የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w26 የካቲት ገጽ 30-ገጽ 31 አን. 7
  • የአንባቢያን ጥያቄዎች

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የአንባቢያን ጥያቄዎች
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2026
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ስለ ሰላምና ደኅንነት መጽሐፍ ቅዱስ ያለው አመለካከት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • የአንባቢያን ጥያቄዎች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • ከሰው ሠራሹ “ሰላምና ደኅንነት” ባሻገር መመልከት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • የሃይማኖቶች ዕጣ ፈንታ ምንድን ነው?—መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይነግረናል?
    ተጨማሪ ርዕሰ ጉዳዮች
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2026
w26 የካቲት ገጽ 30-ገጽ 31 አን. 7
የዓለም መሪዎች በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤት አቅራቢያ ቆመው “ሰላምና ደህንነት ሆነ” ብለው ሲያውጁ፤ የተሰበሰበው ሕዝብ በጣም ተደስቷል።

የአንባቢያን ጥያቄዎች

ብሔራት “ሰላምና ደህንነት ሆነ” ብለው የሚያውጁት መቼ ነው?

በኅዳር 2025 መጠበቂያ ግንብ ላይ በወጣው “የአንባቢያን ጥያቄዎች” ላይ ይሖዋ በቅርቡ ‘በአሥሩ ቀንዶች’ (በሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች) ልብ ውስጥ “ሐሳቡን” ማለትም ኃይላቸውንና ሥልጣናቸውን ‘ለደማቁ ቀይ አውሬ’ ይኸውም ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የመስጠት ሐሳብ እንደሚያኖር ተገልጾ ነበር። ይህ አውሬ “የአውሬው ምስል” ተብሎም ተጠርቷል። (ራእይ 13:14, 15፤ 17:3, 16, 17) ከዚያም “አሥሩ ቀንዶች” እና ከእነሱ ሥልጣን የተቀበለው አውሬ የሐሰት ሃይማኖትን ከመላው ዓለም ያጠፋሉ። ብሔራት “ሰላምና ደህንነት ሆነ” ብለው የሚያውጁትa የሐሰት ሃይማኖት ከመጥፋቱ በፊት ነው ወይስ በኋላ?—1 ተሰ. 5:3

በአጭሩ ለመመለስ፣ ብሔራት “ሰላምና ደህንነት ሆነ” ብለው የሚያውጁበትን ትክክለኛ ጊዜ አናውቅም። ስለዚህ ጉዳይ ሁሉንም ዝርዝር መረጃ ብናውቅ ኖሮ ነቅተን መጠበቅ አያስፈልገንም ነበር። ሆኖም ኢየሱስ ተከታዮቹን “ምንጊዜም ነቅታችሁ ጠብቁ” ሲል በተደጋጋሚ አሳስቧቸዋል። (ማቴ. 24:42፤ 25:13፤ 26:41) እስቲ ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት ለተሰሎንቄ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ የሚገኘውን ይህን ትንቢት በጥልቀት እንመርምር።

ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “‘ሰላምና ደህንነት ሆነ!’ ሲሉ . . . ያልታሰበ ጥፋት ድንገት ይመጣባቸዋል።” (1 ተሰ. 5:2, 3) ጽሑፎቻችን ጳውሎስ የተናገረውን ሐሳብ የሚያብራሩት በዚህ መንገድ ነበር፦ “ሰላምና ደህንነት ሆነ” የሚለው አዋጅ የሚታወጀው ታላቁ መከራ ከመጀመሩ ጥቂት ቀደም ብሎ ነው፤ ታላቁ መከራ የሚጀምረው ደግሞ በዓለም ላይ ያሉትን የሐሰት ሃይማኖቶች በሙሉ በምታመለክተው በታላቂቱ ባቢሎን ጥፋት ነው። ይህ አዋጅ ታላቁ መከራ ሊጀምር መሆኑን የሚያሳይ የመጨረሻ ምልክት እንደሆነ እንገልጽ ነበር።

ሆኖም ይህን ትንቢት በጥንቃቄ ከመረመርን በኋላ ትንቢቱ ፍጻሜውን ሊያገኝ የሚችልበት ሌላም መንገድ እንዳለ ማስተዋል ችለናል። ምናልባት “ሰላምና ደህንነት ሆነ” የሚለው አዋጅ የሚታወጀው የሐሰት ሃይማኖት ከጠፋ በኋላ ሊሆን ይችላል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? እስቲ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ እንሞክር።

በምድር ላይ ለሚካሄዱት ጦርነቶች የሐሰት ሃይማኖት ምን አስተዋጽኦ አበርክቷል? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “በእሷም [“ታላቂቱ አመንዝራ” ተብላ በተጠራችው በታላቂቱ ባቢሎን] ውስጥ . . . በምድር ላይ የታረዱ ሰዎች ሁሉ ደም ተገኝቷል።” (ራእይ 17:1, 5፤ 18:24) በታሪክ ዘመናት ሁሉ ታላቂቱ አመንዝራ ጦርነቶችን ስትደግፍ እንዲሁም የሽብር ጥቃቶችን ስታቀጣጥል ቆይታለች። በመሆኑም ለሰላምና ለደህንነት ሳይሆን ለዓመፅና ለጦርነት ምክንያት ሆናለች። ይህ አንድ ጥያቄ ያስነሳል፦ ብሔራት “ሰላምና ደህንነት ሆነ” ብለው የሚያውጁት ታላቂቱ ባቢሎንን ካጠፉ በኋላ ይሆን? ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም በእርግጠኝነት መናገር አንችልም።

“ሰላምና ደህንነት ሆነ” ከሚለው አዋጅ በኋላ ምን ይከሰታል? ጳውሎስ “ያልታሰበ ጥፋት ድንገት ይመጣባቸዋል” ብሏል። (1 ተሰ. 5:3) ብሔራት “ሰላምና ደህንነት ሆነ” ብለው የሚያውጁት የሐሰት ሃይማኖትን ከማጥፋታቸው በፊት ከሆነ እነሱ ራሳቸው እስኪጠፉ ድረስ የተወሰነ ጊዜ ያልፋል ማለት ነው። ሆኖም ጳውሎስ “ያልታሰበ ጥፋት ድንገት” እንደሚመጣባቸው ስለተናገረ ብሔራት “ሰላምና ደህንነት ሆነ” ብለው የሚያውጁት የሐሰት ሃይማኖትን ካጠፉ በኋላ ሊሆን ይችላል።

የይሖዋ ሕዝቦች እነዚህ ክንውኖች ሲፈጸሙ ምን ይሰማቸዋል? ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፦ “እናንተ ግን ወንድሞች፣ በጨለማ ውስጥ ስላልሆናችሁ ሌሊቱ ድንገት እንደሚነጋበት ሌባ፣ ያ ቀን ድንገት አይደርስባችሁም።” (1 ተሰ. 5:4) “ሰላምና ደህንነት ሆነ” የሚለው አዋጅ የሐሰት ሃይማኖት ከጠፋ በኋላ የሚታወጅ ከሆነ የይሖዋ ሕዝቦች ብሔራት የሚጠፉበት ጊዜ እንደደረሰ ያውቃሉ። ለብሔራት ግን ጥፋታቸው እንደ ሌባ ያለምንም ማስጠንቀቂያ በድንገት ይመጣባቸዋል።

እንግዲያው ምን እንደሚሆን መጠበቅ እንችላለን? በቅርቡ “አሥሩ ቀንዶች” እና ከእነሱ ሥልጣን የተቀበለው አውሬ የሐሰት ሃይማኖትን ያጠፋሉ። ይህ የታላቁ መከራ መጀመሪያ ይሆናል። በተጨማሪም የሆነ ወቅት ላይ ብሔራት “ሰላምና ደህንነት ሆነ” ብለው እንደሚያውጁ እናውቃለን። ይህ የሚሆነው መቼ ነው? ትንቢቱ ፍጻሜውን ሊያገኝ የሚችልባቸውን ሁለት መንገዶች ተመልክተናል። አንደኛ፣ አዋጁ የሚታወጀው የሐሰት ሃይማኖት ከመጥፋቱ በፊት ሊሆን ይችላል። ሁለተኛ፣ አዋጁ የሚታወጀው የፖለቲካ ኃይሎች የሐሰት ሃይማኖትን ሙሉ በሙሉ ካጠፉ በኋላ ሊሆን ይችላል። ትንቢቱ ፍጻሜውን የሚያገኘው በየትኛው መንገድ እንደሆነ ጊዜ ያሳየናል። ብዙውን ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን ሙሉ በሙሉ መረዳት የሚቻለው እየተፈጸሙ እያለ ወይም ከተፈጸሙ በኋላ ነው።—ከዮሐንስ 12:16 ጋር አወዳድር።

እስከዚያው ግን፣ በዋነኝነት ሊያሳስበን የሚገባው ‘“ሰላምና ደህንነት ሆነ” የሚለው አዋጅ የሚታወጀው መቼ ነው’ የሚለው ሳይሆን በአምላክ ፊት ያለን አቋም ነው። ነገሮች የሚከናወኑበት ቅደም ተከተል ምንም ይሁን ምን ሙሉ በሙሉ ዝግጁ ሆነን እንድንገኝ “ነቅተን እንኑር እንዲሁም የማስተዋል ስሜታችንን እንጠብቅ።”—1 ተሰ. 5:6

a ጳውሎስ የተጠቀመበት አገላለጽ አንድን አዋጅ ብቻ ሳይሆን ተከታታይ አዋጆችን ሊያመለክት ይችላል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2026)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2026 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ