የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w26 ግንቦት ገጽ 20-25
  • ተጨማሪ ትምህርት ስትከታተሉ መንፈሳዊነታችሁን ጠብቁ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ተጨማሪ ትምህርት ስትከታተሉ መንፈሳዊነታችሁን ጠብቁ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2026
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ጥሩ መንፈሳዊ ልማድ ይዛችሁ ቀጥሉ
  • ‘የማመዛዘን ችሎታችሁን ጠብቁ’
  • ጊዜያችሁን በአግባቡ ተጠቀሙበት
  • ‘ከጥበበኞች ጋር መሄዳችሁን’ ቀጥሉ
  • ከወዲሁ ተዘጋጁ
  • ከትምህርት ጋር በተያያዘ ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ አድርጉ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2026
  • የሚከተሉትን ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ልብ ብላችሁ አዳምጡ
    የ2025-2026 የወረዳ ስብሰባ ፕሮግራም—የወረዳ የበላይ ተመልካች የሚገኝበት
  • የማታውቋቸው ነገሮች እንዳሉ አምናችሁ በመቀበል ልካችሁን እንደምታውቁ አሳዩ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • ከተጠመቅክ በኋላ ኢየሱስን ‘ያለማቋረጥ ተከተል’
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2024
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2026
w26 ግንቦት ገጽ 20-25

ከሐምሌ 27–ነሐሴ 2, 2026

መዝሙር 56 እውነትን የራስህ አድርግ

ተጨማሪ ትምህርት ስትከታተሉ መንፈሳዊነታችሁን ጠብቁ

“ምንም ያህል እድገት ያደረግን ብንሆን በዚሁ መንገድ በአግባቡ ወደፊት መጓዛችንን እንቀጥል።”—ፊልጵ. 3:16

ዓላማ

ተጨማሪ ትምህርት ለመከታተል ከወሰናችሁ በመንፈሳዊ ጠንካራ ሆናችሁ ለመቀጠል የሚረዷችሁን አራት የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች እንመለከታለን።

1-2. (ሀ) ተጨማሪ ትምህርት ለመከታተል ከወሰናችሁ ምን ማድረጋችሁን መቀጠል ይጠበቅባችኋል? (ለ) “በዚሁ መንገድ በአግባቡ ወደፊት መጓዛችንን እንቀጥል” ሲባል ምን ማለት ነው? (ፊልጵስዩስ 3:16)

አንዳንድ የይሖዋ አገልጋዮች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ተጨማሪ ትምህርት ለመከታተል ወስነዋል። ይህን ውሳኔ ያደረጉት፣ እንዲህ ዓይነቱ ትምህርት በይሖዋ አገልግሎት ሲካፈሉ ራሳቸውን ለማስተዳደር የሚያስችላቸውን ሥራ ለማግኘት እንደሚረዳቸው ተሰምቷቸው ሊሆን ይችላል። እናንተም ተጨማሪ ትምህርት ለመከታተል ወስናችሁ ከሆነ ከይሖዋ ጋር ያላችሁን ወዳጅነት ጠብቃችሁ ለመኖር ምን ይረዳችኋል? (ያዕ 4:8ሀ) እስካሁንም በትምህርት ቤት ቆይታችሁ የእምነት ፈተናዎች አጋጥመዋችሁ ሊሆን እንደሚችል ጥያቄ የለውም። ስለዚህ ‘በዚሁ መንገድ በአግባቡ ወደፊት መጓዛችሁን መቀጠል’ ማለትም እስካሁን እያደረጋችሁት እንዳለው በታማኝነት ይሖዋን ማገልገላችሁን መቀጠል ይኖርባችኋል።—ፊልጵስዩስ 3:16ን አንብብ።

2 ‘በዚሁ መንገድ በአግባቡ ወደፊት መጓዝ’ በሚለው ሐረግ ውስጥ የሚገኘው የግሪክኛ ግስ ከውትድርና ጋር የተያያዘ ትርጉም ነበረው፤ ወታደሮች በሰልፍ የሚገሰግሱበትን መንገድ ያመለክታል። ተጨማሪ ትምህርት ለመከታተል ከወሰናችሁ በይሖዋ አገልግሎት ወደፊት መገስገስ እንጂ ባላችሁበት መቆም ወይም ወደ ኋላ ማፈግፈግ አይኖርባችሁም። ይህ ርዕስ በዚህ ረገድ ሊረዷችሁ የሚችሉ አራት የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ያብራራል። እነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች የምታውቋቸው ናቸው። ከዚህ በፊትም ተግባራዊ ታደርጓቸው ነበር። አሁን ደግሞ ተጨማሪ ትምህርት በምትከታተሉበት ጊዜ እንዲሁም ትምህርቱን ከጨረሳችሁ በኋላ እነዚህኑ መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ማድረግ ይኖርባችኋል።

ጥሩ መንፈሳዊ ልማድ ይዛችሁ ቀጥሉ

3. ተጨማሪ ትምህርት ስትከታተሉ ምን ተፈታታኝ ሁኔታ ሊያጋጥማችሁ ይችላል?

3 ተፈታታኙ ነገር። ተጨማሪ ትምህርት ስትከታተሉ ጊዜያችሁን የሚይዙ አዳዲስ ነገሮች ይኖራሉ። በትምህርታችሁ ጥሩ ውጤት ለማምጣት ካላችሁ ፍላጎት የተነሳ ለይሖዋ አገልግሎት ሁለተኛ ቦታ መስጠት ልትጀምሩ ትችላላችሁ። ይባስ ብሎም ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችን፣ አገልግሎትን፣ የግል ጥናትንና ጸሎትን ችላ ማለት ትጀምሩ ይሆናል።—ራእይ 2:4

4. “የጌታ ሥራ የበዛላችሁ” መሆናችሁ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (1 ቆሮንቶስ 15:58)

4 አንደኛ ቆሮንቶስ 15:58ን አንብብ። አንድ ሰው በብስክሌት ወደፊት መጓዝ ከፈለገ ያለማቋረጥ ፔዳሉን መምታት አለበት። እናንተም መንፈሳዊነታችሁን ጠብቃችሁ ወደ ፊት መጓዝ ከፈለጋችሁ “የጌታ ሥራ የበዛላችሁ” ልትሆኑ ይገባል። ዋናው ነገር በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች የምታሳልፉት ጊዜ ርዝመት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ቅድሚያ የምትሰጡት ለየትኛው ነገር ነው የሚለው ነው። ከተማሪነታችሁ ይበልጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የይሖዋ አገልጋዮች መሆናችሁ እንደሆነ አስታውሱ። (ማቴ. 22:37) ሳማንታ የተባለች ወጣት እህት እንዲህ ብላለች፦ “ትምህርቴ ለይሖዋ ከማቀርበው አገልግሎት ጋር ከተጋጨብኝ ወዲያውኑ እንደማቋርጥ ለራሴ ቃል ገብቼ ነበር።”

5. በመንፈሳዊ ንቁ ሆናችሁ ለመቀጠል ከአሁኑ ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

5 ተጨማሪ ትምህርቱን ከመጀመራችሁ በፊት ምን ማድረግ ትችላላችሁ? ቅድሚያ የምትሰጡት ለየትኛው ነገር እንደሆነ ከወዲሁ ወስኑ። ራሳችሁን እንዲህ እያላችሁ ጠይቁ፦ ‘በቋሚነት በስብሰባና በአገልግሎት ለመካፈል እንዲሁም የግል ጥናት ለማድረግ ምን ዕቅድ አውጥቻለሁ?’ (ኢያሱ 1:8፤ ማቴ. 28:19, 20፤ ዕብ. 10:25) በተጨማሪም እስካሁን ስለነበራችሁ የትምህርት ቤት ቆይታ መለስ ብላችሁ አስቡ። ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ መስጠት የቻላችሁት እንዴት ነበር? በዚህ ረገድ ድክመት እንደነበረባችሁ ካስተዋላችሁ ደግሞ ከዚህ በኋላ ምን ማስተካከያ ማድረግ ትችላላችሁ? ተጨማሪ ትምህርት ስትከታተሉ በይሖዋ አገልግሎት ንቁ ተሳትፎ ለማድረግ ቁርጥ ውሳኔ አድርጉ። ለትምህርታችሁ በቂ ትኩረት መስጠት እንዳለባችሁ ግልጽ ነው፤ ሆኖም ከአምልኳችሁ ጋር ሊጋጭ አይገባም።a—ማቴ. 6:24

6. የትኞቹን ጥያቄዎች በመጠቀም ራሳችሁን መገምገም ትችላላችሁ? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

6 ተጨማሪ ትምህርት በምትከታተሉበት ወቅት በየጊዜው፣ ምናልባትም በየወሩ ራሳችሁን ገምግሙ። እንዲህ ብላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ፦ ‘አሁንም ለትክክለኛው ነገር ቅድሚያ እየሰጠሁ ነው?’ የማስጠንቀቂያ ምልክቶችን በንቃት ተከታተሉ። ለምሳሌ ራሳችሁን እንዲህ ብላችሁ መጠየቅ ትችላላችሁ፦ ‘ስብሰባ የመቅረት ወይም አርፍዶ የመድረስ አዝማሚያ እየታየብኝ ነው? ስብሰባ እየተካሄደ ስለ ትምህርት ወይም ስለ ቤት ሥራዎቼ አስባለሁ? በአካል በስብሰባዎች ላይ ከመገኘት ይልቅ በቪዲዮ ኮንፈረንስ መከታተል አብዝቻለሁ? የጸሎት ወይም መጽሐፍ ቅዱስን የማንበብ ልማዴ ተቀዛቅዟል? አገልግሎት የምወጣው ግዴታ ስለሆነብኝ ብቻ ነው? አገልግሎት በወጣሁ ቁጥር ጨርሼ የምመለስበት ጊዜ ይናፍቀኛል?’ እንዲህ ዓይነት ምልክቶችን ካስተዋላችሁ አፋጣኝ እርምጃ ውሰዱ። ትምህርታችሁ ለይሖዋ አገልግሎት ቅድሚያ ከመስጠት እንቅፋት እንዲሆንባችሁ አትፍቀዱ።

አንድ ወንድም ጥቅስ እያወጣ “መጠበቂያ ግንብ” በጥልቀት ሲያጠና።

ትምህርታችሁ ለይሖዋ አገልግሎት ቅድሚያ ከመስጠት እንቅፋት እንዲሆንባችሁ አትፍቀዱ (አንቀጽ 6ን ተመልከት)


‘የማመዛዘን ችሎታችሁን ጠብቁ’

7. ተጨማሪ ትምህርት ስትከታተሉ ከአስተሳሰባችሁ ጋር በተያያዘ ምን ፈታኝ ሁኔታ ሊያጋጥማችሁ ይችላል?

7 ተፈታታኙ ነገር። አንዳንድ ኮርሶች እንደ አምላክ የለሽነትና ዝግመተ ለውጥ ላሉ ‘ፍልስፍናዎችና ከንቱ ማታለያዎች’ ሊያጋልጧችሁ ይችላሉ። (ቆላ. 2:8) በራስ የመመካት ዝንባሌንም ያበረታታሉ። አንድ ወጣት ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “የትምህርቱ ዓላማ ክህሎት ማስተማር ብቻ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ የምናስብበትን መንገድ መቅረጽ ነው። የምንማረው የአስተሳሰብ ዘይቤ ደግሞ በአብዛኛው ከይሖዋ አስተሳሰብ ጋር የሚቃረን ነው። ለምሳሌ በሕይወታችን ስኬታማ መሆናችን የተመካው በራሳችን ላይ ብቻ እንደሆነ እንማር ነበር። ይህ ደግሞ ይሖዋ በሕይወታችን ውስጥ ያለውን ሚና ከግምት የሚያስገባ አይደለም። በመሆኑም በይሖዋ መታመን ከባድ እየሆነብኝ መጣ።”

8. ‘የማመዛዘን ችሎታችንን መጠበቅ’ ያለብን ለምንድን ነው? (ምሳሌ 5:1, 2)

8 ምሳሌ 5:1, 2ን አንብብ። መጽሐፍ ቅዱስ ‘የማመዛዘን ችሎታችንን እንድንጠብቅ’ ያስጠነቅቀናል። አንድ ነገር ጥበቃ ያስፈልገዋል ከተባለ ለጥቃት ተጋላጭ ነው ማለት ነው። ደግሞም የማመዛዘን ችሎታችን ለጥቃት የተጋለጠ ነው። (1 ጴጥ. 5:8) የዓለም መንፈስ ከሥነ ምግባር፣ ከሕይወት አመጣጥ፣ አልፎ ተርፎም ከአምላክ መኖር ጋር በተያያዘ ያላችሁን እምነት ሊያዳክምባችሁ ይችላል። ሰዎች የዓለምን አስተሳሰብ ሲያስተጋቡ የሠለጠነ አስተሳሰብ እንዳላቸው ሊሰማቸው ይችላል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ይህ አስተሳሰብ “በአምላክ ፊት ሞኝነት ነው።”—1 ቆሮ. 3:18-20

9. የማመዛዘን ችሎታችሁን ለመጠበቅ ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

9 ተጨማሪ ትምህርቱን ከመጀመራችሁ በፊት ምን ማድረግ ትችላላችሁ? የማመዛዘን ችሎታችሁን ለመጠበቅ ትምህርቱን ከመጀመራችሁ በፊት በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ላይ ያላችሁን እምነት አጠናክሩ። ራሳችሁን እንዲህ እያላችሁ ጠይቁ፦ ‘በአምላክ የማምነው ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል እንደሆነ እርግጠኛ የሆንኩት ለምንድን ነው? የመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ከዓለም መሥፈርቶች የተሻሉ እንደሆኑ ያሳመነኝ ምንድን ነው?’ በተጨማሪም እስካሁን ስለነበራችሁ የትምህርት ቤት ቆይታ አስቡ። ያኔም ቢሆን ለዓለማዊ አስተሳሰብ ተጋልጣችሁ ሊሆን እንደሚችል ጥያቄ የለውም። ሌሎች በዝግመተ ለውጥ ላይ ያላቸውን እምነት ስታዩ እምነታችሁ ተዳክሞ ነበር? አብረዋችሁ የሚማሩ ልጆች ያላቸውን መጥፎ ሥነ ምግባር ለመከተል ተፈትናችሁ ነበር? በሆነ መንገድ ድክመት እንደነበረባችሁ ካስተዋላችሁ ከአሁን ጀምሮ እምነታችሁን ማጠናከር የምትችሉት እንዴት ነው? ተጨማሪ ትምህርት ስትከታተሉ የማመዛዘን ችሎታችሁን ለመጠበቅ ቁርጥ ውሳኔ አድርጉ።—2 ጢሞ. 2:16-18b

10. ትምህርቱን ከጀመራችሁ በኋላ የማመዛዘን ችሎታችሁን መጠበቅ የምትችሉት እንዴት ነው?

10 ተጨማሪ ትምህርት ስትከታተሉ በየጊዜው ራሳችሁን ገምግሙ። እንዲህ እያላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ፦ ‘በዙሪያዬ ያሉት ሰዎች የሚከተሉት ሥነ ምግባር የጎደለው አኗኗር ተጽዕኖ እያደረገብኝ ነው? የዓለምን ከንቱ ፍልስፍና ከአምላካዊ ጥበብ መለየት እችላለሁ? የሰው ልጆችን ችግሮች ሊፈታ የሚችለው የአምላክ መንግሥት ብቻ እንደሆነ ሙሉ በሙሉ አምናለሁ?’ የማመዛዘን ችሎታችሁን ለመጠበቅ መጽሐፍ ቅዱስን በጥልቀት ማጥናታችሁን ቀጥሉ። መጽሐፍ ቅዱስን ስታጠኑና ስታሰላስሉ እውነትን እንደያዛችሁ ያላችሁ እምነት ይጠናከራል።—1 ጢሞ. 4:15

ጊዜያችሁን በአግባቡ ተጠቀሙበት

11. ተጨማሪ ትምህርት ስትከታተሉ ከጊዜ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ምን ተፈታታኝ ሁኔታ ሊያጋጥማችሁ ይችላል?

11 ተፈታታኙ ነገር። ተጨማሪ ትምህርት ስትከታተሉ ፕሮግራማችሁ ሊጨናነቅ ይችላል። በተለይ ደግሞ ፈተና ሲቃረብ ወይም አንድን ፕሮጀክት በአጭር ጊዜ ውስጥ እንድታስረክቡ ስትጠየቁ ጊዜያችሁ ሊጣበብ ይችላል። ጊዜያችሁን በአግባቡ ካልተጠቀማችሁበት ለውጥረት ልትዳረጉ ብሎም ጉልበታችሁ ሙሉ በሙሉ ሊሟጠጥ ይችላል። ስለዚህ ለአካላዊና ለስሜታዊ ጤንነታችሁ የተለየ ትኩረት መስጠት ይኖርባችኋል።

12. ‘ጊዜያችሁን በተሻለ መንገድ ለመጠቀም’ የትኞቹን ነገሮች በፕሮግራማችሁ ውስጥ ማካተት ያስፈልጋችኋል? (ኤፌሶን 5:15, 16)

12 ኤፌሶን 5:15, 16ን አንብብ። ማከናወን ካለባችሁ ነገር ብዛት አንጻር ‘ጊዜያችሁን በተሻለ መንገድ መጠቀም’ ተፈታታኝ ሊሆን ይችላል። ለትምህርታችሁ ጊዜ መስጠት ቢኖርባችሁም ከእምነት አጋሮቻችሁና ከቤተሰቦቻችሁ ጋር ጊዜ ማሳለፋችሁ ይበልጥ አስፈላጊ ነው። (መዝ. 133:1፤ ምሳሌ 18:1) ከሁሉ በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ነገር ደግሞ መንፈሳዊ እንቅስቃሴያችሁ ነው። (ማቴ. 6:33) በተጨማሪም ቤተሰባችሁን ማገዝ ወይም የትርፍ ጊዜ ሥራ መሥራት ሊጠበቅባችሁ ይችላል። እንዲሁም በቂ እረፍትና አካላዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ጤንነታችሁን መንከባከባችሁ አስፈላጊ ነው። (መክ. 4:6፤ 1 ጢሞ. 4:8) እነዚህን ሁሉ ነገሮች ማከናወን ጥሩ የጊዜ አጠቃቀም ችሎታ ይጠይቃል።

13. ጊዜያችሁን በተሻለ መንገድ ለመጠቀም ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

13 ተጨማሪ ትምህርቱን ከመጀመራችሁ በፊት ምን ማድረግ ትችላላችሁ? መጽሐፍ ቅዱስ ዕቅድ ማውጣት ለስኬት እንደሚያበቃ ይናገራል። (ምሳሌ 21:5) ስለዚህ ተጨማሪ ትምህርቱን ከመጀመራችሁ በፊት ሚዛናዊ የሆነ ፕሮግራም አውጡ። እስከዛሬ በትምህርት ያሳለፋችሁትን ጊዜ መለስ ብላችሁ ማሰባችሁ ይረዳችኋል። ያኔ የጊዜ አጠቃቀማችሁ እንዴት ነበር? በዚህ ረገድ ድክመት እንደነበረባችሁ ካስተዋላችሁ ከዚህ በኋላ ምን ማስተካከያ ማድረግ ትችላላችሁ? አስፈላጊ ለሆኑ ነገሮች ጊዜ እንዳያጥራችሁ ጥሩ ፕሮግራም አውጡ።c

14. ራሳችሁን ለመገምገም የትኞቹን ጥያቄዎች መጠቀም ትችላላችሁ?

14 ተጨማሪ ትምህርት ስትከታተሉ በየጊዜው ራሳችሁን ገምግሙ። እንዲህ እያላችሁ ራሳችሁን መጠየቅ ትችላላችሁ፦ ‘በቂ እረፍትና አካላዊ እንቅስቃሴ እያደረግኩ ነው? ከእምነት አጋሮቼ ጋር የማሳልፈው በቂ ጊዜ አለኝ? የቤት ሥራዎቼን በጊዜው አጠናቅቃለሁ? ካልሆነ ደግሞ ምክንያቱ ምንድን ነው? በእርግጥ ሥራ ስለበዛብኝ ነው ወይስ የጊዜ አጠቃቀሜ ጥሩ ስላልሆነ? ቤተሰቦቼን ጨምሮ ሌሎች ሰዎች በጊዜ አጠቃቀሜ ረገድ ማስተካከያ ማድረግ እንዳለብኝ ይሰማቸዋል?’ ማስተካከያ ማድረግ እንዳለባችሁ ከተሰማችሁ አፋጣኝ እርምጃ ውሰዱ። ፕሮግራማችሁን ማስተካከል ወይም ራስን የመግዛት ችሎታ ማዳበር ሊያስፈልጋችሁ ይችላል። ምናልባትም በጊዜ አጠቃቀም ረገድ ምሳሌ የሚሆኑ ሰዎችን ልታማክሩ ትችላላችሁ።—ምሳሌ 11:14

‘ከጥበበኞች ጋር መሄዳችሁን’ ቀጥሉ

15. ተጨማሪ ትምህርት ስትከታተሉ የትኛው ተፈታታኝ ሁኔታ ሊያጋጥማችሁ ይችላል?

15 ተፈታታኙ ነገር። ተጨማሪ ትምህርት ስትከታተሉ አብረዋችሁ የሚማሩት ሰዎች ከእነሱ ጋር ጊዜ እንድታሳልፉ ሊጠይቋችሁ ይችላሉ። እናንተም ከእነሱ ጋር አብራችሁ ጊዜ ለማሳለፍ ትፈተኑ ይሆናል። ደግሞም በክፍል ውስጥ አብራችሁ ብዙ ጊዜ ከማሳለፋችሁ አንጻር ብዙ የጋራ ነገር ይኖራችኋል። እንዲያውም ከአንዳንድ ወንድሞችና እህቶች ይበልጥ ከእነሱ ጋር ብዙ የሚያመሳስላችሁ ነገር እንዳለ ሊሰማችሁ ይችላል። ይሁንና ጠንቃቃ መሆን ይኖርባችኋል። ከእነሱ ጋር የሚያመሳስሏችሁ ነገሮች ቢኖሩም የምትመሩባቸው እሴቶች የተለያዩ ናቸው። ከእነሱ ጋር ይበልጥ ጊዜ ባሳለፋችሁ መጠን አስተሳሰባቸው ሊጋባባችሁ ይችላል። (1 ቆሮ. 15:33) የኤሌክትሪክ ባለሙያ ለመሆን የአራት ዓመት ሥልጠና የወሰደው ማይክል እንዲህ ብሏል፦ “አብረውኝ ከሚሠሩት ሰዎች ጋር በሳምንት ከ40 ሰዓት በላይ አሳልፋለሁ። እነዚህ ሰዎች ለተቃራኒ ፆታ ያላቸው አመለካከት፣ የሙዚቃ ምርጫቸው እንዲሁም የሚጠቀሙት ጸያፍ ንግግር በአስተሳሰቤ ላይ ተጽዕኖ ማሳደር ጀምሮ ነበር።”

16. ከምሳሌ 13:20 ምን ትምህርት እናገኛለን?

16 ምሳሌ 13:20ን አንብብ። መጽሐፍ ቅዱስ መጥፎ ጓደኝነት ስላለው አደጋ ያስጠነቅቀናል። በሌላ በኩል ደግሞ “ከጥበበኞች ጋር የሚሄድ ጥበበኛ ይሆናል” ይላል። ነጥቡ ግልጽ ነው፦ አብረናቸው ጊዜ የምናሳልፋቸው ሰዎች ወይ በጥሩ ወይ በመጥፎ ይቀርጹናል። ስለዚህ እንደ እናንተ በሙሉ ልብ ይሖዋን ለማገልገል ከሚፈልጉና ከልባቸው ከሚያስቡላችሁ ሰዎች ጋር ጓደኝነት መሥርቱ።—መዝ. 101:6, 7፤ 119:63

17. ከመጥፎ ጓደኝነት ለመራቅ ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

17 ተጨማሪ ትምህርቱን ከመጀመራችሁ በፊት ምን ማድረግ ትችላላችሁ? አብረዋችሁ ከሚማሩ ሰዎች ጋር ባላችሁ ግንኙነት ምን ዓይነት ገደብ እንደምታበጁ ወስኑ። ትሬንተን የተባለ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “አብረውኝ ከሚማሩ ሰዎች ጋር እግባባለሁ፤ ግን ከትምህርት በኋላ አብሬያቸው ጊዜ አላሳልፍም። የማያቸው እንደ ክፍሌ ተማሪዎች እንጂ እንደ ቅርብ ጓደኞቼ አይደለም።” እናንተስ ምን ዓይነት ገደብ ማበጀት ትችላላችሁ? ይህን ጥያቄ ለመመለስ እስካሁን የነበራችሁን የትምህርት ቤት ቆይታ መለስ ብላችሁ አስቡ። ያኔ አብረዋችሁ ከሚማሩ ልጆች ጋር ባላችሁ ግንኙነት ምን ዓይነት ገደብ አበጅታችሁ ነበር? በዚህ ረገድ ድክመት እንደነበረባችሁ ካስተዋላችሁ ከዚህ በኋላ ምን ማስተካከያ ማድረግ ትችላላችሁ? ‘ከጥበበኞች ጋር መሄዳችሁንና’ ይሖዋን ከማይወዱ ሰዎች መራቃችሁን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ አድርጉ።d

18. ራሳችሁን ለመገምገም የትኞቹን ጥያቄዎች መጠየቅ ትችላላችሁ? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

18 በየጊዜው ራሳችሁን ገምግሙ። እንዲህ እያላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ፦ ‘አብረውኝ ከሚማሩት ሰዎች ጋር ከልክ በላይ እየተቀራረብኩ ነው? አነጋገራቸው፣ አስተሳሰባቸውና ምግባራቸው እየተጋባብኝ ነው? ከእነሱ ጋር ስላለኝ ግንኙነት ይሖዋስ ምን ይሰማዋል?’ (መዝ. 1:1) በራሳችሁ ላይ ደስ የማይሉ ለውጦችን ካስተዋላችሁ አፋጣኝ እርምጃ ውሰዱ። የቅርብ ጓደኛ የምታደርጓቸው ሰዎች እንደ እናንተ ይሖዋን የሚወዱ ሰዎች ሊሆኑ ይገባል። በተጨማሪም አብረዋችሁ ለሚማሩ ሰዎች ከመመሥከር ወደኋላ አትበሉ። እውነትን እንዲማሩ ሊረዳቸው የሚችል ከእናንተ የተሻለ ሰው የለም።

የፀጉር ሥራ ሥልጠና እየወሰደች ያለች አንዲት እህት አብራት ለምትማር ሴት “አምላክ ሁሉንም ሃይማኖቶች ይቀበላል?” የሚለውን ትራክት ስታሳያት።

አብረዋችሁ ለሚማሩ ሰዎች ከመመሥከር ወደኋላ አትበሉ (አንቀጽ 18ን ተመልከት)e


ከወዲሁ ተዘጋጁ

19. ተጨማሪ ትምህርት ስትከታተሉ ሊያጋጥሟችሁ የሚችሉ መንፈሳዊ አደጋዎችን ለመወጣት ዝግጅት ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው? በምሳሌ አስረዱ።

19 ተራራ የሚወጣ አንድ ሰው መንገዱን ከመጀመሩ በፊት ራሱን ያዘጋጃል። በመንገዱ ላይ የሚያጋጥመውን እያንዳንዱን ችግር አስቀድሞ ማወቅ ባይችልም ጥሩ አቋም ላይ መሆኑን ያረጋግጣል፤ ተገቢውን ልብስ ይለብሳል፤ እንዲሁም ግቡን ማለትም መዳረሻውን ጠንቅቆ ያውቃል። እናንተም በተመሳሳይ ተጨማሪ ትምህርት ስትከታተሉ እነዚህኑ ነገሮች ማድረግ ትችላላችሁ። ጥሩ መንፈሳዊ አቋም ይኑራችሁ፤ “ከአምላክ የሚገኘውን ሙሉ የጦር ትጥቅ” ልበሱ፤ እንዲሁም ግባችሁን አስታውሱ። ግባችሁ ዓለም እንደ ስኬት የሚቆጥራቸውን ነገሮች ማግኘት ሳይሆን በምታደርጉት ነገር ሁሉ ለይሖዋ ክብር ማምጣት ነው።—ኤፌ. 6:11-13፤ 1 ቆሮ. 9:26, 27፤ 10:31

20. “በእምነት ውስጥ መሆናችሁን ለማረጋገጥ ዘወትር ራሳችሁን [መፈተሽ]” የምትችሉት እንዴት ነው?

20 መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ የሚል ምክር ይሰጠናል፦ “በእምነት ውስጥ መሆናችሁን ለማረጋገጥ ዘወትር ራሳችሁን ፈትሹ፤ ማንነታችሁን ለማወቅ ዘወትር ራሳችሁን መርምሩ።” (2 ቆሮ. 13:5) ተጨማሪ ትምህርት በምትከታተሉበት ጊዜ እንዲህ ማድረግ ትችላላችሁ። በዚህ ርዕስ ውስጥ ከተጠቀሱት አቅጣጫዎች አንጻር ዘወትር ራሳችሁን ገምግሙ። አሁንም ጥሩ መንፈሳዊ ልማድ አላችሁ? ከንቱ ከሆነው የዓለም ጥበብ አስተሳሰባችሁን እየጠበቃችሁ ነው? ጊዜያችሁን በአግባቡ እየተጠቀማችሁበት ነው? ከመጥፎ ጓደኝነት በመራቅ ከእምነት አጋሮቻችሁ ጋር እየተቀራረባችሁ ነው? በትምህርት ቤት እየተማሩ ያሉ ብቻ ሳይሆኑ በሥራው ዓለም ወይም በሌሎች ሁኔታዎች ውስጥ ያሉ ክርስቲያኖችም እነዚህን ጥያቄዎች ራሳቸውን መጠየቅ ይኖርባቸዋል። ያላችሁበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን በመንፈሳዊ ጠንካሮች ሆናችሁ ለመኖር ቁርጥ ውሳኔ አድርጉ። በዚህ ረገድ የምታደርጉትን ጥረት ይሖዋ እንደሚባርክላችሁ አትጠራጠሩ።—ምሳሌ 3:5, 6

ተጨማሪ ትምህርት ስትከታተሉ የሚከተሉትን ነገሮች ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው?

  • ጥሩ መንፈሳዊ ልማድ ይዞ መቀጠል

  • ‘የማመዛዘን ችሎታችሁን መጠበቅ’

  • ጊዜያችሁን በአግባቡ መጠቀምና ከመጥፎ ጓደኝነት መራቅ

መዝሙር 87 ኑ! እረፍት አግኙ

a በይሖዋ አገልግሎት ንቁ ተሳትፎ ማድረጋችሁን መቀጠል የምትችሉት እንዴት እንደሆነ ለማወቅ “የወጣቶች ጥያቄ . . . ከተጠመቅኩ በኋላ ምን ማድረግ ያስፈልገኛል?—ክፍል 1፦ ጥሩ ልማዶችህን ይዘህ ቀጥል” የሚለውን ርዕስ jw.org ላይ ተመልከቱ።

b የማመዛዘን ችሎታችሁን መጠበቅ የምትችሉት እንዴት እንደሆነ ለማወቅ በግንቦት 2019 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “‘በዚህ ዓለም ጥበብ’ እንዳትታለሉ ተጠንቀቁ” የሚለውን ርዕስ ተመልከቱ።

c ጥሩ ዕለታዊ ፕሮግራም ማውጣት የምትችሉት እንዴት እንደሆነ ለማወቅ “የወጣቶች ጥያቄ . . . ጊዜዬን በአግባቡ መጠቀም የምችለው እንዴት ነው?” የሚለውን ርዕስ jw.org ላይ ተመልከቱ።

d ጓደኞቻችሁን በጥበብና በጥንቃቄ መምረጥ የምትችሉት እንዴት እንደሆነ ለማወቅ ለዘላለም በደስታ ኑር! በተባለው መጽሐፍ ምዕራፍ 48 ላይ የሚገኘውን “ጓደኞችህን በጥበብ ምረጥ” የሚለውን ርዕስ ተመልከቱ።

e የሥዕሉ መግለጫ፦ የፀጉር ሥራ ሥልጠና እየወሰደች ያለች አንዲት እህት አብራት ለምትማር ሴት በዘዴ ስትመሠክር።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2026)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2026 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ