የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w26 ሰኔ ገጽ 20-25
  • እንዴት እንደምታዳምጡ በጥሞና አስቡ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • እንዴት እንደምታዳምጡ በጥሞና አስቡ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2026
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • እያስተማረን ያለው ይሖዋ እንደሆነ አትዘንጉ
  • በስብሰባዎች ላይ በትኩረት ማዳመጥ ያለብን ለምንድን ነው?
  • ሌሎች በስብሰባዎች ላይ ማዳመጥ ቀላል እንዲሆንላቸው አድርጉ
  • ጥሩ አድማጮች ለመሆን ምን ይረዳናል?
  • ይሖዋን ማዳመጣችሁን ቀጥሉ
  • “ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው” ሰዎች ጥሩ ምላሽ ይሰጣሉ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • በአገልግሎት ላይ የማስተማር ችሎታችሁን አሻሽሉ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2026
  • የሚከተሉትን ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ልብ ብላችሁ አዳምጡ
    የ2025-2026 የወረዳ ስብሰባ ፕሮግራም—የወረዳ የበላይ ተመልካች የሚገኝበት
  • በይሖዋ እንደምንታመን የሚያሳዩ ውሳኔዎች
    ክርስቲያናዊ ሕይወታችንና አገልግሎታችን​—የስብሰባው አስተዋጽኦ—2023
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2026
w26 ሰኔ ገጽ 20-25

ከነሐሴ 31-መስከረም 6, 2026

መዝሙር 89 ስማ፣ ታዘዝ፤ ትባረካለህ

እንዴት እንደምታዳምጡ በጥሞና አስቡ

“እንዴት እንደምታዳምጡ በጥሞና አስቡ።”—ሉቃስ 8:18

ዓላማ

በስብሰባዎችና በሌሎች መንፈሳዊ ፕሮግራሞች ላይ በጥሞና ማዳመጥ ያለብን ለምን እንደሆነና ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።

1-2. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ይሖዋ ሕዝቡን በመንፈሳዊ እየተንከባከበ ያለው እንዴት ነው? (መዝሙር 23:1, 2, 5) (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?

በዛሬው ጊዜ ይሖዋ የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ እያቀረበልን ነው። በእርግጥም እንደ ዳዊት “ይሖዋ እረኛዬ ነው። የሚጎድልብኝ ነገር የለም” በማለት አፋችንን ሞልተን መናገር እንችላለን።—መዝሙር 23:1, 2, 5ን አንብብ።

2 በዛሬው ጊዜ ይሖዋ መንፈሳዊ ምግብ የሚያቀርብበት አንዱ መንገድ የጉባኤ ስብሰባ ነው። በአብዛኛው በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ የምንማረው ከዚህ በፊት የምናውቃቸውን ነገሮች ነው። ለበርካታ ዓመታት ‘በእውነት ውስጥ ጸንተን የቆምን’ ብንሆንም እንኳ እነዚህ ማሳሰቢያዎች ያስፈልጉናል። (2 ጴጥ. 1:12) ይሁንና በስብሰባው ላይ የሚቀርበውን ትምህርት ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ የሰማችሁት ከሆነ ትኩረታችሁን ሰብስባችሁ ማዳመጥ ይከብዳችኋል? እንግዲያው ይህ ርዕስ የተዘጋጀው ለእናንተ ነው። በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ በስብሰባዎች ላይ በትኩረት ማዳመጥ ያለብን ለምን እንደሆነ እንመለከታለን። በተጨማሪም በጉባኤ ውስጥ የማስተማር ኃላፊነት የተሰጣቸው ወንድሞች ሌሎች ማዳመጥ ቀላል እንዲሆንላቸው ማድረግ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ እንመረምራለን። ጥሩ አድማጭ ለመሆን የሚረዱንን አንዳንድ ጠቃሚ ሐሳቦችም እንመለከታለን። በቅድሚያ ግን፣ ‘በስብሰባዎች ላይ እያስተማረን ያለው ማን ነው?’ የሚለውን እንመልከት።

እያስተማረን ያለው ይሖዋ እንደሆነ አትዘንጉ

3. ይሖዋ የሚያነጋግረን እንዴት ነው? አገልጋዮቹስ ቃሉን ጥሩ አድርገው የሚጠቀሙት እንዴት ነው?

3 ይሖዋ የሚያነጋግረን በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ነው። (2 ጢሞ. 3:16, 17) ኢየሱስ ይህን ስለሚያውቅ በሚያስተምርበት ጊዜ የአምላክን ቃል ጥሩ አድርጎ ተጠቅሟል። እንዲያውም አድማጮቹ በዚህ በጣም ከመገረማቸው የተነሳ “ይህ ሰው ትምህርት ቤት ገብቶ ሳይማር ቅዱሳን መጻሕፍትን እንዴት እንዲህ ሊያውቅ ቻለ?” ብለው ጠይቀዋል። (ዮሐ. 7:15) ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ኢየሱስ የአምላክን ቃል ሲያብራራ ሲሰሙ በጣም ይደሰቱ ነበር። እንደ ሐዋርያው ጳውሎስና አጵሎስ ያሉ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖችም ሌሎችን ሲያስተምሩ ቅዱሳን መጻሕፍትን በሚገባ ተጠቅመዋል። (ሥራ 17:2, 3፤ 18:24, 28) እኛ የይሖዋ ምሥክሮች ጽሑፎቻችን፣ ብሮድካስቶቻችን፣ የንግግር አስተዋጽኦዎቻችንና ቪዲዮዎቻችን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ እንደሆኑ እናውቃለን። በስብሰባዎቻችን ላይ የሚገኙ በርካታ እንግዶች የይሖዋ ሕዝቦች መጽሐፍ ቅዱስን የሚጠቀሙበት መንገድ በጣም ያስገርማቸዋል። በስብሰባዎች ላይ ክፍል የሚያቀርቡ ወንድሞች ትምህርታቸው በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ያደርጋሉ። ይህን የሚያደርጉት ጥቅሶችን አውጥተው በማንበብ ብቻ ሳይሆን አድማጮች የጥቅሶቹን ትርጉም እንዲረዱና በሥራ ላይ እንዲያውሉ በመርዳት ጭምር ነው።—ሉቃስ 24:32

4. “መስማት” እና “ማዳመጥ” የሚሉት ቃላት ምን ትርጉም ያስተላልፋሉ?

4 “መስማት” እና “ማዳመጥ” የሚሉት ቃላት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙ ጊዜ የተሠራባቸው መታዘዝን ለማመልከት ነው። በስብሰባዎች ላይ ተገኝተን ይሖዋ በቃሉ አማካኝነት የሚያስተምረንን ነገር ስናዳምጥ ፈቃዱ ምን እንደሆነ እንረዳለን። ይህም እሱን መታዘዝ ቀላል እንዲሆንልን ያደርጋል። ይሖዋን ስናዳምጠውና ስንታዘዘው እንደሚደሰት እርግጠኛ መሆን እንችላለን።—ምሳሌ 27:11

በስብሰባዎች ላይ በትኩረት ማዳመጥ ያለብን ለምንድን ነው?

5. ለይሖዋ ያለን ፍቅር ምን ለማድረግ ያነሳሳናል? (ዮሐንስ 4:23, 24፤ 1 ዮሐንስ 5:3)

5 በስብሰባዎች ላይ በትኩረት የምናዳምጠው ይሖዋን ስለምንወደው ነው። (ማቴ. 22:37) ስለ ይሖዋ ይበልጥ ባወቅን መጠን ለእሱ ያለን ፍቅር ያድጋል። ይህ ፍቅር ደግሞ እሱን ለማዳመጥ፣ ለመታዘዝና በቃሉ ውስጥ በነገረን መሠረት እሱን ለማምለክ ያነሳሳናል።—ዮሐንስ 4:23, 24፤ 1 ዮሐንስ 5:3ን አንብብ።

6. ሌሎችን መርዳት ስለምንችልበት መንገድ በስብሰባዎቻችን ላይ ምን እንማራለን?

6 በስብሰባዎች ላይ በትኩረት የምናዳምጠው ሰዎችን ስለምንወድ ነው። (ማቴ. 22:39) በስብሰባዎቻችን ላይ ይሖዋ የእምነት አጋሮቻችንን እንዲሁም እሱን የማያውቁ ሰዎችን እንዴት መርዳት እንደምንችል ያስተምረናል። ለምሳሌ ሰዎችን ውደዱ—ደቀ መዛሙርት አድርጉ የተባለው ብሮሹር በአገልግሎት ላይ የሚጠቅሙ ባሕርያትን እንድናዳብር ይረዳናል። በሳምንቱ መሃል ስብሰባ ላይ በዚህ ብሮሹር ውስጥ የተጠቀሱትን ሐሳቦች እንዴት በሥራ ላይ ማዋል እንደምንችል እንማራለን። ከሰዎች ጋር ጭውውት መጀመር ይከብዳችኋል? ከሆነ በሳምንቱ መሃል ስብሰባ ላይ ክፍል የተሰጣቸው ወንድሞችና እህቶች ጭውውት ለመጀመር ምን ዘዴ እንደሚጠቀሙ በትኩረት ተመልከቱ።

7. ሁልጊዜም ይሖዋን ማዳመጣችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

7 በስብሰባዎች ላይ በትኩረት የምናዳምጠው ሕይወትን ስለምንወድ ነው። ጥንትም ሆነ ዛሬ የአምላክን ቃል መታዘዝ የሞትና የሕይወት ጉዳይ ነው። (ዘዳ. 32:44-47) በስብሰባዎች ላይ ስናዳምጥ መጪውን አዲስ ዓለም በጽናት ለመጠባበቅ የሚያስፈልገንን ማበረታቻ እናገኛለን። (ሮም 8:25) በተለይ በአሁኑ ጊዜ ይሖዋን ማዳመጣችን በጣም ወሳኝ ነው፤ ምክንያቱም የምንኖረው በመጨረሻዎቹ ቀናት ውስጥ ስለሆነ በመንፈሳዊ ንቁ ሆነን መጠበቅ ያስፈልገናል።—ማቴ. 24:42-44፤ ራእይ 1:3

ሌሎች በስብሰባዎች ላይ ማዳመጥ ቀላል እንዲሆንላቸው አድርጉ

8. ከመድረክ የማስተማር መብት ያላቸው ወንድሞች የንግግር ችሎታቸውን እያሻሻሉ መሄድ ያለባቸው ለምንድን ነው?

8 ከመድረክ የሚያስተምሩ በተለይም የሕዝብ ንግግር የሚያቀርቡ ወንድሞች የንግግር ችሎታቸውን እያሻሻሉ መሄድ አለባቸው። ጥሩ ዝግጅት የተደረገበትና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ንግግር ሰዎችን ወደ እውነት የመሳብና የእምነት አጋሮቻችን በእውነት ውስጥ እንዲጸኑ የመርዳት ኃይል አለው። በመሆኑም በስብሰባዎች ላይ ክፍል የሚያቀርቡ ወንድሞች ንግግራቸው ሊያስገኝ የሚችለውን መልካም ውጤት አቅልለው ሊመለከቱት አይገባም። ንግግር የማቅረብ መብት ያላቸው ወንድሞች ከዚህ ቀጥሎ የቀረቡትን ነጥቦች ተግባራዊ ማድረጋቸው ይጠቅማቸዋል። ነጥቦቹ በዋነኝነት ያተኮሩት የሕዝብ ንግግር በሚያቀርቡ ወንድሞች ላይ ቢሆንም ሐሳቡ ሌሎች ንግግሮችን ለሚያቀርቡ ወንድሞችም ይሠራል።—2 ጢሞ. 4:2፤ ቲቶ 1:9

9. አድማጮች የንግግራችን አካሄድ ግልጽ ሊሆንላቸው የሚገባው ለምንድን ነው?

9 ንግግርህን ጥሩ አድርገህ አዋቅር። አድማጮች የንግግርህ አካሄድ ግልጽ ሊሆንላቸው ይገባል። እንዲህ ካልሆነ ግን ትኩረታቸው ሊከፋፈል ይችላል። ታዲያ በደንብ የተዋቀረ ንግግር ለማቅረብ ምን ይረዳሃል? (1) መግቢያህ ላይ የንግግሩን ዋና ዋና ነጥቦች ጥቀስ። (2) ነጥቦቹን አንድ በአንድ አብራራ። ከአንዱ ዋና ነጥብ ወደ ቀጣዩ ስትሻገር ቆም ማለትህና ወደ ቀጣዩ ነጥብ ማለፍህን በግልጽ መናገርህ ጠቃሚ ነው። (3) መደምደሚያህ ላይ ነጥቦቹን በአጭሩ ከልስ።

10. የምናስተምረውን ትምህርት መውደዳችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

10 ትምህርቱን ውደደው። ርዕሰ ጉዳዩን አንተ ራስህ የምትወደው ከሆነ በስሜት መናገርህ አይቀርም። (ምሳሌ 2:4, 5፤ ሥራ 4:20) በጥቅሶቹና ንግግሩ በተመሠረተበት ጽሑፍ ላይ ማሰላሰልህ ርዕሰ ጉዳዩን እንድትወደው ይረዳሃል። በ70ዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኝ በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖር ወንድም በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ሳለ የሰማውን ንግግር አስመልክቶ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ንግግሩ አሁንም ድረስ ትዝ ይለኛል። የአምላክን ቃል ስናነብ በጥልቀት እንድናሰላስል የሚያበረታታ ነበር። ተናጋሪው ንግግሩን ያቀረበው በስሜት ነበር። ማሰላሰል የምንችለው እንዴት እንደሆነም በግልጽ አብራርቶልናል። ያ ንግግር ሕይወቴን ቀይሮታል። መጽሐፍ ቅዱስን በማነብበት መንገድና ከይሖዋ ጋር ባለኝ ዝምድና ላይ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል።”

11. አድማጮችህ ከንግግርህ ጥቅም እንዲያገኙ መርዳት የምትችለው እንዴት ነው? (1 ጢሞቴዎስ 4:13-16)

11 አድማጮችህ ምን እንደሚያስፈልጋቸው አስብ፤ እንዲሁም ትምህርቱን እንዴት ተግባራዊ ሊያደርጉት እንደሚችሉ ግልጽ አድርግ። ጠቅለል ያሉ ሐሳቦችን እንዲሁ በደፈናው ከማቅረብ ይልቅ ቅዱሳን መጻሕፍትን ተጠቅመህ አድማጮችህ ላሉበት ሁኔታ የሚሠራ ማበረታቻና ምክር ስጥ። ለምሳሌ ያህል ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ፣ በኤፌሶን ሲያገለግል በመንፈሳዊ ጠንካራ ሆኖ እንዲቀጥል የሚረዱትን ተግባራዊ ምክሮች ሰጥቶታል። (1 ጢሞቴዎስ 4:13-16ን አንብብ።) አንተም አድማጮችህ ምን እንደሚያስፈልጋቸው አስብ፤ እንዲሁም ትምህርቱን በሕይወታቸው ውስጥ እንዴት ተግባራዊ ሊያደርጉት እንደሚችሉ በግልጽ ንገራቸው።

12. ንግግር ስታቀርብ ተፈጥሯዊ አነጋገርህን መጠቀምህ ጥሩ የሆነው ለምንድን ነው?

12 የራስህን ተፈጥሯዊ አነጋገር ተጠቅመህ መናገር እንድትችል ንግግርህን ጮክ ብለህ ተለማመድ። ንግግርህን ቃል በቃል ጽፈህ ከማንበብ ይልቅ የራስህን ተፈጥሯዊ አነጋገር ተጠቅመህ ስትናገር አድማጮችህ ንግግርህን ማዳመጥና ትምህርቱን መከተል ቀላል ይሆንላቸዋል። ለማንበብ እና ለማስተማር የተቻለህን ሁሉ ጥረት አድርግ የተባለው ብሮሹር እንዲህ ይላል፦ “የራስህን ተፈጥሮአዊ አነጋገር ተጠቅመህ ከልብ በመነጨ ስሜት ተናገር፤ አነጋገርህ ስለ ርዕሰ ጉዳዩም ሆነ ስለ አድማጮችህ ምን እንደሚሰማህ የሚያሳይ ይሁን።” ከልብህ የምትናገር ከሆነ ንግግርህ ሕያው፣ የሚመስጥና ለተግባር የሚያነሳሳ ይሆናል።

13. ተሞክሮ ያላቸውን ተናጋሪዎች ምክር መጠየቅ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

13 ተሞክሮ ያለው ተናጋሪ ምክር እንዲሰጥህ ጠይቅ። ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? ንግግር ከማቅረብህ በፊት ተሞክሮ ላለው ተናጋሪ ማስታወሻህን ልታሳየውና የሰጠህን ሐሳቦች በንግግርህ ላይ ልታካትት ትችላለህ። በተጨማሪም ንግግር ስትሰጥ እንዲያዳምጥህና የማስተማር ችሎታህን ለማሻሻል የሚረዱ ምክሮችን እንዲሰጥህ ጠይቀው። (ምሳሌ 1:5) ሁላችንም የራሳችንን ድክመት ማየት ይከብደናል። ስለዚህ ንግግራችን ቀላልና የሚገባ መሆኑን በራሳችን መገምገም አንችል ይሆናል። አድማጮቻችን በአምላክ ቃል ውስጥ ከሚገኙት መንፈሳዊ ዕንቁዎች የተሟላ ጥቅም ማግኘት እንዲችሉ የመናገርና የማስተማር ችሎታችንን ማሻሻል እንፈልጋለን።a

አንድ ወንድም በስብሰባ አዳራሽ ውስጥ ተሞክሮ ያለው ወንድም እየተከታተለው ንግግግሩን ሲለማመድ፤ ተሞክሮ ያለው ወንድም ማስታወሻ ደብተር ይዟል።

የማስተማር ችሎታህን ለማሻሻል እንዲያግዝህ ተሞክሮ ያለውን ተናጋሪ ጠይቅ (አንቀጽ 13ን ተመልከት)


ጥሩ አድማጮች ለመሆን ምን ይረዳናል?

14. ለአምላክ ማሳሰቢያዎች ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል? (መዝሙር 119:24, 111, 167)

14 ለይሖዋ ማሳሰቢያዎች ያለንን አድናቆት ማሳደጋችን ጥሩ አድማጭ ለመሆን ይረዳናል። ‘ለመቋቋም በሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን’ ውስጥ ስለምንኖር የሚያጋጥሙንን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለመወጣት የአምላክ ማሳሰቢያዎች ያስፈልጉናል። (2 ጢሞ. 3:1) አንዳንድ ጊዜ፣ ትምህርቱ ተደጋጋሚ እንደሆነ ከተሰማን ልክ እንደ መዝሙር 119 ጸሐፊ ለአምላክ ማሳሰቢያዎች አድናቆት ማዳበራችን ይጠቅመናል።—መዝሙር 119:24, 111, 167ን አንብብ።

15. በስብሰባዎች ላይ ለሚቀርብልን መንፈሳዊ ምግብ ያለን አድናቆት እንዳይቀንስ ምን ይረዳናል?

15 ለሚቀርብልን መንፈሳዊ ምግብ ያለንን አድናቆት ይዘን መቀጠላችን በጣም አስፈላጊ ነው። በምድረ በዳ የነበሩት እስራኤላውያን ታሪክ ይህን ያስተምረናል። (ዘፀ. 16:15, 31) መጀመሪያ አካባቢ እስራኤላውያን ከሰማይ ለሚወርድላቸው መና አድናቆት እንደነበራቸው ምንም ጥርጥር የለውም። ምክንያቱም መናው የመጣው ከይሖዋ ነው፤ በዚያ ላይ ጣፋጭ ነበር፤ ሕይወታቸውንም አቆይቶላቸዋል። ውሎ አድሮ ግን አንዳንዶች በየቀኑ መና መብላት ሰለቻቸው። (ዘኁ. 21:5) እኛስ ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? እኛም የሚቀርብልንን መንፈሳዊ ምግብ እንደ ተራ ወይም አሰልቺ ነገር እንዳንመለከተው መጠንቀቅ አለብን። ከዚህ ይልቅ የዚህ ምግብ ምንጭ ይሖዋ እንደሆነ ማስታወስ ይኖርብናል። ደግሞም የይሖዋ ድርጅት ይህን ምግብ የሚያዘጋጅልን በደንብ አስቦበት እንደሆነ ልናስታውስ ይገባል። በተጨማሪም ከትምህርቶቹ የምናገኘው ጥበብ ሕይወታችንን እንደሚታደግልን እንገነዘባለን።—ምሳሌ 3:13, 16-18፤ ዮሐ. 17:3

16. ይሖዋን ለብዙ ዓመታት ያገለገሉ አንዳንድ ክርስቲያኖች በስብሰባዎች ላይ በትኩረት ለማዳመጥ የረዳቸው ምንድን ነው? (“ጥሩ አድማጭ ለመሆን የሚረዱ ምክሮች” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)

16 አንዳንድ ጠቃሚ ምክሮችን ሥራ ላይ ማዋላችን ጥሩ አድማጭ ለመሆን ይረዳናል። ለረጅም ዓመታት ይሖዋን ያገለገሉ አንዳንድ ክርስቲያኖች በስብሰባዎች ላይ በትኩረት ለማዳመጥ የረዳቸው ምን እንደሆነ እንመልከት። ከ30 ለሚበልጡ ዓመታት ይሖዋን ያገለገለች አሽሊ የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “በትኩረት ለማዳመጥ ቁልፉ ዝግጅት ነው። ተዘጋጅቼ ካልሄድኩ ጥያቄዎቹን መመለስ ይከብደኛል፤ ሐሳቤም ይበታተናል።” ለ52 ዓመታት ይሖዋን ያገለገለ ዮሴፍ የተባለ ወንድም ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “ስለማውቀው ርዕሰ ጉዳይ የሚቀርቡ ትምህርቶችን ማዳመጥ ደስ ይለኛል። ምክንያቱም ትምህርቱ ከተለያየ አቅጣጫ ሲብራራ መስማቴ ግንዛቤዬን ያሰፋልኛል።” አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “ንግግሩን የሚያቀርበው ወንድም ጎበዝ ተናጋሪ ባይሆንም እንኳ ወንድም ንግግሩን በሚያቀርብበት መንገድ ላይ ሳይሆን ሊተላለፍ በተፈለገው የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ላይ ትኩረት ለማድረግ እሞክራለሁ።”

ጥሩ አድማጭ ለመሆን የሚረዱ ምክሮች

ለረጅም ጊዜ ይሖዋን ያገለገሉ ክርስቲያኖች “በስብሰባዎች ላይ በትኩረት ለማዳመጥ የረዳችሁ ምንድን ነው?” ተብለው ሲጠየቁ የሚከተሉትን ሐሳቦች ሰጥተዋል፦

  • በ1986 የተጠመቀችው ሱፎን እንዲህ ብላለች፦ “በተናጋሪውና በቪዲዮዎቹ ላይ ትኩረት ማድረግ እንድትችሉ አዳራሽ ውስጥ ከፊት ተቀመጡ።”

  • በ1983 የተጠመቀው ዴቪድ እንዲህ ብሏል፦ “ትኩረቴን ለመሰብሰብ እንዲረዳኝ በተደጋጋሚ ወደ ይሖዋ እጸልያለሁ። በተጨማሪም በስብሰባዎች ላይ መገኘት፣ በትኩረት ማዳመጥና ተሳትፎ ማድረግ የአምልኮዬ ክፍል እንደሆኑ ለማስታወስ እሞክራለሁ።”

  • በ1982 የተጠመቀው ኒኮላስ እንዲህ ብሏል፦ “በስብሰባው ላይ ክፍል የነበረውን እያንዳንዱን ሰው ለማመስገን ግብ አውጡ። የተናገረውን ምሳሌ ወይም የወደዳችሁትን ሐሳብ ለይታችሁ በመጥቀስ አመስግኑት።”

  • በ1988 የተጠመቀው ኦጉስታን እንዲህ ብሏል፦ “ታማኙ ባሪያ ያ ትምህርት ድጋሚ እንዲቀርብ ከወሰነ በዚያ ሰዓት የሚያስፈልገው መንፈሳዊ ምግብ እሱ ነው ማለት ነው፤ ሁሌም ይህን ለማስታወስ እሞክራለሁ።”

17. በስብሰባዎች ላይ በትኩረት ለማዳመጥ ምን ይረዳችኋል? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

17 ከዚህ በታች የቀረቡትን ሐሳቦች ሥራ ላይ ማዋላችን በጥሞና ለማዳመጥ ሊረዳን ይችላል። (1) ከስብሰባ በፊት የምትበሉ ከሆነ በንቃት መከታተል እንዳይከብዳችሁ ቀለል ያለ ምግብ ብሉ። (2) በጊዜ ደርሳችሁ ስብሰባው ከመጀመሩ በፊት ቦታችሁን ያዙ። (3) በስብሰባው ወቅት እንዳይረብሿችሁ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎቻችሁን ድምፅ አጥፉ። (4) ምን ነጥቦች ሊቀርቡ እንደሚችሉ አስቀድማችሁ አስቡ። (5) ተናጋሪውን በትኩረት ተመልከቱ። (6) አጫጭር ማስታወሻዎችን ያዙ፤ ወይም ዋና ዋናዎቹን ነጥቦች በሥዕል አስቀምጡ። (7) ቁልፍ ስለሆኑት ጥቅሶችና ስለ ተያያዥነታቸው ለማሰብ ሞክሩ። (8) ‘ይህን ሐሳብ በጉባኤዬ ወይም በክልሌ ያሉ ሰዎችን ለመርዳት ልጠቀምበት የምችለው እንዴት ነው?’ ብላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ። (9) በወረዳና በክልል ስብሰባዎች ላይ የዕለቱን ጭብጥ፣ የንግግሮቹን ርዕስና ለእያንዳንዱ ንግግር የተመረጡትን ጥቅሶች ከፕሮግራሙ ላይ ቃኙ። (10) ፕሮግራሙ ከመጀመሩ በፊት ጸጥ ብላችሁ በመቀመጥ እንዲሁም ሙዚቃውንና የሙዚቃ ቪዲዮዎቹን በጥሞና በማዳመጥ ልባችሁን አዘጋጁ።

አንድ ወንድም “የመጠበቂያ ግንብ” ጥናት እየተመራ ከጓደኛው ጋር የጽሑፍ መልእክት ሲላላክ።

ኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎቻችሁ የአምላክን ማሳሰቢያዎች እንዳታዳምጡ እንቅፋት እንዲሆኑባችሁ አትፍቀዱ (አንቀጽ 17ን ተመልከት)


ይሖዋን ማዳመጣችሁን ቀጥሉ

18. በስብሰባዎች ላይ በጥሞና ማዳመጣችንን መቀጠል ያለብን ለምንድን ነው?

18 በስብሰባዎች ላይ በትኩረት ማዳመጣችንን መቀጠል አለብን። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ይሖዋ “በጽድቅ መንገድ” እንዲመራን እየፈቀድን ነው። (መዝ. 23:3፤ 31:3) በየጊዜው የሚሰጠን ምክርና እርማት በነፋስ እየተገፋ መስመሩን እንደሚስት ጀልባ እንዳንሆን ይጠብቀናል። እንግዲያው ‘እንዴት እንደምናዳምጥ በጥሞና እናስብ’፤ እንዲሁም በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ የሚሰጠንን ትምህርት በሥራ ላይ እናውል። (ሉቃስ 8:18) ይሖዋን የሚያዳምጡ ሁሉ በአሁኑ ጊዜ ደስታ፣ ወደፊት ደግሞ የዘላለም ሕይወት ያገኛሉ።—መዝ. 119:2, 14

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

  • በስብሰባዎች ላይ በትኩረት ማዳመጥ ያለብን ለምንድን ነው?

  • በስብሰባዎች ላይ የሚያስተምሩ ወንድሞች ሌሎች ማዳመጥ ቀላል እንዲሆንላቸው ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?

  • ጥሩ አድማጭ ለመሆን ምን ይረዳናል?

መዝሙር 87 ኑ! እረፍት አግኙ

a የንግግርና የማስተማር ችሎታህን ለማሻሻል የሚረዱ ተጨማሪ ሐሳቦችን ለማግኘት ለማንበብ እና ለማስተማር የተቻለህን ሁሉ ጥረት አድርግ የተባለውን ብሮሹር እንዲሁም በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም የተባለውን መጽሐፍ ተመልከት።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2026)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2026 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ