ከሚያዝያ 13-19, 2026
መዝሙር 52 ራስን ለአምላክ መወሰን
የጥምቀት ትርጉም ምንድን ነው?
“ሰዎችን [እያጠመቃችሁ] ደቀ መዛሙርት አድርጉ።”—ማቴ. 28:19
ዓላማ
የጥምቀት ትርጉም ምንድን ነው? አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? የሚከናወነውስ እንዴት ነው?
1. ጥምቀት መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ነው የምንለው ለምንድን ነው?
አዲሶች ሲጠመቁ ማየት በጣም ያስደስተናል! የክርስቲያን ጉባኤ ባደረገው የመጀመሪያ ስብሰባ ላይ የተገኙ ክርስቲያኖችም ብዙ ሰዎች ሲጠመቁ ሲያዩ ተደስተው ነበር። በዚያ ወቅት ሐዋርያው ጴጥሮስ ስለ ጥምቀት አስፈላጊነት የሚያብራራ ንግግር ሰጠ። (ሥራ 2:38, 40, 41) ሐዋርያው ጳውሎስ “ስለ ክርስቶስ ከተማርነው መሠረታዊ ትምህርት” አንዱ “ስለ ጥምቀቶች” የሚገልጸው ትምህርት እንደሆነ ተናግሯል። (ዕብ. 6:1, 2) ስለዚህ ጥምቀት መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ነው፤ እኛም በደንብ ልንረዳው ይገባል። ለምን?
2. ስለ ጥምቀት በሚገባ መረዳት የሚኖርብን ለምንድን ነው?
2 አንድ ቤት እንዳይናወጥ ከተፈለገ ጠንካራ መሠረት ሊኖረው ይገባል። በተመሳሳይ እኛም የማይናወጥ እምነት እንዲኖረን ከፈለግን እምነታችን የተመሠረተባቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች በጥልቀት ልንረዳቸው ይገባል። ይህም ስለ ጥምቀት የሚገልጸውን ትምህርት ያካትታል። ለመጠመቅ እየተዘጋጁ ያሉ ሰዎችም ሆኑ ከተጠመቁ ረጅም ጊዜ ያለፋቸው ክርስቲያኖች ስለ ጥምቀት በሚገባ መረዳት ያስፈልጋቸዋል። በመሆኑም በዚህ ርዕስ ውስጥ ለሚከተሉት ጥያቄዎች መልስ እናገኛለን፦ የጥምቀት ትርጉም ምንድን ነው? ጥምቀት የሚከናወነው እንዴት ነው? በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም የምንጠመቀውስ ለምንድን ነው?
መጠመቅህ ያለው ትርጉም
3. መጠመቅህ ምን ያሳያል?
3 ስትጠመቅ ስለ ይሖዋ አምላክና ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ እውነቱን እንደተቀበልክ፣ ከኃጢአትህ ንስሐ እንደገባህ፣ ይሖዋን ለማገልገል ስትል በሕይወትህ ውስጥ ማስተካከያዎችን እንዳደረግክ፣ መዳን የምታገኘው በኢየሱስ በኩል ብቻ እንደሆነ አምነህ እንደተቀበልክ እንዲሁም ከድርጅቱ ጋር በመተባበር የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ በጸሎት ቃል እንደገባህ በሕዝብ ፊት ታሳያለህ። ይህን ቃል በመግባት ራስህን ከወሰንክና ከተጠመቅክ በኋላ ወደ ዘላለም ሕይወት በሚመራው ጎዳና ላይ መጓዝ ትጀምራለህ።
4. ውኃ ውስጥ ሙሉ በሙሉ መጥለቅ ምን ያመለክታል? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
4 ስትጠመቅ ሙሉ በሙሉ ውኃ ውስጥ ትጠልቃለህ፤ ከዚያም ትወጣለህ፤a ይህም ሞቶ ከመቀበርና ትንሣኤ ከማግኘት ጋር ይመሳሰላል። (ከቆላስይስ 2:12 ጋር አወዳድር።) ጥምቀት በሕይወትህ ውስጥ ያደረግከውን ትልቅ ለውጥ በምሳሌያዊ ሁኔታ ያሳያል። እንዴት? ውኃው ውስጥ መግባትህ የቀድሞ አኗኗርህ የሞተ ያህል ሙሉ በሙሉ እንዳበቃ የሚያሳይ ነው። ከውኃው መውጣትህ ደግሞ የአምላክን ፈቃድ በመፈጸም ላይ ያተኮረ አዲስ ሕይወት መምራት እንደጀመርክ ያመለክታል።
ስትጠመቅ የቀድሞ አኗኗርህ ያበቃል፤ ከዚያም የአምላክን ፈቃድ በመፈጸም ላይ ያተኮረ አዲስ ሕይወት መምራት ትጀምራለህ (አንቀጽ 4ን ተመልከት)
5. ለጥምቀት ብቁ ለመሆን የምታደርገው ጥረት ኖኅ መርከቡን ለመገንባት ካከናወነው ሥራ ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው? (1 ጴጥሮስ 3:18-21)
5 አንደኛ ጴጥሮስ 3:18-21ን አንብብ። ለጥምቀት ብቁ ለመሆን የምታደርገው ጥረት ኖኅ መርከቡን ለመገንባት ካከናወነው ሥራ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ስለ ይሖዋ መማር የጀመርከው በቅርቡ ከሆነ ከፊትህ የሚጠብቅህ ሥራ የኖኅን መርከብ የመገንባት ያህል ከባድ ሥራ መስሎ ሊታይህ ይችላል። ግን ይህን ሁሉ ጥረት ማድረግ በእርግጥ አስፈላጊ ነው? አዎ። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? የኖኅን ምሳሌ መለስ ብለህ አስብ። የመርከቡን ንድፍ ያወጣው አምላክ ራሱ ነው፤ ኖኅ ከጥፋት ውኃው ራሱንና ቤተሰቡን ማዳን ከፈለገ ይህን ንድፍ በጥንቃቄ መከተል ነበረበት። ኖኅ እምነት ስለነበረውና ይሖዋ ስለረዳው በታዛዥነት መርከቡን መሥራት ችሏል። አንተም እንደ ኖኅ ‘አምላክ ያዘዘውን ነገር ሁሉ’ በማድረግ ረገድ ሊሳካልህ ይችላል።—ዘፍ. 6:22
6. ጥምቀት ሊያድንህ የሚችለው በምን መንገድ ነው?
6 ሐዋርያው ጴጥሮስ በቁጥር 21 ላይ “ጥምቀት . . . እያዳናችሁ ነው” በማለት ጽፏል። እርግጥ ነው፣ ውኃ ውስጥ መግባትህ በራሱ መዳን አያስገኝልህም ወይም ኃጢአትህን አያጥብልህም። ከኃጢአት ሊያነጻህ የሚችለው የኢየሱስ ደም ብቻ ነው። (1 ዮሐ. 1:7) ሆኖም መጠመቅህ በጣም አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም አምላክ ያዘዘውን ሁሉ መፈጸም መጠመቅንም ያካትታል። እንዲሁም ስትጠመቅ ‘አምላክ ጥሩ ሕሊና እንዲሰጥህ ልመና’ እያቀረብክ ነው። ይሖዋም የለመንከውን ነገር በደስታ ይሰጥሃል። በዚህ መንገድ ጥምቀት ‘ያድንሃል’፤ ወይም የመዳንን መንገድ ይከፍትልሃል።
ጥምቀት የሚከናወነው እንዴት ነው?
7. ጥምቀት መከናወን ያለበት እንዴት ነው?
7 ሙሉ በሙሉ ውኃ ውስጥ መጥለቅ እንደሚያስፈልግ ከሚገልጸው መሥፈርት ውጭ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጥምቀት ብዙ ዝርዝር መመሪያ አይሰጠንም። ያም ሆኖ ቅዱሳን ጽሑፎች ከዚህ ጋር በተያያዘ ማድረግ ያለብንንና የሌለብንን ነገር ለማወቅ ይረዱናል። ለምሳሌ የጥምቀት ዕጩዎች ምን ዓይነት ልብስ መልበስ እንዳለባቸውና ታዳሚዎች ምን ዓይነት ምግባር ማሳየት እንደሚገባቸው የሚጠቁሙ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች አሉ። (1 ቆሮ. 14:40፤ 1 ጢሞ. 2:9) በአብዛኛው የጥምቀት ዕጩዎቹን የሚያጠምቀው አንድ የጉባኤ ሽማግሌ ነው፤ ሆኖም ይህ መብት ለሚሰጣቸው ሽማግሌዎች የተለየ ቦታ ከመስጠት እንቆጠባለን። (1 ቆሮ. 1:14, 15) ጥምቀቱን የሚመለከቱት ሰዎች ብዙም ሆኑ ጥቂት ጥምቀቱ ተቀባይነት ይኖረዋል።—ሥራ 8:36
8. የጥምቀት ዕጩዎች የትኞቹን ሁለት ጥያቄዎች ይጠየቃሉ? ለምንስ? (የሐዋርያት ሥራ 2:38-42) (ሥዕሉንም ተመልከት።)
8 መጽሐፍ ቅዱስ ለመዳን ‘እምነታችንን በይፋ መናገር’ እንዳለብን ይገልጻል። (ሮም 10:9, 10) ከዚህ አንጻር፣ ለመዳን ወሳኝ እርምጃ በሆነው በጥምቀት ወቅት እምነታችንን በይፋ መናገራችን ምንኛ የተገባ ነው! በዚህም ምክንያት፣ የጥምቀት ዕጩዎች ሁለት ጥያቄዎችን ይጠየቃሉ። የመጀመሪያው ጥያቄ እንዲህ ይላል፦ “ከኃጢአታችሁ ንስሐ በመግባት፣ ራሳችሁን ለይሖዋ በመወሰንና ይሖዋ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ያደረገውን የመዳን ዝግጅት በመቀበል ለመጠመቅ ዝግጁ ሆናችኋል?” ይህ ጥያቄ የሚያተኩረው የጥምቀት ዕጩዎች ለጥምቀት ለመዘጋጀት በወሰዷቸው እርምጃዎች ላይ ነው። ይህ ጥያቄ ጴጥሮስ በጴንጤቆስጤ ዕለት ለተሰበሰበው ሕዝብ ከሰጠው ማበረታቻ ጋር ተመሳሳይ ነው። ሁለተኛው ጥያቄ ደግሞ እንዲህ ይላል፦ “መጠመቃችሁ በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ከታቀፉት የይሖዋ ምሥክሮች እንደ አንዱ እንደሚያስቆጥራችሁ ተገንዝባችኋል?” ይህ ጥያቄ የጥምቀት ዕጩዎቹ ወደፊት በሚያደርጉት ነገር ላይ ያተኮረ ነው፤ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች እንዳደረጉት ከይሖዋ ድርጅት የሚመጣውን መመሪያ ለመከተልና ከወንድሞቻቸውና ከእህቶቻቸው ጋር አንድ ላይ በመሆን ይሖዋን ለማገልገል ቃል ገብተዋል። (የሐዋርያት ሥራ 2:38-42ን አንብብ።) ሁለቱንም ጥያቄዎች በልበ ሙሉነት “አዎ” ብለው መመለስ የሚችሉ ሁሉ ለመጠመቅ ብቁ ይሆናሉ።
በምትጠመቅበት ዕለት ‘እምነትህን በይፋ ትናገራለህ’ (አንቀጽ 8ን ተመልከት)d
9. ሁሉም ሰው የአምላክን ሞገስ ማግኘት ከፈለገ የትኞቹን እርምጃዎች መውሰድ ይኖርበታል?
9 እውነትን መማር ከመጀመርህ በፊት የነበረህ አኗኗር መጥፎ የሚባል ላይሆን ይችላል፤ ምንም ዓይነት ከባድ ኃጢአትም አልፈጸምክ ይሆናል። ወይም ደግሞ ያደግከው እውነት ውስጥ ሊሆንና ወላጆችህ ይሖዋን እንድትወድ ረድተውህ ሊሆን ይችላል። ታዲያ የአምላክን ሞገስ ለማግኘት ንስሐ መግባትና መጠመቅ ያስፈልግሃል? አዎ። የቀድሞ ሕይወታችን ምንም ዓይነት ቢሆን ሁላችንም ኃጢአትን እንደወረስን አምነን መቀበል ይኖርብናል፤ ይህ ኃጢአት ደግሞ ከአምላክ አርቆናል። (መዝ. 51:5) ይሖዋን እያወቅነው ስንሄድ ግን ከእኛ ፈቃድ ይልቅ የእሱን ፈቃድ ለማስቀደም እንመርጣለን። ለቀድሞ አኗኗራችን ንስሐ እንገባለን፤ እንዲሁም እንመለሳለን ማለትም በሰማይ ያለውን አባታችንን በሚያስደስት መንገድ መኖር እንጀምራለን። ከዚያም መጠመቅ እንችላለን።—ሥራ 3:19
10. የሌላ ሃይማኖት ተከታይ እያለህ ተጠምቀህ ከነበረ ምን ማድረግ ይኖርብሃል?
10 የሌላ ሃይማኖት አባል እያለህ ተጠምቀህ የነበረ ቢሆንም እንኳ የይሖዋ ምሥክር ለመሆን የግድ መጠመቅ ያስፈልግሃል። ለምን? ምክንያቱም ያኔ የተጠመቅከው ስለ ይሖዋ አምላክና ስለ ኢየሱስ የሚገልጸውን እውነት በበቂ ሁኔታ ሳትረዳ ነው። ራስህን ለአምላክ በጸሎት ወስነህ የነበረ ቢሆን እንኳ ይህን ቃል የገባኸው የአምላክን ፈቃድ በትክክል ተረድተህ አይደለም። ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን ያገኛቸው አንዳንድ ሰዎች ስለ ክርስትና ትምህርቶች በቂ ግንዛቤ ሳይኖራቸው ተጠምቀው ነበር፤ በመሆኑም እነዚህ ሰዎች በድጋሚ እንዲጠመቁ አድርጓል።b (ሥራ 19:1-5) በዛሬው ጊዜም ጥምቀት ተቀባይነት የሚኖረው ስለ አምላክ ፈቃድ ባለን ትክክለኛ እውቀት ላይ የተመሠረተ ከሆነ ብቻ ነው።
“በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም”
11. “በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም” መጠመቅ ሲባል ምን ማለት ነው? (ማቴዎስ 28:18-20)
11 ኢየሱስ አዳዲስ ደቀ መዛሙርት “በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም” እንዲጠመቁ አዟል። (ማቴዎስ 28:18-20ን አንብብ።) ይህን ሲል ምን ማለቱ ነበር? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ስም” የሚለው ቃል ብዙውን ጊዜ የሚያመለክተው አንድ ሰው ያተረፈውን ስም ነው። በተጨማሪም የስሙ ባለቤት ያለውን ቦታና ሥልጣን ሊያመለክት ይችላል። ስለዚህ በአንድ አካል ወይም በአንድ ነገር ስም የሆነ ነገር ስናደርግ የስሙ ባለቤት ላለው ሥልጣን እውቅና እየሰጠን ነው። አብና ወልድ ላላቸው ቦታና ሥልጣን እንዲሁም መንፈስ ቅዱስ ለሚጫወተው ሚና እውቅና መስጠት የምትችለው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።
12. በአብ ስም መጠመቅ ሲባል ምን ማለት ነው? (ራእይ 4:11) (ሥዕሉንም ተመልከት።)
12 በአብ ስም። ይሖዋ በሰማይ ያለ አባታችን ወይም ሕይወት ሰጪያችን እንደሆነ እናምናለን። እሱ ሁሉን ቻይ አምላክና የሁሉም ነገር ፈጣሪ ነው። (ራእይ 4:11ን አንብብ።) ጸሎት ሰሚ እንደሆነ እናውቃለን፤ እንዲሁም ወደ እሱ ስንጸልይና ስለ እሱ ለሌሎች ስንናገር ስሙን በአክብሮት ሆኖም በነፃነት እንጠቀማለን። (መዝ. 65:2) ነገር ግን በአብ ስም መጠመቅ ከዚህ ያለፈ ነገርን ይጨምራል። በጴንጤቆስጤ ዕለት የጴጥሮስን ንግግር ያዳምጡ የነበሩ ሰዎች ቀድሞውንም ቢሆን ስለ ይሖዋ ያውቁ ነበር። ሆኖም በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ዘላለማዊ መዳን የሚያገኙበትን ዝግጅት ያደረገ አፍቃሪ አምላክ እንደሆነ ገና ማወቅ ያስፈልጋቸው ነበር።—ሮም 5:8
ከተጠመቅክ በኋላ አብ ላለው ቦታና ሥልጣን እውቅና መስጠትህን ቀጥል (አንቀጽ 12ን ተመልከት)
13. በወልድ ስም መጠመቅ ሲባል ምን ማለት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
13 በወልድ ስም። ኢየሱስ የአምላክ አንድያ ልጅ እንደሆነ እናምናለን። ኢየሱስ “መንገድ” ነው፤ ከይሖዋ ጋር ጥሩ ወዳጅነት መመሥረት የምንችለው በእሱ አማካኝነት ብቻ ነው። (ዮሐ. 14:6) በተጨማሪም ኢየሱስ እኛ ሕይወት እንድናገኝ ሲል በመሞት ዋጅቶናል። ይህን ማወቃችን በተጠመቅንበት ዕለት ብቻ ሳይሆን በዕድሜያችን ዘመን ሁሉ የእሱን ምሳሌ እንድንከተል ይገፋፋናል። (1 ዮሐ. 2:6) በመሆኑም እንደ እሱ በቅንዓት እንሰብካለን፤ ምንም ነገር ከመስበክ እንዲያግደን አንፈቅድም። (ሉቃስ 4:43) አምላክን በታማኝነት በማገልገላችን የተነሳ የሚደርስብንን ስደትም እንኳ ለመጋፈጥ ፈቃደኞች ነን። (2 ጢሞ. 3:12) ኢየሱስ ‘የጉባኤው ራስ’ እንደሆነ እናምናለን፤ ይህን ሥልጣኑን ስለምናከብር ተከታዮቹን እንዲመሩና እንዲንከባከቡ ለሾማቸው ሰዎች በደስታ እንገዛለን።—ኤፌ. 4:8, 11, 12፤ 5:23
ከተጠመቅክ በኋላ ወልድ ላለው ቦታና ሥልጣን እውቅና መስጠትህን ቀጥል (አንቀጽ 13ን ተመልከት)
14. (ሀ) በመንፈስ ቅዱስ ስም መጠመቅ ሲባል ምን ማለት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።) (ለ) ቅቡዓን ክርስቲያኖች የሚጠመቋቸው ሌሎች ጥምቀቶች የትኞቹ ናቸው? (“ቅቡዓን ክርስቲያኖች የሚጠመቋቸው ጥምቀቶች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)
14 በመንፈስ ቅዱስ ስም። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መንፈስ ቅዱስ የሚያስተምረውን እውነት እንቀበላለን። መንፈስ ቅዱስ ራሱን የቻለ አካል ወይም የሥላሴ ክፍል አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ በሥራ ላይ ያለ የአምላክ ኃይል ነው። መንፈስ ቅዱስ ነቢያትንና የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎችን እንደመራቸው ስለምናምን መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረን እናነባለን፤ እንዲሁም ትምህርቶቹን እንከተላለን። (2 ጴጥ. 1:20, 21) በተጨማሪም ከባድ ኃጢአት ከመሥራት እንቆጠባለን፤ ምክንያቱም እንዲህ ያለው ድርጊት የአምላክ መንፈስ ከእኛ እንዲርቅ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ መንፈሱ በጉባኤው ውስጥ በነፃነት እንዳይሠራ እንቅፋት ሊሆን ይችላል።—ኤፌ. 4:30
ከተጠመቅክ በኋላ መንፈስ ቅዱስ ለሚጫወተው ሚና እውቅና መስጠትህን ቀጥል (አንቀጽ 14ን ተመልከት)
15. ቁርጥ ውሳኔያችን ምን መሆን አለበት?
15 የተጠመቅክ ክርስቲያን ከሆንክ “ስለ ጥምቀቶች” የሚገልጸውን ትምህርትc ሙሉ በሙሉ ለመረዳት እንዲሁም ራስህን ስትወስንና ስትጠመቅ ለይሖዋ የገባኸውን ቃል ጠብቀህ ለመኖር ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። ይሁንና እስካሁን ካልተጠመቅክስ? ይህን ውሳኔ እንዳታደርግ እንቅፋት የሆነብህ ነገር ይኖር ይሆን? የሚቀጥለው ርዕስ ወደ ጥምቀት የሚያደርሱህን እርምጃዎች መውሰድ የምትችለው እንዴት እንደሆነ ያብራራል።
መዝሙር 161 ፈቃድህን ማድረግ ያስደስተኛል
a “መጠመቅ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “መጥለቅ” ወይም “መነከር” የሚል ትርጉም አለው። ስለዚህ መጠመቅ የሚያመለክተው አንዳንድ ሃይማኖቶች እንደሚያስተምሩት ውኃ መረጨትን ሳይሆን ሙሉ በሙሉ ውኃ ውስጥ መጥለቅን ነው።
b በኤፌሶን የነበሩት እነዚያ ሰዎች የተጠመቁት “የዮሐንስን ጥምቀት” ነበር። (ሥራ 19:3) መጥምቁ ዮሐንስ፣ አይሁዳውያን የሙሴን ሕግ በመጣስ ለሠሩት ኃጢአት ንስሐ እንዲገቡ ያሳስብ ነበር፤ ከዚያም ለማሳሰቢያው ምላሽ የሰጡትን አጥምቋቸዋል። (ማር. 1:4, 5) ሆኖም የሙሴ ሕግ ካበቃ በኋላ ይሖዋ ይህን ጥምቀት መቀበሉን አቆመ። ከዚያ ወዲህ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው “አንድ ጥምቀት” ብቻ ነው፤ ይህ ጥምቀት ወደ መዳን ይመራል።—ኤፌ. 4:5
c “የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው” በሚለው ዓምድ ሥር የወጣውን “ጥምቀት ምንድን ነው?” የሚለውን ርዕስ jw.org እና JW ላይብረሪ ላይ ተመልከት።
d የሥዕሉ መግለጫ፦ በወረዳ ስብሰባ ላይ የጥምቀት ዕጩዎች ተነስተው እምነታቸውን በይፋ ሲናገሩ።