ጥቅምት
ዓርብ፣ ጥቅምት 1
በሙሉ ልባቸው ወደ እሱ ላዘነበሉት ሰዎች ብርታቱን ያሳይ ዘንድ የይሖዋ ዓይኖች በምድር ሁሉ ላይ ይመላለሳሉ።—2 ዜና 16:9
በዛሬው ጊዜ ይሖዋ ለሕዝቡ ጥበቃ እንደሚያደርግ የሚያሳዩ ብዙ ማስረጃዎች አሉ። እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት፦ በመላው ምድር ስለ እውነት እየሰበክንና እያስተማርን ነው። (ማቴ. 28:19, 20) በዚህ መንገድ የዲያብሎስን ክፉ ሥራዎች እናጋልጣለን። ሰይጣን ቢሳካለት ኖሮ፣ የምናደርገውን እንቅስቃሴ በሙሉ ሊያስቆመን እንደሚፈልግ ምንም ጥያቄ የለውም፤ ግን ይህን ማድረግ አይችልም። በመሆኑም ክፉ መናፍስትን ልንፈራቸው አይገባም። ለይሖዋ ታማኝ እስከሆንን ድረስ አጋንንት ዘላቂ የሆነ ጉዳት ሊያደርሱብን አይችሉም። ያም ቢሆን ሁላችንም ክፉ መናፍስትን መቃወምና በይሖዋ መታመን ይኖርብናል። ይህን ካደረግን ብዙ በረከቶችን እናጭዳለን፤ በሰይጣን ውሸቶችም አንታለልም። በተጨማሪም በአጋንንት ፍርሃት አንርድም። ከሁሉ በላይ ደግሞ ከይሖዋ ጋር ያለንን ወዳጅነት እናጠናክራለን። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ዲያብሎስን . . . ተቃወሙት፤ እሱም ከእናንተ ይሸሻል። ወደ አምላክ ቅረቡ፤ እሱም ወደ እናንተ ይቀርባል።”—ያዕ. 4:7, 8፤ w19.04 24 አን. 15፤ 25 አን. 18
ቅዳሜ፣ ጥቅምት 2
የማህፀንም ፍሬ ከእሱ የሚገኝ ስጦታ ነው።—መዝ. 127:3
ልጆቻችሁ ይሖዋ በአደራ የሰጣችሁ ስጦታ ወይም “ውርሻ” ናቸው። ይህን አደራ መጠበቅ የእናንተ ኃላፊነት ነው። ታዲያ ልጆቻችሁን ከጥቃት ለመጠበቅ ምን ማድረግ ትችላላችሁ? በመጀመሪያ፣ ስለ ፆታዊ ጥቃት በቂ እውቀት ይኑራችሁ። ልጆችን ስለሚያስነውሩ ሰዎችና እነዚህ ሰዎች ስለሚጠቀሙባቸው ዘዴዎች ለማወቅ ጥረት አድርጉ። ለጥቃት የሚያጋልጡ ሁኔታዎችን በንቃት ተከታተሉ። (ምሳሌ 22:3፤ 24:3) አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ ያለ ጥቃት የሚፈጽሙት፣ ልጆቹ የሚያውቋቸውና የሚያምኗቸው ሰዎች እንደሆኑ አስታውሱ። ሁለተኛ፣ ከልጆቻችሁ ጋር በነፃነት የመነጋገር ልማድ ይኑራችሁ። (ዘዳ. 6:6, 7፤ ያዕ. 1:19) አብዛኛውን ጊዜ ልጆች፣ ፆታዊ ጥቃት እንደተፈጸመባቸው መናገር ሊፈሩ እንደሚችሉ አስታውሱ። ይህን ጉዳይ ቢናገሩ ማንም ሰው እንደማያምናቸው ሊያስቡ ይችላሉ፤ አሊያም ደግሞ ጥቃት የፈጸመባቸው ግለሰብ ለማንም እንዳይናገሩ አስፈራርቷቸው ሊሆን ይችላል። ልጃችሁ የሆነ ችግር እንደደረሰበት ከጠረጠራችሁ ደግነት የሚንጸባረቅባቸው ጥያቄዎች በመጠየቅና የሚሰጠውን መልስ በትዕግሥት በማዳመጥ ያጋጠመውን ነገር እንዲናገር አበረታቱት። ሦስተኛ፣ ልጆቻችሁን አስተምሩ። አንድ ሰው ተገቢ ባልሆነ መንገድ ሊነካቸው ቢሞክር ምን ማለት ወይም ማድረግ እንዳለባቸው አስተምሯቸው። w19.05 13 አን. 19-22
እሁድ፣ ጥቅምት 3
ይሖዋ ኩሩ ልብ ያለውን ሁሉ ይጸየፋል።—ምሳሌ 16:5
ይሖዋ ኩሩ ሰዎችን የሚጸየፈው ለምንድን ነው? አንዱ ምክንያት ራሳቸውን የሚወዱና ለራሳቸው የተጋነነ አመለካከት ያላቸው ሰዎች የሰይጣንን የትዕቢት ዝንባሌ ስለሚያንጸባርቁ ነው። እስቲ አስቡት፦ ሰይጣን፣ አምላክ ሁሉንም ነገሮች ለመፍጠር የተጠቀመበት ኢየሱስ ተደፍቶ ሊሰግድለትና ሊያመልከው እንደሚገባ ተሰምቶት ነበር! (ማቴ. 4:8, 9፤ ቆላ. 1:15, 16) ለራሳቸው እንዲህ ያለ የተጋነነ አመለካከት ያላቸው ሁሉ የዚህ ዓለም ጥበብ በአምላክ ፊት ሞኝነት እንደሆነ የሚያሳዩ ሕያው ማስረጃዎች ናቸው። (1 ቆሮ. 3:19) በአንጻሩ ግን መጽሐፍ ቅዱስ ለራሳችን ሚዛናዊ አመለካከት እንድናዳብር ይረዳናል። በተወሰነ መጠን ራሳችንን መውደድ እንዳለብን ይናገራል። ኢየሱስ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” በማለት የተናገረው ሐሳብ ለራሳችን ፍላጎት መጠነኛ ትኩረት መስጠት እንዳለብን ይጠቁማል። (ማቴ. 19:19) ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ራሳችንን ከሌሎች አስበልጠን መመልከት እንዳለብን አይናገርም። ከዚህ ይልቅ እንዲህ ይላል፦ “ሌሎች ከእናንተ እንደሚበልጡ በትሕትና አስቡ እንጂ በጠበኝነት መንፈስ ወይም በትምክህተኝነት ምንም ነገር አታድርጉ።”—ፊልጵ. 2:3፤ ሮም 12:3፤ w19.05 24 አን. 13-14
ሰኞ፣ ጥቅምት 4
ይህ ሥርዓት እንዲቀርጻችሁ አትፍቀዱ፤ ከዚህ ይልቅ . . . አእምሯችሁን በማደስ ተለወጡ።—ሮም 12:2
መጽሐፍ ቅዱስን ስታጠና እና ይሖዋን ለማገልገል ስትወስን ምን ለውጦች ማድረግ አስፈልጎህ እንደነበረ እስቲ መለስ ብለህ አስብ። ብዙዎቻችን፣ እንፈጽማቸው የነበሩ መጥፎ ድርጊቶችን መተው አስፈልጎናል። (1 ቆሮ. 6:9-11) ይሖዋ እንዲህ ያሉ የኃጢአት ድርጊቶችን እንድንተው ስለረዳን አመስጋኞች ነን! ይሁንና እስካሁን ባደረግነው ለውጥ ረክተን መቀመጥ የለብንም። ከተጠመቅን በኋላ፣ ቀደም ሲል እንፈጽማቸው የነበሩ ከባድ ኃጢአቶችን አንፈጽም ይሆናል፤ ያም ቢሆን ወደ ቀድሞው አኗኗራችን እንድንመለስ ሊፈትኑን የሚችሉ ነገሮችን ለማስወገድ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ አለብን። ይህን ለማድረግ ሁለት እርምጃዎችን መውሰድ ያስፈልገናል። አንደኛ፣ ይህ ዓለም ‘እንዲቀርጸን መፍቀድ’ የለብንም። ሁለተኛ፣ አእምሯችንን በማደስ ‘መለወጥ’ ይኖርብናል። ይህ ለውጥ ላይ ላዩን የሚደረግ ለውጥን ብቻ አያመለክትም። ከዚህ ይልቅ ማንነታችንን ሙሉ በሙሉ የሚቀይር ለውጥን ያመለክታል። አእምሯችንን ይኸውም አመለካከታችንን፣ ስሜታችንን እና ውስጣዊ ዝንባሌያችንን ሙሉ በሙሉ መለወጥ ያስፈልገናል። w19.06 9 አን. 4-6
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 5
ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ረዳቴና አጽናኜ ነህ።—መዝ. 86:17
በምንጨነቅበት ጊዜ፣ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ በመገኘት ኃይላችንን ማደስ እንችላለን። በስብሰባዎች ላይ ስንገኝ ይሖዋ ለእኛ ‘ረዳትና አጽናኝ’ ለመሆን የሚያስችል ተጨማሪ አጋጣሚ ያገኛል። በስብሰባዎች ላይ በቅዱስ መንፈሱ፣ በቃሉ እንዲሁም በአገልጋዮቹ አማካኝነት ያበረታታናል። ስብሰባዎች “እርስ በርሳችን እንድንበረታታ” የሚያደርግ ጥሩ አጋጣሚ ይፈጥሩልናል። (ሮም 1:11, 12) ሶፊያ የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “መጽናት የቻልኩት በይሖዋና በወንድማማች ማኅበራችን እርዳታ ነው። ከሁሉ የበለጠ የጠቀሙኝ የጉባኤ ስብሰባዎቻችን ናቸው። በአገልግሎትና በጉባኤ የማደርገውን እንቅስቃሴ በጨመርኩ መጠን፣ አስጨናቂ ሁኔታዎችን ለመቋቋም ይበልጥ አቅም እንደማገኝ አስተውያለሁ።” የተስፋ መቁረጥ ስሜት በሚያድርብን ጊዜ፣ ይሖዋ ወደፊት ዘላቂ እፎይታ እንደሚሰጠን ብቻ ሳይሆን አሁንም ጭንቀትን ለመቋቋም እንደሚረዳን ልናስታውስ ይገባል። ይሖዋ የተስፋ መቁረጥ ስሜትን ለመቋቋም ‘ፍላጎቱም ሆነ ኃይሉ’ እንዲኖረን ያደርጋል።—ፊልጵ. 2:13፤ w19.06 19 አን. 17-18
ረቡዕ፣ ጥቅምት 6
ሂዱና ወደ ገሊላ እንዲሄዱ ለወንድሞቼ ንገሯቸው፤ እዚያም ያዩኛል።—ማቴ. 28:10
ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ያደረገው የመጀመሪያ ነገር ደቀ መዛሙርቱን ወደዚህ ስብሰባ መጥራት ነው፤ ይህን ያደረገው በዚህ ስብሰባ ላይ በጣም አስፈላጊ መመሪያዎችን ሊሰጣቸው አስቦ መሆን አለበት። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ስለሚያከናውኑት በጣም አስፈላጊ ሥራ በስብሰባው ላይ ነገራቸው፤ ይህ ሥራ በዛሬው ጊዜም እየተከናወነ ነው። ኢየሱስ እንዲህ ብሏቸዋል፦ “ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ፤ . . . ያዘዝኳችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው።” (ማቴ. 28:19, 20) ኢየሱስ ሁሉም ተከታዮቹ እንዲሰብኩ ይፈልጋል። ትእዛዙን የሰጠው ለ11 ታማኝ ሐዋርያቱ ብቻ አይደለም። ይህን እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው? ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ትእዛዝ በገሊላ በሚገኘው ተራራ ላይ በሰጠበት ወቅት በቦታው የነበሩት ሐዋርያት ብቻ ናቸው? መልአኩ ለሴቶቹ “እዚያም [በገሊላ] ታዩታላችሁ” እንዳላቸው እናስታውስ። ስለዚህ በስብሰባው ላይ ታማኝ ሴቶችም ተገኝተው መሆን አለበት። w20.01 2-3 አን. 1-4
ሐሙስ፣ ጥቅምት 7
እኔ ከዓለም መረጥኳችሁ እንጂ የዓለም ክፍል ስላልሆናችሁ ከዚህ የተነሳ ዓለም ይጠላችኋል።—ዮሐ. 15:19
ኢየሱስ ተቃውሞ እንደሚገጥመን ልንጠብቅ የሚገባው ለምን እንደሆነ ገልጿል። የምንጠላው የዓለም ክፍል ስላልሆንን እንደሆነ ተናግሯል። ስደት የይሖዋን በረከት እንዳጣን የሚጠቁም አይደለም። እንዲያውም ትክክለኛውን ነገር እያደረግን መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው! የሰው ልጆች፣ ሁሉን ቻይ አምላክ ለሆነው ለይሖዋ የምናቀርበውን አምልኮ ሊያስቆሙት አይችሉም። ብዙዎች ይህን ለማድረግ ቢሞክሩም አልተሳካላቸውም። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ምን እንደተከሰተ እንመልከት። በዚያ ወቅት የብዙ አገሮች መንግሥታት በአምላክ ሕዝቦች ላይ ከባድ ስደት ያደርሱ ነበር። የጀርመን የናዚ ፓርቲ ብቻ ሳይሆን የአውስትራሊያ፣ የካናዳና የሌሎች አገሮች መንግሥታትም የይሖዋ ምሥክሮችን ሥራ አግደው ነበር። ይሁንና ውጤቱ ምን ሆነ? በ1939 ጦርነቱ ሲጀምር በዓለም ዙሪያ 72,475 አስፋፊዎች ነበሩ። ይሁንና የይሖዋ በረከት ስላልተለያቸው በ1945 ጦርነቱ ሲያበቃ 156,299 አስፋፊዎች እንደነበሩ ሪፖርቶች አሳይተዋል። የአስፋፊዎቹ ቁጥር ከእጥፍ በላይ ጨምሮ ነበር! w19.07 9 አን. 4-5
ዓርብ፣ ጥቅምት 8
እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ።—ዮሐ. 13:35
በአሁኑ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ የምታስጠናው ሰው ባይኖርም እንኳ ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ አስተዋጽኦ ማበርከት የምትችልባቸው ሌሎች መንገዶች አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ አዲሶች ወደ ስብሰባ አዳራሹ ሲመጡ ሞቅ ያለ አቀባበል ልታደርግላቸውና ልትቀርባቸው ትችላለህ። በዚህ መንገድ፣ የእውነተኛ ክርስቲያኖች መለያ የሆነውን ፍቅር እንደምናሳይ እንዲያስተውሉ ልትረዳቸው ትችላለህ። በስብሰባዎች ላይ የምትሰጠው መልስ አጭር ቢሆንም እንኳ ከእኛ ጋር መሰብሰብ የጀመሩ አዲስ ሰዎች የሚያምኑበትን ነገር ከልብ በመነጨና አክብሮት በሚንጸባረቅበት መንገድ እንዴት መግለጽ እንደሚችሉ ያስተምራቸዋል። በተጨማሪም ከአዲስ አስፋፊ ጋር አብረህ አገልግሎት በመውጣት፣ ጥቅሶችን ተጠቅሞ ከሰዎች ጋር መወያየት የሚችለው እንዴት እንደሆነ ልታሳየው ትችላለህ። በዚህ መንገድ፣ ክርስቶስን እንዲመስል ታስተምረዋለህ። (ሉቃስ 10:25-28) በርካታ ክርስቲያኖች አስፈላጊ የሆኑ የተለያዩ ኃላፊነቶች ስላሉባቸው ጊዜያቸው የተጣበበ ነው። ያም ቢሆን ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ለማስጠናት የሚሆን ጊዜ አያጡም፤ ይህን በማድረጋቸውም ከፍተኛ ደስታ አግኝተዋል። w19.07 17 አን. 11, 13
ቅዳሜ፣ ጥቅምት 9
ከኋላዬ ያሉትን ነገሮች እየረሳሁ ከፊቴ ወዳሉት ነገሮች እንጠራራለሁ፤ . . . ግቡ ላይ ለመድረስ እየተጣጣርኩ ነው።—ፊልጵ. 3:13, 14
ሐዋርያው ጳውሎስ ቀደም ሲል ያገኘው ስኬትም ሆነ የሠራቸው ስህተቶች ትኩረቱን እንዲከፋፍሉበት አልፈቀደም። እንዲያውም ‘ከፊት ወዳሉት ነገሮች ለመንጠራራት’ ማለትም ሩጫውን በጽናት ለማጠናቀቅ ‘ከኋላ ያሉትን ነገሮች መርሳት’ እንደሚያስፈልግ ተናግሯል። የጳውሎስን ትኩረት ሊከፋፍሉበት ይችሉ የነበሩ አንዳንድ ነገሮች የትኞቹ ናቸው? በመጀመሪያ ደረጃ፣ ጳውሎስ ክርስቲያን ከመሆኑ በፊት በአይሁድ እምነት ውስጥ ትልቅ ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር። ያም ቢሆን ይህን ስኬቱን “እንደ ጉድፍ” እንደሚቆጥረው ተናግሯል። (ፊልጵ. 3:3-8) ሁለተኛ፣ ቀደም ሲል ክርስቲያኖችን በማሳደዱ የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማው ነበር፤ ይህ ግን ይሖዋን ከማገልገል እንዲያግደው አልፈቀደም። ሦስተኛ፣ በይሖዋ አገልግሎት ያከናወነው ነገር በቂ እንደሆነ በማሰብ ረክቶ አልተቀመጠም። ጳውሎስ ቢታሰርም፣ ቢደበደብም፣ በድንጋይ ቢወገርም፣ የመርከብ መሰበር አደጋ ቢያጋጥመውም አልፎ ተርፎም በምግብና በልብስ እጦት ቢቸገርም ውጤታማ የሆነ አገልግሎት ማከናወን ችሏል። (2 ቆሮ. 11:23-27) ጳውሎስ ቀደም ሲል ብዙ ነገሮችን ማከናወኑም ሆነ የተለያዩ ችግሮችን በጽናት መወጣቱ በይሖዋ አገልግሎት ወደፊት መቀጠል እንዳለበት እንዲዘነጋ አላደረገውም። እኛም ብንሆን እንዲሁ ሊሰማን ይገባል። w19.08 3 አን. 5
እሁድ፣ ጥቅምት 10
በተኩላዎች መካከል እንዳሉ በጎች እልካችኋለሁ።—ማቴ. 10:16
በርካታ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የሚኖሩት በይፋ ወይም ከቤት ወደ ቤት መስበክ በማይቻልባቸው አገሮች በመሆኑ ምሥራቹን ለመስበክ ሌሎች ዘዴዎችን መጠቀም አስፈልጓቸዋል። (ማቴ. 10:17-20) እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ባለበት አንድ አገር ውስጥ የሚያገለግል የወረዳ የበላይ ተመልካች፣ አስፋፊዎቹ ሊሰብኩ የሚችሉበት የየራሳቸው የአገልግሎት ክልል እንዳላቸው ይኸውም ለዘመዶቻቸው፣ ለጎረቤቶቻቸው፣ አብረዋቸው ለሚማሩና ለሚሠሩ ሰዎች እንዲሁም ለሚያውቋቸው ሌሎች ሰዎች መስበክ እንደሚችሉ ሐሳብ ሰጣቸው። በሁለት ዓመት ውስጥ፣ በዚያ ወረዳ ያሉ ጉባኤዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጨመረ። እኛ የምንኖረው ምሥራቹን በነፃነት መስበክ በታገደበት አገር ውስጥ ላይሆን ይችላል። ያም ቢሆን ብልህ ከሆኑት ከእነዚህ ወንድሞችና እህቶች የምንማረው ጠቃሚ ትምህርት አለ፦ ይሖዋ ማንኛውንም እንቅፋት ለመወጣት የሚያስችል ኃይል እንደሚሰጠን በመተማመን፣ በአገልግሎት የተሟላ ተሳትፎ ለማድረግ የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን ምንጊዜም እንፈልግ። (ፊልጵ. 2:13) ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በዛሬው ጊዜ፣ ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይተን ለማወቅ፣ እንከን የማይገኝብን ለመሆን፣ ሌሎችን ላለማሰናከል እንዲሁም የጽድቅ ፍሬ ለማፍራት ጥረት እናድርግ። እንዲህ ካደረግን ፍቅራችን እየጨመረ ይሄዳል፤ እንዲሁም አፍቃሪ የሆነውን አባታችንን ይሖዋን እናስከብራለን። w19.08 12-13 አን. 17-18
ሰኞ፣ ጥቅምት 11
አገልጋዮች በፈረስ ተቀምጠው ሲጓዙ፣ መኳንንት ግን እንደ አገልጋዮች በእግራቸው ሲሄዱ አይቻለሁ።—መክ. 10:7
እኔ ያልኩት ብቻ ካልሆነ ከሚልና የሌሎችን አስተያየት ለመቀበል ፈቃደኛ ካልሆነ ሰው ጋር መሆን የሚያስደስተው ማን አለ? በአንጻሩ ግን ሁላችንም ‘የሌላውን ስሜት ከሚረዱ፣ የወንድማማች መዋደድ ካላቸው፣ ከአንጀት ከሚራሩና ትሑታን ከሆኑ’ የእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር መሆን ደስ ይለናል። (1 ጴጥ. 3:8) እኛ እንዲህ ያለ ባሕርይ ካላቸው ሰዎች ጋር መሆን እንደሚያስደስተን ሁሉ ትሑት ከሆንን ሌሎችም ከእኛ ጋር መሆን ያስደስታቸዋል። በተጨማሪም ትሕትና ከአላስፈላጊ ውጥረት ይጠብቀናል። አንዳንድ ጊዜ ፍትሕ የጎደላቸው ወይም ትክክል ያልሆኑ ነገሮች እንደተፈጸሙ ይሰማን ይሆናል። ጥሩ ችሎታ ያላቸው ሰዎች ተገቢውን እውቅና የማያገኙበት ጊዜ አለ። ያን ያህል ችሎታ የሌላቸው ሰዎች ደግሞ የበለጠ ክብር ሲሰጣቸው እናያለን። ያም ቢሆን ሰለሞን አሉታዊ በሆኑ ነገሮች ላይ ከልክ በላይ ከማተኮር ይልቅ እውነታውን መቀበል ጥበብ እንደሆነ ተገንዝቧል። (መክ. 6:9) ትሑት ከሆንን አንዳንድ ነገሮች እኛ እንዳሰብናቸው ባይሆኑ እንኳ ሁኔታውን ተቀብለን ማለፍ ቀላል ይሆንልናል። w19.09 4-5 አን. 9-10
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 12
አባቶች ሆይ፣ ልጆቻችሁን . . . በይሖዋ ተግሣጽና ምክር አሳድጓቸው።—ኤፌ. 6:4
የተወሰነ ሥልጣን ያላቸው ሰዎች ለምሳሌ አባቶች ሌሎች ሰዎችን የሚጠቅም ነገር ለማከናወን የሚያስችል አጋጣሚ አላቸው። ይሖዋ አባቶችን የቤተሰብ ራስ አድርጎ የሾማቸው ሲሆን ልጆቻቸውን እንዲያሠለጥኑና እንዲገሥጹ ይጠብቅባቸዋል። (1 ቆሮ. 11:3) ሆኖም የአባቶች ሥልጣን ገደብ አለው፤ ለእያንዳንዱ ቤተሰብ ስያሜ በሰጠው በይሖዋ ፊት ተጠያቂ ናቸው። (ኤፌ. 3:14, 15) አባቶች ሥልጣናቸውን አምላክን በሚያስደስት መንገድ በመጠቀም ለይሖዋ እንደሚገዙ ያሳያሉ። ይሖዋ የሰጣችሁን ሥልጣን አላግባብ አትጠቀሙበት። ስህተታችሁን አምናችሁ ተቀበሉ፤ እንዲሁም ሌሎች የሚሰጧችሁን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ለመስማት ፈቃደኞች ሁኑ። በዚህ መልኩ ትሕትና ማሳየታችሁ የቤተሰባችሁን አክብሮት ያተርፍላችኋል። ከቤተሰባችሁ ጋር ስትጸልዩ የልባችሁን አውጥታችሁ ለይሖዋ ተናገሩ፤ ቤተሰባችሁ ምን ያህል በይሖዋ እንደምትታመኑ እንዲያስተውሉ አድርጉ። ከሁሉ በላይ ደግሞ በይሖዋ አገልግሎት ላይ ያተኮረ ሕይወት ለመምራት ተጣጣሩ። (ዘዳ. 6:6-9) ለቤተሰባችሁ ልትሰጡ ከምትችሏቸው ውድ ስጦታዎች መካከል አንዱ የእናንተ መልካም ምሳሌነት ነው። w19.09 15 አን. 8፤ 17 አን. 14፤ 18 አን. 16
ረቡዕ፣ ጥቅምት 13
ማርቆስ . . . ወደ እናንተ ከመጣ [ተቀበሉት]።—ቆላ. 4:10
ማርቆስ ሌሎችን ማገልገል ያስደስተው ነበር። በተለያዩ ጊዜያት ከሐዋርያው ጳውሎስና ከሐዋርያው ጴጥሮስ ጋር አብሮ በማገልገል ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ረድቷቸዋል፤ የማርቆስ ኃላፊነት የሚያስፈልጓቸውን መሠረታዊ ነገሮች ማቅረብ ሊሆን ይችላል። (ሥራ 13:2-5፤ 1 ጴጥ. 5:13) ጳውሎስ ስለ ማርቆስ ሲናገር ‘ለአምላክ መንግሥት አብረውት ከሚሠሩት’ አንዱ እንደሆነና “የብርታት ምንጭ” እንደሆነለት ገልጿል። (ቆላ. 4:11) ማርቆስ ከጳውሎስ የቅርብ ወዳጆች አንዱ ነበር። ይህን የሚያሳይ አንድ ምሳሌ እንመልከት፤ ጳውሎስ በ65 ዓ.ም. ገደማ ሮም ውስጥ ለመጨረሻ ጊዜ በታሰረበት ወቅት ለጢሞቴዎስ ሁለተኛ ደብዳቤ ጽፎለት ነበር። በዚያ ደብዳቤ ላይ ጳውሎስ፣ ማርቆስን ይዞ ወደ ሮም እንዲመጣ ጢሞቴዎስን ጠይቆታል። (2 ጢሞ. 4:11) ጳውሎስ፣ ማርቆስ ቀደም ሲል በታማኝነት ያከናወነውን አገልግሎት ከፍ አድርጎ እንደተመለከተው ጥርጥር የለውም፤ በመሆኑም በዚያ ወሳኝ ወቅት አብሮት እንዲሆን ፈልጓል። ማርቆስ ለጳውሎስ አንዳንድ አስፈላጊ ነገሮች ያደርግለት ምናልባትም ምግብ ወይም ለመጻፍ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን ያቀርብለት ነበር። ጳውሎስ ከመሞቱ በፊት ባሉት የመጨረሻ ቀናት የማርቆስን ማበረታቻና ድጋፍ ማግኘቱ እንዲጸና ረድቶት መሆን አለበት። w20.01 11 አን. 12-13
ሐሙስ፣ ጥቅምት 14
ወደ እኔ ኑ።—ማቴ. 11:28
የመረጥነው ሕይወት የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግንና ጠንክሮ መሥራትን ይጠይቃል። ኢየሱስ ስደት እንደሚደርስብን አስጠንቅቆናል። ሆኖም ይሖዋ ማንኛውንም ተፈታታኝ ሁኔታ ለመወጣት የሚያስችል ብርታት እንደሚሰጠን መጠበቅ እንችላለን። ፈተናዎችን በጽናት በተወጣን ቁጥር ይበልጥ ጠንካሮች እየሆንን እንሄዳለን። (ያዕ. 1:2-4) በተጨማሪም ይሖዋ እንደሚንከባከበን፣ ኢየሱስ እንደ እረኛ እንደሚጠብቀን እንዲሁም ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እንደሚያበረታቱን ልንጠብቅ እንችላለን። (ማቴ. 6:31-33፤ ዮሐ. 10:14፤ 1 ተሰ. 5:11) ኢየሱስ የፈወሳት ‘ደም ይፈስሳት የነበረችው’ ሴት ከሕመሟ በተፈወሰችበት በዚያኑ ዕለት እረፍት አግኝታለች። (ሉቃስ 8:43-48) ለዘላለም እረፍት ማግኘት የምትችለው ግን ታማኝ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ከሆነች ብቻ ነው። ይህች ሴት ምን ውሳኔ አድርጋ ይሆን? የኢየሱስን ቀንበር ለመሸከም መርጣ ከሆነ እንዴት ያለ አስደናቂ ሽልማት እንደሚጠብቃት አስቡት፤ በሰማይ ከኢየሱስ ጋር አብራ የማገልገል መብት ታገኛለች! ክርስቶስን ለመከተል ስትል የምትከፍለው የትኛውም መሥዋዕት ከዚህ በረከት ጋር ሲወዳደር እዚህ ግባ ሊባል አይችልም። ተስፋችን በሰማይም ሆነ በምድር ላይ ለዘላለም መኖር፣ ኢየሱስ “ወደ እኔ ኑ” በማለት ያቀረበውን ግብዣ በመቀበላችን ምንኛ አመስጋኞች ነን! w19.09 25 አን. 21-22
ዓርብ፣ ጥቅምት 15
ቤት በጥበብ ይገነባል፤ በማስተዋልም ይጸናል።—ምሳሌ 24:3
የዳዊት ሰዎች፣ ናባል የተባለውን ሀብታም እስራኤላዊ ጥቂት ምግብ እንዲሰጣቸው ጠየቁት። እነዚህ ሰዎች ናባልን ለመጠየቅ ያልፈሩት፣ በምድረ በዳ ለነበሩ በጎቹ ጥበቃ አድርገውላቸው ስለነበር ነው። ስግብግብ የሆነው ናባል ግን ምንም ነገር መስጠት አልፈለገም። ዳዊት በዚህ በጣም ስለተናደደ ናባልንም ሆነ በቤቱ ውስጥ ያለውን ወንድ ሁሉ ለመግደል ቆርጦ ተነሳ። (1 ሳሙ. 25:3-13, 22) የናባል ሚስት የሆነችው አቢጋኤል ግን አስተዋይና ውብ ሴት ነበረች። የበቀል እርምጃ በመውሰድ በራሱ ላይ የደም ዕዳ እንዳያመጣ ዳዊትን እግሩ ላይ ወድቃ ለመነችው፤ ይህ ትልቅ ድፍረት የሚጠይቅ እርምጃ ነበር። ጉዳዩን በይሖዋ እጅ እንዲተወው በመጠየቅ በዘዴ ምክር ሰጠችው። አቢጋኤል በትሕትና የተናገረችው ሐሳብ እና ማስተዋል የተንጸባረቀበት ድርጊቷ የዳዊትን ልብ ነካው። አቢጋኤልን ወደ እሱ የላካት ይሖዋ እንደሆነ ዳዊት ተገነዘበ። (1 ሳሙ. 25:23-28, 32-34) አቢጋኤል፣ ይሖዋ እንዲጠቀምባት የሚያደርጉ ባሕርያት አዳብራ ነበር። ይሖዋ በዛሬው ጊዜም ዘዴኛና አስተዋይ የሆኑ ክርስቲያን እህቶችን የቤተሰባቸውንና የጉባኤያቸውን አባላት እንዲያበረታቱ ሊጠቀምባቸው ይችላል።—ቲቶ 2:3-5፤ w19.10 23 አን. 10
ቅዳሜ፣ ጥቅምት 16
ሕዝቤ ሆይ፣ የኃጢአቷ ተባባሪ መሆን የማትፈልጉና የሚደርስባት መቅሰፍት ተካፋይ መሆን የማትፈልጉ ከሆነ ከእሷ ውጡ።—ራእይ 18:4
ሁሉም እውነተኛ ክርስቲያኖች ከታላቂቱ ባቢሎን ጋር ምንም ዓይነት ንክኪ እንዳይኖራቸው መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ እውነትን መማር ከመጀመሩ በፊት የሐሰት ሃይማኖት አባል ሊሆን ይችላል። በዚያ ሃይማኖት የአምልኮ ፕሮግራሞች ላይ ይገኝ ወይም በአንዳንድ እንቅስቃሴዎች ይሳተፍ ይሆናል። አሊያም ደግሞ ለድርጅቱ ገንዘብ ያዋጣ ይሆናል። ይሁን እንጂ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ያልተጠመቀ አስፋፊ ሆኖ ለማገልገል እንዲፈቀድለት ከሐሰት ሃይማኖት ጋር ያለውን ግንኙነት ሙሉ በሙሉ ማቋረጥ ይኖርበታል። ቀድሞ ወደነበረበት የሃይማኖት ድርጅት የመልቀቂያ ደብዳቤ መላክ ወይም ከቤተ ክርስቲያኑ ጋር ያለውን ግንኙነት ሙሉ በሙሉ ማቋረጥ አለበት፤ ከታላቂቱ ባቢሎን ጋር ንክኪ ያለው የማንኛውም ድርጅት አባል ከሆነም ይህን ማቋረጥ አለበት። አንድ እውነተኛ ክርስቲያን ሰብዓዊ ሥራው ከታላቂቱ ባቢሎን ጋር የሚያነካካው እንዳይሆን መጠንቀቅ አለበት። (2 ቆሮ. 6:14-17) እንዲህ ያለ ጥብቅ አቋም የምንይዘው ለምንድን ነው? አምላክ ርኩስ እንደሆኑ አድርጎ በሚመለከታቸው ሃይማኖታዊ ድርጅቶች ሥራም ሆነ ኃጢአት ተባባሪ መሆን ስለማንፈልግ ነው።—ኢሳ. 52:11፤ w19.10 12 አን. 16-17
እሁድ፣ ጥቅምት 17
ይሖዋ መሐሪና ሩኅሩኅ . . . ነው። እሱ ሁልጊዜ ስህተት አይፈላልግም፤ ለዘላለምም ቂም አይዝም።—መዝ. 103:8, 9
ኤርምያስ በስሙ የተሰየመውን መጽሐፍ ጽፏል፤ በተጨማሪም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆኑትን የአንደኛና የሁለተኛ ነገሥት መጻሕፍት የጻፈው እሱ ሳይሆን አይቀርም። ኤርምያስ እነዚህን መጻሕፍት ሲጽፍ፣ ይሖዋ ፍጹማን ላልሆኑ የሰው ልጆች ምን ያህል ምሕረት እንደሚያሳይ ይበልጥ ተገንዝቦ መሆን አለበት። ለምሳሌ ያህል፣ ንጉሥ አክዓብ ከመጥፎ ድርጊቱ ንስሐ ስለገባ ይሖዋ በቤተሰቡ ላይ የሚመጣውን ጥፋት እንዳያይ አድርጎታል፤ ኤርምያስ ይህን ያውቅ ነበር። (1 ነገ. 21:27-29) በተመሳሳይም ምናሴ ከአክዓብ ይበልጥ ይሖዋን የሚያስቆጣ ድርጊት እንደፈጸመ ኤርምያስ ያውቅ ነበር። ይሁንና ምናሴ ንስሐ ስለገባ ይሖዋ ይቅር ብሎታል። (2 ነገ. 21:16, 17፤ 2 ዜና 33:10-13) እነዚህ ታሪኮች ኤርምያስም እንደ አምላክ ታጋሽና ይቅር ባይ እንዲሆን አነሳስተውት መሆን አለበት። ባሮክ ለተወሰነ ጊዜ ያህል ትኩረቱ በተከፋፈለበት ወቅት ኤርምያስ ያደረገውን ነገር እንደ ምሳሌ እንመልከት። ወዳጁ እንደማይስተካከል በማሰብ ቶሎ ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ አምላክ የተናገረውን ደግነት የተንጸባረቀበት ግልጽ ምክር በማካፈል ባሮክን ረድቶታል።—ኤር. 45:1-5፤ w19.11 6 አን. 14-15
ሰኞ፣ ጥቅምት 18
አምላክ . . . የምታከናውኑትን ሥራ እንዲሁም ለስሙ ያሳያችሁትን ፍቅር በመርሳት ፍትሕ አያዛባም።—ዕብ. 6:10
የዘሌዋውያን መጽሐፍ እንደሚያሳየው አንድ እስራኤላዊ “አመስጋኝነቱን ለመግለጽ” የኅብረት መሥዋዕት ማቅረብ ይችል ነበር። (ዘሌ. 7:11-13, 16-18) ግለሰቡ ይህን መባ የሚያቀርበው ስለሚጠበቅበት ሳይሆን በራሱ ፍላጎት ተነሳስቶ ነው። በጥንት ዘመን ይቀርቡ እንደነበሩት የኅብረት መሥዋዕቶች ሁሉ እኛም በፈቃደኝነት ለይሖዋ የምናቀርበው አገልግሎት ለእሱ ያለንን ፍቅር የሚያሳይ ነው። ለይሖዋ የምንሰጠው ምርጣችንን ሲሆን ይህን የምናደርገውም ከልባችን ስለምንወደው ነው። ይሖዋ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አገልጋዮቹ ለእሱና ለመሥፈርቶቹ ባላቸው ጥልቅ ፍቅር ተነሳስተው እንደሚያገለግሉት ሲመለከት ምንኛ ይደሰት ይሆን! ይሖዋ የምናደርገውን ነገር ብቻ ሳይሆን አንድን ነገር ለማድረግ የተነሳሳንበትን ምክንያት ጭምር ይመለከታል እንዲሁም ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በዕድሜ የገፋህ ክርስቲያን ከሆንክ እንደ ቀድሞህ የምትፈልገውን ያህል ማገልገል አትችል ይሆናል፤ ሆኖም ይሖዋ የሚመለከተው እያደረግክ ያለኸውን ነገር ብቻ እንዳልሆነ አስታውስ። በይሖዋ አገልግሎት የምታደርገው ተሳትፎ ከቁጥር የማይገባ እንደሆነ ይሰማህ ይሆናል፤ ይሁንና ይሖዋ እሱን አቅምህ በፈቀደ መጠን ለማገልገል ያነሳሳህ ለእሱ ያለህ ፍቅር መሆኑን ይመለከታል። ይሖዋ ለእሱ ምርጥህን በመስጠትህ ይደሰታል። w19.11 22 አን. 9፤ 23 አን. 11-12
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 19
ወደ አንድ ገለል ያለ ስፍራ እንሂድና በዚያ ትንሽ አረፍ በሉ።—ማር. 6:31
ከሥራ ጋር በተያያዘ ሚዛናዊ መሆን አስፈላጊ ነው። ንጉሥ ሰለሞን “ለሁሉም ነገር ጊዜ አለው” ሲል በመንፈስ መሪነት ጽፏል። ሰለሞን ከጠቀሳቸው ነገሮች መካከል መትከል፣ መገንባት፣ ማልቀስ፣ መሳቅና ጭፈራ ይገኙበታል። (መክ. 3:1-8) በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ሥራ እና እረፍት፣ በሕይወት ውስጥ ትልቅ ቦታ ያላቸው ነገሮች ናቸው። ኢየሱስ ለሥራም ሆነ ለእረፍት ሚዛናዊ አመለካከት ነበረው። በአንድ ወቅት ሐዋርያቱ ከስብከት ጉዞ ከተመለሱ በኋላ የተፈጠረውን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት። ሐዋርያቱ በሥራ በጣም ከመጠመዳቸው የተነሳ “ምግብ ለመብላት እንኳ ፋታ አላገኙም” ነበር። በመሆኑም ኢየሱስ በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ የሚገኘውን ሐሳብ ነገራቸው። (ማር. 6:30-34) ኢየሱስ እና ደቀ መዛሙርቱ የሚፈልጉትን ያህል ማረፍ የቻሉት ሁልጊዜ ባይሆንም ኢየሱስ እረፍት እንደሚያስፈልጋቸው ያውቅ ነበር። አንዳንድ ጊዜ፣ ማረፍ ወይም ከተለመደው ፕሮግራማችን ለየት ያለ ነገር ማድረግ ያስፈልገናል። አምላክ ለጥንት ሕዝቦቹ ያደረገው አንድ ዝግጅት ይኸውም ሳምንታዊው የሰንበት እረፍት ለዚህ ማስረጃ ይሆነናል። ክርስቲያኖች በሙሴ ሕግ ሥር ባንሆንም እንኳ ስለ ሰንበት የሚገልጸውን ዘገባ መመርመራችን ይጠቅመናል። w19.12 3 አን. 6-7
ረቡዕ፣ ጥቅምት 20
ፈጽሞ አትጨነቁ።—ማቴ. 6:31
ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን እንደሚንከባከባቸው ቃል የገባ ሲሆን ይህን ቃሉን የመፈጸም ግዴታ እንዳለበት ይሰማዋል። (መዝ. 31:1-3) በተጨማሪም ይሖዋ የቤተሰቡን አባላት ሳይንከባከብ ቢቀር ይህ በጣም ሊያሳዝነን እንደሚችል ያውቃል። ይሖዋ ቁሳዊም ሆነ መንፈሳዊ ፍላጎታችንን ለማሟላት ቃል ገብቷል፤ ደግሞም ይህን ቃሉን እንዳይፈጽም ሊያግደው የሚችል አንዳች ነገር የለም! (ማቴ. 6:30-33፤ 24:45) ይሖዋ ቃሉን የሚጠብቀው ለምን እንደሆነ ማስታወሳችን፣ የኢኮኖሚ ችግር ሲያጋጥመን እሱ እንደሚረዳን እንድንተማመን ያደርገናል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩትን ክርስቲያኖች እንደ ምሳሌ እንመልከት። በኢየሩሳሌም በሚገኘው ጉባኤ ላይ ከባድ ስደት በተነሳበት ወቅት “ከሐዋርያት በስተቀር ደቀ መዛሙርቱ በሙሉ . . . ተበተኑ።” (ሥራ 8:1) ይህ ምን ሊያስከትልባቸው እንደሚችል እስቲ አስበው፤ እነዚህ ክርስቲያኖች በኢኮኖሚ መቸገራቸው አይቀርም። ቤታቸውንና መተዳደሪያቸውን አጥተው ሊሆን ይችላል። ያም ቢሆን ይሖዋ አልተዋቸውም፤ እነሱም ቢሆን ደስታቸውን አላጡም። (ሥራ 8:4፤ ዕብ. 13:5, 6፤ ያዕ. 1:2, 3) ይሖዋ እነዚያን ታማኝ ክርስቲያኖች ደግፏቸዋል፤ እኛንም ቢሆን ይደግፈናል።—መዝ. 37:18, 19፤ w20.01 17-18 አን. 14-15
ሐሙስ፣ ጥቅምት 21
ይሖዋ . . . ትሑት የሆነውን ሰው ይመለከታል።—መዝ. 138:6
ዳዊት የአባቱን በጎች ከአንበሳና ከድብ በታደጋቸው ጊዜ እነዚህን አደገኛ አራዊት እንዲያሸንፍ የረዳው ይሖዋ መሆኑን አስተውሎ ነበር። ግዙፉን ጦረኛ ጎልያድን ድል በነሳበት ወቅትም ይሖዋ እየመራው እንደሆነ በግልጽ አይቷል። (1 ሳሙ. 17:37) ቅናት ከተጠናወተው ከንጉሥ ሳኦል ይሸሽ በነበረበት ወቅት ይሖዋ ከአሳዳጁ እጅ እንዳዳነው ተገንዝቧል። (መዝ. 18 አናት ላይ ያለው መግለጫ) ዳዊት ኩሩ ቢሆን ኖሮ እነዚህን ነገሮች በራሱ ኃይል እንደተወጣቸው ሊሰማው ይችል ነበር። እሱ ግን ትሑት ስለሆነ በሕይወቱ ውስጥ የይሖዋን እርዳታ እንዳገኘ አምኖ ተቀብሏል። ከዚህ የምናገኘው ትምህርት ምንድን ነው? የይሖዋን እርዳታ ከመጠየቅ ባለፈ እንዴት እንደሚረዳን ለማስተዋል ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ያለብንን የአቅም ገደብ በትሕትና አምነን ከተቀበልን ይሖዋ የሚጎድለንን ነገር ሲያሟላልን በግልጽ መመልከት እንችላለን። ይሖዋ እንዴት እንደረዳን ባስተዋልን ቁጥር ደግሞ ከእሱ ጋር ያለን ዝምድና ይበልጥ እየተጠናከረ ይሄዳል። w19.12 20 አን. 18-19
ዓርብ፣ ጥቅምት 22
አባት ደስ የሚሰኝበትን ልጁን እንደሚወቅስ ሁሉ ይሖዋም የሚወዳቸውን ይወቅሳል።—ምሳሌ 3:12
ይሖዋ ውድ አድርጎ እንደሚመለከተን የሚያሳዩ ብዙ ማስረጃዎች አሉ። ወደ ራሱ የሳበን ከመሆኑም ሌላ ምሥራቹን ስንሰማ የሰጠነውን ምላሽ በትኩረት ተመልክቷል። (ዮሐ. 6:44) ወደ እሱ መቅረብ ስንጀምር እሱም ወደ እኛ ይበልጥ ቀርቧል። (ያዕ. 4:8) ከዚህም ሌላ ይሖዋ ውድ እንደሆንን አድርጎ ስለሚመለከተን ጊዜ መድቦ ያስተምረናል። ይሖዋ አሁን ምን ዓይነት ሰዎች እንደሆንን እንዲሁም ለውጥ አድርገን ምን ዓይነት ሰው መሆን እንደምንችል ያውቃል። ደግሞም ስለሚወደን ተግሣጽ ይሰጠናል። ይህ ሁሉ በይሖዋ ፊት ውድ እንደሆንን የሚያሳይ አሳማኝ ማስረጃ ነው! አንዳንድ ሰዎች ንጉሥ ዳዊትን የማይረባ ሰው አድርገው የቆጠሩት ቢሆንም ዳዊት፣ ይሖዋ እንደሚወደውና እንደሚደግፈው ያውቅ ነበር። ይህን ማወቁም ስላለበት ሁኔታ ትክክለኛ አመለካከት እንዲይዝ ረድቶታል። (2 ሳሙ. 16:5-7) እኛም መንፈሳችን ሲደቆስ ወይም ችግሮች ሲያጋጥሙን ያለንበትን ሁኔታ በተለየ መንገድ መመልከት እንዲሁም ማንኛውንም እንቅፋት መሻገር እንድንችል ይሖዋ ይረዳናል። (መዝ. 18:27-29) የይሖዋ እርዳታ እስካልተለየን ድረስ እሱን በደስታ እንዳናገለግል እንቅፋት ሊሆንብን የሚችል ነገር የለም።—ሮም 8:31፤ w20.01 15 አን. 7-8
ቅዳሜ፣ ጥቅምት 23
ያዘዝኳችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ [አስተምሯቸው]።—ማቴ. 28:20
ጥናቱን በጸሎት ጀምር። በጥቅሉ ሲታይ፣ ሰዎችን በቋሚነት መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናት ከጀመርን ብዙም ሳንቆይ ይኸውም ከመጀመሪያዎቹ ሳምንታት አንስቶ ጥናቱን በጸሎት መክፈታችን እና መደምደማችን ጥሩ ነው። የአምላክን ቃል መረዳት የምንችለው በአምላክ መንፈስ እርዳታ ብቻ መሆኑን ጥናታችን እንዲገነዘብ መርዳት ይኖርብናል። አንዳንድ ክርስቲያኖች ለጥናታቸው ስለ ጸሎት አስፈላጊነት ለማንሳት በያዕቆብ 1:5 ላይ የሚገኘውን “ከእናንተ መካከል ጥበብ የጎደለው ሰው ካለ አምላክን ያለማሰለስ ይለምን” የሚለውን ጥቅስ ያነቡለታል። ከዚያም ጥናታቸውን “አምላክ ጥበብ እንዲሰጠን መለመን የምንችለው እንዴት ነው?” ብለው ይጠይቁታል። አብዛኛውን ጊዜ ተማሪው ወደ አምላክ መጸለይ እንዳለብን ይስማማል። ጥናትህን እንዴት መጸለይ እንዳለበት አስተምረው። ከልብ በመነጨ ስሜት የሚያቀርበውን ጸሎት ይሖዋ መስማት እንደሚፈልግ ለጥናትህ አረጋግጥለት። በግላችን ለይሖዋ በምናቀርበው ጸሎት ላይ የልባችንን አውጥተን ልንነግረው ሌላው ቀርቶ ለማንም ሰው የማንነግረውን ነገር እንኳ ልናካፍለው እንደምንችል ለጥናትህ ግለጽለት። ደግሞም ይሖዋ ውስጣዊ ሐሳባችንን ሳንነግረው ያውቃል።—መዝ. 139:2-4፤ w20.01 2 አን. 3፤ 5 አን. 11-12
እሁድ፣ ጥቅምት 24
ይህ የተመካው በአንድ ሰው ፍላጎት ወይም ጥረት ሳይሆን . . . [በአምላክ] ላይ ነው።—ሮም 9:16
ቅቡዓንን የሚመርጥበትን ጊዜ የሚወስነው ይሖዋ ነው። (ሮም 8:28-30) ይሖዋ ቅቡዓንን መምረጥ የጀመረው ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ነው። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት እውነተኛ ክርስቲያኖች በሙሉ ቅቡዓን ሳይሆኑ አይቀሩም። ከዚያ በኋላ ባሉት ዘመናት ውስጥ፣ ክርስቲያን ነን ይሉ የነበሩት አብዛኞቹ ሰዎች እውነተኛ የክርስቶስ ተከታዮች አልነበሩም። ያም ቢሆን በእነዚህ ዓመታት የነበሩትን ጥቂት እውነተኛ ክርስቲያኖች ይሖዋ በመንፈስ ቀብቷቸዋል። እነዚህ ክርስቲያኖች ኢየሱስ እንደጠቀሰው በእንክርዳድ መካከል ያደገ ስንዴ ናቸው። (ማቴ. 13:24-30) በመጨረሻዎቹ ቀናትም ይሖዋ የ144,000ዎቹ አባላት የሚሆኑ ሰዎችን መምረጡን ቀጥሏል። ይሖዋ ለዚህ መብት ብቁ የሚሆኑ አንዳንድ ሰዎችን መጨረሻው ከመምጣቱ ጥቂት ቀደም ብሎ ለመምረጥ ከፈለገ በእሱ ጥበብ ላይ ጥያቄ ለማንሳት እኛ ማን ነን? (ሮም 9:11) ኢየሱስ ከተናገራቸው ምሳሌዎች በአንዱ ላይ እንደጠቀሳቸው ሠራተኞች እንዳንሆን መጠንቀቅ አለብን። እነዚህ ሠራተኞች፣ ጌታቸው በመጨረሻው ሰዓት ለተቀጠሩት ሰዎች ባደረገው ነገር አጉረምርመዋል።—ማቴ. 20:8-15፤ w20.01 30 አን. 14
ሰኞ፣ ጥቅምት 25
አገልጋዮቼ . . . እልል ይላሉ።—ኢሳ. 65:14
ይሖዋ ቤተሰቡ ደስተኛ እንዲሆን ይፈልጋል። በዛሬው ጊዜ ችግሮች እያጋጠሙንም እንኳ ደስተኛ ለመሆን የሚያስችሉን ብዙ ምክንያቶች አሉ። ለምሳሌ፣ የሰማዩ አባታችን በጣም እንደሚወደን እርግጠኞች በመሆናችን ደስተኞች ነን። የአምላክ ቃል ስለሆነው ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛ እውቀት አለን። (ኤር. 15:16) ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋንና ላቅ ያሉ የሥነ ምግባር መሥፈርቶቹን የሚወዱ እንዲሁም እርስ በርስ የሚዋደዱ ሰዎችን ያቀፈ ልዩ ቤተሰብ አባል ነን። (መዝ. 106:4, 5) ወደፊት ደግሞ ሕይወት ከዚህ በጣም የተሻለ እንደሚሆን የተረጋገጠ ተስፋ ስላለን ደስተኞች መሆን እንችላለን። በቅርቡ ይሖዋ ክፉዎችን በሙሉ እንደሚያጠፋ እንዲሁም በመንግሥቱ አመራር ሥር ምድር እንደገና ገነት እንደምትሆን እናውቃለን። በተጨማሪም የሞቱ ሰዎች እንደሚነሱና ከሚወዷቸው ሰዎች ጋር እንደሚገናኙ የሚያረጋግጥ አስደናቂ ተስፋ አለን። (ዮሐ. 5:28, 29) ይህ እንዴት ያለ አስደሳች ጊዜ ይሆናል! ከሁሉ በላይ ደስ የሚለው ነገር ደግሞ በቅርቡ፣ በሰማይም ሆነ በምድር ያለ ፍጥረት በሙሉ ለአፍቃሪው አባታችን የሚገባውን ክብር፣ ውዳሴና አምልኮ እንደሚያቀርብ እርግጠኞች ነን። w20.02 13 አን. 15-16
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 26
አንተን፣ አዎ ከማንም በላይ አንተን በደልኩ።—መዝ. 51:4
ከባድ ኃጢአት ሠርተህ ከሆነ ስህተትህን ለመሸፋፈን አትሞክር። ከዚህ ይልቅ ወደ ይሖዋ በመጸለይ ኃጢአትህን በግልጽ ተናዘዝ። እንዲህ ማድረግህ በሕሊና ወቀሳ የተነሳ የሚሰማህ ጭንቀት በተወሰነ መጠን ቀለል እንዲልልህ ይረዳሃል። ከይሖዋ ጋር ያለህን ወዳጅነት ማደስ ከፈለግህ ግን ወደ እሱ ከመጸለይ የበለጠ ነገር ማድረግ ይጠበቅብሃል። ተግሣጽን መቀበል ይኖርብሃል። ንጉሥ ዳዊትን ከቤርሳቤህ ጋር ስለፈጸመው ኃጢአት እንዲያነጋግረው ይሖዋ ነቢዩ ናታንን በላከው ወቅት ዳዊት ሰበብ ለማቅረብ ወይም ጥፋቱን ለማቃለል አልሞከረም። ዳዊት የቤርሳቤህን ባል፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ ይሖዋን እንደበደለ ወዲያውኑ አምኖ ተቀብሏል። የይሖዋን ተግሣጽ የተቀበለ ሲሆን ይሖዋም ምሕረት አድርጎለታል። (2 ሳሙ. 12:10-14) እኛም ከባድ ኃጢአት ፈጽመን ከሆነ ይሖዋ እረኛ ሆነው እንዲጠብቁን የሾማቸውን ሰዎች ማነጋገር ያስፈልገናል። (ያዕ. 5:14, 15) በተጨማሪም ለስህተታችን ሰበብ አስባብ እንዳናቀርብ መጠንቀቅ ይኖርብናል። የሚሰጠንን ማንኛውንም ተግሣጽ ወዲያውኑ ተቀብለን ተግባራዊ ካደረግን ሰላማችን እና ደስታችን ቶሎ ይመለስልናል። w20.02 24-25 አን. 17-18
ረቡዕ፣ ጥቅምት 27
ከብሔራት ቋንቋዎች ሁሉ የተውጣጡ አሥር ሰዎች የአንድን አይሁዳዊ ልብስ አጥብቀው በመያዝ “አምላክ ከእናንተ ጋር መሆኑን ስለሰማን ከእናንተ ጋር እንሄዳለን” ይላሉ።—ዘካ. 8:23
‘አሥሩ ሰዎች’ በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸውን ሰዎች ያመለክታሉ። እነዚህ ሰዎች፣ ይሖዋ ‘በአይሁዳዊ’ የተመሰሉትን ቅቡዓኑን እየባረካቸው እንደሆነ ስለሚያውቁ ከእነሱ ጋር ሆነው ይሖዋን ማምለካቸውን እንደ መብት ይቆጥሩታል። በዛሬው ጊዜ በምድር ላይ ያለውን የእያንዳንዱን ቅቡዕ ስም ማወቅ ባይቻልም ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖች ከቅቡዓኑ ጋር ‘መሄድ’ ይችላሉ። እንዴት? የዛሬው የዕለት ጥቅስ መልሱን ይሰጠናል። ጥቅሱ ላይ የተገለጸው አይሁዳዊ አንድ ነው። ያም ሆኖ “ከእናንተ” ከሚለው ቃል ማየት እንደሚቻለው ሐሳቡ የሚያመለክተው ከአንድ በላይ የሆኑ ሰዎችን ነው። እንግዲያው እዚህ ላይ የተገለጸው አይሁዳዊ አንድን ሰው ሳይሆን ሁሉንም ቅቡዓን ክርስቲያኖች የሚያመለክት ነው! በመንፈስ ቅዱስ ያልተቀቡ ክርስቲያኖች ከቅቡዓኑ ጋር ሆነው ይሖዋን ያገለግላሉ። ይሁንና መሪያቸው ኢየሱስ እንደሆነ ስለሚገነዘቡ ቅቡዓኑን እንደ መሪዎቻቸው አድርገው አይመለከቷቸውም።—ማቴ. 23:10፤ w20.01 26 አን. 1-2
ሐሙስ፣ ጥቅምት 28
እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ።—ዮሐ. 13:35
ኢየሱስ ተከታዮቹ እውነተኛ ደቀ መዛሙርቱ መሆናቸው የሚታወቀው የእሱን ዓይነት ፍቅር ካሳዩ እንደሆነ ገልጿል። በመጀመሪያው መቶ ዘመንም ሆነ በዘመናችን ይህ ሐሳብ እውነት መሆኑ ታይቷል። የትኛውንም ተፈታታኝ ሁኔታ ተቋቁመን እርስ በርስ መዋደዳችን በእርግጥም በጣም አስፈላጊ ነው! እንግዲያው ‘ተፈታታኝ ሁኔታ ቢያጋጥማቸውም ፍቅር ማሳየታቸውን ከቀጠሉ ወንድሞችና እህቶች ምን ትምህርት ማግኘት እችላለሁ?’ እያልክ ራስህን ጠይቅ። ሁላችንም ፍጹማን ባለመሆናችን እርስ በርስ አጥብቀን መዋደድ ከባድ ሊሆንብን ይችላል። ያም ቢሆን ኢየሱስን ለመምሰል ጥረት ማድረግ አለብን። ኢየሱስ ቅር ከተሰኘብን ወንድም ጋር ሰላም መፍጠር ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ አስተምሯል። (ማቴ. 5:23, 24) አምላክን ማስደሰት ከፈለግን ከሌሎች ጋር ጥሩ ግንኙነት ሊኖረን እንደሚገባ ጎላ አድርጎ ገልጿል። ከወንድሞቻችን ጋር ሰላም ለመፍጠር የቻልነውን ሁሉ ስናደርግ ይሖዋ ይደሰታል። ቂም የምንይዝ ብሎም ሰላም ፈጣሪ ለመሆን ጥረት ለማድረግ እንኳ ፈቃደኛ የማንሆን ከሆነ ግን አምልኳችንን አይቀበልም።—1 ዮሐ. 4:20፤ w20.03 24 አን. 1-4
ዓርብ፣ ጥቅምት 29
በመንፈስ የተነገረውን የእውነት ቃልና በመንፈስ የተነገረውን የስህተት ቃል ለይተን [እናውቃለን]።—1 ዮሐ. 4:6
“የውሸት አባት” የሆነው ሰይጣን ከሰው ልጅ ታሪክ መጀመሪያ አንስቶ ሰዎችን ሲያሳስት ቆይቷል። (ዮሐ. 8:44) ሰይጣን ከሚያስፋፋቸው ውሸቶች መካከል ስለ ሞትና ከሞት በኋላ ስላለው ሕይወት የሚገልጹት የሐሰት ትምህርቶች ይገኙበታል። እነዚህ ትምህርቶች በብዙ አካባቢዎች በስፋት ለሚታዩት ልማዶችና አጉል እምነቶች መሠረት ሆነዋል። ብዙ ሰዎች በእነዚህ ውሸቶች የተታለሉት ለምንድን ነው? ሰይጣን ሰዎች ስለ ሞት ያላቸውን ስሜት ያውቃል፤ ሞትን አስመልክቶ የሚናገራቸው ውሸቶችም ይህን ግምት ውስጥ ያስገቡ ናቸው። የተፈጠርነው ለዘላለም እንድንኖር ስለሆነ መሞት አንፈልግም። (መክ. 3:11) በመሆኑም ሞትን የምንመለከተው እንደ ጠላታችን አድርገን ነው። (1 ቆሮ. 15:26) ሰይጣን ምንም ያህል ጥረት ቢያደርግ ሞትን በተመለከተ እውነቱን መደበቅ አልቻለም። እንዲያውም ከምንጊዜውም ይበልጥ ዛሬ በርካታ ሰዎች፣ ሙታን ስላሉበት ሁኔታና ስላላቸው ተስፋ የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የሚያውቁ ከመሆኑም በላይ ይህን ለሌሎች እያወጁ ነው። (መክ. 9:5, 10፤ ሥራ 24:15) እነዚህን እውነቶች ማወቃችን ያጽናናናል፤ እንዲሁም አስፈላጊ ካልሆነ ፍርሃትና ጭንቀት ይጠብቀናል። w19.04 14 አን. 1፤ 15 አን. 5-6
ቅዳሜ፣ ጥቅምት 30
አንዳችሁ የሌላውን ከባድ ሸክም ተሸከሙ፤ በዚህ መንገድ የክርስቶስን ሕግ ትፈጽማላችሁ።—ገላ. 6:2
ይሖዋ አምላክ አገልጋዮቹን ይወዳል። ጥንትም ሆነ ዛሬ ለአገልጋዮቹ ያለው ስሜት አልተለወጠም፤ ወደፊትም ቢሆን አይለወጥም። በተጨማሪም ይሖዋ ፍትሕን ይወዳል። (መዝ. 33:5) በመሆኑም ስለ ሁለት ነገሮች እርግጠኞች መሆን እንችላለን፦ (1) ይሖዋ በአገልጋዮቹ ላይ የሚፈጸመውን በደል ሲያይ ያመዋል። (2) አገልጋዮቹ ፍትሕ እንዲያገኙ ያደርጋል። አምላክ በሙሴ አማካኝነት ለእስራኤላውያን የሰጠው ሕግ በፍቅር ላይ የተመሠረተ ነበር። በተጨማሪም ይህ ሕግ ሁሉም ሰዎች በተለይም ለጥቃት የተጋለጡ ሰዎች ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንዲያዙ ያደርግ ነበር። (ዘዳ. 10:18) ሕጉ ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ምን ያህል እንደሚያስብ ያሳያል። በ33 ዓ.ም. የክርስቲያን ጉባኤ ሲቋቋም የአምላክ ሕዝቦች በሙሴ ሕግ ሥር መሆናቸው አበቃ። ታዲያ ክርስቲያኖች በፍቅር ላይ የተመሠረተና ፍትሕ እንዲሰፍን የሚያደርግ ሕግ ከለላ አይኖራቸውም ማለት ነው? በፍጹም! ክርስቲያኖች አዲስ ሕግ ተሰጥቷቸዋል፤ ‘በክርስቶስ ሕግ’ ሥር ናቸው። ክርስቶስ ለተከታዮቹ በጽሑፍ የሰፈረ ዝርዝር ሕግ አልሰጣቸውም፤ ሆኖም ሕይወታቸውን ሊመሩባቸው የሚገቡ ትእዛዞች፣ መመሪያዎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች ሰጥቷቸዋል። ‘የክርስቶስ ሕግ’ ኢየሱስ ያስተማራቸውን ነገሮች በሙሉ ያጠቃልላል። w19.05 2 አን. 1-3
እሁድ፣ ጥቅምት 31
የመጽናናት ሁሉ አምላክ . . . በሚደርስብን መከራ ሁሉ ያጽናናናል።—2 ቆሮ. 1:3, 4
ሰዎች በተፈጥሯቸው ማጽናኛ ይሻሉ፤ ሌሎችን የማጽናናት አስደናቂ ችሎታም አላቸው። ለምሳሌ አንድ ትንሽ ልጅ ሲጫወት ቢወድቅና ጉልበቱ ቢደማ እያለቀሰ ወደ እናቱ ወይም ወደ አባቱ መሄዱ አይቀርም። ወላጆቹ ቁስሉን ሊፈውሱለት ባይችሉም ሊያጽናኑት ይችላሉ። ምን እንደደረሰበት ሊጠይቁት፣ እንባውን ሊጠራርጉለት፣ እቅፍ አድርገው ሊያባብሉት፣ መድኃኒት ሊያደርጉለት ወይም ቁስሉን በጨርቅ ሊያስሩለት ይችላሉ። ብዙም ሳይቆይ ልጁ ማልቀሱን ሊያቆም አልፎ ተርፎም ጨዋታውን ሊቀጥል ይችላል። በጊዜ ሂደት ቁስሉም ይድናል። አንዳንድ ጊዜ ግን ልጆች ከዚህ የከፋ ጉዳት ይደርስባቸዋል። አንዳንዶቹ ፆታዊ ጥቃት ይፈጸምባቸዋል። ጥቃቱ አንድ ጊዜ ብቻ የተፈጸመ ወይም ለዓመታት የዘለቀ ሊሆን ይችላል። ጥቃቱ የተፈጸመው አንዴም ሆነ በተደጋጋሚ፣ በግለሰቡ ላይ ከባድ የስሜት ቁስል ማስከተሉ አይቀርም። ጥቃቱን የፈጸመው ሰው ተገቢውን ቅጣት የሚያገኝበት ጊዜ አለ፤ አንዳንድ ጊዜ ግን ከቅጣት ሊያመልጥ ይችላል። ሆኖም በጥፋተኛው ላይ አፋጣኝ የፍርድ እርምጃ ቢወሰድም እንኳ ጥቃት በተፈጸመበት ሰው ላይ የደረሰው ስሜታዊ ቁስል ለበርካታ ዓመታት ላይሽር ይችላል። w19.05 14 አን. 1-2