43 ዮሴፍ
ከባድ አደራ ተቀበለ
ጥሩ አባት መሆን ድፍረት ይጠይቃል። በናዝሬት የሚኖረው አናጺው ዮሴፍ ግን ድፍረቱ የተፈተነው ገና አባት ከመሆኑ በፊት ነው። ሊያገባት ያጫት ሴት ማለትም ማርያም እንደፀነሰች አወቀ። የፀነሰችው ግን ከእሱ አይደለም። ማርያም ስለፀነሰችበት መንገድ ሁሉንም ነገር ነግራዋለች። ያም ሆኖ ዮሴፍ ነገሩን መረዳትም ሆነ ማመን በጣም ከብዶታል። ታዲያ ምን ይወስን ይሆን?
መጽሐፍ ቅዱስ “ዮሴፍ ጻድቅ” እንደሆነ ይነግረናል። ለይሖዋ ሕጎች ታማኝ የሆነው ይህ ምግባረ ቀና ሰው ደግና መሐሪም ነበር። በመሆኑም ነገሩን ‘ካሰበበት’ በኋላ ማርያምን ከኀፍረት ሊታደጋት አሰበ። በዚያ ዘመን መተጫጨት የትዳር ቃል ኪዳንን ያህል ክብደት ይሰጠው ስለነበር በስውር ሊፈታት አቀደ። ሆኖም ይሖዋ ጣልቃ ገባ። ዮሴፍን በሕልም እንዲያነጋግረው አንድ መልአክ ላከ። መልአኩ ለዮሴፍ “[ሚስትህን ማርያምን] ወደ ቤት ለመውሰድ አትፍራ” አለው። ማርያም የነገረችው ነገር በሙሉ እውነት መሆኑን ለዮሴፍ አረጋገጠለት። ልጁ በእርግጥም የአምላክ ልጅ እንደሆነና መሲሕ እንደሚሆን ገለጸለት!
ዮሴፍ ከባድ አደራ ተጥሎበታል፤ ይህም የአምላክን ልጅ ማሳደግ ነው
ዮሴፍ ‘የይሖዋ መልአክ ያዘዘውን አደረገ።’ ውድ ባለቤቱንም ሆነ ከሰው ከተወለዱት ሁሉ ትልቅ ቦታ የሚሰጠውን ሕፃን እንዲንከባከብ ይሖዋ የሰጠውን አደራ እሺ ብሎ ተቀበለ። በእርግጥም ዮሴፍ ትልቅ ድፍረት ያስፈልገው ነበር።
ከተወሰኑ ወራት በኋላ አውግስጦስ ቄሳር የሕዝብ ቆጠራ እንዲካሄድ አዋጅ አወጣ፤ ዮሴፍ ለመመዝገብ ወደ ቤተልሔም መጓዝ ነበረበት። ሕጉ ማርያምም እንድትሄድ የሚያስገድድ ይሁን አይሁን የምናውቀው ነገር የለም፤ ያም ሆነ ይህ ዮሴፍ ለደህንነቷ ሲል ሳይሆን አይቀርም ከጎኑ እንድትለይ አልፈለገም። “የመውለጃ ጊዜዋ [ቢቃረብም]” ረጅሙን ጉዞ አብረው ተያያዙት። ቤተልሔም ሲደርሱ ማርያም ምጥ ጀመራት፤ ከዚያም በከብቶች ማደሪያ ኢየሱስን ወለደች።
ዮሴፍ ቤተሰቡን ለማስተዳደር በትጋት ቢሠራም ድሆች ነበሩ። እሱና ማርያም ልጃቸውን በይሖዋ ፊት ለማቅረብ ኢየሩሳሌም ወደሚገኘው ቤተ መቅደስ በሄዱበት ወቅት መሥዋዕት አድርገው ያቀረቡት ለድሆች የተፈቀደውን እንስሳ ነው። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ፣ በቤተልሔም እየኖሩ ሳለ እንግዶች ሊጠይቋቸው መጡ፤ እንግዳ በሆነ ‘ኮከብ’ እየተመሩ የመጡት እነዚህ ኮከብ ቆጣሪዎች የባቢሎን ሰዎች ሳይሆኑ አይቀሩም። ለሕፃኑ ውድ ስጦታዎችን ያመጡ ሲሆን ለወላጆቹ ሰጧቸው። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ክፉው ንጉሥ ሄሮድስ ሕፃኑን ኢየሱስን ሊገድለው እንደሚፈልግ የይሖዋ መልአክ ዮሴፍን አስጠነቀቀው። ዮሴፍ ቤተሰቡን ይዞ ወደ ግብፅ እንዲሸሽ መልአኩ ነገረው።
ዮሴፍ ራሱን አደፋፍሮ በአስቸኳይ እርምጃ ወሰደ፤ በሌሊት ሚስቱንና ሕፃኑን ይዞ ከቤተልሔም ወጣ። ታዲያ በባዕድ አገር በግብፅ ሲኖር ቤተሰቡን እንዴት ሊያስተዳድር ነው? ከሩቅ ሊጠይቋቸው የመጡት ጎብኚዎች በሰጧቸው ውድ ነገሮች ኑሯቸውን ደጉመው መሆን አለበት። በኋላ ላይ ይሖዋ ቤተሰቡን ይዞ ወደ አገሩ እንዲመለስ ዮሴፍን አዘዘው። ይሁንና ቤተልሔም አንድ ጨካኝ ገዢ በሚያስተዳድረው ክልል ውስጥ ነበረች። በመሆኑም ዮሴፍ በተሰጠው መለኮታዊ ማስጠንቀቂያ መሠረት ቤተሰቡን ይዞ ወደ ናዝሬት ሄደ።
ኑሯቸውን በናዝሬት ያደረጉት ዮሴፍና ማርያም ከኢየሱስ በተጨማሪ ቢያንስ ስድስት ልጆች አሏቸው፤ ዮሴፍ ይህንን ትልቅ ቤተሰብ ለማስተዳደር በአናጺነት ተግቶ ይሠራ ነበር። ከሁሉ በላይ ግን ዮሴፍ ቤተሰቡን በመንፈሳዊ ይንከባከብ ነበር። ስለ ይሖዋ ለመማር አዘውትረው ወደ ምኩራብ የመሄድ ልማድ ነበራቸው፤ በኢየሩሳሌም በሚከበሩት ቅዱስ በዓላት ላይም ይገኙ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ዮሴፍን ለመጨረሻ ጊዜ የሚጠቅሰው እንዲህ ባለው በዓል ላይ ስለተገኙበት አንድ ወቅት በሚናገረው ታሪክ ላይ ነው። ለልጆቹ የሚሳሳው ዮሴፍ የ12 ዓመቱ ኢየሱስ እንደጠፋ ስላሰበ በጣም ተጨንቆ ነበር። ደስ የሚለው ኢየሱስን በደህና አገኙት፤ እሱም ለወላጆቹ “[እንደ ወትሮው] ይገዛላቸው ነበር።”
መጽሐፍ ቅዱስ ዮሴፍ መቼ እንደሞተ አይነግረንም፤ ሆኖም በሕይወት እያለ ለኢየሱስ አስፈላጊውን ሥልጠና ሰጥቶት መሆን አለበት። በኋላ ላይ ኢየሱስ “የአናጺው ልጅ” ብቻ ሳይሆን “አናጺው” ተብሎም ተጠርቷል። በመሆኑም አባቱ ሙያውን አስተምሮት ነበር። ዮሴፍ ይሖዋ ከአባቶች የሚጠብቀውን ሁሉ በመሆን ግሩም ምሳሌ ትቷል። አባቶች ቤተሰባቸውን በድፍረት በመጠበቅ፣ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ የሚያስፈልጋቸውን በማቅረብና በደግነት በማስተማር አምላክ የሰጣቸውን ኃላፊነት መወጣት ይችላሉ።
ታሪኩን ከመጽሐፍ ቅዱስ አንብብ፦
ለውይይት፦
ዮሴፍ ድፍረት ያሳየው በየትኞቹ መንገዶች ነው?
ጠለቅ ብለህ መርምር
1. የሄሊ ልጅ ማርያም ሆና ሳለ ሉቃስ 3:23 ዮሴፍ “የሄሊ ልጅ” እንደሆነ የሚናገረው ለምንድን ነው? (w17.08 32 አን. 4)
2. ዮሴፍ ኢየሱስ ከመወለዱ በፊት ከማርያም ጋር የፆታ ግንኙነት ያልፈጸመው ለምን ሊሆን ይችላል? (w03 12/15 5 አን. 5)
3. ዮሴፍ ታታሪ ሠራተኛ እንደሆነ የሚጠቁመው ምንድን ነው? (ia 166 አን. 15-18) ሀ
ሥዕል ሀ
4. ዮሴፍ የሞተው ኢየሱስ ገና ወጣት እያለ ሳይሆን አይቀርም የምንለው ለምንድን ነው? (w17.07 13 አን. 8 እና ግርጌ)
ምን እንደሚያስተምርህ አስብ
የቤተሰብ ራሶች ዋጋ የሚያስከፍል ቢሆንም እንኳ የይሖዋን መመሪያ መታዘዝን በተመለከተ ከዮሴፍ ምን ይማራሉ? (ማቴ. 1:20, 24፤ 2:13-15, 19-21)
በቤተሰብ ሕይወታችን ለይሖዋ ቅድሚያ መስጠትን በተመለከተ ከዮሴፍ ምን እንማራለን? (ሉቃስ 2:41) ለ
ሥዕል ለ
የዮሴፍን የድፍረት ምሳሌ በየትኞቹ ሌሎች መንገዶች መኮረጅ ትችላለህ?
በትልቁ ነገር ላይ አሰላስል
ይህ ታሪክ ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረኛል?
ይህ ታሪክ ከይሖዋ ዓላማ ጋር ያለው ግንኙነት ምንድን ነው?
ዮሴፍ ከሞት ሲነሳ ምን ልጠይቀው እፈልጋለሁ?
እውቀትህን አስፋ
ዮሴፍ ለይሖዋ ፈቃድ በታዛዥነት የተገዛው እንዴት እንደሆነ በዚህ ድራማ ላይ ተመልከት።
ለእኛ የማይመች ወይም ፍትሐዊ እንደሆነ የማይሰማን የመንግሥት ሕግ ሲወጣ የዮሴፍንና የማርያምን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?