ታኅሣሥ
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 1
ዝም ለማለት ጊዜ አለው።—መክ. 3:7
ንግግራችንን ካልተቆጣጠርን ብዙ ጉዳት ልናደርስ እንችላለን። ለምሳሌ ሥራችን በታገደበት አገር ከሚኖር ወንድም ጋር ብንገናኝ በዚያ አገር ውስጥ የሚከናወነውን ሥራ በተመለከተ ዝርዝር ነገሮችን እንዲነግረን ለመጠየቅ እንፈተን ይሆን? እንዲህ የምናደርገው በቅን ልቦና ተነሳስተን እንደሆነ ጥያቄ የለውም። ወንድሞቻችንን እንወዳቸዋለን እንዲሁም ያሉበት ሁኔታ ያሳስበናል። በተጨማሪም ስለ እነሱ ስንጸልይ አንዳንድ ነገሮችን ለይተን መጥቀስ እንፈልግ ይሆናል። ይሁንና በዚህ ወቅት ከመናገር መታቀብ ይኖርብናል። ሚስጥራዊ መረጃ ያለው ወንድማችን መረጃውን እንዲነግረን ብንጎተጉተው ለእሱም ሆነ ሚስጥራቸውን እንደሚጠብቅላቸው ለሚተማመኑበት ወንድሞችና እህቶች ፍቅር እንደጎደለን የሚያሳይ ይሆናል። ማናችንም ብንሆን ሥራችን በታገደባቸው አገሮች የሚኖሩ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ችግራቸው እንዲባባስ የሚያደርግ ነገር ማድረግ አንፈልግም። በተመሳሳይም እንዲህ ባለው አገር ውስጥ የሚያገለግሉ ወንድሞችና እህቶች በዚያ አገር የሚከናወነውን አገልግሎትና ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴ አስመልክቶ መናገራቸው ተገቢ አይሆንም። w20.03 21 አን. 11-12
ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 2
መሞት እንኳ ፈጽሞ አትሞቱም።—ዘፍ. 3:4
አምላክ የሰው ልጆችን የፈጠረው ለተወሰነ ጊዜ ያህል ኖረው እንዲሞቱ አስቦ አልነበረም። አዳምና ሔዋን ለዘላለም መኖር ከፈለጉ ግን ይሖዋ የሰጣቸውን ቀላል መመሪያ መታዘዝ ነበረባቸው፤ መመሪያው የሚከተለው ነበር፦ “ከመልካምና ክፉ እውቀት ዛፍ . . . አትብላ፤ ምክንያቱም ከዚህ ዛፍ በበላህ ቀን በእርግጥ ትሞታለህ።” (ዘፍ. 2:16, 17) ይሁንና ሰይጣን ጣልቃ ገብቶ ችግር ፈጠረ። በእባብ ተጠቅሞ ሔዋንን በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ያለውን ሐሳብ ነገራት። የሚያሳዝነው፣ ሔዋን የተነገራትን ውሸት በማመን ፍሬውን በላች። በኋላ ላይ ባሏም ፍሬውን በላ። (ዘፍ. 3:6) በዚህ መልኩ ኃጢአትና ሞት በሰው ዘር ላይ ነገሡ። (ሮም 5:12) አምላክ በተናገረው መሠረት አዳምና ሔዋን ሞቱ። ሰይጣን ግን ስለ ሞት ውሸት መናገሩን አላቆመም። ከጊዜ በኋላ ሌሎች ውሸቶችን ማስፋፋት ጀመረ። ከእነዚህ ውሸቶች መካከል አንዱ ‘ሰው ሲሞት ከሥጋው ተለይታ በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ መኖሯን የምትቀጥል ነፍስ አለች’ የሚለው ትምህርት ነው። በተለያየ መልኩ የሚነገረው ይህ ውሸት እስከ ዘመናችን ድረስ የዘለቀ ሲሆን ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ሰዎች አሳስቷል።—1 ጢሞ. 4:1፤ w19.04 14-15 አን. 3-4
ዓርብ፣ ታኅሣሥ 3
ልጅ በነበርኩበት ጊዜ እንደ ልጅ እናገር፣ እንደ ልጅ አስብ እንዲሁም እንደ ልጅ አመዛዝን ነበር።—1 ቆሮ. 13:11
ልጆች የማሰብ፣ የማመዛዘን ወይም አደጋ የሚፈጥሩ ሁኔታዎችን አውቆ ከእነዚህ የመራቅ ችሎታቸው ሙሉ በሙሉ አልጎለበተም። በመሆኑም ሕፃናትን የሚያስነውሩ መሠሪ ሰዎች በቀላሉ ሊያታልሏቸው ይችላሉ። እነዚህ ሰዎች ለልጆቹ አደገኛ ውሸቶችን በመንገር ሊያታልሏቸው ይሞክራሉ፤ ለምሳሌ ጥፋተኞቹ ልጆቹ ራሳቸው እንደሆኑ፣ የተፈጠረውን ነገር ለማንም መናገር እንደሌለባቸው፣ ቢናገሩም እንኳ የሚሰማቸው ወይም ግድ የሚሰጠው አንድም ሰው እንደማይኖር አሊያም በአንድ ልጅና በአንድ አዋቂ መካከል የሚፈጸመው እንዲህ ያለው ድርጊት ምንም ስህተት እንደሌለውና ተገቢ የፍቅር መግለጫ እንደሆነ ይነግሯቸው ይሆናል። ልጆቹ የተነገራቸው ነገር ውሸት እንደሆነ የሚያውቁት ከበርካታ ዓመታት በኋላ ሊሆን ይችላል። እንዲህ ያሉ ውሸቶች የተነገሯቸው ልጆች ንጽሕናቸው እንደጎደፈ፣ ምንም እንደማይጠቅሙ፣ የሚወዳቸው ሰው እንደሌለ ወይም ማጽናኛ ማግኘት እንደማይገባቸው ሊሰማቸው ይችላል። ከእነዚህ ነጥቦች አንጻር ፆታዊ ጥቃት ዘላቂ ጉዳት የሚያስከትል መሆኑ ምንም አያስገርምም። የምንኖረው ሰዎች “ተፈጥሯዊ ፍቅር የሌላቸው” በሆኑበት እንዲሁም “ክፉ ሰዎችና አስመሳዮች . . . በክፋት ላይ ክፋት እየጨመሩ” በሚሄዱበት በመጨረሻዎቹ ቀናት ውስጥ ነው።—2 ጢሞ. 3:1-5, 13፤ w19.05 15 አን. 7-8
ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 4
በዚህ መንገድ የክርስቶስን ሕግ ትፈጽማላችሁ።—ገላ. 6:2
ኢየሱስ ያስተማረው በየትኞቹ መንገዶች ነው? አንደኛ፣ በንግግሩ ሰዎችን አስተምሯል። ኢየሱስ የተናገራቸው ነገሮች ስለ አምላክ እውነቱን ስለሚያስተምሩ፣ ትክክለኛውን የሕይወት ትርጉም ስለሚያስገነዝቡና በሰው ልጆች ላይ ለሚደርሰው ማንኛውም መከራ መፍትሔው የአምላክ መንግሥት እንደሆነ ስለሚጠቁሙ ከፍተኛ ኃይል ነበራቸው። (ሉቃስ 24:19) በተጨማሪም ኢየሱስ ምሳሌ በመሆን አስተምሯል። የኢየሱስ አኗኗር ተከታዮቹ እንዴት መኖር እንዳለባቸው የሚያሳይ ነበር። (ዮሐ. 13:15) ኢየሱስ ያስተማረው መቼ ነው? ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ባከናወነበት ወቅት ያስተምር ነበር። (ማቴ. 4:23) በተጨማሪም ከሞት ከተነሳ ብዙም ሳይቆይ ተከታዮቹን አስተምሯል። ለምሳሌ ያህል፣ ከ500 በላይ ለሚሆኑ ተከታዮቹ “ደቀ መዛሙርት አድርጉ” የሚል ትእዛዝ ሰጥቷቸዋል። (ማቴ. 28:19, 20፤ 1 ቆሮ. 15:6) ኢየሱስ የጉባኤው ራስ እንደመሆኑ መጠን ወደ ሰማይ ከተመለሰ በኋላም ለደቀ መዛሙርቱ መመሪያ መስጠቱን ቀጥሏል። ለምሳሌ በ96 ዓ.ም. አካባቢ ሐዋርያው ዮሐንስን ለቅቡዓን ክርስቲያኖች ማበረታቻና ምክር እንዲሰጥ መርቶታል።—ቆላ. 1:18፤ ራእይ 1:1፤ w19.05 3 አን. 4-5
እሁድ፣ ታኅሣሥ 5
ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይታችሁ [እወቁ]።—ፊልጵ. 1:10
በዛሬው ጊዜ ሰዎች ለኑሮ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ለማሟላት ብዙ ይለፋሉ። በርካታ ወንድሞቻችን ለቤተሰባቸው የሚያስፈልገውን መሠረታዊ ነገር ለማቅረብ ረጅም ሰዓት መሥራት ይጠበቅባቸዋል። ሌሎች ብዙ ክርስቲያኖች ደግሞ ወደ ሥራ ሲሄዱና ከሥራ ሲመለሱ ረጅም ሰዓት በጉዞ ያጠፋሉ። ራሳቸውን ለማስተዳደር ሲሉ አድካሚ የጉልበት ሥራ የሚሠሩም አሉ። እነዚህ ትጉ ወንድሞችና እህቶች በእያንዳንዱ ቀን መጨረሻ ላይ በጣም እንደሚደክማቸው የታወቀ ነው! በዚህ ድካም ላይ፣ ማጥናት የሚባለውን ነገር ሲያስቡት ከባድ ዳገት ሊሆንባቸው ይችላል። ሆኖም ሁላችንም በአምላክ ቃልና በክርስቲያናዊ ጽሑፎቻችን ላይ ጥልቀት ያለው ጥናት የምናደርግበት ጊዜ መመደብ አለብን። ከይሖዋ ጋር ያለን ዝምድናም ሆነ የዘላለም ሕይወት ተስፋችን የተመካው እንዲህ በማድረጋችን ላይ ነው! (1 ጢሞ. 4:15, 16) አንዳንዶች ጸጥታ የሰፈነበትንና አእምሯቸው ንቁ የሆነበትን የጠዋቱን ክፍለ ጊዜ ለጥናት ይጠቀማሉ። ሌሎች ደግሞ ትኩረታቸውን የሚከፋፍሉ ነገሮች በሌሉበት በአመሻሹ ጊዜ ላይ ጥቂት ደቂቃዎችን መድበው መንፈሳዊ ምግብ ይመገባሉ እንዲሁም በዚያ ላይ ያሰላስላሉ። w19.05 26 አን. 1-2
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 6
ይህ ሥርዓት እንዲቀርጻችሁ አትፍቀዱ፤ ከዚህ ይልቅ . . . አእምሯችሁን በማደስ ተለወጡ።—ሮም 12:2
እንደዚህ ያሉ ለውጦች የሚመጡት በአንድ ጀምበር ወይም ያለምንም ጥረት አይደለም። ለዓመታት “ልባዊ ጥረት” ማድረግ ሊያስፈልገን ይችላል። (2 ጴጥ. 1:5) ውስጣዊ ማንነታችንን ለመቀየር የተቻለንን ሁሉ ማድረግ ይኖርብናል። ጸሎት የመጀመሪያው አስፈላጊ እርምጃ ነው። እኛም እንደ መዝሙራዊው “አምላክ ሆይ፣ ንጹሕ ልብ ፍጠርልኝ፤ በውስጤም ጽኑ የሆነ አዲስ መንፈስ አኑር” ብለን መጸለይ ያስፈልገናል። (መዝ. 51:10) አእምሯችንን የሚያሠራው ኃይል መለወጥ እንዳለበት አምነን መቀበልና ይሖዋ በዚህ ረገድ እንዲረዳን መለመን ይኖርብናል። ማሰላሰል ሁለተኛው አስፈላጊ እርምጃ ነው። በየቀኑ የአምላክን ቃል ስናነብ፣ ለውጥ ልናደርግባቸው የሚገቡ አስተሳሰቦችና ስሜቶች የትኞቹ እንደሆኑ ጊዜ ወስደን ማሰላሰል ወይም በጥሞና ማሰብ አለብን። (መዝ. 119:59፤ ዕብ. 4:12፤ ያዕ. 1:25) ዓለማዊ ፍልስፍናዎች በአስተሳሰባችንና በስሜታችን ላይ ተጽዕኖ አሳድረው እንደሆነ ለማወቅ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ያሉብንን ድክመቶች በሐቀኝነት አምነን መቀበልና ማስተካከያ ለማድረግ በትጋት መሥራት ይጠበቅብናል። w19.06 8 አን. 1፤ 10 አን. 10፤ 12 አን. 11-12
ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 7
ጊዜያችሁን በተሻለ መንገድ ተጠቀሙበት።—ኤፌ. 5:16
ውሳኔ ካደረግክ በኋላ ውሳኔህን ተግባራዊ የምታደርግበት ጊዜ መድብ፤ እንዲሁም የመደብከውን ጊዜ አክብረህ ሥራህን አከናውን። ውሳኔህን ተግባራዊ ለማድረግ፣ ሁሉ ነገር እስኪስተካከልልህ አትጠብቅ፤ እንዲህ ዓይነት ጊዜ ላታገኝ ትችላለህ። (መክ. 11:4) እምብዛም አስፈላጊ ያልሆኑ ነገሮች ጊዜህን እንዳይሻሙብህና ይበልጥ አስፈላጊ ለሆኑ ነገሮች የሚያስፈልግህን ጉልበት እንዳያሳጡህ ተጠንቀቅ። (ፊልጵ. 1:10) የሚቻል ከሆነ ሌሎች ነገሮች ትኩረትህን የማይከፋፍሉበትን ጊዜ ምረጥ። የምትሠራው ነገር እንዳለህና እንዳይረብሹህ ለሌሎች ተናገር። አስፈላጊ ከሆነም ስልክህን አጥፋ እንዲሁም በኢ-ሜይል ወይም በማኅበራዊ ድረ ገጽ የሚላኩልህን መልእክቶች ሌላ ጊዜ ተመልከት። ውሳኔህ የሚያስገኘው ውጤት፣ ጉዞ አድርገህ አንድ ቦታ ከመድረስ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ያሰብከው ቦታ ለመድረስ ከልብህ የምትፈልግ ከሆነ መንገዱ ቢዘጋና ሌላ መንገድ መጠቀም ቢያስፈልግህ እንኳ ጉዞህን አታቋርጥም። በተመሳሳይም ውሳኔያችን በሚያስገኘው ውጤት ላይ ትኩረት የምናደርግ ከሆነ እንቅፋት የሚሆኑ ነገሮች ቢያጋጥሙን እንኳ ቶሎ ተስፋ አንቆርጥም።—ገላ. 6:9፤ w19.11 30 አን. 17-18
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 8
የአምላክ ቃል [የልብን] ሐሳብና ዓላማ መረዳት ይችላል።—ዕብ. 4:12
ለመጠመቅ እንድትወስን የሚያነሳሳህ ምን ሊሆን ይገባል? መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት በማጥናትህ ስለ ይሖዋ ባሕርያትና ነገሮችን ስለሚያከናውንበት መንገድ ብዙ ትምህርት ቀስመሃል። ስለ ይሖዋ በተማርከው ነገር ልብህ ስለተነካ ለእሱ ጥልቅ ፍቅር አዳብረሃል። ለመጠመቅ እንድትወስን የሚያነሳሳህ ዋነኛ ምክንያት ለይሖዋ ያለህ ፍቅር መሆን ይኖርበታል። ለመጠመቅ እንድትወስን የሚያነሳሳህ ሌላው ምክንያት የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች መማርህና አምነህ መቀበልህ ነው። ኢየሱስ ለተከታዮቹ ሰዎችን ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ ተልእኮ በሰጠበት ወቅት ምን እንዳለ ልብ በል። (ማቴ. 28:19, 20) ኢየሱስ ሰዎች መጠመቅ ያለባቸው “በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም” እንደሆነ ተናግሯል። ታዲያ ይህ ምን ማለት ነው? በሙሉ ልብህ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ይሖዋ፣ ስለ ልጁ ስለ ኢየሱስና ስለ መንፈስ ቅዱስ የሚያስተምረውን እውነት ማመን አለብህ ማለት ነው። እነዚህ እውነቶች ልብህን የመንካት ከፍተኛ ኃይል አላቸው። w20.03 9 አን. 8-9
ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 9
በሥርዓት የማይሄዱትን አስጠንቅቋቸው፤ . . . ደካሞችን ደግፏቸው፤ ሁሉንም በትዕግሥት ያዙ።—1 ተሰ. 5:14
ይሖዋ፣ መላእክቱን የላከው ሎጥን እንዲያስጠነቅቁት ብቻ ሳይሆን በሰዶም ላይ ከሚመጣው ጥፋት ለማምለጥ እንዲረዱትም ጭምር ነበር። (ዘፍ. 19:12-14, 17) እኛም ወንድማችን የተሳሳተ አካሄድ እየተከተለ እንደሆነ ካስተዋልን ማስጠንቀቅ ያስፈልገን ይሆናል። የተሰጠውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምክር ተግባራዊ ለማድረግ ቢዘገይም እንኳ ትዕግሥት ማሳየት ይኖርብናል። እንደ ሁለቱ መላእክት እንሁን። ተስፋ ቆርጠን ከወንድማችን ከመራቅ ይልቅ እሱን መርዳት የምንችልባቸውን መንገዶች መፈለግ ይኖርብናል። (1 ዮሐ. 3:18) በምሳሌያዊ አነጋገር እጁን ይዘን ልንረዳው ማለትም የተሰጠውን መልካም ምክር በተግባር እንዲያውል እርዳታ ልናደርግለት ይገባል። ይሖዋ በሎጥ ድክመቶች ላይ ትኩረት ማድረግ ቢችልም እንዲህ አላደረገም። እንዲያውም ይሖዋ፣ ከጊዜ በኋላ ሐዋርያው ጴጥሮስ በመንፈስ መሪነት በጻፈው ደብዳቤ ላይ ሎጥን ጻድቅ ሰው ብሎ እንዲጠራው አድርጓል። (መዝ. 130:3) ታዲያ ይሖዋ ለሎጥ የነበረው ዓይነት አመለካከት ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው? ትኩረት የምናደርገው ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ባሏቸው መልካም ባሕርያት ላይ ከሆነ እነሱን በትዕግሥት መያዝ ይቀለናል። እነሱም የምንሰጣቸውን እርዳታ መቀበል አይከብዳቸውም። w19.06 21 አን. 6-7
ዓርብ፣ ታኅሣሥ 10
እያንዳንዱ የራሱን የኃላፊነት ሸክም ይሸከማል።—ገላ. 6:5
የምትኖርበት አገር መንግሥት በአምልኳችን ላይ እገዳ ቢጥል ‘ይሖዋን በነፃነት ማምለክ ወደሚቻልበት አገር ብሄድ ይሻል ይሆን?’ ብለህ ታስብ ይሆናል። ይህ የግል ውሳኔ ነው፤ ማንም ሰው ይህንን ሊወስንልህ አይችልም። አንዳንዶች፣ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች ስደት ሲደርስባቸው ያደረጉትን ነገር ያስታውሱ ይሆናል። በኢየሩሳሌም የነበሩት ደቀ መዛሙርት በይሁዳና በሰማርያ ክልሎች የተበተኑ ሲሆን እንዲያውም አንዳንዶች እስከ ፊንቄ፣ ቆጵሮስና አንጾኪያ ድረስ ሄደዋል። (ማቴ. 10:23፤ ሥራ 8:1፤ 11:19) ይሁንና በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች በሌላ ጊዜ ስደት ባጋጠማቸው ወቅት ሐዋርያው ጳውሎስ በስብከቱ ሥራ ላይ ተቃውሞ የተነሳበትን አካባቢ ለቆ ላለመሄድ ወስኗል። (ሥራ 14:19-23) ከእነዚህ ዘገባዎች ምን ትምህርት እናገኛለን? ወደ ሌላ ቦታ መሄድን በተመለከተ እያንዳንዱ የቤተሰብ ራስ የግሉን ውሳኔ ማድረግ አለበት። ውሳኔ ከማድረጉ በፊት ቤተሰቡ ስላለበት ሁኔታ እንዲሁም ወደ ሌላ አካባቢ መሄዳቸው ስለሚኖሩት ጥቅሞችና ጉዳቶች በጸሎትና በጥሞና ማሰብ አለበት። ሌሎች ምንም ዓይነት ውሳኔ ቢያደርጉ ልንተቻቸው አይገባም። w19.07 10 አን. 8-9
ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 11
ብቸኛው እውነተኛ አምላክ የሆንከውን አንተንና የላክኸውን ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ የዘላለም ሕይወት ነው።—ዮሐ. 17:3
ኢየሱስ “ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ” ብሎናል። (ማቴ. 28:19) የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪውን ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ የሚጠብቀው ምን እንደሆነ ከማስተማር ባለፈ፣ የኢየሱስን ትምህርት በሕይወቱ እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚችል እንዲያውቅ መርዳት ይኖርብናል። የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በተግባር ለማዋል ጥረት ሲያደርግ በትዕግሥት ልንረዳው ይገባል። አንዳንዶች በአመለካከታቸውና በልማዶቻቸው ላይ ለውጥ ለማድረግ ጥቂት ወራት ይበቋቸዋል። ሌሎች ግን ረዘም ያለ ጊዜ ያስፈልጋቸዋል። በፔሩ የነበረ አንድ ሚስዮናዊ ታጋሽ የመሆንን ጥቅም የሚያሳይ ሁኔታ አጋጥሞታል። እንዲህ ብሏል፦ “ራውል ከሚባል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቴ ጋር ሁለት መጻሕፍትን አጥንተን ጨርሰን ነበር። ሆኖም በሕይወቱ ውስጥ ከባድ ችግሮች ነበሩበት። ትዳሩ ውጥረት የነገሠበት ከመሆኑም ሌላ ተሳዳቢ ነበር፤ በዚህም ምክንያት ልጆቹ አያከብሩትም ነበር። ያም ቢሆን ወደ ስብሰባዎች አዘውትሮ ይመጣ ስለነበር እሱንም ሆነ ቤተሰቡን እየሄድኩ መርዳቴን ቀጠልኩ። ከራውል ጋር ከተገናኘን ከሦስት ዓመት በኋላ ለመጠመቅ ብቁ ሆነ።” w19.07 15 አን. 3፤ 19 አን. 15-17
እሁድ፣ ታኅሣሥ 12
ከፍተኛ ተጋድሎ አድርጉ።—ሉቃስ 13:24
ሐዋርያው ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች በጻፈበት ወቅት እያከናወናቸው ስለነበሩት ነገሮች ለማሰብ እንሞክር። በወቅቱ ሮም ውስጥ የቁም እስረኛ ነበር። ሰዎች ወዳሉበት ቦታ ሄዶ መስበክ አይችልም ነበር። ያም ቢሆን ሊጠይቁት ለሚመጡ ሰዎች በመመሥከርና ራቅ ባሉ ቦታዎች ለሚገኙ ጉባኤዎች ደብዳቤ በመጻፍ ተጠምዶ ነበር። እንደ ክርስቶስ ሁሉ እሱም እስከ መጨረሻው ተጋድሎ ማድረግ እንዳለበት ያውቅ ነበር። ጳውሎስ የክርስትናን ሕይወት ከሩጫ ውድድር ጋር ያመሳሰለው ለዚህ ነው። (1 ቆሮ. 9:24-27) በውድድር የሚሳተፍ አንድ ሯጭ በመጨረሻው መስመር ላይ ትኩረት የሚያደርግ ሲሆን ሌሎች ነገሮች ትኩረቱን እንዲከፋፍሉበትም አይፈቅድም። ለምሳሌ ያህል፣ በዛሬው ጊዜ ከተማ ውስጥ በሚደረጉ ውድድሮች የሚካፈሉ ሯጮች፣ በመንገዳቸው ላይ የንግድ ቦታዎችና ትኩረት የሚከፋፍሉ ሌሎች ነገሮች ያጋጥሟቸው ይሆናል። አንድ ሯጭ ሱቆች ውስጥ የተቀመጡ ዕቃዎችን ለማየት ሲል ሩጫውን የሚያቋርጥ ይመስልሃል? በውድድሩ ማሸነፍ ከፈለገ እንዲህ እንደማያደርግ የታወቀ ነው! እኛም በሕይወት ሩጫ ስንካፈል ትኩረታችን በሌሎች ነገሮች እንዳይከፋፈል ጥረት ማድረግ አለብን። ግባችን ላይ በማተኮር ልክ እንደ ጳውሎስ ከፍተኛ ተጋድሎ ካደረግን ሽልማቱን እናገኛለን! w19.08 3 አን. 4፤ 4 አን. 7
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 13
ለራስህና ለምታስተምረው ትምህርት ምንጊዜም ትኩረት ስጥ። . . . ይህን በማድረግ ራስህንም ሆነ የሚሰሙህን ታድናለህ።—1 ጢሞ. 4:16
ሕይወታችንን በአምላክ መሥፈርቶች መሠረት ለመምራት ጥረት ማድረግ ስንጀምር፣ የቤተሰባችን አባላት በምናምንባቸው ነገሮች ላይ እንዲሁም በሕይወታችን ውስጥ ያደረግነውን ለውጥ መቀበል ሊከብዳቸው ይችላል። ብዙውን ጊዜ መጀመሪያ ላይ የሚያስተውሉት ነገር አብረናቸው ሃይማኖታዊ በዓላትን ማክበር እንደተውንና በፖለቲካ ጉዳዮች እንደማንሳተፍ ነው። አንዳንድ የቤተሰባችን አባላት መጀመሪያ ላይ ይበሳጩብን ይሆናል። (ማቴ. 10:35, 36) ሆኖም አመለካከታቸውን ፈጽሞ እንደማይለውጡ ልናስብ አይገባም። የምናምንባቸውን ነገሮች እንዲረዱ ለማድረግ መጣራችንን ካቆምን፣ የዘላለም ሕይወት የማይገባቸው ሰዎች እንደሆኑ አድርገን የፈረድንባቸው ያህል ነው። ይሖዋ የመፍረድ ሥልጣን የሰጠው ለእኛ ሳይሆን ለኢየሱስ ነው። (ዮሐ. 5:22) ትዕግሥተኛ ከሆንን የቤተሰባችን አባላት ከጊዜ በኋላ መልእክታችንን ለማዳመጥ ፈቃደኛ ሊሆኑ ይችላሉ። ተቃውሞን መቋቋም ቢያስፈልገንም እንኳ ዘዴኛ ሆኖም ቆራጥ ልንሆን ይገባል። (1 ቆሮ. 4:12ለ) የቤተሰባችን አባላት፣ ይሖዋን ለማገልገል ያደረግነው ውሳኔ በቁም ነገር ያሰብንበት ጉዳይ እንደሆነ እስኪገነዘቡ ጊዜ ሊወስድ ይችላል። w19.08 17 አን. 10, 13፤ 18 አን. 14
ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 14
ኃይልን በሚሰጠኝ በእሱ አማካኝነት ለሁሉም ነገር የሚሆን ብርታት አለኝ።—ፊልጵ. 4:13
“በራሴ ቢሆን ኖሮ ያን ሁሉ ፈተና ልወጣው አልችልም ነበር” ያልክበት ጊዜ አለ? ብዙዎቻችን እንዲህ ተሰምቶን ያውቃል። ምናልባትም እንዲህ የተሰማህ፣ እንደ ከባድ ሕመም ወይም የሚወዱትን ሰው በሞት እንደ ማጣት ያሉ ችግሮችን ከተቋቋምክ በኋላ ሊሆን ይችላል። የደረሰብህን መከራ መለስ ብለህ ስታስብ፣ እያንዳንዷን ቀን ማለፍ የቻልከው የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ “ከሰብዓዊ ኃይል በላይ [የሆነ] ኃይል” ስለሰጠህ እንደሆነ ይሰማህ ይሆናል። (2 ቆሮ. 4:7-9) ይህ ክፉ ዓለም የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ለመቋቋምም የመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ያስፈልገናል። (1 ዮሐ. 5:19) ከዚህም በተጨማሪ “ከክፉ መንፈሳዊ ኃይሎች” ጋር እንታገላለን። (ኤፌ. 6:12) የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ፣ ተፈታታኝ ሁኔታዎች እያሉም እንኳ ኃላፊነቶቻችንን ለመወጣት የሚያስፈልገንን ኃይል ወይም ጥንካሬ በመስጠት ይረዳናል። ሐዋርያው ጳውሎስ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙትም በአገልግሎቱ መቀጠል የቻለው ‘በክርስቶስ ኃይል’ እንደሆነ ተሰምቶታል።—2 ቆሮ. 12:9፤ w19.11 8 አን. 1-3
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 15
እኔን ያየ ሁሉ አብንም አይቷል።—ዮሐ. 14:9
ኢየሱስ ስላደረገልህ ነገር ትክክለኛውን መረጃ ማግኘት የምትችለው ከመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው። ለኢየሱስ ፍቅር እያዳበርክ ስትሄድ ለይሖዋ ያለህ ፍቅር ያድጋል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ኢየሱስ የአባቱን ባሕርያት ፍጹም በሆነ መንገድ አንጸባርቋል። ስለዚህ ስለ ኢየሱስ ይበልጥ በተማርክ መጠን ስለ ይሖዋ ያለህ እውቀትና ለእሱ ያለህ አድናቆት እየጨመረ ይሄዳል። ለምሳሌ ኢየሱስ ሌሎች ለሚንቋቸው ሰዎች ማለትም ለድሆች፣ ለሕመምተኞችና ለደካሞች ርኅራኄ ያሳየው እንዴት እንደሆነ ለማሰብ ሞክር። በተጨማሪም ኢየሱስ ስለሰጠህ ጠቃሚ ምክር እንዲሁም ምክሩን በመስማትህ ሕይወትህ እንዴት እንደተሻሻለ አስብ። (ማቴ. 5:1-11፤ 7:24-27) ኢየሱስ ኃጢአታችን ይቅር እንዲባልልን ሲል ስለከፈለው መሥዋዕት በጥሞና ማሰብህ ለእሱ ያለህ ፍቅር ይበልጥ እንዲጨምር እንደሚያደርግ ጥያቄ የለውም። (ማቴ. 20:28) ኢየሱስ ለአንተ ሲል እንደሞተ መረዳትህ ንስሐ እንድትገባና የይሖዋን ይቅርታ እንድትፈልግ ሊያነሳሳህ ይችላል። (ሥራ 3:19, 20፤ 1 ዮሐ. 1:9) ለይሖዋና ለኢየሱስ ፍቅር ስታዳብር ደግሞ ይሖዋንና ኢየሱስን ከሚወዱ ሰዎች ጋር ለመቀራረብ መነሳሳትህ አይቀርም። w20.03 5-6 አን. 10-12
ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 16
ይሖዋ ከፍ ያለ ቢሆንም ትሑት የሆነውን ሰው ይመለከታል።—መዝ. 138:6
አንድ ክርስቲያን አንድን ሥራ ለማከናወን ከሁሉ የተሻለ ብቃት ያለው እሱ እንደሆነ ማሰብ ሊጀምር ይችላል። ወይም አንዲት ክርስቲያን ሚስት ‘የእኔ ባል ከወንድም እገሌ የተሻለ ብቃት አለው!’ ብላ ልታስብ ትችላለች። ትሑት ከሆንን ግን እንዲህ ያለ የኩራት መንፈስ በውስጣችን አይኖርም። ሙሴ፣ ሌሎች ሰዎች መብት ሲያገኙ ከሰጠው ምላሽ ትልቅ ትምህርት ማግኘት እንችላለን። ሙሴ የእስራኤልን ብሔር እንዲመራ ለተሰጠው ኃላፊነት አድናቆት ነበረው። ሆኖም ይሖዋ ሌሎች አገልጋዮቹ የሙሴን ሥራ እንዲጋሩ ሲፈቅድ ሙሴ ምን ተሰማው? ቅናት አላደረበትም። (ዘኁ. 11:24-29) ሕዝቡን በመዳኘቱ ሥራ ሌሎችም እንዲያግዙት የተደረገውን ዝግጅት በትሕትና ተቀብሏል። (ዘፀ. 18:13-24) ይህ ዝግጅት እስራኤላውያን የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኙ ያደርጋል። ከዚህ አንጻር፣ ሙሴ ይህን ዝግጅት በትሕትና መቀበሉ ከመብቱ ይልቅ ለሌሎች ጥቅም እንደሚያስብ ያሳያል። እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል! ይሖዋ እንዲጠቀምብን ከፈለግን ትሕትናችን ከችሎታችን ልቆ መታየት እንዳለበት እናስታውስ። w19.09 5-6 አን. 13-14
ዓርብ፣ ታኅሣሥ 17
ይሖዋ ታማኞችን ይጠብቃል።—መዝ. 31:23
መንግሥታት በታላቂቱ ባቢሎን ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ምክንያት አድርገው የሚያቀርቡት ነገር ምን እንደሆነ አናውቅም። መንግሥታት፣ የዓለም ሃይማኖቶች ለሰላም እንቅፋት እንደሆኑና በፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ ሁልጊዜ እጃቸውን እንደሚያስገቡ ይናገሩ ይሆናል። አሊያም ደግሞ እነዚህ የሃይማኖት ድርጅቶች ከልክ ያለፈ ሀብትና ንብረት እንዳካበቱ ይገልጹ ይሆናል። (ራእይ 18:3, 7) በዚህ ጥቃት የሚጠፉት የእነዚህ ሃይማኖቶች አባላት በሙሉ እንዳልሆኑ ማሰቡ ምክንያታዊ ይመስላል። መንግሥታት በሚሰነዝሩት ጥቃት የሚጠፉት የሃይማኖት ድርጅቶቹ ሳይሆኑ አይቀሩም። እነዚህ የሃይማኖት ድርጅቶች ከጠፉ በኋላ የቀድሞ አባሎቻቸው፣ የሃይማኖት መሪዎቻቸው እንዳታለሏቸው ስለሚገነዘቡ ከእነዚህ ሃይማኖቶች ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌላቸው ይገልጹ ይሆናል። የታላቂቱ ባቢሎን ጥፋት በአንጻራዊ ሁኔታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይፈጸማል። (ራእይ 18:10, 21) ይሖዋ፣ ‘ምርጦቹ’ እና እውነተኛው ሃይማኖት ከጥፋቱ እንዲተርፉ ሲል የመከራው ‘ቀኖች እንዲያጥሩ’ እንደሚያደርግ ቃል ገብቷል።—ማር. 13:19, 20፤ w19.10 15 አን. 4-5
ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 18
ወጣት ሴቶችን . . . ልጆቻቸውን [እንዲወዱ ይምከሯቸው]።—ቲቶ 2:4
እናቶች፣ ወላጆቻችሁ በቀላሉ ቱግ የሚሉና ልጆቻቸውን ደግነት በጎደለው መንገድ የሚናገሩ ሊሆኑ ይችላሉ። እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ ማደጋችሁ ልጆችን እንዲህ ባለ መንገድ መያዝ ምንም ችግር እንደሌለው እንዲሰማችሁ አድርጓችሁ ይሆናል። የይሖዋን መሥፈርቶች ከተማራችሁ በኋላም እንኳ ልጆቻችሁን በተረጋጋ መንፈስ ማናገር ተፈታታኝ ሊሆንባችሁ ይችላል፤ በተለይ ደክሟችሁ ባለበት ሰዓት ልጆቻችሁ የሚያበሳጭ ነገር ሲያደርጉ እነሱን በትዕግሥት መያዝ ይበልጥ ከባድ እንደሚሆንባችሁ የታወቀ ነው። (ኤፌ. 4:31) እንዲህ ባሉ ጊዜያት ወደ ይሖዋ በመጸለይ የእሱን እርዳታ መጠየቃችሁ በጣም አስፈላጊ ነው። (መዝ. 37:5) አንዳንድ እናቶች ለልጆቻቸው ፍቅራቸውን መግለጽ ይከብዳቸዋል። ምናልባትም እነዚህ እናቶች ያደጉት በወላጆችና በልጆች መካከል ጥሩ ግንኙነት በሌለበት ቤተሰብ ውስጥ ሊሆን ይችላል። እናንተም ያደጋችሁት እንዲህ ባለ ቤተሰብ ውስጥ ከሆነ የወላጆቻችሁን ስህተት ላለመድገም ጥንቃቄ አድርጉ። ለይሖዋ ፈቃድ የምትገዛ እናት ለልጆቿ ፍቅር መግለጽን መማር ይኖርባታል። እርግጥ ለውጥ ማድረግ ይከብዳት ይሆናል። ሆኖም ይህ ከአቅም በላይ የሆነ ነገር አይደለም። ደግሞም እነዚህን ለውጦች ማድረጓ ራሷንም ሆነ ቤተሰቧን ይጠቅማል። w19.09 18-19 አን. 19-20
እሁድ፣ ታኅሣሥ 19
ለሁለት ጌቶች ባሪያ ሆኖ መገዛት የሚችል ማንም የለም።—ማቴ. 6:24
በአንድ በኩል ይሖዋን እያመለከ በሌላ በኩል ደግሞ ሀብት ለማካበት ከፍተኛ ጥረት የሚያደርግና ብዙ ጊዜ የሚያባክን ሰው፣ ሁለት ጌቶችን ለማገልገል እየሞከረ ነው ሊባል ይችላል። እንዲህ ያለው ሰው ይሖዋን ብቻ እያመለከ ነው ማለት አይቻልም። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. መገባደጃ አካባቢ በሎዶቅያ ከተማ የሚገኘው ጉባኤ አባላት “ሀብታም ነኝ፤ ደግሞም ብዙ ሀብት አከማችቻለሁ፤ ምንም ነገር አያስፈልገኝም” ብለው ይኩራሩ ነበር። ይሖዋና ኢየሱስ ግን “ጎስቋላ፣ ምስኪን፣ ድሃ፣ ዕውርና [የተራቆቱ]” እንደሆኑ አድርገው ይመለከቷቸው ነበር። ኢየሱስ ለእነዚህ ክርስቲያኖች ምክር የሰጣቸው፣ ሀብታም በመሆናቸው ሳይሆን ለገንዘብ ያላቸው ፍቅር ከይሖዋ ጋር ያላቸውን ዝምድና እያበላሸባቸው ስለነበር ነው። (ራእይ 3:14-17) ሀብት የማካበት ፍላጎት በልባችን ውስጥ እያቆጠቆጠ እንደሆነ ካስተዋልን አስተሳሰባችንን ለማስተካከል አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል። (1 ጢሞ. 6:7, 8) እንዲህ ዓይነት እርምጃ ካልወሰድን ልባችን ይከፋፈላል፤ ይሖዋም ለእሱ የምናቀርበውን አምልኮ አይቀበልም። ይሖዋ የሚፈልገው “እሱ ብቻ እንዲመለክ” ነው።—ዘዳ. 4:24፤ w19.10 27 አን. 5-6
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 20
ሰዎች ከአምላክ የተቀበሉትን ትንቢት በመንፈስ ቅዱስ ተገፋፍተው ተናገሩ።—2 ጴጥ. 1:21
“ተገፋፍተው” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ቀጥተኛ ፍቺው “ተነድተው” የሚል ነው። የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍን የጻፈው ሉቃስ ‘በነፋስ እየተነዳ’ ስለሚሄድ መርከብ ሲጽፍ ይህን የግሪክኛ ቃል በሌላ መልኩ ተጠቅሞበታል። (ሥራ 27:15) በመሆኑም ሐዋርያው ጴጥሮስ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች “ተነድተው” እንደጻፉ ሲናገር “ከባሕር ጉዞ ጋር የተያያዘ ትኩረት የሚስብ ዘይቤያዊ አገላለጽ” መጠቀሙ እንደሆነ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር ገልጸዋል። ጴጥሮስ አንድ መርከብ በነፋስ እየተነዳ ጉዞውን እንደሚያጠናቅቅ ሁሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ነቢያትና ጸሐፊዎችም በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ሥራቸውን ዳር ማድረስ እንደቻሉ መግለጹ ነበር። “ነቢያቱ ነፋሱ እንዲነዳቸው ሸራቸውን የወጠሩ ያህል ነው” በማለት እኚሁ ምሁር ተናግረዋል። ይሖዋ የራሱን ድርሻ ተወጥቷል። “ነፋሱን” ይኸውም መንፈስ ቅዱስን ሰጥቷቸዋል። የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎችም የሚጠበቅባቸውን አድርገዋል። ይኸውም የመንፈስ ቅዱስን አመራር በመከተል ሥራቸውን አከናውነዋል። በማዕበል በሚናወጥ ባሕር ላይ የሚጓዝ መርከብ፣ ወደሚፈልገው አቅጣጫ የሚነፍስ ነፋስ ካጋጠመው በሰላም ወደ ወደብ መድረስ እንደሚችል ሁሉ መንፈስ ቅዱስም እንደ ማዕበል ያሉ ፈተናዎችን ተቋቁመን፣ አምላክ ቃል ወደገባልን አዲስ ዓለም እንድንገባ ይረዳናል። w19.11 9 አን. 7-9
ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 21
በመከራ ቀን ተስፋ የምትቆርጥ ከሆነ ጉልበትህ እጅግ ይዳከማል።—ምሳሌ 24:10
አንዳንድ ጊዜ ችግሮች ሲያጋጥሙን ተስፋ እንቆርጥ ይሆናል። ይሁን እንጂ ችግሮቻችን አስተሳሰባችንን እንዲቆጣጠሩት መፍቀድ አይኖርብንም። እንዲህ ካደረግን ይሖዋ የሰጠን አስደናቂ ተስፋ ሊደበዝዝብን ይችላል። (ራእይ 21:3, 4) በዚህም የተነሳ ተስፋ ልንቆርጥ እንችላለን፤ ይህ ደግሞ ኃይላችንን ሊያሟጥጠውና ይሖዋን ማገልገላችንን እንድናቆም ሊያደርገን ይችላል። በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖር አንዲት እህት በጠና የታመመ ባለቤቷን ትንከባከባለች፤ ይህች እህት እምነቷ ጠንካራ ሆኖ እንዲቀጥል ያደረገችው እንዴት እንደሆነ እንመልከት። እንዲህ ስትል ጽፋለች፦ “ያለንበት ሁኔታ አንዳንድ ጊዜ ውጥረት የሚፈጥርና ተስፋ አስቆራጭ ነው፤ ያም ቢሆን በተስፋችን ላይ ጠንካራ እምነት አለን። ከድርጅቱ ለምናገኛቸው እምነት የሚያጠናክሩና የሚያበረታቱ ትምህርቶች በጣም አመስጋኝ ነኝ። እንዲህ ያለውን ምክርና ማበረታቻ ማግኘታችን በጣም ጠቅሞናል። እንድንጸና እንዲሁም [ፈተናዎችን] እንድንቋቋም ይረዳናል።” ይህች እህት የሰጠችው ሐሳብ፣ የተስፋ መቁረጥ ስሜትን መቋቋም እንደምንችል ያስተምረናል። ይህን ስሜት መቋቋም የምንችለው እንዴት ነው? የሚያጋጥሙንን ችግሮች የሰይጣን ፈተና አድርገን እንመልከታቸው። ይሖዋ መጽናኛ እንደሚሰጠን አንዘንጋ። እንዲሁም ይሖዋ ለሚያዘጋጅልን መንፈሳዊ ምግብ አድናቆት ይኑረን። w19.11 16 አን. 9-10
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 22
እምነት የሚጣልበት ሰው . . . ሚስጥር ይጠብቃል።—ምሳሌ 11:13
በተለይ ሽማግሌዎች ይህን መሠረታዊ ሥርዓት በሥራ ላይ ማዋል አለባቸው። ሽማግሌዎች የወንድሞቻቸውንና የእህቶቻቸውን ሚስጥር ማውጣት እንደሌለባቸው ያውቃሉ። ሽማግሌዎች ሚስጥር ካባከኑ የወንድሞችን እምነት ያጣሉ፤ እንዲሁም መልካም ስማቸው ይጎድፋል። በጉባኤ ውስጥ ኃላፊነት የተሰጣቸው ወንድሞች “በሁለት ምላስ የማይናገሩ” ወይም በአንደበታቸው የማያታልሉ ሊሆኑ ይገባል። (1 ጢሞ. 3:8 ግርጌ) ይህም ሲባል መሠሪ ወይም ሐሜተኛ ሊሆኑ አይገባም ማለት ነው። አንድ ሽማግሌ ሚስቱን የሚወድ ከሆነ የማያስፈልጋትን መረጃ በመስጠት ሸክም አይጨምርባትም። የአንድ ሽማግሌ ሚስት ባለቤቷ በሚስጥር መያዝ ያለባቸውን ነገሮች እንዲነግራት ባለመገፋፋት ባለቤቷ መልካም ስሙን ይዞ እንዲቀጥል ልትረዳው ትችላለች። አንዲት ሚስት ይህን ምክር ተግባራዊ የምታደርግ ከሆነ ባለቤቷን እንደምትደግፍ ብሎም ሚስጥራቸውን ለነገሩት ወንድሞች አክብሮት እንዳላት ታሳያለች። ከሁሉም በላይ ደግሞ የጉባኤው ሰላምና አንድነት እንዲጠበቅ አስተዋጽኦ በማድረጓ ይሖዋን ታስደስታለች።—ሮም 14:19፤ w20.03 22 አን. 13-14
ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 23
ይሖዋ . . . ለእናንተ ይገለጣል።—ዘሌ. 9:4
በ1512 ዓ.ዓ. በሲና ተራራ ግርጌ ላይ የማደሪያው ድንኳን በተተከለበት ወቅት አሮንና ልጆቹ ካህናት ሆነው ሲሾሙ ሥርዓቱን የመራው ሙሴ ነበር። (ዘፀ. 40:17፤ ዘሌ. 9:1-5) ይሖዋ አዲስ የተቋቋመውን የክህነት ሥርዓት እንደተቀበለው ያሳየው እንዴት ነው? አሮንና ሙሴ ሕዝቡን ሲባርኩ ይሖዋ በመሠዊያው ላይ የቀረውን ነገር በሙሉ እሳት እንዲበላው አደረገ። (ዘሌ. 9:23, 24) ሊቀ ካህናቱ በተሾመበት ወቅት ይሖዋ ያደረገው አስደናቂ ነገር ምን ትርጉም አለው? በዚህ መንገድ ይሖዋ የአሮንን የክህነት ሥርዓት ሙሉ በሙሉ እንደሚደግፈው አሳይቷል። እስራኤላውያን፣ ይሖዋ ካህናቱን እንደሚደግፍ የሚያሳየውን ግልጽ ማስረጃ መመልከታቸው እነሱም ይህን ዝግጅት ሊደግፉ እንደሚገባ አስገንዝቧቸው መሆን አለበት። ታዲያ ይህ ትኩረታችንን ሊስብ የሚገባ ነገር ነው? አዎ! በእስራኤል የነበረው የክህነት ሥርዓት ከዚያ ለላቀ ክህነት ማለትም ከክርስቶስ ጋር በሰማይ ለሚያገለግሉት 144,000 ካህናት ጥላ ነበር። (ዕብ. 4:14፤ 8:3-5፤ 10:1) በእርግጥም ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ድርጅቱን እየመራና አትረፍርፎ እየባረከ ነው። w19.11 23 አን. 13፤ 24 አን. 14, 16
ዓርብ፣ ታኅሣሥ 24
ብዙ ወጪ በማስወጣት በማናችሁም ላይ ሸክም ላለመሆን ሌት ተቀን በመሥራት እንደክምና እንለፋ ነበር።—2 ተሰ. 3:8
ሐዋርያው ጳውሎስ፣ በቆሮንቶስ በነበረበት ወቅት አቂላ እና ጵርስቅላ ቤት አርፎ “አብሯቸው ይሠራ ነበር፤ ሙያቸውም ድንኳን መሥራት ነበር።” በእርግጥ ጳውሎስ “ሌት ተቀን” እንደሠራ ሲናገር ያለእረፍት እንደሠራ መግለጹ አልነበረም። በሰንበት ቀን እና በሌሎች ጊዜያት ከሥራው ያርፍ ነበር። በዚያ ዕለት እረፍት ማድረጉ፣ እንደ እሱ በሰንበት ከሥራቸው ለሚያርፉት አይሁዳውያን ለመመሥከር አጋጣሚ ሰጥቶታል። (ሥራ 13:14-16, 42-44፤ 16:13፤ 18:1-4) ጳውሎስ ሰብዓዊ ሥራ መሥራት የነበረበት ቢሆንም “የአምላክን ምሥራች በማወጁ ቅዱስ ሥራ” አዘውትሮ ይካፈል ነበር። (ሮም 15:16፤ 2 ቆሮ. 11:23) ሌሎችም እንዲሁ እንዲያደርጉ አበረታቷል። አቂላና ጵርስቅላ ‘በክርስቶስ ኢየሱስ አብረውት የሚሠሩ’ የሥራ ባልደረቦቹ ነበሩ። (ሮም 12:11፤ 16:3) ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችን “የጌታ ሥራ የበዛላችሁ ሁኑ” በማለት አሳስቧቸዋል። (1 ቆሮ. 15:58፤ 2 ቆሮ. 9:8) እንዲያውም “መሥራት የማይፈልግ ሁሉ አይብላ” በማለት በይሖዋ መንፈስ መሪነት ጽፏል።—2 ተሰ. 3:10፤ w19.12 5 አን. 12-13
ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 25
ልጆች ከይሖዋ የተገኙ ውርሻ ናቸው።—መዝ. 127:3
ይሖዋ የመጀመሪያዎቹን ባልና ሚስት የፈጠራቸው ልጅ የመውለድ ፍላጎት እንዲኖራቸው አድርጎ ነው። ይሁንና ‘ልጅ እንውለድ ወይስ አንውለድ? የምንወልድ ከሆነስ መቼ?’ የሚለውን ጉዳይ መወሰን ያለበት ማን ነው? በአንዳንድ ባሕሎች፣ አንድ ወንድና ሴት ከተጋቡ በኋላ ብዙም ሳይቆዩ ልጅ እንዲወልዱ ይጠበቅባቸዋል። ባልና ሚስቱ፣ የቤተሰባቸው አባላት ወይም ሌሎች ሰዎች ይህን ባሕል እንዲከተሉ ጫና እንዳደረጉባቸው ይሰማቸው ይሆናል። ጄትሮ የተባለ በእስያ የሚኖር አንድ ወንድም “በጉባኤያችን ውስጥ የሚገኙ ልጅ ያላቸው አንዳንድ ባለትዳሮች፣ ልጅ የሌላቸውን ባልና ሚስት እንዲወልዱ ይገፋፏቸዋል” ሲል ተናግሯል። ጄፍሪ የተባለ በእስያ የሚገኝ ሌላ ወንድም ደግሞ ያስተዋለውን ሲናገር “አንዳንዶች ልጅ ላልወለዱ ባለትዳሮች፣ ሲያረጁ የሚጦራቸው እንደሌለ ይነግሯቸዋል” ብሏል። ያም ሆኖ ልጅ መውለድ ይኖርባቸው እንደሆነና እንዳልሆነ መወሰን ያለባቸው ባለትዳሮቹ ራሳቸው ናቸው። አዎ፣ ይህን ውሳኔ ማድረግ የእነሱ ኃላፊነት ነው። (ገላ. 6:5) እርግጥ ነው፣ የአዲስ ተጋቢዎቹ ጓደኞችና ቤተሰቦች ባለትዳሮቹ ደስተኛ እንዲሆኑ ይፈልጋሉ። ሆኖም እነዚህ ሰዎች፣ ልጅ መውለድን ወይም አለመውለድን በተመለከተ ውሳኔ ማድረግ ያለባቸው ራሳቸው ጥንዶቹ እንደሆኑ ማስታወስ አለባቸው።—1 ተሰ. 4:11፤ w19.12 22 አን. 1-3
እሁድ፣ ታኅሣሥ 26
እንግዲያው እናንተ በዚህ መንገድ ጸልዩ፦ “. . . አባታችን ሆይ።”—ማቴ. 6:9
አምላክን እንደ አባትህ አድርገህ ማየት ይከብድሃል? አንዳንዶች፣ ከይሖዋ አንጻር እነሱ በጣም ኢምንት እና እዚህ ግቡ የማይባሉ እንደሆኑ ይሰማቸዋል። ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ በግለሰብ ደረጃ እንደሚያስብላቸው መቀበል ይቸግራቸዋል። ይሁንና አፍቃሪው አባታችን እንዲህ እንዲሰማን አይፈልግም። ሕይወት የሰጠን ከመሆኑም ሌላ ከእሱ ጋር ወዳጅነት እንድንመሠርት ይፈልጋል። ሐዋርያው ጳውሎስ በአቴንስ ለነበሩ አድማጮቹ ይህን እውነታ ከተናገረ በኋላ ይሖዋ “ከእያንዳንዳችን የራቀ . . . አይደለም” ብሏቸዋል። (ሥራ 17:24-29) አንድ ልጅ የሚወደውንና የሚያስብለትን አባቱን በነፃነት እንደሚያናግረው ሁሉ አምላክም ሁላችንም ወደ እሱ ቀርበን በነፃነት እንድናነጋግረው ይፈልጋል። ሌሎች ደግሞ ሰብዓዊ አባታቸው ፍቅርና አሳቢነት አሳይቷቸው ስለማያውቅ ይሖዋን እንደ አባታቸው አድርገው መመልከት ይከብዳቸዋል። አንዲት እህት እንዲህ ብላለች፦ “አባቴ በጣም የሚጎዳ ነገር ይናገረኝ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ስጀምር ይሖዋን እንደ ሰማያዊ አባቴ ተመልክቼ ወደ እሱ መቅረብ ከብዶኝ ነበር።” አንተስ እንደዚህ ይሰማሃል? ከሆነ ይሖዋ ከሁሉ የተሻለ አባት መሆኑን በጊዜ ሂደት እንደምትገነዘብ እርግጠኛ ሁን። w20.02 3 አን. 4-5
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 27
ጉልበቴ በሚያልቅበት ጊዜም አትተወኝ።—መዝ. 71:9
ዕድሜያችን እየገፋ ሲሄድ ችሎታችን ወይም የምናከናውነው ሥራ በጣም ውስን እንደሆነ ቢሰማንም እንኳ ይሖዋ በእሱ አገልግሎት የምናደርገውን ተሳትፎ ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው ኢየሱስ አስተምሮናል። (መዝ. 92:12-15፤ ሉቃስ 21:2-4) ስለዚህ ማከናወን በምትችለው ነገር ላይ ትኩረት አድርግ። ለምሳሌ ስለ ይሖዋ ለሰዎች መናገር፣ ለወንድሞችህ መጸለይ እንዲሁም በታማኝነት እንዲጸኑ ሌሎችን ማበረታታት ትችላለህ። ይሖዋ የሥራ አጋሩ አድርጎ የሚመለከትህ ብዙ ነገር ማከናወን ስለቻልክ ሳይሆን በደስታ ስለምትታዘዘው ነው። (1 ቆሮ. 3:5-9) በእርግጥም አገልጋዮቹን ከፍ አድርጎ የሚመለከት እንደ ይሖዋ ያለ አምላክ ስላለን አመስጋኞች ነን! ይሖዋ የፈጠረን የእሱን ፈቃድ እንድናደርግ ነው፤ ደግሞም ሕይወታችን ትርጉም የሚኖረው በእውነተኛው አምልኮ ስንካፈል ነው። (ራእይ 4:11) ዓለም ዋጋ እንደሌለን አድርጎ ቢመለከተንም ይሖዋ ፈጽሞ በእኛ አያፍርም። (ዕብ. 11:16, 38) በሕመም፣ በኢኮኖሚ ችግር ወይም በዕድሜ መግፋት የተነሳ መንፈሳችን ሲደቆስ፣ ከሰማያዊው አባታችን ፍቅር ሊለየን የሚችል አንዳች ነገር እንደሌለ እናስታውስ።—ሮም 8:38, 39፤ w20.01 18 አን. 16፤ 19 አን. 18-19
ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 28
አምላክ ሆይ፣ ንጹሕ ልብ ፍጠርልኝ፤ በውስጤም ጽኑ የሆነ አዲስ መንፈስ አኑር።—መዝ. 51:10
ትሑት ለመሆንና ባለን ነገር ረክተን ለመኖር ጥረት በማድረግ ምቀኝነትን መዋጋት እንችላለን። ልባችን በእነዚህ መልካም ባሕርያት ሲሞላ ምቀኝነት ቦታ አያገኝም። ትሕትና ስለ ራሳችን ከሚገባው በላይ እንዳናስብ ይረዳናል። ትሑት የሆነ ሰው ከሌሎች የበለጠ ማግኘት እንደሚገባው አይሰማውም። (ገላ. 6:3, 4) ባለው ነገር የሚረካ ሰው ደግሞ ራሱን ከሌሎች ጋር አያወዳድርም። (1 ጢሞ. 6:7, 8) ትሑት የሆነና ባለው ነገር የሚረካ ሰው ሌሎች ጥሩ ነገር ሲያገኙ ከእነሱ ጋር አብሮ ይደሰታል። የሥጋ ሥራ የሆነውን ምቀኝነትን አስወግደን በምትኩ ትሕትናን እና ባለን የመርካት ባሕርይን ለማዳበር የአምላክ ቅዱስ መንፈስ እርዳታ ያስፈልገናል። (ገላ. 5:16፤ ፊልጵ. 2:3, 4) የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ውስጣዊ ሐሳባችንን እና ዝንባሌያችንን ለመመርመር ሊረዳን ይችላል። በአምላክ እርዳታ፣ መጥፎ ሐሳቦችንና ስሜቶችን በሚያንጹ ነገሮች መተካት እንችላለን።—መዝ. 26:2፤ w20.02 15 አን. 8-9
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 29
ለራስህና ለምታስተምረው ትምህርት ምንጊዜም ትኩረት ስጥ።—1 ጢሞ. 4:16
ራስን መወሰን ስእለት ነው፤ ይሖዋም ይህን ስእለትህን እንድትፈጽም ይጠብቅብሃል። ስለዚህ ከጉባኤው ጋር ተቀራርበህ ኑር። በጉባኤው ውስጥ ያሉ ወንድሞችና እህቶች መንፈሳዊ ቤተሰቦችህ ናቸው። በስብሰባዎች ላይ አዘውትረህ በመገኘት ከእነሱ ጋር ያለህን ወዳጅነት ማጠናከር ትችላለህ። በየዕለቱ የአምላክን ቃል አንብብ እንዲሁም ባነበብከው ነገር ላይ አሰላስል። (መዝ. 1:1, 2) ስላነበብከው ነገር ጊዜ ወስደህ በጥልቀት አስብ። ይህም ያነበብከው ሐሳብ ልብህን እንዲነካው ያስችላል። በተጨማሪም ‘ሳታሰልስ ጸልይ።’ (ማቴ. 26:41) ልባዊ ጸሎት ማቅረብህ ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድትቀርብ ይረዳሃል። ‘ከሁሉ አስቀድመህ የአምላክን መንግሥት ፈልግ።’ (ማቴ. 6:33) ይህን ማድረግ የምትችለው በሕይወትህ ውስጥ ለስብከቱ ሥራ ቅድሚያ በመስጠት ነው። አዘውትረህ በአገልግሎት መካፈልህ እምነትህ ጠንካራ ሆኖ እንዲቀጥል ይረዳሃል። በዚህ አሮጌ ዓለም ውስጥ የሚያጋጥምህ ማንኛውም ፈተና “ጊዜያዊና ቀላል” ነው። (2 ቆሮ. 4:17) በአንጻሩ ግን ራስህን መወሰንህና መጠመቅህ በአሁኑ ጊዜ አርኪ የሆነ ሕይወት፣ ወደፊት ደግሞ “እውነተኛ የሆነውን ሕይወት” እንድታገኝ መንገድ ይከፍትልሃል። በእርግጥም ይህን ማድረጉ በጭራሽ አያስቆጭም!—1 ጢሞ. 6:19፤ w20.03 13 አን. 19-21
ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 30
የቀረው ጊዜ አጭር [ነው]።—1 ቆሮ. 7:29
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትህ ደረጃ በደረጃ እድገት እያደረገ ካልሆነ ‘ጥናቱን ባቆም ይሻል ይሆን?’ በሚለው ጥያቄ ላይ ቆም ብለህ ማሰብ ሊያስፈልግህ ይችላል። ሁኔታውን በምትገመግምበት ጊዜ ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቴ ካለበት ሁኔታ አንጻር የሚጠበቀውን ያህል እድገት እያደረገ ነው? የተማራቸውን ነገሮች “መጠበቅ” ማለትም ተግባራዊ ማድረግ ጀምሯል?’ (ማቴ. 28:20) የሚያሳዝነው አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች በሕዝቅኤል ዘመን እንደነበሩት እስራኤላውያን ናቸው። ይሖዋ እነዚህን እስራኤላውያን በተመለከተ ሕዝቅኤልን እንዲህ ብሎታል፦ “እነሆ፣ አንተ ለእነሱ ባማረ ድምፅ እንደሚዘፈንና በባለ አውታር መሣሪያ አሳምረው እንደሚጫወቱት የፍቅር ዘፈን ሆነህላቸዋል። ቃልህን ይሰማሉ፤ ሆኖም አንዳቸውም አያደርጉትም።” (ሕዝ. 33:32) ጥናታችንን ከአሁን በኋላ እንደማናስጠናው መንገር ሊከብደን ይችላል። ይሁንና “የቀረው ጊዜ አጭር መሆኑን” አንዘንጋ። እድገት የማያደርግ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በማስጠናት ጊዜያችንን ከማባከን ይልቅ “ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ” እንዳላቸው በግልጽ የሚያሳዩ ሰዎችን በመፈለግ ላይ ትኩረት ልናደርግ ይገባል።—ሥራ 13:48፤ w20.01 6 አን. 17፤ 7 አን. 20
ዓርብ፣ ታኅሣሥ 31
መንግሥትህ ይምጣ። ፈቃድህ በሰማይ እየተፈጸመ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ ይፈጸም።—ማቴ. 6:10
በጥቅሉ ሲታይ የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች ታዛዥ የሰው ልጆች ወደፊት በምድር ላይ ለዘላለም እንደሚኖሩ የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት አያስተምሩም። (2 ቆሮ. 4:3, 4) በዛሬው ጊዜ አብዛኞቹ የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች ጥሩ ሰዎች ሁሉ ሲሞቱ ወደ ሰማይ እንደሚሄዱ ያስተምራሉ። በ1800ዎቹ መገባደጃ ላይ መጠበቂያ ግንብ የተባለውን መጽሔት ያዘጋጁ የነበሩት አነስተኛ ቁጥር ያላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ግን ከዚህ የተለየ አመለካከት ነበራቸው። አምላክ በምድር ላይ ገነትን መልሶ እንደሚያቋቁምና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ታዛዥ ሰዎች በሰማይ ላይ ሳይሆን በዚህችው ምድር ላይ ለዘላለም እንደሚኖሩ ተገንዝበው ነበር። ሆኖም የእነዚህን ታዛዥ ሰዎች ማንነት በትክክል ለመረዳት የተወሰነ ጊዜ ወስዶባቸዋል። እርግጥ ነው፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ‘ከምድር የተዋጁ’ የተወሰኑ ሰዎች ከኢየሱስ ጋር በሰማይ እንደሚገዙም ከቅዱሳን መጻሕፍት ተረድተው ነበር። (ራእይ 14:3) ይህ ቡድን በምድር ላይ ሳሉ ራሳቸውን ወስነው አምላክን በቅንዓትና በታማኝነት ያገለገሉ 144,000 ክርስቲያኖችን ያቀፈ ነው። w19.09 27 አን. 4-5