የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • es26 ገጽ 7-17
  • ጥር

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ጥር
  • ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2026
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ሐሙስ፣ ጥር 1
  • ዓርብ፣ ጥር 2
  • ቅዳሜ፣ ጥር 3
  • እሁድ፣ ጥር 4
  • ሰኞ፣ ጥር 5
  • ማክሰኞ፣ ጥር 6
  • ረቡዕ፣ ጥር 7
  • ሐሙስ፣ ጥር 8
  • ዓርብ፣ ጥር 9
  • ቅዳሜ፣ ጥር 10
  • እሁድ፣ ጥር 11
  • ሰኞ፣ ጥር 12
  • ማክሰኞ፣ ጥር 13
  • ረቡዕ፣ ጥር 14
  • ሐሙስ፣ ጥር 15
  • ዓርብ፣ ጥር 16
  • ቅዳሜ፣ ጥር 17
  • እሁድ፣ ጥር 18
  • ሰኞ፣ ጥር 19
  • ማክሰኞ፣ ጥር 20
  • ረቡዕ፣ ጥር 21
  • ሐሙስ፣ ጥር 22
  • ዓርብ፣ ጥር 23
  • ቅዳሜ፣ ጥር 24
  • እሁድ፣ ጥር 25
  • ሰኞ፣ ጥር 26
  • ማክሰኞ፣ ጥር 27
  • ረቡዕ፣ ጥር 28
  • ሐሙስ፣ ጥር 29
  • ዓርብ፣ ጥር 30
  • ቅዳሜ፣ ጥር 31
ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2026
es26 ገጽ 7-17

ጥር

ሐሙስ፣ ጥር 1

በማስተዋል [ችሎታችሁ] የጎለመሳችሁ ሁኑ።—1 ቆሮ. 14:20

ባለትዳሮች በሕይወታቸው ውስጥ በጣም ከሚደሰቱባቸው ወቅቶች አንዱ ልጃቸው የሚወለድበት ቀን ነው። ይሁንና ወላጆች ሕፃን ልጃቸውን በጣም ቢወዱትም ለዘላለም ሕፃን ሆኖ እንዲኖር አይፈልጉም። እንዲያውም ልጃቸው ካላደገ በጣም መጨነቃቸው አይቀርም። በተመሳሳይም ይሖዋ “ሀ” ብለን ኢየሱስን መከተል ስንጀምር በጣም ይደሰታል፤ ሆኖም በመንፈሳዊ ሕፃን ሆነን እንድንቀር አይፈልግም። (1 ቆሮ. 3:1) ከዚህ ይልቅ ‘የጎለመስን’ ክርስቲያኖች እንድንሆን ይጠብቅብናል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “የጎለመሰ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “የበሰለ፣” “ፍጹም” ወይም “ሙሉ” የሚል ትርጉም ሊያስተላልፍ ይችላል። (1 ቆሮ. 2:6) አንድ ሕፃን አድጎ ጎልማሳ እንደሚሆነው ሁሉ እኛም ከመንፈሳዊ ሕፃንነት አልፈን እድገት ስናደርግ የጎለመስን ክርስቲያኖች መሆን እንችላለን። እርግጥ ነው፣ እዚህ ግብ ላይ ከደረስን በኋላም እንኳ መንፈሳዊ እድገት ማድረጋችንን ማቆም አይኖርብንም።—1 ጢሞ. 4:15፤ w24.04 2 አን. 1, 3

ዓርብ፣ ጥር 2

ድንኳኔ ከእነሱ ጋር ይሆናል፤ እኔም አምላካቸው እሆናለሁ።—ሕዝ. 37:27

ይሖዋ በሕይወትህ ውስጥ ምን ዓይነት ቦታ አለው? ‘ይሖዋ አባቴ፣ አምላኬና ወዳጄ ነው’ ብለህ ትመልስ ይሆናል። ይሖዋን ለመግለጽ ልንጠቀምባቸው የምንችላቸው ሌሎች የማዕረግ ስሞችም አሉ። ሆኖም እንደ ጋባዥህ አድርገህስ ትመለከተዋለህ? ንጉሥ ዳዊት ይሖዋ ከታማኝ አገልጋዮቹ ጋር ያለውን ወዳጅነት አንድ ጋባዥ ከእንግዶቹ ጋር ካለው ዝምድና ጋር አመሳስሎታል። እንዲህ ሲል ጠይቋል፦ “ይሖዋ ሆይ፣ በድንኳንህ ውስጥ በእንግድነት የሚስተናገድ ማን ነው? በተቀደሰ ተራራህ የሚኖር ማን ነው?” (መዝ. 15:1) ዳዊት በመንፈስ መሪነት የጻፋቸው ቃላት የይሖዋ እንግዶች ወይም ወዳጆች መሆን እንደምንችል ያስገነዝቡናል። ይሖዋ የፍጥረት ሥራውን ከመጀመሩ በፊት ብቻውን ነበር። ከዚያ ግን የበኩር ልጁን ፈጠረ። በዚህ መንገድ የመጀመሪያ እንግዳውን ወደ ምሳሌያዊ ድንኳኑ ጋበዘ። ይሖዋ እንግዶችን መቀበል በመጀመሩ በጣም ተደስቷል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ በልጁ የተነሳ ‘ልዩ ደስታ ይሰማው’ እንደነበር ይናገራል። የመጀመሪያ እንግዳው የሆነው ልጁም ‘በይሖዋ ፊት ሁልጊዜ ሐሴት ያደርግ ነበር።’—ምሳሌ 8:30፤ w24.06 2 አን. 1-3

ቅዳሜ፣ ጥር 3

ሳዶቅ . . . ኃያልና ደፋር ወጣት [ነበር]።—1 ዜና 12:28

የሚከተለውን ሁኔታ በምናብህ ለመሣል ሞክር። ከ340,000 የሚበልጡ ሰዎች ዳዊትን በመላው እስራኤል ላይ ለማንገሥ ተሰብስበዋል። እነዚህ ሰዎች ለሦስት ቀን ያህል በኬብሮን አቅራቢያ በሚገኙት ዓለታማ ኮረብቶች ላይ ተሰብስበው ሞቅ ያለ ጭውውት ሲያደርጉና በደስታ የውዳሴ መዝሙር ሲዘምሩ ቆይተዋል። (1 ዜና 12:39) ከእነዚህ ሰዎች መካከል ሳዶቅ የተባለ ወጣትም ይገኝበታል። ከሕዝቡ ብዛት አንጻር ሳዶቅ እዚያ መኖሩን ማንም ልብ ላይል ይችላል። ሆኖም ይሖዋ፣ ሳዶቅ እዚያ መኖሩን እንድናውቅ አድርጓል። (1 ዜና 12:22, 26-28) ሳዶቅ ከሊቀ ካህናቱ ከአብያታር ጋር በቅርበት የሚሠራ ካህን ነበር። በተጨማሪም የአምላክን ፈቃድ የማስተዋል ችሎታና አስደናቂ ጥበብ ያለው ባለራእይ ነበር። (2 ሳሙ. 15:27) ሳዶቅ ደፋር ሰው ነበር። በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ሰይጣን በአምላክ ሕዝቦች ላይ የሚሰነዝረውን ጥቃት አፋፍሟል። (1 ጴጥ. 5:8) ይሖዋ ሰይጣንን እና ክፉ ሥርዓቱን እስኪያጠፋ በምንጠብቅበት ወቅት ደፋር መሆን ያስፈልገናል። (መዝ. 31:24) እንዲህ በማድረግ የሳዶቅን ድፍረት መኮረጅ እንችላለን። w24.07 2 አን. 1-3

እሁድ፣ ጥር 4

አዳም በአጠቃላይ 930 ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ሞተ።—ዘፍ. 5:5

ይሖዋ የመጀመሪያዎቹን ወንድና ሴት ሲፈጥር ደስተኛ እንዲሆኑ ፈልጎ ነበር። የሚያምር የመኖሪያ ቦታ፣ የጋብቻን ስጦታ እንዲሁም አስደሳች ሥራ ሰጥቷቸዋል። ምድርን በዘሮቻቸው የመሙላት እንዲሁም መላዋን ምድር ልክ እንደ ኤደን ገነት ውብ የማድረግ ኃላፊነት ሰጥቷቸዋል። የተከለከሉት አንድ ቀላል ነገር ብቻ ነበር። ደግሞም ይህን ትእዛዝ በመተላለፍ ሆን ብለው በእሱ ላይ ካመፁ ኃጢአታቸው ወደ ሞት እንደሚመራቸው ማስጠንቀቂያ ሰጥቷቸዋል። ቀጥሎ ምን እንደሆነ እናውቃለን። ለአምላክም ሆነ ለእነሱ ምንም ፍቅር የሌለው አንድ መንፈሳዊ ፍጡር ያንን ኃጢአት እንዲፈጽሙ ፈተናቸው። አዳምና ሔዋን በፈተናው ወደቁ። በሚወዳቸው አባታቸው ከመታመን ይልቅ ኃጢአት ሠሩ። እንደምናውቀው የይሖዋ ቃል ተፈጽሟል። ከዚያች ዕለት አንስቶ የኃጢአታቸውን መዘዝ መቀበል ጀመሩ፤ እያረጁ ሄዱ፤ በመጨረሻም ለሞት ተዳረጉ።—ዘፍ. 1:28, 29፤ 2:8, 9, 16-18፤ 3:1-6, 17-19, 24፤ w24.08 3 አን. 3

ሰኞ፣ ጥር 5

ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ . . . ሰሚዎች ብቻ አትሁኑ።—ያዕ. 1:22

ይሖዋ እና የሚወደው ልጁ ደስተኞች እንድንሆን ይፈልጋሉ። የመዝሙር 119:2 ጸሐፊ እንዲህ ብሏል፦ “ማሳሰቢያዎቹን የሚጠብቁ፣ እሱን በሙሉ ልባቸው የሚፈልጉ ደስተኞች ናቸው።” ኢየሱስም “ደስተኞችስ የአምላክን ቃል ሰምተው የሚጠብቁት ናቸው!” በማለት ተጨማሪ ማረጋገጫ ሰጥቷል። (ሉቃስ 11:28) እኛ የይሖዋ አገልጋዮች የአምላክን ቃል አዘውትረን ለማንበብና የተማርነውን ነገር ተግባራዊ ለማድረግ ስንጥር ደስተኛ እንሆናለን። (ያዕ. 1:22-25) ይሖዋን የምናስደስተው እንዲህ ስናደርግ ነው። (መክ. 12:13) በመንፈስ መሪነት በተጻፈው የአምላክ ቃል ላይ ያነበብነውን ነገር በተግባር ስናውል የቤተሰብ ሕይወታችን ይሻሻላል፤ ከእምነት አጋሮቻችን ጋር ያለን ወዳጅነትም ይጠናከራል። ከዚህም በተጨማሪ፣ የይሖዋን መመሪያዎች የማይከተሉ ሰዎች ከሚደርሱባቸው ብዙ ችግሮች እንጠበቃለን። ንጉሥ ዳዊት ከተናገረው ሐሳብ ጋር እንደምንስማማ ጥያቄ የለውም። ዳዊት በመዝሙሩ ላይ ስለ ይሖዋ ሕግ፣ መመሪያዎችና ፍርዶች ከጠቀሰ በኋላ “እነሱን መጠበቅ ትልቅ ወሮታ አለው” ብሏል።—መዝ. 19:7-11፤ w24.09 2 አን. 1-3

ማክሰኞ፣ ጥር 6

የተሰበረ ልብ ያላቸውን ይጠግናል፤ ቁስላቸውን ይፈውሳል።—መዝ. 147:3

ይሖዋ ምድር ላይ ያሉ አገልጋዮቹን ሲመለከት ምን ነገሮችን ያስተውላል? ስንደሰትና ስናዝን ይመለከታል። (መዝ. 37:18) ከስሜት ሥቃይ ጋር እየታገልንም እንኳ አቅማችን በፈቀደ መጠን እያገለገልነው እንደሆነ ሲያይ በጣም ይደሰታል። ከዚህም በተጨማሪ ሊደግፈንና ሊያጽናናን ይጓጓል። መዝሙር 147:3 ይሖዋ የተሰበረ ልብ ያላቸውን ሰዎች ‘ቁስል እንደሚፈውስ’ ይገልጻል። እዚህ ጥቅስ ላይ፣ ይሖዋ የስሜት ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች በርኅራኄ እንደሚንከባከብ ተገልጿል። ከይሖዋ እንክብካቤ ለመጠቀም ምን ማድረግ ይኖርብናል? እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት። ጥሩ ችሎታ ያለው ሐኪም የአንድ ሰው ቁስል እንዲድን መርዳት ይችላል። ሆኖም ጉዳት የደረሰበት ሰው መዳን ከፈለገ የሐኪሙን መመሪያ በጥንቃቄ መከተል አለበት። የስሜት ሥቃይ የደረሰባቸውን ሰዎች ይሖዋ በቃሉ አማካኝነት ያነጋግራቸዋል እንዲሁም ፍቅራዊ ምክር ይሰጣቸዋል። w24.10 6 አን. 1-2

ረቡዕ፣ ጥር 7

ሁሉም ከምድር ላይ ተጠራርገው ጠፉ።—ዘፍ. 7:23

ቀደም ሲል በጽሑፎቻችን ላይ፣ ይሖዋ ጻድቃን አይደሉም ብሎ ፍርድ ያስተላለፈባቸው ሰዎች ምን እንደሚያጋጥማቸው የሚገልጽ ሐሳብ ወጥቶ ነበር። እንዲህ ያሉ ሰዎች ወደፊት የትንሣኤ ተስፋ የላቸውም ብለን እንናገር ነበር። ይሖዋ ጻድቃን ባልሆኑ ሰዎች ላይ ስላስተላለፈው ፍርድ የሚገልጹ የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች አሉ። ለምሳሌ በጥፋት ውኃው ወቅት ቁጥራቸው የማይታወቅ ሰዎች ጠፍተዋል። በተጨማሪም ይሖዋ በተስፋይቱ ምድር ይኖሩ የነበሩትን ሰባት ብሔራት እንዲያጠፉ እስራኤላውያንን አዟቸዋል። ከዚህም ሌላ በአንድ መልአክ አማካኝነት በአንድ ምሽት 185,000 አሦራውያን ወታደሮችን አጥፍቷል። (ዘዳ. 7:1-3፤ ኢሳ. 37:36, 37) ከእነዚህ ታሪኮች ጋር በተያያዘ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ እርምጃ የወሰደባቸው ሰዎች በሙሉ ለዘላለም እንደሚጠፉና የትንሣኤ ተስፋ እንደማይኖራቸው በግልጽ ይናገራል? አይናገርም። ይሖዋ በእያንዳንዱ ግለሰብ ላይ ምን የሚል ፍርድ እንዳስተላለፈ አናውቅም፤ ወይም ደግሞ የጠፉት ሰዎች ስለ ይሖዋ የመማርና ንስሐ የመግባት አጋጣሚ አግኝተው የነበረ መሆን አለመሆኑን አናውቅም። w24.05 3 አን. 5-7

ሐሙስ፣ ጥር 8

ምንጊዜም ክፉውን በመልካም አሸንፍ።—ሮም 12:21

ኢየሱስ ስለ አንዲት መበለት የሚገልጽ ምሳሌ ተናግሮ ነበር። ይህች መበለት አንድን ዳኛ ፍትሕ እንድታገኝ እንዲያደርግ ትወተውተው ነበር። ብዙዎቹ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ይህ ታሪክ ልባቸውን ነክቶት መሆን አለበት፤ ምክንያቱም በዚያ ዘመን የነበሩት ብዙዎቹ ሰዎች የፍትሕ መጓደል ያጋጥማቸው ነበር። (ሉቃስ 18:1-5) ይህ ታሪክ የእኛንም ልብ የሚነካ ነው፤ ምክንያቱም ሁላችንም በተለያዩ ጊዜያት ኢፍትሐዊ ድርጊት ይፈጸምብናል። በምንኖርበት ዓለም ውስጥ ጭፍን ጥላቻ፣ አድልዎና ጭቆና የተለመደ ነገር ነው። ስለሆነም ፍትሕ የጎደለው ነገር ሲፈጸምብን እምብዛም አንገረምም። (መክ. 5:8) ይሁንና ወንድሞቻችን ወይም እህቶቻችን በደል ያደርሱብናል ብለን ላንጠብቅ እንችላለን፤ ሆኖም እንዲህ ያለ ሁኔታ ሊከሰት ይችላል። እርግጥ ነው፣ ከተቃዋሚዎቻችን በተለየ መልኩ ወንድሞቻችን በደል የሚያደርሱብን ሆን ብለው ሳይሆን ፍጹማን ስላልሆኑ ነው። ኢየሱስ ክፉ የሆኑ ተቃዋሚዎች ግፍ ሲፈጽሙበት ከሰጠው ምላሽ ብዙ ትምህርት ማግኘት እንችላለን። ግፍ የሚፈጽሙብንን ተቃዋሚዎች በትዕግሥት መያዝ የምንችል ከሆነ የእምነት አጋሮቻችንንማ ይበልጥ በትዕግሥት መያዝ እንደሚጠበቅብን ምንም ጥያቄ የለውም! w24.11 2 አን. 1-2

ዓርብ፣ ጥር 9

እነዚህ ሰዎች የሚበሉት ዳቦ ከየት ብንገዛ ይሻላል?—ዮሐ. 6:5

በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ዳቦ ለብዙዎች ዋነኛ ምግብ ነበር። (ዘፍ. 18:6፤ ሉቃስ 9:3) እንዲያውም ዳቦ በጣም የተለመደ ምግብ ከመሆኑ የተነሳ አንዳንድ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ “ዳቦ” የሚለውን ቃል ምግብን በአጠቃላይ ለማመልከት ይጠቀምበታል። (ሕዝ. 5:16 ግርጌ፤ ማቴ. 6:11 ግርጌ) ኢየሱስ በፈጸማቸው ሁለት ተአምራት ላይም ዳቦ ትልቅ ቦታ ነበረው። (ማቴ. 16:9, 10) ከእነዚህ ዘገባዎች አንደኛውን የምናገኘው በዮሐንስ ምዕራፍ 6 ላይ ነው። የኢየሱስ ሐዋርያት ዕለቱን በስብከት ካሳለፉ በኋላ እረፍት አስፈልጓቸው ነበር፤ በዚህ ጊዜ ከኢየሱስ ጋር ጀልባ ተሳፍረው የገሊላን ባሕር ተሻገሩ። (ማር. 6:7, 30-32፤ ሉቃስ 9:10) ቤተሳይዳ ውስጥ ወደሚገኝ አንድ ገለል ያለ ስፍራ ሄዱ። ብዙም ሳይቆይ ግን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተሰብስበው ወደ እነሱ መጡ። ኢየሱስ እነዚህን ሰዎች ፊት አልነሳቸውም። ጊዜ ወስዶ በደግነት ስለ መንግሥቱ አስተማራቸው፤ የታመሙትንም ፈወሰ። ቀኑ እየመሸ ሲሄድ ደቀ መዛሙርቱ እነዚያ ሁሉ ሰዎች የሚበሉት ምግብ የሚያገኙት ከየት እንደሆነ ያሳስባቸው ጀመር። ምናልባት አንዳንዶቹ ትንሽ ምግብ ይዘው ሊሆን ይችላል፤ አብዛኞቹ ግን ወደ መንደሮቹ ሄደው ምግብ መግዛት ነበረባቸው።—ማቴ. 14:15፤ w24.12 2 አን. 1-2

ቅዳሜ፣ ጥር 10

አምላክ የሚሰጠው ስጦታ . . . በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ የዘላለም ሕይወት ነው።—ሮም 6:23

የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን አዳምና ሔዋን ፍጹማን የነበሩ ከመሆኑም ሌላ ውብ በሆነች ገነት ውስጥ ይኖሩ ነበር። (ዘፍ. 1:27፤ 2:7-9) አስደሳችና ዘላለማዊ የሆነ ሕይወት የመምራት አጋጣሚ ነበራቸው። በኋላ ግን ሁሉም ነገር ተቀየረ። መኖሪያቸው የሆነችውን ገነት እንዲሁም ለዘላለም የመኖር አጋጣሚያቸውን አጡ። ታዲያ ለልጆቻቸው ያወረሱት ምን ዓይነት ውርስ ነው? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት መልሱን ይነግረናል፦ “በአንድ ሰው [በአዳም] አማካኝነት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ፤ በኃጢአትም ምክንያት ሞት መጣ፤ ሁሉም ኃጢአት ስለሠሩም ሞት ለሰው ሁሉ ተዳረሰ።” (ሮም 5:12) አዳም ያወረሰን ውርስ ኃጢአት ነው፤ ኃጢአት ደግሞ ሞት ያስከትላል። በዘር የወረስነው ኃጢአት እንደ ትልቅ ዕዳ ሊቆጠር ይችላል፤ ማናችንም ብንሆን ይህን ዕዳ መክፈል አንችልም። (መዝ. 49:8) ኢየሱስ ኃጢአትን ‘ከዕዳ’ ጋር አመሳስሎታል። (ማቴ. 6:12፤ ሉቃስ 11:4) ኃጢአት ስንሠራ የይሖዋ ባለዕዳዎች እንደሆንን ሊቆጠር ይችላል። ለሠራነው ኃጢአት የሚገባውን ቅጣት መክፈል ይኖርብናል። ይህ ዕዳ ካልተከፈለ ዕዳችን የሚሰረዝልን ስንሞት ብቻ ነው።—ሮም 6:7፤ w25.02 2-3 አን. 2-3

እሁድ፣ ጥር 11

ስምህን አሳውቄአቸዋለሁ።—ዮሐ. 17:26

ስለ አምላክ መንግሥት የመስበክ መብታችንን እጅግ ከፍ አድርገን እንመለከተዋለን። ይህ መብት የሚሰጠው ለሁሉም አይደለም። ለምሳሌ ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረ ጊዜ አጋንንት ስለ እሱ እንዲመሠክሩ አልፈቀደላቸውም። (ሉቃስ 4:41) በዛሬው ጊዜም አንድ ሰው ከይሖዋ ሕዝቦች ጋር አብሮ መስበክ ከመጀመሩ በፊት ብቃቱን ማሟላት ይጠበቅበታል። ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ ምሥራቹን በመስበክ ለዚህ መብት ያለንን አድናቆት ማሳየት እንችላለን። እንደ ኢየሱስ ሁሉ የእኛም ዓላማ የመንግሥቱን እውነት በሰዎች ልብ ውስጥ መዝራትና ውኃ ማጠጣት ነው። (ማቴ. 13:3, 23፤ 1 ቆሮ. 3:6) የይሖዋ ድርጅትም የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ሰዎች የአምላክን ስም እንዲያውቁ የተቻለውን ሁሉ ጥረት እያደረገ ነው። አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክን ስም በተገቢው ቦታ በመመለስ ስሙን በማሳወቅ ረገድ ጉልህ ሚና ተጫውቷል። በአሁኑ ጊዜ ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በሙሉ ወይም በከፊል ከ270 በሚበልጡ ቋንቋዎች ይገኛል። w24.04 9 አን. 8-9

ሰኞ፣ ጥር 12

ባሏ ተነስቶ ያወድሳታል።—ምሳሌ 31:28

አስደሳች ትዳር ያላቸው አንዳንድ ባሎች፣ በየዕለቱ በሆነ መንገድ ለሚስታቸው ፍቅራቸውን ለመግለጽ ጥረት ያደርጋሉ። (1 ዮሐ. 3:18) አንድ ባል ትናንሽ በሚመስሉ ነገሮች እንኳ ለሚስቱ ያለውን ፍቅር ሊገልጽ ይችላል፤ ለምሳሌ እጇን ሊይዛት ወይም እቅፍ ሊያደርጋት ይችላል። የጽሑፍ መልእክት በመላክ “ናፍቀሽኛል” ወይም “ውሎ እንዴት ነው?” ሊላት ይችላል። አልፎ አልፎ ደግሞ ደብዳቤ በመጻፍ ምን ያህል እንደሚወዳት ሊገልጽላት ይችላል። አንድ ባል እነዚህን ነገሮች ሲያደርግ ለሚስቱ አክብሮት ያሳያል፤ እንዲሁም ትዳራቸውን ያጠናክራል። ሚስቱን በአክብሮት የሚይዝ ባል አድናቆቱን ይገልጽላታል፤ እንዲሁም ያበረታታታል። ይህን ማድረግ የሚችልበት አንዱ መንገድ እሱን ለመደገፍ ስትል ለምታደርገው ነገር ሁሉ አስታውሶ ማመስገን ነው። (ቆላ. 3:15) አንድ ባል ሚስቱን ከልቡ ሲያሞግሳት ደስ ይላታል። ልቧ ይረጋጋል፤ እንዲሁም እንደምትወደድና እንደምትከበር ይሰማታል። w25.01 11 አን. 15፤ 13 አን. 16

ማክሰኞ፣ ጥር 13

ልትሄድበት . . . በሚገባህ መንገድ የምመራህ እኔ ይሖዋ አምላክህ ነኝ።—ኢሳ. 48:17

መዝሙር 15 የሚደመደመው “እነዚህን ነገሮች የሚያደርግ ሰው ሁሉ ፈጽሞ አይናወጥም” የሚል ዋስትና በመስጠት ነው። እዚህ ላይ መዝሙራዊው፣ ይሖዋ አምላክ መሥፈርቶቹን ያወጣበትን ዋነኛ ምክንያት ግልጽ አድርጎልናል። ይሖዋ ደስተኞች እንድንሆን ይፈልጋል። ስለዚህም የእሱን በረከትና ጥበቃ የሚያስገኙልንን መመሪያዎች ይሰጠናል። ይሖዋ በእንግድነት የሚቀበላቸው ሰዎች ብሩህ የወደፊት ተስፋ አላቸው። ኢየሱስ ታማኝ ለሆኑት ቅቡዓን “ብዙ መኖሪያ ቦታ” አዘጋጅቶላቸዋል። (ዮሐ. 14:2) ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ሰዎች ደግሞ በራእይ 21:3 ላይ የተጠቀሰው ተስፋ ሲፈጸም ለማየት ይጓጓሉ። አዎ፣ ይሖዋ ወዳጆቹ እንድንሆን ማለትም በድንኳኑ ውስጥ ለዘላለም እንድንስተናገድ ግብዣ ስላቀረበልን ታላቅ ክብር ይሰማናል!—መዝ. 15:1-5፤ w24.06 13 አን. 19-20

ረቡዕ፣ ጥር 14

ለስሙ የሚገባውን ክብር ለይሖዋ ስጡ።—መዝ. 96:8

ክብር ምንድን ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ክብር” የሚለው ቃል አንድን አካል በሌሎች ዘንድ ከፍ ተደርጎ እንዲታይ የሚያደርገውን ማንኛውንም ነገር ያመለክታል። የእስራኤል ብሔር ከግብፅ ባርነት ነፃ ከወጣ ብዙም ሳይቆይ ይሖዋ አምላክ ክብሩን አስደናቂ በሆነ መንገድ አሳይቷል። እስቲ ሁኔታውን በዓይነ ሕሊናችሁ ለመሣል ሞክሩ፦ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ እስራኤላውያን በአምላካቸው ፊት ለመቅረብ ሲሉ በሲና ተራራ ግርጌ ተሰብስበዋል። ጥቅጥቅ ያለ ደመና ተራራውን ሸፈነው። በድንገት በተራራው ዙሪያ ጭስ እየተትጎለጎለ ይወጣ ጀመር። መሬቱም በኃይል ተንቀጠቀጠ። መብረቅ፣ ነጎድጓድና ከፍተኛ የቀንደ መለከት ድምፅ አካባቢውን አናወጠው። (ዘፀ. 19:16-18፤ 24:17፤ መዝ. 68:8) ይሖዋ ክብሩን እንዲህ ባለ መንገድ ሲገልጥ እስራኤላውያን ምን ያህል ተደምመው ሊሆን እንደሚችል አስቡት። በዛሬው ጊዜ፣ ስለ ይሖዋ ታላቅ ኃይልና ስለ ማራኪ ባሕርያቱ ለሌሎች በመናገር እንዲሁም የምናከናውናቸው ነገሮች እንዲሳኩልን ላደረገልን እርዳታ እውቅና በመስጠት ለእሱ ክብር መስጠት እንችላለን።—ኢሳ. 26:12፤ w25.01 2-3 አን. 2-3

ሐሙስ፣ ጥር 15

ይሖዋ [ልኮኛል]።—ዘኁ. 16:28

እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር እየተጓዙ በነበረበት ወቅት አንዳንድ ተሰሚነት የነበራቸው ሰዎች ሙሴንና ይሖዋ የሰጠውን ሥልጣን ተገዳደሩ። እንዲህ ብለዋል፦ “[ሙሴ ብቻ ሳይሆን] መላው ማኅበረሰብ እኮ ቅዱስ ነው፤ ሁሉም ቅዱስ ናቸው፤ ይሖዋም በመካከላቸው ነው።” (ዘኁ. 16:1-3) በይሖዋ ዓይን መላው ብሔር ቅዱስ መሆኑ እውነት ቢሆንም ሕዝቡን እንዲመራ ይሖዋ የመረጠው ሙሴን ነው። እነዚህ ዓመፀኞች ሙሴን ሲተቹ ይሖዋን እንደተቹ ይቆጠራል። ያተኮሩት ይሖዋ በሚፈልገው ነገር ላይ ሳይሆን እነሱ በሚፈልጉት ማለትም ተጨማሪ ሥልጣንና ተሰሚነት በማግኘት ላይ ነበር። አምላክ ዓመፁን የቀሰቀሱትን ሰዎችና ከእነሱ ጋር የተባበሩትን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አጥፍቷቸዋል። (ዘኁ. 16:30-35, 41, 49) ዛሬም ይሖዋ ለድርጅታዊ መመሪያዎቹ አክብሮት በሌላቸው ሰዎች እንደማይደሰት እርግጠኞች መሆን እንችላለን። w24.07 11 አን. 11

ዓርብ፣ ጥር 16

ራእዩ የተወሰነለትን ጊዜ ገና ይጠብቃል።—ዕን. 2:3

ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ የዚህን ሥርዓት መጨረሻ አስመልክቶ የሚሰጠውን ማስጠንቀቂያ ችላ ይላሉ፤ እንዲያውም በዚህ በማመናችን ያፌዙብናል። (2 ጴጥ. 3:3, 4) ብዙ የማናውቃቸው ነገሮች ቢኖሩም የዚህ ሥርዓት መጨረሻ ይሖዋ በወሰነው ጊዜ እንደሚመጣ እንዲሁም በዚያ ጊዜ ይሖዋ እንደሚንከባከበን ጠንካራ እምነት ሊኖረን ይገባል። ከዚህም ሌላ ይሖዋ እኛን ለመምራት በሚጠቀምበት ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ ላይ ያለንን እምነት ማጠናከር ይኖርብናል። (ማቴ. 24:45) ታላቁ መከራ ሲጀምር ሕይወት አድን የሆኑ ዝርዝር መመሪያዎች ሊሰጡን ይችላሉ። በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች በሚሰጡን መመሪያ ላይ ያለንን እምነት ማጠናከር ያለብን አሁን ነው። ዛሬ እነሱን መታዘዝ የሚከብደን ከሆነ በታላቁ መከራ ወቅት የሚሰጡንን መመሪያ በሙሉ ልብ መታዘዝ ቀላል እንደማይሆንልን የታወቀ ነው። w24.09 11 አን. 11-12

ቅዳሜ፣ ጥር 17

ጥሩ የሆነውን፣ ተቀባይነት ያለውንና ፍጹም የሆነውን የአምላክ ፈቃድ መርምራችሁ [አረጋግጡ]።—ሮም 12:2

ክርስቲያን ወላጆች በአምላክ ላይ የሚኖረን እምነት በዘር የሚወረስ ነገር እንዳልሆነ ይገነዘባሉ። ልጆቻችሁ እያደጉ ሲሄዱ እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎች ሊያሳስቧቸው ይችላሉ፦ ‘አምላክ እንዳለ እርግጠኛ መሆን የምችለው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ በሚናገረው ነገር ላይ መተማመን እችላለሁ?’ መጽሐፍ ቅዱስም ‘የማሰብ ችሎታችንን’ እንድንጠቀምና ‘ሁሉንም ነገር እንድንመረምር’ ያበረታታናል። (ሮም 12:1፤ 1 ተሰ. 5:21) ታዲያ ልጆቻችሁ እምነታቸውን እንዲያጠናክሩ ልትረዷቸው የምትችሉት እንዴት ነው? ልጆቻችሁ እውነትን በራሳቸው መርምረው እንዲያረጋግጡ አበረታቷቸው። ልጆቻችሁ ጥያቄ ሲያነሱ አጋጣሚውን ተጠቅማችሁ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች ማውጫ (እንግሊዝኛ) እና የምርምር መርጃ መሣሪያ ለይሖዋ ምሥክሮች የተባሉትን መሣሪያዎች ተጠቅመው መልስ ማግኘት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ አሳዩአቸው። የምርምር መርጃ መሣሪያ ለይሖዋ ምሥክሮች በተባለው መጽሐፍ ውስጥ “መጽሐፍ ቅዱስ” በሚለው ርዕስ ሥር ያለውን “በአምላክ መንፈስ መሪነት ተጽፏል” የሚለውን ክፍል እንዲመለከቱ ልትጠቁሟቸው ትችላላችሁ። በዚህ ክፍል ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲሁ በሰዎች የተጻፈ ጥሩ መጽሐፍ ሳይሆን “የአምላክ ቃል” መሆኑን የሚያሳዩ ማስረጃዎችን ያገኛሉ።—1 ተሰ. 2:13፤ w24.12 14-15 አን. 4-5

እሁድ፣ ጥር 18

[እነዚህን ነገሮች] ታማኝ ለሆኑ ሰዎች አደራ ስጥ፤ እነሱም በበኩላቸው ሌሎችን ለማስተማር ብቃቱን ያሟላሉ።—2 ጢሞ. 2:2

ሽማግሌዎች የኢየሱስን ምሳሌ መከተል የሚችሉት እንዴት ነው? ወጣቶችን ጨምሮ ወንድሞች ተጨማሪ ኃላፊነቶችን ለመቀበል ብቃቱን እንዲያሟሉ ሊያሠለጥኗቸውና ሊረዷቸው ይገባል። ሽማግሌዎች ከሚያሠለጥኗቸው ወንድሞች ፍጽምና አይጠብቁም። እነዚህ ወጣት ወንድሞች ተሞክሮ እንዲያገኙ እንዲሁም ትሑት፣ ታማኝና ሌሎችን ለማገልገል ፈቃደኛ መሆን ያለውን አስፈላጊነት እንዲገነዘቡ ለመርዳት ፍቅራዊ ምክር ሊሰጧቸው ይገባል። (1 ጢሞ. 3:1፤ 1 ጴጥ. 5:5) ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የመስበክ ብቻ ሳይሆን የማስተማርም ኃላፊነት ሰጥቷቸዋል። ደቀ መዛሙርቱ ይህን ኃላፊነት ለመቀበል ብቁ እንዳልሆኑ ተሰምቷቸው ሊሆን ይችላል። ሆኖም ኢየሱስ ይህን ሥራ ማከናወን እንደሚችሉ አልተጠራጠረም፤ ደግሞም እንደሚተማመንባቸው ነግሯቸዋል። “አብ እኔን እንደላከኝ፣ እኔም እናንተን እልካችኋለሁ” ማለቱ ሙሉ በሙሉ እንደሚተማመንባቸው ያሳያል።—ዮሐ. 20:21፤ w24.10 16 አን. 15፤ 17 አን. 17

ሰኞ፣ ጥር 19

እንደ ልቤ የሆነውን . . . ዳዊትን አገኘሁ።—ሥራ 13:22

ዳዊት በጣም ጥሩ ንጉሥ ነበር። በተጨማሪም ሙዚቀኛ፣ ገጣሚ፣ ተዋጊና ነቢይ ነበር። ዳዊት ብዙ ፈተናዎችን አሳልፏል። ንጉሥ ሳኦል ስለቀናበት ለተወሰኑ ዓመታት ያህል በስደት ለመኖር ተገዷል። ዳዊት ንጉሥ ከሆነ በኋላም ልጁ አቢሴሎም ዙፋኑን ለመንጠቅ በሞከረበት ወቅት ሕይወቱን ለማትረፍ በድጋሚ መሸሽ አስፈልጎታል። ዳዊት ብዙ መከራዎችን ያሳለፈና አንዳንድ ኃጢአቶችን የሠራ ቢሆንም እስከ ሕይወቱ መጨረሻ ድረስ ለአምላክ ታማኝ ሆኖ ቀጥሏል። ይሖዋ ዳዊትን “እንደ ልቤ የሆነ” በማለት ገልጾታል። በመሆኑም የዳዊትን ምክር መስማታችን ተገቢ ነው! (1 ነገ. 15:5) ዳዊት አልጋ ወራሹ ለሆነው ለልጁ ለሰለሞን ምን ምክር እንደሰጠው እንመልከት። ወጣቱ ሰለሞን እውነተኛውን አምልኮ እንዲያስፋፋ እንዲሁም አምላክን የሚያስከብር ቤተ መቅደስ እንዲገነባ ይሖዋ መርጦት ነበር። (1 ዜና 22:5) ሰለሞን ብዙ ፈተናዎችን ማለፍ ይጠበቅበታል። ታዲያ ዳዊት ምን ምክር ይሰጠው ይሆን? ይሖዋን ከታዘዘ በሕይወቱ ስኬታማ እንደሚሆን ለልጁ ነግሮታል።—1 ነገ. 2:2, 3፤ w24.11 10 አን. 9-11

ማክሰኞ፣ ጥር 20

መንገድህን ለይሖዋ አደራ ስጥ፤ በእሱ ታመን፤ እሱም ለአንተ ሲል እርምጃ ይወስዳል።—መዝ. 37:5

በሚስቱ ላይ አካላዊ ጥቃት የሚሰነዝር ወይም የሚሳደብ ባል ከይሖዋም ሆነ ከሚስቱ ጋር ያለውን ዝምድና ለማስተካከል አንዳንድ እርምጃዎችን መውሰድ ይኖርበታል። አንደኛ፣ ከባድ ችግር እንዳለበት አምኖ ይቀበላል። ከይሖዋ እይታ የተሰወረ ምንም ነገር የለም። (መዝ. 44:21፤ መክ. 12:14፤ ዕብ. 4:13) ሁለተኛ፣ ሚስቱን መበደሉን ይተዋል፤ እንዲሁም ባሕሪውን ያስተካክላል። (ምሳሌ 28:13) ሦስተኛ፣ ሚስቱን ይቅርታ ይጠይቃል፤ የይሖዋንም ምሕረት ይለምናል። (ሥራ 3:19) ከዚህም በተጨማሪ፣ ለውጥ ለማድረግ እንዲያነሳሳው እንዲሁም አስተሳሰቡን፣ ንግግሩንና ተግባሩን ለመቆጣጠር እንዲረዳው ይሖዋን ይለምናል። (መዝ. 51:10-12፤ 2 ቆሮ. 10:5፤ ፊልጵ. 2:13) አራተኛ፣ ለማንኛውም ዓይነት ዓመፅና ስድብ ጥላቻ ለማዳበር ጥረት በማድረግ ከጸሎቱ ጋር የሚስማማ እርምጃ ይወስዳል። (መዝ. 97:10) አምስተኛ፣ በጉባኤው ውስጥ ካሉ አፍቃሪ እረኞች እርዳታ ለማግኘት አፋጣኝ እርምጃ ይወስዳል። (ያዕ. 5:14-16) ስድስተኛ፣ ወደፊት እነዚህ ልማዶች እንዳያገረሹበት የሚረዳው ዕቅድ ያወጣል። w25.01 10 አን. 14

ረቡዕ፣ ጥር 21

ታዲያ አሁን ምን ትጠብቃለህ? ተነስና ተጠመቅ።—ሥራ 22:16

ይሖዋን ትወደዋለህ? መልካም ስጦታዎችን ሁሉ ሌላው ቀርቶ ሕይወት እንኳ ያገኘኸው ከእሱ ነው። ታዲያ ለእሱ ያለህን ፍቅር ማሳየት አትፈልግም? ይህን ማድረግ የምትችልበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ ራስህን ለእሱ መወሰንና ይህን ውሳኔህን በውኃ በመጠመቅ ማሳየት ነው። እነዚህን እርምጃዎች ስትወስድ በይሖዋ ቤተሰብ ውስጥ ትታቀፋለህ። በዚህም ምክንያት፣ አባትህና ወዳጅህ የሆነው ይሖዋ ይመራሃል እንዲሁም ይንከባከብሃል፤ ምክንያቱም አሁን የእሱ ንብረት ነህ። (መዝ. 73:24፤ ኢሳ. 43:1, 2) ራስህን ወስነህ መጠመቅህ ለዘላለም በደስታ መኖር የምትችልበት አጋጣሚም ይከፍትልሃል። (1 ጴጥ. 3:21) እንዳትጠመቅ የሚይዝህ ነገር አለ? ይህ ሁኔታ የገጠመህ አንተ ብቻ አይደለህም። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ለጥምቀት ብቁ ለመሆን በምግባራቸውና በአስተሳሰባቸው ላይ ለውጥ ማድረግ አስፈልጓቸዋል። እነዚህ ክርስቲያኖች አሁን ይሖዋን በደስታና በቅንዓት እያገለገሉ ነው። w25.03 2 አን. 1-2

ሐሙስ፣ ጥር 22

በአንተ ዘንድ በእርግጥ ይቅርታ አለ።—መዝ. 130:4

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ኃጢአት ከከባድ ሸክም ጋር ተመሳስሏል። ንጉሥ ዳዊት፣ የሠራቸውን ኃጢአቶች አስመልክቶ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “የፈጸምኳቸው ስህተቶች በራሴ ላይ ያንዣብባሉና፤ እንደ ከባድ ሸክም በጣም ከብደውኛል።” (መዝ. 38:4) ሆኖም ይሖዋ ንስሐ የገቡ ሰዎችን ኃጢአት ይቅር ይላል። (መዝ. 25:18፤ 32:5) በእነዚህ ጥቅሶች ላይ “ይቅር ማለት” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ አገላለጽ “ማንሳት” ወይም “መሸከም” የሚል ትርጉም አለው። ይሖዋ በምሳሌያዊ ሁኔታ የኃጢአታችንን ሸክም ከትከሻችን ላይ እንደሚያነሳና ተሸክሞ እንደሚወስድልን ሊቆጠር ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ ኃጢአታችንን ምን ያህል ከእኛ አርቆ እንደሚወስደው የሚያሳይ ሌላ ዘይቤያዊ አገላለጽ ይጠቀማል። መዝሙር 103:12 “ምሥራቅ ከምዕራብ እንደሚርቅ፣ በደላችንን ከእኛ አራቀ” ይላል። ምሥራቅና ምዕራብ በተለያዩ ጽንፎች የሚገኙ አቅጣጫዎች ናቸው። ፈጽሞ ሊገናኙም አይችሉም። በሌላ አባባል፣ ይሖዋ ኃጢአታችንን ከምንገምተው በላይ ከእኛ አርቆ ይወስደዋል ማለት ነው። የይሖዋን ይቅርታ የሚያሳይ እንዴት ያለ የሚያጽናና አገላለጽ ነው! w25.02 9 አን. 5-6

ዓርብ፣ ጥር 23

ምጽዋት በምትሰጡበት ጊዜ [አስቀድማችሁ] መለከት [አታስነፉ]።—ማቴ. 6:2

ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከተመለሰ በኋላ ሐዋርያው ጴጥሮስ አንድ ተአምር ፈጽሞ ነበር፤ ይህም ሲወለድ ጀምሮ ሽባ የነበረን ሰው መፈወስ ነው። (ሥራ 1:8, 9፤ 3:2, 6-8) እንደሚጠበቀው ይህ አስደናቂ ክስተት የብዙኃኑን ትኩረት ሳበ። (ሥራ 3:11) ከበሬታና ተደማጭነት ትልቅ ቦታ በሚሰጠው ማኅበረሰብ ውስጥ ያደገው ጴጥሮስ ምን ያደርግ ይሆን? ሰዎቹ የሚሰጡትን ክብር ይቀበል ይሆን? በፍጹም። ጴጥሮስ የሕዝቡ ትኩረት በእሱ ላይ እንዲያርፍ አላደረገም፤ ከዚህ ይልቅ ለይሖዋና ለኢየሱስ በትሕትና እውቅና ሰጠ። “የኢየሱስ ስምና እኛ በስሙ ላይ ያለን እምነት ይህን የምታዩትንና የምታውቁትን ሰው አጠነከረው” አለ። (ሥራ 3:12-16) ትሕትና በማዳበር ረገድ የጴጥሮስን ምሳሌ መከተል እንችላለን። ለሌሎች መልካም የምናደርገው ይሖዋንና ሰዎችን ስለምንወድ እንጂ አድናቆት ለማትረፍ ብለን አይደለም። ትሑቶች ከሆንን የምናከናውነውን ተግባር ሌሎች አዩትም አላዩት ይሖዋንና ወንድሞቻችንን ለማገልገል በደስታ የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን።—ማቴ. 6:1-4፤ w25.03 10-11 አን. 11-12

ቅዳሜ፣ ጥር 24

ለራስህና ለምታስተምረው ትምህርት ምንጊዜም ትኩረት ስጥ።—1 ጢሞ. 4:16

ለይሖዋ እና ለሰዎች ባለን ፍቅር ላይ በማተኮር ለስብከቱ ሥራ ያለንን ቅንዓት ማሳደግ እንችላለን። (ማቴ. 22:37-39) ይሖዋ በዚህ ሥራ ስንካፈል ምን ያህል እንደሚደሰትና ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ሲጀምሩ የሚሰማቸውን ደስታ በዓይነ ሕሊናህ ለመሣል ሞክር! ለመልእክታችን አዎንታዊ ምላሽ የሚሰጡ ሰዎች ስለሚያገኙት መዳንም አስብ። (ዮሐ. 6:40) ሁኔታህ ከቤት ለመውጣት የማይፈቅድልህ ከሆነስ? እንዲህ ከሆነ፣ ለይሖዋና ለሰዎች ያለህን ፍቅር ለማሳየት ማድረግ በምትችለው ነገር ላይ አተኩር። በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት ሳሙኤል እና ዳኒያ በቤታቸው ለመቆየት ተገደው ነበር። በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ አዘውትረው በስልክና በደብዳቤ ምሥክርነት ይካፈሉ እንዲሁም በዙም አማካኝነት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ይመሩ ነበር። ሳሙኤል እና ዳኒያ ሁኔታቸው ቢገድባቸውም የሚችሉትን ነገር ሁሉ አድርገዋል፤ በዚህም ደስታ አግኝተዋል። w24.04 18-19 አን. 15-16

እሁድ፣ ጥር 25

ባለሙያ ሚስትን ማን ሊያገኛት ይችላል? ዋጋዋ ከዛጎል እጅግ ይበልጣል።—ምሳሌ 31:10

ደስተኛ ለመሆን ትዳር መመሥረት የግድ አስፈላጊ ባይሆንም ወጣትም ሆኑ አረጋውያን በርካታ ያላገቡ ክርስቲያኖች ማግባት ይፈልጋሉ። እርግጥ ነው፣ መጠናናት ከመጀመርህ በፊት በኢኮኖሚ፣ በመንፈሳዊና በስሜታዊ ለትዳር ዝግጁ መሆን ይኖርብሃል። (1 ቆሮ. 7:36) መጠናናት ከመጀመርህ በፊት ምን ዓይነት የትዳር ጓደኛ እንደምትፈልግ ቆም ብለህ ማሰብህ ጠቃሚ ነው። እንዲህ ካላደረግክ፣ ጥሩ የትዳር አጋር ልትሆንህ የምትችልን ሴት ችላ ብለህ ልታልፍ ወይም ከማትሆንህ ሴት ጋር መጠናናት ልትጀምር ትችላለህ። እርግጥ ነው፣ ለትዳር የምታስባት ሴት የተጠመቀች ክርስቲያን መሆን አለባት። (1 ቆሮ. 7:39) ያም ቢሆን ሁሉም የተጠመቁ እህቶች ጥሩ የትዳር አጋር ይሆኑሃል ማለት አይደለም። ስለዚህ ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘ግቤ ምንድን ነው? ላገባት የማስባት እህት የግድ እንዲኖሯት የምፈልጋቸው ባሕርያት የትኞቹ ናቸው? የምጠብቀው ነገር ምክንያታዊ ነው?’ w24.05 20 አን. 1፤ 21 አን. 3

ሰኞ፣ ጥር 26

አንዳችሁ ለሌላው ደጎች . . . ሁኑ።—ኤፌ. 4:32

በምትጠናኑበት ጊዜ አልፎ አልፎ የሚያጋጥሙ ችግሮችንና አለመግባባቶችን መፍታት የምትችሉት እንዴት ነው? አለመግባባት መፈጠሩ የምትጣጣሙ ሰዎች አይደላችሁም ማለት ነው? ላይሆን ይችላል፤ ሁሉም ጥንዶች አለመግባባት ያጋጥማቸዋል። ጠንካራ ትዳር ልዩነቶቻቸውን ለማሸነፍ ተባብረው መሥራት የሚችሉ ሁለት ሰዎች ጥምረት ነው። ስለዚህ በአሁኑ ወቅት ችግሮቻችሁን የምትፈቱበት መንገድ የሰመረ ትዳር መመሥረት የምትችሉ መሆን አለመሆኑን ሊጠቁም ይችላል። እንዲህ እያላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ፦ ‘በእርጋታና በአክብሮት መወያየት እንችላለን? ድክመቶቻችንን አምነን ለመቀበልና ማሻሻያ ለማድረግ ፈቃደኞች ነን? እሺ ለማለት፣ ይቅርታ ለመጠየቅና ይቅር ለማለት ፈጣኖች ነን?’ (ኤፌ. 4:31) ይሁንና በምትጠናኑበት ወቅት ሁልጊዜ የምትጣሉ ወይም የምትጨቃጨቁ ከሆነ ከተጋባችሁ በኋላ ሁኔታው ይሻሻላል ብሎ መጠበቅ ምክንያታዊ አይደለም። ግለሰቡ ለእናንተ እንደማይሆናችሁ ከተገነዘባችሁ ግንኙነታችሁን ማቆሙ ለሁለታችሁም የተሻለ ነው። w24.05 29 አን. 12

ማክሰኞ፣ ጥር 27

እጆቼን ለውጊያ . . . የሚያሠለጥነው፣ ዓለቴ የሆነው ይሖዋ ይወደስ።—መዝ. 144:1

ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ ቆራጥ ከሆንንና በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ የተመሠረቱ ውሳኔዎችን የምናደርግ ከሆነ በሌሎች ላይ በጎ ተጽዕኖ እናሳድራለን። በእምነትና በትክክለኛ እውቀት እያደግን ስንሄድ በእውነት ውስጥ ሥር እንሰዳለን። ወላዋይ፣ ጽኑ አቋም የሌለን ወይም በሐሰት ትምህርቶችና በዓለም አስተሳሰብ እየተገፋን በቀላሉ ወዲያና ወዲህ የምንዋልል ሰዎች አይደለንም። (ኤፌ. 4:14፤ ያዕ. 1:6-8) መከራ ያጋጠማቸውን ሰዎች መርዳትም እንችላለን። (1 ተሰ. 3:2, 3) ሽማግሌዎች በልማዶቻቸው ልከኛ፣ ጤናማ አስተሳሰብ ያላቸው፣ ሥርዓታማና ምክንያታዊ መሆን ይጠበቅባቸዋል። እነዚህ ወንዶች ‘የታመነውን ቃል በጥብቅ በመከተል’ ሌሎች ጠንካራ አቋም እንዲኖራቸው ይረዳሉ። (ቲቶ 1:9፤ 1 ጢሞ. 3:1-3) ሽማግሌዎች ጥሩ ምሳሌ በመሆንና እረኝነት በማድረግ አስፋፊዎች አዘውትረው በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ እንዲገኙ፣ በአገልግሎት እንዲካፈሉ እንዲሁም የግል ጥናት እንዲያደርጉ ይረዳሉ። ሽማግሌዎች፣ ወንድሞችና እህቶች አስጨናቂ ሁኔታ ሲያጋጥማቸው በይሖዋና በዓላማዎቹ ላይ እንዲያተኩሩ ሊረዷቸው ይችላሉ። w24.06 31 አን. 16-18

ረቡዕ፣ ጥር 28

መንግሥተ ሰማያት ስለቀረበ ንስሐ ግቡ።—ማቴ. 4:17

ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት አባቱ ምን ያህል ይቅር ባይ እንደሆነ አስተምሯል። የአባካኙን ልጅ ምሳሌ እንመልከት። ያ ወጣት ለተወሰነ ጊዜ ያህል የኃጢአት ጎዳና ለመከተል መርጦ ነበር። ያም ቢሆን “ወደ ልቦናው ሲመለስ” ወደ ቤቱ ሄደ። በዚህ ጊዜ አባቱ ምን አደረገ? ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “[ልጁ] ገና ሩቅ ሳለም አባቱ አየው፤ . . . እየሮጠ ሄዶም አንገቱ ላይ ተጠምጥሞ ሳመው።” ልጁ ከአባቱ አገልጋዮች እንደ አንዱ ተደርጎ ለመቆጠር ፈቃደኛ ነበር። አባቱ ግን “ይህ ልጄ” በማለት ጠርቶታል፤ በድጋሚ የቤተሰቡ አባል አድርጎም ተቀብሎታል። አባቱ “ጠፍቶ ነበር፤ ተገኝቷል” ብሏል። (ሉቃስ 15:11-32) ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት ሰማይ ላይ ሳለ አባቱ ስፍር ቁጥር ለሌላቸው ንስሐ የገቡ ኃጢአተኞች እንዲህ ያለ ርኅራኄ ሲያሳይ እንደተመለከተ ምንም ጥያቄ የለውም። ኢየሱስ የተናገረው ልብ የሚነካ ታሪክ አባታችን ይሖዋ እጅግ መሐሪ እንደሆነ ያሳያል። ይህ ምንኛ የሚያጽናና ነው! w24.08 11 አን. 11-12

ሐሙስ፣ ጥር 29

ጤናማ አስተሳሰብ ይኑራችሁ።—1 ጴጥ. 4:7

ጤናማ አስተሳሰብ ያለው አንድ ክርስቲያን ውሳኔ ሲያደርግ የይሖዋን አስተሳሰብ ለማንጸባረቅ ይጥራል። በሕይወቱ ውስጥ ከይሖዋ ጋር ካለው ዝምድና በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ነገር እንደሌለ ይገነዘባል። ስለ ራሱ ሚዛናዊ አመለካከት አለው፤ የማያውቃቸው ነገሮች እንዳሉም ይረዳል። ደግሞም ምንጊዜም የይሖዋ እርዳታ እንደሚያስፈልገው በትሕትና ስለሚገነዘብ አዘውትሮ ይጸልያል። ምንም ዓይነት ተፈጥሯዊ ተሰጥኦ ቢኖረን ምንጊዜም የይሖዋን እርዳታ መጠየቅ አስፈላጊ እንደሆነ እንገነዘባለን። በተለይ ከበድ ያሉ ውሳኔዎችን ከማድረጋችን በፊት ይሖዋ እንዲመራን እንጸልያለን፤ ምክንያቱም ለእኛ የሚበጀውን የሚያውቀው እሱ እንደሆነ እንተማመናለን። ይሖዋ የእሱን ባሕርያት ማንጸባረቅ እንድንችል አድርጎ ስለፈጠረን በጣም አመስጋኞች ነን። (ዘፍ. 1:26) ይሖዋን ፍጹም በሆነ መንገድ መምሰል እንደማንችል የታወቀ ነው።—ኢሳ. 55:9፤ w25.03 11 አን. 13፤ 13 አን. 17-18

ዓርብ፣ ጥር 30

[ፍቅር] ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፣ ሁሉን ነገር በጽናት ይቋቋማል።—1 ቆሮ. 13:7

ሌሎች አመስጋኝ አይደሉም ብለህ ለመደምደም አትቸኩል። ላደረግነው ነገር ሌሎች ባያመሰግኑን እንዲህ እያልን ራሳችንን መጠየቅ እንችላለን፦ ‘በእርግጥ ግለሰቡ አመስጋኝ ስላልሆነ ነው? ወይስ ማመስገን ስለረሳ ነው?’ ግለሰቡ የጠበቅነውን ምላሽ ያልሰጠበት ሌላም ምክንያት ሊኖር ይችላል። አንዳንዶች በልባቸው የአመስጋኝነት ስሜት ቢኖራቸውም ስሜታቸውን መግለጽ ሊከብዳቸው ይችላል። በተለይ ቀደም ሲል ሌሎችን የመርዳት ልማድ ከነበራቸው እርዳታ መቀበል ሊያሳፍራቸው ይችላል። ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን፣ ለሌሎች ክርስቲያናዊ ፍቅር ካለን ስለ እነሱ ቀና ቀናውን ማሰብ ይቀለናል፤ እንዲሁም በመስጠት ደስታ ማግኘት እንችላለን። (ኤፌ. 4:2) ታጋሽ ሁን። ጠቢቡ ንጉሥ ሰለሞን ልግስና ከማሳየት ጋር በተያያዘ እንዲህ ብሏል፦ “ቂጣህን በውኃ ላይ ጣል፤ ከብዙ ቀናት በኋላ መልሰህ ታገኘዋለህና።” (መክ. 11:1) እነዚህ ቃላት እንደሚያሳዩት አንዳንዶች ልግስና ካሳየናቸው “ከብዙ ቀናት በኋላ” ምላሽ ሊሰጡ ይችላሉ። w24.09 30 አን. 18-19

ቅዳሜ፣ ጥር 31

ለሌሎቹ ማስጠንቀቂያ እንዲሆን ኃጢአት የመሥራት ልማድ ያላቸውን ሰዎች በሁሉ ፊት ውቀሳቸው።—1 ጢሞ. 5:20

አንዳንድ ጊዜ አንድ ሰው ወቀሳ እንደተሰጠው ማስታወቂያ ሊነገር ይችላል። በዚህ ጊዜ ይህ ሰው ንስሐ እንደገባና መጥፎ ድርጊቱን እንደተወ ስለምንገነዘብ ከእሱ ጋር መወዳጀታችንን መቀጠል እንችላለን። ይህ ሰው አሁንም የጉባኤው ክፍል ነው፤ ደግሞም ከእምነት አጋሮቹ ጋር ጊዜ በማሳለፍ ማበረታቻ ማግኘት ያስፈልገዋል። (ዕብ. 10:24, 25) አንድ ሰው ከጉባኤ ሲወገድ ግን ሁኔታው ከዚህ በጣም የተለየ ነው። እንዲህ ካለው ሰው ጋር ‘መግጠማችንን እንተዋለን፤ አብረነው ምግብ እንኳ አንበላም።’ (1 ቆሮ. 5:11) ይህ ሲባል ጨርሶ አናነጋግረውም ማለት ነው? እንደዚያ ማለት ላይሆን ይችላል። ከእሱ ጋር ጊዜ እንደማናሳልፍ የታወቀ ነው። ሆኖም ክርስቲያኖች የተወገደውን ሰው ወደ ጉባኤ ስብሰባ ለመጋበዝ በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ሕሊናቸውን ተጠቅመው ሊወስኑ ይችላሉ፤ ምናልባትም ግለሰቡ ዘመዳቸው ወይም ይቀርቡት የነበረ ሰው ሊሆን ይችላል። w24.08 30 አን. 13-14

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2026)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2026 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ