የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w26 ግንቦት ገጽ 14-19
  • ከትምህርት ጋር በተያያዘ ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ አድርጉ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ከትምህርት ጋር በተያያዘ ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ አድርጉ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2026
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ተጨማሪ ትምህርት መከታተል ይኖርብኛል?
  • ለመማር የተነሳሳችሁበትን ዓላማ ገምግሙ
  • ስለ ትምህርቱ የተሟላ መረጃ ለማግኘት ጥረት አድርጉ
  • ተጨማሪ ትምህርት ስትከታተሉ መንፈሳዊነታችሁን ጠብቁ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2026
  • መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት መከታተልን ጨርሶ አያበረታታምን?
    ንቁ!—1999
  • ትምህርትን ይሖዋን ለማወደስ ተጠቀሙበት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
  • ትምህርትን በዓላማ መከታተል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2026
w26 ግንቦት ገጽ 14-19

ከሐምሌ 20-26, 2026

መዝሙር 133 በወጣትነታችሁ ይሖዋን አምልኩ

ከትምህርት ጋር በተያያዘ ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ አድርጉ

“ብልህ . . . አካሄዱን አንድ በአንድ ያጤናል።”—ምሳሌ 14:15

ዓላማ

ተጨማሪ ትምህርት ከመከታተል ጋር በተያያዘ ውሳኔ ስናደርግ ግምት ውስጥ ልናስገባቸው የሚገቡ ሁኔታዎችንና የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን እንመለከታለን።

1-2. (ሀ) ወጣቶች ምን ውሳኔ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል? (ለ) “ተጨማሪ ትምህርት” የሚለው አገላለጽ ምን ያመለክታል? (“ተጨማሪ ማብራሪያ” የሚለውን ተመልከት።)

“ስታድግ ምን መሆን ትፈልጋለህ?” ወጣቶች ከሆናችሁ ይህን ጥያቄ ብዙ ጊዜ ተጠይቃችሁ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። እርግጥ ከሁሉ የተሻለው የሥራ መስክ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ነው። ሆኖም ራሳችሁን ማስተዳደርም ያስፈልጋችኋል። (2 ተሰ. 3:10) ‘ወደፊት ምን ዓይነት ሥራ ሠርቼ ራሴን አስተዳድራለሁ?’ የሚለውን ጉዳይ አስባችሁበት እንደሚሆን የታወቀ ነው።

2 አንዳንድ ወጣቶች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ከጨረሱ በኋላ ሥራ ለማግኘት ሲሉ ከወላጆቻቸው ጋር ተማክረው ተጨማሪ ትምህርት ለመከታተል ይወስናሉ።a እናንተም ‘ተጨማሪ ትምህርት ልከታተል? ከሆነስ ምን ዓይነት ትምህርት?’ ብላችሁ አስባችሁ ሊሆን ይችላል። ይህ ርዕስ ከትምህርት ጋር በተያያዘ ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ለማድረግ የሚረዷችሁን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ይዟል። ርዕሱ በዋነኝነት የተዘጋጀው ለወጣቶች ቢሆንም ተጨማሪ ትምህርት ለመከታተል እያሰቡ ያሉ ክርስቲያኖችን በሙሉ ሊረዳቸው ይችላል። በተጨማሪም ወላጆች በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱትን መሠረታዊ ሥርዓቶች መመርመራቸው ለልጆቻቸው ጥሩ ምክር ለመስጠት ይረዳቸዋል።

ተጨማሪ ትምህርት መከታተል ይኖርብኛል?

3. አንዳንድ ክርስቲያኖች ተጨማሪ ትምህርት ለመከታተል የሚመርጡት ለምን ሊሆን ይችላል?

3 በአንዳንድ አካባቢዎች ወጣቶች ተጨማሪ ትምህርት መከታተል ሳያስፈልጋቸው በቂ ገንዘብ የሚያስገኝ ሥራ ማግኘት ይችላሉ። በሌሎች አካባቢዎች ግን ረጅም ሰዓት መሥራት የማይጠይቅና ጥሩ ገንዘብ የሚያስገኝ ሥራ ለማግኘት ተጨማሪ ትምህርት መከታተል ያስፈልግ ይሆናል። አንድ ክርስቲያን እንዲህ ያለ ሥራ ማግኘቱ በስብከቱ ሥራ ወይም በሌሎች ቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች ለመካፈል ሰፋ ያለ ጊዜ እንዲያገኝ ሊረዳው ይችላል። ያም ሆኖ፣ ተጨማሪ ትምህርት መከታተል አንዳንድ መሥዋዕቶችን መክፈል ሊጠይቅ እንዲሁም አንዳንድ ተፈታታኝ ሁኔታዎችን ሊያስከትል ይችላል።

4. አንድ ክርስቲያን ተጨማሪ ትምህርት መከታተል ይኖርበት እንደሆነና እንዳልሆነ የሚወስነው ማን ነው? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)

4 መጽሐፍ ቅዱስ “እያንዳንዱ የራሱን የኃላፊነት ሸክም ይሸከማል” ይላል። (ገላ. 6:5) ስለዚህ እያንዳንዱ ለአካለ መጠን የደረሰ ክርስቲያን ተጨማሪ ትምህርት ለመከታተል ወይም ላለመከታተል የራሱን ውሳኔ ማድረግ ይጠበቅበታል።b ወላጆች ለአካለ መጠን ካልደረሱ ልጆቻቸው ትምህርት ጋር በተያያዘ ውሳኔ የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው። (ኤፌ. 6:1) ወላጆች ለልጆቻቸው የሚሰጧቸው መመሪያና ሥልጠና ልጆቹ ለአካለ መጠን ሲደርሱ ከትምህርት ጋር በተያያዘ ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ለማድረግ ይረዳቸዋል።—ምሳሌ 22:6

5. አንድ ሰው ተጨማሪ ትምህርትን በተመለከተ ማሰብ የሚኖርበት መቼ ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

5 ወጣቶች ብዙውን ጊዜ ተጨማሪ ትምህርት ለመከታተል ወይም ላለመከታተል ውሳኔ ማድረግ ያለባቸው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ከመጨረሳቸው በፊት ነው። አንድ ወጣት እንዲህ ያለውን ውሳኔ የሚያደርግበት ጊዜ ገና ሳይደርስ በፊት ከወላጆቹ ጋር መማከሩ ጠቃሚ ነው። እንዲህ ማድረጉ አብረው የተለያዩ አማራጮችን ለመፈለግና ምርምር ለማድረግ ጊዜ ይሰጣቸዋል። ምናልባትም ለወደፊት ትምህርቱ ወይም ሥራው የሚያዘጋጁ የትምህርት ዓይነቶችን ከወዲሁ መምረጥ ይችል ይሆናል። ይሁንና ልጁ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ከመጨረሱ በፊት የግድ ውሳኔ ማድረግ ይጠበቅበታል? ላይጠበቅበት ይችላል። (ምሳሌ 21:5) አንዳንድ ወጣቶች ትምህርት ከጨረሱ በኋላ ‘በመጀመሪያ ሥራ ልፈልግና አቅኚነት ልጀምር። ከዚያ ተጨማሪ ትምህርት መከታተል ይኖርብኝ እንደሆነና እንዳልሆነ እወስናለሁ’ ይላሉ። ስለዚህ አንድ ሰው እንዲህ ዓይነቱን ውሳኔ የሚያደርገው ዘግየት ብሎ ሊሆን ይችላል።

አንዲት ወጣት እህት የምትመርጠውን ተጨማሪ ትምህርት አስመልክቶ ከወላጆቿ ጋር ስትማከር። ጠረጴዛው ላይ የተለያዩ ትምህርት ቤቶችን የሚያስተዋውቁ ብሮሹሮች፣ የJW ብሮድካስቲንግ ቪዲዮ የተከፈተበት ታብሌትና መጽሐፍ ቅዱስ አለ።

ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸው ከተጨማሪ ትምህርት ጋር በተያያዘ ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ እንዲያደርጉ ይረዷቸዋል (አንቀጽ 5ን ተመልከት)


6. ተጨማሪ ትምህርት ከመከታተል ጋር በተያያዘ ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ለማድረግ ምን ይረዳናል?

6 ተጨማሪ ትምህርት ከመከታተል ጋር በተያያዘ ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ለማድረግ ምን ይረዳችኋል? ስለ ጉዳዩ ጸልዩበት። (ያዕ. 1:5) በተጨማሪም የሚከተሉትን ሁለት ነገሮች አድርጉ። አንደኛ፣ ለመማር የተነሳሳችሁበትን ዓላማ በሐቀኝነት ገምግሙ። (መዝ. 26:2) ሁለተኛ፣ ለመማር የምታስቡትን ትምህርት በተመለከተ የተሟላ መረጃ ለማግኘት ጥረት አድርጉ። (ምሳሌ 14:15) እስቲ እነዚህን እርምጃዎች አንድ በአንድ እንመልከት።

ለመማር የተነሳሳችሁበትን ዓላማ ገምግሙ

7. ክርስቲያኖች ተጨማሪ ትምህርት ለመከታተል የሚያስቡ ከሆነ ምን ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል?

7 ተጨማሪ ትምህርት ለመከታተል እያሰባችሁ ከሆነ ‘ይህን ትምህርት መማር የፈለግኩት ለምንድን ነው?’ ብላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ። ብዙዎች ትምህርት የሚማሩት የሚያስደስት ወይም ጥሩ ገንዘብ የሚያስገኝ ሥራ ለማግኘት ነው። እነዚህን ነገሮች መፈለግ በራሱ ስህተት አለው? እንደዚያ ማለት አይደለም። (1 ጢሞ. 5:8) ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ፍቅረ ነዋይና በዚህ ሥርዓት ውስጥ አስተማማኝ ነገር ለማግኘት መሞከር አደገኛ እንደሆነ ይናገራል። (ምሳሌ 23:4, 5፤ 1 ጢሞ. 6:8-10፤ 1 ዮሐ. 2:17) ዓላማችሁ ሀብት ማግኘት ወይም አንቱ መባል ከሆነ ለባዶነት ስሜት ልትዳረጉ ይባስ ብሎም ከይሖዋ ጋር ያላችሁ ዝምድና ሊበላሽ ይችላል።

8-9. (ሀ) ክርስቲያኖች ለትምህርት ምን ዓይነት ቦታ ሊሰጡ ይገባል? (ማቴዎስ 6:33) (ለ) ጆሴፊና፣ ሞሪንና አይሪስ ከተናገሩት ነገር ምን ትምህርት አግኝታችኋል?

8 ታዲያ ለትምህርት ምን ዓይነት ቦታ ልንሰጥ ይገባል? ምንም ነገር ይሖዋን ከማገልገል ሊበልጥብን አይገባም። (ማቴ. 22:37, 38፤ ፊልጵ. 3:8) በመሆኑም ትምህርት የምንከታተልበት ዓላማ ይሖዋን በሙሉ ልባችን ስናገለግል ራሳችንን ለማስተዳደር እንዲያግዘን መሆን ይኖርበታል።—ማቴዎስ 6:33ን አንብብ።

9 አንዳንድ ክርስቲያኖች ተጨማሪ ትምህርትን በተመለከተ ተገቢው አመለካከት እንዲኖራቸው የረዳቸው ምን እንደሆነ እንመልከት። በቺሊ የምትኖረው ጆሴፊና እንዲህ ብላለች፦ “ትምህርት የተማርኩት ይሖዋን በተሟላ ሁኔታ ለማገልገል እንዲረዳኝ ብዬ ነው። ትምህርቱን ከመንፈሳዊ ግቦቼ አስቀድሜ አላውቅም፤ ሁሌም ቅድሚያ የምሰጠው ለመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎቼ ነው።” ሞሪን የተባለች እህት ደግሞ የፀጉር ባለሙያ ለመሆን የአንድ ዓመት ሥልጠና ወስዳለች። ይህን ትምህርት የመረጠችበትን ምክንያት ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “ግቤ እርዳታ ወደሚያስፈልግበት ቦታ ሄዶ ማገልገል ነበር። በመሆኑም እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ የሚያስችለኝን ትምህርት መረጥኩ። ትምህርቴን ስጨርስ በዚያ መስክ ሥራ አገኘሁ፤ ይህም እርዳታ ወደሚያስፈልግበት ቦታ ለመዛወር የሚያስፈልገኝን ገንዘብ እንዳጠራቅም ረድቶኛል። የተማርኩት ትምህርት እዚያ ከሄድኩም በኋላ ሥራ ለማግኘት አስችሎኛል።” በጥርስ ሕክምናው መስክ ረዘም ያለ ሥልጠና የወሰደችው አይሪስ ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “ተጨማሪ ትምህርት መከታተል አንዳንድ ጥቅሞች አሉት። ግን መቼም ቢሆን እውነተኛ ስኬትና እርካታ ሊያስገኝልን አይችልም። ቀመሩ በጣም ቀላል ነው፦ በሕይወታችን ውስጥ ይሖዋን ካስቀደምን እውነተኛ እርካታና ስኬት ማግኘታችን የተረጋገጠ ነው።” በእርግጥም፣ ቅድሚያ የምንሰጠው ከይሖዋ ጋር ላለን ወዳጅነት ከሆነ ዘላቂ ደስታ የሚያስገኙ ውሳኔዎችን ማድረግ እንችላለን።

ስለ ትምህርቱ የተሟላ መረጃ ለማግኘት ጥረት አድርጉ

10. ከተጨማሪ ትምህርት ጋር በተያያዘ ውሳኔ ስናደርግ በዘዳግም 32:29 ላይ የሚገኘውን መሠረታዊ ሥርዓት ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

10 ለመከታተል የምታስቡት አንድ የትምህርት ዓይነት ሊኖር ይችላል። ሆኖም በዚያው መስክም ሆነ በሌላ መስክ ሌሎች አማራጮች ይኖሩ እንደሆነ ማሰባችሁ ጠቃሚ ነው። (ከምሳሌ 18:17 ጋር አወዳድር።) ከጥቂት ዓመታት በፊት ያልነበሩ አንዳንድ የትምህርት አጋጣሚዎች ዛሬ ተከፍተዋል። ለምሳሌ በኢንተርኔት ትምህርት መከታተል ይቻላል። ልታስቡበት የሚገባ ሌላም ነገር አለ፤ ያለተጨማሪ ትምህርት ራሳችሁን ማስተዳደር ትችሉ ይሆን? ለምሳሌ በፊንላንድ የምትኖረው ጆሃና ምንም ዓይነት ተጨማሪ ትምህርት አልተከታተለችም። እንዲህ ብላለች፦ “የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ከጨረስኩ በኋላ ሥራ እየሠራሁ በአቅኚነት ማገልገል ጀመርኩ። የተለያዩ ሥራዎችን ሠርቻለሁ። ይሖዋ የሚያስፈልገንን ነገር እንደሚያሟላልን የገባውን ቃል ሲፈጽም አይቻለሁ።” ተጨማሪ ትምህርት ከመከታተል ጋር በተያያዘ የምናደርገው የትኛውም ውሳኔ አዎንታዊም አሉታዊም ጎን እንደሚኖረው አስታውሱ። ስለዚህ አንድ ሰው ተጨማሪ ትምህርት ለመከታተል ወይም ላለመከታተል ሲወስን እንዲሁም የሚማረውን የትምህርት ዓይነት ሲመርጥ ራሱን እንዲህ ብሎ መጠየቁ የተገባ ነው፦ ‘ጥቅሙ ከጉዳቱ ያመዝናል?’ (ዘዳግም 32:29ን አንብብ፤ 1 ቆሮ. 10:23) ይህን ጥያቄ ለመመለስ የሚረዱ አንዳንድ ነጥቦችን እስቲ እንመልከት።

11. የትምህርቱን ፕሮግራም ከግምት ማስገባት ያለብን ለምንድን ነው? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)

11 የትምህርቱ ፕሮግራም። በክፍል ውስጥ ትምህርት በመከታተል፣ ሥልጠና በመውሰድ እንዲሁም የቤት ሥራ በመሥራት በየሳምንቱ ምን ያህል ጊዜ እንደምታጠፉ አስሉ። በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ለመካፈልና ቤተሰባችሁን ለመርዳት ጊዜ ይኖራችኋል? (ፊልጵ. 1:10) አእምሯችሁ በትምህርቱ ከመወጠሩ የተነሳ ለስብሰባዎች ለመዘጋጀት ወይም የግል ጥናት ለማድረግ አቅም ታጣላችሁ? በሕንድ የሚኖረው ጄሮዝ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሞት ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “ትኩረቴን ሰብስቤ በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች መካፈል ከባድ ሆኖብኝ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ከስብሰባ እቀራለሁ። መለስ ብዬ ሳስበው፣ በትምህርቱ የጨረስኩት ጊዜና ጉልበት ካገኘሁት ጥቅም ጋር አይመጣጠንም።” በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ ሥልጠናዎች ያን ያህል ጊዜ አይወስዱም። ምናልባት ትምህርቱ የሚሰጠው በሳምንት ውስጥ ለተወሰኑ ቀናት ብቻ ሊሆን ይችላል፤ ወይም ደግሞ ብዙ የቤት ሥራ ላይኖረው ይችላል። ለምሳሌ በሞዛምቢክ የምትኖረው ረቤካ በመረጠችው ትምህርት ደስተኛ ነች። እንዲህ ብላለች፦ “የምማረው በቀን ሁለት ሰዓት ብቻ ነው። ይህም የዘወትር አቅኚ ሆኜ ማገልገሌን እንድቀጥል ረድቶኛል።”

ሥዕሎች፦ አንድ ወንድም ከተጨማሪ ትምህርት ጎን ለጎን ሌሎች ኃላፊነቶቹንም መወጣት የሚችል መሆኑን ሲያስብ። 1. ስብሰባ ላይ ማይክሮፎን ሲያዞር። 2. ከቤት ወደ ቤት ሲያገለግል። 3. ካፌ ውስጥ ባሪስታ ሆኖ ሲሠራ። 4. ክፍል ውስጥ ተቀምጦ ትምህርቱን ሲከታተል።

ተጨማሪ ትምህርት ለመከታተል እያሰባችሁ ከሆነ ሁሉንም አስፈላጊ ኃላፊነቶቻችሁን ለመወጣት ጊዜ ይኖራችሁ እንደሆነ አስቡ (አንቀጽ 11ን ተመልከት)


12. ከትምህርት ጋር በተያያዘ ጊዜያችንን በተሻለ መንገድ ለመጠቀም የትኞቹን ጥያቄዎች ልናስብባቸው እንችላለን? (መክብብ 12:1)

12 የትምህርቱ ርዝመት። ትምህርቱን ለማጠናቀቅ ስንት ወር ወይም ስንት ዓመት እንደሚፈጅ አስቡ። ይህን ትምህርት ብትማሩ ጊዜያችሁን በተሻለ መንገድ እንደተጠቀማችሁበት የሚያሳይ ይሆናል? (ኤፌ. 5:15-17) ወጣት ከሆናችሁ፣ ትምህርቱ ገና ወጣትነታችሁ ሳያልፍ ለይሖዋ ምርጣችሁን ለመስጠት ምናልባትም በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመካፈል ያስችላችኋል? (መክብብ 12:1ን አንብብ።) በዚያው መስክ አጠር ያሉ ሥልጠናዎች ይኖሩ ይሆን? ለምሳሌ በቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤቶች ገብታችሁ ብትማሩ ከዩኒቨርሲቲዎች ባነሰ ጊዜና ገንዘብ ጠቃሚ ክህሎቶችን ማዳበር ትችሉ ይሆናል። በቺሊ የሚኖረው ማሪዮ እንዲህ ብሏል፦ “የዩኒቨርሲቲን ያህል ብዙ ገንዘብ የማይጠይቅ የሁለት ዓመት የሙያ ሥልጠና መረጥኩ። የምማረው በሳምንት አራት ቀን ብቻ ስለነበር ትምህርቱን እየተማርኩ በአቅኚነት ማገልገል ችያለሁ።”

13. ከቤተሰባችሁ ርቃችሁ መኖራችሁ ምን ተጽዕኖ ሊያሳድርባችሁ ይችላል?

13 ትምህርቱ የሚሰጥበት ቦታ። በቤታችሁ አቅራቢያ የሚሰጥ ትምህርት ማግኘት ትችሉ ይሆናል። ይሁንና ትምህርቱ የሚሰጠው በሌላ ከተማ ቢሆንስ? ወይም ደግሞ ትምህርቱ ካምፓስ ውስጥ ገብታችሁ መኖር የሚጠይቅባችሁ ቢሆንስ? ከቤተሰባችሁ ርቃችሁ መሄዳችሁ ከባድ መንፈሳዊ አደጋ ሊያስከትልባችሁ እንደሚችል ልብ በሉ። በተለይ ደግሞ የምትኖሩት እምነታችሁን ከማይጋሩ ሰዎች ጋር ከሆነ ሁኔታው የከፋ ሊሆን ይችላል። (ምሳሌ 22:3፤ 1 ቆሮ. 15:33) በሞዛምቢክ የሚኖረው ማቲያስ ብዙ ወጪ የማይጠይቅ የአንድ ዓመት ሥልጠና ወስዶ ነበር። ሆኖም ባደረገው ውሳኔ ተቆጭቷል። ለምን? እንዲህ ብሏል፦ “የምኖረው አዳሪ ትምህርት ቤት ውስጥ በመሆኑ በየቀኑ መጥፎ ነገር እንዳደርግ ፈተና ይደርስብኝ ነበር። ወጣቶች ከቤተሰብ ተለይቶ መኖር የማይጠይቅ ትምህርት እንዲከታተሉ እመክራለሁ።” በሩሲያ የምትኖር እህት ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “ካምፓስ ውስጥ ወይም ዶርም ውስጥ ከመኖር ይልቅ ከቤተሰቦቼ ጋር እየኖርኩ መማሬ ከብዙ አደጋዎችና ፈተናዎች ጠብቆኛል።” ምናልባትም በኢንተርኔት የሚሰጡ ትምህርቶችን ማግኘት ትችሉ ይሆናል።

14. በሉቃስ 14:28 ላይ የሚገኘው መሠረታዊ ሥርዓት ከትምህርት ጋር በተያያዘ ውሳኔ ለማድረግ የሚረዳን እንዴት ነው?

14 ትምህርቱ የሚጠይቀው ወጪ። አንዳንድ ትምህርቶችን መከታተል ብዙ ወጪ አይጠይቅም፤ ወይም ወጪው የሚሸፈነው በመንግሥት ሊሆን ይችላል። ሁኔታው እንዲህ ከሆነ፣ ብዙ ገንዘብ ሳታወጡ ሥራ ለማግኘት የሚያስችሉ ክህሎቶችን ማዳበር ትችሉ ይሆናል። አንዳንድ ጊዜ ግን ተጨማሪ ትምህርት ብዙ ወጪ ይጠይቃል። ሌሎች ተጓዳኝ ወጪዎችም ሊኖሩ ይችላሉ። ለምሳሌ የትምህርት ቤቱን የመግቢያ ፈተና ለማለፍ የግል አስጠኚ መቅጠር ሊያስፈልጋችሁ ይችላል። አንዳንድ ትምህርቶች ለዓመታት ከፍላችሁ የማትጨርሱት ዕዳ ውስጥ ሊከቷችሁ ይችላሉ። በሞዛምቢክ የሚኖረው አዲልሶን ባደረገው የትምህርት ምርጫ ተቆጭቷል። እንዲህ ብሏል፦ “ቤተሰቦቼ ለአራት ዓመት ከፍለው ያስተማሩኝ ከጉሮሯቸው ነጥቀው ነው።” አንድ ትምህርት ለመከታተል ስታስቡ እንዲህ እያላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ፦ ‘ትምህርቱ ምን ያህል ወጪ ይጠይቃል? ገንዘቡን ለመክፈል የእኔም ሆነ የቤተሰቤ አቅም ይፈቅዳል? ያን ያህል ብዙ ወጪ የማይጠይቅ ሌላ አማራጭ ይኖር ይሆን?’ (ሉቃስ 14:28ን አንብብ።) ‘ዕዳ ውስጥ ከገባሁ ዕዳውን ለመክፈል ምን ያህል ጊዜ ይወስድብኛል? ሥራ ስቀጠር የማገኘው ገንዘብ ራሴን ለማስተዳደርና ዕዳውን ለመክፈል ይበቃኛል?’—ምሳሌ 22:7

15. አንድን ትምህርት ለመከታተል ከመወሰናችሁ በፊት የሙያውን ተፈላጊነት ከግምት ማስገባት የሚኖርባችሁ ለምንድን ነው?

15 የሙያው ተፈላጊነት። አሁን በምትኖሩበት ወይም መኖር በምትፈልጉበት አካባቢ ተፈላጊ የሆኑት የሥራ መስኮች የትኞቹ ናቸው? በእርግጥ ትምህርቱ ሥራ ለማግኘት ይረዳችኋል? አንዳንድ ትምህርቶች ጥቅም ላይ የሚውል ክህሎት ከማስጨበጥ ይልቅ የጭንቅላት እውቀት ላይ ትኩረት ያደርጋሉ። (ቆላ. 2:8) በሕንድ የምትኖር አንዲት እህት እንዲህ ብላለች፦ “የተማርኩት ትምህርት ቀጣሪዎች የሚፈልጓቸውን ክህሎቶች እንዳዳብር አልረዳኝም። ስለዚህ በተማርኩበት መስክ ሥራ ማግኘት አልቻልኩም።” አንዳንድ ትምህርቶች ደግሞ ጠቃሚ ክህሎቶችን ቢያስጨብጡም የሥራ ዕድል ላያስገኙ ይችላሉ። በመካከለኛው አፍሪካ ሪፑብሊክ የሚኖረው ሰብላይም የተማረው የአየር ማቀዝቀዣ መሣሪያ መጠገን ነው። ሆኖም ውጤቱን ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “በምኖርበት አካባቢ የሚገኙት ብዙዎቹ ሰዎች የራሳቸውን ዕቃ የሚጠግኑት ራሳቸው ናቸው። በመሆኑም ሥራ ማግኘት አስቸጋሪ ሆኖብኛል።”

16. በተማራችሁበት መስክ ምን ዓይነት ሥራ ልታገኙ እንደምትችሉ ማሰባችሁ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

16 በተማራችሁበት መስክ ምን ዓይነት ሥራ ልታገኙ እንደምትችሉም አስቡ። ሥራው ያስደስታችኋል? (መክ. 3:12, 13) ከምን ዓይነት ሰዎች ጋር ነው የምትሠሩት? ሥራው ለአደጋ የሚያጋልጥ፣ ፉክክር የሚበዛበት ወይም ለውጥረት የሚዳርግ ነው? በዚያ የሥራ መስክ ብትሰማሩ ምን ያህል ገንዘብ ታገኛላችሁ? ገንዘቡ ራሳችሁን ለማስተዳደር ይበቃችኋል? ሥራውን ላለማጣት የትምህርት ደረጃችሁን በየጊዜው ማሳደግ ይጠበቅባችኋል? ከሁሉ በላይ ደግሞ፣ ሥራው የአምላክን መንግሥት ለማስቀደም ይረዳችኋል? (መክ. 12:13) እርግጥ ሥራ እንደ ልብ የማይገኝ ከሆነ ከልክ በላይ መራጮች መሆን አንችልም። ሆኖም የምትማሩት ትምህርት የወደፊት ሥራችሁን እንደሚነካ ማወቅ ያስፈልጋችኋል። በሕንድ የምትኖረው ታቢታ ለስድስት ወር የልብስ ስፌት ሙያ ለመማር መርጣለች። እንዲህ ብላለች፦ “ልብስ ስፌትን የመረጥኩት አቅኚ ሆኜ ለማገልገል እንደሚረዳኝ በማሰብ ነው። ሥራው ሁልጊዜ ተፈላጊ ነው፤ በራሴ ፕሮግራም መሥራት እችላለሁ፤ እንዲሁም ሥራውን ለመጀመር ብዙ ገንዘብ አይጠይቅም።” ታቢታ የተማረችው ትምህርት አቅኚ ሆና ለማገልገል የሚያስችላትን ሥራ ለማግኘት ረድቷታል።

17. (ሀ) አንድ ክርስቲያን ከትምህርት ጋር በተያያዘ ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ለማድረግ የሚረዳውን መረጃ እንዴት ማግኘት ይችላል? (ለ) ውሳኔ ለማድረግ የሚረዱን የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ናቸው? (“ልናስብባቸው የሚገቡ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)

17 እስካሁን ከተጨማሪ ትምህርት ጋር በተያያዘ ከግምት ልታስገቧቸው የሚገቡ የተለያዩ ነጥቦችን ተመልክተናል። ይሁንና ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ለማድረግ የሚረዳችሁን መረጃ ከየት ማግኘት ትችላላችሁ? ትምህርቱ ወደሚሰጥበት ተቋም በመሄድ ወይም የተቋሙን ድረ ገጽ በመጎብኘት ስለ ትምህርቱ ምርምር አድርጉ። ሙያው ምን ያህል ተፈላጊ እንደሆነ ለማወቅ የሥራ ማስታወቂያዎችን ተመልከቱ። በተጨማሪም ያንን ሥልጠና የወሰዱ ወይም በዚያ መስክ ሥራ እየሠሩ ያሉ ሰዎችን ልታማክሩ ትችላላችሁ። (ምሳሌ 13:10) ትምህርቱ ወይም ሥራው ስላሉት አዎንታዊና አሉታዊ ጎኖች ጠይቋቸው። እንዲሁም ይሖዋን በደስታ እያገለገሉ ያሉ ሰዎችን አነጋግሩ። (ምሳሌ 15:22) ምን ዓይነት ትምህርት ብትማሩ ወይም ምን ዓይነት ሥራ ብትሠሩ የተሻለ እንደሚሆን ሐሳብ እንዲሰጧችሁ ጠይቋቸው። ምናልባት ጨርሶ ያላሰባችሁበትን የሥራ መስክ ሊጠቁሟችሁ ይችላሉ።

ልናስብባቸው የሚገቡ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች

  • ተጨማሪ ትምህርት መከታተል የፈለግኩት ለምንድን ነው? (ማቴ. 6:33፤ 1 ጢሞ. 6:8-10)

  • በየሳምንቱ ትምህርቱን በመማርና የቤት ሥራ በመሥራት ምን ያህል ሰዓት አጠፋለሁ? (ፊልጵ. 1:10)

  • ትምህርቱ ስንት ዓመት ይወስዳል? (ኤፌ. 5:15-17)

  • የት እየኖርኩ ነው የምማረው? (1 ቆሮ. 15:33)

  • ትምህርቱ ምን ያህል ገንዘብ ይፈጃል? (ሉቃስ 14:28)

  • ትምህርቱ ራሴን ለማስተዳደርና መንፈሳዊ ግቦቼ ላይ ለመድረስ የሚያስችል ሥራ እንዳገኝ ይረዳኛል? (መክ. 12:13)

18. ምን ማስታወስ ይኖርብናል?

18 እስካሁን እንደተመለከትነው፣ ተጨማሪ ትምህርት ጥቅምም አለው፤ ጉዳትም አለው። ስለዚህ ያሏችሁን አማራጮች በጸሎት ታግዛችሁ መርምሩ። እርግጥ ተጨማሪ ትምህርት መማር ጥሩ ገንዘብ የሚያስገኝ ሥራ ለማግኘት ሊረዳችሁ ይችላል፤ ሆኖም እውነተኛ ደስታ ማግኘት የምትችሉት ከይሖዋ ጋር የቅርብ ወዳጅነት ከመሠረታችሁ ብቻ እንደሆነ አስታውሱ። (መዝ. 16:9, 11) ይሖዋ ሕዝቦቹን ምንጊዜም ይንከባከባል፤ ይህ በትምህርት ደረጃቸው ላይ የተመካ አይደለም። (ዕብ. 13:5) ይሁንና ተጨማሪ ትምህርት ለመከታተል ከወሰናችሁስ? በምትማሩበት ወቅት ከይሖዋ ጋር ያላችሁን ወዳጅነት ጠብቃችሁ ለመኖር ምን ይረዳችኋል? የሚቀጥለው ርዕስ ስለዚህ ጉዳይ ያብራራል።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

  • በገላትያ 6:5 ላይ የሚገኘው ሐሳብ ከተጨማሪ ትምህርት ጋር በተያያዘ የሚሠራው እንዴት ነው?

  • ክርስቲያኖች ለተጨማሪ ትምህርት ምን አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል?

  • አንድ ክርስቲያን ተጨማሪ ትምህርት ለመከታተል ወይም ላለመከታተል ሲወስን የትኞቹን ነጥቦች ከግምት ማስገባት ይኖርበታል?

መዝሙር 45 በልቤ የማሰላስለው ነገር

a ተጨማሪ ማብራሪያ፦ በዚህኛውና በሚቀጥለው ርዕስ ላይ “ተጨማሪ ትምህርት” የሚለው አገላለጽ ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በኋላ ያለውን ማንኛውም ትምህርት ወይም ሥልጠና ያመለክታል። እንዲህ ያለው ትምህርት የሚሰጠው በዩኒቨርሲቲዎች፣ በሙያ ትምህርት ቤቶች ወይም በሌሎች ተቋማት ሊሆን ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ አጫጭር ኮርሶችን ወይም ሌሎች ሥልጠናዎችን ያጠቃልላል።

b ቀደም ሲል ጽሑፎቻችን ክርስቲያኖች አንዳንድ የተጨማሪ ትምህርት ዓይነቶችን ከመከታተል እንዲቆጠቡ ያበረታቱ ነበር። ለምሳሌ በጥቅምት 1, 2005 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣው “ወላጆች—ልጆቻችሁ ወደፊት ምን እንዲሆኑ ትፈልጋላችሁ?” የሚለው ርዕስ ከፍተኛ ትምህርት ስላለው አደጋ ገልጾ ነበር። እነዚህ አደጋዎች አሁንም መኖራቸው ባይካድም ተጨማሪ ትምህርት መከታተል ወይም አለመከታተል ለእያንዳንዱ ግለሰብ የተተወ ምርጫ ነው። እያንዳንዱ ክርስቲያን፣ ልጆች ከሆኑ ደግሞ እያንዳንዱ የቤተሰብ ራስ ውሳኔ ከማድረጉ በፊት የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶችና ከትምህርቱ ጋር የተያያዙ አንዳንድ ጉዳዮችን በጸሎት ታግዞ መመርመር ይኖርበታል። አንድ ክርስቲያን በዚህ ረገድ የትኛውንም ምርጫ ቢያደርግ ሽማግሌዎችን ጨምሮ ማንም ሰው ሊፈርድበት አይገባም።—ያዕ. 4:12

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2026)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2026 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ