የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w26 ሐምሌ ገጽ 2-7
  • ከገባኦናውያን ተማሩ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ከገባኦናውያን ተማሩ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2026
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • እምነትና ትሕትና ይኑራችሁ
  • ኢፍትሐዊ ድርጊት ሲፈጸምባችሁ ይሖዋን በትዕግሥት ጠብቁ
  • እውነተኛውን አምልኮ በታማኝነት ደግፉ
  • ጥበበኞቹ ገባዖናውያን
    የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ
  • ስለ ገባኦናውያን ከሚናገረው ታሪክ የምናገኛቸው ትምህርቶች
    ክርስቲያናዊ ሕይወታችንና አገልግሎታችን​—የስብሰባው አስተዋጽኦ—2021
  • ኢያሱና ገባኦናውያን
    ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
  • የአንባቢያን ጥያቄዎች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2022
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2026
w26 ሐምሌ ገጽ 2-7

ከመስከረም 7-13, 2026

መዝሙር 88 መንገድህን አሳውቀኝ

ከገባኦናውያን ተማሩ

“የገባኦን ነዋሪዎች ከእስራኤላውያን ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ፈጥረው በመካከላቸው [ኖሩ]።”—ኢያሱ 10:1

ዓላማ

ገባኦናውያን ከተዉት ምሳሌና ይሖዋ እነሱን ከያዘበት መንገድ ምን ትምህርት እናገኛለን?

1-2. የገባኦናውያንን ታሪክ መመርመራችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?

ጊዜው 1473 ዓ.ዓ. ነው። የእስራኤል ብሔር ተስፋይቱን ምድር መቆጣጠር ጀምሯል። እስራኤላውያን በኢያሪኮና በጋይ ከተሞች ላይ አስደናቂ ድል ተቀዳጅተዋል። በኋላ ግን ያልተጠበቀ ነገር ተከሰተ። የሆኑ ሰዎች መጥተው እስራኤላውያንን አነጋገሯቸው። እነዚህ ሰዎች ከሩቅ አገር እንደመጡ በመግለጽ ከአምላክ ሕዝብ ጋር የሰላም ስምምነት መመሥረት እንደሚፈልጉ ተናገሩ።

2 ሰዎቹ ገባኦናውያን ናቸው። ገባኦናውያን ለመጀመሪያ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሱት እዚህ ዘገባ ላይ ነው። በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች እንደሚያሳዩት ገባኦናውያን ለቀጣዮቹ በርካታ መቶ ዘመናት በእስራኤላውያን መካከል መኖራቸውን ቀጥለዋል። እነዚህ ታሪኮች ጠቃሚ ትምህርት ይዘውልናል፤ ስለ ይሖዋም ብዙ ነገር ያስተምሩናል።

እምነትና ትሕትና ይኑራችሁ

3. (ሀ) ገባኦናውያን እነማን ነበሩ? (ለ) ከእስራኤላውያን ጋር ሰላም ለመፍጠር ጥረት ያደረጉት ለምንድን ነው?

3 እስራኤላውያን የከነአንን ምድር መቆጣጠር በጀመሩ ጊዜ ገባኦናውያን በቅጥር በተመሸገችው የገባኦን ከተማ ይኖሩ ነበር። ገባኦናውያን የሂዋውያን ብሔር አባላት ነበሩ፤ ሂዋውያን ደግሞ ከእስራኤላውያን ይልቅ ‘ብዙ ሕዝብ ካላቸውና ኃያላን ከሆኑት’ ሰባት የከነአን ብሔራት አንዱ ናቸው። (ዘዳ. 7:1) በመሆኑም ገባኦናውያን ኃያል ተዋጊዎች ነበሩ። (ኢያሱ 10:2) ይሁንና ከሌሎቹ ከነአናውያን በተለየ ገባኦናውያን ከእስራኤላውያን ጋር መዋጋት ምንም ፋይዳ እንደሌለው ተገንዝበው ነበር። ይሖዋ ለሕዝቡ እየተዋጋላቸው እንዳለ አስተውለዋል፤ እንዲሁም ከነአናውያንን ከምድሪቱ ለማጥፋት ቃል እንደገባ ያውቃሉ። (ዘፀ. 34:11፤ ኢያሱ 9:24) በመሆኑም እስራኤላውያን ኢያሪኮንና ጋይን ከተቆጣጠሩ በኋላ ገባኦናውያን ከእስራኤላውያን ጋር ሰላም ለመፍጠር ሲሉ በጊልጋል ወደነበረው ወደ ኢያሱ መልእክተኞችንa ላኩ።

4. (ሀ) በኢያሱ 9:8-13 መሠረት ገባኦናውያን እስራኤላውያንን ያታለሏቸው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።) (ለ) ውሸታቸው ከተጋለጠ በኋላ ምን ተፈጠረ?

4 ኢያሱ 9:8-13ን አንብብ። ገባኦናውያን ከሩቅ አገር እንደመጡ በመናገር እስራኤላውያንን አታለሏቸው። ይሖዋ እስራኤላውያንን በግብፅ እንዲሁም የአሞራውያን ነገሥታት በሆኑት በሲሖንና በኦግ ላይ ድል እንዳቀዳጃቸው መስማታቸውን ተናገሩ። ሆኖም መልእክተኞቹ፣ እስራኤላውያን በቅርቡ በኢያሪኮና በጋይ ላይ የተቀዳጁትን ድል አልጠቀሱም። እንዲህ ቢያደርጉ ኖሮ “ከሩቅ አገር” አለመምጣታቸው ይታወቅባቸው ነበር፤ ምክንያቱም ይህ ዜና በዚያ አጭር ጊዜ ውስጥ ሩቅ አገር ድረስ ሊደርስ አይችልም። የእስራኤላውያን አለቆች ገባኦናውያን የተናገሩትን በማመን ይሖዋን ሳይጠይቁ ከእነሱ ጋር የሰላም ቃል ኪዳን አደረጉ። (ኢያሱ 9:14, 15) ብዙም ሳይቆይ የገባኦናውያን ውሸት ተጋለጠ። ሆኖም እስራኤላውያን “በይሖዋ ምለውላቸው ስለነበር” የሰላም ቃል ኪዳኑን አላፈረሱም። (ኢያሱ 9:16-19) ገባኦናውያን “ለማኅበረሰቡና ለይሖዋ መሠዊያ እንጨት ለቃሚዎችና ውኃ ቀጂዎች” በመሆን ባሪያዎች የሚያከናውኑትን ሥራ በቀጣይነት እንዲያከናውኑ ተወሰነባቸው።—ኢያሱ 9:27

የተወሰኑ ገባኦናውያን በኢያሱና በሌሎች እስራኤላውያን ወታደሮች ፊት ተንበርክከው ሲለምኗቸው። ገባኦናውያኑ ልብሳቸውና የወይን ጠጅ አቁማዳቸው እንዳረጀ እያሳዩአቸው ነው።

ገባኦናውያን ኢያሱን በማታለል ከእነሱ ጋር የሰላም ስምምነት እንዲመሠርት አደረጉ (አንቀጽ 4ን ተመልከት)


5. ገባኦናውያን በይሖዋ ላይ እምነት እንዳላቸው ያሳዩት እንዴት ነው?

5 አምስቱ የአሞራውያን ነገሥታት ገባኦናውያን ከእስራኤላውያን ጋር የሰላም ስምምነት እንዳደረጉ በሰሙ ጊዜ ገባኦንን ለመውጋት ተሰበሰቡ። በዚህ ጊዜ ገባኦናውያን ኢያሱን እንዲረዳቸው ለመኑት። (ኢያሱ 10:3-7) ኢያሱ ሠራዊቱን ይዞ ገባኦናውያንን ለመታደግ ተነሳ። ይሖዋም ጥረቱን አሳክቶለታል። ይሖዋ በአሞራውያኑ ላይ ትላልቅ የበረዶ ድንጋዮችን አወረደባቸው፤ በተጨማሪም ውጊያው እስኪያልቅ ድረስ ፀሐይ እንድትቆም አደረገ። (ኢያሱ 10:9-14) ገባኦናውያን ከእስራኤላውያን ጋር የሰላም ስምምነት በማድረግና አደጋ ሲደቀንባቸው የኢያሱን እርዳታ በመጠየቅ በይሖዋ ላይ እምነት እንዳላቸው አሳይተዋል። ይሖዋ ቃሉን እንደሚጠብቅና እንደሚታደጋቸው እርግጠኞች ነበሩ።

6. ይሖዋ ገባኦናውያንን ከያዘበት መንገድ ስለ እሱ ምን እንማራለን?

6 ይህ ዘገባ ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረናል? ይሖዋ ትሑትና መሐሪ ነው። ቀደም ሲል እስራኤላውያንን “የምድሪቱን ነዋሪዎች በሙሉ ከፊታችሁ አባሯቸው” በማለት አዟቸው ነበር፤ ይህ ደግሞ ገባኦናውያንንም ይጨምራል። (ዘኁ. 33:51, 52) ሆኖም እስራኤላውያን ከእነሱ ጋር የሰላም ስምምነት ስላደረጉ ይሖዋ ገባኦናውያን በምድሪቱ ላይ መኖራቸውን እንዲቀጥሉ በመፍቀድ ምሕረት አሳይቷቸዋል። እስራኤላውያን የሰላም ቃል ኪዳን የገቡት እሱን ሳይጠይቁ ቢሆንም ለገባኦናውያን ምሕረት ከማሳየት ወደኋላ አላለም። በተጨማሪም ገባኦናውያንን ተአምራዊ በሆነ መንገድ በመታደግ እስራኤላውያን የገቡትን ቃል እንዲጠብቁ ረድቷቸዋል።—ኢያሱ 9:26፤ 11:19

7. የገባኦናውያንን እምነትና ትሕትና መኮረጅ የምንችለው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

7 የገባኦናውያንን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? በይሖዋ ላይ ጠንካራ እምነት በማዳበር ነው። በዚያ ዘመን ከነበሩት ገባኦናውያን የበለጠ ስለ ይሖዋ ብዙ ነገር ስለምናውቅ በእሱ ሙሉ በሙሉ ለመታመን የሚያበቁ ተጨማሪ ምክንያቶች አሉን። (መዝ. 40:4, 5) በተጨማሪም ይሖዋን ለማገልገል ስንል ዝቅ ተደርገው የሚታዩ ሥራዎችን በትሕትና ለመሥራት ፈቃደኞች በመሆን የገባኦናውያንን ምሳሌ መከተል እንችላለን። (ኢያሱ 9:23, 27) ሉክ የተባለ ወጣት ወንድም በዕድሜ ተለቅ ያለ አንድ ቤቴላዊ ያሳየውን ትሕትና አይረሳውም። ይህ ቤቴላዊ ብዙ ኃላፊነት ቢኖረውም የስብሰባ አዳራሻቸው በሚገነባበት ወቅት አዳራሹን እየጠበቀ ለማደር ራሱን በፈቃደኝነት አቅርቦ ነበር። ሉክ እንዲህ ብሏል፦ “ትሕትና የስሜት ጉዳይ ብቻ እንዳልሆነ ተገነዘብኩ። ትሕትና፣ ለማድረግ ወይም ላለማድረግ በምንመርጠው ነገር በግልጽ ይታያል።” እኛም በዕለት ተዕለት ሕይወታችን አስቸጋሪ ሁኔታ ሲያጋጥመን በይሖዋ በመታመን እምነት እንዳለን ማሳየት እንችላለን። እንዲሁም የትኛውንም ቲኦክራሲያዊ ኃላፊነት ለመወጣት ፈቃደኛ በመሆን ትሑት መሆናችንን ማሳየት እንችላለን።

ሥዕሎች፦ ሰዎች ዝቅ ተደርገው የሚታዩ ሥራዎችን በፈቃደኝነት ሲያከናውኑ የሚያሳዩ ምሳሌዎች። 1. አንድ ገባኦናዊ የውኃ መቅጃ ተሸክሞ። 2. አንድ አረጋዊ ወንድም በስብሰባ አዳራሽ ግቢ ውስጥ አትክልት ሲንከባከብ።

ዝቅ ተደርገው የሚታዩ ሥራዎችን ለማከናወን ፈቃደኛ በመሆን ገባኦናውያንን ምሰሉ (አንቀጽ 7ን ተመልከት)


ኢፍትሐዊ ድርጊት ሲፈጸምባችሁ ይሖዋን በትዕግሥት ጠብቁ

8. ንጉሥ ሳኦል በገባኦናውያን ላይ ምን ግፍ ፈጸመ?

8 ገባኦናውያን በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ በድጋሚ የተጠቀሱት ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ ነው። ንጉሥ ሳኦል “ለእስራኤልና ለይሁዳ ሕዝብ ባለው ቅንዓት ተነሳስቶ” ገባኦናውያንን ከእስራኤል ምድር ለመደምሰስ ሞከረ።b በመሆኑም ብዙ ገባኦናውያን ተገደሉ። (2 ሳሙ. 21:2, 5, 6) ይህ እንዴት ያለ ግፍ ነው! ሳኦል በእስራኤላውያንና በገባኦናውያን መካከል የነበረውን ለረጅም ዘመናት የዘለቀ የሰላም ቃል ኪዳን አፈረሰ።

9. ይሖዋ በገባኦናውያን ላይ በተፈጸመው ነገር በጣም እንዳዘነ ያሳየው መቼ ነው?

9 ይሖዋ በገባኦናውያን ላይ ግፍ የፈጸሙትን ሰዎች ወዲያውኑ አልቀጣቸውም። ይሖዋ ይህ ጉዳይ እንዲታወቅ ያደረገው ንጉሥ ዳዊት ሳኦልን ተክቶ ከነገሠ በኋላ ነው። ይህን ያደረገው በምድሪቱ ላይ ለሦስት ዓመት የዘለቀ ረሃብ በማምጣት ነው። ዳዊት ረሃቡ ለምን እንደተከሰተ ሲጠይቅ ይሖዋ ሳኦል ከዓመታት በፊት ገባኦናውያንን ስለገደለ ሳኦልም ሆነ ቤቱ የደም ዕዳ እንዳለባቸው ነገረው።—2 ሳሙ. 21:1

10. በ2 ሳሙኤል 21:3-6 ላይ ገባኦናውያን የተናገሩት ነገር ለይሖዋ ሕግ አክብሮት እንዳላቸው የሚያሳየው እንዴት ነው?

10 ሁለተኛ ሳሙኤል 21:3-6ን አንብብ። ዳዊት ገባኦናውያንን በማነጋገር ሳኦል የፈጸመባቸውን ግፍ ማስተሰረይ የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ጠየቃቸው። ገባኦናውያን ዳዊትን ገንዘብ በማስከፈል ራሳቸውን ለማበልጸግ አልሞከሩም። ከዚህ ይልቅ “የተፈጠረው ችግር በብርና በወርቅ የሚፈታ አይደለም” በማለት መለሱ። ደግሞም እንዲህ ማለታቸው ተገቢ ነው፤ ምክንያቱም በሕጉ መሠረት ለነፍሰ ገዳይ ቤዛ መቀበል አይገባም። (ዘኁ. 35:30, 31) በተጨማሪም ማንንም ሰው የመግደል መብት እንደሌላቸው አምነው ተቀብለዋል። በመጨረሻም ዳዊት የሳኦል ዘር የሆኑ ሰባት ወንዶች እንዲገደሉ ፈቀደ፤ ምናልባትም እነዚህ ሰዎች በዘር ጭፍጨፋው ላይ እጃቸው ሊኖርበት ይችላል። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ዝናብ ዘነበ፤ ረሃቡም አቆመ። ይህም የይሖዋን መሥፈርት በሚያሟላ ደረጃ ፍትሕ መፈጸሙን የሚያሳይ ነው።—2 ሳሙ. 21:9, 10, 14

11. ይህ ዘገባ ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረናል?

11 ይህ ዘገባ ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረናል? ይሖዋ ፍትሐዊ አምላክ እንደሆነ ግልጽ ማስረጃ ይሰጠናል። (መዝ. 37:28) በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች ከእነሱ የተለየ ዜግነት ወይም ባሕል ባላቸው ሰዎች ላይ መድልዎ ይፈጽማሉ። ይሖዋ ግን ሁሉም ሰው ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንዲያዝ ይፈልጋል። በተጨማሪም ብዙ የአምላክ አገልጋዮች በደል ይፈጸምባቸዋል። ሆኖም ይሖዋ እሱ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ ፍትሕ በመስጠት ይክሳቸዋል። ከዚህም ሌላ፣ ይሖዋ እስራኤላውያን ከገባኦናውያን ጋር የገቡትን የሰላም ቃል ኪዳን እንዲያከብሩ ይጠብቅባቸው እንደነበረ ሁሉ እኛም ቃላችንን እንድናከብር እንደሚጠብቅብን እንማራለን።—ከአሞጽ 1:9 ጋር አወዳድር።

12. ፍትሕ የጎደለው ነገር ሲፈጸምብን የገባኦናውያንን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?

12 የገባኦናውያንን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ፍትሕ የጎደለው ነገር ሲፈጽሙብን ይሖዋን በትዕግሥት መጠበቅ ይኖርብናል። እንዲህ ስናደርግ ይሖዋ በትክክለኛው ጊዜ ችግሩን እንደሚያስተካክል እንደምንተማመን እናሳያለን። የእህት ሎራ ፍሬንችን ተሞክሮ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። እህት ፍሬንች በ1926 በካናዳ ቤቴል ማገልገል ጀመረች። ከአሥር ዓመት ገደማ በኋላ ከባድ የፍትሕ መጓደል አጋጠማት። ከከሃዲዎች ጋር እንደተባበረች ተቆጥራ ከቤቴል እንድትወጣ ተደረገ። ታዲያ ምን ታደርግ ይሆን? ስሜቷ በጣም ቢጎዳም በድርጅቱ ላይ አላጉረመረመችም። በቀጣዮቹ አራት ዓመታት በቅንዓት በአቅኚነት አገለገለች። የሚገርመው በ1940 በድጋሚ በቤቴል እንድታገለግል ተጋበዘች። ምድራዊ ሕይወቷን እስካጠናቀቀችበት ጊዜ ድረስ ለ50 ዓመታት በታማኝነት በቤቴል ማገልገሏን ቀጥላለች። እኛም ፍትሕ የጎደለው ነገር ሲፈጸምብን ትክክል የሆነውን ነገር ማድረጋችንን በመቀጠልና ይሖዋ በራሱ ጊዜ ችግሩን እስኪያስተካክለው በትዕግሥት በመጠበቅ የእህት ፍሬንችን ምሳሌ መከተል እንችላለን።—ኢሳ. 26:3, 4

እውነተኛውን አምልኮ በታማኝነት ደግፉ

13. ‘ናታኒሞች’ እነማን ነበሩ? ከባቢሎን ግዞት በኋላስ ምን አደረጉ?

13 ከንጉሥ ዳዊት ዘመን ከ500 ዓመታት ገደማ በኋላ ገባኦናውያን በመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ላይ እንደገና ብቅ አሉ። የ70 ዓመቱ የባቢሎን ግዞት ካበቃ በኋላ በ537 ዓ.ዓ. የተወሰኑ አይሁዳውያን ግዞተኞች ከገዢው ዘሩባቤል ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። (ዕዝራ 2:1, 2, 58) በ468 ዓ.ዓ. ደግሞ ሌላ ቡድን የአምላክ ሕግ ገልባጭ ከሆነው ከዕዝራ ጋር ተመለሰ። (ዕዝራ 7:1-7) በሁለቱም ጊዜያት ወደ ኢየሩሳሌም የተመለሱት ግዞተኞች ቁጥር በአንጻራዊ ትንሽ ነበር። ሆኖም በሁለቱም ቡድኖች ውስጥ ‘ናታኒሞች’ ነበሩ። (በዕዝራ 2:58 እና 7:7 ላይ የሚገኙትን የግርጌ ማስታወሻዎች ተመልከት።) ናታኒሞች እነማን ናቸው? “እስራኤላውያን ያልሆኑ የቤተ መቅደስ አገልጋዮች ነበሩ”፤ ከእነሱ መካከል ብዙዎቹ የገባኦናውያን ዘሮች ሳይሆኑ አይቀሩም።—“ናታኒም” የሚለውን የቃላት መፍቻ ተመልከት።

14. ገባኦናውያን ለይሖዋ ያላቸውን ታማኝነት ያሳዩት እንዴት ነው? (1 ዜና መዋዕል 9:2 እና የግርጌ ማስታወሻ)

14 አንደኛ ዜና መዋዕል 9:2ንና የግርጌ ማስታወሻውን አንብብ። “የቤተ መቅደሱ አገልጋዮች” ወደ እስራኤል ከተመለሱት የመጀመሪያዎቹ ግዞተኞች መካከል ነበሩ። ይህ በጣም ትኩረት የሚስብ ነው፤ ምክንያቱም ወደ እስራኤል ያልተመለሱ አይሁዳውያን ነበሩ። ብዙ አይሁዳውያን በባቢሎን ሀብት ንብረት አፍርተው ነበር። በመሆኑም መሥዋዕት ከፍለው ወደ እስራኤል ለመመለስና የፈራረሰችውን የትውልድ አገራቸውን መልሰው ለመገንባት ፈቃደኞች አልነበሩም። ሆኖም የገባኦናውያንን ዘሮች ጨምሮ ታማኝ ግዞተኞች እውነተኛው አምልኮ በኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ መልሶ ሲቋቋም ለማየት ይጓጉ ነበር። በመሆኑም ቀላል ባይሆንም ወደ እስራኤል ተመልሰዋል። ከአይሁዳውያን በተለየ የገባኦናውያን ዘሮች በእስራኤል ውስጥ ርስት አልነበራቸውም። ሆኖም በቤተ መቅደሱ ውስጥ የነበራቸውን ሥራ ለማከናወን እንዲሁም የኢየሩሳሌምን ቅጥሮች ለመጠገን ሲሉ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰዋል።—ነህ. 3:26

15. የገባኦናውያን ታሪክ ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረናል?

15 ይህ ዘገባ ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረናል? አምላካችን ታማኝ አገልጋዮቹን ከፍ አድርጎ እንደሚመለከታቸውና ምንጊዜም እንደሚንከባከባቸው እንማራለን። የባቢሎን ግዞት ባበቃበት ወቅት ይሖዋ ገባኦናውያን በተስፋይቱ ምድር እንዲኖሩ ከፈቀደላቸው 1,000 ዓመት ገደማ አልፎ ነበር። ሆኖም እነሱን መባረኩን ቀጥሏል። የገባኦናውያን ዘሮች ይሁዳና ኢየሩሳሌም በ607 ዓ.ዓ. ሲጠፉ በሕይወት ተርፈዋል። ከግዞት ከተመለሱ በኋላ ደግሞ ከሌዋውያን ጋር በቤተ መቅደሱ በማገልገል እውነተኛውን አምልኮ መደገፋቸውን ቀጥለዋል። ከሁኔታዎች መረዳት እንደሚቻለው፣ አንዳንዶቹ የሚኖሩት በቤተ መቅደሱ አቅራቢያ ነበር። (ዕዝራ 2:70፤ ነህ. 11:21) በተጨማሪም በቤተ መቅደሱ ውስጥ በሚያቀርቡት አገልግሎት የተነሳ ቀረጥ፣ ግብር ወይም የኬላ ቀረጥ ከመክፈል ነፃ ሆነው ነበር።—ዕዝራ 7:24

16. ከአምልኳችን ጋር በተያያዘ የገባኦናውያንን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?

16 የገባኦናውያንን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? እኛም እውነተኛውን አምልኮ ለመደገፍ አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ማድረግ እንፈልጋለን። ይሖዋን ስለምንወደውና እሱን ማስደሰት ስለምንፈልግ እሱን ለማገልገል ስንል በፈቃደኝነት መሥዋዕቶችን እንከፍላለን። በፊሊፒንስ የሚኖር አልዊን የተባለ ወንድም ይህን አድርጓል። አልዊን በአንድ የነዳጅ ኩባንያ ውስጥ ብዙ ገንዘብ የሚያስገኝ ሥራ ነበረው። ሆኖም ይሖዋን ይበልጥ ማገልገል ፈለገ። የወረዳ የበላይ ተመልካች ጉባኤያቸውን ሲጎበኝ አልዊን እረፍት ወስዶ ጉብኝቱን የመደገፍ ልማድ ነበረው። በዚህ ወቅት በአገልግሎት ተጨማሪ ተሳትፎ ማድረጉ ያስደስተው ነበር። በጉዳዩ ላይ በደንብ ከጸለየበት በኋላ ሥራውን አቁሞ በዘወትር አቅኚነት ለማገልገል የሚያስችል ሥራ ለመፈለግ ወሰነ። ይህ ውሳኔው ቁሳዊ ነገሮችን መሥዋዕት ማድረግ ጠይቆበታል። ሆኖም ግቡ ላይ ደረሰ። ሚስቱም ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የዘወትር አቅኚ ሆነች። አልዊንና ባለቤቱ 21 ሰዎች እውነትን እንዲማሩ መርዳት ችለዋል። ይሖዋ የከፈሉትን መሥዋዕት ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው ግልጽ ነው። ከእኛ ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ይሖዋ እሱን ለማገልገል ብለን የምንከፍለውን ማንኛውንም መሥዋዕት ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተውና ምንጊዜም የሚያስፈልገንን ነገር በሙሉ እንደሚያሟላልን መተማመን እንችላለን።—ማቴ. 6:33

17. ስለ ገባኦናውያን የሚናገሩትን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች በመመርመር ምን ትምህርት አግኝተናል?

17 ስለ ገባኦናውያን የሚናገሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ስለ ይሖዋ ማራኪ ባሕርያት ያስተምሩናል። እሱ ትሑት፣ መሐሪ፣ ፍትሐዊና ታማኝ አምላክ ነው። ታማኝ አገልጋዮቹን ምንጊዜም ይባርካቸዋል። ከእነዚህ ዘገባዎች ተግባራዊ ትምህርትም እናገኛለን። እንደ ገባኦናውያን በይሖዋ ላይ ጠንካራ እምነት እንዲኖረን እንፈልጋለን። አስፈሪ ሁኔታ ሲያጋጥመን በእሱ እንታመናለን። እንዲህ ያለው እምነት፣ የሚሰጠንን ማንኛውንም ቲኦክራሲያዊ ኃላፊነት በትሕትና እንድንወጣም ያነሳሳናል። የፍትሕ መጓደል ሲያጋጥመን ይሖዋ ችግሩን ሙሉ በሙሉ እንደሚያስተካክለው በመተማመን እሱን በትዕግሥት እንጠብቃለን። እንዲሁም እውነተኛውን አምልኮ በቅንዓትና በታማኝነት እንደግፋለን። እንዲህ በማድረግ የገባኦናውያንን ምሳሌ መከተል እንችላለን።

ከገባኦናውያን ምን ትምህርት እናገኛለን?

  • እምነትና ትሕትና ስለማሳየት

  • ኢፍትሐዊ ድርጊቶችን ስለመቋቋም

  • እውነተኛውን አምልኮ በታማኝነት ስለመደገፍ

መዝሙር 148 ይሖዋ ይታደጋል

a ከገባኦን የመጡት መልእክተኞች ሦስት ሌሎች የሂዋውያን ከተሞችንም ወክለው የነበረ ይመስላል፤ እነሱም ከፊራ፣ በኤሮት እና ቂርያትየአሪም ናቸው።—ኢያሱ 9:17

b መጽሐፍ ቅዱስ ሳኦል ይህን ግፍ የፈጸመው ለምን እንደሆነ በዝርዝር አይናገርም። አንዳንድ ምሁራን ሳኦል ይህን ያደረገው በብሔራዊ ስሜት ተነሳስቶ እንደሆነ ይናገራሉ።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2026)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2026 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ