ኅዳር
እሁድ፣ ኅዳር 1
ለዘላለም ቅር አልሰኝም።—ኤር. 3:12
ሽማግሌዎች ከጉባኤ የተወገደን ሰው የሚይዙበት መንገድ የይሖዋን ርኅራኄ የሚያንጸባርቅ እንዲሆን ጥረት ያደርጋሉ። ለምሳሌ ይሖዋ፣ በጥንቷ እስራኤል የነበሩት ዓመፀኛ ሕዝቦቹ ወደ እሱ ለመመለስ የመጀመሪያውን እርምጃ እንዲወስዱ አልጠበቀባቸውም። ከዚህ ይልቅ፣ እነሱ ምንም ዓይነት የንስሐ ምልክት ከማሳየታቸው በፊት ቅድሚያውን ወስዶ ረድቷቸዋል። ይሖዋ ለሕዝቡ የሚያሳየውን ርኅራኄ ሆሴዕን እንደ ምሳሌ በመጠቀም አሳይቷል። የሆሴዕ ሚስት ገና ኃጢአት መፈጸሟን ባታቆምም እንኳ ሆሴዕ ቅድሚያውን ወስዶ እንዲታረቃት ነግሮታል። (ሆሴዕ 3:1፤ ሚል. 3:7) ክርስቲያን ሽማግሌዎችም የይሖዋን ምሳሌ ስለሚከተሉ ጥፋተኛው እንዲመለስ ከልባቸው ይፈልጋሉ፤ እንዲሁም መመለስ ከባድ እንዲሆንበት አያደርጉም። ኢየሱስ ስለ አባካኙ ልጅ በተናገረው ምሳሌ ላይ አባትየው ልጁ ወደ ቤት ሲመለስ እንዳየው “እየሮጠ [ሄዶ] አንገቱ ላይ ተጠምጥሞ ሳመው።” (ሉቃስ 15:20) አባትየው ልጁ ይቅርታ እስኪጠይቀው ድረስ እንዳልጠበቀ ልብ በል። ከዚህ ይልቅ ማንኛውም አፍቃሪ አባት እንደሚያደርገው ቀድሞ እርምጃ የወሰደው እሱ ነው። w24.08 28 አን. 7-8
ሰኞ፣ ኅዳር 2
ከእናንተ መካከል ጥበብ የጎደለው ሰው ካለ አምላክን ያለማሰለስ ይለምን፤ አምላክ ስህተት ሳይፈላልግ ለሁሉም በልግስና ይሰጣል።—ያዕ. 1:5 ግርጌ
በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ያሉት ቃላት እንደሚያሳዩት ይሖዋ ጥበቡን አይሰስትም። ከዚህ ይልቅ ለሌሎች በልግስና ያካፍላል። ከዚህም ሌላ ይሖዋ ጥበብን የሚሰጠው “ማንንም ሳይነቅፍ” ወይም “ስህተት ሳይፈላልግ” እንደሆነ ልብ በል። የእሱ አመራር እንደሚያስፈልገን አምነን በመቀበላችን የጥፋተኝነት ስሜት እንዲሰማን አይፈልግም። እንዲያውም የእሱን አመራር እንድንጠይቅ አበረታቶናል። (ምሳሌ 2:1-6) እኛስ ጥበባችንን ለሌሎች በማካፈል የይሖዋን ምሳሌ መከተል እንችል ይሆን? (መዝ. 32:8) የይሖዋ ሕዝቦች የተማሩትን ነገር ለሌሎች ለማካፈል የሚያስችል ብዙ አጋጣሚ አላቸው። ለምሳሌ አዳዲስ አስፋፊዎችን በአገልግሎት ለማሠልጠን ብዙ አጋጣሚ እናገኛለን። ሽማግሌዎች፣ የጉባኤ አገልጋዮችንና የተጠመቁ ወንድሞችን በጉባኤ ውስጥ ያላቸውን ኃላፊነት እንዴት መወጣት እንደሚችሉ በትዕግሥት ያሠለጥናሉ። በግንባታና በጥገና ሥራ ተሞክሮ ያላቸው ክርስቲያኖች ደግሞ እምብዛም ተሞክሮ የሌላቸውን ወንድሞች በቲኦክራሲያዊ ፕሮጀክቶች ላይ ያሠለጥናሉ። w24.09 28-29 አን. 11-12
ማክሰኞ፣ ኅዳር 3
በእኛ ዘንድ እጅግ የተወደዳችሁ ነበራችሁ።—1 ተሰ. 2:8
ለሽምግልና ብቃቱን ለማሟላት ‘የማትነቀፍ’ መሆን ይኖርብሃል። ይህም ሲባል ማንም ሰው በመጥፎ ምግባር ስለማይከስህ በጉባኤ ውስጥ ጥሩ ስም ይኖርሃል ማለት ነው። (1 ጢሞ. 3:2) ከዚህም ሌላ በውጭ ባሉት ሰዎች ዘንድ በመልካም የተመሠከረልህ ልትሆን ይገባል። የማያምኑ ሰዎች ክርስቲያናዊ እምነትህን ሊተቹ ይችላሉ፤ ሆኖም በሐቀኝነትህ ወይም በምግባርህ ላይ ጥያቄ ለማንሳት የሚያበቃ መሠረት ሊኖራቸው አይገባም። (ዳን. 6:4, 5) ‘በጉባኤ ውስጥም ሆነ በውጭ ባሉ ሰዎች ዘንድ ጥሩ ስም አትርፌያለሁ?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። ‘ጥሩ የሆነውን ነገር የምትወድ’ ከሆነ የሌሎችን ጥሩ ጎን ትመለከታለህ፤ እንዲሁም ላሏቸው መልካም ባሕርያት ታመሰግናቸዋለህ። (ቲቶ 1:8) ለሌሎች መልካም ማድረግም ያስደስትሃል፤ እንዲያውም ከሚጠበቅብህ አልፈህ ትሄዳለህ። ይህ ባሕርይ ለሽማግሌዎች በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ሽማግሌዎች ለጉባኤው እረኝነት በማድረግና ሌሎች ኃላፊነቶቻቸውን በመወጣት ብዙ ጊዜ ያሳልፋሉ። (1 ጴጥ. 5:1-3) ያም ቢሆን ሌሎችን በማገልገል የምታገኘው ደስታ ከምትከፍለው ከማንኛውም መሥዋዕት በእጅጉ የላቀ ነው።—ሥራ 20:35፤ w24.11 20-21 አን. 3-5
ረቡዕ፣ ኅዳር 4
ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል።—ሥራ 20:35
የጉባኤ አገልጋዮች በጉባኤ ውስጥ ወሳኝ ሥራ ያከናውናሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ ለእነዚህ ታማኝ ወንድሞች አድናቆት ነበረው። ለምሳሌ በፊልጵስዩስ ለነበሩት ክርስቲያኖች ደብዳቤ በጻፈበት ወቅት ሽማግሌዎቹን ብቻ ሳይሆን የጉባኤ አገልጋዮቹንም ለይቶ በመጥቀስ ሰላምታ አቅርቦላቸዋል። (ፊልጵ. 1:1) በየትኛውም የዕድሜ ክልል የሚገኙ በርካታ የተጠመቁ ወንድሞች የጉባኤ አገልጋዮች በመሆናቸው በጣም ደስተኞች ናቸው። ለምሳሌ ዴቨን የጉባኤ አገልጋይ ሆኖ የተሾመው በ18 ዓመቱ ነው። ሉዊስ የተባለ ወንድም ደግሞ አገልጋይ የሆነው በ50ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ እያለ ነው። ሉዊስ ስሜቱን ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “በተለይ ወንድሞችና እህቶች ስላሳዩኝ ጥልቅ ፍቅር ሳስብ የጉባኤ አገልጋይ ሆኜ እነሱን ማገልገል በመቻሌ ትልቅ ክብር ይሰማኛል።” ሌሎች በርካታ የጉባኤ አገልጋዮችም እንዲህ ይሰማቸዋል። ገና የጉባኤ አገልጋይ ሆነህ ያልተሾምክ የተጠመቅክ ወንድም ከሆንክ ይህን ግብ ማውጣት ትችል ይሆን? w24.11 14 አን. 1-3
ሐሙስ፣ ኅዳር 5
ይሖዋ ሆይ፣ . . . በዓይኖችህ ፊት መልካም የሆነውን ነገር እንዳደረግኩ እንድታስታውስ አጥብቄ እለምንሃለሁ።—2 ነገ. 20:3
የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ የ39 ዓመት ጎልማሳ ሳለ የማይድን በሽታ እንዳለበት አወቀ። ይሖዋ፣ ሕዝቅያስ በሕመሙ የተነሳ እንደሚሞት በነቢዩ ኢሳይያስ አማካኝነት ነገረው። (2 ነገ. 20:1) ሕዝቅያስ ምንም ተስፋ ያለው አይመስልም ነበር። ይህን ዜና ሲሰማ ቅስሙ በጣም ስለተሰበረ ምርር ብሎ አለቀሰ። ወደ ይሖዋም አጥብቆ ጸለየ። ይሖዋ፣ ሕዝቅያስ በእንባ ያቀረበውን ልመና ሲሰማ በጣም ስላዘነለት እንዲህ አለው፦ “ጸሎትህን ሰምቻለሁ። እንባህንም አይቻለሁ። ስለሆነም እፈውስሃለሁ።” ይሖዋ የሕዝቅያስን ዕድሜ እንደሚያረዝምለት እንዲሁም ኢየሩሳሌምን ከአሦራውያን እጅ እንደሚታደጋት በነቢዩ ኢሳይያስ አማካኝነት ቃል በመግባት ምሕረት አሳየው። (2 ነገ. 20:4-6) ምንም መፍትሔ የሌለው የሚመስል የጤና ችግር አጋጥሞሃል? በእንባ ጭምር ወደ ይሖዋ ጸልይ። መጽሐፍ ቅዱስ “የምሕረት አባትና የመጽናናት ሁሉ አምላክ የሆነው” ይሖዋ በሚደርስብን መከራ ሁሉ እንደሚያጽናናን ዋስትና ይሰጠናል።—2 ቆሮ. 1:3, 4፤ w24.12 24 አን. 15-17
ዓርብ፣ ኅዳር 6
እነዚህ ሰዎች ራሳቸው ተስፋ እንደሚያደርጉት ጻድቃንም ሆኑ ጻድቃን ያልሆኑ ሰዎች ከሞት እንደሚነሱ በአምላክ ተስፋ አለኝ።—ሥራ 24:15
ከሞት የተነሱ ሰዎችን መቀበል ምን ያህል አስደሳች ሊሆን እንደሚችል ለማሰብ ሞክር። ስፍር ቁጥር የሌላቸውን የፍጥረት ሥራዎች በመመርመር ስለ ይሖዋ ምን ያህል ትምህርት ልታገኝ እንደምትችልም አስብ። (መዝ. 104:24፤ ኢሳ. 11:9) ከሁሉ በላይ ግን፣ ከበደለኝነት ስሜት ሙሉ በሙሉ ነፃ ሆኖ ይሖዋን ማምለክ እንዴት ደስ ይላል! ‘በኃጢአት ለሚገኝ ጊዜያዊ ደስታ’ ብለህ እነዚህን በረከቶች ማጣት ትፈልጋለህ? (ዕብ. 11:25) በጭራሽ! ከእነዚህ በረከቶች አንጻር በአሁኑ ጊዜ የትኛውንም መሥዋዕት ብንከፍል አያስቆጭም። ደግሞም ገነት በሆነች ምድር ውስጥ መኖር ተስፋ ሆኖ እንደማይቀር ልብ በል። እውን ይሆናል። ይሖዋ በፍቅር ተነሳስቶ ልጁን ባይሰጠን ኖሮ ይህን ሁሉ በረከት ልናገኝ አንችልም ነበር። w25.01 29 አን. 12
ቅዳሜ፣ ኅዳር 7
ለመሆኑ የይሖዋ እጅ አጭር ነው?—ዘኁ. 11:23
የዕብራውያን መጽሐፍ ግሩም የእምነት ምሳሌ የሚሆኑ ሰዎችን ይዘረዝራል፤ ከእነዚህ ውስጥ ጎልቶ የሚጠቀሰው ሙሴ ነው። (ዕብ. 3:2-5፤ 11:23-25) ሙሴ እንደ እምነቱ ሆኖለታል፤ አምላክ በዚያ ጠፍ ምድረ በዳ ለሕዝቡ የሚያስፈልገውን ምግብና ውኃ በተአምር አቅርቧል። (ዘፀ. 15:22-25፤ መዝ. 78:23-25) ይሖዋ እስራኤላውያንን በተአምር ከታደገ ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ ግን የሙሴ እምነት ተፈተነ፤ ሙሴ፣ ይሖዋ ለሕዝቡ ሥጋ ማቅረብ መቻሉን ተጠራጠረ። ይሖዋ በዚያ ወና ምድር በሚሊዮኖች የሚቆጠረውን ያን ሁሉ ሕዝብ ሊያጠግብ የሚችል ሥጋ ማግኘት ይችላል ብሎ ማሰብ ሙሴን ከበደው። ስለዚህ ይሖዋ “ለመሆኑ የይሖዋ እጅ አጭር ነው?” በማለት ጠየቀው። (ዘኁ. 11:21-23) በሌላ አባባል ይሖዋ ‘እውነት አደርገዋለሁ ያልኩትን ነገር ማድረግ እንደሚሳነኝ ታስባለህ?’ በማለት የጠየቀው ያህል ነበር። w25.03 26 አን. 1-2
እሁድ፣ ኅዳር 8
[አምላክ] የጥንቱን ዓለም ከመቅጣት ወደኋላ አላለም።—2 ጴጥ. 2:5
ስለ ጥፋት ውኃው የሚገልጸውን ዘገባ እንደ ትንቢታዊ ጥላ ልንመለከተው ይገባል? አይገባም። ለምን? ምክንያቱም እንዲህ ለማለት የሚያበቃ ቀጥተኛ ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረት የለም። ኢየሱስ ‘የኖኅን ዘመን’ ከእሱ መገኘት ጋር አመሳስሎታል። ሆኖም የጥፋት ውኃው ትንቢታዊ ጥላ እንደሆነ ማለትም በዘገባው ውስጥ የተካተተው እያንዳንዱ ግለሰብና እያንዳንዱ ክስተት የሚያመለክተው ነገር እንዳለ አልገለጸም፤ በተጨማሪም የመርከቡ በር መዘጋት ትንቢታዊ ጥላነት እንዳለው አልተናገረም። (ማቴ. 24:37-39) ኖኅ የይሖዋን የማስጠንቀቂያ መልእክት ሲሰማ ምን ምላሽ ሰጠ? መርከብ በመሥራት እምነት እንዳለው አሳይቷል። (ዕብ. 11:7፤ 1 ጴጥ. 3:20) በተመሳሳይም የአምላክን መንግሥት ምሥራች የሚሰሙ ሰዎች በሰሙት ነገር ላይ ተመሥርተው እርምጃ መውሰድ አለባቸው። (ሥራ 3:17-20) ጴጥሮስ ኖኅን “የጽድቅ ሰባኪ” በማለት ጠርቶታል። በዛሬው ጊዜ ዓለም አቀፍ የስብከት ዘመቻ እየተካሄደ ነው፤ እኛም በዚህ ሥራ በቅንዓት ለመካፈል የቻልነውን ሁሉ ጥረት እናደርጋለን። ያም ቢሆን ምንም ያህል ጥረት ብናደርግ መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት ምድር ላይ ላለ ሰው ሁሉ ምሥራቹን ማዳረስ አንችልም። w24.05 9 አን. 3-5
ሰኞ፣ ኅዳር 9
ይሖዋን የሚፈሩትን . . . ያከብራል።—መዝ. 15:4
ለይሖዋ ወዳጆች ደግነትና አክብሮት ማሳየት የምንችልባቸውን መንገዶች ልንፈልግ ይገባል። (ሮም 12:10) ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? መዝሙር 15:4 አንዱን መንገድ ሲጠቅስ በይሖዋ ድንኳን ውስጥ ያለ ሰው ‘ጉዳት ላይ ሊጥለው ቢችልም እንኳ ቃሉን እንደማያጥፍ’ ይናገራል። ቃላችንን ማጠፋችን ሌሎችን ሊጎዳ እንደሚችል ግልጽ ነው። (ማቴ. 5:37) ለምሳሌ ይሖዋ እንግዶቹ የጋብቻ ቃል ኪዳናቸውን እንዲያከብሩ ይጠብቅባቸዋል። ወላጆች ለልጆቻቸው የገቡትን ቃል ለመጠበቅ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ሲመለከትም ይደሰታል። ለአምላክና ለባልንጀራችን ያለን ፍቅር ቃላችንን ለመጠበቅ የምንችለውን ሁሉ እንድናደርግ ያነሳሳናል። የአምላክን ወዳጆች ማክበር የምንችልበት ሌላኛው መንገድ ደግሞ ለጋሶችና እንግዳ ተቀባዮች በመሆን ነው። (ሮም 12:13) ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር በመዝናናት የምናሳልፈው ጊዜ ከእነሱም ሆነ ከይሖዋ ጋር ያለንን ወዳጅነት ለማጠናከር ይረዳናል። ከዚህም ሌላ እንግዳ ተቀባይ ስንሆን ይሖዋን እንመስለዋለን። w24.06 12 አን. 15-16
ማክሰኞ፣ ኅዳር 10
ታስበው ዘንድ ሟች ሰው ምንድን ነው?—መዝ. 8:4
ይሖዋ እውነትን የሚገልጠው ትሑት ለሆኑ ሰዎች ነው። (ማቴ. 11:25) እውነትን እንድንማር የተደረገልንን እርዳታ በትሕትና ተቀብለናል። (ሥራ 8:30, 31) ያም ቢሆን ኩራተኞች እንዳንሆን መጠንቀቅ አለብን። ኩራተኞች ከሆንን የራሳችን አመለካከት ከቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችና ከይሖዋ ድርጅት ከሚገኘው መመሪያ እኩል ትክክል እንደሆነ ልናስብ እንችላለን። ትሑት ሆነን ለመቆየት ከይሖዋ ታላቅነት አንጻር ከቁብ የማንቆጠር መሆናችንን ማስታወስ ይኖርብናል። (መዝ. 8:3, 4) ይሖዋ ትሑታንና ለመማር ፈቃደኞች እንድንሆን እንዲረዳን መጸለይም እንችላለን። ይሖዋ ከራሳችን አስተሳሰብ ይልቅ በቃሉና በድርጅቱ አማካኝነት የነገረንን የእሱን አስተሳሰብ እንድናስቀድም ሊረዳን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስን ስታነብ ይሖዋ ትሕትናን እንደሚወድ እንዲሁም ኩራትን፣ ትዕቢትንና እብሪትን እንደሚጠላ የሚያሳዩ ነጥቦችን ለማስተዋል ሞክር። በተጨማሪም ከፍ ያለ ግምት እንዲሰጥህ የሚያደርግ የአገልግሎት መብት ካገኘህ ትሑት ለመሆን የበለጠ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብሃል። w24.07 10 አን. 8-9
ረቡዕ፣ ኅዳር 11
ጥቂት የሆነው ሺህ፣ ትንሽ የሆነውም ኃያል ብሔር ይሆናል። እኔ ይሖዋ፣ ይህን በራሱ ጊዜ አፋጥነዋለሁ።—ኢሳ. 60:22
ከ1919 ወዲህ ኢየሱስ የስብከቱን ሥራ ለማደራጀትና ለተከታዮቹ መንፈሳዊ ምግብ ለማቅረብ ጥቂት ቅቡዓን ወንዶችን የያዘ ቡድን እየተጠቀመ ነው። (ሉቃስ 12:42) ይሖዋ ይህ ቡድን የሚያከናውነውን ሥራ እየባረከው እንደሆነ በግልጽ ይታያል። (ኢሳ. 65:13, 14) ባንደራጅ ኖሮ ኢየሱስ የሰጠንን ሥራ ማከናወን አንችልም ነበር። (ማቴ. 28:19, 20) ለምሳሌ የአገልግሎት ክልል ባይመደብልን ኖሮ ምን እንደሚፈጠር እስቲ ለማሰብ ሞክር። ሁሉም ሰው የፈለገበት ቦታ ያገለግላል። አንዳንድ ክልሎች በተለያዩ አስፋፊዎች በተደጋጋሚ ይሠራሉ፤ ሌሎች ክልሎች ደግሞ ጨርሶ ሊረሱ ይችላሉ። መደራጀት ያሉትን ሌሎች ጥቅሞችስ ማሰብ ትችላለህ? ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ዘመን ተከታዮቹን እንዳደራጃቸው ሁሉ በዛሬው ጊዜም እያደራጀን ነው። w24.04 8-9 አን. 2-4
ሐሙስ፣ ኅዳር 12
መልካም ወደ ማድረግ ብታዘነብል ኖሮ ሞገስ አታገኝም ነበር? መልካም ወደ ማድረግ ካላዘነበልክ ግን ኃጢአት በደጅህ እያደባ ነው፤ ሊቆጣጠርህም ይፈልጋል።—ዘፍ. 4:7
ቃየን የአዳምና የሔዋን የበኩር ልጅ ነበር። ከወላጆቹ የኃጢአት ዝንባሌን ወርሷል። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ “የእሱ ሥራ ክፉ” እንደነበር ይናገራል። (1 ዮሐ. 3:12) መሥዋዕት ባቀረበበት ወቅት ይሖዋ ‘ቃየንንና ያቀረበውን መባ በጥሩ ፊት ያልተመለከተው’ ለዚህ ሊሆን ይችላል። በዚህ ጊዜ ቃየን አካሄዱን ከማስተካከል ይልቅ “በጣም ተናደደ”፤ እንዲሁም “እጅግ አዘነ።” (ዘፍ. 4:3-7) ታዲያ ይሖዋ ምን አደረገ? ቃየንን አነጋገረው። መልካም ነገር ካደረገ ሞገሱን እንደሚያሳየው በደግነት ነገረው፤ እንዲሁም አካሄዱ ኃጢአት ወደመፈጸም ሊመራው እንደሚችል አስጠነቀቀው። የሚያሳዝነው፣ ቃየን ይሖዋን ለመስማት አሻፈረኝ አለ። ይሖዋ ወደ ንስሐ እንዲመራው ፈቃደኛ አልሆነም። ታዲያ ይሖዋ፣ ቃየን በጎ ምላሽ ስላልሰጠ ከዚያ በኋላ ኃጢአተኞችን ወደ ንስሐ ለመምራት መሞከሩን አቆመ? በጭራሽ! w24.08 10 አን. 8
ዓርብ፣ ኅዳር 13
በሕይወት እንድትኖሩ ሕይወትን ምረጥ።—ዘዳ. 30:19
እስራኤላውያን ከፊታቸው ግሩም ተስፋ ተዘርግቶላቸዋል። በይሖዋ እርዳታ ተስፋይቱ ምድር ውስጥ ረጅም ዘመን መኖር ይችላሉ። ደግሞም ምድሪቱ እጅግ ውብና ፍሬያማ ነበረች። ሙሴ ስለ ተስፋይቱ ምድር ሲናገር እንዲህ ብሏቸዋል፦ “አንተ ያልገነባሃቸውን ታላላቅና ያማሩ ከተሞች፣ አንተ ባልደከምክባቸው የተለያዩ መልካም ነገሮች የተሞሉ ቤቶችን፣ አንተ ያልቦረቦርካቸውን የውኃ ማጠራቀሚያዎች እንዲሁም አንተ ያልተከልካቸውን የወይን ተክሎችና የወይራ ዛፎች [ታገኛለህ]።” (ዘዳ. 6:10, 11) ሙሴ ለእስራኤላውያን ማስጠንቀቂያም ሰጥቷቸዋል። በዚያች ፍሬያማ ምድር ውስጥ መኖራቸውን መቀጠል ከፈለጉ የይሖዋን ትእዛዛት መከተል ነበረባቸው። ሙሴ የይሖዋን ቃል በመስማትና “ከእሱ ጋር በመጣበቅ” ‘ሕይወትን እንዲመርጡ’ አበረታቷቸዋል። (ዘዳ. 30:20) ሆኖም እስራኤላውያን ይሖዋን አልታዘዙም። በመሆኑም አምላክ በአሦራውያን፣ በኋላም በባቢሎናውያን ድል እንዲደረጉና በግዞት እንዲወሰዱ ፈቀደ።—2 ነገ. 17:6-8, 13, 14፤ 2 ዜና 36:15-17, 20፤ w24.11 9 አን. 5-6
ቅዳሜ፣ ኅዳር 14
የላከኝ አብ ካልሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል ሰው የለም።—ዮሐ. 6:44
ክርስቲያን ነን የሚሉ ብዙ ሰዎች ለመዳን የሚጠበቅባቸው በኢየሱስ “ማመን” እንዲሁም እሱን እንደ ግል አዳኛቸው አድርገው መቀበል ብቻ እንደሆነ ይሰማቸዋል። (ዮሐ. 6:29) ይሁንና በገሊላ ከተሰበሰቡት ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ መጀመሪያ በኢየሱስ ቢያምኑም እንኳ በኋላ ትተውት ሄደዋል። ለምን? ኢየሱስ ከመገባቸው ሰዎች መካከል አብዛኞቹ፣ የሚፈልጉትን ነገር እስከሰጣቸው ድረስ እሱን በደስታ ለመከተል ዝግጁ ነበሩ። የሚፈልጉት ተአምራዊ ፈውስ ማግኘት፣ በነፃ ምግብ መብላት እንዲሁም የሚጥማቸውን ትምህርት መስማት ነበር። ይሁንና ኢየሱስ የእሱ እውነተኛ ደቀ መዝሙር መሆን ከዚህ ያለፈ ነገር እንደሚጠይቅ ተናግሯል። ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣበት ዋነኛ ምክንያት የሰዎችን አካላዊ ፍላጎት ለማሟላት አልነበረም። ሰዎች እሱ ያስተማረውን ነገር በሙሉ በመቀበልና በመታዘዝ ‘ወደ እሱ መምጣት’ ይጠበቅባቸዋል።—ዮሐ. 5:40፤ w24.12 12 አን. 12-13
እሁድ፣ ኅዳር 15
ባሎች ሆይ፣ ክርስቶስ ጉባኤውን እንደወደደ . . . ሁሉ እናንተም ሚስቶቻችሁን መውደዳችሁን ቀጥሉ።—ኤፌ. 5:25
አንድ ባል አክብሮት በጎደለውና በሚያዋርድ መንገድ ሚስቱን መያዙን እንዲያቆም ምን ሊረዳው ይችላል? ኢየሱስን ለመምሰል ጥረት ማድረግ ይችላል። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን የያዘበት መንገድ ባሎች ሚስቶቻቸውን እንዴት ሊይዙ እንደሚገባ የሚያሳይ ግሩም ምሳሌ ይሆናል። ኢየሱስ ሐዋርያቱን ከያዘበትና ካነጋገረበት መንገድ ባሎች ምን ትምህርት ሊያገኙ እንደሚችሉ እንመልከት። ኢየሱስ ሐዋርያቱን ደግነት በሚንጸባረቅበትና ክብራቸውን በሚጠብቅ መንገድ ይዟቸዋል። ክፉ ቃል ተናግሯቸው ወይም ጨቁኗቸው አያውቅም። ኃይሉን ተጠቅሞ በእነሱ ላይ ያለውን ሥልጣን ለማሳየት አልሞከረም። ከዚህ ይልቅ በትሕትና አገልግሏቸዋል። (ዮሐ. 13:12-17) እንዲህ ብሏቸዋል፦ “[ከእኔ] ተማሩ፤ እኔ ገርና በልቤ ትሑት ነኝ፤ ለራሳችሁም እረፍት ታገኛላችሁ።” (ማቴ. 11:28-30) ኢየሱስ ገር እንደነበረ ልብ በሉ። አንድ ሰው ገር ነው ሲባል ደካማ ነው ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ራሱን ለመግዛት የሚያስችል ውስጣዊ ጥንካሬ አለው። የሚያበሳጭ ነገር ቢያጋጥመውም እንኳ ይረጋጋል፤ እንዲሁም ስሜቱን ይቆጣጠራል። w25.01 10 አን. 10-11
ሰኞ፣ ኅዳር 16
የምታደርገውን ሁሉ ለይሖዋ አደራ ስጥ።—ምሳሌ 16:3
ይህ ሥርዓት ወደ መጨረሻው እየተቃረበ ሲሄድ የኢኮኖሚው ሁኔታ እየተባባሰ እንደሚመጣ እንጠብቃለን። የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ ጦርነት፣ የተፈጥሮ አደጋ ወይም አዲስ የሚነሳ ወረርሽኝ ያልጠበቅነው ወጪ ሊያስከትልብን አሊያም ሥራችንን፣ ንብረታችንን ወይም ቤታችንን እንድናጣ ሊያደርገን ይችላል። ታዲያ በይሖዋ እጅ እንደምንተማመን የሚያሳዩ ውሳኔዎችን ለማድረግ ምን ይረዳናል? በዋነኝነት ልትወስደው የሚገባው ውጤታማ እርምጃ ያሳሰበህን ነገር ለይሖዋ መንገር ነው። ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ የሚያስችል ጥበብ እንዲሰጥህ ጠይቀው፤ ስላለህበት ሁኔታ ከልክ በላይ ‘እንዳትጨነቅ’ ልብህን እንዲያረጋጋው ለምነው። (ሉቃስ 12:29-31) ለኑሮ የሚያስፈልጉት መሠረታዊ ነገሮች ካሉህ በዚያ ረክተህ ለመኖር እንዲረዳህ ጠይቀው። (1 ጢሞ. 6:7, 8) የገንዘብ ችግር ላጋጠማቸው ሰዎች ጠቃሚ ምክር የያዙ ሐሳቦች ለማግኘት በጽሑፎቻችን ላይ ምርምር አድርግ። ብዙዎች የኢኮኖሚ ችግሮችን መወጣት ስለሚቻልበት መንገድ jw.org ላይ ያገኟቸው ሐሳቦች በጣም ጠቅመዋቸዋል። w25.03 28-29 አን. 10-11
ማክሰኞ፣ ኅዳር 17
አምላክ ማንንም ሰው ንጹሕ ያልሆነ ወይም ርኩስ ማለት እንደማይገባኝ ገልጦልኛል።—ሥራ 10:28
ያልተገረዙ አሕዛብ፣ የአምላክን ሕዝቦች ያቀፈው ጉባኤ ውስጥ እንዲጠቃለሉ የተወሰነው ጊዜ ደርሶ ነበር። መጀመሪያ ላይ ጉባኤውን ከተቀላቀሉት ከአሕዛብ ወገን የመጡ ክርስቲያኖች አንዱ ቆርኔሌዎስ ነው። ለእሱ እንዲሰብክ የተላከው ደግሞ ሐዋርያው ጴጥሮስ ነበር። አይሁዳውያን ከአሕዛብ ጋር መቀራረብ አይፈልጉም ነበር፤ በመሆኑም ይሖዋ ጴጥሮስን ከመላኩ በፊት አስቀድሞ ያዘጋጀው ለምን እንደሆነ መረዳት አይከብድም። ጴጥሮስ አምላክ ስለ ጉዳዩ ያለውን አመለካከት ሲረዳ የራሱን አመለካከት አስተካከለ። በመሆኑም ቆርኔሌዎስ መልእክት ሲልክበት ‘ምንም ሳያንገራግር’ ሄደ። (ሥራ 10:28, 29) ለቆርኔሌዎስና ለቤተሰቡ ሰበከ፤ እነሱም ተጠመቁ። (ሥራ 10:21-23, 34, 35, 44-48) ከዓመታት በኋላ ጴጥሮስ “የሐሳብ ስምምነት” እንዲኖራቸው የእምነት ባልንጀሮቹን አበረታቷል። (1 ጴጥ. 3:8 ግርጌ) እኛ የይሖዋ ሕዝቦች ይሖዋ በቃሉ አማካኝነት የገለጠልንን አስተሳሰቡን የምናንጸባርቅ ከሆነ የሐሳብ ስምምነት ሊኖረን ይችላል። w25.03 9-10 አን. 7-8
ረቡዕ፣ ኅዳር 18
በልዩ ልዩና እንግዳ በሆኑ ትምህርቶች አትወሰዱ።—ዕብ. 13:9
የዓለም አመለካከትና ዝንባሌ ፍጹም ከሆነው የአምላክ አመለካከት ከዕለት ወደ ዕለት እየራቀ ነው። (ምሳሌ 17:15) እንግዲያው ተቃዋሚዎች እኛን ተስፋ ለማስቆረጥ ወይም ከእውነት ለማራቅ የሚጠቀሙባቸውን የሐሰት ትምህርቶች ለይተን እንድናውቅና በእነሱ እንዳንወሰድ ራሳችንን ማስታጠቅ ይኖርብናል። ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ መንፈሳዊ ጉልምስና ለመድረስ እንዲጣጣሩ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች የሰጣቸውን ምክር ልብ ማለት ይኖርብናል። ይህም ስለ እውነት ጠለቅ ብሎ ማወቅን እንዲሁም የይሖዋን አስተሳሰብ ማዳበርን ይጨምራል። ይህ ሂደት ራሳችንን ወስነን ከተጠመቅን በኋላም የሚቀጥል ነው። እውነት ውስጥ የኖርንበት ዘመን ምንም ያህል ቢሆን ሁላችንም የአምላክን ቃል አዘውትረን ማንበብና ማጥናት ይኖርብናል። (መዝ. 1:2) ጥሩ የግል ጥናት ልማድ እምነታችንን ለማጠናከር ይረዳናል፤ ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ስለዚህ ባሕርይ ጎላ አድርጎ ገልጿል።—ዕብ. 11:1, 6፤ w24.09 10 አን. 7-8
ሐሙስ፣ ኅዳር 19
ወደ አምላክ ቅረቡ፤ እሱም ወደ እናንተ ይቀርባል።—ያዕ. 4:8
ይሖዋ እውን ከሆነልን ለእሱ ያለንን ታማኝነት መጠበቅ ቀላል ይሆንልናል። ከዮሴፍ ጋር በተያያዘ ይህ እውነት መሆኑ ታይቷል። ዮሴፍ የሥነ ምግባር ብልግና ላለመፈጸም ቆራጥ እርምጃ ወስዷል። አምላክ ለእሱ እውን ነበር፤ እሱን ማሳዘንም አልፈለገም። (ዘፍ. 39:9) ይሖዋ እውን እንዲሆንልን ከፈለግን ጊዜ መድበን ወደ እሱ መጸለይና ቃሉን ማጥናት ይኖርብናል። እንዲህ ካደረግን ከእሱ ጋር ያለን ወዳጅነት ይጠናከራል። እንደ ዮሴፍ ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ካለን እሱን የሚያሳዝን ምንም ነገር ማድረግ አንፈልግም። ይሖዋ ሕያው አምላክ እንደሆነ የሚረሱ ሰዎች በቀላሉ ከእሱ ሊርቁ ይችላሉ። እስራኤላውያን በምድረ በዳ በነበሩበት ጊዜ ምን እንዳጋጠማቸው እንመልከት። ይሖዋ መኖሩን ያውቁ ነበር፤ ሆኖም እሱ የሚያስፈልጋቸውን ነገር የሚያሟላላቸው መሆኑን መጠራጠር ጀመሩ። (ዘፀ. 17:2, 7) ከዚያ በኋላ በአምላክ ላይ ዓመፁ። የእነሱ ታሪክ የማስጠንቀቂያ ምሳሌ ይሆነናል፤ እነሱ የተከሉትን የዓመፀኝነት ጎዳና መከተል እንደማንፈልግ የተረጋገጠ ነው።—ዕብ. 3:12፤ w24.06 24 አን. 14-15
ዓርብ፣ ኅዳር 20
የይሖዋ ዓይኖች ጻድቃንን ይመለከታሉ፤ ጆሮዎቹም እርዳታ ለማግኘት የሚያሰሙትን ጩኸት ይሰማሉ።—መዝ. 34:15
የምንኖረው በመጨረሻዎቹ ቀናት መጨረሻ ላይ እንደመሆኑ መጠን የሚያስለቅሱ ነገሮች እየጨመሩ እንደሚሄዱ እንጠብቃለን። ይሖዋ እንባችንን ያያል፤ እንዲሁም ስናለቅስ ሲመለከት ስሜቱ በጥልቅ ይነካል። እንባችንን ፈጽሞ በቸልታ አያልፍም። ስለዚህ አስጨናቂ ሁኔታ ሲያጋጥመን የልባችንን አውጥተን ወደ ይሖዋ መጸለይ ይኖርብናል። በጉባኤ ውስጥ ካሉት አፍቃሪ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ራሳችንን አናግልል። በተጨማሪም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙት የሚያበረታቱ ሐሳቦች ማጽናኛ ማግኘታችንን እንቀጥል። በታማኝነት ከጸናን ይሖዋ እንደሚባርከን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ይህም ሐዘን ደርሶብን፣ ክህደት ተፈጽሞብን ወይም ተስፋ ቆርጠን ያነባነውን እንባ በሙሉ የሚያብስበት ጊዜ እንደሚመጣ የሚገልጸውን ተስፋ ይጨምራል። (ራእይ 21:4) ከዚያ በኋላ የምናነባው የደስታ እንባ ብቻ ይሆናል። w24.12 20 አን. 3፤ 24 አን. 19
ቅዳሜ፣ ኅዳር 21
“እናንተ ምሥክሮቼ ናችሁ” ይላል ይሖዋ።—ኢሳ. 43:12
ይሖዋ ምሥክሮቹ እንድንሆን ሾሞናል፤ እንዲሁም ደፋሮች እንድንሆን እንደሚረዳን ቃል ገብቶልናል። (ኢሳ. 43:10, 11) ይህን የሚያደርግባቸውን አራት መንገዶች እንመልከት። አንደኛ፣ ኢየሱስ በስብከቱ ሥራ በምንካፈልበት ጊዜ ሁሉ ከእኛ ጋር ነው። (ማቴ. 28:18-20) ሁለተኛ፣ ይሖዋ መላእክቱን እኛን እንዲያግዙን መድቧቸዋል። (ራእይ 14:6) ሦስተኛ፣ የተማርናቸውን ነገሮች እንድናስታውስ ይሖዋ ረዳት የሆነውን መንፈስ ቅዱስን ይሰጠናል። (ዮሐ. 14:25, 26) አራተኛ፣ ይሖዋ አብረውን የሚያገለግሉ ወንድሞችና እህቶች ሰጥቶናል። የይሖዋ እርዳታና አፍቃሪ የሆነው የወንድማማች ማኅበራችን ድጋፍ ስላለን በስብከቱ ሥራ ስኬታማ መሆን እንችላለን። ሆኖም በክልልህ ውስጥ ያሉትን አብዛኞቹን ሰዎች ቤታቸው ልታገኛቸው አለመቻልህ ተስፋ አስቆርጦህ ከሆነ ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘አብዛኞቹ ሰዎች በዚህ ሰዓት የት ሊገኙ ይችላሉ?’ (ሥራ 16:13) ‘ሥራ ሄደው ወይም ገበያ ወጥተው ይሆን?’ ሁኔታው እንደዚያ ከሆነ፣ በመንገድ ላይ ብታገለግል ተጨማሪ ሰዎችን ታገኝ ይሆን? w24.04 17 አን. 10-11
እሁድ፣ ኅዳር 22
አንድ ሰው የራሱን ቤተሰብ እንዴት እንደሚያስተዳድር ካላወቀ የአምላክን ጉባኤ እንዴት ሊንከባከብ ይችላል?—1 ጢሞ. 3:5
ባለትዳር ከሆንክና ሽማግሌ ለመሆን ብቃቱን ማሟላት የምትፈልግ ከሆነ ቤተሰብህ ያተረፈው ስም ብቃትህን ይነካዋል። በመሆኑም ‘የራስህን ቤተሰብ በተገቢው ሁኔታ ማስተዳደር’ ይኖርብሃል። አፍቃሪና ኃላፊነት የሚሰማው የቤተሰብ ራስ በመሆን ልትታወቅ ይገባል። ይህም በሁሉም የአምልኳችን ገጽታዎች ከቤተሰብህ ጋር መካፈልን ይጨምራል። አባት ከሆንክ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆችህ ‘ታዛዥና ቁም ነገረኛ ሊሆኑ’ ይገባል። (1 ጢሞ. 3:4) እነሱን በፍቅር ማስተማርና ማሠልጠን ይኖርብሃል። እርግጥ ነው፣ እንደ ማንኛውም ልጅ መሳቃቸውና መጫወታቸው አይቀርም። ሆኖም በደንብ አድርገህ ስላሠለጠንካቸው ታዛዥ፣ ሰው አክባሪና ጨዋ ይሆናሉ። ከዚህም ሌላ ልጆችህ ከይሖዋ ጋር ጥሩ ወዳጅነት እንዲመሠርቱ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች እንዲመሩ እንዲሁም እድገት አድርገው እንዲጠመቁ ለመርዳት አቅምህ የፈቀደውን ሁሉ ማድረግ አለብህ። w24.11 22 አን. 10-11
ሰኞ፣ ኅዳር 23
ሕይወቱን ለወዳጆቹ ሲል አሳልፎ ከሚሰጥ ሰው የበለጠ ፍቅር ያለው ማንም የለም።—ዮሐ. 15:13
በይሖዋ አገልግሎት ይበልጥ በተካፈልን መጠን የእሱን ድጋፍ ይበልጥ እናጣጥማለን፤ በውጤቱም በእሱ ላይ ያለን እምነት ይበልጥ ይጠናከራል። (1 ቆሮ. 3:9) ይሁንና ይሖዋ የምታከናውነውን ነገር ከሌሎች ጋር እንደማያወዳድር አስታውስ፤ እሱ የሚያየው ልብህን ነው። ለሰጠህ ውድ ስጦታ ማለትም ለቤዛው ያለህን ልባዊ አመስጋኝነት ሲመለከት ይደሰታል። (1 ሳሙ. 16:7፤ ማር. 12:41-44) ለኃጢአታችን ይቅርታ ማግኘት፣ ከይሖዋ ጋር ወዳጅነት መመሥረት እንዲሁም የዘላለም ሕይወት ተስፋ ማግኘት የቻልነው ቤዛው ስለተከፈለልን ብቻ ነው። ይሖዋ እነዚህን በረከቶች የምናገኝበትን አጋጣሚ በመክፈት ላሳየን ፍቅር ምንጊዜም አመስጋኝነታችንን እናሳይ። (1 ዮሐ. 4:19) በተጨማሪም ሰብዓዊ ሕይወቱን እስኪሰጠን ድረስ እጅግ ለወደደን ለኢየሱስ ያለንን አድናቆት እናሳይ። w25.01 31 አን. 16-18
ማክሰኞ፣ ኅዳር 24
ቀኑን [ሙሉ] ተጨነቅኩ።—መዝ. 73:14
የመዝሙር 73 ጸሐፊ ምን እንደተሰማው አስብ። ይህ መዝሙራዊ ሌሎች ጤናማና ባለጸጋ እንደሆኑ እንዲሁም ከውጥረት ነፃ የሆነ ሕይወት እንደሚመሩ ተሰምቶት ነበር። (መዝ. 73:3-5, 12) ያገኙትን ስኬት ሲመለከት ይሖዋን ለማገልገል ያደረገው ጥረት ምንም ዋጋ እንደሌለው ተሰማው። ይህ ተስፋ አስቆራጭ ሐሳብ ‘ቀኑን ሙሉ አስጨነቀው።’ (መዝ. 73:13, 14) ታዲያ ጭንቀቱን ማሸነፍ የቻለው እንዴት ነው? መዝሙራዊው ሰላማዊ ቦታ ወደሆነው ወደ ይሖዋ መቅደስ ሄደ። (መዝ. 73:16-18) እዚያም ተረጋግቶ ማሰብ ቻለ። የአንዳንድ ሰዎች ሕይወት የተደላደለ ቢመስልም እንኳ የወደፊቱ ሕይወታቸው አስተማማኝ እንዳልሆነ አስተዋለ። መንፈሳዊ ነገሮችን መከታተል ከሁሉ የተሻለ ውሳኔ እንደሆነ በመገንዘቡ የአእምሮ ሰላም አገኘ። በዚህም የተነሳ፣ ይሖዋን ማገልገሉን ለመቀጠል ያለው ቁርጠኝነት በድጋሚ ተቀጣጠለ።—መዝ. 73:23-28፤ w24.10 27 አን. 11-12
ረቡዕ፣ ኅዳር 25
ስምህ ይሖዋ የሆነው አንተ፣ አዎ፣ አንተ ብቻ በመላው ምድር ላይ ልዑል እንደሆንክ ሰዎች ይወቁ።—መዝ. 83:18
ይሖዋ ‘ምሥክሮቹ’ እንድንሆን መርጦናል። (ኢሳ. 43:10-12) ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ከበላይ አካሉ የተላከ አንድ ደብዳቤ እንዲህ የሚል ሐሳብ ይዞ ነበር፦ “ማንኛችንም ልናገኘው ከምንችለው ክብር ሁሉ እጅግ የላቀው የይሖዋ ምሥክር ተብለን መጠራታችን ነው።” እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? አንድ ምሳሌ እንመልከት። ፍርድ ቤት ቀርቦ አንተ ምን ዓይነት ሰው እንደሆንክ የሚመሠክርልህ ሰው ብትፈልግ የምታውቀውና የምታምነው እንዲሁም መልካም ስም በማትረፉ ተአማኒነት ያለው ምሥክርነት ሊሰጥ የሚችል ሰው እንደምትመርጥ የታወቀ ነው። ይሖዋ ምሥክሮቹ እንድንሆን የመረጠን መሆኑ በደንብ እንደሚያውቀን እንዲሁም እሱ ብቻ እውነተኛ አምላክ መሆኑን እንድንመሠክር እንደሚተማመንብን ያሳያል። የእሱ ምሥክር መሆናችን በጣም ስለሚያኮራን ስሙን ለማሳወቅ እንዲሁም ስለ እሱ የተነገሩትን በርካታ ውሸቶች ለማጋለጥ የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን በሙሉ እንጠቀምባቸዋለን። እንዲህ በማድረግ “የይሖዋ ምሥክሮች” የሚለውን የምንኮራበትን መጠሪያችንን በሚመጥን መንገድ እንመላለሳለን!—ሮም 10:13-15፤ w24.05 18 አን. 13
ሐሙስ፣ ኅዳር 26
እየተሠቃዩ የነበሩትን . . . ሁሉ ፈወሰ።—ማቴ. 8:16
ሌሎችን ማገልገል ለኢየሱስ ታላቅ ደስታ ሰጥቶታል። በአንድ ወቅት እጅግ ብዙ ሕዝብ በተሰበሰበ ጊዜ ኢየሱስ ሕዝቡን በማስተማር ብቻ አልተወሰነም። አካላዊ ፍላጎታቸውንም አሟልቶላቸዋል። በተአምራዊ መንገድ ምግቡን ካበዛ በኋላ ለሕዝቡ እንዲያከፋፍሉ ደቀ መዛሙርቱን አዘዛቸው። (ማር. 6:41) በዚህ መንገድ ደቀ መዛሙርቱን ሌሎችን ማገልገል የሚችሉት እንዴት እንደሆነ አስተምሯቸዋል። በተጨማሪም ተግባራዊ አገልግሎቶችም አስፈላጊ እንደሆኑ አሳይቷቸዋል። ሐዋርያቱ ‘ሁሉም በልተው እስኪጠግቡ’ ድረስ ከኢየሱስ ጋር በዚህ ምግብ የማከፋፈል ሥራ በመካፈላቸው ምን ያህል ተደስተው ሊሆን እንደሚችል ለማሰብ ሞክር። (ማር. 6:42) ደግሞም ኢየሱስ ከራሱ ፍላጎት ይልቅ የሌሎችን ፍላጎት ያስቀደመው በዚህ ወቅት ብቻ አይደለም። በምድራዊ ሕይወቱ በሙሉ ሰዎችን ያገለግል ነበር። (ማቴ. 4:23) ኢየሱስ ሌሎችን በማስተማር እንዲሁም እነሱን ለመንከባከብ ሲል በትሕትና በመሥራት ደስታ አግኝቷል። w24.11 16 አን. 10-11
ዓርብ፣ ኅዳር 27
በመጨረሻዎቹ ቀናት ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን [ይመጣል]።—2 ጢሞ. 3:1
በእነዚህ ‘የመጨረሻ ቀናት’ ያለው ሁኔታ እየተባባሰ ሲሄድ አንዳችን ሌላውን ለመርዳት የሚያስችሉ ተጨማሪ አጋጣሚዎችን እንደምናገኝ ጥርጥር የለውም። ከዚህም በተጨማሪ ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ስሜታዊና መንፈሳዊ ከለላ ልንሆንላቸው እንችላለን። እንዲህ ማድረግ የምንችልበት አንደኛው መንገድ ወደ ስብሰባ ሲመጡ እነሱን ማነጋገርና ማጽናናት ነው። ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በስብሰባዎች ላይ ሲገኙ እንደሚወደዱ እንዲሰማቸው፣ መንፈሳቸው እንዲታደስና እንዲረጋጉ የምንችለውን ሁሉ ማድረግ እንፈልጋለን። የጉባኤ ሽማግሌዎች ቃል በቃልም ሆነ በምሳሌያዊ ሁኔታ ማዕበል ላጋጠማቸው ወንድሞችና እህቶች መጠጊያ ሊሆኑ ይችላሉ። የተፈጥሮ አደጋና ድንገተኛ ሕመም በሚያጋጥምበት ጊዜ ሽማግሌዎች ግንባር ቀደም ሆነው ተግባራዊ እርዳታ ይሰጣሉ። መንፈሳዊ እርዳታም ያበረክታሉ። አንድ ሽማግሌ ደግ፣ የሌሎችን ስሜት የሚረዳና ለመስማት ፈቃደኛ በመሆኑ የሚታወቅ ከሆነ ወንድሞችና እህቶች እሱን ቀርበው ማነጋገር ቀላል ይሆንላቸዋል። አንድ ሽማግሌ እንዲህ ያሉ ባሕርያትን የሚያንጸባርቅ ከሆነ ወንድሞችና እህቶች እንደሚያስብላቸው ስለሚሰማቸው እሱ የሚሰጣቸውን ማንኛውንም ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ተግባራዊ ማድረግ ቀላል ይሆንላቸዋል።—1 ተሰ. 2:7, 8, 11፤ w24.06 29 አን. 12-13
ቅዳሜ፣ ኅዳር 28
ለገዛ ልጁ እንኳ [አልሳሳም]።—ሮም 8:32
አምላክ ሁሉን ቻይ ስለሆነ ስሜት የለውም ብለን ልናስብ አይገባም። በእሱ አምሳል የተፈጠሩት ሰዎች ስሜት ካላቸው እሱም ስሜት አለው ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ ‘ስሜቱ እንደተጎዳ’ እና ‘እጅግ እንዳዘነ’ ይናገራል። (መዝ. 78:40, 41) ይሖዋ ልጁ ዓመፀኛ በሆኑ ሰዎች እጅ ተሠቃይቶ ሲገደል ሲመለከት ምንኛ አዝኖ ይሆን! ቤዛው የቅርብ ዘመዶቻችንንና ጓደኞቻችንን ጨምሮ የይሖዋን ያህል የሚወደን ማንም ሰው እንደሌለ ያስገነዝበናል። (ሮም 8:32, 38, 39) ይሖዋ እኛ ራሳችንን ከምንወደውም ይበልጥ ይወደናል። ለዘላለም መኖር ትፈልጋለህ? ከአንተ ይበልጥ ይሖዋ ይህን ይመኝልሃል። ኃጢአትህ ይቅር እንዲባልልህ ትፈልጋለህ? አንተ ኃጢአትህ ይቅር እንዲባል ከምትፈልገው ይበልጥ ይሖዋ ይቅር ሊልህ ይፈልጋል። ይሖዋ ከእኛ የሚፈልገው እምነት በማሳየትና ታዛዥ በመሆን እሱ የሰጠንን የጸጋ ስጦታ እንድንቀበል ብቻ ነው። በእርግጥም ቤዛው የአምላክን ጥልቅ ፍቅር የሚያሳይ ውድ ስጦታ ነው።—መክ. 3:11፤ w25.01 22 አን. 8-9
እሁድ፣ ኅዳር 29
በጌታ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ነገር ምን እንደሆነ ምንጊዜም መርምራችሁ አረጋግጡ።—ኤፌ. 5:10
አንዳንድ ውሳኔዎች ከስሜት ሕዋሶቻችን ባገኘነው መረጃ ላይ ተመሥርተው የሚደረጉ ናቸው። ሆኖም ከስሜት ሕዋሶቻችን የምናገኘው መረጃ የተሳሳተ የሚሆንበት ጊዜ አለ። የምናገኘው መረጃ የተሳሳተ ባይሆንም እንኳ በማየት ብቻ የምንመላለስ ከሆነ ከአምላክ ፈቃድ ወይም ምክር ጋር የሚጋጭ ውሳኔ ልናደርግ እንችላለን። (መክ. 11:9፤ ማቴ. 24:37-39) በእምነት የምንመላለስ ከሆነ ግን የምናደርገው ውሳኔ “በጌታ ዘንድ ተቀባይነት ያለው” ይሆናል። የአምላክን ምክር መከተል ውስጣዊ ሰላምና እውነተኛ ደስታ ያስገኝልናል። (መዝ. 16:8, 9፤ ኢሳ. 48:17, 18) እስከ መጨረሻው በእምነት መመላለሳችንን ከቀጠልን ደግሞ የዘላለም ሕይወት እናገኛለን። (2 ቆሮ. 4:18) የምንመላለሰው በእምነት ይሁን በማየት የምናውቀው እንዴት ነው? ይህን ለማወቅ የሚረዳን ዋናው ቁም ነገር ‘ውሳኔያችንን የሚመራው ምንድን ነው?’ የሚለው ነው። የምንመራው በምናየው ነገር ብቻ ነው? ወይስ በይሖዋ ላይ ባለን እምነት እንዲሁም ከእሱ በምናገኘው ምክር? w25.03 20-21 አን. 3-4
ሰኞ፣ ኅዳር 30
እርስ በርሳችሁ ሰላማዊ ግንኙነት ይኑራችሁ።—1 ተሰ. 5:13
መንፈሳዊው ገነት ለሌሎች የሚስብ እንዲሆን በማድረግ ረገድ እያንዳንዳችን አስፈላጊ ሚና እንጫወታለን። ይህን ኃላፊነታችንን መወጣት የምንችለው ይሖዋን የምንመስል ከሆነ ነው። ይሖዋ ሰዎችን ያለፈቃዳቸው ወደ ድርጅቱ እንዲገቡ አያስገድዳቸውም። ከዚህ ይልቅ ወደ ራሱ ‘የሚስባቸው’ በፍቅር ነው። (ዮሐ. 6:44፤ ኤር. 31:3) ስለ ይሖዋ ፍቅርና ስለ ማራኪ ባሕርያቱ የተማሩ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ወደ እሱ መሳባቸው አይቀርም። እኛስ መልካም ባሕርያትና ጥሩ ምግባር በማሳየት ሌሎችን ወደ መንፈሳዊው ገነት መሳብ የምንችለው እንዴት ነው? አንዱ መንገድ የእምነት አጋሮቻችንን በፍቅርና በደግነት በመያዝ ነው። ጳውሎስ በጥንቱ የቆሮንቶስ ጉባኤ ላይ የተገኙ አማኝ ያልሆኑ ሰዎች “አምላክ በእርግጥ በመካከላችሁ ነው” የሚል መደምደሚያ ላይ ሊደርሱ እንደሚችሉ ተናግሮ ነበር። ዛሬም በስብሰባዎቻችን ላይ የሚገኙ አዳዲስ ሰዎች ተመሳሳይ መደምደሚያ ላይ እንዲደርሱ እንፈልጋለን። (1 ቆሮ. 14:24, 25፤ ዘካ. 8:23) ስለሆነም በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ያለውን ምክር ተግባራዊ ማድረጋችንን መቀጠል አለብን። w24.04 23-24 አን. 16-17