ነሐሴ
ቅዳሜ፣ ነሐሴ 1
ከዓለም መጀመሪያ አንስቶ እስካሁን ድረስ ሆኖ የማያውቅ ዳግመኛም የማይሆን ታላቅ መከራ ይከሰታል።—ማቴ. 24:21
በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎች ለማስጠንቀቂያችን ምላሽ በመስጠት ከአሁኑ በንጹሕ አምልኮ አብረውን መካፈል እንዲጀምሩ እንጸልያለን። ይሁንና የምንወዳቸውን ቤተሰቦቻችንን ጨምሮ በአሁኑ ወቅት ይህን ማስጠንቀቂያ ልብ ስለማይሉ ሰዎችስ ምን ማለት ይቻላል? ባለፈው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው፣ ይሖዋ የታላቂቱ ባቢሎንን ጥፋት ሲያዩ አቋማቸውን የሚያስተካክሉ ሰዎችን ለማዳን ሊወስን ይችላል። ሁኔታው እንደዚያ ከሆነ፣ ማስጠንቀቂያውን ማሰማታችንን መቀጠላችን ይበልጥ አንገብጋቢ ነው ማለት ነው። አሁን የምንነግራቸው ነገር ወደፊት የሚያስታውሱት ነገር እንዲኖር ያደርጋል። (ከሕዝቅኤል 33:33 ጋር አወዳድር።) ምናልባትም ከእኛ የሰሙትን ማስጠንቀቂያ አስታውሰው ጊዜው ከማለፉ በፊት በንጹሕ አምልኮ አብረውን ለመካፈል ይነሳሱ ይሆናል። በፊልጵስዩስ የነበረው የእስር ቤት ጠባቂ አመለካከቱን የቀየረው “ከባድ የምድር ነውጥ” ከተከሰተ በኋላ እንደነበረ ሁሉ አሁን ምላሽ የማይሰጡ አንዳንድ ሰዎች ምድርን የሚያናውጥ ክንውን ከሆነው ከታላቂቱ ባቢሎን ጥፋት በኋላ አመለካከታቸውን ይቀይሩ ይሆናል።—ሥራ 16:25-34፤ w24.05 17 አን. 9-10
እሁድ፣ ነሐሴ 2
ክርስቶስ የሕግ ፍጻሜ ነው።—ሮም 10:4
ሐዋርያው ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች ከጻፈላቸው ሐሳብ ጠቃሚ ትምህርት እናገኛለን። አንዳንዶቹ መንፈሳዊ እድገት ማድረጋቸውን አቁመው ነበር። እንዲያውም “ጠንካራ [መንፈሳዊ] ምግብ ከመመገብ ይልቅ እንደገና ወተት መፈለግ” ጀምረው ነበር። (ዕብ. 5:12) በጉባኤው አማካኝነት ደረጃ በደረጃ እየተገለጠ ካለው እውነት ጋር እኩል መሄድ ተስኗቸዋል። (ምሳሌ 4:18) ለምሳሌ ከ30 ዓመት ገደማ በፊት ሕጉ በክርስቶስ መሥዋዕት አማካኝነት የተሻረ ቢሆንም በርካታ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች አሁንም የሙሴን ሕግ ይከተሉ ነበር። (ቲቶ 1:10) ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት ለዕብራውያን ክርስቲያኖች የጻፈውን ደብዳቤ ያነበበ ማንኛውም ሰው ይህ መጽሐፍ ጠንካራ መንፈሳዊ ምግብ እንደያዘ ማስተዋሉ አይቀርም። ይህ መልእክት እነዚያ ክርስቲያኖች በክርስትና ውስጥ ያለው የአምልኮ ሥርዓት የላቀ መሆኑን እንዲገነዘቡ እንዲሁም በድፍረት መስበካቸውን እንዲቀጥሉ ረድቷቸዋል።—ዕብ. 10:19-23፤ w24.04 6 አን. 15
ሰኞ፣ ነሐሴ 3
ጻድቃንም ሆኑ ጻድቃን ያልሆኑ ሰዎች ከሞት [ይነሳሉ]።—ሥራ 24:15
አዳምና ሔዋን ከሰይጣን ጋር ተባብረው በይሖዋ አምላክ ላይ ካመፁበት ጊዜ አንስቶ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ሞተዋል። እነዚህ ሁሉ ሰዎች ወደፊት ምን ይጠብቃቸዋል? የተወሰነ ቁጥር ያላቸው ታማኝ የክርስቶስ ተከታዮች ማለትም 144,000 ሰዎች ከሞት ተነስተው በሰማይ ላይ የማይሞት ሕይወት ያገኛሉ። (ራእይ 14:1) ይሖዋን የሚወዱ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ታማኝ ወንዶችና ሴቶች ደግሞ ትንሣኤ ከሚያገኙት “ጻድቃን” መካከል ይካተታሉ፤ በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛትና በመጨረሻው ፈተና ወቅት ጻድቅ ሆነው ከቀጠሉ በምድር ላይ ለዘላለም ይኖራሉ። (ዳን. 12:13፤ ዕብ. 12:1) በተጨማሪም ይሖዋን አገልግለው የማያውቁ፣ አልፎ ተርፎም “ክፉ የሠሩ” ሰዎችን ጨምሮ “ጻድቃን ያልሆኑ ሰዎች” በሺህ ዓመቱ ግዛት ወቅት አካሄዳቸውን የማስተካከልና ታማኝ የመሆን አጋጣሚ ይሰጣቸዋል። (ዮሐ. 5:29፤ ሉቃስ 23:42, 43) ይሁንና አንዳንድ ሰዎች በጣም ክፉ በመሆናቸው የተነሳ ይሖዋ እነዚህ ሰዎች ትንሣኤ እንደማያገኙ ወስኗል።—ሉቃስ 12:4, 5፤ w24.05 2 አን. 3፤ 5 አን. 15፤ 6 አን. 17
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 4
ይህ ሕዝብ [በከንፈሩ] ያከብረኛል፤ ልቡ ግን ከእኔ እጅግ የራቀ ነው።—ኢሳ. 29:13
አንድ ሰው ይሖዋ እንዲቀበለው የሚፈልግ ከሆነ ‘በልቡ እውነትን የሚናገር’ መሆን አለበት። (መዝ. 15:2) ይህ ሲባል አለመዋሸት ማለት ብቻ አይደለም። ይሖዋ በሁሉም ነገር ሐቀኞች እንድንሆን ይፈልጋል። (ዕብ. 13:18) ይህ በጣም አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም “ይሖዋ ተንኮለኛን ሰው ይጸየፋል . . . ከቅኖች ጋር ግን የጠበቀ ወዳጅነት አለው።” (ምሳሌ 3:32) ‘በልባቸው እውነትን የሚናገሩ’ ሰዎች በድብቅ የአምላክን ሕግጋት እየጣሱ በሰዎች ፊት ታዛዥ ለመምሰል አይሞክሩም። ከማታለል ይቆጠባሉ። አታላይ ሰው አንዳንድ የይሖዋ መመሪያዎች ጥበብ ያዘሉ መሆናቸውን መጠራጠር ሊጀምር ይችላል። (ያዕ. 1:5-8) ያን ያህል አስፈላጊ እንዳልሆኑ በሚሰሙት ጉዳዮች ይሖዋን ላይታዘዝ ይችላል። አለመታዘዙ ምንም መዘዝ እንዳላስከተለበት ከተሰማው ደግሞ የይሖዋን ሕግጋት የባሰ ለመጣስ ሊደፋፈር ይችላል፤ አምልኮቱም የግብዝነት ይሆንበታል። (መክ. 8:11) እኛ ግን በሁሉም ነገር ሐቀኞች መሆን እንፈልጋለን። w24.06 10 አን. 7-8
ረቡዕ፣ ነሐሴ 5
ወገባችሁን በእውነት ቀበቶ ታጥቃችሁ . . . ጸንታችሁ ቁሙ።—ኤፌ. 6:14
የይሖዋ ሕዝቦች በአምላክ ቃል ውስጥ ላለው እውነት ፍቅር አላቸው። እምነታችን የተገነባው በእሱ ላይ ነው። (ሮም 10:17) ይሖዋ የክርስቲያን ጉባኤን “የእውነት ዓምድና ድጋፍ” አድርጎ እንዳቋቋመው እርግጠኞች ነን። (1 ጢሞ. 3:15) ሰይጣን በመጽሐፍ ቅዱስና የአምላክ ድርጅት በሚሰጠን መመሪያ ላይ እምነት እንድናጣ ለማድረግ የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም። (ኤፌ. 4:14) በቅርቡ ዲያብሎስ ሁሉንም ብሔራት አታሎ ይሖዋን እንዲቃወሙ ለማድረግ ኃይለኛ ፕሮፓጋንዳ ይጠቀማል። (ራእይ 16:13, 14) ሰይጣን የይሖዋን ሕዝቦች ለማሳት የሚያደርገውን ጥረት እንደሚያፋፍምም እንጠብቃለን። (ራእይ 12:9) ስለዚህም እውነትና ውሸት የሆነውን ነገር መለየትና ለእውነት መታዘዝ እንድንችል ራሳችንን ማሠልጠናችን አስፈላጊ ነው። (ሮም 6:17፤ 1 ጴጥ. 1:22) ከታላቁ መከራ መትረፋችን የተመካው በዚህ ላይ ነው! w24.07 8 አን. 1-3
ሐሙስ፣ ነሐሴ 6
እኔ ዛሬ የማዝህ ይህ ትእዛዝ ለአንተ ያን ያህል ከባድ አይደለም፤ ከአንተም የራቀ አይደለም።—ዘዳ. 30:11
ይሖዋ እስራኤላውያንን በብሔር ደረጃ ባዋቀረበት ወቅት ከእነሱ ጋር ቃል ኪዳን ገብቷል። የሰጣቸውን ሕጎች ካከበሩ እንደሚጠብቃቸው እንዲሁም እንደሚባርካቸው ቃል ገብቶላቸዋል። ይሁንና ሌሎች አማልክትን በማምለክ ወይም በሌላ መንገድ በእሱ ላይ ካመፁ በረከቱን ይወስድባቸዋል፤ እነሱም ለመከራ ይዳረጋሉ። ሆኖም ከዚያ በኋላም እንኳ የአምላክን ሞገስ መልሰው ማግኘት ይችሉ ነበር። ‘ወደ አምላካቸው ወደ ይሖዋ መመለስና ቃሉን መስማት’ ይችላሉ። (ዘዳ. 30:1-3, 17-20) በሌላ አባባል፣ ንስሐ መግባት ይችላሉ። እንዲህ ካደረጉ ይሖዋ ወደ እነሱ ይቀርባል፤ እንዲሁም በድጋሚ በረከቱን ያፈስላቸዋል። የይሖዋ ሕዝቦች በተደጋጋሚ ዓምፀውበታል። በዚህም የተነሳ ለመከራ ተዳርገዋል። ይሁንና ይሖዋ ዓመፀኛ በሆኑት ሕዝቦቹ ላይ ተስፋ አልቆረጠባቸውም። በተደጋጋሚ ወደ እነሱ ነቢያትን በመላክ ንስሐ እንዲገቡና ወደ እሱ እንዲመለሱ ያበረታታቸው ነበር።—2 ነገ. 17:13, 14፤ w24.08 9 አን. 4-5
ዓርብ፣ ነሐሴ 7
በኢየሩሳሌም በሚገኘው ጉባኤ ላይ ከባድ ስደት ተነሳ።—ሥራ 8:1
በኢየሩሳሌምና በይሁዳ የሚኖሩ ዕብራውያን ክርስቲያኖች ኢየሱስ ከሞተ በኋላ ባሉት ዓመታት ብዙ ችግሮች አጋጥመዋቸዋል። የክርስቲያን ጉባኤ ከተቋቋመ ብዙም ሳይቆይ በክርስቲያኖች ላይ ከባድ ስደት ተነሳ። ከ20 ዓመታት ገደማ በኋላ ደግሞ የክርስቶስ ተከታዮች ቀደም ሲል በተከሰተው ረሃብ የተነሳ ሳይሆን አይቀርም ለአስከፊ ድህነት ተዳረጉ። (ሥራ 11:27-30) ይሁንና በ61 ዓ.ም. ገደማ ክርስቲያኖች አንጻራዊ ሰላም አገኙ። በዚያ ወቅት ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት ደብዳቤ ጻፈላቸው። ይህ ደብዳቤ በጣም ወቅታዊ ነበር። ለዕብራውያን የተላከው ደብዳቤ ወቅታዊ ነበር የምንለው ክርስቲያኖች በወቅቱ ያገኙት ሰላም ስላልዘለቀ ነው። ጳውሎስ በቅርቡ የሚጠብቃቸውን መከራ በጽናት እንዲቋቋሙ የሚረዳ ተግባራዊ ምክር ሰጥቷቸዋል። w24.09 8 አን. 1-2
ቅዳሜ፣ ነሐሴ 8
የብርታት ምንጭ ሆነውልኛል።—ቆላ. 4:11
መከራ ሲደርስብን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የይሖዋ ፍቅር መገለጫዎች ናቸው። የእምነት አጋሮቻችን በጥሞና በማዳመጥ ወይም አብረውን በመሆን ሊያጽናኑን ይችላሉ። የሚያበረታታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ሊያነቡልን ወይም አብረውን ሊጸልዩ ይችላሉ። (ሮም 15:4) አንዳንድ ጊዜ ደግሞ አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት የይሖዋን አስተሳሰብ እንድናስታውስ በማድረግ ሚዛናችንን እንድንጠብቅ ሊረዱን ይችላሉ። የእምነት አጋሮቻችን ተግባራዊ እርዳታ ሊሰጡንም ይችላሉ፤ ለምሳሌ በተጨነቅንበት ወቅት ምግብ ያመጡልን ይሆናል። ከሌሎች እርዳታ ማግኘት ከፈለግን እርዳታቸውን መጠየቅ ሊያስፈልገን ይችላል። (ምሳሌ 17:17) ምን እንደሚሰማን አሊያም ምን እንደሚያስፈልገን ላያውቁ ይችላሉ። (ምሳሌ 14:10) ስለዚህ የሚሰማህን ነገር ለጎለመሱ ወዳጆችህ ለመናገር ፈቃደኛ ሁን። በምን መንገድ ሊረዱህ እንደሚችሉ ንገራቸው። የምትቀርባቸውን አንድ ወይም ሁለት ሽማግሌዎች ማነጋገር ትችላለህ። አንዳንድ እህቶች ለጎለመሰች እህት ስሜታቸውን አውጥተው መናገራቸው አጽናንቷቸዋል። w24.10 10 አን. 15-16
እሁድ፣ ነሐሴ 9
ወልድን የሚያውቅና በእሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት [ይኖረዋል]።—ዮሐ. 6:40
ብዙ ሰዎች ጤናቸውን ለመጠበቅና ረጅም ዕድሜ ለመኖር ስለሚፈልጉ በሚበሉት ነገር ረገድ ይጠነቀቃሉ፤ እንዲሁም አዘውትረው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያደርጋሉ። ቢሆንም ግን ለዘላለም እንኖራለን ብለው አይጠብቁም። ምክንያቱም ለዘላለም መኖር የሚቻል ነገር እንደሆነ አይሰማቸውም፤ እንዲሁም ከእርጅና ጋር ተያይዘው ከሚመጡት ችግሮች አንጻር ለዘላለም ለመኖር ላይመኙ ይችላሉ። ኢየሱስ ግን በዮሐንስ 3:16 እና 5:24 ላይ “የዘላለም ሕይወት” ማግኘት የሚቻልና አስደሳች ነገር እንደሆነ ተናግሯል። ኢየሱስ በአንድ ወቅት ተአምራዊ በሆነ መንገድ ዓሣና ዳቦ በማቅረብ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን መግቧል። ይህ በጣም አስገራሚ ቢሆንም ኢየሱስ በማግስቱ የተናገረው ነገር ይበልጥ አስደናቂ ነው። በገሊላ ባሕር አቅራቢያ ወደምትገኘው ወደ ቅፍርናሆም ተከትሎት ለመጣው ሕዝብ፣ ሰዎች ከሞት መነሳት እንዲሁም ለዘላለም መኖር እንደሚችሉ ተናግሯል። (ዮሐ. 6:39, 40) ኢየሱስ የተናገረው ነገር በሞት ያንቀላፉ ብዙዎች ከሞት እንደሚነሱ እንዲሁም አንተም ሆንክ ወዳጅ ዘመዶችህ አንድ ላይ ለዘላለም መኖር እንደምትችሉ ያሳያል። w24.12 8 አን. 1-2
ሰኞ፣ ነሐሴ 10
እናንተ ባሎች . . . ከእናንተ ይበልጥ እንደ ተሰባሪ ዕቃ የሆኑትን ሴቶችን አክብሯቸው።—1 ጴጥ. 3:7
የዓለም የጤና ድርጅት በቅርቡ ያወጣው ሪፖርት እንደሚናገረው፣ ብዙ ባሎች በሚስቶቻቸው ላይ አካላዊ ጥቃት ይሰነዝራሉ፤ የሚያቃልል ንግግር ይናገራሉ፤ እንዲሁም ስሜት የሚጎዳ ነገር ያደርጋሉ። እንዲህ ያለው ባል በሌሎች ሰዎች ፊት ሲሆን ሚስቱን በአክብሮት ሊይዛት ይችላል፤ ቤት ውስጥ ግን ይበድላታል። አንዳንድ ባሎች ሚስታቸውን አክብሮት በጎደለው መንገድ የሚይዙት ለምን ሊሆን ይችላል? ግልፍተኛ የሆነ አባት ያሳደጋቸው በመሆኑ የተነሳ ሚስትን መበደል ምንም ችግር እንደሌለው ሊሰማቸው ይችላል። ሌሎች ደግሞ ያደጉበት ባሕል “እውነተኛ ወንድ” የበላይነቱን ለማሳየት ኃይል መጠቀም እንዳለበት እንዲያስቡ አድርጓቸው ሊሆን ይችላል። ሌሎች ወንዶች ቁጣቸውን ጨምሮ ስሜታቸውን መቆጣጠር እንዳለባቸው አልተማሩም። አንዳንድ ወንዶች ደግሞ አዘውትረው ፖርኖግራፊ በመመልከታቸው የተነሳ ለሴቶችም ሆነ ለፆታ ግንኙነት የተዛባ አመለካከት አዳብረዋል። ከዚህም በተጨማሪ፣ አንዳንድ ሪፖርቶች የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሁኔታውን እንዳባባሰው ይናገራሉ። ምክንያቱ ምንም ሆነ ምን፣ ባል ሚስቱን አክብሮት በጎደለው መንገድ መያዙ ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም። w25.01 8 አን. 2-3
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 11
ክርስቶስ በሥጋ መከራ ስለተቀበለ እናንተም ይህንኑ አስተሳሰብ ለማንጸባረቅ ዝግጁ ሁኑ።—1 ጴጥ. 4:1
“አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህ፣ በሙሉ ኃይልህና በሙሉ አእምሮህ ውደድ።” ኢየሱስ በሙሴ ሕግ ውስጥ ካሉ ትእዛዛት ሁሉ የሚበልጠው ይህ እንደሆነ አረጋግጧል። (ሉቃስ 10:27) ከዚህ ማየት እንደምንችለው ይሖዋን መውደድ ልባችንን ይኸውም ዝንባሌዎቻችንን፣ ምኞቶቻችንን እና ስሜቶቻችንን ያካትታል። ከዚህም ሌላ በሙሉ ነፍሳችን ለእሱ ማደርን እንዲሁም በሙሉ ኃይላችን ማለትም ጉልበታችን እሱን ማገልገልን ይጨምራል። ይሁንና ይሖዋን መውደድ አእምሯችንን ይኸውም የምናስብበትን መንገድም ያካትታል። እርግጥ ነው፣ መቼም ቢሆን የይሖዋን አስተሳሰብ ሙሉ በሙሉ መረዳት አንችልም። ይሁንና ‘የክርስቶስን አስተሳሰብ’ በማጥናት ስለ አምላክ አስተሳሰብ ያለንን ግንዛቤ ማሳደግ እንችላለን፤ ምክንያቱም ኢየሱስ የአባቱን አስተሳሰብ ፍጹም በሆነ መንገድ አንጸባርቋል።—1 ቆሮ. 2:16፤ w25.03 8 አን. 1
ረቡዕ፣ ነሐሴ 12
በተትረፈረፈ ጸጋው መሠረት በልጁ ደም አማካኝነት ቤዛውን በመክፈሉ ነፃ ወጥተናል፤ አዎ፣ ለበደላችን ይቅርታ አግኝተናል።—ኤፌ. 1:7
ኢየሱስ የመጀመሪያው ሰው አዳም ኃጢአት ከመሥራቱ በፊት እንደነበረው ፍጹም ሰው ነበር። (1 ቆሮ. 15:45) በመሆኑም የኢየሱስ ሞት የአዳምን ኃጢአት ማስተሰረይ ማለትም አዳም ያጣውን ነገር መተካት ይችላል። (ሮም 5:19) በዚህም የተነሳ ኢየሱስ “የኋለኛው አዳም” ተብሎ ሊጠራ ችሏል። ሌላ ፍጹም ሰው መጥቶ አዳም ላጣው ነገር ዋጋ መክፈል አያስፈልገውም። ኢየሱስ “ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ” ሞቷል። (ዕብ. 7:27፤ 10:12) ታዲያ በስርየትና በቤዛው መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው? ስርየት፣ አምላክ በእሱና በሰው ልጆች መካከል ያለውን ዝምድና ለማደስ የወሰደውን እርምጃ ያመለክታል። ቤዛው ደግሞ ኃጢአተኛ የሆኑ የሰው ልጆች ስርየት እንዲያገኙ የተከፈለውን ዋጋ ያመለክታል። ይህ ዋጋ ለእኛ ሲባል የፈሰሰው የኢየሱስ ውድ ደም ነው።—ዕብ. 9:14፤ w25.02 5 አን. 12-13
ሐሙስ፣ ነሐሴ 13
አምላክ ታማኝ ነው፤ ልትሸከሙት ከምትችሉት በላይ ፈተና እንዲደርስባችሁ አይፈቅድም፤ ከዚህ ይልቅ ፈተናውን በጽናት መቋቋም እንድትችሉ ፈተና ሲደርስባችሁ መውጫ መንገዱን ያዘጋጅላችኋል።—1 ቆሮ. 10:13
ይሖዋ ሕያው አምላክ እንደሆነ ማስታወሳችን ለሚያጋጥሙን ፈተናዎች ትክክለኛ አመለካከት እንዲኖረን ይረዳናል። እንዴት? ከሚያጋጥሙን ፈተናዎች በስተ ጀርባ በይሖዋና በሰይጣን መካከል የተነሳ ትልቅ ጉዳይ እንዳለ እናስታውሳለን። ዲያብሎስ ችግር ሲያጋጥመን ይሖዋን እንደምንተው ተናግሯል። (ኢዮብ 1:10, 11፤ ምሳሌ 27:11) ሆኖም ያጋጠሙንን ፈተናዎች በተሳካ ሁኔታ ስንቋቋም ለይሖዋ ያለንን ፍቅር እናሳያለን፤ ዲያብሎስ ውሸታም እንደሆነም እናረጋግጣለን። የባለሥልጣናት ተቃውሞ፣ የኢኮኖሚ ችግር ወይም በአገልግሎት ላይ የምታገኛቸው ሰዎች የሚሰጡት አሉታዊ ምላሽ ከባድ ፈተና ሆኖብሃል? ወይም ሌላ ዓይነት ፈተና እየተጋፈጥክ ነው? ከሆነ፣ ያጋጠመህ ሁኔታ የይሖዋን ልብ ደስ ለማሰኘት የሚያስችል አጋጣሚ እንደሚሰጥህ አስታውስ። በተጨማሪም እሱ ልትሸከመው ከምትችለው በላይ ፈተና እንዲደርስብህ እንደማይፈቅድ አትርሳ። ለመጽናት የሚያስችል ብርታት ይሰጥሃል። w24.06 22 አን. 9
ዓርብ፣ ነሐሴ 14
እያንዳንዱ ሰው በራሱ ምኞት ሲማረክና ሲታለል ይፈተናል።—ያዕ. 1:14
አንተ በቀላሉ የምትፈተነው በየትኞቹ አቅጣጫዎች እንደሆነ ታውቃለህ? ድክመቶቻችንን ችላ በማለት ወይም በመንፈሳዊ ጠንካራ ስለሆንን ኃጢአት ልንፈጽም እንደማንችል በማሰብ ራሳችንን ማታለላችን አይጠቅመንም። (1 ዮሐ. 1:8) ደግሞም ጳውሎስ እንደተናገረው ‘መንፈሳዊ ብቃት ያላቸው’ ሰዎችም እንኳ ካልተጠነቀቁ ለፈተና እጅ ሊሰጡ ይችላሉ። (ገላ. 6:1) ራሳችንን በሐቀኝነት በመመርመር ጠንካራ ያልሆንባቸውን አቅጣጫዎች አምነን መቀበል ይኖርብናል። (2 ቆሮ. 13:5) ለፈተና ተጋላጭ የሆንባቸውን አቅጣጫዎች ለይተን ካወቅን በኋላ ምን ማድረግ ይኖርብናል? የመከላከል አቅማችንን ማጠናከር ይኖርብናል! ለምሳሌ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የአንዲት ከተማ ቅጥር ይበልጥ ለጥቃት ተጋላጭ የሚሆነው በሮቹ ላይ ነበር። በመሆኑም ከየትኛውም የቅጥሩ ክፍል ይበልጥ ብዙ ጠባቂዎች የሚመደቡት በሮቹ ላይ ነው። እኛም በተመሳሳይ ደካማ ለሆንባቸው አቅጣጫዎች ለየት ያለ ትኩረት መስጠት ይኖርብናል።—1 ቆሮ. 9:27፤ w24.07 15 አን. 5-7
ቅዳሜ፣ ነሐሴ 15
በመልካም ሥራ ሁሉ ፍሬ እያፈራችሁና ስለ አምላክ ትክክለኛ እውቀት በመቅሰም እያደጋችሁ [ሂዱ]።—ቆላ. 1:10
በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ የተገለጸው መልካም ሥራ ምሥራቹን መስበክን ያካትታል። ስለዚህ የአምላክን ቃል ስናነብና ባነበብነው ላይ ስናሰላስል በይሖዋ ላይ ያለን እምነት ያድጋል፤ እንዲሁም የመንግሥቱን መልእክት ለሌሎች ማካፈላችን ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ግልጽ ይሆንልናል። ከአምላክ ቃል የተሟላ ጥቅም ማግኘት እንድንችል በችኮላ ሳይሆን ተረጋግተንና ጊዜ ወስደን ማንበብ፣ ማጥናትና ማሰላሰል ይኖርብናል። አንድን ጥቅስ መረዳት ከከበደህ ችላ ብለኸው አትለፍ። ከዚህ ይልቅ የምርምር መርጃ መሣሪያ ለይሖዋ ምሥክሮች ወይም ሌላ የማጥኛ መሣሪያ በመጠቀም በጥቅሱ ላይ የተሰጡ ማብራሪያዎችን ለማግኘት ሞክር። ጊዜ ወስደህ የምታጠና ከሆነ የአምላክ ቃል እውነት በመሆኑ ላይ ያለህ እምነት ይጠናከራል። (1 ተሰ. 5:21) ይበልጥ እርግጠኛ በሆንክ መጠን ደግሞ የተማርከውን ነገር ለሌሎች ማካፈል ይበልጥ አስደሳች ይሆንልሃል። w24.04 15 አን. 4-5
እሁድ፣ ነሐሴ 16
የጻፍኩላችሁ . . . በሁሉም ነገር ታዛዥ መሆናችሁን ታሳዩ እንደሆነ ለማረጋገጥ ነው።—2 ቆሮ. 2:9
ዳዊት “አንተ ጥሩ ነህና፤ ይቅር ለማለትም ዝግጁ ነህ” ብሏል። (መዝ. 86:5) ሚክያስ ደግሞ “[ኃጢአትን] ይቅር የሚል፣ በደላቸውንም የሚያልፍ እንደ አንተ ያለ አምላክ ማን ነው?” በማለት ጽፏል። (ሚክ. 7:18) ኢሳይያስም እንዲህ ብሏል፦ “ክፉ ሰው መንገዱን፣ መጥፎ ሰውም ሐሳቡን ይተው፤ ምሕረት ወደሚያሳየው አምላካችን ወደ ይሖዋ ይመለስ፤ ይቅርታው ብዙ ነውና።” (ኢሳ. 55:7) በቆሮንቶስ ጉባኤ ውስጥ የነበሩ ወንድሞችና እህቶች ይሖዋን መምሰል ከፈለጉ ንስሐ የገባውን ግለሰብ መቀበልና ለእሱ ያላቸውን ፍቅር ማረጋገጥ እንዳለባቸው ተነግሯቸዋል። የጉባኤው ወንድሞችና እህቶች፣ ይህን መመሪያ በመከተል ‘በሁሉም ነገር ታዛዥ መሆናቸውን አሳይተዋል።’ እውነት ነው፣ ግለሰቡ ከተወገደ በኋላ ያለፉት ጥቂት ወራት ብቻ ናቸው። ሆኖም የተሰጠው ተግሣጽ ወደ ንስሐ መርቶታል። በመሆኑም ወደ ጉባኤው የሚመለስበትን ጊዜ ማዘግየት ምንም ትርጉም የለውም። w24.08 17-18 አን. 12-13
ሰኞ፣ ነሐሴ 17
አንዱ ይወሰዳል፤ ሌላው እዚያው ይተዋል።—ማቴ. 24:40
የምንኖረው ትላልቅ ለውጦች በሚጠበቁበት ጊዜ ውስጥ ነው። በቅርቡ ኢየሱስ በምድር ላይ በሚኖር በእያንዳንዱ ሰው ላይ ፍርድ ያስተላልፋል። ኢየሱስ ይህ የፍርድ ጊዜ መቃረቡን እንዴት ማወቅ እንደምንችል ገልጾልናል፤ በማይታይ ሁኔታ መገኘቱንና ‘የዚህን ሥርዓት መደምደሚያ’ የሚጠቁመውን ትንቢታዊ “ምልክት” ለደቀ መዛሙርቱ ነግሯቸዋል። (ማቴ. 24:3) ይህ ትንቢት በማቴዎስ ምዕራፍ 24 እና 25 እንዲሁም በማርቆስ ምዕራፍ 13 እና በሉቃስ ምዕራፍ 21 ላይ ይገኛል። ኢየሱስ ሦስት ምሳሌዎችን በመጠቀም አስፈላጊ ማስጠንቀቂያዎችን ተናግሯል። እነሱም የበጎቹና የፍየሎቹ፣ የልባሞቹና የሞኞቹ ደናግል እንዲሁም የታላንቱ ምሳሌዎች ናቸው። እያንዳንዱ ምሳሌ፣ ለፍርድ መሠረት የሚሆነው ባሕርይ ምን እንደሆነ ይጠቁመናል። w24.09 20 አን. 1-2
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 18
የምታደርጉትን ነገር ሁሉ በፍቅር አድርጉ።—1 ቆሮ. 16:14
ከሁሉ የላቀ ምሳሌያችን የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ማንኛውንም ነገር የሚያደርገው ለአባቱና ለሰዎች ባለው ፍቅር ተነሳስቶ ነበር። ይህ ፍቅር ሌሎችን ለመርዳት ሲል ተግቶ እንዲሠራና ዝቅ ተደርገው የሚታዩ ሥራዎችን እንዲያከናውን አነሳስቶታል። (ማቴ. 20:28፤ ዮሐ. 13:5, 14, 15) ወንድሞች፣ እናንተም ማንኛውንም ነገር የምታደርጉት በፍቅር ተነሳስታችሁ ከሆነ ይሖዋ ይባርካችኋል፤ እንዲሁም የጉባኤ አገልጋይ እንደመሆን ያሉ መንፈሳዊ ግቦቻችሁ ላይ ለመድረስ ብቃቱን እንድታሟሉ ይረዳችኋል። (1 ጴጥ. 5:5) በምንኖርበት ዓለም ውስጥ ራሳቸውን ከፍ የሚያደርጉ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ይከበራሉ። በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ግን ሁኔታው ከዚህ ፈጽሞ የተለየ ነው። እንደ ኢየሱስ ፍቅር ያለው ወንድም ሥልጣን ወይም ከፍ ያለ ቦታ ለማግኘት አይመኝም። እንዲህ ያለው የሥልጣን ጥመኛ ሰው በጉባኤው ውስጥ ቢሾም የይሖዋን ውድ በጎች ለመንከባከብ የሚያስፈልጉ አንዳንድ ዝቅ ተደርገው የሚታዩ ሥራዎችን ለመሥራት ፈቃደኛ ላይሆን ይችላል። እንዲህ ያሉት ሥራዎች እንደማይመጥኑት ይሰማው ይሆናል።—ዮሐ. 10:12፤ w24.11 15 አን. 6-7
ረቡዕ፣ ነሐሴ 19
መንፈስ ቅዱስ የበላይ ተመልካቾች አድርጎ [ሾሟችኋል]።—ሥራ 20:28
በዓለም ዙሪያ “ስጦታ” የሚሆኑ ተጨማሪ ወንድሞች ያስፈልጉናል። (ኤፌ. 4:8) የተጠመቅክ ወንድም ከሆንክ በዚህ ረገድ “ለመርዳት የሚያስችል አቅም” አለህ? (ምሳሌ 3:27) የጉባኤ አገልጋይ ለመሆን የሚያስፈልገውን ብቃት ለማሟላት ፈቃደኛ ነህ? ወንድሞችህን ይበልጥ መርዳት እንድትችል የጉባኤ ሽማግሌ ለመሆን መጣጣር ትችል ይሆን? ሁኔታህን አመቻችተህ በመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት ለመካፈል ማመልከት ትችላለህ? ይህ ትምህርት ቤት ኢየሱስ ይበልጥ በተሟላ ሁኔታ እንዲጠቀምብህ ያሠለጥንሃል። እነዚህን ነገሮች ለማድረግ ብቁ እንዳልሆንክ የሚሰማህ ከሆነ ወደ ይሖዋ ጸልይ። የተሰጠህን ማንኛውንም ኃላፊነት በተሳካ ሁኔታ መወጣት እንድትችል በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት እንዲረዳህ ጠይቀው። (ሉቃስ 11:13) ኢየሱስ “ስጦታ” አድርጎ የሾማቸው ወንድሞች በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት እሱ እየመራን እንዳለ የሚያሳዩ ማስረጃዎች ናቸው። (ማቴ. 28:20) እሱ ምን እንደሚያስፈልገን ስለሚያውቅ ብቃት ያላቸውን ወንድሞች ሾሞልናል። እንዲህ ያለ ለጋስና አፍቃሪ ንጉሥ ያለን በመሆኑ አመስጋኝ አይደለህም? w24.10 23 አን. 16-17
ሐሙስ፣ ነሐሴ 20
የቀድሞዎቹ ነገሮች አይታሰቡም።—ኢሳ. 65:17
በአምላክ ሕዝብ ላይ ሥቃይና ጭንቀት ስላስከተሉት ነገሮች ምን ማለት ይቻላል? ወደፊት እነዚህ ነገሮች ‘ይረሳሉ፤ እንዲሁም ከአምላክ ዓይን ይሰወራሉ።’ (ኢሳ. 65:16) ይሖዋ የሚያጋጥሙንን ችግሮች በሙሉ ያስወግድልናል፤ እነዚህ ትውስታዎች የሚያስከትሉብንም ሥቃይ በጊዜ ሂደት ይጠፋል። በአሁኑ ወቅትም እንኳ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻችን ላይ ስንገኝ ይህ ክፉ ዓለም በሚያሳድርብን ጭንቀት ላይ መብሰልሰል ትተን እንረጋጋለን። የአምላክ መንፈስ ፍሬ ክፍል የሆኑትን ፍቅርን፣ ደስታን፣ ሰላምን፣ ደግነትንና ገርነትን በማንጸባረቅ መንፈሳዊው ገነት ውስጥ ላለው መረጋጋት አስተዋጽኦ እናበረክታለን። (ገላ. 5:22, 23) በአምላክ ድርጅት ውስጥ መታቀፍ እንዴት ያለ በረከት ነው! ከመንፈሳዊው ገነት ሳይወጡ የሚኖሩ ሰዎች፣ አምላክ “አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር” እንደሚፈጥር የገባው ቃል ሙሉ በሙሉ ሲፈጸም የመመልከት አጋጣሚ ያገኛሉ። w24.04 22 አን. 9-10
ዓርብ፣ ነሐሴ 21
ሰው ቸኩሎ “የተቀደሰ ነው!” ቢልና ከተሳለ በኋላ ስእለቱን መልሶ ማጤን ቢጀምር ወጥመድ ይሆንበታል።—ምሳሌ 20:25
መጠናናት አስደሳች ሊሆን ቢችልም በቁም ነገር ሊታይ የሚገባው እርምጃ ነው፤ ምክንያቱም ወደ ትዳር ሊመራ ይችላል። አንድ ወንድና አንዲት ሴት በሠርጋቸው ቀን፣ በሕይወት እስካሉ ድረስ እርስ በርስ ለመዋደድና ለመከባበር በይሖዋ ፊት ቃል ኪዳን ይገባሉ። ማንኛውንም ቃል ኪዳን ከመግባታችን በፊት ስለ ጉዳዩ በጥንቃቄ ልናስብበት ይገባል። ከጋብቻ ቃል ኪዳን ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። አንድ ወንድና አንዲት ሴት መጠናናታቸው በደንብ ለመተዋወቅና ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ ይረዳቸዋል። አንዳንዶቹ ለመጋባት ይወስኑ ይሆናል፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ለመለያየት ይወስናሉ። አንድ ወንድና አንዲት ሴት ለመለያየት ቢወስኑ መጠናናቱ አልተሳካም ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ መጠናናቱ ዓላማውን አከናውኗል፤ ጥሩ ውሳኔ ላይ እንዲደርሱ ረድቷቸዋል። ከመጠናናት ጋር በተያያዘ ትክክለኛውን አመለካከት መያዝ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ያላገቡ ሰዎች ትክክለኛው አመለካከት ካላቸው ለማግባት ከማያስቡት ሰው ጋር መጠናናት አይጀምሩም። w24.05 26-27 አን. 3-4
ቅዳሜ፣ ነሐሴ 22
ስለ ጌታችን መመሥከር አያሳፍርህ።—2 ጢሞ. 1:8
አንዳንድ ጊዜ ወጣት ክርስቲያኖች ለእምነታቸው ጥብቅና ለመቆም ሊፈሩ ይችላሉ። ክፍል ውስጥ የዝግመተ ለውጥ ርዕሰ ጉዳይ ሲነሳ ሊጨንቃቸው ይችላል። ለምን? እንዲህ የሚሰማቸው አስተማሪዎቻቸው ዝግመተ ለውጥ የተረጋገጠ ሐቅ እንደሆነ ስለሚናገሩ ሊሆን ይችላል። ወላጆች ከሆናችሁ፣ ልጆቻችሁ ለእምነታቸው ጥብቅና ለመቆም የሚያስችል ድፍረት እንዲኖራቸው ልትረዷቸው የምትችሉት እንዴት ነው? ልጆቻችሁ ፍጥረትን በተመለከተ እውነቱን በማወቃቸው ሊያፍሩ እንደማይገባ አረጋግጡላቸው። ብዙ ሳይንቲስቶችም እንኳ ሕይወት እንዲሁ በአጋጣሚ ወይም በራሱ እንዳልተገኘ ያምናሉ። በፍጥረት ላይ ከሚታየው ውስብስብነት አንጻር ጥበበኛ የሆነ ንድፍ አውጪ እንዳለ ይረዳሉ። በመሆኑም የዝግመተ ለውጥን ትምህርት አይቀበሉም። ልጆቻችሁ ሌሎች ወንድሞችና እህቶች ሕይወት በፍጥረት እንደተገኘ እንዲያምኑ ያደረጓቸውን ምክንያቶች በመመርመር የራሳቸውን እምነት ማጠናከር ይችላሉ። w24.12 18 አን. 14-15
እሁድ፣ ነሐሴ 23
በመንፈስ ቅዱስ ሐሴት [አደረገ]።—ሉቃስ 10:21
ኢየሱስ ስለ ስብከቱ ሥራ ሁልጊዜም አዎንታዊ አመለካከት ነበረው። ለአገልግሎት ያለውን ቅንዓት እንዳያጣ የረዳው ይህ ነው። ለምሳሌ በ30 ዓ.ም. መገባደጃ አካባቢ ኢየሱስ ብዙዎች ለስብከቱ ሥራ አዎንታዊ ምላሽ ሲሰጡ ታይቶት ነበር፤ በመሆኑም ሁኔታውን ለመከር ከደረሰ አዝመራ ጋር አመሳስሎታል። (ዮሐ. 4:35) ከአንድ ዓመት በኋላ ደቀ መዛሙርቱን “አዝመራው ብዙ ነው” ብሏቸዋል። (ማቴ. 9:37, 38) በኋላ ላይ ደግሞ “አዝመራው ብዙ ነው፤ . . . የመከሩ ሥራ ኃላፊ ወደ መከሩ፣ ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት” በማለት ይህንኑ አስረግጦ ተናግሯል። (ሉቃስ 10:2) ኢየሱስ ሰዎች ለምሥራቹ አዎንታዊ ምላሽ እንደሚሰጡ ምንጊዜም ተስፋ ያደርግ ነበር፤ ይህን ሲያደርጉ ደግሞ ተደስቷል። ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ ስለሚሰብኩት መልእክት ምንጊዜም አዎንታዊ አመለካከት እንዲኖራቸው አስተምሯል፤ ይህም ቅንዓታቸውን እንዳያጡ ይረዳቸዋል። w25.03 18-19 አን. 15-16
ሰኞ፣ ነሐሴ 24
አምላኬ መጠጊያ ዓለቴ ነው።—መዝ. 94:22
ይሖዋ መጠጊያ ነው። ግዙፍ የሆነ ዓለት አንድን ሰው ከአውሎ ነፋስ ሊከልለው እንደሚችል ሁሉ ይሖዋም አደገኛ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ይጠብቀናል። ደህንነታችን የተጠበቀ እንዲሆንና ዘላቂ ጉዳት እንዳይደርስብን ይከላከልልናል። ወደፊት ደግሞ ከዚህም የበለጠ ነገር እንደሚያደርግልን ቃል ገብቶልናል፤ ሰላማችንንም ሆነ ደህንነታችንን አደጋ ላይ የሚጥልን ማንኛውንም ነገር ያስወግዳል። (ሕዝ. 34:25, 26) ይሖዋን እንደ ዓለት መጠጊያችን ልናደርገው የምንችልበት አንዱ መንገድ ወደ እሱ መጸለይ ነው። ስንጸልይ ይሖዋ ልባችንንና አእምሯችንን የሚጠብቅልንን “የአምላክ ሰላም” ይሰጠናል። (ፊልጵ. 4:6, 7) ይሖዋ ሁልጊዜም ከእኛ ጋር ነው። “የዘላለም ዓለት” ስለሆነ ልንተማመንበት እንችላለን። (ኢሳ. 26:3, 4) እሱ ለዘላለም ሕያው ሆኖ ስለሚኖር የገባልንን ቃል ለመፈጸም፣ ጸሎታችንን ለመስማትና የሚያስፈልገንን ድጋፍ ለማድረግ ሁልጊዜም ዝግጁ ነው። በተጨማሪም ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ታማኝ ስለሆነ እምነት ልንጥልበት እንችላለን። (2 ሳሙ. 22:26) ያከናወንነውን ሥራ ፈጽሞ አይረሳም፤ ምንጊዜም ወሮታችንን ይከፍለናል።—ዕብ. 6:10፤ 11:6፤ w24.06 27 አን. 4-6
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 25
ልብህን ጠብቅ፤ የሕይወት ምንጭ ከእሱ ዘንድ ነውና።—ምሳሌ 4:23
ጤናማ ያልሆነ መዝናኛ ልባችንን ሊከፍለው ይችላል። መጥፎ ጓደኝነትና ፍቅረ ነዋይም ተመሳሳይ ውጤት ሊያስከትሉ ይችላሉ። አንድ ነገር ለይሖዋ ያለንን ፍቅር እያዳከመው እንዳለ ካስተዋልን ይህን ተጽዕኖ ለማስወገድ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል። (ማቴ. 5:29, 30) ልባችን እንዲከፈል ልንፈቅድ አይገባም። በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች እስከተጠመድን ድረስ ከመጥፎ ተጽዕኖዎች መራቅ እንደማያስፈልገን በማሰብ ራሳችንን ልናታልል እንችላለን። ሁኔታውን በምሳሌ ለማስረዳት፣ ኃይለኛ ነፋስና ብርድ ባለበት ቀን ወደ ደጅ ወጥተሃል እንበል። ቤት ስትገባ ማሞቂያ ታበራለህ። ይሁንና በሩን ክፍት ከተውከው ማሞቂያ ማብራትህ ምን ያህል ይጠቅምሃል? ቀዝቃዛው አየር ወዲያውኑ ቤትህን ይሞላዋል። ነጥቡ ምንድን ነው? ከይሖዋ ጋር ያለንን ወዳጅነት የሚያሞቅ መንፈሳዊ ምግብ መመገባችን ብቻውን በቂ አይደለም። የዚህ ዓለም ቀዝቃዛ “አየር” ወይም ዓለማዊ ዝንባሌ ወደ ልባችን ገብቶ እንዳይከፍለው ለመጥፎ ተጽዕኖዎች ልባችንን መዝጋት ይኖርብናል።—ኤፌ. 2:2፤ w24.07 21 አን. 6-7
ረቡዕ፣ ነሐሴ 26
ጠላቶቻችሁን ውደዱ እንዲሁም ስደት ለሚያደርሱባችሁ ጸልዩ።—ማቴ. 5:44
ኢየሱስ የደረሰበትን እንግልትና ውርደት ለመገመት እንኳ ያዳግታል። ያም ሆኖ ኢየሱስ የደረሰበት ግፍ እንዲያሸንፈው አልፈቀደም። እንጨት ላይ ቸንክረው የሰቀሉትን ወታደሮች ከመርገም ይልቅ “አባት ሆይ፣ የሚያደርጉትን ስለማያውቁ ይቅር በላቸው” በማለት ጸልዮአል። (ሉቃስ 23:34) በደል ለሚያደርሱብን ሰዎች መጸለያችን የሚሰማንን ብስጭትና ቁጣ ለመቀነስ አልፎ ተርፎም በደል ላደረሱብን ሰዎች ያለንን አመለካከት ለመቀየር ሊረዳን ይችላል። ይህ ሥርዓት እስኪያበቃ ድረስ ወደፊት ገና የትኞቹ ኢፍትሐዊ ድርጊቶች እንደሚያጋጥሙን አናውቅም። ይሁንና ምንም ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥመን ይሖዋ እንዲረዳን መጸለያችንን አናቋርጥ። በተጨማሪም ኢየሱስ ግፍ ሲደርስበት የሰጠውን ምላሽ መኮረጃችንንና የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ ማዋላችንን እንቀጥል። እንዲህ ካደረግን የይሖዋን በረከት እንደምንወርስ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—1 ጴጥ. 3:8, 9፤ w24.11 6 አን. 16፤ 7 አን. 17, 19
ሐሙስ፣ ነሐሴ 27
አንተ በክፋት የምትደሰት አምላክ አይደለህምና፤ ክፉ ሰው ከአንተ ጋር አይቀመጥም።—መዝ. 5:4
ይሖዋ ልል አምላክ አይደለም፤ ኃጢአትን በቸልታ አያልፍም። (መዝ. 5:4-6) በቃሉ ውስጥ ያስቀመጠልንን የጽድቅ መሥፈርቶች እንድንከተል ይጠብቅብናል። እርግጥ ይሖዋ ፍጹማን ካልሆኑ ሰዎች ፍጽምናን አይጠብቅም። (መዝ. 130:3, 4) ሆኖም “በአምላካችን ጸጋ እያሳበቡ ማንአለብኝነት የሚንጸባረቅበት ድርጊት የሚፈጽሙ” ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ሰዎችን አይታገሥም። (ይሁዳ 4) እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ ‘ፈሪሃ አምላክ የሌላቸውን ሰዎች’ በአርማጌዶን ጦርነት እንደሚያጠፋ ይናገራል። (2 ጴጥ. 3:7፤ ራእይ 16:16) ያም ሆኖ ይሖዋ ማንም እንዲጠፋ አይፈልግም። ይሖዋ “ሁሉ ለንስሐ እንዲበቃ” እንደሚፈልግ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይናገራል። (2 ጴጥ. 3:9) ክርስቲያን ሽማግሌዎች ይሖዋን በመምሰል፣ ጥፋት ያጠፉ ሰዎች አካሄዳቸውን እንዲያስተካክሉና የይሖዋን ሞገስ መልሰው እንዲያገኙ በትዕግሥት ለመርዳት ይሞክራሉ። w24.08 26 አን. 1-2
ዓርብ፣ ነሐሴ 28
አንተ እጅህን ትዘረጋለህ፤ የሕያዋን ፍጥረታትንም ሁሉ ፍላጎት ታሟላለህ።—መዝ. 145:16
እኛም እንደ ይሖዋ በፍቅር ተነሳስተን ለሌሎች ቁሳዊ ነገሮችን መስጠት እንችላለን። ለምሳሌ ምግብ ወይም ልብስ የሚያስፈልገው ክርስቲያን ታውቃለህ? ይሖዋ ይህ አገልጋዩ የሚያስፈልገውን ነገር ለማሟላት ሊጠቀምብህ ይችላል። የይሖዋ ሕዝቦች በተለይ አደጋ በሚያጋጥምበት ጊዜ ልግስና በማሳየታቸው ይታወቃሉ። ለምሳሌ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት ወንድሞችና እህቶች ለተቸገሩ ወንድሞቻቸው ምግብ፣ ልብስና ሌሎች ቁሳቁሶችን ሰጥተዋል። በተጨማሪም ብዙዎች ለዓለም አቀፉ ሥራ በልግስና መዋጮ አድርገዋል። ይህ መዋጮ በዓለም ዙሪያ የእርዳታ ሥራ ለማከናወን አስችሏል። እነዚህ ለጋስ ወንድሞችና እህቶች በዕብራውያን 13:16 ላይ የሚገኘውን ምክር በሥራ ላይ አውለዋል፦ “መልካም ማድረግንና ያላችሁን ነገር ለሌሎች ማካፈልን አትርሱ፤ አምላክ እንዲህ ባሉት መሥዋዕቶች እጅግ ይደሰታልና።” w24.09 27 አን. 6-7
ቅዳሜ፣ ነሐሴ 29
ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይታችሁ [እወቁ]።—ፊልጵ. 1:10
አንድ ምሳሌ እንመልከት። ቤተሰብህን ለማስተዳደር የሚያስችል ሥራ እየፈለግክ ነው እንበል። ሁለት ሥራዎችን አገኘህ። ስለ ሥራዎቹ የተሟላ መረጃ ለማግኘት ጥረት አደረግክ። የሥራውን ዓይነት፣ የሥራ ሰዓቱን፣ ወደ ሥራ ቦታው ለመሄድ የሚፈጅብህን ጊዜ እንዲሁም ሌሎች ነገሮችን አጣራህ። ሁለቱም ሥራዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ጋር የሚጋጩ አይደሉም። ከሥራው ዓይነት ወይም ከደሞዙ አንጻር አንደኛው ሥራ የተሻለ እንደሆነ ሊሰማህ ይችላል። ይሁንና ውሳኔ ከማድረግህ በፊት ከግምት ልታስገባቸው የሚገቡ ሌሎች ነገሮችም አሉ። ለምሳሌ ሥራው ከጉባኤ ስብሰባ ሰዓት ጋር ይጋጭብሃል? ወይም ደግሞ ሥራው የቤተሰብህን ስሜታዊና መንፈሳዊ ፍላጎት ለማሟላት የሚያስችልህን ጊዜ ይሻማብሃል? እንዲህ ያሉ ጥያቄዎችን መጠየቅህ “ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች” ማለትም መንፈሳዊነትህንና ቤተሰብህን ከቁሳዊ ነገሮች እንድታስቀድም ይረዳሃል። በዚህ መንገድ ይሖዋ የሚባርከው ውሳኔ ማድረግ ትችላለህ። w25.01 17-18 አን. 11-13
እሁድ፣ ነሐሴ 30
ይሖዋ ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው።—መዝ. 34:18
ሌሎች ዝቅ አድርገው ቢመለከቱህም እንኳ ይሖዋ እንደሚወድህና ትልቅ ቦታ እንደሚሰጥህ ልትተማመን ትችላለህ። ‘መንፈስህ ሲደቆስብህ’ ይሖዋ በልብህ ውስጥ መልካም ነገር አይቶ በግለሰብ ደረጃ ወደ ራሱ እንደሳበህ አስታውስ። (ዮሐ. 6:44) በእሱ ዘንድ ውድ ስለሆንክ ምንጊዜም ሊረዳህ ዝግጁ ነው። የኢየሱስን ምሳሌ በመመርመር ስለ ይሖዋ ስሜት መማር እንችላለን። ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ባከናወነበት ወቅት ሌሎች ዝቅ አድርገው ለሚመለከቷቸው ሰዎች ትኩረት ሰጥቷል፤ እንዲሁም በርኅራኄ ይዟቸዋል። (ማቴ. 9:9-12) አንዲት ሴት ካለባት የሚያሠቃይ ሕመም ለመፈወስ ብላ ልብሱን በነካች ጊዜ ኢየሱስ አጽናንቷታል፤ እምነት በማሳየቷም አድንቋታል። (ማር. 5:25-34) ኢየሱስ የአባቱን ባሕርይ ፍጹም በሆነ መንገድ አንጸባርቋል። (ዮሐ. 14:9) በመሆኑም ይሖዋ ከፍ አድርጎ እንደሚመለከትህ እንዲሁም እምነትህንና ለእሱ ያለህን ፍቅር ጨምሮ ያሉህን መልካም ባሕርያት እንደሚያስተውል መተማመን ትችላለህ። w24.10 7 አን. 4-5
ሰኞ፣ ነሐሴ 31
እንባዬን በአቁማዳህ አጠራቅም።—መዝ. 56:8
ዳዊት በሕይወት ዘመኑ ውስጥ እንዲያለቅስ የሚያደርጉ ብዙ መከራዎች አጋጥመውታል። የሚጠሉት ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ ያምናቸው የነበሩ አንዳንድ ሰዎችም እንኳ ከድተውታል። (1 ሳሙ. 19:10, 11፤ 2 ሳሙ. 15:10-14, 30) በአንድ ወቅት እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ከመቃተቴ የተነሳ ዝያለሁ፤ ሌሊቱን ሙሉ መኝታዬን በእንባ አርሳለሁ፤ በለቅሶ አልጋዬን አጥለቀልቃለሁ።” (መዝ. 6:6) ዳዊት ብዙ ችግሮች ቢያጋጥሙትም ይሖዋ እንደሚወደው እርግጠኛ ነበር። “ይሖዋ የለቅሶዬን ድምፅ ይሰማል” ሲል ጽፏል። (መዝ. 6:8) በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ የሚገኙት ቃላት የይሖዋን ርኅራኄ ግሩም አድርገው ይገልጻሉ። ዳዊት፣ ይሖዋ በምሳሌያዊ ሁኔታ እንባውን በአቁማዳ እንደሚያጠራቅም ወይም በመጽሐፍ ላይ እንደሚያሰፍረው ተሰምቶት ነበር። ዳዊት፣ ይሖዋ ሥቃዩን ልብ እንደሚልና እንደሚያስታውስ እርግጠኛ ነበር። ዳዊት የሚወደው አባቱ፣ ያሳለፈውን መከራ ብቻ ሳይሆን መከራው ያሳደረበትን ስሜትም ጭምር እንደሚያውቅ ተማምኗል። w24.12 22 አን. 11-12