ግንቦት
ዓርብ፣ ግንቦት 1
በአምላክ ዘንድ አድልዎ የለም።—ሮም 2:11
ይሖዋ ሕዝቡን ከግብፅ ባርነት ነፃ ካወጣቸው በኋላ በማደሪያው ድንኳን የሚያገለግሉ ካህናትን ሾመ። ሌዋውያን ደግሞ ከቅዱሱ ድንኳን ጋር በተያያዘ ሌሎች ኃላፊነቶች ነበሯቸው። ይሖዋ በማደሪያ ድንኳኑ ውስጥ ለሚያገለግሉ ወይም በአቅራቢያው ለሰፈሩ እስራኤላውያን የተለየ እንክብካቤ ያደርግላቸው ነበር? በፍጹም! ይሖዋ አያዳላም። ሁሉም እስራኤላውያን የይሖዋ ወዳጆች የመሆን እኩል አጋጣሚ ነበራቸው። ለምሳሌ ይሖዋ በማደሪያ ድንኳኑ ላይ ያለውን ተአምራዊ የደመና ዓምድና የእሳት ዓምድ መላው ብሔር ማየት እንዲችል አድርጎ ነበር። (ዘፀ. 40:38) ደመናው መንቀሳቀስ ሲጀምር ከማደሪያ ድንኳኑ በጣም ርቀው የሰፈሩ እስራኤላውያን እንኳ ማየት ይችሉ ነበር፤ እነሱም ዕቃቸውን ሰብስበው፣ ድንኳናቸውን አፍርሰው ከቀረው ብሔር ጋር መጓዝ ይችላሉ። (ዘኁ. 9:15-23) ዛሬም በተመሳሳይ የምንኖረው የትም ይሁን የት የይሖዋን ፍቅራዊ እንክብካቤና ጥበቃ ማግኘት እንችላለን። w24.06 4 አን. 10-12
ቅዳሜ፣ ግንቦት 2
ተነሱ፣ እንሽሽ፤ አለዚያ አንዳችንም ከአቢሴሎም እጅ አናመልጥም!—2 ሳሙ. 15:14
የዳዊት ሕይወት አደጋ ላይ ወድቋል። ልጁ አቢሴሎም መንግሥቱን ከእሱ ለመንጠቅ ቆርጦ ተነስቷል። (2 ሳሙ. 15:12, 13) ዳዊት ወዲያውኑ ኢየሩሳሌምን ለቆ መውጣት አለበት። አገልጋዮቹ እየወጡ ሳሉ ዳዊት አንድ ሰው ኢየሩሳሌም ቀርቶ የአቢሴሎምን ዕቅድ ሊያሳውቀው እንደሚገባ ተገነዘበ። ስለዚህ ሰላዮች እንዲሆኑ ሳዶቅንና ሌሎቹን ካህናት ወደ ኢየሩሳሌም መልሶ ላካቸው። (2 ሳሙ. 15:27-29) እነዚህ ሰዎች በጣም መጠንቀቅ ነበረባቸው። ዳዊት ከታማኝ ወዳጆቹ ከሳዶቅና ከኩሲ ጋር በመተባበር አንድ ዕቅድ አወጣ። (2 ሳሙ. 15:32-37) በዚህ ዕቅድ መሠረት ኩሲ አቢሴሎምን የሚደግፍ መስሎ በመቅረብ ዳዊትን ለማጥቃት የሚያስችል ወታደራዊ ምክረ ሐሳብ አቀረበ፤ ይህ ስልት ዳዊት ቅድመ ዝግጅት የሚያደርግበት ጊዜ ይሰጠዋል። ቀጥሎም ኩሲ ዕቅዱን ለሳዶቅና ለአብያታር ነገራቸው። (2 ሳሙ. 17:8-16) ሁለቱ ሰዎች ደግሞ ለዳዊት መልእክት ላኩበት። ይህም የዳዊትን ሕይወት ለመታደግ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል።—2 ሳሙ. 17:21, 22፤ w24.07 4-5 አን. 9-10
እሁድ፣ ግንቦት 3
“ኑና በመካከላችን የተፈጠረውን ችግር ተወያይተን እንፍታ” ይላል ይሖዋ።—ኢሳ. 1:18
አንዳንድ የይሖዋ አገልጋዮች ከመጠመቃቸው በፊት ወይም ከተጠመቁ በኋላ በፈጸሙት ድርጊት የተነሳ በጥፋተኝነት ስሜት ይሠቃያሉ። ይሁንና ይሖዋ በጣም ስለሚወደን ቤዛውን እንዳዘጋጀልን ማስታወስ አለብን። ስለዚህ ስጦታውን እንድንቀበል እንደሚፈልግ ጥያቄ የለውም። ይሖዋ በእኛና በእሱ ‘መካከል የተፈጠረውን ችግር ከፈታን’ በኋላ በኃጢአታችን እንደማይጠይቀን ቃል ገብቶልናል። ይሖዋ ቀደም ሲል የፈጸምናቸውን ኃጢአቶች መርሳቱ ለእኛ ያለውን ጥልቅ ፍቅር ያሳያል! በሌላ በኩል ደግሞ የሠራነውን መልካም ነገር አይረሳም። (መዝ. 103:9, 12፤ ዕብ. 6:10) ቀደም ሲል የፈጸምከው ነገር የሚጸጽትህ ከሆነ ባለፈው ነገር ላይ ከማተኮር ይልቅ በአሁኑና በወደፊቱ ጊዜ ላይ ለማተኮር ሞክር። ያለፈውን መቀየር አትችልም። ሆኖም በአሁኑ ጊዜ አቅምህ በፈቀደ መጠን ይሖዋን ማስከበር እንዲሁም ወደፊት ቃል የገባልህን አስደሳች ጊዜ በተስፋ መጠባበቅ ትችላለህ። w24.10 8 አን. 8-9
ሰኞ፣ ግንቦት 4
አዲሱን ስብዕና ልበሱ።—ቆላ. 3:10
መጽሐፍ ቅዱስን ስታነብና ምክሩን ተግባራዊ ስለማድረግ ስታስብ አንዳንድ ጊዜ ከአቅምህ በላይ እንደሆነ ይሰማህ ይሆናል። ለምሳሌ የዛሬው የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብህ አድልዎን ስለማስወገድ የሚናገር ምክር የያዘ ይሆናል። (ያዕ. 2:1-8) ሌሎችን የምትይዝበትን መንገድ ማስተካከል እንደሚያስፈልግህ ትገነዘብና አንዳንድ ለውጦችን ለማድረግ ትወስናለህ። የነገው የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብህ ደግሞ አንደበትን መቆጣጠር ስላለው አስፈላጊነት የሚያጎላ ነው። (ያዕ. 3:1-12) ንግግርህ በተወሰነ መጠን አሉታዊ እንደሆነ ትረዳ ይሆናል። ስለዚህ አነጋገርህ አዎንታዊና የሚያንጽ እንዲሆን ለማድረግ ግብ ታወጣለህ። በሚቀጥለው ቀን ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብህ የዓለም ወዳጅ መሆንን በተመለከተ ማስጠንቀቂያ ይዟል። (ያዕ. 4:4-12) በመዝናኛ ምርጫህ ረገድ ማሻሻያ ማድረግ እንዳለብህ ትገነዘባለህ። በአራተኛው ቀን፣ ልትሠራባቸው የሚገቡ ነጥቦችን ብዛት ስታስብ ሁኔታው ከአቅምህ በላይ እንደሆነ ሊሰማህ ይችላል። ተስፋ አትቁረጥ። “አዲሱን ስብዕና” መልበስ ቀጣይ የሆነ ሂደት እንደሆነ አስታውስ። w24.09 5-6 አን. 11-12
ማክሰኞ፣ ግንቦት 5
ክርስቶስን እንደ ጌታ አድርጋችሁ በልባችሁ ቀድሱት። እናንተ ስላላችሁ ተስፋ፣ ምክንያት እንድታቀርቡ ለሚጠይቃችሁ ሰው ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር ዝግጁ ሁኑ፤ ይህን ስታደርጉ ግን በገርነት መንፈስና በጥልቅ አክብሮት ይሁን።—1 ጴጥ. 3:15
ኢየሱስ በዋነኝነት ሊያሳስበው የሚገባው የይሖዋ አመለካከት እንደሆነ ያውቅ ነበር። ያጋጠመውን የፍትሕ መጓደል ይሖዋ በትክክለኛው ጊዜ እንደሚያስተካክልለት ተማምኖ ነበር። የፍትሕ መጓደል ሲያጋጥመን አንደበታችንን በመቆጣጠር የኢየሱስን ምሳሌ መከተል እንችላለን። አንዳንድ ጊዜ የሚፈጸሙብን ኢፍትሐዊ ድርጊቶች ያን ያህል ከባድ ስላልሆኑ ሁኔታውን እንዲሁ ዝም ብለን ለማለፍ እንመርጥ ይሆናል። ወይም ደግሞ ሁኔታው እንዲባባስ የሚያደርግ ነገር ላለመናገር ስንል ዝም ለማለት ልንመርጥ እንችላለን። (መክ. 3:7፤ ያዕ. 1:19, 20) አንዳንድ ጊዜ ግን ሌሎች ኢፍትሐዊ ድርጊት ሲፈጸምባቸው ስናይ ወይም ለእውነት ጥብቅና መቆም ሲያስፈልገን መናገራችን የተሻለ ሊሆን ይችላል። (ሥራ 6:1, 2) በምንናገርበት ጊዜም እርጋታና አክብሮት በሚንጸባረቅበት መንገድ ለመናገር አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ማድረግ ይኖርብናል። ‘በጽድቅ ለሚፈርደው ራሳችንን በአደራ በመስጠትም’ የኢየሱስን ምሳሌ መከተል እንችላለን።—1 ጴጥ. 2:23፤ w24.11 5-6 አን. 10-12
ረቡዕ፣ ግንቦት 6
ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በአምላክ መላእክት ዘንድ ደስታ ይሆናል።—ሉቃስ 15:10
ኃጢአት የፈጸመ አንድ ግለሰብ ንስሐ ከገባ ይህ በጣም የሚያስደስት ነገር ነው! (ሉቃስ 15:7) ይሁንና ለዚህ ሊመሰገን የሚገባው ማን ነው? ሽማግሌዎች ናቸው? ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ኃጢአተኞች ሲናገር “ምናልባትም አምላክ . . . ለንስሐ ያበቃቸው ይሆናል” እንዳለ ልብ በል። (2 ጢሞ. 2:25) ለዚህ ጥቅስ የተዘጋጀው ለጥናት የሚረዳ መረጃ እንዲህ ይላል፦ “እንዲህ ላለው የአስተሳሰብ ለውጥ ሊመሰገን የሚገባው ሰው ሳይሆን መንገድ ስቶ የወጣው ክርስቲያን ይህን ወሳኝ ለውጥ እንዲያደርግ የረዳው ይሖዋ ነው። ቀጥሎ ጳውሎስ እንዲህ ያለው ንስሐ የሚያስገኛቸውን አንዳንድ ግሩም ውጤቶች ጠቅሷል፦ ኃጢአተኛው ይበልጥ ትክክለኛ የሆነ የእውነት እውቀት እንዲያገኝ፣ ወደ ልቦናው እንዲመለስ እንዲሁም ከሰይጣን ወጥመድ እንዲያመልጥ ይረዳዋል።—2ጢሞ 2:26” ጥፋት የሠራ ሰው ንስሐ ከገባ በኋላ ኮሚቴው እረኝነት እንዲደረግለት ዝግጅት ያደርጋል፤ ይህም ግለሰቡ ከሰይጣን ወጥመዶች ጋር መታገሉን እንዲቀጥል እንዲሁም ‘እግሩ ዘወትር ቀና በሆነ መንገድ እንዲጓዝ’ ይረዳዋል።—ዕብ. 12:12, 13፤ w24.08 23 አን. 14-15
ሐሙስ፣ ግንቦት 7
የምትፈልጉኝ ተአምራዊ ምልክት ስላያችሁ ሳይሆን ዳቦ ስለበላችሁና ስለጠገባችሁ ነው።—ዮሐ. 6:26
ኢየሱስ የመገባቸው ሰዎች ትኩረታቸው ያረፈው ሰብዓዊ ፍላጎታቸውን በማርካት ላይ ብቻ ነበር። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? በማግስቱ ሲመጡ ኢየሱስና ሐዋርያቱ እንደሄዱ አስተዋሉ። ስለዚህ ከጥብርያዶስ በመጡ ጀልባዎች ላይ ተሳፍረው ኢየሱስን ፍለጋ ወደ ቅፍርናሆም ሄዱ። (ዮሐ. 6:22-24) ይህን ያደረጉበት ዋነኛ ዓላማ ስለ መንግሥቱ መስማት ስለፈለጉ ነው? አይደለም። በዋነኝነት ያሳሰባቸው የምግብ ፍላጎታቸውን ማርካታቸው ነው። ይህን እንዴት እናውቃለን? ሕዝቡ ኢየሱስን ቅፍርናሆም አቅራቢያ ባገኙት ጊዜ ምን እንደተከሰተ ልብ በል። ኢየሱስ በዋነኝነት ያሳሰባቸው የምግብ ጉዳይ እንደሆነ በግልጽ ተናግሯል። ‘ዳቦ በልተው ቢጠግቡም’ ያ ምግብ ‘የሚጠፋ ምግብ’ እንደሆነ ነግሯቸዋል። ‘ዘላቂ ለሆነውና የዘላለም ሕይወት ለሚያስገኘው ምግብ እንዲሠሩም’ መክሯቸዋል። (ዮሐ. 6:26, 27) ኢየሱስ አባቱ እንዲህ ያለውን ምግብ እንደሚሰጣቸው ተናግሯል። w24.12 5 አን. 8-9
ዓርብ፣ ግንቦት 8
የጥበበኛ ሰው ልብ፣ አንደበቱ ጥልቅ ማስተዋል እንዲኖረው ያደርጋል፤ ለንግግሩም የማሳመን ችሎታ ይጨምርለታል።—ምሳሌ 16:23
የማስተማር ችሎታህን ለማሻሻል ከፈለግክ ከመድረክ የምታስተምረው ትምህርትም ሆነ በግል የምትሰጠው ምክር በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይገባል። መጽሐፍ ቅዱስን እንዲሁም ጽሑፎቻችንን በትጋት አጥና። (ምሳሌ 15:28) የአምላክን ቃል ስታጠና የጥቅሱን ትክክለኛ ማብራሪያ እንዲሁም ጥቅሱን እንዴት ልትጠቀምበት እንደምትችል ለማስተዋል ሞክር። እንዲሁም በምታስተምርበት ጊዜ የአድማጮችህን ልብ ለመንካት ጥረት አድርግ። ተሞክሮ ያላቸው ሽማግሌዎች ምክር እንዲሰጡህ በመጠየቅና ምክሩን ተግባራዊ በማድረግ የማስተማር ችሎታህን ማሻሻል ትችላለህ። (1 ጢሞ. 5:17) ሽማግሌዎች ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን ማበረታታት መቻል ይኖርባቸዋል፤ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ደግሞ መምከር አልፎ ተርፎም መውቀስ ይጠበቅባቸዋል። ያም ሆነ ይህ፣ ምንጊዜም ደግ ሊሆኑ ይገባል። ገርና አፍቃሪ ከሆንክ እንዲሁም ትምህርትህ በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ ከሆነ ውጤታማ ትሆናለህ፤ ምክንያቱም ታላቅ አስተማሪ የሆነውን የኢየሱስን ምሳሌ ትከተላለህ።—ማቴ. 11:28-30፤ 2 ጢሞ. 2:24፤ w24.11 24 አን. 16
ቅዳሜ፣ ግንቦት 9
ክብሩን በብሔራት . . . መካከል አስታውቁ።—መዝ. 96:3
ስለ ይሖዋ በምንናገረው ነገር ለእሱ ክብር መስጠት እንችላለን። የይሖዋ ሕዝቦች ‘ለይሖዋ እንዲዘምሩ፣’ ‘ስሙን እንዲያወድሱ፣’ ‘የማዳኑን ምሥራች እንዲያውጁ’ እና ‘ክብሩን በብሔራት መካከል እንዲያስታውቁ’ ተጋብዘዋል። (መዝ. 96:1-3) እነዚህ ሁሉ ለሰማዩ አባታችን ክብር መስጠት የምንችልባቸው መንገዶች ናቸው። (ሥራ 4:29) ባሉን ውድ ነገሮችም ለይሖዋ ክብር መስጠት እንችላለን። ከጥንትም ጀምሮ የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች በዚህ መንገድ ክብር ሰጥተውታል። (ምሳሌ 3:9) ለምሳሌ እስራኤላውያን ለቤተ መቅደሱ ግንባታና እንክብካቤ የሚውል መዋጮ አበርክተዋል። (2 ነገ. 12:4, 5፤ 1 ዜና 29:3-9) አሳቢ የሆኑ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት “በንብረታቸው” እሱንና ሐዋርያቱን አገልግለዋቸዋል። (ሉቃስ 8:1-3) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖችም ለመንፈሳዊ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው የእርዳታ መዋጮ ልከዋል። (ሥራ 11:27-29) እኛም በዛሬው ጊዜ በፈቃደኝነት በምናደርገው መዋጮ ለይሖዋ ክብር መስጠት እንችላለን። w25.01 4 አን. 8፤ 5 አን. 11
እሁድ፣ ግንቦት 10
እነዚህን ሰዎች በውኃ እንዳይጠመቁ ሊከለክላቸው የሚችል አለ?—ሥራ 10:47
ቆርኔሌዎስ እንዲጠመቅ የረዳው ምንድን ነው? ዘገባው “ከመላው ቤተሰቡ ጋር . . . ፈሪሃ አምላክ የነበረው ሰው” እንደነበረ ይናገራል። እንዲሁም ዘወትር ወደ አምላክ የሚማልድ ሰው ነበር። (ሥራ 10:2) ጴጥሮስ ምሥራቹን ሲሰብክላቸው ቆርኔሌዎስና ቤተሰቡ ክርስቶስን ተቀበሉ፤ ወዲያውኑም ተጠመቁ። (ሥራ 10:47, 48) ቆርኔሌዎስ ከቤተሰቡ ጋር ሆኖ ይሖዋን ለማምለክ ሲል የሚጠበቅበትን ማስተካከያ ሁሉ ለማድረግ ፈቃደኛ እንደነበረ ጥያቄ የለውም። (ኢያሱ 24:15፤ ሥራ 10:24, 33) ቆርኔሌዎስ በሰዎች ዘንድ የነበረው ከበሬታ ክርስቲያን እንዳይሆን እንቅፋት ሊሆንበት ይችል ነበር። እሱ ግን ይህ እንዲሆን አልፈቀደም። አንተስ እውነትን መቀበልህ በሕይወትህ ውስጥ ትልቅ ለውጥ እንድታደርግ ይጠይቅብሃል? ከሆነ ይሖዋ ረዳትህ እንደሆነ አስታውስ። ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ጋር በሚስማማ መንገድ እሱን ለማገልገል ያሳየኸውን ቁርጠኝነት ይባርክልሃል። w25.03 5 አን. 12-13
ሰኞ፣ ግንቦት 11
አምላክን [ከሚጻረሩ] የውሸት ታሪኮች ራቅ።—1 ጢሞ. 4:7
የይሖዋን ድርጅት ወይም አመራር የሚሰጡትን ወንድሞች በተመለከተ አሉታዊ ወሬዎችን ከሰማህ፣ የአምላክ ጠላቶች በኢየሱስም ሆነ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በነበሩት ደቀ መዛሙርቱ ላይ ምን እንዳደረጉባቸው አስታውስ። በዛሬው ጊዜ፣ መጽሐፍ ቅዱስ አስቀድሞ በተናገረው መሠረት የይሖዋ ሕዝቦች ስደት እየደረሰባቸውና ስማቸው እየጠፋ ነው። (ማቴ. 5:11, 12) የሐሰት ወሬዎች ምንጭ ማን እንደሆነ ካወቅንና አፋጣኝ እርምጃ ከወሰድን አንታለልም። ይህ አፋጣኝ እርምጃ ምንድን ነው? ከሐሰት ወሬዎች ራቅ። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ የውሸት ታሪኮችን ስንሰማ ምን ማድረግ እንዳለብን ግልጽ መመሪያ ሰጥቷል። ጳውሎስ፣ ጢሞቴዎስ ‘ለፈጠራ ወሬዎች ትኩረት እንዳይሰጡ’ ወንድሞችን እንዲያዝዝ እንዲሁም ‘አምላክን ከሚጻረሩ የውሸት ታሪኮች እንዲርቅ’ መመሪያ ሰጥቶታል። (1 ጢሞ. 1:3, 4) ከሐሰት ወሬዎች የምንርቀው የመረጃው ምንጭ ማን እንደሆነ ስለምናውቅ ነው። ከዚህ ይልቅ የእውነትን “ትክክለኛ ትምህርት” አጥብቀን እንይዛለን።—2 ጢሞ. 1:13፤ w24.04 11 አን. 16፤ 13 አን. 17
ማክሰኞ፣ ግንቦት 12
በለሰለሰ አንደበትና በሽንገላ ቃላት የየዋሆችን ልብ ያታልላሉ።—ሮም 16:18
ለይሖዋ ታማኝ ከሆኑት ጋር ያለህን አንድነት ጠብቅ። ይሖዋ አንድነት ባለው መንገድ እንድናመልከው ይፈልጋል። እውነትን አጥብቀን እስከያዝን ድረስ አንድነታችንን መጠበቅ እንችላለን። እውነትን አጥብቀው የማይዙ ሰዎች በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ መከፋፈል ይፈጥራሉ፤ በመሆኑም አምላክ ከእነሱ ‘እንድንርቅ’ አሳስቦናል። አለዚያ እኛ ራሳችን ከእውነት ልንርቅ እንችላለን። (ሮም 16:17) እውነትን ለይተን ስናውቅና አጥብቀን ስንይዝ መንፈሳዊ ደህንነታችንና ጤንነታችን ይጠበቃል። (ኤፌ. 4:15, 16) ከሰይጣን የሐሰት ትምህርቶችና ፕሮፓጋንዳ እንጠበቃለን። እንዲሁም በታላቁ መከራ ወቅት የይሖዋን ጥበቃና እንክብካቤ እናገኛለን። እንግዲያው እውነት የሆነውን ነገር አጥብቀህ ያዝ፤ ‘የሰላምም አምላክ ከአንተ ጋር ይሆናል።’—ፊልጵ. 4:8, 9፤ w24.07 13 አን. 16-17
ረቡዕ፣ ግንቦት 13
ይህ ሰው . . . ስለ ኃጢአት ለሁልጊዜ የሚሆን አንድ መሥዋዕት [አቅርቧል]።—ዕብ. 10:12
ኢየሱስ የኃጢአት ሸክም ለተጫናቸው ሰዎች ለየት ያለ ትኩረት ይሰጥ ነበር፤ ተከታዮቹ እንዲሆኑም ጋብዟቸዋል። በሰው ልጆች ላይ ለሚደርሰው መከራ ሁሉ ዋነኛው መንስኤ ኃጢአት እንደሆነ ያውቅ ነበር። በመሆኑም በኃጢአተኝነታቸው የሚታወቁ ሰዎችን ለመርዳት ጥረት አድርጓል። ሁኔታውን በምሳሌ ሲያስረዳ “ሐኪም የሚያስፈልጋቸው ሕመምተኞች እንጂ ጤነኞች አይደሉም” ብሏል። አክሎም እንዲህ አለ፦ “እኔ የመጣሁት ጻድቃንን ሳይሆን ኃጢአተኞችን ልጠራ ነው።” (ማቴ. 9:12, 13) ደግሞም ያደረገው ይህንኑ ነው። እግሩን በእንባዋ ያጠበችውን ሴት በርኅራኄ አነጋግሯታል፤ ኃጢአቷንም ይቅር ብሎላታል። (ሉቃስ 7:37-50) በውኃ ጉድጓዱ አጠገብ የነበረችው ሳምራዊት ሴት ሥነ ምግባር የጎደለው ሕይወት እንደምትመራ ቢያውቅም እንኳ ወሳኝ እውነቶችን አስተምሯታል። (ዮሐ. 4:7, 17-19, 25, 26) እንዲያውም አምላክ የኃጢአት የመጨረሻ ውጤት የሆነውን ሞትን እንዲቀለብስ ለኢየሱስ ኃይል ሰጥቶታል። እንዴት? ኢየሱስ ልጅ አዋቂ፣ ወንድ ሴት ሳይል ሰዎችን ከሞት አስነስቷል።—ማቴ. 11:5፤ w24.08 4 አን. 9-10
ሐሙስ፣ ግንቦት 14
በዓለም ላይ በጽድቅ፣ በሕዝቦችም ላይ በታማኝነት ይፈርዳል።—መዝ. 96:13
ይሖዋ በቅርቡ ስሙን የሚያስከብረው እንዴት ነው? በሚያስተላልፋቸው ፍርዶች አማካኝነት ነው። በቅርቡ፣ በስሙ ላይ ነቀፋ ያመጣችውን ታላቂቱ ባቢሎንን ያጠፋታል። (ራእይ 17:5, 16፤ 19:1, 2) የታላቂቱ ባቢሎንን ጥፋት የተመለከቱ አንዳንድ ሰዎች አብረውን በእውነተኛው አምልኮ መካፈል ይጀምሩ ይሆናል። በመጨረሻም፣ ይሖዋ በአርማጌዶን መላውን የሰይጣን ሥርዓት ያጠፋዋል፤ እሱን የሚቃወሙትንና ስሙን የሚሰድቡትን ሁሉ ይደመስሳል። የሚወዱትን፣ የሚታዘዙትንና ለእሱ ክብር በመስጠታቸው የሚኮሩትን ደግሞ ያድናቸዋል። (ማር. 8:38፤ 2 ተሰ. 1:6-10) የክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ሲያበቃ ከሚኖረው የመጨረሻ ፈተና በኋላ ይሖዋ ስሙን ሙሉ በሙሉ ያስቀድሳል። (ራእይ 20:7-10) በዚያ ጊዜ “ውኃ ባሕርን እንደሚሸፍን፣ ምድርም የይሖዋን ክብር በማወቅ ትሞላለች።” (ዕን. 2:14) በምድር ላይ ያለ ሰው ሁሉ ለስሙ የሚገባውን ክብር ለይሖዋ በሚሰጥበት ጊዜ መገኘት ምንኛ ያስደስታል! w25.01 7 አን. 15-16
ዓርብ፣ ግንቦት 15
ተግሣጽ የምትቀበሉበት አንዱ መንገድ ይህ ስለሆነ መከራ ሲደርስባችሁ መጽናት ያስፈልጋችኋል።—ዕብ. 12:7
ዕብራውያን ክርስቲያኖች የሚያጋጥማቸውን ተቃውሞ በጽናት ለመቋቋም ምን ሊረዳቸው ይችላል? ሐዋርያው ጳውሎስ ለሚያጋጥሟቸው ፈተናዎች ትክክለኛው አመለካከት ሊኖራቸው እንደሚገባ ተገንዝቦ ነበር። በመሆኑም አምላክ አንድ ክርስቲያን ሥልጠና እንዲያገኝ ሲል የእምነት ፈተናዎች እንዲደርሱበት ሊፈቅድ እንደሚችል ጳውሎስ አብራራላቸው። እንዲህ ያለው ሥልጠና ግለሰቡ ወሳኝ ክርስቲያናዊ ባሕርያትን እንዲያዳብርና እንዲያሻሽል ይረዳዋል። ዕብራውያን ክርስቲያኖች ፈተናዎቹ በሚያስገኙት ውጤት ላይ ማተኮራቸው መጽናት ቀላል እንዲሆንላቸው ያደርጋል። (ዕብ. 12:11) ዕብራውያን ክርስቲያኖች ፈተናዎችን በጽናት ለመቋቋም ይበልጥ ቁርጠኛ እንዲሆኑ ጳውሎስ አሳስቧቸዋል። ደግሞም ስደትን በጽናት ስለመቋቋም ከተነሳ ጳውሎስ ብዙ የሚያውቀው ነገር አለ። ቀደም ሲል ክርስቲያኖችን ያሳድድ ስለነበር የሚጋፈጡት ስደት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ያውቃል። ስደትን በጽናት መቋቋም የሚቻለው እንዴት እንደሆነም ያውቃል። ምክንያቱም ክርስቲያን ከሆነ በኋላ የተለያየ ዓይነት ተቃውሞ ደርሶበታል።—2 ቆሮ. 11:23-25፤ w24.09 12 አን. 16-17
ቅዳሜ፣ ግንቦት 16
ዘወትር ነቅታችሁ ጠብቁ።—ማቴ. 25:13
ቀን አልፎ ቀን ሲተካ አገልግሎታችን ይበልጥ አጣዳፊ እየሆነ ይሄዳል። ለምን? ምክንያቱም ጊዜው እያለቀ ነው። ማርቆስ 13:10 ላይ ኢየሱስ በመጨረሻዎቹ ቀናት ስለሚከናወነው የስብከት ሥራ ምን እንዳለ ልብ በል። ማቴዎስ በጻፈው ዘገባ መሠረት ኢየሱስ ምሥራቹ “መጨረሻው” ከመምጣቱ በፊት በመላው ምድር እንደሚሰበክ ተናግሯል። (ማቴ. 24:14) ይህ አገላለጽ፣ የሰይጣን ክፉ ሥርዓት ሙሉ በሙሉ የሚጠፋበትን ጊዜ ያመለክታል። ይሖዋ በቅርቡ ለሚከሰቱት ክንውኖች “ቀንና ሰዓት” ወስኗል። (ማቴ. 24:36፤ ሥራ 1:7) እያንዳንዱ ቀን ባለፈ ቁጥር ወደዚህ ዕለት እየተጠጋን ነው። (ሮም 13:11) እስከዚያው ግን፣ መጨረሻው እስኪመጣ ድረስ መስበካችንን መቀጠል ይኖርብናል። ስለ አገልግሎታችን ስናስብ የሚከተለውን ወሳኝ ጥያቄ መጠየቅ ይኖርብናል፦ ምሥራቹን የምንሰብከው ለምንድን ነው? በቀላል አነጋገር፣ እንድንሰብክ የሚያነሳሳን ፍቅር ነው። የስብከቱ ሥራችን ለምሥራቹ ያለንን ፍቅር፣ ለሰዎች ያለንን ፍቅር፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ ለይሖዋና ለስሙ ያለንን ፍቅር ያንጸባርቃል። w24.05 14-15 አን. 2-3
እሁድ፣ ግንቦት 17
አምላክ የሠራውን እያንዳንዱን ነገር ተመለከተ፤ እነሆ፣ እጅግ መልካም ነበር!—ዘፍ. 1:31
ወላጆች፣ ልጆቻችሁ በፍጥረት ላይ እንዲያሰላስሉ አበረታቷቸው። በገጠራማ አካባቢ ስትጓዙ ወይም አትክልት ስትንከባከቡ ልጆቻችሁ በፍጥረት ላይ የሚታዩ ንድፎችን ልብ ብለው እንዲመለከቱ ጋብዟቸው። ለምን? እነዚህ ንድፎች ጥበበኛ የሆነ ንድፍ አውጪ እንዳለ ይመሠክራሉ። ለምሳሌ ሳይንቲስቶች በጥምዝምዝ ቅርጾች ላይ ለረጅም ዓመታት ጥናት ሲያካሂዱ ቆይተዋል። ኒኮላ ፋሜሊ የተባሉ አንድ ሳይንቲስት እንደተናገሩት በተፈጥሮ ላይ የሚገኙ ጥምዝምዝ ቅርጾችን ስንቆጥር ቁጥሮቹ አንድን ቀመር እንደሚከተሉ እናስተውላለን። ይህ ቀመር የፊቦናቺ ቀመር በመባል ይታወቃል። ጥምዝምዝ ቅርጾች በጋላክሲዎች፣ በዛጎሎች፣ በቅጠሎች፣ በሱፍ አበቦችና በሌሎች በርካታ ፍጥረታት ላይ ይታያሉ። w24.12 16 አን. 7
ሰኞ፣ ግንቦት 18
እሱ ሕይወትህ ነው።—ዘዳ. 30:20
ሙሴ፣ ዳዊትና ዮሐንስ የኖሩበት ዘመንም ሆነ የነበሩበት ሁኔታ ከእኛ በእጅጉ የተለየ ነው። ይሁንና ከእነሱ ጋር የሚያመሳስለን ብዙ ነገር አለ። እኛም እንደ እነሱ እውነተኛውን አምላክ እናገለግላለን። እንደ እነሱ ሁሉ እኛም ወደ ይሖዋ እንጸልያለን፤ በእሱ እንታመናለን፤ እንዲሁም ከእሱ መመሪያ ለማግኘት ጥረት እናደርጋለን። በተጨማሪም በጥንት ዘመን እንደኖሩት እንደ እነዚህ ሰዎች ሁሉ እኛም፣ ይሖዋ የሚታዘዙትን ሰዎች አትረፍርፎ እንደሚባርክ እርግጠኞች ነን። እንግዲያው ይሖዋን በመታዘዝ እነዚህ ታማኝ አረጋውያን የሰጡትን ምክር እንከተል። እንዲህ ካደረግን፣ በምናደርገው ነገር ሁሉ እውነተኛ ስኬት እናገኛለን። ‘ረጅም ዕድሜ እንኖራለን’፤ እንዲያውም የዘላለም ሕይወት እናገኛለን። በተጨማሪም ከምንጠብቀውም ሆነ ከምናስበው እጅግ አብልጦ ቃሉን የሚፈጽመውን አፍቃሪውን አባታችንን ማስደሰት የሚያስገኘውን ደስታ እናጣጥማለን።—ኤፌ. 3:20፤ w24.11 13 አን. 20-21
ማክሰኞ፣ ግንቦት 19
አምላክ የተለያዩ የአካል ክፍሎችን . . . በጉባኤ ውስጥ መድቧል።—1 ቆሮ. 12:28
በመጀመሪያው መቶ ዘመን አንዳንድ ወንድሞች የጉባኤ አገልጋዮች ሆነው ተሹመው ነበር። (1 ጢሞ. 3:8) ሐዋርያው ጳውሎስ አንዳንዶች ‘ጠቃሚ አገልግሎት እንደሚያከናውኑ’ ሲጽፍ ስለ እነሱ መጥቀሱ ሳይሆን አይቀርም። ሽማግሌዎች በማስተማሩና በእረኝነቱ ሥራ ላይ ትኩረት ማድረግ እንዲችሉ የጉባኤ አገልጋዮች ሌሎች አስፈላጊ ጉዳዮችን ያከናውኑ እንደነበር ከሁኔታዎች መረዳት ይቻላል። ለምሳሌ የጉባኤ አገልጋዮች የቅዱሳን መጻሕፍትን ግልባጭ በማዘጋጀት ወይም ለዚህ ሥራ የሚያስፈልጉትን ቁሳቁሶች በመግዛት እገዛ አበርክተው ሊሆን ይችላል። በጉባኤያችሁ ያሉ የጉባኤ አገልጋዮች የሚያከናውኗቸውን አንዳንድ ጠቃሚ አገልግሎቶች እንመልከት። (1 ጴጥ. 4:10) የጉባኤውን ሒሳብ እንዲከታተሉ፣ ክልል እንዲያደራጁ፣ ጽሑፎችን እንዲያዝዙና ለአስፋፊዎች እንዲሰጡ፣ የኦዲዮና የቪዲዮ መሣሪያዎች ላይ እንዲሠሩ፣ አስተናጋጅ እንዲሆኑ ወይም በስብሰባ አዳራሹ ጥገና ሥራ እንዲካፈሉ ይመደቡ ይሆናል። ጉባኤው በተገቢው መንገድ ሥራውን እንዲያከናውን እነዚህ አገልግሎቶች የግድ አስፈላጊ ናቸው።—1 ቆሮ. 14:40፤ w24.10 19 አን. 4-5
ረቡዕ፣ ግንቦት 20
ኃይልን በሚሰጠኝ በእሱ አማካኝነት ለሁሉም ነገር የሚሆን ብርታት አለኝ።—ፊልጵ. 4:13
ይሖዋ ሕያው እንደሆነና እኛን ለመርዳት ዝግጁ እንደሆነ ካስታወስን ትንሽም ይሁን ትልቅ ማንኛውንም ፈተና በጽናት መቋቋም እንችላለን። ምክንያቱም እሱ ሁሉን ቻይ አምላክ ስለሆነ ለመጽናት የሚያስችል ብርታት ይሰጠናል። ስለዚህ የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች በልበ ሙሉነት መጋፈጥ እንችላለን። ትናንሽ ፈተናዎች ሲያጋጥሙን የይሖዋን እርዳታ ማየታችን ትላልቅ ፈተናዎች በሚያጋጥሙን ጊዜም እንደሚረዳን እንድንተማመን ያደርገናል። ንጉሥ ዳዊት በይሖዋ ላይ ያለውን እምነት ለማጠናከር የረዱትን ሁለት አጋጣሚዎች እስቲ እንመልከት። በልጅነቱ እረኛ ሳለ አንድ ድብና አንድ አንበሳ መጥተው የአባቱን በጎች ነጥቀው ወስደው ነበር። በሁለቱም ጊዜያት ዳዊት አውሬውን በማሳደድ በጎቹን ማስጣል ችሏል። ያም ቢሆን ይህን ማድረግ የቻለው በራሱ ኃይል እንደሆነ አልተሰማውም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ እንደረዳው ተገንዝቧል። (1 ሳሙ. 17:34-37) ዳዊት በእነዚህ አጋጣሚዎች ላይ ማሰላሰሉ ሕያው የሆነው አምላክ ወደፊትም እንደሚያበረታው እንዲተማመን ረድቶታል። w24.06 21 አን. 5-6
ሐሙስ፣ ግንቦት 21
እውነታውን ከመስማቱ በፊት መልስ የሚሰጥ ሰው፣ ሞኝነት ይሆንበታል፤ ውርደትም ይከናነባል።—ምሳሌ 18:13
አንድ ግብዣ ላይ እንድትገኝ ተጠርተሃል እንበል። በግብዣው ላይ ብትገኝ ይሻላል? ጋባዡን ወይም የተዘጋጀውን ግብዣ በተመለከተ የማታውቅ ከሆነ እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎችን መጠየቅ ይኖርብሃል፦ “ግብዣው የሚካሄደው መቼና የት ነው? ስንት ሰዎች ይገኛሉ? ግብዣውን በኃላፊነት የሚከታተለው ማን ነው? እነማን ይገኛሉ? በግብዣው ላይ ምን ምን ይደረጋል? የአልኮል መጠጥ ይቀርባል?” የእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ለማድረግ ይረዳሃል። ቀጥሎም ያገኘኸውን መረጃ ከግምት በማስገባት አጠቃላይ ሁኔታውን በጥንቃቄ አጢን። ለምሳሌ ለመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች አክብሮት የሌላቸው ሰዎች በግብዣው ላይ እንደሚገኙ ወይም ደግሞ የአልኮል መጠጥ እንደሚቀርብና ግብዣውን በኃላፊነት የሚከታተል ሰው እንደማይኖር ብትገነዘብስ? ግብዣው መረን ወደለቀቀ ድግስ ሊቀየር የሚችልበት አጋጣሚ ይኖር ይሆን? (1 ጴጥ. 4:3) አጠቃላይ ሁኔታውን ካጤንክ በኋላ ጥሩ ውሳኔ ማድረግ ቀላል ይሆንልሃል። w25.01 15 አን. 4-5
ዓርብ፣ ግንቦት 22
ኃጢአታችሁ እንደ ደም ቢቀላ እንደ በረዶ ይነጣል።—ኢሳ. 1:18
ይሖዋ ንስሐ የገቡ ሰዎችን ኃጢአት በቤዛው አማካኝነት የሚደመስሰው እንዴት እንደሆነ እንድንገነዘብ ለመርዳት ሌሎች ዘይቤያዊ አገላለጾችን ተጠቅሟል። ቀይ ቀለም ነክቶት የመነቸከን ጨርቅ ማስለቀቅ በጣም አስቸጋሪ ነው። ያም ቢሆን፣ ይሖዋ በዚህ ዘይቤያዊ አገላለጽ አማካኝነት ኃጢአታችን ጨርሶ የማይታይበት ደረጃ ላይ እስኪደርስ ድረስ ታጥቦ እንደሚነጻ ዋስትና ሰጥቶናል። ኃጢአት ‘ከዕዳ’ ጋርም ተመሳስሏል። (ማቴ. 6:12 ግርጌ፤ ሉቃስ 11:4 ግርጌ) ስለዚህ በይሖዋ ላይ ኃጢአት በሠራን ቁጥር ዕዳ ውስጥ ይበልጥ እየተዘፈቅን እንደምንሄድ ሊቆጠር ይችላል። ለይሖዋ መክፈል የሚጠበቅብን ዕዳ በጣም ከፍተኛ ነው! ሆኖም ይሖዋ ይቅር ሲለን መክፈል የሚጠበቅብንን ዕዳ ሙሉ በሙሉ እንደሚሰርዝልን ሊቆጠር ይችላል። አንድን ኃጢአት ይቅር ካለን በኋላ ዕዳውን እንድንከፍል አይጠብቅብንም። ይሖዋ ይቅር ሲለን የሚሰማንን እፎይታ የሚገልጽ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው! w25.02 10 አን. 9-10
ቅዳሜ፣ ግንቦት 23
ለልጆቻቸው ሀብት ማከማቸት የሚጠበቅባቸው ወላጆች ናቸው እንጂ ልጆች ለወላጆቻቸው አያከማቹም።—2 ቆሮ. 12:14
ወላጆች ዕድሜያቸው እየገፋ ሲሄድ እገዛ ሊያስፈልጋቸው ይችላል፤ ደግሞም ብዙ ልጆች ወላጆቻቸውን በደስታ ይረዳሉ። (1 ጢሞ. 5:4) ይሁንና ክርስቲያን ወላጆች፣ ነገ ላይ እጥፍ ድርብ ደስታ የሚያስገኝላቸው በእርጅናቸው ዘመን የሚጦሯቸው ልጆች ማፍራታቸው ሳይሆን ይሖዋን በታማኝነት የሚያገለግሉ ልጆች ማሳደጋቸው እንደሆነ ይገነዘባሉ። (3 ዮሐ. 4) ልጆቻችሁን ራሳቸውን ችለው ለሚኖሩበት ጊዜ ስታዘጋጇቸው በይሖዋ በመታመን ረገድ ጥሩ ምሳሌ ሁኗቸው። ገና ከትንሽነታቸው አንስቶ ተግቶ መሥራት ያለውን ዋጋ አሳዩአቸው። (ምሳሌ 29:21፤ ኤፌ. 4:28) እያደጉ ሲሄዱ በትምህርታቸው ጠንክረው እንዲሠሩ እርዷቸው። ልጆቻችሁ ምን ትምህርት እንደሚከታተሉ የሚወስኑበት ጊዜ ሲደርስ ደግሞ ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ የሚረዷቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ለማግኘት ምርምር አድርጉ። ይህም ልጆቻችሁ ወደፊት ሥራ ሲይዙ ራሳቸውን ለማስተዳደርና በአገልግሎት የተሟላ ተሳትፎ ለማድረግ የሚረዳቸውን ትምህርት ለመምረጥ ያስችላቸዋል። w25.03 30-31 አን. 15-16
እሁድ፣ ግንቦት 24
አዲሱን ስብዕና [ልበሱ]።—ኤፌ. 4:24
ኢሳይያስ ምዕራፍ 65 ላይ ይሖዋ በመንፈሳዊው ገነት ውስጥ የሚኖሩት ሰዎች ምን ዓይነት ሕይወት እንደሚኖራቸው ተናግሮ ነበር። ትንቢቱ የመጀመሪያ ፍጻሜውን ያገኘው በ537 ዓ.ዓ. ነው። በዚያ ወቅት፣ ንስሐ የገቡ አይሁዳውያን ከባቢሎን ግዞት ነፃ ወጥተው ወደ አገራቸው ተመልሰዋል። ይሖዋ ሕዝቦቹን ባርኳቸዋል፤ እንዲሁም የወደመችውን የኢየሩሳሌም ከተማ መልሰው ውብ አድርገው እንዲገነቡና ቤተ መቅደሱን በድጋሚ የእውነተኛው አምልኮ ማዕከል እንዲያደርጉ ረድቷቸዋል። (ኢሳ. 51:11፤ ዘካ. 8:3) የኢሳይያስ ትንቢት ለሁለተኛ ጊዜ ፍጻሜውን ማግኘት የጀመረው በ1919 በዘመናችን ያሉ የይሖዋ አገልጋዮች ከታላቂቱ ባቢሎን ግዞት ነፃ በወጡበት ጊዜ ነው። ከዚያም መንፈሳዊው ገነት ቀስ በቀስ በመላዋ ምድር መስፋፋት ጀመረ። ቀናተኛ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ብዙ ጉባኤዎችን ያቋቁሙ እና ክርስቲያናዊ ባሕርያትን ያንጸባርቁ ነበር። ቀደም ሲል ዓመፀኛና ጨካኝ የነበሩ ወንዶችና ሴቶች “እንደ አምላክ ፈቃድ የተፈጠረውን . . . አዲሱን ስብዕና መልበስ” ችለዋል። w24.04 20-21 አን. 3-4
ሰኞ፣ ግንቦት 25
እያንዳንዱ የራሱን የኃላፊነት ሸክም ይሸከማል።—ገላ. 6:5
በአንዳንድ አገሮች ላላገቡ ሰዎች የትዳር ጓደኛ የሚመርጡት ወላጆች ወይም ሌሎች አዋቂዎች ናቸው። በሌሎች አገሮች ደግሞ ቤተሰቦች ወይም ጓደኞች ላላገቡ ሰዎች የትዳር ጓደኛ ከፈለጉላቸው በኋላ ግለሰቦቹ ይጣጣሙ እንደሆነ ለማየት ተገናኝተው እንዲነጋገሩ አጋጣሚ ይፈጥሩላቸዋል። ለአንድ ሰው የትዳር ጓደኛ እንድትፈልግ ከተጠየቅክ ወንዱም ሆነ ሴቷ የሚፈልጓቸውን ነገሮች ከግምት አስገባ። ሊሆናቸው የሚችል ሰው ካገኘህላቸው በኋላ ስለ ግለሰቡ ወይም ስለ ግለሰቧ ማንነት፣ ባሕርይ፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ መንፈሳዊነት የቻልከውን ያህል ለማወቅ ጥረት አድርግ። ከገንዘብ፣ ከትምህርት ደረጃ ወይም በማኅበረሰቡ ውስጥ ካላቸው ቦታ የበለጠ አስፈላጊ የሆነው ከይሖዋ ጋር ያላቸው የቅርብ ዝምድና ነው። ያም ቢሆን፣ ትዳር ከመመሥረት ጋር በተያያዘ የመጨረሻውን ውሳኔ ማድረግ ያለባቸው የሚጋቡት ወንድምና እህት እንደሆኑ አስታውስ። w24.05 23 አን. 11
ማክሰኞ፣ ግንቦት 26
እውነተኛ ወዳጅ ምንጊዜም አፍቃሪ ነው።—ምሳሌ 17:17
እየተጠናኑ ያሉ ጥንዶችን መርዳት የምንችልበት አንዱ መንገድ በአንደበት አጠቃቀማችን ነው። አንዳንድ ጊዜ ራሳችንን መቆጣጠር ሊያስፈልገን ይችላል። (ምሳሌ 12:18) ለምሳሌ አንድ ወንድምና አንዲት እህት መጠናናት እንደጀመሩ ለሌሎች ለመናገር እንጓጓ ይሆናል፤ ያም ቢሆን ወሬውን ራሳቸው መናገር ሊፈልጉ ይችላሉ። እየተጠናኑ ስላሉ ጥንዶች ሐሜት ማውራት ወይም ከግል ጉዳዮቻቸው ጋር በተያያዘ እነሱን መተቸት አይኖርብንም። (ምሳሌ 20:19፤ ሮም 14:10፤ 1 ተሰ. 4:11) ከዚህም ሌላ ከጋብቻ ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን በመጠየቅ ወይም ሐሳቦችን በመሰንዘር ጫና ልናሳድርባቸው አይገባም። እየተጠናኑ የነበሩ ጥንዶች ግንኙነታቸውን ለማቋረጥ ቢወስኑስ? ስለ ጉዳዩ ለማወቅ ጥረት ከማድረግ ወይም ወገን ከመያዝ መቆጠብ ይኖርብናል። (1 ጴጥ. 4:15) አንድ ወንድና አንዲት ሴት ለመለያየት ወስነዋል ማለት መጠናናቱ አልተሳካም ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ብዙውን ጊዜ መጠናናቱ ዓላማውን እንዳከናወነ የሚጠቁም ነው፤ ምክንያቱም ጥንዶቹን ጥሩ ውሳኔ ላይ እንዲደርሱ ረድቷቸዋል። ያም ቢሆን ይህ ውሳኔ የስሜት ቁስል ሊያስከትልባቸው ይችላል። ስለዚህ እነሱን መደገፍ የምንችልባቸውን መንገዶች መፈለግ እንችላለን። w24.05 31 አን. 15-16
ረቡዕ፣ ግንቦት 27
በመከራ ቀን ተስፋ የምትቆርጥ ከሆነ ጉልበትህ እጅግ ይዳከማል።—ምሳሌ 24:10
በሕይወታችን ውስጥ ሊያጋጥሙን ከሚችሉት በጣም ተስፋ አስቆራጭ ፈተናዎች አንዱ የቤተሰባችን አባል ወይም የቅርብ ጓደኛችን ይሖዋን ሲተው ማየት ነው። (መዝ. 78:40) ከግለሰቡ ጋር በጣም የምንቀራረብ ከሆነ ደግሞ ሁኔታውን መቀበል የዚያኑ ያህል ከባድ ይሆንብናል። አንተም እንዲህ ያለ ከባድ ፈተና አጋጥሞህ ከሆነ የሳዶቅ የታማኝነት ምሳሌ ሊያበረታታህ ይችላል። ሳዶቅ የቅርብ ጓደኛው አብያታር ታማኝነቱን ባጓደለበት ወቅት ለይሖዋ ታማኝ ሆኖ ቀጥሏል። ሁኔታው የተፈጠረው ዳዊት መሞቻው በተቃረበበት ወቅት ነው፤ ይሖዋ ዳዊትን ተክቶ እንዲነግሥ የመረጠው ሰለሞንን ቢሆንም ልጁ አዶንያስ ዙፋኑን ለመውሰድ አሰበ። (1 ዜና 22:9, 10) አብያታር አዶንያስን ለመደገፍ መረጠ። (1 ነገ. 1:5-8) አብያታር እንዲህ ማድረጉ ለዳዊትና ለሳዶቅ ብቻ ሳይሆን ለይሖዋም ታማኝ እንዳልሆነ የሚያሳይ ነው። ሳዶቅና አብያታር ለብዙ ዓመታት አብረው በክህነት አገልግለዋል።—2 ሳሙ. 8:17፤ 15:29፤ 19:11-14፤ w24.07 6 አን. 14-15
ሐሙስ፣ ግንቦት 28
ምንጊዜም ተጠንቅቆ የሚኖር ሰው ደስተኛ ነው።—ምሳሌ 28:14
ከፈተና ራሳችንን ለመጠበቅ የምናደርገው ጥረት የሚክስ እንደሆነ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ኃጢአት “ጊዜያዊ ደስታ” ሊያስገኝ ቢችልም በይሖዋ መሥፈርቶች መመራት ከዚህ እጅግ የላቀ ደስታ ያስገኝልናል። (ዕብ. 11:25፤ መዝ. 19:8) ምክንያቱም የተፈጠርነው በይሖዋ መሥፈርቶች እንድንመራ ተደርገን ነው። (ዘፍ. 1:27) በመሆኑም ንጹሕ ሕሊና እንዲሁም የዘላለም ሕይወት ተስፋ ይኖረናል። (1 ጢሞ. 6:12፤ 2 ጢሞ. 1:3፤ ይሁዳ 20, 21) እውነት ነው፣ ‘ሥጋ ደካማ ነው።’ (ማቴ. 26:41) ሆኖም ይህ ሲባል ፈተናዎችን ማሸነፍ አንችልም ማለት አይደለም። ይሖዋ የሚያስፈልገንን ኃይል ሊሰጠን ዝግጁ ነው። (2 ቆሮ. 4:7) ይሁንና አምላክ የሚሰጠን ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነውን ኃይል እንደሆነ ልብ በል። ሰብዓዊ ኃይላችንን መጠቀም ማለትም ከፈተና ራሳችንን ለመጠበቅ በየዕለቱ ጥረት ማድረግ የእኛ ኃላፊነት ነው። ይሖዋ በሚያስፈልገን ጊዜ ተጨማሪ ኃይል እንዲሰጠን የምናቀርበውን ጸሎት እንደሚመልስልን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (1 ቆሮ. 10:13) አዎ፣ በይሖዋ እርዳታ ከፈተና ራሳችንን መጠበቅ እንችላለን። w24.07 18-19 አን. 19-21
ዓርብ፣ ግንቦት 29
ኃጢአት የመሥራት ልማድ ያላቸውን ሰዎች በሁሉ ፊት ውቀሳቸው።—1 ጢሞ. 5:20
ሐዋርያው ጳውሎስ በሽምግልና ለሚያገለግለው ለጢሞቴዎስ “ኃጢአት የመሥራት ልማድ ያላቸውን ሰዎች” በተመለከተ በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ያሉትን ቃላት ጽፎለታል። ይሁንና ይህን ሲል ምን ማለቱ ነበር? “በሁሉ ፊት” ሲል መላውን ጉባኤ ማመልከቱ ላይሆን ይችላል። ከዚህ ይልቅ ስለ ኃጢአቱ የሚያውቁትን የተወሰኑ ክርስቲያኖች ማመልከቱ ነው። የዓይን ምሥክሮች ወይም ግለሰቡ ስለ ኃጢአቱ የነገራቸው ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ። ሽማግሌዎች ጉዳዩ እንደታየ እንዲሁም ኃጢአተኛው እርማት እንደተሰጠው ለእነሱ ብቻ ይነግሯቸዋል። አንዳንድ ጊዜ የተፈጸመው ኃጢአት በጉባኤው ውስጥ በስፋት የሚታወቅ ወይም መታወቁ የማይቀር ሊሆን ይችላል። ሁኔታው እንደዚያ ከሆነ “በሁሉ ፊት” የሚለው መላውን ጉባኤ ያካትታል። ስለዚህ አንድ ሽማግሌ፣ ያ ወንድም ወይም ያቺ እህት ወቀሳ እንደተሰጣቸው የሚገልጽ ማስታወቂያ ለጉባኤው ይናገራል። ለምን? ጳውሎስ እንዳለው በኃጢአት እንዳይወድቁ “ለሌሎቹ ማስጠንቀቂያ እንዲሆን” ነው። w24.08 24 አን. 16-17
ቅዳሜ፣ ግንቦት 30
እነዚህ እውነተኛ የአምላክ ቃሎች ናቸው።—ራእይ 19:9
እስከ መጨረሻው ድረስ በይሖዋ አገልግሎት ተግተን ልንሠራ ይገባል። ቅቡዓን ክርስቲያኖች፣ ኢየሱስ ወደ ሰማያዊ ውርሻቸው ‘እንዲወስዳቸው’ እስከ መጨረሻው ንቁ መሆን አለባቸው። (ማቴ. 24:40) እነዚህ ክርስቲያኖች ከኢየሱስ ጋር ለመሆን በሰማይ ‘አንድ ላይ የሚሰበሰቡበትን’ ጊዜ በጉጉት ይጠባበቃሉ። ከአርማጌዶን ጦርነት በኋላ የኢየሱስ ሙሽራ በመሆን በበጉ ሠርግ ላይ ይካፈላሉ። (2 ተሰ. 2:1) ፍርድ የሚሰጥበት ጊዜ በፍጥነት እየተቃረበ ቢሆንም የሚያስፈራን ነገር የለም። ታማኝ ሆነን ከጸናን አፍቃሪ የሆነው የሰማዩ አባታችን ‘በሰው ልጅ ፊት መቆም እንድንችል’ ‘ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነውን ኃይል’ ይሰጠናል። (2 ቆሮ. 4:7፤ ሉቃስ 21:36) ተስፋችን ሰማያዊም ይሁን ምድራዊ፣ በኢየሱስ ምሳሌዎች ውስጥ የሚገኙትን ማስጠንቀቂያዎች ልብ ካልን አባታችን ይደሰትብናል። በይሖዋ ጸጋ ስማችን በሕይወት “መጽሐፍ ላይ ተጽፎ” ይገኛል።—ዳን. 12:1፤ ራእይ 3:5፤ w24.09 24-25 አን. 19-20
እሁድ፣ ግንቦት 31
ወደ አምላክ መቅረብ ይበጀኛል።—መዝ. 73:28
በአምላክ ቃል እርዳታ የአእምሮ ሰላም ማግኘት ትችላለህ። እንዴት? በሰማይ የምታከማቸውን ሀብት ጨምሮ ያገኘሃቸው ነገሮች ያላቸውን ዋጋ አስብ፤ ከዚያም ያገኘኸውን ነገር ሀብት የሚያሳድዱ ሰዎች ካላቸው ነገር ጋር አወዳድር። እነሱ ያላቸው ዓለም የሚሰጣቸው ነገር ብቻ ነው። ለወደፊት ተስፋ የሚያደርጉት ምንም ነገር ስለሌለ የሚታመኑት በዚህ ዓለም በሚያገኙት ስኬት ላይ ብቻ ነው። ለአንተ ግን ይሖዋ ልታስበው ከምትችለው በላይ በረከት እንደሚሰጥህ ቃል ገብቶልሃል። (መዝ. 145:16) ልናስብበት የሚገባው ሌላም ነገር አለ፦ የተለየ ውሳኔ አድርገን ቢሆን ኖሮ ሕይወታችን ምን ይመስል እንደነበር በእርግጥ ማወቅ እንችላለን? ሆኖም ስለ አንድ ነገር እርግጠኞች ነን። ለአምላክና ለሰዎች ባላቸው ፍቅር ተነሳስተው ውሳኔ የሚያደርጉ ሰዎች መልካም ነገር አይጎድልባቸውም። w24.10 27 አን. 12-13