ካሮል አፕልቢ | የሕይወት ታሪክ
ይሖዋ አምስት ልጆቼን ጥሩ አድርጌ እንዳሳድግ ረድቶኛል
ዕድሜዬን በሙሉ የኖርኩት በኖርዝ ዮርክሻየር፣ እንግሊዝ ማልተን የተባለች ከተማ አቅራቢያ ነው። ይህ አካባቢ ተራሮች፣ ዛፎችና አረንጓዴ ሜዳዎች የሞሉበት እንዲሁም ጠመዝማዛ መንገዶችና የሚያማምሩ የድንጋይ ቤቶች ያሉበት ነው። ልጆች ለማሳደግ ምቹ ቦታ ነው። ያም ሆኖ አምስት ልጆችን ማሳደግ ቀላል አልነበረም። እስቲ ታሪኬን ላጫውታችሁ።
ያደግኩት ገጠራማ አካባቢ ነው፤ ዶሮዎች፣ አሳማዎችና ከብቶች ነበሩን። ቤተሰባችን ማለትም ወላጆቼ፣ ሁለት ወንድሞቼና ሁለት እህቶቼ ለኑሮ የሚያስፈልገንን ነገር የምናገኘው ከእነዚህ እንስሳት ነበር። እርግጥ ይህ ዓይነቱ ሕይወት አድካሚ ሥራ አለው፤ ሆኖም ደስተኞች ነበርን።
በ14 ዓመቴ እንስሳት በምናረባበት የገጠር ቤታችን።
ቤተሰባችን የሜቶዲስት ቤተ ክርስቲያን አባል ነበር። አባቴ ጎበዝ ዘማሪ ስለሆነ በመዘምራን ቡድኑ ውስጥ ያገለግላል። በአካባቢያችን ያሉ ሌሎች ቤተ ክርስቲያናትም ወደ እነሱ መጥቶ እንዲዘምር ይጋብዙታል። እኔም በአብዛኛው አብሬው እሄዳለሁ። ትላልቅ የሆኑትና ከድንጋይ የተሠሩት የቤተ ክርስቲያናቱ ሕንፃዎች ክረምት ላይ በጣም ይቀዘቅዛሉ። አባባ የሚዘምረው ከተሰብሳቢዎቹ ፊት ቆሞ ነው። የፊተኞቹ ወንበሮች ላይ እንዲቀመጡ የሚፈቀድላቸው የተከበሩ ሰዎች ብቻ ስለሆኑ እኔ የምቀመጠው ከኋላ ነበር። ያም ሆኖ እሱ ሲዘምር መስማት በጣም ያስደስተኝ ነበር።
አያቴ ማለትም የአባቴ እናት በየሳምንቱ እሁድ እሁድ እየመጣች ትጠይቀን ነበር። የሚያሳዝነው ግን 16 ዓመቴ አካባቢ አረፈች። እቀርባት ስለነበር በጣም አዘንኩ። ‘የት ነው ያለችው? ድጋሚስ አገኛት ይሆን?’ እያልኩ ማሰብ ጀመርኩ። ስለዚህ ለጥያቄዎቼ መልስ ለማግኘት ወደ አንዲት ጠንቋይ ሄድኩ። የጠንቋይዋ ቤት ቀዝቃዛ፣ ቁሽሽ ያለና የሚያስፈራ ነበር። በተደጋጋሚ እየሄድኩ አያቴ ያለችበትን ብጠይቃትም ስለዚህ ጉዳይ ምንም ልትነግረኝ አልቻለችም።
ከጥቂት ዓመታት በኋላ፣ የይሖዋ ምሥክር የሆነ አንድ የአባቴ ዘመድ በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ እንድገኝ ጋበዘኝ። ወጣ ያለ ሃይማኖት ነው ሲባል ብሰማም ለመሄድ ተስማማሁ። ስብሰባው ላይ ያገኘኋት አንዲት ደስ የምትል ሴት መጽሐፍ ቅዱስን መማር እፈልግ እንደሆነ ጠየቀችኝ። ስለ ይሖዋ መማር የጀመርኩት በዚህ መልኩ ነው። እርግጥ እናቴ የይሖዋ ምሥክሮች የሚጠቀሙበት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም የተሳሳተ እንደሆነ ስለነገረችኝ መጀመሪያ ላይ የምጠቀመው የራሴን መጽሐፍ ቅዱስ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ግን እናቴ የነገረችኝ ነገር ልክ እንዳልሆነ ተረዳሁ።
ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚያስተምሩኝን ነገር በጣም ወደድኩት። በተለይ አያቴ መቃብር ውስጥ ‘ተኝታ’ እንዳለችና ወደፊት ከሞት ተነስታ ዳግመኛ ልንገናኝ እንደምንችል መማሬ በጣም አስደሰተኝ!a መጽሐፍ ቅዱስ መማሬን ስቀጥል ስለ አምላክም ሆነ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ምንም እንደማላውቅ ተገነዘብኩ። አባቴም ቢሆን ለብዙ ዓመታት ቤተ ክርስቲያን ቢሄድም ስለ አምላክ ያን ያህል የሚያውቀው ነገር አልነበረም። ብዙ ጊዜ “ታላቁ ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ምራኝ” የሚል መዝሙር እንዘምር የነበረ ቢሆንም ስለ ማን እየዘመርን እንዳለን እንኳ አናውቅም ነበር።
ትዳር መሠረትኩ፤ ከዚያም ያልጠበቅኩት ተቃውሞ ገጠመኝ
የወንድ ጓደኛዬ ኢየን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ማወቅ ስለፈለገ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ማጥናት ጀመረ። የተማረው ነገር በሕይወቱ ውስጥ አንዳንድ ለውጦችን እንዲያደርግ አነሳሳው፤ እንዲያውም ሲጋራ ማጨስም አቆመ። መስከረም 1971 ትዳር መሠረትን። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ የኢየን እናት አረፈች። በዚህ ጊዜ እምነታችንን የሚፈትን ሁኔታ ተፈጠረ። የኢየን ቤተሰቦችና ወዳጆች ከለቅሶው ጋር በተያያዘ አንዳንድ ዝግጅቶችን አድርገው ነበር፤ እኛም እንድንገኝ ይጠብቁብን ስለነበር እንዲህ ባሉ የተወሰኑ ዝግጅቶች ላይ ተገኘን። ችግሩ ግን በእነዚህ ዝግጅቶች ላይ አብዛኞቹ ያጨሱና ብዙ ይጠጡ ነበር። በመሆኑም ኢየን ወደተዋቸው ልማዶች ለመመለስ በጣም ተፈተነ።
የሚያሳዝነው፣ ኢየን ለፈተናው እጅ በመስጠቱ እውነትን አጥብቆ መያዝ አቃተው። ጥናቱን ችላ ማለትና ስብሰባ መቅረት ጀመረ። እኔ ግን መጽሐፍ ቅዱስን መማር፣ ስብሰባ ላይ መገኘትና አገልግሎት መውጣት በጣም ያስደስተኝ ነበር። ስለዚህ በጥናቴ ገፍቼ መጋቢት 9, 1972 ተጠመቅኩ። ኢየን ስጠመቅ ሊያየኝ መጥቶ ነበር። ቀስ በቀስ ግን ይቃወመኝ ጀመር። ተቃውሞውን የጀመረው ጽሑፎችን እንዳላነብ በመከልከል ነው። ከዚያም አገልግሎት እንዳልወጣ ከለከለኝ። ይባስ ብሎ ደግሞ አካባቢያችን ወዳለ መጠጥ ቤት አብሬው ሄጄ የገና በዓልን እንዳከብር ወይም የልደት ግብዣዎች ላይ እንድገኝ ጫና ያደርግብኝ ጀመር። የራስነት ሥልጣኑን ለማክበር ስል በእነዚህ ግብዣዎች ላይ የተገኘሁባቸው ወቅቶች አሉ። ሆኖም በእነዚህ ወቅቶች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚጋጭ ምንም ነገር ላለማድረግ እጠነቀቃለሁ።b ለዚህም እንዲረዳኝ ስል ወደ መጸዳጃ ቤት ሄጄ በተደጋጋሚ ወደ ይሖዋ እጸልያለሁ፤ ለእሱ ታማኝ እንድሆንና ሕሊናዬን የሚያቆሽሽ ምንም ነገር እንዳላደርግ እንዲረዳኝ እጠይቀዋለሁ። ይሖዋም ሁልጊዜ ይረዳኝ ነበር።
ከጊዜ በኋላ እኔና ኢየን ሦስት ወንዶች ልጆች ወለድን፤ ፊሊፕ፣ ናይጀል እና አንድሩ ይባላሉ። ባለቤቴ የከባድ መኪና ሹፌር ስለነበር አብዛኞቹን የሳምንቱን ቀናት ቤት አይኖርም። በአንድ በኩል ለእሱ ጥሩ ሚስት ለመሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ለይሖዋ ምርጤን ለመስጠት ብርቱ ጥረት ማድረግ አስፈልጎኛል። ኢየን ቤት በማይኖርበት ጊዜ አገልግሎት እወጣለሁ። ቅዳሜና እሁድ እሱ ወደ ቤት ሲመለስ ደግሞ አብሬው ጊዜ አሳልፋለሁ። በተጨማሪም ልጆቻችን ፊት ስለ እሱ መጥፎ ነገር ላለመናገር እጠነቀቅ ነበር።
በጉባኤ ውስጥ ብዙ ወዳጆችን አፈራሁ። ከእነዚህ ወዳጆቼ መካከል አንዳንዶቹን ወላጆቼን ለመጠየቅ ስሄድ ይዤያቸው እሄድ ነበር። በዚህም የተነሳ ወላጆቼ እነዚህን ወንድሞችና እህቶች ወደዷቸው። በአንድ ወቅት በጉባኤያችን ያለ በጣም የምንወደው ወንድም ሲሞት እናቴ የስብሰባ አዳራሹ ውስጥ በተደረገው የቀብር ንግግሩ ላይ ተገኘች። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ እናቴ፣ አባቴ፣ ወንድሜ ስታንሊ እና ባለቤቱ አቭሪል መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመሩ፤ ከዚያም ተጠመቁ።
ስታንሊ እና አቭሪል አንድ ወንድና አንዲት ሴት ልጅ አሏቸው። እኔና አቭሪል ልጆቻችንን ይዘን አገልግሎት መውጣት ያስደስተን ነበር። እርግጥ ሁለታችንም መኪና አልነበረንም። ስለዚህ ልጆቻችንን በጋሪ እየገፋን ረጅም ርቀት በእግር እንጓዛለን። አንድሩ ጋሪው ውስጥ፣ ናይጀል ጋሪው ላይ ይቀመጣሉ፤ ፊሊፕ ደግሞ የጋሪውን እጀታ ይዞ ከጎን ከጎን እየተከተለ እናገለግላለን። በዚህ መልኩ ማገልገል በጣም ያስደስተን ነበር።
ፊሊፕ፣ ናይጀል፣ አባቴና እኔ ለትልቅ ስብሰባ ሄደን፤ የምናድረው ድንኳን ውስጥ ነበር
ልጆቼን በይሖዋ መንገድ ማሳደግ
ከሦስቱ ወንዶች ልጆቻችን በኋላ ሁለት ሴቶች ልጆች ወለድን፤ ካሮላይን እና ዴቢ ይባላሉ። ልጆቼን በይሖዋ መንገድ ለማሳደግ ስለቆረጥኩ መጽሐፍ ቅዱስ ለወላጆች የሚሰጠውን ምክር ሁሉ ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት አደርግ ነበር። ልጆቼ ይሖዋን ለማገልገል የገባሁትን ቃል አክብጄ እንደምመለከት እንዲያዩ ስለምፈልግ ማንኛውንም ነገር በይሖዋ መንገድ ለማድረግ እጥራለሁ።
መጀመሪያ በቃሌ ከያዝኳቸው ጥቅሶች አንዱ 1 ቆሮንቶስ 15:33 ነው፤ ጥቅሱ “መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን አመል ያበላሻል” ይላል። አንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ አንዲት እህት ልጆቿን ምን ብላ ትመክራቸው እንደነበር ስትናገር ሰማሁ። “የትምህርት ቤት ጓደኞቻችሁን እዚያው ትምህርት ቤት ተዉአቸው” ትላቸው ነበር። እኔም ልጆቼን እንዲህ ብዬ መምከር አለብኝ ብዬ አሰብኩ፤ ግን ይህን እንዲያደርጉ መርዳት ቀላል አልነበረም። አንዳንዴ ወንዶቹ ልጆቼ ከቤት ተደብቀው ወጥተው አብረዋቸው ከሚማሩ ልጆች ጋር ኳስ ይጫወታሉ። እርግጥ አብዛኞቹ ጓደኞቻቸው መጥፎ አልነበሩም። ሆኖም ይሖዋን ስለማያመልኩ ጥሩ ያልሆነ ነገር የሚናገሩበትና የሚያደርጉበት ጊዜ አለ።
በአንድ ወቅት ወንዶች ልጆቼን “ከትምህርት ቤት በኋላ ኳስ መጫወት ከፈለጋችሁ ከእኔ ጋር መጫወት ትችላላችሁ” አልኳቸው። ግን ይሄ የሚያዛልቅ አልነበረም፤ ምክንያቱም እኔ ኳስ ጨዋታ ጨርሶ ሊሆንልኝ አልቻለም! ያም ቢሆን ልጆቼ ጓደኞቻቸውን በጥበብ መምረጥ እንዳለባቸው ማስተማሬን ቀጠልኩ። ደስ የሚለው በጊዜ ሂደት ልጆቼ ይሖዋን ከማያመልኩ ልጆች ጋር መሆን ሳያስፈልጋቸው ራሳቸውን ችለው መጫወት ጀመሩ።
ሁሌም ከአእምሮዬ የማይጠፋው ሌላው ጥቅስ ደግሞ 1 ዮሐንስ 2:17 ነው፤ ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “ዓለምም ሆነ ምኞቱ ያልፋሉ፤ የአምላክን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል።” የሰይጣን ዓለም እንደሚያልፍ አውቃለሁ፤ ስለዚህ ትኩረት ያደረግኩት ልጆቼ መንፈሳዊ ግቦችን እንዲከታተሉና ለዘላለም የአምላክን ሞገስ እንዲያገኙ በመርዳት ላይ ነው። ቀላልም ሆነ ከባድ ችግር ሲያጋጥመኝ ወደ ይሖዋ እጸልያለሁ፤ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ መመሪያ ለማግኘትም ጥረት አደርጋለሁ። ለልጆቼ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል ስለማሳያቸው መመሪያ እየሰጠኋቸው ያለሁት እኔ ሳልሆን ይሖዋ እንደሆነ ይገነዘባሉ። በተጨማሪም በቃል ብቻ ሳይሆን ምሳሌ በመሆንም እነሱን ለማሠልጠን ጥረት አድርጌያለሁ። ልጆቼም ሥልጠናውን ተቀብለው ሥራ ላይ አውለውታል። ለምሳሌ እያንዳንዳቸው ከትንሽነታቸው ጀምሮ የራሳቸው ተመላልሶ መጠየቆች ነበሯቸው፤ ይህም አገልግሎትን እንዲወዱት አድርጓቸዋል።
ስብሰባ መገኘት ለድርድር የማቀርበው ጉዳይ አልነበረም። በአንድ ወቅት በሳምንቱ መሃል ስብሰባዎች ላይ ልጆቹ በጣም እንደሚደክማቸው አስተዋልኩ። ስለዚህ አንድ መፍትሔ አበጀሁ፦ ስብሰባ ያለን ቀን ላይ ከትምህርት ቤት ካመጣኋቸው በኋላ በጊዜ መክሰሳቸውን አበላቸዋለሁ፤ ከዚያም ትንሽ እንተኛለን። በዚህ መልኩ ችግሩ ተፈታ። ስብሰባ የምንቀረው አንዳችን ከታመምን ብቻ ነበር። በዚህ ጊዜም ቢሆን ትምህርቱን ቤታችን እንወያይበታለን። ቴሌቪዥን መክፈት የሚፈቀደው ከዚያ በኋላ ነው። ኢየን ድንገት ከመጣብን ግን ተሯሩጠን መጽሐፎቻችንን እንደብቅና ቲቪውን እንከፍታለን።
ለቤተሰብ አምልኮም ትልቅ ቦታ እንሰጣለን። አንዳንዴ ስለ ቤቴልና ልጆቹ የትኛው የቤቴል ዲፓርትመንት ውስጥ መሥራት እንደሚፈልጉ እናወራ ነበር።
የምወዳቸው ልጆቼ፤ ከግራ ወደ ቀኝ፦ ፊሊፕ፣ ካሮላይን፣ ዴቢ፣ አንድሩ እና ናይጀል
ግባችን አቅኚ መሆን ነበር
የመጀመሪያው ልጄ ፊሊፕ 16 ዓመት ሲሞላው ሁለት የሥራ አማራጮች ቀረቡለት፤ አንደኛው ሙሉ ጊዜውን የሚይዝ የመካኒክነት ሥራ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ሙሉ ጊዜ መሥራት የማይጠይቅ መስኮት የማጽዳት ሥራ ነበር። ፊሊፕ መስኮት የማጽዳቱን ሥራ አልፈለገውም፤ ምክንያቱም የሙሉ ጊዜ ሥራ በመሥራት ቤተሰቡን በገንዘብ መርዳት እንዳለበት ተሰምቶት ነበር። እኔ ግን ቤተሰቡን የማስተዳደር ኃላፊነት ያለበት እሱ ሳይሆን አባቱ እንደሆነ አስረዳሁት። ደግሞም የሚያስፈልገንን ነገር አጥተን እንደማናውቅ ነገርኩት። “መስኮት እንደማጽዳት ያለ ሙሉ ጊዜህን የማይዝ ሥራ ቶሎ አቅኚ ለመሆን ያስችልሃል” አልኩት።
ፊሊፕ ትምህርቱን እንደጨረሰ የዘወትር አቅኚ ሆነ፤ እኔ ደግሞ ረዳት አቅኚ ሆንኩ። ከጊዜ በኋላ ሁለተኛው ልጄ ናይጀልም ትምህርቱን ጨርሶ አቅኚ ሆነ፤ በዚህ ጊዜ ‘እኔም እኮ ቢያንስ ለአንድ ዓመት አቅኚ ከሆንኩ ከልጆቼ ጋር ማገልገልና የአቅኚዎች ትምህርት ቤት መማር እችላለሁ’ ብዬ አሰብኩ። ስለዚህ አቅኚ ሆንኩ። ደግሞም እንዳሰብኩት ከናይጀል ጋር በአቅኚዎች ትምህርት ቤት መካፈል ቻልኩ።
የአቅኚነት አገልግሎትን በጣም ወደድኩት፤ ደግሞም በዚህ መልኩ ይሖዋን ማገልገሌ ለልጆቼ ጥሩ ምሳሌ ለመሆን እንደሚያስችለኝ ተገንዝቤያለሁ። ይሖዋ ይመስገን፣ ላለፉት 35 ዓመታት በአቅኚነት እያገለገልኩ ነው። ኢየን አቅኚ መሆኔን ቢያውቅ ኖሮ ሊያስቆመኝ መሞከሩ አይቀርም ነበር። እኔም ይህን ስላወቅኩ አገልግሎት የምወጣበትን ሰዓት አስተካከልኩ፤ ሁሌም አገልግሎት የምወጣው በሳምንቱ መሃል እሱ በሥራ ምክንያት ሲጓዝ ብቻ ነው። ቤት በሚሆንበት ጊዜ ግን ሁሌም አብሬው እሆናለሁ።
ከጊዜ በኋላ ልጄ ናይጀል ቤቴል ለማገልገል አመልክቶ ተጠራ። በቤቴል ጥሩ ወዳጆች ያፈራ ሲሆን ግሩም ሥልጠናም አግኝቷል። ይህም ጎልማሳ ክርስቲያን እንዲሆን ረድቶታል። ፊሊፕ እና አንድሩ ደግሞ የአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ገብተው ሠልጥነዋል።c በእኔ አመለካከት ወደዚያ ትምህርት ቤት ስሸኛቸው ልጆች እንደነበሩ፣ ሲመለሱ ግን ሙሉ ሰው ሆነው እንደመጡ ይሰማኛል። (1 ጴጥሮስ 5:10) እውነት ለመናገር ይሖዋ ሕዝቦቹን የሚያሠለጥንባቸው ትምህርት ቤቶች በሙሉ ልዩ ናቸው። ልጆቼ ላገኙት ሥልጠና ይሖዋንና ድርጅቱን ከልቤ አመሰግናለሁ።
ወደ አገልግሎት እየሄድኩ
ተፈታታኝ ሁኔታዎች
ባለፉት ዓመታት ውስጥ የተለያዩ ተፈታታኝ ሁኔታዎች አጋጥመውኛል። ከባድ የምለው አንዱ ፈተና የባለቤቴ ታማኝ አለመሆን ነው። ለ33 ዓመታት በትዳር ከኖርን በኋላ ሌላ ሰው ወዶ ትቶኝ ሄደ። ያጋጠመኝ ሌላው ከባድ ነገር ደግሞ የወላጆቼ በዕድሜ መግፋት ነው። የሚያሳዝነው መጋቢት 1997 አባቴ አረፈ። በዚህ ጊዜ እናቴ ብቻዋን ቀረች። በመሆኑም በከባድ ሐዘንና የብቸኝነት ስሜት ተዋጠች። በዚያ ላይ እናቴ መኪና መንዳት አትችልም። ስለዚህ እደውልላትና “በመኪና ወጣ ብለን ተመላልሶዎቼን አነጋግረን እንምጣ?” እያልኩ እጠይቃት ነበር። ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ እሷም አቅኚ ለመሆን ወሰነች። ይህም ሕይወቷን እንደ አዲስ ለመጀመር አስችሏታል። እስከሞተችበት ጊዜ ድረስ ለአሥር ዓመት ያህል በዚህ አገልግሎት በደስታ ተካፍላለች።
ልጆቼ ይሖዋን ለማገልገል ወይም ላለማገልገል የራሳቸውን ውሳኔ ማድረግ እንዳለባቸው አውቃለሁ። የእነሱን ውሳኔ መቆጣጠር አልችልም። እኔ የማደርገውን ግን መቆጣጠር እችላለሁ። ይህን ስለተገነዘብኩ የአምላክን መመሪያ ለመከተልና በቃልም ሆነ በተግባር ለእነሱ ጥሩ ምሳሌ ሆኜ ለመገኘት የቻልኩትን ሁሉ አድርጌያለሁ። ልጆቼም ይሖዋን ለማገልገል በመምረጣቸው በጣም ደስተኛ ነኝ።d አምስት ልጆችን በእውነት ቤት ውስጥ ማሳደግ ቀላል ባይሆንም ይሖዋ ልጆቼን ጥሩ አድርጌ እንዳሳድግ ረድቶኛል።
በአሁኑ ጊዜ ከልጆቼ ጋር
a ስንሞት ምን እንሆናለን? የሚለውን ቪዲዮ ተመልከት።
b ለዘላለም በደስታ ኑር! መጽሐፍ ተጨማሪ ሐሳብ 5 ላይ የሚገኘውን “በዓላት” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
c ይህ ትምህርት ቤት በመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት ተተክቷል።
d በአሁኑ ጊዜ ፊሊፕ በአየርላንድ የቲኦክራሲያዊ ትምህርት ቤቶች አስተማሪ ሆኖ ያገለግላል። ናይጀል በእንግሊዝ የትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሽ አገልጋይ ነው። አንድሩ የጉባኤ ሽማግሌ ሲሆን በአቅኚነት አገልግሎት 30 ዓመት ሆኖታል። ካሮላይን ለአምስት ዓመት በአቅኚነት አገልግላለች። ዴቢ ደግሞ የምትኖረው ከእኔ ጋር ነው፤ በአገልግሎት ታግዘኛለች።