የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w26 ሐምሌ ገጽ 8-13
  • ከኢሳይያስ መጽሐፍ የምናገኘው መጽናኛ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ከኢሳይያስ መጽሐፍ የምናገኘው መጽናኛ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2026
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • በሕይወታችን ውስጥ ድንገተኛ ለውጥ ሲያጋጥመን
  • ከልክ ባለፈ የጥፋተኝነት ስሜት ስንሠቃይ
  • የምንወደውን ሰው በሞት ስናጣ
  • ይሖዋ “የተሰበረ ልብ ያላቸውን ይጠግናል”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2024
  • መቼም ቢሆን ብቻችንን አይደለንም
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • የማታውቋቸው ነገሮች እንዳሉ አምናችሁ በመቀበል ልካችሁን እንደምታውቁ አሳዩ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • ይሖዋ ይቅር እንዳለህ አምነህ ተቀበል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2026
w26 ሐምሌ ገጽ 8-13

ከመስከረም 14-20, 2026

መዝሙር 41 እባክህ ጸሎቴን ስማ

ከኢሳይያስ መጽሐፍ የምናገኘው መጽናኛ

“ይሖዋ እንዲህ [ይላል፦] ‘እናት ልጇን እንደምታጽናና፣ እኔም እናንተን ሁልጊዜ አጽናናችኋለሁ።’”—ኢሳ. 66:12, 13

ዓላማ

በምናዝንበት ወይም ተስፋ በምንቆርጥበት ጊዜ በኢሳይያስ መጽሐፍ ላይ ማሰላሰላችን የሚያጽናናን እንዴት ነው?

1-2. በሐዘን በምንዋጥበት ጊዜ ይሖዋ የሚረዳን እንዴት ነው?

ምርር ብሎ የሚያለቅስን አንድ ሕፃን ልጅ ለማሰብ ሞክር። ምናልባት የሚያለቅሰው ወላጆቹ ቤት ሊቀይሩ በመሆኑ ከጓደኞቹ መለየቱ አሳዝኖት ሊሆን ይችላል። ወይም ባጠፋው ጥፋት የተነሳ በጣም አዝኖ ሊሆን ይችላል። እንዲህ ባለው ሁኔታ ውስጥ አንዲት አፍቃሪ እናት ምን ታደርጋለች? ልጇን አቅፋ ታባብለዋለች፤ ያሳሰበውን ነገር ሲናገር ታዳምጠዋለች፤ እንዲሁም እንደምትወደው ትነግረዋለች።

2 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይሖዋ ልጇን ከምታጽናና አሳቢና አፍቃሪ እናት ጋር ራሱን አመሳስሏል። “እናት ልጇን እንደምታጽናና፣ እኔም እናንተን ሁልጊዜ አጽናናችኋለሁ” ብሏል። (ኢሳ. 66:13) ይሖዋ ለእኛ ያለው ፍቅር የትኛውም ወላጅ ለልጁ ካለው ፍቅር የላቀ ነው። (ኢሳ. 49:15) ይሖዋ ተስፋ ስንቆርጥ ወይም በጭንቀት ስንዋጥ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት መጽናኛና ብርታት ይሰጠናል።—ሮም 15:4

3. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?

3 የኢሳይያስ መጽሐፍ በሚያጽናኑ ሐሳቦች የተሞላ ነው። (ኢሳ. 40:1) አፍቃሪው አባታችን ይህን መጽሐፍ ያጻፈው አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩትን አይሁዳውያን ለማጽናናት ነው። እኛም የምንኖረው ‘ለመቋቋም በሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን’ ውስጥ ስለሆነ መጽናኛ ያስፈልገናል። (2 ጢሞ. 3:1) በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ የሚከተሉት ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ሊያጽናኑንና ሊያበረታቱን የሚችሉ በኢሳይያስ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ጥቅሶችን እንመለከታለን፦ (1) በሕይወታችን ውስጥ ድንገተኛ ለውጥ ሲያጋጥመን፣ (2) ከልክ ባለፈ የጥፋተኝነት ስሜት ስንሠቃይ እንዲሁም (3) የምንወደውን ሰው በሞት ስናጣ።

በሕይወታችን ውስጥ ድንገተኛ ለውጥ ሲያጋጥመን

4. በሕይወታችን ውስጥ ድንገተኛ ለውጥ ሲያጋጥመን ምን ሊሰማን ይችላል?

4 ሕይወታችን ባልጠበቅነው መንገድ ሊቀየር ይችላል። (መክ. 9:11፤ 1 ቆሮ. 7:31) የጤና እክል፣ የኢኮኖሚ ችግር፣ የፖለቲካ ቀውስ ወይም የምድብ ለውጥ በድንገት ሊያጋጥመን ይችላል። እንዲህ ያለ ለውጥ ሲያጋጥመን ልንጨነቅ ወይም ግራ ልንጋባ እንችላለን። ‘ከዚህ በኋላ ምንድን ነው የማደርገው?’ ብለን እናስብ ይሆናል። ጆሴፍ የተባለ ወንድም እንዲህ ተሰምቶት ነበር። ለ17 ዓመት ያህል በቤቴል ካገለገለ በኋላ በመስኩ ላይ እንዲያገለግል ተመደበ። እንዲህ ብሏል፦ “ለረጅም ዓመት ቤቴል ካገለገልኩ በኋላ አዲስ ሕይወት መጀመር በጣም ከብዶኝ ነበር። ምን እንደማደርግ ግራ ገባኝ።” በሕይወታችን ውስጥ ያልተጠበቀ ለውጥ ሲያጋጥመን ከኢሳይያስ መጽሐፍ ምን መጽናኛ እናገኛለን?

5. በኢሳይያስ 42:16 ላይ ይሖዋ ምን ቃል ገብቶልናል? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

5 ኢሳይያስ 42:16ን አንብብ። ይሖዋ በምሳሌያዊ ሁኔታ ዓይነ ስውራን የሆኑትን ባልለመዱት ጎዳና እንደሚመራቸውና ጨለማውን ወደ ብርሃን እንደሚለውጥላቸው ቃል ገብቷል። “ዓይነ ስውራን፣” “ባልለመዱት ጎዳና፣” “ጨለማ” እና ‘ወጣ ገባ የሆነ ምድር’ የሚሉት አገላለጾች ድንገተኛ ለውጥ ሲያጋጥመን የሚሰማንን ስሜት ጥሩ አድርገው ይገልጻሉ። ጥቅጥቅ ባለ ጫካ ውስጥ መንገድ እንደጠፋበት ሰው እንደሆንን ሊሰማን ይችላል። ሆኖም ይሖዋ በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ የሚያስፈልገንን መመሪያ እንደሚሰጠንና ፈጽሞ እንደማይተወን ቃል ገብቶልናል። እጃችንን ይዞ በጨለማው ውስጥ ይመራናል፤ በመንገዳችን ላይ ብርሃን ያበራልናል፤ እንዲሁም መንገዱን ደልዳላ ያደርግልናል። ይሖዋ ይህን የሚያደርገው እንዴት ነው? በቃሉና በድርጅቱ አማካኝነት ጥበብ የተሞላበት ምክር በመስጠት ነው። (መዝ. 119:105፤ ኢሳ. 30:21) በተጨማሪም የእምነት አጋሮቻችንንና ሌሎችን በመጠቀም ተግባራዊ እርዳታ ይሰጠናል። ስለ ወደፊቱ ጊዜ ስጋት ቢሰማንም እንኳ ይሖዋ በደግነት እንደሚመራንና ስሜታችንን እንደሚረዳልን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ኢሳ. 41:10፤ 1 ጴጥ. 5:6, 7

ሥዕሎች፦ አንድ ባልና ሚስት ይሖዋ በኢሳይያስ 42:16 ላይ ከገባው ‘ባልለመድከው ጎዳና ስትሄድ አልተውህም’ ከሚለው ቃል ጥቅም ሲያገኙ። 1. ባልና ሚስቱ ዕቃቸውን ሲሸክፉ። 2. በአዲሱ ጉባኤያቸው ውስጥ ያለ አንድ ቤተሰብ ሞቅ አድርጎ ሲቀበላቸው።

በሕይወትህ ውስጥ ድንገተኛ ለውጥ ቢያጋጥምህም ይሖዋ ፈጽሞ አይተውህም (አንቀጽ 5ን ተመልከት)b


6. ድንገተኛ ለውጥ ቢያጋጥመን ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን?

6 ቀደም ሲል የተጠቀሰው ጆሴፍ እሱና ባለቤቱ ከቤቴል ከወጡ በኋላ ይሖዋ እንዴት እንደረዳቸው ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “በዚህ ወቅት የይሖዋን ፍቅራዊ እንክብካቤ አይተናል። በወንድሞቻችንና በእህቶቻችን አማካኝነት ረድቶናል። ልክ በሚያስፈልገን ጊዜ ቁሳዊና ስሜታዊ ፍላጎታችንን አሟልቶልናል። አሁንም እየተንከባከበን ነው።” አንተም ድንገተኛ ለውጥ ካጋጠመህ ሁኔታው በጣም አስቸጋሪ ቢመስልም እንኳ ይሖዋ የሚያስፈልግህን ብርታትና አመራር እንደሚሰጥህ መተማመን ትችላለህ። (ኢሳ. 54:10፤ 58:11) ጆሴፍ እንዲህ ብሏል፦ “አንድ ኦሪጅናል መዝሙር ስሜቴን ጥሩ አድርጎ ገልጾታል፤ መዝሙሩ ‘ስጋት አይገባኝም ነገስ ብዬ፤ አይለይም ከኔ፣ ጠባቂዬ’ የሚሉ ስንኞች አሉት።a ነገሮች ባሰብነው መንገድ ላይሄዱ ቢችሉም ስለ አንድ ነገር እርግጠኞች ነን፦ ይሖዋ በመንገዳችን ሁሉ ከእኛ ጋር ይሆናል።”

ከልክ ባለፈ የጥፋተኝነት ስሜት ስንሠቃይ

7. አንዳንዶች ቀደም ሲል በፈጸሙት ኃጢአት ምክንያት ምን ይሰማቸዋል?

7 ከባድ ኃጢአት ስንፈጽም ኃጢአታችንን እንናዘዛለን፤ የሽማግሌዎችን ፍቅራዊ እርዳታ እንቀበላለን፤ እንዲሁም ኃጢአቱን ላለመድገም ጥረት እናደርጋለን። (ምሳሌ 28:13፤ ያዕ. 5:14-16፤ 1 ዮሐ. 1:9) ሆኖም ይሖዋ ይቅር ካለን በኋላም በጥፋተኝነት ስሜት ልንሠቃይ እንችላለን። ‘እንዲህ ያለ ኃጢአት ሠርቼ ይሖዋ እንዴት ይቅር ሊለኝ ይችላል?’ ብለን እናስብ ይሆናል። (2 ቆሮ. 2:7) እንዲህ ቢሰማን አያስገርምም፤ ምክንያቱም ቀደም ሲል የሠራናቸው ስህተቶች እንደ ሸክም ሊጫኑንና ከአእምሯችን በቀላሉ ላይጠፉ ይችላሉ። ንጉሥ ዳዊት “[ከኃጢአቴ] የተነሳ አጥንቶቼ ሰላም የላቸውም። . . . ደነዘዝኩ፤ ፈጽሞም ደቀቅኩ” ብሏል። (መዝ. 38:3, 8) አንተም ቀደም ሲል በፈጸምከው ኃጢአት ምክንያት እንዲህ የሚሰማህ ከሆነ የኢሳይያስ መጽሐፍ ሊያጽናናህ ይችላል።

8-9. በኢሳይያስ 1:18 መሠረት ይሖዋ ይቅር የሚለው እንዴት ነው?

8 ኢሳይያስ 1:18ን አንብብ። ይሖዋ ኃጢአታችንን ሙሉ በሙሉ ይቅር እንደሚል ለመግለጽ ከአእምሮ የማይጠፋ ዘይቤያዊ አነጋገር ተጠቅሟል። ‘ኃጢአታችን እንደ ደም ቢቀላ እንኳ እንደ በረዶ ነጭ እንደሚያደርገው’ ተናግሯል። እንደ ደም ያለ ቀይ ቀለም በቀላሉ አይለቅም። ሆኖም ይሖዋ አንዴ ይቅር ካለን ኃጢአታችንን ምንም ርዝራዥ ሳይተው ሙልጭ አድርጎ እንደሚያጥበው ማረጋገጫ ሰጥቶናል።

9 የንጉሥ ዳዊትን ምሳሌ እንመልከት። እንደ ምንዝርና ነፍስ ማጥፋት ያሉ ኃጢአቶችን ፈጽሞ የነበረ ቢሆንም እንኳ ይሖዋ ይቅር ብሎታል፤ በኋላም በንጹሕ ልብ እንደተመላለሰ ገልጿል። (2 ሳሙ. 11:3, 4, 14, 15፤ 12:13፤ 1 ነገ. 9:4, 5) ይሖዋ ስለ ዳዊት ሲያስብ የሚታየው የፈጸመው ስህተት ሳይሆን ታማኝነቱ ነው። እኛም ንስሐ ከገባን ይሖዋ ይቅር ይለናል፤ እንዲሁም ንጹሕ ሕሊና ይዘን እንድንቀጥል ይረዳናል። ከመጠን ባለፈ የጥፋተኝነት ስሜት ስንዋጥ ከኢሳይያስ መጽሐፍ ሌላስ ምን መጽናኛ እናገኛለን?

10. ኢሳይያስ 38:17 ምን የሚያጽናና ሐሳብ ይዟል?

10 ኢሳይያስ 38:17ን እና የግርጌ ማስታወሻውን አንብብ። “ኃጢአቴን ሁሉ ወደ ኋላህ ጣልክ” የሚለው ሐረግ “ኃጢአቴን ሁሉ ከእይታህ አስወገድክ” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። እዚህ ላይ ይሖዋ፣ አንድ ሰው ንስሐ ከገባ በኋላ ኃጢአቱን ወደ ኋላው እንደሚወረውረው ተገልጿል፤ በመሆኑም ከዚያ በኋላ ኃጢአቱን አያየውም ወይም አያስታውሰውም። አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ እንደገለጸው ይህ ሐሳብ “[ኃጢአቴን] ያልነበረ ያህል አደረግከው” ተብሎም ሊገለጽ ይችላል። ስለዚህ ይሖዋ ኃጢአታችንን ይቅር ሲል ኃጢአቱን ያልተፈጸመ ያህል ይቆጥረዋል። አንዴ ይቅር ካለን በኋላ ያንን ኃጢአት አንስቶ አይወቅሰንም ወይም አይቀጣንም። የኃጢአቱን መዝገብ ሙሉ በሙሉ ይደመስሰዋል። “[ኃጢአትህን] አላስታውስም” በማለት ቃል ገብቷል። (ኢሳ. 43:25) ይህ ምንኛ የሚያጽናና ነው! ታላቁ ዳኛ ይሖዋ ኃጢአታችንን እያስታወሰ የማይኮንነን ከሆነ እኛ ራሳችንን የምንኮንንበት ምንም ምክንያት የለም!

ቀደም ሲል የሠራሃቸው ስህተቶች የአሁኑን ደስታህን እንዲሰርቁብህ አትፍቀድ

11. ይሖዋ የሚያተኩረው በምን ላይ ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

11 ከልክ ያለፈ የጥፋተኝነት ስሜት ሲያገረሽብን ይሖዋ የገባልንን ቃል እናስታውስ። ይሖዋ ይቅር የሚለን ሙሉ በሙሉ ነው። ቀደም ሲል በሠራናቸው ስህተቶች የተነሳ አያፍርብንም፤ እንዲሁም እንደ ሰዎች ቂም አይዝም። (ኢሳ. 57:16) ይሖዋ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ለትናንቱ ሳይሆን ለዛሬውና ለነገው ማንነታችን ነው። (ኢሳ. 55:7) በእርግጥም የምናመልከው አምላክ እጅግ አፍቃሪና መሐሪ ነው! እንግዲያው ቀደም ሲል የሠራናቸው ስህተቶች የአሁኑን ደስታችንን ወይም የወደፊቱን በረከታችንን እንዲሰርቁን ፈጽሞ አንፍቀድ።

ሥዕሎች፦ አንድ ወንድም በኢሳይያስ 38:17 ላይ ከሚገኘው “ኃጢአቴን ሁሉ ወደ ኋላህ ጣልክ” ከሚለው ዋስትና ጥቅም ሲያገኝ። 1. ወንድም ቀደም ሲል በሠራው ኃጢአት ምክንያት በሐዘን ተውጦ። 2. ከጊዜ በኋላ በአቅኚነት አገልግሎት ትምህርት ቤት እየተካፈለ በደስታ መልስ ሲመልስ።

ይሖዋ ቀደም ሲል በፈጸምናቸው ስህተቶች ላይ አያተኩርም (አንቀጽ 11ን ተመልከት)c


የምንወደውን ሰው በሞት ስናጣ

12. የምንወደው ሰው ሲሞት ምን ሊሰማን ይችላል?

12 የምንወደውን ሰው በሞት ስናጣ ለመቋቋም የሚያስቸግርና ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ሐዘን ሊገጥመን ይችላል። ‘ይሖዋ ይህን ለምን ፈቀደ?’ የሚለው ጥያቄ እረፍት ሊነሳን ይችላል። ማይክል የተባለ አንድ ወንድም ወላጆቹን በእሳት አደጋ ካጣ በኋላ ምን እንደተሰማው ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ልቤ ደማ። ወላጆቼ እንዲሞቱ በመፍቀዱ በይሖዋ ላይ ተቆጣሁ። የገደላቸው እሱ እንዳልሆነ አውቃለሁ፤ ግን እንዳይሞቱ ማድረግ ይችል ነበር።” አንተም እንዲህ ተሰምቶህ ሊሆን ይችላል። እንዲህ ያለ ሐዘን ሲያጋጥመን ይሖዋ መጽናኛና ተስፋ የሚሰጠን እንዴት ነው?

13. በኢሳይያስ 25:8 ላይ ይሖዋ ምን ተስፋ ሰጥቶናል?

13 ኢሳይያስ 25:8ን አንብብ። ይሖዋ ‘ሞትን ለዘላለም እንደሚውጥ’ ቃል ገብቷል። ሞት የማይኖርበት ጊዜ ምን እንደሚመስል እስቲ ለማሰብ ሞክር። የምትወደውን ሰው በሞት አጥተህ ሐዘን አትቀመጥም። (ኢሳ. 35:10) ወይም ደግሞ የምትወደውን ሰው ቀብረህ አትመለስም። ከዚህ ይልቅ ‘ወዳጅ ዘመዶቼን በሞት አጣለሁ’ የሚል ስጋት ሳይኖርብህ ለዘላለም በሰላምና በጤና አብረሃቸው የመኖር ተስፋ አለህ። ይህ ተስፋ እንዲሁ ምኞት ብቻ አይደለም። እንዲህ ያለውን ነገር መፈጸም የሚችለው ይሖዋ ብቻ ነው፤ ይህን ተስፋ የሰጠን ደግሞ እሱ ራሱ ነው።—ራእይ 21:4, 5

14. በትንሣኤ ተስፋ ላይ ስታሰላስል ምን ይሰማሃል? (ኢሳይያስ 26:19) (ሥዕሉንም ተመልከት።)

14 ኢሳይያስ 26:19ን አንብብ። ይሖዋ ሞትን እንደሚያስቀር ብቻ ሳይሆን የሞቱ ወዳጅ ዘመዶቻችንን እንደሚያስነሳም ቃል ገብቷል። ስለ እነሱ ሲናገር “የእኔ አስከሬኖች ይነሳሉ” ብሏል። ይህም የግል ንብረቱ አድርጎ እንደሚቆጥራቸው ያሳያል። ፈጽሞ አይረሳቸውም። የቀጠረው ጊዜ ሲደርስ ትንሣኤ ይሰጣቸዋል። የማለዳ ጠል የደረቁ ዕፀዋትን እንደሚያለመልም ሁሉ የሕይወት ምንጭ የሆነው ይሖዋ የሞቱ ወዳጅ ዘመዶቻችንን ከሞት ያስነሳቸዋል። በዚያ ወቅት እነሱን መቀበል ምንኛ የሚያስደስት ይሆናል!—ከማርቆስ 5:42 ጋር አወዳድር።

ሥዕሎች፦ አንዲት እህት ይሖዋ በኢሳይያስ 26:19 ላይ ከሰጠው “ሙታንህ ሕያዋን ይሆናሉ” ከሚለው ተስፋ ጥቅም ስታገኝ። 1. ልጇን በሞት ያጣች አንዲት እናት የልጇ መኝታ ቤት ውስጥ ብቻዋን ቁጭ ብላ አንድ ፎቶግራፍ ይዛለች። 2. ልጇ ከሞት ከተነሳች በኋላ በደስታ ስታቅፋት።

የሞቱብን ሰዎች እንደሚነሱ የሚናገረው ተስፋ አስተማማኝ ነው (አንቀጽ 14ን ተመልከት)


15. የትንሣኤ ተስፋ ሐዘናችንን እንድንቋቋም የሚረዳን እንዴት ነው?

15 አምላክ የሰጠን የትንሣኤ ተስፋ ሐዘናችንን ሙሉ በሙሉ ባያስወግድልንም ይሖዋ የሞቱብንን ሰዎች እንዳልረሳቸው ማወቃችን ያጽናናናል። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ማይክል ይህ ተስፋ አጽናንቶታል። እንዲህ ብሏል፦ “ኢሳይያስ 26:19 ይሖዋ ወላጆቼን እንደ ውድ ንብረቱ እንደሚቆጥራቸው እንድገነዘብ አስችሎኛል። እስካሁን አልረሳቸውም፤ ወደፊትም አይረሳቸውም። ደግሞም የቀጠረው ጊዜ ሲደርስ ከሞት ያስነሳቸዋል። ይህን ማወቄ መጽናኛና ብርታት ሰጥቶኛል።” እኛም የምንወዳቸውን ሰዎች መልሰን ስለምናገኝበት ጊዜ እናሰላስል። እንዲህ ማድረጋችን ሐዘኑን መቋቋም እንድንችል ይረዳናል።

16. አስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ ስትሆን የሚያጽናናህ ጥቅስ የትኛው ነው?

16 በሕይወታችን ውስጥ ድንገተኛ ለውጥ ሲያጋጥመን፣ ከልክ ባለፈ የጥፋተኝነት ስሜት ስንሠቃይ እንዲሁም የምንወደውን ሰው በሞት ስናጣ ሊያጽናኑን የሚችሉ በኢሳይያስ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙ ጥቂት ጥቅሶችን ተመልክተናል። ይሖዋ በቃሉ አማካኝነት ስለሚያጽናናንና ስለሚያረጋጋን ምንኛ አመስጋኞች ነን! (መዝ. 94:19) አንተስ አስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ ስትሆን የሚያጽናናህ ጥቅስ አለ? ጥቅሱን በቃልህ ለመያዝ ሞክር፤ ማስታወሻ ደብተርህ ላይ ጻፈው፤ ወይም በግልጽ የምታየው ቦታ ላይ ለጥፈው። እንግዲያው አፍቃሪው አባታችን ይሖዋ ከተናገራቸው ቃላት ምንጊዜም መጽናኛ ማግኘትህን ቀጥል።

የሚከተሉት ጥቅሶች የሚያጽናኑህ እንዴት ነው?

  • ኢሳይያስ 42:16

  • ኢሳይያስ 1:18፤ 38:17

  • ኢሳይያስ 25:8፤ 26:19

መዝሙር 3 ኃይላችን፣ ተስፋችን፣ ትምክህታችን

a እነዚህ ስንኞች የተወሰዱት “ይሖዋን ይዤ” ከሚለው ኦሪጅናል መዝሙር ነው።

b የሥዕሉ መግለጫ፦ ከቤቴል የወጡ አንድ ባልና ሚስት በአዲሱ ጉባኤያቸው ጥሩ አቀባበል ሲደረግላቸው።

c የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ ወንድም የቀድሞ አኗኗሩን ረስቶ በአቅኚነት አገልግሎት ትምህርት ቤት በደስታ ሲካፈል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2026)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2026 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ