ዓይነ ስውራንን ለማገዝ የተደረጉ ዝግጅቶች
በዓለም ዙሪያ፣ ሙሉ በሙሉ ማየት የተሳናቸው 43 ሚሊዮን ሰዎች እንዲሁም የማየት ውስንነትa ያለባቸው 295 ሚሊዮን ሰዎች እንዳሉ ይገመታል። የሚያሳዝነው ግን ብዙዎቹ ይበደላሉ ብሎም ግፍ ይፈጸምባቸዋል።
አምላክ ስለ ዓይነ ስውራን ምን ይሰማዋል? መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እነሱ ምን ይላል? የይሖዋ ምሥክሮችስ እነሱን ለማገዝ ምን ዝግጅቶች አድርገዋል?
አምላክ ስለ ዓይነ ስውራን ምን ይሰማዋል?
መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ይሖዋb ለዓይነ ስውራን በጣም ያስባል። ፈጽሞ እንዲበደሉ አይፈልግም፤ እሱ ከሚሰጠው ትምህርት እንዲጠቀሙ ይፈልጋል። ደግሞም መጪውን ጊዜ በደስታ እንዲጠብቁ የሚያደርግ ተስፋ ሰጥቷቸዋል።
ጥቅስ፦ “ዓይነ ስውሩን መንገድ የሚያሳስት የተረገመ ይሁን።”—ዘዳግም 27:18
ትርጓሜው፦ አምላክ ለጥንት ሕዝቦቹ የሰጠው ሕግ ዓይነ ስውራን እንዳይበደሉ ከለላ ያደርግ ነበር።
ጥቅስ፦ ‘አምላክ አያዳላም።’—የሐዋርያት ሥራ 10:34
ትርጓሜው፦ አምላክ በዓይነ ስውራን እና ማየት በሚችሉ ሰዎች መካከል ልዩነት አያደርግም፤ ሁሉንም እኩል ይወዳቸዋል።
ጥቅስ፦ ‘ኢየሱስ የብዙ ዓይነ ስውራንን ዓይን አበራ።’—ሉቃስ 7:21
ትርጓሜው፦ ኢየሱስ ምድር ላይ ሳለ የዓይን ብርሃናቸውን የመለሰላቸው ሰዎች ነበሩ፤ ይህም የአምላክ መንግሥት ወደፊት ለሚያደርገው ነገር ማሳያ ነው።
ጥቅስ፦ “የዓይነ ስውራን ዓይን ይገለጣል።”—ኢሳይያስ 35:5
ትርጓሜው፦ የአምላክ መንግሥት በቅርቡ ምድርን ማስተዳደር ሲጀምር ዓይነ ስውራን ሁሉ ማየት እንደሚችሉ አምላክ ቃል ገብቷል።
የይሖዋ ምሥክሮች ለዓይነ ስውራን ምን እገዛ ያደርጋሉ?
በዓለም ዙሪያ ያለን የይሖዋ ምሥክሮች፣ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን የተስፋ መልእክት ለዓይነ ስውራን እያበሰርን ነው። ይህን እያደረግን ያለነው እንዴት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስን እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ ማጥኛ ጽሑፎችን እና ቪዲዮዎችን አዘጋጅተናል፤ በብሬል፣ በትላልቅ ፊደላት እና በድምፅ ፎርማቶች ስለሚዘጋጁ ዓይነ ስውራን እና የማየት ውስንነት ያለባቸው ሰዎች በቀላሉ ሊጠቀሟቸው ይችላሉ።
ሳምንታዊ ስብሰባዎቻችን ዓይነ ስውራንን ጨምሮ ለሁሉም ሰው ክፍት ናቸው።
አስተማሪ ተመድቦላቸው መጽሐፍ ቅዱስን መማር ለሚፈልጉ አሳታፊ የመጽሐፍ ቅዱስ ኮርስ አዘጋጅተናል።c
እነዚህ ዝግጅቶች በሙሉ ክፍያ አይጠየቅባቸውም። ለምን? ኢየሱስ “በነፃ እንደተቀበላችሁ በነፃ ስጡ” ብሎ ስላዘዘን ነው።—ማቴዎስ 10:8
የይሖዋ ምሥክሮች ለዓይነ ስውራን ከልብ ያስባሉ። አብረውን ለሚያመልኩ ዓይነ ስውራን የእምነት አጋሮቻችን ድጋፍ እናደርጋለን። ለናሙና ያህል፣ ዓይነ ስውራን የሆኑ አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮችን የሕይወት ተሞክሮ እናጋራህ።
ታሊታ አልናሺ የምትኖረው ስዊድን ውስጥ ነው፤ ስትወለድ ጀምሮ ከፍተኛ የማየት ውስንነት አለባት። ወላጆቿ መጽሐፍ ቅዱስን ያስተማሯት እንዴት እንደሆነ እንዲሁም እሷና ቤተሰቧ ከእምነት አጋሮቻቸው ምን ድጋፍ እንደተደረገላቸው ተመልከት።
በአሜሪካ የሚኖረው ጄምስ ራያን ሲወለድ ጀምሮ መስማት የተሳነው ነው፤ በኋላ ላይ ደግሞ ዓይነ ስውር ሆነ። ሕይወቱ ትርጉም እንዲኖረው የረዳው ምን እንደሆነ ሲናገር ስማ።
ሲንቲያ ፓብሎ የምትኖረው ፊሊፒንስ ውስጥ ሲሆን ማየትም መስማትም የተሳናት ናት። በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት የእምነት አጋሮቿ የደገፏት እንዴት ነው? “በወረርሽኙ ወቅት አንድ ጉባኤ ማየትና መስማት ለተሳናት እህት ያደረገው ድጋፍ” የሚለው ርዕስ ላይ ተመልከት።
መጽሐፍ ቅዱስን ለማስተማር የትኞቹን አጋዥ መሣሪያዎች አዘጋጅተናል?
በብሬይል የተዘጋጁ ጽሑፎች። በተወሰኑ ቋንቋዎች ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ ወይም በከፊል በብሬይል አሳትመናል። (የቋንቋዎቹን ዝርዝር ለማግኘት “አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በብሬይል” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችንም በብሬይል እናዘጋጃለን። ብሬይል መማር ለሚፈልጉ ደግሞ የብሬይል መማሪያ (በአማርኛ አይገኝም) የሚል ጽሑፍ አዘጋጅተናል። ይህ ጽሑፍ የተዘጋጀው ዓይነ ስውራን፣ ማየት በሚችል ሰው እርዳታ በብሬይል ማንበብን እንዲማሩ ለመርዳት ታስቦ ነው።
በወረቀት የታተሙ የብሬይል ጽሑፎችን ለማግኘት አንድ የይሖዋ ምሥክር አነጋግር ወይም የይሖዋ ምሥክሮች መጥተው እንዲያነጋግሩህ ጥያቄ አቅርብ።
ለኖትቴከር መሣሪያዎችd የተዘጋጁ ፋይሎችን ከjw.org አውርድ።
በትላልቅ ፊደላት የሚታተሙና ጎላ ሊደረጉ የሚችሉ ኤሌክትሮኒክ ጽሑፎች። የማየት ውስንነት ያለባቸውን ሰዎች ለማገዝ ሲባል ብዙዎቹ ጽሑፎቻችን በትላልቅ ፊደላት ይታተማሉ። jw.org ድረ ገጻችን የተዘጋጀው ጎላ በሚደረግበት ጊዜም እንኳ ይዘቱን ለማንበብ እንዳያስቸግር ተደርጎ ነው። JW Library አፕሊኬሽናችን ላይ ደግሞ እንደ ግለሰቡ ፍላጎት ጽሑፉን ማተለቅ ይቻላል።
በትላልቅ ፊደላት የታተሙ ጽሑፎችን ለማግኘት አንድ የይሖዋ ምሥክር አነጋግር ወይም የይሖዋ ምሥክሮች መጥተው እንዲያነጋግሩህ ጥያቄ አቅርብ።
በወረቀት የሚታተመውን የትላልቅ ፊደላት ጽሑፍ በኤሌክትሮኒክ ቅጂ ማግኘት ከፈለግህ ከjw.org ላይ አውርድ።
በድምፅ የተቀረጹ ጽሑፎች። አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ከ200 በሚበልጡ ቋንቋዎች በድምፅ ተቀርጿል። ብዙዎቹ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቻችንም በድምፅ ተቀድተዋል። እነዚህ ቅጂዎች ብዙውን ጊዜ ሥዕሎችን የሚያብራራ መግለጫ አላቸው።
jw.org ድረ ገጽ እና JW Library አፕሊኬሽን ላይ የድምፅ ቅጂዎችን በቀጥታ አጫውት ወይም አውርድ።
እንደ ስክሪን ሪደር እና ዲጂታል ቶኪንግ ቡክ ፕሌየርe ላሉ ማንበቢያዎች የተዘጋጁ ፋይሎችን ከjw.org አውርድ።
የድምፅ መግለጫ ያላቸው ቪዲዮዎች።f የይሖዋ ምሥክሮች የድምፅ መግለጫ የተካተተባቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቪዲዮዎችን ያዘጋጃሉ፤ እነዚህ ቪዲዮዎች ከ100 በሚበልጡ ቋንቋዎች ይገኛሉ። የቪዲዮዎቹ ዓላማ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ጠቃሚ ምክር እንዲያስተውሉና ተግባራዊ እንዲያደርጉ መርዳት ነው።
ለአብነት ያህል፣ በሚከተሉት ዓምዶች ሥር ያሉ አንዳንድ ቪዲዮዎች የድምፅ መግለጫ አላቸው፦
ሳምንታዊና ዓመታዊ ስብሰባዎች። በዓለም ዙሪያ በየሳምንቱ ለትምህርትና ለአምልኮ የምንሰባሰብባቸው ጉባኤዎች አሉን። መጽሐፍ ቅዱስን የምንማርባቸው ዓመታዊ ፕሮግራሞችም እናዘጋጃለን። በእነዚህ ፕሮግራሞች ላይ ቪዲዮ ሲታይ የድምፅ መግለጫ የተካተተበትን ቪዲዮ መስማት የሚቻልበት አማራጭ ይዘጋጃል። ማየትም መስማትም የተሳናቸው ሰዎች በሚኖሩበት ጊዜ ደግሞ ከተቻለ ታክታይል በተባለ የመልእክት ማስተላለፊያ መንገድ (እጅ ለእጅ የምልክት ቋንቋ) ስብሰባው ይተረጎምላቸዋል። ስብሰባዎቻችን ለሁሉም ሰው ክፍት ናቸው፤ አድልዎና መድልዎ የለም።
ዓመታዊ ስብሰባዎቻችን ምን እንደሚመስሉ ተመልከት።
በኢየሱስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ ተገኝ፤ ይህ በዓመቱ ውስጥ ትልቅ ቦታ የምንሰጠው ፕሮግራም ነው።
ሆሴ ሉዊስ አያላ የሚኖረው ሜክሲኮ ውስጥ ነው። ሲወለድ ጀምሮ መስማት የተሳነው ነው፤ በ29 ዓመቱ ደግሞ ዓይነ ስውር ሆነ። ስብሰባዎቻችን በሕይወቱ ላይ ምን ለውጥ እንዳመጡና ጎበዝ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪ እንዲሆን ምን እገዛ እንደተደረገለት ተመልከት።
a “የማየት ውስንነት” ስንል ሊስተካከል የማይችልና ለዕለት ተዕለት ሕይወት እክል የሚፈጥርን የእይታ ችግር ማመልከታችን ነው። በዚህ ርዕስ ላይ “ዓይነ ስውር” የሚለው ቃል ሙሉ በሙሉ ማየት የማይችሉትንም ሆነ የማየት ውስንነት ያለባቸውን ሰዎች ያካትታል።
b ይሖዋ የአምላክ የግል ስም ነው። (መዝሙር 83:18) “ይሖዋ ማን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
c ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ኮርስ የሚሰጥበትን መንገድ እንዲያሳዩህ የይሖዋ ምሥክሮችን መጠየቅ ትችላለህ።
d ኖትቴከር ተንቀሳቃሽ ኤሌክትሮኒክ መሣሪያ ሲሆን የብሬይል ዲስፕሌይ ወይም በኮምፒውተር የተፈጠረ ድምፅ ይጠቀማል፤ ሁለቱንም ነገሮች ሊያካትትም ይችላል። ዲስፕሌዩ ላይ ያሉት ቁልፎች ወጣና ገባ እያሉ የብሬይል ፊደላትን ይጽፋሉ። ኖትቴከር፣ ብዙ ቦታ የሚይዙ በወረቀት የታተሙ የብሬይል ጽሑፎች ለማስቀረት ያግዛል።
e እንደ ስክሪን ሪደር እና ዲጂታል ቶኪንግ ቡክ ፕሌየር ያሉት ማንበቢያዎች፣ በኮምፒውተር የተፈጠሩ ወይም የተቀዱ ድምፆችን በመጠቀም ጽሑፍን ጮክ ብለው ያነባሉ። እነዚህ ቴክኖሎጂዎች፣ ተጠቃሚዎች ጽሑፉ ላይ ወደሚፈልጉት ቦታ እንዲሄዱ የሚያስችል ገጽታ አላቸው።
f የድምፅ መግለጫዎች፣ ቪዲዮ ላይ የሚካተቱ ሲሆን ስክሪኑ ላይ የሚታዩ ነገሮችን የሚናገሩ በድምፅ የተዘጋጁ ማብራሪያዎች ናቸው።