40 ነህምያ
ቅጥሩን ዳግመኛ ገነባ
ነህምያ የሚኖረው የፋርስ ከተማ በሆነችው በሹሻን ነው፤ ልቡ ያለው ግን ርቃ በምትገኘው በኢየሩሳሌም ነው። የይሖዋ ቤተ መቅደስ መቀመጫ በመሆኗ ይህችን ከተማ ይወዳታል። ለብዙ ዓመታት በግዞት የቆዩት የአምላክ ሕዝቦች ወደዚያ እንዲመለሱ ከተፈቀደላቸው ሰንበትበት ብሏል፤ ንጹሑ አምልኮ ግን አሁንም መስመር አልያዘም። የከተማይቱ ቅጥሮች እንደፈራረሱ ናቸው። በዚያ ዘመን ደግሞ ቅጥር የሌላቸው ከተሞች በቀላሉ በወራሪዎች ይደፈራሉ፤ ስለዚህ ብዙ ሰዎች እንዲህ ባሉ ከተሞች ውስጥ መኖር አይፈልጉም።
ነህምያ በፋርሱ ንጉሥ በአርጤክስስ ቤተ መንግሥት ውስጥ የተከበረ ባለሥልጣን ነበር። ከሁሉ በላይ ግን ነህምያ የይሖዋ ታማኝ አገልጋይ ነው። አንድ ቀን የነህምያ ወንድም ኢየሩሳሌም ስላለችበት “በጣም አሳዛኝ ሁኔታ” የሚገልጽ ዜና ይዞ ወደ ነህምያ መጣ። የከተማዋ ቅጥሮች እንደፈራረሱ ይባስ ብሎም ነዋሪዎቿ “መሳለቂያ” እንደሆኑ ነገረው።
ነህምያ በጣም አዘነ። በኋላ ላይ እንደጻፈው ‘ለቀናት ቁጭ ብሎ አለቀሰ።’ ሕዝቡን እንዲያስታውስና እንዲደርስላቸው ይሖዋን ተማጸነው። በኋላ ላይ ለንጉሥ አርጤክስስ የወይን ጠጅ ሲያቀርብ ፊቱ እንደጠቆረ ነበር፤ ንጉሡም የከፋው ለምን እንደሆነ ጠየቀው። ነህምያ ፈርቶ የነበረ ቢሆንም እውነቱን ተናገረ። ኢየሩሳሌም ስላለችበት አስከፊ ሁኔታ ገለጸለት። አርጤክስስ ምን እንደሚፈልግ ነህምያን ጠየቀው። ነህምያ “ወዲያውኑ ወደ ሰማይ አምላክ ጸለይኩ” ሲል ጽፏል። ከዚያም ለተወሰነ ጊዜ ሥራውን ትቶ ወደ ኢየሩሳሌም መሄድ እንዲሁም ቅጥሮቿንና በሮቿን መልሶ በመገንባቱ ሥራ መካፈል ይችል እንደሆነ ንጉሡን ጠየቀው። የነህምያ ጥያቄ በሙሉ የንጉሡን ይሁንታ አገኘ!
ነህምያ ረጅምና አደገኛ ጉዞ አድርጎ ኢየሩሳሌም ደረሰ። ከዚያም የከተማዋ ቅጥሮች የሚገኙበትን ሁኔታ በሌሊት ተነስቶ መገምገም ጀመረ። ሕዝቡን በማስተባበር በመልሶ ግንባታው እንዲካፈሉ አበረታታ። እሱ ራሱ በሥራው በመሳተፍ ምሳሌ ሆነ። ባለጸጋና ታዋቂ የሆኑትን ለምሳሌ ወርቅ አንጥረኞቹንና መኳንንቱን ጨምሮ ሕዝቡ ሆ ብሎ ተነሳ፤ ከመኳንንቱ አንዱ ከሴት ልጆቹ ጋር ሳይቀር በሥራው ተካፍሏል።
ኢየሩሳሌም ደህንነቷ የተጠበቀ ጠንካራ ከተማ እንድትሆን የማይፈልጉ በርካታ የአይሁዳውያን ጠላቶች ነበሩ። የመጀመሪያው ዘዴያቸው ፌዝና ስላቅ ነበር። እንዲያውም አንደኛው ተቃዋሚ ነህምያና ሕዝቡ እየገነቡት ያሉት ቅጥር ቀበሮ እንኳ ቢወጣበት እንደሚፈርስ በመናገር ተሳለቀባቸው። ነህምያ ግን ለፌዝ ጆሮ ሳይሰጥ ሠራተኞቹን ማበረታታቱን ቀጠለ።
ፌዝ፣ ዛቻና ማስፈራሪያ ቢደርስበትም የኢየሩሳሌምን ቅጥሮች መልሶ ገነባ
ተቃውሞው እየተጠናከረ ሄደ። የቅጥሩ ግንባታ ሲጋመስ ጠላቶች ከሁሉም አቅጣጫ ለጥቃት መዘጋጀት ጀመሩ! ነህምያም ከተማዪቱን ለመጠበቅ እርምጃዎች ወሰደ። ጠላቶቻቸው ይህን ሲያዩ በቀጥታ ጥቃት የመሰንዘር ሐሳባቸውን ተዉ። ከዚያ ጊዜ ወዲህ ከሠራተኞቹ ግማሽ የሚሆኑት ቅጥሩን ሲገነቡ ነህምያና የቀሩት ደግሞ ታጥቀው ዘብ መቆም ጀመሩ። ጠላቶቻቸው ግን አሁንም ተስፋ አልቆረጡም።
ቀጣዩ ዘዴያቸው የግድያ ዛቻ ነበር፤ ነህምያ ለሕይወቱ ሰግቶ በይሖዋ ቤተ መቅደስ ውስጥ በመደበቅ የአምላክን ሕግ እንዲጥስ ማድረግ ፈልገው ነበር። ነህምያ በዚህ አልተበገረም። “እንደ እኔ ያለ ሰው መሸሽ ይገባዋል?” አለ። እያከናወኑት ያለው ሥራ ይሖዋ የሚፈልገውና የሚደግፈው እንደሆነ በመተማመን ሥራውን ቀጠለ። ደግሞም የይሖዋ ድጋፍ አልተለያቸውም! በ52 ቀናት ብቻ ቅጥሩን ገንብተው ጨረሱ። ሲያፌዙባቸውና ሲያሳድዷቸው የነበሩት ጠላቶቻቸው ኀፍረት ተከናነቡ።
ነህምያ ከገዛ ወገኖቹ ጋር በተያያዘም ድፍረት የሚጠይቅ ነገር ገጥሞታል። ሕዝቡ ይሖዋን በትክክለኛው መንገድ እንዲያገለግል ለመርዳት ቅድሚያውን መውሰድ ነበረበት። ለምሳሌ ያህል፣ በከፍተኛ ወለድ በማበደር ድሆችን የሚጨቁኑ ባለጸጎች ነበሩ፤ ነህምያ እነዚህን ሰዎች በድፍረት አውግዟቸዋል። በኋላ ላይ ደግሞ የባዕድ አገር ሴቶችን በማግባት የይሖዋን ሕግ የጣሱ አይሁዳውያን እንዳሉ ሲረዳ በድፍረት በመውቀስ የይሖዋን ሕግ አስከብሯል።
በአንድ ወቅት ሕዝቡ በገዛ ድክመታቸውና ኃጢአታቸው የተነሳ ተስፋ ቆርጠው ነበር። በዚህ ጊዜ ነህምያ “የይሖዋ ደስታ ምሽጋችሁ [ነው]” በማለት አስደናቂ እውነት አስተምሯቸዋል። ደስተኛውን አምላክ ማገልገል ጥልቅ እርካታ እንደሚያስገኝ ነህምያ ያውቃል። ከዚህ የተሻለ ጥበቃ ሊያስገኝ የሚችል አንድም ቅጥር ወይም ምሽግ የለም። ዛሬም የይሖዋ አገልጋዮች እውነተኛ ድፍረት ማሳየት የቻሉት በዚህ ደስታ የተነሳ ነው።
ታሪኩን ከመጽሐፍ ቅዱስ አንብብ፦
ለውይይት፦
ነህምያ ድፍረት ያሳየው በየትኞቹ መንገዶች ነው?
ጠለቅ ብለህ መርምር
1. ነህምያ የንጉሡ መጠጥ አሳላፊ ሆኖ የሚያከናውነው ሥራ ምን ነገሮችን ይጨምር ነበር? (w10 7/1 9 አን. 5-7) ሀ
National Museum of Iran, Tehran, Iran/Bridgeman Images
ሥዕል ሀ፦ የታላቁ ዳርዮስን (የአርጤክስስ አያት) መጠጥ አሳላፊ የሚያሳይ የፋርስ የተቀረጸ ምስል
2. ታዋቂ ከሆኑ የተቆአ ሰዎች በተቃራኒ የሻሉም ሴቶች ልጆች ምን አድርገዋል? (ነህ. 3:5, 12፤ w19.10 23 አን. 11)
3. ሸክም የሚሸከሙት ሰዎች ‘በአንድ እጃቸው ሥራውን እየሠሩ በሌላ እጃቸው የጦር መሣሪያ መያዝ’ የቻሉት እንዴት ነው? (ነህ. 4:17, 18፤ w06 2/1 9 አን. 1) ለ
ሥዕል ለ
4. አንዳንድ አይሁዳውያን ልጆች ዕብራይስጥ መናገር አለመቻላቸው ነህምያን ያሳሰበው ለምንድን ነው? (ነህ. 13:23-27፤ w16.10 14 አን. 4)
ምን እንደሚያስተምርህ አስብ
ሽማግሌዎች በሚከተሉት መንገዶች ነህምያን መምሰል የሚችሉት እንዴት ነው?
በይሖዋ አገልግሎት ተጨማሪ ነገር ለማድረግ ሲሉ የተመቻቸ ኑሯቸውን ለመተው ፈቃደኛ የሚሆኑ ሁሉ ስለሚያገኙት ወሮታ ከነህምያ ምሳሌ ምን እንማራለን?
የነህምያን የድፍረት ምሳሌ በየትኞቹ ሌሎች መንገዶች መኮረጅ ትችላለህ?
በትልቁ ነገር ላይ አሰላስል
ይህ ታሪክ ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረኛል?
ይህ ታሪክ ከይሖዋ ዓላማ ጋር ያለው ግንኙነት ምንድን ነው?
ነህምያ ከሞት ሲነሳ ምን ልጠይቀው እፈልጋለሁ?
እውቀትህን አስፋ
የነህምያ ታሪክ ጸሎት ስላለው ኃይል ምን ያስተምረናል?
ነህምያ ከጠላቶቹ ለሚመጣበት የማያባራ ተቃውሞ በድፍረት ምላሽ የሰጠው እንዴት እንደሆነ በዚህ ድራማ ላይ ተመልከት።