ሚያዝያ
ረቡዕ፣ ሚያዝያ 1
የአባቴ ፈቃድ ወልድን የሚያውቅና በእሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው ነው።—ዮሐ. 6:40
ከኢየሱስ ሥጋና ደም ጥቅም ማግኘት ከፈለግን በቤዛው ማመን ያስፈልገናል። (ኤፌ. 1:7) ኢየሱስ “ሌሎች በጎች” በማለት የጠራቸው ሰዎች በዓመታዊው የጌታ ራት ወቅት ከቂጣውና ከወይን ጠጁ አይካፈሉም፤ መካፈልም የለባቸውም። (ዮሐ. 10:16) ያም ቢሆን ከኢየሱስ ሥጋና ደም ጥቅም ያገኛሉ። ይህን የሚያደርጉት እሱ ያቀረበው መሥዋዕት ባለው የመዋጀት ኃይል ላይ እምነት በማሳደር ነው። (ዮሐ. 6:53) በአንጻሩ ግን፣ ከቂጣውና ከወይን ጠጁ የሚካፈሉት ሰዎች የአዲሱ ቃል ኪዳን ክፍል እንደሆኑና የሰማያዊው መንግሥት ወራሾች ለመሆን እንደተመረጡ ያሳያሉ። ከዚህ እንደምንረዳው፣ ቅቡዓን ክርስቲያኖችም ሆንን የሌሎች በጎች ክፍል እምነት ማሳየት ይኖርብናል። የዘላለም ሕይወት ማግኘታችን የተመካው በዚህ ላይ ነው። w24.12 12 አን. 14፤ 13 አን. 16
የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች፦ ኒሳን 12) ማቴዎስ 26:1-5, 14-16፤ ሉቃስ 22:1-6
የመታሰቢያው በዓል የሚከበርበት ዕለት
ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ
ሐሙስ፣ ሚያዝያ 2
አንተ ትንሽ መንጋ አትፍራ፤ አባታችሁ መንግሥት ሊሰጣችሁ ወስኗልና።—ሉቃስ 12:32
በጌታ ራት ወቅት ኢየሱስ ለሐዋርያቱ ቂጣ ከሰጣቸው በኋላ ሥጋውን እንደሚያመለክት ነገራቸው። ከዚያም የወይን ጠጁን ሰጣቸውና ‘የቃል ኪዳን ደሙን’ እንደሚያመለክት ተናገረ። (ማር. 14:22-25፤ ሉቃስ 22:20፤ 1 ቆሮ. 11:24) አዲሱ ቃል ኪዳን የተገባው በአምላክ መንግሥት ውስጥ ቦታ ከሚኖራቸው “[ከመንፈሳዊ] እስራኤል ቤት ጋር” ነው። (ዕብ. 8:6, 10፤ 9:15) ኢየሱስ በጌታ ራት ላይ ትኩረት ያደረገው ‘በትንሹ መንጋ’ ላይ ነበር። የዚህ አነስተኛ ቡድን የመጀመሪያ አባላት እዚያ ክፍል ውስጥ ከኢየሱስ ጋር አብረው የነበሩት ታማኝ ሐዋርያቱ ናቸው። ከኢየሱስ ጋር አብረው እንዲሆኑ በሰማይ ቦታ የሚያገኙት እነሱ ናቸው። w24.12 11 አን. 9-10
የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች፦ ኒሳን 13) ማቴዎስ 26:17-19፤ ማርቆስ 14:12-16፤ ሉቃስ 22:7-13 (ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ የተከናወኑ ነገሮች፦ ኒሳን 14) ዮሐንስ 13:1-5፤ 14:1-3
ዓርብ፣ ሚያዝያ 3
አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ በልጁ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ሲል አንድያ ልጁን ሰጥቷል።—ዮሐ. 3:16
ኢየሱስ ተከድቷል፣ ታስሯል፣ ተሰድቧል፣ ስሙ ጠፍቷል፣ ተፈርዶበታል እንዲሁም ተገርፏል። ከዚያም ወታደሮች ወደሚገደልበት ቦታ ወስደው በእንጨት ላይ በምስማር ቸነከሩት። ኢየሱስ ይህን ሁሉ ሥቃይ በታማኝነት የተቋቋመ ቢሆንም በዚያ ሰዓት ከእሱ ይበልጥ የተሠቃየ ሌላ አካል አለ። እሱም ይሖዋ አምላክ ነው። ገደብ የለሽ ኃይል ቢኖረውም ጣልቃ ከመግባት ራሱን ገቷል። ለምን? በአጭር አነጋገር እንዲህ ለማድረግ ያነሳሳው ፍቅር ነው። የኢየሱስ መሥዋዕት ይሖዋ አንተን ምን ያህል እንደሚወድህ ያሳያል። አንተን ከኃጢአትና ከሞት ለማዳን ሲል በራሱ ላይ እጅግ ከፍተኛ ሥቃይ እንዲደርስ ፈቅዷል። (1 ዮሐ. 4:9, 10) በእርግጥም እያንዳንዳችን ከኃጢአት ጋር እንድንዋጋ አልፎ ተርፎም እንድናሸንፍ ይፈልጋል! w24.08 6 አን. 13-14
የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች፦ ኒሳን 14) ዮሐንስ 19:1-42
ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 4
ክርስቶስ . . . ስለ እናንተ መከራ ተቀብሏል።—1 ጴጥ. 2:21
ቤዛው ይሖዋን ምን ያህል ዋጋ እንዳስከፈለው ስናስብ የፍቅሩን ጥልቀት እንገነዘባለን። ሰይጣን ማንኛውም የይሖዋ አገልጋይ ከባድ ሁኔታ ሲያጋጥመው ለእሱ ታማኝ ሆኖ አይቀጥልም የሚል ክስ ሰንዝሯል። ይሖዋ ለዚህ ክስ ምላሽ ለመስጠት ሲል ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት እንዲሠቃይ ፈቅዷል። (ኢዮብ 2:1-5) ኢየሱስ ተቃዋሚዎቹ ሲያሾፉበት፣ ወታደሮች ሲገርፉትና በእንጨት ላይ ሲቸነከር ይሖዋ እየተመለከተ ነበር። ከዚያም ይሖዋ የሚወደው ልጁ ተሠቃይቶ ሲሞት አይቷል። (ማቴ. 27:28-31, 39) ይሖዋ በልጁ ላይ የሚደርሰውን መከራ በየትኛውም ሰዓት ላይ ጣልቃ ገብቶ ማስቆም ይችል ነበር። (ማቴ. 27:42, 43) ሆኖም አምላክ ጣልቃ ቢገባ ኖሮ ቤዛው አይከፈልም ነበር፤ እኛም ያለተስፋ እንቀር ነበር። ስለሆነም ይሖዋ፣ ልጁ የመጨረሻ ትንፋሹን እስኪተነፍስ ድረስ እንዲሠቃይ ፈቅዷል። w25.01 22 አን. 7
የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች፦ ኒሳን 15) ማቴዎስ 27:62-66 (ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ የተከናወኑ ነገሮች፦ ኒሳን 16) ዮሐንስ 20:1
እሁድ፣ ሚያዝያ 5
እነሱም ለ40 ቀናት [አዩት]።—ሥራ 1:3
ዕለቱ ኒሳን 16, 33 ዓ.ም. ነው። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በሐዘንና በፍርሃት ተውጠዋል። ከደቀ መዛሙርቱ መካከል ሁለቱ ከኢየሩሳሌም ወጥተው ወደ ኤማሁስ መጓዝ ጀመሩ። አንድ ሰው ወደ እነሱ ጠጋ ብሎ አብሯቸው መጓዝ ጀመረ። ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ ባጋጠመው ነገር የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን ለሰውየው ነገሩት። ከዚያም ሰውየው ሕይወታቸውን የሚቀይር ማብራሪያ ሰጣቸው። መሲሑ መሠቃየትና መሞት ያለበት ለምን እንደሆነ “ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ” አብራራላቸው። ሦስቱ ሰዎች ኤማሁስ ሲደርሱ ደቀ መዛሙርቱ የሰውየውን ማንነት አወቁ። ለካስ ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ነው! (ሉቃስ 24:13-35) ኢየሱስ በምድር ላይ ባሳለፋቸው የመጨረሻ 40 ቀናት ለደቀ መዛሙርቱ በተደጋጋሚ ተገልጦላቸዋል። በሐዘንና በፍርሃት ተውጠው የነበሩት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በዚያ ጊዜ ውስጥ ተለውጠው በደስታ፣ በልበ ሙሉነትና በድፍረት ስለ መንግሥቱ መስበክና ማስተማር ጀመሩ። w24.10 12 አን. 1-3
የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች፦ ኒሳን 16) ዮሐንስ 20:2-18
ሰኞ፣ ሚያዝያ 6
እጅግ ቅዱስ በሆነው እምነታችሁ ላይ ራሳችሁን ገንቡ።—ይሁዳ 20
አንድ ልጅ ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ትልቅ ሰው መሆኑ አይቀርም። መንፈሳዊ ጉልምስና ግን በራሱ የሚመጣ ነገር አይደለም። ለምሳሌ በቆሮንቶስ የነበሩት ወንድሞችና እህቶች ምሥራቹን ተቀብለዋል፤ ተጠምቀዋል፤ መንፈስ ቅዱስን ተቀብለዋል፤ እንዲሁም ሐዋርያው ጳውሎስ ለረጅም ጊዜ አስተምሯቸዋል። (ሥራ 18:8-11) ያም ቢሆን ከተጠመቁ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላም ብዙዎቹ በመንፈሳዊ አልጎለመሱም ነበር። (1 ቆሮ. 3:2) ጉልምስና ደረጃ ላይ ለመድረስ በመጀመሪያ ጎልማሳ የመሆን ፍላጎት ልናዳብር ይገባል። ‘አላዋቂነትን የሚወዱ’ ማለትም በመንፈሳዊ ሕፃን ሆነው መኖር የሚፈልጉ ሰዎች እድገት ማድረግ አይችሉም። (ምሳሌ 1:22) ትልቅ ሰው ከሆኑ በኋላም ያለወላጆቻቸው እርዳታ ውሳኔ ማድረግ እንደማይችሉ ሰዎች መሆን አንፈልግም። ከዚህ ይልቅ መንፈሳዊ እድገት ማድረግ የራሳችን ኃላፊነት እንደሆነ አምነን መቀበል ይኖርብናል። በአሁኑ ወቅት ጉልምስና ደረጃ ላይ ለመድረስ ጥረት እያደረግክ ከሆነ ይሖዋ ‘ለተግባር የሚያነሳሳ ፍላጎት እንዲያድርብህም ሆነ ኃይል እንድታገኝ’ እንዲረዳህ ጸልይ።—ፊልጵ. 2:13፤ w24.04 4 አን. 9-10
ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 7
ይሖዋ . . . ማንም እንዲጠፋ [አይፈልግም]።—2 ጴጥ. 3:9
ይሖዋ በሰዎች ላይ ፍርድ ከሚያስተላልፍበት መንገድ ጋር በተያያዘ ምን እንደሚሰማው በደግነት ገልጾልናል። (ሕዝ. 33:11) ይሖዋ ሰዎችን ለዘላለም ለማጥፋት አይቸኩልም። እሱ እጅግ መሐሪ ነው፤ የሚቻል በሚሆንበት ጊዜ ሁሉ ምሕረት ያሳያል። ትንሣኤ የማያገኙትን ሰዎች በተመለከተ ምን እናውቃለን? መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠን ጥቂት ምሳሌዎችን ብቻ ነው። ኢየሱስ የአስቆሮቱ ይሁዳ ትንሣኤ እንደማያገኝ ጠቁሟል። (ማር. 14:21፤ ዮሐ. 17:12) ይሁዳ ሆን ብሎ፣ እያወቀ ይሖዋ አምላክንና ልጁን ተቃውሟል። (ማር. 3:29) በተመሳሳይም ኢየሱስ እሱን ከተቃወሙት የሃይማኖት መሪዎች አንዳንዶቹ የትንሣኤ ተስፋ የሌለው ጥፋት እንደሚጠብቃቸው ተናግሯል። (ማቴ. 23:33) ሐዋርያው ጳውሎስም ንስሐ የማይገቡ ከሃዲዎች ትንሣኤ እንደማያገኙ ገልጿል።—ዕብ. 6:4-8፤ 10:29፤ w24.05 4 አን. 10-11
ረቡዕ፣ ሚያዝያ 8
ይሖዋ ታማኞችን ይጠብቃል።—መዝ. 31:23
ይሖዋን የሙጥኝ ካልን ሰይጣን ዘላቂ ጉዳት ሊያደርስብን አይችልም። (1 ዮሐ. 3:8) በአዲሱ ዓለም ውስጥ ደግሞ ይሖዋ ወዳጆቹን ከመንፈሳዊ ጉዳት ብቻ ሳይሆን ከሞትም እንኳ ይጠብቃቸዋል። (ራእይ 21:4) በይሖዋ ድንኳን ውስጥ እንግዳ መሆን ይኸውም ከእሱ ጋር በግለሰብ ደረጃ ዘላቂ ዝምድና መመሥረት ታላቅ ክብር ነው። (ሕዝ. 37:27) የእሱ እንግዶች ሆነን መቀጠል ከፈለግን ምን ዓይነት ምግባር ሊኖረን ይገባል? አንድ ሰው ወደ ቤቱ ከጋበዘህ ከአንተ ምን እንደሚጠብቅ ማወቅ እንደምትፈልግ ጥያቄ የለውም። በተመሳሳይም ይሖዋ የእሱ እንግዶች ሆነው መቀጠል ከሚፈልጉ ሰዎች ምን እንደሚጠብቅባቸው ማወቅ እንፈልጋለን። ለይሖዋ ያለን ፍቅር ‘እሱን ሙሉ በሙሉ ለማስደሰት’ አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ እንድናደርግ ያነሳሳናል። (ቆላ. 1:10) ይሖዋ ያለውን ሥልጣን በመገንዘብ ምንጊዜም ለእሱ ጥልቅ አክብሮት ሊኖረን ይገባል። እንዲህ ያለው አክብሮት እሱን የሚያሳዝን ምግባር እንዳይኖረን ይረዳናል። ‘ልካችንን አውቀን ከአምላካችን ጋር መሄድ’ እንፈልጋለን።—ሚክ. 6:8፤ w24.06 4 አን. 8-9
ሐሙስ፣ ሚያዝያ 9
ስለ ሕግ [ተላላፊዎች] ማልዷል።—ኢሳ. 53:12
ይሖዋ አብርሃምን ልጁን ይስሐቅን መሥዋዕት አድርጎ እንዲያቀርብ ጠየቀው። ይህ ትእዛዝ አብርሃምን በጣም አስጨንቆት እንደሚሆን ምንም ጥያቄ የለውም። ያም ቢሆን አብርሃም ይሖዋን ታዘዘ። ሆኖም ልጁን መሥዋዕት ከማድረጉ በፊት አምላክ አስቆመው። ይሁንና ይህ ምሳሌ ለሁሉም የእምነት ሰዎች ወሳኝ ትምህርት ይዟል። ይሖዋ የሚወደውን ልጁን መሥዋዕት አድርጎ ለማቅረብ ፈቃደኛ ሆኗል። ይሖዋ ለሰው ልጆች ያለው ፍቅር ያን ያህል ታላቅ ነው። (ዘፍ. 22:1-18) በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ ለእስራኤል ብሔር የተሰጠው ሕግ የአምላክ ሕዝቦች ኃጢአታቸውን ለማስተሰረይ ብዙ መሥዋዕቶችን እንዲያቀርቡ ያዝዝ ነበር። (ዘሌ. 4:27-29፤ 17:11) እነዚህ መሥዋዕቶች የሰው ልጆችን ከኃጢአት ሙሉ በሙሉ ለሚያድነው የላቀ መሥዋዕት ጥላ ነበሩ። የአምላክ ነቢያት፣ ተስፋ የተሰጠበት ዘር አንተን ጨምሮ የሰው ልጆችን ከኃጢአትና ከሞት ለማዳን ሲል መከራ እንደሚቀበልና እንደሚገደል በመንፈስ ተመርተው ተናግረዋል።—ኢሳ. 53:1-12፤ w24.08 4 አን. 7-8
ዓርብ፣ ሚያዝያ 10
ሕግህን ምንኛ ወደድኩ! ቀኑን ሙሉ አሰላስለዋለሁ።—መዝ. 119:97
መጽሐፍ ቅዱስን ስታነብ ትምህርቱን ተግባራዊ የምታደርግባቸውን መንገዶች ፈልግ። የተወሰነ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ካነበብክ በኋላ ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘በአሁኑ ወቅት ወይም በቅርቡ ይህን ትምህርት ተግባራዊ ማድረግ የምችለው እንዴት ነው?’ ለምሳሌ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብህ 1 ተሰሎንቄ 5:17, 18ን ያካተተ ነው እንበል። ይህን ጥቅስ ካነበብክ በኋላ ስለ ጸሎት ልማድህ ቆም ብለህ ልታስብ ትችላለህ። ምን ያህል አዘውትረህ ትጸልያለህ? ጸሎትህስ ምን ያህል ጥልቀት ያለው ነው? ልታስብበት የምትችለው ሌላው ነገር ደግሞ ‘ስለ የትኞቹ ነገሮች አመስጋኝ መሆን እችላለሁ?’ የሚለው ነው። ምናልባት ሦስት ነገሮችን ጠቅሰህ ይሖዋን ለማመስገን ልትወስን ትችላለህ። ለጥቂት ደቂቃዎች ብቻ እንኳ ትኩረትህን ሰብስበህ ማሰብህ የአምላክን ቃል የምትሰማና የምታደርግ እንድትሆን የሚረዳህ እንዴት እንደሆነ አስተዋልክ? በየዕለቱ ከምታደርገው የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ጋር በተያያዘ ይህንኑ ብታደርግ ምን ያህል ልትጠቀም እንደምትችል እስቲ አስበው! አዎ፣ የአምላክን ቃል በማድረግ ረገድ እየተሻሻልክ ትሄዳለህ። w24.09 4-5 አን. 9-10
ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 11
ሙሉ ሽልማት እንድታገኙ እንጂ የደከምንባቸውን ነገሮች እንዳታጡ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።—2 ዮሐ. 8
ይሖዋ የፈጠረን ልዩ ችሎታ ሰጥቶ ነው። መቀበል የሚያስደስተን ቢሆንም ስንሰጥ የበለጠ ደስታ እናገኛለን። የእምነት አጋሮቻችንን ስንረዳ ደስ ይለናል። ምስጋናቸውን ሲገልጹልንም እንደሰታለን። ይሁንና ልግስና ያሳየናቸው ሰዎች ቢያመሰግኑንም ባያመሰግኑንም ትክክል የሆነውን ነገር በማድረጋችን መደሰት እንችላለን። ለሌሎች የምትሰጠው ነገር ምንም ይሁን ምን “ይሖዋ ከዚህ እጅግ የሚበልጥ ሊሰጥህ [እንደሚችል]” ፈጽሞ አትርሳ። (2 ዜና 25:9) መቼም ቢሆን ይሖዋ ከሚሰጠን ይበልጥ መስጠት አንችልም! ደግሞም በይሖዋ ከመካስ የበለጠ አስደሳች ነገር የለም። እንግዲያው ለጋስ የሆነውን የሰማዩን አባታችንን መምሰላችንን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። w24.09 31 አን. 20-21
እሁድ፣ ሚያዝያ 12
ይሖዋ አምላኬ ሆይ፣ በሙሉ ልቤ አወድስሃለሁ፤ ስምህንም ለዘላለም ከፍ ከፍ አደርጋለሁ።—መዝ. 86:12
ይሖዋ መሐሪና ሩኅሩኅ ነው። (መዝ. 103:13፤ ኢሳ. 49:15) ስሜታችንን ይረዳልናል፤ ሥቃያችን ይሰማዋል። (ዘካ. 2:8) ወደ እሱ እንድንቀርብና ወዳጆቹ እንድንሆን ፈቅዶልናል። (መዝ. 25:14፤ ሥራ 17:27) ትሑት ነው፤ “ሰማይንና ምድርን ለማየት ወደ ታች ያጎነብሳል፤ ችግረኛውን ከአፈር ያነሳል።” (መዝ. 113:6, 7) ታዲያ ለታላቁ አምላካችን ክብር ለመስጠት ብንነሳሳ ምን ያስገርማል? ለይሖዋ ክብር የምንሰጠው ሌሎች ስለ እሱ እንዲያውቁ ስለምንፈልግ ነው። ብዙዎች ስለ ይሖዋ እውነቱን አያውቁም። ለምን? ምክንያቱም ሰይጣን ስለ ይሖዋ መርዘኛ ውሸቶችን በመንዛት አእምሯቸውን አሳውሯል። (2 ቆሮ. 4:4) ሰይጣን፣ ይሖዋ በቀለኛ፣ ለሰዎች የማያስብ እንዲሁም በዓለም ላይ ላሉት ችግሮች መንስኤ እንደሆነ ሰዎችን አሳምኗል። እኛ ግን ስለ አምላካችን እውነቱን እናውቃለን! ስለ ይሖዋ እውነቱን በመናገር ለእሱ ክብር የማምጣት አጋጣሚ አግኝተናል።—ኢሳ. 43:10፤ w25.01 3 አን. 6-7
ሰኞ፣ ሚያዝያ 13
[ሰይጣን] መላውን ዓለም እያሳሳተ [ነው]።—ራእይ 12:9
የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ፍጹም ነበር፤ እንዲሁም አስደናቂ ተአምራትን ፈጽሟል። ያም ቢሆን የሰይጣን ደጋፊዎች ስለ እሱ ብዙ ውሸት ተናግረዋል። ለምሳሌ የሃይማኖት መሪዎቹ፣ ኢየሱስ አጋንንትን የሚያስወጣው “በአጋንንት አለቃ” ኃይል እንደሆነ ለሕዝቡ ተናግረዋል። (ማር. 3:22) ኢየሱስ ለፍርድ ቀርቦ በነበረበት ጊዜ የሃይማኖት መሪዎቹ ‘አምላክን ተሳድቧል’ ብለው የከሰሱት ከመሆኑም ሌላ ሕዝቡን እሱ እንዲገደል እንዲጠይቁ አግባብተዋል። (ማቴ. 27:20) ከጊዜ በኋላም የክርስቶስ ተከታዮች ምሥራቹን ሲሰብኩ ተቃዋሚዎቻቸው “ሰዎች በማነሳሳት በወንድሞች ላይ ጥላቻ እንዲያድርባቸው” እና እንዲያሳድዷቸው አደረጉ። (ሥራ 14:2, 19) የሐዋርያት ሥራ 14:2ን በተመለከተ የታኅሣሥ 1, 1998 መጠበቂያ ግንብ እንዲህ ብሏል፦ “አይሁዳውያን ተቃዋሚዎች መልእክቱን ለመቀበል እምቢ ማለታቸው ሳይበቃቸው ክርስቲያኖች በአሕዛብ ዘንድ እንዲጠሉ ለማድረግ የስም ማጥፋት ዘመቻ አፋፍመው ነበር።” ዛሬም ሰይጣን “መላውን ዓለም እያሳሳተ” ነው። w24.04 11 አን. 15-16
ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 14
የምድር ሁሉ ዳኛ ትክክል የሆነውን ነገር አያደርግም?—ዘፍ. 18:25
ሰዎች ዘላለማዊ ሕይወት የማግኘታቸው አጋጣሚ የተመካው በሚሞቱበት ጊዜ ላይ አይደለም። ይሖዋ ፍጹም የሆነ ዳኛ ስለሆነ የሚያደርጋቸው ውሳኔዎች ትክክለኛና ፍትሐዊ ናቸው። (መዝ. 33:4, 5) “የምድር ሁሉ ዳኛ” ትክክል የሆነውን ነገር እንደሚያደርግ መተማመን እንችላለን። በተጨማሪም ሰዎች የዘላለም ሕይወት የማግኘታቸው አጋጣሚ በሚኖሩበት አካባቢ ላይ የተመካ አይደለም ብሎ ማመን ምክንያታዊ ነው። ይሖዋ በሚኖሩበት አገር የተነሳ ለመንግሥቱ መልእክት ምላሽ ለመስጠት አጋጣሚ ያላገኙ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን እዚያ አካባቢ በመኖራቸው ብቻ ‘ፍየል ናቸው’ ብሎ ይፈርድባቸዋል ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው። (ማቴ. 25:46) ጻድቅ የሆነው የምድር ሁሉ ዳኛ ከማናችንም በላይ ለእነዚህ ሰዎች ያስባል። ይሖዋ በታላቁ መከራ ወቅት ሁኔታዎችን እንዴት እንደሚያመቻች አናውቅም። ምናልባትም ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ስለ ይሖዋ የመማር፣ በእሱ የማመን እንዲሁም በብሔራት ሁሉ መካከል ራሱን በሚቀድስበት ጊዜ ከእሱ ጎን የመሰለፍ አጋጣሚ ያገኙ ይሆናል።—ሕዝ. 38:16፤ w24.05 12 አን. 14-15
ረቡዕ፣ ሚያዝያ 15
እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ።—ዮሐ. 15:12
የይሖዋ ሕዝቦች እርስ በርስ መረዳዳት ያስደስታቸዋል። (2 ቆሮ. 8:4) ይሁንና አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ማድረግ ድፍረት ይጠይቃል። ለምሳሌ ጦርነት በሚቀሰቀስበት ጊዜ የጉባኤ ሽማግሌዎች ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ማበረታቻ፣ ድጋፍ እንዲሁም መንፈሳዊ ምግብና ቁሳዊ እርዳታ ሊያስፈልጋቸው እንደሚችል ይገነዘባሉ። ሽማግሌዎች ለመንጋው ፍቅር ስላላቸው የራሳቸውን ደህንነት አደጋ ላይ መጣል ቢጠይቅባቸውም እንኳ ወንድሞቻቸው የሚያስፈልጋቸውን ነገር ያቀርባሉ። እንዲህ ባሉት ሁኔታዎች ውስጥ ስንሆን አንድነታችንን መጠበቃችን በጣም አስፈላጊ ነው። ከቅርንጫፍ ቢሮው ያገኘኸውን መመሪያ ተከተል። (ዕብ. 13:17) ሽማግሌዎች ለአደጋ ከመዘጋጀት እንዲሁም አደጋ ሲከሰት መወሰድ ካለባቸው እርምጃዎች ጋር በተያያዘ ያሉትን መመሪያዎች አዘውትረው መከለስ ይኖርባቸዋል። (1 ቆሮ. 14:33, 40) ደፋር ሆኖም ጠንቃቃ ሁን። (ምሳሌ 22:3) የማመዛዘን ችሎታህን ተጠቀም። ሳያስፈልግ ራስህን አደጋ ላይ አትጣል። በይሖዋ ታመን። ይሖዋ ደህንነትህን አደጋ ላይ ሳትጥል ወንድሞችህን እንድትደግፍ ሊረዳህ ይችላል። w24.07 4 አን. 8፤ 5 አን. 11
ሐሙስ፣ ሚያዝያ 16
በጭንቅ ውስጥ ሳለሁ ይሖዋን ጠራሁት፤ . . . እርዳታ ለማግኘት የማሰማውም ጩኸት ወደ ጆሮው ደረሰ።—መዝ. 18:6
ንጉሥ ዳዊት ይሖዋን ያውቀውና ይታመንበት ነበር። ንጉሥ ሳኦልን ጨምሮ ጠላቶቹ ሲያሳድዱት ዳዊት ይሖዋ እንዲረዳው ጸልዮአል። አምላክ ጸሎቱን በመስማት ከታደገው በኋላ ዳዊት “ይሖዋ ሕያው ነው!” በማለት ስሜቱን ገልጿል። (መዝ. 18:46) ዳዊት ይህን ሲል አምላክ መኖሩን መናገሩ ብቻ አልነበረም። አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ እንደሚገልጸው ዳዊት ይህን ሲል ይሖዋ “ሕዝቦቹን ለመርዳት ሁልጊዜ እርምጃ የሚወስድ ሕያው አምላክ መሆኑን” በእርግጠኝነት እንደሚያምን መናገሩ ነው። አዎ፣ ዳዊት አምላኩ ሕያው መሆኑን በገዛ ሕይወቱ አይቷል፤ ይህ እምነቱ ደግሞ ይሖዋን ለማገልገልና ለማወደስ ያለውን ቁርጠኝነት አጠናክሮለታል። (መዝ. 18:28, 29, 49) ይሖዋ ሕያው አምላክ እንደሆነ ማመናችን እሱን በቅንዓት ለማገልገል ይረዳናል። ፈተናዎችን በጽናት ለመቋቋም የሚያስችል ብርታትና አምላክን በትጋት ማገልገላችንን ለመቀጠል የሚያስችል ተነሳሽነት ይኖረናል። ከዚህም ሌላ፣ ከይሖዋ ጋር ተቀራርበን ለመኖር ያለንን ቁርጠኝነት ያጠናክርልናል። w24.06 20-21 አን. 3-4
ዓርብ፣ ሚያዝያ 17
ማንም ሰው በምንም መንገድ አያሳስታችሁ።—2 ተሰ. 2:3
ሐዋርያው ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ክርስቲያኖች ከተናገረው ሐሳብ ምን እንማራለን? ከመጽሐፍ ቅዱስ ከተማርናቸው እውነቶች ጋር የማይስማማ ነገር ወይም አስደንጋጭ ወሬ ስንሰማ የማስተዋል ችሎታችንን መጠቀም ይኖርብናል። በቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ውስጥ ጠላቶቻችን ከዋናው መሥሪያ ቤት የተላከ የሚመስል ደብዳቤ አሰራጭተው ነበር። ደብዳቤው አንዳንድ ወንድሞች የራሳቸውን ድርጅት እንዲያቋቁሙ የሚያበረታታ ነበር። ደብዳቤው ሲታይ እውነተኛ ይመስላል። ታማኝ የሆኑ ወንድሞች ግን በዚህ አልተታለሉም። ደብዳቤው የያዘው መልእክት አስቀድመው ከተማሯቸው ነገሮች ጋር እንደማይስማማ አስተዋሉ። ዛሬም የእውነት ጠላቶች አንዳንድ ጊዜ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ግራ እንድንጋባና በመካከላችን መከፋፈል እንዲፈጠር ለማድረግ ይጥራሉ። ‘የማመዛዘን ችሎታችን በቀላሉ እንዲናወጥ’ ከመፍቀድ ይልቅ የሰማነው ወይም ያነበብነው ነገር ከተማርናቸው እውነቶች ጋር የሚስማማ መሆን አለመሆኑን በመመዘን ራሳችንን መጠበቅ እንችላለን።—2 ተሰ. 2:2፤ 1 ዮሐ. 4:1፤ w24.07 12 አን. 14-15
ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 18
ማንም ኃጢአት ቢሠራ . . . ረዳት አለን።—1 ዮሐ. 2:1
አንድ ሰው በሕይወቱ ውስጥ የሚያደርገው ትልቁ ውሳኔ ራሱን ለይሖዋ ወስኖ የይሖዋን አገልጋዮች ያቀፈውን ቤተሰብ መቀላቀል ነው። ይሖዋ ሁሉም ሰው ይህን ውሳኔ እንዲያደርግ ይፈልጋል። ለምን? የእሱ ወዳጆች እንዲሆኑና ለዘላለም እንዲኖሩ ይፈልጋል። (ዘዳ. 30:19, 20፤ ገላ. 6:7, 8) ያም ቢሆን ይሖዋ ማንንም ሰው እንዲያገለግለው አያስገድድም። እያንዳንዱ ግለሰብ የራሱን ውሳኔ እንዲያደርግ ፈቅዷል። አንድ የተጠመቀ ክርስቲያን የአምላክን ሕግ በመጣስ ከባድ ኃጢአት ቢፈጽምስ? ንስሐ ካልገባ ከጉባኤው መወገድ ይኖርበታል። (1 ቆሮ. 5:13) ያም ሆኖ እንኳ ይሖዋ ጥፋተኛው ግለሰብ ወደ እሱ እንደሚመለስ ተስፋ ያደርጋል። እንዲያውም ቤዛውን ያዘጋጀበት አንዱ ወሳኝ ምክንያት ንስሐ የገቡ ኃጢአተኞች ይቅርታ እንዲያገኙ ሲል ነው። አምላካችን ጥፋት የሠሩ ግለሰቦች ንስሐ እንዲገቡ ፍቅራዊ ግብዣ አቅርቦላቸዋል።—ዘካ. 1:3፤ ሮም 2:4፤ ያዕ. 4:8፤ w24.08 14 አን. 1-2
እሁድ፣ ሚያዝያ 19
ልብህ ጥበበኛ ቢሆን፣ የእኔ ልብ ሐሴት ያደርጋል።—ምሳሌ 23:15
ሐዋርያው ዮሐንስ ሦስተኛውን ደብዳቤ በጻፈበት ወቅት የሐሰት ትምህርቶችን የሚያስፋፉና ክፍፍል የሚፈጥሩ አንዳንድ ሰዎች ነበሩ። ሌሎች ክርስቲያኖች ግን ‘በእውነት ውስጥ መመላለሳቸውን’ ቀጥለዋል። ይሖዋን ይታዘዙ እንዲሁም ‘በትእዛዛቱ መሠረት ይመላለሱ’ ነበር። (2 ዮሐ. 4, 6) እነዚህ ታማኝ ክርስቲያኖች ዮሐንስን ብቻ ሳይሆን ይሖዋንም አስደስተውታል። (ምሳሌ 27:11) ምን ትምህርት እናገኛለን? ታማኝነት ደስታ ያስገኛል። (1 ዮሐ. 5:3) ይሖዋን እያስደሰትን እንዳለ ማወቃችን ያስደስተናል። ይሖዋ የዓለምን ፈተናዎች አሸንፈን ቃሉን ስንታዘዝ ይደሰታል። መላእክትም ይህን ሲያዩ ይደሰታሉ። (ሉቃስ 15:10) በተጨማሪም ሌሎች ታማኝነታቸውን እንደጠበቁ ስንመለከት እኛም እንደሰታለን። (2 ተሰ. 1:4) ይህ ሥርዓት ከጠፋ በኋላ ደግሞ፣ ሰይጣን በሚቆጣጠረው ዓለም ውስጥም እንኳ ለይሖዋ ያለንን ታማኝነት እንዳስመሠከርን ማወቃችን ጥልቅ እርካታ ያስገኝልናል። w24.11 12 አን. 17-18
ሰኞ፣ ሚያዝያ 20
እያንዳንዱ ሰው ምንጊዜም የራሱን ጥቅም ሳይሆን የሌላውን ሰው ጥቅም ይፈልግ።—1 ቆሮ. 10:24
የፍቅር ስሜትህን ከመናገርህ በፊት ለምን ያህል ጊዜ ልትመለከታት ይገባል? ስሜትህን ቶሎ ከነገርካት በችኮላ ውሳኔ እንዳደረግክ ሊሰማት ይችላል። (ምሳሌ 29:20) በሌላ በኩል ደግሞ፣ በተለይ ስሜትህን ካስተዋለች በኋላ ረጅም ጊዜ ከወሰድክ ውሳኔ ማድረግ እንደምትቸገር ሊሰማት ይችላል። (መክ. 11:4) እሷን ከመጠየቅህ በፊት እንደምታገባት እርግጠኛ መሆን እንደማያስፈልግህ አስታውስ። ሆኖም ለትዳር ዝግጁ መሆንህን እንዲሁም እሷ ጥሩ የትዳር ጓደኛ ልትሆንህ እንደምትችል እርግጠኛ መሆን ይኖርብሃል። ሆኖም አንዲት እህት አንተን ለትዳር እያሰበችህ እንደሆነ ብትገነዘብስ? ከእሷ ጋር ለመጠናናት የማታስብ ከሆነ ይህን በድርጊትህ በግልጽ ለማሳየት ሞክር። አንተ የመጠናናት ሐሳብ ሳይኖርህ ለእሷ ተስፋ መስጠት ደግነት አይደለም።—ኤፌ. 4:25፤ w24.05 23 አን. 9-10
ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 21
እንደገና መጥቼ እኔ ወዳለሁበት እወስዳችኋለሁ።—ዮሐ. 14:3
ኢየሱስ ወደ ሰማያዊው መንግሥት የሚወስደው እውነተኛና ታማኝ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ብቻ ናቸው። በመንፈሳዊ ንቁ ያልሆነ ማንኛውም ቅቡዕ ክርስቲያን ‘ከተመረጡት’ ጋር አይሰበሰብም። (ማቴ. 24:31) ይህ ማስጠንቀቂያ በተዘዋዋሪ መንገድ ለሁሉም የአምላክ አገልጋዮች ይሠራል፤ ተስፋችን ምንም ይሁን ምን ሁላችንም ነቅተን መጠበቅና ታማኞች መሆን ይኖርብናል። ይሖዋን በደንብ ስለምናውቀው ፍርዱ ትክክል እንደሆነ እንተማመናለን። ይሖዋ በአሁኑ ጊዜ አንዳንድ ክርስቲያኖችን በመንፈስ ቅዱስ ለመቀባት ቢመርጥ ጉዳዩ አያስጨንቀንም። ኢየሱስ በወይን እርሻው ምሳሌ ላይ በ11ኛው ሰዓት ስለተቀጠሩት ሠራተኞች የተናገረውን ሐሳብ እናስታውሳለን። (ማቴ. 20:1-16) በቀኑ መገባደጃም ሆነ ቀደም ብለው የተቀጠሩት ሠራተኞች ክፍያቸው ተመሳሳይ ነበር። በተመሳሳይም ቅቡዓን ክርስቲያኖች የተመረጡት መቼም ይሁን መች ታማኝነታቸውን እስከጠበቁ ድረስ ሽልማታቸውን ያገኛሉ። w24.09 24 አን. 15-17
ረቡዕ፣ ሚያዝያ 22
ክርስቶስ . . . የእሱን ፈለግ በጥብቅ እንድትከተሉ አርዓያ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራ ተቀብሏል።—1 ጴጥ. 2:21
የፍትሕ መጓደልን መቋቋም ከሚቻልበት መንገድ ጋር በተያያዘ ኢየሱስ ፍጹም ምሳሌ ትቷል። ኢየሱስ በቤተሰቡም ሆነ በሌሎች ሰዎች ብዙ ኢፍትሐዊ ድርጊት ተፈጽሞበታል። አማኝ ያልሆኑት ዘመዶቹ አእምሮውን እንደሳተ ተናግረዋል፤ የሃይማኖት መሪዎቹ ሥራውን የሚያከናውነው በአጋንንት ኃይል እንደሆነ በመግለጽ ወንጅለውታል፤ ሮማውያን ወታደሮች ደግሞ አፊዘውበታል፤ አንገላተውታል፤ በስተ መጨረሻም ገድለውታል። (ማር. 3:21, 22፤ 14:55፤ 15:16-20, 35-37) ያም ቢሆን ኢየሱስ ምንም አጸፋ ሳይመልስ ይህን ሁሉ ግፍ ተቋቁሟል። ከእሱ ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን? (1 ጴጥ. 2:21-23) የፍትሕ መጓደል ሲያጋጥመን ማድረግ ያለብንን ነገር በተመለከተ ኢየሱስ ፍጹም ምሳሌ ትቶልናል። ኢየሱስ መቼ ዝም ማለት፣ መቼ ደግሞ መናገር እንዳለበት ያውቅ ነበር። (ማቴ. 26:62-64) የሐሰት ክስ በተሰነዘረበት ቁጥር ምላሽ አልሰጠም። (ማቴ. 11:19) በተናገረባቸው ጊዜያትም አሳዳጆቹን አልሰደባቸውም ወይም አልዛተባቸውም። w24.11 4-5 አን. 9-10
ሐሙስ፣ ሚያዝያ 23
ክርስቶስ ኢየሱስ ኃጢአተኞችን ለማዳን ወደ ዓለም መጣ።—1 ጢሞ. 1:15
ለአንድ ለምትወደው ሰው ውብና ጠቃሚ የሆነ ልዩ ስጦታ ሰጠኸው እንበል። ግለሰቡ ስጦታውን ሣጥን ውስጥ ቢያስቀምጠውና ከዚያ በኋላ ጨርሶ ባያስታውሰው ምን ይሰማሃል? እንደምታዝን የታወቀ ነው። በሌላ በኩል ግን ግለሰቡ ስጦታውን በሚገባ ሲጠቀምበትና አድናቆቱን ሲገልጽልህ እንደምትደሰት ጥያቄ የለውም። ነጥቡ ምንድን ነው? ይሖዋ ልጁን ሰጥቶናል። ለዚህ ውድ ስጦታና ቤዛውን በማዘጋጀት ላሳየን ፍቅር አመስጋኝነታችንን ስናሳይ ይሖዋ ምንኛ ይደሰት ይሆን! (ዮሐ. 3:16፤ ሮም 5:7, 8) ይሁንና ጊዜ እያለፈ ሲሄድ የቤዛውን ስጦታ አቅልለን መመልከት ልንጀምር እንችላለን። በምሳሌያዊ ሁኔታ የአምላክን ስጦታ ሣጥን ውስጥ እንዳስቀመጥነው ሊቆጠር ይችላል። ስጦታው ስለተሰጠን ደስተኞች ነን፤ ሆኖም ስጦታውን መለስ ብለን አናየውም። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ እንዳያጋጥመን፣ አምላክና ክርስቶስ ላደረጉልን ነገር ያለንን አመስጋኝነት በየጊዜው ማደስ ይኖርብናል። w25.01 26 አን. 1-2
ዓርብ፣ ሚያዝያ 24
እድገትህ በሁሉም ሰዎች ዘንድ በግልጽ እንዲታይ በእነዚህ ነገሮች ላይ አሰላስል፤ እንዲሁም ትኩረትህ ሙሉ በሙሉ በእነዚህ ነገሮች ላይ ያረፈ ይሁን።—1 ጢሞ. 4:15
የጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ የሚሾም ወንድም አዲስ ክርስቲያን ሊሆን አይገባም። ከተጠመቅክ ብዙ ዓመት መቆጠር ባያስፈልገውም የጎለመስክ ክርስቲያን እንድትሆን የተወሰነ ጊዜ ሊያልፍ ይገባል። ሽማግሌ ሆነህ ከመሾምህ በፊት ልክ እንደ ኢየሱስ ትሑት እንደሆንክና ይሖዋ ኃላፊነት እስኪሰጥህ ድረስ በትዕግሥት ለመጠበቅ ፈቃደኛ እንደሆንክ ማሳየት አለብህ። (ማቴ. 20:23፤ ፊልጵ. 2:5-8) ይሖዋን የሙጥኝ በማለትና የጽድቅ መሥፈርቶቹን በጥብቅ በመከተል እንዲሁም በድርጅቱ በኩል የምታገኘውን መመሪያ በመታዘዝ ታማኝ መሆንህን ታሳያለህ። ቅዱሳን መጻሕፍት የበላይ ተመልካች የሚሆን ሰው የማስተማር ብቃት ያለው ሊሆን እንደሚገባ በግልጽ ይናገራሉ። ታዲያ ይህ ሲባል ከመድረክ ስታስተምር አንደበተ ርቱዕ መሆን አለብህ ማለት ነው? አይደለም። ብቃት ያላቸው በርካታ ሽማግሌዎች ከመድረክ ሲያስተምሩ አንደበተ ርቱዕ ባይሆኑም እንኳ በአገልግሎትና በእረኝነት ጉብኝት ወቅት ውጤታማ በሆነ መንገድ ያስተምራሉ። w24.11 23 አን. 14-15
ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 25
ትእዛዛትህን ከወርቅ፣ ምርጥ ከሆነ ወርቅ ይበልጥ እወዳለሁ።—መዝ. 119:127
አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ መረዳት ከከበደህ ምርምር አድርግ። ከዚያም የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴህን በምታከናውንበት ጊዜ ስታጠና ስላገኘኸው ሐሳብ እንዲሁም ስለ ይሖዋ፣ ስለ ልጁና እነሱ ለእኛ ስላላቸው ፍቅር ስላገኘኸው ትምህርት አሰላስል። (መዝ. 119:97 ግርጌ) ባነበብክ ወይም ምርምር ባደረግክ ቁጥር አዲስ ወይም አስገራሚ ትምህርት አታገኝ ይሆናል፤ ሆኖም ተስፋ ልትቆርጥ አይገባም። ሁኔታው ወርቅ ለማግኘት ከሚደረግ ፍለጋ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ወርቅ የሚፈልጉ ሰዎች አንዲት አነስተኛ የወርቅ ቅንጣት ለማግኘት እንኳ ለሰዓታት ወይም ለቀናት በትዕግሥት ጥረት ማድረግ ሊጠይቅባቸው ይችላል። ሆኖም እያንዳንዱ የወርቅ ቅንጣት ለእነሱ ትልቅ ዋጋ ስላለው ጥረት ማድረጋቸውን ይቀጥላሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው እያንዳንዱ መንፈሳዊ ዕንቁ ደግሞ ከወርቅም የበለጠ ዋጋ አለው! (ምሳሌ 8:10) ስለዚህ ታጋሽ በመሆን መጽሐፍ ቅዱስን በቋሚነት ማንበብህን ቀጥል።—መዝ. 1:2፤ w25.01 24-25 አን. 14-15
እሁድ፣ ሚያዝያ 26
ይሖዋ በነፃ ይቅር እንዳላችሁ ሁሉ እናንተም እንዲሁ አድርጉ።—ቆላ. 3:13
ይሖዋ፣ ጉዳት ያደረሱብንን ሰዎች ይቅር ለማለት ዝግጁ እንድንሆን ይጠብቅብናል። (መዝ. 86:5፤ ሉቃስ 17:4፤ ኤፌ. 4:32) በተለይ የቅርብ ጓደኛችን ወይም የቤተሰባችን አባል በንግግሩ ወይም በድርጊቱ ሲበድለን ከባድ የስሜት ጉዳት ሊደርስብን ይችላል። (መዝ. 55:12-14) አንዳንድ ጊዜ፣ የደረሰብን የስሜት ሥቃይ ከባድ ከመሆኑ የተነሳ በስለት እንደተወጋን ያህል ሊሰማን ይችላል። (ምሳሌ 12:18) የተጎዳውን ስሜታችንን ለማፈን ወይም ችላ ለማለት እንሞክር ይሆናል። ሆኖም እንዲህ ማድረግ፣ በስለት ከተወጋን በኋላ ስለቱን እዚያው ቁስሉ ውስጥ እንደመተው ሊቆጠር ይችላል። በተመሳሳይም የተጎዳውን ስሜታችንን ችላ ካልነው ሊያገግም አይችልም። አንድ ሰው ሲበድለን በመጀመሪያ የሚቀናን መበሳጨት ሊሆን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ጊዜ ልንቆጣ እንደምንችል ይናገራል። ሆኖም ይህ ስሜት እንዲቆጣጠረን እንዳንፈቅድ ያስጠነቅቀናል። (መዝ. 4:4፤ ኤፌ. 4:26) ለምን? ምክንያቱም ቁጣ ብዙውን ጊዜ ጥሩ ውጤት አያስገኝም። (ያዕ. 1:20) ይህን ምንጊዜም አስታውስ፦ መቆጣት ተፈጥሯዊ ነው፤ ተቆጥቶ መቆየት ግን የምርጫ ጉዳይ ነው። w25.02 15 አን. 4-6
ሰኞ፣ ሚያዝያ 27
ጥበብ የባለቤቷን ሕይወት ጠብቃ [ታቆያለች]።—መክ. 7:12
ኢየሱስ “በአምላክ ዘንድ . . . ሀብታም” ሳንሆን ቁሳዊ ነገሮችን ማከማቸት ምን ያህል ሞኝነት እንደሆነ የሚያሳይ ምሳሌ ተናግሯል። (ሉቃስ 12:16-21) ነገ የሚያመጣውን ማንም አያውቅም። (ምሳሌ 23:4, 5፤ ያዕ. 4:13-15) የክርስቶስ ተከታዮች በመሆናችን ብቻ ሊገጥመን የሚችል ተፈታታኝ ሁኔታም አለ። ኢየሱስ እንደተናገረው የእሱ ደቀ መዛሙርት ለመሆን ስንል ካስፈለገ ንብረታችንን ሁሉ ‘ለመተው’ ዝግጁ መሆን አለብን። (ሉቃስ 14:33 ግርጌ) በመጀመሪያው መቶ ዘመን በይሁዳ የነበሩት ክርስቲያኖች እንዲህ ዓይነት እጦት ሲገጥማቸው ሁኔታውን በደስታ ተቀብለውታል። (ዕብ. 10:34) ዛሬ ያሉ ብዙ ወንድሞችም ለአንድ የፖለቲካ ሥርዓት ድጋፍ ላለመስጠት ሲሉ ቁሳዊ ነገሮችን መሥዋዕት አድርገዋል። (ራእይ 13:16, 17) እንዲህ ያለ አቋም ለመውሰድ የረዳቸው ምንድን ነው? ይሖዋ “ፈጽሞ አልተውህም፤ በምንም ዓይነት አልጥልህም” በማለት በገባው ቃል ላይ ሙሉ እምነት ማሳደራቸው ነው። (ዕብ. 13:5) እንግዲያው ለወደፊቱ ጊዜ ጥሩ ዕቅድ ማውጣታችን ተገቢ ነው፤ ያልተጠበቁ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙን ደግሞ ይሖዋ ምንጊዜም እንደሚደግፈን መተማመን አለብን። w25.03 29 አን. 13-14
ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 28
ስለ ክርስቶስ ከተማርነው መሠረታዊ ትምህርት አልፈን ስለሄድን ወደ ጉልምስና ለመድረስ እንጣጣር፤ መሠረትን ደግመን አንመሥርት።—ዕብ. 6:1
ይሖዋ በራሳችን ጥረት ብቻ ጉልምስና ደረጃ ላይ እንድንደርስ አይጠብቅብንም። በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ እረኞችና አስተማሪዎች ሆነው የሚያገለግሉት ወንድሞች በመንፈሳዊ “ሙሉ ሰው ወደ መሆን ይኸውም እንደ ክርስቶስ የተሟላ የጉልምስና ደረጃ ላይ” እንድንደርስ እኛን ለመርዳት ዝግጁ ናቸው። (ኤፌ. 4:11-13) ከዚህም ሌላ ይሖዋ ቅዱስ መንፈሱን በመስጠት “የክርስቶስ አስተሳሰብ” እንዲኖረን ይረዳናል። (1 ቆሮ. 2:14-16) በተጨማሪም አምላክ በመንፈስ መሪነት አራቱ ወንጌሎች እንዲጻፉልን አድርጓል፤ እነዚህ ወንጌሎች ኢየሱስ ምድር ላይ ሳለ አስተሳሰቡ፣ አነጋገሩና ድርጊቱ ምን ይመስል እንደነበር ያስተምሩናል። የኢየሱስን አስተሳሰብና ምግባር በመኮረጅ ክርስቲያናዊ ጉልምስና ላይ የመድረስ ግባችንን ማሳካት እንችላለን። ሆኖም ወደ ጉልምስና ደረጃ ለመድረስ “ስለ ክርስቶስ ከተማርነው መሠረታዊ ትምህርት” ማለትም መሠረታዊ ከሆኑት የክርስትና ትምህርቶች አልፈን መሄድ ይኖርብናል። w24.04 4-5 አን. 11-12
ረቡዕ፣ ሚያዝያ 29
የማመዛዘን ችሎታ ምንጊዜም ይጠብቅሃል፤ ጥልቅ ግንዛቤም ይጋርድሃል።—ምሳሌ 2:11
በየዕለቱ ውሳኔዎችን ማድረግ ያስፈልገናል። አንዳንዶቹን ውሳኔዎች ማድረግ ቀላል ነው፤ ለምሳሌ ‘ቁርስ ምን ልብላ’ ወይም ‘ስንት ሰዓት ልተኛ’ የሚለውን መወሰን ቀላል ነው። አንዳንዶቹን ውሳኔዎች ማድረግ ግን ከባድ ሊሆን ይችላል። እነዚህ ውሳኔዎች በጤንነታችን፣ በደስታችን፣ በወዳጅ ዘመዶቻችን ወይም በአምልኳችን ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ። እኛንም ሆነ ቤተሰቦቻችንን የሚጠቅሙ ውሳኔዎችን ማድረግ እንፈልጋለን። ከሁሉ በላይ ደግሞ ውሳኔዎቻችን ይሖዋን የሚያስደስቱ እንዲሆኑ እንፈልጋለን። (ሮም 12:1, 2) ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ የሚረዳህ አንዱ ወሳኝ እርምጃ የተሟላ መረጃ ማግኘት ነው። ለምን? ለምሳሌ አንድ ታማሚ ያጋጠመውን ከባድ የጤና ችግር አስመልክቶ ሐኪሙን አማከረ እንበል። ሐኪሙ በመጀመሪያ ታማሚውን ሳይመረምረው ወይም ጥያቄዎችን ሳይጠይቀው ምን ዓይነት ሕክምና እንደሚሰጠው ይወስናል? እንዲህ እንደማያደርግ የታወቀ ነው። አንተም በመጀመሪያ ከጉዳዩ ጋር የተያያዙ መረጃዎችን ለማግኘት ጥረት ካደረግክ ጥሩ ውሳኔ ማድረግ ትችላለህ። w25.01 14 አን. 1-3
ሐሙስ፣ ሚያዝያ 30
ይሖዋ . . . ኃጢአትህን ይቅር ይላል። አትሞትም።—2 ሳሙ. 12:13
የይሖዋን ምሕረት በተመለከተ ምን እናውቃለን? ይሖዋ ‘ማንም እንዲጠፋ እንደማይፈልግ’ ያሳየው እንዴት ነው? (2 ጴጥ. 3:9) ከባድ ኃጢአት ለፈጸሙ አንዳንድ ሰዎች ያሳየውን ምሕረት እንመልከት። ንጉሥ ዳዊት ምንዝርንና ነፍስ ግድያን ጨምሮ ከባድ ኃጢአቶችን ፈጽሟል። ያም ቢሆን ዳዊት ንስሐ ስለገባ ይሖዋ በምሕረት ይቅር ብሎታል። (2 ሳሙ. 12:1-12) ንጉሥ ምናሴ በአብዛኛው የሕይወቱ ክፍል እጅግ ክፉ ሰው ነበር። ይሁንና በጣም ክፉ የነበረው ይህ ሰውም እንኳ ንስሐ ሲገባ ይሖዋ ምሕረት በማሳየት ይቅር ብሎታል። (2 ዜና 33:9-16) እነዚህ ምሳሌዎች፣ ይሖዋ ምሕረት ለማሳየት የሚያስችል መሠረት እስካገኘ ድረስ ምሕረት እንደሚያሳይ ያስታውሱናል። እንዲህ ያሉት ሰዎች ከባድ ኃጢአት መፈጸማቸውን ተገንዝበው ንስሐ ስለገቡ ይሖዋ ከሞት ያስነሳቸዋል። w24.05 4 አን. 12