38 ሦስቱ ዕብራውያን
“የእሳትን ኃይል አጥፍተዋል”
ሃናንያህ፣ ሚሳኤልና አዛርያስ እምነታቸውን የሚፈትን ያልጠበቁት ሁኔታ አጋጥሟቸዋል። የእምነት ሰው የሆነው ወዳጃቸው ዳንኤል አጠገባቸው ቢሆን ምንኛ ደስ ባላቸው! ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ የሚል የባቢሎናውያን ስም የወጣላቸው እነዚህ ሦስት ወጣቶች ሕይወታቸውን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ በገጠማቸው በዚህ ወቅት ግን ዳንኤል በቦታው የነበረ አይመስልም።
ነገሩ የጀመረው ናቡከደነጾር ግዙፍ ሐውልት ባቆመበት ወቅት ነው። ርዝመቱ ከስምንት ፎቅ ሕንፃ ጋር የሚተካከል ሲሆን ወርዱ ሦስት ሜትር ገደማ ይሆናል። ንጉሡ ለሐውልቱ ምረቃ ትልቅ ክብረ በዓል አዘጋጀ፤ የመንግሥት ባለሥልጣናቱ ሁሉ ክብረ በዓሉ ላይ እንዲገኙም አዘዘ። ሦስቱ ዕብራውያን ይህን ንጉሣዊ ድንጋጌ ታዝዘው ሥነ ሥርዓቱ ላይ መገኘት ነበረባቸው።
አዋጅ ነጋሪው የንጉሡን ትእዛዛት ሲያሰማ፣ በተሰበሰበው ሕዝብ መሃል ጸጥታ ሰፈነ። በመጀመሪያ የሙዚቃ ድምፅ እንደሚሰማ ተናገረ፤ ዓላማው የተሰበሰቡትን ሰዎች ስሜት መቀስቀስ ሳይሆን አይቀርም። ከዚያም በቦታው ያሉት ሁሉ ‘በግንባራቸው ተደፍተው ለምስሉ መስገድ’ ይጠበቅባቸዋል። ጣዖት አምልኮን የሚያወግዘውን የይሖዋን ሕግ አሳምረው የሚያውቁት እነዚህ ሦስት ዕብራውያን ምን ሊያደርጉ ነው?—ዘፀ. 20:4, 5
ለጣዖት ካልሰገዱ እንደሚገደሉ በብዙ ተመልካች ፊት ተዛተባቸው
ሙዚቃው ጀመረ። በዚህ ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ በግንባሩ ተደፍቶ ለምስሉ ሰገደ። ሦስቱ ወንዶች ግን እንደቆሙ ቀሩ። የሁሉም ሰው ዓይን በእነሱ ላይ አረፈ። የተወሰኑ ከለዳውያን አጋጣሚውን ተጠቅመው እነዚህን ወጣት አይሁዳውያን መወንጀልና ስማቸውን ማጥፋት ጀመሩ። ለናቡከደነጾር እንዲህ አሉት፦ “ንጉሥ ሆይ፣ እነዚህ ሰዎች ለአንተ አክብሮት የላቸውም። አማልክትህን አያገለግሉም እንዲሁም ላቆምከው የወርቅ ምስል ለመስገድ እንቢተኞች ሆነዋል።” ንጉሡም ሦስቱን ወጣቶች አስጠራና የተወነጀሉበት ክስ በእርግጥ እውነት መሆኑን በቁጣ ጠየቃቸው። ለመመለስ እንኳ እድል ሳይሰጣቸው ዛተባቸው። የንጉሡን ትእዛዝ ማክበር የሚችሉበት አንድ ዕድል ብቻ እንደሚሰጣቸው፣ እንደዚያ ካላደረጉ ግን “ወዲያውኑ ወደሚንበለበለው የእቶን እሳት [እንደሚጣሉ]” ነገራቸው። ሊታደጋቸው የሚችል አምላክ እንደሌለ አፉን ሞልቶ ተናገረ።
ሃናንያህ፣ ሚሳኤልና አዛርያስ ፍንክች አላሉም። ‘ወደ እሳቱ የሚጣሉ ከሆነ’ አምላካቸው ከዚህ አሰቃቂ ሞት ሊታደጋቸው እንደሚችል ለንጉሡ ነገሩት። ሆኖም አክለው “እሱ ባያስጥለንም እንኳ ንጉሥ ሆይ፣ የአንተን አማልክት እንደማናገለግልና ላቆምከው የወርቅ ምስል እንደማንሰግድ እወቅ” አሉት። ናቡከደነጾር ይባሱኑ ተቆጣ። የእቶኑ እሳት ከወትሮው የበለጠ እንዲነድና ሦስቱ ወጣቶች ታስረው ወደ ነበልባሉ እንዲጣሉ አዘዘ። እሳቱ በጣም ኃይለኛ ከመሆኑ የተነሳ ዕብራውያኑን ወደ እቶኑ የወሰዷቸው ወንዶች እንኳ በወላፈኑ ተቃጥለው ሞቱ!
ከዚያ ግን ናቡከደነጾር የሚያስደነግጥ ነገር ተመለከተ። በነበልባሉ መሃል ሦስት ሳይሆን አራት ሰዎች ነበሩ። እሳቱ ውስጥ ወዲያ ወዲህ ይላሉ፤ ጫፋቸውን የነካቸውም አይመስልም! አራተኛው ሰው ደግሞ “የአማልክትን ልጅ [እንደሚመስል]” ናቡከደነጾር ተናገረ። ንጉሡ የሚችለውን ያህል ወደ እቶኑ ከተጠጋ በኋላ ወጣቶቹ ከእሳቱ እንዲወጡ ተጣራ።
ሦስቱ ወጣቶች እሳቱ በጨረፍታ እንኳ ሳይነካቸው ከእቶኑ ሲወጡ የተሰበሰበው ሕዝብ ምን ያህል እንደሚደመም አስበው። በልብሳቸውም ሆነ በሰውነታቸው ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት አልደረሰም፤ የእሳቱ ሽታ እንኳ በላያቸው የለም። አሁን የተለወጠ ነገር ቢኖር የታሰሩበት ነገር መፈታቱ ነው። ኩሩው ናቡከደነጾር በአድናቆት ተዋጠ። አምላካቸውን በመታዘዛቸው ሦስቱን ዕብራውያን አመሰገናቸው። ‘በአምላካቸው እንደታመኑ’ ከገለጸ በኋላ “የንጉሡን ትእዛዝ ለመቀበል ፈቃደኞች አልሆኑም፤ የራሳቸውን አምላክ ትተው ሌላ አምላክ ከማገልገል ወይም ከማምለክ ይልቅ ሞትን መርጠዋል” አለ።
እብሪተኛው ንጉሥ በግዛቱ ውስጥ በይሖዋ ላይ መጥፎ ነገር የሚናገር ማንኛውም ሰው በሞት እንዲቀጣ ደነገገ። ለሦስቱ ወጣቶች ደግሞ የደረጃ እድገት ሰጣቸው። የይሖዋ ወሮታ ግን ከዚህም እጅግ የላቀ ነው፤ ያደረጉትን ነገር ፈጽሞ አልረሳም። ለምሳሌ ከበርካታ ዘመናት በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ አስደናቂ እምነት ስላሳዩ ሰዎች በመንፈስ መሪነት ሲጽፍ አንዳንዶች “የእሳትን ኃይል [እንዳጠፉ]” ተናግሯል። ይህን ያለው ደፋሮቹን ሃናንያህን፣ ሚሳኤልንና አዛርያስን በአእምሮው ይዞ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም።
ታሪኩን ከመጽሐፍ ቅዱስ አንብብ፦
ለውይይት፦
ሃናንያህ፣ ሚሳኤልና አዛርያስ ድፍረት ያሳዩት በየትኞቹ መንገዶች ነው?
ጠለቅ ብለህ መርምር
1. የአርኪኦሎጂ ግኝቶች በዳንኤል ምዕራፍ 3 ላይ የሚገኘውን ታሪክ ትክክለኛነት ያረጋገጡት እንዴት ነው? (w23.07 31) ሀ
© The Trustees of the British Museum. Licensed under CC BY-NC-SA 4.0. Source. Modifications: Box added
ሥዕል ሀ፦ የናቡከደነጾር ስም የተቀረጸበት የተተኮሰ ጡብ
2. ለሦስቱ ዕብራውያን የተሰጡት የባቢሎን ስሞች ትርጉማቸው ምን ሊሆን ይችላል? (dp 35-36 አን. 14)
3. ናቡከደነጾር ሃይማኖተኛ ሰው እንደነበር የሚጠቁም ምን ማስረጃ አለ? (dp 69 አን. 3) ለ
ሥዕል ለ፦ ናቡከደነጾር የበርካታ ባቢሎናውያን አማልክትን ቤተ መቅደሶች ገንብቷል ወይም ጠግኗል
4. “ከተለያዩ ብሔራትና ቋንቋዎች የተውጣጡት ሕዝቦች” የየራሳቸው አማልክት እያሏቸው ናቡከደነጾር ላቆመው ምስል ለመስገድ ፈቃደኛ የሆኑት ለምን ሊሆን ይችላል? (ዳን. 3:7፤ dp 73 አን. 10)
ምን እንደሚያስተምርህ አስብ
ሦስቱ ዕብራውያን ከምግብ ጋር በተያያዘ አቋማቸውን አላላሉም። በኋላ ላይ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ የሚጥል ነገር ሲያጋጥማቸውም በአቋማቸው ጸንተዋል። ታዲያ ቀላል በሚመስሉ ነገሮችም ጭምር ታማኝ መሆንን በተመለከተ ከዚህ ምን እንማራለን? (ሉቃስ 16:10) ሐ
ሥዕል ሐ
ስደት ሲደርስብን እንደ ሦስቱ ዕብራውያን የሚከተሉትን ባሕርያት ማንጸባረቅ የምንችለው እንዴት ነው? (ዳን. 3:16-18)
ትሕትና
ገርነት
ታማኝነት
የእነዚህን ሦስት ሰዎች የድፍረት ምሳሌ በየትኞቹ መንገዶች መኮረጅ ትችላለህ?
በትልቁ ነገር ላይ አሰላስል
ይህ ታሪክ ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረኛል?
ይህ ታሪክ ከይሖዋ ዓላማ ጋር ያለው ግንኙነት ምንድን ነው?
ሃናንያህ፣ ሚሳኤልና አዛርያስ ከሞት ሲነሱ ምን ልጠይቃቸው እፈልጋለሁ?
እውቀትህን አስፋ
አንድ ክርስቲያን ብሔራዊ ሥነ ሥርዓቶች ላይ የገለልተኝነት አቋሙን በአክብሮት ማሳየት የሚችለው እንዴት ነው?
ይህ ታሪክ ሕያው እንዲሆንልህ በማድረግ ምን ተጨማሪ ቁም ነገሮች እንደምትማር ተመልከት።