የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • es26
  • መጋቢት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • መጋቢት
  • ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2026
  • ንዑስ ርዕሶች
  • እሁድ፣ መጋቢት 1
  • ሰኞ፣ መጋቢት 2
  • ማክሰኞ፣ መጋቢት 3
  • ረቡዕ፣ መጋቢት 4
  • ሐሙስ፣ መጋቢት 5
  • ዓርብ፣ መጋቢት 6
  • ቅዳሜ፣ መጋቢት 7
  • እሁድ፣ መጋቢት 8
  • ሰኞ፣ መጋቢት 9
  • ማክሰኞ፣ መጋቢት 10
  • ረቡዕ፣ መጋቢት 11
  • ሐሙስ፣ መጋቢት 12
  • ዓርብ፣ መጋቢት 13
  • ቅዳሜ፣ መጋቢት 14
  • እሁድ፣ መጋቢት 15
  • ሰኞ፣ መጋቢት 16
  • ማክሰኞ፣ መጋቢት 17
  • ረቡዕ፣ መጋቢት 18
  • ሐሙስ፣ መጋቢት 19
  • ዓርብ፣ መጋቢት 20
  • ቅዳሜ፣ መጋቢት 21
  • እሁድ፣ መጋቢት 22
  • ሰኞ፣ መጋቢት 23
  • ማክሰኞ፣ መጋቢት 24
  • ረቡዕ፣ መጋቢት 25
  • ሐሙስ፣ መጋቢት 26
  • ዓርብ፣ መጋቢት 27
  • ቅዳሜ፣ መጋቢት 28
  • እሁድ፣ መጋቢት 29
  • ሰኞ፣ መጋቢት 30
  • ማክሰኞ፣ መጋቢት 31
ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2026
es26

መጋቢት

እሁድ፣ መጋቢት 1

የሞተ ከኃጢአቱ ነፃ ወጥቷል።—ሮም 6:7

መጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ጻድቃን ከጊዜ በኋላ መጥፎ ጎዳና መከተል እንደጀመሩ ይናገራል። እንዲህ ካሉት ሰዎች መካከል ንጉሥ ሰለሞን ይገኝበታል። ሰለሞን የአምላክን መንገዶች በሚገባ ተምሯል፤ ይሖዋም አትረፍርፎ ባርኮታል። ያም ቢሆን ውሎ አድሮ የሐሰት አማልክትን ማምለክ ጀመረ። ሰለሞን የሠራው ኃጢአት ይሖዋን እጅግ አስቆጥቶታል፤ በብሔሩም ላይ ለበርካታ መቶ ዘመናት የዘለቀ መዘዝ አስከትሏል። እርግጥ ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስ ሰለሞን ‘ከአባቶቹ ጋር እንዳንቀላፋ’ ይናገራል፤ አባቶቹ ከተባሉት መካከል እንደ ንጉሥ ዳዊት ያሉ ታማኝ ሰዎች ይገኙበታል። (1 ነገ. 11:5-9, 43፤ 2 ነገ. 23:13) ይሁንና ሰለሞን የተቀበረበት መንገድ ትንሣኤ እንደሚያገኝ ዋስትና ይሆናል? መጽሐፍ ቅዱስ ይህን በቀጥታ አይናገርም። ትንሣኤ አፍቃሪ የሆነው አምላካችን የሚሰጠው ስጦታ ነው። ይህን ስጦታ የሚሰጠው ለዘላለም እሱን የማገልገል አጋጣሚ ሊሰጣቸው ለሚፈልጋቸው ሰዎች ነው። (ኢዮብ 14:13, 14፤ ዮሐ. 6:44) ታዲያ ሰለሞን ይህን ስጦታ ያገኝ ይሆን? አናውቅም፤ መልሱን የሚያውቀው ይሖዋ ብቻ ነው። የምናውቀው ነገር ቢኖር ይሖዋ ትክክል የሆነውን ነገር እንደሚያደርግ ነው። w24.05 4 አን. 9

ሰኞ፣ መጋቢት 2

በድንኳንህ ለዘላለም በእንግድነት እቀመጣለሁ።—መዝ. 61:4

ራሳችንን ወስነን የይሖዋ ወዳጆች ስንሆን በእሱ ምሳሌያዊ ድንኳን ውስጥ እንግዶቹ እንሆናለን። የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ እናገኛለን፤ እንዲሁም ከሌሎቹ የይሖዋ እንግዶች ጋር ጥሩ ወዳጅነት ይኖረናል። የይሖዋ ምሳሌያዊ ድንኳን በአንድ ቦታ የተወሰነ አይደለም። የይሖዋ ታዛዥ አገልጋዮች ባሉበት ቦታ ሁሉ ድንኳኑ አለ። (ራእይ 21:3) በሞት ስላንቀላፉ የአምላክ ታማኝ አገልጋዮችስ ምን ማለት ይቻላል? አሁንም በይሖዋ ድንኳን ውስጥ እንግዶች ናቸው ብሎ መደምደም ምክንያታዊ ነው? በሚገባ! እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም እነዚህን ሰዎች ይሖዋ ስለማይረሳቸው በእሱ ዘንድ ሕያው ናቸው። ኢየሱስ ሁኔታውን ሲያብራራ እንዲህ ብሏል፦ “ሙሴም እንኳ ስለ ቁጥቋጦው በሚገልጸው ታሪክ ላይ ይሖዋን ‘የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅ አምላክና የያዕቆብ አምላክ’ ብሎ በጠራው ጊዜ ሙታን እንደሚነሡ አስታውቋል። እሱ የሕያዋን እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም፤ በእሱ ፊት ሁሉም ሕያዋን ናቸውና።”—ሉቃስ 20:37, 38፤ w24.06 3-4 አን. 6-7

ማክሰኞ፣ መጋቢት 3

ይሖዋ ብርታቴና ጋሻዬ ነው።—መዝ. 28:7

ሳዶቅ ወደ ኬብሮን የሄደው መሣሪያ ታጥቆና ለጦርነት ተዘጋጅቶ ነው። (1 ዜና 12:38) ዳዊትን ተከትሎ ለመዋጋትና እስራኤልን ከጠላቶቹ ለመታደግ ፈቃደኛ ነበር። ሳዶቅ የውጊያ ተሞክሮ ሊጎድለው ቢችልም አስደናቂ ድፍረት ነበረው። ሳዶቅ ካህን ከመሆኑ አንጻር እንዲህ ያለ አስደናቂ ድፍረት ሊኖረው የቻለው እንዴት ነው? በዙሪያው የነበሩት ሰዎች ጠንካራና ደፋር ነበሩ። ከእነሱ ምሳሌ እንደተጠቀመ ምንም ጥያቄ የለውም። ለምሳሌ ዳዊት “እስራኤል ወደ ጦርነት ሲወጣ” በድፍረት ሕዝቡን በመምራት ረገድ የተወው ምሳሌ ሁሉም እስራኤላውያን በሙሉ ልባቸው እንዲደግፉት አነሳስቷቸዋል። (1 ዜና 11:1, 2) ዳዊት ምንጊዜም ጠላቶቹን ለማሸነፍ የይሖዋን እርዳታ በመጠየቅ በእሱ ይታመን ነበር። (መዝ. 138:3) ሳዶቅ ሌሎች ግሩም ምሳሌዎችም ነበሩት፤ ከእነዚህ መካከል ዮዳሄና ተዋጊ የነበረው ልጁ በናያህ እንዲሁም ከዳዊት ጎን የቆሙት 22 አለቆች ይገኙበታል።—1 ዜና 11:22-25፤ 12:26-28፤ w24.07 3 አን. 5-6

ረቡዕ፣ መጋቢት 4

አምላክ በደግነቱ ወደ ንስሐ ሊመራህ እየሞከረ [ነው]።—ሮም 2:4

የጠርሴሱ ሳኦል የክርስቶስን ውድ ተከታዮች ክፉኛ ያሳድድ ነበር። አብዛኞቹ ክርስቲያኖች፣ ሳኦል ንስሐ ሊገባ እንደማይችል አስበው መሆን አለበት። ይሁንና የኢየሱስ አመለካከት እንዲህ ካለው የተሳሳተ ሰብዓዊ አስተሳሰብ በእጅጉ የላቀ ነው። እሱና አባቱ፣ ሳኦል መልካም ባሕርያት እንዳሉት ተመልክተዋል። ኢየሱስ ‘ይህ ሰው ለእኔ የተመረጠ ዕቃ ነው’ ብሏል። (ሥራ 9:15) እንዲያውም ኢየሱስ ሳኦልን ወደ ንስሐ ለመምራት ሲል ተአምር ፈጽሟል። (ሥራ 7:58–8:3፤ 9:1-9, 17-20) ሳኦል ክርስቲያን ከሆነና ሐዋርያው ጳውሎስ ተብሎ መጠራት ከጀመረ በኋላ፣ ለተደረገለት ደግነትና ምሕረት አመስጋኝነቱን በተደጋጋሚ ገልጿል። (1 ጢሞ. 1:12-15) ጳውሎስ በቆሮንቶስ በሚገኘው የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የፆታ ብልግና እንደተፈጸመ ሲሰማ ጉዳዩን የያዘው እንዴት ነው? ጉዳዩን የያዘበት መንገድ ስለ ይሖዋ ፍቅራዊ ተግሣጽ እንዲሁም ምሕረት ማሳየት ስላለው አስፈላጊነት ብዙ ትምህርት ይሰጠናል። w24.08 13 አን. 15-16

ሐሙስ፣ መጋቢት 5

የአምላክ ልጅ የተገለጠው የዲያብሎስን ሥራ ለማፍረስ ነው።—1 ዮሐ. 3:8

ላለፉት መቶ ዘመናት ይሖዋ ኃጢአተኛ የሆኑ የሰው ልጆች ወደ እሱ መቅረብ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ደረጃ በደረጃ ግልጽ አድርጓል። በኤደን ዓመፅ ከተቀሰቀሰ በኋላ በይሖዋ ላይ እምነት የጣለው የመጀመሪያው ሰው የአዳምና የሔዋን ሁለተኛ ልጅ የሆነው አቤል ነው። አቤል ይሖዋን ስለሚወደው እንዲሁም እሱን ማስደሰትና ወደ እሱ መቅረብ ስለሚፈልግ መሥዋዕት አቀረበ። አቤል እረኛ ስለነበር ከጠቦቶቹ የተወሰኑትን አርዶ ለይሖዋ አቀረበ። በዚህ ጊዜ ይሖዋ ምን ተሰማው? “አቤልንና ያቀረበውን መባ በጥሩ ፊት [ተመለከተ]።” (ዘፍ. 4:4) ይሖዋ እሱን የሚወዱና በእሱ የሚታመኑ ሰዎች ያቀረቧቸውን ሌሎች መሥዋዕቶችም በሞገስ ዓይን ተመልክቷል፤ ለምሳሌ ኖኅ ያቀረበውን መሥዋዕት ተቀብሏል። (ዘፍ. 8:20, 21) ይሖዋ እንዲህ ያሉ መሥዋዕቶችን በመቀበል ኃጢአተኛ የሆኑ የሰው ልጆች የእሱን ሞገስ ማግኘትና ወደ እሱ መቅረብ እንደሚችሉ አሳይቷል። w24.08 3 አን. 5-6

ዓርብ፣ መጋቢት 6

እግሮቼ ከመንገድ ሊወጡ ተቃርበው ነበር፤ አዳልጦኝ ልወድቅ ምንም አልቀረኝም።—መዝ. 73:2

የፍትሕ መጓደል ሲያጋጥመን ስሜታችን በጥልቅ ሊጎዳና ልናዝን እንችላለን። (መክ. 7:7) እንደ ኢዮብና ዕንባቆም ያሉ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮችም እንደዚህ ተሰምቷቸው ነበር። (ኢዮብ 6:2, 3፤ ዕን. 1:1-3) እንዲህ ዓይነት ስሜት የሚሰማን መሆኑ የሚጠበቅ ነገር ቢሆንም የምንሰጠውን ምላሽ በተመለከተ ልንጠነቀቅ ይገባል፤ አለዚያ የሞኝነት ድርጊት ልንፈጽምና ሁኔታውን ልናባብሰው እንችላለን። ኢፍትሐዊ ድርጊት የሚፈጽሙ ሰዎች ለድርጊታቸው ምንም ቅጣት እንዳልተቀበሉ ሲሰማን ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ ጥቅም ያለው መሆኑን ልንጠራጠር እንችላለን። መዝሙራዊው፣ ክፉዎች ጻድቃንን ቢበድሉም እንኳ በሕይወታቸው ስኬታማ እንደሆኑ ተሰምቶት ነበር። “ክፉዎች እንደዚህ ናቸው፤ ሁልጊዜ ሳይጨናነቁ ይኖራሉ” ብሏል። (መዝ. 73:12) በተጨማሪም በዙሪያው የሚያየው የፍትሕ መጓደል በጣም ስላሳዘነው ይሖዋን ማገልገል ጥቅም ያለው መሆኑን መጠራጠር ጀምሮ ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “ይህን ለመረዳት በሞከርኩ ጊዜ፣ የሚያስጨንቅ ሆነብኝ።”—መዝ. 73:14, 16፤ w24.11 3 አን. 5-7

ቅዳሜ፣ መጋቢት 7

እናንተ የሕዝብ ነገዶች፣ ለይሖዋ የሚገባውን ስጡ፤ ከክብሩና ከብርታቱ የተነሳ ለይሖዋ የሚገባውን ስጡ።—መዝ. 96:7

ለይሖዋ ክብር የምንሰጠው አክብሮት ስለሚገባው ነው። ይሖዋ ሁሉን ቻይ ነው፤ ኃይሉ ገደብ የለውም። (መዝ. 96:4-7) ጥበቡ ጥልቅ መሆኑ ከፈጠራቸው ነገሮች በግልጽ ይታያል። ሕይወትንም ሆነ ለመኖር የሚያስፈልጉንን ነገሮች በሙሉ የሰጠን እሱ ነው። (ራእይ 4:11) ታማኝ ነው። (ራእይ 15:4) የሚያከናውነው ነገር ሁሉ ይሳካል፤ ቃሉንም ሁልጊዜ ይጠብቃል። (ኢያሱ 23:14) ነቢዩ ኤርምያስ ስለ ይሖዋ እንዲህ ማለቱ የሚያስገርም አይደለም፦ “ከብሔራት ጠቢባን ሁሉ እንዲሁም ከመንግሥቶቻቸው ሁሉ መካከል እንደ አንተ ያለ ማንም የለም።” (ኤር. 10:6, 7) በእርግጥም ለሰማያዊ አባታችን ክብር ለመስጠት የሚያነሳሱን አጥጋቢ ምክንያቶች አሉን። ሆኖም ይሖዋን ማክበር ብቻ ሳይሆን በጣም እንወደዋለን። ለይሖዋ ክብር የምንሰጥበት ዋነኛው ምክንያት ከልባችን ስለምንወደው ነው። w25.01 3 አን. 5-6

እሁድ፣ መጋቢት 8

ክፉውን ሰው ከመካከላችሁ አስወግዱት።—1 ቆሮ. 5:13

የአምላክ ጠላቶች የድርጅቱን መልካም ገጽታዎች መጥፎ አስመስለው ለማቅረብ ይሞክራሉ። ለምሳሌ ይሖዋ አገልጋዮቹ አካላዊ፣ ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ ንጽሕናቸውን እንዲጠብቁ እንደሚፈልግ ከቅዱሳን መጻሕፍት ተምረናል። የኃጢአት ጎዳና የሚከተሉና ንስሐ የማይገቡ ሁሉ ከጉባኤው እንዲወገዱ መመሪያ ሰጥቷል። (1 ቆሮ. 5:11, 12፤ 6:9, 10) ይህን ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያ በጥብቅ እንከተላለን። እንዲህ ስናደርግ ግን ተቃዋሚዎቻችን የሌሎችን ምርጫ እንደማናከብር፣ በሌሎች ላይ እንደምንፈርድና ፍቅር እንደሌለን በመግለጽ ይከሱናል። የእነዚህን ጥቃቶች ምንጭ መለየት ይኖርብናል። ከሐሰት ወሬዎች በስተ ጀርባ ያለው ሰይጣን ዲያብሎስ ነው። እሱ “የውሸት አባት” ነው። (ዮሐ. 8:44፤ ዘፍ. 3:1-5) በመሆኑም ሰይጣን ደጋፊዎቹን በመጠቀም ስለ ይሖዋ ድርጅት የሐሰት ወሬዎችን እንደሚያናፍስ መጠበቅ ይኖርብናል። w24.04 10-11 አን. 13-14

ሰኞ፣ መጋቢት 9

ይፈጸማል።—ሕዝ. 33:33

ታላቁ መከራ ከጀመረ በኋላም እንኳ፣ ‘የታላቂቱ ባቢሎንን’ ጥፋት ያዩ አንዳንድ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች ከረጅም ጊዜ በፊት ስለዚህ ክንውን ይናገሩ እንደነበር ያስታውሱ ይሆናል። እነዚህን ክንውኖች የሚያዩ አንዳንድ ሰዎች አቋማቸውን ያስተካክሉ ይሆን? (ራእይ 17:5) እንዲህ ከሆነ፣ በሙሴ ዘመን በግብፅ ከተፈጠረው ነገር ጋር የሚመሳሰል ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። በወቅቱ ከእስራኤላውያን ጋር አብሮ የወጣ “እጅግ ብዙ ድብልቅ ሕዝብ” እንደነበር አስታውስ። ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ፣ ሙሴ ስለ አሥሩ መቅሰፍቶች የተናገረው ማስጠንቀቂያ መፈጸሙን ሲያዩ እምነት ማዳበር ጀምረው ሊሆን ይችላል። (ዘፀ. 12:38) የታላቂቱን ባቢሎን ጥፋት ተከትሎ እንዲህ ያለ ሁኔታ ካጋጠመ፣ መጨረሻው ልክ ሊደርስ ሲል ከእኛ ጋር የተቀላቀሉ ሰዎች በመኖራቸው እናዝናለን? በፍጹም! “መሐሪና ሩኅሩኅ . . . ለቁጣ የዘገየ፣ ታማኝ ፍቅሩና እውነቱ እጅግ ብዙ የሆነ” አምላክ የሆነውን የሰማዩን አባታችንን መምሰል እንፈልጋለን።—ዘፀ. 34:6፤ w24.05 11 አን. 12-13

ማክሰኞ፣ መጋቢት 10

[የትክክለኛውን] ትምህርት መሥፈርት . . . አጥብቀህ ያዝ።—2 ጢሞ. 1:13

‘የትክክለኛውን ትምህርት መሥፈርት’ አጥብቀን ባንከተል ምን ሊከሰት ይችላል? አንድ ምሳሌ እንመልከት። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች መካከል ‘የይሖዋ ቀን ደርሷል’ የሚል ወሬ መዛመት ጀምሮ የነበረ ይመስላል። እንዲህ ዓይነት ሐሳብ የያዘ በሐዋርያው ጳውሎስ የተጻፈ የሚመስል ደብዳቤ ደርሷቸው ሊሆን ይችላል። አንዳንድ የተሰሎንቄ ክርስቲያኖች ጊዜ ወስደው እውነታውን ሳያጣሩ ወሬውን ያመኑ ከመሆኑም በተጨማሪ ለሌሎች አሰራጭተውት ነበር። ጳውሎስ ከእነሱ ጋር በነበረበት ጊዜ ያስተማራቸውን ነገር ቢያስታውሱ ኖሮ እንዲህ ባለው ወሬ ባልተታለሉ ነበር። (2 ተሰ. 2:1-5) ጳውሎስ ወንድሞቹን የሰሙትን ሁሉ እንዳያምኑ መክሯቸዋል። ጳውሎስ የተሰሎንቄ ክርስቲያኖች በድጋሚ ለስህተት እንዳይጋለጡ ሲል ሁለተኛውን ደብዳቤውን የደመደመው እንዲህ በማለት ነው፦ “እኔ ጳውሎስ በገዛ እጄ የጻፍኩላችሁ ሰላምታ ይድረሳችሁ፤ ይህ የእጅ ጽሑፍ የደብዳቤዎቼ ሁሉ መለያ ነው፤ አጻጻፌ እንዲህ ነው።”—2 ተሰ. 3:17፤ w24.07 12 አን. 13-14

ረቡዕ፣ መጋቢት 11

መጽናት ያስፈልጋችኋል።—ዕብ. 10:36

በይሁዳ ያለው ሁኔታ እየተባባሰ ሲሄድ ዕብራውያን ክርስቲያኖች የእምነት ፈተናዎችን ለመቋቋም ጽናት ያስፈልጋቸዋል። አንዳንድ ዕብራውያን ክርስቲያኖች ከባድ ስደት ያሳለፉ ቢሆንም ብዙዎቹ ክርስትናን የተቀበሉት አንጻራዊ ሰላም በነበረበት ጊዜ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ እነዚህ ክርስቲያኖች ከባድ የእምነት ፈተናዎችን በጽናት የተቋቋሙ ቢሆንም የኢየሱስን ያህል ማለትም እስከ ሞት ድረስ እንዳልተፈተኑ ገልጿል። (ዕብ. 12:4) ሆኖም ክርስትና እየተስፋፋ ሲሄድ አይሁዳውያን ተቃዋሚዎች ጥላቻቸውና ጽንፈኝነታቸው እየጨመረ መጣ። ጳውሎስ ደብዳቤውን ከመጻፉ ከጥቂት ዓመታት በፊት ከ40 የሚበልጡ አይሁዳውያን ጳውሎስን “እስኪገድሉ ድረስ እህል ውኃ ላለመቅመስ” ተማምለው ነበር። (ሥራ 22:22፤ 23:12-14) እነዚህ ክርስቲያኖች እንዲህ ያለ ሃይማኖታዊ ጥላቻና ጽንፈኝነት በሰፈነበት አካባቢ ለአምልኮ መሰብሰብ፣ ምሥራቹን መስበክ እንዲሁም እምነታቸውን ጠብቀው መኖር ይጠበቅባቸዋል። w24.09 11 አን. 15

ሐሙስ፣ መጋቢት 12

ኢየሱስ እናቱን . . . “አንቺ ሴት፣ ልጅሽ ይኸውልሽ!” አላት።—ዮሐ. 19:26

ዮሐንስ ኢየሱስ የሚወደው ሐዋርያ ነበር። (ማቴ. 10:2) ዮሐንስ፣ ኢየሱስ አገልግሎቱን ባከናወነበት ወቅት አብሮት ተጉዟል፤ የፈጸማቸውን ተአምራት ተመልክቷል፤ እንዲሁም በአስቸጋሪ ወቅት ለእሱ ታማኝ ሆኖ ቀጥሏል። ኢየሱስ ሲሰቀል ተመልክቷል፤ ከሞት ከተነሳ በኋላም አግኝቶታል። በተጨማሪም በመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስትና ሲስፋፋ አይቷል፤ ጥቂት ታማኝ ሰዎችን ያቀፈ ቡድን ከመሆን ተነስቶ “[ምሥራቹ] ከሰማይ በታች ላለ ፍጥረት ሁሉ ተሰብኳል” የሚባልበት ደረጃ ላይ እስኪደርስ ድረስ ለማየት በቅቷል። (ቆላ. 1:23) ዮሐንስ በረጅም የሕይወት ዘመኑ ማብቂያ አካባቢ በመንፈስ መሪነት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን የመጻፍ መብት አግኝቷል። ‘ኢየሱስ ክርስቶስ የገለጠለትን’ አስደናቂ ራእይ ዘግቧል። (ራእይ 1:1) ዮሐንስ በስሙ የተጠራውን ወንጌል ጽፏል። በተጨማሪም በመንፈስ መሪነት ሦስት ደብዳቤዎችን ጽፏል። ዮሐንስ ሦስተኛውን ደብዳቤ የጻፈው ጋይዮስ ለተባለ ታማኝ ክርስቲያን ነው፤ ዮሐንስ ጋይዮስን እንደ መንፈሳዊ ልጁ አድርጎ ይመለከተው ነበር። (3 ዮሐ. 1) ይህ ታማኝ አረጋዊ የጻፈው ደብዳቤ እስከ ዘመናችን ድረስ ሁሉንም የኢየሱስ ተከታዮች እያበረታታ ነው። w24.11 12 አን. 15-16

ዓርብ፣ መጋቢት 13

እናንተ ባሎች . . . አክብሯቸው።—1 ጴጥ. 3:7

ሚስቱን የሚወድ ባል ትልቅ ቦታ ይሰጣታል፤ እንዲሁም ይሳሳላታል። ከይሖዋ ያገኛት ውድ ስጦታ እንደሆነች አድርጎ ይመለከታታል። (ምሳሌ 18:22፤ 31:10) ከፆታ ግንኙነት ጋር በተያያዙ ጉዳዮችም ጭምር በደግነትና በአክብሮት ይይዛታል። የማትፈልገውን፣ እንደሚያዋርዳት የሚሰማትን ወይም ሕሊናዋ የማይፈቅድላትን ፆታዊ ተግባር እንድትፈጽም አይጠይቃትም። እሱም ራሱ ቢሆን በይሖዋ ፊት ንጹሕ ሕሊና ይዞ ለመኖር ጥረት ያደርጋል። (ሥራ 24:16) ባሎች፣ በሁሉም የሕይወታችሁ ክፍሎች ሚስታችሁን በአክብሮት ለመያዝ የምታደርጉትን ጥረት ይሖዋ እንደሚመለከትና እንደሚያደንቅ እርግጠኞች መሆን ትችላላችሁ። አክብሮት ከጎደለው ድርጊት በመራቅ እንዲሁም ለሚስታችሁ ደግነትና ፍቅር በማሳየት እሷን በአክብሮት ለመያዝ ቁርጥ ውሳኔ አድርጉ። እንዲህ ካደረጋችሁ ሚስታችሁን እንደምትወዷትና ከፍ አድርጋችሁ እንደምትመለከቷት ታሳያላችሁ። ሚስታችሁን በአክብሮት በመያዝ ከምንም ይበልጥ ትልቅ ዋጋ ያለውን ከይሖዋ ጋር ያላችሁን ዝምድና ከአደጋ መጠበቅ ትችላላችሁ።—መዝ. 25:14፤ w25.01 13 አን. 17-18

ቅዳሜ፣ መጋቢት 14

ክርስቶስ . . . እኛን ነፃ ለማውጣትና ለመልካም ሥራ የሚቀና ልዩ ንብረቱ የሆነ ሕዝብ ለራሱ ለማንጻት ሕይወቱን ለእኛ ሰጥቷል።—ቲቶ 2:14

የይሖዋ አገልጋዮችን ከአስመሳይ ክርስቲያኖች የሚለያቸው አንዱ ነገር ለአገልግሎት ያላቸው ቅንዓት ነው። ታዲያ የስብከቱን ሥራ በቅንዓት ማከናወናችንን ለመቀጠል ብሎም ቅንዓታችንን ለመጨመር ምን ሊረዳን ይችላል? የኢየሱስን ምሳሌ መመርመራችን በቅንዓት እንድንሰብክ የሚረዳ ቁም ነገር ያስተምረናል። ኢየሱስ አገልግሎቱን ባከናወነበት ጊዜ ሁሉ ቅንዓቱ አልበረደም። እንዲያውም ጊዜ እያለፈ ሲሄድ የአገልግሎት እንቅስቃሴውን ጨምሯል። ኢየሱስ በምሳሌው ላይ የጠቀሰው የወይን አትክልት ሠራተኛ አንዲትን የበለስ ዛፍ ለመንከባከብ ሦስት ዓመት ቢደክምም ፍሬ አላገኘም፤ ኢየሱስም እንዲሁ ለአይሁዳውያን ሦስት ዓመት ያህል ቢሰብክም አብዛኞቹ ጥሩ ምላሽ አልሰጡም። ይሁንና የወይን አትክልት ሠራተኛው በበለስ ዛፏ ተስፋ እንዳልቆረጠ ሁሉ ኢየሱስም በሕዝቡ ተስፋ አልቆረጠም፤ የአገልግሎት እንቅስቃሴውንም አልቀነሰም። (ሉቃስ 13:6-9) ያስተማረውን ነገር ተግባራዊ ማድረጋችንና ፈለጉን መከተላችን በዛሬው ጊዜ ቅንዓታችንን ጠብቀን ለመቀጠል ይረዳናል። w25.03 14-15 አን. 1-4

እሁድ፣ መጋቢት 15

ብልህ ሰው ተግባሩን በእውቀት ያከናውናል።—ምሳሌ 13:16

አንዲት እህት ተስማሚ የትዳር ጓደኛ ልትሆንህ እንደምትችል ከተሰማህስ? ስሜትህን ወዲያውኑ ልትነግራት ይገባል? መጽሐፍ ቅዱስ፣ ጥበበኛ ሰው እርምጃ ከመውሰዱ በፊት እውቀት ለማግኘት ጥረት እንደሚያደርግ ይናገራል። ስለዚህ ስሜትህን ለእሷ ከመንገርህ በፊት ለተወሰነ ጊዜ ያህል ከርቀት ብትመለከታት የተሻለ ነው። ለትዳር የምታስባትን እህት ከርቀት መመልከት የምትችለው እንዴት ነው? በጉባኤ ስብሰባዎች ወይም በማኅበራዊ ግብዣዎች ላይ ስለ መንፈሳዊነቷ፣ ስለ ባሕርይዋ እና ስለ ምግባሯ የሚጠቁሙ ነገሮችን ትመለከት ይሆናል። ጓደኞቿ እነማን ናቸው? ስለ ምን ጉዳይ ማውራት ትወዳለች? (ሉቃስ 6:45) ግባችሁ ተመሳሳይ ነው? የጉባኤ ሽማግሌዎቿን ወይም እሷን በደንብ የሚያውቁ የጎለመሱ ክርስቲያኖችን ማነጋገር ትችል ይሆናል። (ምሳሌ 20:18) ስላተረፈችው ስምና ስለ ባሕርያቷ መጠየቅ ትችላለህ። (ሩት 2:11) ሆኖም እህትን በምትመለከትበት ጊዜ ምቾቷን የሚነሳ ነገር አታድርግ። ለስሜቷ አክብሮት ይኑርህ፤ እንዲሁም እሷ ባለችበት ሁሉ ለመገኘት ወይም ስለ እሷ ሁሉንም ነገር ለማወቅ ጥረት አታድርግ። w24.05 22 አን. 7-8

ሰኞ፣ መጋቢት 16

በመጨረሻ ኃጢአቴን ለአንተ ተናዘዝኩ።—መዝ. 32:5

ሽማግሌዎች ጥፋት የሠራ አንድ ግለሰብ ንስሐ አይገባም ብለው ለመደምደም አይቸኩሉም። አንዳንዶች ኮሚቴው ለመጀመሪያ ጊዜ ሲያነጋግራቸው ንስሐ ሊገቡ ይችላሉ፤ ሌሎች ግን ተጨማሪ ጊዜ ሊያስፈልጋቸው ይችላል። በመሆኑም ሽማግሌዎች ኃጢአተኛውን ከአንድ ጊዜ በላይ ለማነጋገር ዝግጅት ሊያደርጉ ይችላሉ። ኃጢአተኛው ከኮሚቴው ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ከተነጋገረ በኋላ የተባለውን ነገር አስመልክቶ በቁም ነገር ማሰብ ሊጀምር ይችላል። በትሕትና ወደ ይሖዋ ሊጸልይ ይችላል። (መዝ. 38:18) በዚህም የተነሳ በቀጣዩ ጊዜ ሲያነጋግሩት በመጀመሪያው ውይይታቸው ወቅት ካሳየው የተለየ መንፈስ ሊያሳይ ይችላል። ሽማግሌዎች ኃጢአተኛውን ወደ ንስሐ ለመምራት ጥረት በሚያደርጉበት ጊዜ ስሜቱን ይረዱለታል፤ ደግነትም ያሳዩታል። ይሖዋ ጥረታቸውን እንዲባርክላቸው ይጸልያሉ፤ እንዲሁም ኃጢአተኛው ክርስቲያን ወደ ልቦናው እንደሚመለስና ንስሐ እንደሚገባ ተስፋ ያደርጋሉ።—2 ጢሞ. 2:25, 26፤ w24.08 22-23 አን. 12-13

ማክሰኞ፣ መጋቢት 17

“እኔ በማንም ሰው ሞት ደስ አልሰኝም” ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ። “ስለዚህ ተመለሱና በሕይወት ኑሩ።”—ሕዝ. 18:32

ይሖዋ ማንም ሰው እንዲጠፋ አይፈልግም! ኃጢአተኞች ከእሱ ጋር እንዲታረቁ ይፈልጋል። (2 ቆሮ. 5:20) በታሪክ ዘመናት ሁሉ ይሖዋ ዓመፀኛ ሕዝቦቹንና ዓመፀኛ ግለሰቦችን ንስሐ እንዲገቡና ወደ እሱ እንዲመለሱ በተደጋጋሚ ሲያሳስብ የኖረው ለዚህ ነው። የጉባኤ ሽማግሌዎች፣ ኃጢአተኞች ንስሐ እንዲገቡ በመርዳት ከይሖዋ ጋር የመሥራት ትልቅ መብት አግኝተዋል። (ሮም 2:4፤ 1 ቆሮ. 3:9) ኃጢአተኞች ንስሐ ሲገቡ በሰማይ ምን ያህል ደስታ እንደሚኖር ለማሰብ ሞክር። አንድ የጠፋ በግ ወደ ጉባኤ በተመለሰ ቁጥር የሰማዩ አባታችን ይሖዋ ታላቅ ደስታ ይሰማዋል። በይሖዋ ርኅራኄ፣ ምሕረትና ጸጋ ላይ ባሰላሰልን ቁጥር ለእሱ ያለን ፍቅር እያደገ ይሄዳል።—ሉቃስ 1:78፤ w24.08 31 አን. 16-17

ረቡዕ፣ መጋቢት 18

ኢየሱስ ሰዎቹ መጥተው ሊይዙትና ሊያነግሡት እንዳሰቡ ስላወቀ ብቻውን ዳግመኛ ወደ ተራራ ገለል አለ።—ዮሐ. 6:15

ኢየሱስ ሕዝቡ እንዲያነግሡት ቢፈቅድላቸው ኖሮ በሮም አገዛዝ ሥር በነበሩት አይሁዳውያን ፖለቲካ ውስጥ እጁን ማስገባት ይሆንበት ነበር። ኢየሱስ ወዲያውኑ ‘ወደ ተራራ ገለል ብሏል።’ ስለዚህ ኢየሱስ ሌሎች ጫና ቢያሳድሩበትም በፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ ለመግባት ፈቃደኛ አልሆነም። እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል! መቼም ሰዎች በተአምር እንድንመግባቸው፣ የታመሙትን እንድንፈውስ አሊያም ደግሞ ንጉሥ ወይም የአገር መሪ እንድንሆን ይጠይቁናል ብለን አናስብም። ሆኖም ነገሮችን ያሻሽላል ብለው የሚያስቡትን ሰው በመደገፍ ወይም ለእሱ ድምፅ በመስጠት በፖለቲካዊ ጉዳዮች እጃችንን እንድናስገባ ይገፋፉን ይሆናል። ነገር ግን ኢየሱስ የተወው ምሳሌ የሚያሻማ አይደለም። በፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ ለመግባት ፈቃደኛ አልሆነም። እንዲያውም ከጊዜ በኋላ “መንግሥቴ የዚህ ዓለም ክፍል አይደለም” ብሏል። (ዮሐ. 17:14፤ 18:36) በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖችም የኢየሱስን አስተሳሰብና ምግባር መኮረጃቸው ተገቢ ነው። መንግሥቱን እንደግፋለን፤ ስለ መንግሥቱ እንሰብካለን፤ እንዲሁም መንግሥቱ እንዲመጣ እንጸልያለን።—ማቴ. 6:10፤ w24.12 4 አን. 5-6

ሐሙስ፣ መጋቢት 19

እኔን የሚወደኝ ትእዛዛቴን የሚቀበልና የሚጠብቅ ነው። እኔን የሚወደኝን ሁሉ ደግሞ አባቴ ይወደዋል፤ እኔም እወደዋለሁ፤ ራሴንም እገልጥለታለሁ።—ዮሐ. 14:21

በምታጠናበት ጊዜ ያገኘኸውን ትምህርት በሥራ ላይ ማዋል የምትችልበትን መንገድ አስብ። ለምሳሌ ሌሎችን ከአድልዎ ነፃ በሆነ መንገድ በመያዝ የይሖዋን ፍትሕ ለመኮረጅ ሞክር። ለይሖዋ ስም ስትል መከራ ለመቀበል ፈቃደኛ በመሆንና ራስህን ሳትቆጥብ ወንድሞችህን በማገልገል ኢየሱስ ለአባቱና ለሌሎች ያሳየውን ፍቅር ኮርጅ። በተጨማሪም ለሌሎች በመመሥከር የኢየሱስን ምሳሌ ተከተል፤ እንዲህ ካደረግክ እነሱም የይሖዋን ውድ ስጦታ መቀበል የሚችሉበት አጋጣሚ ይከፈትላቸዋል። ስለ ቤዛው ይበልጥ በተማርንና አድናቆታችንን ባሳደግን መጠን ለይሖዋና ለልጁ ያለን ፍቅር ይጨምራል። እነሱም በምላሹ እኛን ይበልጥ ይወዱናል። (ያዕ. 4:8) እንግዲያው ይሖዋ ያደረገልንን ዝግጅቶች በመጠቀም ስለ ቤዛው መማራችንን እንቀጥል። w25.01 25 አን. 16-17

ዓርብ፣ መጋቢት 20

ኃጢአቴን ሁሉ ወደ ኋላህ ጣልክ።—ኢሳ. 38:17

የዛሬው የዕለት ጥቅስ “ኃጢአቴን ሁሉ ከእይታህ አስወገድክ” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። ይህ ዘይቤያዊ አገላለጽ፣ ይሖዋ ንስሐ የገቡ ሰዎችን ኃጢአት አንስቶ ከእይታ አርቆ እንደሚጥለው ያመለክታል። ይህ አገላለጽ “[ኃጢአቴን] ያልነበረ ያህል አደረግከው” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ በሚክያስ 7:18, 19 ላይ ይህን ነጥብ ይበልጥ የሚያጎላ ሌላ ዘይቤያዊ አገላለጽ ይጠቀማል። ጥቅሱ፣ ይሖዋ ኃጢአታችንን ወደ ጥልቅ ባሕር እንደሚጥለው ይናገራል። በጥንት ዘመን፣ ወደ ጥልቅ ባሕር የተጣለን ነገር መልሶ ማግኘት የሚቻልበት ምንም ዓይነት መንገድ አልነበረም። ከእነዚህ ዘይቤያዊ አገላለጾች እንደተማርነው ይሖዋ ይቅር ሲለን ከኃጢአት ሸክም ይገላግለናል። በእርግጥም ዳዊት እንደተናገረው “የዓመፅ ሥራቸው ይቅር የተባለላቸው፣ ኃጢአታቸውም የተሸፈነላቸው ደስተኞች ናቸው።” (ሮም 4:7) እውነተኛ ይቅርታ ማለት ይህ ነው! w25.02 9 አን. 7-8

ቅዳሜ፣ መጋቢት 21

በምፈጥረው ነገር ለዘላለም ደስ ይበላችሁ፤ ሐሴትም አድርጉ።—ኢሳ. 65:18

በዛሬው ጊዜ መልካም ሥራ በመሥራት የተጠመዱ ብዙ ሰዎችን ያቀፈ ምሳሌያዊ ቦታ አለ። ይህ ምሳሌያዊ ቦታ እውነተኛ ሰላም በሚያጣጥሙ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች የተሞላ ነው። በዚህ ቦታ ውስጥ ያሉት ሰዎች ከዚህ ቦታ ፈጽሞ ላለመውጣት ቁርጥ ውሳኔ አድርገዋል። ሌሎች ብዙ ሰዎችም በዚህ ቦታ አብረዋቸው እንዲኖሩ ይፈልጋሉ። ይህ ቦታ ምንድን ነው? መንፈሳዊው ገነት ነው! ሰይጣን በጥላቻ፣ በክፋትና በአደገኛ ሁኔታዎች በሞላው በዚህ ዓለም ውስጥ ይሖዋ እንዲህ ያለ ሰላማዊ ሁኔታ መፍጠሩ በእርግጥም የሚያስደንቅ ነው። (1 ዮሐ. 5:19፤ ራእይ 12:12) አፍቃሪ የሆነው አምላካችን ይህ ሥርዓት ሊያደርስብን የሚችለውን ጉዳት ስለሚያውቅ በመንፈሳዊ ለማበብ የሚያስችለን ደህንነቱ የተጠበቀ ሁኔታ አመቻችቶልናል። የአምላክ ቃል መንፈሳዊውን ገነት እንደ አስተማማኝ “መጠጊያ” እና “ውኃ እንደሚጠግብ የአትክልት ቦታ” አድርጎ ገልጾታል። (ኢሳ. 4:6፤ 58:11) በዚህ ገነት ውስጥ የሚኖሩት ሰዎች የይሖዋ በረከት ስላልተለያቸው በእነዚህ አስቸጋሪ የመጨረሻ ቀናትም አስደሳችና የተረጋጋ ሕይወት መምራት ችለዋል።—ኢሳ. 54:14፤ 2 ጢሞ. 3:1፤ w24.04 20 አን. 1-2

እሁድ፣ መጋቢት 22

ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ።—ፊልጵ. 4:6

ማግባት የምትፈልግ ከሆነ፣ የትዳር ጓደኛ ለማግኘት እንዲረዳህ ወደ ይሖዋ ጸልየህ እንደሚሆን ጥያቄ የለውም። እርግጥ ነው፣ ይሖዋ ለማንም ሰው የትዳር አጋር እንደሚሰጥ ቃል አልገባም። ያም ቢሆን የሚያስፈልግህ ነገርና ስሜትህ ያሳስበዋል፤ እንዲሁም የትዳር ጓደኛ ለማግኘት በምታደርገው ጥረት ሊረዳህ ይችላል። ስለዚህ ፍላጎትህንና ስሜትህን ለእሱ መንገርህን ቀጥል። (መዝ. 62:8) ትዕግሥትና ጥበብ እንዲሰጥህ ጸልይ። (ያዕ. 1:5) ተስማሚ የትዳር ጓደኛ ወዲያውኑ ባታገኝም እንኳ ይሖዋ አካላዊና ስሜታዊ ፍላጎቶችህን ማሟላቱን እንደሚቀጥል ቃል ገብቶልሃል። (መዝ. 55:22) ሆኖም አንድ መጠንቀቅ ያለብህ ነገር አለ፤ የትዳር ጓደኛ ለማግኘት የምታደርገው ጥረት ሕይወትህን እንዲቆጣጠረው አትፍቀድ። (ፊልጵ. 1:10) እውነተኛ ደስታ ማግኘትህ የተመካው በማግባትህ ወይም ባለማግባትህ ላይ ሳይሆን ከይሖዋ ጋር ባለህ ዝምድና ላይ ነው። (ማቴ. 5:3) ደግሞም ነጠላ መሆንህ አገልግሎትህን ለማስፋት የሚያስችል ተጨማሪ ነፃነት ሊሰጥህ ይችላል። (1 ቆሮ. 7:32, 33) ይህን ጊዜ ጥሩ አድርገህ ተጠቀምበት። w24.05 21 አን. 4፤ 22 አን. 6

ሰኞ፣ መጋቢት 23

ስለ ራሳችሁ ፍላጎት ብቻ ከማሰብ ይልቅ እያንዳንዳችሁ ለሌሎች ሰዎች ፍላጎትም ትኩረት ስጡ።—ፊልጵ. 2:4

ለምን ያህል ጊዜ እየተጠናናችሁ ልትቆዩ ይገባል? የችኮላ ውሳኔ ማድረግ ብዙውን ጊዜ አስከፊ መዘዝ ያስከትላል። (ምሳሌ 21:5) ስለዚህ በደንብ እስክትተዋወቁ ድረስ እየተጠናናችሁ ልትቆዩ ይገባል። ሆኖም የምትጠናኑበትን ጊዜ ሳያስፈልግ ማራዘም አይኖርባችሁም። መጽሐፍ ቅዱስም “የዘገየ ተስፋ ልብን ያሳምማል” ይላል። (ምሳሌ 13:12) በመጠናናት ላይ ያሉ ጥንዶችን ልንረዳቸው የምንችለው እንዴት ነው? አብረውን እንዲመገቡ፣ በቤተሰብ አምልኳችን ላይ እንዲገኙ ወይም አብረውን እንዲዝናኑ ልንጋብዛቸው እንችላለን። (ሮም 12:13) ብቻቸውን እንዳይሆኑ አብረናቸው ልንሆን፣ በመኪና ልንወስዳቸው ወይም በነፃነት የሚያወሩበት ቦታ ልናመቻችላቸው እንችላለን። (ገላ. 6:10) የሚጠናኑ ጥንዶች ብቻቸውን እንዳይሆኑ አብረሃቸው እንድትሆን ከጠየቁህ አክብረው ስለጋበዙህ ልትደሰት ይገባል። ሙሉ በሙሉ ብቻቸውን እንዳትተዋቸው ተጠንቀቅ፤ ሆኖም ለብቻቸው ማውራት ሊፈልጉ ስለሚችሉ አጋጣሚውን ስጣቸው። w24.05 30 አን. 13-14

ማክሰኞ፣ መጋቢት 24

ንስሐ እንድትገባ ጊዜ ሰጠኋት።—ራእይ 2:21

ሽማግሌዎች ግለሰቡን ወደ ኃጢአት የመራው ምን እንደሆነ ለማወቅ ጥረት ያደርጋሉ። ለምሳሌ ግለሰቡ የግል ጥናቱን ወይም አገልግሎቱን ችላ በማለቱ የተነሳ ቀስ በቀስ መንፈሳዊነቱ ተዳክሞ ይሆን? አዘውትሮ መጸለዩን አቁሞ ወይም የጸሎቱን ጥልቀት ቀንሶ ይሆን? መጥፎ ምኞቶችን ለማሸነፍ መታገሉን አቁሞ ይሆን? በጓደኛ ወይም በመዝናኛ ረገድ ጥበብ የጎደለው ምርጫ አድርጎ ይሆን? እንዲህ ያለ ምርጫ ማድረጉ በልቡ ላይ ምን ተጽዕኖ አሳድሯል? ውሳኔዎቹና ድርጊቶቹ በአባቱ በይሖዋ ላይ ምን ስሜት እንደፈጠሩበት ገብቶታል? ሽማግሌዎች ሳያስፈልግ በግለሰቡ የግል ሕይወት ውስጥ ሳይገቡ አስፈላጊ ጥያቄዎችን በደግነት በመጠየቅ ስሜቱን አውጥቶ እንዲናገርና አካሄዱን መለስ ብሎ እንዲመረምር ሊረዱት ይችላሉ። (ምሳሌ 20:5) በተጨማሪም ግለሰቡ የፈጸመው ድርጊት ምን ያህል ስህተት እንደሆነ እንዲገነዘብ ለመርዳት ጥሩ ምሳሌዎችን መጠቀም ይችላሉ። ምናልባት በመጀመሪያ ውይይታቸው ወቅት ግለሰቡ በድርጊቱ ከልቡ ማዘን ሊጀምር ይችላል። እንዲያውም ንስሐ ሊገባ ይችላል። w24.08 22 አን. 9-11

ረቡዕ፣ መጋቢት 25

ለሌሎች ከተሞችም የአምላክን መንግሥት ምሥራች ማወጅ አለብኝ፤ ምክንያቱም የተላክሁት ለዚህ ዓላማ ነው።—ሉቃስ 4:43

ኢየሱስ “የአምላክን መንግሥት ምሥራች” በቅንዓት የሰበከው አምላክ እንዲሠራ የፈለገው ሥራ ይህ እንደሆነ ስለተገነዘበ ነው። አገልግሎቱ በኢየሱስ ሕይወት ውስጥ ትልቅ ቦታ ነበረው። በአገልግሎቱ መገባደጃ ላይም እንኳ “በየከተማውና በየመንደሩ እያስተማረ” ይጓዝ ነበር። (ሉቃስ 13:22) በተጨማሪም በሥራው አብረውት እንዲሆኑ ደቀ መዛሙርቱን ለስብከት አሠልጥኗቸዋል። (ሉቃስ 10:1) ዛሬም ይሖዋና ኢየሱስ እንድናከናውነው የሚፈልጉት ተቀዳሚው ሥራ ምሥራቹን መስበክ ነው። (ማቴ. 24:14፤ 28:19, 20) ለአገልግሎት ያለንን ቅንዓት ለማሳደግ የሚረዳን ለሰዎች የይሖዋ ዓይነት አመለካከት መያዝ ነው። እሱ የሚፈልገው በተቻለ መጠን ብዙዎች ምሥራቹን ሰምተው እውነትን እንዲቀበሉ ነው። (1 ጢሞ. 2:3, 4) ይህን ሕይወት አድን መልእክት ለሌሎች ስንናገር ይበልጥ ውጤታማ እንድንሆን የሚያሠለጥነንም ለዚሁ ነው። ሰዎች አሁን ላይ ጆሮ ባይሰጡ እንኳ ወደፊት ታላቁ መከራ ከማብቃቱ በፊት ይህን ማድረግ የሚችሉበት አጋጣሚ ያገኙ ይሆናል። w25.03 15-16 አን. 5-7

ሐሙስ፣ መጋቢት 26

ሰላም የሚለው ሰው የክፉ ሥራው ተባባሪ ይሆናል።—2 ዮሐ. 11

እያንዳንዱ ክርስቲያን ከጉባኤ የተወገደን ሰው ስለሚይዝበት መንገድ በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ሕሊናውን ተጠቅሞ መወሰን ይኖርበታል። አንዳንዶች ለግለሰቡ ሰላምታ ለመስጠት ወይም ወደ ስብሰባ ከመጣ ‘እንኳን ደህና መጣህ’ ለማለት ነፃነት ሊሰማቸው ይችላል። ይሁንና ከግለሰቡ ጋር ረዘም ያለ ጭውውት አናደርግም፤ ወይም በሌሎች እንቅስቃሴዎች ከእሱ ጋር ጊዜ አናሳልፍም። አንዳንዶች ‘መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያለውን ሰው ሰላም የሚል ክርስቲያን የክፉ ሥራው ተባባሪ እንደሚሆን ይናገር የለ እንዴ?’ ብለው ይጠይቁ ይሆናል። (2 ዮሐ. 9-11) የጥቅሱ አውድ እንደሚጠቁመው ይህ መመሪያ የሚመለከተው ከሃዲዎችንና መጥፎ ምግባርን የሚያስፋፉ ሌሎች ሰዎችን ነው። (ራእይ 2:20) ስለዚህ አንድ ሰው የክህደት ትምህርቶችንና መጥፎ ምግባርን የሚያስፋፋ ከሆነ ሽማግሌዎች ይህን ሰው ለማነጋገር ዝግጅት አያደርጉም። እርግጥ እንዲህ ያለውም ሰው ወደ ልቦናው ሊመለስ ይችላል። ሆኖም ይህ እስኪሆን ድረስ እንዲህ ያለውን ሰው ሰላም አንለውም፤ ወይም ወደ ስብሰባ እንዲመጣ አንጋብዘውም። w24.08 30-31 አን. 14-15

ዓርብ፣ መጋቢት 27

ልባቸው አሁንም መረዳት ተስኖት ነበር።—ማር. 6:52

ኢየሱስ ሕዝቡን ከመገበ በኋላ ሐዋርያቱ ጀልባ ተሳፍረው ወደ ቅፍርናሆም እንዲመለሱ አደረገ። እሱ ግን ሊያነግሡት የሞከሩትን ሰዎች ትቶ በመሄድ ወደ ተራራ ወጣ። (ዮሐ. 6:16-20) ሐዋርያቱ በጀልባ ላይ ሳሉ ኃይለኛ ነፋስና ማዕበል ተነሳ። ከዚያም ኢየሱስ በውኃው ላይ እየተራመደ ወደ እነሱ መጣ። ሐዋርያው ጴጥሮስንም በውኃው ላይ እየተራመደ እንዲመጣ ነገረው። (ማቴ. 14:22-31) ኢየሱስ ጀልባው ላይ ሲወጣ አውሎ ነፋሱ ጸጥ አለ። በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ተደንቀው “አንተ በእርግጥ የአምላክ ልጅ ነህ” አሉት። (ማቴ. 14:33) ያም ቢሆን፣ በዚህኛው ተአምርና ኢየሱስ ቀደም ሲል ሕዝቡን በመመገብ በፈጸመው ተአምር መካከል ያለውን ተያያዥነት አላስተዋሉም ነበር። በማርቆስ ዘገባ ውስጥ የሚከተለውን ተጨማሪ መረጃ እናገኛለን፦ “በዚህ ጊዜ በከፍተኛ የአድናቆት ስሜት ተዋጡ፤ ይህም የሆነው የዳቦውን ተአምር ትርጉም ባለማስተዋላቸው ነው።” (ማር. 6:50-52) ሐዋርያቱ፣ ይሖዋ ለኢየሱስ የሰጠው ተአምር የመፈጸም ኃይል ሕዝቡን በመመገብ ብቻ የሚወሰን እንዳልሆነ አላስተዋሉም ነበር። w24.12 5 አን. 7

ቅዳሜ፣ መጋቢት 28

[የአምላክ] ፈቃድ ሁሉም ዓይነት ሰዎች እንዲድኑና የእውነትን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ ነው።—1 ጢሞ. 2:4

በመታሰቢያው በዓል ሰሞን ለቤዛው ያለንን አመስጋኝነት ለይሖዋ በማሳየት ለይሖዋ ፍቅር ያለንን አድናቆት መግለጽ እንችላለን። እኛ ራሳችን በመታሰቢያው በዓል ላይ ከመገኘት ባለፈ ሌሎችም እንዲገኙ ልንጋብዝ እንችላለን። ለምትጋብዛቸው ሰዎች በመታሰቢያው በዓል ላይ ምን እንደሚከናወን ንገራቸው። ኢየሱስ የሞተው ለምንድን ነው? እና የኢየሱስ ሞት መታሰቢያ የተባሉትን ቪዲዮዎች ከ​jw.org ላይ ልታሳያቸው ትችላለህ። ሽማግሌዎች የቀዘቀዙ ክርስቲያኖችን ለመጋበዝ ለየት ያለ ጥረት ሊያደርጉ ይገባል። ከጠፉ የይሖዋ በጎች መካከል አንዳንዶቹ ወደ መንጋው ለመመለስ ቢነሳሱ በሰማይም ሆነ በምድር ምን ያህል ደስታ እንደሚኖር ለማሰብ ሞክር። (ሉቃስ 15:4-7) በመታሰቢያው በዓል ላይ እርስ በርስ ሰላም ከመባባል በተጨማሪ አዲሶችንና ለረጅም ጊዜ በበዓሉ ላይ ያልተገኙ ሰዎችን ሰላም ለማለት ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ጥሩ አቀባበል ልናደርግላቸው እንፈልጋለን።—ሮም 12:13፤ w25.01 29 አን. 15

እሁድ፣ መጋቢት 29

አምላክ . . . ስለወደደንና ለኃጢአታችን የማስተሰረያ መሥዋዕት እንዲሆን ልጁን ስለላከ ነው።—1 ዮሐ. 4:10

ቤዛው የይሖዋን ፍትሕ እንድንረዳ ከማድረግ በተጨማሪ እሱ ለእኛ ያለው ፍቅር ምን ያህል ጥልቅ እንደሆነም ያስገነዝበናል። (ዮሐ. 3:16፤ 1 ዮሐ. 4:9, 10) ይሖዋ ቤዛውን የከፈለው ለዘላለም እንድንኖር ብቻ ሳይሆን የእሱ ቤተሰብ አባላት እንድንሆንም ጭምር ነው። እስቲ አስበው፦ አዳም ኃጢአት በሠራ ጊዜ ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን ካቀፈው ቤተሰቡ አባረረው። በመሆኑም ሁላችንም ስንወለድ ጀምሮ የአምላክ ቤተሰብ አባላት አይደለንም። ሆኖም ይሖዋ ቤዛውን መሠረት በማድረግ ኃጢአታችንን ይቅር ይለናል፤ እንዲሁም እምነት ያላቸውና ታዛዥ የሆኑ የሰው ዘሮች ቤተሰቡን እንዲቀላቀሉ ይፈቅድላቸዋል። አሁንም እንኳ ከይሖዋና አብረውን እሱን ከሚያገለግሉ ሰዎች ጋር የቅርብ ወዳጅነት መመሥረት እንችላለን። በእርግጥም አምላክ ታላቅ ፍቅር አሳይቶናል!—ሮም 5:10, 11፤ w25.01 21 አን. 6

የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች፦ ኒሳን 9) ዮሐንስ 12:12-19፤ ማርቆስ 11:1-11

ሰኞ፣ መጋቢት 30

የአምላክ ፍቅር . . . በዚህ መንገድ ተገልጧል።—1 ዮሐ. 4:9

ቤዛው በዋጋ የማይተመን ስጦታ ነው ቢባል እንደምትስማማ ምንም ጥርጥር የለውም! (2 ቆሮ. 9:15) ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረት የቻልነው ኢየሱስ ሰብዓዊ ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ ስለከፈለ ነው። የዘላለም ሕይወት ተስፋም አስገኝቶልናል። ይሖዋ በፍቅር ተነሳስቶ የቤዛውን ዝግጅት ስላደረገልን አመስጋኝ መሆናችን ምንኛ የተገባ ነው! (ሮም 5:8) ኢየሱስ አመስጋኝ ሆነን እንድንቀጥልና ቤዛውን አቅልለን እንዳንመለከት ሲል የሞቱን መታሰቢያ በዓል በየዓመቱ እንድናከብር አዞናል። (ሉቃስ 22:19, 20) በዚህ ዓመት የመታሰቢያው በዓል የሚከበረው ሐሙስ፣ ሚያዝያ 2, 2026 ነው። ሁላችንም ለመገኘት እንደምንፈልግ ጥርጥር የለውም። በመታሰቢያው በዓል ሰሞን ይሖዋና ልጁ ስላደረጉልን ነገር ጊዜ ወስደን ማሰላሰላችን በእጅጉ ይጠቅመናል። w25.01 20 አን. 1-2

የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች፦ ኒሳን 10) ዮሐንስ 12:20-50

ማክሰኞ፣ መጋቢት 31

ከብር ይልቅ ተግሣጼን፣ ጥራት ካለውም ወርቅ ይልቅ እውቀትን ተቀበሉ።—ምሳሌ 8:10

ይሖዋ አምላክና ኢየሱስ ክርስቶስ ባደረጉልን ነገር ላይ ማሰላሰልህን ከቀጠልክ ለእኛ ስላላቸው ፍቅር ይበልጥ መማር ትችላለህ። ምናልባትም የመታሰቢያው በዓል በሚከበርበት ሰሞን አንዳንዶቹን የወንጌል መጻሕፍት በጥሞና ለማንበብ ጥረት ልታደርግ ትችላለህ። በአንድ ጊዜ ብዙ ምዕራፎችን ለማንበብ አትሞክር። ከዚህ ይልቅ፣ ረጋ ብለህ ይሖዋንና ኢየሱስን ለመውደድ የሚያነሳሱንን ተጨማሪ ምክንያቶች ለማግኘት ሞክር። በእውነት ውስጥ ለብዙ ዓመታት ቆይተህ ከሆነ ስለ ይሖዋ ፍትሕ፣ ስለ ፍቅሩ፣ ስለ ቤዛው ወይም እንደዚህ ስለመሳሰሉ የተለመዱ ርዕሰ ጉዳዮች አዲስ እውቀት ማግኘት የምትችል አይመስልህ ይሆናል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ስለ እነዚህም ሆነ ስለ ሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች ገና የማናውቀው ብዙ ነገር አለ። በጽሑፎቻችን ውስጥ ደግሞ ብዙ መረጃ ይገኛል፤ ስለዚህ ጽሑፎቻችንን ጥሩ አድርገህ ተጠቀምባቸው። w25.01 24-25 አን. 13-15

የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች፦ ኒሳን 11) ሉቃስ 21:1-36

    የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ ጽሑፎች (2011-2026)
    ውጣ
    ግባ
    • የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2026 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ