ፒተር ሃማዴ | የሕይወት ታሪክ
ይሖዋ ጥበብ ያለበት ውሳኔ እንድናደርግ ረድቶናል
የተወለድኩት በ1952 ካርሎቪ ቫሪa የተባለች ከተማ ውስጥ ነው፤ ይህች ከተማ የምትገኘው በቀድሞዋ ቼኮስሎቫኪያ ምዕራባዊ ጫፍ፣ በጀርመን ድንበር አቅራቢያ ነው። እኔና ታላቅ ወንድሜ ሚላን ጀርመናውያን ስለሆንን ትምህርት ቤት ውስጥ ብዙ በደል ይደርስብን ነበር። በዚህ የተነሳ በ1966 ቤተሰባችን ወደ ፍራንክፈርት፣ ጀርመን ተዛወረ።
ወላጆቼ የይሖዋ ምሥክሮች ነበሩ። የሚያሳዝነው ግን ገና ትንሽ ልጅ እያለሁ ከጉባኤ ተወገዱ። ስለዚህ ያደግኩት እውነት ውስጥ አይደለም።
ከጊዜ በኋላ ወላጆቼ ወደ እውነት ተመለሱ። ወንድሜ ሚላንም የተማረውን እውነት ስለወደደው በሃኖቨር በሚደረግ አንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ ለመጠመቅ ወሰነ። እኔም ከእሱ ጋር አብሬ ለመጠመቅ ወሰንኩ። በወቅቱ 15 ዓመቴ ነበር። ከተጠመቅኩ ብዙም ሳይቆይ ግን ወደ በርሊን እንድሄድ እንዲፈቅዱልኝ ወላጆቼን አሳመንኳቸው። እዚያ ሄጄ የሥነ ጥበብ ትምህርት ተማርኩ።
በሠዓሊነት ሙያ እየሠለጠንኩ ሳለ በአእምሮዬ የሚጉላሉ ሁለት ጥያቄዎች ነበሩ። ‘በእርግጥ ፈጣሪ አለ? መጽሐፍ ቅዱስስ በእርግጥ የአምላክ ቃል ነው?’ እያልኩ ራሴን እጠይቅ ነበር። ሥነ ጥበብ ስማር እንዳስተዋልኩት በተፈጥሮ ላይ የሚታየውን ውበት በሥዕል ለማስቀመጥ ብዙ ሥራ ይጠይቃል። ያን ሁሉ ተጨንቀን የሣልነው ሥዕል ግን የራሱን የተፈጥሮን ያህል ውበት የለውም። ስለዚህ እነዚህ ሥዕሎች በአጋጣሚ የተገኙ ካልሆኑ በተፈጥሮ ላይ ያለው ውበትም በአጋጣሚ ሊመጣ አይችልም ብዬ ደመደምኩ።
ለሁለተኛው ጥያቄዬ መልስ ያገኘሁት ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች በትክክል እንደተፈጸሙ በሚያረጋግጡ የጥንት ታሪኮች ላይ ምርምር በማድረግ ነው። ቀስ በቀስ መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥ የአምላክ ቃል እንደሆነ እርግጠኛ እየሆንኩ ሄድኩ።—1 ተሰሎንቄ 2:13
ከሣልኳቸው ሥዕሎች መካከል አንዱ፣ 1980
በግሌ ካደረግኩት ምርምር በተጨማሪ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ በግለሰብ ደረጃ ትኩረት ሰጥቶ ረድቶኛል። ከእሱ ጋር ያደረግኳቸው ረጅም ውይይቶች በጣም ጠቅመውኛል። በሕይወቴ ውስጥ ትልቁን ቦታ የምሰጠው ለሠዓሊነት ሙያዬ ነበር፤ በይሖዋ ላይ ያለኝ እምነት ደረጃ በደረጃ እያደገ ሲሄድ ግን ይህ ተቀየረ። በ1972 በርሊን ውስጥ አቅኚ ሆኜ ማገልገል ጀመርኩ፤ ይህ በሕይወቴ ውስጥ ካደረግኳቸው ምርጥ ውሳኔዎች አንዱ ነው። እርግጥ መጀመሪያ ላይ ያሰብኩት ለሦስት ወር ብቻ በአቅኚነት ለማገልገል ነበር።
አገልግሎቴን ማስፋት
በርሊን ውስጥ አቅኚ ሆኖ ማገልገል በጣም ከባድ ነበር። ምሥራቹ በዚህች ከተማ ወደ 100 ለሚጠጉ ዓመታት የተሰበከ ቢሆንም ብዙም ምላሽ የሚሰጥ ሰው አልነበረም። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ፈቃደኛ የሆነ ሰው ሳገኝ ተአምር እንደሆነ ተሰማኝ። ይህ አጋጣሚ በይሖዋ እርዳታ የትም ቦታ መስበክ እንደምችል ስላሳመነኝ በአቅኚነቴ ለመቀጠል ወሰንኩ።
ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ ቅርንጫፍ ቢሮው የሰርቦ-ክሮሽያኛb ቋንቋን መማር እችል እንደሆነ ጠየቀኝ፤ ይህን ቋንቋ ተምሬ ለሥራ ወደ ጀርመን ለመጡ ዩጎዝላቪያውያን እንድሰብክ ተፈልጎ ነበር። እኔም ግብዣውን በደስታ ተቀበልኩ። ከዚያም በፍራንክፈርት እያገለገልኩ በቅርቡ ከጊልያድ ትምህርት ቤት ከተመረቁት ከሃንስ ስሞድ እና ከባለቤቱ ከሶንያ ጋር ሰርቦ-ክሮሽያኛ ተማርኩ። ለሦስት ወራት ከእነሱ ጋር ከቆየሁ በኋላ በሽቱትጋርት ልዩ አቅኚ ሆኜ እንዳገለግል ተመደብኩ። በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ማለትም ከ1973 እስከ 1975 ባለው ጊዜ ውስጥ ደግሞ ከአምስት የተለያዩ አቅኚዎች ጋር በተለያዩ ቦታዎች አገልግያለሁ።
ከጊዜ በኋላ በካርልዝሩወ በሚገኝ የሰርቦ-ክሮሽያኛ ቡድን ውስጥ እንዳገለግል ተመደብኩ። እዚያ እያለሁ ሌንካ የተባለች ታታሪ ልዩ አቅኚ እህት ተዋወቅኩ። ሌንካን እንዳወቅኳት ነው የወደድኳት። ብዙም ሳይቆይ ተጋባንና የሕይወት አጋሬ ሆነች። ከተጋባን ከጥቂት ጊዜ በኋላ ማለትም በ1978 በወረዳ ሥራ እንድንካፈል ተጋበዝን፤ ከዚያም በዩጎዝላቪያ ቋንቋዎች የሚመሩ ጉባኤዎችን መጎብኘት ጀመርን።
ከሌንካ ጋር
ከባድ ውሳኔ
ለአሥር ዓመት ያህል በተለያዩ የአውሮፓ ክፍሎች ተበታትነው የሚገኙ ቡድኖችንና ጉባኤዎችን ስንጎበኝ ቆየን። ይህ ዓይነቱ ሕይወት አስደሳች ቢሆንም በጊዜ ሂደት ጫና እየፈጠረብን መጣ። ሌንካ አቅሟ በሚሟጠጥበት ጊዜ ከማረፍ ይልቅ ጭራሽ ይበልጥ መሥራት እንዳለባት ይሰማት ነበር። ይህ የጥበብ እርምጃ አልነበረም፤ ግን በወቅቱ፣ ያለን አማራጭ ይሄ ብቻ እንደሆነ ተሰምቶን ነበር። ትክክለኛውን አቅጣጫ እንዲያሳየን ይሖዋን በጸሎት ለመንነው።
በወረዳ ሥራ ስንካፈል
አንድን ሐኪም ባማከርንበት ወቅት ለጸሎታችን መልስ አገኘን። አካላዊና ስሜታዊ ጤንነታችንን ከግምት ማስገባትና አቅማችንን ያገናዘበ ሕይወት መምራት እንዳለብን በደግነት መከረን። (ሚክያስ 6:8) በዚህ ጊዜ የወረዳ ሥራችንን ማቆም እንዳለብን ተገነዘብን፤ ግን ይህንን እውነታ መቀበል ቀላል አልነበረም። ያለንበትን ሁኔታ በተመለከተ አንዳንድ በቤቴል ያሉ ተሞክሮ ያላቸው የበላይ ተመልካቾችን አማከርን። እነሱም በኦስትሪያ ቅርንጫፍ ቢሮ የሰርቦ-ክሮሽያኛ ቋንቋ ተርጓሚዎች ሆነን እንድናገለግል ሐሳብ አቀረቡልን፤ ይህ ፈጽሞ ያልጠበቅነው ነገር ነው። እንዲህ ዓይነት ማስተካከያ ማድረጋችን ሌንካ፣ ይሰማት ከነበረው ከባድ የመዛል ስሜት ቀስ በቀስ እንድታገግም ረዳት። ይሖዋ ጥበበኛ አማካሪዎች በመስጠት፣ የችኮላ ውሳኔ ከማድረግ ጠብቆናል።—ምሳሌ 15:22
በጦርነት ወቅት ያደረግናቸው ከባድ ውሳኔዎች
እኔና ሌንካ በቪየና፣ ኦስትሪያ ለሁለት ዓመት ካገለገልን በኋላ በዛግሬብ፣ ክሮኤሺያ ወደሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ተዛወርን፤ በወቅቱ በቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ የሚከናወነውን ሥራ በበላይነት የሚከታተለው ይህ ቅርንጫፍ ቢሮ ነበር። የተለያየ ባሕልና ሃይማኖት ያላቸው ቢሆንም አብዛኞቹ ዩጎዝላቪያውያን በሰላም አብረው ይኖሩ ነበር። በ1991 የእርስ በርስ ጦርነት ሲነሳ ግን ይህ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ተቀየረ። ጦርነቱ ከመጀመሩ ከጥቂት ወራት በፊት፣ በክሮኤሺያ የነበረው የአገር ኮሚቴ ከሁሉም የዩጎዝላቪያ ክፍሎች የሚመጡ የይሖዋ ምሥክሮች የሚገኙበት ዓለም አቀፍ ስብሰባ ለማካሄድ እየተዘጋጀ ነበር።
ሌንካ በቪየና፣ ኦስትሪያ በሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ተርጓሚ ሆና ስትሠራ
ጦርነቱ ሲፈነዳ፣ በአገር ኮሚቴው ውስጥ የነበርነው ወንድሞች ስለ ጉዳዩ ጸለይን፤ ተነጋገርንበት፤ ከዚያም ስብሰባውን ለማካሄድ የምናደርጋቸውን ዝግጅቶች ለመቀጠል ወሰንን። ለስብሰባው ከውጭ የሚመጡ እንግዶቻችንን ደህንነት ለማስጠበቅም ከአካባቢው ባለሥልጣናት ጋር በቅርበት መሥራት ጀመርን። አምስት የበላይ አካል አባላት በስብሰባው ላይ በመገኘታቸው በጣም ተደሰትን! በስብሰባው አማካኝነት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ልክ በወቅቱ የሚያስፈልጋቸውን ማበረታቻ አግኝተዋል።
ጦርነቱ ከጀመረ ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ የአገር ኮሚቴው በሳራዬቮና በሌሎች የቦስኒያ ክፍሎች የሚኖሩ ወንድሞቻችን ምግብ፣ የማገዶ እንጨትና መድኃኒት እያለቀባቸው እንደሆነ የሚገልጽ ሪፖርት ደረሰው። ከተሞቻቸው በሰርቢያ ጦር ተከበው ስለነበር እነዚህን ቁሳቁሶች ሊያመጣላቸው የሚችል ማንም አልነበረም። ወንድሞቻችንን ለመርዳት ምን ብናደርግ እንደሚሻል እንዲያሳውቀን ወደ ይሖዋ አጥብቀን ጸለይን።
በወቅቱ የነበረው አደገኛ ሁኔታ ሳይበግረን በኦስትሪያ ቅርንጫፍ ቢሮ አስተባባሪነት የእርዳታ ቁሳቁሶችን ወደ እነዚህ ቦታዎች ለመላክ ዝግጅት አደረግን። ጥቅምት 26, 1993 በቦስኒያ ለሚኖሩ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የሚሆን 16 ቶን የሚመዝን የእርዳታ ቁሳቁስ በመኪና ጭነን ከቪየና ተነሳን።c
በሳራዬቮ ላሉ የይሖዋ ምሥክሮች የእርዳታ ቁሳቁስ በማድረሱ ሥራ ስንካፈል
ውጊያ እየተካሄደ ባለባቸው ቦታዎች አቋርጠን ስናልፍ የይሖዋ እጅ ሕዝቦቹን ‘ለማዳን አጭር እንዳልሆነ’ በገዛ ሕይወታችን ተመልክተናል። (ኢሳይያስ 59:1) በተለይ ከዜኒትሳ እስከ ሳራዬቮ ያደረግነውን አደገኛ ጉዞ መቼም አንረሳውም። ሳራዬቮ ልንደርስ 40 ኪሎ ሜትር ብቻ ሲቀረን መንገድ ቀይረን በጫካ ውስጥ መጓዝ አስፈለገን፤ በዚህም የተነሳ ተጨማሪ 140 ኪሎ ሜትር ለመጓዝ ተገደድን።
ወደተከበበችው ከተማ ስንደርስ አዛዡን እንዲያገናኙን ጠየቅኩ፤ እንደ አጋጣሚ ሆኖ አዛዡ የጦር ጄኔራል ነበር። የመጣነው ለወንድሞቻችን የእርዳታ ቁሳቁሶችን ለማድረስ እንደሆነ ለጄኔራሉ ስንነግረው በጦርነቱ የተነሳ ይህን ማድረግ ከባድ እንደሆነ ነገረን። የይሖዋ ምሥክሮች እንደሆንን ሲሰማ አጅሩዲን የተባለ ሰው አውቅ እንደሆነ ጠየቀኝ። እኔም ጓደኛችን እንደሆነ ነገርኩት። በዚህ ጊዜ ጄኔራሉ እንዲህ አለኝ፦ “ለእኔም እኮ ጓደኛዬ ነው። አብረን ነው የተማርነው። የይሖዋ ምሥክር ከሆነ በኋላ ደግሞ ለእሱ ያለኝ አክብሮት ይበልጥ ጨምሯል።”
ከፍተኛ ማዕረግ ያለው ይህ የጦር አዛዥ ስለምናምንባቸው ነገሮችም ብዙ ጥያቄዎች ጠየቀን፤ ከዚያም በሳራዬቮ ላሉ ወንድሞቻችን ያመጣነውን የእርዳታ ቁሳቁስ ወታደሮች በሚጠቀሙበት ሚስጥራዊ መተላለፊያ በኩል እንድናጓጉዝ ፈቀደልን። እንዲያውም ለሁለት ምሽት ወታደሮቹ ለጦር ሠራዊቱ የመጣውን ዕቃ ማጓጓዛቸውን ትተው የእኛን ዕቃ እንዲያጓጉዙ አዘዘ። በእነዚያ ሁለት ምሽቶች ወታደሮቹ እያንዳንዳቸው 27 ኪሎ ግራም የሚመዝኑ ዕቃዎችን በዚያ ጠባብ መተላለፊያ በኩል አጓጓዙልን። እንዲህ ያለውን ነገር በራሳችን ፈጽሞ ልናደርግ አንችልም ነበር!
በቦስኒያ ጦርነቱ ካበቃ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ሃሊም ክዩሪ ከተባለ በሳራዬቮ ያለ የጉባኤ ሽማግሌ ጋር ሚስጥራዊውን መተላለፊያ ልንጎበኝ ሄደን
የወታደሮቹ እርዳታ በዚህ ብቻ አላበቃም፤ ቁሳቁሶቹን በሚስጥራዊ መተላለፊያው በኩል ካጓጓዙልን በኋላ አመቺ ወደሆነ ቦታ በመውሰድ ወንድሞቻችንን አገዟቸው። በተጨማሪም በዚያ ላሉ ወንድሞችና ለጎረቤቶቻቸው ምግብ በማከፋፈልም አግዘዋል። የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ አንዳንድ ሰዎች የይሖዋ ድርጅት ባደረገላቸው እርዳታ ልባቸው በጣም ስለተነካ በአካባቢው ካሉ ወንድሞች ጋር አብረው ተንበርክከው በመጸለይ ይሖዋን አመስግነዋል።—2 ቆሮንቶስ 9:13
ወታደሮች ፍተሻ በሚያደርጉባቸው ኬላዎች ስናልፍ የገለልተኝነት አቋማችን ብዙ ጊዜ ጥበቃ ሆኖልናል። ሆኖም ገለልተኝነት የይሖዋ ምሥክሮች መሆናችንን የሚያሳይ ባጅ ከማድረግ ያለፈ ነገርን ይጨምራል። በአስተሳሰባችንም ሆነ በስሜታችን ምንጊዜም ገለልተኛ ለመሆን ብርቱ ትግል ማድረግ አስፈልጎናል። ለዚህም ስንል የዜና ዘገባዎችን ብዙ ላለመስማት እንጠነቀቅ ነበር። ምክንያቱም ከሁለቱም ወገኖች የሚቀርቡት የሚያሸብሩ ሪፖርቶች በውስጣችን አንዱን ወገን እንድንይዝ አልፎ ተርፎም ጥላቻ እንዲቀሰቀስብን የሚያደርጉ እንደሆኑ ተገንዝበን ነበር።
ከ1990ዎቹ ጀምሮ በክሮኤሺያ ከዚያም በቼክ-ስሎቫክ ቅርንጫፍ ቢሮ የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል ሆኜ አገልግያለሁ። ያገለገልኩባቸው የተለያዩ ምድቦች ውሳኔ ስለማድረግ ትልቅ ነገር አስተምረውኛል። አንደኛ፣ ይሖዋ አንድን ችግር ለመፍታት ማንንም፣ ሌላው ቀርቶ የጦር አዛዥን እንኳ ሊጠቀም ይችላል። ሁለተኛ ደግሞ የቱንም ያህል ተሞክሮ ያካበትኩ ቢሆን በራሴ ሳይሆን ይሖዋ በድርጅቱ አማካኝነት በሚሰጠው አመራር መታመን እንዳለብኝ ተምሬያለሁ።
ያልተጠበቀ የጤና ችግር
በ2023 አጠቃላይ ምርመራ ለማድረግ ስሄድ አደገኛ የሆነ የካንሰር ዓይነት እንዳለብኝ ተነገረኝ። ከዚህ በፊት ከባድ ሕመም አሞኝ ስለማያውቅ ሁኔታው በጣም አስጨነቀን። እኔና ሌንካ በተደጋጋሚ ወደ ይሖዋ በመጸለይ ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ እንዲረዳን ጠየቅነው። ከጸሎታችን ጋር የሚስማማ እርምጃም ወሰድን። ምርምር አደረግን እንዲሁም ሐኪሞችን አማከርን። የምወስደውን የሕክምና ዓይነት ከወሰንን በኋላ ጭንቀቱ ቀለል አለልን።
በተጨማሪም ስለ ነገ ከልክ በላይ ላለመጨነቅ ቁርጥ ውሳኔ አደረግን። (ማቴዎስ 6:34) ደግሞም ደስተኛ የምንሆንባቸው ብዙ ምክንያቶች አሉን! ለምሳሌ ለሕክምና ወደ ጀርመን ከመሄዳችን በፊት በብራቲስላቫ፣ ስሎቫኪያ ላለው የቤቴል ቤተሰባችን ደብዳቤ በመጻፍ ስለ ሁኔታችን ነገርናቸው። እነዚህ ውድ ወዳጆቻችንም በምላሹ ብዙ መልእክቶችን ጻፉልን፤ እንደሚጸልዩልንና እንደሚወዱንም ነገሩን። ይሖዋ በእምነት ባልንጀሮቻችን አማካኝነት ለመጽናት እንደሚረዳንና “ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ” የሆነውን ሰላም እንደሚሰጠን በገዛ ሕይወታችን ተመልክተናል።—ፊልጵስዩስ 4:7
እንደ እውነቱ ከሆነ ማናችንም ነገ ምን ይዞ እንደሚመጣ አናውቅም፤ የማይድን በሽታ ሊይዘን፣ አልፎ ተርፎም ሞትን መጋፈጥ ሊያስፈልገን ይችላል። (መክብብ 9:11፤ ያዕቆብ 4:14) በመሆኑም ገና በወጣትነቴ ይሖዋን ለማገልገልና ለእሱ ምርጤን ለመስጠት በመምረጤ በጣም ደስተኛ ነኝ፤ ይሖዋ ይህን ውሳኔ እንዳደርግ ስለረዳኝ አመሰግነዋለሁ። ትርጉም ያለው ሕይወት ለመምራት የሚያስችል ከዚህ የተሻለ ምንም ውሳኔ ሊኖር አይችልም!d
a ካርሎቪ ቫሪ በጀርመንኛ ካርልስባት ተብላም ትጠራለች።
b ሰርቦ-ክሮሽያኛ የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ የሥራ ቋንቋ ነበር።
c ስለ እርዳታ እንቅስቃሴው ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በኅዳር 1, 1994 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 23-27 ላይ የወጣውን “በቦስኒያ የሚኖሩትን የእምነት ቤተሰቦቻችን መርዳት” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
d ወንድም ሃማዴ የሕይወት ታሪኩ በመዘጋጀት ላይ እያለ ጥር 28, 2025 አርፏል።