የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች
© 2026 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
ከግንቦት 4-10
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት ኢሳይያስ 58–59
የይሖዋን የተትረፈረፈ በረከት ማግኘት የምንችልባቸው መንገዶች
“ሕግህን ምንኛ ወደድሁ!”
9 በአሁኑ ጊዜ የአምላክ ሕዝቦች ቃል በቃል የ24 ሰዓት የሰንበት እረፍት እንዲያደርጉ አይጠበቅባቸውም፤ ሆኖም ሰንበት እንዲሁ ያለፈ ታሪክ ብቻ አይደለም። (ቈላስይስ 2:16) እኛም ብንሆን መንፈሳዊ ጉዳዮችን ማስቀደም እንዳለብን የሚያሳስብ ሕግ አይደለም? ቁሳዊ ነገሮችን ለማካበት መሯሯጥ ወይም መዝናናት ከአምልኮታችን ጋር የተያያዙ እንቅስቃሴዎችን ከማከናወን መቅደም የለባቸውም። (ዕብራውያን 4:9, 10) ስለዚህ ራሳችንን እንዲህ እያልን መጠየቅ እንችላለን፦ “በሕይወቴ ውስጥ የማስቀድመው ነገር ምንድን ነው? ለጥናት፣ ለጸሎት፣ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘትና የመንግሥቱን ምሥራች በመስበኩ ሥራ ለመካፈል ቅድሚያውን እሰጣለሁ? ወይስ ሌሎች ጉዳዮች እንዲህ ላሉት እንቅስቃሴዎች ጊዜ አሳጥተውኛል?” መንፈሳዊ ጉዳዮችን የምናስቀድም ከሆነ ለመኖር የሚያስፈልጉንን ነገሮች እንደማናጣ ይሖዋ አረጋግጦልናል።—ማቴዎስ 6:24-33
ምንም ነገር ከይሖዋ እንዲያርቃችሁ አትፍቀዱ
5 ሥራ እየፈለግህ ነው እንበል። የምትኖረው ሥራ ማግኘት አስቸጋሪ በሆነበት አገር ውስጥ ከሆነ መጀመሪያ የምታገኘውን ማንኛውንም ሥራ ዓይንህን ሳታሽ ለመቀበል ትፈተናለህ? የሥራው ዓይነት ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚጋጭ ቢሆንስ? የሥራው ጸባይ ብዙ ሰዓት እንድትሠራ ወይም እንድትጓዝ የሚጠይቅ በመሆኑ ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎችህን የሚያስተጓጉልብህ ወይም ከቤተሰብህ የሚያርቅህ ቢሆንስ? ሥራ አጥቶ ከመቀመጥ ይሻላል በሚል የማይሆን ሥራ ትይዛለህ? የተሳሳተ ጎዳና መከተል ከይሖዋ እንደሚያርቅህ አትዘንጋ። (ዕብ. 2:1) ሥራ ለመቀጠርም ሆነ ሥራ ለመቀየር እያሰብክ ከሆነ ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?
6 ቀደም ሲል እንደተገለጸው መድረሻህን በአእምሮህ መያዝህ ጠቃሚ ነው። ‘ይህ ሥራ እንዲያደርሰኝ የምፈልገው የት ነው?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። ሰብዓዊ ሥራን የምትመለከተው ግብህ ላይ ለመድረስ ይኸውም ራስህንና ቤተሰብህን እያስተዳደርክ ይሖዋን ለማገልገል እንደሚያስችል ነገር አድርገህ ከሆነ ይሖዋ ጥረትህን ይባርከዋል። (ማቴ. 6:33) ሥራህን ብታጣ ወይም ድንገተኛ የገንዘብ ችግር ቢያጋጥምህ ይሖዋ ዝም ብሎ እንደማይመለከትህ አስታውስ። (ኢሳ. 59:1) ይሖዋ ለእሱ “ያደሩ ሰዎችን ከፈተና እንዴት እንደሚያድን” ያውቃል።—2 ጴጥ. 2:9
ግብዝነታቸው ተጋለጠ!
6 ሕዝቡ በአንድ በኩል እየጾሙ፣ ለታይታ የሚደረግ ጽድቅ እየሠሩና አልፎ ተርፎም የይሖዋን የጽድቅ ፍርድ እየጠየቁ በሌላ በኩል የራሳቸውን ተድላና ቁሳዊ ጥቅም ያሳድዱ ነበር። ድርጊታቸው ሁሉ ጠብ፣ ግፍና አመፅ የሞላበት ነበር። ይህን ምግባራቸውን ለመሸፋፈን ሲሉ ለታይታ የሚደረጉ የሐዘን መግለጫዎችን በመፈጸም ማለትም ራሳቸውን እንደ እንግጫ ዝቅ በማድረግና ማቅ ለብሰው አመድ ላይ በመቀመጥ ከኃጢአታቸው ንስሐ እንደገቡ ለማስመሰል ይሞክራሉ። ይሁንና ከአመፅ ድርጊታቸው ካልተመለሱ ይህ ሁሉ ምን ፋይዳ ይኖረዋል? ከእውነተኛ ጾም ጋር ሊታይ የሚገባውን አምላክ የሚፈልገውን ዓይነት ጸጸትና የንስሐ ፍሬ አላሳዩም። ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ዋይታቸውን ቢያቀልጡትም በሰማይ ተሰሚነት አላገኙም።
8 ይሖዋ ሕዝቡ ለሠሩት ኃጢአት እንዲጾሙ ብቻ ሳይሆን ንስሐ እንዲገቡም ይፈልጋል። እንዲህ ካደረጉ ሞገሱን ያገኛሉ። (ሕዝቅኤል 18:23, 32) ይሖዋ አንድ ሰው መጾሙ ዋጋ ሊኖረው የሚችለው ቀደም ሲል የፈጸማቸውን የኃጢአት ድርጊቶች እስከተወ ድረስ ብቻ እንደሆነ ገልጿል። ይሖዋ በመቀጠል ያቀረባቸውን እውነተኛ ዝንባሌን ለመመርመር የሚያስችሉ ጥያቄዎች ተመልከት፦ “እኔስ የመረጥሁት ጾም ይህ አይደለምን? የበደልን እስራት [“ሰንሰለት፣” አ.መ.ት] ትፈቱ ዘንድ፣ የቀንበርንስ ጠፍር ትለቅቁ ዘንድ፣ የተገፉትንስ አርነት ትሰድዱ ዘንድ፣ ቀንበሩንስ ሁሉ ትሰብሩ ዘንድ አይደለምን?”—ኢሳይያስ 58:6
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it “ድብ” አን. 6
ድብ
የተራቡ ድቦች የሚያድኑትን እንስሳ ሲያሸቱ እንስሳውን ለመብላት በመጓጓት የጉርምርምታ ድምፅ ያሰማሉ። በተመሳሳይም ነቢዩ ኢሳይያስ፣ እስራኤላውያን ፍትሕና መዳን ለማግኘት በመጓጓት ‘እንደ ድቦች እንዳጉረመረሙ’ ገልጿል፤ ሆኖም ተስፋቸው ሳይፈጸም በመቅረቱ በተደጋጋሚ ለሐዘን ተዳርገዋል። (ኢሳ 59:11) በተጨማሪም ምስኪን የሆነውን ሕዝቡን የሚያንገላታና የሚጨቁን ክፉ ገዢ ተንደርድሮ ከሚመጣ ድብ ጋር ተመሳስሏል።—ምሳሌ 28:15
ከግንቦት 11-17
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት ኢሳይያስ 60–61
“አንቺ ሴት ሆይ፣ ተነሺ፣ ብርሃን አብሪ”
የአንባቢያን ጥያቄዎች
ኢሳይያስ 60:1 እንዲህ ይላል፦ “አንቺ ሴት ሆይ፣ ተነሺ፣ ብርሃን አብሪ፤ ብርሃንሽ መጥቷልና። የይሖዋ ክብር በአንቺ ላይ ያበራል።” ከአውዱ እንደምንረዳው እዚህ ላይ የተጠቀሰችው “ሴት” ጽዮን ወይም በወቅቱ የይሁዳ ዋና ከተማ የነበረችው ኢየሩሳሌም ነች። (ኢሳ. 60:14፤ 62:1, 2) ይህች ከተማ መላውን ብሔር ትወክላለች። ኢሳይያስ የተናገራቸው ቃላት ሁለት ጥያቄዎችን ያስነሳሉ፦ አንደኛ፣ ኢየሩሳሌም ‘የተነሳችው’ እና መንፈሳዊ ብርሃን ያበራችው መቼና እንዴት ነው? ሁለተኛ፣ ኢሳይያስ የተናገራቸው ቃላት በዘመናችን በላቀ ሁኔታ ፍጻሜያቸውን እያገኙ ነው?
ኢየሩሳሌም ‘የተነሳችው’ እና መንፈሳዊ ብርሃን ያበራችው መቼና እንዴት ነው? አይሁዳውያን በባቢሎን በግዞት በነበሩባቸው 70 ዓመታት ውስጥ ኢየሩሳሌምና ቤተ መቅደሷ ፈራርሰው ቆይተዋል። ባቢሎን በሜዶናውያንና በፋርሳውያን እጅ ከወደቀች በኋላ ግን በመላው የባቢሎን ግዛት የሚኖሩት እስራኤላውያን ወደ አገራቸው ተመልሰው እውነተኛውን አምልኮ ዳግመኛ እንዲያቋቁሙ ተፈቀደላቸው። (ዕዝራ 1:1-4) ከ537 ዓ.ዓ. አንስቶ ከ12ቱም ነገዶች የተውጣጡ ታማኝ ቀሪዎች ይህን አድርገዋል። (ኢሳ. 60:4) ለይሖዋ መሥዋዕቶችን ማቅረብ፣ በዓላትን ማክበር እንዲሁም ቤተ መቅደሱን መልሰው መገንባት ጀመሩ። (ዕዝራ 3:1-4, 7-11፤ 6:16-22) የአምላክ ክብር በድጋሚ በኢየሩሳሌም ማለትም መልሰው በተቋቋሙት የአምላክ ሕዝቦች ላይ ማብራት ጀመረ። እነሱም በበኩላቸው፣ በመንፈሳዊ ጨለማ ላይ ለነበሩት ብሔራት የብርሃን ምንጭ ሆነዋል።
የአንባቢያን ጥያቄዎች
ይሁንና ኢሳይያስ የተናገራቸው የተሃድሶ ትንቢቶች በጥንቷ ኢየሩሳሌም ላይ የተፈጸሙት በከፊል ብቻ ነበር። በጥቅሉ ሲታይ፣ እስራኤላውያን አምላክን መታዘዛቸውን አልቀጠሉም። (ነህ. 13:27፤ ሚል. 1:6-8፤ 2:13, 14፤ ማቴ. 15:7-9) እንዲያውም ከጊዜ በኋላ መሲሑን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመቀበል አሻፈረን ብለዋል። (ማቴ. 27:1, 2) በ70 ዓ.ም. ኢየሩሳሌምና ቤተ መቅደሷ ለሁለተኛ ጊዜ ጠፉ።
ይሖዋ ይህ አሳዛኝ ሁኔታ እንደሚከሰት አስቀድሞ ተናግሯል። (ዳን. 9:24-27) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው፣ ይሖዋ በኢሳይያስ ምዕራፍ 60 ላይ የሚገኙት የተሃድሶ ትንቢቶች በምድራዊቷ ኢየሩሳሌም ላይ ሙሉ በሙሉ እንዲፈጸሙ ዓላማው አልነበረም።
የአንባቢያን ጥያቄዎች
ኢሳይያስ የተናገራቸው ቃላት በዘመናችን በላቀ ሁኔታ ፍጻሜያቸውን እያገኙ ነው? አዎ፣ ሆኖም ፍጻሜያቸውን እያገኙ ያሉት ከሌላ ምሳሌያዊት ሴት ማለትም ‘ከላይኛዪቱ ኢየሩሳሌም’ ጋር በተያያዘ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ስለዚህች ሴት ሲናገር “እሷም እናታችን ናት” ብሏል። (ገላ. 4:26) ላይኛዪቱ ኢየሩሳሌም ታማኝ መንፈሳዊ ፍጥረታትን ያቀፈውን የአምላክ ድርጅት ሰማያዊ ክፍል ታመለክታለች። ልጆቿ ኢየሱስንና እንደ ጳውሎስ ሰማያዊ ተስፋ ያላቸውን በመንፈስ የተቀቡ 144,000 ክርስቲያኖች ያካትታሉ። እነዚህ ቅቡዓን ክርስቲያኖች “ቅዱስ ብሔር” ይኸውም ‘የአምላክ እስራኤል’ ናቸው።—1 ጴጥ. 2:9፤ ገላ. 6:16
ላይኛዪቱ ኢየሩሳሌም ‘የተነሳችው’ እና ‘ብርሃን ያበራችው’ እንዴት ነው? በምድር ላይ ባሉት ቅቡዓን ልጆቿ አማካኝነት ነው። እነዚህ ክርስቲያኖች ያጋጠማቸውን ሁኔታ በኢሳይያስ ምዕራፍ 60 ላይ ከሚገኘው ትንቢት ጋር ለማወዳደር እንሞክር።
ቅቡዓን ክርስቲያኖች ‘መነሳት’ ያስፈለጋቸው ከሁለተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. አንስቶ ኢየሱስ በትንቢቱ ላይ በጠቀሰው የክህደት እንክርዳድ ተውጠው በመንፈሳዊ ጨለማ ውስጥ ገብተው ስለነበር ነው። (ማቴ. 13:37-43) በዚህ መንገድ፣ በዓለም ላይ ያሉትን የሐሰት ሃይማኖቶች በሙሉ በምታመለክተው በታላቂቱ ባቢሎን ግዞት ሥር ወደቁ። ቅቡዓኑ ‘እስከዚህ ሥርዓት መደምደሚያ’ ድረስ በግዞት ቆይተዋል፤ ይህ ጊዜ የጀመረው በ1914 ነው። (ማቴ. 13:39, 40) ከዚያ ብዙም ሳይቆይ በ1919 ነፃ ወጡ፤ ወዲያውኑም በስብከቱ ሥራ በመጠመድ መንፈሳዊ ብርሃን ማብራት ጀመሩ። ባለፉት ዓመታት፣ በኢሳይያስ 60:3 ላይ የተጠቀሱትን “ነገሥታት” ማለትም የአምላክን እስራኤል ቀሪዎች ጨምሮ ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ሰዎች ወደዚህ ብርሃን መጥተዋል።—ራእይ 5:9, 10
ወደፊት ቅቡዓን ክርስቲያኖች የይሖዋን ብርሃን ከዚህም በላቀ ሁኔታ ያንጸባርቃሉ። በምን መንገድ? ምድራዊ ሕይወታቸውን ሲያጠናቅቁ የክርስቶስ ሙሽራ የሆነችው ‘የአዲሲቱ ኢየሩሳሌም’ ክፍል ይሆናሉ፤ “አዲሲቱ ኢየሩሳሌም” ከክርስቶስ ጋር አብረው ነገሥታትና ካህናት የሚሆኑትን 144,000 ቅቡዓን ታመለክታለች።—ራእይ 14:1፤ 21:1, 2, 24፤ 22:3-5
አዲሲቱ ኢየሩሳሌም በኢሳይያስ 60:1 ፍጻሜ ረገድ ቁልፍ ሚና ትጫወታለች። (ኢሳይያስ 60:1, 3, 5, 11, 19, 20ን ከራእይ 21:2, 9-11, 22-26 ጋር አወዳድር።) ምድራዊቷ ኢየሩሳሌም የጥንቷ እስራኤል መንግሥት መቀመጫ እንደነበረች ሁሉ አዲሱን ሥርዓት የሚያስተዳድረው መንግሥት ክርስቶስንና አዲሲቱን ኢየሩሳሌም ያቀፈ ነው። አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ‘ከሰማይ ከአምላክ ዘንድ የምትወርደው’ እንዴት ነው? ትኩረቷን ወደ ምድር በማዞር ነው። ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሰዎች “በእሷ ብርሃን ይጓዛሉ።” እነዚህ ሰዎች ከኃጢአትና ከሞትም ጭምር ነፃ ይወጣሉ። (ራእይ 21:3, 4, 24) በውጤቱም ኢሳይያስና ሌሎቹ ነቢያት እንደተነበዩት ‘ሁሉም ነገሮች ሙሉ በሙሉ ይታደሳሉ።’ (ሥራ 3:21) ይህ ታላቅ ተሃድሶ የጀመረው ክርስቶስ ንጉሥ በሆነበት ወቅት ሲሆን የሚጠናቀቀው ደግሞ በሺህ ዓመት ግዛቱ መጨረሻ ላይ ነው።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
ይሖዋ ነፃ የምንወጣበት ዝግጅት አድርጎልናል
10 የአምላክ ልጅ የመጣው ሰዎች ከሁለት ነገሮች ነፃ እንዲወጡ ለመርዳት ነው። አንደኛ፣ የሃይማኖት መሪዎቹ ከሚያስተምሯቸው በሕዝቡ ላይ ጫና የሚያሳድሩ ትምህርቶች ነፃ መውጣት የሚቻልበትን መንገድ ከፍቷል። በዚያ ዘመን የነበሩ በርካታ አይሁዳውያን በተለያዩ ወጎችና በተሳሳቱ እምነቶች ባርነት ሥር ነበሩ። (ማቴ. 5:31-37፤ 15:1-11) መንፈሳዊ መመሪያ እንዲሰጡ የሚጠበቅባቸው ሰዎች ደግሞ ታውረው ነበር ማለት ይቻላል። መሲሑንና እሱ ያስገኘውን መንፈሳዊ ብርሃን ለመቀበል ፈቃደኞች ባለመሆናቸው በጨለማ ውስጥ እንዲሁም በኃጢአት ባርነት ሥር ለመኖር መርጠዋል። (ዮሐ. 9:1, 14-16, 35-41) ኢየሱስ ግን ትክክለኛ ትምህርቶችን በማስተማርና ጥሩ ምሳሌ በመተው፣ መንፈሳዊ ነፃነት የሚገኝበትን መንገድ ለቅኖች አሳውቋል።—ማር. 1:22፤ 2:23 እስከ 3:5
11 ሁለተኛ፣ ኢየሱስ የሰው ልጆች ከአዳም የወረሱት ኃጢአት ካስከተለባቸው ባርነት ነፃ መውጣት የሚችሉበትን መንገድ ከፍቷል። የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ስለተከፈለ አምላክ፣ እምነት ያላቸውንና እሱ ያዘጋጀውን ቤዛ የሚቀበሉ ሰዎችን ኃጢአት ይቅር ማለት ይችላል። (ዕብ. 10:12-18) ኢየሱስ “ወልድ ነፃ ካወጣችሁ፣ በእርግጥ ነፃ ትሆናላችሁ” ብሏል። (ዮሐ. 8:36) ይህ ነፃነት በእስራኤል ይከበር የነበረው የኢዮቤልዩ ዓመት ከሚያስገኘው ነፃነት እጅግ የላቀ እንደሆነ ጥርጥር የለውም! አንድ ምሳሌ እንውሰድ፦ በኢዮቤልዩ አማካኝነት ከባርነት ነፃ የወጣ ሰው መልሶ ባሪያ ሊሆን ይችላል፤ ደግሞም ይህ ሰው ከሞት ባርነት ማምለጥ አይችልም።
ከግንቦት 18-24
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት ኢሳይያስ 62–64
አፍቃሪና ሩኅሩኅ የሆነው ሸክላ ሠሪ
‘ከአንጀት የሚራራልን አምላካችን’
7 ይሖዋ ለእስራኤል ሕዝብ ያደረገው ነገር ርኅራኄውን በግልጽ የሚያሳይ ነው። በ16ኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. ማብቂያ አካባቢ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ እስራኤላውያን በግብፅ በባርነት ይኖሩ ነበር፤ በዚያ ከባድ ጭቆና ይደርስባቸው ነበር። ግብፃውያን “የሸክላ ጭቃ በማስቦካት፣ ጡብ በማሠራትና . . . ማንኛውንም ዓይነት የባርነት ሥራ እንዲሠሩ በማድረግ ሕይወታቸውን መራራ [አድርገውባቸው]” ነበር። (ዘፀአት 1:11, 14) እስራኤላውያን ሥቃዩ ሲበዛባቸው እርዳታ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ጮኹ። ታዲያ ሩኅሩኅ የሆነው አምላክ ምላሽ የሰጠው እንዴት ነበር?
8 ይሖዋ በእጅጉ አዘነላቸው። እንዲህ ሲል ተናገረ፦ “በግብፅ የሚኖረውን የሕዝቤን መከራ በእርግጥ አይቻለሁ፤ አስገድደው በሚያሠሯቸው ሰዎች የተነሳ የሚያሰሙትን ጩኸት ሰምቻለሁ፤ እየደረሰባቸው ያለውንም ሥቃይ በሚገባ አውቃለሁ።” (ዘፀአት 3:7) ይሖዋ በሕዝቦቹ ላይ የሚደርሰውን ሥቃይ ሲያይ ወይም ጩኸታቸውን ሲሰማ አንጀቱ አልቻለም። በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 24 ላይ እንዳየነው ይሖዋ የሌላውን ችግር እንደ ራሱ የሚያይ አዛኝ አምላክ ነው። የሕዝቡን ሥቃይ እንደ ራሱ ሥቃይ አድርጎ መመልከቱ እንዲራራ አድርጎታል። ይሁንና የይሖዋ አዘኔታ በስሜት ብቻ አልተወሰነም፤ ከዚህ ይልቅ እነሱን ለመርዳት እርምጃ ወስዷል። ኢሳይያስ 63:9 “በፍቅሩና በርኅራኄው ተቤዣቸው” ይላል። ይሖዋ እስራኤላውያንን “በብርቱ እጅ” ከግብፅ ነፃ አወጣቸው። (ዘዳግም 4:34) ከዚያም በተአምር እየመገበ ለም ወደሆነች ምድር አስገባቸው።
9 ይሖዋ ለእስራኤላውያን ያሳየው ርኅራኄ በዚህ ብቻ አላበቃም። እስራኤላውያን ተስፋይቱ ምድር ከገቡ በኋላ በተደጋጋሚ ጊዜያት በአምላክ ላይ በማመፃቸው ለችግር ይዳረጉ ነበር። ሆኖም ይሖዋ ተጸጽተው ወደ እሱ በጮኹ ቁጥር ያድናቸው ነበር። ለምን? ‘ለሕዝቡ ስለራራ ነው።’—2 ዜና መዋዕል 36:15፤ መሳፍንት 2:11-16
አስፈላጊ ሸክሞችን ተሸከሙ፤ የቀረውን ጣሉ
8 የምናደርጋቸው ውሳኔዎች የሚያስከትሉት ውጤት። ይሖዋ ልዩ ስጦታ የሆነውን የመምረጥ ነፃነት ሰጥቶናል፤ ጥሩ ውሳኔዎችን ማድረግ የሚያስገኘውን ደስታ እንድናጣጥምም ይፈልጋል። ሆኖም መጥፎ ውሳኔዎች ከሚያስከትሉት መዘዝ ከለላ አያደርግልንም። (ገላ. 6:7, 8) በዚህም የተነሳ መጥፎ ምርጫ ስናደርግ፣ ያልታሰበበት ቃል ስንናገር እንዲሁም የችኮላ እርምጃ ስንወስድ መዘዙን እንቀበላለን። አንዳንድ ጊዜ ባደረግነው ነገር የተነሳ ሕሊናችን ይረብሸን ይሆናል። ሆኖም ለውሳኔዎቻችን ኃላፊነት መውሰዳችን ኃጢአታችንን እንድንናዘዝ፣ ስህተታችንን እንድናርም እንዲሁም ጥፋቱን ላለመድገም እንድንጠነቀቅ ያነሳሳናል። እንዲህ ያሉ እርምጃዎችን መውሰዳችን በሕይወት ሩጫ ላይ እንድንቀጥል ይረዳናል።
9 ይህን ሸክም መሸከም የምትችለው እንዴት ነው? ያደረግከውን መጥፎ ውሳኔ መቀልበስ ካልቻልክ፣ ያለህበትን ሁኔታ አምነህ ተቀበል። የፈሰሰ ውኃ እንደማይታፈስ አስታውስ። ሰበብ በማቅረብ ወይም ላደረግከው ውሳኔ ራስህንም ሆነ ሌሎችን በመኮነን ጉልበት አታጥፋ። ከዚህ ይልቅ ስህተትህን አምነህ ተቀበል፤ እንዲሁም አሁን ማድረግ በምትችለው ነገር ላይ አተኩር። በሠራኸው ስህተት የተነሳ ሕሊናህ የሚወቅስህ ከሆነ በትሕትና ወደ ይሖዋ ጸልይ፤ ጥፋትህን እመን፤ እንዲሁም ይቅር እንዲልህ ጠይቀው። (መዝ. 25:11፤ 51:3, 4) የበደልካቸው ሰዎች ካሉ ይቅርታ ጠይቅ፤ አስፈላጊ ከሆነ ደግሞ የሽማግሌዎችን እርዳታ ለማግኘት ጥረት አድርግ። (ያዕ. 5:14, 15) ከስህተትህ ተማር፤ ጥፋትህን ላለመድገምም ተጠንቀቅ። እንዲህ ካደረግክ ይሖዋ ምሕረቱን እንደሚያሳይህና የሚያስፈልግህን እርዳታ እንደሚሰጥህ መተማመን ትችላለህ።—መዝ. 103:8-13
ተለውጣችኋል?
15 ኢሳይያስ 64:8ን አንብብ። ነቢዩ ኢሳይያስ የተጠቀመው ዘይቤያዊ አገላለጽ ተግባራዊ ልናደርገው የሚገባ አንድ ነጥብ እንዳለ ያስገነዝበናል። በሸክላ ሠሪ የተመሰለው ይሖዋ እንደ ሸክላ አፈር የምንቆጠረውን እኛን የሚቀርጸን እንዴት ነው? ይሖዋ ይበልጥ ማራኪ እንድንሆን ወይም ጥሩ ቁመና እንዲኖረን በአካላችን ላይ ለውጥ እንደማያደርግ የታወቀ ነው። ይሖዋ አካላዊ ሳይሆን መንፈሳዊ ሥልጠና የምናገኝበትን ዝግጅት አድርጎልናል። ይሖዋ እንዲቀርጸን የምንፈቅድ ከሆነ ውስጣዊ ወይም መንፈሳዊ ለውጥ እናደርጋለን፤ ይህ ደግሞ የዓለምን ተጽዕኖዎች ለመቋቋም ያስችለናል። ታዲያ ይሖዋ የሚቀርጸን እንዴት ነው?
16 ሸክላ ሠሪው ጥሩ የሸክላ ዕቃ ለመሥራት በጣም ምርጥ የሆነ የሸክላ አፈር ይጠቀማል። ከዚህም በተጨማሪ ሊያደርጋቸው የሚገቡ ሁለት ነገሮች አሉ። በመጀመሪያ አፈሩ ከማያስፈልጉ ባዕድ ነገሮች ነፃ እንዲሆን መታጠብ ይኖርበታል። ከዚያም በተገቢው መጠን ውኃ ከተደረገበት በኋላ በደንብ መቦካት አለበት፤ ይህ ደግሞ ተፈላጊውን ቅርጽ እንዲይዝ ይረዳዋል።
17 ውኃው ለሁለት ዓላማ ይኸውም አፈሩን ከማያስፈልጉ ባዕድ ነገሮች ለማንጻትና የተፈለገውን ቅርጽ ለመስጠት በሚያስችል መጠን ጭቃውን ለማቡካት እንደሚያገለግል ልብ በል፤ በዚህ መንገድ የተለያዩ ዕቃዎችን አልፎ ተርፎም ውድ የሆኑ ቁሳቁሶችን መሥራት ይቻላል። የአምላክ ቃልም ቢሆን በሕይወታችን ውስጥ ተመሳሳይ ሚና ይጫወታል። ቃሉ አምላክን ከማወቃችን በፊት የነበረንን አስተሳሰብ እንድናስወግድ የሚረዳን ከመሆኑም ሌላ እንድንለወጥና በእሱ ፊት ውድ ዋጋ ያለን ሰዎች እንድንሆን ያስችለናል። (ኤፌ. 5:26) መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ እንድናነብና የአምላክ ቃል በሚጠናባቸው ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትረን እንድንገኝ ምን ያህል ጊዜ ምክር እንደተሰጠን እስቲ አስበው። እነዚህን ነገሮች እንድናደርግ የምንበረታታው ለምንድን ነው? ምክንያቱም እንዲህ ማድረጋችን በይሖዋ ለመቀረጽ ራሳችንን ማቅረባችንን የሚያሳይ ነው።—መዝ. 1:2፤ ሥራ 17:11፤ ዕብ. 10:24, 25
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
ይሖዋ ለራሱ የከበረ ስም ያደርጋል
18 ይሁን እንጂ የአምላክን ፍቅራዊ ደግነት በፍጹም አላግባብ ልንጠቀምበት አይገባም። ኢሳይያስ በመቀጠል እንዲህ አለ፦ “እነርሱ ግን ዐመፁ ቅዱስ መንፈሱንም አስመረሩ፤ ስለዚህ ተመልሶ ጠላት ሆናቸው፣ እርሱም ተዋጋቸው።” (ኢሳይያስ 63:10) ይሖዋ መሐሪና አሳቢ አምላክ ቢሆንም እንኳ ‘በደለኛውን ሳይቀጣ ዝም ብሎ እንደማይተው’ [አ.መ.ት ] አስጠንቅቋል። (ዘጸአት 34:6, 7) እስራኤላውያን በተደጋጋሚ በአምላክ ላይ በማመፅ ራሳቸውን ለቅጣት ዳርገዋል። ሙሴ እንዲህ ሲል አሳስቧቸው ነበር፦ “አምላክህን እግዚአብሔርን በምድረ በዳ እንዳስቈጣኸው፤ ከግብፅ አገር ከወጣህበት ቀን ጀምሮ ወደዚህ ስፍራ እስከ መጣችሁ ድረስ በእግዚአብሔር ላይ እንዳመፃችሁ . . . አትርሳ።” (ዘዳግም 9:7) የአምላክ መንፈስ የሚያሳድርባቸውን በጎ ተጽዕኖ ለመቀበል አሻፈረን በማለት መንፈሱን አስመርረዋል ወይም አሳዝነዋል። (ኤፌሶን 4:30) ይሖዋ ጠላታቸው እንዲሆን አስገድደውታል።—ዘሌዋውያን 26:17፤ ዘዳግም 28:63
ከግንቦት 25-31
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት ኢሳይያስ 65–66
በመንፈሳዊው ገነት ውስጥ መኖር መታደል ነው!
“ጥሩነቱ ምንኛ ታላቅ ነው!”
12 ኢየሱስ “‘ሰው ከይሖዋ አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በምግብ ብቻ አይኖርም’ ተብሎ ተጽፏል” ሲል ተናግሯል። (ማቴዎስ 4:4) በእርግጥም ይሖዋ ያደረገልን መንፈሳዊ ዝግጅቶች የዘላለም ሕይወት የሚያስገኙልን በመሆናቸው እሱ ከሰጠን ሰብዓዊ ምግብም ይበልጥ ጠቃሚ ናቸው። በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 8 ላይ ይሖዋ ለማደስ በሚጠቀምበት ኃይሉ አማካኝነት በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት መንፈሳዊ ገነት እውን እንዲሆን እንዳደረገ ተመልክተናል። የዚህ መንፈሳዊ ገነት አንዱ ቁልፍ ገጽታ የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ ነው።
14 ስለ ቤተ መቅደሱ የሚገልጸው ራእይ ይሖዋ ንጹሑን አምልኮ መልሶ እንደሚያቋቁም የሚያመለክት ነው። ለይሖዋ የሚቀርበው አምልኮ እንደገና የእሱን የጽድቅ መሥፈርቶች የሚያሟላ ይሆናል። በራእዩ ላይ እንደታየው ወንዝ ሁሉ፣ አምላክ ለዘላለም ሕይወት ያደረገው ዝግጅትም በየጊዜው እየጨመረ ነው። ንጹሕ አምልኮ መልሶ ከተቋቋመበት ከ1919 ጀምሮ ይሖዋ ሕይወት ሰጪ በሆኑ ዝግጅቶች ሕዝቦቹን መባረኩን ቀጥሏል። እንዴት? መጽሐፍ ቅዱሶች፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎች እንዲሁም የጉባኤና ትላልቅ ስብሰባዎች በጣም አስፈላጊ የሆኑ እውነቶች በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች እንዲደርሱ እያደረጉ ነው። ይሖዋ በእነዚህ ዝግጅቶች አማካኝነት ከሁሉ ስለላቀው ስጦታው ማለት ስለ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ለሰዎች በማስተማር ላይ ነው። ይሖዋን ከልብ የሚወዱና የሚፈሩ ሰዎች በፊቱ ንጹሕ አቋም እንዲያገኙና የዘላለም ሕይወት ተስፋ እንዲኖራቸው ያስቻለው ይህ ቤዛዊ መሥዋዕት ነው። በመሆኑም ዓለም በመንፈሳዊ ጠኔ እየተሠቃየ ባለበት በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት የይሖዋ ሕዝቦች የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ በመመገብ ላይ ናቸው።—ኢሳይያስ 65:13
ከመንፈሳዊው ገነት ፈጽሞ አትውጣ
9 ዘና የሚያደርግና የመረጋጋት ስሜት የሚፈጥር። ኢሳይያስ 65:14 ከመንፈሳዊው ገነት ውጭ ለመኖር የሚመርጡ ሰዎች ‘ከልባቸው ሐዘን የተነሳ እንደሚጮኹና መንፈሳቸው ስለተሰበረም ዋይ ዋይ እንደሚሉ’ ይናገራል። ይሁንና በአምላክ ሕዝብ ላይ ሥቃይና ጭንቀት ስላስከተሉት ነገሮችስ ምን ማለት ይቻላል? ወደፊት እነዚህ ነገሮች ‘ይረሳሉ፤ እንዲሁም ከአምላክ ዓይን ይሰወራሉ።’ (ኢሳይያስ 65:16, 17ን አንብብ።) ይሖዋ የሚያጋጥሙንን ችግሮች በሙሉ ያስወግድልናል፤ እነዚህ ትውስታዎች የሚያስከትሉብንም ሥቃይ በጊዜ ሂደት ይጠፋል።
10 በአሁኑ ወቅትም እንኳ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻችን ላይ ስንገኝ ይህ ክፉ ዓለም በሚያሳድርብን ጭንቀት ላይ መብሰልሰል ትተን እንረጋጋለን። የአምላክ መንፈስ ፍሬ ክፍል የሆኑትን ፍቅርን፣ ደስታን፣ ሰላምን፣ ደግነትንና ገርነትን በማንጸባረቅ መንፈሳዊው ገነት ውስጥ ላለው መረጋጋት አስተዋጽኦ እናበረክታለን። (ገላ. 5:22, 23) በአምላክ ድርጅት ውስጥ መታቀፍ እንዴት ያለ በረከት ነው! ከመንፈሳዊው ገነት ሳይወጡ የሚኖሩ ሰዎች፣ አምላክ “አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር” እንደሚፈጥር የገባው ቃል ሙሉ በሙሉ ሲፈጸም የመመልከት አጋጣሚ ያገኛሉ።
ከመንፈሳዊው ገነት ፈጽሞ አትውጣ
13 ሰላም የሰፈነበትና አስተማማኝ። ቀደም ሲል የአውሬ ዓይነት ባሕርይ የነበራቸው ብዙ ሰዎች በይሖዋ መንፈስ እርዳታ በሕይወታቸው ላይ ከፍተኛ ለውጥ ማድረግ ችለዋል። (ኢሳይያስ 65:25ን አንብብ።) የነበሯቸውን መጥፎ ባሕርያት አሸንፈዋል። (ሮም 12:2፤ ኤፌ. 4:22-24) እርግጥ አሁንም ቢሆን እኛ የአምላክ ሕዝቦች ፍጹማን አይደለንም፤ ስለዚህ ስህተት መሥራታችን አይቀርም። ሆኖም ይሖዋ ‘ሁሉንም ዓይነት ሰዎች’ ሊበጠስ በማይችል የፍቅርና የሰላም ሰንሰለት አስተሳስሯል። (ቲቶ 2:11) ይህ ሁሉን ቻዩ አምላክ ብቻ ሊፈጽመው የሚችል ተአምር ነው!
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የእሳት ሐይቅ ምንድን ነው? ገሃነም ነው? ወይስ ሲኦል?
ኢየሱስ ገሃነምን የጠቀሰው ዘላለማዊ ጥፋትን ለማመልከት ነው። (ማቴዎስ 23:33) “በገሃነም ትላቸው አይሞትም፤ እሳቱም አይጠፋም” በማለት ተናግሯል። (ማርቆስ 9:47, 48) ኢየሱስ የተናገረው ይህ ሐሳብ፣ በሄኖም ሸለቆ ያለውን ሁኔታ እንዲሁም በኢሳይያስ 66:24 ላይ የሚገኘውን “ወጥተውም በእኔ ላይ ያመፁትን ሰዎች ሬሳ ያያሉ፤ ትላቸው አይሞትም፤ እሳታቸው አይጠፋም” የሚለውን ትንቢት ያስታውሰናል። በመሆኑም የኢየሱስ ምሳሌ የሚገልጸው መሠቃየትን ሳይሆን ሙሉ በሙሉ መጥፋትን ነው። ትሎቹ እና እሳቱ የሚበሉት ሬሳዎችን እንጂ በሕይወት ያሉ ሰዎችን አይደለም።
ከሰኔ 1-7
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት ኤርምያስ 1–3
“አትፍራ፤ . . . ‘እኔ ከአንተ ጋር ነኝና’ ”
የይሖዋ ንብረት መሆን ጸጋ ነው
7 ይሖዋ ብርታት ለማግኘት በእሱ እስከተማመንን ድረስ የሚያስፈልገንን ማበረታቻ ምንጊዜም ይሰጠናል። ለምሳሌ ያህል፣ ኤርምያስ በተፈጥሮው ደፋር አልነበረም። ይሖዋ ነቢይ አድርጎ ሲሾመው ኤርምያስ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ እንዴት እንደምናገር አላውቅም፤ ገና ሕፃን ልጅ ነኝና” ብሏል። እንዲያውም ከጊዜ በኋላ “ከእንግዲህ የእርሱን ስም አላነሣም” በማለት ተናግሯል። (ኤር. 1:6፤ 20:9) ይሁንና ኤርምያስ ይሖዋ በሰጠው ማበረታቻ ታግዞ ብዙዎች ሊሰሙት የማይፈልጉትን መልእክት ለ40 ዓመታት መስበክ ችሏል። ይሖዋ “ልታደግህና፣ ላድንህም፣ እኔ ከአንተ ጋር ነኝ” በማለት በተደጋጋሚ ጊዜ አበረታቶታል።—ኤር. 1:8, 19፤ 15:20
8 ይሖዋ ሙሴንና ኤርምያስን እንዳበረታታቸው ሁሉ እኛም በዛሬው ጊዜ ከሚገኙት ክርስቲያኖች የሚጠበቀውን ነገር ለማድረግ ስንጥር ይረዳናል። ዋናው ነገር በአምላክ መታመን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር [“በይሖዋ፣” NW] ታመን፤ በራስህ ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን ዕወቅ፤ እርሱም ጐዳናህን ቀና ያደርገዋል።” (ምሳሌ 3:5,6) በይሖዋ እንደምንታመን ማሳየት የምንችለው በቃሉና በጉባኤ አማካኝነት የሚሰጠንን እርዳታ በመቀበል ነው። ይሖዋ አካሄዳችንን እንዲመራልን የምንፈቅድ ከሆነ ለእሱ ታማኝ ከመሆን የሚያግደን ምንም ነገር አይኖርም።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
“ጸንታችሁ ቁሙ፤ አትነቃነቁ”
4 ከጣዖት አምልኮ እንርቃለን፤ ይሖዋን ብቻ እናመልካለን። ይሖዋ እሱን ብቻ እንዲያመልኩ እስራኤላውያንን አዟቸዋል። (ዘዳ. 5:6-10) ኢየሱስም በዲያብሎስ በተፈተነበት ወቅት ልናመልክ የሚገባው ይሖዋን ብቻ እንደሆነ በግልጽ ተናግሯል። (ማቴ. 4:8-10) ስለዚህ ጣዖት አናመልክም። ደግሞም ለየትኛውም ሰው አምልኮ አከል ክብር አንሰጥም፤ የሃይማኖት መሪዎችም ሆኑ ፖለቲከኞች ወይም የስፖርቱና የመዝናኛው ዓለም ኮከቦች ጣዖት እንዲሆኑብን አንፈቅድም። ከይሖዋ ጎን እንቆማለን፤ የምናመልከው ‘ሁሉንም ነገሮች የፈጠረውን’ እሱን ብቻ ነው።—ራእይ 4:11ን አንብብ።
ከሰኔ 8-14
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት ኤርምያስ 4–6
የይሁዳን ሰዎች ካጋጠማቸው መንፈሳዊ ሕመም ተማሩ
ይሖዋን “የሚያውቅ ልብ” አለህ?
8 አምላክ አይሁዳውያን ሊያደርጉት የሚገባውን ነገር በተመለከተ የሰጣቸው ማሳሰቢያ ‘ያልተገረዘ ልብ’ የሚለው አነጋገር ምን ማለት እንደሆነ ፍንጭ ይሰጠናል፦ “እናንተ የይሁዳ ሰዎች፣ የኢየሩሳሌምም ነዋሪዎች . . . የልባችሁንም ሸለፈት አስወግዱ፤ አለዚያ ስለ ሠራችሁት ክፋት፣ ቍጣዬ እንደ እሳት ይንበለበላል።” ይሁንና የሠሩት ክፋት ከየት የመነጨ ነበር? ከውስጥ ይኸውም ከልባቸው የመነጨ ነበር። (ማርቆስ 7:20-23ን አንብብ።) አዎ፣ አምላክ በኤርምያስ አማካኝነት አይሁዳውያኑ መጥፎ ነገር እንዲሠሩ ያነሳሳቸው ምን እንደሆነ በትክክል መርምሮ ደርሶበታል። ልባቸው እልኸኛና ዓመፀኛ ነበር። ውስጣዊ ፍላጎታቸውና አስተሳሰባቸው እሱን አላስደሰተውም። (ኤርምያስ 5:23, 24፤ 7:24-26ን አንብብ።) አምላክ “ለእግዚአብሔር ተገረዙ፤ የልባችሁንም ሸለፈት አስወግዱ” ብሏቸዋል።—ኤር. 4:4፤ 18:11, 12
9 በመሆኑም በሙሴ ጊዜ እንደነበሩት እስራኤላውያን ሁሉ በኤርምያስ ዘመን የነበሩት አይሁዳውያንም ምሳሌያዊ የልብ ቀዶ ሕክምና ማድረግ ይኸውም ‘ልባቸውን መገረዝ’ አስፈልጓቸው ነበር። (ዘዳ. 10:16፤ 30:6) ‘የልባቸውን ሸለፈት መግረዝ’ ሲባል ልባቸው ደንዳና እንዲሆን ያደረገውን ነገር ይኸውም ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚቃረነውን አስተሳሰባቸውን፣ ፍላጎታቸውን ወይም ዝንባሌያቸውን ማስወገድ ማለት ነው።—ሥራ 7:51
jr 114 አን. 2
በየዕለቱ “ይሖዋ የት አለ?” ብለህ ትጠይቃለህ?
2 ይሁንና የይሁዳ ሰዎች የሚፈልጉት ምንም ችግር እንደሌለባቸው የሚነግሯቸውን የሃይማኖት መሪዎቻቸውን መስማት ነበር፤ ይሖዋ ስለ ምግባራቸው ያለውን አመለካከት የማወቅ እውነተኛ ፍላጎት አልነበራቸውም። (ኤር 5:31፤ 6:14) ያሉባቸውን ከባድ የጤና ችግሮች ችላ በማለት የሚያጽናና ነገር የሚነግራቸው ሐኪም ከሚፈልጉ ሕመምተኞች ጋር ሊመሳሰሉ ይችላሉ። በጠና ብንታመም ቶሎ መታከም እንድንችል በሽታው በትክክል እንዲታወቅልን እንደምንፈልግ ምንም ጥያቄ የለውም። በተመሳሳይም፣ በኤርምያስ ዘመን የነበሩት አይሁዳውያን መንፈሳዊ ሕመማቸውን በትክክል የሚነግራቸው ለማግኘት ጥረት ማድረግ ነበረባቸው። “ይሖዋ የት አለ?” ብለው መጠየቅ ነበረባቸው።—ኤር. 2:6, 8
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የኤርምያስ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
4:10፤ 15:18—ይሖዋ ዓመጸኛ የሆኑትን ሕዝቦቹን ያታለላቸው በምን መንገድ ነው? በኤርምያስ ዘመን ‘የሐሰት ትንቢት የሚናገሩ’ ነቢያት ነበሩ። (ኤርምያስ 5:31፤ 20:6፤ 23:16, 17, 25-28, 32) ይሖዋ እነዚህን የሐሰት ነቢያት አሳሳች የሆኑ መልእክቶች እንዳይናገሩ አልከለከላቸውም።
ከሰኔ 15-21
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት ኤርምያስ 7–8
ለይሖዋ ቤተ መቅደስ ንቀት አሳይተዋል
jr 21 አን. 12
“በዘመኑ መጨረሻ” ይሖዋን ማገልገል
12 በኢዮዓቄም ግዛት መጀመሪያ ላይ ይሖዋ ኤርምያስን ወደ ቤተ መቅደሱ ሄዶ አይሁዳውያንን ለክፋታቸው አጥብቆ እንዲያወግዛቸው ነገረው። እነዚህ አይሁዳውያን የይሖዋ ቤተ መቅደስ በመካከላቸው በመኖሩ ብቻ ተአምራዊ ጥበቃ እንደሚያገኙ ተሰምቷቸው ነበር። ሆኖም ‘መስረቃቸውን፣ መግደላቸውን፣ ማመንዘራቸውን፣ በሐሰት መማላቸውን፣ ለባአል መሥዋዕት ማቅረባቸውንና የማያውቋቸውን አማልክት መከተላቸውን’ ካላቆሙ ይሖዋ ቤተ መቅደሱን እንደሚተወው ተነግሯቸዋል። በሊቀ ካህናቱ ኤሊ ዘመን ይሖዋ የማደሪያ ድንኳኑን እንደተወው ሁሉ በቤተ መቅደሱ ውስጥ አምልኮ የሚያቀርቡትን ግብዞችም ይተዋቸዋል። የይሁዳ ምድር “የፍርስራሽ ክምር ትሆናለች።” (ኤር. 7:1-15, 34፤ 26:1-6) ኤርምያስ ይህን መልእክት ለማወጅ ምን ያህል ድፍረት ጠይቆበት ሊሆን እንደሚችል አስበው! ይህን ያደረገው ታዋቂ በሆኑና በተከበሩ ሰዎች ፊት ሳይሆን አይቀርም። በዛሬው ጊዜም አንዳንድ ወንድሞችና እህቶች መንገድ ላይ መስበክ ወይም ሀብታምና ታዋቂ ለሆኑ ሰዎች መመሥከር ድፍረት ይጠይቅባቸዋል። ሆኖም ይሖዋ ኤርምያስን እንደረዳው ሁሉ እኛንም እንደሚረዳን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ዕብ. 10:39፤ 13:6
it “ይሖዋ” አን. 78
ይሖዋ
በእስራኤል ብሔር ታሪክ በሙሉ ይሖዋ የስሙ ቅድስና ያለውን አስፈላጊነት ሕዝቡ ምንጊዜም እንዲያስታውሱ ያደርግ ነበር። የጽዮን ተራራ የሚገኝባት የኢየሩሳሌም ከተማ የብሔሩ መዲና ነበረች፤ ይሖዋ ‘ስሙን ሊያጸናባትና ማደሪያ ስፍራው ሊያደርጋት’ የመረጣት ይቺን ከተማ ነው። (ዘዳ 12:5, 11፤ 14:24, 25፤ ኢሳ 18:7፤ ኤር 3:17) ኢየሩሳሌም ውስጥ የተገነባው ቤተ መቅደስ ‘ለይሖዋ ስም የተሠራ ቤት’ ነበር። (1ዜና 29:13-16፤ 1ነገ 8:15-21, 41-43) በቤተ መቅደሱና በኢየሩሳሌም ውስጥ የሚፈጸመው ማንኛውም ጥሩም ሆነ መጥፎ ድርጊት የይሖዋን ስም ይነካዋል፤ ይሖዋም ትኩረት ሰጥቶ ይመለከተዋል። (1ነገ 8:29፤ 9:3፤ 2ነገ 21:4-7) በዚህ ቦታ የይሖዋ ስም ከተሰደበ ይሖዋ ከተማዋ እንድትጠፋ ያደርጋል፤ ቤተ መቅደሱንም ይተወዋል። (1ነገ 9:6-8፤ ኤር 25:29፤ 7:8-15፤ ኢየሱስ ማቴ 21:12, 13፤ 23:38 ላይ ከተናገረውና ካደረገው ነገር ጋር አወዳድር።) ኤርምያስና ዳንኤል ሕዝባቸውንና ከተማዋን አስመልክቶ ሲጸልዩ ይሖዋ ‘ለራሱ ስም ሲል’ ምሕረት እንዲያደርግላቸውና እንዲረዳቸው የለመኑት ከእነዚህ ነጥቦች አንጻር ነው።—ኤር 14:9፤ ዳን 9:15-19
ይሖዋን እንደምንወደው ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
17 በሳሙኤል ዘመን በአንድ ወቅት እስራኤላውያን ከፍልስጥኤማውያን ጋር ባደረጉት ውጊያ ከባድ ሽንፈት ደርሶባቸው ነበር። በዚህ ጊዜ አምላክ እንዲረዳቸውና እንዲጠብቃቸው ፈልገው ነበር። ታዲያ ምን አደረጉ? “አብሮን እንዲሆንና ከጠላቶቻችን እጅ እንዲያድነን የይሖዋን የቃል ኪዳን ታቦት ከሴሎ ይዘነው እንሂድ” አሉ። ውጤቱስ ምን ሆነ? “በጣም ብዙ ሕዝብ አለቀ፤ ከእስራኤላውያንም ወገን 30,000 እግረኛ ወታደር ሞተ። የአምላክም ታቦት ተማረከ።” (1 ሳሙ. 4:2-4, 10, 11) እስራኤላውያን ታቦቱን ይዘው መሄዳቸው ይሖዋ እንዲረዳቸው የፈለጉ ሊመስል ይችላል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን የይሖዋን መመሪያ ለማግኘት ጥረት አላደረጉም፤ ከዚህ ይልቅ በራሳቸው አመለካከት በመመራታቸው ለከፋ ጥፋት ተዳርገዋል።—ምሳሌ 14:12ን አንብብ።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
ፍጥረትን በማየት ስለ ይሖዋ ይበልጥ ተማሩ
6 ይሖዋ የጊዜ ሰሌዳ አለው። እስራኤላውያን በየዓመቱ ከየካቲት መጨረሻ አንስቶ እስከ ግንቦት አጋማሽ ድረስ ራዛዎች ወደ ሰሜን ሲፈልሱ የማየት አጋጣሚ ነበራቸው። አምላክ “በሰማይ የምትበረው ራዛ . . . ወቅቷን ታውቃለች” በማለት ለእስራኤላውያን ነግሯቸዋል። (ኤር. 8:7) ይሖዋ ለእነዚህ ወፎች የሚፈልሱበት ጊዜ እንደመደበላቸው ሁሉ ፍርዱን የሚያስፈጽምበትንም ጊዜ መድቧል። በዛሬው ጊዜ የሚፈልሱ ወፎችን ስንመለከት ይሖዋ ይህን ክፉ ዓለም ለማጥፋት ‘የወሰነው ጊዜ’ እንዳለ መተማመን እንችላለን።—ዕን. 2:3
ከሰኔ 22-28
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት ኤርምያስ 9–10
የምትኩራሩት በምንድን ነው?
ከሚገባው በላይ ስለ ራሳችሁ በማሰብ ራሳችሁን ከፍ አድርጋችሁ አትመልከቱ
13 በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የወጡ ነገሮችን በማየት ብዙ ጊዜ የሚያሳልፉ ሰዎች ለብቸኝነትና ለመንፈስ ጭንቀት ሊዳረጉ እንደሚችሉ አንዳንድ ጥናቶች ያሳያሉ። ይህ የሚሆነው ለምንድን ነው? አንዱ ምክንያት ብዙ ሰዎች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚያወጡት፣ ለየት ያሉ የሕይወት እንቅስቃሴዎቻቸውን የሚያሳዩ ፎቶግራፎችን ስለሆነ ነው፤ የራሳቸውንና የጓደኞቻቸውን ቆንጆ ፎቶግራፍ ወይም የጎበኟቸውን አስገራሚ ቦታዎች የሚያሳዩ ፎቶግራፎችን ብቻ መርጠው ያወጣሉ። እነዚህን ፎቶግራፎች የሚያይ ሰው የእሱ ሕይወት ከእነዚህ ሰዎች ሕይወት ጋር ሲነጻጸር አስደሳች እንዳልሆነ እንዲያውም አሰልቺ እንደሆነ ሊሰማው ይችላል። አንዲት የ19 ዓመት እህታችን “ቅዳሜና እሁድ ስልችት ብሎኝ ቤቴ ቁጭ ብዬ ሌሎች ግን አስደሳች ጊዜ እያሳለፉ እንደሆነ ሳይ መቅናት ጀመርኩ” ብላለች።
14 እርግጥ ነው፣ ማኅበራዊ ሚዲያን ለጥሩ ዓላማ መጠቀም ይቻላል፤ ለምሳሌ ከቤተሰቦቻችንና ከጓደኞቻችን ጋር ለመገናኘት ልንጠቀምበት እንችላለን። ይሁንና ሰዎች ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ አንዳንድ ነገሮችን የሚያወጡት የሌሎችን አድናቆት ለማትረፍ ብቻ እንደሆነ አስተውለሃል? “እዩኝ! እዩኝ!” የሚል መልእክት ማስተላለፍ የፈለጉ ይመስላል። ሌሎች ደግሞ ራሳቸውም ሆኑ ሌሎች ባወጧቸው ፎቶግራፎች ላይ አክብሮት የጎደለው ወይም የብልግና ሐሳብ ይጽፋሉ። ሆኖም ክርስቲያኖች ትሕትናና የሌሎችን ስሜት የመረዳት ባሕርይ እንዲያዳብሩ የተበረታቱ ከመሆኑ አንጻር እንዲህ ማድረጋቸው ተገቢ አይደለም።—1 ጴጥሮስ 3:8ን አንብብ።
15 ማኅበራዊ ሚዲያ የምትጠቀም ከሆነ ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘የምጽፋቸው ሐሳቦች ወይም የማወጣቸው ፎቶግራፎችና ቪዲዮዎች ጉራ እየነዛሁ እንዳለ የሚያስመስሉ ናቸው? ሌሎች ሰዎች እንዲቀኑ እያደረግኩ ይሆን?’ መጽሐፍ ቅዱስ “በዓለም ያለው ነገር ሁሉ ይኸውም የሥጋ ምኞት፣ የዓይን አምሮትና ኑሮዬ ይታይልኝ ማለት ከዓለም እንጂ ከአብ የሚመነጭ አይደለም” በማለት ይናገራል። (1 ዮሐ. 2:16) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም “ኑሮዬ ይታይልኝ ማለት” የሚለውን ሐረግ “ተፈላጊ ሰው መስሎ ለመታየት መሞከር” በማለት ተርጉሞታል። ክርስቲያኖች ራሳቸውን ከፍ ከፍ ለማድረግ አይሞክሩም። ከዚህ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ “በመካከላችን የፉክክር መንፈስ በማነሳሳትና አንዳችን ሌላውን በመመቅኘት በከንቱ አንመካ” በማለት የሚሰጠውን ምክር በሥራ ላይ ያውላሉ። (ገላ. 5:26) ትሕትና ማዳበራችን በዓለም ላይ የሚታየው የኩራትና ራስን ከፍ ከፍ የማድረግ መንፈስ እንዳይጋባብን ይረዳናል።
የይሖዋ ስም—ልንሰጠው የሚገባው ቦታ
14 በይሖዋ ስም እንኮራለን። (መዝሙር 105:3ን አንብብ።) ይሖዋ በስሙ ስንኩራራ በጣም ደስ ይለዋል። (ኤር. 9:23, 24፤ 1 ቆሮ. 1:31፤ 2 ቆሮ. 10:17) ‘በይሖዋ መኩራራት’ ሲባል እሱ አምላካችን በመሆኑ መኩራት ማለት ነው። የእሱን ስም ማክበርና ከስሙ ጎን መቆም መቻላችንን እንደ ትልቅ መብት እንቆጥረዋለን። ለሥራ ባልደረቦቻችን፣ አብረውን ለሚማሩ ልጆች፣ ለጎረቤቶቻችን እንዲሁም ለሌሎች ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች መሆናችንን ለመናገር ፈጽሞ ማፈር የለብንም! ዲያብሎስ ስለ ይሖዋ ስም ለሌሎች መናገራችንን እንድናቆም ይፈልጋል። (ኤር. 11:21፤ ራእይ 12:17) እንዲያውም ሰይጣንና እሱ የሚጠቀምባቸው ሐሰተኛ ነቢያት ሰዎች የይሖዋን ስም እንዲረሱ ማድረግ ይፈልጋሉ። (ኤር. 23:26, 27) እኛ ግን ለይሖዋ ስም ያለን ፍቅር “ቀኑን ሙሉ” በስሙ ሐሴት እንድናደርግ ያነሳሳናል።—መዝ. 5:11፤ 89:16
“ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው” ሰዎች ጥሩ ምላሽ ይሰጣሉ
12 ከመጀመሪያ አንስቶ ግባችሁ ጥናቶቻችሁ ይሖዋንና ኢየሱስን እንዲያውቁና ለእነሱ ፍቅር እንዲያዳብሩ መርዳት መሆን አለበት። ይህን የምታደርጉት ጥናቱ በእናንተ ወይም እናንተ ባላችሁ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ላይ ሳይሆን በአምላክ ቃል ላይ እንዲያተኩር በማድረግ ነው። (ሥራ 10:25, 26) ሐዋርያው ጳውሎስ ሰዎችን በሚያስተምርበት ጊዜ በዋነኝነት ያተኮረው ይሖዋ እሱን ለማወቅና ለመውደድ እንዲረዳን ሲል በላከልን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ነበር። (1 ቆሮ. 2:1, 2) በተጨማሪም ጳውሎስ አዳዲስ ደቀ መዛሙርት በወርቅ፣ በብርና በከበሩ ድንጋዮች የተመሰሉ ግሩም ባሕርያትን እንዲያዳብሩ መርዳት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ገልጿል። (1 ቆሮ. 3:11-15) እንዲህ ካሉት ግሩም ባሕርያት መካከል እምነት፣ ጥበብ፣ ጥልቅ ግንዛቤና ይሖዋን መፍራት ይገኙበታል። (መዝ. 19:9, 10፤ ምሳሌ 3:13-15፤ 1 ጴጥ. 1:7) ጥናቶቻችሁ ጠንካራ እምነት እንዲያዳብሩና አፍቃሪ ከሆነው ሰማያዊ አባታቸው ጋር በግለሰብ ደረጃ ዝምድና እንዲመሠርቱ በመርዳት የጳውሎስን ምሳሌ ተከተሉ።—2 ቆሮ. 1:24
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
እረኞች፣ ከሁሉ የላቁትን እረኞች አርዓያ ተከተሉ
12 ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች የሚሰጡት አመራር ምንጊዜም በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስን በሚገባ መጠቀማቸውና በውስጡ የያዘውን ሐሳብ በጥብቅ መከተላቸው በጣም አስፈላጊ ነው። ሽማግሌዎች እንዲህ ማድረጋቸው በሥልጣናቸው አላግባብ ከመጠቀም እንዲቆጠቡ ይረዳቸዋል። መቼም ቢሆን የበታች እረኞች መሆናቸውን መዘንጋት የለባቸውም፤ እያንዳንዱ የጉባኤው አባል ለሚያደርጋቸው ውሳኔዎች በይሖዋና በኢየሱስ ዘንድ ተጠያቂ ነው።—ገላ. 6:5, 7, 8
ከሰኔ 29–ሐምሌ 5
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት ኤርምያስ 11–12
‘ከፈረሶች ጋር መወዳደር’ የምንችለው እንዴት ነው?
ስደት ቢደርስባቸውም ደስተኞች ናቸው
12 በዛሬው ጊዜ የምንገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ብዙውን ጊዜ ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገረውን ምሥራች በቅንዓት ስለምንሰብክ ስደት ይደርስብናል። ጠላቶቻችን “የሰዎችን ሃይማኖት በግድ ያስቀይራሉ” ብለው ይከሱናል፤ ሆኖም ከእኛ በፊት የነበሩ ታማኝ የይሖዋ አምላኪዎች ተመሳሳይ ክስ ይቀርብባቸው እንደነበር እናውቃለን። (ኤርምያስ 11:21፤ 20:8, 11) ከጥንቶቹ ታማኝ ነቢያት ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ የሚደርስብንን ስደት እንደ መብት እንቆጥረዋለን። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “ወንድሞች ሆይ፤ በጌታ ስም የተናገሩትን ነቢያት የመከራና የትዕግሥት ምሳሌ አድርጋችሁ ተመልከቱ። በትዕግሥት የጸኑትን የተባረኩ [“ደስተኞች፣” NW] አድርገን እንደምንቈጥር ታውቃላችሁ” ሲል ጽፏል።—ያዕቆብ 5:10, 11
እንደ ኤርምያስ በንቃት ተጠባበቁ
19 ጊዜው ከመንግሥቱ ሥራ ጋር በተያያዘ ቅንዓታችን የሚቀዘቅዝበት ሳይሆን ኤርምያስ 12:5 ላይ የሚገኘው ጥቅስ ያለውን ትርጉም የምናስተውልበት ነው። (ጥቅሱን አንብብ።) ሁላችንም ጽናት የሚጠይቁ መከራዎች ያጋጥሙናል። እነዚህ የእምነት ፈተናዎች አብረናቸው ከምንሮጥ “እግረኞች” ጋር ሊመሳሰሉ ይችላሉ። ይሁንና ‘ታላቁ መከራ’ እየቀረበ ሲመጣ የሚደርሱብን መከራዎች እየተባባሱ እንደሚሄዱ መጠበቅ እንችላለን። (ማቴ. 24:21) ወደፊት ከሚገጥሙን ይበልጥ አስቸጋሪ የሆኑ ሁኔታዎች ጋር የምናደርገው ትግል “ከፈረሰኞች ጋር” እንደ መወዳደር ሊቆጠር ይችላል። አንድ ሰው በግልቢያ ላይ ካሉ ፈረሶች እኩል በጽናት ለመሮጥ ከፍተኛ ኃይል ይጠይቅበታል። እንግዲያው በአሁኑ ጊዜ የሚደርሱብንን መከራዎች በጽናት መቋቋማችን አስፈላጊ ነው፤ እንዲህ ማድረጋችን የወደፊቱን ጊዜ በጽናት ለመወጣት ሊያዘጋጀን ይችላል።
ለታላቁ መከራ ተዘጋጅተሃል?
15 በብዙዎቹ ጉባኤዎች ውስጥ የተለያየ አስተዳደግና ባሕርይ ያላቸው ወንድሞችና እህቶች ይገኛሉ። ባሏቸው መልካም ባሕርያት ላይ በማተኮር ለሁሉም ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ያለንን ፍቅር ማሳደግ እንችላለን። ቫኔሳ የተባለች በኒው ዚላንድ የምትኖር እህት ምን እንዳደረገች እንመልከት፤ በጉባኤዋ ካሉ አንዳንድ ክርስቲያኖች ጋር መግባባት ተቸግራ ነበር። በኋላ ግን ብዙም የማይጥማት ባሕርይ ካላቸው ክርስቲያኖች ከመራቅ ይልቅ ከእነሱ ጋር ይበልጥ ጊዜ ለማሳለፍ ወሰነች። ይህን ማድረጓ ይሖዋ ለምን እንደሚወዳቸው እንድታስተውል ረድቷታል። እንዲህ ብላለች፦ “ባለቤቴ የወረዳ የበላይ ተመልካች ከሆነ ወዲህ አብዛኛውን ጊዜያችንን የምናሳልፈው የተለያየ ባሕርይ ካላቸው ወንድሞችና እህቶች ጋር ነው። አሁን ከእነሱ ጋር መግባባት አይቸግረኝም። እንዲያውም ልዩነታችንን ወድጄዋለሁ። ይሖዋም እንደሚወደው ይሰማኛል፤ ምክንያቱም እሱን እንዲያመልኩ የፈቀደላቸው ሰዎች ልዩ ልዩ ናቸው።” ሌሎችን በይሖዋ ዓይን በማየት እንደምንወዳቸው እናስመሠክራለን።—2 ቆሮ. 8:24
16 በታላቁ መከራ ወቅት ፍቅር በጣም አስፈላጊ ነገር ይሆናል። መከራው ሲጀምር ጥበቃ ማግኘት የምንችለው የት ነው? ይሖዋ በጥንቷ ባቢሎን ላይ ጥቃት ሲሰነዘር ለሕዝቡ ምን መመሪያ እንደሰጠ እንመልከት፦ “ሕዝቤ ሆይ፣ ሂድ ወደ ውስጠኛው ክፍልህ ግባ፤ በርህንም ከኋላህ ዝጋ። ቁጣው እስኪያልፍ ድረስ ለጥቂት ጊዜ ተሸሸግ።” (ኢሳ. 26:20) እነዚህ ቃላት ታላቁን መከራ ለምንጋፈጥ ክርስቲያኖችም የሚሠሩ ይመስላል። “ውስጠኛው ክፍል” የተባለው ጉባኤዎቻችንን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። በታላቁ መከራ ወቅት ይሖዋ ቃል የገባውን ጥበቃ የምናገኘው ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር አንድነት ካለን ነው። እንግዲያው ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን መቻል ብቻ በቂ አይደለም፤ ከአሁኑ ከልብ ለመዋደድም ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ይህ የሕይወትና የሞት ጉዳይ ነው!
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የጸሎትህን ይዘት ማሻሻል የምትችለው እንዴት ነው?
15 ኤርምያስ 12:1ን አንብብ። በአንድ ወቅት ነቢዩ ኤርምያስ ክፉዎች ሲሳካላቸው በማየቱ ተረብሾ ነበር። እስራኤላውያን ወገኖቹ የሰነዘሩበት ፌዝም ቅስሙን ሰብሮታል። (ኤር. 20:7, 8) እኛም ክፉ ሰዎች ሲሳካላቸው ስናይ ወይም ፌዝ ሲሰነዘርብን የእሱ ዓይነት ስሜት ሊሰማን ይችላል። ኤርምያስ የተሰማውን ቅሬታ ቢገልጽም በአምላክ ፍትሕ ላይ ጥያቄ አላነሳም። ኤርምያስ፣ ይሖዋ ለዓመፀኛ ሕዝቦቹ የሰጣቸውን ተግሣጽ ሲመለከት በአምላክ ፍትሕ ላይ ያለው እምነት ተጠናክሮ መሆን አለበት። (ኤር. 32:19) እኛም በአሁኑ ወቅት የሚያጋጥመንን ማንኛውንም የፍትሕ መጓደል ይሖዋ በተገቢው ጊዜ እንደሚያስተካክልልን በመተማመን የሚሰማንን ቅሬታ በጸሎታችን ላይ በነፃነት መግለጽ እንችላለን።