ኅዳር
ሰኞ፣ ኅዳር 1
ሌሎች ከእናንተ እንደሚበልጡ አስቡ።—ፊልጵ. 2:3
በሌሎች ዘንድ እንደ ጥበበኛ የሚቆጠሩ በርካታ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ለራሳችን ሊኖረን ስለሚገባው አመለካከት የሚሰጠውን ምክር ያጣጥላሉ። ሌሎች ከእኛ እንደሚበልጡ አድርገን የምናስብ ከሆነ ራሳችንን ለጥቃት እንደምናጋልጥና የሌሎች መጠቀሚያ እንደምንሆን ይናገራሉ። ይሁንና የሰይጣን ዓለም የሚያራምደው ለራስ ትልቅ ቦታ የመስጠት ዝንባሌ ምን ውጤት አስከትሏል? ራስ ወዳድ የሆኑ ሰዎች ደስተኛ ናቸው? አስደሳች የቤተሰብ ሕይወትና እውነተኛ ወዳጆች አሏቸው? ከአምላክ ጋር የጠበቀ ዝምድና መመሥረት ችለዋል? ካያችሁት ነገር በመነሳት ምን አስተያየት ትሰጣላችሁ? የተሻለ ውጤት የሚያስገኘው በዚህ ዓለም ጥበብ መመራት ነው ወይስ በአምላክ ቃል ውስጥ በሚገኘው ጥበብ መመራት? (1 ቆሮ. 3:19) ዓለም እንደ ጥበበኛ አድርጎ የሚመለከታቸውን ሰዎች ምክር መከተል፣ እሱ ራሱ መንገድ ጠፍቶበት እየተደናበረ ወዳለ ሰው ሄዶ አቅጣጫ ከመጠየቅ ተለይቶ አይታይም። ኢየሱስ በዘመኑ የነበሩ ሰዎች ጥበበኛ አድርገው የሚቆጥሯቸውን ሰዎች አስመልክቶ ሲናገር “እነሱ ዕውር መሪዎች ናቸው። ስለዚህ ዕውር ዕውርን ቢመራ ሁለቱም ጉድጓድ ውስጥ ይወድቃሉ” ብሏል። (ማቴ. 15:14) በእርግጥም የዚህ ዓለም ጥበብ በአምላክ ፊት ሞኝነት ነው። w19.05 24-25 አን. 14-16
ማክሰኞ፣ ኅዳር 2
ለእሱ የተመረጡትን ይሰበስባሉ።—ማቴ. 24:31
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በመታሰቢያው በዓል ላይ ከቂጣውና ከወይን ጠጁ የሚወስዱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው። ታዲያ ቁጥሩ መጨመሩ ሊያሳስበን ይገባል? አይገባም። “ይሖዋ የእሱ የሆኑትን ያውቃል።” (2 ጢሞ. 2:19) በመታሰቢያው በዓል ላይ ከቂጣውና ከወይን ጠጁ የሚወስዱ ሰዎችን የሚቆጥሩት ወንድሞች ግን በእርግጥ በመንፈስ የተቀባው ማን እንደሆነ ማወቅ አይችሉም። በመሆኑም ከቂጣውና ከወይን ጠጁ የሚወስዱት ሰዎች ቁጥር፣ ቅቡዓን ነን ብለው በስህተት የሚያስቡ ሰዎችንም ይጨምራል። ለምሳሌ፣ በአንድ ወቅት ከቂጣውና ከወይን ጠጁ ይወስዱ የነበሩ አንዳንዶች ከጊዜ በኋላ ይህን ማድረጋቸውን አቁመዋል። ሌሎች ደግሞ ከክርስቶስ ጋር በሰማይ እንደሚገዙ አድርገው የሚያስቡት ከአእምሮ ወይም ከስሜት ጋር የተያያዘ ችግር ስላለባቸው ሊሆን ይችላል። ከዚህ በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው በምድር ላይ የቀሩትን ቅቡዓን ትክክለኛ ቁጥር አናውቅም። ኢየሱስ ቅቡዓኑን ወደ ሰማይ ለመውሰድ በሚመጣበት ጊዜ በብዙ የዓለም ክፍሎች ቅቡዓን ይኖራሉ። እርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ፣ በመጨረሻዎቹ ቀናት በምድር ላይ የሚቀሩት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ጥቂት እንደሚሆኑ ይናገራል። (ራእይ 12:17) ይሁንና ታላቁ መከራ ሲጀምር በምድር ላይ ምን ያህል ቅቡዓን እንደሚኖሩ አይናገርም። w20.01 29-30 አን. 11-13
ረቡዕ፣ ኅዳር 3
አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ . . . አንድያ ልጁን ሰጥቷል።—ዮሐ. 3:16
ኢየሱስ የይሖዋን አባታዊ ፍቅር በምሳሌ ለማስረዳት ስለ አባካኙ ልጅ የሚገልጸውን ታሪክ ተናግሯል። (ሉቃስ 15:11-32) በዚያ ምሳሌ ላይ የተጠቀሰው አባት ልጁ እንደሚመለስ ሁልጊዜ ተስፋ ያደርግ ነበር። በኋላ ላይ ልጁ ወደ ቤት ሲመለስ አባትየው በደስታ ተቀብሎታል። እኛም ከይሖዋ ርቀን ሊሆን ይችላል፤ ንስሐ ከገባን ግን አፍቃሪው አባታችን እኛን ለመቀበል ፈቃደኛና ዝግጁ እንደሆነ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። አባታችን ይሖዋ፣ አዳም ያስከተለውን ጉዳት በሙሉ ያስተካክለዋል። አዳም ካመፀ በኋላ ይሖዋ ከሰው ዘሮች መካከል 144,000 ሰዎችን እንደ ልጆቹ አድርጎ ለመውሰድ ወሰነ፤ እነዚህ ሰዎች ከልጁ ጋር በሰማይ ነገሥታትና ካህናት ሆነው ያገለግላሉ። ኢየሱስና እነዚህ ተባባሪ ገዢዎች በአዲሱ ዓለም ውስጥ ታዛዥ የሰው ልጆች ወደ ፍጽምና እንዲደርሱ ይረዳሉ። ወደ ፍጽምና የደረሱት የሰው ልጆች የመጨረሻውን ፈተና ካለፉ በኋላ አምላክ የዘላለም ሕይወት ይሰጣቸዋል። ከዚያ በኋላ አባታችን፣ ምድር ፍጹማን በሆኑ ወንዶችና ሴቶች ልጆቹ ስትሞላ በማየት ይደሰታል። ይህ እንዴት ያለ አስደናቂ ጊዜ ይሆናል! w20.02 6-7 አን. 17-19
ሐሙስ፣ ኅዳር 4
አእምሯችሁን የሚያሠራው ኃይል እየታደሰ ይሂድ።—ኤፌ. 4:23
ሁላችንም እንደሚከተለው ብለን ራሳችንን መጠየቅ አለብን፦ ‘ክርስቶስን ለመምሰል ስል የማደርገው ለውጥ እንዲሁ የታይታ ነው? ወይስ ሥር ነቀል ለውጥ እያደረግኩ ነው?’ በሁለቱ መካከል ሰፊ ልዩነት አለ። ኢየሱስ በማቴዎስ 12:43-45 ላይ ምን ማድረግ እንደሚያስፈልገን ተናግሯል። ይህ ጥቅስ አንድ አስፈላጊ ትምህርት ይዞልናል፦ የተሳሳቱ ሐሳቦችን ከአእምሯችን ማስወገድ ብቻውን በቂ አይደለም፤ በምትኩ አእምሯችን አምላክን በሚያስደስቱ ሐሳቦች እንዲሞላ ማድረግ ያስፈልገናል። ዝንባሌያችንን ወይም ውስጣዊ ማንነታችንን መለወጥ የሚቻል ነገር ነው? የአምላክ ቃል ይህን ማድረግ እንደሚቻል ሲገልጽ እንዲህ ይላል፦ “እንደ አምላክ ፈቃድ የተፈጠረውንና ከእውነተኛ ጽድቅና ታማኝነት ጋር የሚስማማውን አዲሱን ስብዕና መልበስ ይኖርባችኋል።” (ኤፌ. 4:24) ስለዚህ ውስጣዊ ማንነታችንን መለወጥ እንችላለን፤ ይህን ማድረግ ቀላል ነው ማለት ግን አይደለም። መጥፎ ምኞቶችን መቆጣጠርና መጥፎ ነገር ከመፈጸም መቆጠብ ብቻውን በቂ አይደለም። ‘አእምሯችንን የሚያሠራውን ኃይል’ መለወጥ ያስፈልገናል። ይህም ምኞታችንን፣ ዝንባሌያችንንና አንድን ነገር ለማድረግ የሚገፋፋንን ስሜት መቀየርን ይጠይቃል። ለዚህ ደግሞ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ አስፈላጊ ነው። w19.06 9-10 አን. 6-7
ዓርብ፣ ኅዳር 5
ይህን ስፍራ ልናጠፋው ነው።—ዘፍ. 19:13
ይሖዋ ሎጥንና ቤተሰቡን ከጥፋት ለማዳን መላእክትን በመላክ ርኅራኄ አሳይቶታል። ሎጥ ግን “ዘገየ።” በመሆኑም መላእክቱ እጁን በመያዝ እሱንና ቤተሰቡን ከከተማዋ ማስወጣት አስፈልጓቸው ነበር። (ዘፍ. 19:15, 16) ከዚያም ወደ ተራራማው አካባቢ እንዲሸሽ ለሎጥ ነገሩት። ሎጥ ግን ይሖዋን ከመታዘዝ ይልቅ ቅርብ ወዳለች አንዲት ከተማ ለመሄድ ጠየቀ። (ዘፍ. 19:17-20) ይሖዋም የሎጥን ጥያቄ በትዕግሥት ያዳመጠ ሲሆን ሎጥ ወደፈለገው ከተማ እንዲሸሽ ፈቀደለት። በኋላ ላይ ግን ሎጥ በዚያች ከተማ መኖር ስለፈራ ወደ ተራራማው አካባቢ ሄዶ መኖር ጀመረ፤ ይሖዋ መጀመሪያውኑም ቢሆን እንዲሄድ የነገረው ወደዚህ ቦታ ነበር። (ዘፍ. 19:30) ይሖዋ ያሳየው ትዕግሥት እንዴት አስደናቂ ነው! እንደ ሎጥ ሁሉ የመንፈሳዊው ቤተሰባችን አባላትም የተሳሳተ ውሳኔ ያደርጉ ይሆናል፤ በዚህም የተነሳ ከባድ ችግር ሊያጋጥማቸው ይችላል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ቢፈጠር ምን እናደርጋለን? የተሳሳተ ውሳኔ ያደረገው ሰው፣ የዘራውን እያጨደ እንደሆነ ለመናገር እንፈተን ይሆናል፤ ደግሞም እውነታው ይህ ሊሆን ይችላል። (ገላ. 6:7) ሆኖም ይሖዋ ሎጥን በያዘበት መንገድ ወንድማችንን ብንረዳው የተሻለ ይሆናል። w19.06 20 አን. 3፤ 21 አን. 4-5
ቅዳሜ፣ ኅዳር 6
ይሖዋ ረዳቴ ነው፤ አልፈራም።—ዕብ. 13:6
ጠላቶቻችን በአምልኳችን ላይ እገዳ ሲጥሉ፣ ዓላማቸው ፈርተን ይሖዋን ማገልገላችንን እንድንተው ማድረግ ነው። እገዳ ከመጣል በተጨማሪ ስለ እኛ የሐሰት ወሬ ያናፍሱ፣ በፖሊሶች ቤታችን እንዲፈተሽ ያደርጉ፣ ፍርድ ቤት ያቀርቡን ሌላው ቀርቶ አንዳንዶቻችንን ያስሩን ይሆናል። ፍላጎታቸው ከመካከላችን ጥቂት ሰዎችን በማሰር እኛን ማስፈራራት ነው። በፍርሃት እንድንርድ እንዲያደርጉን ከፈቀድን እኛው ራሳችን በአምልኳችን ላይ እገዳ እንጥላለን። በዘሌዋውያን 26:36, 37 ላይ እንደተገለጹት ሰዎች መሆን አንፈልግም። ፍርሃት፣ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎቻችንን እንድንቀንስ ወይም እንድናቆም እንዲያደርገን መፍቀድ የለብንም። በይሖዋ ሙሉ በሙሉ የምንታመን ሲሆን ፈጽሞ አንደናገጥም። (ኢሳ. 28:16) ይሖዋ መመሪያ እንዲሰጠን እንጸልያለን። ይሖዋ ከእኛ ጋር እስከሆነ ድረስ በጣም ኃያል የሚባለው ሰብዓዊ መንግሥትም ቢሆን አምላካችንን በታማኝነት ከማምለክ ሊያግደን እንደማይችል እናውቃለን። ተቃውሞ በፍርሃት እንድንሽመደመድ ከማድረግ ይልቅ ይሖዋን ይበልጥ እንድናገለግል ሊያነሳሳን ይችላል። w19.07 9-10 አን. 6-7
እሁድ፣ ኅዳር 7
ቃሉን ስበክ።—2 ጢሞ. 4:2
አገልግሎትህ ውጤታማ እንዳልሆነ ቢሰማህም እንኳ ደቀ መዛሙርት የሚሆኑ ሰዎች ለማግኘት በምታደርገው ጥረት ተስፋ አትቁረጥ። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ ዓሣ ከማጥመድ ጋር እንዳመሳሰለው አስታውስ። ዓሣ አጥማጆች፣ ዓሣ ለመያዝ ረጅም ሰዓት መሥራት ሊያስፈልጋቸው ይችላል። አብዛኛውን ጊዜ በጣም አምሽተው አሊያም በሌሊት ተነስተው መሥራት ይኖርባቸው ይሆናል፤ አንዳንድ ጊዜም በጀልባቸው ረጅም ርቀት መጓዝ አለባቸው። (ሉቃስ 5:5) ከዚህ ጋር በሚመሳሰል መልኩ፣ ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ የሚካፈሉ አንዳንድ ክርስቲያኖች ሰዎችን በመፈለጉ ሥራ ረጅም ሰዓት የሚያሳልፉ ሲሆን በተለያየ ጊዜና ቦታ በትዕግሥት መረባቸውን ይጥላሉ። ይህን የሚያደርጉት ለምንድን ነው? በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎችን ማግኘት ስለሚፈልጉ ነው። ብዙውን ጊዜ በዚህ ረገድ ተጨማሪ ጥረት የሚያደርጉ ክርስቲያኖች፣ ለመልእክቱ ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች በማግኘት ይካሳሉ። አንተስ ሰዎችን በምታገኝበት ሰዓት ወይም ቦታ ለመስበክ ይበልጥ ጥረት ማድረግ ትችል ይሆን? የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን መምራት ትዕግሥት የሚጠይቀው ለምንድን ነው? አንዱ ምክንያት፣ ተማሪው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን መሠረተ ትምህርቶች እንዲያውቅና እንዲወድ ከመርዳት ያለፈ ነገር ማድረግ ያለብን መሆኑ ነው። የምናስጠናው ሰው የመጽሐፍ ቅዱስ ባለቤት የሆነውን ይሖዋን እንዲያውቅና እንዲወደው ልንረዳው ይገባል። w19.07 18-19 አን. 14-15
ሰኞ፣ ኅዳር 8
ከኋላዬ ያሉትን ነገሮች [እረሳለሁ]።—ፊልጵ. 3:13
አንዳንዶቻችን ቀደም ሲል በሠራነው ኃጢአት የተነሳ ከሚሰማን የጥፋተኝነት ስሜት ጋር መታገል ይኖርብን ይሆናል። አንተም እንዲህ የሚሰማህ ከሆነ የክርስቶስን ቤዛዊ መሥዋዕት በተመለከተ ጥልቀት ያለው ጥናት ማድረግህ ይጠቅምሃል። እንዲህ ስላለው የሚያበረታታ ርዕሰ ጉዳይ ማጥናታችን፣ ማሰላሰላችንና መጸለያችን በውስጣችን የሚሰማን አላስፈላጊ የጥፋተኝነት ስሜት እንዲቀንስ ያደርጋል። አልፎ ተርፎም ይሖዋ ኃጢአታችንን ይቅር እንዳለን ስለምንተማመን የጥፋተኝነት ስሜታችን ሙሉ በሙሉ ሊወገድ ይችላል። ከጳውሎስ የምንማረው ሌላም ነገር አለ። አንዳንዶች በይሖዋ አገልግሎት የበለጠ ለመካፈል ሲሉ ጥሩ የሚባል ሥራቸውን ትተው ሊሆን ይችላል። እኛም እንዲህ አድርገን ከሆነ ልናገኛቸው እንችል የነበሩ ቁሳዊ ነገሮችን እያሰብን ከመቆጨት ይልቅ ‘ከኋላ ያሉትን ነገሮች ለመርሳት’ ጥረት እናደርጋለን? (ዘኁ. 11:4-6፤ መክ. 7:10) ‘ከኋላ ያሉት ነገሮች’ የሚለው አገላለጽ ቀደም ሲል በይሖዋ አገልግሎት ያከናወንናቸውን ነገሮች አሊያም በጽናት ያሳለፍናቸውን ችግሮች ሊጨምር ይችላል። እርግጥ ነው፣ ባለፉት ዓመታት ይሖዋ እንዴት እንደባረከንና እንደደገፈን መለስ ብለን ማሰባችን ወደ አባታችን ይበልጥ እንድንቀርብ ይረዳናል። ይሁን እንጂ ያከናወንነው ነገር በቂ እንደሆነ በማሰብ በዚህ ረክተን መቀመጥ አንፈልግም።—1 ቆሮ. 15:58፤ w19.08 3 አን. 5-6
ማክሰኞ፣ ኅዳር 9
ዘወትር ጸልዩ።—1 ተሰ. 5:17
በየትኛውም ቦታም ሆነ ጊዜ፣ በአክብሮት ወደ አምላካችን መጸለይ እንችላለን። ይሖዋ የእኛን ጸሎት ለመስማት የሚሆን ጊዜ አያጣም፤ ምንጊዜም ቢሆን ጸሎታችንን በትኩረት ያዳምጣል። ይሖዋ ጸሎታችንን እንደሚሰማ ስንመለከት ወደ እሱ ይበልጥ ለመቅረብ እንነሳሳለን። መዝሙራዊው “ይሖዋ ድምፄን . . . ስለሚሰማ እወደዋለሁ” ብሏል። (መዝ. 116:1) አባታችን የምናቀርበውን ጸሎት ከመስማት ባለፈ ለጸሎታችን ምላሽ ይሰጠናል። ሐዋርያው ዮሐንስ “የምንጠይቀው ነገር ምንም ይሁን ምን ከፈቃዱ ጋር በሚስማማ ሁኔታ እስከለመንን ድረስ [አምላክ] ይሰማናል” የሚል ማረጋገጫ ሰጥቶናል። (1 ዮሐ. 5:14, 15) እርግጥ ይሖዋ ለጸሎታችን መልስ የሚሰጠን በጠበቅነው መንገድ ላይሆን ይችላል። ይሖዋ ለእኛ የሚበጀውን ያውቃል፤ በመሆኑም አንዳንድ ጊዜ የጠየቅነውን ነገር ላይሰጠን አሊያም ደግሞ መልስ ሳይሰጠን የተወሰነ ጊዜ እንዲያልፍ ሊያደርግ ይችላል። (2 ቆሮ. 12:7-9) ይሖዋ የሚያስፈልገንን ነገር ያሟላልናል። ከሁሉም አባቶች የሚጠብቀውን ነገር እሱም ያደርጋል። (1 ጢሞ. 5:8) የልጆቹን ቁሳዊ ፍላጎት ያሟላል። ስለ ምግብ፣ ልብስ ወይም መጠለያ እንድንጨነቅ አይፈልግም። (ማቴ. 6:32, 33፤ 7:11) ይሖዋ አፍቃሪ አባት በመሆኑ ወደፊት የሚያስፈልጉንን ነገሮች እንኳ ሙሉ በሙሉ ለማሟላት ዝግጅት አድርጓል። w20.02 5 አን. 10-12
ረቡዕ፣ ኅዳር 10
ሁሉም አንድ መንጋ ይሆናሉ፤ አንድ እረኛም ይኖራቸዋል።—ዮሐ. 10:16
በሰማይ የመኖር ተስፋ ካላቸው መካከል ‘የታማኝና ልባም ባሪያ’ ክፍል የሆኑት ሁሉም አይደሉም። (ማቴ. 24:45-47) እንደ መጀመሪያው መቶ ዘመን ሁሉ በዛሬው ጊዜም ይሖዋና ኢየሱስ በጥቂት ወንድሞች ተጠቅመው ብዙኃኑን እየመገቡ ወይም እያስተማሩ ነው። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይሖዋ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍትን ለማስጻፍ የተጠቀመው በጥቂት ቅቡዓን ነበር። ዛሬም በተመሳሳይ ለአምላክ ሕዝብ “በተገቢው ጊዜ” መንፈሳዊ ምግብ የማቅረብ ኃላፊነት ያለባቸው ጥቂት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ብቻ ናቸው። ይሖዋ ለአብዛኞቹ የሰው ልጆች በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ሰጥቷቸዋል፤ ለጥቂቶች ደግሞ ከኢየሱስ ጋር በሰማይ የመግዛት ተስፋ ሰጥቷቸዋል። ይሖዋ ‘በአይሁዳዊው’ ለተመሰሉትም ሆነ ‘በአሥሩ ሰዎች’ ለተመሰሉት አገልጋዮቹ ወሮታ ይከፍላል፤ ደግሞም ሁለቱንም ቡድኖች ተመሳሳይ ሕጎችን እንዲታዘዙና ታማኝ ሆነው እንዲኖሩ ይጠብቅባቸዋል። (ዘካ. 8:23) ሁሉም ምንጊዜም ትሑት መሆን አለባቸው። እንዲሁም ሁሉም በኅብረት ሊያገለግሉትና አንድነት ሊኖራቸው ይገባል። በተጨማሪም ሁሉም በጉባኤ ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን ጥረት ማድረግ አለባቸው። ወደ መጨረሻው ይበልጥ እየተቃረብን ስንሄድ ሁላችንም እንደ “አንድ መንጋ” ሆነን ክርስቶስን መከተላችንን እና ይሖዋን ማገልገላችንን እንቀጥል። w20.01 31 አን. 15-16
ሐሙስ፣ ኅዳር 11
ለቃሉ የማይታዘዙ . . . ካሉ ያለቃል . . . ሊማረኩ [የሚችሉት] ንጹሕ ምግባራችሁንና የምታሳዩትን ጥልቅ አክብሮት ሲመለከቱ ነው።—1 ጴጥ. 3:1, 2
የቤተሰባችን አባላት ምሥራቹን እንዲቀበሉ ማስገደድ አንችልም፤ ሆኖም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት መቀበል ቀላል እንዲሆንላቸው መርዳት እንችላለን። (2 ጢሞ. 3:14, 15) በምግባራችሁ ምሥክርነት ስጡ። ብዙውን ጊዜ፣ ከምንናገረው ነገር ይልቅ የቤተሰባችንን አባላት ይበልጥ የሚማርከው ድርጊታችን ነው። የቤተሰባችሁን አባላት ለመርዳት የምታደርጉትን ጥረት አታቋርጡ። ይሖዋ በዚህ ረገድ ምሳሌ ይሆነናል። ሰዎች ምሥራቹን በመቀበል ሕይወት ማግኘት እንዲችሉ ‘ደግሞ ደጋግሞ’ አጋጣሚ ይሰጣቸዋል። (ኤር. 44:4) ሐዋርያው ጳውሎስም ጢሞቴዎስን፣ ሌሎችን ለመርዳት በሚያደርገው ጥረት እንዲጸና አበረታቶታል። ለምን? ምክንያቱም ይህን ሲያደርግ ራሱንም ሆነ የሚሰሙትን ያድናል። (1 ጢሞ. 4:16) እኛም የቤተሰባችንን አባላት ስለምንወዳቸው በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትን እውነቶች እንዲያውቁ እንፈልጋለን። w19.08 14 አን. 2፤ 16 አን. 8-9
ዓርብ፣ ኅዳር 12
ከተሰወረ ፍቅር ይልቅ የተገለጠ ወቀሳ ይሻላል።—ምሳሌ 27:5
አንድ ሰው ሁኔታችን አሳስቦት እኛን እስከ መምከር ከደረሰ፣ ከምናስበው በላይ አልፈን ሄደን ሊሆን እንደሚችል ማስታወስ ይኖርብናል። ምክር ሲሰጠን በአብዛኛው የሚቀናን ምክሩን ላለመቀበል ሰበብ አስባብ መደርደር ሊሆን ይችላል። ምክሩን የሰጠንን ግለሰብ ወይም ምክሩ የተሰጠበትን መንገድ እንተች ይሆናል። ትሑት ከሆንን ግን ለተሰጠን ምክር ትክክለኛውን አመለካከት ለመያዝ ጥረት እናደርጋለን። ትሑት ሰው ምክር ሲሰጠው በደስታ ይቀበላል። ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ በአንድ ክርስቲያናዊ ስብሰባ ላይ ተገኝተሃል እንበል። ከተለያዩ ወንድሞችና እህቶች ጋር ስትጫወት ከቆየህ በኋላ አንድ ወንድም ለብቻህ ወስዶ ጥርስህ ላይ የሆነ ነገር ስላለ እንድታጸዳው ይነግርሃል። ሁኔታው ሊያሳፍርህ እንደሚችል የታወቀ ነው። ሆኖም ወንድም እንዲህ ብሎ ስለነገረህ አመስጋኝ አትሆንም? እንዲያውም ‘ምነው የሆነ ሰው ቀደም ብሎ በነገረኝ ኖሮ!’ ብለህ ልታስብ ትችላለህ። በተመሳሳይም አንድ የእምነት ባልንጀራችን ድፍረት በማሳየት አስፈላጊውን ምክር ሲሰጠን ትሑት በመሆን ምክሩን በአመስጋኝነት መቀበል ይኖርብናል። እንዲህ ያለ ምክር የሰጠንን ሰው እንደ ወዳጃችን እንጂ እንደ ጠላታችን አናየውም።—ምሳሌ 27:6፤ ገላ. 4:16፤ w19.09 5 አን. 11-12
ቅዳሜ፣ ኅዳር 13
ልጄ ሆይ፣ የአባትህን ትእዛዝ ጠብቅ፤ የእናትህንም መመሪያ ቸል አትበል።—ምሳሌ 6:20
ይሖዋ ለእናቶች በቤተሰብ ውስጥ የተከበረ ቦታ ሰጥቷቸዋል፤ እናቶች በልጆቻቸው ላይ የተወሰነ ሥልጣን አላቸው። እንዲያውም አንዲት እናት በልጆቿ ላይ የምታሳድረው ተጽዕኖ ከፍተኛና እስከ ዕድሜ ልክ የሚዘልቅ ሊሆን ይችላል። (ምሳሌ 22:6) እናቶች ከኢየሱስ እናት ከማርያም ብዙ ትምህርት ማግኘት ይችላሉ። ማርያም ቅዱሳን መጻሕፍትን ጠንቅቃ ታውቅ ነበር። ለይሖዋ ጥልቅ አክብሮት የነበራት ከመሆኑም ሌላ ከእሱ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መሥርታ ነበር። መላ ሕይወቷን የሚነካባት ቢሆንም እንኳ ለይሖዋ አመራር ለመገዛት ፈቃደኛ ነበረች። (ሉቃስ 1:35-38, 46-55) እናቶች፣ የማርያምን ምሳሌ መከተል የምትችሉባቸው በርካታ መንገዶች አሉ። አንደኛ፣ መጽሐፍ ቅዱስን በግላችሁ በማጥናትና ብቻችሁን የምትጸልዩበት ጊዜ በመመደብ ከይሖዋ ጋር የመሠረታችሁትን የጠበቀ ወዳጅነት ይዛችሁ ቀጥሉ። ሁለተኛ፣ ይሖዋን ለማስደሰት ስትሉ በሕይወታችሁ ውስጥ ለውጦችን ለማድረግ ፈቃደኛ ሁኑ። w19.09 18 አን. 17-19
እሁድ፣ ኅዳር 14
እነሆ . . . እጅግ ብዙ ሕዝብ።—ራእይ 7:9
ሐዋርያው ዮሐንስ አንድ አስደሳች ትንቢታዊ ራእይ ተመለከተ። በራእዩ ላይ መላእክት፣ የአምላክን ባሪያዎች ያቀፈ አንድ ቡድን የመጨረሻው ማኅተም እስኪደረግበት ድረስ አውዳሚ የሆኑትን ነፋሳት አግደው እንዲይዙ ተነገራቸው። (ራእይ 7:1-3) ይህ ቡድን ከኢየሱስ ጋር በሰማይ የሚገዙትን 144,000 የአምላክ አገልጋዮች ያቀፈ ነው። (ሉቃስ 12:32፤ ራእይ 7:4) ቀጥሎም ዮሐንስ ስለ አንድ ሌላ ቡድን ተናገረ፤ በዚህ ቡድን ውስጥ ያሉት ሰዎች ብዛት ፈጽሞ ያልጠበቀው ስለሆነ ሳይሆን አይቀርም “እነሆ” የሚለውን አግራሞትን የሚያሳይ አገላለጽ ተጠቅሟል። ዮሐንስ የተመለከተው ምንድን ነው? “ከሁሉም ብሔራት፣ ነገዶች፣ ሕዝቦችና ቋንቋዎች የተውጣጡ አንድም ሰው ሊቆጥራቸው የማይችል እጅግ ብዙ ሕዝብ ነጭ ልብስ ለብሰው በዙፋኑና በበጉ ፊት ቆመው ነበር።” (ራእይ 7:9-14) ወደፊት ከእውነተኛው አምልኮ ጎን የሚሰለፉ እልፍ አእላፍ ሰዎች እንደሚኖሩ ሲያውቅ ዮሐንስ ምን ያህል ተደስቶ እንደሚሆን እስቲ አስቡት! ይህ ራእይ የዮሐንስን እምነት አጠናክሮለት እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። ራእዩ ፍጻሜውን እያገኘ ባለበት በዛሬው ጊዜ ለምንኖረው ለእኛ ደግሞ ይበልጥ እምነታችንን እንደሚያጠናክርልን ግልጽ ነው! ከታላቁ መከራ በሕይወት ተርፈው በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸው በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲሰበሰቡ በገዛ ዓይናችን የመመልከት አጋጣሚ አግኝተናል። w19.09 26 አን. 2-3
ሰኞ፣ ኅዳር 15
ያልታሰበ ጥፋት ድንገት ይመጣባቸዋል፤ ደግሞም በምንም ዓይነት አያመልጡም።—1 ተሰ. 5:3
መንግሥታት አስቀድሞ በትንቢት የተነገረውን “ሰላምና ደህንነት ሆነ!” የሚለውን አዋጅ ሲያውጁ የሚኖረውን ሁኔታ ለማሰብ እንሞክር። በዓለም ላይ ታይቶ የማይታወቅ ሰላም እንደሰፈነ በመግለጽ ይፎክሩ ይሆናል። መንግሥታት በዓለም ላይ ያሉትን ሁኔታዎች በቁጥጥራቸው ሥር ማድረግ እንደቻሉ ሊያሳምኑን ይሞክራሉ። ይሁን እንጂ ከዚያ በኋላ የሚፈጸሙት ነገሮች ጨርሶ ከቁጥጥራቸው ውጭ ናቸው። “ታላቂቱ ባቢሎን” ትጠፋለች! (ራእይ 17:5, 15-18) ‘አምላክ ሐሳቡን ዳር እንዲያደርሱ በልባቸው ያኖረዋል።’ ይህ ሐሳብ ምንድን ነው? ሕዝበ ክርስትናን ጨምሮ በዓለም ላይ ያሉ የሐሰት ሃይማኖቶችን በሙሉ ማጥፋት ነው። አምላክ ይህን ሐሳብ ‘በደማቁ ቀይ አውሬ አሥር ቀንዶች’ ልብ ውስጥ ያኖረዋል። አሥሩ ቀንዶች፣ ‘አውሬውን’ ይኸውም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን የሚደግፉትን የፖለቲካ ኃይሎች በሙሉ ያመለክታሉ። (ራእይ 17:3, 11-13፤ 18:8) እነዚህ የፖለቲካ ኃይሎች በሐሰት ሃይማኖት ላይ ጥቃት መሰንዘራቸው ታላቁ መከራ መጀመሩን የሚጠቁም ምልክት ይሆናል። ይህም በዓለም ላይ ያሉ ሰዎችን ሁሉ የሚነካ ድንገተኛና አስደንጋጭ ክንውን ይሆናል። w19.10 14 አን. 1, 3
ማክሰኞ፣ ኅዳር 16
በመካከላቸው የመሪነት ቦታ መያዝ የሚፈልገው ዲዮጥራጢስ ከእኛ በአክብሮት የሚቀበለው ምንም ነገር የለም።—3 ዮሐ. 9
በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖረው ዲዮጥራጢስ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ አመራር የሚሰጡ ወንድሞችን ይመቀኝ ነበር። በጉባኤው ውስጥ “የመሪነት ቦታ መያዝ” ይፈልግ ነበር፤ በመሆኑም ስለ ሐዋርያው ዮሐንስና በኃላፊነት ቦታ ላይ ስለሚያገለግሉ ሌሎች ወንድሞች መጥፎ ወሬ በማናፈስ ጉባኤው ለእነሱ ያለውን አክብሮት እንዲያጣ ለማድረግ ሞክሯል። (3 ዮሐ. 10) እንደ ዲዮጥራጢስ ዓይነት እርምጃ ባንወስድም እንኳ የምንጓጓለትን ቲኦክራሲያዊ ኃላፊነት ያገኘን አንድ ክርስቲያን መመቅኘት ልንጀምር እንችላለን፤ በተለይ ደግሞ ይህን ኃላፊነት ለመቀበል የእሱን ያህል ብቁ እንደሆንን ከተሰማን ይህ ዝንባሌ ሊታገለን ይችላል። ምቀኝነት እንደ መርዛማ አረም ነው። በልባችን ውስጥ አንዴ ሥር መስደድ ከጀመረ ነቅለን ማውጣት ከባድ ነው። እንደ ቅናት፣ ኩራትና ራስ ወዳድነት ያሉት መጥፎ ባሕርያት ምቀኝነት ይበልጥ ሥር እየሰደደ እንዲሄድ ሊያደርጉ ይችላሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ምቀኝነት እንደ ፍቅር፣ ርኅራኄና ደግነት ያሉትን ግሩም ባሕርያት አንቆ ሊያስቀራቸው ይችላል። ምቀኝነት በልባችን ውስጥ ማቆጥቆጥ እንደጀመረ ካስተዋልን ወዲያውኑ ነቅለን ልናወጣው ይገባል። w20.02 15 አን. 6-7
ረቡዕ፣ ኅዳር 17
ሥጋዬን የሚወጋ እሾህ ተሰጠኝ።—2 ቆሮ. 12:7
ሐዋርያው ጳውሎስ በጣም የሚያሠቃይ አንድ ዓይነት ችግር እንዳጋጠመው መግለጹ ነበር። ጳውሎስ ይህን ችግር “ዘወትር የሚያሠቃየኝ [“የሚመታኝ፣” ግርጌ] የሰይጣን መልአክ” በማለት ጠርቶታል። ጳውሎስ ላይ እሾሁን የሰኩበት ይኸውም ላጋጠመው ችግር መንስኤ የሆኑት ሰይጣን ወይም አጋንንቱ ላይሆኑ ይችላሉ። ሆኖም እነዚህ ክፉ መናፍስት ጳውሎስ የገጠመውን ችግር ወይም “እሾህ” ሲመለከቱ እሾሁ ወደ ሰውነቱ ጠልቆ እንዲገባ ለማድረግ በሌላ አባባል ሥቃዩን ለማባባስ ሞክረው ሊሆን ይችላል። ታዲያ ጳውሎስ ምን አደረገ? መጀመሪያ ላይ ጳውሎስ ‘እሾሁ’ እንዲወገድለት ፈልጎ ነበር። “ይህ ነገር ከእኔ እንዲርቅ [ይሖዋን] ሦስት ጊዜ ለመንኩት” ብሏል። ጳውሎስ እንዲህ ያለ ጸሎት ቢያቀርብም ሥጋውን የሚወጋው እሾህ አልተወገደም። ታዲያ ይሖዋ የጳውሎስን ጸሎት አልመለሰለትም ማለት ነው? በፍጹም። ጸሎቱን መልሶለታል። ይሖዋ ችግሩን ከማስወገድ ይልቅ ችግሩን ለመቋቋም የሚያስችል ጥንካሬ ለጳውሎስ ሰጥቶታል። ይሖዋ “ኃይሌ ፍጹም የሚሆነው በምትደክምበት ጊዜ ነው” ብሎታል። (2 ቆሮ. 12:8, 9) ደግሞም ጳውሎስ በአምላክ እርዳታ ደስታውንና ውስጣዊ ሰላሙን ጠብቆ መኖር ችሏል።—ፊልጵ. 4:4-7፤ w19.11 9 አን. 4-5
ሐሙስ፣ ኅዳር 18
ይሖዋ እሱ ብቻ እንዲመለክ የሚፈልግ . . . አምላክ ነው።—ናሆም 1:2
ይሖዋ ፈጣሪያችንና ሕይወት ሰጪያችን በመሆኑ ልናመልክ የሚገባው እሱን ብቻ ነው። (ራእይ 4:11) ይሁንና ይህን ማድረግ ተፈታታኝ ሊሆን ይችላል። ለይሖዋ ፍቅርና አክብሮት ቢኖረንም እንኳ ለእሱ ብቻ የሚገባውን አምልኮ እንዳናቀርብ እንቅፋት የሚሆኑብን ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ፣ ይሖዋን ብቻ ማምለክ ለእሱ ጥልቅ ፍቅር ከማዳበር ጋር ተያይዞ ተገልጿል። በመሆኑም ይሖዋ በልባችን ውስጥ ሊኖረው የሚገባውን ቦታ፣ ማንኛውም አካል ወይም ነገር እንዲይዝ አንፈቅድም። (ዘፀ. 34:14) ይሖዋን የምንወደው እንዲያው በጭፍን አይደለም። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ይሖዋን የወደድነው ስለ እሱ ባወቅናቸው ነገሮች ላይ ተመሥርተን ነው። ግሩም ለሆኑት የይሖዋ ባሕርያት አድናቆት አዳብረናል። እሱ የሚወዳቸውንና የሚጠላቸውን ነገሮች አውቀናል፤ እኛም የእሱ ዓይነት አመለካከት አለን። ለሰው ልጆች ያለውን ዓላማ የተረዳን ከመሆኑም ሌላ ዓላማውን እንደግፋለን። ይሖዋ ወዳጆቹ የመሆን አጋጣሚ ስለከፈተልን እንዳከበረን ይሰማናል። (መዝ. 25:14) ስለ ፈጣሪያችን የምንማረው እያንዳንዱ ነገር ወደ እሱ ይበልጥ እንድንቀርብ ያነሳሳናል።—ያዕ. 4:8፤ w19.10 26 አን. 1-3
ዓርብ፣ ኅዳር 19
እውነተኛ ወዳጅ ምንጊዜም አፍቃሪ ነው፤ ደግሞም ለመከራ ቀን የተወለደ ወንድም ነው።—ምሳሌ 17:17
በዛሬው ጊዜ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የተለያዩ ችግሮች ያጋጥሟቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ብዙዎች በተፈጥሮ ወይም በሰው ሠራሽ አደጋዎች የተነሳ ችግር ደርሶባቸዋል። እንዲህ ያሉ አደጋዎች በሚከሰቱበት ወቅት አንዳንዶቻችን እነዚህን ወንድሞቻችንን ቤታችን ማሳረፍ እንችል ይሆናል። ሌሎች ደግሞ የገንዘብ ድጋፍ ያደርጉ ይሆናል። ሁላችንም ልናደርገው የምንችለው ሌላ ነገር ደግሞ ይሖዋ፣ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን እንዲረዳቸው መጠየቅ ነው። በሌላ በኩል አንድ ወንድማችን ወይም አንዲት እህታችን ተስፋ እንደቆረጡ አስተውለን ይሆናል፤ ይሁንና ምን ማለት ወይም ምን ማድረግ እንዳለብን ግራ ይገባን ይሆናል። ሆኖም ሁላችንም እርዳታ ማበርከት የምንችልባቸው የተለያዩ መንገዶች አሉ። ለምሳሌ ችግር ከገጠመው ወንድማችን ጋር ጊዜ ማሳለፍ እንችላለን። ወንድማችን ሲናገር አሳቢነት በሚንጸባረቅበት መንገድ ማዳመጥ እንችላለን። የምንወደውን የሚያጽናና ጥቅስ ልንነግረውም እንችላለን። (ኢሳ. 50:4) ዋናው ነገር ወዳጆቻችን የእኛ እርዳታ በሚያስፈልጋቸው ወቅት ከጎናቸው መሆናችን ነው። ከወንድሞቻችን እና ከእህቶቻችን ጋር ከአሁኑ ጠንካራ ወዳጅነት መመሥረታችንና ወዳጅነታችንን ጠብቀን ለማቆየት ጥረት ማድረጋችን በጣም አስፈላጊ ነው። ወዳጅነታችን እስከዚህ ሥርዓት ፍጻሜ ብቻ ሳይሆን ለዘላለም ይዘልቃል! w19.11 7 አን. 18-19
ቅዳሜ፣ ኅዳር 20
አንድ ሰው ለይሖዋ የሚያቀርበውን የኅብረት መሥዋዕት በተመለከተ . . . ሕጉ ይህ ነው።—ዘሌ. 7:11
የኅብረት መሥዋዕት፣ አንድ ሰው ለአምላኩ ለይሖዋ ባለው ፍቅር ተነሳስቶ በፈቃደኝነት የሚያቀርበው መባ ነው። መባውን የሚያቀርበው ሰው፣ ቤተሰቡ እንዲሁም ካህናቱ መሥዋዕት ሆኖ የቀረበውን እንስሳ ሥጋ ይበሉ ነበር። ሆኖም የእንስሳው የተወሰኑ ክፍሎች ለይሖዋ ብቻ መቅረብ ነበረባቸው። እነዚህ የትኞቹ ክፍሎች ናቸው? ይሖዋ ስቡን ከእንስሳው የሰውነት ክፍሎች ሁሉ ምርጡ እንደሆነ አድርጎ ይቆጥረው ነበር። በተጨማሪም ኩላሊቶቹን ጨምሮ አንዳንድ የሰውነቱ ክፍሎች ልዩ ቦታ እንደሚሰጣቸው ገልጾ ነበር። (ዘሌ. 3:6, 12, 14-16) በመሆኑም አንድ እስራኤላዊ እነዚህን የእንስሳው ክፍሎችና ስቡን መሥዋዕት አድርጎ ሲያቀርብ ይሖዋ በጣም ይደሰት ነበር። እንዲህ ያለውን መባ የሚያቀርብ እስራኤላዊ ለአምላክ ምርጡን የመስጠት ልባዊ ፍላጎት እንዳለው ያሳያል። በተመሳሳይም ኢየሱስ ለይሖዋ ባለው ፍቅር ተነሳስቶ እሱን በሙሉ ነፍሱ በማገልገል በፈቃደኝነት ለይሖዋ ምርጡን ሰጥቷል። (ዮሐ. 14:31) ኢየሱስ የአምላክን ፈቃድ ማድረግ ያስደስተው ነበር። (መዝ. 40:8) ይሖዋ፣ ኢየሱስ በፈቃደኝነት እንደሚያገለግለው ሲመለከት ምንኛ ተደስቶ ይሆን! w19.11 22-23 አን. 9-10
እሁድ፣ ኅዳር 21
ሰባተኛው ቀን . . . ሙሉ በሙሉ የሚታረፍበት ሰንበት ነው። ለይሖዋ የተቀደሰ ነው።—ዘፀ. 31:15
ይሖዋ ከስድስት የፍጥረት ቀናት በኋላ፣ በምድር ላይ ከሚያከናውነው የፍጥረት ሥራ አረፍ እንዳለ የአምላክ ቃል ይናገራል። (ዘፍ. 2:2) ይሁንና ይሖዋ ሥራ ስለሚወድ ከሌሎች ነገሮች ጋር በተያያዘ ‘እስካሁንም እየሠራ ነው።’ (ዮሐ. 5:17) በዘፍጥረት መጽሐፍ ላይ እንደተገለጸው ይሖዋ ስድስት ቀን ሠርቶ በሰባተኛው ቀን አርፏል፤ ሳምንታዊው የሰንበት ዝግጅትም ይህን አካሄድ የሚከተል ነው። አምላክ፣ ሰንበት በእሱና በእስራኤላውያን መካከል ያለ ምልክት እንደሆነ ተናግሯል። (ዘፀ. 31:12-14) በዚህ ዕለት ልጆችንና ባሪያዎችን ጨምሮ ማንኛውም ሰው ሥራ እንዳይሠራ ሕጉ ያዝዝ ነበር፤ ሌላው ቀርቶ የቤት እንስሳት እንኳ ሥራ መሥራት አልነበረባቸውም። (ዘፀ. 20:10) ይህ ዝግጅት እስራኤላውያን ለመንፈሳዊ ጉዳዮች ይበልጥ ትኩረት እንዲሰጡ ያስችላቸው ነበር። በኢየሱስ ዘመን የነበሩ በርካታ የሃይማኖት መሪዎች ይህ ዝግጅት ከልክ በላይ ጥብቅ እና ጫና የሚፈጥር እንዲሆን አድርገው ነበር። በሰንበት ቀን እሸት መቅጠፍ ወይም የታመመን ሰው መፈወስ እንኳ ሕጉን መጣስ እንደሆነ ይናገሩ ነበር። (ማር. 2:23-27፤ 3:2-5) እንዲህ ያለው አመለካከት የአምላክን አስተሳሰብ አያንጸባርቅም፤ ኢየሱስም ለአድማጮቹ ይህን ግልጽ አድርጎላቸዋል። w19.12 3-4 አን. 8-9
ሰኞ፣ ኅዳር 22
የተወደዳችሁ ልጆቹ በመሆን አምላክን የምትመስሉ ሁኑ።—ኤፌ. 5:1
ስለ ይሖዋ ባሕርያት ይበልጥ ባወቅን መጠን እሱን ይበልጥ እየመሰልን እንሄዳለን። ዳዊት የሰማይ አባቱን በደንብ ያውቀው ስለነበር ከሌሎች ጋር ባለው ግንኙነት ይሖዋን መምሰል ችሏል። ዳዊት ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ዝምድና ስለነበረው በእስራኤል ውስጥ በጣም ተወዳጅ ንጉሥ ለመሆን በቅቷል፤ ይሖዋም ሌሎች የእስራኤል ነገሥታትን የሚመዝነው ከእሱ አንጻር ነበር። (1 ነገ. 15:11፤ 2 ነገ. 14:1-3) ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? ‘አምላክን መምሰል’ አለብን። የአምላክን ባሕርያት ለመምሰል የምንጥር ከሆነ የእሱ ልጆች መሆናችንን እናረጋግጣለን። (ኤፌ. 4:24) ስለ ይሖዋ መማራችንን መቼም ቢሆን አናቆምም። (መክ. 3:11) ዋናው ነገር ‘ስለ ይሖዋ ምን ያህል እናውቃለን?’ የሚለው ሳይሆን ‘ባወቅነው ነገር ምን እናደርጋለን?’ የሚለው ነው። የተማርነውን በተግባር የምናውልና አፍቃሪ አባታችንን ለመምሰል ጥረት የምናደርግ ከሆነ እሱም ወደ እኛ ይበልጥ ይቀርባል። (ያዕ. 4:8) ይሖዋ፣ እሱን የሚሹትን ሰዎች ፈጽሞ እንደማይተው በቃሉ አማካኝነት አረጋግጦልናል። w19.12 20 አን. 20፤ 21 አን. 21, 23
ማክሰኞ፣ ኅዳር 23
ልብ ከምንም ነገር በላይ ከዳተኛ ነው።—ኤር. 17:9
ያዕቆብ ሁሉንም ልጆቹን ይወዳቸው የነበረ ቢሆንም ለ17 ዓመቱ ዮሴፍ ለየት ያለ ፍቅር ነበረው። ታዲያ የዮሴፍ ወንድሞች ይህን ሲያዩ ምን ተሰማቸው? ዮሴፍን የተመቀኙት ሲሆን ይህ ደግሞ እንዲጠሉት አደረጋቸው። ዮሴፍን ለባርነት የሸጡት ከመሆኑም ሌላ ለአባታቸው የሚወደውን ልጁን አውሬ በልቶት እንደሞተ በመናገር ዋሹት። ምቀኛ መሆናቸው የቤተሰባቸው ሰላም እንዲደፈርስና የአባታቸው ልብ በሐዘን እንዲሰበር አድርጓል። (ዘፍ. 37:3, 4, 27-34) ምቀኝነት አንድ ሰው የአምላክን መንግሥት እንዳይወርስ ከሚያግዱና ወደ ሞት ከሚመሩ “የሥጋ ሥራዎች” መካከል ተጠቅሷል። (ገላ. 5:19-21) እንደ ጥላቻ፣ ጠብና በቁጣ መገንፈል ላሉት ጎጂ ባሕርያት ብዙውን ጊዜ መንስኤ የሚሆነው ምቀኝነት ነው። የዮሴፍ ወንድሞች ታሪክ እንደሚያሳየው ምቀኝነት ግንኙነትን የሚያሻክር ከመሆኑም ሌላ በቤተሰብ ውስጥ ያለውን ሰላም ያደፈርሳል። ማናችንም ብንሆን የዮሴፍ ወንድሞች ያደረጉትን ነገር አናደርግ ይሆናል፤ ያም ቢሆን የሁላችንም ልብ ኃጢአተኛና ከዳተኛ ነው። በመሆኑም አንዳንድ ጊዜ ከምቀኝነት ዝንባሌ ጋር መታገል ቢያስፈልገን የሚያስገርም አይሆንም። w20.02 14 አን. 1-3
ረቡዕ፣ ኅዳር 24
ሌሎች ከእናንተ እንደሚበልጡ በትሕትና አስቡ።—ፊልጵ. 2:3
በአንድ ወቅት ይሖዋ ለሙሴ ከሰጠው መንፈስ ቅዱስ ወስዶ በመገናኛው ድንኳን አጠገብ ለቆሙት እስራኤላውያን ሽማግሌዎች ሰጥቷቸው ነበር። ብዙም ሳይቆይ ሙሴ፣ ወደ መገናኛው ድንኳን ያልመጡ ሁለት ሽማግሌዎችም መንፈስ ቅዱስን እንደተቀበሉና እንደ ነቢያት እንደሆኑ ሰማ። ታዲያ እነዚህን ሁለት ሽማግሌዎች እንዲከለክላቸው ኢያሱ ሲጠይቀው ሙሴ ምን አደረገ? ሙሴ፣ ይሖዋ ለእነዚህ ሁለት ሰዎች ባደረገው ነገር አልተመቀኘም። ከዚህ ይልቅ እንዲህ ያለ መብት በማግኘታቸው አብሯቸው በመደሰት ትሕትና አሳይቷል። (ዘኁ. 11:24-29) ከሙሴ ምን ትምህርት እናገኛለን? የጉባኤ ሽማግሌ ከሆንክ በኃላፊነት የተሰጠህንና በጣም የምትወደውን አንድ የጉባኤ ኃላፊነት ሌላ ሰው እንዲያከናውነው እንድታሠለጥን ተጠይቀህ ታውቃለህ? እንደ ሙሴ ትሑት ከሆንክ በጊዜ ሂደት ይህን ኃላፊነት መረከብ እንዲችል አንድን ወንድም እንድታሠለጥን ብትጠየቅ ቦታዬን አጣለሁ የሚል ስጋት አያድርብህም። እንዲያውም ወንድምህን በደስታ ትረዳዋለህ። w20.02 15 አን. 9፤ 17 አን. 10-11
ሐሙስ፣ ኅዳር 25
በሰው ልብ ውስጥ ያለ ጭንቀት ልቡ እንዲዝል ያደርገዋል፤ መልካም ቃል ግን ደስ ያሰኘዋል።—ምሳሌ 12:25
ሕመም፣ ስሜታችንን ሊጎዳው ይችላል። ሰዎች አቅማችን ውስን መሆኑን መመልከታቸው አሊያም የሌሎች እርዳታ የሚያስፈልገን መሆኑ ያሸማቅቀን ይሆናል። ሌሎች ስለ ሕመማችን ባያውቁ እንኳ የቀድሟችንን ያህል ማድረግ እንደማንችል ማወቃችን ስለ ራሳችን መጥፎ እንዲሰማን ሊያደርግ ይችላል። እንዲህ ባለው አስጨናቂ ጊዜ ይሖዋ መንፈሳችንን ያነቃቃዋል። እንዴት? ይሖዋ ብንታመምም እንኳ በእሱ ፊት ውድ እንደሆንን የሚያስታውሱን በርካታ መልካም ቃሎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲሰፍሩልን አድርጓል። (መዝ. 31:19፤ 41:3) በመንፈስ መሪነት በተጻፉት በእነዚህ ሐሳቦች አማካኝነት ይሖዋ በሕመማችን ምክንያት የሚሰማንን አሉታዊ ስሜት እንድናሸንፍ ይረዳናል። ይሖዋ ያለህበትን ሁኔታ እንደሚያውቅ አትጠራጠር። ስለ ሁኔታው ትክክለኛ አመለካከት ለማዳበር እንዲረዳህ ይሖዋን ለምነው። ከዚያም በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያስቀመጠልህን መልካም ቃላት ለማግኘት ጥረት አድርግ። ይሖዋ አገልጋዮቹን ምን ያህል ውድ አድርጎ እንደሚመለከታቸው በሚገልጹ ጥቅሶች ላይ ትኩረት አድርግ። ይህን ስታደርግ ይሖዋ በታማኝነት ለሚያገለግሉት ሁሉ መልካም እንደሆነ ማስተዋልህ አይቀርም።—መዝ. 84:11፤ w20.01 15-16 አን. 9-10፤ 17 አን. 12
ዓርብ፣ ኅዳር 26
መጥፎ የሆነውን አትከተል፤ ይልቁንም ጥሩ የሆነውን ተከተል።—3 ዮሐ. 11
ይስሐቅ ሀብታም ሰው በመሆኑ ፍልስጤማውያን ተመቅኝተውት ነበር። (ዘፍ. 26:12-14) በዚህም የተነሳ የይስሐቅ መንጎች የሚጠጡባቸውን የውኃ ጉድጓዶች ደፈኗቸው። (ዘፍ. 26:15, 16, 27) እንደ እነዚያ ፍልስጤማውያን ሁሉ በዛሬው ጊዜ ያሉ አንዳንድ ሰዎችም ከእነሱ የበለጠ ቁሳዊ ሀብት ያላቸውን ሰዎች ይመቀኛሉ። የሰዎቹን ሀብት ከመመኘትም አልፈው እነዚያ ሰዎች ሀብታቸውን ቢያጡ ደስ ይላቸዋል። ኢየሱስ በተራው ሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነት ስለነበረው የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ተመቅኝተውታል። (ማቴ. 7:28, 29) ኢየሱስ የአምላክ ወኪል ከመሆኑም ሌላ እውነትን ያስተምር ነበር። ያም ቢሆን እነዚህ የሃይማኖት መሪዎች ስለ እሱ ውሸት በማሰራጨት ስሙን ለማጥፋት ጥረት አድርገዋል። (ማር. 15:10፤ ዮሐ. 11:47, 48፤ 12:12, 13, 19) ከዚህ ዘገባ ምን የማስጠንቀቂያ ትምህርት እናገኛለን? ባሏቸው መልካም ባሕርያት የተነሳ በጉባኤው ውስጥ ተወዳጅነት ያተረፉ ክርስቲያኖችን የመመቅኘት ዝንባሌ ጨርሶ በውስጣችን እንዳያድር መታገል ይኖርብናል። ከዚህ ይልቅ የእነሱን ጥሩ ምሳሌ ለመከተል ጥረት ማድረግ አለብን።—1 ቆሮ. 11:1፤ w20.02 15 አን. 4-5
ቅዳሜ፣ ኅዳር 27
እንዲህ ያደረገ ሰው ይገደላል።—አስ. 4:11
የዛሬ 2,500 ዓመት ገደማ በፋርስ ግዛት ውስጥ እየኖርክ ነው እንበል። ንጉሡን ማነጋገር ፈልገሃል። ሆኖም የንጉሡን ፈቃድ ሳታገኝ እሱ ፊት መቅረብ ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር ነው። እንዲህ ለማድረግ መድፈር ሕይወትህን ሊያሳጣህ ይችላል! ይሖዋ እንደዚያ የፋርስ ንጉሥ ባለመሆኑ ምንኛ አመስጋኞች ነን! በማንኛውም ጊዜ እኛን ለማዳመጥ ፈቃደኛ ነው። በነፃነት እንድንቀርበው ይፈልጋል። ይሖዋ ታላቅ ፈጣሪ፣ ሁሉን ቻይ እና ሉዓላዊ ጌታ እንደሚሉት ባሉ የላቀ ሥልጣኑን የሚያሳዩ የማዕረግ ስሞች ይጠራል፤ ያም ቢሆን ወደ እሱ ስንጸልይ “አባታችን” በሚለው ቀረቤታን የሚያሳይ ቃል እንድንጠቀም ጋብዞናል። (ማቴ. 6:9) ይሖዋ በዚህ ደረጃ እንድንቀርበው የሚፈልግ መሆኑ ምንኛ የሚያስደስት ነው! ይሖዋ የሕይወታችን ምንጭ ከመሆኑ አንጻር እሱን “አባታችን” ብለን መጥራታችን የተገባ ነው። (መዝ. 36:9) ይሖዋ፣ አባታችን ስለሆነ እሱን መታዘዝ ይኖርብናል። እሱ ያዘዘንን ስናደርግ አስደናቂ በረከቶችን እናገኛለን። (ዕብ. 12:9) ከእነዚህ በረከቶች አንዱ በሰማይ ወይም በምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ማግኘት ነው። w20.02 2 አን. 1-3
እሁድ፣ ኅዳር 28
ደቀ መዛሙርት አድርጉ።—ማቴ. 28:19
ግባችን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርግ መርዳት ነው። (ኤፌ. 4:13) አንድ ሰው ከእኛ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ሲስማማ በዋነኝነት የሚያሳስበው ከጥናቱ የሚያገኘው ጥቅም ሊሆን ይችላል። ለይሖዋ ያለው ፍቅር እያደገ ሲሄድ ግን የጉባኤውን አባላት ጨምሮ ሌሎች ሰዎችን መርዳት ስለሚችልበት መንገድ ማሰብ መጀመሩ አይቀርም። (ማቴ. 22:37-39) የመንግሥቱን ሥራ በገንዘብ የመደገፍ መብት እንዳለው ለጥናትህ ማሳወቁ ተገቢ እንደሆነ በሚሰማህ ጊዜ ላይ ይህን ከማድረግ ወደኋላ አትበል። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትህን ችግሮች በሚያጋጥሙት ጊዜ ምን ማድረግ እንደሚችል አሠልጥነው። አንድ ምሳሌ እንውሰድ፤ ያልተጠመቀ አስፋፊ የሆነ ጥናትህ በጉባኤ ውስጥ ያለ አንድ ሰው ቅር እንዳሰኘው ነገረህ እንበል። ከአንደኛው ወገን ከመቆም ይልቅ ጥናትህ ሊወስድ ስለሚችለው እርምጃ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጣቸውን አማራጮች ለምን አታሳየውም? ጥናትህ ቅር ያሰኘውን ወንድም በይቅርታ ማለፍ ይችል ይሆናል፤ ይህን ማድረግ ከከበደው ደግሞ ‘ወንድሙን የማትረፍ’ ግብ ይዞ በደግነትና በፍቅር ሊያነጋግረው ይችላል። (ከማቴዎስ 18:15 ጋር አወዳድር።) ጥናትህ ወንድምን ምን ብሎ እንደሚያነጋግረው እንዲዘጋጅ እርዳው። w20.01 5-6 አን. 14-15
ሰኞ፣ ኅዳር 29
ኃጢአቴን ለአንተ ተናዘዝኩ፤ ስህተቴን አልሸፋፈንኩም። . . . አንተም ስህተቴንና ኃጢአቴን ይቅር አልክ።—መዝ. 32:5
ይሖዋ ይቅር እንዲለን በመጸለይ፣ ተግሣጽን በመቀበልና ስህተታችንን ላለመድገም ጥረት በማድረግ የይሖዋን ምሕረት እንደምናደንቅ ማሳየት እንችላለን። እነዚህን እርምጃዎች ከወሰድን ውስጣዊ ሰላማችን ይመለስልናል። ‘ይሖዋ ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ እንደሆነና መንፈሳቸው የተደቆሰባቸውን እንደሚያድን’ ማወቃችን ምንኛ የሚያጽናና ነው። (መዝ. 34:18) እነዚህ የመጨረሻ ቀናት ወደ ማብቂያቸው እየተቃረቡ ሲሄዱ፣ ለጭንቀት መንስኤ የሚሆኑ ነገሮች መጨመራቸው አይቀርም። የሚያስጨንቁ ሐሳቦች ሲመጡብህ ወዲያውኑ የይሖዋን እርዳታ ጠይቅ። መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት አጥና። ሐና፣ ሐዋርያው ጳውሎስና ንጉሥ ዳዊት ከተዉት ምሳሌ ትምህርት ውሰድ። የጭንቀትህን መንስኤ ለማወቅ እንዲረዳህ የሰማዩ አባትህን ጠይቀው። (መዝ. 139:23) በተለይ ከቁጥጥርህ ውጭ የሆነ ሁኔታ ሲያጋጥምህ ሸክምህን በእሱ ላይ ጣለው። እንዲህ ካደረግህ እንደሚከተለው በማለት እንደዘመረው መዝሙራዊ ይሰማሃል፦ “በጭንቀት በተዋጥኩ ጊዜ፣ አጽናናኸኝ፤ ደግሞም አረጋጋኸኝ።”—መዝ. 94:19፤ w20.02 24 አን. 17፤ 25 አን. 20-21
ማክሰኞ፣ ኅዳር 30
ቅዱሳን መጻሕፍት ሁሉ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፉ ናቸው።—2 ጢሞ. 3:16
“በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፉ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል በቀጥታ ሲተረጎም “አምላክ የተነፈሰበት” የሚል ፍቺ አለው። አምላክ ሐሳቡን ለመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች “ለመተንፈስ” ማለትም ሐሳቡን ለማስተላለፍ በቅዱስ መንፈሱ ተጠቅሟል። መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብና ባነበብነው ነገር ላይ ስናሰላስል የአምላክ ትምህርቶች ወደ አእምሯችንና ልባችን ጠልቀው ይገባሉ። በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፉት እነዚህ ትምህርቶች ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ ሕይወታችንን ለመምራት ያነሳሱናል። (ዕብ. 4:12) ከመንፈስ ቅዱስ የተሟላ ጥቅም ለማግኘት ግን መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረን የምናነብበትና ባነበብነው ነገር ላይ የምናሰላስልበት ጊዜ መመደብ ያስፈልገናል። የአምላክ ቃል በአነጋገራችንና በድርጊታችን ላይ ተጽዕኖ ማሳደር የሚችለው እንዲህ ስናደርግ ነው። በተጨማሪም ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ሆነን ይሖዋን ማምለክ ይኖርብናል። (መዝ. 22:22) በስብሰባዎች ላይ የይሖዋ መንፈስ ይኖራል። (ራእይ 2:29) ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ለአምልኮ ስንሰበሰብ፣ መንፈስ ቅዱስን ለማግኘት እንጸልያለን፤ በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረቱትን የመንግሥቱን መዝሙሮች እንዘምራለን እንዲሁም በአምላክ ቅዱስ መንፈስ የተሾሙ ወንድሞች የሚያቀርቧቸውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርቶች እናዳምጣለን። ሆኖም ከመንፈስ ቅዱስ የተሟላ ጥቅም ማግኘት ከፈለግን በስብሰባዎች ላይ ተሳትፎ ለማድረግ ተዘጋጅተን መምጣት ይኖርብናል። w19.11 11 አን. 13-14