ከመስከረም 21-27, 2026
መዝሙር 12 ታላቁ አምላክ ይሖዋ
ይሖዋን ይበልጥ ማወቅህን ቀጥል
“የአባትህን አምላክ እወቅ፤ በሙሉ ልብ . . . አገልግለው።”—1 ዜና 28:9
ዓላማ
ይሖዋን ማወቅ ሲባል ምን ማለት ነው? እሱን ይበልጥ ማወቅ ያለብን ለምንድን ነው? ይህን ማድረግ የምንችለውስ እንዴት ነው?
1. ይሖዋ ስላለው እውቀትና ጥበብ እንዲሁም ስላከናወናቸው ነገሮች ስናስብ ምን ይሰማናል?
የይሖዋ እውቀት ምን ያህል ሰፊ እንደሆነ፣ ጥበቡ ምን ያህል ጥልቅ እንደሆነ ወይም ያከናወናቸው ነገሮች ምን ያህል አስደናቂ እንደሆኑ ስታስብ ምን ይሰማሃል? ስለ ፈጣሪያችን ስናስብ ራሳችንን ዝቅ ለማድረግ እንነሳሳለን። ምናልባትም እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ዓይነት ስሜት ይሰማህ ይሆናል፤ ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የአምላክ ብልጽግና፣ ጥበብና እውቀት እንዴት ጥልቅ ነው! ፍርዱም ፈጽሞ የማይመረመር ነው! መንገዱም የማይደረስበት ነው!”—ሮም 11:33, 34
2. ይሖዋን ማወቅ ይቻላል የምንለው ለምንድን ነው?
2 መቼም ቢሆን ስለ ይሖዋ ሁሉንም ነገር ማወቅ አንችልም፤ ሆኖም በተወሰነ ደረጃ የእሱን ማንነት ማወቅ እንችላለን። ንጉሥ ዳዊት ለልጁ ለሰለሞን እንዲህ ብሎታል፦ “የአባትህን አምላክ እወቅ፤ በሙሉ ልብ [አገልግለው።] ብትፈልገው ይገኝልሃል።” (1 ዜና 28:9) በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ ደግሞ ሐዋርያው ዮሐንስ የእምነት አጋሮቹን ‘ስለ እውነተኛው አምላክ እውቀት ማግኘት እንደሚችሉ’ ነግሯቸዋል። (1 ዮሐ. 5:20) ኢየሱስም ቢሆን ‘ወልድ ሊገልጥለት የሚፈቅድ’ ሁሉ ይሖዋን ማወቅ እንደሚችል ተናግሯል።—ማቴ. 11:27
3. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?
3 ራሳቸውን ለይሖዋ የወሰኑ ክርስቲያኖች በሙሉ ስለ እሱ ብዙ ነገር ተምረዋል። ያም ሆኖ፣ መቼም ቢሆን ይሖዋን ‘ማወቃችንን’ አናቆምም። (ዮሐ. 17:3፤ የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።) እሱን ማስደሰት እንዲሁም በእሱ ላይ ያለንን እምነት ማጠናከር ስለምንችልበት መንገድ ሁሌም ተጨማሪ እውቀት መቅሰም እንችላለን። በዚህ ርዕስ ውስጥ የሚከተሉትን ሦስት ጥያቄዎች እንመልሳለን፦ ይሖዋን ማወቅ ሲባል ምን ማለት ነው? ይሖዋን ይበልጥ ማወቃችንን መቀጠል ያለብን ለምንድን ነው? እሱን ይበልጥ ማወቅ የምንችለውስ እንዴት ነው? ይሖዋን ስናገለግል የቆየነው ለአጭር ጊዜም ይሁን ለረጅም የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ማወቃችን ጠቃሚ ነው።
ይሖዋን ማወቅ ሲባል ምን ማለት ነው?
4. ይሖዋን ማወቅ ምን ያካትታል?
4 ይሖዋ ከግዞት ስለሚመለሱት አይሁዳውያን የተናገረው ነገር እሱን ማወቅ ምን እንደሚያካትት ለመረዳት ያስችለናል። እንዲህ ብሏል፦ “እኔ ይሖዋ መሆኔን እንዲያውቁም ልብ እሰጣቸዋለሁ።” (ኤር. 24:7) ከባቢሎን የተመለሱት አይሁዳውያን ስለ ይሖዋ መሠረታዊ እውቀት እንደነበራቸው ምንም ጥያቄ የለውም። ሆኖም ከጥቅሱ እንደምንረዳው ይሖዋን ማወቅ ከልባቸው ማለትም ከስሜታቸውና ከውስጣዊ ዝንባሌያቸው ጋር የተያያዘ ነገር ነው። አንድ ማመሣከሪያ ጽሑፍ እንዲህ ይላል፦ “ስለ አምላክ በማወቅና አምላክን በማወቅ መካከል ሰፊ ልዩነት አለ። ልዩነቱ ስለ ፍቅር በሚያነብ ሰውና ፍቅር በያዘው ሰው መካከል ካለው ልዩነት ጋር ሊመሳሰል ይችላል።” ይሖዋ ስም እንዳለውና እሱ አምላክ እንደሆነ ማወቃችን ብቻውን በቂ አይደለም። የእሱን ግሩም ባሕርያትም ማወቅ ይኖርብናል።
5. ይሖዋን ማወቅ ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ከንጉሥ ኢዮስያስ ታሪክ ምን እንማራለን?
5 ይሖዋን እያወቅን ስንሄድ እሱን ምን እንደሚያስደስተውና ምን እንደሚያሳዝነው እንገነዘባለን። ንጉሥ ኢዮስያስ በዚህ ረገድ ጥሩ ምሳሌ ይሆነናል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እሱ ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “በነገሠ በ8ኛው ዓመት፣ ገና ልጅ ሳለ የአባቱን የዳዊትን አምላክ መፈለግ ጀመረ።” (2 ዜና 34:3) ሆኖም ኢዮስያስ ይሖዋን የፈለገው ስለ እሱ በማጥናት ብቻ አይደለም። የተማረውን ነገር በሥራ ላይ አውሏል። ይሖዋ በነቢዩ ኤርምያስ አማካኝነት ስለ ኢዮስያስ ሲናገር ‘ለፍትሕና ለጽድቅ እንደቆመ’ እንዲሁም ለተጎሳቆለው ሰውና ለድሃው እንደተሟገተ ገልጿል። ከዚያም ይሖዋ “እኔን ማወቅ ማለት ይህ አይደለም?” ብሏል።—ኤር. 22:15, 16
6. በመዝሙር 9:10 መሠረት ይሖዋን ማወቃችን ምን ለማድረግ ያነሳሳናል?
6 መዝሙር 9:10ን አንብብ። ይሖዋን ይበልጥ እያወቅነው ስንሄድ በእሱ ይበልጥ እንታመናለን። የሐዋርያው ጳውሎስ ታሪክ ይህ እውነት መሆኑን ያሳያል። ጳውሎስ ለመጨረሻ ጊዜ በታሰረበት ወቅት ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “አላፍርበትም። ያመንኩበትን እሱን አውቀዋለሁና።” (2 ጢሞ. 1:12) ጳውሎስ በሕይወቱ ውስጥ ያገኘው እውቀትና ያሳለፈው ተሞክሮ በይሖዋ ሙሉ በሙሉ እንዲታመን አነሳስቶታል። ጳውሎስ፣ ይሖዋ እሱንም ሆነ በታማኝነት ያከናወነውን አገልግሎት እንደሚያስታውስ እንዲሁም ከሞት እንደሚያስነሳው እርግጠኛ ነበር።
ይሖዋን ማወቃችንን መቀጠል ያለብን ለምንድን ነው?
7. ይሖዋን ለበርካታ ዓመታት ካገለገልን በኋላ ምን አዝማሚያ ሊታይብን ይችላል?
7 እውነትን በሰማንበት ወቅት ይሖዋን ለማወቅ ከፍተኛ ጥረት እናደርግ ነበር። ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ግን ይህን ጥረታችንን ልንቀንስ እንችላለን። ለምሳሌ በግላችንም ሆነ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ ‘ትምህርቱን እንዴት በሥራ ላይ ላውለው እችላለሁ?’ ወይም ‘ሌሎችን ለመርዳት እንዴት ልጠቀምበት እችላለሁ?’ በሚለው ላይ እናተኩር ይሆናል። እንዲህ ማድረጋችን ተገቢ ነው። መጽሐፍ ቅዱስም ይህን እንድናደርግ ያበረታታናል። (2 ጢሞ. 3:16, 17) ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ይሖዋም ብዙ ነገር ያስተምረናል። (መዝ. 25:8-10) መጽሐፍ ቅዱስ ለእኛም ሆነ ለሌሎች ያለውን ተግባራዊ ጠቀሜታ ማሰባችን ተገቢ ቢሆንም ዋናውን ነገር ልንረሳ አይገባም። ‘ይህ ዘገባ ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረኛል?’ ብለን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል።a
8. ይሖዋን ይበልጥ ማወቃችን ከእሱ ጋር ባለን ወዳጅነት ላይ ምን ለውጥ ያመጣል? (መዝሙር 73:24-28)
8 ይሖዋን ይበልጥ እያወቅነው ስንሄድ ከእሱ ጋር ያለን ወዳጅነት ይበልጥ ይጠናከራል። ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስን ካነበብክ፣ ወርሃዊ ብሮድካስት ከተመለከትክ ወይም በትልቅ ስብሰባ ላይ ከተገኘህ በኋላ ምን ይሰማሃል? ብዙዎቻችን ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንደቀረብን ይሰማናል። ለምን? ምክንያቱም ስለ እሱ ተጨማሪ እውቀት አግኝተናል። በዚህም ምክንያት እሱን ለማወደስና ለማመስገን እንነሳሳለን። የመዝሙራዊውን ስሜት እንጋራለን። መዝሙራዊው ይሖዋ ስላደረገለት እንክብካቤ ካሰላሰለ በኋላ “አምላክ . . . ለዘላለም የልቤ ዓለትና ድርሻዬ ነው” ብሏል። (መዝሙር 73:24-28ን አንብብ።) ይሖዋን ይበልጥ ለማወቅ የምናደርገው ጥረት ከእሱ ጋር ያለንን ውድ ወዳጅነት ይበልጥ ከፍ አድርገን እንድንመለከተው ያነሳሳናል።
9. ይሖዋን ‘ግምት ውስጥ ማስገባታችን’ የምናደርጋቸውን ውሳኔዎች የሚነካው እንዴት ነው? በምሳሌ አስረዳ።
9 ይሖዋን ‘ግምት ውስጥ ካስገባን’ ማለትም ስለ እሱ የተማርነውን ነገር ካስታወስንና የምናደርገው ነገር በእሱ ላይ የሚፈጥረውን ስሜት ካሰብን ጥሩ ውሳኔዎችን እናደርጋለን። (ምሳሌ 3:5, 6) ለምሳሌ በርካታ ወንድሞችና እህቶች የትዳር አጋራቸውን ፎቶግራፍ በጠረጴዛቸው፣ በኪስ ቦርሳቸው ወይም በስልካቸው ላይ ያስቀምጣሉ። ይህም ስለ ትዳር አጋራቸው አዘውትረው እንዲያስቡ፣ የትዳር አጋራቸውን የሚያስደስት ውሳኔ እንዲያደርጉ እንዲሁም የትዳር አጋራቸውን የሚጎዳ ነገር ከማድረግ እንዲቆጠቡ ይረዳቸዋል። እኛም በተመሳሳይ ስለ ይሖዋ አዘውትረን የምናስብ ከሆነ እሱን የሚያስደስቱ ውሳኔዎችን ማድረግ ይበልጥ ቀላል ይሆንልናል።—መዝ. 19:13, 14
10. ስለ ይሖዋ ይበልጥ መማራችን ምን ለማድረግ ይረዳናል?
10 የተፈጠርነው በይሖዋ መልክ ስለሆነ የእሱን ባሕርያት የማንጸባረቅ ችሎታ አለን። (ዘፍ. 1:26) ስለ ይሖዋ ባሕርያት ይበልጥ ስናውቅ ደግሞ እሱን መምሰል የምንችልበት መንገድ ይበልጥ ግልጽ ይሆንልናል። ኢየሱስ ጸሐፍትና ፈሪሳውያን አምላካዊ ባሕርያትን ባለማሳየታቸው አውግዟቸዋል። በሕጉ ውስጥ ለተጠቀሱት ጥቃቅን ጉዳዮች ትኩረት የሚሰጡ ቢሆንም ‘እንደ ፍትሕ፣ ምሕረትና ታማኝነት ያሉ ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ችላ ብለዋል።’ (ማቴ. 23:23) እኛ ግን ከእነዚህ የሃይማኖት መሪዎች በተለየ በይሖዋ ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ የተንጸባረቁትን ባሕርያቱን ለመረዳት ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። እንዲህ ማድረጋችን እነዚህን ባሕርያት ለመኮረጅ ይረዳናል።—1 ዮሐ. 4:8, 11
ይሖዋን ይበልጥ ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው?
11. ከይሖዋ ጋር የተዋወቅከው እንዴት ነው?
11 ከይሖዋ ጋር ያስተዋወቀህ ማን ነው? ያደግከው እውነት ቤት ውስጥ ከሆነ ወላጆችህ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችንና የፍጥረት ሥራዎችን ተጠቅመው የይሖዋን ባሕርያት እንድታውቅ ረድተውህ ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ አንድ የይሖዋ ምሥክር ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለውን መጽሐፍ አሊያም ሌላ የማስጠኛ ጽሑፍ ተጠቅሞ መጽሐፍ ቅዱስን አስጠንቶህ ሊሆን ይችላል። ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችና ከፍጥረት ሥራዎች የይሖዋን ማራኪ ባሕርያት ማስተዋል የምትችለው እንዴት እንደሆነ እንድትገነዘብ ረድቶህ መሆን አለበት።b (ነህ. 8:8፤ ሥራ 14:17) ታዲያ ስለ ይሖዋ መማርህን መቀጠል የምትችለው እንዴት ነው?
12-13. መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ ስለ ይሖዋ ይበልጥ ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? ምሳሌ ስጥ። (ኤርምያስ 39:15-18) (ሥዕሉንም ተመልከት።)
12 ይሖዋን ይበልጥ ማወቅ የምንችልበት አንዱ መንገድ ቃሉን በማንበብና በማጥናት ነው። አንዳንድ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋን ባሕርያት በቀጥታ ይገልጻል። (ዘፀ. 34:6, 7) ይሁንና አብዛኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች የሚናገሩት ሰዎች ስላደረጓቸው ነገሮች ነው። እንዲህ ያሉ ታሪኮችን ስታነብ ዘገባዎቹ ስለ ይሖዋ ምን እንደሚያስተምሩህ ቆም ብለህ አስብ።
13 አንድ ምሳሌ እንመልከት። በኤርምያስ 38:6-13 ላይ ኢትዮጵያዊው ኤቤድሜሌክ ኤርምያስን ያዳነው እንዴት እንደሆነ እናነባለን። ይህን ዘገባ ስታነብ የኤቤድሜሌክን ምሳሌ መኮረጅ የምትችልባቸውን መንገዶች ወዲያውኑ ማስተዋልህ አይቀርም። ለምሳሌ የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈሱን፣ ድፍረቱን ወይም ለእምነት አጋሮቹ የነበረውን ፍቅር መኮረጅ ትችላለህ። ይሁንና ከዚህ ዘገባ ስለ ይሖዋ ባሕርያትስ መማር ትችል ይሆን? (ኤርምያስ 39:15-18ን አንብብ።) ለምሳሌ ይህ ታሪክ ይሖዋ አድናቂ፣ ፍትሐዊና የማያዳላ አምላክ እንደሆነ የሚያሳየው እንዴት ነው? ከዚህ ዘገባ ሌሎች የይሖዋ ባሕርያትንስ ማስተዋል ትችላለህ? አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ባነበብክ ቁጥር በዘገባው ላይ የተንጸባረቁት የይሖዋ ባሕርያት የትኞቹ እንደሆኑ ለማስተዋል ሞክር፤ ከዚያም እነዚህን ባሕርያት በመጥቀስ ይሖዋን አመስግነው እንዲሁም አወድሰው።
ኤርምያስ ጉድጓድ ውስጥ በተጣለበት ወቅት ኤቤድሜሌክ በድፍረት ሲታደገው (አንቀጽ 12-13ን ተመልከት)
14. ከተፈጥሮ ትምህርት ማግኘት ከፈለግን ምን ማድረግ ይኖርብናል?
14 ስለ ይሖዋ ይበልጥ መማር የምንችልበት ሁለተኛው መንገድ በፍጥረት ሥራዎቹ ላይ በማሰላሰል ነው። (መዝ. 145:9, 10) እርግጥ ነው፣ ተፈጥሮን መመልከታችን ብቻውን በቂ አይደለም። አንዳንዶች ዕድሜ ልካቸውን ስለ ተፈጥሮ እያጠኑ ቢኖሩም የይሖዋን ባሕርያት አያስተውሉም፤ ይባስ ብሎም እሱ መኖሩን እንኳ ይክዳሉ! ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የማይታዩት ባሕርያቱ . . . ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ በግልጽ ይታያሉ፤ ምክንያቱም ባሕርያቱን ከተሠሩት ነገሮች ማስተዋል ይቻላል።” (ሮም 1:20) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ይህን ጥቅስ ‘የአምላክ ባሕርያት በማስተዋል ዓይን ይታያሉ’ በማለት ተርጉሞታል። ስለዚህ ይሖዋ ስለፈጠራቸው አስደናቂ ነገሮች ቆም ብለን ማሰብ እንዲሁም ‘ስለ ይሖዋ ባሕርያት ምን ያስተምሩኛል?’ ብለን መጠየቅ ይኖርብናል።
15. ፓትሪክ ይሖዋን ይበልጥ ማወቅ የቻለው እንዴት ነው? አንተስ ተመሳሳይ ነገር ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
15 ብዙዎቻችን የምንኖረው ከተማ ውስጥ በመሆኑ ተፈጥሮን ለማየት የሚያስችል ብዙ አጋጣሚ እንደሌለን ይሰማን ይሆናል። ይሁንና ከተማ ውስጥ እየኖርንም ከተፈጥሮ መማር የምንችልበት መንገድ ይኖር ይሆን? በኮንጎ ሪፑብሊክ ውስጥ በሚገኝ ብራዛቪል የተባለ ትልቅ ከተማ ውስጥ የሚኖረውን የፓትሪክን ምሳሌ እንመልከት። ፓትሪክ እንዲህ ብሏል፦ “በረንዳዬ ላይ ቆሜ ተፈጥሮን ለመመልከት እሞክራለሁ። ብዙውን ጊዜ ጥቃቅን ነፍሳት ወይም ትናንሽ ወፎች ምግብና መጠለያ ለማግኘት ወዲያ ወዲህ ሲሉ አያለሁ። በአንድ ወቅት የተወሰኑ ወፎች ጎጆ ሲሠሩ ተመለከትኩ። ጫጩቶችን ለማሳደግ ተስማሚ የሆኑ ቁሳቁሶችን ከሰፈራችን ሰብስበው ጎጇቸውን ሠሩ።” ሆኖም ፓትሪክ ወፎቹን በመመልከት ብቻ አላቆመም፤ ስለ ፈጣሪው በጥልቀት ማሰብ ጀመረ። እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ ትናንሽ ፍጥረታትን ጨምሮ ለፍጥረታቱ በሙሉ እንደሚያስብ ተገነዘብኩ። ይህን ማየቴ ለእኔም እንደሚያስብልኝና የሚያስፈልገኝን ነገር ሁሌም እንደሚያሟላልኝ እንድተማመን አደረገኝ።”
በተፈጥሮ ላይ በማሰላሰል ይሖዋን ይበልጥ ለማወቅ ጥረት አድርግ (አንቀጽ 15ን ተመልከት)
16. ማርያም ይሖዋን ይበልጥ እንድታውቅ የረዳት ምንድን ነው? እኛስ የእሷን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
16 ይሖዋን ይበልጥ ማወቅ የምንችልበት ሦስተኛው መንገድ በሕይወታችን ውስጥ የእሱን እርዳታ ባየንባቸው ጊዜያት ላይ በማሰላሰል ነው። የኢየሱስ እናት ማርያም እንዲህ አድርጋለች። ማርያም ቀድሞውንም ቢሆን ይሖዋን በደንብ ታውቀው ነበር፤ እንዲያውም ‘በፊቱ ሞገስ አግኝታለች።’ (ሉቃስ 1:30) በኋላ ግን የአምላክን ልጅ ወልዶ የማሳደግ ከባድ ኃላፊነት ተሰጣት። በዚህ ወቅት ይሖዋ መልአኩን ገብርኤልንና ዘመዷን ኤልሳቤጥን በመጠቀም ማርያምን አበረታታት። ከጊዜ በኋላ ማርያም ባገኘችው ማበረታቻ ላይ በማሰላሰል ስለ ይሖዋ ትምህርት ቀስማለች። ለምሳሌ ኃይሉን፣ ምሕረቱን፣ የማያዳላ አምላክ መሆኑን እንዲሁም ዝቅ ያሉትን በትኩረት የሚመለከት መሆኑን አስተውላለች። (ሉቃስ 1:46-55) ማርያም አምላክ ላደረገላት እርዳታ አድናቆት ነበራት። እኛም ይሖዋ “በሚያስፈልገን ጊዜ” እርዳታ ሲሰጠን አመስጋኞች ነን። (ዕብ. 4:16) በሕይወትህ ውስጥ የይሖዋን እጅ ካየህ በኋላ ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘ይህ ሁኔታ ስለ ይሖዋ ምን አስተምሮኛል? የትኞቹን የይሖዋን ባሕርያት አስተውያለሁ?’
ይሖዋ ባደረገልህ እርዳታ ላይ በማሰላሰል እሱን ይበልጥ ለማወቅ ጥረት አድርግ (አንቀጽ 16ን ተመልከት)c
ስለ ይሖዋ መማራችንን አናቆምም
17-18. መቼም ቢሆን ስለ ይሖዋ መማራችንን አናቆምም የምንለው ለምንድን ነው?
17 በአዲሱ ዓለም ስለ ይሖዋ ምን ያህል እንደምንማር ለማሰብ ሞክር። እሱ ከእኛ ምን እንደሚፈልግ የሚገልጹ አዳዲስ ጥቅልሎች ይከፈቱልናል። (ራእይ 20:12) ተፈጥሮን ይበልጥ በቅርበት ማጥናት እንችላለን። (ኢሳ. 11:6-9) በተጨማሪም በሕይወታችን ውስጥ የይሖዋን እጅ በአዳዲስ መንገዶች ስናይ ለምሳሌ የሞቱ ወዳጅ ዘመዶቻችን ሲነሱ እንዲሁም ዕለት ዕለት ወደ ፍጽምና ይበልጥ እየተጠጋን ስንሄድ ስለ ይሖዋ ያለን እውቀት ይጨምራል።
18 መቼም ቢሆን ስለ ይሖዋ መማራችንን አናቆምም። ይሖዋ ለዘላለም ኖሯል፤ “ማስተዋሉም ወሰን የለውም።” (መዝ. 90:2፤ 147:5) ‘እውነተኛው አምላክ ከመጀመሪያው አንስቶ እስከ መጨረሻው ድረስ ያከናወነውን ሥራ በምንም ዓይነት መርምረን ልንደርስበት አንችልም።’ (መክ. 3:11) እንግዲያው እውነት ውስጥ የቆየንበት ዘመን ምንም ያህል ረጅም ቢሆን ስለ አፍቃሪው አባታችን ለማወቅ የሚያስችለንን እያንዳንዱን አጋጣሚ በሚገባ እንጠቀምበት።
መዝሙር 28 የይሖዋ ወዳጅ መሆን
b ለዘላለም በደስታ ኑር! ከተባለው መጽሐፍ ላይ ምዕራፍ 07 ከነጥብ 5-7ን ተመልከት።
c የሥዕሉ መግለጫ፦ ክፍል ማቅረብ በጣም የሚያስፈራው አንድ ወንድም ከዚህ በፊት በሳምንቱ መሃል ስብሰባ ላይ ክፍል ሲያቀርብ ይሖዋ የረዳው እንዴት እንደሆነ ሲያሰላስል።