ከሐምሌ 13-19, 2026
መዝሙር 127 ምን ዓይነት ሰው መሆን አለብኝ?
የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ተጠቅማችሁ ሕሊናችሁን አሠልጥኑ
“እያንዳንዱ የራሱን የኃላፊነት ሸክም ይሸከማል።”—ገላ. 6:5
ዓላማ
ሕሊናችን ጥሩ አመራር እንዲሰጠን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ተጠቅመን ልናሠለጥነው የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።
1-2. (ሀ) አዳምና ሔዋን የትኛው ስጦታ ተሰጥቷቸዋል? (ለ) ለዚህ ስጦታ ያላቸውን አድናቆት ለማሳየት ምን ማድረግ ነበረባቸው?
እንስሳት ማንኛውንም ነገር የሚያደርጉት በደመ ነፍስ ነው። ማሽኖችም አንድን ሥራ የሚያከናውኑት የተጫነላቸውን ፕሮግራም መሠረት አድርገው ነው። ሰዎች ግን ከዚህ የተለዩ ናቸው። ይሖዋ ሲፈጥረን አንድ ልዩ ስጦታ ሰጥቶናል። ይህ ስጦታ የመምረጥ ነፃነት ማለትም የራሳችንን ውሳኔና ምርጫ የማድረግ ችሎታ ነው። እውነተኛ ክርስቲያኖች ይህን ስጦታ ከፍ አድርገው ይመለከቱታል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ የመጀመሪያው ሰው አዳም የተፈጠረው በአምላክ መልክ ወይም አምሳል እንደሆነ ይናገራል። (ዘፍ. 1:26, 27) አዳምም ሆነ ሚስቱ ሔዋን የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጥረታት ስለነበሩ የራሳቸውን ውሳኔ የማድረግ ችሎታ ተሰጥቷቸዋል።
2 ይሖዋ ለአዳምና ለሔዋን ዝርዝር ሕጎችን አልሰጣቸውም። ያዘዛቸው ምድርን እንዲንከባከቡ፣ ልጆች ወልደው ምድርን እንዲሞሉ እንዲሁም ማድረግ ያለባቸውንና የሌለባቸውን ነገር የመወሰን ሥልጣን ያለው እሱ እንደሆነ አምነው እንዲቀበሉ ብቻ ነው። (ዘፍ. 1:28፤ 2:16, 17) አዳምና ሔዋን የመምረጥ ነፃነት ለሰጣቸው አምላክ ያላቸውን አድናቆት ለማሳየት ምን ማድረግ ነበረባቸው? ይሖዋ ካደረገላቸው በርካታ መልካም ነገሮች አንጻር ለእሱ ባላቸው ፍቅርና እሱን ለማስደሰት ባላቸው ፍላጎት ተነሳስተው እነዚህን ቀላል ትእዛዞች መታዘዝ ነበረባቸው።—ምሳሌ 23:15
3. አዳምና ሔዋን የመምረጥ ነፃነታቸውን የተጠቀሙበት እንዴት ነው?
3 መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው፣ አዳምና ሔዋን የመምረጥ ነፃነታቸውን በአግባቡ አልተጠቀሙበትም። ይሖዋን ላለመታዘዝ መረጡ። እንዲህ ያለ ውሳኔ ያደረጉት ራስ ወዳዶች ስለነበሩ ነው፤ ለይሖዋ ፍቅርና አድናቆት አልነበራቸውም። (ዘፍ. 3:1-7) ይህ ውሳኔ ያስከተለውን መዘዝ እኛም እያጨድን ነው።—ሮም 5:12
4. (ሀ) በገላትያ 6:5 መሠረት ሁላችንም ምን ማድረግ ይጠበቅብናል? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ ስለ የትኛው ሌላ ስጦታ እንመለከታለን?
4 በዛሬው ጊዜ በየዕለቱ ውሳኔ የሚጠይቁ በጣም ብዙ ጉዳዮች ያጋጥሙናል። (ገላትያ 6:5ን አንብብ።) አንዳንዶቹን ውሳኔዎች ማድረግ ቀላል ነው፤ አንዳንዶቹ ግን ከባድ ናቸው። ታዲያ ይሖዋን የሚያስደስቱ ውሳኔዎችን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ፣ የይሖዋ እርዳታ እንደሚያስፈልገን አምነን መቀበል ይኖርብናል። (ምሳሌ 16:3፤ ኤር. 10:23) ፍጹም ሰው የነበረው ኢየሱስ እንኳ የአምላክ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ተገንዝቦ ነበር። (ዕብ. 5:7) ፍጹማን ያልሆንነው እኛማ የአምላክ አመራር ይበልጥ እንደሚያስፈልገን ምንም ጥያቄ የለውም። ከዚህ በመቀጠል፣ ጥሩ ውሳኔዎች ለማድረግ የሚረዳንን ከአምላክ ያገኘነውን ሌላ ስጦታ እንመለከታለን፤ እሱም ሕሊናችን ነው።
ሕሊና ምንድን ነው?
5. (ሀ) ሕሊና ምንድን ነው? (ለ) ሕሊና የሚረዳን እንዴት ነው? (ሮም 2:14, 15)
5 ሕሊና ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር የሚነግረን በውስጣችን ያለ ድምፅ ነው። የአምላክን ሕጎች የማያውቁ ሰዎችም ሕሊና አላቸው። (2 ቆሮ. 4:2) ሕሊና ልክ እንደ ዳኛ ነው፤ አስተሳሰባችንንና ድርጊታችንን በተመለከተ ወይ ይከሰናል ወይም ደግሞ ጥፋተኛ አይደላችሁም ይለናል። (ሮም 2:14, 15ን አንብብ።) ሕሊናችን ስህተት እንደሆነ የምናውቀውን ነገር እንዳናደርግ ያስጠነቅቀናል። (1 ሳሙ. 26:8-11) ወይም ደግሞ ትክክል እንደሆነ የምናውቀውን ነገር እንድናደርግ ይገፋፋናል። የመምረጥ ነፃነት አለን ማለት የምናደርገው ውሳኔ ሁሉ ይሖዋን ያስደስተዋል ማለት አይደለም። ሕሊናችን የምናደርገው ውሳኔ ጥሩ ወይም መጥፎ መሆኑን ለይተን እንድናውቅ ይረዳናል።
6. ሕሊናችን በትክክል እንዳይሠራ የሚያደርገው ምንድን ነው?
6 ሆኖም ሕሊናችን ሁልጊዜ በትክክል ይሠራል ማለት አይደለም። እኛ ፍጹማን እንዳልሆንን ሁሉ ሕሊናችንም ፍጹም አይደለም። አስተዳደጋችን፣ ባሕላችን እንዲሁም ኃጢአት የመሥራት ዝንባሌያችን በሕሊናችን ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያሳድሩበት ይችላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ሕሊና ‘ሊደክም፣’ ‘ሊረክስ፣’ ‘በጋለ ብረት የተጠበሰ ያህል ሊደነዝዝ፣’ ይባስ ብሎም “ክፉ” ሊሆን እንደሚችል ይናገራል። (1 ቆሮ. 8:12፤ ቲቶ 1:15፤ 1 ጢሞ. 4:2፤ ዕብ. 10:22) እንዲህ ያለው ሕሊና ጥሩ መሪ ሊሆን አይችልም። ወደ ኋላ የቀረ ሰዓት በድጋሚ መሞላት እንደሚያስፈልገው ሁሉ ሕሊናችንም ጥሩ አመራር መስጠቱን እንዲቀጥል በሚገባ መሠልጠን ይኖርበታል። (1 ጴጥ. 3:16) ታዲያ ሕሊናችንን ማሠልጠን የምንችለው እንዴት ነው?
ሕሊናችንን ማሠልጠን የምንችለው እንዴት ነው?
7-8. (ሀ) ሕሊናችንን ለማሠልጠን ምን ይረዳናል? (ለ) የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የሚመሩን እንዴት ነው? በምሳሌ አስረዳ። (ሥዕሉንም ተመልከት።)
7 ሕሊናችንን ማሠልጠን የምንችለው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረን በማንበብ ከይሖዋ አመለካከት አንጻር ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር ማወቅ ይኖርብናል። የአምላክን ሕጎች ማጥናታችን የእሱን አስተሳሰብ ለማወቅ ይረዳናል። ሆኖም ባለፈው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው ሕጎች የሚሠሩት ለተወሰኑ ሁኔታዎች ብቻ ሊሆን ይችላል። የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ለማግኘት ጥረት ማድረግ ያለብን ለዚህ ነው። መሠረታዊ ሥርዓቶች የይሖዋን አስተሳሰብና ስሜት በተሻለ ሁኔታ ለመረዳት ያስችሉናል።—ኢሳ. 55:9
8 የሕይወት ጉዟችን በምድረ በዳ ከሚደረግ ጉዞ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። በግልጽ የሚታይ መንገድ ወይም የመንገድ ምልክት በሌለበት ምድረ በዳ ውስጥ እየተጓዝን ነው እንበል። ፀሐይዋ ያለችበትን ቦታ መመልከታችን ወደምንፈልገው ቦታ ለመድረስ በየትኛው አቅጣጫ መጓዝ እንዳለብን ለማወቅ ይረዳን ይሆናል። ሆኖም በአካባቢው ላይ ጎላ ብለው የሚታዩ ነገሮችን የሚያሳይ ካርታ ቢኖረን ወደምንፈልገው ቦታ መድረስ ይበልጥ እንደሚቀለን ምንም ጥያቄ የለውም። እንዲህ ያለው ካርታ በትክክለኛው መንገድ እየተጓዝን ነው ወይስ አቅጣጫ ስተናል የሚለውን ለማወቅ ይረዳናል። በሕይወት መንገድ ላይ ስንጓዝ መዳረሻችን ወይም ግባችን ይሖዋን ማስደሰት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛውን አቅጣጫ እንደሚጠቁመን ካርታ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ደግሞ በአካባቢው ያሉትን ጎላ ያሉ ነገሮች እንደሚያሳዩ ምልክቶች ናቸው። ከእነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ተስማምተን ከኖርን ወደ መዳረሻችን እንደምንደርስ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።
የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች በአካባቢው ጎላ ብለው የሚታዩ ነገሮችን እንደሚያሳዩ ምልክቶች በትክክለኛው አቅጣጫ እየተጓዝን መሆኑን ለማወቅ ይረዱናል (አንቀጽ 8ን ተመልከት)
9. በሮም 9:1 መሠረት ሕሊናችንን ለማሠልጠን የሚረዳን ሌላው ነገር ምንድን ነው?
9 ሕሊናችን በትክክል እንዲሠራ ለማሠልጠን የአምላክ ቅዱስ መንፈስ እርዳታ ያስፈልገናል። (ሮም 9:1ን አንብብ።) መንፈስ ቅዱስ፣ ይሖዋ ስለተለያዩ ነገሮች ያለውን አመለካከት ለማወቅ ይረዳናል። በተጨማሪም መንፈስ ቅዱስ ከይሖዋ ፈቃድ ጋር በሚስማማ ሁኔታ ሕይወታችንን ለመምራት ፍላጎት እንዲኖረንም ሆነ ኃይል እንድናገኝ ይረዳናል። (ፊልጵ. 2:13) ይሁንና የመንፈስ ቅዱስን እርዳታ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?
10. የመንፈስ ቅዱስን እርዳታ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? (ሉቃስ 11:10, 13)
10 መንፈስ ቅዱስን ለማግኘት ጸልዩ። (ሉቃስ 11:10, 13ን አንብብ።) ይሖዋ ቅዱስ መንፈሱን ለእኛ ለመስጠት ፈቃደኛ እንደሆነ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (ዮሐ. 3:34) የመንፈስ ቅዱስን አመራር ለሚከተሉ ሁሉ መንፈሱን በልግስና ይሰጣቸዋል። (ምሳሌ 1:23፤ ያዕ. 1:5) ሕሊናችንን ለማሠልጠን የሚረዳን ሌላው ነገርስ ምንድን ነው?
11. (ሀ) የሕይወታችን ዋነኛ ግብ ምን ሊሆን ይገባል? (ለ) በሚገባ የሠለጠነ ሕሊና የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?
11 ሁልጊዜ ይሖዋን ለማስደሰት ጥረት አድርጉ። (ምሳሌ 8:34, 35) የሕይወታችን ዋነኛ ግብ ይህ ሊሆን ይገባል። በሕይወታችን ውስጥ ማንኛውም ሁኔታ ሲያጋጥመን ይህን ግብ ማስታወሳችን ሕሊናችንን ለማሠልጠን ሊረዳን ይችላል። በሚገባ የሠለጠነ ሕሊና የሁለት ነገሮች ድምር ውጤት ነው፤ በይሖዋ አስተሳሰብ የተቃኘ አእምሮና ‘ይሖዋ ምን ይሰማዋል’ የሚለው ጉዳይ የሚያሳስበው ልብ። በሕይወታችን ውስጥ ካሉት ውሳኔ የሚጠይቁ ነገሮች ብዛት አንጻር በሚገባ የሠለጠነ ሕሊና በጣም ያስፈልገናል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በቀጥታ ያልተጠቀሱ ሁኔታዎች ብዙ ጊዜ ያጋጥሙናል። እነዚህ ሁኔታዎች ከመዝናኛ፣ ከሥራ፣ ከትምህርት ወይም ከሌሎች ጋር ካለን ግንኙነት ጋር የተያያዙ ሊሆኑ ይችላሉ። ታዲያ በእነዚህ ጉዳዮች ረገድ የምናደርገው ውሳኔ ይሖዋን የሚያስደስት መሆኑን እርግጠኞች መሆን የምንችለው እንዴት ነው?—2 ቆሮ. 1:12
12. ሕሊናችን በትክክለኛው አቅጣጫ እየመራን መሆኑን ለማወቅ ምን ይረዳናል? (ኤፌሶን 5:10)
12 በአምላክ ቃል ላይ አሰላስሉ። (መዝ. 49:3) መጽሐፍ ቅዱስን ስታነቡ የአምላክን አስተሳሰብ ለመረዳት የሚያስችሉ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ፈልጉ። (ኤፌሶን 5:10ን አንብብ።) የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች መፈለጋችን በዚህ አስቸጋሪ ዓለም ውስጥ ስንኖር ሕሊናችን በትክክለኛው አቅጣጫ እየመራን ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ለማወቅ ይረዳናል። (ምሳሌ 2:4-9, 11-13) እነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች በሕሊናችን ላይ አስፈላጊውን ማስተካከያ በማድረግ ከመስመር ሳንወጣ እንድንኖር ይረዱናል።—ዕብ. 5:14
13. ምን ከማድረግ መቆጠብ ይኖርብናል? ምሳሌ ስጥ።
13 የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን የምትፈልጉት አስቀድማችሁ ውሳኔ ካደረጋችሁ በኋላ መሆን የለበትም። ኢየሩሳሌም በ607 ዓ.ዓ. ከጠፋች በኋላ በይሁዳ ምድር የቀሩት እስራኤላውያን ያደረጉትን ነገር መኮረጅ አንፈልግም። እነዚህ እስራኤላውያን ኤርምያስን “አምላክህ ይሖዋ በየት መሄድ እንደሚገባንና ምን ማድረግ እንዳለብን ይንገረን” አሉት። (ኤር. 42:3-6) ሆኖም ምን እንደሚያደርጉ አስቀድመው ወስነው ነበር። የይሖዋ መመሪያ እነሱ ከፈለጉት የተለየ ሆኖ ሲገኝ በቀድሞ ውሳኔያቸው ጸኑ። ይህም አስከፊ መዘዝ አስከትሎባቸዋል። (ኤር. 42:19-22፤ 43:1, 2, 4) እኛም የይሖዋን አስተሳሰብ ለማወቅ የሚያስችሉ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን መፈለግ ያለብን ውሳኔ ከማድረጋችን በፊት ነው፤ ከዚያም ከመሠረታዊ ሥርዓቶቹ ጋር የሚስማማ እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል።
14. በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ የተመሠረተ ውሳኔ ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው?
14 ውሳኔያችሁ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ የተመሠረተ ይሁን። (ማቴ. 7:24-29፤ ያዕ. 1:23-25) በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ ተመሥርተን ውሳኔ ስናደርግ የመንፈስ ቅዱስን አመራር እየተከተልን ነው። ይሖዋም ይህን ሲያይ መንፈሱን ለእኛ መስጠቱን ይቀጥላል። (ሥራ 5:32) የይሖዋን መንፈስ አመራር ችላ የምንል ከሆነ ግን መንፈስ ቅዱስን ‘ልናሳዝን፣’ አልፎ ተርፎም መንፈሱን እንደ መቃወም ሊቆጠርብን ይችላል። (ኤፌ. 4:30፤ ኢሳ. 63:10፤ ሥራ 7:51) ይሖዋም መንፈሱን ሊወስድብን ይችላል። (መዝ. 51:11፤ 1 ተሰ. 5:19) ይህ ደግሞ በጣም ይጎዳናል፤ ምክንያቱም ከመንፈስ ቅዱስ የሚገኘው ኃይልና ብርታት የግድ ያስፈልገናል።—ኤፌ. 3:16
ለውሳኔ የሚረዱ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?
15-16. (ሀ) ውሳኔ ለማድረግ የሚረዱ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማጨሱን ለማቆም የሚያስችል አቅም እንዲያገኝ የሚረዱት የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ናቸው?
15 ምርምር ለማድረግ የሚረዱ መሣሪያዎችን ተጠቀሙ። የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በሥራ ላይ ማዋል እንድንችል በመጀመሪያ መሠረታዊ ሥርዓቶቹን ለይተን ማውጣት ይኖርብናል። ለምሳሌ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችሁ ማጨሱን ለማቆም ፈቃደኛ አልሆነም እንበል። እንዲህ ይል ይሆናል፦ ‘መጽሐፍ ቅዱስ አታጭሱ አይልም። ታዲያ ማጨስ ስህተት እንደሆነ በምን እናውቃለን?’ በዚህ ጊዜ ከዚህ ጉዳይ ጋር የተያያዙ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን እንዲያገኝ ልትረዱት የምትችሉት እንዴት ነው? የምርምር መርጃ መሣሪያ ለይሖዋ ምሥክሮች የተባለው ጽሑፍ በዚህ ረገድ ይረዳችኋል። “ትምባሆ እና ማጨስ” የሚለውን ንዑስ ርዕስ ለጥናታችሁ ልታሳዩት ትችላላችሁ። በዚህ ንዑስ ርዕስ ሥር “ማጨስ በአምላክ ዘንድ እንዴት ይታያል?” የሚል ጥያቄ ይገኛል። (የሰኔ 1, 2014ን መጠበቂያ ግንብ ተመልከቱ።) ጥናታችሁ ያንን ጽሑፍ ሲያነብ የትኞቹን ጥቅሶችና መሠረታዊ ሥርዓቶች ያገኛል?
16 በዚያ ጽሑፍ ላይ ከተጠቀሱት መሠረታዊ ሥርዓቶች አምስቱን እንመልከት። (1) ሞት ለሚያስከትል ነገር ባሪያ መሆን የለብንም። (ሮም 6:16) (2) ሰውነታችንን ከሚጎዳ ከማንኛውም ነገር መራቅ ይኖርብናል። (2 ቆሮ. 7:1) (3) ይሖዋ በሙሉ ነፍሳችን እንድናገለግለው ይፈልጋል። (ማቴ. 22:37) (4) ሌሎችን የሚጎዳ ነገር ማድረግ አይኖርብንም። (ማቴ. 22:39፤ 1 ቆሮ. 10:24) (5) ይሖዋ ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ የሚያስችል ብርታት ይሰጠናል። (ፊልጵ. 4:13) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ‘አታጭሱ’ የሚል ቀጥተኛ መመሪያ ባይኖርም እነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጥናታችሁ የይሖዋን አመለካከት እንዲገነዘብ ይረዱታል።
17. ሠርጋቸውን እያቀዱ ያሉ ክርስቲያን ጥንዶች ለውሳኔ የሚረዱ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ከየት ማግኘት ይችላሉ?
17 ሠርጋቸውን እያቀዱ ያሉ ክርስቲያን ጥንዶች ጥሩ ውሳኔዎችን ለማድረግ የሚረዱ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ከየት ማግኘት ይችላሉ? የምርምር መርጃ መሣሪያ እነሱንም ይረዳቸዋል። “ሠርግ እና ድግስ” በሚለው ንዑስ ርዕስ ሥር የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን የያዙ በርካታ ርዕሶች ይገኛሉ። ሙሽሮቹ የሚከተሉትን ስድስት መሠረታዊ ሥርዓቶች ከግምት ማስገባት ይችላሉ፦ (1) ሁሉም ዝግጅቶች ይሖዋን የሚያስከብሩ ሊሆኑ ይገባል። (1 ቆሮ. 10:31, 32) (2) አለባበሳችን ተገቢ፣ ልከኛና ሌሎችን የማያሰናክል መሆን ይኖርበታል። (1 ጢሞ. 2:9፤ 1 ጴጥ. 3:3, 4) (3) በሰይጣን ዓለም ውስጥ ከተስፋፋው ኑሮዬ ይታይልኝ የሚል መንፈስ መራቅ ይኖርብናል። (ዮሐ. 17:14፤ ያዕ. 1:27፤ 1 ዮሐ. 2:15, 16) (4) ዝግጅቱ በሚገባ የተደራጀ መሆን ይኖርበታል። (1 ቆሮ. 14:40) (5) በድግሱ ላይ ስካርና መረን የለቀቀ ፈንጠዝያ ሊኖር አይገባም። (ገላ. 5:21) (6) ፕሮግራሙን በበላይነት የሚቆጣጠር ሰው ሊመደብ ይገባል።—ዮሐ. 2:8, 9
18-19. (ሀ) ሊረዳን የሚችለው ሌላው መሣሪያ ምንድን ነው? (ለ) ከበዓላት ጋር የተያያዙ ውሳኔዎችን ስናደርግ በዚህ መጽሐፍ ላይ የትኞቹን መሠረታዊ ሥርዓቶች ማግኘት እንችላለን? (“መሠረታዊ ሥርዓቶቹን ለይታችሁ ማውጣት ትችላላችሁ?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)
18 ብዙዎች ጠቃሚ ሆኖ ያገኙት ሌላው መሣሪያ ደግሞ ጥቅሶች ለክርስቲያናዊ ሕይወት የተባለው መጽሐፍ ነው። መጽሐፉ የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮችን ይዳስሳል። በእያንዳንዱ ርዕሰ ጉዳይ ሥር ጥያቄዎችና የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ለማስተዋል የሚረዱ ጥቅሶች ይገኛሉ። ለምሳሌ አንድ ክርስቲያን በሆነ በዓል ላይ መገኘት ይኖርበት እንደሆነና እንዳልሆነ መወሰን ፈልጓል እንበል። “በዓላት” በሚለው ርዕስ ሥር “ክርስቲያኖች የማያከብሯቸው በዓላት” የሚል ንዑስ ርዕስ ይገኛል።
19 “ከሐሰት ሃይማኖት ጋር ንክኪ ያላቸውን በዓላት ማክበር የሌለብን ለምንድን ነው? (1ቆሮ 10:21፤ 2ቆሮ 6:14-18፤ ኤፌ 5:10, 11)” በሚለው ጥያቄ ሥር ያሉትን ሐሳቦች መመልከት ይቻላል። ከሥሩ ከሐሰት ሃይማኖት ጋር ንክኪ ያላቸው አንዳንድ በዓላት ተጠቅሰዋል። “ብሔራዊ በዓላት” በሚለው ንዑስ ርዕስ ሥር ደግሞ አንድ ክርስቲያን በአንድ አገር ታሪክ ውስጥ ወሳኝ ፖለቲካዊ ክንውኖች በሚታሰቡባቸው በዓላት፣ በአገራት መካከል የተደረጉ ጦርነቶችን በሚዘክሩ በዓላት ወይም ለታዋቂ ሰዎች አምልኮ አከል ክብር በሚሰጡ በዓላት ላይ መገኘት ይኖርበት እንደሆነና እንዳልሆነ ለመወሰን የሚረዱ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ይገኛሉ። የይሖዋ ድርጅት ሕሊናችንን ለማሠልጠን የሚረዱ እንዲህ ያሉ መሣሪያዎችን ስላዘጋጀልን ምንኛ አመስጋኞች ነን!
በሚገባ የሠለጠነ ሕሊና እንዳላችሁ አሳዩ
20. በሚገባ የሠለጠነ ሕሊና እንዳለን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
20 ይሖዋ የመምረጥ ነፃነት ስለሰጠን በጣም አመስጋኞች ነን። ሆኖም የመምረጥ ነፃነታችንን በአግባቡ መጠቀም ከፈለግን ሕሊናችንን ማሠልጠን እንደሚኖርብን እንገነዘባለን። በሚገባ የሠለጠነ ሕሊና ለይሖዋ ክብር የሚያመጡና ከፈቃዱ ጋር የሚስማሙ ውሳኔዎችን ለማድረግ ይረዳናል። ሕሊናችንን ለማሠልጠን የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ እርዳታ ያስፈልገናል። ስለዚህ መንፈስ ቅዱስን ለማግኘት መጸለይ፣ ከዚያም የመንፈሱን አመራር መከተል ይኖርብናል። የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችም ሕሊናችንን ለማሠልጠን ይረዱናል። እነዚህን ስጦታዎች በአግባቡ ከተጠቀምንባቸው የአምላክ ቃል ያለውን ኃይል በሕይወታችን ማየት እንችላለን።—2 ጢሞ. 3:16, 17፤ ዕብ. 4:12
መዝሙር 135 የይሖዋ ፍቅራዊ ግብዣ፦ ‘ልጄ ሆይ፣ ጥበበኛ ሁን’