የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w26 ግንቦት ገጽ 26-31
  • የሌሎችን ውሳኔ አክብሩ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የሌሎችን ውሳኔ አክብሩ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2026
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • በሌሎች ላይ ልንፈርድ የምንችለው በየትኞቹ ሁኔታዎች ውስጥ ነው?
  • የሌሎችን የግል ውሳኔ ማክበር ያለብን ለምንድን ነው?
  • የሌሎችን አመለካከት ማክበር የምንችለው እንዴት ነው?
  • ይሖዋን የሚያስደስቱ ውሳኔዎችን አድርግ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • በይሖዋ እንደምንታመን የሚያሳዩ ውሳኔዎች
    ክርስቲያናዊ ሕይወታችንና አገልግሎታችን​—የስብሰባው አስተዋጽኦ—2023
  • እምነት በማዳበር ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ አድርጉ!
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2017
  • አምላክን የሚያስከብር ውሳኔ አድርጉ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2011
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2026
w26 ግንቦት ገጽ 26-31

ከነሐሴ 3-9, 2026

መዝሙር 113 ከአምላክ ያገኘነው ሰላም

የሌሎችን ውሳኔ አክብሩ

“በአመለካከት ልዩነት ላይ ተመሥርታችሁ አትፍረዱ።”—ሮም 14:1

ዓላማ

የእምነት አጋሮቻችን እኛ የማንስማማበትን ውሳኔ ሲያደርጉ ውሳኔያቸውን ማክበር የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።

1-2. አንዳንድ ጊዜ የምናደርጋቸው ውሳኔዎች ከሌሎች ክርስቲያኖች የተለዩ የሆኑት ለምንድን ነው?

ባደረጋችሁት ውሳኔ ምክንያት ሌሎች ተችተዋችሁ ያውቃሉ? እናንተስ ሌሎችን ባደረጉት ውሳኔ ምክንያት ተችታችሁ ታውቃላችሁ? አብዛኞቻችን ሁለቱንም ጥያቄዎች “አዎ” ብለን እንደምንመልስ ጥርጥር የለውም።

2 አንዳንድ ጊዜ እኛ የምናደርገው ውሳኔ ሌሎች ክርስቲያኖች ከሚያደርጉት ውሳኔ የተለየ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ይህ የሚያስገርም አይደለም። ለምን? ምክንያቱም ሁላችንም የተለያየን ነን። በተጨማሪም ሁላችንም የየራሳችን አመለካከት አለን። ባሕላችን፣ አስተዳደጋችንና በሕይወታችን ውስጥ ያጋጠሙን ነገሮች አስተሳሰባችንን ይቀርጹታል። ያም ቢሆን የተለያየ አመለካከት ያለን መሆኑ የጉባኤውን ሰላምና አንድነት እንዲያደፈርስ ልንፈቅድ አይገባም።—ኤፌ. 4:3

3. ሌሎችን ባደረጉት ውሳኔ ምክንያት እንድንተች የሚያነሳሳን ምን ሊሆን ይችላል?

3 አንድ የእምነት አጋራችን እኛ የማንስማማበት ውሳኔ ሲያደርግ ሐሳቡን ማስቀየር እንዳለብን ሊሰማን ወይም የተሳሳተ ውሳኔ እንዳደረገ ለሌሎች ልንናገር እንችላለን። ይህን የምናደርገው በቅን ልቦና ተነሳስተን እንደሆነ ጥያቄ የለውም። ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን እንወዳቸዋለን፤ እንዲሳካላቸውም እንፈልጋለን። (ምሳሌ 17:17) ስለዚህ በኋላ የሚጸጸቱበትን ወይም መንፈሳዊነታቸውን ሊጎዳ የሚችል ውሳኔ እንዲያደርጉ አንፈልግም።

4-5. አንድ የእምነት አጋራችን እኛ የማንስማማበት ውሳኔ ቢያደርግ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

4 ወንድማችን ባደረገው ውሳኔ የማንስማማ ከሆነ ስሜታችንን ልንገልጽለት ይገባል? ይህ በሁኔታዎች ላይ የተመካ ነው። ለምሳሌ ወንድማችን ለማድረግ ያሰበው ነገር የመጽሐፍ ቅዱስን ትእዛዝ የሚጥስ ከሆነ ለእሱ ባለን ፍቅር ተነሳስተን አስተሳሰቡን እንዲያስተካክል ልንረዳው ይገባል። (ምሳሌ 27:5, 6) ይሁንና ወንድም ሊያደርግ ያሰበው ነገር የአምላክን ሕግ የሚጥስ ካልሆነስ? ውሳኔውን እኛ ስላልተስማማንበት ብቻ ተቃውሟችንን ልንገልጽ ይገባል? የጭብጡ ጥቅሳችን መልሱን ይሰጠናል። ‘በአመለካከት ልዩነት ላይ ተመሥርተን አንፈርድም።’—ሮም 14:1

5 ያም ቢሆን ውሳኔውን ማክበር ሊከብደን ይችላል። በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ የሌሎችን ውሳኔ ማክበር ያለብን ለምን እንደሆነና እንዲህ ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን። በመጀመሪያ ግን፣ በሌሎች ላይ ልንፈርድ የምንችለው በየትኞቹ ሁኔታዎች ውስጥ እንደሆነ የሚያሳዩ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት።

በሌሎች ላይ ልንፈርድ የምንችለው በየትኞቹ ሁኔታዎች ውስጥ ነው?

6-7. በሌሎች ላይ ልንፈርድ የምንችለው በየትኞቹ ሁኔታዎች ውስጥ ነው?

6 ቀደም ሲል እንደተመለከትነው፣ በአስተዳደጋችን ወይም በሕይወታችን ውስጥ ባጋጠሙን ነገሮች የተነሳ በአንዳንድ ጉዳዮች ረገድ ጠንካራ አቋም ሊኖረን ይችላል። ሌሎችም የእኛን አመለካከት እንደሚጋሩ እናስብ ይሆናል። ሆኖም እውነታው ከዚያ የተለየ ሊሆን ይችላል። አንዳንድ ምሳሌዎችን እስቲ እንመልከት። ምሳሌ 1፦ አንድ ወንድም ልጅ እያለ አባቱ የአልኮል ሱሰኛ ነበር። ወንድም እውነትን ከሰማ በኋላ አንዳንድ ክርስቲያኖች በአንድ ግብዣ ላይ መጠጥ ሲጠጡ ይመለከታል። በዚህ ጊዜ ተበሳጭቶ የአልኮል መጠጥ መጠጣታቸው ትክክል እንዳልሆነ ይነግራቸዋል። ምሳሌ 2፦ አንዲት እህት ከባድ ሕመም ይዟት የነበረ ቢሆንም ከሕመሟ መዳን ችላለች። ከጊዜ በኋላ አንዲት ሌላ እህት ያው ሕመም እንዳለባት ሰማች። በዚህ ጊዜ ልትረዳት ስለፈለገች የእሷን ዓይነት ሕክምና እንድትከታተል ገፋፋቻት፤ ምናልባት የሆነ ዓይነት የአመጋገብ ዘይቤ እንድትከተል፣ አንድ መድኃኒት እንድትወስድ ወይም የባሕል ሕክምና እንድትሞክር ትገፋፋት ይሆናል። ምሳሌ 3፦ አንድ ወንድም ቀደም ሲል የሐሰት ሃይማኖት አባል ነበር። የቀድሞውን አኗኗሩን በጣም ይጠላዋል። አንድ የእምነት አጋሩ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሚካሄድ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ እንደተገኘ ሲሰማ ቅር ተሰኘ።a

7 ሌሎች ምሳሌዎችንም እንመልከት። ምሳሌ 4፦ አንድ ወንድም ያደገው ወንዶች ጢማቸውን ማሳደጋቸው እንዲሁም ሴቶች ሥርዓታማ አለባበስ በሚጠይቁ ፕሮግራሞች ላይ ሲገኙ ሱሪ መልበሳቸው ተገቢ እንዳልሆነ በሚታመንበት ዘመን ነው። ወንድም ድርጅቱ በቅርቡ ያደረገውን ማስተካከያ ቢያውቅም ወንድሞች ጢማቸውን ማሳደግ እንደሌለባቸው፣ እህቶች ደግሞ በቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች ሲካፈሉ ቀሚስ መልበስ እንዳለባቸው አጥብቆ ይከራከራል። ምሳሌ 5፦ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ፣ ዩኒቨርሲቲ ከገባ በኋላ እውነትን የተወ ወንድም ያውቃል። አሁን ደግሞ በሽማግሌው ጉባኤ ውስጥ ያለ አንድ ወጣት ወንድም ከፍተኛ ትምህርት ለመከታተል ወስኗል። ሽማግሌው ጉዳዩ ስላሳሰበው ወጣቱን ወንድምና ወላጆቹን ሐሳባቸውን ለማስቀየር ይሞክራል።

8. (ሀ) አንድ ወላጅ በሌሎች ወላጆች ላይ እንዲፈርድ የሚያነሳሳው ምን ሊሆን ይችላል? (ለ) በሌሎች ላይ መፍረዳችን በጉባኤው ላይ ምን ውጤት ሊያስከትል ይችላል?

8 አሁን ደግሞ ወላጆችን የሚመለከት ሌላ ሁኔታ እናንሳ። ምሳሌ 6፦ ወላጆች እንደመሆናችሁ መጠን ልጆቻችሁን “በይሖዋ ተግሣጽና ምክር” ለማሳደግ አቅማችሁ የፈቀደውን ሁሉ ታደርጋላችሁ። (ኤፌ. 6:4) በዚህም ምክንያት ለልጆቻችሁ አንዳንድ ሕጎችንና ገደቦችን ታወጣላችሁ። ሆኖም ሌሎች ወላጆች ልል እንደሆኑ ይሰማችሁ ይሆናል። ለምሳሌ ልጆቻቸው አምሽተው እንዲገቡ፣ ዓመፅ የሚንጸባረቅበት እስካልሆነ ድረስ ቪዲዮ ጌሞችን እንዲጫወቱ ወይም በልጅነታቸው ስልክ እንዲይዙ ይፈቅዱላቸው ይሆናል። በዚህም ምክንያት ልጆቻችሁ እናንተ ከልክ በላይ ጥብቅ እንደሆናችሁ ይሰማቸዋል። “የእገሌ ወላጆች እኮ ይህን እንዲያደርግ ይፈቅዱለታል” ይሏችሁ ይሆናል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥማችሁ እነዚያን ወላጆች ለመተቸት ልትፈተኑ ትችላላችሁ። እስካሁን የተመለከትነው ጥቂት ምሳሌዎችን ብቻ ነው። አንድ ክርስቲያን በሌሎች ጉዳዮችም እኛ የማንስማማበትን ውሳኔ ሲያደርግ በመካከላችን አለመግባባት ሊፈጠር ይችላል። ለምሳሌ በገንዘብ አጠቃቀሙ ወይም በመዝናኛ ምርጫው የተነሳ እንፈርድበት ይሆናል። ሆኖም በግል አመለካከታችን ላይ ተመሥርተን በሌሎች ላይ ከፈረድን የጉባኤውን አንድነት ልናናጋ እንችላለን። ይህ እንዲሆን ደግሞ እንደማንፈልግ የታወቀ ነው።

9. ሁላችንም ግባችን ምንድን ነው? ምን ከማድረግስ መቆጠብ ይኖርብናል? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

9 አንድ ክርስቲያን ያደረገው ውሳኔ ከሌላ ክርስቲያን የተለየ ነው ማለት አንደኛው ውሳኔ ትክክል፣ ሌላኛው ደግሞ ስህተት ነው ማለት አይደለም። (ሮም 14:5) እርግጥ ክርስቲያኖች ከይሖዋ መሥፈርቶች ጋር በተያያዘ ‘በሐሳብ መስማማት’ እንዳለባቸው ተነግሯቸዋል፤ ይህ ሲባል ግን በሁሉም የግል ጉዳዮቻችን ረገድ አንድ ዓይነት ሐሳብ ሊኖረን ይገባል ማለት አይደለም። (2 ቆሮ. 13:11) ሁኔታውን በምሳሌ ለማስረዳት፣ ወደ አንድ ቦታ ለመጓዝ እያሰብን ነው እንበል። ወደዚያ ቦታ ለመድረስ የሚያስችሉ የተለያዩ መንገዶች አሉ። መንገዶቹ የተለያዩ ቢሆኑም የሚያደርሱት ወደዚያው ቦታ ነው። ስለዚህ አቅማችንንና ሁኔታችንን ያገናዘበ ምርጫ እናደርጋለን። በተመሳሳይም ክርስቲያኖች በግል ጉዳዮቻቸው ረገድ የተለያየ ምርጫ ያደርጋሉ። ሆኖም መዳረሻችን አንድ ዓይነት ነው፤ ግባችን ይሖዋን ማስደሰት ነው። በመሆኑም ሌሎች በሚያደርጉት የግል ውሳኔ ላይ ተመሥርተን አንፈርድባቸውም።—ማቴ. 7:1፤ 1 ተሰ. 4:11

ወደ አንድ ቦታ የሚያደርሱ የተለያዩ መንገዶችንና የመጓጓዣ ዘዴዎችን የሚያሳይ በስልክ ላይ የተከፈተ ካርታ።

ወደ አንድ ቦታ ለመድረስ ካሉት መንገዶች የፈለግነውን መምረጥ እንችላለን፤ በተመሳሳይም ክርስቲያኖች በአንድ ጉዳይ ላይ የተለያየ ውሳኔ ሊያደርጉ ይችላሉ (አንቀጽ 9ን ተመልከት)


የሌሎችን የግል ውሳኔ ማክበር ያለብን ለምንድን ነው?

10. በያዕቆብ 4:12 መሠረት ምን የማድረግ መብት የለንም? ለምንስ?

10 መጽሐፍ ቅዱስ የሌሎችን የግል ውሳኔ እንድናከብር የሚያነሳሱ በርካታ ምክንያቶችን ይዟል። አንዳንዶቹን እስቲ እንመልከት። በሌሎች የግል ጉዳይ ውስጥ ገብተን በእነሱ ላይ የመፍረድ መብት የለንም። (ያዕቆብ 4:12ን አንብብ።) ሕግ የመስጠትም ሆነ የመፍረድ ብቃት ያለው ይሖዋ ነው። የምንመራባቸውን መሥፈርቶችና ሕጎች የማውጣት መብት ያለውም እሱ ብቻ ነው። ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ስላደረጉት ውሳኔ መልስ የሚሰጡት ለእኛ ሳይሆን ለይሖዋ ነው። (ሮም 14:10) ስለዚህ በራሳችን መሥፈርትና አመለካከት ላይ ተመሥርተን የሌሎችን ውሳኔ የመንቀፍ ወይም በእነሱ ላይ የመፍረድ መብት የለንም።b

11. ለጉባኤው አንድነት አስተዋጽኦ ማበርከት የምንችለው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

11 ይሖዋ አገልጋዮቹ አንድነት እንዲኖራቸው እንጂ አንድ ዓይነት እንዲሆኑ አይጠብቅም። እንዲያውም አምላካችን ልዩነት ይወዳል! ይህንንም በፈጠራቸው ነገሮች ላይ ማየት እንችላለን። ለምሳሌ እያንዳንዱ ደመና ቅርጹ የተለያየ ነው። ስለ ሰዎችስ ምን ማለት ይቻላል? በምድር ላይ ካሉት ከስምንት ቢሊዮን የሚበልጡ ሰዎች መካከል በመልክም ሆነ በባሕርይ ፍጹም ተመሳሳይ የሆኑ ሰዎች የሉም። ይሖዋ የፈጠረን የተለያየን እንድንሆን አድርጎ ነው። አንዳችን የሌላው ፎቶ ኮፒ እንድንሆን አይፈልግም። አንድነት እንዲኖረን ግን ይፈልጋል። ስለዚህ ልዩነታችን እንዲከፋፍለን ከመፍቀድ ይልቅ ሰላም ለማስፈን ጥረት እናደርጋለን። ከራሳችን አመለካከትና ምርጫ ይልቅ ለጉባኤው አንድነት ትልቅ ቦታ እንሰጣለን።—ሮም 14:19

የተለያየ ዘርና ዕድሜ ያላቸው ወንድሞችና እህቶች አብረው በደስታ ሲመገቡ። አንዳንዶቹ የአልኮል መጠጥ እየጠጡ ነው፤ ሌሎቹ ግን አይጠጡም። አንዳንዶቹ ወንድሞች ጢማቸውን አሳድገዋል፤ ሌሎቹ ግን አላሳደጉም።

ይሖዋ የፈጠረን የተለያየን እንድንሆን አድርጎ ነው፤ ሆኖም አንድነት እንዲኖረን ይፈልጋል (አንቀጽ 11ን ተመልከት)


የሌሎችን አመለካከት ማክበር የምንችለው እንዴት ነው?

12-13. አንድ ሰው “የተሳሳተ ጎዳና” እንደተከተለ ከተሰማን ምን ማድረግ ይኖርብናል? (ገላትያ 6:1፤ “በሌሎች ውሳኔ ካልተስማማን” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)

12 ሌሎች በግል ጉዳዮቻቸው ረገድ ውሳኔ ሲያደርጉ። እንዲህ እያላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ፦ ‘በእርግጥ ግለሰቡ “የተሳሳተ ጎዳና” ተከትሏል? ወይስ ውሳኔውን ያልወደድኩት እኔ በእሱ ቦታ ብሆን ኖሮ ከማደርገው ውሳኔ የተለየ ስለሆነ ብቻ ነው?’ ግለሰቡ የተሳሳተ ጎዳና ተከትሎ ማለትም የመጽሐፍ ቅዱስን ትእዛዝ ጥሶ ከሆነ ደግሞ ራሳችሁን እንዲህ እያላችሁ ጠይቁ፦ ‘ስለዚህ ጉዳይ ምክር መስጠት ያለብኝ እኔ ነኝ? ወይስ ሌላ የተሻለ ሰው አለ?’ እሱን ለመርዳት ብቃቱ ካላችሁ በገርነት መንፈስ አነጋግሩት። (ገላትያ 6:1ን አንብብ።) ይሁንና ብዙውን ጊዜ በሌሎች ውሳኔ የማንስማማው ከእኛ አመለካከት የተለየ ስለሆነ ብቻ ነው። ሁኔታው እንደዚያ ከሆነ፣ በግለሰቡ ውሳኔ ላይ ጥያቄ አታንሱ፤ ወይም ስለ ውሳኔው አሉታዊ ነገር አትናገሩ። የራሱን ውሳኔ የማድረግ መብቱን አክብሩለት፤ እንዲሁም በእሱ ላይ ከመፍረድ ተቆጠቡ።—ሮም 14:2-4

13 አንድ ምሳሌ እንመልከት። ከአንድ ጓደኛችሁ ጋር ምግብ ቤት ብትሄዱ ጓደኛችሁ እናንተ ያዘዛችሁትን ምግብ እንዲያዝ ታስገድዱታላችሁ? እንዲህ እንደማታደርጉ የታወቀ ነው። የፈለገውን ምግብ የመብላት መብት እንዳለው አምናችሁ ትቀበላላችሁ። ደግሞም እሱ የትኛውንም ምግብ ለመብላት ቢመርጥ በእናንተ ላይ ምንም የሚያመጣው ለውጥ የለም። እናንተም ብትሆኑ ጓደኛችሁ እሱ የሚወደውን ምግብ ከሚያዝላችሁ የራሳችሁን ምርጫ ብታደርጉ ደስ እንደሚላችሁ የታወቀ ነው። በተመሳሳይም፣ ሌሎች የራሳቸውን ውሳኔ እንዲያደርጉ በመፍቀድና አመለካከታችንን በእነሱ ላይ ባለመጫን እንደምናከብራቸው ማሳየት እንችላለን።

በሌሎች ውሳኔ ካልተስማማን

አንድ ክርስቲያን ባደረገው ውሳኔ ካልተስማማችሁ ከታች የተዘረዘሩትን ጥያቄዎች ራሳችሁን ጠይቁ። ይህን ማድረጋችሁ ከአላስፈላጊ ጭንቀት ሊጠብቃችሁ ይችላል።—ገላ. 6:5

  • ውሳኔው ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ጋር ይጋጫል?

  • ውሳኔያችን የተለያየ የሆነው አስተዳደጋችን የተለያየ ስለሆነ ነው?

  • ያደረገው ውሳኔ በእርግጥ ይጎዳዋል? ወይስ ሁኔታውን አጋንኜ እየተመለከትኩት ነው?

  • ያደረገው ውሳኔ የትኞቹን ጥቅሞች ሊያስገኝ ይችላል?

  • በእርግጥ “የተሳሳተ ጎዳና” ተከትሏል? ወይስ ውሳኔውን ያልወደድኩት እኔ በእሱ ቦታ ብሆን ኖሮ ከማደርገው ውሳኔ የተለየ ስለሆነ ብቻ ነው?

  • የተሳሳተ አካሄድ ተከትሎ ከሆነ ደግሞ ለእሱ ምክር ለመስጠት ብቃቱ አለኝ?

14. ውሳኔ በምናደርግበት ወቅት አንድነትን ማስፈን የምንችለው እንዴት ነው? (1 ቆሮንቶስ 8:12, 13)

14 በግል ጉዳዮቻችሁ ረገድ ውሳኔ ስታደርጉ። ሌሎችን ቅር የሚያሰኝ ነገር ላለማድረግ በመጠንቀቅ አንድነትን ማስፈን ትችላላችሁ። (1 ቆሮንቶስ 8:12, 13ን አንብብ።) ልታደርጉ ያሰባችሁት ነገር ‘የተፈቀደ’ ወይም ተቀባይነት ያለው ሊሆን ይችላል። ይሁንና ወንድማችሁን ቅር የሚያሰኘው ከሆነ ያንን ውሳኔ ማድረጋችሁ በእርግጥ “ይጠቅማል”?c (1 ቆሮ. 10:23, 24) እንዲህ ባሉ ሁኔታዎች ውስጥ መብታችንን ለማስከበር ከመሟገት ይልቅ ምርጫችንን ወደ ጎን ገሸሽ ብናደርግ ጥሩ ሊሆን ይችላል። (ሮም 15:1) ይሁንና ሌሎች በግል ጉዳዮቻችን ረገድ የምናደርጋቸውን ውሳኔዎች ማክበር እንዳለባቸው ተመልክተን አልነበረም እንዴ? እውነት ነው። እኛ የሌሎችን ምርጫ እንደምናከብር ሁሉ እነሱም የእኛን ምርጫ ማክበር ይኖርባቸዋል። ሆኖም በሮም 12:18 ላይ የሚገኘውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ማስታወስ ይኖርብናል። ጥቅሱ “ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር በእናንተ በኩል የተቻላችሁን ሁሉ አድርጉ” ይላል። ስለዚህ ከሌሎች ጋር በሰላም ለመኖርና ሳያስፈልግ እነሱን ቅር ላለማሰኘት በእኛ በኩል የቻልነውን እናደርጋለን።

15. ሽማግሌዎች ለጉባኤው አንድነት አስተዋጽኦ ማበርከት የሚችሉት እንዴት ነው? (1 ቆሮንቶስ 4:6)

15 ሽማግሌዎች የሌሎችን ውሳኔ ያከብራሉ። ሽማግሌዎች በግል ጉዳዮች ረገድ የራሳቸውን ሕግ ባለማውጣትና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ‘ከተጻፈው ባለማለፍ’ ለጉባኤው አንድነት አስተዋጽኦ ያበረክታሉ። (1 ቆሮንቶስ 4:6ን አንብብ።) በተጨማሪም በጽሑፎቻችን ላይ ተጽፎ ከሚገኘው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ምክር አልፈው አይሄዱም። ከዚህም ሌላ፣ አንድ ክርስቲያን ምክር ሲጠይቃቸው በራሳቸው ተሞክሮ ላይ ብቻ ተመሥርተው ምክር ከመስጠት ይልቅ በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ ምክር ለመስጠት ጥረት ያደርጋሉ።—ኢሳ. 48:17, 18

16. አንድ ሽማግሌ የሽማግሌዎች አካል ያደረገውን ውሳኔ ማክበር የሚችለው እንዴት ነው?

16 አንድ ሽማግሌ የሽማግሌዎች አካል በጋራ ያደረገውን ውሳኔም ያከብራል። የሽማግሌዎች አካል መንፈስ ቅዱስን ለማግኘት ጸልዮ እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስን መርምሮ አንድ ውሳኔ ላይ ከደረሰ በኋላ እያንዳንዱ ሽማግሌ ውሳኔው ከእሱ አመለካከት ጋር የሚስማማ ባይሆንም እንኳ ውሳኔውን መደገፍ ይኖርበታል። (ኤፌ. 5:17) በተጨማሪም ሽማግሌዎች ቲኦክራሲያዊ መመሪያዎችን ያለቦታቸው በመጥቀስ የራሳቸውን አመለካከት እንዲደግፉላቸው ለማድረግ አይሞክሩም። ለምሳሌ አንድ ሽማግሌ በጽሑፎቻችን ውስጥ የሚገኝን አንድ ዓረፍተ ነገር ከአውዱ ውጭ በመጥቀስ የራሱን አመለካከት ለማራመድ አይሞክርም።

17. የሌሎችን ውሳኔ ማክበራችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል?

17 እስካሁን እንደተመለከትነው፣ ሁላችንም የተለያየን ነን። ሁላችንም የየራሳችን አመለካከትና ምርጫ አለን። እንዲህ ያለው ልዩነት መኖሩ ጥሩ ነገር ነው። ጉባኤው አስደሳች እንዲሆን ያደረገው የተለያየ አስተዳደግና ባሕርይ ያላቸውን ሰዎች ያቀፈ መሆኑ ነው። ስለዚህ ልዩነቶቻችን እንዲከፈፍሉን ከመፍቀድ ይልቅ ሰላም እናሰፍናለን። ሌሎችን ቅር የሚያሰኝ ነገር ላለማድረግ እንጠነቀቃለን። ሌሎች በግል ጉዳዮቻቸው ረገድ የሚያደርጉትን ውሳኔ እናከብራለን። እንዲህ ስናደርግ ግሩም ውጤት እናገኛለን። ጉባኤያችን ደስታና አንድነት የሰፈነበት ይሆናል።—መዝ. 133:1፤ ማቴ. 5:9

የሚከተሉት ጥቅሶች የሌሎችን አመለካከትና ውሳኔ እንድናከብር የሚረዱን እንዴት ነው?

  • ያዕቆብ 4:12

  • ገላትያ 6:1

  • 1 ቆሮንቶስ 4:6፤ 8:12, 13

መዝሙር 89 ስማ፣ ታዘዝ፤ ትባረካለህ

a አንድ ክርስቲያን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሚካሄድ የሠርግ ወይም የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ለመገኘት ከመወሰኑ በፊት የተለያዩ ነገሮችን ከግምት ማስገባት አለበት። በግንቦት 15, 2002 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “የአንባብያን ጥያቄዎች” ተመልከት።

b አልፎ አልፎ ሽማግሌዎች ከባድ ኃጢአት በፈጸሙ ክርስቲያኖች ላይ የፍርድ ውሳኔ ማስተላለፍ ሊኖርባቸው ይችላል። ሆኖም በዚህ ጊዜ ሽማግሌዎች ለይሖዋ እንደሚፈርዱ ማስታወስ ይኖርባቸዋል፤ የፍርድ ውሳኔ የሚያደርጉት በራሳቸው መሥፈርቶች ላይ ሳይሆን በይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች ላይ ተመሥርተው ነው።—ከ2 ዜና መዋዕል 19:6 ጋር አወዳድር።

c አንዳንድ ምሳሌዎችን ለማየት ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 35 ነጥብ 5ን ተመልከት።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2026)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2026 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ