የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች
© 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
ከመጋቢት 2-8
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት ኢሳይያስ 41-42
“አትፍራ”
አንተንም የሚመለከቱ አጽናኝ ትንቢታዊ ቃላት
10 ይሖዋ 200 ዓመታት ወደፊት አሻግሮ በመመልከት የዓለም መልክ ምን እንደሚመስል ይቃኛል። በቂሮስ የሚመራ ኃያል ሠራዊት ተቃዋሚዎችን ሁሉ ድል እያደረገ በፍጥነት ይገሰግሳል። በደሴቶች ማለትም ርቀው በሚገኙ ቦታዎች የሚኖሩ ሕዝቦች ሳይቀሩ በግስጋሴው ይርዳሉ። በፍርሃት ተውጠው ይሖዋ የቅጣት ፍርድ እንዲያስፈጽም ከምሥራቅ የጠራውን ለመቃወም ግንባር ይፈጥራሉ። አንዳቸው ሌላውን “አይዞህ” በማለት እርስ በርስ ለመበረታታት ይሞክራሉ።
ኢሳይያስ 41:10—“እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ”
“እኔ ከአንተ ጋር ነኝ።” ይሖዋ አገልጋዮቹ መፍራት የሌለባቸው ለምን እንደሆነ ነግሯቸዋል፦ ብቻቸውን አይደሉም። እሱ ያሉበትን ሁኔታ ይመለከታል እንዲሁም ጸሎታቸውን ይሰማል፤ በመሆኑም ልክ ከጎናቸው ያለ ያህል ነው።—መዝሙር 34:15፤ 1 ጴጥሮስ 3:12
“እኔ አምላክህ ነኝ።” ይሖዋ ሕዝቡን አሁንም ቢሆን አምላካቸው እንደሆነና እነሱም አገልጋዮቹ እንደሆኑ በመግለጽ አረጋግቷቸዋል። አምላክ ለእነሱ ሲል እርምጃ እንዳይወስድ ሊያግደው የሚችል ምንም ዓይነት ሁኔታ እንደሌለ እርግጠኞች መሆን ይችላሉ።—መዝሙር 118:6፤ ሮም 8:32፤ ዕብራውያን 13:6
“አበረታሃለሁ፤ አዎ እረዳሃለሁ፤ በጽድቅ ቀኝ እጄ አጥብቄ እይዝሃለሁ።” ይሖዋ ተመሳሳይ ሐሳብ የሚያስተላልፉ ሦስት አገላለጾችን በመጠቀም አገልጋዮቹን እንደሚደግፍ ማረጋገጫ ሰጥቷል። ሕዝቡ እርዳታ ሲያስፈልጋቸው የሚወስደውን እርምጃ በዓይነ ሕሊና ለመሣል የሚያስችል ዘይቤያዊ አነጋገር ተጠቅሟል። አንድ ሰው ከወደቀ አምላክ ቀኝ እጁን ዘርግቶ ያነሳዋል።—ኢሳይያስ 41:13
አምላክ አገልጋዮቹን የሚያበረታታበትና የሚደግፍበት ዋነኛው መንገድ ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። (ኢያሱ 1:8፤ ዕብራውያን 4:12) ለምሳሌ የአምላክ ቃል እንደ ድህነት፣ ሕመም ወይም የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣት ያሉ ፈታኝ ሁኔታዎች ላጋጠሟቸው ሰዎች ጠቃሚ ምክር ይሰጣል። (ምሳሌ 2:6, 7) በተጨማሪም አምላክ ፈተናዎችን ለመቋቋም የሚያስችል ስሜታዊና አእምሯዊ ጥንካሬ ለአገልጋዮቹ ለመስጠት መንፈስ ቅዱሱን ይጠቀማል።—ኢሳይያስ 40:29፤ ሉቃስ 11:13
“አትፍራ። እረዳሃለሁ”
ይህ ሐሳብ የሚያበረታታ አይደለም? ይሖዋ የገባልንን ቃል በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር። ከይሖዋ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዞ መሄድ ደስ የሚል ነገር ቢሆንም ጥቅሱ ላይ የተገለጸው ሁኔታ ይህ እንዳልሆነ ልብ በል። ከይሖዋ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘህ እየሄድክ ቢሆን፣ በቀኝ እጁ የሚይዘው ግራ እጅህን ይሆን ነበር። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ ‘የጽድቅ ቀኝ እጁን’ ዘርግቶ “ቀኝ እጅህን” እንደሚይዝህ ተገልጿል፤ ይሖዋ በሕይወትህ ውስጥ ከገጠመህ አስጨናቂ ሁኔታ ጎትቶ የሚያወጣህ ያህል ነው። ይህን በሚያደርግበት ጊዜም “አትፍራ። እረዳሃለሁ” የሚል ማረጋገጫ ይሰጥሃል።
ይሖዋን የምትመለከተው፣ የሚያስጨንቅ ሁኔታ ሲያጋጥምህ ለእርዳታ እንደሚደርስልህ አፍቃሪ አባትና ወዳጅ አድርገህ ነው? እሱ ስለ አንተ ያስባል፤ ስለ ደህንነትህ ይጨነቃል እንዲሁም ምንጊዜም ሊረዳህ ዝግጁ ነው። መከራ ሲደርስብህ ወይም አስቸጋሪ ሁኔታ ሲያጋጥምህ ይሖዋ የመረጋጋት ስሜት እንዲሰማህ ይፈልጋል፤ ምክንያቱም በጣም ይወድሃል። በእርግጥም ይሖዋ “በጭንቅ ጊዜ ፈጥኖ የሚደርስልን ረዳታችን ነው።”—መዝ. 46:1
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
ታማኝ መሆን ማለት ምን ማለት ነው?
ይሖዋ ወዳጁን አብርሃምን “እኔ ለአንተ ጋሻህ ነኝ” ብሎት ነበር። (ዘፍጥረት 15:1፤ ኢሳይያስ 41:8) ይሖዋ ይህን ተናግሮ ብቻ ዝም አላለም። አብርሃምንም ሆነ ቤተሰቡን ከፈርኦንና ከአቤሜሌክ ጥቃት ጠብቋቸዋል እንዲሁም አድኗቸዋል። ግንባር ፈጥረው ከመጡበት አራት ነገሥታት ሎጥን እንዲያስጥል ረድቶታል። ተስፋ የተሰጠበት ዘር በእነርሱ የዘር ሐረግ በኩል መምጣት እንዲችል ይሖዋ የ100 ዓመቱን አብርሃምንና የ90 ዓመቷን ሣራን ልጅ የመውለድ ችሎታ አድሶላቸዋል። ይሖዋ ከአብርሃም ጋር በራእይ፣ በሕልምና በመላእክት አማካኝነት ዘወትር የሐሳብ ግንኙነት ያደርግ ነበር። እንዲያውም ይሖዋ አብርሃም በሕይወት በነበረበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን ከሞተ ከብዙ ዓመታት በኋላም ታማኝነትን አሳይቶታል። የአብርሃም ዘር የሆኑት እስራኤላውያን አስቸጋሪዎች የነበሩ ቢሆኑም ይሖዋ የገባላቸውን ቃል ለብዙ መቶ ዓመታት ጠብቋል። ይሖዋ ከአብርሃም ጋር የነበረው ግንኙነት ፍቅር በተግባር ሲገለጽ የሚያሳይ የእውነተኛ ታማኝነት ግሩም ምሳሌ ነው።—ዘፍጥረት ከምዕራፍ 12 እስከ 25
ከመጋቢት 9-15
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት ኢሳይያስ 43-44
ሁለት መቶ ዓመታት ቀድሞ የተጻፈ ትንቢት
ፍጻሜያቸውን ያገኙ ትንቢቶች
16 በ539 ከዘአበ ብርቱው የፋርስ ገዥ ቂሮስ በሜዶናውያን ጦር እየታገዘ በከተማይቱ ላይ በዘመተ ጊዜ የባቢሎን የዓለም ኃያልነት አከተመ። ይሁን እንጂ ቂሮስ የገጠመው ነገር ቀላል ነበር ማለት አይደለም። ባቢሎን በጣም ግዙፍ በሆነ ቅጥር ተከብባለች፤ የምትደፈር አትመስልም። ታላቁ የኤፍራጥስ ወንዝም የሚያልፈው በከተማዋ መሀል በመሆኑ ለከተማዋ መከላከያ የማይናቅ አስተዋጽኦ ነበረው።
17 ቂሮስ ይህን ሁኔታ እንዴት እንደተወጣው ሲገልጽ ግሪካዊው ታሪክ ጸሐፊ ሄሮዶተስ እንዲህ ብሏል፦ “የተወሰኑ ወታደሮችን ውኃው ወደ ከተማ በሚገባበት ቦታ ላይ፣ ሌሎቹን ደግሞ ውኃው ከከተማዋ በሚወጣበት ቦታ ካቆመ በኋላ ውኃው ጎድሎ ለመሻገር አመቺ ሲሆን ወዲያው ወንዙን አቋርጠው ወደ ከተማይቱ እንዲዘልቁ ትእዛዝ ሰጠ። . . . የኤፍራጥስንም ወንዝ በቦይ አድርጎ ረግረግ ወደነበረው ጎድጓዳ ስፍራ [በቀድሞው የባቢሎን ገዥ ወደ ተቆፈረ ሰው ሠራሽ ሐይቅ] እንዲፈስ አደረገው። ወንዙ በጣም ስለጎደለ በዚያ መሻገር ቀላል ሊሆን ችሏል። በዚህ ጊዜ ለዚሁ ዓላማ ሲባል በባቢሎን ወንዝ አጠገብ የቀሩት የፋርስ ወታደሮች ውኃው ቀንሶ እስከ ጭን በሚደርሰው ወንዝ አቋርጠው ወደ ከተማይቱ ዘለቁ።”
it “ቂሮስ” አን. 7
ቂሮስ
ባቢሎንን ድል ማድረግ። አሁን ቂሮስ ኃያሏን ባቢሎንን መገዳደር የሚችልበት አቅም ላይ ደረሰ፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜ ላይ ቂሮስን የምናገኘው ከዚህ በኋላ ነው። ኢሳይያስ ኢየሩሳሌምንና ቤተ መቅደሷን አስመልክቶ በመንፈስ መሪነት ባሰፈረው የተሃድሶ ትንቢት ላይ ይህን የፋርስ ገዢ በስም ጠቅሶታል፤ ይሖዋ አምላክ፣ ቂሮስን እንደሚቀባ እና ባቢሎንን በመገልበጥ በግዞት የያዘቻቸውን አይሁዳውያን ለማስለቀቅ እንደሚጠቀምበት ትንቢቱ ይናገራል። (ኢሳ 44:26 እስከ 45:7) ይሖዋ ይህን ትንቢት ያስነገረው ቂሮስ ወደ ሥልጣን ከመምጣቱ ከ150 ዓመት በፊት ነው፤ ይሁዳ በጠፋችበት ጊዜ እንኳ ቂሮስ የተወለደ አይመስልም፤ ያም ቢሆን ይሖዋ ቂሮስ የተባለን ሰው ለአይሁዳውያን “እረኛ” አድርጎ እንደሚሾም ተናግሮ ነበር። (ኢሳ 44:28፤ ከሮም 4:17 ጋር አወዳድር።) ቂሮስ የተመረጠው በዚህ መንገድ አስቀድሞ በመሆኑ ይሖዋ ‘የቀባው’ ተብሏል፤ እዚህ ላይ ‘የቀባው’ ተብሎ የተተረጎመው ቃል መሺያክ፣ (መሲሕ) ከተባለው የዕብራይስጥ ቃል እና ክሪስቶስ (ክርስቶስ) ከተባለው የግሪክኛ ቃል ጋር ዝምድና አለው። (ኢሳ 45:1) አምላክ “በስምህ እጠራሃለሁ” ብሎ አስቀድሞ መናገሩ ይህ ሰው ሲወለድ ቂሮስ ብሎ ስም እንደሚያወጣለት የሚጠቁም አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ይሖዋ እንዲህ ያለ ስም ያለው ሰው እንደሚነሳ አስቀድሞ እንደሚያውቅ እንዲሁም የይሖዋ ጥሪ እንዲሁ በስም ለማይታወቅ ሰው ሳይሆን በማያሻማ መልኩ በስም ለሚታወቅ ሰው መሆኑን የሚያስረግጥ ነው።
it “ቂሮስ” አን. 17
ቂሮስ
ከቀድሞዎቹ አረማውያን ነገሥታት በተለየ መልኩ ቂሮስ አይሁዳውያንን ተባብሯቸዋል። ዳግማዊ ናቡከደነጾር ወደ ባቢሎን ያጋዛቸውን ውድ የቤተ መቅደስ ዕቃዎች መልሶላቸዋል፤ የአርዘ ሊባኖስ ሳንቃዎችን ከሊባኖስ እንዲያስመጡ ንጉሣዊ ፈቃድ ሰጥቷቸዋል እንዲሁም የግንባታው ወጪ ከንጉሡ ቤት እንዲከፈል አድርጓል። (ዕዝራ 1:7-11፤ 3:7፤ 6:3-5) የቂሮስ ሲሊንደር ተብሎ የሚጠራው ሸክላ እንደሚጠቁመው ይህ የፋርስ ገዢ በግዛቱ ውስጥ ካሉ በምርኮ የተወሰዱ ሕዝቦች ጋር በተያያዘ በጥቅሉ ሲታይ ሰብዓዊነትና ሆደ ሰፊነት የሚንጸባረቅበት ፖሊሲ ነበረው። ሲሊንደሩ ቂሮስ እንዲህ ብሎ እንደተናገረ ይገልጻል፦ “የአምልኮ ስፍራዎቻቸው ከፈራረሱባቸው ረጅም ዘመናት ላስቆጠሩት በጤግሮስ ማዶ ለሚገኙ [ቀደም ሲል ለተጠቀሱት አንዳንድ] ቅዱስ ከተሞች በዚያ የነበሩትን ዕቃዎቻቸውን መልሼላቸዋለሁ፤ እንዲሁም በቋሚነት እንዲቀመጡባቸው መቅደሶች ሠርቼላቸዋለሁ። (በተጨማሪም የቀድሞ) ነዋሪዎቻቸውን በሙሉ ሰብስቤ ወደ ትውልድ ስፍራቸው መልሻለሁ።”—ጥንታዊ የቅርብ ምሥራቅ ጽሑፎች (Ancient Near Eastern Texts) ገጽ 316
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የአንባቢያን ጥያቄዎች
ሁለተኛው ምሳሌ፣ ቂሮስ የተባለ ተዋጊ አይሁዳውያንን ከግዞት ነፃ እንደሚያወጣቸውና የይሖዋ ቤተ መቅደስ መልሶ እንዲገነባ እንደሚያዝዝ የሚገልጸው ትንቢት ነው። (ኢሳ. 44:26–45:4) የፋርሱ ንጉሥ ቂሮስ ይህ ትንቢት እንዲፈጸም አድርጓል። (ዕዝራ 1:1-4) ይሁንና ቂሮስ እውነተኛውን አምላክ አላመለከም። ይሖዋ ቂሮስ ያለውን ማንን እንደሚያመልክ የመምረጥ መብት ሳይነካ ቂሮስ ትንቢቱን እንዲፈጽም አድርጓል።—ምሳሌ 21:1
ከመጋቢት 16-22
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት ኢሳይያስ 45–47
“እኔ አምላክ ነኝ፤ እንደ እኔም ያለ ማንም የለም”
“ስምህ ይቀደስ”
14 ይሖዋ ዓላማውን እንዳያሳካ ለማድረግ ሰይጣን የቻለውን ያህል ሲጥር ቆይቷል። ሆኖም በተደጋጋሚ ያደረገው ሙከራ አልተሳካለትም። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ ስለወሰዳቸው እርምጃዎች የሚገልጽ ከመሆኑም ሌላ እንደ ይሖዋ ያለ አምላክ እንደሌለ ያረጋግጣል። እርግጥ ነው፣ ሰይጣንም ሆነ ከእሱ ጎራ የተሰለፉት ሁሉ በይሖዋ ላይ ማመፃቸው አምላካችንን በእጅጉ አሳዝኖታል። (መዝ. 78:40) ሆኖም ለተሰነዘረበት ነቀፋ ምላሽ የሰጠው ጥበብ፣ ትዕግሥትና ፍትሕ በሚንጸባረቅበት መንገድ ነው። ከዚህም ሌላ ገደብ የለሽ ኃይሉን በብዙ መንገዶች አሳይቷል። ከሁሉ በላይ ደግሞ ያደረጋቸው ነገሮች በሙሉ ፍቅሩን የሚያሳዩ ናቸው። (1 ዮሐ. 4:8) ይሖዋ ስሙን ለመቀደስ የሚያስፈልገውን እርምጃ መውሰዱን አላቆመም።
‘ይሖዋ ኃይሉ ታላቅ ነው’
14 ወደፊት አንድ በአንድ እንደምንመለከተው አምላክ ኃይሉን ለመፍጠር፣ ለማጥፋት፣ አገልጋዮቹን ለመጠበቅ፣ አንድን ነገር ለማደስና በአጠቃላይ ፍጹም የሆነውን ዓላማውን ሁሉ ለማስፈጸም ይጠቀምበታል። (ኢሳይያስ 46:10) አንዳንድ ጊዜ ይሖዋ ኃይሉን በመጠቀም፣ በጣም አስፈላጊ የሆኑ ባሕርያቱንና መሥፈርቶቹን ይገልጣል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ፈቃዱን ለመፈጸም ይኸውም በመሲሐዊ መንግሥቱ አማካኝነት ስሙን ለማስቀደስ እና የእሱ አገዛዝ ከሁሉ የላቀ መሆኑን ለማሳየት ይጠቀምበታል። ይህን ዓላማ ሊያከሽፍ የሚችል ምንም ነገር የለም።
it “በባቢሎን የነበሩ ግዞተኞች ተመለሱ” አን. 1
በባቢሎን የነበሩ ግዞተኞች ተመለሱ
በ607 ዓ.ዓ. አይሁዳውያን በምርኮ ወደ ባቢሎን ተወሰዱ፤ የተወሰኑ ቀሪዎች ደግሞ ወደ ግብፅ ሸሹ፤ በመሆኑም በአንድ ወቅት በነዋሪዎች የተሞላው የይሁዳ ምድር “ሰው የማይኖርበት ባድማ” ሆነ። (ኤር 9:11) ለሕዝቡ ታማኝ ፍቅር የሚያሳየው አምላክ ግን እስከ ወዲያኛው በግዞት እንዲኖሩ አይተዋቸውም። “የባቢሎንን ንጉሥ 70 ዓመት [ካገለገሉት]” በኋላ ታማኝ ቀሪዎችን ከግዞት እንደሚያወጣቸው አስቀድሞ ተናግሯል። (ኤር 25:11, 12፤ 29:10-14) ባቢሎን የማትደፈር የምትመስል የዓለም ኃያል መንግሥት ብትሆንም እንኳ አምላክ አደርገዋለሁ ብሎ የተናገረውን ነገር ማድረግ አይሳነውም። አይሁዳውያን ግዞተኞች ወደ አገራቸው መመለሳቸው ይሖዋ ያስነገራቸው ትንቢቶች አንድም ሳይቀር እንደሚፈጸሙ ማረጋገጫ ይሆናል።
ይሖዋ በመንገዱ ስለሚመራን ደስተኞች ነን
18 እንደ ቀድሞው ሁሉ ዛሬም በይሖዋ መንገድ ለመመላለስ ታማኝ መሆን ማለትም እርሱን ብቻ ለማገልገል ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ይጠይቃል። በይሖዋ ላይ መታመን ማለትም ይሖዋ የሰጠው ተስፋ እምነት የሚጣልበት እንደሆነና ፍጻሜውን እንደሚያገኝ ሙሉ በሙሉ ማመን ይጠይቃል። በይሖዋ መንገድ ለመመላለስ ወደ ግራ ወይም ወደ ቀኝ ሳይሉ ሕግጋቱን በመከተልና ከፍተኛ የአቋም ደረጃዎቹን በመጠበቅ መታዘዝ ይጠይቃል። “እግዚአብሔር ጻድቅ ነውና፣ ጽድቅንም ይወድዳል።”—መዝሙር 11:7
19 አካዝ ደህንነት ለማግኘት ፊቱን ያዞረው ወደ ሶርያውያን አማልክት ነበር። ወደ ግብፅ የወረዱት እስራኤላውያንም ‘የሰማይ ንግሥት’ ተብላ የምትታወቀው በጥንቱ የመካከለኛው ምሥራቅ በስፋት የምትመለከው የሴት አምላክ ቁሳዊ ብልጽግና ታመጣልናለች ብለው ተስፋ አድርገው ነበር። በዛሬው ጊዜ ያሉት አብዛኞቹ አማልክት ቃል በቃል ጣዖታት አይደሉም። ኢየሱስ ከይሖዋ ይልቅ ‘ለገንዘብ’ መገዛትን አውግዞ ተናግሯል። (ማቴዎስ 6:24) ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ጣዖትን ማምለክ ስለሆነው ስለ መጎምጀት’ ተናግሯል። (ቆላስይስ 3:5) “ሆዳቸው አምላካቸው” ስለሆነ ሰዎችም ተናግሯል። (ፊልጵስዩስ 3:19) አዎን፣ በዛሬው ጊዜ በዋነኛነት ከሚመለኩት አማልክት መካከል ገንዘብና ቁሳዊ ነገሮች ይገኙበታል። እንደ እውነቱ ከሆነ ሃይማኖታዊ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎችንም ጨምሮ በርካታ ሰዎች ‘ተስፋቸውን የጣሉት በሚያልፍ ባለ ጠግነት’ ላይ ነው። (1ጢሞቴዎስ 6:17) ብዙዎች ላባቸው ጠብ እስኪል ድረስ በመሥራት እነዚህን አማልክት ያገለግሏቸዋል። አንዳንዶች ምርጥ በተባሉ ቤቶች ውስጥ በመኖር፣ ውድ የሆኑ ነገሮች በማካበትና የቅንጦት ምግቦች በመመገብ የልፋታቸውን ዋጋ አግኝተዋል። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው የተንደላቀቀ ኑሮ ያላቸው ሁሉም አይደሉም። እንዲህ የመሰለው ኑሮ ያላቸውም ቢሆኑ ውለው አድረው እነዚህ ነገሮች በራሳቸው እርካታ እንደማያመጡ ይገነዘባሉ። እንዲህ ያለው ኑሮ አስተማማኝ ያልሆነ፣ ጊዜያዊና መንፈሳዊ ፍላጎቶችን የማያሟላ ነው።—ማቴዎስ 5:3
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
አዳምና ሔዋን እንደሚሳሳቱ አምላክ ያውቅ ነበር?
ቅዱሳን መጻሕፍት ይሖዋ “ብቻ ጥበበኛ” እንደሆነም ይናገራሉ። (ሮም 16:27) በሰማይ ያሉት መላእክት ይሖዋ ወደር የሌለው ጥበቡን በብዙ መንገዶች ሲገልጥ የመመልከት አጋጣሚ አግኝተዋል። አምላክ በምድር ላይ ያሉ ፍጥረታትን ወደ ሕልውና ሲያመጣ መላእክት “እልል” ብለው ነበር። (ኢዮብ 38:4-7) እነዚህ የማሰብ ችሎታ ያላቸው መንፈሳዊ ፍጥረታት በኤደን ገነት ውስጥ የተከናወኑትን ሁኔታዎች በታላቅ ጉጉት ተከታትለው እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። እንዲህ ያለው ጥበበኛ አምላክ ዕጹብ ድንቅ የሆነውን አጽናፈ ዓለምና በምድር ላይ ያሉ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ነገሮች ከፈጠረ በኋላ መጨረሻቸው እንደማያምር እያወቀ ሁለት ልዩ ፍጥረታትን በመላእክቱ ፊት ወደ ሕልውና ያመጣል ብሎ ማሰብ ስሜት ይሰጣል? እንዲህ ዓይነት ጥፋት ለማምጣት ማቀድ ምክንያታዊ እንደማይሆን ግልጽ ነው።
ያም ሆኖ አንድ ሰው፣ ‘ለጥበቡ ወደር የማይገኝለት አምላክ እንዴት አስቀድሞ ማወቅ አይችልም?’ የሚል ጥያቄ ያነሳ ይሆናል። እርግጥ ነው፣ “የመጨረሻውን ከመጀመሪያው” ማወቅ የይሖዋ ጥበብ አንዱ ገጽታ ነው። (ኢሳይያስ 46:9, 10) ይሁን እንጂ አምላክ ገደብ የለሽ ኃይሉን ሁልጊዜ ሙሉ በሙሉ መጠቀም እንደማያስፈልገው ሁሉ አስቀድሞ የማወቅ ችሎታውንም ሁልጊዜ መጠቀም አያስፈልገውም። ይሖዋ ይህንን ችሎታውን መቼ መጠቀም እንዳለበት በጥበብ ይወስናል። ይህንን ችሎታውን የሚጠቀመው ምክንያታዊ ብሎም ከሁኔታዎች አንጻር ተገቢ እንደሆነ በሚሰማው ጊዜ ነው።
ከመጋቢት 23-29
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት ኢሳይያስ 48–49
ይሖዋን በመስማት በረከት አግኙ
it “አስተማሪ፣ ማስተማር” አን. 2
አስተማሪ፣ ማስተማር
ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ አምላክ ለአገልጋዮቹ ታላቅ አስተማሪ ነው። (1ነገ 8:36፤ መዝ 27:11፤ 86:11፤ 119:102፤ ኢሳ 30:20፤ 54:13) የፍጥረት ሥራው በራሱ፣ ሁሉን አዋቂ አምላክ እንዳለ ያስተምራል፤ ፍጥረት አሁንም ድረስ ብዙ ያልተነካ የምርምርና የትምህርት መስክ ነው። (ኢዮብ 12:7-9) ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ አምላክ ለሰው ልጆች ለየት ባለ መንገድ በመገለጥ ስሙን፣ ዓላማውንና ሕጎቹን አስተምሯቸዋል። (ከዘፀ 4:12, 15፤ 24:12፤ 34:5-7 ጋር አወዳድር።) ይሖዋ የገለጣቸው እነዚህ ነገሮች የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበዋል፤ እንዲሁም ፈቃዱን በተመለከተ ትክክለኛ ትምህርት ለማስተማር መሠረት ይሆናሉ። (ሮም 15:4፤ 2ጢሞ 3:14-17) የአምላክ መንፈስም አስተማሪ ሆኖ ያገለግላል።—ዮሐ 14:26
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መምረጥ ነፃነት ምን ይላል? አምላክ ዕድልህን ወስኖታል?
● አምላክ ሰውን የፈጠረው በራሱ መልክ ወይም አምሳል ነው። (ዘፍጥረት 1:26) በዋነኝነት በደመ ነፍስ ከሚንቀሳቀሱት ከእንስሳት በተለየ እንደ ፍቅርና ፍትሕ የመሳሰሉ ባሕርያትን በማንጸባረቅ ፈጣሪያችንን መምሰል እንችላለን። ደግሞም ልክ እንደ ፈጣሪያችን ነፃ ምርጫ ማድረግ እንችላለን።
● የወደፊቱ ሕይወታችን በአብዛኛው በእኛ ምርጫ ላይ የተመካ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ‘የአምላክን ቃል በማዳመጥ’ ማለትም ሕጎቹን በመታዘዝ ‘ሕይወትን እንድንመርጥ’ ያበረታታናል። (ዘዳግም 30:19, 20) የመምረጥ ነፃነት ባይኖረን ኖሮ እንዲህ ያለው ግብዣ ትርጉም የለሽ እንዲያውም ጭካኔ ይሆን ነበር። አምላክ እሱ የሚፈልገውን እንድንፈጽም ከማስገደድ ይልቅ ‘ትእዛዜን ሰምተህ ብቻ ቢሆን ኖሮ፣ ሰላምህ እንደ ወንዝ ይሆናል’ የሚል ፍቅራዊ ግብዣ አቅርቦልናል።—ኢሳይያስ 48:18
‘እጅግ ቅዱስ በሆነው እምነታችሁ ራሳችሁን ገንቡ’
8 እዚህ ላይ ይሖዋ እሱን ብንታዘዝ እንደምንጠቀም እያሳሰበን ነው። ትእዛዛቱን ብንጠብቅ ሁለት በረከቶች እንደምናገኝ ቃል ገብቶልናል። በመጀመሪያ፣ ሰላማችን እንደ ወንዝ የተረጋጋ፣ የተትረፈረፈና የማይቋረጥ ይሆናል። ሁለተኛ፣ ጽድቃችን እንደ ባሕር ሞገድ ይሆናል። አንድ ባሕር ዳርቻ ላይ ቆመህ እየተከታተሉ የሚመጡትን ሞገዶች ብትመለከት ፈጽሞ እንደማይቋረጡ ማስተዋልህ አይቀርም። ወደፊትም ለዘመናት ሞገዶቹ ወደ ባሕሩ ዳርቻ መምጣታቸውን እንደሚቀጥሉ ታውቃለህ። ይሖዋ ጽድቅህ ማለትም ትክክል የሆነውን በማድረግ የምትከተለው አካሄድ ልክ እንደ ባሕር ሞገድ ዘላለማዊ መሆን እንደሚችል ተናግሯል። ለእሱ ታማኝ ሆነህ ለመኖር እስከተጣጣርክ ድረስ እንዲሳካልህ እንደሚረዳህ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ! (መዝሙር 55:22ን አንብብ።) እንደነዚህ ያሉት የሚያጽናኑ ቃላት በይሖዋና በጽድቅ መሥፈርቶቹ ላይ ያለህን እምነት አያጠናክሩልህም?
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it “የበጎ ፈቃድ ጊዜ” አን. 1-3
የበጎ ፈቃድ ጊዜ
ሐዋርያው ጳውሎስ 2 ቆሮንቶስ 6:2 ላይ የጻፈው ሐሳብ የተወሰደው በኢሳይያስ 49:8 ላይ ከሚገኘው ከሚከተለው ትንቢት ነው፦ “ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ሞገስ [“በጎ ፈቃድ፣” ግርጌ] በማሳይበት ዘመን መልስ ሰጥቼሃለሁ፤ በመዳንም ቀን ረድቼሃለሁ፤ ለሰዎች ቃል ኪዳን አድርጌ እሰጥህ ዘንድ ጠብቄሃለሁ፤ ይህም ምድሪቱን ዳግመኛ እንድታቋቁም፣ የወደመውን ርስታቸውን መልሰህ እንድታወርሳቸው [ነው]።’” አውዱ እንደሚጠቁመው በዚህ ጥቅስ ላይ አንተ የተባለው ኢሳይያስ ሲሆን የእስራኤልን ብሔር እንደወከለ ተደርጎ ተገልጿል። (ኢሳ 49:3) በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ይህ ትንቢት የተሃድሶ ትንቢት ነው፤ የመጀመሪያ ፍጻሜውን ያገኘውም እስራኤል ከባቢሎን ቀንበር ነፃ በወጣበትና እስራኤላውያን እስረኞች “ኑ ውጡ!” በተባሉበት ጊዜ ነው። ከዚያ በኋላ ወደ ትውልድ አገራቸው ተመልሰው ባድማ የነበረውን ምድር ዳግመኛ አቋቁመዋል።—ኢሳ 49:9
ይሁንና በዚህ ምዕራፍ ቁጥር 8 ላይ ከሚገኘው “ለሰዎች ቃል ኪዳን አድርጌ እሰጥህ ዘንድ” ከሚለው ሐሳብ እንዲሁም ቀደም ብሎ ቁጥር 6 ላይ ይህ የይሖዋ ‘አገልጋይ’ የአምላክ “የማዳን [ሥራ] እስከ ምድር ዳርቻ ይደርስ ዘንድ ለብሔራት ብርሃን” እንደሚሆን ከሚናገረው ሐሳብ በመነሳት በእርግጠኝነት መደምደም እንደሚቻለው ይህ ትንቢት መሲሐዊ ትንቢት ነው፤ በመሆኑም የአምላክ ‘አገልጋይ’ ሆኖ በተቀባው በክርስቶስ ኢየሱስ ላይ ፍጻሜውን ያገኛል። (ኢሳ 42:1-4, 6, 7ን ከማቴ 12:18-21 ጋር አነጻጽር።) ‘የበጎ ፈቃድ ጊዜ’ ይሖዋ ለአገልጋዩ ‘መልስ የሚሰጥበት’ እና ‘እርዳታ የሚያደርግበት’ ወቅት በመሆኑ ፍጻሜውን ያገኘው ኢየሱስ ምድር ላይ ባሳለፈው ሕይወት መሆን አለበት፤ ምክንያቱም በዚህ ወቅት ኢየሱስ “ከሞት ሊያድነው ለሚችለው በከፍተኛ ጩኸትና እንባ ብዙ ምልጃና ልመና [አቅርቧል]፤ አምላካዊ ፍርሃት ስለነበረውም ጸሎቱ [ተሰምቶለታል]።” (ዕብ 5:7-9፤ ከዮሐ 12:27, 28፤ 17:1-5፤ ሉቃስ 22:41-44፤ 23:46 ጋር አወዳድር።) በመሆኑም ይህ ወቅት ለአምላክ ልጅ ‘የመዳን ቀን’ ነው፤ ንጹሕ አቋም ጠባቂነቱን ፍጹም በሆነ መንገድ ያስመሠከረበት ወቅት ሲሆን በውጤቱም “የሚታዘዙት ሁሉ ዘላለማዊ መዳን እንዲያገኙ ምክንያት [ሆኖላቸዋል]።”—ዕብ 5:9
ጳውሎስ ከዚህ ትንቢት ተውሶ ከጻፈው ሐሳብ እንደምንረዳው ትንቢቱ ተጨማሪ ፍጻሜ አለው፤ ጳውሎስ ‘የአምላክን ጸጋ ከተቀበሉ በኋላ ዓላማውን እንዳይስቱ’ ክርስቲያኖችን ካሳሰበ በኋላ ኢሳይያስ 49:8 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ ጠቀሰ፤ ከዚያም “እነሆ፣ አምላክ ሞገስ የሚያሳይበት ልዩ ጊዜ አሁን ነው። እነሆ፣ የመዳን ቀን አሁን ነው” አላቸው። (2ቆሮ 6:1, 2) እነዚህ ክርስቲያኖች በ33 ዓ.ም. ከተከበረው ጴንጤቆስጤ በኋላ ‘የአምላክ እስራኤል’ መሆን ችለዋል (ገላ 6:16)፤ ይሁንና ‘የበጎ ፈቃድ ጊዜ’ ለእነሱ ‘የመዳን ቀን’ እንዲሆንላቸው ከፈለጉ የአምላክ ጸጋ የሚገባቸው ሰዎች መሆናቸውን ማስመሥከር ያስፈልጋቸዋል።
ከሚያዝያ 6-12
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት ኢሳይያስ 50–51
የአምላክ ተማሪ የሚለውን ስሙ
የመንግሥቱን አገልጋዮች ማሠልጠን
5 ወልድ በምድር ላይ ስለሚያከናውነው አገልግሎት ጊዜው ሲደርስ ይሖዋ አስተምሮታል። በታላቁ አስተማሪና በበኩር ልጁ መካከል ስላለው ግንኙነት የተነገረ አንድ ትንቢት እንመልከት። (ኢሳይያስ 50:4, 5ን አንብብ።) ይሖዋ፣ ልጁን “በየማለዳው” እንደሚያነቃው ትንቢቱ ይገልጻል። ይህ ምሳሌያዊ አገላለጽ፣ ተማሪውን ለማሠልጠን ሲል በማለዳ የሚቀሰቅሰውን አስተማሪ እንድናስብ ያደርገናል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ማመሳከሪያ ጽሑፍ እንዲህ ይላል፦ “ይሖዋ . . . አገልጋዩን ልክ እንደ አንድ ተማሪ በምሳሌያዊ መንገድ ትምህርት ቤት ወስዶ ምን እና እንዴት እንደሚሰብክ ያስተምረዋል።” ይሖዋ በሰማይ ባለው በዚያ “ትምህርት ቤት” ልጁን ‘ምን እንደሚልና ምን እንደሚናገር’ አስተምሮታል። (ዮሐ. 12:49) በተጨማሪም ወልድ እንዴት ማስተማር እንዳለበት አብ አሠልጥኖታል። ኢየሱስ ያገኘውን ሥልጠና፣ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት አገልግሎቱን ለማከናወን ብቻ ሳይሆን ተከታዮቹ አገልግሎታቸውን እንዴት እንደሚያከናውኑ ለማሠልጠንም ጭምር ተጠቅሞበታል።
‘እኔ አብን እወደዋለሁ’
13 ወልድ ሰው ሆኖ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት በጉጉት ከአባቱ ትምህርት ሲቀስም ቆይቷል። በኢሳይያስ 50:4-6 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ትንቢት እንደሚጠቁመው ይሖዋ ለልጁ መሲሕ በመሆን የሚጫወተውን ሚና በተመለከተ ትምህርት ሰጥቶታል። ይህ ትምህርት ይሖዋ በቀባው ላይ ስለሚደርሱት መከራዎች መማርን የሚጨምር ቢሆንም ወልድ ትምህርቱን በጉጉት ይከታተል ነበር። ኢየሱስ ወደ ምድር ከመጣና ትልቅ ሰው ከሆነም በኋላ ሁልጊዜ ወደ አባቱ ቤት ለመሄድ ይጓጓ ነበር፤ ይሖዋ በዚያ እንዲቀርብ በሚፈልገው አምልኮና ትምህርት መሳተፍ ያስደስተው ነበር። ኢየሱስ አዘውትሮ ወደ ቤተ መቅደሱና ወደ ምኩራብ ይሄድ እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። (ሉቃስ 4:16፤ 19:47) እኛም ለይሖዋ ያለን ፍቅር ሕያው ሆኖ እንዲቀጥልና እንዲያብብ የምንፈልግ ከሆነ አዘውትረን በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት አለብን፤ ስብሰባዎች ይሖዋን ለማምለክ እንዲሁም ስለ እሱ ያለንን እውቀትና አድናቆት ለማሳደግ አጋጣሚ ይሰጡናል።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it “ካባ” አን. 2
ካባ
ይሖዋ በነቢዩ ኢሳይያስ አማካኝነት ባስጻፈው ሐሳብ ላይ ስለ ካባ እና በዚያ ስለሚከናወነው ሥራ ማራኪ የሆነ ዘይቤያዊ አገላለጽ ተጠቅሟል። (ኢሳ 51:1) ቀጣዩ ቁጥር እንደሚጠቁመው “ዓለት” የተባለው አብርሃም መሆን አለበት፤ የብሔሩ ሰብዓዊ አባት እሱ ነው። ‘ካባው’ ደግሞ የሚያመለክተው ሣራን ነው፤ ምክንያቱም በተቆፈረ ጉድጓድ የተመሰለው ማህፀኗ የእስራኤልን አባት ይስሐቅን አፍርቷል። (ኢሳ 51:2) ይሁንና የይስሐቅ መወለድ በመለኮታዊ ጣልቃ ገብነት የተከናወነ ተአምር በመሆኑ ከካባ ተቆፍሮ ስለመውጣት የሚናገረው ዘይቤያዊ አገላለጽ ላቅ ያለ መንፈሳዊ ትርጓሜም ሊኖረው ይችላል። ዘዳግም 32:18 ላይ ይሖዋ ለእስራኤል ‘አባት የሆነው ዓለት’ ተብሎ የተጠራው ለዚህ ነው፤ በተጨማሪም ‘የወለደህ አምላክ’ ተብሏል፤ እዚህ ላይ ‘የወለደህ’ ተብሎ የተተረጎመው ግስ ኢሳይያስ 51:2 ላይ ከሣራ ጋር በተያያዘ ተሠርቶበታል።
ከሚያዝያ 13-19
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት ኢሳይያስ 52–53
ኢየሱስ ያሳየው ታላቅ ፍቅር!
እናንት ወጣቶች—የእኩዮቻችሁን ተጽዕኖ ተቋቋሙ
2 እኩዮችህ የሚያሳድሩብህ ጫና በጣም ያስጨንቅሃል? ከሆነ እንዲህ የሚሰማህ ለምን ሊሆን ይችላል? በእኩዮችህ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ስለምትፈልግ ይሆን? በሌሎች ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት መፈለግ ያለ ነገር ነው። ትልልቅ ሰዎችም እንኳ በእኩዮቻቸው ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት ይፈልጋሉ። ወጣትም ሆነ አዋቂ ማንኛውም ሰው ቢሆን ሰዎች ሲያገሉት ደስ አይለውም። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ትክክል እንደሆነ ላመንክበት ነገር አቋም መውሰድህ በሌሎች ዘንድ ተቀባይነት የሚያስገኝልህ ሁልጊዜ ላይሆን ይችላል። ኢየሱስም እንኳ እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሞት ነበር። ያም ቢሆን ምንጊዜም ትክክል የሆነውን ነገር አድርጓል። አንዳንዶች ኢየሱስን የተከተሉት ከመሆኑም በላይ ደቀ መዛሙርቱ ለመሆን ችለዋል፤ ሌሎች ግን የአምላክን ልጅ በመናቅ ‘ሳያከብሩት’ ቀርተዋል።—ኢሳ. 53:3
ይሖዋ መሲሐዊ አገልጋዩን ከፍ ከፍ ያደርገዋል
25 መሲሑ መከራ ለመቀበልና ለመሞት ፈቃደኛ ነበርን? ኢሳይያስ እንዲህ ይላል፦ “ተጨነቀ ተሣቀየም [“መከራን ታግሦ ተቀበለ፣” የ1980 ትርጉም] አፉንም አልከፈተም፤ ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት፣ በሸላቶቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ፣ እንዲሁ አፉን አልከፈተም።” (ኢሳይያስ 53:7) ኢየሱስ ሰው ሆኖ በምድር ላይ ባሳለፈው የመጨረሻ ሌሊት “ከአሥራ ሁለት ጭፍሮች የሚበዙ መላእክት” መጥተው እንዲረዱት ማድረግ ይችል ነበር። ሆኖም “እንዲህ ከሆነስ፦ እንደዚህ ሊሆን ይገባል የሚሉ መጻሕፍት እንዴት ይፈጸማሉ?” ሲል ተናግሯል። (ማቴዎስ 26:53, 54) በመሆኑም “የእግዚአብሔር በግ” ምንም ዓይነት የአጸፋ እርምጃ አልወሰደም። (ዮሐንስ 1:29) የካህናት አለቆችና ሽማግሌዎች በጲላጦስ ፊት በሐሰት ሲከሱት “ምንም አልመለሰም።” (ማቴዎስ 27:11-14) የአምላክን ፈቃድ ሊያስተጓጉል የሚችል ነገር መናገር አልፈለገም። ኢየሱስ የእሱ ሞት ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆችን ከኃጢአት፣ ከበሽታና ከሞት ሊቤዥ እንደሚችል በሚገባ በመገንዘቡ የመሥዋዕት በግ ሆኖ ለመሞት ፈቃደኛ ነበር።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it “ዕቃዎች” አን. 2
ዕቃዎች
ኬሊ የሚለው ቃል በመቅደሱ ውስጥ ጥቅም ላይ ከሚውሉ ዕቃዎች ጋር በተያያዘ ብዙ ጊዜ ተሠርቶበታል። ከእነዚህ ዕቃዎች መካከል ሳህኖች፣ ማንቆርቆሪያዎች፣ አካፋዎች፣ ጎድጓዳ ሳህኖች፣ ሹካዎች፣ መኮስተሪያዎች፣ የእሳት ማጥፊያዎች፣ መቆንጠጫዎች፣ ገንዳዎች እና ጽዋዎች ይገኙበታል። (ዘፀ 25:29, 30, 39፤ 27:3, 19፤ 37:16, 23፤ 38:3፤ 1ነገ 7:40-50፤ 2ዜና 4:11-22) ዕቃዎቹ የሚውሉት ለተቀደሰ ዓላማ በመሆኑ “ቅዱስ” ናቸው። (1ነገ 8:4) በመሆኑም በ537 ዓ.ዓ. አይሁዳውያን ከባቢሎን ሲወጡ ቀደም ሲል ንጉሥ ናቡከደነጾር ከኢየሩሳሌም የወሰዳቸውን የተቀደሱ ዕቃዎች እንዲሸከሙ መብት ስለተሰጣቸው ሃይማኖታዊና ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናቸውን መጠበቅ ነበረባቸው። የሚከተለው ትንቢታዊ ትእዛዝ እነሱን የሚመለከት ነበር፦ “እናንተ የይሖዋን ዕቃ የምትሸከሙ፣ ገለል በሉ፣ ገለል በሉ፤ [ከባቢሎን] ውጡ፤ ማንኛውንም ርኩስ ነገር አትንኩ! ከመካከሏ ውጡ፤ ንጽሕናችሁን ጠብቁ።” (ኢሳ 52:11) ይህ እንዲሁ ለሃይማኖታዊ ሥርዓት ሲባል ውጫዊ ንጽሕናን ከመጠበቅ ያለፈ ነገር ነው። ልብን ንጹሕ ማድረግን የሚጠይቅ ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ክርስቲያኖችም ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ነገር ራሳቸውን ማንጻት እንዳለባቸው ለማሳሰብ ኢሳይያስ 52:11 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ ተጠቅሞበታል።—2ቆሮ 6:14-18፤ 7:1
ከሚያዝያ 20-26
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት ኢሳይያስ 54–55
ምን ያህል ለመክፈል ፈቃደኛ ናችሁ?
መለኮታዊ ትምህርት ያለው የላቀ ዋጋ
3 ይሖዋ ፍጽምና የጎደላቸውን የሰው ልጆች ለማስተማር ፈቃደኛ በመሆን ጥሩነቱን አሳይቷል። ቅቡዓን ክርስቲያኖችን በተመለከተ በኢሳይያስ 54:13 ላይ “ወንዶች ልጆችሽ ሁሉ ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ፤ የልጆችሽም ሰላም ታላቅ ይሆናል” የሚል ትንቢት ተናግሯል። ይህ ጥቅስ በመሠረታዊ ሥርዓት ደረጃ ለክርስቶስ ‘ሌሎች በጎችም’ ይሠራል። (ዮሐ. 10:16) በዘመናችን እየተፈጸመ ያለ አንድ ትንቢት ይህንን በግልጽ ያሳያል። ኢሳይያስ ከሕዝቦች ሁሉ የተውጣጡ ሰዎች ወደ እውነተኛው አምልኮ ሲጎርፉ በራእይ ተመልክቷል። እነዚህ ሰዎች እርስ በርሳቸው እንዲህ በማለት እንደሚነጋገሩ ገልጿል፦ “ወደ እግዚአብሔር ተራራ፣ ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንውጣ፤ እርሱ መንገዱን ያስተምረናል፤ በጐዳናውም እንሄዳለን።” (ኢሳ. 2:1-3) ከአምላክ የተማሩ መሆን እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው!
‘እውነትን ግዛ፤ ፈጽሞም አትሽጠው’
6 ኢሳይያስ 55:1-3ን አንብብ። ይሖዋ በኢሳይያስ በኩል የተናገራቸው ቃላት እውነትን መግዛት ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ይበልጥ ግልጽ ያደርጉልናል። በዚህ ጥቅስ ላይ ይሖዋ ቃሉን ከውኃ፣ ከወተትና ከወይን ጠጅ ጋር አመሳስሎታል። ኩልል እንዳለ ቀዝቃዛ ውኃ ሁሉ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙት እውነቶችም መንፈሳችንን ያድሱልናል። በተጨማሪም ወተት ጥንካሬ እንደሚሰጥና ለልጆች እድገት እንደሚጠቅም ሁሉ ገንቢ የሆኑት የይሖዋ ሐሳቦችም ያጠነክሩናል እንዲሁም በመንፈሳዊ እንድናድግ ይረዱናል። ከዚህም ሌላ ይሖዋ የተናገራቸው ቃላት ከወይን ጠጅ ጋር ተመሳስለዋል። በምን መንገድ? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የወይን ጠጅ ከደስታ ጋር ተያይዞ ተገልጿል። (መዝ. 104:15) ይሖዋ ‘የወይን ጠጅ እንዲገዙ’ ለሕዝቡ የተናገረው ሕይወታችንን በእሱ መመሪያዎች መምራታችን ደስታ እንደሚያስገኝልን ስለሚያውቅ ነው። (መዝ. 19:8) በእርግጥም ይህ ንጽጽር በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትን እውነቶች መማራችንና ተግባራዊ ማድረጋችን የሚያስገኘውን ጥቅም ግሩም አድርጎ ይገልጻል! እውነትን ለማግኘት የምናደርገውን ጥረት እውነትን ለመግዛት እንደምንከፍለው ዋጋ አድርገን ልንቆጥረው እንችላለን። ከዚህ በመቀጠል እውነትን ለመግዛት ስንል ልንከፍላቸው የምንችላቸውን አምስት ነገሮች እንመለከታለን።
እውነትን ለመግዛት ስትሉ ምን ነገሮችን መሥዋዕት አድርጋችኋል?
7 ጊዜ። እውነትን መግዛት የሚፈልግ ሁሉ ጊዜውን መሥዋዕት ማድረግ አለበት። የመንግሥቱን መልእክት ለመስማት፣ መጽሐፍ ቅዱስንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ለማንበብ፣ የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማድረግ እንዲሁም በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ጥሩ ዝግጅት አድርጎ ለመገኘት ጊዜ ያስፈልጋል። ለእነዚህ ነገሮች የሚሆን ጊዜ ለማግኘት እምብዛም አስፈላጊ ካልሆኑ እንቅስቃሴዎች ላይ ‘ጊዜ መግዛት’ ወይም መውሰድ ይኖርብናል። (ኤፌሶን 5:15, 16ን እና የግርጌ ማስታወሻውን አንብብ።) መሠረታዊ ስለሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ትክክለኛውን እውቀት ለመቅሰም ምን ያህል ጊዜ ያስፈልገናል? ይህ እንደ ግለሰቡ ሁኔታ ይለያያል። ይሖዋ ስላለው ጥበብ፣ ስለ መንገዶቹና ስለ ሥራዎቹ መቼም ቢሆን ተምረን መጨረስ አንችልም። (ሮም 11:33) የመጀመሪያው የመጠበቂያ ግንብ እትም እውነትን ከአንድ “ትንሽ አበባ” ጋር ያመሳሰለው ሲሆን የሚከተለውን ሐሳብ ይዟል፦ “አንድ የእውነት አበባ ስላገኘህ ብቻ አትርካ። አንድ ብቻ በቂ ቢሆን ኖሮ ተጨማሪ አበቦች ባልኖሩ ነበር። መሰብሰብህን አታቋርጥ፤ ፍለጋህን ቀጥል።” እንግዲያው ‘የያዝኩት የአበባ እቅፍ ምን ያህል ትልቅ ነው?’ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን አስፈላጊ ነው። ለዘላለም ብንኖር እንኳ ሁልጊዜ ስለ ይሖዋ የምንማረው አዲስ ነገር ይኖራል። በዛሬው ጊዜ ግን ጊዜያችንን በጥበብ በመጠቀም ሁኔታችን የሚፈቅደውን ያህል ብዙ እውነት መግዛታችን አስፈላጊ ነው። እስቲ እውነትን ለማግኘት ከፍተኛ ጉጉት የነበራትን አንዲት ሴት ተሞክሮ እንመልከት።
“እንዴት እንደምታዳምጡ በጥንቃቄ አስቡ”
በጥሞና እንዳናዳምጥ እንቅፋት የሚሆኑብን ብዙ ነገሮች አሉ። በአእምሮአችን ውስጥ የሚጉላላ ብዙ ሐሳብ ይኖር ይሆናል። በአድማጮች መካከልም ሆነ ከስብሰባው ቦታ ውጭ የሚፈጠር ድምፅ ወይም የሚደረግ እንቅስቃሴ ሐሳባችንን ሊሰርቅብን ይችላል። ምቾታችንን የሚነፍጉ ሁኔታዎች ሐሳባችንን ሰብስበን እንዳንከታተል እንቅፋት ሊሆኑብን ይችላሉ። ሕፃናት ልጆች ያሏቸው ብዙውን ጊዜ ሐሳባቸው ይከፋፈላል። ፕሮግራሙን በትኩረት እንድንከታተል ምን ሊረዳን ይችላል?
ብዙውን ጊዜ ትኩረታችን የሚያርፈው ዓይናችን ባረፈበት ነገር ላይ ነው። ዓይኖችህ ተናጋሪው ላይ እንዲያርፉ ካደረግህ ሐሳብህን ሰብስበህ ማዳመጥ ትችላለህ። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ሲጠቅስ ጥቅሱን የምታውቀው ቢሆንም እንኳ አውጥተህ ተከታተል። ድምፅ በተሰማ ወይም አንድ ነገር ውልብ ባለ ቁጥር ወደዚያ ዞረህ እንዳታይ ራስህን መግታት ይኖርብሃል። ዓይንህ እዚህም እዚያም እያማተረ ሐሳብህ የሚከፋፈል ከሆነ ከሚተላለፈው ትምህርት አብዛኛው ያመልጥሃል።
‘በውስጥህ የሚያስጨንቅህ’ ነገር ኖሮ ሐሳብህን ሰብስበህ ፕሮግራሙን መከታተል ከተቸገርህ ይሖዋ በጥሞና ለመከታተል የሚያስችል የአእምሮና የልብ መረጋጋት እንዲሰጥህ ጸልይ። (መዝ. 94:19 አ.መ.ት፤ ፊልጵ. 4:6, 7) ካስፈለገም ደጋግመህ ጸልይ። (ማቴ. 7:7, 8) የጉባኤ ስብሰባዎች ይሖዋ ለእኛ ያደረገልን ዝግጅቶች ስለሆኑ ከእነዚህ ስብሰባዎች እንድትጠቀም እንደሚፈልግ አትጠራጠር።—1ዮሐ. 5:14, 15
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
“እኔ አምላክህ ነኝና አትጨነቅ”
14 አንደኛ፣ የክርስቶስ ተከታዮች እንደመሆናችን መጠን ሰዎች እንደሚጠሉን እንጠብቃለን። (ማቴ. 10:22) ኢየሱስ በመጨረሻዎቹ ቀናት ደቀ መዛሙርቱ ከባድ ስደት እንደሚደርስባቸው አስቀድሞ ተናግሯል። (ማቴ. 24:9፤ ዮሐ. 15:20) ሁለተኛ፣ የኢሳይያስ ትንቢት ተቃዋሚዎቻችን እኛን በመጥላት ብቻ እንደማይመለሱ ከዚህ ይልቅ እኛን ለማጥቃት የተለያዩ መሣሪያዎችን እንደሚጠቀሙ አስጠንቅቋል። እነዚህ መሣሪያዎች መሠሪ ማታለያዎችን፣ ዓይን ያወጡ ውሸቶችንና ከባድ ስደትን ያካትታሉ። (ማቴ. 5:11) ጠላቶቻችን እኛን ለመውጋት እነዚህን መሣሪያዎች እንዳይጠቀሙ ይሖዋ አይከለክላቸውም። (ኤፌ. 6:12፤ ራእይ 12:17) ሆኖም መፍራት አይኖርብንም። ለምን?
15 ሦስተኛው እውነታ መልሱን ይሰጠናል። ይሖዋ እኛን ለማጥቃት የተሠራ ‘ማንኛውም መሣሪያ እንደሚከሽፍ’ ተናግሯል። አንድ ግንብ፣ አውዳሚ ከሆነ ውሽንፍር እንደሚከልል ሁሉ ይሖዋም ‘ከጨቋኞች ቁጣ’ ይከልለናል። (ኢሳይያስ 25:4, 5ን አንብብ።) ጠላቶቻችን በእኛ ላይ ዘላቂ ጉዳት ለማድረስ የሚያደርጉት ጥረት ሁሉ ይከሽፋል።—ኢሳ. 65:17
ከሚያዝያ 27–ግንቦት 3
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት ኢሳይያስ 56–57
ይሖዋ አምላካችን በመሆኑ ደስተኞች ነን
ይሖዋ የተሰበረ ልብ ያላቸውን ሰዎች መንፈስ ያነቃቃል
14 ይሁን እንጂ የይሖዋ ትዕግሥት የሚያበቃበት ዘመን ይመጣል። ይሖዋ ያን ጊዜ አሻግሮ በመመልከት እንዲህ አለ፦ “እኔ ጽድቅሽን እናገራለሁ፣ ሥራሽም አይረባሽም። ወደ አንቺ የሰበሰብሻቸው በጮኽሽ ጊዜ ይታደጉሽ፤ ንፋስ ግን ይወስዳቸዋል ሽውሽውታም ሁሉን ያስወግዳቸዋል።” (ኢሳይያስ 57:12, 13ሀ) ይሖዋ የይሁዳን የይስሙላ ጽድቅ ያጋልጠዋል። የግብዝነት ድርጊቷ የሚፈይድላት ነገር አይኖርም። ‘የሰበሰበቻቸው ነገሮች’ ማለትም ያከማቸቻቸው ጣዖታት አያድኗትም። ጥፋት በሚመጣበት ጊዜ የታመነችባቸው አማልክት በንፋስ ሽውታ ብን ብለው ይጠፋሉ።
15 ይሖዋ የተናገራቸው ቃላት በ607 ከዘአበ ተፈጽመዋል። የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ኢየሩሳሌምን ያወደመው፣ ቤተ መቅደሱን ያቃጠለውና አብዛኛውን ነዋሪ የማረከው በዚያ ወቅት ነው። “እንዲሁ ይሁዳ ከአገሩ ተማረከ።”—2 ነገሥት 25:1-21
16 በተመሳሳይም ሕዝበ ክርስትና ያከማቸቻቸው በርካታ ጣዖታት በይሖዋ የቁጣ ቀን አያድኗትም። (ኢሳይያስ 2:19-22፤ 2 ተሰሎንቄ 1:6-10) ሕዝበ ክርስትና የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ከሆነው ከተቀረው ‘የታላቂቱ ባቢሎን’ ክፍል ጋር ትጠፋለች። ምሳሌያዊው ቀይ አውሬና አሥር ቀንዶቹ “[ታላቂቱ ባቢሎንን] ባዶዋንና ራቁትዋንም ያደርጓታል፣ ሥጋዋንም ይበላሉ፣ በእሳትም ያቃጥሉአታል።” (ራእይ 17:3, 16, 17) “ሕዝቤ ሆይ፣ በኃጢአትዋ እንዳትተባበሩ ከመቅሠፍትዋም እንዳትቀበሉ ከእርስዋ ዘንድ ውጡ” የሚለውን ትእዛዝ በማክበራችን ምንኛ ደስተኞች ነን! (ራእይ 18:4, 5) ዳግመኛ ወደ እሷ መመለስም ሆነ በመንገዶቿ መመላለስ አይኖርብንም።
“መንግሥቴ የዚህ ዓለም ክፍል አይደለም”
16 በእርግጥም እንዲህ ዓይነት ለውጥ ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነው! መጽሐፍ ቅዱስ የሰውን ዘር፣ ጸጥ ማለት ከማይችል የሚናወጥ ባሕር ጋር ያመሳስለዋል። (ኢሳ. 17:12፤ 57:20, 21፤ ራእይ 13:1) ፖለቲካዊ ጉዳዮች ሰዎች እርምጃ ለመውሰድ እንዲነሳሱ፣ እንዲከፋፈሉ እንዲሁም ዓመፅ እንዲቀሰቅሱ ቢያደርጓቸውም እኛ ግን ሰላማዊ ለመሆንና አንድነታችንን ለመጠበቅ ጥረት እናደርጋለን። ይሖዋ እንዲህ ባለው የተከፋፈለ ዓለም ውስጥ በሕዝቡ መካከል ያለውን አንድነት ሲመለከት ምንኛ ይደሰት ይሆን!—ሶፎንያስ 3:17ን አንብብ።
it “ምድር” አን. 21
ምድር
ምድር የሚለው ቃል በአንጻራዊ ሁኔታ ይበልጥ ረጋ እና ደልደል ያሉ የሰው ዘር ክፍሎችን ለማመልከትም ተሠርቶበታል። በአንጻሩ ያልሰከነውና አስተማማኝነት የሌለው የሰው ዘር ክፍል የነውጠኝነት ባሕርይ ባለው ባሕር ተመስሏል።—ኢሳ 57:20፤ ያዕ 1:6፤ ይሁዳ 13፤ ራእይ 12:16፤ 20:11፤ 21:1
it “ሰላም” አን. 3
ሰላም
ሰላምን ማግኘት። ይሖዋ የሰላም አምላክ ነው (1ቆሮ 14:33፤ 2ቆሮ 13:11፤ 1ተሰ 5:23፤ ዕብ 13:20)፤ የሰላም ምንጭም ነው (ዘኁ 6:26፤ 1ዜና 22:9፤ መዝ 4:8፤ 29:11፤ 147:14፤ ኢሳ 45:7፤ ሮም 15:33፤ 16:20)፤ ምክንያቱም ሰላም የእሱ መንፈስ ፍሬ ውጤት ነው። (ገላ 5:22) በመሆኑም እውነተኛ ሰላም ሊያገኙ የሚችሉት ከአምላክ ጋር ሰላም ያላቸው ሰዎች ብቻ ናቸው። አንድ ሰው ከባድ ኃጢአት ሲሠራ ከአምላክ ጋር ያለው ወዳጅነት ይረበሻል፤ ይህ ደግሞ ግለሰቡ ሰላም እንዲያጣ ያደርጋል። መዝሙራዊው “[ከኃጢአቴ] የተነሳ አጥንቶቼ ሰላም የላቸውም” ብሏል። (መዝ 38:3) በመሆኑም ሰላምን የሚፈልጉና የሚከተሉት ሁሉ ‘ክፉ ከሆነ ነገር መራቅ እና መልካም የሆነውን ማድረግ’ አለባቸው። (መዝ 34:14) ጽድቅ ከሌለ ሰላም ሊኖር አይችልም። (መዝ 72:3፤ 85:10፤ ኢሳ 32:17) ክፉዎች ሰላም የሌላቸው ለዚህ ነው። (ኢሳ 48:22፤ 57:21፤ ከኢሳ 59:2-8 ጋር አወዳድር።) በአንጻሩ ግን ለይሖዋ ሙሉ በሙሉ ያደሩ፣ ሕጎቹን የሚወዱና (መዝ 119:165) ትእዛዛቱን የሚያከብሩ ሰዎች ሰላምን ንብረታቸው ማድረግ ይችላሉ።—ኢሳ 48:18
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የኢሳይያስ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች—ክፍል 2
56:6—“መጻተኞች” የተባሉት እነማን ናቸው? ‘[የይሖዋን] ቃል ኪዳን የሚጠብቁትስ’ በየትኞቹ መንገዶች ነው? “መጻተኞች” የተባሉት የኢየሱስ “ሌሎች በጎች” ናቸው። (ዮሐንስ 10:16) እነዚህ ሰዎች ከቃል ኪዳኑ ጋር የተያያዙ ሕጎችን በመታዘዝ፣ በቃል ኪዳኑ በኩል የተደረጉ ዝግጅቶችን በሙሉ ልብ በመደገፍ፣ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከሚመገቡት መንፈሳዊ ማዕድ በመመገብ እንዲሁም በመንግሥቱ ስብከትና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ቅቡዓኑን በመደገፍ አዲሱን ቃል ኪዳን ይጠብቃሉ።
ቅዱስ ለሆኑት ስብሰባዎቻችን አክብሮት ማሳየት
ይሖዋ ሕዝቡ የሆኑትን ቅቡዓን ክርስቲያኖችንና አጋሮቻቸውን እርሱን ወደሚያመልኩበት ‘ወደ ተቀደሰው ተራራው’ ሰብስቧቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ “ለሕዝቦች ሁሉ የጸሎት ቤት” በሆነው መንፈሳዊ ቤተ መቅደሱ ማለትም ‘በጸሎት ቤቱ’ ውስጥ ደስ እንዲሰኙ እያደረጋቸው ነው። (ኢሳይያስ 56:7፤ ማርቆስ 11:17) ይሖዋ ሕዝቦቹ እርሱን ለማምለክ በአንድነት እንዲሰበሰቡ ማድረጉ ለእርሱ የሚቀርበው አምልኮ ቅዱስ፣ ንጹሕና ከምንም በላይ ከፍ ያለ መሆኑን ይጠቁማል። እኛም ለጥናትና ለአምልኮ ለምንገናኝባቸው ስብሰባዎች ተገቢ አክብሮት በመስጠት ይሖዋ ለቅዱስ ነገሮች ያለውን አመለካከት እንደምናንጸባርቅ ማሳየት እንችላለን።