መጋቢት
ሰኞ፣ መጋቢት 1
“ከመካከላቸው ውጡና ራሳችሁን ለዩ” ይላል ይሖዋ፤ “ርኩስ የሆነውንም ነገር አትንኩ።”—2 ቆሮ. 6:17
ቤተሰቦቻችን ወይም ወዳጆቻችን ከሙታን ጋር በተያያዙ ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ልማዶች እንድንካፈል ጫና በሚያደርጉብን ጊዜም እንኳ፣ ለአምላክና ለቃሉ ያለን ፍቅር ይሖዋን ለመታዘዝ ብርታት ይሰጠናል። እነዚህ ሰዎች ለሞተው ግለሰብ ፍቅር ወይም አክብሮት እንደሌለን በመናገር ሊያሸማቅቁን ይሞክሩ ይሆናል። አሊያም ደግሞ በእነዚህ ልማዶች አለመካፈላችን ሟቹ በሕይወት ባሉት ላይ በሆነ መንገድ ጉዳት እንዲያደርስ ሊያደርገው እንደሚችል ይገልጹ ይሆናል። በአንዲት የካሪቢያን ደሴት፣ አንድ ሰው ሲሞት “መንፈሱ” በአካባቢው ሊቆይና በደል ያደረሱበትን ሰዎች ሊቀጣ እንደሚችል በስፋት ይታመናል። እንዲያውም የሟቹ መንፈስ “በማኅበረሰቡ ላይ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል” የሚል እምነት እንዳለ አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ ገልጿል። በአንዳንድ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ደግሞ ሰዎች በሟቹ ቤት ውስጥ ያሉትን መስታወቶች የሚሸፍኑ ከመሆኑም ሌላ የግለሰቡን ፎቶግራፎች ወደ ግድግዳ ያዞራሉ። እንዲህ የሚያደርጉት ለምንድን ነው? አንዳንዶች፣ የሞቱ ሰዎች ራሳቸውን ማየት እንደሌለባቸው ይናገራሉ! የይሖዋ አገልጋዮች ግን የሰይጣንን ውሸቶች የሚያስፋፉ አጉል እምነቶችን አይቀበሉም፤ ከዚህ ጋር በተያያዙ ድርጊቶችም ጨርሶ አይካፈሉም!—1 ቆሮ. 10:21, 22፤ w19.04 16 አን. 11-12
ማክሰኞ፣ መጋቢት 2
ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር ሁሉ እናንተም አድርጉላቸው።—ማቴ. 7:12
ኢየሱስ ተከታዮቹ ሌሎችን ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንዲይዙ የሚያበረታቱ መሠረታዊ ሥርዓቶችን አስተምሯል። ወርቃማውን ሕግ እንደ ምሳሌ መውሰድ እንችላለን። ሁላችንም፣ ሌሎች ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንዲይዙን እንፈልጋለን። ስለዚህ እኛም ሌሎችን በዚሁ መንገድ መያዝ ይኖርብናል። እንዲህ ካደረግን እነሱም እኛን ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ለመያዝ ሊነሳሱ ይችላሉ። ይሁንና ፍትሕ የጎደለው ድርጊት ተፈጽሞብን ከሆነስ? ኢየሱስ፣ ይሖዋ “ቀን ከሌት ወደ እሱ የሚጮኹት ምርጦቹ ፍትሕ እንዲያገኙ” እንደሚያደርግ በማስተማር ተከታዮቹ በአምላክ ላይ እምነት እንዲጥሉ አበረታቷል። (ሉቃስ 18:6, 7) ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ የሚከተለውን ዋስትና ይሰጠናል፦ ፍትሐዊ የሆነው አምላካችን በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች የሚያውቅ ከመሆኑም ሌላ በትክክለኛው ጊዜ ላይ ፍትሕ እንድናገኝ ያደርጋል። (2 ተሰ. 1:6) ኢየሱስ ያስተማራቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶች መከተላችን ሌሎችን ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ለመያዝ ይረዳናል። በተጨማሪም በሰይጣን ዓለም ውስጥ ኢፍትሐዊ ድርጊት ተፈጽሞብን ከሆነ ይሖዋ ፍትሕ እንድናገኝ እንደሚያደርግ ማወቃችን ያጽናናናል። w19.05 5 አን. 18-19
ረቡዕ፣ መጋቢት 3
እናንተ ስላላችሁ ተስፋ፣ ምክንያት እንድታቀርቡ ለሚጠይቃችሁ ሰው ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር ዝግጁ ሁኑ፤ ይህን ስታደርጉ ግን በገርነት መንፈስና በጥልቅ አክብሮት ይሁን።—1 ጴጥ. 3:15
ትምህርት በመከታተል ላይ ያለህ ወጣት ነህ? ክፍል ውስጥ ስለ ዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ እየተማራችሁ ነው እንበል። በዚህ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት ደግፈህ መናገር ብትፈልግም ብቃቱ እንደሌለህ ይሰማህ ይሆናል። ስለዚህ በጉዳዩ ላይ ምርምር ማድረግ ያስፈልግሃል ማለት ነው! ምርምር በምታደርግበት ጊዜ ሁለት ግቦችን በአእምሮህ ልትይዝ ትችላለህ፤ እነሱም (1) አምላክ ሁሉንም ነገሮች እንደፈጠረ ያለህን እምነት ማጠናከር (2) የምታምንበትን ነገር አሳማኝ በሆነ መንገድ ለሌሎች ማስረዳት ናቸው። (ሮም 1:20) በቅድሚያ ‘አስተማሪው ሕይወት በዝግመተ ለውጥ እንደመጣ ለማስተማር የትኞቹን ማስረጃዎች አቅርቧል?’ ብለህ ራስህን ልትጠይቅ ትችላለህ። ከዚያም ጽሑፎቻችንን ተጠቅመህ ጥልቀት ያለው ምርምር አድርግ። የምታምንበትን ነገር ለሌሎች ማስረዳት የምታስበውን ያህል ከባድ ላይሆን ይችላል። አብዛኞቹ ሰዎች በዝግመተ ለውጥ የሚያምኑት አንድ የሚያከብሩት ሰው ይህ ጽንሰ ሐሳብ እውነት እንደሆነ ስለነገራቸው ብቻ ነው። አንድ ወይም ሁለት አሳማኝ ነጥቦችን ካገኘህ በቅን ልቦና ተነሳስተው ጥያቄ ለሚያቀርቡ ሰዎች አጥጋቢ መልስ መስጠት ትችላለህ።—ቆላ. 4:6፤ w19.05 29 አን. 13
ሐሙስ፣ መጋቢት 4
እናት ልጇን እንደምታጽናና፣ እኔም እናንተን ሁልጊዜ አጽናናችኋለሁ።—ኢሳ. 66:13
ነቢዩ ኤልያስ ሕይወቱን ለማትረፍ እየሸሸ በነበረበት ወቅት በጣም ተስፋ ከመቁረጡ የተነሳ ሞቱን ተመኝቶ ነበር። በዚህ ጊዜ ይሖዋ በሐዘን የተደቆሰውን አገልጋዩን ለማበረታታት አንድ ኃያል መልአክ ላከ። መልአኩም ለኤልያስ ተግባራዊ የሆነ እርዳታ ሰጠው። ትኩስ ምግብ ካቀረበለት በኋላ እንዲበላ አበረታታው። (1 ነገ. 19:5-8) ይህ ዘገባ አንድ ጠቃሚ እውነት ያስተምረናል፦ አንዳንድ ጊዜ፣ ቀላል የሚመስል የደግነት ተግባር ማከናወናችን ትልቅ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል። ሻይ ቡና እንደማለት፣ ምግብ እንደመጋበዝ እንዲሁም አነስ ያለ ስጦታ ወይም አሳቢነታችንን የሚገልጽ ካርድ እንደመስጠት ያሉ ቀላል የሚመስሉ ነገሮች ተስፋ የቆረጠ ወንድማችንን ሊያበረታቱት ብሎም እንደምንወደውና እንደምናስብለት ሊያረጋግጡለት ይችላሉ። ያጋጠሙትን አሳዛኝ ሁኔታዎች አንስተን ከእሱ ጋር ማውራት ቢከብደን እንኳ እንዲህ ባሉ መንገዶች ተግባራዊ እርዳታ ልንሰጠው እንችላለን። ይሖዋ ኤልያስን እስከ ኮሬብ ተራራ ድረስ መሄድ እንዲችል ተአምራዊ በሆነ መንገድ ረድቶታል። ምናልባትም ኤልያስ ሊጎዱት የሚፈልጉ ሰዎች በዚህ ስፍራ ጨርሶ ሊያገኙት እንደማይችሉ ተሰምቶት ይሆናል። ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? ፆታዊ ጥቃት የተፈጸመባቸውን ሰዎች ለማጽናናት በቅድሚያ የደህንነት ስሜት እንዲሰማቸው ማድረግ ሊያስፈልገን ይችላል፤ አንዳንዶች በስብሰባ አዳራሹ፣ ሌሎች ደግሞ ቤታቸው ውስጥ ብናነጋግራቸው ይመርጡ ይሆናል። w19.05 16 አን. 11፤ 17 አን. 13-14
ዓርብ፣ መጋቢት 5
ምድሪቱም ታለቅሳለች፤ . . . የናታን ቤት ቤተሰብ ለብቻው።—ዘካ. 12:12
በዘካርያስ ምዕራፍ 12 ላይ የሚገኘውን ስለ መሲሑ ሞት የሚናገረውን ትንቢት እያነበባችሁ ነው እንበል። (ዘካ. 12:10) ቁጥር 12 ላይ ስትደርሱ “የናታን ቤት” በመሲሑ ሞት ምክንያት አምርሮ እንደሚያለቅስ የሚገልጽ ዘገባ አነበባችሁ። ይህን ነጥብ እንዲሁ አንብባችሁ ከማለፍ ይልቅ ቆም ብላችሁ ‘በናታን ቤትና በመሲሑ መካከል ያለው ዝምድና ምንድን ነው?’ በማለት ራሳችሁን ልትጠይቁ ትችላላችሁ። ከዚያም ምርምር ማድረግ ትጀምራላችሁ። ለዚህ ጥቅስ የተዘጋጀው የኅዳግ ማጣቀሻ ወደ 2 ሳሙኤል 5:13, 14 ይመራችኋል፤ እዚያ ላይ ናታን ከንጉሥ ዳዊት ልጆች መካከል አንዱ እንደሆነ ታነብባላችሁ። በኅዳግ ማጣቀሻው ላይ የተጠቀሰው ሁለተኛው ጥቅስ ማለትም ሉቃስ 3:23, 31 ደግሞ ናታን በማርያም የትውልድ ሐረግ መስመር በኩል የኢየሱስ ቅድመ አያት እንደሆነ ይገልጻል። አሁን የማወቅ ጉጉታችሁ ይበልጥ ይጨምራል! ኢየሱስ በዳዊት የዘር ሐረግ በኩል እንደሚመጣ በትንቢት መነገሩን ታውቃላችሁ። (ማቴ. 22:42) ሆኖም ዳዊት ከ20 የሚበልጡ ወንዶች ልጆች አሉት። ታዲያ ዘካርያስ የናታንን ቤት ለይቶ በመጥቀስ በኢየሱስ ሞት እንደሚያለቅስ መናገሩ የሚገርም አይደለም? w19.05 30 አን. 17
ቅዳሜ፣ መጋቢት 6
ጥሩ የሆነውን፣ ተቀባይነት ያለውንና ፍጹም የሆነውን የአምላክ ፈቃድ መርምራችሁ ማረጋገጥ ትችሉ ዘንድ አእምሯችሁን በማደስ ተለወጡ።—ሮም 12:2
ምን ማድረግ ይኖርብናል? የአምላክን ቃል አዘውትረን በማጥናት፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማርናቸውን እውነቶች መርምረን ማረጋገጥ እንችላለን። በተጨማሪም የይሖዋ መሥፈርቶች ትክክል መሆናቸውን እርግጠኞች እንሆናለን። ይህም ጠንካራ ሥር እንዳለው ዛፍ ሥር ሰድደን እና ‘በእምነት ጸንተን ለመኖር’ ያስችለናል። (ቆላ. 2:6, 7) በእምነት ጸንታችሁ ለመኖር የሚያስፈልገውን እርምጃ መውሰድ ያለባችሁ እናንተው ራሳችሁ እንደሆናችሁ አስታውሱ። ስለዚህ አእምሯችሁን የሚያሠራው ኃይል እየታደሰ ይሂድ። አዘውትራችሁ ጸልዩ፤ የአምላክን መንፈስ እርዳታ ለማግኘት ይሖዋን ለምኑ። በጥልቀት አሰላስሉ፤ አስተሳሰባችሁንና ዝንባሌያችሁን ሁልጊዜ መርምሩ። ጥሩ ጓደኞች ምረጡ፤ አስተሳሰባችሁን ለመለወጥ የሚረዱ ወዳጆች ይኑሯችሁ። እንዲህ ካደረጋችሁ፣ የሰይጣን ዓለም የሚያሳድረውን እንደ መርዝ ያለ ተጽዕኖ ማርከስ እንዲሁም “ስለ አምላክ የሚገልጸውን እውቀት የሚጻረሩ የተሳሳቱ ሐሳቦችንና ይህን እውቀት የሚያግድን ማንኛውንም ከፍ ያለ ነገር” ማፍረስ ትችላላችሁ።—2 ቆሮ. 10:5፤ w19.06 13 አን. 17-18
እሁድ፣ መጋቢት 7
በአምላካችንና በአባታችን ዓይን ንጹሕና ያልረከሰ አምልኮ ‘ወላጅ አልባ የሆኑ ልጆችንና መበለቶችን በመከራቸው መርዳት’ [ነው]።—ያዕ. 1:27
ሩት፣ መበለት ከሆነችው ከናኦሚ ጎን እንዳልተለየች ሁሉ እኛም የሚወዱትን ሰው በሞት ላጡ ሰዎች ቀጣይ የሆነ ድጋፍ ማድረግ ይኖርብናል። (ሩት 1:16, 17) ፖላ እንዲህ ብላለች፦ “ባለቤቴ እንደሞተ አካባቢ ብዙዎች ድጋፍ አድርገውልኛል። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሁሉም ወደ ዕለታዊ ሕይወታቸው ተመለሱ። እኔ ግን ሕይወቴ ሙሉ በሙሉ ተቀይሯል። ሐዘን የደረሰበት ግለሰብ፣ የሚወደውን ሰው በሞት ካጣ ከወራት ሌላው ቀርቶ ከዓመታት በኋላም እንኳ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ሌሎች መገንዘባቸው በጣም አስፈላጊ ነው።” በእርግጥ ሁኔታው ከሰው ሰው ይለያያል። አንዳንዶች ሁኔታውን ለመቀበል ብዙ ጊዜ ላይወስድባቸው ይችላል። ሌሎች ግን ከሚወዱት ሰው ጋር ያከናውኑት የነበረው እያንዳንዱ ነገር ሐዘናቸውን ይቀሰቅስባቸዋል። ሰዎች የሚያዝኑበት መንገድ የተለያየ ነው። ይሖዋ የትዳር ጓደኛቸውን በሞት ያጡ ሰዎችን የመርዳት መብትና ኃላፊነት እንደሰጠን እናስታውስ። w19.06 24 አን. 16
ሰኞ፣ መጋቢት 8
ክፉ ሰው ከእኔ ጋር እስካለ ድረስ አፌን ለመጠበቅ ልጓም አስገባለሁ።—መዝ. 39:1
በእገዳ ሥር ስንሆን “ዝም ለማለት ጊዜ” እንዳለው መገንዘብ ይኖርብናል። (መክ. 3:7) የወንድሞቻችንንና የእህቶቻችንን ስም፣ ስብሰባ የምናደርግባቸውን ቦታዎች፣ አገልግሎታችንን የምናከናውንበትንና መንፈሳዊ ምግብ የምናገኝበትን መንገድ እንዲሁም እንደነዚህ ያሉ በሚስጥር ሊያዙ የሚገባቸው መረጃዎችን በጥንቃቄ መያዝ አለብን። እንዲህ ያሉ መረጃዎችን ለመንግሥት ባለሥልጣናት መናገር የለብንም፤ በአገር ውስጥም ሆነ በሌላ አገር ላሉ ወዳጆቻችን ወይም ዘመዶቻችንም ቢሆን አንናገርም። በዚህ ረገድ ካልተጠነቀቅን ወንድሞቻችንን አደጋ ላይ ልንጥል እንችላለን። በትናንሽ ጉዳዮች የተነሳ መከፋፈል እንዳይፈጠር ተጠንቀቁ። ሰይጣን እርስ በርሱ የተለያየ ቤት ጸንቶ ሊቆም እንደማይችል ያውቃል። (ማር. 3:24, 25) በመሆኑም በመካከላችን መከፋፈል ለመፍጠር የማያቋርጥ ጥረት ያደርጋል። በዚህ መንገድ፣ ከእሱ ጋር ከመዋጋት ይልቅ እርስ በርስ እንድንዋጋ ሊያደርገን ይፈልጋል። የጎለመሱ ክርስቲያኖችም እንኳ በዚህ ወጥመድ እንዳይወድቁ መጠንቀቅ ያስፈልጋቸዋል። እኛም ከወንድሞቻችን ጋር ያሉን ልዩነቶች ችግር እንዳይፈጥሩብን የተቻለንን ሁሉ የምናደርግ ከሆነ ልዩነቶቻችን ለመከፋፈል ምክንያት አይሆኑም።—ቆላ. 3:13, 14፤ w19.07 11-12 አን. 14-16
ማክሰኞ፣ መጋቢት 9
የጌታ ባሪያ . . . ለሰው ሁሉ ገር፣ ለማስተማር ብቁ የሆነ . . . ሊሆን ይገባዋል።—2 ጢሞ. 2:24-26
አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች መልእክታችንን እንዲያዳምጡ የሚያደርጋቸው የምንናገረው ነገር ሳይሆን የምንናገርበት መንገድ ነው። በደግነትና በዘዴ ከያዝናቸው እንዲሁም በግለሰብ ደረጃ እንደምናስብላቸው ከተሰማቸው ደስ ብሏቸው ያዳምጡናል። የእኛን አመለካከት እንዲያዳምጡ አናስገድዳቸውም። ከዚህ ይልቅ ስለ ሃይማኖት ያላቸውን አመለካከት ለማስተዋል እና ስሜታቸውን ለማክበር ጥረት እናደርጋለን። ለምሳሌ ያህል፣ ጳውሎስ ከአይሁዳውያን ጋር ሲወያይ ከቅዱሳን መጻሕፍት እየጠቀሰ ያስረዳ ነበር። በአርዮስፋጎስ ከግሪክ ፈላስፎች ጋር ሲወያይ ግን በቀጥታ ከመጽሐፍ ቅዱስ አልጠቀሰም። (ሥራ 17:2, 3, 22-31) እኛስ የጳውሎስን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? የምናነጋግረው ሰው በመጽሐፍ ቅዱስ የማያምን ከሆነ በቀጥታ ከመጽሐፍ ቅዱስ አለመጥቀሳችን የተሻለ ሊሆን ይችላል። ግለሰቡ ከእኛ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ሲያነብ መታየት እንደጨነቀው ከተሰማን ደግሞ ትኩረት በማይስብ መንገድ ለምሳሌ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችን በመጠቀም ጥቅሱን ልናሳየው እንችላለን። w19.07 21 አን. 5-6
ረቡዕ፣ መጋቢት 10
ልባችሁ እንዳይታለልና ዞር ብላችሁ ሌሎች አማልክትን እንዳታመልኩ . . . ተጠንቀቁ።—ዘዳ. 11:16
ሰይጣን በዘዴ ተጠቅሞ እስራኤላውያንን በጣዖት አምልኮ እንዲካፈሉ ፈትኗቸዋል። እስራኤላውያንን የፈተናቸው የዕለት እንጀራ የማግኘት ፍላጎታቸውን በመጠቀም ነው። እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ሲገቡ እህል የሚያመርቱበትን መንገድ መቀየር አስፈልጓቸው ነበር። በግብፅ እያሉ ከአባይ ወንዝ ላይ ውኃ በመጥለፍ እርሻቸውን በመስኖ ያጠጡ ነበር። በተስፋይቱ ምድር ግን ገበሬዎች እርሻቸውን የሚያለሙት ከትልቅ ወንዝ ውኃ በመጥለፍ ሳይሆን ወቅቱን ጠብቆ የሚጥለውን ዝናብና መሬቱ ላይ የሚያርፈውን ጠል በመጠቀም ነበር። (ዘዳ. 11:10-15፤ ኢሳ. 18:4, 5) በመሆኑም እስራኤላውያን አዲስ የግብርና ዘዴ መማር ነበረባቸው። ይሁንና ይሖዋ አዲስ የግብርና ዘዴ ስለመማር እየተናገረ ባለበት ወቅት የሐሰት አማልክትን ስለማምለክ ማስጠንቀቂያ የሰጠው ለምንድን ነው? እስራኤላውያን አንዳንድ ጠቃሚ የግብርና ዘዴዎችን በዙሪያቸው ካሉት አረማውያን ለመማር እንደሚፈተኑ ይሖዋ ያውቅ ነበር። ከነዓናውያን ገበሬዎች ደግሞ ከባአል ጋር በተያያዘ የሚያምኑባቸው ነገሮች በአስተሳሰባቸው ላይ ተጽዕኖ ያሳድሩ ነበር።—ዘኁ. 25:3, 5፤ መሳ. 2:13፤ 1 ነገ. 18:18፤ w19.06 3 አን. 4-6
ሐሙስ፣ መጋቢት 11
ፍቅራችሁ . . . ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንዲሄድ መጸለዬን እቀጥላለሁ።—ፊልጵ. 1:9
ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ሲላስ፣ ሉቃስና ጢሞቴዎስ በፊልጵስዩስ ከተማ የመንግሥቱን መልእክት ለማዳመጥ ፈቃደኛ የሆኑ በርካታ ሰዎችን አግኝተው ነበር። እነዚህ አራት ቀናተኛ ወንድሞች በዚህች ከተማ ጉባኤ እንዲቋቋም አደረጉ፤ ደቀ መዛሙርቱ በሙሉ አንድ ላይ መሰብሰብ የጀመሩ ሲሆን የሚሰበሰቡትም ሊዲያ በተባለች እንግዳ ተቀባይ የሆነች ክርስቲያን ቤት ሳይሆን አይቀርም። (ሥራ 16:40) ብዙም ሳይቆይ ግን አዲስ የተቋቋመው ጉባኤ አስቸጋሪ ሁኔታ አጋጠመው። ሰይጣን የእውነት ጠላቶችን በማነሳሳት፣ እነዚህ ታማኝ ክርስቲያኖች የሚያከናውኑት የስብከት ሥራ ከፍተኛ ተቃውሞ እንዲገጥመው አደረገ። ጳውሎስና ሲላስ ተይዘው በበትር ከተደበደቡ በኋላ እስር ቤት ተጣሉ። በኋላም ከእስር ሲፈቱ አዲሶቹን ደቀ መዛሙርት በመጎብኘት አበረታቷቸው። ከዚያም ጳውሎስ፣ ሲላስና ጢሞቴዎስ ከተማዋን ለቀው ሄዱ፤ ሉቃስ ግን እዚያው የቀረ ይመስላል። ታዲያ አዲሱ ጉባኤ እንዴት ሆነ? አዲሶቹ አማኞች በይሖዋ መንፈስ እርዳታ እሱን በቅንዓት ማገልገላቸውን ቀጠሉ። (ፊልጵ. 2:12) በእርግጥም ጳውሎስ በእነሱ ለመኩራት የሚያበቃ ምክንያት ነበረው! w19.08 8 አን. 1-2
ዓርብ፣ መጋቢት 12
[ተበዳሪ] የአበዳሪው ባሪያ ነው።—ምሳሌ 22:7
በቅርቡ ወደ ሌላ ቦታ ተዛውራችኋል? ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ መዛወር ያልተጠበቀ ወጪ ሊያስከትል ይችላል፤ በመሆኑም ሳታስቡት ዕዳ ውስጥ ልትገቡ ትችላላችሁ። ዕዳ ውስጥ እንዳትዘፈቁ፣ የማያስፈልጋችሁን ነገር በዱቤ ከመግዛት ተቆጠቡ። (ምሳሌ 22:3) የቤተሰባችንን አባል እንደ ማስታመም ያለ ውጥረት የሚፈጥር ሁኔታ ውስጥ ስንሆን፣ ምን ያህል መበደር እንደሚያስፈልገን መወሰን ከባድ ሊሆንብን ይችላል። እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥማችሁ ‘ጸሎትና ምልጃ’ ማቅረባችሁ ጥበብ የተንጸባረቀበት ውሳኔ ለማድረግ እንደሚረዳችሁ አስታውሱ። ይሖዋም ጸሎታችሁን በመስማት “ልባችሁንና አእምሯችሁን” ለመጠበቅ የሚያስችል ሰላም ይሰጣችኋል፤ ይህም ጉዳዩን በተረጋጋ መንፈስ እንድታስቡበት ይረዳችኋል። (ፊልጵ. 4:6, 7፤ 1 ጴጥ. 5:7) ምንጊዜም ጥሩ ወዳጆች ይኑሯችሁ። ስሜታችሁንና ያጋጠሟችሁን ነገሮች ለምትቀርቧቸው ወዳጆቻችሁ በተለይ እንደ እናንተ ዓይነት ሁኔታ ላሳለፉ ጓደኞቻችሁ ማካፈላችሁ ይጠቅማችኋል። እንዲህ ማድረጋችሁ ስሜታችሁ እንዲረጋጋ ይረዳችኋል። (መክ. 4:9, 10) ወደ አዲሱ ቦታ ከመዛወራችሁ በፊት ካፈራችኋቸው ጓደኞቻችሁ ጋር ያላችሁ ወዳጅነት እንደማይቋረጥ የታወቀ ነው። w19.08 22 አን. 9-10
ቅዳሜ፣ መጋቢት 13
አርማጌዶን ወደሚባል ስፍራ ሰበሰቧቸው።—ራእይ 16:16
ይሖዋ ታላቁን ጦርነት ከመጊዶ ጋር ያያያዘው ለምንድን ነው? መጊዶና በአቅራቢያው የሚገኘው የኢይዝራኤል ሸለቆ በርካታ ጦርነቶች የተካሄዱባቸው ቦታዎች ናቸው። እንዲያውም በአንዳንዶቹ ጦርነቶች ላይ ይሖዋ ራሱ በቀጥታ ጣልቃ ገብቶ ነበር። ለምሳሌ እስራኤላዊው መስፍን ባርቅ፣ ሲሳራ በተባለ የጦር አዛዥ ከሚመራው የከነአን ሠራዊት ጋር “በመጊዶ ውኃዎች አጠገብ” በተዋጋበት ጊዜ አምላክ ድል እንዲጎናጸፍ ረድቶታል። ባርቅና ነቢዪቱ ዲቦራ ተአምራዊ በሆነ መንገድ ላገኙት ድል ይሖዋን አመስግነዋል። እንዲህ በማለትም ዘምረዋል፦ “ከዋክብት ከሰማይ . . . ከሲሳራ ጋር ተዋጉ። . . . ይሖዋ ሆይ፣ ጠላቶችህ ሁሉ ይጥፉ፣ አንተን የሚወዱ ግን ደምቃ እንደምትወጣ ፀሐይ ይሁኑ።” (መሳ. 5:19-21, 31) በተመሳሳይም በአርማጌዶን ጦርነት ወቅት የአምላክ ጠላቶች በሙሉ የሚጠፉ ሲሆን አምላክን የሚወዱ ደግሞ መዳን ያገኛሉ። ሆኖም ባርቅ ባካሄደው ጦርነትና በአርማጌዶን ጦርነት መካከል አንድ ትልቅ ልዩነት አለ። በአርማጌዶን ጦርነት ላይ የአምላክ ሕዝቦች አይዋጉም። መዋጋት ቀርቶ የጦር መሣሪያ እንኳ አይዙም! በይሖዋና በሰማይ ባለው ሠራዊቱ ‘ተማምነው በመኖር ብርቱ መሆናቸውን ያሳያሉ።’—ኢሳ. 30:15፤ ራእይ 19:11-15፤ w19.09 9 አን. 4-5
እሁድ፣ መጋቢት 14
ወደ እኔ ኑ።—ማቴ. 11:28
ወደ ኢየሱስ የምንሄድበት አንዱ መንገድ እሱ ስለተናገራቸውና ስላደረጋቸው ነገሮች የቻልነውን ያህል በመማር ነው። (ሉቃስ 1:1-4) በእኛ ምትክ ይህን ሊያደርግልን የሚችል ሌላ ሰው የለም፤ ስለ ኢየሱስ የሚናገሩትን ዘገባዎች እኛ ራሳችን ልናጠናቸው ይገባል። በተጨማሪም ለመጠመቅና የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ለመሆን ውሳኔ በማድረግ ወደ ኢየሱስ መሄድ እንችላለን። ኢየሱስ “ወደ እኔ ኑ” በማለት ያቀረበውን ግብዣ የምንቀበልበት ሌላው መንገድ ደግሞ እርዳታ ሲያስፈልገን ወደ ጉባኤ ሽማግሌዎች መሄድ ነው። ኢየሱስ በጎቹን ለመንከባከብ እነዚህን ‘ስጦታ የሆኑ ሰዎች’ ይጠቀማል። (ኤፌ. 4:7, 8, 11፤ ዮሐ. 21:16፤ 1 ጴጥ. 5:1-3) ቅድሚያውን ወስደን የእነሱን እርዳታ ለማግኘት ጥረት ማድረግ አለብን። ሽማግሌዎች ልባችንን አንብበው ምን እንደሚያስፈልገን እንዲያውቁ ልንጠብቅ አንችልም። ጁሊየን የተባለ አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “የሽማግሌዎችን እርዳታ ጠየቅኩ። እነሱ ያደረጉልኝ የእረኝነት ጉብኝት እስከዛሬ ከተቀበልኳቸው ልዩ ስጦታዎች መካከል አንዱ ነው።” ለጁሊየን እረኝነት እንዳደረጉለት ሁለት ወንድሞች ያሉ ታማኝ ሽማግሌዎች ‘የክርስቶስን አስተሳሰብ’ እንድናውቅ ማለትም የእሱን አመለካከት እንድንረዳና አርዓያውን እንድንከተል ያግዙናል። (1 ቆሮ. 2:16፤ 1 ጴጥ. 2:21) በእርግጥም ይህ ከእነሱ ልንቀበለው የምንችለው ከሁሉ የላቀ ስጦታ ነው። w19.09 21 አን. 4-5
ሰኞ፣ መጋቢት 15
ከዚህ ጉረኖ ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ።—ዮሐ. 10:16
ቅዱሳን መጻሕፍት መንፈስ ቅዱስ በሕይወታቸው ውስጥ ከፍተኛ ተጽዕኖ ስላሳደረባቸው ታማኝ ወንዶችና ሴቶች ይናገራሉ፤ ሆኖም እነዚህ ሰዎች የ144,000ዎቹ አባል አይደሉም። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ መጥምቁ ዮሐንስ ነው። (ማቴ. 11:11) ሌላው ደግሞ ዳዊት ነው። (ሥራ 2:34) እነዚህን ጨምሮ ስፍር ቁጥር የሌላቸው በርካታ ሰዎች ከሞት ተነስተው ገነት በሆነች ምድር ላይ ይኖራሉ። ሁሉም ከእጅግ ብዙ ሕዝብ ጋር በመሆን ለይሖዋ ታማኝ እንደሆኑና ሉዓላዊነቱን እንደሚደግፉ የሚያሳዩበት አጋጣሚ ያገኛሉ። አምላክ በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ የአሁኑን ያህል ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በአንድነት እሱን እንዲያመልኩ ያደረገበት ጊዜ የለም። ተስፋችን በሰማይ መኖርም ሆነ በምድር፣ የቻልነውን ያህል ብዙ ሰዎች ‘የሌሎች በጎች’ ክፍል የሆነው የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባል እንዲሆኑ መርዳት ይኖርብናል። በቅርቡ ይሖዋ በትንቢት የተነገረውን ታላቁን መከራ ያመጣል፤ በዚያን ጊዜ በሰው ዘር ላይ መከራ ያስከተሉት መንግሥታትና ሃይማኖቶች ይጠፋሉ። የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት እንዴት ያለ ግሩም ተስፋ ይጠብቃቸዋል! ይሖዋን በምድር ላይ ለዘላለም የማገልገል አጋጣሚ ያገኛሉ።—ራእይ 7:14፤ w19.09 31 አን. 18-19
ማክሰኞ፣ መጋቢት 16
በመጨረሻዎቹ ቀናት . . . ፌዘኞች ይመጣሉ።—2 ጴጥ. 3:3
የሰይጣን ሥርዓት ወደ ፍጻሜው እየተቃረበ ሲሄድ ለአምላክም ሆነ ለመንግሥቱ ያለን ታማኝነት ይበልጥ እንደሚፈተን እንጠብቃለን። ሰዎች የሚሰነዝሩብን ፌዝ የሚቀጥል ይመስላል። በተለይ ደግሞ በዚያን ጊዜ የገለልተኝነት አቋማችንን የሚፈትኑ ተጨማሪ ሁኔታዎች ስለሚያጋጥሙን መዘባበቻ መሆናችን አይቀርም። በታላቁ መከራ ወቅት ታማኝነታችንን መጠበቅ እንድንችል ከአሁኑ ታማኝነታችንን ማጠናከር ይኖርብናል። በታላቁ መከራ ወቅት፣ በምድር ላይ ሥራውን ከሚመሩት ወንድሞች ጋር በተያያዘ ለውጥ ይኖራል። ታላቁ መከራ ከጀመረ በኋላ የሆነ ወቅት ላይ፣ በምድር ላይ የቀሩት ቅቡዓን ክርስቲያኖች በሙሉ በአርማጌዶን ጦርነት ለመካፈል ወደ ሰማይ ይሰበሰባሉ። (ማቴ. 24:31፤ ራእይ 2:26, 27) በመሆኑም የበላይ አካሉ በምድር ላይ ከእኛ ጋር አይሆንም ማለት ነው። ያም ቢሆን የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት እንደተደራጁ ይቀጥላሉ። የሌሎች በጎች አባላት የሆኑ ብቃት ያላቸው ወንድሞች ሥራውን ተረክበው አመራር ይሰጣሉ። እነዚህን ወንድሞች በመደገፍና አምላክ ለእነሱ የሚሰጣቸውን መመሪያ በመከተል ለይሖዋ ታማኝ መሆናችንን ማሳየት ይኖርብናል። በሕይወት መትረፋችን የተመካው ይህን በማድረጋችን ላይ ነው! w19.10 17 አን. 13-14
ረቡዕ፣ መጋቢት 17
ወደምትሄጂበት እሄዳለሁ፤ . . . በምትሞቺበት እሞታለሁ።—ሩት 1:16, 17
ናኦሚ ይሖዋን የምትወድ ታማኝ ሴት ነበረች። ባሏንና ሁለት ወንዶች ልጆቿን በሞት ካጣች በኋላ ግን ስሟ ናኦሚ መሆኑ ቀርቶ “ማራ” እንዲባል ፈልጋ ነበር፤ “ማራ” የሚለው ስም “መራራ” የሚል ትርጉም አለው። (ሩት 1:3, 5, 20 ግርጌ፣ 21) ናኦሚ ይህ ሁሉ መከራ ሲደርስባት፣ ምራቷ ሩት ከጎኗ አልተለየችም። ሩት፣ ናኦሚ የሚያስፈልጓትን ነገሮች ከማድረግ በተጨማሪ አጽናንታታለች። ሩት ናኦሚን እንደምትወዳትና ከጎኗ እንደምትሆን ከልብ በመነጩ ያልተወሳሰቡ ቃላት ገልጻላታለች። የመንፈሳዊ ቤተሰባችን አባል የሆነ ሰው የትዳር ጓደኛውን በሞት ሲያጣ የእኛ ድጋፍ ያስፈልገዋል። ባልና ሚስት፣ አጠገብ ለአጠገብ ከተተከሉ ሁለት ዛፎች ጋር ሊመሳሰሉ ይችላሉ። ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ የዛፎቹ ሥሮች እርስ በርስ ይተሳሰራሉ። በመሆኑም አንደኛው ዛፍ ሲነቀል ሌላኛው ዛፍ ይጎዳል። በተመሳሳይም አንድ ሰው የትዳር ጓደኛውን በሞት ሲያጣ ስሜቱ በጣም ሊደቆስ ይችላል፤ ይህ ሁኔታም ለረጅም ጊዜ ይዘልቅ ይሆናል። w19.06 23 አን. 12-13
ሐሙስ፣ መጋቢት 18
እያንዳንዱ ሰው በራሱ ምኞት ሲማረክና ሲታለል ይፈተናል።—ያዕ. 1:14
ከመዝናኛ ጋር በተያያዘ ሊያሳስበን የሚገባው የመዝናኛው ዓይነት ብቻ ሳይሆን በመዝናናት የምናሳልፈው ጊዜም ጭምር ነው። ጥንቃቄ ካላደረግን ይሖዋን ለማገልገል ከምናሳልፈው የበለጠ ጊዜ በመዝናኛ ልናሳልፍ እንችላለን። ስለዚህ በቅድሚያ በመዝናኛ ምን ያህል ጊዜ እያሳለፍክ እንዳለህ እወቅ። በአንድ ሳምንት ውስጥ በመዝናኛ የምታሳልፈውን ጊዜ ለምን አትመዘግብም? ቴሌቪዥን በመመልከት፣ ኢንተርኔት በማሰስ እና በሞባይልህ ጌም በመጫወት የምታሳልፈውን ጊዜ ጻፍ። በመዝናኛ ከመጠን ያለፈ ጊዜ እያሳለፍክ እንዳለህ ከተሰማህ ፕሮግራም ለማውጣት ሞክር። ፕሮግራም ስታወጣ በመጀመሪያ፣ ይበልጥ አስፈላጊ ለሆኑት ነገሮች ቅድሚያ ስጥ፤ ከዚያ የተረፈውን ጊዜ ለመዝናኛ ልትጠቀምበት ትችላለህ። በመቀጠልም ፕሮግራምህን በጥብቅ ለመከተል እንዲረዳህ ወደ ይሖዋ ጸልይ። እንዲህ ካደረግህ ለግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ለቤተሰብ አምልኮ፣ ለጉባኤ ስብሰባዎች እንዲሁም በስብከቱና በማስተማሩ ሥራ በመካፈል ይሖዋን ለማገልገል የሚሆን ጊዜና ጉልበት ይኖርሃል። በተጨማሪም በመዝናኛ በምታሳልፈው ጊዜ ረገድ የጥፋተኝነት ስሜት አይሰማህም። w19.10 30 አን. 14, 16፤ 31 አን. 17
ዓርብ፣ መጋቢት 19
መልካም የሆነውን ነገር የማድረግ ፍላጎት እንጂ የመፈጸም ችሎታ የለኝም።—ሮም 7:18
በ55 ዓ.ም. ገደማ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች አንድ አስፈላጊ ውሳኔ አድርገው ነበር። እነዚህ ክርስቲያኖች በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ያሉ ወንድሞቻቸው እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ሲያውቁ እነሱን ለመርዳት መዋጮ ለማድረግ ወሰኑ። (1 ቆሮ. 16:1፤ 2 ቆሮ. 8:6) ይህ ከሆነ የተወሰኑ ወራት ቢያልፉም የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ውሳኔያቸውን ተግባራዊ አላደረጉም። በዚህም ምክንያት የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የሚልኩት የልግስና ስጦታ ከሌሎች ጉባኤዎች መዋጮ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ለመድረስ ዝግጁ የሚሆን አይመስልም ነበር። (2 ቆሮ. 9:4, 5) የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ጥሩ ውሳኔ አድርገው ነበር፤ ጳውሎስም ቢሆን አስደናቂ ለሆነው እምነታቸው እንዲሁም ልግስና ለማድረግ ለነበራቸው ጉጉት አመስግኗቸዋል። ሆኖም የጀመሩትን ዳር እንዲያደርሱ ማበረታታትም አስፈልጎታል። (2 ቆሮ. 8:7, 10, 11) ይህ ዘገባ ታማኝ ክርስቲያኖችም እንኳ ያደረጉትን ጥሩ ውሳኔ በተግባር ማዋል ተፈታታኝ ሊሆንባቸው እንደሚችል ያስገነዝበናል። ለምን? ፍጹማን ባለመሆናችን ዛሬ ነገ የማለት ልማድ ይኖረን ይሆናል። አሊያም ደግሞ ያልተጠበቁ ክስተቶች ውሳኔያችንን በተግባር ማዋል አዳጋች እንዲሆንብን ሊያደርጉ ይችላሉ።—መክ. 9:11፤ w19.11 26-27 አን. 3-5
ቅዳሜ፣ መጋቢት 20
ትልቅ የእምነት ጋሻ አንሱ።—ኤፌ. 6:16
ትልቅ ጋሻ የአንድን ወታደር አብዛኛውን የሰውነት ክፍል ከጥቃት እንደሚከላከል ሁሉ፣ እምነትህም በሥነ ምግባር ብልግና እንዲሁም በዓመፅ የተሞላውና አምላክ የለሽ የሆነው ይህ ሥርዓት ከሚያሳድረው ተጽዕኖ ይጠብቅሃል። ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን በመንፈሳዊ ውጊያ ላይ ነን፤ ከጠላቶቻችን መካከል ደግሞ ክፉ መንፈሳዊ ኃይሎች ይገኙበታል። (ኤፌ. 6:10-12) ታዲያ ፈተናዎችን ለመቋቋም ዝግጁ መሆን አለመሆንህን ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ የአምላክን እርዳታ ለማግኘት ጸልይ። ከዚያም እምነትህ አምላክ በሚፈልገው ሁኔታ ላይ መሆን አለመሆኑን ለማወቅ የአምላክን ቃል ተጠቅመህ ራስህን መርምር። (ዕብ. 4:12) መጽሐፍ ቅዱስ “በሙሉ ልብህ በይሖዋ ታመን፤ ደግሞም በገዛ ራስህ ማስተዋል አትመካ” ይላል። (ምሳሌ 3:5, 6) ይህን ነጥብ በአእምሮህ በመያዝ፣ በቅርብ ጊዜ ስላደረግካቸው ውሳኔዎች ለማሰብ ሞክር። ለምሳሌ ያህል፣ ከባድ የገንዘብ ችግር አጋጥሞህ ነበር? በዚህ ጊዜ በዕብራውያን 13:5 ላይ ይሖዋ “ፈጽሞ አልተውህም፤ በምንም ዓይነት አልጥልህም” በማለት የገባው ቃል ትዝ ብሎህ ነበር? ይህ ጥቅስ ይሖዋ እንደሚረዳህ እንድትተማመን ረድቶህ ነበር? ከሆነ የእምነት ጋሻህ ጠንካራ ነው ማለት ነው። w19.11 14 አን. 1, 4
እሁድ፣ መጋቢት 21
ልጆች ከይሖዋ የተገኙ ውርሻ ናቸው።—መዝ. 127:3
ልጆችን መንከባከብ ብዙ ጊዜና ጉልበት ይጠይቃል፤ ደግሞም ወላጆች ለልጆቻቸው እንዲህ ማድረጋቸው ተገቢ ነው። ስለዚህ ባለትዳሮች በላይ በላዩ የሚወልዱ ከሆነ ለእያንዳንዱ ልጅ የሚያስፈልገውን ትኩረት ለመስጠት ሊቸገሩ ይችላሉ። አከታትለው ልጆች የወለዱ አንዳንድ ባለትዳሮች ነገሮች ከአቅማቸው በላይ ሆነውባቸው እንደነበር ሳይሸሽጉ ተናግረዋል። አንዲት እናት ኃይሏ እንደተሟጠጠና እንደዛለች ሊሰማት ይችላል። ይህ ደግሞ አዘውትራ ለማጥናት፣ ለመጸለይና በአገልግሎት ለመካፈል የሚያስችል ብርታት እንዳይኖራት ሊያደርግ ይችላል። ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚያጋጥመው ሌላው ተፈታታኝ ነገር ደግሞ በስብሰባዎች ላይ በትኩረት ማዳመጥ አለመቻል ነው። እርግጥ ነው፣ አፍቃሪ የሆነ አንድ ባል በስብሰባ ላይም ሆነ ቤት ውስጥ ልጆቻቸውን በመንከባከብ ረገድ ሚስቱን ለማገዝ የሚችለውን ያደርጋል። ለምሳሌ፣ የቤት ውስጥ ሥራዎችን በመሥራት ሚስቱን ሊረዳት ይችላል። ሁሉንም ሊጠቅም የሚችል ቋሚ የሆነ የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራም እንዲኖር ለማድረግ ጠንክሮ ይሠራል። በተጨማሪም ክርስቲያን አባቶች ከቤተሰባቸው አባላት ጋር አዘውትረው በአገልግሎት ይካፈላሉ። w19.12 24 አን. 8
ሰኞ፣ መጋቢት 22
ሃምሳኛው ዓመት ለእናንተ ኢዮቤልዩ ይሆንላችኋል።—ዘሌ. 25:11
ኢዮቤልዩ እስራኤላውያንን የጠቀማቸው እንዴት ነበር? ዕዳ ውስጥ የገባን አንድ እስራኤላዊ እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ ይህ ሰው ዕዳውን ለመክፈል ሲል መሬቱን ለመሸጥ ተገደደ። በኢዮቤልዩ ዓመት ይህ ሰው መሬቱ ይመለስለታል። በመሆኑም ሰውየው ‘ወደ ርስቱ ይመለሳል’፤ ለልጆቹ የሚያወርሰው ርስትም ይኖረዋል። በሌላ በኩል ደግሞ አንድ እስራኤላዊ ያለበትን ዕዳ ለመክፈል ሲል ከልጆቹ አንዱን ወይም ራሱን ለባርነት ይሸጥ ይሆናል። በኢዮቤልዩ ዓመት ግን ባሪያ ሆኖ የተሸጠው ሰው ‘ወደ ቤተሰቡ ይመለሳል።’ (ዘሌ. 25:10) በመሆኑም ነፃ የመውጣት አጋጣሚ ሳይኖረው ለዘላለም ባሪያ ሆኖ የሚቀር ሰው አይኖርም! በተጨማሪም ይሖዋ ለእስራኤል ሕዝብ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “አምላክህ ይሖዋ ርስት አድርገህ እንድትወርሳት በሚሰጥህ ምድር ላይ ይሖዋ ስለሚባርክህ ከእናንተ መካከል ማንም ድሃ አይሆንም።” (ዘዳ. 15:4) ይህ ሁኔታ፣ በሀብታሞችና በድሆች መካከል ያለው ልዩነት በጣም እየሰፋ በሚሄድበት በዚህ ዓለም ላይ ከሚታየው ነገር ምንኛ የተለየ ነው! w19.12 8-9 አን. 3-4
ማክሰኞ፣ መጋቢት 23
ልጄ ሆይ . . . ጥበበኛ ሁን፤ ልቤንም ደስ አሰኘው።—ምሳሌ 27:11
ኢየሱስ ፈተና ሲያጋጥመው “በከፍተኛ ለቅሶና እንባ” ጸልዮአል። (ዕብ. 5:7) አጥብቆ መጸለዩ ለይሖዋ ታማኝ ለመሆን ያለውን ፍላጎት የሚያሳይ ከመሆኑም ሌላ በታዛዥነት ለመጽናት ያለውን ቁርጠኝነት አጠናክሮለታል። ኢየሱስ ያቀረበው ጸሎት በይሖዋ ፊት ጥሩ መዓዛ እንዳለው ዕጣን ነበር። ኢየሱስ በምድር ላይ ባሳለፈው ሕይወት የይሖዋን ልብ በጣም ደስ ያሰኘ ከመሆኑም ሌላ አባቱ ሉዓላዊነቱን የሚጠቀምበት መንገድ ትክክለኛ መሆኑን አረጋግጧል። እኛም ንጹሕ አቋማችንን ጠብቀን ለመኖርና በሕይወታችን ውስጥ የይሖዋን ሕጎች በታማኝነት ለመታዘዝ የቻልነውን ሁሉ በማድረግ የኢየሱስን ምሳሌ መከተል እንችላለን። ይሖዋን ማስደሰት ስለምንፈልግ፣ ፈተናዎች ሲያጋጥሙን የእሱን እርዳታ ለማግኘት አጥብቀን እንጸልያለን። እነዚህን ነገሮች በማድረግ፣ የይሖዋን አገዛዝ እንደምንደግፍ ማሳየት እንችላለን። ይሖዋ የሚያወግዘውን ነገር የምናደርግ ከሆነ ጸሎታችን ተሰሚነት እንደማይኖረው እናውቃለን። በሌላ በኩል ደግሞ ከይሖዋ መሥፈርቶች ጋር በሚስማማ መንገድ የምንኖር ከሆነ የምናቀርበው ከልብ የመነጨ ጸሎት በይሖዋ ፊት ጥሩ መዓዛ እንዳለው ዕጣን እንደሚሆን መተማመን እንችላለን። እንዲሁም ንጹሕ አቋማችንን መጠበቃችንና በታማኝነት መታዘዛችን የሰማዩን አባታችንን እንደሚያስደስተው እርግጠኞች መሆን እንችላለን። w19.11 21-22 አን. 7-8
የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች፦ ኒሳን 9) ሉቃስ 19:29-44
ረቡዕ፣ መጋቢት 24
ታማኝና ልባም ባሪያ በእርግጥ ማን ነው?—ማቴ. 24:45
በ1919 ኢየሱስ የተወሰኑ ቅቡዓን ወንድሞችን “ታማኝና ልባም ባሪያ” አድርጎ ሾማቸው። ይህ ባሪያ የስብከቱን ሥራ የሚመራ ከመሆኑም ሌላ ለክርስቶስ ተከታዮች “በተገቢው ጊዜ ምግባቸውን” ይሰጣቸዋል። ለመሆኑ አምላክ ታማኝና ልባም ባሪያን እንደሚደግፈው የሚያሳይ ግልጽ ማስረጃ አለ? ሰይጣንና በእሱ ቁጥጥር ሥር ያለው ዓለም፣ የታማኝና ልባም ባሪያን ሥራ ተፈታታኝ እንዲያውም ከሰብዓዊ አመለካከት አንጻር የማይቻል እንዲሆን ለማድረግ ያልቆፈሩት ጉድጓድ የለም። ሁለት የዓለም ጦርነቶች ከመካሄዳቸውና ዓለም አቀፍ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ከመከሰቱም ሌላ የአምላክ ሕዝቦች የማያባራ ስደት እንዲሁም ግፍ ደርሶባቸዋል፤ እነዚህ ሁሉ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ቢኖሩም ታማኝና ልባም ባሪያ በምድር ላይ ላሉት የክርስቶስ ተከታዮች መንፈሳዊ ምግብ ማቅረቡን አላቋረጠም። በዛሬው ጊዜ ከ900 በሚበልጡ ቋንቋዎች ያለምንም ክፍያ የምናገኘውን የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ እስቲ አስበው! ይህም ታማኙ ባሪያ መለኮታዊ ድጋፍ እንዳለው የሚያሳይ የማያሻማ ማስረጃ ነው። የይሖዋ በረከት የሚታይበትን ሌላ አቅጣጫ ይኸውም የስብከቱን ሥራም ለማሰብ ሞክር። ምሥራቹ “በመላው ምድር” ላይ እየተሰበከ እንደሆነ በግልጽ እየታየ ነው።—ማቴ. 24:14፤ w19.11 24 አን. 15-16
የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች፦ ኒሳን 10) ሉቃስ 19:45-48፤ ማቴዎስ 21:18, 19, 12, 13
ሐሙስ፣ መጋቢት 25
ክርስቶስ . . . አምላካዊ ፍርሃት [ስለነበረው] ጸሎቱ ተሰማለት።—ዕብ. 5:7
በዓመታዊው የስርየት ቀን ሊቀ ካህናቱ መሥዋዕቶቹን ከማቅረቡ በፊት ዕጣኑን ማጨስ ነበረበት። ይህን ማድረጉ፣ መሥዋዕቱን ከማቅረቡ በፊት የአምላክን ሞገስ ለማግኘት ያስችለዋል። ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት፣ ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ ከማቅረቡ በፊት ሊያከናውነው የሚገባ በጣም አስፈላጊ ነገር ነበር፤ ይህም ለሰው ልጆች መዳን ከማስገኘት ይበልጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር ነበር። ታዲያ ሊያከናውነው የሚገባው ነገር ምን ነበር? በምድር ላይ ባሳለፈው ሕይወት በሙሉ ንጹሕ አቋሙን መጠበቅና በታማኝነት መመላለስ ነበረበት፤ የሚያቀርበው መሥዋዕት በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት የሚያገኘው እንዲህ ካደረገ ነው። ኢየሱስ ይህን በማድረግ፣ ሕይወታችንን ልንመራበት የሚገባው ትክክለኛው አካሄድ የይሖዋን መሥፈርቶች መከተል እንደሆነ አሳይቷል። ኢየሱስ፣ የአባቱ ሉዓላዊነት ማለትም አገዛዙ ትክክለኛና ፍትሐዊ መሆኑን አረጋግጧል። ኢየሱስ በምድር ላይ ባሳለፈው ሕይወት ሁሉ የይሖዋን የጽድቅ መሥፈርቶች ፍጹም በሆነ መንገድ ታዟል። ምንም ዓይነት ፈተና ወይም መከራ ቢደርስበትም ሌላው ቀርቶ ተሠቃይቶ እንደሚሞት ቢያውቅም እንኳ የአባቱን አገዛዝ ከመደገፍ ወደኋላ አላለም።—ፊልጵ. 2:8፤ w19.11 21 አን. 6-7
የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች፦ ኒሳን 11) ሉቃስ 20:1-47
ዓርብ፣ መጋቢት 26
እናንተ በፈተናዎቼ ከጎኔ ሳትለዩ ቆይታችኋል።—ሉቃስ 22:28
በፈተና በተሞላው የኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎት ወቅት ታማኝ ሐዋርያቱ የኢየሱስ እውነተኛ ወዳጆች መሆናቸውን አስመሥክረዋል። (ምሳሌ 18:24) ኢየሱስ እንዲህ ላሉት ወዳጆቹ ከፍ ያለ ግምት ነበረው። አገልግሎቱን ባከናወነባቸው ጊዜያት ከሥጋ ወንድሞቹ መካከል አንዳቸውም አላመኑበትም ነበር። (ዮሐ. 7:3-5) እንዲያውም በአንድ ወቅት ዘመዶቹ አእምሮውን እንደሳተ ሰው ቆጥረውታል። (ማር. 3:21) ከዚህ በተቃራኒ ግን ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ላይ ታማኝ ሐዋርያቱን አስመልክቶ በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ያለውን ሐሳብ ተናግሯል። እርግጥ ነው፣ ሐዋርያቱ ኢየሱስን የሚያሳዝን ድርጊት የፈጸሙባቸው ጊዜያት ነበሩ፤ ኢየሱስ ግን በሠሯቸው ስህተቶች ላይ ከማተኮር ይልቅ በእሱ ላይ ያላቸውን እምነት ተመልክቷል። (ማቴ. 26:40፤ ማር. 10:13, 14፤ ዮሐ. 6:66-69) ከመገደሉ በፊት ከእነሱ ጋር ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት ላይ ታማኝ ደቀ መዛሙርቱን “ከአባቴ የሰማሁትን ነገር ሁሉ ስላሳወቅኳችሁ ወዳጆች ብዬ ጠርቻችኋለሁ” ብሏቸዋል። (ዮሐ. 15:15) የኢየሱስ ወዳጆች ከፍተኛ የብርታት ምንጭ እንደሆኑለት ምንም ጥርጥር የለውም። w19.04 11 አን. 11-12
የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች፦ ኒሳን 12) ሉቃስ 22:1-6፤ ማርቆስ 14:1, 2, 10, 11
የመታሰቢያው በዓል የሚከበርበት ዕለት
ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ
ቅዳሜ፣ መጋቢት 27
የአምላክ ልጆች መሆናችንን ይህ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ሆኖ ይመሠክራል።—ሮም 8:16
አንድ ሰው ሰማያዊ ጥሪ ማግኘቱን የሚያውቀው እንዴት ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ቅዱሳን እንዲሆኑ ለተጠሩት’ በሮም ለሚገኙ ክርስቲያኖች የጻፈው ደብዳቤ ለዚህ ግልጽ መልስ ይሆናል። ጳውሎስ በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ከሰፈረው ሐሳብ በተጨማሪ እንዲህ ብሏቸዋል፦ “ዳግመኛ ለፍርሃት የሚዳርጋችሁን የባርነት መንፈስ አልተቀበላችሁም፤ ከዚህ ይልቅ አምላክ ልጆቹ አድርጎ እንዲወስዳችሁ የሚያስችል መንፈስ አግኝታችኋል፤ ይህም መንፈስ ‘አባ፣ አባት!’ ብለን እንድንጣራ ይገፋፋናል።” (ሮም 1:7፤ 8:15) ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው ቅቡዓን ክርስቲያኖች ሰማያዊ ጥሪ ማግኘታቸውን አምላክ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ግልጽ ያደርግላቸዋል። (1 ተሰ. 2:12) ይሖዋ፣ ሰማያዊ ጥሪ ያቀረበላቸው ክርስቲያኖች ስለዚህ ጉዳይ በልባቸው ውስጥ አንዳች ጥርጣሬ እንዳያድር ያደርጋል። (1 ዮሐ. 2:20, 27) ቅቡዓን ክርስቲያኖች ለመቀባታቸው ማረጋገጫ የሚሰጣቸው ሌላ አካል አያስፈልጋቸውም። w20.01 22 አን. 7-8
የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች፦ ኒሳን 13) ሉቃስ 22:7-13፤ ማርቆስ 14:12-16 (ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ የተከናወኑ ነገሮች፦ ኒሳን 14) ሉቃስ 22:14-65
እሁድ፣ መጋቢት 28
ሕይወቱን ለወዳጆቹ ሲል አሳልፎ ከሚሰጥ ሰው የበለጠ ፍቅር ያለው ማንም የለም።—ዮሐ. 15:13
‘የክርስቶስ ሕግ’ ከሁሉ በተሻለ መሠረት ላይ ይኸውም በፍቅር ላይ የተገነባ ነው። (ገላ. 6:2) ኢየሱስ ማንኛውንም ነገር ያደርግ የነበረው በፍቅር ተነሳስቶ ነው። ፍቅር የሚገለጸው ደግሞ ለሌሎች ባለን የርኅራኄ ወይም የአዘኔታ ስሜት ነው። ኢየሱስ በርኅራኄ ተነሳስቶ ሕዝቡን አስተምሯል፣ የታመሙትን ፈውሷል፣ የተራቡትን መግቧል እንዲሁም የሞቱትን አስነስቷል። (ማቴ. 14:14፤ 15:32-38፤ ማር. 6:34፤ ሉቃስ 7:11-15) እነዚህን ነገሮች ማከናወን፣ ጊዜውንና ጉልበቱን መሥዋዕት ማድረግ የሚጠይቅበት ቢሆንም ከራሱ ይልቅ የሌሎችን ፍላጎት ለማስቀደም ፈቃደኛ ሆኗል። ከሁሉ በላይ ደግሞ ለሰው ልጆች ሲል ሕይወቱን አሳልፎ በመስጠት ታላቅ ፍቅር አሳይቷል። ከራሳችን ይልቅ ለሌሎች ሰዎች ፍላጎት ቅድሚያ በመስጠት የኢየሱስን ምሳሌ መከተል እንችላለን። በተጨማሪም በአገልግሎት ክልላችን ውስጥ ላሉ ሰዎች ርኅራኄ ለማሳየት ጥረት በማድረግ የኢየሱስን አርዓያ እንከተላለን። በርኅራኄ ተነሳስተን ምሥራቹን በመስበክና ሰዎችን በማስተማር የክርስቶስን ሕግ እንደምንታዘዝ እናሳያለን። w19.05 4 አን. 8-10
የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች፦ ኒሳን 14) ሉቃስ 22:66-71
ሰኞ፣ መጋቢት 29
[ይሖዋ] ለተማረኩት ነፃነትን . . . እንዳውጅ፣ የተጨቆኑትን ነፃ እንዳወጣ [ልኮኛል]።—ሉቃስ 4:18
ኢየሱስ የሃይማኖት መሪዎቹ ከሚያስተምሯቸው በሕዝቡ ላይ ጫና የሚያሳድሩ ትምህርቶች ነፃ መውጣት የሚቻልበትን መንገድ ከፍቷል። በዚያ ዘመን የነበሩ በርካታ አይሁዳውያን በተለያዩ ወጎችና በተሳሳቱ እምነቶች ባርነት ሥር ነበሩ። (ማቴ. 5:31-37፤ 15:1-11) መንፈሳዊ መመሪያ እንዲሰጡ የሚጠበቅባቸው ሰዎች ደግሞ ታውረው ነበር ማለት ይቻላል። መሲሑንና እሱ ያስገኘውን መንፈሳዊ ብርሃን ለመቀበል ፈቃደኞች ባለመሆናቸው በጨለማ ውስጥ እንዲሁም በኃጢአት ባርነት ሥር ለመኖር መርጠዋል። (ዮሐ. 9:1, 14-16, 35-41) ኢየሱስ ግን ትክክለኛ ትምህርቶችን በማስተማርና ጥሩ ምሳሌ በመተው፣ መንፈሳዊ ነፃነት የሚገኝበትን መንገድ ለቅኖች አሳውቋል። (ማር. 1:22፤ 2:23 እስከ 3:5) ሁለተኛ፣ ኢየሱስ የሰው ልጆች ከአዳም የወረሱት ኃጢአት ካስከተለባቸው ባርነት ነፃ መውጣት የሚችሉበትን መንገድ ከፍቷል። የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ስለተከፈለ አምላክ፣ እምነት ያላቸውንና እሱ ያዘጋጀውን ቤዛ የሚቀበሉ ሰዎችን ኃጢአት ይቅር ማለት ይችላል።—ዕብ. 10:12-18፤ w19.12 10 አን. 8፤ 11 አን. 10-11
የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች፦ ኒሳን 15) ማቴዎስ 27:62-66
ማክሰኞ፣ መጋቢት 30
ካመናችሁ በኋላ በእሱ አማካኝነት፣ ቃል በተገባው መንፈስ ቅዱስ ታትማችኋል፤ ይህም . . . ለውርሻችን አስቀድሞ የተሰጠ ማረጋገጫ ነው።—ኤፌ. 1:13, 14 ግርጌ
ከዚህ ለማየት እንደሚቻለው ይሖዋ፣ ቅዱስ መንፈሱን በመጠቀም ቅቡዓን ክርስቲያኖች መመረጣቸውን ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ እንዲሆኑ ያደርጋል። ከዚህ አንጻር መንፈስ ቅዱስ፣ ወደፊት በምድር ላይ ሳይሆን በሰማይ የዘላለም ሕይወት እንደሚያገኙ እንዲተማመኑ ለማድረግ ለእነዚህ ክርስቲያኖች የሚሰጣቸው “ማረጋገጫ [ዋስትና ወይም መያዣ]” ነው። (2 ቆሮ. 1:21, 22) አንድ ክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስ ስለተቀባ ብቻ ሰማያዊ ሽልማቱን በእርግጠኝነት ያገኛል ማለት ነው? አይደለም። ይህ ክርስቲያን ወደ ሰማይ ለመሄድ እንደተመረጠ እርግጠኛ ነው። ያም ቢሆን የሚከተለውን ማሳሰቢያ ማስታወስ ይኖርበታል፦ “ወንድሞች፣ መጠራታችሁንና መመረጣችሁን አስተማማኝ ለማድረግ ከበፊቱ ይበልጥ ትጉ፤ እነዚህን ነገሮች የምታደርጉ ከሆነ ፈጽሞ አትወድቁም።” (2 ጴጥ. 1:10) ከዚህ ለማየት እንደሚቻለው አንድ ቅቡዕ ክርስቲያን ወደ ሰማይ ለመሄድ ቢመረጥም ወይም ቢጠራም፣ ሽልማቱን የሚያገኘው ታማኝ ሆኖ ከጸና ብቻ ነው።—ፊልጵ. 3:12-14፤ ዕብ. 3:1፤ ራእይ 2:10፤ w20.01 21-22 አን. 5-6
የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች፦ ኒሳን 16) ሉቃስ 24:1-12
ረቡዕ፣ መጋቢት 31
ሳይታሰብበት የሚነገር ቃል እንደ ሰይፍ ይወጋል፤ የጥበበኞች ምላስ ግን ፈውስ ነው።—ምሳሌ 12:18
ሦስቱ የኢዮብ አጽናኞች ለእሱ ርኅራኄ ማሳየት እንዲከብዳቸው ያደረገው አንዱ ምክንያት፣ ያጋጠመውን ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ለመረዳት አለመሞከራቸው ነው። በዚህም የተነሳ የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ ስለደረሱ ያለርኅራኄ በኢዮብ ላይ ፈርደዋል። እኛስ ተመሳሳይ ስህተት እንዳንሠራ ምን ሊረዳን ይችላል? አንድ ሰው ስላለበት ሁኔታ የተሟላ መረጃ ያለው፣ ይሖዋ ብቻ መሆኑን እናስታውስ። ችግር የደረሰበት ሰው የሚናገረውን ነገር በትኩረት እናዳምጥ። የሚናገረው ነገር ብቻ ሳይሆን ሥቃዩም ይሰማን። የወንድማችንን ወይም የእህታችንን ስሜት መረዳት የምንችለው እንዲህ ካደረግን ብቻ ነው። ርኅራኄ፣ ሌሎች ከገጠማቸው ችግር ጋር በተያያዘ ሐሜት ከማሰራጨት እንድንቆጠብ ያደርገናል። ሐሜተኛ ሰው ጉባኤውን ከማነጽ ይልቅ መከፋፈል እንዲፈጠር ያደርጋል። (ምሳሌ 20:19፤ ሮም 14:19) መከራ እየደረሰበት ያለውን ሰው ይበልጥ ይጎዳዋል። (ኤፌ. 4:31, 32) በግለሰቡ መልካም ባሕርያት ላይ ትኩረት ማድረጋችንና ያጋጠሙትን ችግሮች ለመቋቋም እንዴት ልንረዳው እንደምንችል ማሰባችን ምንኛ የተሻለ ይሆናል! w19.06 21-22 አን. 8-9