39 አስቴር
“ከጠፋሁም ልጥፋ”
አንዲት ወጣት ወደ ንጉሡ ዙፋን እያመራች ነው። በንጉሡ ጥሪ ሳይደረግላት ፊቱ መቅረቧ ሊያስገድላት እንደሚችል ታውቃለች፤ ስለዚህ ፈርታለች። ሆኖም ጉዞዋን ቀጠለች። ለመሆኑ ይህች ወጣት ማን ነች? እዚህ ሁኔታ ውስጥ ልትገባ የቻለችውስ እንዴት ነው?
ወጣቷ አስቴር ትባላለች። ወላጆቿ የሞቱት ገና ትንሽ ልጅ ሳለች ነው፤ በዕድሜ ብዙ የሚበልጣት የአጎቷ ልጅ መርዶክዮስ “እንደ ራሱ ልጅ አድርጎ ወሰዳት”፤ አሳዳጊዋም ሆነ። የሚኖሩት የፋርስ ግዛት ንጉሣዊ ከተማ በሆነችው በሹሻን ሲሆን መርዶክዮስ ቤተ መንግሥቱ ውስጥ ያገለግል ነበር። አስቴር እያደገች ስትሄድ “ቁመናዋ ያማረ፣ መልኳም ቆንጆ” ሆነች።
አንድ ቀን ንጉሥ አሐሽዌሮስ (ቀዳማዊ ጠረክሲስ ሳይሆን አይቀርም) ሚስት ለማግባት ወሰነ፤ በመሆኑም በግዛቱ ሁሉ ቆንጆ ደናግል ይፈለጉለት ጀመር። አስቴር በጣም ቆንጆ እንደሆነች ያስተዋሉ የንጉሡ አገልጋዮች ወደ ቤተ መንግሥቱ አመጧት። ከአስቴር ለመለየት የተገደደው መርዶክዮስ ከመሰነባበታቸው በፊት አይሁዳዊ መሆኗን “ለማንም እንዳትናገር” አዘዛት።
ቤተ መንግሥቱ ውስጥ “አስቴር ባዩአት ሁሉ ዘንድ ሞገስ [አገኘች]።” ለ12 ወራት የውበት እንክብካቤ ከተደረገላት በኋላ ወደ ንጉሡ ተወሰደች። በእሱም ዘንድ “ሞገስና ተቀባይነት አገኘች”፤ ከሌሎቹ ሴቶች ሁሉ እሷን ሚስቱ አድርጎ መረጠ። በዚህ መንገድ አስቴር የዘመኑ የዓለም ኃያል መንግሥት ንግሥት ሆነች! ያም ቢሆን መርዶክዮስ እንደነገራት አይሁዳዊ መሆኗን ለማንም አልተናገረችም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሃማ የተባለ ሰው የንጉሡ ምክትል እንዲሆን ተሾመ። ሃማ መርዶክዮስን ይጠላው ነበር፤ ምክንያቱም ሊሰግድለት ፈቃደኛ አልነበረም። የይሖዋ ታማኝ አገልጋይ የሆነው መርዶክዮስ ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ ያልሆነው፣ ሃማ የአምላክ ጠላት ተደርጎ ከሚቆጠር ሕዝብ ስለተወለደ ሳይሆን አይቀርም። ያም ሆነ ይህ የመርዶክዮስ ሁኔታ ሃማን አስቆጣው፤ በግዛቱ ያሉ አይሁዳውያንን በሙሉ ለመፍጀት ሴራ ጠነሰሰ። መርዶክዮስ የሃማን ዕቅድ ሲያውቅ በጣም አዘነ። ወደ አስቴር መልእክት ልኮ ንጉሡ ፊት እንድትቀርብና ወገኖቿን ለመታደግ አንድ ነገር እንድታደርግ አሳሰባት። አሁን የአስቴር ድፍረት በእጅጉ ሊፈተን ነው።
አስቴር ጥሪ ሳይደረግላት ወደ ንጉሡ ብትገባ በሞት ልትቀጣ እንደምትችል ለመርዶክዮስ አስረዳችው። ደግሞም ንጉሡ በቀላሉ ቱግ በማለት የሚታወቅ ሰው ነበር። ይሁንና መርዶክዮስ፣ አስቴር ንግሥት የሆነችው እንዲህ ላለው ጊዜ ማለትም የይሖዋን ሕዝብ ለመታደግ ሊሆን እንደሚችል በማስታወስ ደፍራ እንድትገባ አበረታታት። ስለዚህ አስቴር ራሷን አደፋፈረች። “ከጠፋሁም ልጥፋ” አለች። ብቻ ወገኖቿ ለሦስት ቀናት እንዲጾሙላት ጠየቀች። እሷም ሆነች ወገኖቿ ስለ ጉዳዩ ብዙ ጸልየው እንደሚሆን ጥያቄ የለውም። ከዚያም ወደ ንጉሡ ገባች።
አሐሽዌሮስ አስቴርን በንጉሡ ቤት ግቢ ቆማ ሲያያት አልተቆጣም። ስለዚህ እንድትገደል አላዘዘም። ከዚህ ይልቅ ምን እንደምትፈልግ ጠየቃት። እሷም ንጉሡ እና ሃማ ባዘጋጀችው ግብዣ ላይ እንዲገኙ ጥሪ አቀረበች። በግብዣው ላይ ስለ ሃማ ዕቅድ አልተናገረችም፤ በማስተዋል አንደበቷን ገታች። ንጉሡ እና ሃማ በቀጣዩ ቀን በምታዘጋጀው ግብዣ ላይ እንዲገኙላት ብቻ ጠየቀች። እስከዚያ ባለው ጊዜ ሃማ በመርዶክዮስ ላይ የጎነጎነውን ሴራ አጠናከረ፤ መርዶክዮስ የሚሰቀልበት እንጨት አስተከለ። ይሁንና የሃማ ደባ ዞሮ ዞሮ ለራሱ መትረፉ አልቀረም።
በወገኖቿ ላይ የተቃጣውን ጭፍጨፋ ለማስቆም ስትል ንጉሠ ነገሥት የሆነውን ባሏን ማግባባት ነበረባት
በሁለተኛው ግብዣ ላይ አሐሽዌሮስ ምን እንዲያደርግላት እንደምትፈልግ አስቴርን በድጋሚ ጠየቃት። በዚህ ጊዜ አቤቱታዋን አቀረበች። እሷንም ሆነ ወገኖቿን ለመፍጀት የተጠነሰሰ ሴራ እንዳለ በአክብሮት ነገረችው። ይህ ሴራ ራሱን ንጉሡን የሚጎዳ ባይሆን ኖሮ ጉዳዩን በዝምታ ታልፈው እንደነበር ለንጉሡ ገለጸችለት። ነገሩ ድንገተኛ የሆነበት አሐሽዌሮስ ይህን ለማድረግ የደፈረው ማን እንደሆነ ጠየቀ። አሁን አስቴር ሴረኛውን አጋለጠች፦ ሃማ እንደሆነ ፍርጥ አድርጋ ተናገረች! ንጉሡ በጣም ተቆጥቶ ሃማን እንዲገድሉት አዘዘ። በመጨረሻም ሃማ ለመርዶክዮስ ብሎ ባስተከለው ምሰሶ ላይ ራሱ ተሰቀለበት።
እንደ ሃማ ምኞት ቢሆን ኖሮ መርዶክዮስም ሆነ በመላው የፋርስ ግዛት የሚኖሩ የአምላክ ሕዝቦች በሙሉ ጠፍተው ነበር። ሆኖም ነገሩ የተገላቢጦሽ ሆነና ሃማ እንዲሁም ሌሎች የይሖዋና የሕዝቡ ጠላቶች ጠፉ። በዚህ መንገድ ይሖዋ፣ አስደናቂ እምነትና ድፍረት ያላትን ሴት በመጠቀም ሕዝቡን ከጥፋት ታደገ።
ታሪኩን ከመጽሐፍ ቅዱስ አንብብ፦
ለውይይት፦
አስቴር ድፍረት ያሳየችው በየትኞቹ መንገዶች ነው?
ጠለቅ ብለህ መርምር
1. የዚህን ታሪክ ትክክለኛነት የሚደግፍ ምን ማስረጃ አለ? (ia 138 ሣጥን) ሀ
Ungnad, Arthur. “Neubabylonische Privaturkunden aus der Sammlung Amherst.” Archiv für Orientforschung, vol. 19, 1959, pp. 74–82
ሥዕል ሀ፦ ማርዱካ (መርዶክዮስ) የሚለውን ስም የሚጠቅስ ጥንታዊ የፋርስ ጽላት
2. መርዶክዮስ ለሃማ ለመስገድ ፈቃደኛ ያልሆነው ለምን ሊሆን ይችላል? (ia 131 አን. 18)
3. አይሁዳውያን እንዲጠፉ በተጠነሰሰው ሴራ የሰይጣንና የአጋንንቱ እጅ እንዳለበት የሚጠቁመው ምንድን ነው? (g 12/02 7 አን. 3 እስከ 8 አን. 2) ለ
Cube. Lot of Yahali, puru. Neo-Assyrian Clay. (YPM BC 021122). Courtesy of the Peabody Museum, Division of Anthropology, Babylonian Collection, Yale University; peabody.yale.edu
ሥዕል ለ፦ በጥንት ዘመን ዕጣ ለመጣል የሚያገለግል ድንጋይ
4. አስቴርና መርዶክዮስ የትኛው ትንቢት ፍጻሜውን እንዲያገኝ አድርገዋል? (ia 142 ሣጥን)
ምን እንደሚያስተምርህ አስብ
አስቴር ሌሎች የይሖዋ አገልጋዮች አጠገቧ ባይኖሩም አስተዋይና ታዛዥ ነበረች። ዛሬ ያሉ ወጣቶች ከእሷ ምን ይማራሉ?
አስቴር በትዕግሥት፣ በዘዴና በግልጽ ሐሳቧን በመናገር የባሏን ልብ መግዛት ችላለች። ክርስቲያን ሚስቶች እሷን መምሰል የሚችሉት እንዴት ነው? ሐ
ሥዕል ሐ
የአስቴርን የድፍረት ምሳሌ በየትኞቹ ሌሎች መንገዶች መኮረጅ ትችላለህ?
በትልቁ ነገር ላይ አሰላስል
ይህ ታሪክ ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረኛል?
ይህ ታሪክ ከይሖዋ ዓላማ ጋር ያለው ግንኙነት ምንድን ነው?
አስቴር ከሞት ስትነሳ ምን ልጠይቃት እፈልጋለሁ?
እውቀትህን አስፋ
በዚህ የሙዚቃ ቪዲዮ ላይ ልጆች ከአስቴር የሚማሯቸውን ቁም ነገሮች ተመልከት።
በዘመናችን ወንድሞች እንደ አስቴር የእምነት አጋሮቻቸውን ከአደጋ ለመጠበቅ ሲሉ ምን አድርገዋል?
አምላክ ቃል የገባቸውን ነገሮች በትዕግሥት የሚወርሱትን ምሰሉ—መርዶክዮስ እና አስቴር (3:05)