የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች
© 2026 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
ከሐምሌ 6-12
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት ኤርምያስ 13-15
ይሖዋን ልንታዘዘው ይገባል
jr 51-52 አን. 17-18
ከዳተኛ ልባችሁ እንዳያታልላችሁ ተጠንቀቁ
17 ኤርምያስ የተሰጠው ተልእኮ የአምላክን አመራር መከተልን የሚጠይቅ ነበር። አንተ ኤርምያስን ብትሆን ኖሮ የሚሰጡህን መመሪያዎች ሁሉ በፈቃደኝነት ትቀበል ነበር? በአንድ ወቅት ይሖዋ ኤርምያስን ከተልባ እግር የተሠራ ቀበቶ ገዝቶ እንዲታጠቅ አዞት ነበር። ከዚያም ወደ ኤፍራጥስ እንዲሄድ አዘዘው። ካርታ አውጥተህ ብትመለከት ይህ ጉዞ 500 ኪ.ሜ. (300 ማይል) የሚሸፍን እንደሆነ ትረዳለህ። ኤርምያስ እዚያ ሲደርስ ቀበቶውን በቋጥኝ ስንጥቅ ውስጥ ከደበቀ በኋላ እንደገና ወደ ኢየሩሳሌም መጓዝ ነበረበት። የተወሰነ ጊዜ ካለፈ በኋላ አምላክ ኤርምያስን ቀበቶውን ሄዶ እንዲያመጣ አዘዘው። (ኤርምያስ 13:1-9ን አንብብ።) ኤርምያስ በድምሩ 1,900 ኪ.ሜ. (1,200 ማይል) ተጉዟል። የመጽሐፍ ቅዱስ ተቺዎች፣ ኤርምያስ ወራት ሊፈጅ የሚችለውን ይህን ጉዞ እንዳደረገ ማመን ይከብዳቸዋል። (ዕዝራ 7:9) ያም ሆነ ይህ፣ አምላክ የሰጠው ትእዛዝም ሆነ ኤርምያስ ያደረገው ነገር ይህንኑ ነው።
18 ይህ ነቢይ የይሁዳን ተራሮች ካቋረጠ በኋላ በምድረ በዳው በኩል አድርጎ ወደ ኤፍራጥስ ሲሄድ በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። ይህን አድካሚ ጉዞ የሚያደርገው ቀበቶውን ለመደበቅ ነበር! ኤርምያስ ለረጅም ጊዜ ከሰፈሩ መጥፋቱ የአካባቢውን ሰዎች ሳያነጋግር አልቀረም። ሲመለስ ከተልባ እግር የተሠራውን ቀበቶ አልያዘም ነበር። ከብዙ ቀናት በኋላ አምላክ ኤርምያስን በድጋሚ ያንን ረጅም ጉዞ እንዲያደርግና በወቅቱ “ተበላሽቶና ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጭ ሆኖ” የሚገኘውን ቀበቶ እንዲያመጣ አዘዘው። ኤርምያስ ‘እንዴ፣ አሁንስ አልበዛም? እንዲህ ማድረግ ለምን አስፈለገ?’ ብሎ ሊያስብ ይችል ነበር። ኤርምያስ ግን አምላክ ጥሩ አድርጎ እንዲቀርጸው ስለፈቀደ እንዲህ ያለ ምላሽ አልሰጠም። በአምላክ ላይ ከማጉረምረም ይልቅ የታዘዘውን ፈጽሟል!
jr 52 አን. 19
ከዳተኛ ልባችሁ እንዳያታልላችሁ ተጠንቀቁ
19 አምላክ ጉዳዩን ለኤርምያስ ያብራራለት ኤርምያስ ሁለተኛውን ጉዞ ካደረገ በኋላ ነበር። ኤርምያስ ያደረገው ነገር የሚከተለውን ጠንካራ መልእክት የሚያውጅበትን ሁኔታ አመቻችቶለታል፦ “ቃሌን ለመታዘዝ አሻፈረኝ ያለው፣ ግትር ሆኖ የገዛ ልቡን የሚከተለው እንዲሁም ሌሎች አማልክትን የሚከተለው፣ የሚያገለግለውና ለእነሱ የሚሰግደው ይህ ክፉ ሕዝብ ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጭ እንደሆነው እንደዚህ ቀበቶ ይሆናል።” (ኤር. 13:10) ይሖዋ ሕዝቡን ያስተማረው እንዴት ባለ አስገራሚ መንገድ ነው! ኤርምያስ ምንም ጥቅም የሌለው ሊመስል በሚችል ጉዳይም እንኳ ታዛዥ መሆኑ ይሖዋ የሕዝቡን ልብ ለመንካት ባደረገው ጥረት ትልቅ አስተዋጽኦ ለማበርከት አስችሎታል።—ኤር. 13:11
በመከራ ወቅት ሰላም ማግኘት ትችላላችሁ
16 በሥራችን ላይ እገዳ ወይም ከፍተኛ ገደብ በሚጣልበት ወቅት ከቅርንጫፍ ቢሮው ወይም ከሽማግሌዎች መመሪያ ሊሰጠን ይችላል። የእነዚህ መመሪያዎች ዓላማ እኛን ከጉዳት መጠበቅ፣ መንፈሳዊ ምግብ ማግኘታችንን እንድንቀጥል ማድረግ እንዲሁም ሁኔታው በሚፈቅደው መጠን መስበካችንን እንድንቀጥል መርዳት ነው። መመሪያው የተሰጠበት ምክንያት ሙሉ በሙሉ ባይገባህም እንኳ የተሰጠህን መመሪያ ለመታዘዝ አቅምህ የፈቀደውን ሁሉ አድርግ። (ያዕ. 3:17) በተጨማሪም ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ወይም ከጉባኤው እንቅስቃሴዎች ጋር የተያያዙ መረጃዎችን ማወቅ ለማይገባቸው ሰዎች እንዳትናገር ተጠንቀቅ።—መክ. 3:7
የይሖዋን ሥልጣን ተቀበሉ
7 በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ መመሪያዎች የተሰጡበትን ምክንያት ሙሉ በሙሉ ባንረዳም እንኳ የይሖዋን ሥልጣን እንቀበላለን እንዲሁም እንታዘዘዋለን። እንዲህ የምናደርገው በጭፍን እምነት ስለምንመራ ሳይሆን በአምላክ ላይ ስለምንተማመን ነው። ይህም ይሖዋ ለእኛ የሚበጀንን እንደሚያውቅ ከልባችን እንደምንተማመን የሚያሳይ ነው። በተጨማሪም አምላክን መታዘዛችን እሱን እንደምንወደው ያሳያል፤ ሐዋርያው ዮሐንስ “እግዚአብሔርን መውደድ ትእዛዛቱን መፈጸም ነውና” ብሏል። (1 ዮሐ. 5:3) ይሁንና ከመታዘዝ ጋር በተያያዘ ችላ ልንለው የማይገባ ሌላም ነጥብ አለ።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የኤርምያስ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
15:16, 17፦ ልክ እንደ ኤርምያስ እኛም የተስፋ መቁረጥ ስሜትን መቋቋም እንችላለን። ትርጉም ያለው የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ በአገልግሎት የይሖዋን ስም ከፍ ከፍ ማድረግና ከክፉ ጓደኞች መራቅ ይህን እንድናደርግ ያስችለናል።
ከሐምሌ 13-19
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት ኤርምያስ 16-17
መታመን ያለብን በማን ነው?
‘ቅጠሉ የማይጠወልግ’ ዛፍ
በጥንት ዘመን በሶርያና በፓለስቲና ምድር ትልልቅ የአኻያ ዛፎች በወንዞችና በጅረቶች ዳርቻ ላይ ይበቅሉ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የአኻያ ዛፎች በአብዛኛው የተጠቀሱት ከጅረቶች ወይም ‘ከወንዞች’ ጋር በተያያዘ ነው። (ዘሌዋውያን 23:40 የ1954 ትርጉም) እነዚህ ዛፎች ውኃ እንደ ልብ ባለበት ቦታ በብዛት ሊገኙ ይችላሉ። (ሕዝቅኤል 17:5) ለምለም የሆኑት እነዚህ ትልልቅ ዛፎች መዝሙራዊውም ሆነ ኤርምያስ ሊያስተላልፉት የፈለጉትን የሚከተለውን መልእክት በሚገባ ይገልጻሉ፦ የአምላክን ሕግ የመከተል ፍላጎት ያላቸውና በእሱ ሙሉ በሙሉ የሚታመኑ ሰዎች በመንፈሳዊ ጤናማ ሆነው የሚኖሩ ከመሆኑም ሌላ ‘የሚሠሩት ሁሉ ይከናወንላቸዋል።’ ደግሞስ የምንፈልገው የምንሠራው ሁሉ እንዲከናወንልን ማለትም ሕይወታችን ስኬታማ እንዲሆን አይደለም?
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
በይሖዋ አሠራር ላይ እምነት አላችሁ?
7 ይሖዋ ምንጊዜም ትክክለኛውን ነገር እንደሚያደርግ በሙሉ ልባችን እንተማመናለን። ፈተና የሚሆንብን ግን ሰብዓዊ ወኪሎቹ ላይ እምነት መጣል ሊሆን ይችላል። ‘በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ኃላፊነት ያላቸው ሰዎች ውሳኔ የሚያደርጉት የይሖዋን መመሪያ ተከትለው ነው ወይስ በራሳቸው?’ ብለን የምናስብበት ጊዜ ሊኖር ይችላል። በጥንት ዘመን የኖሩ አንዳንድ ሰዎችም እንደዚህ ተሰምቷቸው ሊሆን ይችላል። በአንቀጽ 3 ላይ የተጠቀሱትን ታሪኮች እንደ ምሳሌ እንመልከት። የሰንበትን ሕግ የጣሰው ሰው ዘመድ የሆነ አንድ ግለሰብ ‘እውነት ሙሴ የሞት ፍርዱን ያስተላለፈው ይሖዋን ጠይቆ ነው?’ ብሎ አስቦ ሊሆን ይችላል። ዳዊት ሚስቱን የወሰደበት የሂታዊው የኦርዮ ጓደኞችም፣ ዳዊት ቅጣት የሚገባው ሆኖ ሳለ ሥልጣኑን ተጠቅሞ እንዳመለጠ ሊያስቡ ይችላሉ። ልናስታውሰው የሚገባ አንድ ሐቅ ግን አለ፦ ይሖዋ በሚያምናቸውና በሾማቸው ምድራዊ ወኪሎቹ የማንተማመን ከሆነ በእሱ እንተማመናለን ማለት አንችልም።
8 በዛሬው ጊዜ ይሖዋ የድርጅቱን ምድራዊ ክፍል የሚመራው ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ አማካኝነት ነው። (ማቴ. 24:45) በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበረው የበላይ አካል ሁሉ ይህ ባሪያም በመላው ዓለም የሚገኙ የአምላክ ሕዝቦችን ይመራል እንዲሁም ለጉባኤ ሽማግሌዎች መመሪያ ያስተላልፋል። (የሐዋርያት ሥራ 16:4, 5ን አንብብ።) ሽማግሌዎች ደግሞ የተሰጣቸው መመሪያ በጉባኤዎች ውስጥ ተፈጻሚነት እንዲኖረው ያደርጋሉ። ከድርጅቱ እና ከሽማግሌዎች የምናገኘውን መመሪያ በመታዘዝ በይሖዋ አሠራር እንደምንተማመን እናሳያለን።
ከሐምሌ 20-26
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት ኤርምያስ 18-19
ወደቅን ማለት አበቃልን ማለት አይደለም
“የምታገለግሉትን . . . ምረጡ”
10 እንደ ኢየሱስ ሁሉ እኛም ይሖዋን የምናገለግልበት ዋነኛ ምክንያት እሱን በጣም ስለምንወደው ነው። (ማቴዎስ 22:37ን አንብብ።) ስለ ይሖዋ ባሕርያት ስንማር ወደ እሱ ይበልጥ ለመቅረብ እንነሳሳለን። ይሖዋ የሚያሳየንን ትዕግሥት እንደ ምሳሌ እንውሰድ። እስራኤላውያን ባመፁበት ወቅት “እባካችሁ፣ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ” በማለት ተማጽኗቸዋል። (ኤር. 18:11) ይሖዋ ፍጽምና እንደሚጎድለንና አፈር እንደሆንን ያስታውሳል። (መዝሙር 103:13, 14ን አንብብ።) በይሖዋ ትዕግሥትና በሌሎቹ ማራኪ ባሕርያቱ ላይ ስታሰላስል እሱን ለዘላለም ለማገልገል አትነሳሳም?
ከመጥፎ ምኞቶች ጋር በምናደርገው ትግል አሸናፊዎች መሆን የምንችለው እንዴት ነው?
11 ኃጢአተኛ በመሆናችን የተነሳ፣ አቅመ ቢስ እንደሆንን ማለትም መጥፎ ምኞቶችን ማሸነፍ እንደማንችል ሊሰማን ይችላል። ሆኖም እንዲህ ብሎ የሚነግረንን በውስጣችን ያለውን ድምፅ ልንሰማው አይገባም። ለምን? ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ኃጢአት በእኛ ላይ “መንገሡን” እንዲቀጥል አለመፍቀድ እንደምንችል ይናገራል። (ሮም 6:12ን አንብብ።) ይህም ሲባል፣ መጥፎ ምኞቶችን ላለመፈጸም መምረጥ እንችላለን ማለት ነው። (ገላ. 5:16) ይሖዋ ፈተናን ማሸነፍ እንደምንችል ይተማመንብናል፤ ባይተማመንብን ኖሮ እንዲህ እንድናደርግ አይጠብቅብንም ነበር። (ዘዳ. 30:11-14፤ ሮም 6:6፤ 1 ተሰ. 4:3) በእርግጥም ከመጥፎ ምኞቶች ጋር በምናደርገው ትግል አቅመ ቢስ አይደለንም።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
ከመሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች አሁንም መማር ትችላለህ?
5 ይሖዋ ፈጣሪ ነው የሚለው እውነት ትሕትና ያስተምረናል። ኢዮብ በራሱና በሌሎች ሰዎች ላይ ከልክ በላይ ባተኮረ ጊዜ ይሖዋ፣ ሁሉን ቻይ ፈጣሪ መሆኑን አስታውሶታል። (ኢዮብ 38:1-4) ይህም ኢዮብ የአምላክ መንገድ ከሰዎች መንገድ እጅግ የላቀ እንደሆነ እንዲገነዘብ ረድቶታል። ከጊዜ በኋላ ነቢዩ ኢሳይያስ “ሸክላ፣ ሠሪውን ‘የምትሠራው ምንድን ነው?’ ይለዋል?” በማለት ጽፏል።—ኢሳይያስ 45:9-12ን አንብብ።
ከሐምሌ 27–ነሐሴ 2
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት ኤርምያስ 20-21
ደፋር ሰባኪ ነበር
እንደ ኤርምያስ በንቃት ተጠባበቁ
9 ይሖዋ መጀመሪያ ባናገረው ወቅት ኤርምያስ ኃላፊነቱን ላለመቀበል ሰበብ አስባብ ደርድሮ ነበር። ከዚህ ማየት እንደሚቻለው በኋላ ላይ ያሳየው ድፍረትና ቆራጥነት በተፈጥሮው ያገኘው ነገር አልነበረም። ኤርምያስ በነቢይነት ባገለገለበት ወቅት አስደናቂ ጥንካሬ ሊኖረው የቻለው በአምላክ ሙሉ በሙሉ ይታመን ስለነበር ነው። በእውነትም ይሖዋ “እንደ ኀያል ተዋጊ” ከነቢዩ ጋር ስለነበር ኤርምያስን ደግፎታል፤ እንዲሁም ተልእኮውን እንዲወጣ ብርታት ሰጥቶታል። (ኤር. 20:11) ኤርምያስ ያለ ፍርሃት በድፍረት በመናገር በጣም ይታወቅ ስለነበር ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ሲያከናውን ያዩት አንዳንዶች ኤርምያስ ተመልሶ እንደመጣ አስበው ነበር!—ማቴ. 16:13, 14
‘የአምላክን ቃል በድፍረት ተናገሩ’
8 ነቢዩ ኤርምያስ ድፍረት ለማግኘት ምን እንደረዳውም እንመልከት። ይሖዋ ኤርምያስን ለሕዝቦች ነቢይ እንዲሆን በሾመው ጊዜ ኤርምያስ “እንዴት እንደምናገር አላውቅም፤ ገና ሕፃን ልጅ ነኝና” በማለት መልሶለት ነበር። (ኤር. 1:4-6) ከጊዜ በኋላ ግን ኤርምያስ የስብከቱን ሥራ በጽናትና በድፍረት ከማከናወኑ የተነሳ ብዙ ሰዎች መዓት እንደሚያውጅ አድርገው ተመልክተውት ነበር። (ኤር. 38:4) የይሖዋን የፍርድ መልእክት ከ65 ለሚበልጡ ዓመታት በድፍረት አውጇል። ኤርምያስ ያለ ምንም ፍርሃት በድፍረት በመስበኩ በእስራኤል ውስጥ በጣም ታውቆ ስለነበር ከ600 ዓመት ገደማ በኋላ ኢየሱስ በድፍረት ሲሰብክ አንዳንዶች ኤርምያስ ዳግም ሕያው የሆነ መስሏቸው ነበር። (ማቴ. 16:13, 14) መጀመሪያ ላይ ይህን ሥራ ለመጀመር አመንትቶ የነበረው ነቢዩ ኤርምያስ ዓይን አፋርነቱን ለማሸነፍ የቻለው እንዴት ነው? “ቃሉ በልቤ እንደ እሳት፣ በዐጥንቴም ውስጥ እንደ ረመጥ ሆነብኝ፤ ዐፍኜ መያዝ አቃተኝ” በማለት ተናግሯል። (ኤር. 20:9) አዎን፣ የይሖዋ ቃል ለኤርምያስ ኃይል የሰጠው ከመሆኑም ሌላ እንዲናገር ገፋፍቶታል።
9 ሐዋርያው ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ እንዲህ ብሏል፦ “የአምላክ ቃል ሕያውና ኃይለኛ ነው፤ በሁለት በኩል ስለት ካለው ከየትኛውም ሰይፍ የበለጠ ስለታም ነው፤ ነፍስንና መንፈስን እንዲሁም መገጣጠሚያንና መቅኒን እስኪለያይ ድረስ ሰንጥቆ ይገባል፤ የልብንም ሐሳብና ዓላማ መረዳት ይችላል።” (ዕብ. 4:12) የአምላክ ቃል ወይም መልእክት ልክ እንደ ኤርምያስ ለእኛም ድፍረት ሊሰጠን ይችላል። አምላክ መጽሐፍ ቅዱስን ያስጻፈው በሰዎች ተጠቅሞ ቢሆንም ይህ መጽሐፍ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ እንጂ ሰብዓዊ ጥበብ የያዙ መጻሕፍት ስብስብ እንዳልሆነ አስታውስ። ሁለተኛ ጴጥሮስ 1:21 እንዲህ ይላል፦ “መቼም ቢሆን ትንቢት በሰው ፈቃድ አልመጣም፤ ከዚህ ይልቅ ሰዎች ከአምላክ የተቀበሉትን ትንቢት በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው ተናገሩ።” ጊዜ ወስደን ትርጉም ያለው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስናደርግ አእምሯችን በመንፈስ ቅዱስ መሪነት በተጻፈው መልእክት ይሞላል። (1ቆሮንቶስ 2:10ን አንብብ።) ይህ መልእክት በውስጣችን “እንደ እሳት” ስለሚሆንብን አፍነን መያዝ ያቅተናል።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
ይሖዋን “የሚያውቅ ልብ” አለህ?
11 ይሖዋ እያንዳንዳችን በእሱ ፊት ተቀባይነት ያለው አቋም እንድንይዝና ይህን አቋሟችንን ጠብቀን እንድንኖር ይፈልጋል። ኤርምያስ ጻድቁን ሰው በተመለከተ ሲናገር “ጻድቁን የምትፈትን ልብንና አእምሮን የምትመረምር፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ሆይ” ብሏል። (ኤር. 20:12) ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ የጻድቁን ሰው ልብ እንኳ የሚመረምር ከሆነ እኛም ልባችንን በሐቀኝነት መመርመር አይኖርብንም? (መዝሙር 11:5ን አንብብ።) እንዲህ በምናደርግበት ጊዜ በቸልታ ልናልፈው የማይገባ አመለካከት ወይም ግብ እንዳለን አሊያም ደግሞ አንድ ዓይነት ስሜት እንደተጠናወተን እንገነዘብ ይሆናል። ልባችን በተወሰነ መጠን እንዲደነዝዝ ያደረገ ምሳሌያዊ ‘የልብ ሸለፈት’ እንዳለ ልናስተውልና ማስወገድ እንደሚኖርብን ልንገነዘብ እንችላለን። በዚህ መንገድ ምሳሌያዊ የልብ ቀዶ ሕክምና እናደርጋለን። ምሳሌያዊ ልብህን መመርመርህ ጥሩ እንደሆነ ከተገነዘብክ ትኩረት ማድረግ የሚያስፈልግህ ምን ላይ ነው? አስፈላጊውን ማስተካከያ ማድረግ የምትችለውስ እንዴት ነው?—ኤር. 4:4
ከነሐሴ 3-9
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት ኤርምያስ 22-23
ጥሩ እረኞች በመንጋው ላይ በጎ ተጽዕኖ ያሳድራሉ
ይሖዋ በሐሰተኛ አስተማሪዎች ላይ ያስተላለፈው ፍርድ
4 አዎን፣ እነዚህ ነቢያት ወይም አስተማሪዎች በመጥፎ ሥነ ምግባራቸው መጥፎ አርዓያ በመሆናቸው ሕዝቡም እነርሱ የሚያደርጉትን የመሰለ ድርጊት እንዲፈጽም አደፋፍረውታል። በአሁኑ ጊዜ በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ያለውን ሁኔታ ተመልከቱ! በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ያለው ሁኔታ በኤርምያስ ዘመን ከነበረው ጋር አንድ ዓይነት አይደለምን? በአሁኑ ጊዜ ቀሳውስት አመንዝሮችና ግብረ ሰዶም ፈጻሚዎች ከቅስናቸው ሳይወርዱ እንዲቆዩ፣ እንዲያውም ቤተ ክርስቲያናዊ ሥርዓቶችን እንዲመሩ ፈቅደዋል። ታዲያ የአብያተ ክርስቲያናት አባሎች የሆኑ በጣም ብዙ ሰዎች ምግባረ ብልሹ መሆናቸው ያስደንቃልን?
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የኤርምያስ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
23:33—“የእግዚአብሔር ሸክም” ምንድን ነው? በኤርምያስ ዘመን ነቢዩ ስለ ኢየሩሳሌም ጥፋት ያወጀው ክብደት ያለው የፍርድ መልእክት ለወገኖቹ ሸክም ሆኖባቸው ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ ይሖዋ እርሱን የማይሰሙት ሰዎች ሸክም ስለሆኑበት ይወረውራቸዋል። በተመሳሳይም በሕዝበ ክርስትና ላይ ስለሚመጣው ጥፋት የሚናገረው ቅዱስ ጽሑፋዊ መልእክት ለሕዝበ ክርስትና ሸክም ሆኖባታል። ይህን መልእክት ሰምተው እርምጃ የማይወስዱ ሰዎች ደግሞ ለአምላክ ከባድ ሸክም ሆነውበታል።
ከነሐሴ 10-16
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት ኤርምያስ 24-25
አንድን “በለስ” ጥሩ ወይም መጥፎ ነው እንዲባል የሚያደርገው ምንድን ነው?
ጥሩና መጥፎ ፍሬዎች
6 ኢኮንያን ወይም ኢዮአቂን ኢየሩሳሌምን በፈቃዱ ለናቡከደናፆር አሳልፎ በሰጠበት ጊዜ በይሁዳ ላይ ከነገሠ ገና ሦስት ወር ከአሥር ቀኑ ነበር። ከእርሱ ጋር ወደ ግዞት ከተወሰዱት ሰዎች መካከል ዳንኤልና አናንያ፣ ሚሳኤልና አዛርያ የተባሉት ሦስቱ ባልንጀሮቹ እንዲሁም ሕዝቅኤል ይገኙ ነበር። የባቢሎን ንጉሥ የእነዚህ ሰዎች ሕይወት እንዲጠበቅ ስላደረገ ይሖዋ ‘ወደ ከለዳውያን ምድር የሰደደውን የይሁዳን ምርኮ ሁሉ ለበጎነት ተመልክቷል’ ሊባል ይቻላል። በተጨማሪም “ዓይኔንም ለበጎነት በእነርሱ ላይ አደርጋለሁ” እንዳለ አስተውለሃልን? ይህ ትንቢት የተፈጸመው እንዴት ነበር? ከ80 ዓመት በኋላ፣ በ537 ከዘአበ ይሖዋ ንጉሥ ቂሮስ ከዘሮቻቸው ቀሪዎች ወደ ይሁዳ እንዲመለሱ የሚፈቅድ አዋጅ እንዲያወጣ አደረገው። እነዚህ ታማኝ አይሁዶች የኢየሩሳሌምን ከተማ መልሰው ሠሩ፤ አምላካቸው ይሖዋ የሚመለክበትን አዲስ ቤተ መቅደስ አነጹ፤ በሙሉ ልባቸውም ወደ ይሖዋ ተመለሱ። ስለዚህ በይሖዋ ዓይን እነዚህ ምርኮኞችና ዘሮቻቸው አስቀድሞ እንደ ደረሰ በጣም ጥሩ በለስ ነበሩ ሊባል ይቻላል።
ጥሩና መጥፎ ፍሬዎች
10 በእውነትም ሴዴቅያስ በይሖዋ ዓይን ‘ክፉ በለስ’ ሆኗል። ለንጉሥ ናቡከደነፆር በይሖዋ ስም የማለውን መሐላ አፍርሶ ከማመፁም በላይ ይሖዋ በኤርምያስ በኩል የዘረጋለትን ምሕረት በጭራሽ አልቀበልም አለ። እንዲያውም ኤርምያስን እስከማሳሰር ደርሶ ነበር! ዕዝራ የዚህን ንጉሥ ዝንባሌ አጠቃልሎ ሲገልጽ በ2 ዜና መዋዕል 36:12 ላይ “በአምላኩም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ፤ በእግዚአብሔርም . . . ፊት ራሱን አላዋረደም” ማለቱ አያስደንቅም። ሴዴቅያስና በኢየሩሳሌም ቀርተው የነበሩት ሰዎች በይሖዋ ዓይን የተባላሸና የበሰበሰ በለስ እንዳለበት ቅርጫት ነበሩ!
ይሖዋን “የሚያውቅ ልብ” አለህ?
3 በመጀመሪያ አምላክ በኤርምያስ ዘመን ስለ በለስ የተናገረውን ሐሳብ እንመልከት። በ617 ዓ.ዓ. የይሁዳ ብሔር በአስከፊ መንፈሳዊ ሁኔታ ላይ ይገኝ ነበር። አምላክ ወደፊት ምን እንደሚመጣ በራእይ ያሳወቀ ሲሆን ሁኔታውን በሁለት ዓይነት የበለስ ፍሬ ይኸውም “መልካም” በሆነና “እጅግ መጥፎ” በሆነ በለስ በምሳሌያዊ መንገድ ገልጾታል። (ኤርምያስ 24:1-3ን አንብብ።) መጥፎው በለስ፣ በንጉሥ ናቡከደነፆርና በወታደሮቹ ከባድ ቅጣት ይጠብቃቸው የነበሩትን ንጉሥ ሴዴቅያስንና መሰሎቹን ያመለክታል። በወቅቱ በባቢሎን የነበሩትን ሕዝቅኤልን፣ ዳንኤልንና ሦስቱ ጓደኞቹን እንዲሁም ከጥቂት ጊዜ በኋላ ወደዚያ የተወሰዱትን አንዳንድ አይሁዳውያን በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል? እነዚህ ሰዎች በመልካም በለስ ተመስለዋል። ከእነሱ መካከል የሚቀሩት ሰዎች ኢየሩሳሌምንና ቤተ መቅደሷን ዳግመኛ ለመገንባት ወደዚያ የመመለስ ተስፋ ነበራቸው። ይህም ጊዜውን ጠብቆ ተፈጽሟል።—ኤር. 24:8-10፤ 25:11, 12፤ 29:10
ይሖዋን “የሚያውቅ ልብ” አለህ?
10 አምላክ ምሳሌያዊውን ልብ ጠንቅቀን ማወቅ እንድንችል ስለሚረዳን እጅግ አመስጋኞች ነን! ይሁንና አንዳንዶች ‘ይህ ጉዳይ በዛሬው ጊዜ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮችን ለምን ያሳስባቸዋል?’ ብለው ይጠይቁ ይሆናል። ይህ የሆነው በየጉባኤው ያሉት በርካታ ክርስቲያኖች በጥንት ዘመን እንደነበሩት አይሁዳውያን መጥፎ አካሄድ ስለተከተሉ ወይም “መጥፎ በለስ” ስለሆኑ አይደለም። ይልቁንም በዛሬው ጊዜ ያሉ የአምላክ አገልጋዮች ለእሱ ያደሩ ንጹሕ ሕዝቦች ናቸው። ይሁንና ጻድቅ የነበረው ዳዊት እንኳ “እግዚአብሔር ሆይ፤ መርምረኝ፤ ልቤንም ዕወቅ፤ ፈትነኝ፤ ሐሳቤንም ዕወቅ፤ የክፋት መንገድ በውስጤ ቢኖር እይ” ብሎ ይሖዋን እንደለመነ አትዘንጋ።—መዝ. 17:3፤ 139:23, 24
11 ይሖዋ እያንዳንዳችን በእሱ ፊት ተቀባይነት ያለው አቋም እንድንይዝና ይህን አቋሟችንን ጠብቀን እንድንኖር ይፈልጋል። ኤርምያስ ጻድቁን ሰው በተመለከተ ሲናገር “ጻድቁን የምትፈትን ልብንና አእምሮን የምትመረምር፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ሆይ” ብሏል። (ኤር. 20:12) ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ የጻድቁን ሰው ልብ እንኳ የሚመረምር ከሆነ እኛም ልባችንን በሐቀኝነት መመርመር አይኖርብንም? (መዝሙር 11:5ን አንብብ።) እንዲህ በምናደርግበት ጊዜ በቸልታ ልናልፈው የማይገባ አመለካከት ወይም ግብ እንዳለን አሊያም ደግሞ አንድ ዓይነት ስሜት እንደተጠናወተን እንገነዘብ ይሆናል። ልባችን በተወሰነ መጠን እንዲደነዝዝ ያደረገ ምሳሌያዊ ‘የልብ ሸለፈት’ እንዳለ ልናስተውልና ማስወገድ እንደሚኖርብን ልንገነዘብ እንችላለን። በዚህ መንገድ ምሳሌያዊ የልብ ቀዶ ሕክምና እናደርጋለን። ምሳሌያዊ ልብህን መመርመርህ ጥሩ እንደሆነ ከተገነዘብክ ትኩረት ማድረግ የሚያስፈልግህ ምን ላይ ነው? አስፈላጊውን ማስተካከያ ማድረግ የምትችለውስ እንዴት ነው?—ኤር. 4:4
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
ትንቢት ምንድን ነው?
አይደለም፤ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ስለ ወደፊቱ ጊዜ ብቻ የተነገሩ አይደሉም። ሆኖም ከአምላክ የሚመጡት አብዛኞቹ መልእክቶች በተዘዋዋሪም ቢሆን ስለ ወደፊቱ ጊዜ ይናገራሉ። ለምሳሌ ያህል፣ የአምላክ ነቢያት እስራኤላውያን መጥፎ መንገዳቸውን እንዲተዉ በተደጋጋሚ አስጠንቅቀው ነበር። እነዚህ ማስጠንቀቂያዎች፣ እስራኤላውያን ማስጠንቀቂያውን ከሰሙ ወደፊት የሚያገኙትን በረከት ካልሰሙ ደግሞ ወደፊት የሚጠብቃቸውን ቅጣት የሚገልጹ ነበሩ። (ኤርምያስ 25:4-6) ውጤቱ እስራኤላውያን ለመከተል በሚመርጡት ጎዳና ላይ የተመካ ነበር።—ዘዳግም 30:19, 20
ከነሐሴ 17-23
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት ኤርምያስ 26-28
በሐሰት ነቢያት አትታለሉ
እውነትን ለይተህ ማወቅ ትችላለህ?
13 ‘የትክክለኛውን ትምህርት መሥፈርት አጥብቀህ ያዝ።’ (2 ጢሞ. 1:13) ‘የትክክለኛው ትምህርት መሥፈርት’ የሚለው አገላለጽ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ክርስቲያናዊ ትምህርቶች ያመለክታል። (ዮሐ. 17:17) የምናምንባቸው ነገሮች ሁሉ የተመሠረቱት በእነዚህ ትምህርቶች ላይ ነው። የይሖዋ ድርጅት ይህን መሥፈርት አጥብቀን እንድንከተል አስተምሮናል። ይህን ማድረጋችንን እስከቀጠልን ድረስ እንባረካለን።
14 ‘የትክክለኛውን ትምህርት መሥፈርት’ አጥብቀን ባንከተል ምን ሊከሰት ይችላል? አንድ ምሳሌ እንመልከት። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች መካከል ‘የይሖዋ ቀን ደርሷል’ የሚል ወሬ መዛመት ጀምሮ የነበረ ይመስላል። እንዲህ ዓይነት ሐሳብ የያዘ በሐዋርያው ጳውሎስ የተጻፈ የሚመስል ደብዳቤ ደርሷቸው ሊሆን ይችላል። አንዳንድ የተሰሎንቄ ክርስቲያኖች ጊዜ ወስደው እውነታውን ሳያጣሩ ወሬውን ያመኑ ከመሆኑም በተጨማሪ ለሌሎች አሰራጭተውት ነበር። ጳውሎስ ከእነሱ ጋር በነበረበት ጊዜ ያስተማራቸውን ነገር ቢያስታውሱ ኖሮ እንዲህ ባለው ወሬ ባልተታለሉ ነበር። (2 ተሰ. 2:1-5) ጳውሎስ ወንድሞቹን የሰሙትን ሁሉ እንዳያምኑ መክሯቸዋል። ጳውሎስ የተሰሎንቄ ክርስቲያኖች በድጋሚ ለስህተት እንዳይጋለጡ ሲል ሁለተኛውን ደብዳቤውን የደመደመው እንዲህ በማለት ነው፦ “እኔ ጳውሎስ በገዛ እጄ የጻፍኩላችሁ ሰላምታ ይድረሳችሁ፤ ይህ የእጅ ጽሑፍ የደብዳቤዎቼ ሁሉ መለያ ነው፤ አጻጻፌ እንዲህ ነው።”—2 ተሰ. 3:17
15 ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ክርስቲያኖች ከተናገረው ሐሳብ ምን እንማራለን? ከመጽሐፍ ቅዱስ ከተማርናቸው እውነቶች ጋር የማይስማማ ነገር ወይም አስደንጋጭ ወሬ ስንሰማ የማስተዋል ችሎታችንን መጠቀም ይኖርብናል። በቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ውስጥ ጠላቶቻችን ከዋናው መሥሪያ ቤት የተላከ የሚመስል ደብዳቤ አሰራጭተው ነበር። ደብዳቤው አንዳንድ ወንድሞች የራሳቸውን ድርጅት እንዲያቋቁሙ የሚያበረታታ ነበር። ደብዳቤው ሲታይ እውነተኛ ይመስላል። ታማኝ የሆኑ ወንድሞች ግን በዚህ አልተታለሉም። ደብዳቤው የያዘው መልእክት አስቀድመው ከተማሯቸው ነገሮች ጋር እንደማይስማማ አስተዋሉ። ዛሬም የእውነት ጠላቶች አንዳንድ ጊዜ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ግራ እንድንጋባና በመካከላችን መከፋፈል እንዲፈጠር ለማድረግ ይጥራሉ። ‘የማመዛዘን ችሎታችን በቀላሉ እንዲናወጥ’ ከመፍቀድ ይልቅ የሰማነው ወይም ያነበብነው ነገር ከተማርናቸው እውነቶች ጋር የሚስማማ መሆን አለመሆኑን በመመዘን ራሳችንን መጠበቅ እንችላለን።—2 ተሰ. 2:2፤ 1 ዮሐ. 4:1
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
ኤርምያስ መናገሩን አላቆመም
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ባለሥልጣኖቹና ሕዝቡም ሁሉ ለካህናትና ለነቢያት፣ ‘ይህ ሰው በአምላካችን በእግዚአብሔር ስም ተናግሮአልና ሊገደል አይገባውም’ አሉ።” ኤርምያስ፣ ፈርቶ የተሰጠውን ተልዕኮ ከመፈጸም ወደኋላ ስላላለ ይሖዋ ጠብቆታል። አሁን ደግሞ ከኤርምያስ የተለየ እርምጃ የወሰደ ኦርዮ የተባለ አንድ ሌላ ነቢይ ምን እንደደረሰበት እንመልከት።
‘ኦርዮም እንደ ኤርምያስ በኢየሩሳሌም ከተማ ላይ ትንቢት ተናግሮ’ እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ንጉሥ ኢዮአቄም በኦርዮ በተናደደ ጊዜ ግን ኦርዮ ምን እንዳደረገ ታውቃለህ?— በጣም ስለፈራ የአምላክን ፈቃድ ማድረጉን ትቶ ወደ ግብፅ ሸሸ። ንጉሡም ኦርዮን ፈልገው እንዲያመጡት ወደ ግብፅ ሰዎችን ላከ። ሰዎቹ ኦርዮን ይዘው በመጡ ጊዜ ክፉው ንጉሥ ምን እንዳደረገ ታውቃለህ?— ኦርዮን በሰይፍ ገደለው!—ኤርምያስ 26:8-24
ኤርምያስ የይሖዋን ጥበቃ ያገኘው፣ ኦርዮ ግን የተገደለው ለምን ይመስልሃል?— ኤርምያስ ልክ እንደ ኦርዮ ፈርቶ እንደነበር ግልጽ ነው። ሆኖም የተሰጠውን ተልዕኮ ከመፈጸም ወደኋላ አላለም። ይሖዋን ማገልገሉን አላቆመም። ከኤርምያስ ታሪክ ምን ትምህርት ማግኘት የምንችል ይመስልሃል?— አንዳንድ ጊዜ የአምላክን ትእዛዝ መፈጸም ከባድ ሊሆንብን ይችላል፤ ሆኖም ምንጊዜም በአምላክ መታመንና ትእዛዛቱን መፈጸም ይኖርብናል።
ከነሐሴ 24-30
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት ኤርምያስ 29-30
ይሖዋ አገልጋዮቹን የሚገሥጸው በተገቢው መጠን ነው
ኤርምያስ 33:3—“ጥራኝ፤ እኔም እመልስልሃለሁ”
“ጥራኝ፤ እኔም እመልስልሃለሁ።” “ጥራኝ” የሚለው ቃል እንዲሁ የአምላክን ስም መጥራትን ብቻ የሚያመለክት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ‘አምላክን መጥራት’ የሚለው አገላለጽ በዚህ አገባቡ የሚያመለክተው በጸሎት አማካኝነት የአምላክን እርዳታና አመራር መፈለግን ነው።—መዝሙር 4:1፤ ኤርምያስ 29:12
አባታችን ይሖዋ በጣም ይወደናል
14 ይሖዋ ያሠለጥነናል። እኛ እንደ ኢየሱስ ፍጹማን አይደለንም። ስለዚህ አፍቃሪው አባታችን እኛን ለማሠልጠን ሲል አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ተግሣጽ ይሰጠናል። ቃሉ “ይሖዋ የሚወዳቸውን ይገሥጻል” ይላል። (ዕብ. 12:6, 7) ይሖዋ በተለያዩ መንገዶች ተግሣጽ ይሰጠናል። ለምሳሌ ያህል፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የምናነበው ነገር ወይም በስብሰባዎች ላይ የምናዳምጠው ትምህርት ማስተካከያ እንደሚያስፈልገን ሊጠቁመን ይችላል። አሊያም ደግሞ ሽማግሌዎች የሚያስፈልገንን እርዳታ ሊሰጡን ይችላሉ። ይሖዋ ተግሣጽ የሚሰጥበት መንገድ ምንም ይሁን ምን፣ ምንጊዜም ይህን የሚያደርገው በፍቅር ተነሳስቶ ነው።—ኤር. 30:11
ታማኝነታችሁ ሲፈተን የማስተዋል ስሜታችሁን ጠብቁ
6 ተግሣጽ ስሜታችንን ሊጎዳው ይችላል። ሆኖም በሚሰማን ስሜት ላይ ብቻ ካተኮርን ተግሣጹ ለእኛ እንደማይሠራና ከመጠን ያለፈ እንደሆነ ልናስብ እንችላለን። ይህ ደግሞ አንድ ውድ ነገር ያሳጣናል፤ ተግሣጹ የይሖዋ ፍቅር መገለጫ እንደሆነ ማየት ይሳነናል። (ዕብራውያን 12:5, 6, 11ን አንብብ።) ስሜታችን እንዲቆጣጠረን ከፈቀድን ደግሞ ሰይጣን ጥቃት እንዲሰነዝርብን አጋጣሚ እንሰጠዋለን። ሰይጣን የሚፈልገው ተግሣጹን ችላ እንድንል ይባስ ብሎም ራሳችንን ከይሖዋና ከጉባኤው እንድናርቅ ነው። አንተስ ተግሣጽ ተሰጥቶህ ከሆነ የማስተዋል ስሜትህን መጠበቅ የምትችለው እንዴት ነው?
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
ለልጆቻችሁ ተግሣጽ መስጠት የሚኖርባችሁ እንዴት ነው?
ይሖዋ ምንጊዜም ተግሣጽ የሚሰጠው በተገቢው ‘መጠን’ ነው። (ኤርምያስ 30:11፤ 46:28) ይሖዋ ተግሣጽ ሲሰጥ በግልጽ የማይታዩትን ጨምሮ ሁሉንም ሁኔታዎች ከግምት ያስገባል። ወላጆችስ እንዲህ ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው? በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው ስቲቨን እንዲህ ብሏል፦ “ናታሊ ቀለበቱን መስረቋን መካዷ ያሳዘነን ከመሆኑም ሌላ እንዲህ ያደረገችበትን ምክንያት መረዳት ቢከብደንም ዕድሜዋንና የብስለት ደረጃዋን ከግምት ለማስገባት ጥረት አደረግን።”
የኒኮል ባል ሮበርትም ሁኔታዎችን ሁሉ ከግምት ለማስገባት ጥረት ያደርጋል። ልጆቹ አጓጉል ጠባይ ሲያሳዩ ራሱን እንደሚከተለው በማለት ይጠይቃል፦ ‘ልጁ እንዲህ ዓይነት ድርጊት ሲፈጽም የመጀመሪያው ነው ወይስ ልማድ ሆኖበታል? ደክሞት ወይም አሞት ይሆን? ይህ ጠባይ ሌላ ችግር እንዳለበት የሚጠቁም ይሆን?’
በተጨማሪም ምክንያታዊ የሆኑ ወላጆች፣ ልጆች እንደ አዋቂ ሊያስቡ እንደማይችሉ ይገነዘባሉ። ክርስቲያኑ ሐዋርያው ጳውሎስ “ሕፃን በነበርኩበት ጊዜ እንደ ሕፃን እናገር፣ እንደ ሕፃን አስብ . . . ነበር” ብሎ ሲጽፍ ይህን ገልጿል። (1 ቆሮንቶስ 13:11) ሮበርት እንዲህ ይላል፦ “ነገሮችን እንዳመዛዝንና ከመጠን በላይ እንዳልናደድ የሚረዳኝ አንዱ ነገር እኔ ራሴ ልጅ ሳለሁ ምን አደርግ እንደነበረ መለስ ብዬ ማሰቤ ነው።”
ከልጃችሁ በምትጠብቁት ነገር ረገድ ምክንያታዊ መሆን የሚያስፈልጋችሁ ቢሆንም በአንፃሩ ደግሞ መጥፎ ምግባርን ወይም ዝንባሌን ችላ ማለት አሊያም እንዲህ ላለው ነገር ሰበብ መፍጠር ተገቢ አይደለም። የልጃችሁን ችሎታዎች፣ የአቅም ገደቦችና ሌሎችንም ሁኔታዎች ከግምት የምታስገቡ ከሆነ ሚዛናዊና ምክንያታዊ ተግሣጽ መስጠት ትችላላችሁ።
ከነሐሴ 31–መስከረም 6
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት ኤርምያስ 31
“አዲስ ቃል ኪዳን የምገባበት ጊዜ ይመጣል”
“የመንግሥት ካህናት” ትሆናላችሁ
7 የሕጉ ቃል ኪዳን ከመሻሩ ከብዙ ጊዜ በፊት ይሖዋ ከእስራኤል ብሔር ጋር “አዲስ ቃል ኪዳን” እንደሚገባ በነቢዩ ኤርምያስ አማካኝነት ተናግሮ ነበር። (ኤርምያስ 31:31-33ን አንብብ።) ይህ ቃል ኪዳን ከሕጉ ቃል ኪዳን በተለየ፣ የእንስሳት መሥዋዕት ሳይቀርብ የኃጢአት ይቅርታ እንዲገኝ ያደርጋል። እንዴት?
“የመንግሥት ካህናት” ትሆናላችሁ
9 አዲሱ ቃል ኪዳን የጸናው በፈሰሰው የኢየሱስ ደም አማካኝነት ነው። ይህ ደም የሰው ልጆች ከኃጢአታቸው ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይቅርታ እንዲያገኙም ያደርጋል። ኢየሱስ፣ በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ ከታቀፉት አካላት አንዱ አልነበረም። ኢየሱስ ኃጢአት ስለሌለበት የኃጢአት ይቅርታ ማግኘት አያስፈልገውም። ሆኖም አምላክ የፈሰሰውን የኢየሱስን ደም ዋጋ የአዳምን ዘሮች ለመጥቀም አውሎታል። በተጨማሪም ታማኝ የሆኑ የተወሰኑ ሰዎችን በመንፈስ ቅዱስ በመቀባት “እንደ ልጅ የመቆጠር” መብት ሰጥቷቸዋል። (ሮም 8:14-17ን አንብብ።) እነዚህ ሰዎች በአምላክ ፊት ኃጢአት እንደሌለባቸው ሆነው ስለሚቆጠሩ ኃጢአት እንደሌለበት የአምላክ ልጅ ማለትም እንደ ኢየሱስ ናቸው ሊባል ይችላል። እነዚህ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ‘ከክርስቶስ ጋር አብረው ወራሾች’ ይሆናሉ፤ እንዲሁም “የመንግሥት ካህናት” የመሆን መብት ያገኛሉ። ሕጉ ለእስራኤል ብሔር ይህን መብት ያስገኝላቸው ነበር። ሐዋርያው ጴጥሮስ ‘ከክርስቶስ ጋር አብረው ወራሾች’ ስለሆኑት ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “እናንተ . . . ከጨለማ ወደ አስደናቂ ብርሃኑ የጠራችሁን የእሱን ‘ድንቅ ባሕርያት በስፋት እንድታስታውቁ የተመረጠ ዘር፣ ንጉሣዊ ካህናት፣ ቅዱስ ብሔር፣ ልዩ ንብረት እንዲሆን የተለየ ሕዝብ’ ናችሁ።” (1 ጴጥ. 2:9) በእርግጥም አዲሱ ቃል ኪዳን በጣም አስፈላጊ ነው! የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የአብርሃም ዘር ሁለተኛ ክፍል እንዲሆኑ አስችሏቸዋል።
12 የሕጉ ቃል ኪዳን ከአዲሱ ቃል ኪዳን ጋር ሲወዳደር ምን ይመስላል? የሕጉ ቃል ኪዳን የተደረገው በይሖዋ እና በሥጋዊ እስራኤላውያን መካከል ሲሆን አዲሱ ቃል ኪዳን የተደረገው ደግሞ በይሖዋ እና በመንፈሳዊ እስራኤላውያን መካከል ነው። የቀድሞው ቃል ኪዳን መካከለኛ ሙሴ ሲሆን የአዲሱ ቃል ኪዳን መካከለኛ ደግሞ ኢየሱስ ነው። የሕጉ ቃል ኪዳን የጸናው በእንስሳት ደም አማካኝነት ሲሆን አዲሱ ቃል ኪዳን የጸናው ግን በፈሰሰው የኢየሱስ ደም አማካኝነት ነው። በሕጉ ቃል ኪዳን ሥር የነበረው የእስራኤል ብሔር መሪ ሙሴ ነበር፤ በአዲሱ ቃል ኪዳን ሥር ላሉት ግን መሪያቸው የጉባኤው ራስ የሆነው ኢየሱስ ነው።—ኤፌ. 1:22
አንድ መንጋ አንድ እረኛ
14 በኢየሱስ መንግሥት አገዛዝ ሥር በምድር ላይ ስለሚኖሩ ሰዎችስ ምን ማለት ይቻላል? እነዚህ ሰዎች የአዲሱ ቃል ኪዳን ተጠቃሚዎች ናቸው። (ገላ. 3:8,9) እነዚህ ክርስቲያኖች የዚህ ቃል ኪዳን ተካፋዮች ባይሆኑም እንኳ ነቢዩ ኢሳይያስ አስቀድሞ እንደተናገረው የሚፈለግባቸውን በማሟላት ቃል ኪዳኑን ‘ይጠብቃሉ’፤ ኢሳይያስ እንዲህ ብሏል፦ “እርሱን ለማገልገል፣ ራሳቸውን ከእግዚአብሔር [“ከይሖዋ፣” NW] ጋር ያቈራኙ መጻተኞች፣ የእግዚአብሔርን [“የይሖዋን፣” NW] ስም በመውደድ፣ እርሱንም በማምለክ፣ ሰንበትን ሳያረክሱ የሚያከብሩትን ሁሉ፣ ቃል ኪዳኔንም የሚጠብቁትን፣ ወደ ተቀደሰው ተራራዬ አመጣቸዋለሁ፤ በጸሎት ቤቴም ውስጥ ደስ አሰኛቸዋለሁ።” በመቀጠልም ይሖዋ “ቤቴ፣ ለሕዝቦች ሁሉ የጸሎት ቤት ተብሎ ይጠራል” በማለት ተናግሯል።—ኢሳ. 56:6, 7
jr 177 አን. 18
ከአዲሱ ቃል ኪዳን ተጠቃሚ መሆን ትችላለህ
18 አዲሱ ቃል ኪዳን ይሖዋ ኃጢአተኛ የሆኑ የሰው ልጆችን ይኸውም በቃል ኪዳኑ የታቀፉትን ቅቡዓንንም ሆነ በምድር ላይ የመኖር ተስፋ ያላቸውን ሰዎች የሚይዝበትን አስገራሚ መንገድ ጎላ አድርጎ ያሳያል። ይሖዋ ኃጢአታችንን አንዴ ይቅር ካለ በኋላ ዳግመኛ እንደማያነሳው እርግጠኞች መሆን እንችላለን። አምላክ አዲሱን ቃል ኪዳን እንደሚያቋቁም ከገባው ቃል እያንዳንዳችን ግሩም ትምህርት ማግኘት እንችላለን። ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘የበደሉኝን ሰዎች ይቅር እንዳልኳቸው ከተናገርኩ በኋላ በደላቸውን ዳግመኛ ባለማንሳት ይሖዋን ለመምሰል ጥረት አደርጋለሁ?’ (ማቴ. 6:14, 15) ይህ ትምህርት ቀላል ከሆኑ በደሎችም ሆነ እንደ ምንዝር ካሉ ከባድ በደሎች ጋር በተያያዘ ይሠራል። ተበዳዩ ወገን ምንዝር የፈጸመውን ግለሰብ ይቅር ለማለት ፈቃደኛ እንደሆነ ከገለጸ በኋላ ‘ኃጢአታቸውን ከእንግዲህ አላስታውስም’ ያለውን የይሖዋን ምሳሌ ለመከተል ጥረት ማድረጉ ተገቢ አይሆንም? እርግጥ ነው፣ የተፈጸመብንን በደል መርሳት ቀላል ላይሆን ይችላል፤ ሆኖም ይህ ይሖዋን መምሰል የምንችልበት አንዱ መንገድ ነው።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
ኤርምያስ፣ ራሔል ስለ ልጆቿ እንዳለቀሰች ሲናገር ምን ማለቱ ነበር?
የኤርምያስ መጽሐፍ በተጻፈበት ጊዜ፣ አሥሩን ነገድ ያቀፈው ሰሜናዊው መንግሥት በአሦራውያን እጅ ወድቆና አብዛኞቹ ሕዝቦቹ በምርኮ ተወስደው ነበር። ይሁን እንጂ አንዳንዶቹ የኤፍሬም ዝርያዎች ወደ ይሁዳ ክልል ሸሽተው ሊሆን ይችላል። በ607 ዓ.ዓ. ባቢሎናውያን ሁለት ነገዶችን ያቀፈውን የደቡቡን የይሁዳ መንግሥት ድል አደረጉ። ከምርኮኞቹ ብዙዎቹ ከኢየሩሳሌም በስተ ሰሜን 8 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው በራማ ተሰብስበው ነበር። (ኤር. 40:1) ምናልባትም አንዳንዶቹ የተገደሉት የብንያም ክልል በሆነውና ራሔል በተቀበረችበት በዚህ ስፍራ ሳይሆን አይቀርም። (1 ሳሙ. 10:2) ስለዚህ ራሔል ስለ ልጆቿ እንዳለቀሰች የሚገልጸው ሐሳብ በምሳሌያዊ ሁኔታ በአጠቃላይ ስለ ብንያማውያን ወይም በተለይ በራማ ስለነበሩት ማልቀሷን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። አሊያም ደግሞ ይህ አገላለጽ የአምላክ ሕዝቦች እናቶች በሙሉ፣ ስለሞቱት ወይም በምርኮ ስለተወሰዱት እስራኤላውያን ማልቀሳቸውን የሚያመለክት ይሆናል።
በዚያም ሆነ በዚህ ኤርምያስ፣ ራሔል ስለ ልጆቿ ማልቀሷን አስመልክቶ የተናገረው ሐሳብ ከብዙ መቶ ዘመናት በኋላ የሕፃኑ የኢየሱስ ሕይወት አደጋ ላይ ወድቆ በነበረበት ወቅት የተፈጸመውን ሁኔታ የሚገልጽ ትንቢት ነበር። ንጉሥ ሄሮድስ፣ ከኢየሩሳሌም በስተ ደቡብ በኩል በነበረችው በቤተልሔም የሚገኙ ዕድሜያቸው ሁለት ዓመትና ከዚያ በታች የሚሆኑ ወንድ ልጆች በሙሉ እንዲገደሉ ትእዛዝ አውጥቶ ነበር። በመሆኑም እነዚያ ወንዶች ልጆች ስለተገደሉ “የሉም” ሊባል ይችላል። ልጆቻቸው የተገደሉባቸው እናቶች ጩኸትና ለቅሶ በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ! ለቅሷቸው ከኢየሩሳሌም በስተ ስሜን በኩል እስከምትገኘው እስከ ራማ ድረስ የተሰማ ያህል ነበር።—ማቴ. 2:16-18