የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • es26 ገጽ 98-108
  • ጥቅምት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ጥቅምት
  • ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2026
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ሐሙስ፣ ጥቅምት 1
  • ዓርብ፣ ጥቅምት 2
  • ቅዳሜ፣ ጥቅምት 3
  • እሁድ፣ ጥቅምት 4
  • ሰኞ፣ ጥቅምት 5
  • ማክሰኞ፣ ጥቅምት 6
  • ረቡዕ፣ ጥቅምት 7
  • ሐሙስ፣ ጥቅምት 8
  • ዓርብ፣ ጥቅምት 9
  • ቅዳሜ፣ ጥቅምት 10
  • እሁድ፣ ጥቅምት 11
  • ሰኞ፣ ጥቅምት 12
  • ማክሰኞ፣ ጥቅምት 13
  • ረቡዕ፣ ጥቅምት 14
  • ሐሙስ፣ ጥቅምት 15
  • ዓርብ፣ ጥቅምት 16
  • ቅዳሜ፣ ጥቅምት 17
  • እሁድ፣ ጥቅምት 18
  • ሰኞ፣ ጥቅምት 19
  • ማክሰኞ፣ ጥቅምት 20
  • ረቡዕ፣ ጥቅምት 21
  • ሐሙስ፣ ጥቅምት 22
  • ዓርብ፣ ጥቅምት 23
  • ቅዳሜ፣ ጥቅምት 24
  • እሁድ፣ ጥቅምት 25
  • ሰኞ፣ ጥቅምት 26
  • ማክሰኞ፣ ጥቅምት 27
  • ረቡዕ፣ ጥቅምት 28
  • ሐሙስ፣ ጥቅምት 29
  • ዓርብ፣ ጥቅምት 30
  • ቅዳሜ፣ ጥቅምት 31
ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2026
es26 ገጽ 98-108

ጥቅምት

ሐሙስ፣ ጥቅምት 1

ይሖዋን በጉጉት እጠባበቃለሁ።—ሚክ. 7:7

አምልኳችንን ስለምናከናውንበት መንገድ በየጊዜው ቲኦክራሲያዊ መመሪያዎች ይሰጡናል። መመሪያው የሚመጣው ከጉባኤያችን ሽማግሌዎች፣ ከወረዳ የበላይ ተመልካች፣ ከቅርንጫፍ ቢሮው ወይም ከበላይ አካሉ ሊሆን ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ግን መመሪያዎቹ የተሰጡበት ምክንያት አይገባን ይሆናል። እኛን የሚታየን መመሪያውን ተግባራዊ ማድረግ አስቸጋሪ መሆኑ ሊሆን ይችላል። አልፎ ተርፎም መመሪያውን በሰጡት ወንድሞች ድክመት ላይ ማተኮር ልንጀምር እንችላለን። በእምነት የምንመላለስ ከሆነ ይሖዋ ድርጅቱን እንደሚመራና ያለንበትን ሁኔታ እንደሚያውቅ እንተማመናለን። በመሆኑም በፍጥነትና በደስታ መመሪያውን እንታዘዛለን። (ዕብ. 13:17) ታዛዥ መሆናችን ለጉባኤው አንድነት አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት እንገነዘባለን። (ኤፌ. 4:2, 3) አመራር የሚሰጡት ወንድሞች ፍጹም ባይሆኑም እንኳ ለታዛዥነታችን ይሖዋ እንደሚባርከን እርግጠኞች ነን። (1 ሳሙ. 15:22) መታረም ያለበት ነገር ካለ ደግሞ ይሖዋ በራሱ ጊዜ ያስተካክለዋል። w25.03 23-24 አን. 13-14

ዓርብ፣ ጥቅምት 2

ሚስጥርን የሚገልጥ አምላክ በሰማያት አለ።—ዳን. 2:28

የምንኖርበት ዘመን አስደናቂ ነው። በየዕለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ሲፈጸሙ በዓይናችን እንመለከታለን። ለምሳሌ ‘የሰሜኑ ንጉሥ’ እና “የደቡቡ ንጉሥ” ዓለምን ለመቆጣጠር እርስ በርሳቸው ሲታገሉ እናያለን። (ዳን. 11:40 ግርጌ) የአምላክ መንግሥት ምሥራች ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ እየተሰበከ ነው፤ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችም አዎንታዊ ምላሽ እየሰጡ ነው። (ኢሳ. 60:22፤ ማቴ. 24:14) በተጨማሪም “በተገቢው ጊዜ” የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ እየቀረበልን ነው። (ማቴ. 24:45-47) ይሖዋ በቅርቡ ስለሚከሰቱ ጉልህ ክንውኖች ይበልጥ ግልጽ የሆነ ግንዛቤ እንዲኖረን እየረዳን ነው። (ምሳሌ 4:18) ታላቁ መከራ በሚጀምርበት ወቅት፣ ያንን አስቸጋሪ ጊዜ በታማኝነት ለማለፍና በመንፈሳዊ ለማበብ የሚያስፈልገንን ነገር ሁሉ እንደምናውቅ መተማመን እንችላለን። ይሁንና በቅርቡ ከሚከሰቱት ነገሮች ጋር በተያያዘ የማናውቃቸው ነገሮች መኖራቸውን አምነን መቀበል ይኖርብናል። w24.05 8 አን. 1-2

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 3

በአንደበቱ ስም አያጠፋም።—መዝ. 15:3

መዝሙራዊው ስም ማጥፋትን ለይቶ ጠቅሷል። ስም ማጥፋት ምንድን ነው? አንድ ሰው በሌሎች ዘንድ ያተረፈውን መልካም ስም ለማጠልሸት ተብሎ የሚነገር የሐሰት ወሬ ነው። መዝሙር 15:3 በይሖዋ ድንኳን ውስጥ በእንግድነት የሚስተናገዱ ሰዎች በባልንጀሮቻቸው ላይ መጥፎ ነገር እንደማይሠሩና የወዳጆቻቸውን ስም እንደማያጎድፉም ይናገራል። (መዝ. 15:1) ይህ ምንን ያካትታል? ስለ አንድ ሰው አሉታዊ መረጃ በማስተላለፍ ሳይታወቀን ስሙን ልናጎድፍ እንችላለን። አንዳንድ ሁኔታዎችን እንደ ምሳሌ እንውሰድ፦ (1) አንዲት እህት የሙሉ ጊዜ አገልግሎቷን አቆመች፤ (2) አንድ ባልና ሚስት በቤቴል ማገልገላቸውን አቆሙ፤ (3) አንድ ወንድም የጉባኤ ሽማግሌ ወይም የጉባኤ አገልጋይ ሆኖ ማገልገሉን አቆመ። ለእነዚህ ለውጦች ምክንያት የሆነውን ነገር መገመትና ግምታችንን ለሌሎች መናገር ተገቢ ይሆናል? ለእነዚህ ለውጦች ምክንያት የሚሆኑ እኛ የማናውቃቸው ብዙ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ። ከዚህም በተጨማሪ በይሖዋ ድንኳን ውስጥ በእንግድነት የሚስተናገድ ሰው “በባልንጀራው ላይ መጥፎ ነገር አይሠራም፤ የወዳጆቹንም ስም አያጎድፍም።” w24.06 11-12 አን. 11-13

እሁድ፣ ጥቅምት 4

ይሖዋን ሁልጊዜ በፊቴ አደርገዋለሁ። እሱ በቀኜ ስላለ ፈጽሞ አልናወጥም።—መዝ. 16:8

ለይሖዋ ያለንን ፍርሃት ለማጠናከር ማንኛውንም ውሳኔ ከማድረጋችን በፊት እሱን የሚያስደስተው ምን እንደሆነ ማሰብ ይኖርብናል። የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን ስታነብ ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘እኔ በዚያ ሁኔታ ውስጥ ብሆን ኖሮ ምን ዓይነት ውሳኔ አደርግ ነበር?’ ለምሳሌ አሥሩ የእስራኤል የነገድ አለቆች ይሖዋ ለእስራኤላውያን እንደሚሰጥ ቃል የገባትን ምድር ከሰለሉ በኋላ አሉታዊ ነገር በተናገሩበት ወቅት በቦታው እንደነበርክ አድርገህ አስብ። እነሱ ያመጡትን ወሬ አምነህ ለፍርሃት እጅ ትሰጥ ነበር? ወይስ ለይሖዋ ያለህ ፍቅርና እሱን ለማስደሰት ያለህ ፍላጎት ያሸንፍ ነበር? በወቅቱ የነበረው የእስራኤል ትውልድ ኢያሱና ካሌብ የተናገሩት ነገር እውነት መሆኑን ሳይገነዘብ ቀርቷል። በመሆኑም ወደ ተስፋይቱ ምድር የመግባት አጋጣሚውን አጣ።—ዘኁ. 14:10, 22, 23፤ w24.07 10 አን. 7

ሰኞ፣ ጥቅምት 5

ልብን የሚመረምር . . . ይሖዋ ነው።—ምሳሌ 17:3

የነቢዩ ሆሴዕ ሚስት የሆነችው ጎሜር ሆሴዕን ትታ ወደ ሌሎች ወንዶች ሄደች። ታዲያ ጎሜር ምንም ተስፋ የላትም ማለት ነው? ልብን ማንበብ የሚችለው ይሖዋ ሆሴዕን እንዲህ አለው፦ “የእስራኤል ሕዝብ ሌሎች አማልክትን የሚከተሉ . . . ሆነው ሳለ ይሖዋ እንደወደዳቸው ሁሉ፣ አንተም ሄደህ በሌላ ሰው የተወደደችውንና ምንዝር የምትፈጽመውን ሴት ዳግመኛ ውደዳት።” (ሆሴዕ 3:1፤ ምሳሌ 16:2) በወቅቱ የሆሴዕ ሚስት ከባድ ኃጢአት መፈጸሟን እንዳላቆመች ልብ በል። ያም ቢሆን፣ ሆሴዕ ቅድሚያውን ወስዶ ይቅር እንዲላትና እንዲታረቃት ይሖዋ ነግሮታል። በተመሳሳይም ይሖዋ ልበ ደንዳና በሆኑት ሕዝቦቹ ላይ ተስፋ አልቆረጠባቸውም። በከባድ ኃጢአት ተጠላልፈው የነበረ ቢሆንም እንኳ ይወዳቸው ነበር፤ እንዲሁም ንስሐ እንዲገቡና አካሄዳቸውን እንዲያስተካክሉ ለመርዳት መሞከሩን ቀጥሏል። ይህ ምሳሌ፣ አንድ ሰው ከባድ ኃጢአት መፈጸሙን ባያቆምም እንኳ ‘ልብን የሚመረምረው’ ይሖዋ ቅድሚያውን ወስዶ ይህን ሰው ወደ ንስሐ ለመምራት እንደሚሞክር ያሳያል። w24.08 10 አን. 7

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 6

ሕጉ ወደፊት ለሚመጡት መልካም ነገሮች ጥላ ነው።—ዕብ. 10:1

ከአይሁድ እምነት የመጡ የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ትልቅ ፈተና ነበረባቸው። በአንድ ወቅት አይሁዳውያን ይሖዋ የመረጣቸው ሕዝቦች ነበሩ። ኢየሩሳሌም የአምላክን መንግሥት የሚወክሉት ነገሥታት መቀመጫ ነበረች፤ ቤተ መቅደሱ ደግሞ የንጹሕ አምልኮ ማዕከል ነበር። ሁሉም ታማኝ አይሁዳውያን የሙሴን ሕግ እንዲሁም የሃይማኖት መሪዎቻቸው በዚህ ሕግ ላይ ተመሥርተው ያወጧቸውን ደንቦች ይከተሉ ነበር። እነዚህ ደንቦች አመጋገብን፣ የግርዘትን ጉዳይ አልፎ ተርፎም ከአሕዛብ ጋር ሊኖራቸው የሚገባውን ግንኙነት የሚነኩ ነበሩ። ይሁንና ኢየሱስ ከሞተ በኋላ ይሖዋ በአይሁድ ሥርዓት መሠረት የሚቀርቡትን መሥዋዕቶች መቀበሉን አቆመ። ይህም ሕጉን ሲከተሉ ለኖሩት አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ትልቅ ፈተና ነው። (ዕብ. 10:1, 4, 10) እንደ ሐዋርያው ጴጥሮስ ያሉ የጎለመሱ ክርስቲያኖች እንኳ ከእነዚህ ለውጦች አንዳንዶቹን መቀበል ከብዷቸው ነበር። (ሥራ 10:9-14፤ ገላ. 2:11-14) እነዚህ ክርስቲያኖች በአዲሱ እምነታቸው የተነሳ የአይሁድ የሃይማኖት መሪዎች የስደት ዒላማ ሆኑ። w24.09 9 አን. 4

ረቡዕ፣ ጥቅምት 7

የአምላክን ቃል የነገሯችሁን በመካከላችሁ ሆነው አመራር የሚሰጡትን አስቡ።—ዕብ. 13:7

ይሖዋ ለሕዝቦቹ ሥራ ሲሰጣቸው ሥራውን በተደራጀ መልኩ እንዲያከናውኑት ይጠብቅባቸዋል። (1 ቆሮ. 14:33) ለምሳሌ አምላክ ምሥራቹ በመላው ምድር እንዲሰበክ ይፈልጋል። (ማቴ. 24:14) ይሖዋ ይህን ሥራ እንዲመራ ኢየሱስን ሾሞታል። ኢየሱስም ሥራው በተደራጀ መልኩ እንዲከናወን አድርጓል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ጉባኤዎች በተለያዩ ቦታዎች ሲቋቋሙ አመራር የሚሰጡ ሽማግሌዎች ተሹመው ነበር። (ሥራ 14:23) በኢየሩሳሌም ደግሞ ሐዋርያትንና ሽማግሌዎችን ያቀፈ ማዕከላዊ የሽማግሌዎች አካል ነበር፤ እነዚህ ወንድሞች የሚያደርጉትን ውሳኔ ሁሉም ጉባኤዎች መታዘዝ ነበረባቸው። (ሥራ 15:2፤ 16:4) ጉባኤዎቹ የተሰጣቸውን መመሪያ በመታዘዛቸው “በእምነት እየጠነከሩና ከዕለት ወደ ዕለት በቁጥር እየጨመሩ ሄዱ።”—ሥራ 16:5፤ w24.04 8 አን. 1

ሐሙስ፣ ጥቅምት 8

መግደላዊቷ ማርያም መጥታ “ጌታን አየሁት!” ብላ ለደቀ መዛሙርቱ አበሰረቻቸው።—ዮሐ. 20:18

ኒሳን 16 ማለዳ ላይ የተወሰኑ ታማኝ ሴቶች ኢየሱስ ወደተቀበረበት ቦታ ሄዱ። (ሉቃስ 24:1, 10) ከእነሱ መካከል አንዷ መግደላዊቷ ማርያም ነች። ማርያም ወደ መቃብሩ ስትደርስ መቃብሩ ባዶ ነበር። ይህን ለጴጥሮስና ለዮሐንስ ለመናገር እየሮጠች ሄደች። ከዚያም እነሱን ተከትላ ወደ መቃብሩ ተመለሰች። ጴጥሮስና ዮሐንስ መቃብሩ ባዶ መሆኑን ካረጋገጡ በኋላ ወደ ቤታቸው ተመለሱ። ማርያም ግን አልተመለሰችም። እያለቀሰች እዚያው ቆየች። ኢየሱስ እያያት እንደሆነ አላወቀችም ነበር። ኢየሱስ የዚህችን ታማኝ ሴት እንባ ሲመለከት በጣም አዘነላት። በመሆኑም ለማርያም ተገለጠላት። ቀጥሎ ያደረገው ነገር ማርያምን በእጅጉ አበረታቷታል። አነጋገራት፤ እንዲሁም ወሳኝ ኃላፊነት ሰጣት። መነሳቱን ለወንድሞቹ እንድታበስር ነገራት።—ዮሐ. 20:17, 18፤ w24.10 13 አን. 7

ዓርብ፣ ጥቅምት 9

በግብፅ [ምድር] ምልክቶቼንና ተአምራቴን አበዛለሁ።—ዘፀ. 7:3

ሙሴ ነቢይ፣ ፈራጅ፣ የጦር አዛዥና ታሪክ ጸሐፊ ሆኖ አገልግሏል። የእስራኤል ብሔርን እየመራ ከግብፅ ባርነት ነፃ አውጥቷል፤ እንዲሁም ይሖዋ የፈጸማቸውን በርካታ ተአምራት በዓይኑ ተመልክቷል። የመጀመሪያዎቹን የመጽሐፍ ቅዱስ አምስት መጻሕፍት፣ መዝሙር 90ን ምናልባት ደግሞ መዝሙር 91ንም ጭምር እንዲጽፍ ይሖዋ ተጠቅሞበታል። የኢዮብ መጽሐፍንም የጻፈው እሱ ሳይሆን አይቀርም። ሙሴ ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ የ120 ዓመት አረጋዊ ሳለ መላውን የእስራኤል ማኅበረሰብ በመሰብሰብ ያዩአቸውንና ያሳለፏቸውን አንዳንድ ነገሮች አስታወሳቸው። ይሖዋ የፈጸማቸውን በርካታ ተአምራት እንዲሁም በግብፅ ላይ ያስተላለፈውን ፍርድ ተመልክተዋል። (ዘፀ. 7:4) ቀይ ባሕር ሲከፈል በመካከሉ ተራምደው አልፈዋል፤ የፈርዖን ሠራዊት ሲጠፋም አይተዋል። (ዘፀ. 14:29-31) በምድረ በዳ የይሖዋን ጥበቃና እንክብካቤ አጣጥመዋል። (ዘዳ. 8:3, 4) አሁን ብሔሩ ወደ ተስፋይቱ ምድር ሊገባ ተቃርቧል። ሙሴ ይህን የመጨረሻ አጋጣሚ ተጠቅሞ ሕዝቡን አበረታታ። w24.11 8-9 አን. 3-4

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 10

ከዚህ ምግብ የሚበላ ሁሉ ለዘላለም ይኖራል፤ ምግቡ ደግሞ ለዓለም ሕይወት ስል የምሰጠው ሥጋዬ ነው።—ዮሐ. 6:51

በገሊላ ከነበረው ሁኔታ በተለየ መልኩ ኢየሱስ በጌታ ራት ላይ ለሐዋርያቱ የተናገረው ሐሳብ የሚመለከተው ጥቂት ሰዎችን ብቻ ነው። በገሊላ የተናገረው ሐሳብ ግን ብዙ ሰዎችን ይመለከታል። ኢየሱስ በ32 ዓ.ም. በገሊላ ያነጋገራቸው አብዛኞቹ ሰዎች በዋነኝነት የፈለጉት ምግብ ማግኘት ነበር። ይሁንና ምግብ ከመብላት የበለጠ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ይኸውም የዘላለም ሕይወት የሚያስገኝ ዝግጅት እንዳለ ነገራቸው። በተጨማሪም ኢየሱስ የሞቱ ሰዎች በመጨረሻው ቀን እንደሚነሱና ለዘላለም እንደሚኖሩ ተናግሯል። በጌታ ራት ላይ ካደረገው በተለየ መልኩ ኢየሱስ በዚህ ወቅት የተናገረው ስለተመረጡ ጥቂት ሰዎች ብቻ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ያተኮረው ሁሉም ሰዎች ማግኘት በሚችሉት በረከት ላይ ነው። w24.12 11 አን. 10-11

እሁድ፣ ጥቅምት 11

ባሎች ሆይ፣ ሚስቶቻችሁን መውደዳችሁን ቀጥሉ።—ቆላ. 3:19

ይሖዋ ዓመፀኞችን ይጠላል። (መዝ. 11:5) በሚስታቸው ላይ ጥቃት የሚሰነዝሩ ባሎችን በቀጥታ አውግዟል። (ሚል. 2:16) ባል ሚስቱን በአክብሮት የማይዝ ከሆነ ከይሖዋ ጋር ያለው ዝምድና ይበላሻል። ይሖዋ ጸሎቱን እንኳ ላይሰማው ይችላል። (1 ጴጥ. 3:7) አንዳንድ ባሎች ሚስታቸውን በቁጣና ስሜትን በሚጎዳ ቃል ይናገራሉ። ይሁንና ይሖዋ ‘ቁጣን፣ ንዴትን፣ ጩኸትንና ስድብን’ ይጠላል። (ኤፌ. 4:31, 32) ሚስቱን በአጉል ቃላት የሚያነጋግር ባል አደጋ ላይ የሚጥለው ትዳሩን ብቻ ሳይሆን ከአምላክ ጋር ያለውን ወዳጅነትም ጭምር ነው። (ያዕ. 1:26) ፖርኖግራፊ ከሚመለከት ባል ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። እሱም ከይሖዋ ጋር ያለውን ወዳጅነት ያበላሻል። በተጨማሪም ሚስቱን ያዋርዳል። ይሖዋ፣ ባሎች ለሚስቶቻቸው በተግባር ብቻ ሳይሆን በአስተሳሰብም ጭምር ታማኝ እንዲሆኑ ይጠብቅባቸዋል። ኢየሱስ እንደተናገረው፣ አንዲትን ሴት በፍትወት ስሜት የሚመለከት ሰው “በልቡ” ከእሷ ጋር አመንዝሯል።—ማቴ. 5:28, 29፤ w25.01 9 አን. 6-8

ሰኞ፣ ጥቅምት 12

አንድ ሰው የሚጸድቀው . . . በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ብቻ [ነው]።—ገላ. 2:16

ጻድቅ ተደርገን ተቆጥረናል ሲባል ክሳችን ተሰርዞልናል፤ እንዲሁም የኃጢአት መዝገባችን ተደምስሷል ማለት ነው። ይሖዋ ይህን የሚያደርገው የራሱን የፍትሕ መሥፈርት ጥሶ አይደለም። ይሖዋ ጻድቅ አድርጎ የሚቆጥረን በራሳችን ጥረት አይደለም፤ ወይም ደግሞ ኃጢአታችንን በቸልታ ያልፋል ማለት አይደለም። ሆኖም በስርየት ዝግጅቱ እንዲሁም በተከፈለልን የቤዛ ዋጋ ላይ እምነት ስላለን ይሖዋ ዕዳችንን የሚሰርዝበት መሠረት አለው። (ሮም 3:24) ይህ ለእያንዳንዳችን ምን ትርጉም አለው? በሰማይ ላይ ከኢየሱስ ጋር እንዲገዙ የተመረጡት ሰዎች የአምላክ ልጆች በመሆን ጻድቃን ተደርገው ተቆጥረዋል። (ቲቶ 3:7፤ 1 ዮሐ. 3:1) ኃጢአታቸው ይቅር ተብሎላቸዋል። በሌላ አባባል፣ የወንጀል መዝገባቸው ተሰርዞላቸዋል ሊባል ይችላል። በመሆኑም ወደ መንግሥቱ ለመግባት ብቁ ናቸው። (ሮም 8:1, 2, 30) ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ሰዎች ደግሞ የአምላክ ወዳጆች በመሆን ጻድቃን ተደርገው ተቆጥረዋል፤ ኃጢአታቸውም ይቅር ተብሎላቸዋል።—ያዕ. 2:21-23፤ w25.02 5 አን. 17-18

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 13

የሰውን እንጂ የአምላክን ሐሳብ [አታስብም]።—ማቴ. 16:23

ሐዋርያው ጴጥሮስ የይሖዋን አስተሳሰብ ማንጸባረቅ ተስኖት የነበረበትን አንድ አጋጣሚ እንመልከት። ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም መሄድ እንዳለበት በዚያም ለሃይማኖት መሪዎች አልፎ እንደሚሰጥ፣ መከራ እንደሚደርስበትና በመጨረሻም እንደሚገደል ለሐዋርያቱ እየነገራቸው ነው። (ማቴ. 16:21) ጴጥሮስ ይህን ሲሰማ ከበደው፤ ይሖዋ፣ ተስፋ የተሰጠበትና እስራኤልን የሚያድነው መሲሕ እንዲገደል ይፈቅዳል ብሎ መቀበል ቸገረው። (ማቴ. 16:16) ስለዚህ ኢየሱስን ለብቻው በመውሰድ “ጌታ ሆይ፣ በራስህ ላይ እንዲህ አትጨክን፤ በምንም ዓይነት እንዲህ ያለ ነገር አይደርስብህም” አለው። (ማቴ. 16:22) ጴጥሮስ በዚህ ወቅት የይሖዋን አስተሳሰብ ማንጸባረቅ ስለተሳነው ከኢየሱስ ጋር በሐሳብ መስማማት አልቻለም። የጴጥሮስ ምክር ከቅንነት የመነጨ ቢሆንም ኢየሱስ አልተቀበለውም። ምክንያቱም ይሖዋ ለኢየሱስ ያሰበው ሕይወት መሥዋዕትነት የሚያስከፍል ነው። ይህ አጋጣሚ ጴጥሮስ አስተሳሰቡን በአምላክ አስተሳሰብ መቃኘት እንዳለበት ትልቅ ቁም ነገር አስተምሮታል። ይህ እኛም ልንማረው የሚገባ ቁም ነገር ነው። w25.03 9 አን. 5-6

ረቡዕ፣ ጥቅምት 14

ይሖዋ ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፤ መንፈሳቸው የተደቆሰባቸውንም ያድናል።—መዝ. 34:18

አንድ ሰው እንደጠበቅከው ሆኖ ስላልተገኘ ወይም የምታምነው ሰው ስለከዳህ ስሜትህ ተጎድቷል? ሰዎች ምንም ቢያደርጉ የሰማዩ አባትህ ይወድሃል። ክህደት ሲፈጸምብን ዳዊት በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ የተናገራቸውን የሚያበረታቱ ቃላት ማስታወሳችን ሊያጽናናን ይችላል። አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ እንደሚገልጸው “መንፈሳቸው የተደቆሰባቸው” የሚለው አገላለጽ “የወደፊቱ ጊዜ የጨለመባቸው” የሚል መልእክት ሊያስተላልፍ ይችላል። ይሖዋ እንዲህ ዓይነት ስሜት የሚሰማቸውን ሰዎች የሚረዳቸው እንዴት ነው? በጭንቀት የተዋጠ ልጁን አቅፎ እንደሚያባብል ወላጅ፣ ይሖዋም ለእኛ “ቅርብ ነው።” እጅግ ይራራልናል፤ እንዲሁም በተፈጸመብን ክህደት የተነሳ መንፈሳችን ሲደቆስ ሊረዳን ምንጊዜም ዝግጁ ነው። የተሰበረውን ልባችንንና የተደቆሰውን መንፈሳችንን ለመጠገን ይጓጓል። በተጨማሪም ስለ ወደፊቱ ጊዜ ግሩም ተስፋዎችን ሰጥቶናል፤ እነዚህ ተስፋዎች በአሁኑ ጊዜ የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች ለመቋቋም ይረዱናል።—ኢሳ. 65:17፤ w24.12 23 አን. 13-14

ሐሙስ፣ ጥቅምት 15

ከይሖዋ ዘንድ . . . ሽልማት [ትቀበላላችሁ]።—ቆላ. 3:24

በዛሬው ጊዜ ያሉ ሽማግሌዎች ይሖዋ የሚያከናውኑትን ሥራ እንደሚያስተውልና እንደሚያደንቅ እርግጠኛ መሆን ይችላሉ። እረኝነት ከማድረግ፣ ከማስተማርና ከመስበክ በተጨማሪ በርካታ ሽማግሌዎች በግንባታ ፕሮጀክቶችና በአደጋ ጊዜ እርዳታ ሥራ ይካፈላሉ። ሌሎች ደግሞ በሕሙማን ጠያቂ ቡድኖች ወይም በሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴዎች ውስጥ ያገለግላሉ። እንዲህ ላሉት ሥራዎች ራሳቸውን የሚያቀርቡ ሽማግሌዎች ጉባኤው የይሖዋ ዝግጅት እንደሆነ ይገነዘባሉ። ሥራቸውን በሙሉ ልባቸው ያከናውናሉ፤ አምላክ ላከናወኑት ሥራ ወሮታቸውን እንደሚከፍላቸውም ሙሉ በሙሉ ይተማመናሉ። (ቆላ. 3:23, 24) እርግጥ ሽማግሌ ሆኖ ማገልገል የሚችለው ሁሉም ሰው አይደለም። ሆኖም ሁላችንም ለይሖዋ መስጠት የምንችለው ነገር አለን። አምላካችን እሱን ለማገልገል አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ስናደርግ ይደሰታል። መጠኑ አነስተኛ ቢሆንም እንኳ ለዓለም አቀፉ ሥራ የምናደርገውን መዋጮ ይመለከታል። የደረሰብንን በደል ትተን ስናልፍና ይቅር ስንልም ልቡ ሐሴት ያደርጋል። ይሖዋ የምታከናውነውን ሥራ ከፍ አድርጎ እንደሚመለከት እርግጠኛ ሁን። እሱን ለማገልገል ጥረት በማድረግህ ይወድሃል፤ ወሮታህንም ይከፍልሃል።—ሉቃስ 21:1-4፤ w24.06 23-24 አን. 12-13

ዓርብ፣ ጥቅምት 16

ልባችሁን ወደ መንገዷ አታዘንብሉ። መንገድ ስታችሁ ወደ ጎዳናዋ አትግቡ።—ምሳሌ 7:25

ሰለሞን የጻፈው ዘገባ ማንኛውም የይሖዋ አገልጋይ ምን ሊያጋጥመው እንደሚችል ያሳያል። ከባድ ኃጢአት ከፈጸመ በኋላ ሁሉም ነገር “በድንገት” እንደተከሰተ ሊሰማው ይችላል። ወይም ደግሞ “ሳላስበው ነው የሆነው” ይል ይሆናል። ያም ቢሆን፣ ቆም ብሎ ካሰበበት ኃጢአት ወደመፈጸም የመራው ጥበብ የጎደላቸውን አንዳንድ እርምጃዎች መውሰዱ እንደሆነ መገንዘቡ አይቀርም። ምናልባትም ከመጥፎ ጓደኞች ጋር ገጥሞ፣ ጤናማ ባልሆነ መዝናኛ መካፈል ጀምሮ ወይም በአካልም ሆነ በኢንተርኔት አማካኝነት አጠያያቂ የሆኑ ቦታዎችን ማዘውተር ጀምሮ ሊሆን ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ መጸለዩን፣ መጽሐፍ ቅዱስ ማንበቡን፣ በስብሰባዎች ላይ መገኘቱን ወይም በአገልግሎት መካፈሉን አቁሞ ሊሆን ይችላል። በምሳሌ መጽሐፍ ላይ እንደተጠቀሰው ወጣት ሁሉ እሱም ኃጢአት የፈጸመው በድንገት ላይሆን ይችላል። ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? ከኃጢአት ብቻ ሳይሆን ወደ ኃጢአት ከሚመሩት እርምጃዎችም መራቅ ይኖርብናል። ሰለሞን ታሪኩን ከተናገረ በኋላ ይህን ነጥብ ግልጽ አድርጓል።—ማቴ. 5:29, 30፤ w24.07 16 አን. 10-11

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 17

ይህ ውድ ሀብት በሸክላ ዕቃ ውስጥ አለን።—2 ቆሮ. 4:7

ውድ ሀብት የተባለው ምንድን ነው? ሕይወት አድን የሆነው የመንግሥቱን መልእክት የመስበኩ ሥራ ነው። (2 ቆሮ. 4:1) የሸክላ ዕቃ የተባሉትስ እነማን ናቸው? ምሥራቹን ለሰዎች የሚያደርሱት የአምላክ አገልጋዮች ናቸው። በጳውሎስ ዘመን ነጋዴዎች እንደ ምግብ፣ የወይን ጠጅ እና ገንዘብ የመሰሉ ውድ ነገሮችን ለማጓጓዝ የሸክላ ዕቃዎችን ይጠቀሙ ነበር። ይሖዋም በተመሳሳይ ውድ የሆነውን ምሥራች በአደራ ሰጥቶናል። በይሖዋ እርዳታ ይህን ምሥራች ለሰዎች የማዳረሱን ሥራ በታማኝነት ለማከናወን ብርታት ይኖረናል። አንዳንድ ጊዜ ሰዎችን ወይም ተቃውሞን እንፈራ ይሆናል። ይህን ፈተና መቋቋም የምንችለው እንዴት ነው? ሐዋርያቱ መስበክ እንዲያቆሙ በታዘዙ ጊዜ ያቀረቡትን ጸሎት አስታውስ። በፍርሃት ከመሸነፍ ይልቅ ‘በድፍረት መናገራቸውን እንዲቀጥሉ’ ይሖዋ እንዲረዳቸው ጠይቀዋል። ይሖዋም ለጸሎታቸው አፋጣኝ ምላሽ ሰጥቷቸዋል። (ሥራ 4:18, 29, 31) አልፎ አልፎ ሰዎችን የምትፈራ ከሆነ ለሰዎች ያለህ ፍቅር ከፍርሃትህ በላይ እንዲያይል እንዲረዳህ ይሖዋን ጠይቀው። w24.04 16 አን. 8-9

እሁድ፣ ጥቅምት 18

በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ።—ማቴ. 6:9

ለይሖዋ ያለን ፍቅር ስሙን ለማስቀደስ ያነሳሳናል። ስሙ በሰይጣን መርዘኛ ውሸቶች የተነሳ ከተሰነዘረበት ነቀፋ ነፃ እንዲሆን በማድረግ ረገድ የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማበርከት እንፈልጋለን። (ዘፍ. 3:1-5፤ ኢዮብ 2:4፤ ዮሐ. 8:44) በአገልግሎታችን ሰሚ ጆሮ ላላቸው ሁሉ ስለ አምላካችን እውነቱን በመናገር ለእሱ ጥብቅና ለመቆም እንጓጓለን። አምላክ ዋነኛ ባሕርይው ፍቅር እንደሆነ፣ አገዛዙ ጽድቅና ፍትሕ የሚንጸባረቅበት እንደሆነ እንዲሁም መንግሥቱ በቅርቡ መከራን ሁሉ አስወግዶ ለመላው የሰው ዘር ሰላምና ደስታ እንደሚያሰፍን ሁሉም ሰው እንዲያውቅ እንፈልጋለን። (መዝ. 37:10, 11, 29፤ 1 ዮሐ. 4:8) በአገልግሎታችን ለይሖዋ ጥብቅና በመቆም ስሙን እናስቀድሰዋለን። ከዚህም ሌላ፣ እንደ ስማችን እየኖርን መሆኑን ማወቃችን ያስደስተናል። w24.05 18 አን. 12

ሰኞ፣ ጥቅምት 19

ግብዣ በምታደርግበት ጊዜ ድሆችን፣ ሽባዎችን፣ አንካሶችንና ዓይነ ስውራንን ጥራ፤ ብድር ሊመልሱልህ ስለማይችሉ ደስተኛ ትሆናለህ። ምክንያቱም በጻድቃን ትንሣኤ ብድራት ይመለስልሃል።—ሉቃስ 14:13, 14

ለቅርብ ጓደኞችህ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም መልካም ነገር የምታደርግ ከሆነ “እንግዳ ተቀባይ” መሆንህን ታሳያለህ። (1 ጴጥ. 4:9) አንድ ማመሣከሪያ እንግዳ ተቀባይ ስለሆነ ሰው ሲናገር “የቤቱም ሆነ የልቡ በር ለእንግዶች ክፍት መሆን አለበት” ይላል። ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘እንግዶችን በመቀበል ረገድ ምን ዓይነት ስም አትርፌያለሁ?’ (ዕብ. 13:2, 16) እንግዳ ተቀባይ የሆነ ሰው ያለውን ነገር ለሁሉም ዓይነት እንግዶች ያካፍላል፤ ይህም የተቸገሩ ሰዎችን እንዲሁም እንደ ወረዳ የበላይ ተመልካቾችና የሕዝብ ተናጋሪዎች ያሉ ታታሪ የአምላክ አገልጋዮችን ያካትታል።—ዘፍ. 18:2-8፤ ምሳሌ 3:27፤ ሥራ 16:15፤ ሮም 12:13፤ w24.11 21 አን. 6

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 20

ተዘጋጅተው የነበሩት ደናግል . . . ወደ ሠርጉ ድግስ ገቡ።—ማቴ. 25:10

ኢየሱስ በደናግሉ ምሳሌ ላይ አንድን ሙሽራ ሊቀበሉ ስለወጡ አሥር ደናግል ተናግሯል። (ማቴ. 25:1-4) ሁሉም ሙሽራውን አጅበው ወደ ሠርጉ ድግስ ለመግባት እየተጠባበቁ ነበር። ኢየሱስ አምስቱ “ልባሞች፣” አምስቱ ደግሞ “ሞኞች” እንደሆኑ ተናግሯል። ልባሞቹ ደናግል ሙሽራው ምንም ያህል ቢዘገይ እሱን ለመጠበቅ ተዘጋጅተው ነበር። በጨለማ እንዲያበራላቸው መብራት ይዘዋል። ሙሽራው ከታሰበው በላይ ቢዘገይ ሊጠቀሙበት የሚችሉት ትርፍ ዘይት እንኳ ይዘዋል። ስለዚህ መብራቶቻቸውን እንደበሩ ለማቆየት ተዘጋጅተው ነበር። (ማቴ. 25:6-10) ሙሽራው ሲመጣ ልባሞቹ ደናግል ከእሱ ጋር አብረው ወደ ድግሱ ገቡ። በተመሳሳይም፣ ክርስቶስ እስኪመጣ ድረስ ንቁና ታማኝ በመሆን ዝግጁ መሆናቸውን ያስመሠከሩ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከሙሽራው ኢየሱስ ጋር ወደ ሰማያዊ መንግሥቱ ለመግባት ብቁ እንደሆኑ ይፈረድላቸዋል።—ራእይ 7:1-3፤ w24.09 21 አን. 6

ረቡዕ፣ ጥቅምት 21

ከሁሉም ብሔራት . . . የተውጣጡ . . . እጅግ ብዙ ሕዝብ [አየሁ]።—ራእይ 7:9

ዛሬ በስብከቱ ሥራ በዓለም ዙሪያ ማከናወን የተቻለውን ነገር ስንመለከት በቅንዓት መስበካችንን ለመቀጠል እንነሳሳለን። በየዓመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች በመታሰቢያው በዓል ላይ ይገኛሉ እንዲሁም ከእኛ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ያጠናሉ። መቶ ሺዎች ደግሞ ተጠምቀው በስብከቱ ሥራ ከጎናችን ይሰለፋሉ። ለስብከቱ ሥራችን አዎንታዊ ምላሽ የሚሰጡ ምን ያህል ሰዎች እንደቀሩ አናውቅም። ሆኖም ይሖዋ መጪውን ታላቅ መከራ በሕይወት የሚሻገር እጅግ ብዙ ሕዝብ እየሰበሰበ እንደሆነ እናውቃለን። (ራእይ 7:9, 14) የመከሩ ጌታ አሁንም መሰብሰብ ያለበት አዝመራ እንዳለ ይታየዋል፤ በመሆኑም መስበካችንን የምንቀጥልበት አጥጋቢ ምክንያት አለን። (ሉቃስ 10:2) የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ከጥንትም ጀምሮ በቅንዓት በሚያከናውኑት የስብከት ሥራ ተለይተው ይታወቃሉ። ሐዋርያቱ በድፍረት ሲሰብኩ የተመለከቱ ሰዎች “ከኢየሱስ ጋር እንደነበሩ” ተገንዝበዋል። (ሥራ 4:13) ዛሬም አገልግሎታችንን ስናከናውን የሚመለከቱ ሰዎች የኢየሱስ ቅንዓት ወደ እኛም እንደተጋባ ይመሠክሩ ዘንድ ምኞታችን ነው። w25.03 18 አን. 15፤ 19 አን. 17-18

ሐሙስ፣ ጥቅምት 22

ይሖዋ ሆይ፣ ታስተውለው ዘንድ ሰው ምንድን ነው?—መዝ. 144:3

መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ ይሖዋ ሌሎች ትኩረት ለማይሰጧቸው ሰዎች ትኩረት እንደሚሰጥ እንማራለን። ለምሳሌ ይሖዋ ከእሴይ ልጆች መካከል አንዱን የእስራኤል ንጉሥ አድርጎ እንዲቀባ ነቢዩ ሳሙኤልን ልኮት ነበር። እሴይ ከስምንት ልጆቹ መካከል ሰባቱን ወደ ሳሙኤል አመጣቸው። ይሁንና የመጨረሻውን ልጁን ዳዊትን አላመጣውም። ያም ቢሆን ይሖዋ የመረጠው ዳዊትን ነበር። (1 ሳሙ. 16:6, 7, 10-12) ይሖዋ የዳዊትን ውስጣዊ ማንነት ተመልክቷል፤ ዳዊት ለመንፈሳዊ ነገሮች አድናቆት ያለው ወጣት ነበር። ይሖዋ ትኩረት እንደሚሰጥህ ያሳየባቸውን መንገዶች ለማሰብ ሞክር። ለአንተ ሁኔታ የሚስማማ ምክር እንደሚሰጥህ ቃል ገብቷል። (መዝ. 32:8) አንተን በደንብ የማያውቅህ ከሆነ እንዴት ይህን ሊያደርግ ይችላል? (መዝ. 139:1) የሚሰጥህን ምክር በሥራ ላይ ማዋልህ ምን ጥቅም እንዳስገኘልህ ስትመለከት ይሖዋ ትኩረት እንደሚሰጥህ እርግጠኛ ትሆናለህ። (1 ዜና 28:9፤ ሥራ 17:26, 27) ይሖዋ ጥረትህን ያስተውላል። መልካም ባሕርያትህን ይመለከታል፤ ሊረዳህም ይፈልጋል።—ኤር. 17:10፤ w24.10 25-26 አን. 7-9

ዓርብ፣ ጥቅምት 23

እረኛ እንደሌላቸው በጎች ስለነበሩም በጣም አዘነላቸው።—ማር. 6:34

ይሖዋን እንደምትወደውና ሌሎችን ማገልገል እንደምትፈልግ ምንም ጥያቄ የለውም። ታዲያ ሌሎችን ለማገልገል ያለህን ፍላጎት ማሳደግ የምትችለው እንዴት ነው? ወንድሞችህንና እህቶችህን ማገልገል ስለሚያስገኘው ደስታ ለማሰብ ሞክር። ኢየሱስ “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል” ብሏል። (ሥራ 20:35) እሱም ቢሆን በሕይወቱ ይህንኑ አድርጓል። ሌሎችን በማገልገል እውነተኛ ደስታ አግኝቷል። በማርቆስ 6:31-34 ላይ የሚገኝ አንድ ምሳሌ እንመልከት። በዚህ ወቅት ኢየሱስና ሐዋርያቱ ስለደከማቸው አረፍ ለማለት ገለል ወዳለ ስፍራ እየሄዱ ነበር። ሆኖም ብዙ ሰዎች ኢየሱስ እንዲያስተምራቸው ስለፈለጉ ቀድመዋቸው ደረሱ። ኢየሱስ “አላስተምራችሁም” ማለት ይችል ነበር። ደግሞም እሱና ሐዋርያቱ “ምግብ ለመብላት እንኳ ፋታ አላገኙም” ነበር። ወይም ደግሞ ኢየሱስ አንድ ወይም ሁለት ነገር ብቻ ካስተማራቸው በኋላ ሊያሰናብታቸው ይችል ነበር። ሆኖም ፍቅር ስለነበረው ‘ያስተምራቸው ጀመር።’ ‘ሰዓቱ እስኪገፋ’ ድረስ እነሱን ማስተማሩን ቀጥሏል።—ማር. 6:35፤ w24.11 16 አን. 9-10

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 24

የድካማችሁን ዋጋ [ታገኛላችሁ]።—2 ዜና 15:7

ወላጆች፣ ልጆቻችሁ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለሌሎች ለማካፈል የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን እንዲፈልጉ አበረታቷቸው። (ሮም 10:10) ስለ እምነታቸው ለመናገር የሚያደርጉት ጥረት አንድን የሙዚቃ መሣሪያ ለመጫወት ከሚደረገው ጥረት ጋር ሊመሳሰል ይችላል። አንድ ሰው በመጀመሪያ ቀላል የሆኑ ዜማዎችን መጫወት ይለማመዳል። በጊዜ ሂደት ሙዚቃ መጫወት እየቀለለው ይመጣል። በተመሳሳይም ወጣት ክርስቲያኖች መጀመሪያ ላይ ቀላል አቀራረቦችን በመጠቀም ስለ እምነታቸው ለሌሎች መናገር ይችላሉ። ለምሳሌ አብሯቸው የሚማርን አንድ ልጅ እንዲህ ብለው ሊጠይቁት ይችላሉ፦ “ብዙ ጊዜ መሐንዲሶች በተፈጥሮ ላይ የሚታዩ ንድፎችን እንደሚኮርጁ ታውቃለህ? አንድ የሚያስገርም ቪዲዮ ላሳይህ።” ከዚያም ንድፍ አውጪ አለው? በሚለው ክፍል ሥር ካሉት ቪዲዮዎች መካከል አንዱን ካሳዩት በኋላ እንዲህ ሊሉት ይችላሉ፦ “አንድ ሳይንቲስት በተፈጥሮ ላይ ያየውን ንድፍ ኮርጆ ለሠራው ነገር እውቅና የሚሰጠው ከሆነ ለዋናው ንድፍ እውቅና ሊሰጠው የሚገባው ማን ነው?” እንዲህ ያለው ቀላል አቀራረብ ትኩረቱን ሊስበውና ይበልጥ ለማወቅ እንዲነሳሳ ሊያደርገው ይችላል። w24.12 19 አን. 17-18

እሁድ፣ ጥቅምት 25

በአንድ ሰው አማካኝነት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ፤ በኃጢአትም ምክንያት ሞት መጣ።—ሮም 5:12

ይሖዋ እኛን ከኃጢአትና ከሞት ነፃ ለማውጣት ሲል ልጁ ቤዛ እንዲሆንልን አደረገ። ይሁንና የአንድ ፍጹም ሰው ሕይወት መሥዋዕት መሆኑ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ነፃ ሊያወጣ የሚችለው እንዴት ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ በማለት መልሱን ሰጥቶናል፦ “በአንዱ ሰው [በአዳም] አለመታዘዝ ብዙዎች ኃጢአተኞች እንደሆኑ ሁሉ በአንዱ ሰው [በኢየሱስ] መታዘዝም ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉ።” (ሮም 5:19፤ 1 ጢሞ. 2:6) በሌላ አባባል፣ ለኃጢአትና ለሞት ባርነት የዳረገን የአንድ ፍጹም ሰው አለመታዘዝ እንደሆነ ሁሉ ነፃ የምንወጣውም በአንድ ፍጹም ሰው መታዘዝ ምክንያት ነው። ይሖዋ ቀና ልብ ያላቸው የአዳም ዘሮች ለዘላለም እንዲኖሩ እንዲሁ ሊፈቅድላቸው አይችልም ነበር? ፍጹማን ካልሆኑ ሰዎች አመለካከት አንጻር ይህ የተሻለ መፍትሔ መስሎ ሊታይ ይችላል። ሆኖም ይህ አመለካከት የይሖዋን ፍጹም ፍትሕ ከግንዛቤ ያስገባ አይደለም። ይሖዋ ፍትሐዊ አምላክ ስለሆነ የአዳምን ዓይን ያወጣ ዓመፅ በቸልታ ሊያልፈው አይችልም። w25.01 21 አን. 3-4

ሰኞ፣ ጥቅምት 26

የምንመላለሰው በእምነት እንጂ በማየት አይደለም።—2 ቆሮ. 5:7

ሐዋርያው ጳውሎስ ሞት እንደሚጠብቀው ተረድቷል፤ ሕይወቱን መለስ ብሎ ሲያስብ ግን እርካታ ይሰማዋል። “ሩጫውን ጨርሻለሁ፤ እምነትን ጠብቄአለሁ” በማለት ተናግሯል። (2 ጢሞ. 4:6-8) ጳውሎስ ራሱን ለክርስቲያናዊ አገልግሎት ሙሉ በሙሉ በመስጠት ጥበብ የተንጸባረቀበት ውሳኔ አድርጓል፤ ይሖዋ እንደተደሰተበትም እርግጠኛ ነው። እኛም አምላክ የሚደሰትበት ጥሩ ውሳኔ ማድረግ እንፈልጋለን። ታዲያ ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ጳውሎስ ስለ ራሱና ስለ ሌሎች ታማኝ ክርስቲያኖች ሲናገር “የምንመላለሰው በእምነት እንጂ በማየት አይደለም” ብሏል። መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ‘መመላለስ’ የሚለው ቃል አንድ ሰው የሚመርጠውን የሕይወት ጎዳና ሊያመለክት ይችላል። በእምነት የሚመላለስ ሰው ውሳኔውን የሚመራለት በይሖዋ ላይ ያለው እምነት ነው። የሚወስዳቸው እርምጃዎች፣ አምላክ ወሮታ እንደሚከፍለው እንዲሁም በአምላክ ቃል ውስጥ ያሉትን ምክሮች ተግባራዊ ማድረግ እንደሚጠቅመው ያለውን ጠንካራ እምነት ያሳያሉ።—መዝ. 119:66፤ ዕብ. 11:6፤ w25.03 20 አን. 1-2

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 27

አእምሯችሁን በማደስ ተለወጡ።—ሮም 12:2

ቀደም ሲል የአውሬ ዓይነት ባሕርይ የነበራቸው ብዙ ሰዎች በይሖዋ መንፈስ እርዳታ በሕይወታቸው ላይ ከፍተኛ ለውጥ ማድረግ ችለዋል። (ኢሳ. 65:25) የነበሯቸውን መጥፎ ባሕርያት አሸንፈዋል። (ኤፌ. 4:22-24) እርግጥ አሁንም ቢሆን እኛ የአምላክ ሕዝቦች ፍጹማን አይደለንም፤ ስለዚህ ስህተት መሥራታችን አይቀርም። ሆኖም ይሖዋ ‘ሁሉንም ዓይነት ሰዎች’ ሊበጠስ በማይችል የፍቅርና የሰላም ሰንሰለት አስተሳስሯል። (ቲቶ 2:11) ይህ ሁሉን ቻዩ አምላክ ብቻ ሊፈጽመው የሚችል ተአምር ነው! እሱ የገባው ቃል ምንጊዜም ቢሆን ይፈጸማል። (ኢሳ. 55:10, 11) መንፈሳዊው ገነት አሁንም በእውን ያለ ነገር ነው። ይሖዋ በዓይነቱ ልዩ የሆነ የወንድማማች ማኅበር ፈጥሯል። በእሱ ሕዝቦች መካከል በመሆናችን በዚህ በዓመፅ የተሞላ ዓለም ውስጥ አንጻራዊ የሆነ ሰላምና መረጋጋት አግኝተናል። (መዝ. 72:7) በእነዚህ ምክንያቶች የተነሳ፣ በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎች ክርስቲያናዊ የወንድማማች ማኅበራችንን እንዲቀላቀሉ መርዳት እንፈልጋለን። እንዲህ ማድረግ የምንችለው ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ላይ በማተኮር ነው።—ማቴ. 28:19, 20፤ w24.04 23 አን. 13, 15

ረቡዕ፣ ጥቅምት 28

የክርስቶስ አስተሳሰብ አለን።—1 ቆሮ. 2:16

ኢየሱስ ይሖዋን በሙሉ አእምሮው ይወደዋል። አምላክ ለእሱ ያለው ፈቃድ ምን እንደሆነ ያውቅ ነበር፤ ይህን ፈቃዱን መፈጸም መከራ እንደሚያስከትልበት ቢያውቅም በዚያ መንገድ ለመኖር ቆርጧል። ሕይወቱ ሙሉ በሙሉ ያተኮረው የአባቱን ፈቃድ በመፈጸም ላይ ነው፤ ምንም ነገር ትኩረቱን እንዲከፋፍልበት አልፈቀደም። ጴጥሮስና ሌሎቹ ሐዋርያት ከኢየሱስ ጋር ጊዜ የማሳለፍ እንዲሁም ስለሚያስብበት መንገድ ከራሱ የመማር ልዩ አጋጣሚ አግኝተዋል። ጴጥሮስ በመንፈስ መሪነት ከጻፋቸው ደብዳቤዎች በመጀመሪያው ላይ ክርስቲያኖች የክርስቶስ ዓይነት አስተሳሰብ ለማንጸባረቅ ዝግጁ እንዲሆኑ አበረታቷል። (1 ጴጥ. 4:1) እዚህ ጥቅስ ላይ “ዝግጁ ሁኑ” ተብሎ የተተረጎመው አገላለጽ በኩረ ጽሑፉ ላይ ለውጊያ መታጠቅን የሚያመለክት ወታደራዊ አገላለጽ ነው። ስለዚህ የኢየሱስን አስተሳሰብ ማንጸባረቅ፣ ክርስቲያኖች ከኃጢአትና በሰይጣን ከሚመራው ዓለም ጋር በሚያደርጉት ውጊያ ድል የሚያጎናጽፋቸው ሁነኛ ትጥቅ ይሆንላቸዋል።—2 ቆሮ. 10:3-5፤ ኤፌ. 6:12፤ w25.03 8-9 አን. 1-3

ሐሙስ፣ ጥቅምት 29

በሰው ልብ ውስጥ ያለ ሐሳብ እንደ ጥልቅ ውኃ ነው፤ አስተዋይ ሰው ግን ቀድቶ ያወጣዋል።—ምሳሌ 20:5

በምትጠናኑበት ወቅት ስለ ግለሰቡ ምን ማወቅ ይኖርባችኋል? በስሜት በጣም ከመቀራረባችሁ በፊት ግቦቻችሁን ጨምሮ ስለ አንዳንድ አስፈላጊ ጉዳዮች መወያየታችሁ ጠቃሚ ነው። የግለሰቡን ውስጣዊ ማንነት ማወቅ የምትችሉት እንዴት ነው? እንዲህ ማድረግ ከሚቻልባቸው ግሩም መንገዶች አንዱ በግልጽና በሐቀኝነት መነጋገር፣ ጥያቄዎችን መጠየቅ እንዲሁም በጥሞና ማዳመጥ ነው። (ያዕ. 1:19) ለዚህም ሲባል ለማውራት በሚያመቹ እንቅስቃሴዎች መካፈላችሁ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ አብራችሁ መብላት፣ ሰዋራ ባልሆኑ ቦታዎች ላይ በእግር መንሸራሸር ወይም አብራችሁ ማገልገል ትችላላችሁ። ከጓደኞቻችሁና ከቤተሰቦቻችሁ ጋር አብራችሁ ጊዜ ማሳለፋችሁም እርስ በርስ ለመተዋወቅ ሊረዳችሁ ይችላል። ከዚህም ሌላ፣ ግለሰቡ በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ እንዲሁም ከተለያዩ ሰዎች ጋር ሲሆን ምን ዓይነት ምግባር እንደሚያሳይ ለማወቅ በሚያስችሏችሁ እንቅስቃሴዎች ተካፈሉ። w24.05 28 አን. 6-7

ዓርብ፣ ጥቅምት 30

የተወደዳችሁ ልጆቹ በመሆን አምላክን የምትመስሉ ሁኑ።—ኤፌ. 5:1

በቅርቡ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በይሖዋ መታመን የሚጠይቁ ፈተናዎችን መጋፈጣችን አይቀርም። የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችና በዘመናችን ያሉ ወንድሞችና እህቶች ተሞክሮዎች አምላክ አገልጋዮቹን ለመደገፍ እንደ ዓለት ያሉ ባሕርያት ያሳየው እንዴት እንደሆነ ለማስተዋል ይረዱናል። በእነዚህ ታሪኮች ላይ በጥልቀት አሰላስል። ይህም ይሖዋን ዓለትህ ለማድረግ ይረዳሃል።በተጨማሪም ጉባኤውን ለማነጽ ይበልጥ ብቁ ትሆናለህ። ለምሳሌ ኢየሱስ ለስምዖን “ኬፋ” (ወይም “ጴጥሮስ”) የሚል ስም ሰጥቶታል፤ ይህ ስም “ትንሽ ዓለት” የሚል ትርጉም አለው። (ዮሐ. 1:42) ይህም ጴጥሮስ ለጉባኤው የመጽናኛና የብርታት ምንጭ እንደሚሆን የሚጠቁም ነው። የጉባኤ ሽማግሌዎች “እንደ ትልቅ ቋጥኝ ጥላ” ተደርገው ተገልጸዋል። ይህም በጉባኤው ውስጥ ላሉት ከለላ እንደሚሆኑ የሚያሳይ ምሳሌያዊ አገላለጽ ነው። (ኢሳ. 32:2) እርግጥ ነው፣ ሁሉም ወንድሞችና እህቶች ይሖዋን በመምሰል እንደ ዓለት ያሉ ባሕርያትን ማንጸባረቅ ይችላሉ፤ ይህም ጉባኤውን ይጠቅማል። w24.06 28 አን. 10-11

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 31

ይሖዋ . . . እሱ ብቻ እንዲመለክ የሚፈልግ አምላክ ነው።—ዘዳ. 4:24

ይሖዋ ታማኝ አድርጎ የቆጠራቸው የእስራኤል ነገሥታት እውነተኛውን አምልኮ የሙጥኝ ብለዋል። ይሖዋ ታማኝ እንዳልሆኑ አድርጎ ከቆጠራቸው ነገሥታት መካከል አብዛኞቹ የይሖዋን ሕግ ትተው በሐሰት አምልኮ ተካፍለዋል። (1 ነገ. 21:25, 26፤ 2 ዜና 12:1) ይሖዋ ለአምልኮ ጉዳይ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ለምንድን ነው? በመጀመሪያ ደረጃ፣ ነገሥታቱ የአምላክ ሕዝቦች በእውነተኛው አምልኮ እንዲካፈሉ ግንባር ቀደም ሆነው የመርዳት ኃላፊነት ነበረባቸው። ከዚህም ሌላ፣ የሐሰት አምልኮ ወደ ሌሎች ኃጢአቶችና ኢፍትሐዊ ድርጊቶች መምራቱ አይቀርም። (ሆሴዕ 4:1, 2) ይህ ብቻ ሳይሆን ነገሥታቱና ተገዢዎቻቸው ለይሖዋ የተወሰኑ ሰዎች ነበሩ። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህ ሰዎች በሐሰት አምልኮ መካፈላቸውን ከምንዝር ጋር ያመሳስለዋል። (ኤር. 3:8, 9) ቃል በቃል ምንዝር የሚፈጽም ሰው የትዳር አጋሩን በቀጥታ ይበድላል። በተመሳሳይም ለይሖዋ የተወሰነ አንድ ሰው በሐሰት አምልኮ ሲካፈል እሱን በቀጥታ ይበድለዋል።—ዘዳ. 4:23፤ w24.07 22-23 አን. 12-15

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2026)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2026 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ