።—1 ዮሐንስ 2:17
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዓለም ጥፋት ሲናገር ምን ማለቱ ነው? መልሱን ለማወቅ “በዓለም ላይ ጥፋት እየመጣ ነው? አፖካሊፕስ ምንድን ነው?” የሚለውን ርዕስ አንብብ።
በዓለም ላይ ጥፋት የሚመጣው መቼ ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ጥያቄ የሚሰጠውን መልስ ማወቅ ከፈለግክ “የዓለም መጨረሻ የሚመጣው መቼ ነው?” የሚለውን ርዕስ አንብብ።
አዎንታዊ የምትሆንበት ምክንያት አለህ
ዓለማችን በተለያዩ ችግሮች እየተፈተነች ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስ አዎንታዊ እንድንሆን ይረዳናል። እንዴት?
መጽሐፍ ቅዱስ ጠቃሚ ምክር ይዟል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) ለምሳሌ ያህል፣ የኑሮ ውጣ ውረዶችን በአዎንታዊነት መወጣት የምትችልበትን ጥበብ ያስተምርሃል፤ ስለዚህ ጉዳይ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት “የሚያስጨንቁ ነገሮችን መቆጣጠር የሚቻለው እንዴት ነው?” የሚለውን ርዕስ አንብብ።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ ወደፊት የተሻለ ጊዜ እንደሚመጣ እምነት የሚጣልበት ተስፋ ይሰጣል። (ሮም 15:4) አሁን ባለንበት ጊዜም ሆነ ወደፊት ምን እንደሚከሰት በግልጽ አስቀምጦልናል፤ ይህን ማወቃችን የዓለም ሁኔታ ቢመሰቃቀልም እንዳንሰጋ ይረዳናል።
መጽሐፍ ቅዱስ የያዘውን ሐሳብ ይበልጥ ማወቅ ትፈልጋለህ? በአስተማሪ እገዛ በነፃ የምንሰጠውን የመጽሐፍ ቅዱስ ኮርስ አሁኑኑ እንድትሞክረው እናበረታታሃለን።
a “የመዓት ቀን ሰዓት፣ በገዛ እጃችን በሠራናቸው አደገኛ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ዓለማችንን ለማጥፋት ምን ያህል እንደተቃረብን የዓለምን ሕዝብ ለማስጠንቀቅ የተዘጋጀ ንድፍ ነው። ተምሳሌታዊ ትርጉም ያለው ነው፤ በፕላኔቷ ላይ ሕልውናችን እንዲቀጥል ከተፈለገ ትኩረት ልንሰጣቸው የሚገቡ አደጋዎችን የሚያስታውሰን ማንቂያ ነው።”—ቡለቲን ኦቭ ዚ አቶሚክ ሳይንቲስትስ