መስከረም
ማክሰኞ፣ መስከረም 1
በእምነት ውስጥ መሆናችሁን ለማረጋገጥ ዘወትር ራሳችሁን ፈትሹ።—2 ቆሮ. 13:5
ወደ ጉልምስና ለመድረስ ብቻ ሳይሆን ምንጊዜም ጎልማሳ ሆነን ለመኖርም ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ይህም ከልክ በላይ በራስ ከመተማመን መቆጠብን ይጠይቃል። (1 ቆሮ. 10:12) አሁንም እድገት እያደረግን መሆኑን ለማረጋገጥ ‘ዘወትር ራሳችንን መፈተሽ’ ይኖርብናል። ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆላስይስ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ጎልማሳ ሆኖ የመኖርን አስፈላጊነት በድጋሚ ጎላ አድርጎ ገልጿል። እነዚያ ክርስቲያኖች ወደ ጉልምስና ደረጃ የደረሱ ቢሆንም እንኳ ጳውሎስ ዓለማዊ አስተሳሰብ ወጥመድ እንዳይሆንባቸው አስጠንቅቋቸዋል። (ቆላ. 2:6-10) በተጨማሪም ያንን ጉባኤ በደንብ የሚያውቀው ኤጳፍራ፣ እነዚያ ክርስቲያኖች “ፍጹም” ወይም ጎልማሳ ሆነው ‘እስከ መጨረሻው እንዲቆሙ’ ዘወትር ይጸልይ ነበር። (ቆላ. 4:12) ነጥቡ ምንድን ነው? ጳውሎስም ሆነ ኤጳፍራ ጎልማሳ ሆኖ ለመቀጠል፣ ጥረት ማድረግና የአምላክን ድጋፍ ማግኘት እንደሚያስፈልግ ተገንዝበዋል። የቆላስይስ ክርስቲያኖች የሚያጋጥሟቸውን ተፈታታኝ ሁኔታዎች በሙሉ ተቋቁመው ጎልማሳ ሆነው እንዲቀጥሉ ይፈልጉ ነበር። w24.04 6-7 አን. 16-17
ረቡዕ፣ መስከረም 2
ይሖዋ ከእኛ ጋር ነው። ፈጽሞ አትፍሯቸው።—ዘኁ. 14:9
ለይሖዋ ተገቢውን ፍርሃት ስናዳብር እሱን ከመውደዳችን የተነሳ የሚያሳዝነውን ምንም ነገር ከማድረግ እንቆጠባለን። የይሖዋን ሞገስ ማግኘት ስለምንፈልግ ትክክልና ስህተት እንዲሁም እውነትና ውሸት በሆነው ነገር መካከል ያለውን ልዩነት ለማወቅ እንነሳሳለን። (ምሳሌ 2:3-6፤ ዕብ. 5:14) ከአምላክ ይልቅ ሰዎችን የምንፈራ ከሆነ ከእውነት ልንርቅ እንችላለን። ይሖዋ እስራኤላውያን እንደሚወርሱት ቃል የገባላቸውን ምድር እንዲሰልሉ የተላኩትን 12 የነገድ አለቆች እንደ ምሳሌ እንውሰድ። አሥሩ ሰላዮች ለከነአናውያን ያደረባቸው ፍርሃት ለይሖዋ ካላቸው ፍቅር ይበልጥ ነበር። ለእስራኤላውያን ወገኖቻቸው “ሰዎቹ ከእኛ ይልቅ ብርቱዎች ስለሆኑ ወጥተን ልንዋጋቸው አንችልም” ብለዋቸው ነበር። (ዘኁ. 13:27-31) እርግጥ ከሰብዓዊ እይታ አንጻር ከነአናውያን ይበልጥ ብርቱ መሆናቸው እውነት ነው። ነገር ግን እስራኤላውያን ጠላቶቻቸውን ማሸነፍ አይችሉም የሚለው ሐሳብ ይሖዋን ከግንዛቤ ያስገባ አልነበረም። w24.07 9 አን. 5-6
ሐሙስ፣ መስከረም 3
የምድር ሁሉ ዳኛ ትክክል የሆነውን ነገር አያደርግም?—ዘፍ. 18:25
ይሖዋ ምሕረት ለማሳየትም ሆነ ለማጥፋት የሚያስተላልፈው ማንኛውም ፍርድ ትክክል እንደሆነ ለመተማመን የሚያበቃ ምክንያት አለን? በሚገባ! አብርሃም እንደተገነዘበው ይሖዋ ፍጹም፣ ጥበበኛና መሐሪ የሆነ “የምድር ሁሉ ዳኛ” ነው። ልጁንም አሠልጥኖታል፤ እንዲሁም የመፍረዱን ሥልጣን በሙሉ ለእሱ ሰጥቶታል። (ዮሐ. 5:22) አብም ሆነ ወልድ የእያንዳንዱን ሰው ልብ ማንበብ ይችላሉ። (ማቴ. 9:4) ስለዚህ በእያንዳንዱ ሰው ላይ በሚፈርዱበት ጊዜ “ትክክል የሆነውን ነገር” ያደርጋሉ! ይሖዋ ምንጊዜም ከሁሉ የተሻለውን ነገር እንደሚያደርግ ለመተማመን ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። እኛ የመፍረድ ብቃት እንደሌለን አምነን እንቀበላለን። እሱ ግን ብቃቱ አለው! (ኢሳ. 55:8, 9) ስለዚህ የመፍረዱን ሥራ በሙሉ ለእሱ እንዲሁም የአባቱን ፍትሕና ምሕረት ፍጹም በሆነ መንገድ ላንጸባረቀው ለንጉሣችን ለኢየሱስ እንተዋለን።—ኢሳ. 11:3, 4፤ w24.05 7 አን. 18-19
ዓርብ፣ መስከረም 4
ይሖዋ ተንኮለኛን ሰው [ይጸየፋል]፤ ከቅኖች ጋር ግን የጠበቀ ወዳጅነት አለው።—ምሳሌ 3:32
ኢየሱስ ናትናኤልን ሲያገኘው ከተከሰተው ሁኔታ ሐቀኛ ልብ የመያዝን አስፈላጊነት እንመለከታለን። ፊልጶስ ጓደኛውን ናትናኤልን ወደ ኢየሱስ ባመጣው ጊዜ ትኩረት የሚስብ ነገር ተከስቷል። ኢየሱስ ከዚያ በፊት ናትናኤልን አግኝቶት ባያውቅም “ተንኮል የሌለበት እውነተኛ እስራኤላዊ ይኸውላችሁ!” አለ። (ዮሐ. 1:47) ኢየሱስ በናትናኤል ልብ ውስጥ አስደናቂ የሆነ ሐቀኝነት ተመልክቷል። ናትናኤል ልክ እንደ እኛ ፍጽምና የጎደለው ሰው ነው። ሆኖም ምንም ዓይነት ግብዝነት አልነበረበትም። ኢየሱስ ናትናኤልን ለሐቀኝነቱ አድንቆታል እንዲሁም አመስግኖታል። በመዝሙር 15 ላይ ከተዘረዘሩት ይሖዋን ለማስደሰት የሚያስችሉ መሥፈርቶች መካከል አብዛኞቹ ሌሎችን በምንይዝበት መንገድ ላይ ያተኮሩ ናቸው። መዝሙር 15:3 እንደሚናገረው በይሖዋ ድንኳን ውስጥ በእንግድነት የተጋበዘ ሰው “በአንደበቱ ስም አያጠፋም፤ በባልንጀራው ላይ መጥፎ ነገር አይሠራም፤ የወዳጆቹንም ስም አያጎድፍም።” አንደበታችንን እንደዚህ በመሰሉ መንገዶች ያለአግባብ መጠቀማችን በሌሎች ላይ ከባድ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል።—ያዕ. 1:26፤ w24.06 10 አን. 7፤ 11 አን. 9-10
ቅዳሜ፣ መስከረም 5
ጌታ ሆይ፣ አጋንንት እንኳ በስምህ ተገዙልን።—ሉቃስ 10:17
ለአገልግሎት በደንብ ከተዘጋጀህ ከሌሎች ጋር መነጋገር እየቀለለህ ይሄዳል። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ወደ አገልግሎት ከመላኩ በፊት እንዲዘጋጁ ረድቷቸዋል። (ሉቃስ 10:1-11) እነሱም ኢየሱስ ያስተማራቸውን ተግባራዊ ስላደረጉ በአገልግሎት ባገኙት ስኬት ከፍተኛ ደስታ ተሰምቷቸዋል። ለአገልግሎት መዘጋጀት የምንችለው እንዴት ነው? መልእክቱን በራሳችን አነጋገርና ውጤታማ በሆነ መንገድ ማስረዳት የምንችለው እንዴት እንደሆነ ማሰብ አለብን። በአገልግሎት ክልላችን ውስጥ ሊያጋጥሙን የሚችሉ ሁለት ወይም ሦስት ዓይነት ምላሾችን አስቀድመን ማሰባችንና ምን መልስ እንደምንሰጥ መዘጋጀታችንም ይጠቅመናል። ከዚያም ሰዎችን ዘና ብለን በፈገግታ ማነጋገር እንዲሁም ወዳጃዊ ስሜት ማሳየት እንችላለን። w24.04 16 አን. 6-7
እሁድ፣ መስከረም 6
ይሖዋ አምላካችን፣ ሁሉንም ነገሮች ስለፈጠርክ . . . ግርማ፣ ክብርና ኃይል ልትቀበል ይገባሃል።—ራእይ 4:11
ምሥራቹን ለመስበክ የሚያነሳሳን ዋነኛ ምክንያት ለይሖዋ አምላክና ለቅዱስ ስሙ ያለን ፍቅር ነው። አገልግሎታችንን የምንወደውን አምላክ ለማወደስ እንደሚያስችለን አጋጣሚ አድርገን እንመለከተዋለን። ይሖዋ አምላክ ከታማኝ አገልጋዮቹ ግርማ፣ ክብርና ኃይል ሊቀበል እንደሚገባው በሙሉ ልባችን እንስማማለን። እሱ ‘ሁሉንም ነገሮች እንደፈጠረ’ እንዲሁም በሕይወት ልንኖር የቻልነው በእሱ የተነሳ እንደሆነ የሚያሳየውን አሳማኝ ማስረጃ ለሰዎች በመናገር ግርማና ክብር እንሰጠዋለን። ሁኔታችን በፈቀደልን መጠን ጊዜያችንን፣ ጉልበታችንን እና ገንዘባችንን ተጠቅመን በአገልግሎት የተሟላ ተሳትፎ ስናደርግ ኃይላችንን እንሰጠዋለን። (ማቴ. 6:33፤ ሉቃስ 13:24፤ ቆላ. 3:23) በአጭር አነጋገር፣ ስለምንወደው አምላክ መናገር ያስደስተናል። በተጨማሪም ስለ ስሙ እና ስሙ ስለሚወክለው አካል ለሌሎች ለመናገር እንገፋፋለን። w24.05 17 አን. 11
ሰኞ፣ መስከረም 7
ከልብ ለሚፈልጉት . . . ወሮታ ከፋይ [ነው]።—ዕብ. 11:6
ይሖዋ በአሁኑ ጊዜ ሰላምና እርካታ፣ ወደፊት ደግሞ የዘላለም ሕይወት ይሰጠናል። ይሖዋ ለእኛ ወሮታ ለመክፈል ፍላጎቱም ሆነ ኃይሉ እንዳለው በመተማመን ተስፋችንን በእሱ ላይ መጣል እንችላለን። ይህን ማመናችን በጥንት ዘመን እንደነበሩት ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች አገልግሎታችንን በትጋት ለማከናወን ያነሳሳናል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖረው ጢሞቴዎስ ይህን አድርጓል። (ዕብ. 6:10-12) ጢሞቴዎስ ሕያው በሆነው አምላክ ላይ ተስፋውን ጥሏል። (1 ጢሞ. 4:10) ይህም ይሖዋንና ሌሎችን ለማገልገል ጠንክሮ እንዲሠራና ብርቱ ጥረት እንዲያደርግ አነሳስቶታል። ይህን ያደረገው በየትኞቹ መንገዶች ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ የማስተማርና ንግግር የማቅረብ ችሎታውን እንዲያሳድግ አበረታቶታል። በተጨማሪም ጢሞቴዎስ ወጣቶችንና አረጋውያንን ጨምሮ ለእምነት አጋሮቹ ጥሩ ምሳሌ መሆን ይጠበቅበት ነበር። አንዳንድ ከባድ ኃላፊነቶችም ተሰጥተውታል፤ ለምሳሌ ምክር ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ጠንካራ ሆኖም ፍቅር የሚንጸባረቅበት ምክር መስጠት ነበረበት። (1 ጢሞ. 4:11-16፤ 2 ጢሞ. 4:1-5) ጢሞቴዎስ ይሖዋ ወሮታውን እንደሚከፍለው እርግጠኛ መሆን ይችል ነበር።—ሮም 2:6, 7፤ w24.06 22-23 አን. 10-11
ማክሰኞ፣ መስከረም 8
ይሖዋ በነቢያቱ ሁሉ . . . አማካኝነት እስራኤልንና ይሁዳን . . . በተደጋጋሚ ያስጠነቅቃቸው ነበር።—2 ነገ. 17:13
ይሖዋ ነቢያቱን ተጠቅሞ ሕዝቦቹን ለማስጠንቀቅና ለማረም በተደጋጋሚ ሞክሯል። ለምሳሌ አምላክ በኤርምያስ አማካኝነት እንዲህ ብሏል፦ “ከዳተኛይቱ እስራኤል ሆይ፣ ተመለሽ . . . እኔ ታማኝ ስለሆንኩ እናንተን በቁጣ አልመለከትም . . . ለዘላለም ቅር አልሰኝም። ብቻ የሠራሽውን በደል አምነሽ ተቀበይ፤ በአምላክሽ በይሖዋ ላይ ዓምፀሻልና።” (ኤር. 3:12, 13) በኢዩኤል አማካኝነት ደግሞ ይሖዋ “በሙሉ ልባችሁ ወደ እኔ ተመለሱ” ብሏል። (ኢዩ. 2:12, 13) በተጨማሪም በኢሳይያስ አማካኝነት እንዲህ ብሏል፦ “ታጠቡ፤ ራሳችሁንም አንጹ፤ ክፉ ሥራችሁን ከፊቴ አስወግዱ፤ መጥፎ ድርጊት መፈጸማችሁን አቁሙ።” (ኢሳ. 1:16-19) ከዚህም ሌላ በሕዝቅኤል አማካኝነት እንዲህ ሲል ጠይቋል፦ “እኔ በክፉ ሰው ሞት ደስ እሰኛለሁ? . . . እኔ ደስ የምሰኘው ከመንገዱ ቢመለስና በሕይወት ቢኖር አይደለም? እኔ በማንም ሰው ሞት ደስ አልሰኝም . . . ስለዚህ ተመለሱና በሕይወት ኑሩ።” (ሕዝ. 18:23, 32) ይሖዋ ሰዎች ንስሐ ሲገቡ ሲያይ ይደሰታል። ምክንያቱም በሕይወት መኖራቸውን እንዲቀጥሉ፣ አልፎ ተርፎም ለዘላለም እንዲኖሩ ይፈልጋል! w24.08 9 አን. 5-6
ረቡዕ፣ መስከረም 9
ቅዱሳን መጻሕፍት ሁሉ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፉ ናቸው፤ እንዲሁም . . . ይጠቅማሉ።—2 ጢሞ. 3:16
ሁሉም የይሖዋ ሕዝቦች የሚያስፈልጋቸውን መንፈሳዊ ምግብ፣ መመሪያና ጥበቃ ያገኛሉ። ይሖዋ እንደማያዳላ የሚያሳየው አንዱ ምሳሌ በዓለም ዙሪያ ያሉ ሰዎች በሙሉ መጽሐፍ ቅዱስን ማግኘት እንዲችሉ ማድረጉ ነው። ቅዱሳን መጻሕፍት በመጀመሪያ የተጻፉት በሦስት ቋንቋዎች ማለትም በዕብራይስጥ፣ በአረማይክና በግሪክኛ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ የተጻፈባቸውን ቋንቋዎች ማንበብ የሚችሉ ሰዎች ቋንቋዎቹን ከማይችሉ ሰዎች ይበልጥ ወደ ይሖዋ መቅረብ ይችላሉ? አይችሉም። (ማቴ. 11:25) ይሖዋ ለእኛ ያለው ፍቅር በትምህርት ደረጃችን ወይም በቋንቋ ችሎታችን ላይ የተመሠረተ አይደለም። ይሖዋ ጥበቡን፣ የተማሩ ሰዎች ብቻ እንዲያገኙት ከማድረግ ይልቅ የተማሩም ይሁኑ ያልተማሩ በመላው ዓለም የሚኖሩ ሰዎች እንዲያገኙት አድርጓል። በመንፈስ መሪነት የተጻፈው ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስ በሺዎች በሚቆጠሩ ቋንቋዎች ተተርጉሟል። በመሆኑም በዓለም ዙሪያ ያሉ ሰዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ መጠቀም እንዲሁም የይሖዋ ወዳጆች መሆን የሚችሉት እንዴት እንደሆነ መማር ይችላሉ።—2 ጢሞ. 3:16, 17፤ w24.06 6-7 አን. 13-15
ሐሙስ፣ መስከረም 10
[የኢየሩሳሌም መጥፊያ] እንደቀረበ እወቁ።—ሉቃስ 21:20
ኢየሱስ በትንቢት የተናገረለት የአይሁድ ሥርዓት ጥፋት እየቀረበ ነበር። ክርስቲያኖች የቀረውን ጊዜ ተጠቅመው እንደ እምነትና ጽናት ያሉትን ባሕርያት በማዳበር ራሳቸውን ማዘጋጀት ይችሉ ነበር። (ዕብ. 10:25፤ 12:1, 2) እኛም ዕብራውያን ክርስቲያኖች ካጋጠማቸው እጅግ የከፋ መከራ ከፊታችን ይጠብቀናል። (ማቴ. 24:21፤ ራእይ 16:14, 16) ይሖዋ ለእነዚያ ክርስቲያኖች ከሰጣቸው ተግባራዊ ምክሮች መካከል አንዳንዶቹን እስቲ እንመልከት፤ እነዚህ ምክሮች እኛንም ይጠቅሙናል። ሐዋርያው ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ የእምነት አጋሮቹ የአምላክን ቃል በጥልቀት እንዲቆፍሩ አበረታቷቸዋል። (ዕብ. 5:14–6:1) ጳውሎስ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን በመጠቀም የክርስትና የአምልኮ ሥርዓት ከአይሁድ እምነት ያለውን ብልጫ አብራርቶላቸዋል። ጳውሎስ እነዚህ ክርስቲያኖች እውቀታቸውንና ግንዛቤያቸውን ማሳደጋቸው እንደሚጠቅማቸው ያውቅ ነበር። ምክንያቱም እንዲህ ማድረጋቸው ከእውነት ጎዳና ስተው እንዲወጡ የሚያደርጉ የሐሰት ትምህርቶችን ለይተው እንዲያውቁና ከእነዚህ ትምህርቶች እንዲርቁ ይረዳቸዋል። w24.09 8-9 አን. 2-3, 6
ዓርብ፣ መስከረም 11
ጌታ በእርግጥ ተነስቷል።—ሉቃስ 24:34
የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ማበረታቻ ያስፈልጋቸው ነበር። ለምን? አንዳንዶቹ ሙሉ ጊዜያቸውን ተጠቅመው ኢየሱስን ለመከተል ሲሉ ቤታቸውን፣ ቤተሰባቸውንና ሥራቸውን ትተዋል። (ማቴ. 19:27) ሌሎቹ ደግሞ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በመሆናቸው የተነሳ ከማኅበረሰቡ ተገልለዋል። (ዮሐ. 9:22) እነዚህን መሥዋዕቶች የከፈሉት ኢየሱስ ተስፋ የተሰጠበት መሲሕ መሆኑን ስላመኑ ነው። (ማቴ. 16:16) ሆኖም ኢየሱስ ሲገደል ተስፋቸው ጨለመ፤ በሐዘንም ተዋጡ። ኢየሱስ የደቀ መዛሙርቱን ሐዘን እንደ መንፈሳዊ ድክመት አልቆጠረውም፤ ከዚህ ይልቅ በእሱ ሞት ማዘናቸው የሚጠበቅ ነገር እንደሆነ ተሰምቶታል። በመሆኑም ከሞት በተነሳበት በዚያው ቀን ወዳጆቹን ማበረታታት ጀመረ። ለምሳሌ መግደላዊቷ ማርያም መቃብሩ ጋ ቆማ እያለቀሰች ሳለ ተገልጦላታል። (ዮሐ. 20:11, 16) ወደ ኤማሁስ ለተጓዙት ሁለት ደቀ መዛሙርትም ተገልጦላቸዋል። በተጨማሪም ለሐዋርያው ጴጥሮስ ተገልጦለታል። w24.10 13 አን. 5-6
ቅዳሜ፣ መስከረም 12
እናንተ ስላላችሁ ተስፋ፣ ምክንያት እንድታቀርቡ ለሚጠይቃችሁ ሰው ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር ዝግጁ ሁኑ።—1 ጴጥ. 3:15
ወላጆች፣ ልጆቻችሁ በፈጣሪ የሚያምኑበትን ምክንያት እንዲያብራሩ አዘጋጇቸው።ከልጆቻችሁ ጋር በjw.org ላይ የሚገኙትን “የወጣቶች ጥያቄ—ፍጥረት ወይስ ዝግመተ ለውጥ?” የሚሉትን ተከታታይ ርዕሶች አብራችሁ መከለሳችሁ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ከዚያም ልጆቻችሁ ፈጣሪን በተመለከተ ለሌሎች እውነቱን ለማስረዳት ይበልጥ አሳማኝ እንደሆነ የሚሰማቸውን ነጥብ ተወያዩ። ጥሩ ውይይት ለማድረግ ፈቃደኛ የሆነ ሰው ካገኙ ቀላል የሆነ ማብራሪያ ተጠቅመው እንዲያወያዩት አበረታቷቸው። ለምሳሌ አንድ ልጅ “የማምነው የማየውን ነገር ብቻ ነው፤ አምላክን ደግሞ አይቼው አላውቅም” ይላቸው ይሆናል። አንድ ክርስቲያን ወጣት እንዲህ ብሎ ሊመልስ ይችላል፦ “ሰዎች ከሚኖሩበት አካባቢ በጣም ርቆ በሚገኝ ጫካ ውስጥ በድንጋይ የተገነባ የውኃ ጉድጓድ አገኘህ እንበል። ምን መደምደሚያ ላይ ትደርሳለህ? አንድ የውኃ ጉድጓድ መኖሩ የሠራው ሰው እንዳለ የሚያረጋግጥ ከሆነ የጽንፈ ዓለሙ መኖር ፈጣሪ እንዳለ የሚያረጋግጥ አይደለም?” w24.12 18 አን. 16
እሁድ፣ መስከረም 13
በዕድሜ በገፉት መካከል ጥበብ፣ ከረጅም ዕድሜስ ጋር ማስተዋል አይገኝም?—ኢዮብ 12:12
ሁላችንም በሕይወታችን ውስጥ አስፈላጊ ውሳኔዎችን ስናደርግ ምክር ያስፈልገናል። ከጉባኤ ሽማግሌዎችና ከሌሎች የጎለመሱ ክርስቲያኖች እንዲህ ያለውን ምክር ማግኘት እንችላለን። ዕድሜያቸው ከእኛ በጣም የሚበልጥ ከሆነ ምክራቸው ዘመን ያለፈበት እንደሆነ ማሰብ አይኖርብንም። ይሖዋ ከአረጋውያን እንድንማር ይፈልጋል። ከእኛ የበለጠ ረጅም ዕድሜ ስለኖሩ ተሞክሮ፣ ማስተዋልና ጥበብ ማካበት ችለዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ይሖዋ ሕዝቦቹን ለማበረታታትና ለመምራት ታማኝ አረጋውያንን ተጠቅሟል። ሙሴን፣ ዳዊትንና ሐዋርያው ዮሐንስን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። እነዚህ ሰዎች የኖሩት በተለያየ ዘመን ነው፤ የነበሩበት ሁኔታም ቢሆን በእጅጉ ይለያያል። የሕይወታቸው ማብቂያ ሲቃረብ ለወጣቶች ጥበብ የሚንጸባረቅበት ምክር ሰጥተዋል። ሦስቱም ታማኝ አረጋውያን አምላክን መታዘዝ ያለውን ጥቅም ጎላ አድርገው ገልጸዋል። ወጣቶችም ሆንን አረጋውያን የእነሱን ምክር መመርመራችን ይጠቅመናል።—ሮም 15:4፤ 2 ጢሞ. 3:16፤ w24.11 8 አን. 1-2
ሰኞ፣ መስከረም 14
የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁና ደሙን ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም።—ዮሐ. 6:53
በኖኅ ዘመን አምላክ፣ ሰዎች ደም እንዳይበሉ ከልክሎ ነበር። (ዘፍ. 9:3, 4) ይሖዋ ይህንኑ ትእዛዝ ለእስራኤላውያን በሰጠው ሕግ ውስጥም አካቶታል። ሕጉ፣ ደም የሚበላ ማንኛውም ሰው “ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ እንዲጠፋ ይደረግ” ይላል። (ዘሌ. 7:27) ኢየሱስም ይህን ሕግ ያከብራል። (ማቴ. 5:17-19) ስለዚህ ኢየሱስ፣ ሕዝቡ ቃል በቃል ሥጋውን እንዲበሉ ወይም ደሙን እንዲጠጡ ይነግራቸዋል ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው። ኢየሱስ በምሳሌያዊ ሁኔታ እየተናገረ ነበር። ከዚያ ቀደምም ሳምራዊቷን ሴት ባነጋገረበት ወቅት ምሳሌያዊ አገላለጽ ተጠቅሟል። ‘እኔ የምሰጠው ውኃ የዘላለም ሕይወት ያስገኛል’ ብሏታል። (ዮሐ. 4:7, 14) ኢየሱስ ሳምራዊቷ ሴት ከሆነ ምንጭ የፈለቀ ውኃ በመጠጣት ብቻ የዘላለም ሕይወት እንደምታገኝ መናገሩ እንዳልነበር ግልጽ ነው። በተመሳሳይም በቅፍርናሆም ያነጋገራቸው ሰዎች ቃል በቃል ሥጋውን ቢበሉና ደሙን ቢጠጡ የዘላለም ሕይወት እንደሚያገኙ መናገሩ አልነበረም። w24.12 9 አን. 4-6
ማክሰኞ፣ መስከረም 15
ሰውነታችሁን ሕያው፣ ቅዱስና በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው መሥዋዕት አድርጋችሁ [አቅርቡ]፤ ይህም የማሰብ ችሎታችሁን ተጠቅማችሁ የምታቀርቡት ቅዱስ አገልግሎት ነው።—ሮም 12:1
ክርስቲያን ባሎች ለሴቶች ተገቢ ያልሆነ አመለካከት እንዳያዳብሩ መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል። ለምን? አንዱ ምክንያት፣ የአንድ ሰው አስተሳሰብ ወደ ተግባር ሊያመራው የሚችል መሆኑ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም የነበሩትን ቅቡዓን ክርስቲያኖች “ይህ ሥርዓት እንዲቀርጻችሁ አትፍቀዱ” በማለት አስጠንቅቋቸዋል። (ሮም 12:1, 2) ጳውሎስ በሮም ለነበሩት ክርስቲያኖች ደብዳቤ በጻፈበት ወቅት ጉባኤው ከተቋቋመ ረዘም ያለ ጊዜ አልፎ ነበር። ሆኖም ጳውሎስ የተናገረው ሐሳብ፣ ጉባኤው ውስጥ የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች የዓለም ልማድና አስተሳሰብ አሁንም ተጽዕኖ እያሳደረባቸው እንደነበር ይጠቁማል። አስተሳሰባቸውንና ባሕርያቸውን እንዲያስተካክሉ የመከራቸው ለዚህ ነው። ይህ ምክር ዛሬ ላሉ ክርስቲያን ባሎችም ይሠራል። የሚያሳዝነው፣ አንዳንድ ክርስቲያን ባሎች የዓለም አስተሳሰብ ተጽዕኖ ስላሳደረባቸው በሚስቶቻቸው ላይ ጥቃት እስከመሰንዘር ደርሰዋል። w25.01 9 አን. 4
ረቡዕ፣ መስከረም 16
የበላይ ተመልካቾች ሆናችሁ በማገልገል በአደራ የተሰጣችሁን የአምላክን መንጋ እንደ እረኞች ሆናችሁ ተንከባከቡ።—1 ጴጥ. 5:2
በዛሬው ጊዜ ያሉ ሽማግሌዎች ብዙ ሥራ አለባቸው። ወንጌላውያን ናቸው። (2 ጢሞ. 4:5) ግንባር ቀደም ሆነው በስብከቱ ሥራ በቅንዓት ይካፈላሉ፤ በክልላቸው ውስጥ የስብከቱን ሥራ ያደራጃሉ፤ እንዲሁም ውጤታማ በሆነ መንገድ መስበክና ማስተማር እንድንችል ያሠለጥኑናል። በተጨማሪም ምሕረት በሚንጸባረቅበትና ከአድልዎ ነፃ በሆነ መንገድ የፍርድ ሥራ ያከናውናሉ። አንድ ክርስቲያን ከባድ ኃጢአት በሚፈጽምበት ጊዜ ሽማግሌዎች ከይሖዋ ጋር ያለውን ወዳጅነት እንዲያድስ ለመርዳት ጥረት ያደርጋሉ። በሌላ በኩል ደግሞ የጉባኤውን ንጽሕና ለማስጠበቅ ጥረት ያደርጋሉ። (1 ቆሮ. 5:12, 13፤ ገላ. 6:1) በዋነኝነት ደግሞ ሽማግሌዎች እረኞች ናቸው። (1 ጴጥ. 5:1-3) ጥሩ ዝግጅት አድርገው ቅዱስ ጽሑፋዊ ንግግሮችን ያቀርባሉ፤ በጉባኤው ውስጥ ያለውን እያንዳንዱን ሰው ለማወቅ ይጥራሉ፤ እንዲሁም የእረኝነት ጉብኝት ያደርጋሉ። አንዳንድ ሽማግሌዎች ደግሞ ከእነዚህ ኃላፊነቶች በተጨማሪ በስብሰባ አዳራሽ ግንባታና ጥገና ሥራ ይካፈላሉ፤ የክልል ስብሰባዎችን ያደራጃሉ፤ እንዲሁም በሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴዎችና በሕሙማን ጠያቂ ቡድኖች ውስጥ ያገለግላሉ። በእርግጥም ሽማግሌዎች እኛን ለመርዳት በትጋት ይሠራሉ! w24.10 20 አን. 9
ሐሙስ፣ መስከረም 17
ሁሉም በአዳም እንደሚሞቱ ሁሉም በክርስቶስ ሕያው ይሆናሉ።—1 ቆሮ. 15:22
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “መዋጀት” የሚለው ቃል፣ ቤዛው በመከፈሉ ምክንያት ነፃ መውጣታችንን ያመለክታል። ሐዋርያው ጴጥሮስ ጉዳዩን ሲያብራራ እንዲህ ብሏል፦ “እናንተ ከቀድሞ አባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከንቱ አኗኗር ነፃ የወጣችሁት ሊበላሹ በሚችሉ ነገሮች ይኸውም በብር ወይም በወርቅ እንዳልሆነ ታውቃላችሁና። ከዚህ ይልቅ ነፃ የወጣችሁት [ቃል በቃል “የተዋጃችሁት”] ነውርና እንከን እንደሌለበት በግ ደም ባለ ውድ ደም ይኸውም በክርስቶስ ደም ነው።” (1 ጴጥ. 1:18, 19 ግርጌ) በቤዛዊ መሥዋዕቱ የተነሳ ከኃጢአትና ከሞት ጭቆና ነፃ መውጣት እንችላለን። (ሮም 5:21) በእርግጥም፣ ውድ በሆነው የኢየሱስ ደም ወይም ሕይወት በመዋጀታችን ይሖዋንና ኢየሱስን የምናመሰግንበት በቂ ምክንያት አለን። w25.02 5 አን. 15-16
ዓርብ፣ መስከረም 18
ምንጊዜም ተጠንቅቆ የሚኖር ሰው ደስተኛ ነው።—ምሳሌ 28:14
ራሳችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው? በምሳሌ ምዕራፍ 7 ላይ ከተጠቀሰው ወጣት ምን ትምህርት እንደምናገኝ እንመልከት። ይህ ወጣት ከአንዲት ባለጌ ሴት ጋር የፆታ ብልግና ፈጽሟል። ቁጥር 22 ወጣቱ ይህችን ሴት “በድንገት” እንደተከተላት ይናገራል። ሆኖም ያለፉት ቁጥሮች እንደሚያሳዩት ቀስ በቀስ ወደ ኃጢአት የመሩት ከዚያ በፊት የወሰዳቸው የተለያዩ እርምጃዎች ናቸው። ይህ ወጣት ኃጢአት ከመፈጸሙ በፊት የትኞቹን ነገሮች አድርጓል? በመጀመሪያ፣ ምሽት ላይ በዚህች ሴትዮ ቤት ‘አቅራቢያ በሚገኝ መታጠፊያ አልፏል።’ ከዚያም ወደ ቤቷ አቅጣጫ አመራ። (ምሳሌ 7:8, 9) ቀጥሎም ሴትየዋን ሲያያት አካባቢውን ጥሎ አልሄደም። ከዚህ ይልቅ እንድትስመው ፈቀደላት፤ እንዲሁም ስላቀረበችው የኅብረት መሥዋዕት ስትናገር አዳመጣት፤ ይህን ያለችው መጥፎ ሰው እንዳልሆነች እንዲሰማው ለማድረግ ብላ ሊሆን ይችላል። (ምሳሌ 7:13, 14, 21) ወጣቱ ወደ ኃጢአት ከመሩት አደገኛ ሁኔታዎች ቢርቅ ኖሮ በፈተና ከመውደቅና ኃጢአት ከመፈጸም ራሱን መጠበቅ ይችል ነበር። w24.07 16 አን. 8-9፤ 18 አን. 19
ቅዳሜ፣ መስከረም 19
በደግነት ይቅር ልትሉትና ልታጽናኑት ይገባል።—2 ቆሮ. 2:7
ይሖዋ በሕዝቦቹ መካከል የሚፈጸምን ከባድ ጥፋት በቸልታ አያልፍም። ንስሐ የማይገቡ ኃጢአተኞች “በምሕረት” ታልፈው ከታማኝ አገልጋዮቹ ጋር መቀራረባቸውን እንዲቀጥሉ አይፈቅድላቸውም። ይሖዋ መሐሪ ቢሆንም ልል አይደለም፤ መሥፈርቱንም ዝቅ አያደርግም። (ይሁዳ 4) ደግሞም እንዲህ ማድረግ ምሕረት ሊባል አይችልም፤ ምክንያቱም በጉባኤው ውስጥ ያሉትን ሁሉ አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል። (ምሳሌ 13:20፤ 1 ቆሮ. 15:33) ያም ቢሆን ይሖዋ ማንም እንዲጠፋ እንደማይፈልግ እንማራለን። የሚቻል እስከሆነ ድረስ ሰዎች እንዲድኑ ይፈልጋል። ንስሐ ገብተው ከእሱ ጋር ያላቸውን ዝምድና ማደስ ለሚፈልጉ ሁሉ ምሕረት ያሳያል። (ሕዝ. 33:11፤ 2 ጴጥ. 3:9) በመሆኑም ይሖዋ በቆሮንቶስ የነበረው ወንድም ንስሐ ገብቶ ከኃጢአት ጎዳናው በተመለሰ ጊዜ ጉባኤው ይቅር ሊለውና መልሶ ሊቀበለው እንደሚገባ በሐዋርያው ጳውሎስ አማካኝነት ገልጿል። w24.08 17 አን. 7፤ 18-19 አን. 14-15
እሁድ፣ መስከረም 20
ከሁሉ ከሚያንሱት ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ ያደረጋችሁት ሁሉ ለእኔ እንዳደረጋችሁት ይቆጠራል።—ማቴ. 25:40
በበጎቹና በፍየሎቹ ምሳሌ ላይ ኢየሱስ ፍርድ የሚያስተላልፈው ሰዎች ለቅቡዓን ወንድሞቹ በሚሰጡት ድጋፍ ላይ ተመሥርቶ እንደሆነ እንመለከታለን። (ማቴ. 25:31-46) ኢየሱስ ፍርድ የሚያስተላልፈው ‘በታላቁ መከራ’ ወቅት ልክ ከአርማጌዶን በፊት ነው። (ማቴ. 24:21) አንድ እረኛ በጎቹን ከፍየሎቹ እንደሚለይ ሁሉ ኢየሱስም ቅቡዓን ተከታዮቹን በታማኝነት የደገፉትን ሰዎች ካልደገፉት ሰዎች ይለያል። የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት እንደሚጠቁመው ኢየሱስ በይሖዋ የተሾመ ፈራጅ እንደመሆኑ መጠን በጽድቅ ይፈርዳል። (ኢሳ. 11:3, 4) የሰዎችን ድርጊት፣ አመለካከትና አነጋገር ይመለከታል፤ ይህም ሰዎች ቅቡዓን ወንድሞቹን የሚይዙበትን መንገድ ይጨምራል። (ማቴ. 12:36, 37) ኢየሱስ ቅቡዓን ወንድሞቹንም ሆነ ሥራቸውን የደገፉት እነማን እንደሆኑ ያውቃል። በበግ የተመሰሉት ሰዎች የክርስቶስን ወንድሞች ከሚደግፉባቸው ዋነኛ መንገዶች አንዱ በስብከቱ ሥራ እነሱን መርዳት ነው። w24.09 20-21 አን. 3-4
ሰኞ፣ መስከረም 21
ሁሉንም ነገር መርምሩ።—1 ተሰ. 5:21
ስለ አንድ ነገር ጥርጣሬ ካደረብን መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚያ ጉዳይ ምን እንደሚል ለማወቅ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ለምሳሌ በአምላክ ዓይን ምንም ዋጋ እንደሌለው የተሰማውን ወጣት መለስ ብለን እናስብ። ይህ ሐሳብ እውነት ነው ብሎ መደምደም ይኖርበታል? በፍጹም። ከዚህ ይልቅ፣ ይሖዋ ስለ ጉዳዩ ያለውን አመለካከት ለማወቅ ጥረት በማድረግ ‘ሁሉንም ነገር መመርመር’ ይኖርበታል። የአምላክን ቃል ስናነብ ይሖዋ ሲያነጋግረን እያዳመጥን ነው ሊባል ይችላል። ይሁንና ከአንድ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ያለውን አመለካከት ለማወቅ ከፈለግን የተለየ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። የመጽሐፍ ቅዱስ ንባባችን ጥያቄ በፈጠረብን ርዕሰ ጉዳይ ላይ ያተኮረ ሊሆን ይገባል። የይሖዋ ድርጅት ባዘጋጃቸው በርካታ የምርምር መሣሪያዎች ተጠቅመን በዚያ ጉዳይ ላይ ምርምር ልናደርግ እንችላለን። (ምሳሌ 2:3-6) ይሖዋ ምርምር ስናደርግ እንዲመራንና ከዚያ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ያለውን አመለካከት ለማወቅ እንዲያግዘን በጸሎት ልንጠይቀው እንችላለን። ከዚያም ለእኛ ሁኔታ የሚሠሩ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችንና ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ምክሮችን መፈለግ እንችላለን። w24.10 25 አን. 4-5
ማክሰኞ፣ መስከረም 22
[ፍቅር] የራሱን ፍላጎት አያስቀድምም።—1 ቆሮ. 13:5
ይሖዋ በኩራት ወይም በራስ ወዳድነት ተነሳስቶ መብት ለማግኘት የሚጣጣርን ሰው አይባርክም። (1 ቆሮ. 10:24, 33፤ 13:4) የኢየሱስ የቅርብ ወዳጆችም እንኳ ተገቢ ባልሆነ ምክንያት ተነሳስተው መብት ለማግኘት የሞከሩበት ጊዜ አለ። የኢየሱስ ሐዋርያት የሆኑት ያዕቆብና ዮሐንስ ምን እንዳደረጉ ልብ በል። በመንግሥቱ ውስጥ ለየት ያለ ቦታ እንዲሰጣቸው ኢየሱስን ጠይቀውት ነበር። ኢየሱስ ይህን በመመኘታቸው አላመሰገናቸውም። ከዚህ ይልቅ ለ12ቱም ሐዋርያት እንዲህ አላቸው፦ “ከመካከላችሁ ታላቅ መሆን የሚፈልግ ሁሉ አገልጋያችሁ ሊሆን ይገባል፤ እንዲሁም ከመካከላችሁ ፊተኛ መሆን የሚፈልግ ሁሉ፣ የሁሉ ባሪያ ሊሆን ይገባል።” (ማር. 10:35-37, 43, 44) በትክክለኛው የልብ ዝንባሌ ተነሳስተው፣ ማለትም ሌሎችን ለማገልገል ብለው መብት ለማግኘት የሚጣጣሩ ወንድሞች ለጉባኤው በረከት ይሆናሉ።—1 ተሰ. 2:8፤ w24.11 15-16 አን. 7-8
ረቡዕ፣ መስከረም 23
በብዙ አማካሪዎች . . . ይሳካል።—ምሳሌ 15:22
ፍቅር ውሳኔ በምናደርግበት ጊዜ “የሌላውን ሰው ጥቅም” እንድንፈልግና ልከኛ እንድንሆን ያነሳሳናል። (1 ቆሮ. 10:23, 24, 32፤ 1 ጢሞ. 2:9, 10) በዚህ መንገድ ለሌሎች ያለንን ፍቅርና አክብሮት የሚያንጸባርቅ ውሳኔ ማድረግ እንችላለን። ትልቅ ውሳኔ የምታደርግ ከሆነ ውሳኔውን በሥራ ላይ ማዋል ምን እንደሚጠይቅ አስብ። ኢየሱስ ‘ወጪያችንን እንድናሰላ’ አሳስቦናል። (ሉቃስ 14:28) እንግዲያው ውሳኔውን ስኬታማ ለማድረግ ምን ያህል ጊዜ፣ ገንዘብ ወይም ጥረት እንደሚጠይቅብህ አስላ። ምናልባትም እያንዳንዱ የቤተሰብህ አባል ያደረግከውን ውሳኔ ስኬታማ ለማድረግ ምን አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚችል ከቤተሰብህ ጋር መወያየት ትችል ይሆናል። በዚህ መንገድ ዕቅድ ማውጣትህ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው? ይህን ስታደርግ በውሳኔህ ላይ አንዳንድ ማስተካከያዎችን ማድረግ እንዳለብህ ወይም ሌላ አማራጭ ብትከተል የተሻለ እንደሚሆን ትገነዘብ ይሆናል። ደግሞም ከቤተሰብህ አባላት ጋር መወያየትህና የሚሰጡህን ሐሳብ ማዳመጥህ ውሳኔውን ስኬታማ ለማድረግ እንዲተባበሩህ ሊያነሳሳቸው ይችላል። w25.01 18-19 አን. 14-15
ሐሙስ፣ መስከረም 24
ደስ ይበላችሁ፤ ሐሴትም አድርጉ።—ኢሳ. 65:18
ኢሳይያስ በመንፈሳዊው ገነት ውስጥ በመሆናችን ‘ደስ ሊለንና ሐሴት ልናደርግ’ የሚገባው ለምን እንደሆነ ገልጿል። ይህን መንፈሳዊ ገነት የፈጠረው ይሖዋ ነው። (ኢሳ. 65:18, 19) ይሖዋ፣ ሰዎች በዚህ አሮጌ ዓለም ውስጥ ካሉት በመንፈሳዊ ድርቅ የተመቱ ድርጅቶች ወጥተው ውብ ወደሆነው መንፈሳዊ ገነት እንዲገቡ እንድንጋብዝ እየተጠቀመብን ያለው ለዚህ ነው። በእውነት ውስጥ በመሆናችን ምክንያት ላገኘናቸው በረከቶች በጣም አመስጋኞች ነን፤ ለሌሎችም ይህንን ለመናገር እንጓጓለን። (ኤር. 31:12) በመንፈሳዊው ገነት ውስጥ በመኖራችን ምክንያት ላገኘናቸው ተስፋዎችም አመስጋኞች ነን። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ቤቶችን እንሠራለን፤ በዚያም እንኖራለን፤ ወይንንም እንተክላለን፤ ፍሬውንም እንበላለን’ ይላል። ‘ይሖዋ ስለሚባርከን በከንቱ አንለፋም።’ እውነተኛ ዓላማ ያለው አስተማማኝና አርኪ ሕይወት እንደሚኖረን ቃል ገብቶልናል። እያንዳንዳችን የሚያስፈልገንን ነገር ያውቃል፤ “የሕያዋን ፍጥረታትንም ሁሉ ፍላጎት” ያሟላል።—ኢሳ. 65:20-24፤ መዝ. 145:16፤ w24.04 22-23 አን. 11-12
ዓርብ፣ መስከረም 25
[አምላክ] ጠንካራ ዓለቴና መጠጊያዬ ነው።—መዝ. 62:7
በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ በመታመን ዓለታችን እናደርገዋለን። በአስቸጋሪ ጊዜያትም እንኳ እሱን መታዘዝ ጥቅም እንደሚያስገኝልን እንተማመናለን። (ኢሳ. 48:17, 18) የእሱን ድጋፍ በሕይወታችን ባየን ቁጥር በእሱ ላይ ያለን እምነት ያድጋል። ከይሖዋ እርዳታ ውጭ ልንቋቋማቸው የማንችላቸውን ፈተናዎች ለመጋፈጥ ይበልጥ ዝግጁ እንሆናለን። ልክ እንደ ግዙፍ ዓለት ይሖዋ የማይለወጥ አምላክ ነው። ይሖዋ ባሕርዩም ሆነ ዓላማው አይቀየርም። (ሚል. 3:6) በኤደን ዓመፅ በተነሳበት ጊዜ ይሖዋ ዓላማውን አልቀየረም። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደጻፈው ይሖዋ “ራሱን ሊክድ አይችልም።” (2 ጢሞ. 2:13) ይህም ማለት ምንም ነገር ቢፈጠር ወይም ሌሎች ምንም ነገር ቢያደርጉ ይሖዋ አምላክ ባሕርያቱን፣ ዓላማውን ወይም መሥፈርቶቹን አይቀይርም ማለት ነው። በማይለወጠው አምላካችን በመተማመን እንዲያድነንና አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ለመቋቋም እንዲረዳን ልንጠይቀው እንችላለን።—መዝ. 62:6, 7፤ w24.06 27-28 አን. 7-8
ቅዳሜ፣ መስከረም 26
ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው . . . የልብ ሰው [ነው]።—1 ጴጥ. 3:4
እየተጠናናችሁ ከሆነ ለመጋባት ወይም ላለመጋባት ለመወሰን ምን ሊረዳችሁ ይችላል? በደንብ ተዋወቁ። መጠናናት ከመጀመራችሁ በፊትም ስለ ግለሰቡ አንዳንድ ነገሮችን እንደምታውቁ ምንም ጥያቄ የለውም። አሁን ግን ‘የተሰወረውን የልብ ሰው’ ለማወቅ የሚያስችል አጋጣሚ አግኝታችኋል። ይህም ለማግባት ስለምታስቡት ሰው መንፈሳዊነት፣ ባሕርይና አስተሳሰብ በደንብ ማወቅን ይጨምራል። ጊዜ እያለፈ ሲሄድ እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎችን መመለስ መቻል ይኖርባችኋል፦ ‘ግለሰቡ ጥሩ የትዳር አጋር ይሆነኛል?’ (ምሳሌ 31:26, 27, 30፤ ኤፌ. 5:33፤ 1 ጢሞ. 5:8) ‘አንዳችን የሌላውን ስሜታዊ ፍላጎት ማሟላት እንችላለን? አንዳችን የሌላውን ድክመት ችለን መኖር እንችላለን?’ (ሮም 3:23) ይበልጥ እየተዋወቃችሁ ስትሄዱ የሚከተለውን ነጥብ አስታውሱ፦ እርስ በርስ የምትጣጣሙ መሆናችሁ በዋነኝነት የተመካው ምን ያህል ትመሳሰላላችሁ በሚለው ላይ ሳይሆን ልዩነታችሁን ምን ያህል አቻችላችሁ መኖር ትችላላችሁ በሚለው ላይ ነው። w24.05 27 አን. 5
እሁድ፣ መስከረም 27
በይሖዋ ላይ ኃጢአት ሠርቻለሁ።—2 ሳሙ. 12:13
ንጉሥ ዳዊት ከባድ ኃጢአት ፈጽሟል። ሆኖም በሠራው ኃጢአት ምክንያት ነቢዩ ናታን ሲገሥጸው በትሕትና ንስሐ ገባ። (መዝ. 51:3, 4, 17 እና አናት ላይ ያለው መግለጫ) ንጉሥ ሕዝቅያስም በይሖዋ ላይ ኃጢአት ሠርቷል። (2 ዜና 32:25) ሆኖም እንደ ዳዊት ሁሉ ሕዝቅያስም በትሕትና ንስሐ ገባ። (2 ዜና 32:26) ይሖዋም እሱን ‘በፊቱ ትክክል የሆነውን ነገር ያደረገ’ ታማኝ ንጉሥ አድርጎ ተመልክቶታል። (2 ነገ. 18:3) ከዚህ ምን እንማራለን? ከኃጢአታችን ንስሐ መግባትና ስህተታችንን ላለመድገም አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ማድረግ አለብን። ይሁንና ቀላል በሚመስሉ ጉዳዮችም ቢሆን የጉባኤ ሽማግሌዎች ምክር ቢሰጡንስ? ይሖዋም ሆነ ሽማግሌዎች እንደማይወዱን ሊሰማን አይገባም። ጥሩዎቹ የእስራኤል ነገሥታትም እንኳ ምክርና ተግሣጽ ተሰጥቷቸዋል። (ዕብ. 12:6) እርማት ሲሰጠን (1) ምክሩን በትሕትና መቀበል፣ (2) አስፈላጊዎቹን ማስተካከያዎች ማድረግ እንዲሁም (3) በሙሉ ልባችን ይሖዋን ማገልገላችንን መቀጠል ይኖርብናል። ከኃጢአታችን ንስሐ ከገባን ይሖዋ ይቅር ይለናል።—2 ቆሮ. 7:9, 11፤ w24.07 21 አን. 8፤ 22 አን. 9, 11
ሰኞ፣ መስከረም 28
ክፉውን ሰው ከመካከላችሁ አስወግዱት።—1 ቆሮ. 5:13
አንድ ጥፋተኛ ከጉባኤ የሚወገደው ሽማግሌዎች እሱን ወደ ንስሐ ለመምራት በተደጋጋሚ ያደረጉትን ጥረት ሳይቀበል ከቀረ ነው።። (2 ነገ. 17:12-15) የይሖዋን መሥፈርቶች ላለመታዘዝ እንደመረጠ በተግባሩ አሳይቷል። (ዘዳ. 30:19, 20) በመሆኑም ከእንግዲህ በኋላ የይሖዋ ምሥክር እንዳልሆነ የሚገልጽ ማስታወቂያ ለጉባኤው ይነገራል። የዚህ ማስታወቂያ ዓላማ ጥፋተኛውን ማሸማቀቅ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ዓላማው፣ ወንድሞችና እህቶች ከዚህ ሰው ጋር ‘መግጠማቸውን እንዲተዉ አልፎ ተርፎም እንዲህ ካለው ሰው ጋር ምግብ እንኳ እንዳይበሉ’ የሚያዘውን ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያ እንዲከተሉ መርዳት ነው። (1 ቆሮ. 5:9-11) ይህ መመሪያ የተሰጠበት አጥጋቢ ምክንያት አለ። ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ጥቂት እርሾ ሊጡን ሁሉ ያቦካዋል’ ሲል ጽፏል። (1 ቆሮ. 5:6) ንስሐ የማይገቡ ኃጢአተኞች በይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች ለመመራት ጥረት የሚያደርጉ ሰዎችን ቁርጠኝነት ያዳክማሉ።—ምሳሌ 13:20፤ 1 ቆሮ. 15:33፤ w24.08 27 አን. 3-4
ማክሰኞ፣ መስከረም 29
ኃይልን በሚሰጠኝ በእሱ አማካኝነት ለሁሉም ነገር የሚሆን ብርታት አለኝ።—ፊልጵ. 4:13
ለሌሎች ቃል በቃል ኃይል ወይም ብርታት መስጠት አንችልም። ሆኖም ኃይላችንን እነሱን ለመርዳት ልንጠቀምበት እንችላለን። ለምሳሌ በዕድሜ ለገፉ ወይም ለታመሙ ክርስቲያኖች ልንላላክላቸው ወይም የቤት ውስጥ ሥራ በመሥራት ልናግዛቸው አሊያም ደግሞ በስብሰባ አዳራሽ ጽዳት ወይም ጥገና ሥራ ለመካፈል ራሳችንን ልናቀርብ እንችል ይሆናል። ቃላትም ኃይል እንዳላቸው አትዘንጋ። አንድን ወንድም ወይም አንዲትን እህት ከልብ በማመስገን ልታበረታታቸው ትችል ይሆን? ማጽናኛ የሚያስፈልገው ሰው ታውቃለህ? ከሆነ፣ ቅድሚያውን ወስደህ ግለሰቡን ለማነጋገር ለምን አትሞክርም? በአካል ልትጠይቀው፣ ስልክ ልትደውልለት አሊያም ደግሞ ፖስት ካርድ፣ ኢሜይል ወይም የጽሑፍ መልእክት ልትልክለት ትችላለህ። የምትናገረው ነገር በደንብ የተቀነባበረ መሆን አያስፈልገውም። የእምነት አጋርህ ታማኝነቱን ጠብቆ ያንን ቀን እንዲያልፍ ወይም ስላለበት ሁኔታ አዎንታዊ አመለካከት እንዲኖረው ለመርዳት ከልብ የመነጩ ጥቂት ቃላት ብቻ እንኳ በቂ ሊሆኑ ይችላሉ።—ምሳሌ 12:25፤ ኤፌ. 4:29፤ w24.09 28 አን. 8-10
ረቡዕ፣ መስከረም 30
የበላይ ተመልካች ለመሆን የሚጣጣር ሰው መልካም ሥራን ይመኛል።—1 ጢሞ. 3:1
የጉባኤ አገልጋይ ሆነህ እያገለገልክ ከሆነ ሽማግሌ ሆኖ ለማገልገል የሚያስፈልጉትን ብቃቶች እያሟላህ ሊሆን ይችላል። ታዲያ ይህን “መልካም ሥራ” ለመሥራት መጣጣር ትችል ይሆን? የሽማግሌዎች ሥራ የትኞቹን ነገሮች ያካትታል? በስብከቱ ሥራ በግንባር ቀደምትነት ይካፈላሉ፤ ለማስተማርና እረኝነት ለማድረግ ተግተው ይሠራሉ፤ እንዲሁም በንግግራቸውና በመልካም ምሳሌነታቸው ጉባኤውን ያንጻሉ። በዚህም የተነሳ መጽሐፍ ቅዱስ በትጋት የሚሠሩትን ሽማግሌዎች “ስጦታ” በማለት ይጠራቸዋል። (ኤፌ. 4:8) የጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ ለማገልገል ብቃቱን ማሟላት የምትችለው እንዴት ነው? ሽማግሌ ለመሆን የሚያስፈልገውን ብቃት ማሟላት ሥራ ለመቀጠር የሚያስፈልገውን ብቃት ከማሟላት የተለየ ነው። ሥራ ለመቀጠር ካሰብክ ቀጣሪህ የሚፈልጋቸው ክህሎቶች እስካሉህ ድረስ ሥራውን ማግኘት ትችላለህ። በአንጻሩ ግን፣ ሽማግሌ ሆነህ ለመሾም ከፈለግክ የመስበክና የማስተማር ክህሎት ማዳበርህ ብቻውን በቂ አይደለም። በ1 ጢሞቴዎስ 3:1-7 እና በቲቶ 1:5-9 ላይ የተገለጹትን ከሽማግሌዎች የሚጠበቁ ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶች ማሟላት ይኖርብሃል። w24.11 20 አን. 1-3