የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • es26 ገጽ 67-77
  • ሐምሌ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ሐምሌ
  • ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2026
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ረቡዕ፣ ሐምሌ 1
  • ሐሙስ፣ ሐምሌ 2
  • ዓርብ፣ ሐምሌ 3
  • ቅዳሜ፣ ሐምሌ 4
  • እሁድ፣ ሐምሌ 5
  • ሰኞ፣ ሐምሌ 6
  • ማክሰኞ፣ ሐምሌ 7
  • ረቡዕ፣ ሐምሌ 8
  • ሐሙስ፣ ሐምሌ 9
  • ዓርብ፣ ሐምሌ 10
  • ቅዳሜ፣ ሐምሌ 11
  • እሁድ፣ ሐምሌ 12
  • ሰኞ፣ ሐምሌ 13
  • ማክሰኞ፣ ሐምሌ 14
  • ረቡዕ፣ ሐምሌ 15
  • ሐሙስ፣ ሐምሌ 16
  • ዓርብ፣ ሐምሌ 17
  • ቅዳሜ፣ ሐምሌ 18
  • እሁድ፣ ሐምሌ 19
  • ሰኞ፣ ሐምሌ 20
  • ማክሰኞ፣ ሐምሌ 21
  • ረቡዕ፣ ሐምሌ 22
  • ሐሙስ፣ ሐምሌ 23
  • ዓርብ፣ ሐምሌ 24
  • ቅዳሜ፣ ሐምሌ 25
  • እሁድ፣ ሐምሌ 26
  • ሰኞ፣ ሐምሌ 27
  • ማክሰኞ፣ ሐምሌ 28
  • ረቡዕ፣ ሐምሌ 29
  • ሐሙስ፣ ሐምሌ 30
  • ዓርብ፣ ሐምሌ 31
ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2026
es26 ገጽ 67-77

ሐምሌ

ረቡዕ፣ ሐምሌ 1

ጻድቅ ሰው ሲጣል . . . አላየሁም።—መዝ. 37:25

አንዳንድ የይሖዋ አገልጋዮች በዕድሜ መግፋት፣ በጤና መቃወስ ወይም በአካል ጉዳት የተነሳ አቅማቸው ተገድቧል። በዚህም ምክንያት በይሖዋ ዘንድ ስላላቸው ዋጋ ጥርጣሬ ሊገባቸው ይችላል። ‘ይሖዋ አሁንም ሊጠቀምብኝ ይችላል?’ ብለው ይጠይቁ ይሆናል። የመዝሙር 71 ጸሐፊ እንዲህ ያለ ስሜት ተሰምቶት ነበር። “ጉልበቴ በሚያልቅበት ጊዜም አትተወኝ” በማለት ጸልዮአል። (መዝ. 71:9, 18) ያም ቢሆን ይህ መዝሙራዊ ይሖዋን በታማኝነት እስካገለገለ ድረስ እሱ እንደሚመራውና እንደሚደግፈው እርግጠኛ ነበር። መዝሙራዊው እንደተገነዘበው፣ ይሖዋ የአቅም ገደብ ቢኖርባቸውም እሱን ለማገልገል ልባዊ ጥረት በሚያደርጉ ሰዎች ይደሰታል። (መዝ. 37:23-25) አረጋውያን፣ ያላችሁበትን ሁኔታ በተመለከተ የይሖዋ ዓይነት አመለካከት ይኑራችሁ። አካላችሁ ቢደክምም እንኳ ይሖዋ በመንፈሳዊ እንድታብቡ ሊረዳችሁ ይችላል። (መዝ. 92:12-15) አሁን ማድረግ በማትችሉት ነገር ላይ ከማተኮር ይልቅ ማድረግ በምትችሉት ነገር ላይ አተኩሩ። w24.10 28 አን. 14-16

ሐሙስ፣ ሐምሌ 2

ለጣዖቶች የቀረበ ምግብ መብላትን በተመለከተ፣ በዓለም ላይ ጣዖት ከንቱ እንደሆነ . . . እናውቃለን።—1 ቆሮ. 8:4

ብዙውን ጊዜ፣ ያልጎለመሱ ክርስቲያኖች በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ ማመዛዘንና በሥራ ላይ ማዋል የሚጠይቁ ሁኔታዎች ሲያጋጥሟቸው ይቸገራሉ። አንዳንዶች ስለ ጉዳዩ የሚናገር የመጽሐፍ ቅዱስ ሕግ ከሌለ የፈለጉትን ማድረግ እንደሚችሉ ይሰማቸው ይሆናል። ሌሎች ደግሞ ሕግ በማያስፈልግበት ቦታ ሕግ እንዲሰጣቸው ሊጠይቁ ይችላሉ። ለምሳሌ በቆሮንቶስ የነበሩት ክርስቲያኖች ለጣዖት የተሠዋ እንስሳን ሥጋ ከመብላት ጋር በተያያዘ ሐዋርያው ጳውሎስ መመሪያ እንዲሰጣቸው ጠይቀው የነበረ ይመስላል። ጳውሎስ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ከመናገር ይልቅ ሕሊና ስለሚጫወተው ሚና እና እያንዳንዱ ሰው ስላለው ‘የመምረጥ መብት’ ነገራቸው። እያንዳንዱ ሰው ሌላውን ሰው ሳያሰናክል ሕሊናው የሚፈቅድለትን ነገር ማድረግ የሚችለው እንዴት እንደሆነ የሚያሳዩ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ጠቀሰላቸው። (1 ቆሮ. 8:7-9) በዚህ መንገድ ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ሌሎች ውሳኔ እንዲያደርጉላቸው ወይም ሕግ እንዲሰጧቸው ከመጠበቅ ይልቅ የራሳቸውን የማመዛዘን ችሎታ መጠቀም እንዲችሉ ሲል በመንፈሳዊ እንዲያድጉ እየረዳቸው ነበር። w24.04 5 አን. 14

ዓርብ፣ ሐምሌ 3

እኔ ይሖዋ፣ ለእያንዳንዱ እንደ መንገዱ . . . ለመስጠት ልብን እመረምራለሁ።—ኤር. 17:10

በዮናስ ዘመን የነነዌ ሰዎች ንስሐ ለመግባት የሚያስችል አጋጣሚ አግኝተዋል። ከዚህም ሌላ ኢየሱስ ስለ “ፍርድ ትንሣኤ” ምን እንደተናገረ አስታውስ። “ክፉ የሠሩ” ሰዎችም በዚህ ትንሣኤ ውስጥ ይካተታሉ። (ዮሐ. 5:29) ከዚህ አንጻር የሰዶምና የገሞራ ሰዎችም የተወሰነ ተስፋ ያላቸው ይመስላል። ከእነሱ መካከል ቢያንስ አንዳንዶቹ ከሞት ይነሱ ይሆናል። እኛም እነሱን ስለ ይሖዋና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የማስተማር አጋጣሚ ልናገኝ እንችላለን። ይሖዋ ከጥንትም ጀምሮ ‘ልብን ይመረምራል፤ የውስጥ ሐሳብንም ይፈትናል።’ ሁልጊዜ እንደሚያደርገው ሁሉ ወደፊት በሚከናወነው ትንሣኤ ወቅትም “ለእያንዳንዱ እንደ መንገዱ” ይሰጠዋል። ይሖዋ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ጥብቅ ይሆናል፤ የሚቻል በሚሆንበት ጊዜ ሁሉ ደግሞ ምሕረት ያሳያል። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ በቀጥታ ካልተናገረ በስተቀር አንድ ሰው የትንሣኤ ተስፋ የለውም ብለን መደምደም አይኖርብንም። w24.05 5-6 አን. 15-16

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 4

አትፍራ። እረዳሃለሁ።—ኢሳ. 41:13

ባለፉት ዘመናት ከባድ ኃላፊነት የተሰጣቸው የአምላክ አገልጋዮች ከቃሉ ብርታት ማግኘት ችለዋል። የነቢዩ ኤርምያስን ምሳሌ እንመልከት። ይሖዋ የሰጠውን የመስበክ ኃላፊነት ለመቀበል አመንትቶ ነበር። ኤርምያስ “እኔ ገና ልጅ ስለሆንኩ ምን ብዬ እንደምናገር አላውቅም” ብሎ ነበር። (ኤር. 1:6) ታዲያ ፍርሃቱን ማሸነፍ የቻለው እንዴት ነው? አምላክ ከተናገረው ቃል ብርታት አግኝቷል። እንዲህ ብሏል፦ “በአጥንቶቼም ውስጥ እንደገባ የሚነድ እሳት ሆነብኝ፤ አፍኜ መያዝ አቃተኝ።” (ኤር. 20:8, 9) ኤርምያስ ያገለገለው በአስቸጋሪ ክልል ውስጥ ቢሆንም እንዲያውጅ የተሰጠው መልእክት ሥራውን ለማከናወን የሚያስችል ብርታት ሰጥቶታል። በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘው መልእክት ለክርስቲያኖች ብርታት ይሰጣቸዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ወንድሞቹ ትክክለኛ እውቀት ማግኘታቸው ‘ለይሖዋ በሚገባ ሁኔታ እንዲመላለሱ’ እና ‘በመልካም ሥራ ሁሉ ፍሬ ማፍራታቸውን’ እንዲቀጥሉ እንደሚረዳቸው ገልጿል።—ቆላ. 1:9, 10፤ w24.04 14-15 አን. 2-4

እሁድ፣ ሐምሌ 5

ካህኑ ሳዶቅ . . . ሰለሞንን ቀባው።—1 ነገ. 1:39

ካህኑ አብያታር የዳዊትን ዙፋን ለመውሰድ ያሰበውን የዳዊትን ልጅ አዶንያስን በመደገፍ ታማኝነቱን ቢያጓድልም ሳዶቅ ለይሖዋ ታማኝ ሆኖ ቀጥሏል። ዳዊት የሳዶቅን ታማኝነት ተጠራጥሮ አያውቅም። የአዶንያስ ሴራ ሲጋለጥ ዳዊት ሰለሞንን ንጉሥ አድርገው እንዲቀቡት ሳዶቅን፣ ናታንን እና በናያህን ጠየቃቸው። (1 ነገ. 1:32-34) ሳዶቅ እንደ ናታን እና እንደ ሌሎቹ የንጉሥ ዳዊት ደጋፊዎች ካሉ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ጋር አብሮ መሆኑ አጠናክሮትና አበረታቶት መሆን አለበት። ሰለሞን ንጉሥ ከሆነ በኋላ “በአብያታር ቦታ . . . ካህኑን ሳዶቅን ሾመው።” (1 ነገ. 2:35) አንተስ የሳዶቅን ምሳሌ መከተል የምትችለው እንዴት ነው? አንድ የምትቀርበው ሰው ይሖዋን ለመተው ከመረጠ አንተ ለይሖዋ ታማኝ ለመሆን መምረጥህን በግልጽ አሳይ። (ኢያሱ 24:15) ይሖዋ የሚያስፈልግህን ብርታትና ድፍረት ይሰጥሃል። ወደ ይሖዋ ጸልይ፤ እንዲሁም ከሌሎች ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ጋር ተቀራረብ። ይሖዋ ታማኝነትህን ከፍ አድርጎ ይመለከታል፤ ወሮታህንም ይከፍልሃል።—2 ሳሙ. 22:26፤ w24.07 6-7 አን. 16-17

ሰኞ፣ ሐምሌ 6

ተስፋ ቆርጠን መልካም ሥራ መሥራታችንን አንተው።—ገላ. 6:9

መዝሙር 15:2 የአምላክ ወዳጅ የሚሆነው “ያለነቀፋ የሚመላለስ” እና “ትክክል የሆነውን የሚያደርግ” ሰው እንደሆነ ይናገራል። “የሚመላለስ” እና “የሚያደርግ” የሚሉት ቃላት ማዘውተርንና ቀጣይነትን የሚጠቁሙ ናቸው። ይሁንና በእርግጥ ‘ያለነቀፋ መመላለስ’ እንችላለን? አዎ። ፍጹም የሆነ ሰው ባይኖርም ይሖዋን ለመታዘዝ የምንችለውን ያህል ጥረት የምናደርግ ከሆነ ‘ያለነቀፋ እንደምንመላለስ’ አድርጎ ይመለከተናል። ራሳችንን ስንወስንና ስንጠመቅ ከአምላክ ጋር የምናደርገውን ጉዞ ገና መጀመራችን ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን አንድ ሰው የእስራኤል ብሔር አባል መሆኑ ብቻውን የይሖዋ እንግዳ ለመሆን ብቁ እንደማያደርገው ልናስታውስ ይገባል። አንዳንዶች አምላክን የሚጠሩ ቢሆንም የሚጠሩት “በእውነትና በጽድቅ” አልነበረም። (ኢሳ. 48:1) የይሖዋ እንግዶች የመሆን ልባዊ ፍላጎት ያላቸው እስራኤላውያን የይሖዋን መሥፈርቶች መማርና ተግባራዊ ማድረግ ነበረባቸው። ዛሬም በተመሳሳይ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት መጠመቃችንና ከክርስቲያን ጉባኤ ጋር መሰብሰባችን ብቻ በቂ አይደለም። ‘ትክክል የሆነውን ማድረጋችንን’ መቀጠል ይኖርብናል። w24.06 9 አን. 4፤ 10 አን. 6

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 7

አምላክን የምትመስሉ ሁኑ።—ኤፌ. 5:1

ይሖዋ ልግስና የሚያሳየው እንዴት ነው? አንዳንድ ምሳሌዎችን እስቲ እንመልከት። ይሖዋ ቁሳዊ ነገሮችን ይሰጠናል። የተንደላቀቀ ሕይወት ባንመራም እንኳ ይሖዋ የሚያስፈልጉን ነገሮች እንዲሟሉልን ያደርጋል። ለምሳሌ ምግብ፣ ልብስና መጠለያ እንድናገኝ ይረዳናል። (መዝ. 4:8፤ ማቴ. 6:31-33፤ 1 ጢሞ. 6:6-8) ይሖዋ የሚያስፈልገንን ቁሳዊ ነገር የሚያሟላልን ግዴታ እንዳለበት ስለሚሰማው ብቻ ነው? በፍጹም! ኢየሱስ በማቴዎስ 6:25, 26 ላይ ምን እንዳለ ልብ በል። ስለ ወፎች ሲናገር “አይዘሩም፣ አያጭዱም ወይም በጎተራ አያከማቹም” ብሏል። ሆኖም ቀጥሎ ምን እንዳለ ልብ በል፦ “በሰማይ ያለው አባታችሁ ይመግባቸዋል።” ከዚያም ኢየሱስ እንዲህ በማለት ጠየቀ፦ “ታዲያ እናንተ ከእነሱ አትበልጡም?” ነጥቡ ምንድን ነው? ይሖዋ እንስሳት የሚያስፈልጋቸውን ነገር የሚያሟላላቸው ከሆነ ለእኛማ እንዴት አብልጦ አያደርግ! አሳቢ የሆኑ አባቶች እንደሚያደርጉት ይሖዋ በፍቅር ተነሳስቶ ቤተሰቡን ይንከባከባል።—መዝ. 145:16፤ ማቴ. 6:32፤ w24.09 26-27 አን. 4-6

ረቡዕ፣ ሐምሌ 8

በተገቢው ሁኔታ የሚያገለግሉ ወንዶች ለራሳቸው መልካም ስም የሚያተርፉ ከመሆናቸውም በላይ . . . ስላላቸው እምነት አፋቸውን ሞልተው ለመናገር የሚያስችል ነፃነት ያገኛሉ።—1 ጢሞ. 3:13

የጉባኤ አገልጋይ የሚባለው በጉባኤ ውስጥ የተለያዩ ጠቃሚ ሥራዎችን በማከናወን ሽማግሌዎችን እንዲረዳ በመንፈስ ቅዱስ የተሾመ የተጠመቀ ወንድም ነው። የጉባኤ አገልጋዮች በዋነኝነት መንፈሳዊ ሰዎች መሆን ይጠበቅባቸዋል። ይሖዋን ይወዳሉ፤ በጽድቅ መሥፈርቶቹም ይመራሉ። እንዲሁም ለክርስቲያን ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ጥልቅ ፍቅር አላቸው። (ማቴ. 22:37-39) ታዲያ አንድ የተጠመቀ ወንድም የጉባኤ አገልጋይ ለመሆን መጣጣር የሚችለው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ የጉባኤ አገልጋይ ሆነው የሚሾሙ ወንድሞች ሊያሟሏቸው የሚገቡ ብቃቶችን ይዘረዝራል። (1 ጢሞ. 3:8-10, 12) ስለ እነዚህ ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶች በማጥናት ከዚያም ብቃቶቹን ለማሟላት ተግተህ በመሥራት ይህን መብት ለማግኘት መጣጣር ትችላለህ። በቅድሚያ ግን፣ የጉባኤ አገልጋይ ለመሆን የተነሳሳህበትን ምክንያት በጥንቃቄ ማጤን ይኖርብሃል። w24.11 14-15 አን. 4-5

ሐሙስ፣ ሐምሌ 9

እንደ ሰው ቃል ሳይሆን እንደ አምላክ ቃል አድርጋችሁ ተቀብላችሁታል፤ ደግሞም የአምላክ ቃል ነው።—1 ተሰ. 2:13

አንዳንድ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ደጋግመው እንዳነበቡት ይናገራሉ። ይሁንና በመጽሐፍ ቅዱስ ያምናሉ ሊባል ይችላል? ምክሮቹን ተግባራዊ ያደርጋሉ? ወይም ቃሉ ሕይወታቸውን እንዲመራላቸው ፈቅደዋል? የሚያሳዝነው፣ በአብዛኛው ሁኔታው እንደዚህ አይደለም። የአምላክ ሕዝቦች ግን ከዚህ በጣም የተለዩ ናቸው። የአምላክ ቃል በእኛ ላይ እየሠራ እንደሆነ ለማሳየት ጥረት እናደርጋለን። ያም ሆኖ የአምላክን ቃል ማንበብና ተግባራዊ ማድረግ ሁልጊዜ ቀላል አይደለም። ለማንበብ የሚሆን ጊዜ ለማግኘት ልንቸገር እንችላለን። ወይም በችኮላ የማንበብ ልማድ ይኖረን ይሆናል፤ ይህም መልእክቱ ወደ ልባችን ጠልቆ እንዳይገባ እንቅፋት ይሆንብናል። ወይም ማድረግ ስላለብን ማሻሻያዎች ስናስብ ሁኔታው ከአቅማችን በላይ እንደሆነ ይሰማን ይሆናል። ያጋጠመህ ፈታኝ ሁኔታ ምንም ዓይነት ቢሆን ልትወጣው የማትችለው አይደለም። በይሖዋ እርዳታ ልታሸንፈው ትችላለህ። ቃሉን የምናደርግ ለመሆን ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። የአምላክን ቃል ባነበብንና በሕይወታችን ውስጥ ተግባራዊ ባደረግነው መጠን ይበልጥ ደስተኞች እንደምንሆን ምንም ጥርጥር የለውም።—ያዕ. 1:25፤ w24.09 7 አን. 15-16

ዓርብ፣ ሐምሌ 10

ደጋግማችሁ ለምኑ፣ ይሰጣችኋል።—ሉቃስ 11:9

አስከፊ መከራ ወይም ሐዘን ሲደርስብን ይሖዋ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ያጽናናናል። ልብ የሚሰብር መከራ አጋጥሞህ ከሆነ በማንኛውም ጊዜ እንዲሁም ለፈለግከው ያህል ሰዓት ወደ ይሖዋ መጸለይ ትችላለህ። (መዝ. 86:3፤ 88:1) ይሖዋ ቅዱስ መንፈሱን እንዲሰጥህ በተደጋጋሚ ጠይቀው። እሱ ጥያቄህን ፈጽሞ ችላ አይልም። የደረሰብህ ከባድ ፈተና አቅምህን አሟጦታል? መንፈስ ቅዱስ ይሖዋን በታማኝነት ማገልገልህን እንድትቀጥል ኃይል ሊሰጥህ ይችላል። (ኤፌ. 3:16) መንፈስ ቅዱስን ለማግኘት ካቀረብከው ልመና ጋር የሚስማማ እርምጃ መውሰድ የምትችለው እንዴት ነው? የአምላክ መንፈስ በአንተ ላይ እንዲሠራ በሚያደርጉ እንቅስቃሴዎች ተካፈል። ይህም በስብሰባዎች ላይ መገኘትንና ለሌሎች መስበክን ይጨምራል። በየዕለቱ የይሖዋን ቃል በማንበብ አእምሮህ በእሱ ሐሳቦች እንዲሞላ አድርግ። (ፊልጵ. 4:8, 9) ቃሉን ስታነብ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ባለታሪኮች መከራ ባጋጠማቸው ወቅት ይሖዋ እንዲጸኑ የረዳቸው እንዴት እንደሆነ ልብ በል። w24.10 9 አን. 12-14

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 11

አምላክ ዓለምን እጅግ [ወዷል]።—ዮሐ. 3:16

እንደ ይሖዋና እንደ ልጁ እኛም ሰዎችን እንወዳለን። (ምሳሌ 8:31) “ያለተስፋና ያለአምላክ” ለሚኖሩ ሰዎች ጥልቅ ርኅራኄ ይሰማናል። (ኤፌ. 2:12) እነዚህ ሰዎች በሚያጋጥሟቸው ችግሮች የተነሳ በጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ እንዳሉ ሊቆጠር ይችላል። እኛ ግን ከጉድጓዱ ሊያወጣቸው የሚችል ገመድ አለን፤ እሱም የአምላክ መንግሥት ምሥራች ነው። እንዲህ ላሉት ሰዎች ያለን ፍቅርና ርኅራኄ ምሥራቹን ለእነሱ ለመናገር አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ እንድናደርግ ያነሳሳናል። ይህ ውድ መልእክት ልባቸው በተስፋ እንዲሞላ፣ በአሁኑ ጊዜ ከሁሉ የተሻለውን ሕይወት መምራት እንዲችሉ እንዲሁም በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ “እውነተኛ የሆነውን ሕይወት” ማለትም የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋ እንዲኖራቸው ያስችላል። (1 ጢሞ. 6:19) ለሰዎች ያለን ፍቅር እየቀረበ ስላለው የዚህ ክፉ ዓለም መጨረሻ እንድናስጠነቅቃቸውም ያነሳሳናል። (ሕዝ. 33:7, 8) በታላቁ መከራ ወቅት የሚከናወነውን ነገር እንዲያውቁ እንፈልጋለን። የሐሰት ሃይማኖት ይጠፋል፤ እሱን ተከትሎ ደግሞ ይህ ክፉ ሥርዓት ሙሉ በሙሉ ይወገዳል።—ራእይ 16:14, 16፤ 17:16, 17፤ 19:11, 19, 20፤ w24.05 16-17 አን. 8-9

እሁድ፣ ሐምሌ 12

የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ ራሳችሁ አትበቀሉ፤ ከዚህ ይልቅ “‘በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ’ ይላል ይሖዋ” ተብሎ ስለተጻፈ ለቁጣው ዕድል ስጡ።—ሮም 12:19

ሐዋርያው ጳውሎስ ለይሖዋ ‘ቁጣ ዕድል እንዲሰጡ’ ክርስቲያኖችን መክሯቸዋል። ለይሖዋ ቁጣ ዕድል የምንሰጠው እሱ በመረጠው ጊዜና በመረጠው መንገድ ችግሩን እንዲያስተካክል በመፍቀድ ነው። ጆን የተባለ ወንድም ኢፍትሐዊ ድርጊት ከተፈጸመበት በኋላ እንዲህ ብሏል፦ “በራሴ መንገድ ችግሩን ለማስተካከል ተፈትኜ ነበር። ሆኖም ሮም 12:19 ይሖዋን እንድጠብቅ ረድቶኛል።” ይሖዋ ችግሩን እስኪያስተካክል መጠበቃችን ይጠቅመናል። እንዲህ ካደረግን፣ በራሳችን መንገድ ችግሩን ለመፍታት መሞከር ከሚያስከትለው ሸክምና ብስጭት እንጠበቃለን። ይሖዋ ሊረዳን ፈቃደኛ ነው። “ጉዳዩን ለእኔ ተዉት። እኔ ራሴ አስተካክለዋለሁ” እንዳለን ሊቆጠር ይችላል። ይሖዋ “እኔ ብድራትን እመልሳለሁ” በማለት በገባው ቃል ከተማመንን እሱ ከሁሉ በተሻለ መንገድ ችግሩን እንደሚያስተካክለው እርግጠኛ በመሆን ጉዳዩን ለእሱ መተው እንችላለን። w24.11 6 አን. 14-15

ሰኞ፣ ሐምሌ 13

የዕለቱን ምግባችንን ለዕለቱ የሚያስፈልገንን ያህል ስጠን።—ሉቃስ 11:3

ለቁሳዊ ነገሮች ከተገቢው ያለፈ ትኩረት ልንሰጥ አይገባም። ሐዋርያው ጳውሎስ በአይሁድ ሥርዓት መደምደሚያ ላይ ይኖሩ ለነበሩት ክርስቲያኖች በጻፈበት ወቅት ይህን ሐሳብ ጎላ አድርጎ ገልጿል። ጳውሎስ እስራኤላውያን በጥንት ዘመን ያጋጠሟቸውን ነገሮች ጠቅሷል፤ ከእነዚህም መካከል በሲና ተራራ አቅራቢያ ያደረጉት ነገር ይገኝበታል። “[እስራኤላውያን] ጎጂ የሆኑ ነገሮችን እንደተመኙ እኛም እንዳንመኝ” በማለት ለክርስቲያኖች ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። (1 ቆሮ. 10:6, 7, 11) እስራኤላውያን የምግብ ፍላጎታቸው ይሖዋ በተአምር ያደረገላቸው ዝግጅትም እንኳ ‘ጎጂ ነገር’ እንዲሆንባቸው አድርጓል። (ዘኁ. 11:4-6, 31-34) የወርቅ ጥጃ በሠሩበት ጊዜ ደግሞ በልተዋል፣ ጠጥተዋል እንዲሁም ጨፍረዋል። (ዘፀ. 32:4-6) ጳውሎስ የጥንቶቹ እስራኤላውያን ያጋጠማቸውን ነገር በ70 ዓ.ም. የአይሁድ ሥርዓት መጨረሻ ከመምጣቱ በፊት ለኖሩት ክርስቲያኖች ማስጠንቀቂያ አድርጎ ጠቅሶታል። እኛም የምንኖረው የዚህ ሥርዓት መጨረሻ በተቃረበበት ዘመን ስለሆነ የጳውሎስን ምክር በቁም ነገር ልንመለከተው ይገባል። w24.12 6 አን. 13

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 14

ከወጣትነት [ሚስትህ] ጋር ደስ ይበልህ።—ምሳሌ 5:18

ይሖዋ ‘ደስተኛ አምላክ’ ነው፤ እኛም ደስተኞች እንድንሆን ይፈልጋል። (1 ጢሞ. 1:11) በሕይወታችን ደስተኛ እንድንሆን የሚያስችሉንን ብዙ ስጦታዎች ሰጥቶናል። (ያዕ. 1:17) ከእነዚህ ስጦታዎች አንዱ ትዳር ነው። አንድ ወንድና አንዲት ሴት ሲጋቡ አንዳቸው ሌላውን ለመውደድ፣ ለማክበርና ለመንከባከብ ቃል ይገባሉ። ፍቅራቸውን እያጠናከሩ መኖራቸው እውነተኛ ደስታ ያስገኝላቸዋል። የሚያሳዝነው፣ በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙ ባለትዳሮች በሠርጋቸው ዕለት የገቡትን ቃል ይረሳሉ። በዚህም ምክንያት ደስታ ርቋቸዋል። ይሖዋ፣ ባሎች ሚስቶቻቸውን በምን መንገድ እንዲይዙ ይጠብቅባቸዋል? ይሖዋ፣ ባሎች ሚስቶቻቸውን እንዲያከብሩ አዟቸዋል። ሚስቱን የሚያከብር ባል ደግነትና ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ ይይዛታል።—1 ጴጥ. 3:7፤ w25.01 8 አን. 1-2፤ 9 አን. 4-5

ረቡዕ፣ ሐምሌ 15

ይሖዋ ረዳቴ ነው፤ አልፈራም።—ዕብ. 13:6

ሐዋርያው ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች የጻፈላቸው ደብዳቤ ወደፊት ለሚጠብቃቸው መከራ እንዳዘጋጃቸው ምንም ጥያቄ የለውም። ጳውሎስ ጥልቅ የቅዱሳን መጻሕፍት እውቀት እንዲኖራቸው ወንድሞቹን አበረታቷቸዋል። እንዲህ ማድረጋቸው እምነታቸውን የሚያዳክሙ ትምህርቶችን ለይተው እንዲያውቁና ከእነዚህ ትምህርቶች እንዲርቁ ይረዳቸዋል። የኢየሱስንም ሆነ በጉባኤ ውስጥ አመራር የሚሰጡትን ወንድሞች መመሪያ በፍጥነት መታዘዝ ይችሉ ዘንድ እምነታቸውን እንዲያጠናክሩ አበረታቷቸዋል። በተጨማሪም ለፈተና ትክክለኛውን አመለካከት በመያዝ ጽናትን እንዲያዳብሩ ረድቷቸዋል። ፈተናዎችን በአፍቃሪ አባታቸው ለመሠልጠን የሚያስችሉ አጋጣሚዎች አድርገው እንዲመለከቷቸው ነግሯቸዋል። እኛም በመንፈስ መሪነት የተሰጠውን ይህን ምክር እንከተል። እንዲህ ካደረግን እስከ መጨረሻው በታማኝነት መጽናት እንችላለን።—ዕብ. 3:14፤ w24.09 13 አን. 17, 19

ሐሙስ፣ ሐምሌ 16

ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መሥዋዕት ሆኖ በቀረበው የኢየሱስ ክርስቶስ አካል አማካኝነት ተቀድሰናል።—ዕብ. 10:10

በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ቤዛ የሚያመለክተው ስርየትንና እርቅን ለማስገኘት የተከፈለውን ዋጋ ነው። ቤዛው፣ ይሖዋ የታጣውን ነገር መልሶ እንዲሰጠን የሚያስችል መሠረት ይሆናል። በምን መንገድ? አዳምና ሔዋን ፍጹም ሕይወታቸውን እንዲሁም ለዘላለም የመኖር አጋጣሚያቸውን እንዳጡ አስታውስ። ስለዚህ ቤዛው ከታጣው ነገር ጋር ተመጣጣኝ ዋጋ ሊኖረው ይገባል። (1 ጢሞ. 2:6) ቤዛውን መክፈል የሚችለው (1) ፍጹም የሆነ፣ (2) በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ ያለው እንዲሁም (3) ይህን ሕይወቱን ለእኛ ሲል ለመተው ወይም መሥዋዕት ለማድረግ ፈቃደኛ የሆነ ለአካለ መጠን የደረሰ ወንድ ብቻ ነው። ኢየሱስ የቤዛውን ዋጋ መክፈል የቻለባቸውን ሦስት ምክንያቶች እንመልከት። (1) ፍጹም ነበር፤ “ምንም ኃጢአት አልሠራም።” (1 ጴጥ. 2:22) (2) በዚህም የተነሳ በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ ነበረው። (3) ለእኛ ሲል ለመሞትና ሕይወቱን አሳልፎ ለመስጠት ፈቃደኛ ሆኗል።—ዕብ. 10:9፤ w25.02 4-5 አን. 11-12

ዓርብ፣ ሐምሌ 17

አምላክ መንፈሱን ቆጥቦ አይሰጥም።—ዮሐ. 3:34

ይሖዋ ይወድሃል እንዲሁም የቤተሰቡ ክፍል እንድትሆን ይፈልጋል። ለመጠመቅ ስትል የምትታገለው ነገር ምንም ይሁን ምን ይህ እውነታ አይቀየርም። ኢየሱስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩ ደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ብሏቸዋል፦ “የሰናፍጭ ቅንጣት የምታክል እምነት ካላችሁ ይህን ተራራ ‘ከዚህ ተነስተህ ወደዚያ ሂድ’ ብትሉት ይሄዳል፤ የሚሳናችሁም ነገር አይኖርም።” (ማቴ. 17:20) ኢየሱስ ይህን ሲል የሰሙት ሰዎች እሱን ካወቁት ገና ጥቂት ዓመታቸው ነው፤ በመሆኑም እምነታቸው ገና በእንጭጩ ነበር። በመሆኑም ኢየሱስ ጠንካራ እምነት ማዳበር ከቻሉ ይሖዋ እንደ ተራራ ያሉ እንቅፋቶችን ለመወጣት እንደሚረዳቸው እያረጋገጠላቸው ነው። ይሖዋ አንተንም እንዲህ እንድታደርግ ይረዳሃል! እንዳትጠመቅ እንቅፋት የሆነብህን ነገር ለይተህ አውቀሃል? ከሆነ ዛሬ ነገ ሳትል እንቅፋቱን ለማስወገድ እርምጃ ውሰድ። ራስህን ለይሖዋ ወስነህ ለመጠመቅ እንድትነሳሳ እንመኛለን። ይህ ፈጽሞ የማትቆጭበት ውሳኔ ነው! w25.03 7 አን. 18-20

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 18

ይሖዋ ከጎኔ ነው፤ አልፈራም።—መዝ. 118:6

ሕያው የሆነው አምላክ ሊረዳን ዝግጁ እንደሆነ ካስታወስን ፈተናዎችን በተሳካ ሁኔታ መወጣት እንችላለን። ይሖዋ ቀደም ሲል ያደረጋቸውን ነገሮች መመርመራችን በዚህ እውነታ ላይ ያለንን እምነት ያጠናክርልናል። (ኢሳ. 37:17, 33-37) በተጨማሪም ይሖዋ በዘመናችን ያሉ ወንድሞችና እህቶችን የረዳቸው እንዴት እንደሆነ የሚያሳዩ jw.org ላይ የወጡ ዘገባዎችን ተመልከት። ከዚህም ሌላ ይሖዋ ለአንተ ሲል እርምጃ የወሰደባቸውን ጊዜያት አስታውስ። እርግጥ አስደናቂ ተሞክሮ ማስታወስ አትችል ይሆናል። ያም ቢሆን ይሖዋ በሕይወትህ ውስጥ ብዙ ነገሮችን እንዳደረገልህ የተረጋገጠ ነው። አንተን ወደ ራሱ በመሳብ ከእሱ ጋር ወዳጅነት እንድትመሠርት አድርጎሃል። (ዮሐ. 6:44) ከዚህ በፊት ጸሎትህን የመለሰልህ፣ በትክክለኛው ጊዜ የሚያስፈልግህን እርዳታ የሰጠህ ወይም አንድን አስቸጋሪ ሁኔታ ለመቋቋም የረዳህ እንዴት እንደሆነ ለማስታወስ እንዲረዳህ ለምን አትጠይቀውም? እንዲህ ባሉ ተሞክሮዎች ላይ ማሰላሰልህ ይሖዋ አንተን መርዳቱን እንደሚቀጥል ያለህን እምነት ያጠናክርልሃል። w24.06 21 አን. 8

እሁድ፣ ሐምሌ 19

ሁሉም ኃጢአት ስለሠሩም ሞት ለሰው ሁሉ ተዳረሰ።—ሮም 5:12

ምንም ነገር ከይሖዋ እንዲያርቀን ላለመፍቀድ ቁርጥ ውሳኔ አድርገን ይሆናል። ያም ቢሆን ፍጹማን ስላልሆንን በፈተና ልንሸነፍ እንችላለን። (ሮም 7:21-23) ሳናስበው፣ የተሳሳተ ጎዳና መከተል አጓጊ መስሎ እንዲታየን የሚያደርግ ሁኔታ ውስጥ ልንገባ እንችላለን። ለይሖዋና ለልጁ ያለንን ታማኝነት መጠበቅ ከፈለግን ኢየሱስ በኃጢአት ፈተና እንዳንወድቅ ራሳችንን እንድንጠብቅ የሰጠውን ምክር መከተል ይኖርብናል። ሁላችንም ኃጢአት የመፈጸም ዝንባሌ ይፈታተነናል። ሆኖም እያንዳንዳችን ደካማ የሆንበት አቅጣጫ ይለያያል፤ ስለዚህ የሚፈትነን ነገር የተለያየ ነው። ለምሳሌ አንዳንዶች እንደ ፆታ ብልግና ያለ ከባድ ኃጢአት ለመፈጸም ከሚያድርባቸው ግፊት ጋር ይታገላሉ። ሌሎች ደግሞ እንደ ማስተርቤሽን ወይም ፖርኖግራፊ እንደመመልከት ያሉ ርኩስ ልማዶችን ለመፈጸም ይፈተናሉ። ሰውን እንደመፍራት፣ በራስ እንደመመራት ወይም እንደ ቁጣ ካሉ ዓለማዊ አስተሳሰቦች ጋር የሚታገሉም አሉ። w24.07 14 አን. 3፤ 15 አን. 5

ሰኞ፣ ሐምሌ 20

ከልክ በላይ በሐዘን እንዳይዋጥ በደግነት ይቅር ልትሉትና ልታጽናኑት ይገባል።—2 ቆሮ. 2:7

አንድ ግለሰብ እውነተኛ ንስሐ ከገባ በኋላ ሽማግሌዎቹ ወደ ጉባኤው እንዳይመለስ ቢከለክሉት ወይም ደግሞ ከተመለሰ በኋላ ጉባኤው ለእሱ ፍቅር ለማሳየት ፈቃደኛ ባይሆን ምን እንደሚከሰት ለማሰብ ሞክር። ግለሰቡ “ከልክ በላይ በሐዘን” ይዋጣል። ምንም ተስፋ እንደሌለው ሊሰማው ይችላል። ከአምላክ ጋር ያለውን ዝምድና ለማደስ ጥረት ማድረጉን ሊያቆምም ይችላል። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ በጉባኤው ውስጥ ያሉ ሌሎች ወንድሞችና እህቶች ንስሐ የገባውን ኃጢአተኛ ይቅር ለማለት ፈቃደኛ ካልሆኑ እነሱ ራሳቸው ከአምላክ ጋር ያላቸውን ወዳጅነት ሊያበላሹ ይችላሉ። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ንስሐ ለገቡ ኃጢአተኞች ምሕረት የሚያሳየውን ይሖዋን ሳይሆን ጨካኝና ምሕረት የለሽ የሆነውን ሰይጣንን መምሰል ይሆንባቸዋል። እንዲህ ካደረጉ፣ ዲያብሎስ ግለሰቡን በመንፈሳዊ ለማጥፋት የሚጠቀምበት መሣሪያ ሊሆኑ ይችላሉ።—2 ቆሮ. 2:10, 11፤ ኤፌ. 4:27፤ w24.08 17 አን. 7, 10-11

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 21

ወደ ላይ በወጣ ጊዜ [ሰዎችን] ስጦታ አድርጎ ሰጠ።—ኤፌ. 4:8

ክርስቶስ ኢየሱስ በሌላ መንገድ የሚያገለግሉ ‘ስጦታ የሆኑ ሰዎችንም’ ሰጥቷል። በኢየሩሳሌም የነበሩት ሽማግሌዎች በእሱ አመራር ሥር ሆነው ጳውሎስን፣ በርናባስንና ሌሎችን ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች አድርገው ልከዋቸው ነበር። (ሥራ 11:22) ለምን? ዓላማው የጉባኤ አገልጋዮችና ሽማግሌዎች ከሚሾሙበት ምክንያት ጋር ተመሳሳይ ነው፦ ጉባኤዎችን ማነጽ። (ሥራ 15:40, 41) የወረዳ የበላይ ተመልካቾች ሁልጊዜ ጉዞ ላይ ናቸው። አንዳንዶቹ ከአንዱ ጉባኤ ወደ ሌላው ጉባኤ ለመሄድ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን መጓዝ ያስፈልጋቸዋል። አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች በየሳምንቱ የተለያዩ ንግግሮችን ያቀርባል፤ እረኝነት ያደርጋል፤ እንዲሁም የአቅኚዎች ስብሰባ፣ የሽማግሌዎች ስብሰባና የስምሪት ስብሰባዎችን ይመራል። ንግግሮችን ይዘጋጃል፤ እንዲሁም የወረዳ ስብሰባዎችንና የክልል ስብሰባዎችን ያደራጃል። በአቅኚዎች ትምህርት ቤት ላይ ያስተምራል፤ በወረዳው ውስጥ ካሉ አቅኚዎች ጋር የሚደረገውን ልዩ ስብሰባ ያደራጃል፤ እንዲሁም ቅርንጫፍ ቢሮው የሚሰጠውን ሌሎች ኃላፊነቶች ይወጣል፤ እነዚህ ኃላፊነቶች አንዳንድ ጊዜ አስቸኳይ ሊሆኑ ይችላሉ። w24.10 21 አን. 12-13

ረቡዕ፣ ሐምሌ 22

በደላቸውን ይቅር እላለሁና፤ ኃጢአታቸውንም ከእንግዲህ አላስታውስም።—ኤር. 31:34

ነቢዩ ኤርምያስ፣ ይሖዋ በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ያለውን ሐሳብ እንደተናገረ ጽፏል። ሐዋርያው ጳውሎስም ይህን ሐሳብ በመጥቀስ “ኃጢአታቸውንም ከእንግዲህ ወዲህ አላስታውስም” ሲል ጽፏል። (ዕብ. 8:12) ይሁንና ይህ ሲባል ምን ማለት ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ማስታወስ” ወይም “ማሰብ” የሚለው ቃል አንድን ነገር ወደ አእምሮ ማምጣትን ብቻ አያመለክትም። ከዚህ ይልቅ እርምጃ መውሰድንም ያካትታል። ከኢየሱስ አጠገብ የተሰቀለው ወንጀለኛ “ኢየሱስ ሆይ፣ ወደ መንግሥትህ ስትመጣ አስበኝ” በማለት ጠይቆታል። (ሉቃስ 23:42, 43) ይህን ሲል፣ ኢየሱስ በዚያ ወቅት ስለ እሱ እንዲያስብ መጠየቁ ብቻ አይደለም። ኢየሱስ የሰጠው ምላሽ፣ ወንጀለኛውን በማስነሳት እርምጃ እንደሚወስድ ይጠቁማል። ስለዚህ ይሖዋ ኃጢአታችንን አያስታውስም ሲባል በኃጢአታችን ምክንያት እርምጃ አይወስድብንም ማለት ነው። አንድን ኃጢአት ይቅር ካለን በኋላ ወደፊት በዚያ ኃጢአት የተነሳ አይቀጣንም። w25.02 10-11 አን. 14-15

ሐሙስ፣ ሐምሌ 23

እጅግ ቅዱስ ስለሆነው አምላክ [ማወቅ] ማስተዋል ነው።—ምሳሌ 9:10

እውነተኛ ማስተዋል የሚገኘው የይሖዋን ባሕርያት፣ ዓላማውን እንዲሁም እሱ የሚወዳቸውንና የሚጠላቸውን ነገሮች ከማወቅ ነው። ‘ስለ ይሖዋ ከማውቀው ነገር አንጻር እሱን የሚያስደስተው ውሳኔ የትኛው ነው?’ እያልክ ራስህን ጠይቅ። (ኤፌ. 5:17) አንዳንድ ጊዜ፣ ይሖዋን ለማስደሰት ስንል በዙሪያችን ያሉትን ሰዎች የሚያሳዝን ውሳኔ ማድረግ ሊኖርብን ይችላል። ለምሳሌ ያህል አንዳንድ ወላጆች በአሳቢነት ተነሳስተው ሴት ልጃቸው ሀብታም ባል እንድታገባ ጫና ያሳድሩባት ይሆናል፤ ሆኖም ግለሰቡ በመንፈሳዊ ጠንካራ ላይሆን ይችላል። ልጃቸው የተመቻቸ ሕይወት እንድትመራ መፈለጋቸው የሚያስገርም ነገር አይደለም። ሆኖም ‘ይህ ሰው መንፈሳዊነቴን እንዳጠናክር ይረዳኛል?’ ብላ ራሷን መጠየቅ ይኖርባታል። ይሖዋ ስለዚህ ጉዳይ ምን አመለካከት አለው? ማቴዎስ 6:33 መልሱን ይሰጠናል። ይህ ጥቅስ ክርስቲያኖች ‘ከሁሉ አስቀድመው የአምላክን መንግሥትና ጽድቁን መፈለግ’ እንዳለባቸው ይናገራል። ወላጆቻችንንም ሆነ በማኅበረሰባችን ውስጥ ያሉትን ሰዎች የምናከብር ቢሆንም ዋነኛው ፍላጎታችን ይሖዋን ማስደሰት ነው። w25.01 17 አን. 9-10

ዓርብ፣ ሐምሌ 24

ጌታ አጠገቤ ቆሞ ኃይል ሰጠኝ።—2 ጢሞ. 4:17

ዛሬም ተቃውሞ እያለም በቅንዓት መስበካችንን ለመቀጠል የይሖዋ እርዳታ ያስፈልገናል። (ራእይ 12:17) ታዲያ ይሖዋ እንደሚደግፍህ መተማመን የምትችለው ለምንድን ነው? በዮሐንስ ምዕራፍ 17 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን የኢየሱስ ጸሎት ተመልከት። ኢየሱስ ሐዋርያቱን እንዲጠብቃቸው ይሖዋን ለምኗል፤ ይሖዋም ይህን ልመናውን ሰምቶታል። የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ዘገባ፣ ሐዋርያቱ ስደት እያለም በቅንዓት መስበካቸውን እንዲቀጥሉ ይሖዋ እንዴት እንደረዳቸው ያትታል። ኢየሱስ ጸሎቱ ላይ ይሖዋ እንዲጠብቃቸው የለመነው ሐዋርያቱን ብቻ ሳይሆን የእነሱን መልእክት ሰምተው እምነት የሚጥሉትን ሰዎችም ጭምር ነው። ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንተም ትገኝበታለህ። ይሖዋ ለኢየሱስ ልመና ምላሽ መስጠቱን ቀጥሏል፤ ሐዋርያቱን እንደረዳቸው ሁሉ አንተንም ይረዳሃል። (ዮሐ. 17:11, 15, 20) ወደ ፍጻሜው እየተጠጋን ስንሄድ ምሥራቹን መስበክ ከባድ እየሆነብን ሊመጣ ይችላል። ያም ቢሆን የሚያስፈልገንን ድጋፍ ሁሉ እናገኛለን።—ሉቃስ 21:12-15፤ w25.03 18 አን. 13-14

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 25

አገልጋዮቼ ከልባቸው ደስታ የተነሳ እልል ይላሉ።—ኢሳ. 65:14

የአምላክ አገልጋዮች ልባቸው በአድናቆት ስለሚሞላ በደስታ “እልል ይላሉ።” በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙት የሚያንጹ እውነቶችና ይሖዋ ቃል የገባልን ነገሮች እንዲሁም በክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ የተመሠረተው ጠንካራ ተስፋችን ‘ልባችን በደስታ’ እንዲሞላ ያደርጋሉ። ስለ እነዚህ ነገሮች ስናወራ እውነተኛ ደስታ እናገኛለን። (መዝ. 34:8፤ 133:1-3) በይሖዋ ሕዝቦች መካከል ያለው ፍቅርና አንድነት የመንፈሳዊው ገነት ሁለት ዋነኛ መገለጫዎች ናቸው። ይህ “የአንድነት ማሰሪያ” በአዲሱ ዓለም የሚኖረው ሕይወት ምን ዓይነት እንደሚሆን ይጠቁመናል፤ በዚያ ወቅት የይሖዋ ሕዝቦች ከአሁኑም ይበልጥ ፍቅርና አንድነት ይኖራቸዋል። (ቆላ. 3:14) እውነተኛ ደስታና እርካታ ማግኘት የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ይህን መንፈሳዊ ገነት መቅመስ አለበት። ዓለም ለይሖዋ አገልጋዮች ያለው አመለካከት ምንም ይሁን ምን፣ በይሖዋ ዓለም አቀፋዊ ቤተሰብ መካከል ግን የተከበረ ስም አላቸው።—ኢሳ. 65:15፤ w24.04 21 አን. 7-8

እሁድ፣ ሐምሌ 26

እርስ በርስ ተናነጹ።—1 ተሰ. 5:11

ትዳር መመሥረት የሚፈልጉ ክርስቲያኖችን መርዳት የምንችለው እንዴት ነው? አንዱ መንገድ ስለምንናገረው ነገር ጠንቃቆች በመሆን ነው። (ኤፌ. 4:29) ራሳችንን እንዲህ ብለን ልንጠይቅ እንችላለን፦ ‘ማግባት በሚፈልጉ ክርስቲያኖች ላይ አጉል ቀልድ እቀልድባቸዋለሁ? አንድ ነጠላ ወንድምና አንዲት ነጠላ እህት ሲያወሩ ስላየሁ ብቻ በመካከላቸው የሆነ ነገር እንዳለ ይሰማኛል?’ (1 ጢሞ. 5:13) ከዚህም በተጨማሪ ያላገቡ ክርስቲያኖች ትዳር ባለመመሥረታቸው የተነሳ የሆነ የጎደላቸው ነገር እንዳለ እንዲሰማቸው ማድረግ አንፈልግም። ከዚህ ይልቅ፣ ያላገቡ ክርስቲያኖችን የምናመሰግንባቸውን አጋጣሚዎች ብንፈልግ ምንኛ የተሻለ ነው! አንድ ወንድምና አንዲት እህት ጥሩ ባልና ሚስት ሊወጣቸው እንደሚችል ቢሰማህስ? መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሌሎች ስሜት እንድናስብ ይመክረናል። (ሮም 15:2) በርካታ ያላገቡ ክርስቲያኖች ሌሎች ለትዳር የሚሆን ሰው እንዲያስተዋውቋቸው አይፈልጉም፤ ደግሞም ፍላጎታቸውን ልናከብርላቸው ይገባል። (2 ተሰ. 3:11) ሌሎች ግን እገዛ ቢያገኙ ደስ ይላቸው ይሆናል፤ ሆኖም ሳንጠየቅ ለመርዳት መሞከር የለብንም።—ምሳሌ 3:27፤ w24.05 24-25 አን. 14-15

ሰኞ፣ ሐምሌ 27

የእነሱ ዓለት እንደ እኛ ዓለት አይደለም።—ዘዳ. 32:31

በምንኖርበት ዓለም ውስጥ የሚከሰቱ ያልተጠበቁ ሁኔታዎች ሕይወታችንን በከፍተኛ ደረጃ ወይም ሙሉ በሙሉ ሊቀይሩት ይችላሉ። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥመን እርዳታ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ዞር ማለት በመቻላችን ምንኛ አመስጋኞች ነን! የእሱን ድጋፍ በሕይወታችን ስናይ ‘ይሖዋ ሕያው እንደሆነ’ እርግጠኞች እንሆናለን። (መዝ. 18:46) ነገር ግን ዳዊት ይህን ሐሳብ ከተናገረ በኋላ አምላክን “ዓለቴ” በማለት ጠርቶታል። ዳዊት ይሖዋን ግዑዝ ከሆነ ዓለት ጋር ያመሳሰለው ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ያሉትን አንዳንድ ባሕርያት ለመግለጽ “ዓለት” የሚለውን ቃል ይጠቀማል። ይህ ቃል በአብዛኛው የሚገኘው ይሖዋ አቻ የሌለው አምላክ መሆኑን በሚገልጹ ጥቅሶች ላይ ነው። ይሖዋ “ዓለት” ተብሎ የተጠራበት የመጀመሪያው ጥቅስ ዘዳግም 32:4 ነው። ሐና በጸሎቷ ላይ “እንደ አምላካችን ያለ ዓለት የለም” ብላለች። (1 ሳሙ. 2:2) ዕንባቆም ይሖዋን “ዓለቴ” ብሎ ጠርቶታል። (ዕን. 1:12) የመዝሙር 73 ጸሐፊ አምላክን “የልቤ ዓለት” በማለት ጠርቶታል። (መዝ. 73:26) ይሖዋም ቢሆን ራሱን ዓለት ብሎ የጠራበት ጊዜ አለ።—ኢሳ. 44:8፤ w24.06 26 አን. 1, 3

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 28

[ኢዮሳፍጥ] ይሖዋን በሙሉ ልቡ [ፈልጓል]።—2 ዜና 22:9

ይሖዋን ያስደሰቱት የእስራኤል ነገሥታት እሱን በሙሉ ልባቸው አገልግለውታል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኢዮስያስ ሲናገር “በሙሉ ልቡ . . . ወደ ይሖዋ የተመለሰ እንደ እሱ ያለ ንጉሥ ከእሱ በፊት አልነበረም” ይላል። (2 ነገ. 23:25) በስተ እርጅናው መጥፎ ነገር ስለሠራው ስለ ሰለሞንስ ምን ማለት ይቻላል? “[ልቡ] በአምላኩ በይሖዋ ዘንድ ሙሉ አልነበረም።” (1 ነገ. 11:4) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ታማኝ ንጉሥ ስላልነበረው ስለ አብያም ሲናገር “[ልቡ] በአምላኩ በይሖዋ ዘንድ ሙሉ አልነበረም” ይላል። (1 ነገ. 15:3) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙውን ጊዜ “ልብ” የሚለው ቃል የአንድን ሰው ምኞት፣ አስተሳሰብ፣ ዝንባሌ፣ አመለካከት፣ ችሎታ፣ ተነሳሽነትና ግብ ጨምሮ ውስጣዊ ማንነቱን በሙሉ ለማመልከት ተሠርቶበታል። ታዲያ ይሖዋን በሙሉ ልብ ማገልገል ሲባል ምን ማለት ነው? ልቡ ሙሉ የሆነ ሰው ይሖዋን የሚያመልከው በዘልማድ አይደለም። ከዚህ ይልቅ በመላው ሕይወቱ በፍቅርና በታማኝነት ተነሳስቶ አምላክን ያገለግላል። w24.07 21 አን. 4-5

ረቡዕ፣ ሐምሌ 29

[የፈጸምኳቸውን] ስህተቶች ሁሉ አስወግድ።—መዝ. 51:9

ይሖዋ ኃጢአታችንን የሚደመስሰው እንዴት እንደሆነ ለመግለጽ ዘይቤያዊ አገላለጽ ተጠቅሟል። እንዲህ ብሏል፦ “በደልህን በደመና፣ ኃጢአትህንም ጥቅጥቅ ባለ ደመና እሸፍነዋለሁ።” (ኢሳ. 44:22) ይሖዋ ኃጢአታችንን ይቅር ሲል በደላችንን ጥቅጥቅ ባለ ደመና የመሸፈን ያህል ከእይታ ውጭ እንዲሆን ያደርገዋል ማለት ነው። ይህ ለእኛ ምን ትርጉም አለው? ይሖዋ ኃጢአታችንን ይቅር ካለን በኋላ የኃጢአቱን ቆሻሻ ዕድሜ ልካችንን ይዘነው እንደምንኖር ሊሰማን አይገባም። በኢየሱስ ክርስቶስ ደም አማካኝነት ዕዳችን ሙሉ በሙሉ ተሰርዞልናል። የዕዳችን መዝገብ እንኳ ሊታይ አይችልም። ለኃጢአታችን ንስሐ ስንገባ እንዲህ ያለውን እውነተኛ ይቅርታ ከይሖዋ እናገኛለን። በተጨማሪም የይሖዋ ምሕረት ከእሱ ጋር ጥሩ ዝምድና እንዲኖረን ያስችለናል። በጥፋተኝነት ስሜት እንዳንዋጥም ይረዳናል። w25.02 10 አን. 11-14

ሐሙስ፣ ሐምሌ 30

አምላክ በደግነቱ ወደ ንስሐ ሊመራህ እየሞከረ [ነው]።—ሮም 2:4

በኮሚቴ ውስጥ የሚያገለግሉ ሽማግሌዎች የጉባኤውን ንጽሕና እንዲያስጠብቁ ይሖዋ ይጠብቅባቸዋል። (1 ቆሮ. 5:7) የሚቻል ከሆነ ደግሞ ጥፋት የሠሩት ሰዎች ንስሐ እንዲገቡ ይፈልጋሉ። ለዚህም ሲባል ሽማግሌዎች አዎንታዊ አመለካከት ለመያዝ ጥረት ያደርጋሉ። ለምን? “እጅግ አፍቃሪና መሐሪ” የሆነውን ይሖዋን መምሰል ስለሚፈልጉ ነው። (ያዕ. 5:11) ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ ያለውን መንፈስ ያሳየው እንዴት እንደሆነ ልብ በል። እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የተወደዳችሁ ልጆቼ፣ እነዚህን ነገሮች የምጽፍላችሁ ኃጢአት እንዳትሠሩ ነው። ማንም ኃጢአት ቢሠራ ግን በአብ ዘንድ ረዳት አለን፤ እሱም ጻድቅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።” (1 ዮሐ. 2:1) የሚያሳዝነው፣ አንዳንድ ጊዜ ኃጢአት የፈጸመው ክርስቲያን ንስሐ ለመግባት ፈቃደኛ ላይሆን ይችላል። ሁኔታው እንደዚያ ከሆነ፣ ከጉባኤው መወገድ ይኖርበታል። w24.08 25 አን. 19-20

ዓርብ፣ ሐምሌ 31

በእምነት ጸንታችሁ ቁሙ።—1 ቆሮ. 16:13

የምታከናውነውን ነገር ከሌሎች ጋር ለማወዳደር ትፈተን ይሆናል። ሆኖም እንዲህ ልታደርግ አይገባም። ለምን? ምክንያቱም ይሖዋ ሰዎችን በዚህ መልኩ አያወዳድርም። (ገላ. 6:4) ለምሳሌ ማርያም ለኢየሱስ እጅግ ውድ የሆነና ጥሩ መዓዛ ያለው ዘይት ሰጥታው ነበር። (ዮሐ. 12:3-5) ድሃዋ መበለት ደግሞ በቤተ መቅደሱ መዋጮ ያደረገችው በጣም አነስተኛ ዋጋ ያላቸውን ሁለት ትናንሽ ሳንቲሞች ነው። (ሉቃስ 21:1-4) ሆኖም ኢየሱስ እነዚህን ሴቶች አላወዳደራቸውም። ከዚህ ይልቅ ያተኮረው ሁለቱም ባሳዩት እምነት ላይ ነው። ኢየሱስ የአባቱ ፍጹም ነጸብራቅ ነው። የምታከናውነው ነገር ለአንተ በጣም ትንሽ ቢመስልህም እንኳ ለይሖዋ ባለህ ፍቅርና ታማኝነት ተነሳስተህ እስካደረግከው ድረስ በእሱ ዘንድ ትልቅ ዋጋ አለው። ሁላችንም አልፎ አልፎ ጥርጣሬ ያድርብናል። ይሁንና አስተማማኝና እውነተኛ የሆነው የአምላክ ቃል ጥርጣሬያችንን ለማሸነፍ ይረዳናል። ጥርጣሬህን በእምነት ተካው። ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ትኩረት ይሰጥሃል። የከፈልካቸውን መሥዋዕቶች ያደንቃል፤ ወሮታ እንደሚከፍልህም ቃል ገብቷል። ይሖዋ ሁሉንም ታማኝ አገልጋዮቹን ይወዳቸዋል እንዲሁም ትኩረት ይሰጣቸዋል። w24.10 25 አን. 3፤ 29 አን. 17-18

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2026)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2026 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ