ሰኔ
ሰኞ፣ ሰኔ 1
ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ጥሩ ነህና፤ ይቅር ለማለትም ዝግጁ ነህ።—መዝ. 86:5
አሁንም እንኳ ከክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት እየተጠቀምን ነው። ለምሳሌ ቤዛውን መሠረት በማድረግ ይሖዋ ኃጢአታችንን ይቅር ይለናል። ይሖዋ እኛን ይቅር የማለት ግዴታ የለበትም። ሆኖም ይቅር ሊለን ይፈልጋል። (መዝ. 103:3, 10-13) አንዳንዶች የይሖዋ ይቅርታ እንደማይገባቸው ይሰማቸው ይሆናል። እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ማናችንም ብንሆን የይሖዋ ይቅርታ አይገባንም። ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ሐዋርያ ተብሎ ሊጠራ እንደማይገባው’ ተገንዝቦ ነበር። ሆኖም “አሁን የሆንኩትን ለመሆን የበቃሁት በአምላክ ጸጋ ነው” ብሏል። (1 ቆሮ. 15:9, 10) ለኃጢአታችን ንስሐ ከገባን ይሖዋ ይቅር ይለናል። ለምን? ስለሚገባን ሳይሆን ስለሚወደን ነው። የዋጋ ቢስነት ስሜት የሚሰማህ ከሆነ ይሖዋ ቤዛውን ያዘጋጀው ኃጢአት ለሌለባቸው ሰዎች ሳይሆን ንስሐ ለገቡ ኃጢአተኞች መሆኑን አስታውስ።—ሉቃስ 5:32፤ 1 ጢሞ. 1:15፤ w25.01 26-27 አን. 3-4
ማክሰኞ፣ ሰኔ 2
ደግ ሰው ራሱን ይጠቅማል፤ ጨካኝ ሰው ግን በራሱ ላይ መከራ ያመጣል።—ምሳሌ 11:17
ሌሎች የሚናገሩትን ወይም የሚያደርጉትን ነገር መቆጣጠር አንችልም፤ ሆኖም የምንሰጠውን ምላሽ ለመቆጣጠር መሞከር እንችላለን። ብዙውን ጊዜ ከሁሉ የተሻለው ምላሽ ይቅር ማለት ነው። ለምን? ምክንያቱም ይሖዋን እንወደዋለን፤ እሱ ደግሞ ይቅር ባዮች እንድንሆን ይፈልጋል። ተቆጥተን ከቆየንና ይቅር ካላልን የሞኝነት እርምጃ ልንወስድ፣ ምናልባትም ጤንነታችንን ልንጎዳ እንችላለን። (ምሳሌ 14:17, 29, 30) ያደረብንን ቂም ስንተው ልባችን በምሬት እንዳይጎዳ እንጠብቀዋለን። በተጨማሪም ለራሳችን ስጦታ እንደሰጠን ሊቆጠር ይችላል፤ ጉዳዩን ረስተን ሕይወታችንን በደስታ መቀጠል እንችላለን። የተጎዳውን ስሜትህን ማከም የምትችለው እንዴት ነው? አንዱ መንገድ እስክታገግም ድረስ ለራስህ ጊዜ በመስጠት ነው። አንድ ሰው ከባድ የአካል ጉዳት ከደረሰበት፣ ሕክምና ከተደረገለት በኋላ ሰውነቱ እስኪያገግም ድረስ ጊዜ ያስፈልገዋል። በተመሳሳይም፣ አንድን ሰው ከልባችን ይቅር ለማለት ዝግጁ ከመሆናችን በፊት ስሜታችን እንዲያገግም ጊዜ መስጠት ሊያስፈልገን ይችላል። (መክ. 3:3፤ 1 ጴጥ. 1:22) ወደ ይሖዋ በመጸለይ ይቅር ባይ ለመሆን እንዲረዳህ ጠይቀው። w25.02 15-16 አን. 8-11
ረቡዕ፣ ሰኔ 3
ጠንካራ ምግብ [ለጎልማሳ] ሰዎች ነው።—ዕብ. 5:14
ከመሠረታዊ ትምህርቶች መካከል ስለ ንስሐ፣ ስለ እምነት፣ ስለ ጥምቀትና ስለ ትንሣኤ የሚናገሩት ትምህርቶች ይገኙበታል። (ዕብ. 6:1, 2) እነዚህ ትምህርቶች የክርስትና መሠረት ናቸው። በዚህም የተነሳ በጴንጤቆስጤ ዕለት ሐዋርያው ጴጥሮስ ሕዝቡን ባስተማረበት ወቅት ስለ እነዚህ ነገሮች ተናግሯል። (ሥራ 2:32-35, 38) የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ለመሆን እነዚህን መሠረታዊ ትምህርቶች መቀበል ይኖርብናል። ለምሳሌ ጳውሎስ፣ የትንሣኤን ትምህርት የማይቀበል ሁሉ ክርስቲያን ሊባል እንደማይችል ተናግሯል። (1 ቆሮ. 15:12-14) ሆኖም የእውነትን መሠረታዊ እውቀት በማግኘት ብቻ ረክተን መቀመጥ የለብንም። መሠረታዊ ከሆኑት ትምህርቶች በተለየ መልኩ ጠንካራ ምግብ የይሖዋን ሕጎች ብቻ ሳይሆን መሠረታዊ ሥርዓቶቹንም ያካትታል፤ እነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች የእሱን አስተሳሰብ ለመረዳት ያግዙናል። እንዲህ ካለው ምግብ ለመጠቀም የአምላክን ቃል ማጥናትና ማሰላሰል እንዲሁም አቅማችን በፈቀደ መጠን በሥራ ላይ ማዋል ይኖርብናል። እንዲህ ስናደርግ ይሖዋን የሚያስደስቱ ውሳኔዎችን ለማድረግ ራሳችንን እናሠለጥናለን። w24.04 5 አን. 12-13
ሐሙስ፣ ሰኔ 4
የነነዌ ሰዎች . . . በፍርድ ወቅት [ይነሳሉ]።—ማቴ. 12:41
አምላክ የነነዌ ሰዎች ‘ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር ለይተው እንደማያውቁ’ ለዮናስ ነግሮታል። (ዮናስ 1:1, 2፤ 3:10፤ 4:9-11) ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ ስለ ይሖዋ ፍትሕና ምሕረት ለማስተማር የእነሱን ታሪክ ምሳሌ አድርጎ ተጠቅሞበታል። የነነዌ ሰዎች ‘በፍርድ ወቅት ይነሳሉ’ ሲባል ምን ማለት ነው? ኢየሱስ ወደፊት ‘የፍርድ ትንሣኤ’ እንደሚኖር ተናግሯል። (ዮሐ. 5:29) ይህን ሲል “ጻድቃንም ሆኑ ጻድቃን ያልሆኑ ሰዎች” ስለሚነሱበት የሺህ ዓመት ግዛቱ መናገሩ ነበር። (ሥራ 24:15) ጻድቃን ያልሆኑ ሰዎች የሚያገኙት ትንሣኤ ‘የፍርድ ትንሣኤ’ ነው። ይህም ሲባል ይሖዋና ኢየሱስ የእነዚህን ሰዎች ምግባር እንዲሁም ለሚሰጣቸው መለኮታዊ ትምህርት የሚሰጡትን ምላሽ ይከታተላሉ ማለት ነው። ትንሣኤ ያገኘ አንድ የነነዌ ሰው በንጹሕ አምልኮ ለመካፈል ፈቃደኛ ካልሆነ ‘ጥፋት ይገባዋል’ የሚል ፍርድ ይተላለፍበታል። (ኢሳ. 65:20) ይሖዋን በታማኝነት ለማገልገል የሚመርጡ ሁሉ ግን አዎንታዊ ፍርድ ይሰጣቸዋል። ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ ይኖራቸዋል!—ዳን. 12:2፤ w24.05 5 አን. 13-14
ዓርብ፣ ሰኔ 5
የሰው ልጅ የመጣው የጠፋውን ለመፈለግና ለማዳን ነው።—ሉቃስ 19:10
ኢየሱስ የአባቱን ምሕረት ፍጹምና ሕያው በሆነ መንገድ አንጸባርቋል። (ዮሐ. 14:9) መሐሪና ሩኅሩኅ የሆነው አባቱ ሰዎችን እንደሚወድ እንዲሁም ከኃጢአት ጋር በሚያደርጉት ውጊያ አሸናፊዎች እንዲሆኑ ሊረዳቸው እንደሚፈልግ በንግግሩም ሆነ በተግባሩ አሳይቷል። ኢየሱስ ኃጢአተኛ የሆኑ ሰዎች መንገዳቸውን ለማስተካከልና እሱን ለመከተል እንዲነሳሱ ረድቷቸዋል። (ሉቃስ 5:27, 28) ኢየሱስ ከፊቱ ምን እንደሚጠብቀው ያውቅ ነበር። አልፎ እንደሚሰጥና በእንጨት ላይ እንደሚሰቀል ለተከታዮቹ በተደጋጋሚ ነግሯቸዋል። (ማቴ. 17:22፤ 20:18, 19) የእሱ መሥዋዕት የዓለምን ኃጢአት እንደሚያስወግድ ያውቅ ነበር። በተጨማሪም ኢየሱስ ሕይወቱን አሳልፎ ከሰጠ በኋላ “ሁሉንም ዓይነት ሰዎች” ወደ ራሱ እንደሚስብ ተናግሯል። (ዮሐ. 12:32) ኃጢአተኛ የሆኑ የሰው ልጆች ኢየሱስን እንደ ጌታቸው አድርገው በመቀበልና የእሱን ፈለግ በመከተል ይሖዋን ማስደሰት ይችላሉ። እንዲህ ካደረጉ “ከኃጢአት ነፃ” ይወጣሉ። (ሮም 6:14, 18, 22፤ ዮሐ. 8:32) በመሆኑም ኢየሱስ ይህን አሰቃቂ ሞት በድፍረትና በፈቃደኝነት ተጋፍጧል።—ዮሐ. 10:17, 18፤ w24.08 5 አን. 11-12
ቅዳሜ፣ ሰኔ 6
አስቀድሞም ምሥራቹ ለብሔራት ሁሉ መሰበክ አለበት።—ማር. 13:10
በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን እውነት ለመጀመሪያ ጊዜ ስትሰማ ምን ተሰምቶህ እንደነበር ለማስታወስ ሞክር። የሰማዩ አባትህ እንደሚወድህ፣ አገልጋዮቹን ያቀፈውን ቤተሰብ እንድትቀላቀል እንደሚፈልግ፣ መከራንና ሥቃይን ለማስወገድ ቃል እንደገባ፣ በሞት ያጣሃቸው ወዳጅ ዘመዶችህ በአዲሱ ዓለም ውስጥ ከሞት ተነስተው ልታገኛቸው እንደምትችል እንዲሁም ሌሎች ብዙ ነገሮችን ተማርክ። (ማር. 10:29, 30፤ ዮሐ. 5:28, 29፤ ሮም 8:38, 39፤ ራእይ 21:3, 4) እነዚህ እውነቶች ልብህን ነኩት። (ሉቃስ 24:32) የተማርከውን ነገር በጣም ስለወደድከው እነዚህን ውድ እውነቶች ለሌሎች ለመንገር ተነሳሳህ። (ከኤርምያስ 20:9 ጋር አወዳድር።) ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ያለን ፍቅር በልባችን ውስጥ ሥር ከሰደደ ዝም ማለት አንችልም። (ሉቃስ 6:45) በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ዓይነት ስሜት ይሰማናል። እነዚህ ደቀ መዛሙርት “ስላየነውና ስለሰማነው ነገር ከመናገር ወደኋላ ማለት አንችልም” ብለዋል። (ሥራ 4:20) እውነትን በጣም ስለምንወደው በተቻለ መጠን ለብዙ ሰዎች ልናካፍለው እንፈልጋለን። w24.05 15 አን. 5፤ 16 አን. 7
እሁድ፣ ሰኔ 7
ይሖዋን በደስታ አገልግሉት።—መዝ. 100:2
የይሖዋ ሕዝቦች እንደመሆናችን መጠን የምንሰብከው የሰማዩን አባታችንን ስለምንወደውና ሰዎች እሱን እንዲያውቁት መርዳት ስለምንፈልግ ነው። አንዳንዶች ግን በስብከቱ ሥራ መካፈል ያን ያህል አያስደስታቸውም። ለምን? አንዳንዶቹ ዓይናፋር ናቸው፤ እንዲሁም በራስ የመተማመን ስሜት ይጎድላቸዋል። ሌሎች ደግሞ ሳይጋበዙ ወደ ሰዎች ቤት መሄድ ይጨንቃቸዋል። አንዳንዶች በአገልግሎት ተቃውሞ ሊያጋጥመኝ ይችላል ብለው ይፈራሉ። በምንም ምክንያት ከሌሎች ጋር መጋጨት የማይፈልጉም ይኖራሉ። እነዚህ ወንድሞችና እህቶች ለማያውቁት ሰው ምሥራቹን መስበክ ይከብዳቸዋል። አንተስ እንዲህ ባሉ ስሜቶች የተነሳ ከአገልግሎትህ ደስታ ማግኘት ከብዶህ ያውቃል? እንዲህ የሚሰማህ ከሆነ ተስፋ አትቁረጥ። ፍርሃት የሚሰማህ መሆኑ ትሑት እንደሆንክና የሌሎችን ትኩረት መሳብ እንደማትፈልግ እንዲሁም ከሌሎች ጋር በሰላም መኖር እንደምትፈልግ የሚጠቁም ሊሆን ይችላል። ማንኛውም ሰው በተለይ ለሌሎች መልካም ነገር ለማድረግ ተነሳስቶ ሳለ አሉታዊ ምላሽ እንዲሰጠው አይፈልግም። የሰማዩ አባትህ የሚያጋጥሙህን ፈተናዎች በሙሉ ያውቃል፤ እንዲሁም ሊረዳህ ይፈልጋል።—ኢሳ. 41:13፤ w24.04 14 አን. 1-2
ሰኞ፣ ሰኔ 8
ልካቸውን በሚያውቁ ዘንድ . . . ጥበብ ትገኛለች።—ምሳሌ 11:2
መጽሐፍ ቅዱስን ስታነብ ያነበብከውን ነገር ሁሉ በአንድ ጊዜ ተግባራዊ ለማድረግ ከመሞከር ይልቅ ጥቂት ግቦችን ብቻ አውጣ። እንዲህ ልታደርግ ትችላለህ፦ ልትሠራባቸው የምትፈልጋቸውን ነገሮች ዘርዝረህ ጻፍ፤ ከዚያም አንዱን ወይም ሁለቱን ብቻ መርጠህ በመጀመሪያ በእነሱ ላይ ሥራ። የቀሩትን በጊዜ ሂደት ልትሠራባቸው ትችላለህ። ታዲያ ከየትኛው ብትጀምር ይሻላል? በቀላሉ ከምትደርስበት ግብ ልትጀምር ትችላለህ። ወይም ይበልጥ ማሻሻያ ልታደርግበት በሚገባው ግብ ልትጀምር ትችላለህ። ልትሠራበት የምትፈልገውን ግብ ከመረጥክ በኋላ ስለ ጉዳዩ በጽሑፎቻችን ላይ ምርምር አድርግ። ስለ ግብህ ጸልይ፤ ‘ለተግባር የሚያነሳሳ ፍላጎትም ሆነ ኃይል’ እንዲሰጥህ ይሖዋን ጠይቀው። (ፊልጵ. 2:13) ከዚያም የተማርከውን ተግባራዊ አድርግ። የመጀመሪያው ግብህ እንደተሳካልህ ስታይ በሌሎች ግቦችህ ላይ ለመሥራት ያለህ ፍላጎትም ይጨምራል። ደግሞም በአንድ የክርስቲያናዊ ሕይወት መስክ ወይም ባሕርይ ረገድ ማሻሻያ ስታደርግ በሌሎች አቅጣጫዎች ረገድ ማሻሻያ ማድረግ እየቀለለህ ይሄዳል። w24.09 6 አን. 13-14
ማክሰኞ፣ ሰኔ 9
በዚህ ጉዳይ ንጹሕ መሆናችሁን በሁሉም ረገድ አስመሥክራችኋል።—2 ቆሮ. 7:11
ቀደም ሲል የፈጸምከው ስህተት ሌሎችን በመጉዳቱ የተነሳ ትረበሽ ይሆናል። ታዲያ ምን ሊረዳህ ይችላል? የተፈጠረውን ችግር ለማስተካከል አቅምህ የፈቀደውን ሁሉ ለማድረግ ሞክር፤ ይህም ከልብ ይቅርታ መጠየቅን ይጨምራል። ይሖዋ የጎዳሃቸውን ሰዎች እንዲረዳቸው በጸሎት ጠይቀው። ይሖዋ፣ አንተም ሆንክ የጎዳሃቸው ሰዎች እንድትጸኑና ሰላማችሁ እንዲመለስላችሁ ሊረዳችሁ ይችላል። ካለፈው ስህተትህ ተማር፤ እንዲሁም ይሖዋ በመረጠው መንገድ እንዲጠቀምብህ ፈቃደኛ ሁን። ነቢዩ ዮናስን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ዮናስ፣ አምላክ ባዘዘው መሠረት ወደ ነነዌ ከመሄድ ይልቅ ወደ ተቃራኒው አቅጣጫ ሸሸ። ይሖዋ ለዮናስ ተግሣጽ ሰጥቶታል፤ እሱም ከስህተቱ ተምሯል። (ዮናስ 1:1-4, 15-17፤ 2:7-10) ይሖዋ በዮናስ ላይ ተስፋ አልቆረጠበትም። ወደ ነነዌ የሚሄድበት ሌላ አጋጣሚ ሰጠው። ዮናስም ወዲያውኑ ታዘዘ። ቀደም ሲል በሠራው ስህተት የተነሳ የተሰማው ጸጸት ይሖዋ የሰጠውን ኃላፊነት ከመቀበል እንዲያግደው አልፈቀደም።—ዮናስ 3:1-3፤ w24.10 8-9 አን. 10-11
ረቡዕ፣ ሰኔ 10
ኃጢአታችሁ እንዲደመሰስ ንስሐ ግቡ፣ ተመለሱም፤ ከይሖዋም ዘንድ የመታደስ ዘመን ይመጣላችኋል።—ሥራ 3:19
ይሖዋ ዕዳችንን ወይም ኃጢአታችንን መሰረዝ ብቻ ሳይሆን ይደመስሰዋል። አንድን ዕዳ ለመሰረዝ ከመዝገቡ ላይ ቁጥሩን መሰረዝ ይቻላል። ሆኖም የተሰረዘው ቁጥር አሁንም ከሥር ሊታይ ይችላል። መደምሰስ የሚለው ቃል ግን ከዚህ ያለፈ ነገርን ያመለክታል። ይህን ዘይቤያዊ አገላለጽ ለመረዳት፣ በጥንት ዘመን ሰዎች ለመጻፍ ይጠቀሙበት የነበረው ቀለም ከካርቦን፣ ከሙጫ እና ከውኃ የተሠራ እንደነበር ማስታወስ ይኖርብናል። አንድ ሰው በእርጥብ ስፖንጅ ጽሑፉን ሙልጭ አድርጎ ሊያጠፋው ይችላል። ስለዚህ ዕዳ “ተደምስሷል” ሲባል ሙሉ በሙሉ ጠፍቷል ማለት ነው። ቀደም ሲል ተጽፎ የነበረውን ጽሑፍ ጨርሶ ማየት አይቻልም። መዝገቡ ያልነበረ ያህል ይሆናል። ይሖዋ ኃጢአታችንን መሰረዝ ብቻ ሳይሆን ሙሉ በሙሉ እንደሚደመስሰው ማወቃችን ምንኛ የሚያጽናና ነው!—መዝ. 51:9፤ w25.02 10 አን. 11
ሐሙስ፣ ሰኔ 11
ተበሳጭተህ ክፉ ነገር አትሥራ።—መዝ. 37:8
ሌሎች በተሳሳተ መንገድ ሲረዱን ወይም ተገቢ ያልሆነ ነገር ሲያደርጉብን ይሖዋ እውነቱን እንደሚያውቅ እንተማመናለን። ይህን ማመናችን ኢፍትሐዊ ድርጊቶችን ለመቋቋም ይረዳናል፤ ምክንያቱም ይዋል ይደር እንጂ ይሖዋ ጉዳዩን እንደሚያስተካክል እናውቃለን። ጉዳዩን ለይሖዋ መተዋችን ቁጣና ጥላቻ በልባችን ውስጥ ሥር እንዳይሰድ ይረዳናል። እነዚህ ስሜቶች ተገቢ ያልሆነ ነገር እንድናደርግ፣ ደስታችንን እንድናጣ ብሎም ከይሖዋ ጋር ያለን ወዳጅነት እንዲበላሽ ሊያደርጉ ይችላሉ። እርግጥ ነው፣ መቼም ቢሆን የኢየሱስን ምሳሌ ፍጹም በሆነ መንገድ መከተል አንችልም። አንዳንድ ጊዜ፣ በኋላ ላይ የምንጸጸትበት ነገር ልንናገር ወይም ልናደርግ እንችላለን። (ያዕ. 3:2) በተጨማሪም የሚፈጸሙብን አንዳንድ ኢፍትሐዊ ድርጊቶች ለመቋቋም የሚያዳግት አካላዊ ወይም ስሜታዊ ጠባሳ ትተውብን ሊያልፉ ይችላሉ። እናንተም እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሟችሁ ከሆነ ይሖዋ ያላችሁበትን ሁኔታ እንደሚረዳ እርግጠኛ ሁኑ። በርካታ ኢፍትሐዊ ድርጊቶችን የተቋቋመው ኢየሱስም ስሜታችሁን ይረዳላችኋል። (ዕብ. 4:15, 16) ይሖዋ የፍትሕ መጓደልን እንድንቋቋም የሚረዱ ተግባራዊ ምክሮችን ስለሚሰጠን ምንኛ ደስተኞች ነን! w24.11 6 አን. 12-13
ዓርብ፣ ሰኔ 12
አምላክ የሚቀበለው ሥራማ እሱ በላከው ሰው ማመን ነው።—ዮሐ. 6:29
‘የዘላለም ሕይወት ለማግኘት’ በኢየሱስ ማመን አስፈላጊ ነው። (ዮሐ. 3:16-18, 36፤ 17:3) ብዙ አይሁዳውያን ኢየሱስ ‘አምላክ ስለሚቀበለው’ አዲስ “ሥራ” የሰጠውን ትምህርት አልተቀበሉም። “ታዲያ አይተን እንድናምንብህ ምን ተአምራዊ ምልክት ትፈጽማለህ?” ብለው ጠየቁት። (ዮሐ. 6:30) አባቶቻቸው በሙሴ ዘመን መና እንደወረደላቸው ተናገሩ። (ነህ. 9:15፤ መዝ. 78:24, 25) በግልጽ ማየት እንደሚቻለው አእምሯቸው አሁንም ያተኮረው የምግብ ፍላጎታቸውን በማርካት ላይ ብቻ ነበር። ኢየሱስ ሕይወት ሰጪ የሆነውን በመና የተመሰለውን ‘ከሰማይ የወረደ እውነተኛ ምግብ’ አስመልክቶ ሲናገር እንኳ ማብራሪያ አልጠየቁትም። (ዮሐ. 6:32) ያተኮሩት በምግብ ፍላጎታቸው ላይ ብቻ ስለነበር ኢየሱስ ሊያካፍላቸው እየሞከረ የነበረውን መንፈሳዊ እውነት መረዳት አልቻሉም። w24.12 5-6 አን. 10-11
ቅዳሜ፣ ሰኔ 13
ሁሉን ነገር የሠራው . . . አምላክ ነው።—ዕብ. 3:4
ልጆቻችሁ በሳይንስ ትምህርታቸው ወቅት የብዙ ነገሮች ቅርጽ የተመሠረተው በተፈጥሮ ሕጎች ላይ እንደሆነ መረዳታቸው አይቀርም። ለምሳሌ ዛፎችን ብንመለከት ግንዱ ቅርንጫፎችን ያወጣል፤ እያንዳንዱ ቅርንጫፍ ተጨማሪ ቅርንጫፎችን ያወጣል፤ እነዚህ ቅርንጫፎች ደግሞ ቀንበጦችን ያወጣሉ። እንዲህ ያለው ንድፍ በሌሎች ፍጥረታትም ላይ ይታያል። ታዲያ እነዚህን ውብ ንድፎች ያስገኘውን ሕግ የፈጠረው ማን ነው? ተፈጥሮ በዚህ መልኩ ሥርዓቱን እንዲጠብቅ ያስቻለው ማን ነው? ልጆቻችሁ በእነዚህ ነገሮች ላይ ይበልጥ ባሰላሰሉ መጠን ሁሉንም ነገሮች የፈጠረው አምላክ ስለመሆኑ ያላቸው እምነት መጠናከሩ አይቀርም። ከዚያም እንዲህ ብላችሁ ልትጠይቋቸው ትችላላችሁ፦ “የፈጠረን አምላክ ከሆነ ደስተኛ እንድንሆን የሚረዱንን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ይሰጠናል ብሎ መደምደሙ ምክንያታዊ አይሆንም?” በተጨማሪም እንዲህ ያለው ጠቃሚ መመሪያ የሚገኘው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደሆነ ልትጠቁሟቸው ትችላላችሁ። w24.12 16 አን. 8
እሁድ፣ ሰኔ 14
በመካከላችሁ የፆታ ብልግና እንደተፈጸመ ይወራል፤ እንዲህ ዓይነቱ ብልግና ደግሞ በአሕዛብ መካከል እንኳ ታይቶ አይታወቅም፤ ከአባቱ ሚስት ጋር የሚኖር ሰው አለ ተብሏል።—1 ቆሮ. 5:1
ሐዋርያው ጳውሎስ ንስሐ የማይገባ ኃጢአተኛ ከጉባኤው መወገድ እንዳለበት የሚገልጽ ደብዳቤ በመንፈስ መሪነት ጽፏል። (1 ቆሮ. 5:13) ታማኝ ክርስቲያኖች ከዚህ ግለሰብ ጋር ምን ዓይነት ግንኙነት ሊኖራቸው ይገባል? ጳውሎስ ከዚህ ሰው ጋር ‘መግጠማቸውን እንዲተዉ’ ነግሯቸዋል። ምን ማለቱ ነበር? ጳውሎስ ይህ መመሪያ ‘እንዲህ ካለው ሰው ጋር ምግብ እንኳ አለመብላትን’ እንደሚያካትት ገልጿል። (1 ቆሮ. 5:11) ከአንድ ሰው ጋር ተቀምጦ ምግብ መብላት ከእሱ ጋር ወዳጅነት ለመመሥረት በር ይከፍታል። ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው፣ ጳውሎስ ጉባኤው ከግለሰቡ ጋር መቀራረብ እንደሌለበት መመሪያ መስጠቱ ነበር። ይህም ጉባኤው ግለሰቡ ከሚያሳድረው በካይ ተጽዕኖ እንዲጠበቅ ያስችላል። (1 ቆሮ. 5:5-7) በተጨማሪም በጉባኤው ውስጥ ያሉ ወንድሞችና እህቶች ከግለሰቡ ጋር አለመቀራረባቸው ግለሰቡ ከይሖዋ መንገዶች ምን ያህል እንደራቀ እንዲገነዘብና ኀፍረት ተሰምቶት ንስሐ እንዲገባ ሊያነሳሳው ይችላል። w24.08 15 አን. 4-5
ሰኞ፣ ሰኔ 15
አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ . . . አንድያ ልጁን ሰጥቷል።—ዮሐ. 3:16
ይሖዋ፣ እስራኤላውያን ከእሱ ጋር ጥሩ ዝምድና መመሥረት እንዲችሉ ሲል ኃጢአታቸውን ይቅር ለማለት የሚያስችል ጊዜያዊ ዝግጅት አቋቁሞ ነበር። እስራኤላውያን በየዓመቱ የስርየትን ቀን ያከብሩ ነበር። በዚያ ዕለት ሊቀ ካህናቱ ሕዝቡን ወክሎ የእንስሳት መሥዋዕቶችን ያቀርባል። እርግጥ ነው፣ የእንስሳት መሥዋዕቶች የማንንም ኃጢአት ሙሉ በሙሉ ማስተሰረይ አይችሉም፤ ምክንያቱም እንስሳት ከሰዎች ያንሳሉ። ያም ቢሆን፣ ንስሐ የገቡ እስራኤላውያን ይሖዋ የሚጠብቀውን መሥዋዕት እስካቀረቡ ድረስ እሱ ኃጢአታቸውን ይቅር ለማለት ፈቃደኛ ነበር። (ዕብ. 10:1-4) ይህ ዝግጅትእስራኤላውያን ኃጢአተኛ መሆናቸውን እንዲያስታውሱ ያደርጋቸዋል። ሆኖም ይሖዋ የሰዎችን ኃጢአት ይቅር ለማለት የሚያስችል ዘላቂ ዝግጅት አድርጓል። የሚወደው ልጁ “የብዙዎችን ኃጢአት ለመሸከም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መሥዋዕት ሆኖ” እንዲቀርብ አደረገ። (ዕብ. 9:28) ኢየሱስ “በብዙ ሰዎች ምትክ ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ” ሰጥቷል።—ማቴ. 20:28፤ w25.02 4 አን. 9-10
ማክሰኞ፣ ሰኔ 16
ወደ ፈተና እንዳትገቡ ነቅታችሁ ጠብቁ፤ ሳታሰልሱም ጸልዩ።—ማቴ. 26:41
“መንፈስ ዝግጁ ነው፤ ሥጋ ግን ደካማ ነው።” (ማቴ. 26:41ለ) ኢየሱስ የተናገራቸው ቃላት ፍጹማን አለመሆናችንን እንደሚረዳ ያሳያሉ። ሆኖም እነዚህ ቃላት ማስጠንቀቂያም ይዘዋል፦ ከልክ በላይ በራሳችሁ አትተማመኑ። በዚያ ምሽት ደቀ መዛሙርቱ ከጌታቸው ላለመለየት ቁርጠኛ እንደሆኑ በልበ ሙሉነት ገልጸው ነበር። (ማቴ. 26:35) ሐሳባቸው ጥሩ ነው። ያም ቢሆን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሲሆኑ በፍጥነት ሊዳከሙ እንደሚችሉ አልተገነዘቡም። በመሆኑም ኢየሱስ በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ያለውን ማስጠንቀቂያ ሰጣቸው። የሚያሳዝነው፣ ደቀ መዛሙርቱ ነቅተው ሳይጠብቁ ቀርተዋል። ኢየሱስ በተያዘበት ወቅት ከእሱ ጎን ቆሙ? ወይስ ለፈተና እጅ በመስጠት ጥለውት ሸሹ? ደቀ መዛሙርቱ ነቅተው ስላልጠበቁ ፈጽሞ እንደማያደርጉ የተናገሩትን ነገር አደረጉ፤ ኢየሱስን ጥለውት ሸሹ።—ማቴ. 26:56፤ w24.07 14 አን. 1-2
ረቡዕ፣ ሰኔ 17
በልጁ ሞት አማካኝነት ከአምላክ ጋር [ታረቅን]።—ሮም 5:10
አዳምና ሔዋን ከአባታቸው ከይሖዋ ጋር የነበራቸውን ውድ ዝምድና አጥተዋል። መጀመሪያ ላይ አዳምና ሔዋን የአምላክ ቤተሰብ አባላት ነበሩ። (ሉቃስ 3:38) በይሖዋ ላይ ካመፁ በኋላ ግን ከእሱ ቤተሰብ ተባረሩ፤ ይህ የሆነው ልጆች ከመውለዳቸው በፊት ነው። (ዘፍ. 3:23, 24፤ 4:1) እኛም የእነሱ ዘሮች እንደመሆናችን መጠን ከይሖዋ ጋር መታረቅ ያስፈልገናል። (ሮም 5:10, 11) በሌላ አባባል ከእሱ ጋር ጥሩ ዝምድና መመሥረት ያስፈልገናል። አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ እንደሚገልጸው፣ ከላይ ያለው ጥቅስ ላይ “መታረቅ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “ጠላትን ወዳጅ ማድረግ” የሚል ትርጉም ሊኖረው ይችላል። የሚገርመው፣ ይህ እንዲሆን ቅድሚያውን ወስዶ ዝግጅት ያደረገው ይሖዋ ነው። እንዴት? ይሖዋ ኃጢአተኛ የሆኑ ሰዎች ከእሱ ጋር መልሰው ጥሩ ዝምድና መመሥረት እንዲችሉ ሲል ባደረገው የስርየት ዝግጅት አማካኝነት ነው። ስርየት አንድን ነገር ተመጣጣኝ ዋጋ ባለው ሌላ ነገር መቀየርን ይጠይቃል። የጠፋን ወይም የተበላሸን ነገር በዚህ መንገድ መልሶ ማግኘት ወይም መተካት ይቻላል። w25.02 3-4 አን. 7-8
ሐሙስ፣ ሰኔ 18
ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ ማዘን ለመዳን የሚያበቃ ንስሐ ያስገኛል።—2 ቆሮ. 7:10
ሐዋርያው ጳውሎስ “እንዲህ ዓይነቱ ሰው ከእናንተ አብዛኞቻችሁ የሰጣችሁት ተግሣጽ ይበቃዋል” ብሏል። (2 ቆሮ. 2:5-8) በሌላ አባባል፣ ከእንጀራ እናቱ ጋር የፆታ ግንኙነት ይፈጽም ለነበረው ሰው የተሰጠው ተግሣጽ ዓላማውን አከናውኗል። (1 ቆሮ. 5:1) ዓላማው ምን ነበር? ግለሰቡን ወደ ንስሐ መምራት ነው። (ዕብ. 12:11) በመሆኑም ጳውሎስ፣ ኃጢአት የሠራውን ወንድም ‘በደግነት ይቅር እንዲሉትና እንዲያጽናኑት’ እንዲሁም ‘ለእሱ ያላቸውን ፍቅር እንዲያረጋግጡለት’ መመሪያ ሰጠ። ጳውሎስ የፈለገው ወንድሞች ግለሰቡን ወደ ጉባኤው እንዲመልሱት ብቻ አይደለም። ወንድሞች ንስሐ የገባውን ግለሰብ ከልባቸው ይቅር እንዳሉትና እንደሚወዱት በቃላቸውና በተግባራቸው እንዲያረጋግጡለት ፈልጎ ነበር። በዚህ መንገድ፣ ወንድም በመመለሱ በጣም እንደተደሰቱ በግልጽ ያሳያሉ። w24.08 15 አን. 4፤ 16-17 አን. 6-8
ዓርብ፣ ሰኔ 19
በአደባባይ ለነቀፋና ለመከራ የተጋለጣችሁባቸው ጊዜያት ነበሩ።—ዕብ. 10:33
ሐዋርያው ጳውሎስ ለመጽናት ምን እንደሚያስፈልግ በእርግጠኝነት መናገር ይችላል። ክርስቲያኖች ፈተናዎችን በጽናት መቋቋም ከፈለጉ በራሳቸው ሳይሆን በይሖዋ መታመን እንዳባቸው አሳስቧል። ጳውሎስ በልበ ሙሉነት “ይሖዋ ረዳቴ ነው፤ አልፈራም” ማለት የቻለው ይህን በማድረጉ ነው። (ዕብ. 13:6) አንዳንድ ወንድሞቻችን በአሁኑ ወቅት ስደትን በጽናት እየተቋቋሙ ይገኛሉ። ስለ እነሱ በመጸለይ በታማኝነት ልንደግፋቸው እንችላለን፤ አንዳንድ ጊዜም ተግባራዊ እርዳታ ልንሰጣቸው እንችል ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ እንደሚናገረው ግን “የክርስቶስ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በመሆን ለአምላክ ያደሩ ሆነው መኖር የሚፈልጉ ሁሉ ስደት ይደርስባቸዋል።” (2 ጢሞ. 3:12) በመሆኑም ሁላችንም ከፊታችን ለሚጠብቀን አስቸጋሪ ጊዜ መዘጋጀት ይኖርብናል። በይሖዋ ሙሉ በሙሉ መታመናችንን እንቀጥል፤ ይሖዋ የሚያጋጥመንን ማንኛውንም ፈተና በጽናት ለመቋቋም እንደሚረዳን እርግጠኞች እንሁን። እሱ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ ለታማኝ አገልጋዮቹ በሙሉ እረፍት ይሰጣቸዋል።—2 ተሰ. 1:7, 8፤ w24.09 12-13 አን. 17-18
ቅዳሜ፣ ሰኔ 20
መልእክቱን የሰሙ በርካታ የቆሮንቶስ ሰዎችም አምነው ይጠመቁ ጀመር።—ሥራ 18:8
የቆሮንቶስ ሰዎች እንዲጠመቁ የረዳቸው ምንድን ነው? (2 ቆሮ. 10:4, 5) የአምላክ ቃልና ኃያል የሆነው ቅዱስ መንፈሱ በሕይወታቸው ውስጥ ትልቅ ለውጥ እንዲያደርጉ ረድቷቸዋል። (ዕብ. 4:12) ስለ ክርስቶስ የሚገልጸውን ምሥራች የተቀበሉት የቆሮንቶስ ሰዎች እንደ ስካር፣ ስርቆትና ግብረ ሰዶማዊነት ያሉትን ልማዶችና ምግባሮች እርግፍ አድርገው መተው ችለዋል። (1 ቆሮ. 6:9-11) ወደ ክርስትና የመጡት የቆሮንቶስ ሰዎች ሊያስወግዷቸው የሚገቡ ሥር የሰደዱ ልማዶች ነበሯቸው፤ ሆኖም ክርስቲያን ለመሆን የሚያስፈልገውን ብቃት ማሟላት ከአቅማቸው በላይ እንደሆነ አልተሰማቸውም። ወደ ዘላለም ሕይወት በሚወስደው ቀጭን መንገድ ላይ ለመጓዝ ብርቱ ተጋድሎ አድርገዋል። (ማቴ. 7:13, 14) አንተስ ለመጠመቅ ስትል ልታስወግደው የሚገባህ መጥፎ ልማድ ወይም ምግባር አለህ? ትግሉ ከባድ ቢሆንም ፈጽሞ እጅ አትስጥ! የተሳሳተ ነገር እንድትፈጽም የሚፈትንህን ስሜት ለመቋቋም እንዲያግዝህ ይሖዋ መንፈሱን እንዲሰጥህ ለምነው። w25.03 6 አን. 15-17
እሁድ፣ ሰኔ 21
ከእናንተ መካከል ጥበብ የጎደለው ሰው ካለ አምላክን ያለማሰለስ ይለምን።—ያዕ. 1:5
ይሖዋ አንድ ውሳኔ እሱን የሚያስደስት መሆን አለመሆኑን ለማስተዋል የሚያስችል ጥበብ እንደሚሰጠን ቃል ገብቶልናል። እንዲህ ያለውን ጥበብ “ማንንም ሳይነቅፍ ለሁሉም በልግስና ይሰጣል።” የይሖዋን አመራር ለማግኘት ከጸለይክ በኋላ መልሱን ለማስተዋል ጥረት አድርግ። ሁኔታውን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ ጉዞ ላይ እያለህ መንገድ ጠፍቶብህ የአካባቢው ነዋሪ የሆነን አንድ ሰው እርዳታ ጠየቅክ እንበል። ግለሰቡ ገና መልስ ሳይሰጥህ በፊት ትተኸው ትሄዳለህ? እንዲህ እንደማታደርግ የታወቀ ነው። የሚሰጥህን መመሪያ በጥንቃቄ ታዳምጣለህ። በተመሳሳይም ይሖዋ ጥበብ እንዲሰጥህ ከጸለይክ በኋላ ካለህበት ሁኔታ ጋር የሚያያዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ሕጎችንና መሠረታዊ ሥርዓቶችን ለማግኘት ጥረት በማድረግ ይሖዋ የሚሰጥህን ምላሽ ለማስተዋል ሞክር። ለምሳሌ በአንድ ግብዣ ላይ ለመገኘት ወይም ላለመገኘት በምትወስንበት ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ መረን ስለለቀቀ ድግስ፣ ስለ መጥፎ ጓደኝነት እንዲሁም ከግል ምርጫችን ይልቅ የመንግሥቱን ጉዳዮች ስለማስቀደም የሚናገረውን ሐሳብ ከግምት ልታስገባ ትችላለህ።—ማቴ. 6:33፤ ሮም 13:13፤ 1 ቆሮ. 15:33፤ w25.01 16 አን. 6-7
ሰኞ፣ ሰኔ 22
እነሆ፣ አገልጋዮቼ ይበላሉ፤ እናንተ ግን ትራባላችሁ።—ኢሳ. 65:13
የኢሳይያስ ትንቢት በመንፈሳዊው ገነት ውስጥ ባሉ ሰዎችና ከመንፈሳዊው ገነት ውጭ ባሉ ሰዎች መካከል ያለውን ልዩነት ግልጽ በሆነ መንገድ ይናገራል። ይሖዋ አገልጋዮቹ የሚያስፈልጋቸውን መንፈሳዊ ነገር በተትረፈረፈ ሁኔታ ያሟላላቸዋል። መንፈስ ቅዱስን፣ በጽሑፍ የሰፈረውን ቃሉን እንዲሁም የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ ስለሰጠን ‘መብላት፣ መጠጣትና መደሰት’ እንችላለን። (ከራእይ 22:17 ጋር አወዳድር።) ከዚህ በተቃራኒ ከመንፈሳዊው ገነት ውጭ ያሉ ሰዎች ‘ይራባሉ፣ ይጠማሉ እንዲሁም ኀፍረት ይከናነባሉ።’ የሚያስፈልጓቸው መንፈሳዊ ነገሮች አይሟሉላቸውም። (አሞጽ 8:11) ይሖዋ ለሕዝቦቹ መንፈሳዊ ምግብን ጨምሮ የሚያስፈልጋቸውን ነገር በሙሉ አትረፍርፎ እንደሚሰጣቸው ገልጿል። (ኢዩ. 2:21-24) ይህን የሚያደርገው በመጽሐፍ ቅዱስ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተመሠረቱ ጽሑፎቻችን፣ በድረ ገጻችን እንዲሁም በጉባኤ፣ በወረዳና በክልል ስብሰባዎቻችን አማካኝነት ነው። ከእነዚህ መንፈሳዊ ዝግጅቶች በየዕለቱ መጠቀም እንችላለን፤ ይህም ጤናማ እንድንሆንና መንፈሳችን እንዲታደስ ይረዳናል። w24.04 21 አን. 5-6
ማክሰኞ፣ ሰኔ 23
ንግግራችሁ ምንጊዜም . . . ለዛ ያለው ይሁን።—ቆላ. 4:6
ከአንዲት እህት ጋር ለመጠናናት ካሰብክ ለማውራት በሚያመች ግልጽ ቦታ ላይ ተገናኝታችሁ ወይም በስልክ ልታነጋግራት ትችላለህ። ሐሳብህን በግልጽ ንገራት። (1 ቆሮ. 14:9) አስፈላጊ ከሆነ ስለ ጉዳዩ አስባበት መልስ እንድትሰጥህ ጊዜ ስጣት። (ምሳሌ 15:28) እህት ከአንተ ጋር መጠናናት ካልፈለገች ደግሞ ስሜቷን አክብርላት። አንዲት እህት ከአንተ ጋር ለመጠናናት እንደምትፈልግ ብትነግርህስ? አንተን ለማነጋገር ድፍረት ጠይቆባት እንደሚሆን ጥያቄ የለውም፤ ስለዚህ በደግነትና በአክብሮት አነጋግራት። ስለ ጉዳዩ ለማሰብ ጊዜ የሚያስፈልግህ ከሆነ በግልጽ ንገራት። ያም ቢሆን በተቻለ ፍጥነት መልስ ለመስጠት ጥረት አድርግ። (ምሳሌ 13:12) ከእሷ ጋር ለመጠናናት ፍላጎት ከሌለህ ይህን በደግነትና በግልጽ ንገራት። ከእሷ ጋር ለመጠናናት ካሰብክ ደግሞ ስሜትህን ንገራት፤ እንዲሁም የመጠናናቱ ሂደት እንዴት እንዲቀጥል እንደምትፈልጉ በግልጽ ተነጋገሩ። አንተ የምታስበው ነገር እሷ ከምታስበው የተለየ ሊሆን ይችላል። w24.05 23-24 አን. 12-13
ረቡዕ፣ ሰኔ 24
በሠራዊት ጌታ በይሖዋ ስም እመጣብሃለሁ።—1 ሳሙ. 17:45
ዳዊት ገና በአሥራዎቹ ዕድሜ እያለ ወደ እስራኤላውያን የጦር ሰፈር ሄደ። በዚያም ጎልያድ የተባለ ግዙፍ ፍልስጤማዊ ‘ለውጊያ በተሰለፈው የእስራኤል ሠራዊት ላይ በመሳለቁ’ የተነሳ ወታደሮቹ በፍርሃት እንደተሸበሩ አየ። (1 ሳሙ. 17:10, 11) ወታደሮቹ የተሸበሩት በሰውየው ግዝፈትና በተናገረው ግድድር ላይ በማተኮራቸው ነው። (1 ሳሙ. 17:24, 25) ዳዊት ግን ሁኔታውን የተመለከተው ከሌላ አቅጣጫ ነው። ሁኔታውን በእስራኤል ሠራዊት ላይ እንደተሰነዘረ ግድድር ብቻ ሳይሆን “ሕያው በሆነው አምላክ ሠራዊት ላይ” እንደተሰነዘረ ግድድር አድርጎ ቆጥሮታል። (1 ሳሙ. 17:26) ዳዊት በይሖዋ ላይ አተኩሯል። ዳዊት እረኛ ሳለ የረዳው አምላክ በዚህ ሁኔታ ውስጥም እንደሚረዳው ተማምኖ ነበር። አምላክ እንደሚረዳው በመተማመን ጎልያድን ገጠመው፤ ደግሞም አሸነፈው።—1 ሳሙ. 17:45-51፤ w24.06 21 አን. 7
ሐሙስ፣ ሰኔ 25
እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ። እኔ አምላክህ ነኝና አትጨነቅ። አበረታሃለሁ፤ አዎ እረዳሃለሁ፤ በጽድቅ ቀኝ እጄ አጥብቄ እይዝሃለሁ።—ኢሳ. 41:10
ይሖዋን ባናገለግል ኖሮ ሕይወታችን ምን ይመስል እንደነበር ማሰብ እንችላለን። እንዲህ ማድረጋችን ታማኝነታችንን እንድንጠብቅ እንዲሁም እንደ መዝሙራዊው “እኔ ግን ወደ አምላክ መቅረብ ይበጀኛል” የሚል መደምደሚያ ላይ እንድንደርስ ይረዳናል። (መዝ. 73:28) “ሕያው የሆነውንና እውነተኛውን አምላክ” ስለምናገለግል በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት የሚያጋጥመንን ማንኛውንም ፈተና መጋፈጥ እንችላለን። (1 ተሰ. 1:9) ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ሲል እርምጃ የሚወስድ እውን የሆነ አምላክ ነው። በጥንት ዘመን ከአገልጋዮቹ ጋር እንደነበር አስመሥክሯል፤ በአሁኑ ጊዜም ከእኛ ጋር ነው። በቅርቡ፣ በምድር ላይ ሆኖ የማያውቅ ታላቅ መከራ ይጠብቀናል። ሆኖም ታላቁን መከራ የምንጋፈጠው ብቻችንን አይደለም። እንግዲያው ሁላችንም “በሙሉ ልብ ‘ይሖዋ ረዳቴ ነው፤ አልፈራም። ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል?” እንበል።—ዕብ. 13:5, 6፤ w24.06 25 አን. 17-18
ዓርብ፣ ሰኔ 26
በጻድቁና በክፉው . . . መካከል ያለውን ልዩነት . . . ታያላችሁ።—ሚል. 3:18
መጽሐፍ ቅዱስ በእስራኤል ላይ ነገሥታት ሆነው ስለገዙ ከ40 የሚበልጡ ሰዎች ይናገራል። ጥሩዎቹ ነገሥታት አንዳንድ መጥፎ ነገሮችን አድርገዋል። ጥሩ ንጉሥ የነበረውን ዳዊትን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ይሖዋ ‘አገልጋዬ ዳዊት በፊቴ ትክክል የሆነውን ነገር ብቻ በማድረግ በሙሉ ልቡ ተከትሎኛል’ ብሏል። (1 ነገ. 14:8) ያም ቢሆን ዳዊት ባለትዳር ከሆነች ሴት ጋር የፆታ ብልግና ፈጽሟል፤ እንዲሁም ባሏ በጦርነት ላይ እንዲገደል ሴራ ጠንስሷል። (2 ሳሙ. 11:4, 14, 15) በሌላ በኩል ደግሞ ታማኝ ካልነበሩት ነገሥታት መካከል ብዙዎቹ አንዳንድ ጥሩ ነገሮችን አድርገዋል። ሮብዓምን እንደ ምሳሌ እንመልከት። ሮብዓም በይሖዋ ዓይን ‘ክፉ ነገር አድርጓል።’ (2 ዜና 12:14) ያም ቢሆን ሮብዓም፣ አምላክ አሥሩ ነገዶች ከመንግሥቱ እንዲገነጠሉ የሰጠውን ትእዛዝ አክብሯል። በተጨማሪም የተመሸጉ ከተሞችን በመገንባት ብሔሩን የሚጠቅም ነገር አድርጓል። (1 ነገ. 12:21-24፤ 2 ዜና 11:5-12) ይሖዋ አንድን ንጉሥ በእሱ ዓይን ታማኝ አድርጎ የሚመለከተው ምንን መሠረት አድርጎ ነው? የልቡን ሁኔታ፣ ንስሐ መግባቱን እንዲሁም እውነተኛውን አምልኮ የሙጥኝ ማለቱን ከግምት እንደሚያስገባ ከሁኔታዎች መረዳት ይቻላል።። w24.07 20-21 አን. 1-3
ቅዳሜ፣ ሰኔ 27
በይሖዋ ተግሣጽና ምክር አሳድጓቸው።—ኤፌ. 6:4
ከ18 ዓመት በታች የሆነ የተጠመቀ ልጅ ከባድ ኃጢአት ቢፈጽምስ? የሽማግሌዎች አካል፣ ሁለት ሽማግሌዎች ልጁን ከክርስቲያን ወላጆቹ ጋር እንዲያነጋግሩት ዝግጅት ያደርጋል። ሽማግሌዎቹ፣ ወላጆቹ ልጁን ወደ ንስሐ ለመምራት የትኞቹን እርምጃዎች እንደወሰዱ ለማወቅ ጥረት ያደርጋሉ። ልጁ ጥሩ ዝንባሌ ካለውና የወላጆቹን እርዳታ እየተቀበለ ከሆነ ሁለቱ ሽማግሌዎች ሌላ ተጨማሪ እርምጃ መውሰድ እንደማያስፈልግ ሊወስኑ ይችላሉ። ደግሞም ለልጆች ፍቅራዊ እርማት መስጠት አምላክ ለወላጆች የሰጠው ኃላፊነት ነው። (ዘዳ. 6:6, 7፤ ምሳሌ 6:20፤ 22:6፤ ኤፌ. 6:2-4) ከዚያ በኋላ ሽማግሌዎቹ ለአካለ መጠን ያልደረሰው ልጅ አስፈላጊውን እርዳታ እያገኘ መሆኑን ለማረጋገጥ አልፎ አልፎ ወላጆቹን በመጠየቅ ያጣራሉ። ይሁንና አንድ የተጠመቀ ልጅ ንስሐ ባይገባና የኃጢአት ጎዳና መከተሉን ቢቀጥልስ? ሁኔታው እንደዚያ ከሆነ፣ የሽማግሌዎች ኮሚቴ ከክርስቲያን ወላጆቹ ጋር አብሮ ያነጋግረዋል። w24.08 24 አን. 18
እሁድ፣ ሰኔ 28
ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል።—ሥራ 20:35
ሁላችንም ከተሞክሮ እንደምናውቀው ስጦታ ሲሰጠን ደስ ይለናል። የበለጠ የምንደሰተው ግን ለሌሎች በምንሰጥበት ጊዜ ነው። ይሖዋ በዚህ መልኩ ስለፈጠረን ደስታችን በተወሰነ መጠንም ቢሆን በእኛው እጅ ነው። ለሌሎች ለመስጠት የሚያስችሉ ተጨማሪ አጋጣሚዎችን በመፈለግ ደስታችንን ማሳደግ እንችላለን። ይሖዋ በዚህ መልኩ የፈጠረን መሆኑ አስደናቂ አይደለም? (መዝ. 139:14) ቅዱሳን መጻሕፍት መስጠት ደስታ እንደሚያስገኝ ይናገራሉ፤ በመሆኑም ይሖዋ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ደስተኛው አምላክ” ተብሎ መጠራቱ አያስገርምም። (1 ጢሞ. 1:11) የመጀመሪያውም ሆነ ከሁሉ የላቀው ሰጪ እሱ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳለው “ሕይወት ያገኘነው፣ የምንንቀሳቀሰውና የምንኖረው በእሱ ነው።” (ሥራ 17:28) በእርግጥም “መልካም ስጦታ ሁሉና ፍጹም ገጸ በረከት ሁሉ” ከይሖዋ ነው። (ያዕ. 1:17) ሁላችንም በመስጠት የሚገኘውን ደስታ ይበልጥ ማጣጣም እንደምንፈልግ ምንም ጥያቄ የለውም። የይሖዋን ልግስና መኮረጃችን ይህን ለማድረግ ይረዳናል።—ኤፌ. 5:1፤ w24.09 26 አን. 1-4
ሰኞ፣ ሰኔ 29
ምንም ያህል እድገት ያደረግን ብንሆን በዚሁ መንገድ በአግባቡ ወደፊት መጓዛችንን እንቀጥል።—ፊልጵ. 3:16
አንዳንድ የጉባኤ አገልጋዮች ሽማግሌ ሆኖ ለማገልገል የቀረቡትን ብቃቶች ከተመለከቱ በኋላ ፈጽሞ ብቃቱን ማሟላት እንደማይችሉ ይሰማቸው ይሆናል። ሆኖም ይሖዋም ሆነ ድርጅቱ እነዚህን ባሕርያት ፍጹም በሆነ መንገድ እንድታንጸባርቅ እንደማይጠብቁብህ አስታውስ። (1 ጴጥ. 2:21) ደግሞም እነዚህን ብቃቶች እንድታሟላ የሚረዳህ ኃያል የሆነው የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ነው። (ፊልጵ. 2:13) ማሻሻል የምትፈልገው አንድ ባሕርይ አለ? ከሆነ፣ ስለ ጉዳዩ ወደ ይሖዋ ጸልይ። ምርምር አድርግ፤ እንዲሁም አንድን ሽማግሌ እንዴት ማሻሻል እንደምትችል ምክር እንዲሰጥህ ጠይቀው። እድገት ማድረግህን ቀጥል! ይሖዋ እሱንም ሆነ ጉባኤውን ይበልጥ ማገልገል እንድትችል እንዲያሠለጥንህና እንዲቀርጽህ በጸሎት ጠይቀው። (ኢሳ. 64:8) ይሖዋ በሽምግልና ለማገልገል የሚያስፈልጉትን ብቃቶች ለማሟላት የምታደርገውን ጥረት አብዝቶ እንዲባርክልህ እንመኛለን። w24.11 24-25 አን. 17-18
ማክሰኞ፣ ሰኔ 30
አምላክ ቅዱሳንን በማገልገልም ሆነ ወደፊትም ማገልገላችሁን በመቀጠል የምታከናውኑትን ሥራ እንዲሁም ለስሙ ያሳያችሁትን ፍቅር በመርሳት ፍትሕ አያዛባም።—ዕብ. 6:10
በይሖዋ አገልግሎት ለበርካታ ዓመታት የተካፈልን ቢሆንም እንኳ ማናችንም ብንሆን የይሖዋ ምሕረት እንደሚገባን ሊሰማን አይገባም። እርግጥ ነው፣ ይሖዋ ያስመዘገብነውን የታማኝነት ታሪክ ከፍ አድርጎ ይመለከታል። ሆኖም ይሖዋ ልጁን የሰጠን ነፃ ስጦታ አድርጎ ነው እንጂ ላከናወንነው አገልግሎት ክፍያ አድርጎ አይደለም። ባከናወንነው አገልግሎት የተነሳ ምሕረት ወይም ለየት ያለ አስተያየት ሊደረግልን እንደሚገባ የሚሰማን ከሆነ ክርስቶስ የሞተው በከንቱ ነው እንደማለት ይሆንብናል። (ከገላትያ 2:21 ጋር አወዳድር።) ሐዋርያው ጳውሎስ በራሱ ጥረት የአምላክን ሞገስ ማግኘት እንደማይችል ያውቅ ነበር። ታዲያ በይሖዋ አገልግሎት በትጋት የሠራው ለምንድን ነው? የይሖዋ ሞገስ የሚገባው ሰው ሆኖ ለመገኘት ሳይሆን ለይሖዋ ጸጋ ያለውን አድናቆት ለማሳየት ነው። (ኤፌ. 3:7) እንደ ጳውሎስ ሁሉ እኛም በቅንዓት የምናገለግለው የይሖዋ ምሕረት የሚገባን ሰዎች ሆነን ለመገኘት ሳይሆን ለይሖዋ ምሕረት ያለንን አድናቆት ለማሳየት ነው። w25.01 27 አን. 5-6