የካቲት
እሁድ፣ የካቲት 1
ሰው ከጠብ መራቁ ያስከብረዋል፤ ሞኝ የሆነ ሁሉ ግን ጥል ውስጥ ይዘፈቃል።—ምሳሌ 20:3
ግሩም ክርስቲያናዊ ባሕርያትን የሚያንጸባርቁ ወንድሞች ለጉባኤው ውድ ሀብት ናቸው። ምክንያታዊ የሆነ ሰው ሰላም ያሰፍናል። ምክንያታዊ በመሆንህ መታወቅ የምትፈልግ ከሆነ ሌሎች ሲናገሩ አዳምጥ፤ እንዲሁም አመለካከታቸውን ለማስተናገድ ፈቃደኛ ሁን። ለምሳሌ በሽማግሌዎች ስብሰባ ወቅት የመጽሐፍ ቅዱስ ሕግ ወይም መሠረታዊ ሥርዓት እስካልተጣሰ ድረስ የብዙሃኑን ውሳኔ ለመደገፍ ፈቃደኛ ትሆናለህ? ‘እኔ ያልኩት ካልሆነ’ ብለህ ድርቅ አትበል። ብዙ አማካሪዎች መኖራቸው ጥቅም እንዳለው ልትገነዘብ ይገባል። (ዘፍ. 13:8, 9፤ ምሳሌ 15:22) ሻካራ ወይም ብስጩ ከመሆን ይልቅ ገርና ዘዴኛ ሁን። ሰላማዊ ሰው በመሆን ውጥረት በሚፈጥሩ ሁኔታዎች ውስጥም ሰላም ለመፍጠር ቅድሚያውን ውሰድ። (ያዕ. 3:17, 18) ደግነት የሚንጸባረቅባቸው ቃላት መጠቀምህ የተቃዋሚዎችን ልብ ሳይቀር ሊያለሰልስ ይችላል።—መሳ. 8:1-3፤ ምሳሌ 25:15፤ ማቴ. 5:23, 24፤ w24.11 23 አን. 13
ሰኞ፣ የካቲት 2
መላእክቱን ልኮ ከአራቱ ነፋሳት፣ ከምድር ዳርቻ እስከ ሰማይ ዳርቻ ለእሱ የተመረጡትን ይሰበስባል።—ማር. 13:27
ኢየሱስ የሞተው “ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ” ቢሆንም አሁንም ብዙ ነገሮችን እያደረገልን ነው። (ሮም 6:10) እንዴት? ከቤዛው ጥቅም እንድናገኝ አሁንም እየሠራ ነው። እስቲ ምን እያደረገ እንደሆነ ለማሰብ ሞክር። ንጉሣችን፣ ሊቀ ካህናታችንና የጉባኤው ራስ ሆኖ እያገለገለ ነው። (1 ቆሮ. 15:25፤ ኤፌ. 5:23፤ ዕብ. 2:17) ታላቁ መከራ ከማብቃቱ በፊት የሚጠናቀቀውን ቅቡዓኑንና እጅግ ብዙ ሕዝብን የመሰብሰቡን ሥራ በበላይነት እየመራ ነው። (ማቴ. 25:32) በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ታማኝ አገልጋዮቹ የሚያስፈልጋቸውን መንፈሳዊ ምግብ እንዲያገኙ እያደረገ ነው። (ማቴ. 24:45) በሺህ ዓመት ግዛቱም እኛን የሚጠቅሙ ነገሮችን ማከናወኑን ይቀጥላል። በእርግጥም ይሖዋ ልጁን የሰጠን እንዲሞትልን ብቻ ሳይሆን የሚጠቅሙንን ብዙ ነገሮች እንዲያደርግልንም ጭምር ነው። w25.01 24 አን. 12
ማክሰኞ፣ የካቲት 3
ክርስቶስ ኢየሱስ የከፈለው ቤዛ በሚያስገኘው ነፃነት አማካኝነት በጸጋው ጻድቃን ናችሁ መባላቸው እንዲሁ የተገኘ ነፃ ስጦታ ነው።—ሮም 3:24
ይሖዋ ይቅር የሚለው በተሟላ ሁኔታና በዘላቂነት ነው። ይህም ከሰማዩ አባታችን ጋር ጥሩ ዝምድና እንዲኖረን ያስችለናል። በሌላ በኩል ደግሞ እውነተኛ ይቅርታ ስጦታ እንደሆነ ማስታወስ ይኖርብናል። ይሖዋ እንዲህ ያለውን ይቅርታ የሚያደርግልን ኃጢአተኛ ለሆኑ የሰው ልጆች ባለው ፍቅርና በጸጋው ተነሳስቶ ነው። እንዲህ ያለው ይቅርታ ማንም ሰው ይገባኛል የሚለው መብት አይደለም። ይሖዋ እውነተኛ ይቅርታ የሚያሳይ አምላክ በመሆኑ ሁላችንም በጣም አመስጋኞች ነን! (መዝ. 130:4፤ ሮም 4:8) ይሁንና ለኃጢአታችን ይቅርታ ማግኘታችን የተመካው በአንድ አስፈላጊ ነገር ላይ ነው። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “የበደሏችሁን ሰዎች ይቅር ካላላችሁ አባታችሁም በደላችሁን ይቅር አይላችሁም።” (ማቴ. 6:14, 15) በግልጽ ማየት እንደሚቻለው፣ የይሖዋን ይቅርታ መኮረጃችን በጣም አስፈላጊ ነው። w25.02 13 አን. 18-19
ረቡዕ፣ የካቲት 4
ጻድቃንም ሆኑ ጻድቃን ያልሆኑ ሰዎች ከሞት [ይነሳሉ]።—ሥራ 24:15
በሰዶምና በገሞራ የነበሩትን ሰዎች ሁኔታ እንመልከት። ጻድቅ ሰው የነበረው ሎጥ በመካከላቸው ይኖር ነበር። ይሁንና ሎጥ ለሁሉም ሰብኮላቸው እንደነበር በእርግጠኝነት እናውቃለን? አናውቅም። ሁሉም ክፉዎች እንደነበሩ ምንም ጥያቄ የለውም፤ ግን ሁሉም ክፉና ደጉን የሚያውቁ ሰዎች ነበሩ? በዚያ ከተማ የነበሩ ብዙ ወንዶች ተሰብስበው የሎጥን እንግዶች ለመድፈር እንደመጡ አስታውስ። መጽሐፍ ቅዱስ ከእነዚህ ሰዎች መካከል ‘ልጆችም’ እንደነበሩ ይናገራል። (ዘፍ. 19:4፤ 2 ጴጥ. 2:7) መሐሪ አምላክ የሆነው ይሖዋ ማናቸውም ትንሣኤ አይገባቸውም ብሎ እንደፈረደ በእርግጠኝነት መናገር እንችላለን? ይሖዋ በከተማዋ ውስጥ አሥር ጻድቃን እንኳ እንደሌሉ ለአብርሃም ነግሮታል። (ዘፍ. 18:32) ስለዚህ ሰዎቹ ጻድቃን እንዳልነበሩ ግልጽ ነው፤ በመሆኑም ይሖዋ ለድርጊታቸው ተጠያቂ ያደረጋቸው መሆኑ ተገቢ ነው። ይሁንና አንዳቸውም “ጻድቃን ያልሆኑ ሰዎች” በሚያገኙት ትንሣኤ ውስጥ እንደማይካተቱ በእርግጠኝነት መናገር እንችላለን? አንችልም! w24.05 2 አን. 3፤ 3 አን. 8
ሐሙስ፣ የካቲት 5
ከሁሉ አስቀድማችሁ የአምላክን መንግሥትና ጽድቅ ፈልጉ፤ እነዚህም ነገሮች ሁሉ ይሰጧችኋል።—ማቴ. 6:33
አንዳንዶች ባጋጠማቸው የኢኮኖሚ ችግር የተነሳ ከቤተሰባቸው ተለይተው መኖርን የሚጠይቅ የሥራ አጋጣሚ ለመቀበል ተፈትነዋል። ይህ ግን ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ እንዳልሆነ በተደጋጋሚ ታይቷል። ሥራ ስትመርጥ ከገንዘብ አንጻር የሚያስገኝልህን ጥቅም ብቻ ሳይሆን በመንፈሳዊነትህ ረገድ የሚያስከፍልህን ነገርም ግምት ውስጥ አስገባ። (ሉቃስ 14:28) ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘ከትዳር ጓደኛዬ ተለይቼ መኖሬ በትዳሬ ላይ ምን ተጽዕኖ ይኖረዋል? ርቄ መሄዴ የስብሰባና የአገልግሎት ልማዴን እንዲሁም ከወንድሞች ጋር የማሳልፈውን ጊዜ የሚነካብኝ እንዴት ነው?’ ልጆች ካሉህ ደግሞ ልታነሳው የሚገባ ሌላ አስፈላጊ ጥያቄም አለ፦ ‘ከልጆቼ ጋር በአካል አብሬያቸው ካልሆንኩ “በይሖዋ ተግሣጽና ምክር” ላሳድጋቸው የምችለው እንዴት ነው?’ (ኤፌ. 6:4) ውሳኔ ስታደርግ በአምላክ አስተሳሰብ እንጂ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ተግባራዊ በማያደርጉ የቤተሰብ አባላት ወይም ወዳጆች አመለካከት አትመራ። w25.03 29 አን. 12
ዓርብ፣ የካቲት 6
ከእንግዲህ ሕፃናት መሆን የለብንም።—ኤፌ. 4:14
ያልጎለመሰ ክርስቲያን ‘በማታለያ ዘዴና በተንኮል በተወጠነ አሳሳች ሐሳብ’ በቀላሉ ይታለላል፤ የሴራ ተንታኞችንና ከሃዲዎችን ሊያምን ይችላል። በሌሎች የመቅናት፣ ክፍፍል የመፍጠር፣ በቀላሉ የመበሳጨት ወይም ለፈተና እጅ የመስጠት ዝንባሌ ይኖረው ይሆናል። (1 ቆሮ. 3:3) መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ክርስቲያን ወደ ጉልምስና ደረጃ የሚደርስበትን መንገድ አንድ ሕፃን እድገት ከሚያደርግበት መንገድ ጋር ያመሳስለዋል። (ኤፌ. 4:15) ሕፃናት ማስተዋል ይጎድላቸዋል፤ ክትትልም ያስፈልጋቸዋል። ለምሳሌ አንዲት እናት፣ ልጇ ትንሽ ሳለች እጇን ይዛ መንገድ ታሻግራት ይሆናል። ልጅቷ እያደገች ስትሄድ ግን ብቻዋን መንገድ እንድትሻገር እናቷ ትፈቅድላት ይሆናል፤ ያም ቢሆን መንገድ ስትሻገር ግራ ቀኟን እንድታይ ታሳስባታለች። ልጅቷ አዋቂ ከሆነች በኋላ ግን እንዲህ ካሉ አደገኛ ሁኔታዎች ራሷን መጠበቅ ትችላለች። የጎለመሱ ክርስቲያኖችም የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በመጠቀም ይሖዋ ስለ ጉዳዩ ያለውን አመለካከት ለማወቅ ጥረት ያደርጋሉ፤ ከዚያም ተገቢውን ውሳኔ ይወስናሉ። w24.04 3 አን. 5-6
ቅዳሜ፣ የካቲት 7
ይሖዋ ሆይ፣ በድንኳንህ ውስጥ በእንግድነት የሚስተናገድ ማን ነው?—መዝ. 15:1
ለተወሰነ ጊዜ ያህል ይሖዋ ወዳጆች የነበሩት እሱ በሚኖርበት በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ ብቻ ነበር። በኋላ ግን ሰዎችን ፈጠረ። በዚህ መንገድ ድንኳኑን በማስፋት በምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎችንም እንዲያካትት አደረገ። ከይሖዋ እንግዶች መካከል ሄኖክ፣ ኖኅ፣ አብርሃምና ኢዮብ ይገኙበታል። እነዚህ ሰዎች የአምላክ ወዳጆች እንደሆኑ ወይም ‘ከእውነተኛው አምላክ ጋር እንደሄዱ’ ተገልጿል። (ዘፍ. 5:24፤ 6:9፤ ኢዮብ 29:4፤ ኢሳ. 41:8) ባለፉት ዘመናት ሁሉ ይሖዋ ወዳጆቹን ወደ ድንኳኑ ሲጋብዝ ቆይቷል። (ሕዝ. 37:26, 27) ለምሳሌ የሕዝቅኤል ትንቢት፣ አምላክ ታማኝ አገልጋዮቹ ከእሱ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንዲኖራቸው እንደሚፈልግ ያሳያል። ከእነሱ ጋር ‘የሰላም ቃል ኪዳን እንደሚገባ’ ተናግሯል። ይህ ትንቢት ሰማያዊ ተስፋ ያላቸውና ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖች በምሳሌያዊ ድንኳኑ ውስጥ “አንድ መንጋ” የሚሆኑበት ጊዜ እንደሚመጣ ያሳያል። (ዮሐ. 10:16) ይህ ትንቢት በአሁኑ ጊዜ እየተፈጸመ ነው። w24.06 2 አን. 2፤ 3 አን. 4-5
እሁድ፣ የካቲት 8
በአምላካችን እርዳታ እንደ ምንም ብለን ድፍረት አገኘን።—1 ተሰ. 2:2
የይሖዋ ሕዝቦች እንደመሆናችን መጠን በሙሉ ልባችን ከአምላክ መንግሥት ጎን እንቆማለን። ሆኖም ብዙውን ጊዜ እንዲህ ማድረግ ድፍረት ይጠይቃል። (ማቴ. 6:33) ለምሳሌ በዚህ ክፉ ዓለም ውስጥ በይሖዋ መሥፈርቶች ለመመራትና የመንግሥቱን ምሥራች ለመስበክ ድፍረት ያስፈልገናል። በተጨማሪም ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በፖለቲካዊ ጉዳዮች በተከፋፈለው በዚህ ዓለም ውስጥ ገለልተኝነታችንን መጠበቅ ድፍረት ይጠይቃል። (ዮሐ. 18:36) በፖለቲካዊ ወይም በወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ለመካፈል ፈቃደኛ ባለመሆናቸው የተነሳ የገንዘብ ኪሳራ የደረሰባቸው፣ አካላዊ ጥቃት የተሰነዘረባቸው አልፎ ተርፎም የታሰሩ በርካታ የይሖዋ ሕዝቦች አሉ። በድፍረት ከይሖዋ አገዛዝ ጎን የቆሙ ሰዎችን ምሳሌ መመርመራችን ብርታትና ድፍረት ይሰጠናል። ንጉሣችን ክርስቶስ ኢየሱስ በሰይጣን ፖለቲካዊ ሥርዓት ውስጥ እጁን እንዲያስገባ የተደረገበትን ጫና በጽናት ተቋቁሟል። (ማቴ. 4:8-11፤ ዮሐ. 6:14, 15) ብርታት ለማግኘት ምንጊዜም በይሖዋ ይታመን ነበር። w24.07 3 አን. 4፤ 4 አን. 7
ሰኞ፣ የካቲት 9
ከዛፉ ፍሬ ወስዳ በላች። ባሏም አብሯት ሲሆን ለእሱም ሰጠችው፤ እሱም በላ።—ዘፍ. 3:6
ይሖዋ ይህ አሳዛኝ ታሪክ እንዲጻፍ ያደረገው ለእኛ ጥቅም ነው። ይህ ታሪክ፣ ይሖዋ ኃጢአትን በጣም የሚጠላው ለምን እንደሆነ እንድንገነዘብ ይረዳናል። ኃጢአት ከአባታችን ይነጥለናል፤ እንዲሁም ወደ ሞት ይመራናል። (ኢሳ. 59:2) የዚህ ሁሉ ችግር ጠንሳሽ የሆነው ዓመፀኛው ሰይጣን ኃጢአትን የሚወደውና ለማስፋፋት ጥረት የሚያደርገው ለዚህ ነው። ሰይጣን በኤደን ትልቅ ድል እንደተቀዳጀ ተሰምቶት ሊሆን ይችላል። ይሁንና ይሖዋ ምን ያህል አፍቃሪ እንደሆነ አልገባውም። አምላክ ለአዳምና ለሔዋን ዘሮች ያወጣውን ዓላማ አልቀየረም። እሱ ሰዎችን በጣም ስለሚወድ ወዲያውኑ ለሁሉም የሰው ልጆች ተስፋ ሰጠ። (ሮም 8:20, 21) ይሖዋ ከአዳምና ከሔዋን ዘሮች መካከል አንዳንዶቹ እሱን ለመውደድ እንደሚመርጡ እንዲሁም ከኃጢአት ጋር በሚያደርጉት ውጊያ የእሱን እርዳታ እንደሚፈልጉ ያውቅ ነበር። እሱም አባታቸውና ፈጣሪያቸው እንደመሆኑ መጠን ከኃጢአት ነፃ የሚወጡበትንና ወደ እሱ መቅረብ የሚችሉበትን መንገድ ያዘጋጅላቸዋል። w24.08 3 አን. 3-4
ማክሰኞ፣ የካቲት 10
ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይታችሁ [እወቁ]።—ፊልጵ. 1:10
አብዛኞቹ የይሖዋ አገልጋዮች ጊዜያቸው የተጣበበ ነው። ራሳችንንም ሆነ ቤተሰባችንን ለማስተዳደር ሰብዓዊ ሥራ እንሠራለን። (1 ጢሞ. 5:8) ብዙ ክርስቲያኖች የታመሙ ወይም በዕድሜ የገፉ የቤተሰባቸውን አባላት ይንከባከባሉ። እንዲሁም ሁላችንም የራሳችንን ጤና መንከባከብ አለብን፤ ይህም ጊዜ የሚጠይቅ ነገር ነው። ከእነዚህ ሁሉ ነገሮች በተጨማሪ ደግሞ በጉባኤ ውስጥ ኃላፊነቶች አሉብን። በስብከቱ ሥራ በቅንዓት መካፈል ትልቁ ኃላፊነታችን ነው። መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ለክርስቲያኖች ‘ይበልጥ አስፈላጊ ከሆኑት ነገሮች’ መካከል አንዱ ነው፤ ስለዚህ ቅድሚያ ልንሰጠው ይገባል። የመጀመሪያው መዝሙር ስለ ደስተኛ ሰው ሲናገር “በይሖዋ ሕግ ደስ ይለዋል፤ ሕጉንም በቀንና በሌሊት በለሆሳስ ያነበዋል” ይላል። (መዝ. 1:1, 2) ይህ ጥቅስ፣ ለመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ጊዜ መመደብ እንዳለብን በግልጽ ያሳያል። መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ ከሁሉ የተሻለው ጊዜ የትኛው ነው? መልሱ ከሰው ሰው የተለያየ ሊሆን ይችላል። ዋናው ነገር፣ አዘውትረን ለማንበብ የሚቀለንን ጊዜ መምረጣችን ነው። w24.09 3 አን. 5-6
ረቡዕ፣ የካቲት 11
እያንዳንዱ የራሱን የኃላፊነት ሸክም ይሸከማል።—ገላ. 6:5
የጎለመሱ ክርስቲያኖች የሌሎች እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ጊዜ አለ? አዎ። የጎለመሱ ክርስቲያኖች እርዳታ መጠየቅ የሚያስፈልጋቸው ጊዜ ይኖር ይሆናል። ያልጎለመሰ ክርስቲያን፣ ሌሎች ምን ማድረግ እንዳለበት እንዲነግሩት ወይም በእሱ ፋንታ ውሳኔ እንዲያደርጉለት ይጠብቅ ይሆናል። በሌላ በኩል ግን የጎለመሰ ክርስቲያን ከሌሎች ጥበብና ተሞክሮ ለመጠቀም ጥረት ቢያደርግም ይሖዋ “የራሱን የኃላፊነት ሸክም” እንዲሸከም እንደሚጠብቅበት ይገነዘባል። ሁሉም አዋቂዎች አንድ ዓይነት መልክና ቁመና እንደማይኖራቸው ሁሉ የጎለመሱ ክርስቲያኖችም ተለይተው የሚታወቁበት ባሕርይ የተለያየ ሊሆን ይችላል፤ ለምሳሌ በጥበባቸው፣ በድፍረታቸው፣ በልግስናቸው ወይም በአሳቢነታቸው ተለይተው ሊታወቁ ይችላሉ። በተጨማሪም ሁለት የጎለመሱ ክርስቲያኖች በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ የተለያየ መደምደሚያ ላይ ሊደርሱ ይችላሉ፤ ሆኖም ሁለቱም መደምደሚያዎች ቅዱስ ጽሑፋዊ ተቀባይነት ይኖራቸዋል። በተለይ ለሕሊና በተተዉ ጉዳዮች ረገድ እንዲህ ያለ ሁኔታ ሊያጋጥም ይችላል። የጎለመሱ ክርስቲያኖች ይህን ስለሚገነዘቡ እንዲህ ባሉ ጉዳዮች በሌሎች ላይ ለመፍረድ አይቸኩሉም። ከዚህ ይልቅ አንድነታቸውን በመጠበቅ ላይ ትኩረት ያደርጋሉ።—ሮም 14:10፤ 1 ቆሮ. 1:10፤ w24.04 4 አን. 7-8
ሐሙስ፣ የካቲት 12
በጭንቀት በተዋጥኩ ጊዜ፣ አጽናናኸኝ፤ ደግሞም አረጋጋኸኝ።—መዝ. 94:19
የዋጋ ቢስነት ስሜት የሚሰማህ ከሆነ ምን ማድረግ ትችላለህ? በይሖዋ ዘንድ ያለህን ዋጋ የሚያሳዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን አንብብ፤ እንዲሁም አሰላስልባቸው። አንድ ግብ ላይ መድረስ ወይም የሌሎችን ያህል መሥራት ባለመቻልህ ተስፋ ከቆረጥክ ማከናወን ባልቻልከው ነገር ላይ አታተኩር። ይሖዋ ከአንተ በሚጠብቀው ነገር ረገድ ምክንያታዊ ነው። (መዝ. 103:13, 14) አካላዊ፣ ስሜታዊ ወይም ፆታዊ ጥቃት ደርሶብህ ከሆነ ለደረሰብህ ነገር ራስህን አትውቀስ። ጥፋተኛው አንተ አይደለህም! ይሖዋ ተጠያቂ የሚያደርገው ጥፋተኞችን እንጂ ተበዳዮችን አይደለም። (1 ጴጥ. 3:12) ይሖዋ ሌሎችን ለመርዳት ሊጠቀምብህ እንደሚችል አትጠራጠር። በክርስቲያናዊ አገልግሎት ከእሱ ጋር አብረህ እንድትሠራ በመጋበዝ አክብሮሃል። (1 ቆሮ. 3:9) በሕይወትህ ውስጥ ያጋጠመህ ነገር ለሌሎች አዘኔታ እንድታዳብርና ስሜታቸውን እንድትረዳ እንዳስቻለህ ምንም ጥያቄ የለውም። ስለዚህ እነሱን መርዳት ትችላለህ። w24.10 7-8 አን. 6-7
ዓርብ፣ የካቲት 13
አምላክ በትዕግሥት የሚይዛቸውና ቀን ከሌት ወደ እሱ የሚጮኹት ምርጦቹ ፍትሕ እንዲያገኙ አያደርግም? እላችኋለሁ፣ በቶሎ ፍትሕ እንዲያገኙ ያደርጋል።—ሉቃስ 18:7, 8
ይሖዋ ሌሎች እኛን የሚይዙበት መንገድ በጥልቅ ያሳስበዋል። “ይሖዋ ፍትሕን ይወዳል።” (መዝ. 37:28) በተገቢው ጊዜ አገልጋዮቹ “በቶሎ ፍትሕ እንዲያገኙ” እንደሚያደርግ ኢየሱስ ዋስትና ሰጥቶናል። በቅርቡ ደግሞ እስካሁን የደረሰብንን ጉዳት በሙሉ ያስተካክላል፤ እንዲሁም ማንኛውንም ዓይነት የፍትሕ መጓደል ያስወግዳል። (መዝ. 72:1, 2) ጽድቅ የሚሰፍንበትን ጊዜ በምንጠባበቅበት ወቅት ይሖዋ የሚፈጸሙብንን ኢፍትሐዊ ድርጊቶች እንድንቋቋም ይረዳናል። (2 ጴጥ. 3:13) ኢፍትሐዊ ድርጊት ሲፈጸምብን ጥበብ የጎደለው ነገር ከማድረግ መቆጠብ የምንችለው እንዴት እንደሆነ ያስተምረናል። ይህን የሚያደርግበት አንዱ መንገድ ልጁ በተወው ፍጹም ምሳሌ አማካኝነት ነው። በተጨማሪም ፍትሕ የጎደለው ነገር ሲያጋጥመን ምን ማድረግ እንደምንችል ተግባራዊ ምክር ይሰጠናል። w24.11 2-3 አን. 3-4
ቅዳሜ፣ የካቲት 14
የሚበሉት ነገር ስጧቸው።—ማቴ. 14:16
ኢየሱስ ባዘዘው መሠረት ሕዝቡን መመገብ ቀላል አይደለም። ምክንያቱም በቦታው ሴቶችንና ልጆችን ሳይጨምር 5,000 ገደማ ወንዶች ነበሩ። ስለዚህ ምግብ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር 15,000 ሊደርስ ይችላል። (ማቴ. 14:21) በዚህ ጊዜ እንድርያስ እንዲህ አለ፦ “አምስት የገብስ ዳቦና ሁለት ትናንሽ ዓሣ የያዘ አንድ ትንሽ ልጅ እዚህ አለ። ይህ ግን ለዚህ ሁሉ ሕዝብ እንዴት ይበቃል?” (ዮሐ. 6:9) በወቅቱ የገብስ ዳቦ ድሆችም ሆኑ ሌሎች ሰዎች የሚመገቡት የተለመደ ምግብ ነበር፤ ትናንሾቹ ዓሣዎች ደግሞ በጨው ተቀምመው የደረቁ ሊሆኑ ይችላሉ። ያም ቢሆን ልጁ የያዘው ምግብ ያንን ሁሉ ሰው ለመመገብ ሊበቃ አይችልም። ኢየሱስ ለሕዝቡ ደግነት ማድረግ ስለፈለገ በቡድን በቡድን ሆነው ሣሩ ላይ እንዲቀመጡ አዘዘ። (ማር. 6:39, 40፤ ዮሐ. 6:11-13) ኢየሱስ ለዳቦውና ለዓሣው አባቱን እንዳመሰገነ ዘገባው ይናገራል። ደግሞም እንዲህ ማድረጉ ተገቢ ነበር፤ ምክንያቱም የምግቡ ምንጭ አምላክ ነው። እኛም የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ከመመገባችን በፊት መጸለይ ይኖርብናል። ከዚያም ኢየሱስ ምግቡን አከፋፈለ፤ ሰዎቹም በልተው ጠገቡ። w24.12 3 አን. 3-4
እሁድ፣ የካቲት 15
አምላካችሁን ይሖዋን አወድሱ።—1 ዜና 29:20
ኢየሱስ በምድር ላይ ሳለ፣ ተአምር መሥራት የቻለው በአምላክ እርዳታ እንደሆነ በመናገር ለአባቱ ክብር ሰጥቷል። (ማር. 5:18-20) ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ ስለ አባቱ በተናገረው ነገርና ሰዎችን በያዘበት መንገድ ለይሖዋ ክብር ሰጥቷል። ለምሳሌ በአንድ ወቅት ኢየሱስ በምኩራብ እያስተማረ ነበር። ከሚያዳምጡት ሰዎች መካከል፣ ባደረባት ጋኔን የተነሳ ለ18 ዓመታት ስትሠቃይ የኖረች ሴት ነበረች። ከጋኔኑ የተነሳ በጣም ስለጎበጠች ፈጽሞ ቀና ማለት አትችልም ነበር። እንዴት የሚያሳዝን ነው! ኢየሱስ ለሴትየዋ ስለራራላት ቀረብ ብሎ በደግነት አነጋገራት፤ “አንቺ ሴት፣ ከበሽታሽ ተገላግለሻል” አላት። ከዚያም እጁን ሲጭንባት ወዲያውኑ ቀጥ አለች፤ “አምላክንም ማመስገን ጀመረች።” (ሉቃስ 13:10-13) ሴትየዋ ጤንነቷ ስለተመለሰላት ለአምላክ ክብር ለመስጠት ተነሳስታለች። እኛም እንደ እሷ ለአምላክ ክብር ለመስጠት የሚያነሳሳ አጥጋቢ ምክንያት አለን። w25.01 3 አን. 3-4
ሰኞ፣ የካቲት 16
ኃጢአታችንን ይቅር በለን።—ሉቃስ 11:4
አዳምና ሔዋን ያጡትን ነገር በሙሉ መልሰን ማግኘት እንችላለን? በራሳችን ጥረት አንችልም። (መዝ. 49:7-9) እርዳታ ካላገኘን፣ ወደፊት በሕይወት የመኖርም ሆነ ከሞት የመነሳት ተስፋ አይኖረንም። ልክ እንደ እንስሳት ሞተን እንቀራለን ማለት ነው። (መክ. 3:19፤ 2 ጴጥ. 2:12) የሚወደን አባታችን ይሖዋ ከአዳም የወረስነውን የኃጢአት ዕዳ ለመክፈል የሚያስችል ስጦታ ሰጥቶናል። ኢየሱስ ሁኔታውን ሲያብራራ እንዲህ ብሏል፦ “አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ በልጁ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ሲል አንድያ ልጁን ሰጥቷል።” (ዮሐ. 3:16) በተጨማሪም ይህ ስጦታ ከይሖዋ ጋር ጥሩ ዝምድና መመሥረት የምንችልበት አጋጣሚ ይሰጠናል። ከዚህ ግሩም ስጦታ መጠቀምና ለኃጢአታችን ይቅርታ ማግኘት እንችላለን። w25.02 3 አን. 3-6
ማክሰኞ፣ የካቲት 17
ከዚያም [ሳኦል] ተነስቶ ተጠመቀ።—ሥራ 9:18
ሳኦል እንዲጠመቅ የረዳው ምንድን ነው? ክብር የተጎናጸፈው ጌታ ኢየሱስ ሲገለጥለት ሳኦል ዓይኑ ታወረ። (ሥራ 9:3-9) ከዚያ በኋላ ለሦስት ቀናት ፆመ፤ መንገድ ላይ ስላጋጠመው ነገር አሰላስሎ እንደሚሆንም ጥያቄ የለውም። ሳኦል ኢየሱስ መሲሕ እንደሆነና ተከታዮቹ እውነተኛውን ሃይማኖት እንደያዙ አመነ። ከሳኦል የምናገኛቸው ትምህርቶች አሉ። ኩራት ወይም የሰው ፍርሃት እንዳይጠመቅ እንቅፋት ሊሆንበት ይችል ነበር። እሱ ግን እነዚህ ነገሮች እንዲያሰናክሉት አልፈቀደም። ስደት እንደማይቀርለት ቢያውቅም ክርስቲያን ለመሆን ፈቃደኛ ሆኗል። (ሥራ 9:15, 16፤ 20:22, 23) ከተጠመቀ በኋላ በይሖዋ በመታመን የተለያዩ ፈተናዎችን በጽናት መወጣት ችሏል። (2 ቆሮ. 4:7-10) አንተም ተጠምቀህ የይሖዋ ምሥክር በመሆንህ የእምነት ፈተና ወይም መከራ ሊገጥምህ ይችላል። ሆኖም እርዳታ ታገኛለህ፤ የአምላክና የክርስቶስ ድጋፍ እንደማይለይህ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ።—ፊልጵ. 4:13፤ w25.03 4 አን. 8-9
ረቡዕ፣ የካቲት 18
ያለግብ አልሮጥም።—1 ቆሮ. 9:26
መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ የሚበረታታ ግብ ነው። ሆኖም ከመጽሐፍ ቅዱስ ንባባችን የተሟላ ጥቅም ማግኘት ከፈለግን ከዚህ የበለጠ ነገር ማድረግ ይኖርብናል። ለንጽጽር ያህል አንድ ምሳሌ እንመልከት፦ በዝናብ መልክ የሚወርደው ውኃ ለሕይወት በጣም አስፈላጊ ነው። ነገር ግን ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከዘነበ መሬቱ ይጥለቀለቃል። እንዲህ ያለው ዝናብ ጠቃሚ ሊሆን አይችልም። ውኃው መሬት ውስጥ ሰርጎ እንዲገባና ተክሎችን መጥቀም እንዲችል ጊዜ ያስፈልጋል። መጽሐፍ ቅዱስን ከማንበብ ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። በችኮላ ካነበብን መልእክቱን መረዳት፣ ማስታወስና በሥራ ላይ ማዋል እንቸገራለን። (ያዕ. 1:24) አንዳንድ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን የምታነበው በችኮላ እንደሆነ አስተውለህ ይሆን? ከሆነ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? ቀስ በል። በምታነብበት ወቅት ወይም ካነበብክ በኋላ፣ ስላነበብከው ነገር ቆም ብለህ ለማሰብ ጥረት አድርግ። ለማሰብ ወይም ለማሰላሰል እንዲያስችልህ የምታጠናበትን ጊዜ ረዘም ልታደርግ ትችል ይሆናል። w24.09 4 አን. 7-9
ሐሙስ፣ የካቲት 19
በመካከላችሁ ሆነው አመራር ለሚሰጧችሁ ታዘዙ።—ዕብ. 13:17
ሽማግሌዎች መመሪያ ሲሰጣቸው በጥንቃቄ ማንበብና በተቻላቸው መጠን ተግባራዊ ለማድረግ መሞከር አለባቸው። በጉባኤ ውስጥ ክፍሎችንና ጸሎቶችን እንዴት ማቅረብ እንዳለባቸው ብቻ ሳይሆን የክርስቶስን በጎች እንዴት መንከባከብ እንዳለባቸውም መመሪያ ይሰጣቸዋል። ሽማግሌዎች ድርጅታዊ መመሪያዎችን የሚከተሉ ከሆነ ወንድሞችና እህቶች ይሖዋ እንደሚወዳቸውና እንደሚንከባከባቸው እንዲተማመኑ ይረዷቸዋል። ሽማግሌዎች መመሪያ ሲሰጡን በፈቃደኝነት ልንታዘዝ ይገባል። እንዲህ ካደረግን አመራር የሚሰጡት ወንድሞች ሥራቸውን መሥራት ቀላል ይሆንላቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ አመራር ለሚሰጡን ወንድሞች እንድንታዘዝና እንድንገዛ ያበረታታናል። (ዕብ. 13:7, 17) ሆኖም እንዲህ ማድረግ አንዳንድ ጊዜ ተፈታታኝ ሊሆን ይችላል። ለምን? ምክንያቱም እነዚህ ወንድሞች ፍጹማን አይደሉም። ይሁንና በመልካም ባሕርያቸው ላይ ከማተኮር ይልቅ በድክመታቸው ላይ ካተኮርን ጠላቶቻችንን መተባበር ይሆንብናል። በምን መንገድ? ምክንያቱም እንዲህ ካደረግን በአምላክ ድርጅት ላይ ያለን እምነት እየተሸረሸረ ይሄዳል። w24.04 10 አን. 11-12
ዓርብ፣ የካቲት 20
ሰዎችን አንዱን ከሌላው ይለያል።—ማቴ. 25:32
ታላቁ መከራ ከጀመረ በኋላ የሞቱ ሁሉ ትንሣኤ ላያገኙ ለዘላለም ይጠፋሉ? ይሖዋና ሠራዊቱ በአርማጌዶን ጦርነት ላይ የሚያጠፏቸው ተቃዋሚዎች ከሞት እንደማይነሱ ቅዱሳን መጻሕፍት በግልጽ ይናገራሉ። (2 ተሰ. 1:6-10) ሆኖም ስለ ሌሎቹ ሰዎችስ ምን ማለት ይቻላል? ለምሳሌ በዚያ ወቅት በተፈጥሯዊ ምክንያት፣ በአደጋ ወይም በሰው እጅ ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎች ምን ይሆናሉ? (መክ. 9:11፤ ዘካ. 14:13) ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ በአዲሱ ዓለም ውስጥ ከሚነሱት “ጻድቃን ያልሆኑ ሰዎች” መካከል ይገኙ ይሆን? (ሥራ 24:15) የዚህን ጥያቄ መልስ አናውቀውም። ሆኖም ወደፊት ከሚከናወኑት ነገሮች ጋር በተያያዘ የምናውቃቸው አንዳንድ ነገሮች አሉ። ለምሳሌ በአርማጌዶን ወቅት ሰዎች የሚፈረድባቸው ለክርስቶስ ወንድሞች ባደረጉት ነገር መሠረት እንደሆነ እናውቃለን። (ማቴ. 25:40) ደግሞም “በጎች” ተብለው የሚፈረድላቸው ለቅቡዓኑና ለክርስቶስ ድጋፍ ያደረጉ ሰዎች ናቸው።—ራእይ 12:17፤ w24.05 10-11 አን. 9-11
ቅዳሜ፣ የካቲት 21
ይሖዋ ሕያው ነው! ዓለቴ ይወደስ! የመዳኔ አምላክ ከፍ ከፍ ይበል።—መዝ. 18:46
“ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን”—መጽሐፍ ቅዱስ የምንኖርበትን ዘመን የሚገልጸው በዚህ መንገድ ነው። (2 ጢሞ. 3:1) በዚህ ሥርዓት ውስጥ በሁሉም ሰው ላይ ከሚደርሱት ችግሮች በተጨማሪ የይሖዋ ሕዝቦች ተቃውሞንና ስደትን መቋቋም ያስፈልጋቸዋል። እነዚህ ችግሮች እያሉም ይሖዋን ማምለካችንን ለመቀጠል ምን ይረዳናል? ከሚረዱን ወሳኝ ነገሮች አንዱ፣ ይሖዋ “ሕያው አምላክ” መሆኑን ማስታወስ ነው። (ኤር. 10:10፤ 2 ጢሞ. 1:12) ይሖዋ ፈተና ሲያጋጥመን የሚያበረታንና እኛን ለመደገፍ የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን የሚፈልግ እውን የሆነ አምላክ ነው። (2 ዜና 16:9፤ መዝ. 23:4) እሱ ሕያው አምላክ መሆኑን ማስታወሳችን የሚያጋጥመንን ማንኛውንም ፈተና በተሳካ ሁኔታ ለመጋፈጥ ይረዳናል። w24.06 20 አን. 1-2
እሁድ፣ የካቲት 22
የጻድቃን መንገድ . . . ፍንትው ብሎ እንደሚወጣ የማለዳ ብርሃን ነው፤ እንደ ቀትር ብርሃን ቦግ ብሎ እስኪበራም ድረስ እየደመቀ ይሄዳል።—ምሳሌ 4:18
በይሖዋ ድርጅት ላይ ምንጊዜም እምነት መጣል ይኖርብናል። አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የተረዳንበት መንገድ ወይም የመንግሥቱ ሥራ የተደራጀበት መንገድ ማስተካከያ እንደሚያስፈልገው ግልጽ ሲሆን አመራር የሚሰጡት ወንድሞች አስፈላጊውን ማስተካከያ ከማድረግ ወደኋላ አይሉም። ይህን የሚያደርጉት ከምንም ነገር በላይ ይሖዋን ማስደሰት ስለሚፈልጉ ነው። በተጨማሪም ውሳኔዎቻቸው የይሖዋ ሕዝቦች ሁሉ ሊከተሉት የሚገባ መሥፈርት በሆነው በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረቱ እንዲሆኑ ለማድረግ የሚችሉትን ሁሉ ያደርጋሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ ‘የትክክለኛውን ትምህርት መሥፈርት አጥብቀህ ያዝ’ የሚል ምክር ሰጥቷል። (2 ጢሞ. 1:13) ‘የትክክለኛው ትምህርት መሥፈርት’ የሚለው አገላለጽ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ክርስቲያናዊ ትምህርቶች ያመለክታል። (ዮሐ. 17:17) የምናምንባቸው ነገሮች ሁሉ የተመሠረቱት በእነዚህ ትምህርቶች ላይ ነው። የይሖዋ ድርጅት ይህን መሥፈርት አጥብቀን እንድንከተል አስተምሮናል። ይህን ማድረጋችንን እስከቀጠልን ድረስ እንባረካለን። w24.07 11-12 አን. 12-13
ሰኞ፣ የካቲት 23
ይሖዋ . . . እናንተን የታገሠው፣ ሁሉ ለንስሐ እንዲበቃ እንጂ ማንም እንዲጠፋ ስለማይፈልግ ነው።—2 ጴጥ. 3:9
ሐዋርያው ጴጥሮስ በሕይወቱ ያየው ነገር ስላለ ለሌሎች ስለ ንስሐና ስለ ይቅርታ ሊያስተምር ችሏል። ከጴንጤቆስጤ በዓል በኋላ ጴጥሮስ አማኝ ላልሆኑ አይሁዳውያን ንግግር ባቀረበበት ወቅት መሲሑን እንደገደሉት ነግሯቸዋል። ሆኖም እንዲህ የሚል ፍቅራዊ ማሳሰቢያ ሰጣቸው፦ “ኃጢአታችሁ እንዲደመሰስ ንስሐ ግቡ፣ ተመለሱም፤ ከይሖዋም ዘንድ የመታደስ ዘመን ይመጣላችኋል።” (ሥራ 3:14, 15, 17, 19) በዚህ መንገድ ጴጥሮስ፣ ንስሐ አንድን ኃጢአተኛ እንዲመለስ ማለትም የተሳሳተ አስተሳሰቡንና ምግባሩን እንዲያስተካክል እንዲሁም አምላክን የሚያስደስት አዲስ ጎዳና እንዲከተል እንደሚያነሳሳው አሳይቷል። በተጨማሪም ጴጥሮስ፣ ይሖዋ ኃጢአታቸውን እንደሚደመስስላቸው ነግሯቸዋል። ከባድ ኃጢአት ብንፈጽምም እንኳ ይሖዋ ይቅር እንደሚለን ማወቅ ምንኛ የሚያጽናና ነው! w24.08 12 አን. 14
ማክሰኞ፣ የካቲት 24
አኗኗራችሁ ከገንዘብ ፍቅር ነፃ ይሁን።—ዕብ. 13:5
የዚህ ሥርዓት መጨረሻ በቅርቡ እንደሚመጣ ጠንካራ እምነት ካለን ከፍቅረ ነዋይ ለመራቅ እንነሳሳለን። ሰዎች “በይሖዋ የቁጣ ቀን ብራቸውም ሆነ ወርቃቸው ሊያድናቸው” እንደማይችል ስለሚገነዘቡ “ብራቸውን በየጎዳናው ይጥላሉ።” (ሕዝ. 7:19) የምንችለውን ያህል ብዙ ገንዘብ በማከማቸት ላይ ትኩረት ከማድረግ ይልቅ ቀላል ሆኖም ሚዛናዊ ሕይወት ለመምራት የሚረዱንን ውሳኔዎች ማድረግ ይኖርብናል። ለምሳሌ አላስፈላጊ ዕዳ ውስጥ ከመግባት ወይም የእኛን ጊዜና እንክብካቤ የሚፈልጉ ብዙ ቁሳዊ ነገሮችን ከመሰብሰብ እንቆጠባለን። አሁን ላሉን ቁሳዊ ንብረቶችም ከመጠን ያለፈ ፍቅር እንዳይኖረን እንጠነቀቃለን። (ማቴ. 6:19, 24) የዚህን ሥርዓት መጨረሻ በምንጠባበቅበት ወቅት ከቁሳዊ ነገሮችም ሆነ ከሌሎች ነገሮች ጋር በተያያዘ እምነታችን ሊፈተን ይችላል። w24.09 11 አን. 13-14
ረቡዕ፣ የካቲት 25
የቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ።—1 ቆሮ. 10:12
አንዳንድ ድክመቶቻችንን ሙሉ በሙሉ ማሸነፍ እንችል ይሆናል። ይሁንና ሌሎች ዝንባሌዎች በቀጣይነት ሊያታግሉን ይችላሉ። የሐዋርያው ጴጥሮስን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ኢየሱስን ሦስት ጊዜ የካደው ለሰው ፍርሃት እጅ በመስጠቱ ነው። (ማቴ. 26:69-75) ጴጥሮስ በሳንሄድሪን ሸንጎ ፊት በድፍረት ምሥክርነት በሰጠበት ወቅት ፍርሃቱን ማሸነፍ የቻለ ይመስል ነበር። (ሥራ 5:27-29) ይሁንና ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ “ከተገረዙት ወገን የሆኑትን በመፍራት” ለተወሰነ ጊዜ ያህል ከአሕዛብ ክርስቲያኖች ጋር መብላት አቁሞ ነበር። (ገላ. 2:11, 12) ጴጥሮስ ፍርሃቱ አገርሽቶበታል። ምናልባት ቀድሞውንም ይህን ድክመት ሙሉ በሙሉ አላሸነፈው ይሆናል። እኛም ተመሳሳይ ሁኔታ ሊያጋጥመን ይችላል። እያታገለን ያለ ዝንባሌ ካለ ኢየሱስ “ነቅታችሁ ጠብቁ” በማለት የሰጠውን ምክር መከተላችን በፈተናው እንዳንሸነፍ ይረዳናል። (ማቴ. 26:41) ጠንካራ እንደሆንክ በሚሰማህ ጊዜም ጭምር ወደ ፈተና ሊመሩህ ከሚችሉ ሁኔታዎች መራቅህን ቀጥል። እንዲሳካልህ የረዱህን ዘዴዎች በሥራ ላይ ማዋልህን አታቋርጥ።—2 ጴጥ. 3:14፤ w24.07 18 አን. 17-19
ሐሙስ፣ የካቲት 26
[ሰዎችን] ስጦታ አድርጎ ሰጠ።—ኤፌ. 4:8
የኢየሱስን ያህል ልግስና ያሳየ ማንም ሰው የለም። ምድር ላይ በነበረበት ወቅት ተአምር የመፈጸም ችሎታውን ተጠቅሞ ሌሎችን በተደጋጋሚ ረድቷል። (ሉቃስ 9:12-17) ሕይወቱን ለእኛ ሲል አሳልፎ በመስጠት ከሁሉ የላቀውን ስጦታ ሰጥቶናል። (ዮሐ. 15:13) ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላም ልግስና ማሳየቱን ቀጥሏል። ቃል በገባው መሠረት፣ የሚያስተምረንንና የሚያጽናናንን መንፈስ ቅዱስን እንዲሰጠን ይሖዋን ጠይቆታል። (ዮሐ. 14:16, 17 ግርጌ፤ 16:13) በተጨማሪም ኢየሱስ በመላው ዓለም ሰዎችን ደቀ መዛሙርት እንድናደርግ በጉባኤ ስብሰባዎቻችን አማካኝነት እኛን ማስታጠቁን ቀጥሏል። (ማቴ. 28:18-20) ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከወጣ በኋላ ‘ሰዎችን ስጦታ አድርጎ እንደሰጠ’ ገልጿል። (ኤፌ. 4:7, 8) ጳውሎስ፣ ኢየሱስ ይህን ስጦታ የሰጠን ጉባኤውን በተለያዩ መንገዶች ለመደገፍ እንደሆነ ተናግሯል። (ኤፌ. 1:22, 23፤ 4:11-13) እርግጥ ነው፣ እነዚህ ሰዎች ፍጹማን ስላልሆኑ ስህተት መሥራታቸው አይቀርም። (ያዕ. 3:2) ሆኖም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ለመርዳት በእነዚህ ውድ ወንድሞች ይጠቀማል። w24.10 18 አን. 1-2
ዓርብ፣ የካቲት 27
ጥልቅ ግንዛቤ . . . ይጋርድሃል።—ምሳሌ 2:11
ዳዊት፣ ልጁ ሰለሞን ስኬታማ የሚሆነው ይሖዋ አምላክን እስከታዘዘ ድረስ ብቻ እንደሆነ ነግሮታል። የሚያሳዝነው፣ ሰለሞን በሸመገለ ጊዜ ሌሎች አማልክትን ማምለክ ጀመረ። በዚህ ጊዜ ይሖዋ ሞገሱን ወሰደበት፤ ሰለሞንም ሕዝቡን በጽድቅና በፍትሕ ለማስተዳደር የሚያስችለውን ጥበብ አጣ። (1 ነገ. 11:9, 10፤ 12:4) ምን ትምህርት እናገኛለን? ታዛዥነት ስኬት ያስገኛል። (መዝ. 1:1-3) እርግጥ ነው፣ ይሖዋ እንደ ሰለሞን ሀብትና ክብር እንደሚሰጠን ቃል አልገባልንም። ሆኖም አምላክን ከታዘዝን ጥሩ ውሳኔዎችን ለማድረግ የሚያስችል ጥበብ ይሰጠናል። (ምሳሌ 2:6, 7፤ ያዕ. 1:5) እሱ የሰጠን መሠረታዊ ሥርዓቶች እንደ ሥራ፣ ትምህርት፣ መዝናኛና ገንዘብ ካሉ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ውሳኔ ስናደርግ ይረዱናል። አምላካዊ ጥበብን በሥራ ላይ ማዋላችን ዘላቂ ጉዳት እንዳይደርስብን ይጠብቀናል። (ምሳሌ 2:10, 11) ጥሩ ወዳጆች እናገኛለን። አስደሳች የቤተሰብ ሕይወት መመሥረትም እንችላለን። w24.11 10-11 አን. 11-12
ቅዳሜ፣ የካቲት 28
ሁሉንም ነገር መርምሩ፤ መልካም የሆነውን አጥብቃችሁ ያዙ።—1 ተሰ. 5:21
ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ስለ መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ በአምላክ ላይ እምነት ስለማሳደር አስደሳች ውይይት ማድረግ የሚችሉባቸው የተለያዩ አጋጣሚዎች አሉ። እንዲህ የመሰሉ አጋጣሚዎች የሚፈጠሩላችሁ ሙዚየሞችን ስትጎበኙ ሊሆን ይችላል። ልጆቻችሁ የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኛነት የሚያረጋግጡ ታሪካዊ ዘገባዎችን ወይም ቅርሶችን ልብ ብለው እንዲመለከቱ ልትጠቁሟቸው ትችሉ ይሆናል። ልጆቻችሁ “የሞዓባውያን ጽላት” ተብሎ በሚታወቅ 3,000 ዓመት ያስቆጠረ አንድ ጥንታዊ ድንጋይ ላይ የይሖዋ ስም እንደሚገኝ ያውቃሉ? ዎርዊክ፣ ኒው ዮርክ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ውስጥ ባለው “መጽሐፍ ቅዱስ እና መለኮታዊው ስም” በሚለው ሙዚየም ውስጥ ከኦሪጅናሉ ጋር ተመሳስሎ የተሠራ የሞዓባውያን ጽላት አለ። ይህ ጽላት የሞዓብ ንጉሥ ሜሻ በእስራኤል ላይ እንዳመፀ ይናገራል። ይህም መጽሐፍ ቅዱስ ከሚናገረው ነገር ጋር የሚስማማ ነው። (2 ነገ. 3:4, 5) ልጆቻችሁ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነተኛነትና ትክክለኛነት የሚያሳዩ ማስረጃዎችን በገዛ ዓይናቸው ሲመለከቱ እምነታቸው ይጠናከራል። w24.12 14 አን. 4፤ 15 አን. 6