የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • wcg ምዕ. 42 ገጽ 192-195
  • እሺ ለማለት ድፍረት አገኘች

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • እሺ ለማለት ድፍረት አገኘች
  • በድፍረት ከአምላክ ጋር ሂድ
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ጠለቅ ብለህ መርምር
  • ምን እንደሚያስተምርህ አስብ
  • በትልቁ ነገር ላይ አሰላስል
  • እውቀትህን አስፋ
  • “እነሆ፣ እኔ የይሖዋ ባሪያ ነኝ!”
    በእምነታቸው ምሰሏቸው
  • “እነሆ! እኔ የጌታ ባሪያ ነኝ”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2008
  • ማርያም ከተወችው ምሳሌ ምን ልንማር እንችላለን?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2009
  • “የምትችለውን አድርጋለች”
    በድፍረት ከአምላክ ጋር ሂድ
ለተጨማሪ መረጃ
በድፍረት ከአምላክ ጋር ሂድ
wcg ምዕ. 42 ገጽ 192-195

42 ማርያም

እሺ ለማለት ድፍረት አገኘች

በወረቀት የሚታተመው
በወረቀት የሚታተመው

ይሖዋ ፍጹማን ላልሆኑ የሰው ልጆች ከሰጣቸው ኃላፊነቶች ሁሉ እጅግ ከባዱ የትኛው ነው? ማርያም የተባለች አንዲት አይሁዳዊት ድንግል ያጋጠማትን እንመልከት። ይህች ወጣት በገሊላ ክልል በናዝሬት ትኖር ነበር። አንድ ቀን አንድ ያልተለመደ እንግዳ ቤቷ መጣ፤ መልአኩ ገብርኤል!

መልአኩ “እጅግ የተባረክሽ ሆይ፣ ሰላም ለአንቺ ይሁን፤ ይሖዋ ከአንቺ ጋር ነው” አላት። ማርያም ይህን ስትሰማ ‘በጣም ደነገጠች።’ እንዲህ ዓይነት ውዳሴ የሚገባት ሴት እንደሆነች አልተሰማትም። ገብርኤል “በአምላክ ፊት ሞገስ [እንዳገኘች]” በመንገር አጽናናት። ከዚያም ለየትኛውም የሰው ልጅ ተሰጥቶ የማያውቅ አንድ ልዩ ተልእኮ እንድትፈጽም በይሖዋ መመረጧን አበሰራት። “ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ” አላት። አክሎም “እሱም ታላቅ ይሆናል፤ የልዑሉም አምላክ ልጅ ይባላል” በማለት ነገራት። ልጇ የንጉሥ ዳዊት ዙፋን ወራሽ እና ታላቅ ንጉሥ ይሆናል።

ማርያም እንደምንም ደፈር ብላ ግራ ያጋባትን ነገር አነሳችለት። ለአንድ ሰው የታጨች ቢሆንም ገና አላገባችም፤ ከወንድ ጋር ግንኙነት ፈጽማም አታውቅም። በመሆኑም “ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?” ብላ ጠየቀች። ገብርኤል የይሖዋ ኃይል ይኸውም ቅዱስ መንፈሱ በላይዋ ‘እንደሚያርፍ’ አስረዳት፤ በዚህም የተነሳ ፍጹም የሆነ ልጅ ትፀንሳለች። እሱም “ቅዱስና የአምላክ ልጅ ይባላል።” አክሎም ገብርኤል ይሖዋ ለዘመዷ ለኤልሳቤጥ ያደረገላትን ነገር ነገራት። ማርያም ከዚህ በላይ ማስረጃ አላስፈለጋትም። “እነሆ፣ እኔ የይሖዋ ባሪያ ነኝ! እንደ ቃልህ ይሁንልኝ” ብላ በትሕትና መልስ ሰጠች። ማርያም ይሖዋን፣ የሚወዳት ጌታዋ አድርጋ ተመልክታዋለች። ራሷን ደግሞ እንደ ታዛዥ ባሪያ ቆጥራለች። የእሱን ፈቃድ እስካደረገች ድረስ ኃያል በሆኑት እጆቹ ውስጥ ሆና ደህንነቷ ምንጊዜም እንደሚጠበቅ ተማምናለች። ይህ ከባድ ተልእኮ ሲመጣ ‘እሺ’ ለማለት ድፍረት ያገኘችው እንዲህ ዓይነት እምነት ስለነበራት ነው።

ማርያም መልአኩን ገብርኤልን እያነጋገረች ነው፤ ስሜቷ በጥልቅ ተነክቶ በጉልበቷ ተንበርክካለች።

መልአኩ ከሄደ በኋላ ማርያም ኤልሳቤጥን ለመጠየቅ ጉዞ ጀመረች። ሁለቱ ሴቶች ከፊታቸው የሚጠብቃቸውን ተልእኮ ለመወጣት እርስ በርስ ተበረታቱ። ማርያም ለኤልሳቤጥ እምነቷን የገለጸችበት መንገድ ከድፍረቷ በስተ ጀርባ ያለው ሚስጥር ምን እንደሆነ ይጠቁመናል። የተናገረችው ሐሳብ አጭር ቢሆንም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ከ20 ጊዜ በላይ ጠቅሳለች! የእምነት ሰው የሆነችው ማርያም በአምላክ ቃል ላይ በጥልቀት ታሰላስል ነበር። በዚህም የተነሳ ይሖዋን በሚገባ አውቃዋለች፤ እሱ የገባውን ቃል ለማመንም በቂ ምክንያት አግኝታለች። ማርያም ከኤልሳቤጥ ጋር ሦስት ወር ያህል ከሰነበተች በኋላ ወደ ቤቷ ተመለሰች። ዮሴፍን ስታገኘው እንደፀነሰችም ሆነ ይህ ሊሆን የቻለበትን መንገድ መንገር ትልቅ ድፍረት ጠይቆባታል። መጀመሪያ ላይ ዮሴፍ ማርያም የነገረችውን ነገር ማመን ከብዶት ነበር፤ ሆኖም የይሖዋ መልአክ ጣልቃ ገብቶ ሐቋን አስረዳላት።

በመጨረሻ ማርያምና ዮሴፍ ተጋቡ፤ በኋላም የመውለጃ ጊዜዋ እየተቃረበ መጣ። ይሁንና ሰው ሁሉ እንዲመዘገብ በወጣው የቄሳር አዋጅ ምክንያት ዮሴፍ ወደ ቤተልሔም ይዟት ሄደ። ማርያም ባለችበት ሁኔታ በአህያ ላይ ሆኖ 150 ኪሎ ሜትር ገደማ የሚሆን ርቀት መጓዝ ከባድ እንደሆነ ጥርጥር የለውም። እሷ ግን ሄደች። ጊዜዋ ሲደርስ ሌላ አማራጭ ስላልነበራት የከብቶች ጋጣ ውስጥ ወለደች፤ ሕፃኑንም ግርግም ውስጥ አስተኛችው። ሁኔታው ምቹ ባይሆንም ድፍረቷ አልተለያትም። ይህን ውድ ልጅ ለመንከባከብ አቅሟ የፈቀደላትን ሁሉ ለማድረግ ቆርጣለች።

ማርያም ለሰው ልጅ ተሰጥቶ የማያውቅ ልዩ ተልእኮ እንድትወጣ በአምላክ እንደተመረጠች አንድ መልአክ ነገራት

ቀናት እንዲሁም ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ የማርያም ድፍረት በብዙ አቅጣጫዎች ተፈትኗል። በንጉሥ ሄሮድስ የግድያ ሐሳብ ምክንያት ከዮሴፍና ከሕፃኑ ኢየሱስ ጋር ወደ ግብፅ በሸሸችበት ወቅት ድፍረት አስፈልጓታል። ከዮሴፍ ጋር ሆና ኢየሱስን ጨምሮ ቢያንስ ሰባት ልጆችን በድህነት ማሳደግ ድፍረት ይጠይቃል። ውዱ ባለቤቷ ዮሴፍ፣ ኢየሱስ መሲሕ ከመሆኑ በፊት ሕይወቱ ሳያልፍ አልቀረም፤ በዚህ ወቅትም ቢሆን ድፍረት አስፈልጓታል። ኢየሱስ አገልግሎቱን ለመጀመር ከቤት ሲወጣ ድፍረቷ ተፈትኗል። ከሁሉ በላይ ግን ድፍረቷ የተፈተነው ኢየሱስ በሐሰት ተከስሶና ወንጀለኛ ተብሎ በተገደለበት ወቅት ነው። በመጨረሻም ከልጇ ተከታዮች ጋር ሆና ይሖዋን ስታገለግል የአይሁዳውያንን የመረረ ጥላቻ በድፍረት መጋፈጥ ነበረባት።

ማርያም የተሰጣት ተልእኮ እንዴት ከባድ ነው! ተልእኮውን ዳር ለማድረስ የሚያስችላትን ድፍረት ያገኘችው ከየት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ማርያም እምነቷን የሚያጠናክር መረጃ ስታገኝ በልቧ ትይዘው ነበር። ስለዚህ ልቧ ውስጥ የካበተ መንፈሳዊ ሀብት ነበር። አንዳንዱን የሰማችው ከአምላክ ቃል ነው፤ አንዳንዱን ከመላእክትና ከሌሎች የይሖዋ አገልጋዮች፤ አንዳንዱን ደግሞ ከልጇ ነው። ማርያም በሰማቻቸው መንፈሳዊ እውነቶች ላይ ታሰላስል ስለነበር በሕይወቷ በሙሉ ያጋጠማትን እያንዳንዱን ፈተና በስኬት መወጣት ችላለች።

ታሪኩን ከመጽሐፍ ቅዱስ አንብብ፦

  • ሉቃስ 1:26-56፤ 2:1-7, 19, 48-51

ለውይይት፦

ማርያም ድፍረት ያሳየችው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

ጠለቅ ብለህ መርምር

  1. 1. በሉቃስ 2:1-3 ላይ የሚገኘው ሐሳብ እውነት መሆኑን የሚያረጋግጥ ምን የታሪክ ማስረጃ አለ? (g 4/11 11 አን. 4-5) ሀ

    British Library, London, UK, from the British Library archive/Bridgeman Images

    ሥዕል ሀ፦ በግብፅ ላይ የተሾመ ሮማዊ አገረ ገዢ ያወጣው የሕዝብ ቆጠራ አዋጅ፣ 104 ዓ.ም.

  2. 2. ከናዝሬት ወደ ቤተልሔም መጓዝ ለማርያም ከባድ ሊሆን የሚችለው ለምንድን ነው? (ia 153-155 አን. 4-7)

  3. 3. ኢየሱስ ገና ሕፃን በነበረበት ወቅት ማርያም “[በአንቺ] ውስጥ ትልቅ ሰይፍ ያልፋል” ተብላ ነበር። ይህ ሐሳብ ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው? (ሉቃስ 2:35፤ w08 3/15 31 አን. 1)

  4. 4. ማርያም ሰማያዊ ሽልማት እንዳገኘች መደምደም የምንችለው ለምንድን ነው? (w18.07 10 አን. 14) ለ

    ማርያምና ሦስት ወንዶች ልጆቿ ሰው በሚበዛበት የኢየሩሳሌም ጎዳና ላይ በእግራቸው ሲጓዙ።

    ሥዕል ለ፦ በ33 ዓ.ም. ከዋለው ጴንጤቆስጤ በፊት ባሉት ቀናት ማርያምና ወንዶች ልጆቿ ኢየሩሳሌም ነበሩ

ምን እንደሚያስተምርህ አስብ

  • ማርያም ማበረታቻ ባስፈለጋት ወቅት ኤልሳቤጥን ለመጠየቅ ሄዳለች። (ሉቃስ 1:39, 40) እኛም ፈተና ሲገጥመን ወይም ተልእኳችንን መወጣት ሲከብደን እርዳታ መጠየቅ ያለብን ለምንድን ነው? ሐ

    ሥዕሎች፦ 1. በጣም የጨነቃት አንዲት እህት ጠረጴዛዋ አጠገብ ተቀምጣ ላፕቶፗና ሄልሜቷ ላይ አፍጥጣለች። ግድግዳው ላይ የተሰቀለው ቀን መቁጠሪያ በብዙ ፕሮግራሞች ተጨናንቋል። 2. ይህች እህት ተሞክሮ ካላት እህት ጋር ከቤት ወደ ቤት እያገለገለች ነው፤ እህትን እያነጋገረቻት ነው።

    ሥዕል ሐ

  • ማርያም ለዮሴፍ ታጭታ የነበረ ቢሆንም ይሖዋ መጀመሪያ መልአኩን የላከው ወደ እሷ ነው። ይሖዋ ታማኝ ሴቶችን ስለሚያይበት መንገድ ከዚህ ምን እንማራለን?

  • የማርያምን የድፍረት ምሳሌ በየትኞቹ መንገዶች መኮረጅ ትችላለህ?

በትልቁ ነገር ላይ አሰላስል

  • ይህ ታሪክ ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረኛል?

  • ይህ ታሪክ ከይሖዋ ዓላማ ጋር ያለው ግንኙነት ምንድን ነው?

  • ማርያም ከክርስቶስ ጋር በሰማይ ከሚገዙት መካከል ልትሆን እንደምትችል ስታስብ አመስጋኝ የምትሆነው ለምንድን ነው?

እውቀትህን አስፋ

ማርያም ልጆቿን ስታሳድግ ታታሪና ለራሷ የማትሳሳ እናት የነበረችው እንዴት እንደሆነ ተመልከት።

“ማርያም ከተወችው ምሳሌ ምን ልንማር እንችላለን?” (w09 1/1 5 አን. 4–6 አን. 2)

ማርያም ለአንድ ልዩና ከባድ ተልእኮ እንደተመረጠች ገብርኤል ሲነግራት ምን ተሰምቷት ሊሆን ይችላል?

“እነሆ፣ እኔ የይሖዋ ባሪያ ነኝ!” (3:40)

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2026)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2026 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ