ቪርጊሊዩስ ፑድጁዪስ | የሕይወት ታሪክ
ይሖዋ ሁሌም መውጫ መንገዱን ያዘጋጃል
አክስቴና አጎቴ በ1976 ሊጠይቁን የመጡበትን ጊዜ ቤተሰባችን ፈጽሞ አይረሳውም። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር እያጠና የነበረው አጎቴ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አዲስ ነገር እንደተማረ ለወላጆቼ ነገራቸው። በመጀመሪያ ኢየሱስ በዘመኑ የነበሩትን የሃይማኖት መሪዎች በተመለከተ ማቴዎስ ምዕራፍ 23 ላይ ምን እንዳለ ነገራቸው። ከዚያም በኢየሱስ ዘመን በነበሩትና በዘመናችን ባሉት የሃይማኖት መሪዎች መካከል ያለውን ተመሳሳይነት ገለጸላቸው። አጥባቂ ካቶሊክ የነበረችው እናቴ ኢየሱስ የሃይማኖት መሪዎቹን እንዲህ በገሃድ እንዳወገዛቸው ማመን ከበዳት። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን ነገር በገዛ ዓይኗ ለማየት ወሰነች።
የምንኖረው ሊትዌኒያ ነበር፤ ሊትዌኒያ በወቅቱ የቀድሞው ሶቪየት ኅብረት አካል ነበረች። መንግሥት በሃይማኖቶች እንቅስቃሴ ላይ ጥብቅ ገደቦችን ይጥል ስለነበር መጽሐፍ ቅዱስ ያላቸው ሰዎች በጣም ጥቂት ነበሩ። ስለዚህ እናቴ ከቤተክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስ ተዋሰች፤ ከዚያም ኢየሱስ በወቅቱ የነበሩትን የሃይማኖት መሪዎች በግብዝነታቸው ምክንያት እንዳወገዛቸው በቀጥታ በማንበብ ማረጋገጥ ቻለች። እናቴ መጽሐፍ ቅዱስ ስለሚያስተምራቸው ሌሎች ትምህርቶችም የማወቅ ጉጉት ስላደረባት አጎቴን ያስጠኑት ከነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች ጽሑፍ ተቀበለች።
ብዙም ሳይቆይ ቤተሰባችን በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመረ። የይሖዋ ምሥክሮች እንቅስቃሴ ታግዶ ስለነበር ስብሰባ የሚያደርጉበት ቦታ በየጊዜው ይቀያየር ነበር፤ እንዲያውም አንዳንዴ የሚሰበሰቡት በአቅራቢያችን ባለ ጫካ ውስጥ ነው። በ1978 እኔ፣ መንትያ እህቴ ዳንጉዎሌ እና እናታችን ተጠምቀን የይሖዋ ምሥክር ሆንን። በወቅቱ እኔና እህቴ 15 ዓመታችን ነበር። ከጥቂት ዓመታት በኋላ ደግሞ አባታችንም ተጠመቀ።
እኔና መንትያ እህቴ ዳንጉዎሌ በአራት ዓመታችን
ወጣት ሳለሁ ይሖዋ መውጫ መንገዱን አዘጋጅቶልኛል
እኔና ዳንጉዎሌ ከተጠመቅን ከአንድ ወር በኋላ በትምህርት ቤት ስደት ይደርስብን ጀመር። በትምህርት ቤታችን አዳራሽ በተካሄደ ልዩ ፕሮግራም ላይ የሶቪየት ኅብረት ብሔራዊ መዝሙር ይዘመር ነበር፤ እኔና እህቴ ግን በክርስቲያናዊ ገለልተኝነት አቋማችን ምክንያት ከተቀመጥንበት እንዳልተነሳን አስተማሪዎቹ አስተዋሉ። በመሆኑም ስማችንን ለርዕሰ መምህሩ ሰጡ። ርዕሰ መምህሩም ኬጂቢ ተብለው ለሚጠሩት የሚስጥር ፖሊሶች ጉዳዩን አሳወቀ። ብዙም ሳይቆይ ፖሊሶቹ ወደ ቤታችን መጥተው ምርመራ አካሄዱብን።
እኔና ዳንጉዎሌ አምላክ የለሽነትን የሚያስፋፉ ፕሮፓጋንዳዎችንም መቋቋም ነበረብን። ለምሳሌ የ16 ዓመት ልጆች ሳለን የክፍሉ ተማሪዎች በሙሉ “በአምላክ የማላምንበት ምክንያት” በሚል ርዕስ ጽሑፍ እንድናዘጋጅ ተነገረን። እኔ በዚህ ርዕስ ስላልተስማማሁ “በአምላክ አምናለሁ” ብዬ ቁራጭ ወረቀት ላይ ከጻፍኩ በኋላ ዴስኬ ላይ አስቀመጥኩት። አስተማሪዋ ወረቀቱን ስታይ ተበሳጭታ “እንግዲያው የምታምንበትን ምክንያት ጻፋ!” ብላ ጮኸችብኝ። ስለማምንበት ነገር መጻፍ የምችልበት አጋጣሚ በማግኘቴ ተደሰትኩ፤ እህቴም ስለምታምንባቸው ነገሮች መጻፍ ጀመረች። ሌሎች ሁለት ልጆች እኛ የምንጽፈውን ነገር ሲያዩ እነሱም በአምላክ የሚያምኑበትን ምክንያት ለመጻፍ ወሰኑ። ይህ አጋጣሚ ይሖዋ ከባድ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ‘መውጫ መንገዱን እንደሚያዘጋጅልን’ ካየሁባቸው በርካታ አጋጣሚዎች መካከል አንዱ ብቻ ነው።—1 ቆሮንቶስ 10:13
ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ከጠፋችው ገነት ወደምትመለሰው ገነት የተባለውን መጽሐፍ ለአንድ ወር ያህል አዋሱን። ካልተሳሳትኩ በወቅቱ በሊትዌኒያ ያሉት የዚህ መጽሐፍ ቅጂዎች ከአራት ወይም ከአምስት አይበልጡም ነበር። እኔና ዳንጉዎሌ “አቤት! ይህን መጽሐፍ መመለስ ባይኖርብን ኖሮ” ተባባልን። ግን ከመመለስ ውጭ ምንም አማራጭ ስላልነበረን አንድ ዘዴ ቀየስን፤ ሙሉውን መጽሐፍ በእጃችን ገለበጥነው! እጃችንን ቢያመንም እምነታችንን የሚገነባልንን ይህን ጽሑፍ ማግኘት በመቻላችን በጣም ተደሰትን።
በ1982 ማለትም 19 ዓመት ከሞላኝ ብዙም ሳይቆይ የጦር ሠራዊቱን ለመቀላቀል ፈቃደኛ ባለመሆኔ የሁለት ዓመት እስራት ተፈረደብኝ። ወንጀለኞች በሞሉበት እስር ቤት ውስጥ መታሰር ከባድ ነበር። ሆኖም በዚያው የእስር ቤት ካምፕ ውስጥ ካለ ሌላ የይሖዋ ምሥክር ጋር አልፎ አልፎ መገናኘት መቻሌ አስደሰተኝ። ከዚያም የእስር ጊዜዬን አጠናቅቄ ነፃ ተለቀቅኩ። ሆኖም የእስር ቤት ታሪኬ በዚህ አያበቃም።
ይሖዋን የምትወድ ሚስት አገኘሁ
እኔና ሊዲያ ከመጋባታችን ከጥቂት ጊዜ በፊት
በ1984 ከእስር ከተፈታሁ በኋላ በዩክሬን ከምትኖር ሊዲያ ከተባለች ውብና መንፈሳዊ እህት ጋር ተዋውቀን ትዳር መሠረትን። ከተጋባን በኋላ ሊዲያ ከእኔ ጋር ለመሆን ስትል የትውልድ አገሯን ትታ ወደ ሊትዌኒያ ተዛወረች። ሊዲያና ወላጆቿ የይሖዋ ምሥክሮች ስለሆኑ እሷም ተማሪ ሳለች ልክ እንደ እኔ ከባድ ስደት ደርሶባታል። በዚያ ፈታኝ ወቅት በናዚ ማጎሪያ ካምፕ ውስጥ የነበሩትን እንዲሁም ወደ ሳይቤሪያ በግዞት የተወሰዱትን ወንድሞችና እህቶች ተሞክሮ ማሰቧ ብርታት ሰጥቷታል።
በ1980ዎቹ በሊትዌኒያ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ገና በእገዳ ሥር ነበሩ። ስለዚህ የይሖዋ ምሥክሮች የጋብቻ ሥነ ሥርዓቶች በአብዛኛው የሁለት ቀን ትላልቅ ስብሰባዎችን ለማድረግ እንደ ሽፋን ያገለግሉ ነበር። ከእኛ ሠርግ ጋር በተያያዘም የሆነው ይኸው ነው። እንግዶቻችን በሠርጋችን ላይ ከመታደማቸውም በተጨማሪ ሁላችንም አብረን የተለያዩ ንግግሮችን ማዳመጥ፣ በርካታ መዝሙሮችን መዘመር፣ አልፎ ተርፎም አራት የመጽሐፍ ቅዱስ ድራማዎችን የማየት አጋጣሚ አግኝተናል። እስከማስታውሰው ድረስ ከመላው ሶቪየት ኅብረት የመጡ ዘመዶቼን ጨምሮ 450 ገደማ የሚሆኑ ሰዎች በስብሰባው ላይ ተገኝተዋል። እንዲያውም ከአንዳንድ ወንድሞች እንደሰማነው ድንኳን ሰብረው የመጡ የኬጂቢ ፖሊሶችም በስብሰባው ላይ ተገኝተዋል!
የጋብቻ ሥነ ሥርዓታችን የተካሄደው ለሁለት ቀን በተደረገ ትልቅ ስብሰባ ላይ ነው። የአጎቴ ልጅና እጮኛዋም በዚያኑ ዕለት ስለተጋቡ መድረክ ላይ የተቀመጥነው አብረን ነው
ድጋሚ ችሎት ፊት ቀረብኩ
አንድ የይሖዋ ምሥክር እስረኛ በእስር ጊዜው ውስጥ በሚሰጠው የማንቂያ ትምህርት ተለውጦ ከሶቪየት መርሆች ጋር ካልተስማማ መንግሥት ድጋሚ እንዲታሰር የሚወስንባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ። ስለዚህ ከተጋባን ገና አንድ ዓመት ሳይሞላን በድጋሚ ችሎት ፊት ቀረብኩ። እኔ ቀኑን ሙሉ ፍርድ ቤት ሳሳልፍ እርጉዝ የነበረችው ሊዲያ በአቅራቢያችን የሚገኝ ሆስፒታል ገብታ ነበር። ክሴ በፍርድ ቤት በሚታይበት ጊዜ ሁሉ እሷን ሄጄ እንድጠይቃት አይፈቀድልኝም ነበር። አንድ ቀን ግን ችሎቱ ለእረፍት ተቋርጦ ሳለ ሊዲያ ወደተኛችበት ሆስፒታል የመሄድ አጋጣሚ አገኘሁ። ክፍሏ ጋ ሄጄ በውጭ በኩል ስቆም ሊዲያ መስኮቱን ከፈተችው። ለጥቂት ደቂቃዎችም ቢሆን እርስ በርስ የምንበረታታበት ደስ የሚል አጋጣሚ አገኘን። በዚያኑ ዕለት የሦስት ዓመት እስራት ተፈረደብኝ።
የሚያሳዝነው ከሁለት ቀን በኋላ ሊዲያ ጽንሱ ጨነገፈባት። በወቅቱ በስለት ለሁለት የተሰነጠቀች ያህል ከባድ የስሜት ሥቃይ እንደደረሰባት ተናግራለች። ሊዲያ ከዚህ አሳዛኝ ክስተት በተጨማሪ በአዲስ አገር ውስጥ ከወላጆቼ ጋር እየኖረች ኑሮን እንደ አዲስ ለመላመድ እየታገለች ነበር። ወላጆቼ ደግሞ ሊዲያ የምትችላቸውን ዩክሬንኛም ሆነ ሩሲያኛ ቋንቋዎች ትንሽ ትንሽ ብቻ ነበር የሚችሉት። ያም ሆኖ በዚያ ከባድ ጊዜ ሊዲያ ሙሉ በሙሉ በይሖዋ ታምናለች፤ ወላጆቼም በተቻላቸው መጠን እሷን ለመንከባከብና ለማጽናናት ጥረት አድርገዋል።
ይሖዋ መውጫ መንገድ ማዘጋጀቱን ቀጠለ
ለመጀመሪያ ጊዜ ስታሰር የተማርኩት ነገር ለሁለተኛ እስራቴ ጠቅሞኛል። ለመጽናት የረዳኝ አንዱ ነገር ለሌሎች መስበኬ ነው። ለምሳሌ ወደ እስር ቤት የተወሰድነው በመኪኖችና በባቡሮች ውስጥ ታጭቀን ነው። አንዳንዴ አምስት ወይም ስድስት ሰዎች በሚይዝ ቦታ ውስጥ ከ15 እስከ 20 ወንዶች እንዲገቡ ይደረግ ነበር። ይህን አጋጣሚ አብረውኝ ለታሰሩ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለመንገር ተጠቅሜበታለሁ። በጦርነትና በፖለቲካ ጉዳዮች ገለልተኛ የሆንኩት ለምን እንደሆነና ተይዤ የታሰርኩት በዚህ የተነሳ እንደሆነ እነግራቸው ነበር። በተጨማሪም አምላክ አለ ብሎ ማመን ምክንያታዊ የሆነው ለምን እንደሆነ አብራራላቸው ነበር።
የታሰርኩት በማሪያምፖሌa በሚገኝ እስር ቤት ውስጥ ነው። እስከማውቀው ድረስ በዚያ ከታሰሩት 2,000 የሚያህሉ ከባድ ወንጀለኞች መካከል ብቸኛው የይሖዋ ምሥክር እኔ ነኝ። ኃይለኛ ድብደባ የደረሰብኝ አንዴ ብቻ ቢሆንም እስረኞች በተደጋጋሚ ማስፈራሪያ ይደርስባቸው፣ ይደበደቡ፣ አልፎ ተርፎም ይገደሉ ነበር። የታሰርኩት አስከፊ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ቢሆንም ያዘኑትን ለማበረታታትና ርኅራኄ ለማሳየት ጥረት አደርግ ነበር፤ ለእነዚያ እስረኞች እንዲህ ባለ መንገድ የሚይዛቸው ሰው ማግኘት ብርቅ ነበር።
የኬጂቢ ወኪሎች በእስር ቤት ውስጥ ሥነ ልቦናዊ ጫናም ያደርሱብናል። ፖሊሶቹ የቤተሰቤ አባላት ቤት ውስጥ የሚያወሩትን ወሬ በሆነ መንገድ እየሰሙ ለእኔ መጥተው ይነግሩኛል። ሆኖም ወሬውን የሚነግሩኝ ቤተሰቦቼ እየተጣሉ እንደሆነና እርስ በርስ እንደተከፋፈሉ በሚያስመስል መንገድ ነው። ወኪሎቹ የሚናገሩትን ነገር አምኜ ባላውቅም የእነሱን ንግግር ቤተሰቦቼ በእርግጥ ካሉት ነገር ጋር ማወዳደር የቻልኩት ከእስር ቤት ከወጣሁ በኋላ ነው።—ማቴዎስ 10:16
በአንድ ወቅት አንዲት እህት ጎረቤቷ የሆነን በደንብ የምታውቀውን ጠባቂ ትንሽዬ የሩሲያኛ መጽሐፍ ቅዱስ በድብቅ እንዲሰጠኝ ጠየቀችው። ምሽት ላይ ከኢየሱስ የተራራ ስብከት የተወሰዱ ጥቂት ጥቅሶችን ቁራጭ ወረቀት ላይ እገለብጣለሁ፤ ይህን የማደርገው በቀጣዩ ቀን በእስር ቤቱ ፋብሪካ ውስጥ ስሠራ ማንም ሳያየኝ ጥቅሶቹን በተደጋጋሚ ማንበብ እንድችል ነው። ሩሲያኛ የአፍ መፍቻ ቋንቋዬ ባይሆንም የኢየሱስን የተራራ ስብከት በሩሲያኛ በቃሌ የያዝኩት በዚህ መንገድ ነው። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ጠባቂዎቹ መጽሐፍ ቅዱሱን አግኝተው ወሰዱብኝ። ደግነቱ ኢየሱስ የተናገራቸውን ነገሮች ቀደም ብዬ በአእምሮዬና በልቤ ውስጥ አስቀምጬ ነበር።
ሊዲያ የምትጽፍልኝ ደብዳቤዎችም ትልቅ የብርታት ምንጭ ሆነውልኛል፤ ሊዲያ በየቀኑ ማለት ይቻላል ደብዳቤ ትጽፍልኛለች። እኔ መልሼ እንድጽፍላት የሚፈቀድልኝ ግን በወር ሁለቴ ብቻ ነው። ያም ሆኖ እነዚያ ደብዳቤዎች ስለ ሦስት ወሳኝ ነገሮች እርግጠኛ እንድትሆን እንደረዷት ነግራኛለች፦ በሕይወት እንዳለሁ፣ አሁንም ለይሖዋ ታማኝ እንደሆንኩ እና ለእሷ ያለኝ ፍቅር እንዳልተቀየረ።
ይሖዋ ጸሎቴን በመመለስ መውጫ መንገዱን አዘጋጅቶልኛል
በአንድ ወቅት አንድ የእስረኞች የሥራ ቡድን አባላት፣ ኃላፊዎቹ በሥራ ቦታ ያለውን ሁኔታ እንዲያሻሽሉ ጥያቄ አነሱ። ያቀረቡት ጥያቄ መልስ እስኪያገኝ ድረስም የሥራ አድማ አደረጉ። እንደሚጠበቀው እነዚህ እስረኞች በማመፃቸው ከባድ ቅጣት ደረሰባቸው። ከዚያም ኃላፊዎቹ እኔና ሌሎች እስረኞች ዓመፀኞቹን እስረኞች ለመተካት በተቋቋመ አዲስ የሥራ ቡድን ውስጥ እንድንሠራ መመደባችንን በግል ነገሩኝ።
ይህን አዲስ ምድብ አልቀበልም ብል ከባድ ቅጣት ይጠብቀኛል። እሺ ብዬ ከተቀበልኩ ደግሞ እስረኞቹ እንደ ከሃዲ ቆጥረው የበቀል እርምጃ ይወስዱብኛል፤ ይህም በአብዛኛው ድብደባን ወይም በስለት ተወግቶ መገደልን ይጨምራል። አጣብቂኝ ውስጥ ስለገባሁ በጣም ተጨነቅኩ፤ ምን ማድረግ እንዳለብኝም ግራ ገባኝ። (2 ዜና መዋዕል 20:12) ስለዚህ ወደ ይሖዋ ደጋግሜ በመጸለይ እንዲረዳኝ ለመንኩት።
በድንገት፣ በወቅቱ ባለሁበት የሥራ ቡድን ውስጥ የነበረ አንድ እስረኛ ተሰብስበን ሄደን የሥራ ኃላፊውን እንድናነጋግረው ሐሳብ አቀረበ። ይህ እስረኛ ጓደኛዬ አልነበረም፤ አብረን ከመሥራት ውጭ ሌላ ምንም ትውውቅ የለንም። ያም ሆኖ ከመጀመሪያው ቡድኔ ልለቅ እንደማይገባ ሽንጡን ገትሮ ተከራከረ። በዚህም የተነሳ በእስረኛውና በኃላፊው መካከል ከባድ ጭቅጭቅ ተነሳ። አንድ ነገር ካለ ፈጽሞ ሐሳቡን ባለመቀየር የሚታወቀው ኃላፊያችን በመጨረሻ ከቢሮው አባረረንና በመጀመሪያው የሥራ ቡድኔ እንድቀጥል ፈቀደልኝ፤ በዚህ ጊዜ ትልቅ እፎይታ ተሰማኝ። (2 ጴጥሮስ 2:9) በእስር ባሳለፍኳቸው ዓመታት ሁሉ አንድ እስረኛ እንዲህ ባለ ቅንዓት ለሌላ እስረኛ ጥብቅና ሲቆም አይቼ አላውቅም። ይህ አጋጣሚ ይሖዋ ለጸሎታችን መልስ ለመስጠት ማንንም ሊጠቀም እንደሚችል አስተምሮኛል።
ይሖዋ ለሊዲያ መውጫ መንገዱን አዘጋጅቶላታል
እኔ በእስር ቤት ሳለሁ ሊዲያ ያጋጠማትን ነገር ልንገራችሁ። ሥራ ማግኘት ያስፈልጋት ነበር። ሆኖም እኔ እስር ቤት ስለነበርኩ አብዛኞቹ አሠሪዎች ከኬጂቢ ጋር የሚያነካካቸው ነገር እንዳይፈጠር በመስጋት እሷን ለመቅጠር ፈቃደኛ አልሆኑም። በመጨረሻ በቀን ውስጥ ለ12 ሰዓት ያህል ልጆችን የመንከባከብ ሥራ አገኘች፤ የምትንከባከባቸው ልጆች 30 ነበሩ። በጣም አድካሚ ሥራ ነበር! ይሖዋ ግን በየዕለቱ ይህን ሥራ ለማከናወን የሚያስችል ብርታት ሰጥቷታል። በተጨማሪም በተለያዩ የሊትዌኒያ ክፍሎች የሚኖሩ ወንድሞችና እህቶች እሷን ለማጽናናት፣ አብረዋት ለመሆንና በሩሲያኛ ቋንቋ የተዘጋጁ ጽሑፎችን ለእሷ ለማድረስ ሲሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ነድተው ይመጡ ነበር። ብቻዋን እንደሆነች ተሰምቷት አያውቅም።
በቤተሰብ ደረጃ ይሖዋን ማገልገል
ከእስር ከተፈታሁ በኋላ፣ በድብቅ የሚከናወነውን ጽሑፎቻችንን ወደ ሊትዌኒያኛ የመተርጎሙን ሥራ በማደራጀት አግዝ ነበር። ከጥቂት ዓመታት በኋላ ሶቪየት ኅብረት የፈረሰ ሲሆን ሥራችን በሊትዌኒያ ሕጋዊ እውቅና አገኘ። ከጊዜ በኋላ ቋሚ የሆነ የሊትዌኒያኛ የትርጉም ቢሮ ተቋቋመ። ወደ ቢሮው ለመድረስ ከአንድ ሰዓት ተኩል በላይ በመኪና መጓዝ ቢጠይቅብኝም በትርጉም ሥራ መርዳት በመቻሌ ደስተኛ ነበርኩ፤ ለአምስት ዓመት ያህል በየሳምንቱ እንዲህ አድርጌያለሁ።
ነሐሴ 1997 እኔና ሊዲያ በሊትዌኒያ በሚገኘው ቤቴል ተብሎ በሚጠራው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ እንድናገለግል ተጋበዝን። ይህ ግብዣ ሲቀርብልን በጣም ተደሰትን። በወቅቱ ሁለት ሴት ልጆች ነበሩን፤ ኦክሳና ዘጠኝ ዓመቷ፣ ስቫዩኔ ደግሞ አምስት ዓመቷ ነበር። ቤቴል አቅራቢያ ወዳለ አፓርታማ ለመዛወርና ኦክሳናን አዲስ ትምህርት ቤት ለማስመዝገብ የነበረን ሦስት ቀን ብቻ ነበር።
የቤተሰብ አምልኳችን ትርጉም ያለውና አስደሳች እንዲሆን እንፈልግ ነበር፤ ፎቶግራፉ አሐሽዌሮስን፣ አስቴርንና መርዶክዮስን ሆነን ስንተውን ያሳያል
ኃላፊነቶቻችንን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ማስኬድ የቻልነው እንዴት ነው? እኔ በየቀኑ በማለዳ ተነስቼ ወደ ቤቴል እሄዳለሁ፤ ሊዲያ ደግሞ ልጆቹን ወደ ትምህርት ቤት ከሸኘች በኋላ ወደ ቤቴል ትመጣለች። ከዚያም ሊዲያ ልጆቹ ባዶ ቤት እንዳይጠብቃቸው ስትል ከእነሱ ቀድማ ወደ ቤት ትመለሳለች።
የሊትዌኒያ ቅርንጫፍ ቢሮ የማስፋፊያ ፕሮጀክት ተጠናቆ በ2003 ሲወሰን የሊትዌኒያ ባሕላዊ ልብስ ለብሰን የተነሳነው ፎቶግራፍ
መላው ቤተሰባችን ዓርብ ምሽትን በጉጉት ነበር የሚጠብቀው። አብረን ምግብ እናበስላለን፤ ቤት እናጸዳለን፤ የቤተሰብ አምልኮ እናደርጋለን፤ እንዲሁም እንጫወታለን። ልጆቻችን የይሖዋን ፍጥረት የሚያዩበትና ዓለም አቀፉን የወንድማማች ማኅበር ፍቅር የሚያጣጥሙበት አጋጣሚ እንዲያገኙ ስንል ወደ ተራሮች፣ ወደ ባሕር ዳርቻዎችና አውሮፓ ውስጥ ወዳሉ ሌሎች ቤቴሎች እንጓዝ ነበር። እኔም ሆንኩ ሊዲያ በልጆቻችን በጣም እንኮራለን፤ ሁለቱም የዘወትር አቅኚ የሆኑት በ15 ዓመታቸው ነው። በአሁኑ ጊዜ ኦክሳና እና ባለቤቷ ዣን-በኑዋ በሊትዌኒያኛ የርቀት የትርጉም ቢሮ፣ ስቫዩኔ እና ባለቤቷ ኒኮላስ ደግሞ በፈረንሳይ ቤቴል እያገለገሉ ይገኛሉ።
እኔና ሊዲያ “አንድ ሥጋ” እንድንሆን የረዳን ትልቁ ነገር የይሖዋ አገልግሎት ሁሌም በሕይወታችን ውስጥ ቅድሚያውን እንዲይዝ ማድረጋችን ነው። (ኤፌሶን 5:31፤ መክብብ 4:12) ለብዙ ዓመታት ‘የተደቆስንና’ ስደት የደረሰብን ቢሆንም አንዴም ቢሆን አልተተውንም፤ ‘መውጫ ቀዳዳ አጥተንም’ አናውቅም። (2 ቆሮንቶስ 4:8, 9) ይሖዋ በተደጋጋሚ መውጫ መንገዱን ሲያዘጋጅልን አይተናል፤ ወደፊትም እንዲህ ማድረጉን እንደሚቀጥል አንጠራጠርም።
ከውዷ ባለቤቴ ከሊዲያ ጋር
a ከ1955 እስከ 1990 ድረስ ካፕሱካስ ተብላ ትጠራ ነበር።