37 ዳንኤል
“ላለመርከስ በልቡ ቁርጥ ውሳኔ አደረገ”
ዳንኤል የሚኖረው ከአገሩ ርቆ ነው። ከትውልድ አገራቸው ከይሁዳ በግዞት ወደ ባቢሎን ከተወሰዱት በርካታ አይሁዳውያን መካከል የእሱም ቤተሰብ ይገኝበታል። ጉዞው አራት ወር ገደማ ሳይፈጅ አይቀርም። ከግዞተኞቹ መካከል ደግሞ ዳንኤልና የተወሰኑ ወጣቶች ከቤተሰቦቻቸው ተነጥለው ወደ ዋና ከተማዋ ተወሰዱ። ዳንኤል እንዲሁም ሃናንያህ፣ ሚሳኤልና አዛርያስ የተባሉት ዕብራውያን ወጣቶች ጓደኛሞች ሆኑ። የባቢሎናውያን ገዢዎቻቸው ዓላማ እነሱን ባቢሎናውያን ማድረግ እንደሆነ ለመረዳት ጊዜ አልወሰደባቸውም።
ከአገሩና ከቤተሰቡ ርቆ ለመኖር የተገደደው ዳንኤል አቋሙን እንዲያላላ ብዙ ጫና ደርሶበታል
ገና ከመነሻው የባቢሎኑ ንጉሥ ናቡከደነጾር በሰጠው ትእዛዝ መሠረት፣ አሽፈኔዝ የተባለው ዋና የቤተ መንግሥቱ ባለሥልጣን ስማቸውን ቀየረው። የብዙ ዕብራውያን ስሞች እውነተኛውን አምላክ የሚያወድሱ ናቸው። ለምሳሌ “ዳንኤል” ማለት “አምላክ ፈራጄ ነው” ማለት ነው። በባቢሎናውያን ዘንድም ቢሆን አማልክቶቻቸውን የሚያወድሱ ስሞችን ማውጣት የተለመደ ነበር። ለምሳሌ ለዳንኤል የተሰጠው ብልጣሶር የሚለው ስም፣ ቤል የተባለው ጣዖት የንጉሡን ሕይወት እንዲጠብቅ ከሚቀርብ ጸሎት ላይ የተወሰደ ሳይሆን አይቀርም። ንጉሡ የእነዚህን ወጣቶች አስተሳሰብ ለመቅረጽም ጥረት አድርጓል። በቤተ መንግሥቱ ውስጥ እሱን ማገልገል ይችሉ ዘንድ በከለዳውያን ቋንቋ መናገርና መጻፍ እንዲማሩ ትእዛዝ ሰጥቷል። ይሁንና ነገሩ በዚህ ብቻ አያበቃም።
ንጉሡ ለእነዚህ ወጣት ግዞተኞች የሚሰጠውን ሥልጠና እንዲከታተል አሽፈኔዝን ሾመው። ከንጉሡ ማዕድ ላይ ምርጥ የተባሉ ምግቦችን ይመገባሉ፤ ለእሱ ከሚቀርበው ምርጥ የወይን ጠጅም ይጠጣሉ። አንዳንድ ወጣቶች ይህ ትልቅ ክብር እንደሆነ ተሰምቷቸው ይሆናል። ዳንኤል የታየው ግን ልዩ መብት ከሚመስለው ከዚህ ዝግጅት በስተ ጀርባ ያለው ስውር አደጋ ነው። ያሳሰበው ነገር ምን ይሆን?
ዳንኤል እነዚህን ሐሳቦች አውጥቶና አውርዶ ሊሆን ይችላል፦ ‘በይሖዋ ሕግ የተነሳ የማንመገባቸው ምግቦች እንዳሉ የማረኩን ሰዎች ያውቃሉ። ይሖዋ ርኩስ ያላቸውን ምግቦች በማቅረብ ትእዛዙን እንድንጥስ ሊያደርጉን ይሞክሩ ይሆን? የሚያቀርቡልን ሥጋ ለመብላት የተፈቀደ ቢሆን እንኳ ደሙን በአግባቡ ያፈሱታል? ወይስ ይሖዋ ደም እንዳንበላ የሰጠውን ሕግ በተንኮል ሊያስጥሱን ይሞክሩ ይሆን? ምናልባት ከዚህ ማዕድ ብንበላ በጣዖት አምልኮ እንደተካፈልን ሊቆጠር ይችላል? ደግሞስ ከሚያቀርቡልን ብዙ የወይን ጠጅ ብንጠጣ የማመዛዘን ችሎታችንን መጠበቅ ከባድ አይሆንብንም?’a
ዳንኤል ስለ ጉዳዩ ብዙ ጸልዮና ሦስቱን ጓደኞቹን አማክሮ መሆን አለበት። ይሖዋን የሚያስደስተውን ነገር ለማድረግ “በልቡ ቁርጥ ውሳኔ አደረገ።” ከዚያም ወደ አሽፈኔዝ ቀርቦ በዘዴ አነጋገረው፤ እሱና ሦስት ጓደኞቹ ከሚያረክሱ ምግቦች አለመብላት ይፈቀድላቸው እንደሆነ ጠየቀው። ይሖዋ ከዳንኤል ጋር ስለነበር ዋናው ባለሥልጣን ሞገስ እንዲያሳየው አደረገ። ያም ቢሆን ባለሥልጣኑ የቀረበላቸውን ምግብ ካልበሉ ጤንነታቸው እንዳይጎዳ ሰግቶ ነበር። ይህ ከሆነ ናቡከደነጾር ተጠያቂ እንደሚያደርገው ያውቃል። በዚህ ጊዜ ዳንኤል አልተከራከረም። ቆየት ብሎ ግን ዳንኤል፣ አሽፈኔዝ በወጣቶቹ ላይ ለሾመው ጠባቂ አንድ የመፍትሔ ሐሳብ በድፍረት አቀረበ፦ ለአሥር ቀናት አትክልትና ውኃ ብቻ እንዲሰጣቸው ከዚያም የአራቱን ወጣቶች ሁኔታ ከሌሎቹ ወጣቶች ጋር እንዲያወዳድር ጠየቀው። ጠባቂው ሙከራውን ለማድረግ ተስማማ!
ከአሥር ቀናት በኋላ ውጤቱ ግልጽ ሆነ፤ የአራቱ ወጣቶች መልክና ቁመና ከሌሎቹ ወጣቶች ሁሉ የተሻለ እንደሆነ ታየ! እንዲያውም ሙከራው አመርቂ ውጤት በማስገኘቱ ከዚያ በኋላ ተመሳሳይ የአመጋገብ ሥርዓት እንዲከተሉ ተፈቀደላቸው። ዳንኤልና ጓደኞቹ እምነትና ድፍረት በማሳየታቸው ይሖዋ እንደባረካቸው በግልጽ ታይቷል። ይህም ፈጽሞ የማይረሱት ቁም ነገር አስተምሯቸዋል።
ቀጣዩ ምዕራፍ እንደሚያሳየው ከጊዜ በኋላ የዳንኤል ሦስት ጓደኞች ድፍረታቸውን በእጅጉ የሚፈታተን አስፈሪ ሁኔታ ገጥሟቸዋል። ዳንኤልም በበኩሉ በሕይወት በኖረባቸው 100 ዓመታት ገደማ ድፍረቱ ተፈትኗል። ይሖዋ ለናቡከደነጾር ያሳየውን ሕልም እንዲተረጉም በተጠየቀበት ወቅት ሕልሙ ይህን እብሪተኛ ንጉሥና መንግሥቱን በተመለከተ መጥፎ ዜና የያዘ ቢሆንም ፍቺውን ከመናገር ወደኋላ አላለም። ከአሥርተ ዓመታት በኋላ ደግሞ በመለኮታዊ ጣልቃ ገብነት ግድግዳ ላይ የተጻፈን ጽሑፍ እንዲተረጉም ተጠይቆ ነበር። መልእክቱ በወቅቱ ንጉሥ ሆኖ ያስተዳድር ለነበረው ለቤልሻዛር ውግዘት የያዘ ቢሆንም ፍቺውን በድፍረት ተናግሯል። ዕድሜው ገፍቶ እርጅና በተጫጫነው ወቅት ደግሞ ከዚህም የከፋ አደገኛ ሁኔታ አጋጥሞታል፤ የተራቡ አንበሶች በሞሉበት ጉድጓድ ውስጥ ተጥሏል። በእነዚህ ጊዜያት ሁሉ ወጣት ሳለ ያሳየው ድፍረት አልተለየውም። ታዲያ አንድ የይሖዋ መልአክ “እጅግ የተወደድክ” ቢለው ምን ይገርማል!
ታሪኩን ከመጽሐፍ ቅዱስ አንብብ፦
ለውይይት፦
ዳንኤል ድፍረት ያሳየው በየትኞቹ መንገዶች ነው?
ጠለቅ ብለህ መርምር
1. ዳንኤል 1:1 ከኤርምያስ 25:1 ጋር ይጋጫል? (dp 18-19 አን. 14-15)
2. መጽሐፍ ቅዱስ ‘የናቡከደነጾርን አምላክ ግምጃ ቤት’ ይጠቅሳል፤ አንድ የባቢሎናውያን የተቀረጸ ጽሑፍ ይህን ሐሳብ የሚደግፈው እንዴት ነው? (ዳን. 1:2፤ it “ግምጃ ቤት” አን. 3-wcgr) ሀ
© The Trustees of the British Museum. Licensed under CC BY-NC-SA 4.0. Source. Modifications: Box added
ሥዕል ሀ፦ የናቡከደነጾር የተቀረጸ ጽሑፍ፣ በሜሮዳክ ቤተ መቅደስ ውስጥ “ግምጃ ቤት” እንዳለ ይጠቁማል
3. “አስማተኛ ካህናት” በማኅበረሰቡ ውስጥ ምን ቦታ ነበራቸው? (ዳን. 1:20፤ it “አስማት እና መተት” አን. 2-6-wcgr) ለ
ሥዕል ለ፦ በርኩስ መንፈስ የተጠቃ ሰው “ፈውስ” ስለሚያገኝበት መንገድ የሚገልጽ የባቢሎናውያን ጽላት
4. ለዳንኤልና ለሦስቱ ጓደኞቹ የቀረበው አትክልት ምንን ሊያጠቃልል ይችላል? (ዳን. 1:12፤ dp 40 አን. 25)
ምን እንደሚያስተምርህ አስብ
ወጣቶች ቤተሰቦቻቸው በማያዩአቸው ጊዜም እንኳ ለይሖዋ ታማኝ መሆንን በተመለከተ ከዳንኤል ምን ይማራሉ?
ዳንኤል አስቀድሞ “በልቡ ቁርጥ ውሳኔ [ማድረጉ]” ደፋር እንዲሆን የረዳው እንዴት ነው? (ዳን. 1:8) የእሱን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? ሐ
ሥዕል ሐ
የዳንኤልን የድፍረት ምሳሌ በየትኞቹ ሌሎች መንገዶች መኮረጅ ትችላለህ?
በትልቁ ነገር ላይ አሰላስል
ይህ ታሪክ ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረኛል?
ይህ ታሪክ ከይሖዋ ዓላማ ጋር ያለው ግንኙነት ምንድን ነው?
ዳንኤል ከሞት ሲነሳ ምን ልጠይቀው እፈልጋለሁ?
እውቀትህን አስፋ
በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ላይ የሚገኙትን ክንውኖች የሚያሳይ ድራማ ተመልከት።
ዛሬ ያሉ ወጣቶች ድፍረትና ታማኝነት በማሳየት ዳንኤልን መምሰል የሚችሉት እንዴት ነው?