ነቅታችሁ ጠብቁ!
ማንነት ተኮር ወንጀሎች የማይኖሩበት ጊዜ ይመጣል—መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
በጥላቻ አነሳሽነት ማንነት ተኮር ወንጀሎች እንደተፈጸሙ መስማት የተለመደ ሆኗል። ሰዎች በዘራቸው፣ በሃይማኖታቸው፣ በፆታቸው ወይም በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ የጥቃት ዒላማ ይሆናሉ። እንዲህ ዓይነት ጥቃት ሲከሰት በማኅበረሰቡ ውስጥ ፍርሃት ይነግሣል፤ ብዙዎች የማይሽር የስሜት ጠባሳ ብሎም አካላዊ ጉዳት ይደርስባቸዋል። ከዚህ የከፋው ደግሞ ሕይወታቸውን የሚያጡ ይኖራሉ።
መጽሐፍ ቅዱስ አሁን ስላለንበት ጊዜ ሲናገር ሰዎች “ጨካኞች፣ ጥሩ ነገር የማይወዱ” እንዲሁም “ተፈጥሯዊ ፍቅር የሌላቸው” እንደሚሆኑ ይገልጻል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) ታዲያ ማንነት ተኮር ወንጀሎች የማይኖሩበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
ማንነት ተኮር ወንጀሎች የማይኖሩበት ጊዜ ይመጣል—እንዴት?
መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ክፋት ማስወገድ የሚችለው አምላክ እንደሆነና በቅርቡ ይህን እንደሚያደርግ ይገልጻል።
“ክፉ አድራጊዎች ይጠፋሉ . . . የዋሆች ግን ምድርን ይወርሳሉ፤ በብዙ ሰላምም እጅግ ደስ ይላቸዋል።” (መዝሙር 37:9-11) ክፉ ሰዎች ለዘላለም ሌሎችን እየጎዱ እንዲኖሩ አምላክ አይፈቅድም።
“[አምላክ] እንባን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም።” (ራእይ 21:4) አምላክ፣ የጥቃት ሰለባዎች ከደረሰባቸው አካላዊ፣ አእምሯዊና ስሜታዊ ጉዳት እንዲፈወሱ ያደርጋል።
“ሰዎች ከሞት [ይነሳሉ]።” (የሐዋርያት ሥራ 24:15) አምላክ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከሞት ያስነሳል፤ ከእነዚህም መካከል በማንነት ተኮር ወንጀል ምክንያት በአጭሩ የተቀጩ ሰዎች ይገኙበታል።
ዛሬ ላይ የጥላቻን ሰንሰለት መበጠስ
መጽሐፍ ቅዱስ ወደፊት ብሩህ ጊዜ እንደሚመጣ ከመናገር ባለፈ፣ ዛሬ በዓለም ላይ ተስፋፍቶ የሚታየውን ጥላቻ ለማሸነፍ የሚረዱ ምክሮችን ይዟል። መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ረገድ የያዘውን ሐሳብ እንድትመረምር እናበረታታሃለን፤ ለምሳሌ ለሚከተሉት ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል፦
ብዙ ሰዎችን ለጥቃት የሚያነሳሳውን ጥላቻ ለማሸነፍ ዛሬ ላይ ምን ማድረግ እንችላለን? “የጥላቻን ሰንሰለት መበጠስ” የሚል ርዕስ ባለው መጠበቂያ ግንብ መጽሔት ላይ የቀረበውን የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ተመልከት።
አምላክ በሰው ልጆች ላይ የሚደርሰውን መከራ ጣልቃ ገብቶ የማያስቆመው ለምንድን ነው? አምላክ መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው? የሚለው ቪዲዮ ላይ የቀረበውን ግልጽ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማብራሪያ ተመልከት።