ከኢየሱስ ተማሩ
ዓለም በሙሉ ሰላም ይሆናል
ሰላም የሁሉም ሰው ምኞት ነው፤ ዓለማችን ላይ ሰላም ሰፍኖ ለማየት እንጓጓለን። መሪዎች በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ግጭቶችን ለመቋጨት እና ሰላም ለማስፈን ሲጥሩ ቆይተዋል። ጥረታቸው ለተወሰነ ጊዜ ይሳካ ይሆናል። የሚያሳዝነው ግን ብዙውን ጊዜ ግጭቱ መልሶ ያገረሻል። ታዲያ ዓለም በሙሉ ሰላም የሚሆንበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? አዎ! ይህን ጉዳይ በተመለከተ ከኢየሱስ ምን እንደምንማር ተመልከት።
ኢየሱስ ምን እርምጃ ይወስዳል?
ኢየሱስ በዓለም ላይ ሰላም ለማስፈን ሲል በቅርቡ የሚወስዳቸውን እርምጃዎች መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመልከት።
“[ኢየሱስ] የሰላም መስፍን ይባላል። . . . እየተጠናከረ የሚሄደው አገዛዙም ሆነ ሰላሙ ፍጻሜ አይኖረውም።” (ኢሳይያስ 9:6, 7) የአምላክ መንግሥት ንጉሥ የሆነው ኢየሱስ ፍጻሜ የሌለው ሰላም ያመጣል።
“እርዳታ ለማግኘት የሚጮኸውን ድሃ፣ እንዲሁም . . . ረዳት የሌለውን ሁሉ ይታደጋል።” (መዝሙር 72:12-14) ኢየሱስ ንግሥናውን ተጠቅሞ ሁሉም ሰው ፍትሕ እንዲያገኝ ያደርጋል፤ በዚህም ምክንያት ለጦርነት፣ ለግጭት ወይም ለመከራ መንስኤ የሚሆን ነገር አይኖርም።
“አንዱ ብሔር በሌላው ብሔር ላይ ሰይፍ አያነሳም፤ ከእንግዲህ ወዲህ ጦርነት አይማሩም።” (ኢሳይያስ 2:4) ኢየሱስ ምድርን በሚያስተዳድርበት ወቅት ሰላምን እንጂ ጦርነትን የሚማር ሰው አይኖርም።
ኢየሱስ ለዓለም ሰላም የሚያመጣው እንዴት ነው? አንተስ ሰላም በሰፈነበት በዚያ ዓለም ላይ ለመኖር ምን ይጠበቅብሃል? የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ለማወቅ የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው? የሚለውን አጭር ቪዲዮ ተመልከት።
ኢየሱስ ምን አስተምሯል?
የኢየሱስን ትምህርቶች ለመከተል ጥረት የሚያደርጉ ሚሊዮኖች ዛሬም እንኳ በሰላም መኖር ችለዋል። ኢየሱስ በታዋቂው የተራራ ስብከቱ ላይ ከሌሎች ጋር በሰላም ለመኖር የሚረዱ ምክሮችን አስተምሯል። ለአብነት ያህል ጥቂቶቹን ተመልከት።
“ሰላም ፈጣሪዎች ደስተኞች ናቸው።” (ማቴዎስ 5:9) ይህ የኢየሱስ ምክር ከጠብ እንድንርቅ ብቻ ሳይሆን ሰላም ለመፍጠር ጥረት እንድናደርግም የሚያበረታታ ነው።
“በመጀመሪያ ከወንድምህ ጋር ታረቅ፤ ከዚያም ተመልሰህ መባህን አቅርብ።” (ማቴዎስ 5:23, 24) ኢየሱስ አለመግባባት ሲፈጠር ቶሎ እንዲፈቱት አድማጮቹን አሳስቧል። ከአምላክ ጋር ሰላም ሊሆኑ የሚችሉት ከሰዎች ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ካላቸው እንደሆነ አስተምሯል።
“እንዳይፈረድባችሁ በሌሎች ላይ አትፍረዱ።” (ማቴዎስ 7:1) ኢየሱስ፣ ኮናኝ መሆን ወይም እኛ ራሳችን የማናደርገውን ነገር ከሌሎች መጠበቅ እንደሌለብን መክሯል። እንከን ፈላጊ ከመሆን ይልቅ የባልንጀራችንን ስህተት ‘ይቅር ብለን’ እንድናልፍ አስተምሯል።—ሉቃስ 6:37
በዓለም በሙሉ ብዙዎች የኢየሱስን ትምህርቶች ተግባራዊ በማድረጋቸው ተጠቅመዋል። ግጭት ወይም ክፍፍል በገነነባቸው አካባቢዎችም እንኳ አለመግባባትን በረጋ መንፈስ ማብረድ፣ በደልን በይቅርታ ማለፍ እንዲሁም ክፉ ለሚያደርጉባቸው ሰዎች በመልካም መመለስ ችለዋል።
የኢየሱስን ምክሮች ተግባራዊ በማድረጋቸው ሰላም ያገኙ ሰዎችን ታሪክ ለማንበብ “ጦርነት እና ግጭት ቢኖርም ሰላም ማግኘት” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።