የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • es21 ገጽ 17-26
  • የካቲት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የካቲት
  • ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2021
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ሰኞ፣ የካቲት 1
  • ማክሰኞ፣ የካቲት 2
  • ረቡዕ፣ የካቲት 3
  • ሐሙስ፣ የካቲት 4
  • ዓርብ፣ የካቲት 5
  • ቅዳሜ፣ የካቲት 6
  • እሁድ፣ የካቲት 7
  • ሰኞ፣ የካቲት 8
  • ማክሰኞ፣ የካቲት 9
  • ረቡዕ፣ የካቲት 10
  • ሐሙስ፣ የካቲት 11
  • ዓርብ፣ የካቲት 12
  • ቅዳሜ፣ የካቲት 13
  • እሁድ፣ የካቲት 14
  • ሰኞ፣ የካቲት 15
  • ማክሰኞ፣ የካቲት 16
  • ረቡዕ፣ የካቲት 17
  • ሐሙስ፣ የካቲት 18
  • ዓርብ፣ የካቲት 19
  • ቅዳሜ፣ የካቲት 20
  • እሁድ፣ የካቲት 21
  • ሰኞ፣ የካቲት 22
  • ማክሰኞ፣ የካቲት 23
  • ረቡዕ፣ የካቲት 24
  • ሐሙስ፣ የካቲት 25
  • ዓርብ፣ የካቲት 26
  • ቅዳሜ፣ የካቲት 27
  • እሁድ፣ የካቲት 28
ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2021
es21 ገጽ 17-26

የካቲት

ሰኞ፣ የካቲት 1

[ይሖዋ] ፍትሕን ይወዳል።—መዝ. 33:5

“ፍትሕ” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሠራበት፣ በአምላክ ዓይን ትክክል የሆነውን ነገር ያለምንም አድልዎ ማድረግን ለማመልከት ነው። ኢየሱስ ያደረጋቸው ነገሮች እሱ ለፍትሕ ያለውን አመለካከት የሚያንጸባርቁት እንዴት እንደሆነ እንመልከት። በኢየሱስ ዘመን የነበሩት የአይሁድ የሃይማኖት መሪዎች አይሁዳዊ ያልሆኑ ሰዎችን ይጠሉ፣ ሃይማኖታዊ ትምህርት ያልተማሩ አይሁዳውያንን ያንቋሽሹ እንዲሁም ሴቶችን ይንቁ ነበር። ኢየሱስ ግን ሁሉንም ፍትሐዊ በሆነና አድልዎ በሌለበት መንገድ ይይዝ ነበር። አይሁዳዊ ያልሆኑ ሰዎች በእምነት ወደ እሱ ሲቀርቡ በደስታ ተቀብሏቸዋል። (ማቴ. 8:5-10, 13) ሀብታም ድሃ ሳይል ለሁሉም ያለአድልዎ ሰብኳል። (ማቴ. 11:5፤ ሉቃስ 19:2, 9) ሴቶችን ዝቅ የሚያደርግ ወይም የሚያንቋሽሽ ነገር በጭራሽ አድርጎ አያውቅም። ከዚህ በተቃራኒ፣ በሌሎች ዘንድ ዝቅ ተደርገው የሚታዩ ሴቶችን ጨምሮ ሁሉንም ሴቶች በአክብሮትና በደግነት ይይዝ ነበር። (ሉቃስ 7:37-39, 44-50) ሌሎችን ከአድልዎ ነፃ በሆነ መንገድ በመያዝ እንዲሁም የኑሮ ደረጃቸው ወይም ሃይማኖታቸው ምንም ሆነ ምን፣ ምሥራቹን ለመስማት ፈቃደኛ ለሆኑ ሁሉ በመስበክ ኢየሱስን መምሰል እንችላለን። ክርስቲያን ወንዶች ለሴቶች አክብሮት በማሳየት ኢየሱስን መምሰል ይችላሉ። w19.05 2 አን. 1፤ 5 አን. 15-17

ማክሰኞ፣ የካቲት 2

የምታጠባ እናት ልጆቿን በፍቅር እንደምትንከባከብ እኛም በመካከላችሁ በነበርንበት ጊዜ በገርነት ተንከባከብናችሁ።—1 ተሰ. 2:7

በዛሬው ጊዜ ያሉ ታማኝ ሽማግሌዎችም ለተጎዱት ቅዱስ ጽሑፋዊ ማጽናኛ ለመስጠት ደግነትና ገርነት የተንጸባረቀባቸው ቃላት ይጠቀማሉ። ፆታዊ ጥቃት የተፈጸመባቸውን ሰዎች የማጽናናት ኃላፊነት ያለባቸው ሽማግሌዎች ብቻ ናቸው? አይደሉም። እያንዳንዱ ክርስቲያን “ሁልጊዜ እርስ በርሳችሁ ተጽናኑ” የሚለውን ምክር ተግባራዊ የማድረግ ኃላፊነት አለበት። (1 ተሰ. 4:18) በተለይም በመንፈሳዊ የጎለመሱ እህቶች፣ ማጽናኛ የሚያስፈልጋቸውን እህቶች ሊያጽናኗቸው ይችላሉ። ይሖዋ አምላክ ራሱን ልጇን ከምታጽናና እናት ጋር ማመሳሰሉ የተገባ ነው። (ኢሳ. 66:13) መጽሐፍ ቅዱስ በጭንቀት የተዋጡ ሰዎችን ስላጽናኑ ሴቶች ይናገራል። (ኢዮብ 42:11) በዛሬው ጊዜም ይሖዋ ስሜታዊ ሥቃይ ያለባቸውን እህቶቻቸውን ለማጽናናት የሚሞክሩ ክርስቲያን ሴቶችን ሲያይ ምንኛ ይደሰት ይሆን! አንዳንድ ጊዜ ሽማግሌዎች በመንፈሳዊ የጎለመሰችን አንዲት እህት ፆታዊ ጥቃት የተፈጸመባትን እህት እንድታጽናና በጥበብ ሊጠይቋት ይችላሉ። እርግጥ ነው፣ የእምነት ባልንጀራችን ሚስጥር አድርጎ መያዝ የሚፈልጋቸውን ነገሮች ለማውጣጣት እንዳንሞክር መጠንቀቅ አለብን።—1 ተሰ. 4:11፤ w19.05 16-17 አን. 10-12

ረቡዕ፣ የካቲት 3

ማንኛውም ጉዳይ ሁለት ወይም ሦስት ምሥክሮች በሚሰጡት የምሥክርነት ቃል [ይጸናል]።—ማቴ. 18:16

የጉባኤ ሽማግሌዎች አንድን ጉዳይ በተመለከተ የፍርድ እርምጃ ከመውሰዳቸው በፊት ቢያንስ ሁለት ምሥክሮች የሚያስፈልጉት ለምንድን ነው? ላቅ ያለው የመጽሐፍ ቅዱስ የፍትሕ መሥፈርት እንዲህ እንዲደረግ ስለሚጠይቅ ነው። ግለሰቡ ኃጢአቱን ካልተናዘዘ ሽማግሌዎች ክስ መመሥረትና የፍርድ ኮሚቴ ማቋቋም እንዲችሉ ሁለት ምሥክሮች ያስፈልጋሉ። (ዘዳ. 19:15፤ 1 ጢሞ. 5:19) ክሱ የቀረበበት ግለሰብ ድርጊቱን እንዳልፈጸመ ከተናገረ ሽማግሌዎች ምሥክሮች የሚሰጡትን ቃል ይመረምራሉ። ክሱ ቢያንስ በሁለት ሰዎች ማለትም ክሱን ባቀረበው ሰውና ሊመሠክር በሚችል ሌላ ሰው ከተረጋገጠ የፍርድ ኮሚቴ ይቋቋማል። ሁለተኛ ምሥክር አልተገኘም ማለት ክሱን ያቀረበው ሰው ዋሽቷል ማለት አይደለም። አንድ ክስ በሁለት ምሥክሮች ባይረጋገጥ እንኳ ሽማግሌዎች ከባድ ኃጢአት ተፈጽሞ ሊሆን እንደሚችል ይገነዘባሉ። በመሆኑም ለተጎዱት ሰዎች ቀጣይ የሆነ ድጋፍ ያደርጋሉ፤ እንዲሁም በጉባኤው ላይ ጉዳት ሊያስከትል ስለሚችል ሽማግሌዎች በቅርበት ይከታተሉታል።—ሥራ 20:28፤ w19.05 11 አን. 15-16

ሐሙስ፣ የካቲት 4

እድገትህ በሁሉም ሰዎች ዘንድ በግልጽ እንዲታይ በእነዚህ ነገሮች ላይ አሰላስል።—1 ጢሞ. 4:15

ልጆች እንዴት ማጥናት እንደሚችሉ መማራቸው አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ ለጉባኤ ስብሰባዎች እንዴት መዘጋጀት እንደሚችሉ ወይም በትምህርት ቤት ባጋጠማቸው ጉዳይ ላይ ምርምር ማድረግ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ መማር አለባቸው። (ዕብ. 5:14) ልጆች ጊዜ ወስደው ስለ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ርዕሰ ጉዳይ የማጥናት ልማድ ካዳበሩ በጉባኤ፣ በወረዳና በክልል ስብሰባዎች ላይ የሚቀርቡትን ንግግሮች መከታተል ቀላል ይሆንላቸዋል። እርግጥ ነው፣ ለእያንዳንዱ የጥናት ፕሮግራም የምንመድበው ጊዜ ርዝማኔ የልጆቹን ዕድሜና ባሕርይ ያገናዘበ መሆን ይኖርበታል። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችንም እንዴት ማጥናት እንደሚችሉ መማር አለባቸው። አዲሶች ሳሉ ለጥናታቸው ወይም ለጉባኤ ስብሰባዎች ሲዘጋጁ መልሱን አስምረው ስለመጡ ብቻ ደስ ይለናል። ሆኖም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን ራሳቸውን ችለው ምርምር ማድረግና ትርጉም ባለው መንገድ ማጥናት እንዲችሉ ልናሠለጥናቸው ይገባል። ይህም ችግር ሲያጋጥማቸው በጽሑፎቻችን ላይ ምርምር አድርገው ጠቃሚ ምክር እንዲያገኙ ይረዳቸዋል። w19.05 26 አን. 2፤ 28 አን. 10-11

ዓርብ፣ የካቲት 5

ስለ አምላክ የሚገልጸውን እውቀት የሚጻረሩ የተሳሳቱ ሐሳቦችንና ይህን እውቀት የሚያግድን ማንኛውንም ከፍ ያለ ነገር እናፈርሳለን።—2 ቆሮ. 10:5

ሰይጣን አስተሳሰባችንን ለመቀየር ቆርጦ ተነስቷል። በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘው እውነት የሚያሳድረውን በጎ ተጽዕኖ ለማፍረስ፣ ስህተት የሆኑ የተለያዩ ሐሳቦችን ይጠቀማል። ሰይጣን በኤደን ገነት ውስጥ ሔዋንን የጠየቃትን ዓይነት ጥያቄ ዛሬም ያቀርባል፤ ሔዋንን “በእርግጥ አምላክ [እንዲህ] ብሏችኋል?” በማለት ጠይቋት ነበር። (ዘፍ. 3:1) በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ባለው በዚህ ዓለም ውስጥም ጥርጣሬ የሚፈጥሩ እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎች ሲነሱ እንሰማለን፦ ‘በእርግጥ አምላክ ግብረ ሰዶማዊነትን ያወግዛል? በእርግጥ አምላክ ገናን እና ልደትን እንዳታከብሩ ይከለክላል? በእርግጥ አምላካችሁ ደም እንዳትወስዱ ያዛል? በእርግጥ አፍቃሪ የሆነ አምላክ ከተወገዱ ቤተሰቦቻችሁና ጓደኞቻችሁ ጋር እንዳትቀራረቡ ይጠብቅባችኋል?’ የምናምንባቸው ነገሮች ትክክል ስለመሆናቸው ሙሉ በሙሉ እርግጠኞች ልንሆን ይገባል። ስለምናምንባቸው ነገሮች ለሚፈጠሩብን ጥያቄዎች መልስ ካላገኘን በውስጣችን ጥርጣሬ ሊያቆጠቁጥ ይችላል። እንዲህ ያለው ጥርጣሬ ደግሞ ውሎ አድሮ አስተሳሰባችንን ሊያዛባውና እምነታችንን ሊያጠፋው ይችላል። w19.06 12-13 አን. 15-17

ቅዳሜ፣ የካቲት 6

ሁላችሁም የአስተሳሰብ አንድነት ይኑራችሁ፤ የሌላውን ስሜት የምትረዱ ሁኑ፤ የወንድማማች መዋደድ ይኑራችሁ፤ ከአንጀት የምትራሩ ሁኑ፤ ትሑታን ሁኑ።—1 ጴጥ. 3:8

ይሖዋ በጣም ይወደናል። (ዮሐ. 3:16) እኛም አፍቃሪውን አባታችንን መምሰል እንፈልጋለን። በመሆኑም ‘የሌላውን ስሜት ለመረዳት፣ የወንድማማች መዋደድ ለማዳበር እንዲሁም ከአንጀት የምንራራ ለመሆን’ ጥረት እናደርጋለን፤ ለሁሉም ሰው በተለይ ደግሞ “በእምነት ለሚዛመዱን ሰዎች” እነዚህን ባሕርያት እናሳያለን። (ገላ. 6:10) የመንፈሳዊ ቤተሰባችን አባላት፣ አስጨናቂ ሁኔታዎች ሲያጋጥሟቸው ልንረዳቸው እንፈልጋለን። የትዳር ጓደኛውን በሞት ያጣን ሰው ማጽናናት የምንችለው እንዴት ነው? ልናደርገው የሚገባው የመጀመሪያው ነገር ግለሰቡን ማነጋገር ነው፤ ይህን ማድረግ ቢጨንቀን ወይም ምን ማለት እንዳለብን ግራ ቢገባንም እንኳ ሐዘን የደረሰበትን ሰው ከማነጋገር ወደኋላ ማለት የለብንም። ባሏን በድንገት በሞት ያጣችው ፖላ እንዲህ ብላለች፦ “ሰዎች፣ ሐዘን የደረሰበትን ሰው ማዋራት ሊጨንቃቸው እንደሚችል ይገባኛል። ቅር የሚያሰኝ ነገር እንዳይናገሩ ይፈሩ ይሆናል። ሆኖም ምንም ነገር አለመናገራቸው የባሰ እንደሆነ ይሰማኛል።” ሐዘን የደረሰበት ሰው ጥልቀት ያለው ሐሳብ እንድንናገር አይጠብቅብንም። ፖላ “ወዳጆቼ ‘ባለቤትሽን በማጣትሽ በጣም አዝነናል’ ማለታቸው ብቻ ለእኔ በቂ ነው” ብላለች። w19.06 20 አን. 1፤ 23 አን. 14

እሁድ፣ የካቲት 7

ይሖዋ ሆይ፣ ዛቻቸውን ተመልከት፤ ባሪያዎችህም ቃልህን በፍጹም ድፍረት መናገራቸውን እንዲቀጥሉ እርዳቸው።—ሥራ 4:29

በሥራችን ላይ እገዳ ከተጣለ፣ ሽማግሌዎች የተቃዋሚዎችን ትኩረት በማይስብ መልኩ ስብሰባዎች እንዲካሄዱ ዝግጅት ያደርጋሉ። በትናንሽ ቡድኖች እንድንሰበሰብ መመሪያ ይሰጡ እንዲሁም የስብሰባዎቹ ሰዓትና ቦታ በየጊዜው እንዲቀያየር ያደርጉ ይሆናል። ከስብከቱ ሥራ ጋር በተያያዘ ሁኔታው ከቦታ ቦታ ሊለያይ ይችላል። ይሁን እንጂ ይሖዋን ስለምንወድና ስለ መንግሥቱ ለሌሎች መናገር ስለሚያስደስተን ለመስበክ የሚያስችሉ መንገዶችን እንፈልጋለን። (ሉቃስ 8:1) ኤምሊ ብሩደርለ ቤረን የተባሉ የታሪክ ምሁር በቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ስለነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል፦ “የይሖዋ ምሥክሮች ስለ እምነታቸው ለሌሎች እንዳይናገሩ መንግሥት ሲከለክላቸው ለጎረቤቶቻቸው፣ ለሥራ ባልደረቦቻቸውና ለወዳጆቻቸው ይሰብኩ ነበር። ይህን በማድረጋቸው ምክንያት የጉልበት ሥራ ወደሚሠራባቸው ካምፖች ሲላኩ ደግሞ አብረዋቸው የታሰሩ ሰዎችን አማኝ ማድረግ ጀመሩ።” በዚያ የነበሩት ወንድሞቻችን በእገዳ ሥር ቢሆኑም መስበካቸው አላቆሙም። አንተም እንዲህ ዓይነት ቆራጥነት ይኑርህ! w19.07 11 አን. 12-13

ሰኞ፣ የካቲት 8

ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ።—ማቴ. 28:19

ሃይማኖት የሌላቸውን ሰዎች አምላክን እንዲወዱና የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ መርዳት የምንችለው እንዴት ነው? አንድ ሰው ያደገበት አካባቢ ለመልእክታችን በሚሰጠው ምላሽ ላይ ተጽዕኖ ሊያደርግ እንደሚችል መገንዘብ አለብን። ለምሳሌ፣ በአውሮፓ ያደገ ሰው የሚሰጠው ምላሽ ከእስያ የመጣ ሰው ከሚሰጠው ምላሽ የተለየ ሊሆን ይችላል። ለምን? በአውሮፓ የሚኖሩ ብዙዎቹ ሰዎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ በተወሰነ ደረጃ ያውቃሉ፤ እንዲሁም ሁሉንም ነገሮች የፈጠረው አምላክ እንደሆነ ሲነገር ሰምተዋል። እስያ ውስጥ ግን አብዛኞቹ ሰዎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ቢያውቁ እንኳ እውቀታቸው አነስተኛ ነው፤ በፈጣሪ መኖርም ላያምኑ ይችላሉ። ስለዚህ አዎንታዊ ሁኑ። ሃይማኖት የሌላቸው በርካታ ሰዎች በየዓመቱ ተጠምቀው የይሖዋ ምሥክሮች ይሆናሉ። ከእነዚህ መካከል ብዙዎቹ ቀድሞውንም ቢሆን ጥሩ ሥነ ምግባር ያላቸው ሰዎች ሲሆኑ በሃይማኖቶች ውስጥ በሚያዩት ግብዝነት ይመረሩ ነበር። ሌሎቹ ግን ጥሩ ሥነ ምግባር የሌላቸው ነበሩ፤ ብዙዎቹ መጥፎ ልማዶቻቸውን ማስወገድ አስፈልጓቸዋል። በእርግጥም “ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው” ሰዎችን በይሖዋ እርዳታ እንደምናገኝ መተማመን እንችላለን።—ሥራ 13:48፤ 1 ጢሞ. 2:3, 4፤ w19.07 20-21 አን. 3-4

ማክሰኞ፣ የካቲት 9

ተስፋ አንቆርጥም።—2 ቆሮ. 4:16

ተስፋችን ወደ ሰማይ መሄድም ሆነ ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም መኖር፣ ግባችን ላይ ለመድረስ ምንጊዜም መጣጣር ይኖርብናል። ያለንበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን፣ ከኋላችን ያሉትን ነገሮች መርሳት ይኖርብናል፤ እንዲሁም ማንኛውም ነገር ወደፊት ከመጓዝ እንዲያግደን መፍቀድ የለብንም። (ፊልጵ. 3:16) የምንጠብቃቸው ነገሮች እኛ ባሰብነው ጊዜ አይፈጸሙ ይሆናል፤ ወይም አካላዊ ጥንካሬያችን እየቀነሰ ሊሄድ ይችላል። አሊያም ለበርካታ ዓመታት ስደትንና መከራን መቋቋም አስፈልጎን ሊሆን ይችላል። በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ብትሆኑ “ስለ ምንም ነገር አትጨነቁ።” ከዚህ ይልቅ ልመናችሁንና ምልጃችሁን ለአምላክ አቅርቡ፤ እሱም ከምታስቡት ሁሉ በላይ የሆነ ሰላም ይሰጣችኋል። (ፊልጵ. 4:6, 7) አንድ ሯጭ ወደ መጨረሻው መስመር ሲጠጋ ትኩረቱን ውድድሩን በማጠናቀቅ ላይ እንደሚያደርግ ሁሉ እኛም የሕይወትን ሩጫ ለማጠናቀቅ እየተቃረብን በሄድን መጠን ትኩረታችን በሙሉ በሽልማታችን ላይ ይሁን። ከፊታችን የሚጠብቁንን አስደናቂ ነገሮች ለማግኘት አቅማችንና ሁኔታችን በፈቀደው መጠን ከፍተኛ ተጋድሎ ማድረጋችንን እንቀጥል። w19.08 7 አን. 16-17

ረቡዕ፣ የካቲት 10

ከሚያለቅሱ ጋር አልቅሱ።—ሮም 12:15

በሐዘን የተዋጠ የእምነት ባልንጀራችንን ምን ብለን ልናጽናናው እንደምንችል ግራ ይገባን ይሆናል። አንዳንድ ጊዜ፣ አብረነው ማልቀሳችን ብቻ ከምንናገረው ነገር ይበልጥ ስሜታችንን ሊገልጽ ይችላል። የኢየሱስ ወዳጅ አልዓዛር ሲሞት ማርያምና ማርታ ውድ ወንድማቸውን በማጣታቸው፣ ሌሎቹ ሰዎች ደግሞ ወዳጃቸው በመሞቱ አልቅሰዋል። ኢየሱስ ወደ ስፍራው የደረሰው አልዓዛር ከሞተ ከአራት ቀን በኋላ ነበር፤ አልዓዛርን ሊያስነሳው እንደሆነ ቢያውቅም እሱም ‘እንባውን አፍስሷል።’ (ዮሐ. 11:17, 33-35) ኢየሱስ እንባውን ማፍሰሱ ይሖዋ በአልዓዛር ሞት ምን እንደተሰማው ያሳያል። በተጨማሪም ኢየሱስ ለዚህ ቤተሰብ ያለውን ጥልቅ ፍቅር ያረጋግጣል፤ ማርያምና ማርታ ይህን በማወቃቸው በጣም እንደተጽናኑ ምንም ጥርጥር የለውም። በተመሳሳይም ወንድሞቻችን እንደምንወዳቸውና እንደምናስብላቸው ሲመለከቱ ብቻቸውን እንዳልሆኑ እንዲሁም የሚያስቡላቸውና ከጎናቸው የማይለዩ ወዳጆች እንዳሏቸው ይሰማቸዋል። አንዳንድ ጊዜ ጥሩ አድማጭ መሆን ብቻ ሊበቃ ይችላል። የእምነት ባልንጀራችሁ የልቡን አውጥቶ እንዲገልጽ ዕድል ስጡት፤ ‘እንዳመጣለት ቢናገር’ እንኳ ቅር አትሰኙበት። (ኢዮብ 6:2, 3) የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ ዘመዶቹ የሚያደርሱበት ጫና ተጨማሪ ውጥረት ፈጥሮበት ሊሆን ይችላል። ስለዚህ አብራችሁት ጸልዩ። “ጸሎት ሰሚ” የሆነው አምላክ፣ ወንድማችሁ ተረጋግቶ ማሰብ እንዲችል እንዲረዳውና ብርታት እንዲሰጠው ጸልዩ።—መዝ. 65:2፤ w19.04 18-19 አን. 18-19

ሐሙስ፣ የካቲት 11

ልባችሁን በፊቱ አፍስሱ።—መዝ. 62:8

የምናገለግለው መስክ ላይም ሆነ ቤቴል ውስጥ፣ በምድባችን ላይ ላሉት ሰዎች ሌላው ቀርቶ ለምናገለግልበት ቦታ ጭምር ፍቅር ቢኖረን አያስገርምም። ስለዚህ በሆነ ምክንያት ምድባችንን መተው ቢያስፈልገን በእጅጉ ማዘናችን አይቀርም። በምድባችን ላይ የነበሩት ወንድሞችና እህቶች ይናፍቁናል፤ በተለይ ደግሞ ምድባችንን ትተን የሄድነው በስደት ምክንያት ከሆነ የእነሱ ሁኔታ ያሳስበናል። (ማቴ. 10:23፤ 2 ቆሮ. 11:28, 29) ከዚህም ሌላ በማናውቀው አካባቢ እንድናገለግል ስንመደብ ወይም ወደ ትውልድ አገራችን ተመልሰን ስንሄድ እንኳ የባሕል ለውጥ ሊያጋጥመን ይችላል። የአገልግሎት ምድባቸው የተለወጠ አንዳንድ ክርስቲያኖች ደግሞ ያልተጠበቁ ወጪዎች ያጋጥሟቸው ይሆናል። እነዚህ ክርስቲያኖች ግራ ይጋቡ፣ ስጋት ያድርባቸውና ተስፋ ይቆርጡ ይሆናል። ታዲያ ምን ሊረዳቸው ይችላል? ወደ ይሖዋ ይበልጥ ቅረቡ። (ያዕ. 4:8) ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? “ጸሎት ሰሚ” በሆነው አምላክ በመታመን ነው። (መዝ. 65:2) ይሖዋ “ከምንጠይቀው ወይም ከምናስበው ሁሉ በላይ እጅግ አብልጦ ማድረግ” ይችላል። (ኤፌ. 3:20) ይሖዋ በጸሎታችን ላይ ለይተን የጠየቅነውን ነገር በመስጠት ብቻ አይወሰንም። ለችግሮቻችን መፍትሔ ለመስጠት ሲል በፍጹም ያላሰብነውንና ጨርሶ ያልጠበቅነውን ነገር ሊያደርግልን ይችላል። w19.08 21 አን. 5-6

ዓርብ፣ የካቲት 12

አርማጌዶን ወደሚባል ስፍራ ሰበሰቧቸው።—ራእይ 16:16

አንዳንድ ሰዎች “አርማጌዶን” የሚለውን ቃል ከኑክሌር ጦርነት ወይም አካባቢን ከሚያወድም የተፈጥሮ አደጋ ጋር አያይዘው ይጠቅሱታል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን፣ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አርማጌዶን የሚገልጸው ነገር ለሰው ልጆች ምሥራች የሚያበስር ነው! (ራእይ 1:3) የአርማጌዶን ጦርነት የሰውን ዘር የሚያጠፋ ሳይሆን የሚታደግ ክንውን ነው! እንዴት? ሰብዓዊ አገዛዝን በማስወገድ ነው። ይህ ጦርነት ክፉዎች እንዲጠፉና ጻድቃን በሕይወት እንዲተርፉ በማድረግ ለሰዎች መዳን ያስገኛል። በተጨማሪም ግዑዟን ምድራችንን ከጥፋት በመታደግ የሰው ልጆችን ያድናል። (ራእይ 11:18) “አርማጌዶን” የሚለው ቃል በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የተጠቀሰው አንድ ጊዜ ብቻ ሲሆን “የመጊዶ ተራራ” የሚል ትርጉም ካለው የዕብራይስጥ ቃል የተገኘ ነው። (ራእይ 16:16 ግርጌ) መጊዶ በጥንቷ እስራኤል የምትገኝ ከተማ ነበረች። (ኢያሱ 17:11) ሆኖም አርማጌዶን ቃል በቃል በምድር ላይ ያለን ቦታ አያመለክትም። ከዚህ ይልቅ ‘የዓለም ነገሥታት ሁሉ’ ይሖዋን ተቃውመው የሚሰበሰቡበትን ሁኔታ ያመለክታል።—ራእይ 16:14፤ w19.09 8 አን. 1-3

ቅዳሜ፣ የካቲት 13

ሊፈውሳት የቻለ አንድም ሰው አልነበረም።—ሉቃስ 8:43

ይህች ሴት ያለችበት ሁኔታ በጣም አሳዛኝ ነበር። ከሕመሟ ፈውስ ለማግኘት ስትል ብዙ ሐኪሞች ጋ ሄዳለች። ለ12 ዓመት ያህል በከባድ ሕመም ብትሠቃይም ምንም መፍትሔ ማግኘት አልቻለችም። ሴትየዋ በሕጉ መሠረት እንደ ርኩስ ትቆጠር ነበር። (ዘሌ. 15:25) ከጊዜ በኋላ ግን ኢየሱስ የታመሙትን እንደሚፈውስ ሰማች። በመሆኑም እሱን ፍለጋ ሄደች። ባገኘችው ጊዜ ሄዳ የልብሱን ዘርፍ ነካች፤ ወዲያውኑም ከሕመሟ ተፈወሰች! ሆኖም ኢየሱስ ሴትየዋ አካላዊ ፈውስ እንድታገኝ በማድረግ ብቻ አልተወሰነም፤ ከዚህ ይልቅ ሰብዓዊ ክብሯንም መልሳ እንድታገኝ ረድቷታል። ለምሳሌ ከእሷ ጋር ሲያወራ አክብሮትና ወዳጃዊ ስሜት የሚንጸባረቅበትን “ልጄ ሆይ” የሚለውን አገላለጽ ተጠቅሟል። ይህች ሴት ምንኛ ተበረታታና እረፍት አግኝታ ይሆን! (ሉቃስ 8:44-48) ሴትየዋ ከሕመሟ ፈውስ ለማግኘት ቅድሚያውን ወስዳ ወደ ኢየሱስ እንደሄደች ልብ በሉ። በዛሬው ጊዜም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው፤ ወደ ኢየሱስ ለመሄድ እኛ ራሳችን ቅድሚያውን መውሰድ አለብን። በዘመናችን ኢየሱስ ወደ እሱ የሚመጡትን ሰዎች ተአምራዊ በሆነ መንገድ ከአካላዊ ሕመማቸው አይፈውሳቸውም። ሆኖም “ወደ እኔ ኑ፤ እኔም እረፍት እሰጣችኋለሁ” የሚል ግብዣ አቅርቦልናል።—ማቴ. 11:28፤ w19.09 20 አን. 2-3

እሁድ፣ የካቲት 14

ከዚህ በኋላ አየሁ፤ . . . እጅግ ብዙ ሕዝብ . . . በዙፋኑና በበጉ ፊት ቆመው ነበር።—ራእይ 7:9

ነቢዩ ዘካርያስም ከዚያ በፊት ተመሳሳይ ነገር ተንብዮ ነበር፤ እንዲህ ብሏል፦ “በዚያን ጊዜ ከብሔራት ቋንቋዎች ሁሉ የተውጣጡ አሥር ሰዎች የአንድን አይሁዳዊ ልብስ አጥብቀው በመያዝ ‘አምላክ ከእናንተ ጋር መሆኑን ስለሰማን ከእናንተ ጋር እንሄዳለን’ ይላሉ።” (ዘካ. 8:23) የይሖዋ ምሥክሮች፣ ከሁሉም ቋንቋዎች የተውጣጡ ሰዎች እንዲሰበሰቡ ከተፈለገ ምሥራቹ በብዙ ቋንቋዎች መሰበክ እንዳለበት ተገንዝበዋል። በአሁኑ ጊዜ በታሪክ ዘመናት ሁሉ ታይቶ በማይታወቅ መጠን ጽሑፎቻችን በመቶዎች በሚቆጠሩ ቋንቋዎች እየተተረጎሙ ነው። ይሖዋ የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላትን ከሁሉም ብሔራት በመሰብሰብ በዘመናችን ድንቅ ተአምር እየፈጸመ እንደሆነ በግልጽ ማየት ይቻላል። መንፈሳዊ ምግብ የሚቀርብባቸው ቋንቋዎች ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመሩ በመሄዳቸው ከተለያዩ ሕዝቦች የተውጣጣው ይህ ቡድን በአምልኮ አንድ ሊሆን ችሏል። ደግሞም የይሖዋ ምሥክሮች በስብከቱ ሥራ በቅንዓት በመካፈላቸውና የወንድማማች ፍቅር በማሳየታቸው ተለይተው ይታወቃሉ። ይህ እንዴት እምነት የሚያጠናክር ነው!—ማቴ. 24:14፤ ዮሐ. 13:35፤ w19.09 30 አን. 16-17

ሰኞ፣ የካቲት 15

ከዓለም መጀመሪያ አንስቶ እስካሁን ድረስ ሆኖ የማያውቅ ዳግመኛም የማይሆን ታላቅ መከራ ይከሰታል።—ማቴ. 24:21

በታላቁ መከራ ወቅት፣ በዓለም ላይ ያሉ የማይናወጡ መስለው የሚታዩ ነገሮች መጥፋት ሲጀምሩ ሰዎች በድንጋጤ ይዋጣሉ። በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ከሁሉ በከፋው በዚያ ጊዜ፣ ሰዎች ለገዛ ሕይወታቸው ስለሚሰጉ “የሚያደርጉት ጠፍቷቸው ይጨነቃሉ።” (ሶፎ. 1:14, 15) በዚያ ወቅት የይሖዋ ሕዝቦችም ጭምር ሕይወት የበለጠ አስቸጋሪ ሊሆንባቸው ይችላል። የዓለም ክፍል አለመሆናችን አንዳንድ ችግሮችን ሊያስከትልብን ይችላል። ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑ መሠረታዊ ነገሮችን እንኳ እናጣ ይሆናል። “ታማኝና ልባም ባሪያ” ታላቁን መከራ በታማኝነት ማለፍ እንድንችል ሲያዘጋጀን ቆይቷል። (ማቴ. 24:45) ይህን ያደረገባቸው በርካታ መንገዶች አሉ፤ ለአብነት ያህል፣ ከ2016-2018 ያደረግናቸውን ወቅታዊ የክልል ስብሰባዎች መጥቀስ እንችላለን። የይሖዋ ቀን እየተቃረበ ሲሄድ የሚያስፈልጉንን ባሕርያት እንድናዳብር በእነዚህ የክልል ስብሰባዎች ላይ ተበረታተናል። w19.10 14 አን. 2፤ 16 አን. 10፤ 17 አን. 12

ማክሰኞ፣ የካቲት 16

“ከይሖዋ ማዕድ” እና ከአጋንንት ማዕድ መካፈል አትችሉም።—1 ቆሮ. 10:21

አንድን ምግብ ከዋጥነው በኋላ በምግቡ ውስጥ ያሉት ንጥረ ነገሮች ከሰውነታችን ጋር የሚዋሃዱበትን መንገድ መቆጣጠር አንችልም። ጥሩ ምግብ ጤናማ እንድንሆን አስተዋጽኦ ያደርጋል፤ ጤናማ ያልሆነ ምግብ ግን በጤንነታችን ላይ ጉዳት ያስከትላል። የምንመገበው ምግብ የሚያስከትለው ውጤት በአንድ ጀምበር የሚታይ ባይሆንም እንኳ ውሎ አድሮ መታየቱ አይቀርም። በተመሳሳይም መዝናኛ ስንመርጥ ወደ አእምሯችን የምናስገባውን ነገር መቆጣጠር እንችላለን። አንዴ ወደ አእምሯችን ከገባ በኋላ ግን መዝናኛው በአእምሯችንና በልባችን ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ መቆጣጠር አንችልም። ጥሩ መዝናኛ መንፈሳችንን ያድስልናል፤ ጤናማ ያልሆነ መዝናኛ ግን ይጎዳናል። (ያዕ. 1:14, 15) መጥፎ መዝናኛ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ወዲያውኑ ግልጽ ባይሆንም እንኳ ውሎ አድሮ መታየቱ አይቀርም። መጽሐፍ ቅዱስ የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ የሚሰጠን ለዚህ ነው፦ “አንድ ሰው ምንም ዘራ ምን ያንኑ መልሶ ያጭዳል፤ ምክንያቱም ለሥጋው ብሎ የሚዘራ ከሥጋው መበስበስን ያጭዳል።” (ገላ. 6:7, 8) በእርግጥም ይሖዋ የሚጠላቸውን ነገሮች ከሚያበረታታ ማንኛውም መዝናኛ መራቃችን በጣም አስፈላጊ ነው!—መዝ. 97:10፤ w19.10 30 አን. 12-14

ረቡዕ፣ የካቲት 17

የተወደዳችሁ ልጆቹ በመሆን አምላክን የምትመስሉ ሁኑ፤ በፍቅር መመላለሳችሁን ቀጥሉ።—ኤፌ. 5:1, 2

ይሖዋ ልጁን ቤዛ አድርጎ በመስጠት ለእኛ ያለውን ታላቅ ፍቅር አሳይቷል። (ዮሐ. 3:16) ፍቅር በማሳየት ረገድ ይሖዋን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው? ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን በግለሰብ ደረጃ ከፍ አድርገን እንመለከታቸዋለን፤ እንዲሁም አንድ ‘የጠፋ በግ’ ወደ ይሖዋ ሲመለስ በደስታ እንቀበለዋለን። (መዝ. 119:176፤ ሉቃስ 15:7, 10) ጊዜያችንንና ጉልበታችንን ሳንሰስት ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን በመስጠት እንደምንወዳቸው እናሳያለን፤ በተለይም በችግራቸው ወቅት ከጎናቸው በመሆን እንረዳቸዋለን። (1 ዮሐ. 3:17) ኢየሱስ ተከታዮቹ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር እንዲያሳዩ አዟል። (ዮሐ. 13:34, 35) ኢየሱስ የሰጠው ይህ ትእዛዝ አዲስ ነው፤ ምክንያቱም በሙሴ ሕግ ሥር፣ እስራኤላውያን እንዲህ ያለ ፍቅር እንዲያሳዩ አይጠበቅባቸውም ነበር። የኢየሱስ ተከታዮች ግን ኢየሱስ እንደወደዳቸው እነሱም ወንድሞቻቸውን እንዲወዱ ታዘዋል። ይህን ትእዛዝ መፈጸም ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ማሳየትን ይጠይቃል። ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ከራሳችንም እንኳ አስበልጠን መውደድ ይኖርብናል። ለወንድሞቻችን ያለን ጥልቅ ፍቅር ልክ እንደ ኢየሱስ ሕይወታችንን ጭምር አሳልፈን እንድንሰጥ ሊያነሳሳን ይገባል። w19.05 4 አን. 11-13

ሐሙስ፣ የካቲት 18

ደጋግማችሁ ለምኑ፣ ይሰጣችኋል፤ ሳታሰልሱ ፈልጉ፣ ታገኛላችሁ፤ ደጋግማችሁ አንኳኩ፣ ይከፈትላችኋል።—ሉቃስ 11:9

የመንፈስ ቅዱስን እርዳታ ማግኘት ከፈለግን ሳናሰልስ መጸለይ ይኖርብናል። (ሉቃስ 11:13) ኢየሱስ በሉቃስ 11:5-9 ላይ የተናገረው ምሳሌ፣ ይሖዋ መንፈስ ቅዱስን የሚሰጠን ለምን እንደሆነም ይጠቁመናል። በምሳሌው ላይ የተጠቀሰው ግለሰብ እንግዳውን ጥሩ አድርጎ ማስተናገድ ፈልጎ ነበር። ከመሸ በኋላ ለመጣው እንግዳው ምግብ ማቅረብ ቢፈልግም የሚያቀርብለት ምንም ነገር አልነበረውም። ኢየሱስ እንደገለጸው ጎረቤትየው የተጠየቀውን ዳቦ ለመስጠት ፈቃደኛ የሆነው ሰውየው ስለወተወተው ነው። ታዲያ ኢየሱስ ማስተማር የፈለገው ነገር ምንድን ነው? ፍጹም ያልሆነ ሰው፣ ጎረቤቱ ስለወተወተው ሊረዳው ፈቃደኛ ከሆነ ደግ የሆነው የሰማዩ አባታችንማ ሳያሰልሱ ለሚለምኑት አገልጋዮቹ መንፈስ ቅዱስን እንደሚሰጣቸው አያጠራጥርም! እንግዲያው ይሖዋ መንፈስ ቅዱስን እንዲሰጠን የምናቀርበውን ልመና እንደሚመልስልን በመተማመን መጸለይ እንችላለን። (መዝ. 10:17፤ 66:19) ሰይጣን እኛን ለመጣል ያላሰለሰ ጥረት ቢያደርግም ድል አድራጊዎች እንደምንሆን እርግጠኞች ነን። w19.11 13 አን. 17-19

ዓርብ፣ የካቲት 19

ወደ አንድ ገለል ያለ ስፍራ እንሂድና በዚያ ትንሽ አረፍ በሉ።—ማር. 6:31

ኢየሱስ፣ እሱና ሐዋርያቱ አልፎ አልፎ እረፍት እንደሚያስፈልጋቸው ያውቅ ነበር። በዚያ ዘመንም ሆነ በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙ ሰዎች ያላቸው አመለካከት ግን ኢየሱስ በተናገረው ምሳሌ ላይ ከተጠቀሰው ሀብታም ሰው ጋር የሚመሳሰል ነው። ይህ ሰው፣ ነፍሱን “ዘና በይ፣ ብዪ፣ ጠጪ፣ ደስም ይበልሽ” ብሏታል። (ሉቃስ 12:19፤ 2 ጢሞ. 3:4) ይህ ሰው ትኩረት ያደረገው በእረፍትና በተድላ ላይ ነበር። ከዚህ በተቃራኒ ኢየሱስና ሐዋርያቱ ራሳቸውን በማስደሰት ላይ ያተኮረ ሕይወት አልመሩም። በዛሬው ጊዜ ያለን ክርስቲያኖች፣ ከሥራ ነፃ የምንሆንበትን ጊዜ ለማረፍ ብቻ ሳይሆን ለሰዎች ለመመሥከርና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት በማዋል የኢየሱስን ምሳሌ ለመከተል እንጥራለን። እንዲያውም ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ እና ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችን ከፍ አድርገን ስለምንመለከታቸው በእነዚህ ቅዱስ ሥራዎች አዘውትረን ለመካፈል የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን። (ዕብ. 10:24, 25) ለእረፍት ወደ ሌላ አካባቢ በምንጓዝበት ጊዜም እንኳ በሄድንበት ቦታ ስብሰባ ላይ በመገኘት እንዲሁም ለምናገኛቸው ሰዎች ምሥራቹን መናገር የምንችልበት አጋጣሚ በመፈለግ መንፈሳዊ ልማዶቻችንን እንቀጥላለን።—2 ጢሞ. 4:2፤ w19.12 7 አን. 16-17

ቅዳሜ፣ የካቲት 20

የጀመራችሁትን ሥራ ዳር አድርሱት።—2 ቆሮ. 8:11

ይሖዋ፣ በሕይወታችን ውስጥ የራሳችንን ውሳኔ እንድናደርግ ፈቅዶልናል። ጥሩ ውሳኔዎችን ማድረግ እንድንችል የሚያሠለጥነን ከመሆኑም ሌላ እሱን የሚያስደስቱ ውሳኔዎችን ስናደርግ ያሰብነው እንዲሳካልን ይረዳናል። (መዝ. 119:173) በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን ጥበብ ተግባራዊ ባደረግን መጠን ደግሞ ጥሩ ውሳኔ የማድረግ ችሎታችን እየተሻሻለ ይሄዳል። (ዕብ. 5:14) ይሁንና ያደረግነው ውሳኔ ጥበብ የተንጸባረቀበት ቢሆንም እንኳ የጀመርነውን ዳር ማድረስ ተፈታታኝ ሊሆንብን ይችላል። በዚህ ረገድ እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት፦ አንድ ወጣት ወንድም መጽሐፍ ቅዱስን ከዳር እስከ ዳር አንብቦ ለመጨረስ ይወስናል። በዕቅዱ መሠረት ለተወሰኑ ሳምንታት ያህል ሲያነብ ቢቆይም በዚያው መቀጠል አልቻለም። አንዲት እህት የዘወትር አቅኚ ሆና ለማገልገል ብትወስንም ዛሬ ነገ ስትል አቅኚነት መጀመር አልቻለችም። የአንድ ጉባኤ የሽማግሌዎች አካል፣ በጉባኤው ውስጥ ላሉ አስፋፊዎች እረኝነት በማድረግ ረገድ የበለጠ ለመሥራት በአንድ ድምፅ ወሰነ፤ ሆኖም ከወራት በኋላም ሽማግሌዎቹ ውሳኔያቸውን ተግባራዊ አላደረጉም። ከላይ የተጠቀሱት ሁኔታዎች የተለያዩ ቢሆኑም አንድ የሚያመሳስላቸው ነገር አለ። ግለሰቦቹ ውሳኔያቸውን ዳር ማድረስ አልቻሉም። w19.11 26 አን. 1-2

እሁድ፣ የካቲት 21

የትጉ ሰው ዕቅድ ለስኬት ያበቃዋል።—ምሳሌ 21:5

ኢየሱስ ያለንበትን ጊዜ ‘ከኖኅ ዘመን’ ጋር አመሳስሎታል፤ ደግሞም የምንኖረው ‘ለመቋቋም በሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን’ ውስጥ ነው። (ማቴ. 24:37፤ 2 ጢሞ. 3:1) አንዳንድ ባለትዳሮች ይህን እውነታ ግምት ውስጥ በማስገባት ልጅ ሳይወልዱ ለመቆየት መርጠዋል፤ ይህም በክርስቲያናዊ አገልግሎት ሰፋ ያለ ጊዜ ለማሳለፍ አስችሏቸዋል። ጥበበኛ የሆኑ ባለትዳሮች ልጅ መውለድ ይኖርባቸው እንደሆነና እንዳልሆነ እንዲሁም ስንት ልጅ መውለድ እንደሚፈልጉ ከመወሰናቸው በፊት ‘ወጪያቸውን ያሰላሉ።’ (ሉቃስ 14:28, 29) ብዙ ወላጆች፣ ልጅ ማሳደግ ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ጊዜና ጉልበትም እንደሚጠይቅ ያውቃሉ። ስለዚህ አንድ ባልና ሚስት እንደሚከተሉት ባሉ ጥያቄዎች ላይ መወያየታቸው አስፈላጊ ነው፦ ‘የቤተሰቡን መሠረታዊ ፍላጎት ለማሟላት ሁለታችንም መሥራት ይጠበቅብናል? መሠረታዊ ፍላጎት የምንላቸው ነገሮች የትኞቹ እንደሆኑ ተስማምተናል? ሁለታችንም መሥራት ካለብን ልጆቻችንን የሚንከባከበው ማን ነው? የልጆቻችንን አስተሳሰብና ድርጊት የሚቀርጸው ማን ይሆናል?’ በእነዚህ ጥያቄዎች ላይ በቁም ነገር የሚወያዩ ባልና ሚስት በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ የሚገኘውን ምክር ተግባራዊ ያደርጋሉ። w19.12 23-24 አን. 6-7

ሰኞ፣ የካቲት 22

ለአምላክ መንግሥት አብረውኝ የሚሠሩት እነዚህ . . . ናቸው፤ እነሱም የብርታት ምንጭ ሆነውልኛል።—ቆላ. 4:11

ሐዋርያው ጳውሎስ በተደጋጋሚ ጊዜያት ሕይወቱ አደጋ ላይ ወድቆ ነበር። (2 ቆሮ. 11:23-28) በተጨማሪም “ሥጋዬን የሚወጋ እሾህ” ያለው ነገር ያስከተለበትን ሥቃይ መቋቋም ነበረበት፤ ይህ እሾህ የጤና ችግር ሊሆን ይችላል። (2 ቆሮ. 12:7) ከዚህም ሌላ በአንድ ወቅት የሥራ አጋሩ የነበረው ዴማስ “በአሁኑ ጊዜ ያለውን ሥርዓት ወዶ” ጥሎት መሄዱ ሐዘን አስከትሎበት ነበር። (2 ጢሞ. 4:10) ጳውሎስ ሌሎችን ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ መንገድ የሚያገለግልና ደፋር የሆነ ቅቡዕ ክርስቲያን ነበር፤ ሆኖም እሱም እንኳ ተስፋ የቆረጠባቸው ጊዜያት ነበሩ። (ሮም 9:1, 2) ጳውሎስ የሚያስፈልገውን ማጽናኛና ድጋፍ አግኝቷል። በምን መንገድ? ይሖዋ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ጳውሎስን እንዳጠናከረው ጥርጥር የለውም። (2 ቆሮ. 4:7፤ ፊልጵ. 4:13) በተጨማሪም ይሖዋ፣ ጳውሎስን ለማጽናናት በእምነት ባልንጀሮቹ ተጠቅሟል። ጳውሎስ ስለ አንዳንድ የሥራ አጋሮቹ ሲናገር “በእጅጉ አጽናንተውኛል” ብሏል። (ቆላ. 4:11) በስም ከጠቀሳቸው መካከል አርስጥሮኮስ፣ ቲኪቆስና ማርቆስ ይገኙበታል። እነዚህ ክርስቲያኖች ጳውሎስን በማበረታታት እንዲጸና ረድተውታል። w20.01 8 አን. 2-3

ማክሰኞ፣ የካቲት 23

የልባችሁ ዓይኖች እንዲበሩ አድርጓል።—ኤፌ. 1:18

“ዳግመኛ መወለድ” ወይም ‘ከመንፈስ መወለድ’ ሲባል ምን ማለት እንደሆነ፣ በመንፈስ ቅዱስ ያልተቀባ ሰው ሙሉ በሙሉ እንዲረዳው ማድረግ የማይቻል ነገር መሆኑን ኢየሱስ ተናግሯል። (ዮሐ. 3:3-8 ግርጌ) ወደ ሰማይ የሚሄዱ ክርስቲያኖች በመንፈስ ሲቀቡ በአስተሳሰባቸው ላይ ምን ለውጥ ያጋጥማቸዋል? እነዚህ ክርስቲያኖች በይሖዋ መንፈስ ከመቀባታቸው በፊት፣ በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋን ከፍ አድርገው ይመለከቱት ነበር። ይሖዋ ክፋትን ሁሉ አስወግዶ ይህችን ምድር ገነት የሚያደርግበትን ጊዜ በታላቅ ጉጉት ይጠባበቁ ነበር። ምናልባትም በሞት የተለያቸውን የቤተሰብ አባል ወይም ወዳጃቸውን በትንሣኤ ሲቀበሉ በዓይነ ሕሊናቸው ይታያቸው ነበር። በመንፈስ ከተቀቡ በኋላ ግን አስተሳሰባቸው ይቀየራል። ለምን? በምድር ላይ የመኖር ተስፋ ስላላረካቸው አይደለም። አስተሳሰባቸው የተለወጠው ጭንቀት ወይም መከራ ስለበዛባቸው አይደለም። በምድር ላይ ለዘላለም መኖር አሰልቺ እንደሆነ ተሰምቷቸው በድንገት ሐሳባቸውን ስለቀየሩም አይደለም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት አስተሳሰባቸውንና ከፍ አድርገው የሚመለከቱትን ተስፋ ስለለወጠው ነው። w20.01 22 አን. 9-11

ረቡዕ፣ የካቲት 24

ሰው ሁሉ ለበላይ ባለሥልጣናት ይገዛ።—ሮም 13:1

በሙሴ ሕግ ሥር፣ ኃላፊነት የተሰጣቸው ወንዶች መንፈሳዊ ጉዳዮችን ብቻ ሳይሆን የፍትሐ ብሔርና የወንጀል ጉዳዮችን ጭምር ይመለከቱ ነበር። ‘በክርስቶስ ሕግ’ ሥር ግን ሽማግሌዎች አንድ ኃጢአት ሲፈጸም ጉዳዩን የሚመለከቱት ከመንፈሳዊ ነገሮች አንጻር ብቻ ነው። (ገላ. 6:2) ሽማግሌዎች፣ አምላክ የፍትሐ ብሔርና የወንጀል ጉዳዮችን የመመልከት ኃላፊነት የሰጠው ለሰብዓዊ ባለሥልጣናት እንደሆነ ይገነዘባሉ። ይህም ጥፋተኛው የገንዘብ ቅጣት እንዲጣልበት፣ እንዲታሰር ወይም በሌላ መንገድ እንዲቀጣ የማድረግ ኃላፊነትን ይጨምራል። (ሮም 13:2-4) ሽማግሌዎች አንድ ከባድ ኃጢአት ሲፈጸም ጉዳዩን ከመንፈሳዊ ነገሮች አንጻር የሚመለከቱት እንዴት ነው? ቅዱሳን መጻሕፍትን ተጠቅመው ጉዳዩን ከመረመሩ በኋላ ውሳኔ ያስተላልፋሉ። የክርስቶስ ሕግ የተመሠረተው በፍቅር ላይ እንደሆነ አይዘነጉም። በመሆኑም በፍቅር ተነሳስተው የሚከተለውን ጥያቄ ያጤናሉ፦ ‘በተፈጸመው ኃጢአት ምክንያት በጉባኤው ውስጥ የተጎዱ ካሉ እነሱን መርዳት የሚቻለው እንዴት ነው?’ በተጨማሪም ፍቅር፣ በደል ከፈጸመው ግለሰብ ጋር በተያያዘ የሚከተሉትን ነገሮች እንዲያመዛዝኑ ያደርጋቸዋል፦ ‘ግለሰቡ ንስሐ ገብቷል? ከመንፈሳዊ ሕመሙ እንዲያገግም ልንረዳው እንችላለን?’ w19.05 7 አን. 23-24

ሐሙስ፣ የካቲት 25

[ከአብ] የተነሳ በሕይወት [እኖራለሁ]።—ዮሐ. 6:57

ኢየሱስ ከላይ የሰፈረውን ሐሳብ በመናገር፣ ሕይወት የሰጠውና ለሕይወት የሚያስፈልገውን ነገር የሚያሟላለት አባቱ እንደሆነ ገልጿል። ኢየሱስ በአባቱ ሙሉ በሙሉ ይተማመን ነበር፤ ይሖዋም ለመኖር የሚያስፈልጉትን ነገሮች ለልጁ አሟልቶለታል። ከሁሉ በላይ ደግሞ ይሖዋ የኢየሱስን መንፈሳዊ ፍላጎት አሟልቶለታል። (ማቴ. 4:4) ይሖዋ ለእኛም መንፈሳዊ ፍላጎታችንን ያሟላልናል። ይሖዋ በቃሉ አማካኝነት ስለ ራሱ፣ ስለ ዓላማው፣ ስለ ሕይወት ትርጉም እንዲሁም ስለ ወደፊቱ ጊዜ እውነቱን ነግሮናል። እውነትን መማር ስንጀምር በግለሰብ ደረጃ ትኩረት ሰጥቶናል፤ ይኸውም በወላጆቻችን አሊያም በመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪያችን በመጠቀም ስለ እሱ እንድናውቅ ረድቶናል። አፍቃሪ በሆኑ የጉባኤ ሽማግሌዎች እንዲሁም በጎለመሱ ወንድሞችና እህቶች አማካኝነት በደግነት እኛን መርዳቱን ቀጥሏል። በተጨማሪም ይሖዋ ከመንፈሳዊ ቤተሰባችን አባላት ጋር ሆነን በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ከእሱ እንድንማር ዝግጅት አድርጓል። ይሖዋ በእነዚህና በሌሎች መንገዶች ሁላችንንም እንደ አባት እንደሚንከባከበን አሳይቷል።—መዝ. 32:8፤ w20.02 3 አን. 8፤ 5 አን. 13

ዓርብ፣ የካቲት 26

ሰላም የሚገኝበትንና እርስ በርሳችን የምንተናነጽበትን ነገር ለማድረግ የተቻለንን ሁሉ ጥረት እናድርግ።—ሮም 14:19

ምቀኝነት ሥር እንዲሰድ ከፈቀድን ሰላም አይኖርም። ምቀኝነትን ከልባችን ነቅለን ማውጣት ብቻ ሳይሆን ሌሎችም እንዲህ ዓይነት ስሜት እንዲፈጠርባቸው ላለማድረግ መጠንቀቅ ይኖርብናል። ታዲያ ሌሎች ምቀኝነት እንዳያድርባቸው የትኞቹን እርምጃዎች መውሰድ እንችላለን? ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ የምንችለውስ እንዴት ነው? አመለካከታችንና ድርጊታችን በሌሎች ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። ዓለም፣ ያለኝ ነገር “ይታይልኝ” የሚል መንፈስ እንድናንጸባርቅ ያበረታታናል። (1 ዮሐ. 2:16) ይሁንና እንዲህ ያለው መንፈስ ሌሎች ምቀኝነት እንዲያድርባቸው ያደርጋል። ስላሉን ወይም ልንገዛቸው ስላሰብናቸው ነገሮች ሁልጊዜ ባለማውራት ሌሎች ምቀኝነት እንዳያድርባቸው ማድረግ እንችላለን። ሌሎች ምቀኝነት እንዳያድርባቸው መከላከል የምንችልበት ሌላው መንገድ ደግሞ በጉባኤ ውስጥ ያሉንን ኃላፊነቶች በተመለከተ ትሑት መሆን ነው። ስላገኘናቸው መብቶች ለሌሎች ብዙ የምናወራ ከሆነ በውስጣቸው ምቀኝነት ሥር እንዲሰድ መንገድ እንከፍታለን። ከዚህ በተቃራኒ ለሌሎች በግለሰብ ደረጃ ትኩረት የምንሰጥ እንዲሁም ያከናወኑትን መልካም ሥራ ጠቅሰን የምናመሰግናቸው ከሆነ ባላቸው ነገር እንዲረኩ እንረዳቸዋለን፤ ይህም በጉባኤ ውስጥ አንድነትና ሰላም እንዲሰፍን ያደርጋል። w20.02 18 አን. 15-16

ቅዳሜ፣ የካቲት 27

የማይታዩት ባሕርያቱ . . . ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ በግልጽ ይታያሉ፤ ምክንያቱም ባሕርያቱን ከተሠሩት ነገሮች ማስተዋል ይቻላል።—ሮም 1:20

የፍጥረት ሥራዎችን በመመርመር ስለ ይሖዋ መማር ትችላለህ። (ራእይ 4:11) በዕፀዋትና በእንስሳት ላይ በተንጸባረቀው የይሖዋ ጥበብ ላይ አሰላስል። ድንቅ ስለሆነው የሰውነትህ አሠራር ለመማር ጥረት አድርግ። (መዝ. 139:14) ይሖዋ በፀሐይ ውስጥ ስላኖረው ኃይል ለማሰብ ሞክር፤ ከዚያ ደግሞ ፀሐይ በቢሊዮኖች ከሚቆጠሩ ከዋክብት መካከል አንዷ ብቻ እንደሆነች አስታውስ። (ኢሳ. 40:26) እንዲህ ስታደርግ ለይሖዋ ያለህ አክብሮት ይጨምራል። ይሁንና ከይሖዋ ጋር ዝምድና ለመመሥረት እሱ ጥበበኛና ኃያል መሆኑን መገንዘብህ ብቻ በቂ አይደለም። ለይሖዋ ጥልቅ ፍቅር ማዳበር ከፈለግክ ስለ እሱ ይበልጥ ማወቅ ይኖርብሃል። ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ እንደሚያስብልህ እርግጠኛ ልትሆን ይገባል። ‘ብትፈልገው እንደሚገኝልህ’ አስታውስ። (1 ዜና 28:9) ይሖዋ ‘ወደ ራሱ ስቦሃል።’ (ኤር. 31:3) ይሖዋ ላደረገልህ ነገር ያለህ አድናቆት በጨመረ መጠን ለእሱ ያለህ ፍቅርም እያደገ ይሄዳል። w20.03 4 አን. 6-7

እሁድ፣ የካቲት 28

ይህ አገልግሎት ስላለን ተስፋ አንቆርጥም።—2 ቆሮ. 4:1

ሐዋርያው ጳውሎስ ለአገልግሎቱ ቅድሚያ በመስጠት ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። በሁለተኛው ሚስዮናዊ ጉዞው ወቅት በቆሮንቶስ ሳለ፣ ወጪውን ለመሸፈን ገንዘብ ስላስፈለገው ለተወሰነ ጊዜ ያህል ድንኳን ለመሥራት ተገዶ ነበር። በዚህ ሙያ የተሰማራው ራሱን በመደገፍ በቆሮንቶስ ለነበሩ ሰዎች ምሥራቹን “ያለዋጋ” ለመስበክ ማለትም በእነሱ ላይ ሸክም ላለመሆን ሲል ነው። (2 ቆሮ. 11:7) ጳውሎስ የተወሰነ ሰብዓዊ ሥራ መሥራት ያስፈለገው ቢሆንም ለአገልግሎቱ ምንጊዜም ቅድሚያ ይሰጥ የነበረ ከመሆኑም ሌላ በየሰንበቱ ይሰብክ ነበር። ያለበት ሁኔታ ሲስተካከል ግን በስብከቱ ሥራ ላይ ይበልጥ ማተኮር ችሏል። ጳውሎስ “ቃሉን በመስበኩ ሥራ በእጅጉ [በመጠመድ] ኢየሱስ በእርግጥ ክርስቶስ መሆኑን እያስረዳ ለአይሁዳውያን ይመሠክር ነበር።” (ሥራ 18:3-5፤ 2 ቆሮ. 11:9) ከጊዜ በኋላም በሮም ውስጥ ለሁለት ዓመት ያህል የቁም እስረኛ ሳለ፣ ደብዳቤዎችን ይጽፍ እንዲሁም ሊጠይቁት ለሚመጡ ሰዎች ይመሠክር ነበር። (ሥራ 28:16, 30, 31) ጳውሎስ ለአገልግሎቱ የሚሰጠውን ትኩረት ምንም ነገር እንዳይከፋፍልበት ቁርጥ ውሳኔ አድርጎ ነበር። w19.04 4 አን. 9

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2026)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2026 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ