የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • es21 ገጽ 88-97
  • መስከረም

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • መስከረም
  • ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2021
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ረቡዕ፣ መስከረም 1
  • ሐሙስ፣ መስከረም 2
  • ዓርብ፣ መስከረም 3
  • ቅዳሜ፣ መስከረም 4
  • እሁድ፣ መስከረም 5
  • ሰኞ፣ መስከረም 6
  • ማክሰኞ፣ መስከረም 7
  • ረቡዕ፣ መስከረም 8
  • ሐሙስ፣ መስከረም 9
  • ዓርብ፣ መስከረም 10
  • ቅዳሜ፣ መስከረም 11
  • እሁድ፣ መስከረም 12
  • ሰኞ፣ መስከረም 13
  • ማክሰኞ፣ መስከረም 14
  • ረቡዕ፣ መስከረም 15
  • ሐሙስ፣ መስከረም 16
  • ዓርብ፣ መስከረም 17
  • ቅዳሜ፣ መስከረም 18
  • እሁድ፣ መስከረም 19
  • ሰኞ፣ መስከረም 20
  • ማክሰኞ፣ መስከረም 21
  • ረቡዕ፣ መስከረም 22
  • ሐሙስ፣ መስከረም 23
  • ዓርብ፣ መስከረም 24
  • ቅዳሜ፣ መስከረም 25
  • እሁድ፣ መስከረም 26
  • ሰኞ፣ መስከረም 27
  • ማክሰኞ፣ መስከረም 28
  • ረቡዕ፣ መስከረም 29
  • ሐሙስ፣ መስከረም 30
ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2021
es21 ገጽ 88-97

መስከረም

ረቡዕ፣ መስከረም 1

አባቴ እስካሁን እየሠራ ነው፤ እኔም እሠራለሁ።—ዮሐ. 5:17

ይሖዋ እና ኢየሱስ ተግቶ በመሥራት ረገድ የተዉት ምሳሌ እረፍት ማድረግ እንደማያስፈልገን የሚያሳይ ነው? በፍጹም። ይሖዋ ፈጽሞ ስለማይደክመው እረፍት ማድረግ አያስፈልገውም። በእርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ ሰማያትንና ምድርን ከፈጠረ በኋላ ‘ሥራውን እንዳቆመና እንዳረፈ’ ይናገራል። (ዘፀ. 31:17) ሆኖም ይህ ሐሳብ ይሖዋ ሥራውን ቆም አድርጎ፣ ያከናወነውን ነገር በመመልከት በሥራው እንደተደሰተ የሚጠቁም ሳይሆን አይቀርም። ኢየሱስም ቢሆን ምድር ላይ ሳለ ተግቶ ቢሠራም እረፍት ለማድረግና ከወዳጆቹ ጋር ለመመገብ የሚሆን ጊዜ ለማግኘት ይጥር ነበር። (ማቴ. 14:13፤ ሉቃስ 7:34) መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ አገልጋዮችን ሥራ እንዲወዱ ያበረታታል። የአምላክ አገልጋዮች፣ ታታሪ ሠራተኞች እንጂ ሰነፎች መሆን የለባቸውም። (ምሳሌ 15:19) አንተም ቤተሰብህን ለማስተዳደር ሰብዓዊ ሥራ ትሠራ ይሆናል። በተጨማሪም ሁሉም የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ምሥራቹን በመስበኩ ሥራ የመካፈል ኃላፊነት አለባቸው። ያም ቢሆን በቂ እረፍት ማድረግ ያስፈልግሃል። w19.12 2 አን. 2፤ 3 አን. 4-5

ሐሙስ፣ መስከረም 2

[ክርስቶስ] የእሱን ፈለግ በጥብቅ እንድትከተሉ አርዓያ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራ ተቀብሏል።—1 ጴጥ. 2:21

ስለ አጋንንት የሚገልጹ ታሪኮችን ከማውራት ተቆጠቡ። በዚህ ረገድ ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ መከተል እንፈልጋለን። ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት በሰማይ ስለኖረ ስለ ሰይጣንና ስለ አጋንንቱ ብዙ ነገር ያውቃል። ሆኖም እነዚህ ክፉ መናፍስት ስላከናወኗቸው ነገሮች የማውራት ልማድ አልነበረውም። ኢየሱስ የመጣው ስለ ይሖዋ ለመመሥከር እንጂ ስለ ሰይጣን ለማስተዋወቅ አይደለም። እኛም ስለ አጋንንት የሚገልጹ ታሪኮችን ከማውራት በመቆጠብ ኢየሱስን እንምሰል። ‘ልባችንን የሚያነሳሳው መልካም የሆነ ነገር’ ማለትም እውነት እንደሆነ በንግግራችን ማሳየት እንችላለን። (መዝ. 45:1) ክፉ መናፍስትን አትፍሯቸው። በምንኖርበት ዓለም ውስጥ የተለያዩ መጥፎ ነገሮች ሊደርሱብን ይችላሉ። ድንገተኛ አደጋ፣ ሕመም አልፎ ተርፎም ሞት በሕይወት ውስጥ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ነገሮች ናቸው። ሆኖም እነዚህ ነገሮች እንዲደርሱብን ያደረጉት ክፉ መናፍስት ናቸው ብለን ሁልጊዜ ልንደመድም አይገባም። መጽሐፍ ቅዱስ “መጥፎ ጊዜና ያልተጠበቁ ክስተቶች” ማንም ሰው ላይ ሊደርሱ እንደሚችሉ ይናገራል። (መክ. 9:11) ደግሞም ይሖዋ ከአጋንንት በላይ ኃይል እንዳለው አሳይቷል። w19.04 23-24 አን. 13-14

ዓርብ፣ መስከረም 3

ያሉት ባለሥልጣናት አንጻራዊ ቦታቸውን ያገኙት ከአምላክ ነው።—ሮም 13:1

ሽማግሌዎች ሕፃናትን ከማስነወር ጋር የተያያዙ ክሶች ለሕግ አካላት ሪፖርት እንዲደረጉ የሚጠይቁ ሰብዓዊ ሕጎችን ይታዘዛሉ? አዎ። አንዳንድ አገሮች ሕፃናትን ከማስነወር ጋር የተያያዙ ክሶች ለሕግ አካላት ሪፖርት እንዲደረጉ የሚጠይቁ ሕጎች አሏቸው፤ በእነዚህ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ሽማግሌዎች እንዲህ ያሉ ሕጎችን ይታዘዛሉ። እነዚህ ሕጎች ከአምላክ ሕግ ጋር አይጋጩም። (ሥራ 5:28, 29) በመሆኑም ሽማግሌዎች ሕፃናትን ከማስነወር ጋር የተያያዘ ክስ ሲደርሳቸው ወዲያውኑ እነዚህን ሕጎች መፈጸም የሚችሉበትን መንገድ ለማወቅ ጥረት ያደርጋሉ። ሽማግሌዎች ጥቃቱ ለተፈጸመባቸው ግለሰቦች፣ ለወላጆቻቸው እንዲሁም ስለ ጉዳዩ ለሚያውቁ ሌሎች ሰዎች ክሱን ለሕግ አካላት የማሳወቅ ነፃነት እንዳላቸው ሊነግሯቸው ይገባል። ይሁንና ክሱ የቀረበበት ሰው የጉባኤው አባል ቢሆንና ጉዳዩ በማኅበረሰቡ ዘንድ ቢታወቅስ? ክሱን ያቀረበው ግለሰብ በአምላክ ስም ላይ ነቀፋ እንዳመጣ ሊሰማው ይገባል? በፍጹም። በአምላክ ስም ላይ ነቀፋ ያመጣው ፆታዊ ጥቃት የፈጸመው ግለሰብ ነው። w19.05 10 አን. 13-14

ቅዳሜ፣ መስከረም 4

የዚህ ዓለም ጥበብ በአምላክ ፊት ሞኝነት ነው።—1 ቆሮ. 3:19

መጽሐፍ ቅዱስ ባለትዳሮች እርስ በርስ እንዲከባበሩና የጋብቻ ቃል ኪዳናቸውን ጠብቀው እንዲኖሩ ያዛል። ባልና ሚስት ጥምረታቸው ምን ያህል የጠበቀና ዘላቂ መሆን እንዳለበት ሲናገር “ሰው ከአባቱና ከእናቱ ይለያል፤ ከሚስቱም ጋር ይጣበቃል። ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ” ይላል። (ዘፍ. 2:24) በዚህ ዓለም ጥበብ የሚመሩ ሰዎች ግን ከዚህ ተቃራኒ የሆነ አመለካከት ያራምዳሉ፤ ባልም ሆነ ሚስት ለራሳቸው ፍላጎት ብቻ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው ይናገራሉ። ፍቺን በተመለከተ የተጻፈ አንድ መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “በአንዳንድ የጋብቻ ሥነ ሥርዓቶች ላይ፣ ‘በሕይወት አብረን እስከኖርን ድረስ’ የሚለው የተለመደ ቃለ መሐላ ‘እርስ በርስ እስከተዋደድን ድረስ’ በሚለው ቃለ መሐላ ተተክቷል።” የጋብቻ ቃለ መሐላን የሚያቃልለው እንዲህ ያለው አመለካከት፣ በርካታ ቤተሰቦች እንዲፈራርሱና ብዙዎች ለከባድ ስሜታዊ ሥቃይ እንዲዳረጉ ምክንያት ሆኗል። በእርግጥም ዓለም ለጋብቻ ያለው አመለካከት ሞኝነት የሚንጸባረቅበት ነው። w19.05 24 አን. 12

እሁድ፣ መስከረም 5

ይህ ሥርዓት እንዲቀርጻችሁ አትፍቀዱ።—ሮም 12:2

አንዳንድ ክርስቲያኖች የሰይጣን ዓለም በሚያስፋፋቸው የተሳሳቱ ሐሳቦችና ፍልስፍናዎች እየተማረኩ የነበረ ይመስላል፤ ይህ ሁኔታ ደግሞ ጳውሎስን አሳስቦት ነበር። (ኤፌ. 4:17-19) ማናችንም ብንሆን እንዲህ ባለው ተጽዕኖ ልንሸነፍ እንችላለን። የዚህ ሥርዓት አምላክ የሆነው ሰይጣን እኛን ከይሖዋ ለማራቅ የሚጠቀምባቸው የተለያዩ ዘዴዎች አሉ። ለምሳሌ፣ ከፍ ያለ ቦታ ወይም እውቅና የማግኘት ፍላጎት ካለን በዚህ ይጠቀማል። በሌላ በኩል ደግሞ ያሳለፍነው ሕይወት፣ ባሕላችን እንዲሁም የቀሰምነው ትምህርት በእኛ ላይ የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ በመጠቀም አስተሳሰባችንን በራሱ መንገድ ለመቅረጽ ይጥራል። ታዲያ እንደ “ምሽግ” ጠንካራ የሆኑና ሥር የሰደዱ አስተሳሰቦችን ከውስጣችን ማስወገድ እንችላለን? (2 ቆሮ. 10:4) ጳውሎስ ምን እንዳለ ልብ እንበል፦ “ስለ አምላክ የሚገልጸውን እውቀት የሚጻረሩ የተሳሳቱ ሐሳቦችንና ይህን እውቀት የሚያግድን ማንኛውንም ከፍ ያለ ነገር እናፈርሳለን፤ እንዲሁም ማንኛውንም ሐሳብ እየማረክን ለክርስቶስ እንዲታዘዝ እናደርጋለን።” (2 ቆሮ. 10:5) በእርግጥም የተሳሳቱ አስተሳሰቦችን በይሖዋ እርዳታ ከውስጣችን ነቅለን ማውጣት እንችላለን። w19.06 8 አን. 1-3

ሰኞ፣ መስከረም 6

እኔ ግን ወደ አምላክ መቅረብ ይበጀኛል። ሉዓላዊውን ጌታ ይሖዋን መጠጊያዬ አድርጌዋለሁ።—መዝ. 73:28

ሃና፣ ዳዊትና አንድ መዝሙራዊ በጣም በተጨነቁበት ጊዜ እርዳታ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ዞር ብለዋል። ያስጨነቃቸውን ነገር በተመለከተ ወደ ይሖዋ አጥብቀው ጸልየዋል። የተጨነቁበትን ምክንያት በግልጽ ነግረውታል። ይሖዋ ወደሚመለክበት ቦታ መሄዳቸውንም አላቆሙም። (1 ሳሙ. 1:9, 10፤ መዝ. 55:22፤ 73:17፤ 122:1) ይሖዋም በርኅራኄ ተነሳስቶ ለእያንዳንዳቸው መልስ ሰጥቷቸዋል። ለምሳሌ ሐና ውስጣዊ ሰላም አግኝታለች። (1 ሳሙ. 1:18) ዳዊትም “የጻድቅ ሰው መከራ ብዙ ነው፤ ይሖዋ ግን ከመከራው ሁሉ ይታደገዋል” ሲል ጽፏል። (መዝ. 34:19) ከአሳፍ ዘሮች አንዱ የሆነው መዝሙራዊ ደግሞ ይሖዋ ‘ቀኝ እጁን እንደያዘው’ እና ፍቅር በሚንጸባረቅበት ምክር እንደሚመራው ከጊዜ በኋላ ተገንዝቧል። (መዝ. 73:23, 24) ከእነዚህ ምሳሌዎች ምን ትምህርት እናገኛለን? አንዳንድ ጊዜ፣ በጣም የሚያስጨንቁ ችግሮች ያጋጥሙናል። ይሁን እንጂ ይሖዋ ሌሎችን እንዴት እንደረዳ በሚገልጹ ታሪኮች ላይ ማሰላሰላችን፣ ይሖዋ እንዲረዳን አዘውትረን ወደ እሱ መጸለያችን እንዲሁም እሱ የሚሰጠንን መመሪያ መታዘዛችን ጭንቀታችንን ለመቋቋም ይረዳናል።—መዝ. 143:1, 4-8፤ w19.06 17 አን. 14-15

ማክሰኞ፣ መስከረም 7

ለጽድቅ ስትሉ መከራ ብትቀበሉ ደስተኞች ናችሁ።—1 ጴጥ. 3:14

ከይሖዋ አንጻር ኢምንት የሆኑት የሰው ልጆች የሚናገሩት ወይም የሚያደርጉት ማንኛውም ነገር የይሖዋ ምሥክር በመሆናችሁ እንድታፍሩ ሊያደርጋችሁ አይገባም። (ሚክ. 4:5) በኢየሩሳሌም የነበሩት ሐዋርያት፣ ኢየሱስ ከተገደለ ብዙም ሳይቆይ ያደረጉትን ነገር እንመልከት። ሐዋርያቱ፣ የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ምን ያህል እንደሚጠሏቸው ያውቁ ነበር። (ሥራ 5:17, 18, 27, 28) ይሁን እንጂ በየቀኑ ወደ ቤተ መቅደሱ መሄዳቸውንና የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንደሆኑ በይፋ ማወጃቸውን አላቆሙም። (ሥራ 5:42) በፍርሃት አልተሽመደመዱም። እኛም በሥራ ቦታም ሆነ በትምህርት ቤት እንዲሁም በምንኖርበት አካባቢ፣ የይሖዋ ምሥክሮች መሆናችንን አዘውትረን በይፋ መናገራችን የሰው ፍርሃትን ለማሸነፍ ይረዳናል። (ሥራ 4:29፤ ሮም 1:16) ሐዋርያት ደስተኞች እንዲሆኑ የረዳቸው ምንድን ነው? ለምን እንደሚጠሉ ያውቁ ነበር፤ ደግሞም የይሖዋን ፈቃድ በማድረጋቸው መንገላታትን እንደ ክብር ቆጥረውት ነበር። (ሉቃስ 6:23፤ ሥራ 5:41፤ 1 ጴጥ. 2:19-21) የምንጠላው ትክክል የሆነውን ነገር በማድረጋችን እንደሆነ ከተገነዘብን ሰዎች ስለጠሉን በፍርሃት አንሸነፍም። w19.07 7 አን. 19-20

ረቡዕ፣ መስከረም 8

በሰንበት መልካም ነገር ማድረግ ተፈቅዷል።—ማቴ. 12:12

ኢየሱስና አይሁዳውያን ተከታዮቹ፣ በሙሴ ሕግ ሥር ስለነበሩ ሰንበትን ያከብሩ ነበር። ያም ቢሆን ኢየሱስ የሰንበትን ሕግ ከማክበር ጋር በተያያዘ ምክንያታዊ መሆን እንደሚያስፈልግ እንዲሁም በዚህ ዕለት ደግነት ማሳየትና መልካም ማድረግ እንደሚፈቀድ ተናግሯል፤ በድርጊቱም ቢሆን ይህን አሳይቷል። (ማቴ. 12:9-11) በሰንበት ዕለት ደግነት ማሳየትና መልካም ማድረግ ከሕጉ ጋር እንደሚጋጭ አልተሰማውም። ኢየሱስ ያደረገው ነገርም የሰንበት ሕግ የተሰጠበትን ዋነኛ ምክንያት እንደተገነዘበ የሚያጎላ ነው። በዚህ ቀን የአምላክ አገልጋዮች ከዕለት ተዕለት ሥራቸው ስለሚያርፉ በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ማተኮር ይችላሉ። ኢየሱስ ያደገው የሰንበት ቀንን ለመንፈሳዊ ነገሮች በሚያውል ቤተሰብ ውስጥ ነው። ኢየሱስ ወዳደገበት ወደ ናዝሬት ከተማ በሄደበት ወቅት ያደረገው ነገር ይህን ያሳያል፤ ዘገባው “እንደ ልማዱም በሰንበት ቀን ወደ ምኩራብ ገባ፤ ሊያነብም ተነስቶ ቆመ” ይላል። (ሉቃስ 4:15-19) ደቀ መዛሙርቱም ለሰንበት ሕግ ከፍተኛ አክብሮት ስለነበራቸው፣ የሰንበት ቀን እስኪያበቃ ድረስ ከኢየሱስ አስከሬን ጋር በተያያዘ የሚያደርጉትን ዝግጅት አቁመው ነበር።—ሉቃስ 23:55, 56፤ w19.12 4 አን. 10

ሐሙስ፣ መስከረም 9

ያለተስፋ . . . ትኖሩ [ነበር]።—ኤፌ. 2:12

ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች ፈልጎ በማግኘቱ ሥራ ሁሉም ክርስቲያኖች ድርሻ አላቸው። ይህን ሥራ፣ የጠፋን ልጅ ፈልጎ ከማግኘት ጋር ልናመሳስለው እንችላለን። እንዴት? አንድን እውነተኛ ታሪክ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ጠፍቶ የነበረ አንድ የሦስት ዓመት ልጅን ለማግኘት 500 ገደማ የሚሆኑ ሰዎች ተሰማርተው ነበር። ልጁ ከጠፋ ከ20 ሰዓታት ገደማ በኋላ፣ ለፍለጋ ከተሰማሩት ሰዎች አንዱ ልጁን በበቆሎ እርሻ ውስጥ አገኘው። ይህ ሰው ልጁን በማግኘቱ የተለየ ምስጋና እንደሚገባው አልተሰማውም። “ልጁ የተገኘው በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ባደረጉት ጥረት ነው” በማለት ተናግሯል። ብዙ ሰዎች ልክ እንደዚህ ልጅ ናቸው። ተስፋ የሚያደርጉት ነገር ስለሌላቸው እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። እንደነዚህ ያሉትን መልእክቱን መስማት የሚገባቸው ሰዎች ለማግኘት ከስምንት ሚሊዮን የምንበልጥ ክርስቲያኖች ተሰማርተናል። አንተ በግልህ መጽሐፍ ቅዱስን የማጥናት ፍላጎት ያለው ሰው ፈልገህ አጥተህ ይሆናል። ይሁንና በዚያው ክልል ውስጥ የሚሰብኩ ሌሎች አስፋፊዎች በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን እውነት መማር የሚፈልግ ሰው ሊያገኙ ይችላሉ። አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት የክርስቶስ ደቀ መዝሙር የሚሆን ሰው ሲያገኙ በፍለጋው ሥራ የተካፈሉ ሁሉ ይደሰታሉ። w19.07 16 አን. 9-10

ዓርብ፣ መስከረም 10

ግቡ ላይ ለመድረስ እየተጣጣርኩ ነው።—ፊልጵ. 3:14

ሐዋርያው ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ለነበሩ ክርስቲያኖች በሩጫው መጽናታቸው አስፈላጊ እንደሆነ ማሳሰቢያ ሰጥቷቸዋል። ይህ ጉባኤ ገና ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ስደትና ተቃውሞ ገጥሞት ነበር። እንዴት? ጳውሎስና ሲላስ ‘ወደ መቄዶንያ እንዲሻገሩ’ የቀረበላቸውን መለኮታዊ ግብዣ ተቀብለው በ50 ዓ.ም. ወደ ፊልጵስዩስ ሄዱ። (ሥራ 16:9) በዚያም ሊዲያ የተባለች አንዲት ሴት አገኙ፤ ሊዲያ ጳውሎስ የሚናገረውን ‘ያዳመጠች’ ሲሆን ይሖዋም ምሥራቹን እንድትሰማ “ልቧን በደንብ ከፈተላት።” (ሥራ 16:14) ብዙም ሳይቆይ ሊዲያና በቤቷ የሚኖሩ ሰዎች ተጠመቁ። ይሁንና ዲያብሎስ ይህን በዝምታ አልተመለከተውም። የከተማዋ ነዋሪዎች፣ ጳውሎስንና ሲላስን እየጎተቱ በሕግ አስከባሪዎቹ ፊት ያቀረቧቸው ሲሆን ‘ሁከት እየፈጠሩ ነው’ ብለው በሐሰት ከሰሷቸው። በዚህም ምክንያት ጳውሎስንና ሲላስን ደብድበው አሰሯቸው፤ በኋላ ላይ ደግሞ ከተማዋን ለቀው እንዲሄዱ ጠየቋቸው። (ሥራ 16:16-40) ታዲያ ጳውሎስና ሲላስ ተስፋ ቆረጡ? በፍጹም! አዲስ በተቋቋመው ጉባኤ ውስጥ የነበሩት ወንድሞችና እህቶችስ? ደስ የሚለው እነሱም ጸኑ! ጳውሎስና ሲላስ የተዉት ግሩም ምሳሌ እነዚህን ክርስቲያኖች በእጅጉ እንዳበረታታቸው ጥርጥር የለውም። w19.08 2 አን. 1-2

ቅዳሜ፣ መስከረም 11

የተትረፈረፈ የጽድቅ ፍሬ [አፍሩ]።—ፊልጵ. 1:11

እዚህ ላይ “የጽድቅ ፍሬ” የተባለው ነገር ለይሖዋና ለሕዝቡ ያለንን ፍቅር እንደሚጨምር ግልጽ ነው። ከዚህም ሌላ በኢየሱስ ላይ ስላለን እምነትና አስደናቂ ስለሆነው ተስፋችን ለሌሎች መናገርን ይጨምራል። በጣም አስፈላጊ በሆነው ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ በትጋት ስንካፈል “የጽድቅ ፍሬ” እናፈራለን። (ማቴ. 28:18-20) ምንም ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ብንሆን እንደ ብርሃን አብሪዎች ማብራት እንችላለን። አንዳንድ ጊዜ፣ ምሥራቹን እንዳናውጅ እንቅፋት እንደሆነ የሚሰማን ነገር ለመስበክ የሚያስችል ጥሩ አጋጣሚ ይከፍት ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች ደብዳቤ በጻፈበት ወቅት ሮም ውስጥ የቁም እስረኛ ነበር። ይሁን እንጂ እስረኛ መሆኑ፣ ለጠባቂዎቹና ሊጠይቁት ለሚመጡ ሰዎች እንዳይሰብክ አላገደውም። ጳውሎስ እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥም ሆኖ በቅንዓት ሰብኳል፤ ይህም ወንድሞች “የአምላክን ቃል ያለፍርሃት ለመናገር” የሚያስችል የልበ ሙሉነት ስሜትና ድፍረት እንዲኖራቸው አድርጓል።—ፊልጵ. 1:12-14፤ 4:22፤ w19.08 11-12 አን. 15-16

እሁድ፣ መስከረም 12

ስለዚህ በተገቢው ጊዜ ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኃይለኛው የአምላክ እጅ በታች ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ።—1 ጴጥ. 5:6

ትሕትናን እንድናዳብር የሚያነሳሳን ዋነኛው ምክንያት ይህ ባሕርይ ይሖዋን ደስ ስለሚያሰኘው ነው። ሐዋርያው ጴጥሮስ በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ የሚገኘውን ሐሳብ ሲጽፍ ይህን ነጥብ ግልጽ የሚያደርግ ሐሳብ ተናግሯል። “ተከታዬ ሁን” የተባለው መጽሐፍ ምዕራፍ 3 አንቀጽ 23 ጴጥሮስ የተናገረውን ሐሳብ ሲያብራራ እንዲህ ብሏል፦ “ትዕቢት ልክ እንደ መርዝ ነው። ለውድቀት ሊዳርግ ይችላል። እንዲህ ያለው ባሕርይ ጥሩ ተሰጥኦ ያለውን ሰው በአምላክ ፊት ዋጋ ቢስ ሊያደርገው ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ትሕትና ዝቅ ተደርጎ የሚታየውን ሰው እንኳ ይሖዋ እንዲጠቀምበት ሊያደርገው ይችላል። . . . አንተም ትሕትና የምታሳይ ከሆነ አምላካችን ወሮታ ይከፍልሃል።” ደግሞስ የይሖዋን ልብ ደስ ከማሰኘት የበለጠ ምን ነገር ሊኖር ይችላል? (ምሳሌ 23:15) ትሕትናን ማዳበራችን ይሖዋን ደስ ከማሰኘት ባለፈ ሌሎች በርካታ ጥቅሞችን ያስገኝልናል። ትሕትና፣ ሰዎች ወደ እኛ እንዲቀርቡ ያደርጋል። ይህ የሆነበትን ምክንያት ለመረዳት ራሳችሁን በሌሎች ቦታ ለማስቀመጥ ሞክሩ።—ማቴ. 7:12፤ w19.09 4 አን. 8-9

ሰኞ፣ መስከረም 13

ይሖዋ ኩሩ ልብ ያለውን ሁሉ ይጸየፋል።—ምሳሌ 16:5

ሽማግሌዎች ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን ለመርዳት ሲሉ ጠንክረው ይሠራሉ። እንዲሁም የተሰጣቸው ሥልጣን ከሌሎች የተሻሉ እንደሚያደርጋቸው አይሰማቸውም። ከዚህ ይልቅ ጉባኤውን ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ ይይዛሉ። (1 ተሰ. 2:7, 8) ለጉባኤው ያላቸው ፍቅርና ትሕትናቸው ሌሎችን በሚያናግሩበት መንገድ ላይ በግልጽ ይታያል። ለበርካታ ዓመታት በሽምግልና ያገለገለ አንድሩ የተባለ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “በጥቅሉ ሲታይ ሽማግሌዎች ደግና አፍቃሪ ከሆኑ የወንድሞችንና የእህቶችን ልብ በቀላሉ መንካት እንደሚችሉ አስተውያለሁ። እነዚህ ባሕርያት ጉባኤው ከሽማግሌዎች ጋር ተባብሮ እንዲሠራ ያነሳሳሉ።” ቶኒ የተባለ ለብዙ ዓመታት በሽምግልና ያገለገለ ወንድምም እንዲህ ብሏል፦ “በፊልጵስዩስ 2:3 ላይ በሚገኘው ምክር መሠረት ሌሎች ከእኔ እንደሚበልጡ አድርጌ ለማሰብ ሁሌም ጥረት አደርጋለሁ። ይህም ፈላጭ ቆራጭ እንዳልሆን ረድቶኛል።” ሽማግሌዎች ልክ እንደ ይሖዋ ትሑት መሆን አለባቸው። ይሖዋ የጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዢ ቢሆንም “ወደ ታች [አጎንብሶ] ችግረኛውን ከአፈር ያነሳል።” (መዝ. 18:35፤ 113:6, 7) በሌላ በኩል ግን ይሖዋ ኩሩና እብሪተኛ ሰዎችን ይጸየፋል። w19.09 16-17 አን. 11-12

ማክሰኞ፣ መስከረም 14

ቀንበሬን ተሸከሙ።—ማቴ. 11:29

በኢየሱስ ቀንበር ሥር ምንጊዜም እረፍት ማግኘት ከፈለግን ትክክለኛ አመለካከት መያዝ ይኖርብናል። የምንሠራው የይሖዋን ሥራ ስለሆነ ሥራውን በእሱ መንገድ መሥራት አለብን። እኛ ሠራተኞች፣ ይሖዋ ደግሞ አሠሪያችን ነው። (ሉቃስ 17:10) የይሖዋን ሥራ በራሳችን መንገድ ለመሥራት መሞከር ከቀንበሩ ጋር እንደ መታገል ይቆጠራል። በሌላ በኩል ደግሞ የይሖዋን አመራር የምንከተል ከሆነ የማይቻሉ የሚመስሉ ነገሮችን እንኳ ማከናወንና ማንኛውንም እንቅፋት መወጣት እንችላለን። የይሖዋ ፈቃድ እንዳይፈጸም ሊያግድ የሚችል ማንም እንደሌለ እናስታውስ! (ሮም 8:31፤ 1 ዮሐ. 4:4) ግባችን አፍቃሪ የሆነውን አባታችንን ይሖዋን ማስከበር ነው። በስግብግብነት ወይም በራስ ወዳድነት ተነሳስተው ክርስቶስን ይከተሉ የነበሩ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖሩ ሰዎች ብዙም ሳይቆይ ደስታቸውን ያጡ ሲሆን የኢየሱስን ቀንበር መሸከማቸውን አቁመዋል። (ዮሐ. 6:25-27, 51, 60, 66፤ ፊልጵ. 3:18, 19) በተቃራኒው ግን ለአምላክና ለሰዎች ባላቸው ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ተነሳስተው ክርስቶስን የተከተሉ ሰዎች በምድራዊ ሕይወታቸው በሙሉ ቀንበሩን በደስታ መሸከማቸውን ቀጥለዋል፤ ወደፊትም ከክርስቶስ ጋር በሰማይ የመግዛት መብት ያገኛሉ። እኛም በትክክለኛው ውስጣዊ ግፊት ተነሳስተን የክርስቶስን ቀንበር መሸከማችን ምንጊዜም ደስተኛ ለመሆን ያስችለናል። w19.09 20 አን. 1፤ 24 አን. 19-20

ረቡዕ፣ መስከረም 15

እውነትንም ታውቃላችሁ፤ እውነትም ነፃ ያወጣችኋል።—ዮሐ. 8:32

ከዚህ ቀደም ታምንባቸው ከነበሩ ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ትምህርቶች ባርነት ነፃ መውጣትህ ስላስገኘልህ በረከቶች ለማሰብ ሞክር። እንዲህ ያለ ነፃነት ማግኘት ምንኛ አስደሳች ነው! ወደፊት ደግሞ ከዚህ የላቀ ነፃነት እንደምታገኝ መጠበቅ ትችላለህ። በቅርቡ ኢየሱስ የሐሰት ሃይማኖትንና ብልሹ የሆነውን ሰብዓዊ አገዛዝ ለማጥፋት እርምጃ ይወስዳል። አምላክ አገልጋዮቹ የሆኑትን “እጅግ ብዙ ሕዝብ” ከጥፋቱ የሚያድናቸው ሲሆን ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ብዙ በረከቶችን እንዲያገኙ ያደርጋል። (ራእይ 7:9, 14) በዚያ ጊዜ ትንሣኤ የሚያገኙት በጣም ብዙ ሰዎች የአዳም ኃጢአት ካስከተላቸው ጉዳቶች ሁሉ ነፃ የመውጣት አጋጣሚ ያገኛሉ። (ሥራ 24:15) ኢየሱስና ተባባሪ ገዢዎቹ በሺህ ዓመት ግዛቱ ወቅት፣ የሰው ልጆች በአካላዊ ሁኔታ ወደ ፍጽምና እንዲደርሱ እና የአምላክ ልጆች መሆን እንዲችሉ ያደርጋሉ። ይህ የተሃድሶና የነፃነት ጊዜ በእስራኤል ይከበር እንደነበረው ኢዮቤልዩ ይሆናል። በዚያ ወቅት፣ ይሖዋን በታማኝነት የሚያገለግሉ በምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ፍጹም ይኸውም ከኃጢአት ሙሉ በሙሉ ነፃ ይሆናሉ። w19.12 12-13 አን. 14-16

ሐሙስ፣ መስከረም 16

በርናባስ ረዳው።—ሥራ 9:27

በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. ዮሴፍ (በርናባስ ተብሎም ተጠርቷል) የተባለ ለጋስ ሰው፣ ይሖዋ እንዲጠቀምበት ራሱን አቅርቦ ነበር። (ሥራ 4:36, 37) ሳኦል ክርስቲያን ከሆነ በኋላ ብዙዎቹ ወንድሞች እሱን ለመቅረብ ፈርተው ነበር፤ ምክንያቱም ሳኦል ጉባኤዎችን በማሳደድ ይታወቅ ነበር። ይሁን እንጂ አፍቃሪ የሆነው በርናባስ ሳኦልን ረዳው። (ሥራ 9:21, 26-28) ከጊዜ በኋላ፣ በኢየሩሳሌም ያሉት ሽማግሌዎች ርቃ በምትገኘው በሶርያ አንጾኪያ ያሉትን ወንድሞች ማበረታታት እንደሚያስፈልግ ተሰማቸው። ታዲያ ይህን ኃላፊነት እንዲወጣ ማንን ላኩ? የላኩት በርናባስን ነው! ደግሞም ጥሩ ምርጫ አድርገዋል። በርናባስ “ሁሉም በጽኑ ልብ ለጌታ ታማኞች ሆነው እንዲቀጥሉ” እንዳበረታታቸው መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ሥራ 11:22-24) ዛሬም በተመሳሳይ ይሖዋ ለእምነት ባልንጀሮቻችን “የመጽናናት ልጅ” እንድንሆን ሊረዳን ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ የሚወዱትን ሰው በሞት ያጡ ወንድሞቻችንን እንድናጽናና ሊጠቀምብን ይችላል። አሊያም የታመመን ወይም የመንፈስ ጭንቀት ያለበትን ሰው በአካል ሄደን ወይም ስልክ ደውለን የሚያበረታታ ሐሳብ እንድናካፍለው ያነሳሳን ይሆናል። ይሖዋ ልክ እንደ በርናባስ አንተንም እንዲጠቀምብህ ራስህን ታቀርባለህ?—1 ተሰ. 5:14፤ w19.10 22 አን. 8

ዓርብ፣ መስከረም 17

በደልን ይቅር የሚል ሁሉ ፍቅርን ይሻል፤ አንድን ጉዳይ ደጋግሞ የሚያወራ ግን የልብ ጓደኛሞችን ይለያያል።—ምሳሌ 17:9

ከወዳጆቻችን ጋር አብረን ስንሠራ መልካም ጎናቸውን ብቻ ሳይሆን አንዳንድ ጊዜ ድክመታቸውንም ማስተዋላችን አይቀርም። ታዲያ ወዳጅነታችንን ጠብቀን ለመቀጠል የሚረዳን ምንድን ነው? ከወንድሞቻችን እና ከእህቶቻችን ፍጽምና መጠበቅ አንችልም። በመሆኑም ከሌሎች ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ከመሠረትን በኋላ ወዳጅነታችንን ጠብቀን ለማቆየት ከፍተኛ ጥረት ማድረግ አለብን። ወዳጆቻችን ስህተት ቢሠሩ በአምላክ ቃል ላይ ተመሥርተን በደግነት ሆኖም በግልጽ ምክር መስጠት ሊያስፈልገን ይችላል። (መዝ. 141:5) የሚያስከፋን ነገር ካደረጉ ደግሞ ይቅር ልንላቸው ይገባል። አንዴ ይቅር ካልናቸው በኋላ በሌላ ጊዜ ጥፋታቸውን ላለማንሳት መጠንቀቅ ይኖርብናል። በዚህ አስጨናቂ ዘመን ውስጥ በወንድሞቻችንና በእህቶቻችን ድክመት ላይ ሳይሆን በመልካም ጎናቸው ላይ ትኩረት ማድረጋችን ምንኛ አስፈላጊ ነው! እንዲህ ማድረጋችን ወዳጅነታችንን ያጠናክረዋል፤ ደግሞም በታላቁ መከራ ወቅት የቅርብ ወዳጆች ያስፈልጉናል። w19.11 6 አን. 13, 16

ቅዳሜ፣ መስከረም 18

ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ፤ . . . ያዘዝኳችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ [አስተምሯቸው]።—ማቴ. 28:19, 20

መጽሐፍ ቅዱስን የምናስጠናቸው ሰዎች፣ ኢየሱስ ‘ያዘዛቸውን ሁሉ እንዲጠብቁ ለማስተማርና ደቀ መዛሙርት’ እንዲሆኑ ለመርዳት አቅማችን የፈቀደውን ያህል መጣር ይኖርብናል። ሰዎች ከይሖዋና ከእሱ መንግሥት ጎን መቆማቸው ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ እንዲገነዘቡ መርዳት አለብን። ይህም የተማሩትን ነገር በተግባር ለማዋል እንዲሁም ሕይወታቸውን ለይሖዋ ወስነው ለመጠመቅ እንዲነሳሱ መርዳትን ይጠይቃል። ከይሖዋ ቀን መትረፍ የሚችሉት እንዲህ ካደረጉ ብቻ ነው። (1 ጴጥ. 3:21) የዚህ ሥርዓት ፍጻሜ በጣም ቀርቧል። ከዚህ አንጻር የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት የመሆን ዓላማ የሌላቸውን ሰዎች ለማስጠናት የሚሆን ጊዜ የለንም። (1 ቆሮ. 9:26) ሥራችን አጣዳፊ ነው! ጊዜው ከማለቁ በፊት የመንግሥቱን መልእክት መስማት የሚያስፈልጋቸው ብዙ ሰዎች አሉ። w19.10 11-12 አን. 14-15

እሁድ፣ መስከረም 19

ዕጣኑን በይሖዋ ፊት ባለው እሳት ላይ ይጨምረዋል።—ዘሌ. 16:13

በየዓመቱ በስርየት ቀን ላይ የእስራኤል ብሔር አንድ ላይ የሚሰበሰብ ሲሆን የእንስሳት መሥዋዕቶች ይቀርቡ ነበር። እነዚህ መሥዋዕቶች፣ እስራኤላውያንን ከኃጢአት መንጻት እንደሚያስፈልጋቸው ያስታውሷቸው ነበር። በመጀመሪያ ግን ሊቀ ካህናቱ ቅዱሱን ዕጣን በጥንቃቄ ፍሙ ላይ በመጨመር ክፍሉ ደስ በሚል መዓዛ እንዲታወድ ማድረግ ነበረበት። ይህ ምን ያስተምረናል? መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች የሚያቀርቡት ጸሎት እንደ ዕጣን እንደሆነ ይገልጻል። (መዝ. 141:2፤ ራእይ 5:8) ሊቀ ካህናቱ፣ ዕጣኑን ይዞ ወደ ይሖዋ ፊት የሚገባው በታላቅ አክብሮት ነበር። እኛም በተመሳሳይ በጸሎት ወደ ይሖዋ የምንቀርበው በጥልቅ አክብሮት ሊሆን ይገባል። ፈጣሪያችን፣ አንድ ልጅ አባቱን የሚቀርበውን ያህል ወደ እሱ እንድንቀርብና በጸሎት እንድናነጋግረው ስለፈቀደልን በጣም አመስጋኝ ነን። (ያዕ. 4:8) ይሖዋ እንደ ወዳጆቹ አድርጎ ይመለከተናል! (መዝ. 25:14) ይህን መብት በጣም ከፍ አድርገን ስለምንመለከተው ፈጽሞ እሱን ማሳዘን አንፈልግም። w19.11 20-21 አን. 3-5

ሰኞ፣ መስከረም 20

ይሖዋ ሆይ፣ ሥራህ ምንኛ ብዙ ነው! ሁሉንም በጥበብ ሠራህ። ምድር በፈጠርካቸው ነገሮች ተሞልታለች።—መዝ. 104:24

በምትኖርበት አካባቢ ያሉ አብዛኞቹ ሰዎች ለሥራ ምን አመለካከት አላቸው? በብዙ አገሮች ውስጥ ሰዎች ከበፊቱ የበለጠ ለረጅም ሰዓት አድካሚ የሆነ ሥራ ይሠራሉ። ከመጠን በላይ የሚሠሩ ሰዎች ደግሞ ለእረፍት፣ ከቤተሰባቸው ጋር አብሮ ለመሆን ወይም መንፈሳዊ ፍላጎታቸውን ለማሟላት የሚሆን ጊዜ ለማግኘት ይቸገራሉ። (መክ. 2:23) በሌላ በኩል ግን ሥራ ጨርሶ የማይወዱና ላለመሥራት ሰበብ የሚፈላልጉ ሰዎችም አሉ። (ምሳሌ 26:13, 14) ዓለም ለሥራ ካለው ሚዛናዊ ያልሆነ አመለካከት በተቃራኒ ይሖዋ እና ኢየሱስ ለሥራ ምን አመለካከት እንዳላቸው እስቲ እንመልከት። ይሖዋ ሥራ እንደሚወድ ምንም ጥያቄ የለውም። ኢየሱስ “አባቴ እስካሁን እየሠራ ነው፤ እኔም እሠራለሁ” በማለት ይህን እውነታ አረጋግጧል። (ዮሐ. 5:17) አምላክ እጅግ በጣም ብዙ መንፈሳዊ ፍጥረታትንና ግዙፉን ጽንፈ ዓለም ሲፈጥር ምን ያህል ሥራ እንዳከናወነ ለማሰብ እንሞክር። በምንኖርባት ውብ ምድር ላይም የአምላክን የፍጥረት ሥራዎች የሚያሳዩ ብዙ ማስረጃዎች እናገኛለን። w19.12 2 አን. 1-2

ማክሰኞ፣ መስከረም 21

እንደ ልቤ የሆነውን . . . ዳዊትን አገኘሁ።—ሥራ 13:22

ዳዊት ከይሖዋ ጋር ይህን ያህል ሊቀራረብ የቻለው እንዴት ነው? ዳዊት ከፍጥረት ስለ ይሖዋ ተምሯል። ዳዊት፣ ልጅ እያለ የአባቱን በጎች በመጠበቅ መስክ ላይ በርካታ ሰዓታት ያሳልፍ ነበር። ይሖዋ በፈጠራቸው ነገሮች ላይ ማሰላሰል የጀመረው በዚህ ጊዜ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ፣ ዳዊት በምሽቱ ሰማይ ላይ የተረጩትን ከዋክብት በማድነቅ ብቻ አልተወሰነም። ከዋክብቱን የፈጠራቸውን አምላክ ባሕርያትም አስተውሎ መሆን አለበት። (መዝ. 19:1, 2) ዳዊት፣ የሰው ልጆች ስለተሠሩበት መንገድ ማሰላሰሉ የይሖዋን ድንቅ ጥበብ ለማስተዋል አስችሎታል። (መዝ. 139:14) ዳዊት የይሖዋን ሥራዎች ለመረዳት ያደረገው ጥረት እሱ ከይሖዋ አንጻር ሲታይ ኢምንት መሆኑን እንዲገነዘብ አድርጎታል። (መዝ. 139:6) ከዚህ የምናገኘው ትምህርት ምንድን ነው? በዙሪያችሁ ባሉት የፍጥረት ሥራዎች ይኸውም በተክሎች፣ በእንስሳት እንዲሁም በሰዎች አካል ላይ በየዕለቱ በማሰላሰል እነዚህ ነገሮች ስለ ይሖዋ ምን እንደሚያስተምሯችሁ ለማሰብ ሞክሩ። እንዲህ ካደረጋችሁ በእያንዳንዱ ቀን ስለ አፍቃሪው አባታችሁ የምትማሩት ብዙ ነገር ይኖራል። (ሮም 1:20) እንዲሁም በእያንዳንዱ ቀን ለይሖዋ ያላችሁ ፍቅር እያደገ ይሄዳል። w19.12 19-20 አን. 15-17

ረቡዕ፣ መስከረም 22

ሙሴ ካደገ በኋላ የፈርዖን የልጅ ልጅ ተብሎ ለመጠራት በእምነት እንቢ አለ።—ዕብ. 11:24

ሙሴ በተማረው ነገር ላይ ተመሥርቶ ውሳኔ አድርጓል። ሙሴ 40 ዓመት ገደማ ሲሆነው፣ “የፈርዖን የልጅ ልጅ” ተብሎ ከመጠራት ይልቅ የአምላክ ሕዝቦች ከሆኑት ዕብራውያን ጋር መተባበርን መረጠ። ሙሴ የነበረውን ከፍተኛ ቦታ መሥዋዕት አድርጓል። በግብፅ ባሪያ ከሆኑት ዕብራውያን ጋር የወገነ ሲሆን ይህን ያደረገው፣ ውሳኔው ኃያል ገዢ የነበረውንና እንደ አምላክ የሚታየውን ፈርዖንን ሊያስቆጣው እንደሚችል እያወቀ ነው። ይህ እንዴት ያለ አስደናቂ እምነት ነው! ሙሴ በይሖዋ ታምኗል። እንዲህ ዓይነቱ የመተማመን ስሜት ደግሞ ዘላቂ ለሆነ ወዳጅነት የመሠረት ድንጋይ ነው። (ምሳሌ 3:5) ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? ሁላችንም እንደ ሙሴ ልናደርገው የሚገባ ውሳኔ አለ፦ አምላክን ለማገልገልና ከሕዝቡ ጋር ለመተባበር እንመርጣለን? አምላክን ለማገልገል ስንል መሥዋዕት መክፈል ያስፈልገን ይሆናል፤ እንዲሁም ይሖዋን ከማያውቁ ሰዎች ተቃውሞ ሊያጋጥመን ይችላል። በሰማዩ አባታችን የምንታመን ከሆነ ግን እንደሚረዳን መተማመን እንችላለን! w19.12 17 አን. 5-6

ሐሙስ፣ መስከረም 23

ይሖዋ አምላክም ሰውን ከምድር አፈር ሠራው፤ በአፍንጫውም የሕይወትን እስትንፋስ እፍ አለበት።—ዘፍ. 2:7

የተሠራነው ከምድር አፈር ቢሆንም ከአፈር እጅግ የላቀ ዋጋ አለን። በይሖዋ ፊት ውድ እንደሆንን እንድንተማመን የሚያደርጉንን አንዳንድ ምክንያቶች እስቲ እንመልከት። ይሖዋ የሰው ልጆችን የፈጠረው የእሱን ባሕርያት ማንጸባረቅ እንዲችሉ አድርጎ ነው። (ዘፍ. 1:27) ይህም በምድር ላይ ካሉት ሌሎች ፍጥረታቱ የበለጠ ቦታ እንደሰጠን የሚያሳይ ነው፤ ምድርንና እንስሳትን እንዲቆጣጠሩ ለሰው ልጆች ሥልጣን ሰጥቷቸዋል። (መዝ. 8:4-8) አዳም ኃጢአት ከሠራ በኋላም ይሖዋ ለሰው ልጆች ያለው አክብሮት አልቀነሰም። ይሖዋ እኛን በጣም ከፍ አድርጎ ከመመልከቱ የተነሳ፣ የሚወደውን ልጁን ኢየሱስን ለኃጢአታችን ቤዛ እንዲሆን ሰጥቶናል። (1 ዮሐ. 4:9, 10) ቤዛው ያስገኘውን ጥቅም መሠረት በማድረግ ይሖዋ በአዳም ኃጢአት ምክንያት የሞቱ ‘ጻድቃንንም ሆነ ዓመፀኞችን’ ወደፊት ያስነሳቸዋል። (ሥራ 24:15) የጤንነታችን ሁኔታ፣ የኢኮኖሚ አቅማችን ወይም ዕድሜያችን ምንም ይሁን ምን በእሱ ፊት ውድ እንደሆንን የአምላክ ቃል ያረጋግጥልናል።—ሥራ 10:34, 35፤ w20.01 15 አን. 5-6

ዓርብ፣ መስከረም 24

በሌሎች ሰዎች ጉዳይ ጣልቃ [አትግቡ]።—1 ተሰ. 4:11

ሰማያዊ ጥሪ ከቤተሰብ የሚወረስ ነገር አይደለም። እንዲህ ያለውን ግብዣ የሚያቀርበው አምላክ ነው። (1 ተሰ. 2:12) በመሆኑም ሌሎች እንዲያዝኑ ሊያደርጉ የሚችሉ ጥያቄዎች ከማንሳት መቆጠብ አለብን። ለምሳሌ ያህል፣ ቅቡዕ የሆነ ባል ያላትን አንዲት እህት፣ ወደፊት ምድር ገነት በምትሆንበት ጊዜ ከባለቤቷ ጋር እንደማትኖር ስታስብ ምን እንደሚሰማት ልንጠይቃት አይገባም። ደግሞም በአዲሱ ዓለም ውስጥ ይሖዋ ‘የሕያዋን ፍጥረታትን ሁሉ ፍላጎት እንደሚያሟላ’ ሙሉ በሙሉ መተማመን እንችላለን። (መዝ. 145:16) ለቅቡዓን ክርስቲያኖች ከሌሎች የበለጠ ቦታ አለመስጠታችን ለእኛም ጥበቃ ይሆንልናል። እንዴት? መጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ታማኝነታቸውን ሊያጎድሉ እንደሚችሉ ይናገራል። (ማቴ. 25:10-12፤ 2 ጴጥ. 2:20, 21) ‘ሌሎችን ከመካብ’ የምንቆጠብ ከሆነ ቅቡዓንን ጨምሮ በሌሎች ዘንድ በስፋት የሚታወቅም ሆነ ይሖዋን ለረጅም ጊዜ ያገለገለ የማንኛውም ሰው ተከታይ አንሆንም። (ይሁዳ 16) እንዲህ ማድረጋችን፣ ግለሰቡ ታማኝነቱን ቢያጎድል ወይም ከጉባኤ ቢርቅ በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት እንዳናጣ አሊያም እሱን ማገልገላችንን እንዳናቆም ጥበቃ ይሆንልናል። w20.01 29 አን. 9-10

ቅዳሜ፣ መስከረም 25

የተወደዳችሁ ልጆቹ በመሆን አምላክን የምትመስሉ ሁኑ።—ኤፌ. 5:1

የይሖዋ ‘የተወደዱ ልጆች’ እንደመሆናችን መጠን እሱን ለመምሰል የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን። ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት አፍቃሪ፣ ደግ እና ይቅር ባይ በመሆን የእሱን ባሕርያት ለማንጸባረቅ እንሞክራለን። አምላክን የማያውቁ አንዳንድ ሰዎች መልካም ምግባራችንን ሲመለከቱ ስለ እሱ ለመማር ሊነሳሱ ይችላሉ። (1 ጴጥ. 2:12) ክርስቲያን ወላጆችም ልጆቻቸውን ከሚይዙበት መንገድ ጋር በተያያዘ ይሖዋን መምሰላቸው ተገቢ ነው። ይህን ማድረጋቸው ልጆቻቸውም ከአፍቃሪው አባታችን ጋር የራሳቸውን ወዳጅነት ለመመሥረት እንዲነሳሱ ሊያደርጋቸው ይችላል። በሰማዩ አባታችን በይሖዋ ስለምንኮራ ስለ እሱ ለሌሎች መናገር እንፈልጋለን። ሁላችንም “በይሖዋ እኩራራለሁ” ብሎ እንደጻፈው እንደ ንጉሥ ዳዊት ይሰማናል። (መዝ. 34:2) ይሁንና ስለ ይሖዋ መናገር ቢያስፈራንስ? ድፍረት እንድናገኝ ምን ሊረዳን ይችላል? ስለ ይሖዋ መናገራችን እሱን ምን ያህል እንደሚያስደስተው እንዲሁም ሌሎች ስለ እሱ መማራቸው ምን ያህል እንደሚጠቅማቸው ማሰባችን ድፍረት ለማዳበር ይረዳናል። ይሖዋ የሚያስፈልገንን ድፍረት ይሰጠናል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ወንድሞቻችንን ደፋር እንዲሆኑ እንደረዳቸው ሁሉ እኛንም ይረዳናል።—1 ተሰ. 2:2፤ w20.02 11 አን. 12-13

እሁድ፣ መስከረም 26

ስለዚህ ሂዱና . . . እያጠመቃችኋቸው . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው።—ማቴ. 28:19, 20

መጽሐፍ ቅዱስን የሚያጠኑ ብዙ ሰዎች እድገት አድርገው ይጠመቃሉ። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስን በቋሚነት ከእኛ ጋር የሚያጠኑ አንዳንድ ሰዎች የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ለመሆን የሚያመነቱ ይመስላል። እነዚህ ሰዎች፣ ጥናቱ ቢያስደስታቸውም እድገት አድርገው ለመጠመቅ አይጥሩም። መጽሐፍ ቅዱስን የምታስጠናው ሰው ካለ ጥናትህ የተማረውን ነገር ተግባራዊ እንዲያደርግና የክርስቶስ ደቀ መዝሙር መሆን እንዲችል መርዳት እንደምትፈልግ ጥያቄ የለውም። ይሖዋ የሚፈልገው ሰዎች ለእሱ ባላቸው ፍቅር ተነሳስተው እንዲያገለግሉት ነው። ስለዚህ ግባችን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን፣ ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ በጥልቅ እንደሚያስብላቸውና በጣም እንደሚወዳቸው እንዲገነዘቡ መርዳት ነው። ይሖዋን “አባት ለሌላቸው ልጆች አባት፣ ለመበለቶች ደግሞ ጠባቂ” እንደሆነ አድርገው እንዲመለከቱት መርዳት እንፈልጋለን። (መዝ. 68:5) ጥናቶቻችን አምላክ እንደሚወዳቸው ሲገነዘቡ ልባቸው መነካቱና ለእሱ ያላቸው ፍቅር ማደጉ አይቀርም። ስለዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችህ፣ አፍቃሪው አምላካችን የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ እንደሚፈልግ እንዲሁም እዚህ ግብ ላይ እንዲደርሱ ሊረዳቸው ዝግጁ መሆኑን እንዲገነዘቡ እርዳቸው። w20.01 3 አን. 7-8

ሰኞ፣ መስከረም 27

ስለምታሳየው ፍቅር በመስማቴ እጅግ ተደስቻለሁ እንዲሁም ተጽናንቻለሁ።—ፊልሞና 7

ሐዋርያው ጳውሎስ ትሑት ስለነበር የወዳጆቹ ማበረታቻ እንደሚያስፈልገው ያውቅ ነበር፤ ያደረጉለትን እርዳታም ተቀብሏል። የሚያስጨንቅ ሁኔታ ባጋጠመው ጊዜ ሌሎች እንዳጽናኑት መናገሩ እንደ ደካማ ሰው ሊያስቆጥረው እንደሚችል በማሰብ ስጋት አላደረበትም። (ቆላ. 4:7-11) ማበረታቻ እንደሚያስፈልገን በትሕትና አምነን ስንቀበል ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የሚያስፈልገንን ነገር በደስታ ያደርጉልናል። ጳውሎስ ቅዱሳን መጻሕፍት እንደሚያጽናኑት ያውቅ ነበር። (ሮም 15:4) እነዚህ መጻሕፍት ማንኛውንም ችግር ለመወጣት የሚያስችል ጥበብም ይሰጡታል። (2 ጢሞ. 3:15, 16) ጳውሎስ ለሁለተኛ ጊዜ በሮም በታሰረበት ወቅት የሚሞትበት ጊዜ እንደተቃረበ ተሰምቶት ነበር። ጢሞቴዎስን “የመጽሐፍ ጥቅልሎቹን” ይዞ በቶሎ ወደ እሱ እንዲመጣ ጠይቆታል። (2 ጢሞ. 4:6, 7, 9, 13) ለምን? የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን የተወሰኑ ክፍሎች እንደያዙ የሚገመቱትን እነዚያን ጥቅልሎች ለግል ጥናቱ ሊጠቀምባቸው ስላሰበ ይሆናል። እኛም እንደ ጳውሎስ የአምላክን ቃል አዘውትረን የምናጠና ከሆነ ምንም ዓይነት ፈተና ቢያጋጥመን ይሖዋ በቅዱሳን መጻሕፍት ተጠቅሞ ሊያረጋጋን ይችላል። w20.02 23 አን. 14-15

ማክሰኞ፣ መስከረም 28

እንዳይፈረድባችሁ በሌሎች ላይ አትፍረዱ።—ማቴ. 7:1

ኤሊፋዝ፣ በልዳዶስና ሶፋር ኢዮብን እንዴት እንደሚረዱት ጊዜ ወስደው ለማሰብ አልሞከሩም። ከዚህ ይልቅ ኢዮብ ኃጢአት እንደሠራ እንዴት እንደሚያሳምኑት እያሰቡ ነበር። እርግጥ ነው የተናገሯቸው አንዳንዶቹ ሐሳቦች ትክክል ነበሩ፤ ሆኖም ስለ ኢዮብም ሆነ ስለ ይሖዋ የተናገሩት አብዛኛው ነገር ደግነት የጎደለው ወይም ከእውነታው የራቀ ነበር። ኢዮብን ያለርኅራኄ ፈርደውበታል። (ኢዮብ 32:1-3) ታዲያ ይሖዋ ምን ተሰማው? በሦስቱ ሰዎች ላይ ቁጣው ነደደ። ሰዎቹ ሞኞች እንደሆኑ የተናገረ ከመሆኑም ሌላ ኢዮብ እንዲጸልይላቸው እንዲጠይቁት አድርጓል። (ኢዮብ 42:7-9) ከኤሊፋዝ፣ ከበልዳዶስና ከሶፋር መጥፎ ምሳሌ ብዙ ትምህርት እናገኛለን። በመጀመሪያ ደረጃ፣ በወንድሞቻችን ላይ መፍረድ የለብንም። (ማቴ. 7:2-5) ከዚህ ይልቅ ከመናገራችን በፊት በጥሞና ልናዳምጣቸው ይገባል። ሁኔታቸውን መረዳት የምንችለው እንዲህ ካደረግን ብቻ ነው። (1 ጴጥ. 3:8) በሁለተኛ ደረጃ፣ በምንናገርበት ጊዜ ከአንደበታችን የሚወጣው ቃል ደግነት የሚንጸባረቅበትና እውነተኛ መሆን ይኖርበታል። (ኤፌ. 4:25) በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ ይሖዋ እርስ በርስ የምንነጋገረው ነገር እንደሚያሳስበው እንማራለን። w20.03 22-23 አን. 15-16

ረቡዕ፣ መስከረም 29

በማንኛውም ጊዜ . . . መጸለያችሁን ቀጥሉ።—ኤፌ. 6:18

ሌሎችን ስለ ይሖዋ ስናስተምር ብዙ ጊዜ እኛም እሱን ይበልጥ እያወቅነው እንሄዳለን። ለምሳሌ፣ ይሖዋ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ወዳላቸው ሰዎች ሲመራን የእሱን ርኅራኄ ይበልጥ መመልከት እንችላለን። (ዮሐ. 6:44፤ ሥራ 13:48) መጽሐፍ ቅዱስን የምናስጠናቸው ሰዎች ከመጥፎ ልማዳቸው ተላቀው አዲሱን ስብዕና መላበስ ሲጀምሩ የአምላክ ቃል ያለውን ኃይል እናያለን። (ቆላ. 3:9, 10) በተጨማሪም ይሖዋ በክልላችን ያሉ ብዙ ሰዎች ስለ እሱ ተምረው ለመዳን የሚያስችሏቸው የተለያዩ አጋጣሚዎች እንዲያገኙ ማድረጉ ስለ ትዕግሥቱ ያስተምረናል። (ሮም 10:13-15) ይሁንና ይሖዋን ለረጅም ዓመታት ስናገለግል ብንቆይም ከእሱ ጋር ያለንን ዝምድና ፈጽሞ አቅልለን መመልከት የለብንም። ከአምላክ ጋር ያለንን ወዳጅነት ከፍ አድርገን እንደምንመለከት ከምናሳይባቸው መንገዶች አንዱ ከእሱ ጋር በጸሎት መነጋገር ነው። ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት ጠንካራ ዝምድና ለመመሥረት እጅግ አስፈላጊ ነው። ስለዚህ አዘውትረህ በመጸለይ ወደ አምላክ ቅረብ፤ የውስጥ ስሜትህን አውጥተህ ለእሱ ለመንገር ፈጽሞ አትፍራ። w19.12 19 አን. 11, 13-14

ሐሙስ፣ መስከረም 30

ኃጢአታችሁ ይቅር [ተብሎላችኋል]።—1 ዮሐ. 2:12

ይህን ማሰባችን ከፍተኛ እፎይታ ያስገኝልናል! ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ እንደመሆኑ መጠን ሰይጣንና እሱ የሚቆጣጠረው ሥርዓት በእኛ ላይ ያደረሱትን ማንኛውንም ጉዳት ያስወግድልናል። (ኢሳ. 65:17፤ 1 ዮሐ. 3:8፤ ራእይ 21:3, 4) ይህ ምንኛ የሚያጽናና ተስፋ ነው! በተጨማሪም ኢየሱስ ከባድ ኃላፊነት የሰጠን ቢሆንም እስከዚህ ሥርዓት መጨረሻ ድረስ ከእኛ ጋር በመሆን ይደግፈናል። (ማቴ. 28:19, 20) ይህም ደፋሮች እንድንሆን ያደርገናል! እፎይታ፣ ተስፋና ድፍረት ደግሞ የአእምሮ ሰላማችንን ጠብቀን ለመኖር የሚረዱ በጣም ወሳኝ ነገሮች ናቸው። ታዲያ ከባድ ፈተናዎች ሲደርሱብህ የአእምሮ ሰላምህን ጠብቀህ መኖር የምትችለው እንዴት ነው? ኢየሱስ ያደረጋቸውን ነገሮች በማድረግ ነው። አንደኛ፣ ጸልይ እንዲሁም በጸሎት ጽና። ሁለተኛ፣ ከባድ በሚሆንበት ጊዜም እንኳ ይሖዋን በመታዘዝ ምሥራቹን በቅንዓት ስበክ። ሦስተኛ፣ ወዳጆችህ የሚሰጡህን እርዳታ ተቀበል። እነዚህን ነገሮች የምታደርግ ከሆነ የአምላክ ሰላም አእምሮህንና ልብህን ይጠብቅልሃል። (ፊልጵ. 4:6, 7) በተጨማሪም ልክ እንደ ኢየሱስ ማንኛውንም ፈተና ማሸነፍ ትችላለህ።—ዮሐ. 16:33፤ w19.04 13 አን. 16-17

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2026)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2026 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ