የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w26 መጋቢት ገጽ 2-7
  • በአገልግሎት ላይ የማስተማር ችሎታችሁን አሻሽሉ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • በአገልግሎት ላይ የማስተማር ችሎታችሁን አሻሽሉ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2026
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ለምታስተምሯቸው ሰዎች አስቡላቸው
  • የአምላክን ቃል ተጠቀሙ
  • በይሖዋ ላይ እንዲያተኩሩ እርዷቸው
  • የማስተማር ችሎታችሁን ማሻሻላችሁን ቀጥሉ
  • የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችሁ እርምጃ እንዲወስዱ እርዷቸው
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • “ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው” ሰዎች ጥሩ ምላሽ ይሰጣሉ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • በይሖዋ እንደምንታመን የሚያሳዩ ውሳኔዎች
    ክርስቲያናዊ ሕይወታችንና አገልግሎታችን​—የስብሰባው አስተዋጽኦ—2023
  • የማታውቋቸው ነገሮች እንዳሉ አምናችሁ በመቀበል ልካችሁን እንደምታውቁ አሳዩ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2026
w26 መጋቢት ገጽ 2-7

ከግንቦት 4-10, 2026

መዝሙር 53 ለአገልግሎት መዘጋጀት

በአገልግሎት ላይ የማስተማር ችሎታችሁን አሻሽሉ

‘በብዙ ትዕግሥትና በማስተማር ጥበብ ቃሉን ስበክ።’—2 ጢሞ. 4:2

ዓላማ

በአገልግሎት ላይ የማስተማር ችሎታችንን ማሻሻል የምንችልባቸውን ሦስት መንገዶች እንመለከታለን።

1. የትኛውን ችሎታ ማዳበር ይኖርብናል? ለምንስ? (2 ጢሞቴዎስ 4:2) (ሥዕሉንም ተመልከት።)

ኢየሱስ ተከታዮቹን እንዲህ በማለት አዟቸዋል፦ ‘ሂዱና ሰዎችን ያዘዝኳችሁን ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው።’ (ማቴ. 28:19, 20) ይህ መመሪያ ሁሉም ክርስቲያኖች የማስተማር ኃላፊነት እንዳለባቸው ይጠቁማል። እውነት ነው፣ ‘ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸውን’ ሰዎች ወደ ራሱ የሚስበው ይሖዋ ነው፤ መላእክት ደግሞ እነዚህን ሰዎች እንድናገኝ ይረዱናል። (ሥራ 13:48፤ ዮሐ. 6:44፤ ራእይ 14:6) ያም ቢሆን እኛም የራሳችንን ድርሻ መወጣት ይኖርብናል። ጳውሎስና በርናባስ የተዉትን ምሳሌ እስቲ እንመልከት። መጽሐፍ ቅዱስ ጳውሎስና በርናባስ በኢቆንዮን በሚገኝ ምኩራብ ውስጥ ባስተማሩበት ወቅት ስለሆነው ነገር ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “ጥሩ ንግግር ስለሰጡ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አይሁዳውያንና ግሪካውያን አማኞች ሆኑ።” (ሥራ 14:1) ከዚህ እንደምንረዳው ጳውሎስና በርናባስ ‘የማስተማር ጥበብ’ አዳብረው ነበር። (2 ጢሞቴዎስ 4:2ን አንብብ።) እኛም ይህን ጥበብ ማዳበር ይኖርብናል።

ጳውሎስ ምኩራብ ውስጥ በልበ ሙሉነት ሲያስተምር ሰዎቹ በጥሞና እያዳመጡት ነው። በርናባስ፣ ጳውሎስ ሲያስተምር በደስታ እየተመለከተው ነው።

ኢየሱስም ሆነ እንደ ጳውሎስና በርናባስ ያሉ ደቀ መዛሙርቱ የተዉትን ምሳሌ በመመርመር ‘የማስተማር ጥበብን’ በተመለከተ ብዙ ትምህርት ማግኘት እንችላለን (አንቀጽ 1ን ተመልከት)


2. አንዳንድ ክርስቲያኖች መቼም ቢሆን ጥሩ የማስተማር ችሎታ እንደማይኖራቸው የሚሰማቸው ለምን ሊሆን ይችላል?

2 አንዳንዶች መቼም ቢሆን ጥሩ የማስተማር ችሎታ እንደማይኖራቸው ይሰማቸዋል። እንዲህ የሚሰማቸው በትምህርት ብዙም ስላልገፉ ወይም የማስተማር ተሰጥኦ ስለሌላቸው ሊሆን ይችላል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ አንዳንድ ሰዎችም እንዲህ ተሰምቷቸው ነበር። (ዘፀ. 4:10፤ ኤር. 1:6) ሌሎች ደግሞ በአገልግሎት ላይ እምብዛም ውጤት ስለማያገኙ ጥሩ አስተማሪዎች እንዳልሆኑ ይሰማቸዋል። ይሁንና በአገልግሎት ላይ የምናገኘው ሰው ሁሉ ጥሩ ምላሽ ይሰጣል ብለን አንጠብቅም። ደግሞም ውጤት ማግኘታችን የተመካው በእኛ ጥረት ላይ ብቻ አይደለም። ቀደም ሲል እንደተገለጸው፣ ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች እንድናገኝ የሚረዱን ይሖዋና መላእክቱ ናቸው። ያም ቢሆን ግን ምሥራቹን ማራኪ በሆነ መንገድ ለማቅረብ አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ማድረግ ይኖርብናል። ይህ ርዕስ በዚህ ረገድ ይረዳናል። በአገልግሎት ላይ የማስተማር ችሎታችንን ማሻሻል የምንችልባቸውን ሦስት መንገዶች እንመለከታለን።

ለምታስተምሯቸው ሰዎች አስቡላቸው

3. ኢየሱስ የአድማጮቹን ልብ ለመንካት የረዳው ምንድን ነው?

3 መጽሐፍ ቅዱስ፣ ኢየሱስ “በሰው ውስጥ ያለውን ያውቅ” እንደነበር ይናገራል። (ዮሐ. 2:25) ይህ አገላለጽ፣ ኢየሱስ የሰዎችን አስተሳሰብና ስሜት እንደሚያውቅ የሚያሳይ ነው። ኢየሱስ የአድማጮቹን ልብ መንካት የቻለው ምን እንደሚያስፈልጋቸው በሚገባ ስለተረዳ ነው። ሕዝቡ በመንፈሳዊ እንደተራቡና የሃይማኖት መሪዎቻቸው ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ሕጎች በማውጣት ሸክም እንደጫኑባቸው ተረድቶ ነበር። (ማቴ. 9:36፤ 23:4) በመሆኑም በተራራ ስብከቱ ላይ ስለ እነዚህ ጉዳዮች አስተምሯል። የብዙ ሰዎችን ልብ መንካት የቻለው በግለሰብ ደረጃ ስለሚያሳስባቸው ነገር ስላስተማረ ነው።

4. ለሰዎች እንደምናስብ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)

4 ለምናነጋግራቸው ሰዎች እንደምናስብ ማሳየት የምንችልበት አንዱ መንገድ ምን እንደሚያስጨንቃቸው ለማወቅ ጥረት በማድረግ ነው። የምንሰብክላቸው ሰዎች በሙሉ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ የሰይጣን ክፉ ዓለም ጉዳት እያደረሰባቸው ነው። ይህን ማስታወሳችን በክልላችን ውስጥ ላሉት ሰዎች እንድናዝንላቸው ያነሳሳናል። ለምሳሌ በክልላችን ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች በአካባቢያቸው የተከሰተ አንድ ነገር እያስጨነቃቸው ነው? ወላጆች ልጆቻቸው በትምህርት ቤት የሚያጋጥማቸው ነገር ያሳስባቸዋል? በአካባቢያችን ያሉ ሰዎች ሥራ ለማግኘት ይቸገራሉ? መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ተስፋ ሳያውቁ በዚህ አስጨናቂ ዓለም ውስጥ መኖር ምን ያህል ከባድ ሊሆን እንደሚችል አስቡ።—2 ጢሞ. 3:1፤ ኢሳ. 65:13, 14

ሥዕሎች፦ አንዲት እህት በክልሏ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ስላሉበት ሁኔታ በማሰላሰል ለአገልግሎት ስትዘጋጅ። 1. አንድ ሰውዬ አንዲትን እናትና ትንሽ ልጇን በቡጢ ሊመታቸው ሲያስፈራራቸው እናትየው ልጇን ከጉዳት ለመጠበቅ እቅፍ አድርጋዋለች። 2. አንዲት ወጣት ሲጋራ ስታጨስ። 3. አንዲት አረጋዊት ሐኪም ጋ ቀርበው ሐኪሙ ስለ ጤንነታቸው ሁኔታ መጥፎ ዜና ሲነግራቸው።

የምታስተምሯቸው ሰዎች ያሉበትን ሁኔታ ለመረዳትና ለእነሱ አሳቢነት ለማሳየት ጥረት አድርጉ (አንቀጽ 4ን ተመልከት)


5. ኢየሱስ ሰዎችን የያዘበት መንገድ ከፈሪሳውያን የሚለየው እንዴት ነው? (ማቴዎስ 11:28-30)

5 ኢየሱስ ለሚያስተምራቸው ሰዎች ያስብ ነበር፤ እነሱም ቢሆኑ ይህን አስተውለዋል። ኢየሱስ እነሱን የያዘበት መንገድ ከፈሪሳውያን በጣም የተለየ ነበር። ፈሪሳውያን ለተራው ሕዝብ ከፍተኛ ንቀት ነበራቸው። (ማቴ. 23:13፤ ዮሐ. 7:49) ኢየሱስ ግን ሰዎችን የያዘው በደግነትና በአክብሮት ነው። ኢየሱስ ‘ገርና በልቡ ትሑት’ ነበር። (ማቴዎስ 11:28-30ን አንብብ።) ውጤታማ አስተማሪ እንዲሆን ያስቻለው አንዱ ነገር ይህ ነው። እኛም የምናስተምራቸውን ሰዎች በደግነትና በአክብሮት ልንይዛቸው ይገባል።

6. መልእክታችንን ለማይቀበሉ ወይም ለሚቃወሙ ሰዎች ደግነትና አክብሮት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

6 አንዳንዶች መልእክታችንን ላይቀበሉ አልፎ ተርፎም ሊቃወሙን ይችላሉ። ታዲያ በዚህ ጊዜ ምን ዓይነት ምላሽ መስጠት ይኖርብናል? ኢየሱስ ተቃዋሚዎቻችንን ችለን እንድናልፍ ብቻ ሳይሆን ‘ለሚጠሉን መልካም እንድናደርግ፣ የሚረግሙንን እንድንመርቅ እንዲሁም ለሚሰድቡን እንድንጸልይ’ አስተምሮናል። (ሉቃስ 6:27, 28) ሰዎቹ የተቃወሙን ለምን ሊሆን እንደሚችል ቆም ብለን ካሰብን ኢየሱስ የሰጠንን መመሪያ መከተል ቀላል ይሆንልናል። እርግጥ ነው፣ አንዳንዶች የሚቃወሙን መልእክታችንን ስለሚጠሉ ነው። ሌሎች ግን የተቃወሙን እኛን ጠልተውን ሳይሆን የቤተሰብ ችግር ወይም ሌላ አስጨናቂ ሁኔታ ስላጋጠማቸው ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ ያነጋገርናቸው አጉል ሰዓት ላይ ሊሆን ይችላል። ሰዎቹ የተቃወሙበት ምክንያት ምንም ይሁን ምን የሚከተለውን መመሪያ ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብናል፦ “ለእያንዳንዱ ሰው እንዴት መልስ መስጠት እንደሚገባችሁ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ ምንጊዜም በጨው የተቀመመ ያህል ለዛ ያለው ይሁን።” (ቆላ. 4:6) ስሜታቸውን ከተረዳንና የሚያስፈልጋቸውን ነገር ለማወቅ ጥረት ካደረግን በቀላሉ ከመበሳጨት ይልቅ እነሱን በመርዳት ላይ እናተኩራለን።

የአምላክን ቃል ተጠቀሙ

7. የኢየሱስ ትምህርት በምን ላይ የተመሠረተ ነበር? (ዮሐንስ 7:14-16)

7 ኢየሱስ ሰዎችን ያስተማረው ከራሱ አመንጭቶ አልነበረም። ትምህርቱ የተመሠረተው በአምላክ ቃል ላይ ነበር። ያስተማረበት መንገድም በጣም ቀላል ስለነበር አድማጮቹ ትምህርቱን ለመረዳትና ለማስታወስ አልተቸገሩም። ኢየሱስ “እንደ ጸሐፍት ሳይሆን እንደ ባለሥልጣን ያስተምራቸው ስለነበረ ሕዝቡ በትምህርት አሰጣጡ እጅግ ተደነቁ።” (ማር. 1:22) በኢየሱስ ዘመን የነበሩት ጸሐፍት የሚያስተምሩት ታዋቂ ረቢዎች የተናገሩትን ሐሳብ በመጥቀስ ነበር። በአንጻሩ ግን ኢየሱስ ይጠቅስ የነበረው በመንፈስ መሪነት ከተጻፈው የአምላክ ቃል ላይ ነው። የአምላክ ልጅ እንደመሆኑ መጠን በሰማይ ሲኖር ያካበተውን እውቀት ተጠቅሞ ከአእምሯቸው በላይ የሆነ ነገር በመናገር አድማጮቹን ማስደመም ይችል ነበር። እሱ ግን እንደዚህ አላደረገም። ከዚህ ይልቅ፣ ቅዱሳን መጻሕፍትን ተጠቅሞ አምላክ የሚጠብቅባቸውን ነገር አስተምሯቸዋል። (ዮሐንስ 7:14-16ን አንብብ።) በእርግጥም ኢየሱስ ለተከታዮቹ ግሩም ምሳሌ ትቶላቸዋል።

8. ሐዋርያው ጴጥሮስ የኢየሱስን ምሳሌ የተከተለው እንዴት ነው?

8 የኢየሱስ ደቀ መዛሙርትም በሚያስተምሩበት ጊዜ የአምላክን ቃል ይጠቀሙ ነበር። በ33 ዓ.ም. በዋለው የጴንጤቆስጤ ዕለት ሐዋርያው ጴጥሮስ የሰጠውን ንግግር እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ጴጥሮስ የተማረ ሰው አልነበረም። ሆኖም የአምላክን ቃል ተጠቅሞ በኢየሱስ ላይ ፍጻሜያቸውን ያገኙ ትንቢቶችን ባብራራበት ወቅት ብዙዎች ልባቸው ተነክቷል። (ሥራ 2:14-37) “ስለዚህ ቃሉን በደስታ የተቀበሉ ተጠመቁ፤ በዚያም ቀን 3,000 ገደማ የሚሆኑ ሰዎች ተጨመሩ።”—ሥራ 2:41

9. ሰዎችን ስናስተምር መጽሐፍ ቅዱስን መጠቀም ያለብን ለምንድን ነው?

9 የሰዎችን ልብ ለመንካት የሚያስችለን ከሁሉ የተሻለው መሣሪያ የአምላክ ቃል ነው። (ዕብ. 4:12) በመሆኑም ስናስተምር መጽሐፍ ቅዱስን መጠቀም ይኖርብናል። የራሳችንን ሐሳብ ሳይሆን ‘ቃሉን ልንሰብክ’ ይገባል። (2 ጢሞ. 4:2) ምሳሌ 2:6 “ይሖዋ ራሱ ጥበብ ይሰጣል . . . ከአፉ እውቀትና ጥልቅ ግንዛቤ ይወጣል” ይላል። መጽሐፍ ቅዱስን ተጠቅመን ስናስተምር ይሖዋ እንዲናገር አጋጣሚውን እየሰጠነው ነው ሊባል ይችላል። (ሚል. 2:7) የምናስተምራቸው ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ሰዎች ከሚሰጡት ከማንኛውም ምክር እጅግ የላቀ እንደሆነ እንዲያውቁ እንፈልጋለን። መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው በአምላክ መንፈስ መሪነት ነው፤ በተጨማሪም ፈጣሪያችንን ማስደሰት እንዲሁም አስደሳችና አርኪ ሕይወት መምራት የምንችለው እንዴት እንደሆነ ያስተምረናል።—2 ጢሞ. 3:16, 17

10. ጥናታችን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንዲያተኩር መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?

10 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመምራት ስትዘጋጁ ጥናታችሁ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንዲያተኩር መርዳት የምትችሉባቸውን መንገዶች አስቡ። ሥዕሎችና ቪዲዮዎች ትምህርቱን ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ እንደሚረዱ የታወቀ ነው፤ ሆኖም ጥናታችሁ በዋነኝነት እየተማረ ያለው መጽሐፍ ቅዱስን እንደሆነ ሊረዳ ይገባል። በመሆኑም ቁልፍ ጥቅሶችን አውጥታችሁ አንብቡ፤ እንዲሁም ጥናታችሁ የጥቅሶቹ ዓላማ እንዲገባው እርዱት። ሥዕል ወይም ቪዲዮ ስትጠቀሙ ጥናታችሁ በዚያ ሥዕል ወይም በዚያ ቪዲዮ አማካኝነት እንዲማር የተፈለገው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በደንብ የገባው መሆኑን አረጋግጡ። ይህን ለማድረግ ብዙ ማውራት ወይም ብዙ ጥቅስ ማንበብ አያስፈልጋችሁም። ከዚህ ይልቅ አንድን ጥቅስ ካነበባችሁ በኋላ ጥናታችሁ የጥቅሱን ትርጉም በደንብ እንዲረዳ ጊዜ ስጡት፤ ካስፈለገም ጥቅሱን በድጋሚ አንብቡት። እንዲህ ካደረጋችሁ የምታስጠኑት አንድን መጽሐፍ፣ አንድን ሥዕል ወይም አንድን ቪዲዮ ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱስን ይሆናል።—1 ቆሮ. 2:13

11-12. (ሀ) የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችንን በትዕግሥት መያዝ የምንችለው እንዴት ነው? (የሐዋርያት ሥራ 17:1-4) (ሥዕሉንም ተመልከት።) (ለ) አንዳንዶች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ያላቸው እውቀት ምን ያህል ነው? ልንረዳቸው የምንችለውስ እንዴት ነው?

11 ጥናታችሁ አንድን ትምህርት መረዳት ከከበደው ቃሉን መስበክ “ብዙ ትዕግሥት” እንደሚፈልግ አስታውሱ። ጥናቶች እድገት የሚያደርጉበት ፍጥነት ይለያያል። አንዳንድ ጥናቶች እኛ በቀላሉ የምንረዳቸውን እውነቶች ለመረዳት ብዙ ጊዜ ሊወስድባቸው ይችላል። ጳውሎስ በተሰሎንቄ ለነበሩት አይሁዳውያን ሲሰብክ አንዳንዶቹ የሚያስተምራቸውን ነገር የተረዱት በተደጋጋሚ ካስተማራቸውና ከቅዱሳን መጻሕፍት ላይ እየጠቀሰ ካብራራላቸው በኋላ ነው።—የሐዋርያት ሥራ 17:1-4ን አንብብ።

12 የጥናቶቻችንን አመለካከት ለመረዳት ጥረት በምናደርግበት ጊዜም ትዕግሥት ማሳየት ያስፈልገናል። ጥያቄዎችን ጠይቋቸው፤ ከዚያም መልስ እስኪሰጡ ድረስ በትዕግሥት ጠብቋቸው። በሚናገሩበት ጊዜም በጥሞና አዳምጧቸው፤ እንደዚያ የተሰማቸው ለምን እንደሆነ ለመረዳት ሞክሩ። ከዚያም ይሖዋ ስለ ጉዳዩ ያለውን አመለካከት እንዲገነዘቡ ለመርዳት አንዳንድ ጥቅሶችን አንብባችሁ አወያዩአቸው። ልናስታውስ የሚገባን ሌላም ነገር አለ፤ አንዳንድ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደያዘ ወይም ስለ ምን እንደሚናገር ጨርሶ አያውቁም። ስለዚህ በአዲስ ዓለም ትርጉም መግቢያ ላይ ያለውን “ከአምላክ ቃል ጋር ተዋወቅ” የሚለውን ክፍል በማሳየት መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ጠቃሚ ትምህርቶችን እንደያዘ ልትነግሯቸው ትችላላችሁ። ከዚያም በጥያቄ 15 ሥር ከተዘረዘሩት ጥቅሶች መካከል አንዱን ወይም ሁለቱን በማንበብ መጽሐፍ ቅዱስ በሕይወታችን ደስተኛ እንድንሆን የሚረዳን እንዴት እንደሆነ ልታስረዷቸው ትችላላችሁ። የአምላክ ቃል ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ ለጥናቶቻችን ካስገነዘብናቸው ውጤታማ አስተማሪዎች እንሆናለን።

ቀደም ባለው ሥዕል ላይ የነበረችው እህት ሲጋራ ስታጨስ የነበረችውን ወጣት ደጅ ያለ አግዳሚ ወንበር ላይ ተቀምጣ መጽሐፍ ቅዱስ ስታስጠናት። ወጣቷ ስሜቷን ስትገልጽ እህት በጥሞና ታዳምጣታለች።

ጎበዝ አስተማሪ ብዙ ከማውራት ይልቅ ጊዜ ሰጥቶ ያዳምጣል (አንቀጽ 11-12ን ተመልከት)


በይሖዋ ላይ እንዲያተኩሩ እርዷቸው

13. ሰዎችን በምናስተምርበት ወቅት ትኩረታቸው በማን ላይ እንዲያርፍ ማድረግ ይኖርብናል? በምሳሌ አስረዳ።

13 ዓላማችን የምናስተምራቸው ሰዎች ይሖዋን እንዲያውቁና ወደ እሱ እንዲቀርቡ መርዳት ነው። (ያዕ. 4:8) ከዚህ አንጻር ሥራችን ቲያትር ቤት ውስጥ የመድረኩን መብራት የሚቆጣጠረው ሰው ከሚያከናውነው ሥራ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። የመብራት ተቆጣጣሪው ቲያትሩ በሚታይበት ወቅት መብራቱን የሚያበራው በራሱ ላይ አይደለም። ከዚህ ይልቅ በተዋንያኑ ላይ በማብራት ተመልካቾች በደንብ እንዲያዩአቸው ያደርጋል። እኛም በተመሳሳይ ሰዎችን በምናስተምርበት ወቅት ትኩረታቸው እንዲያርፍ የምንፈልገው በእኛ ላይ ሳይሆን በይሖዋ ላይ ነው።

14. ጥናቶቻችን በይሖዋ ላይ እንዲያተኩሩ ልንረዳቸው የምንችለው እንዴት ነው?

14 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በምትመሩበት ወቅት ጥናታችሁ ይሖዋን የማስደሰት ፍላጎት እንዲያድርበት ልትረዱት ይገባል። (ምሳሌ 27:11) የመጽሐፍ ቅዱስን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች መከተል አንድ ድርጅት ውስጥ ለመግባት የሚያስፈልጉትን ብቃቶች የማሟላት ጉዳይ ብቻ አይደለም። ጥናታችሁ ለውጥ ማድረግ ያለበት ይሖዋን ለማስደሰት ባለው ፍላጎት ተነሳስቶ ነው። ለምሳሌ ጥናታችሁ አንድን መጥፎ ልማድ ለማሸነፍ ከተቸገረ እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎችን ልትጠይቁት ትችላላችሁ፦ “ይሖዋ ይህን ድርጊት የሚጠላው ለምንድን ነው? ይሖዋ ይህን ነገር እንደምትወደው እያወቀ እንድትተወው የሚጠብቅብህ ለምንድን ነው? ይሖዋ ይህን መመሪያ የሰጠህ መሆኑ እንደሚወድህ የሚያሳየው እንዴት ነው?” ጥናታችሁ ስለ ይሖዋ ይበልጥ እንዲያስብ ከረዳችሁት ይሖዋን እንደ አፍቃሪ አባቱ አድርጎ መመልከት ይጀምራል። ይህ ደግሞ ይሖዋን የማስደሰት ልባዊ ፍላጎት እንዲያድርበት ያደርጋል።

የማስተማር ችሎታችሁን ማሻሻላችሁን ቀጥሉ

15. የማስተማር ችሎታችንን ማሻሻላችንን ለመቀጠል ምን ይረዳናል?

15 ይሖዋ የማስተማር ችሎታችንን ለመገምገምና ማሻሻል የምንችልባቸውን አቅጣጫዎች ለማስተዋል እንዲረዳን በጸሎት ልንጠይቀው እንችላለን። (1 ዮሐ. 5:14) ከዚያም ይሖዋ በጉባኤ ስብሰባዎች አማካኝነት የሚሰጠንን ሥልጠና በቁም ነገር በመመልከት ከጸሎታችን ጋር የሚስማማ እርምጃ እንወስዳለን። በተጨማሪም ጥናት በምንመራበት ወቅት ጥሩ የማስተማር ችሎታ ያላቸውን ወንድሞችና እህቶች መጋበዝ ከዚያም ሐሳብ እንዲሰጡን መጠየቅ እንችላለን። ከዚህም ሌላ፣ ትምህርቱ ለእኛ በጣም ቀላል ቢሆንም እንኳ ለጥናታችን ከባድ ሊሆንበት እንደሚችል ማስታወስ ይኖርብናል። ለጥናቱ ስንዘጋጅ ራሳችንን በእሱ ቦታ ለማስቀመጥ መሞከራችን ተገቢ ነው። ጥናታችን ትምህርቱ በግለሰብ ደረጃ እንደሚጠቅመውና በእርግጥም የምሥራች እንደሆነ እንዲገነዘብ ልንረዳው ይገባል። ትምህርቱ ከይሖዋ ጋር የቅርብ ወዳጅነት እንዲመሠርት እንዲሁም ደስተኛ እንዲሆን ይረዳዋል።—መዝ. 1:1-3

16. የማስተማር ችሎታችንን ማሻሻላችንን መቀጠል ያለብን ለምንድን ነው?

16 ሌሎችን ስለ ይሖዋ ማስተማር በጣም የሚያስደስት ነገር ነው። ይህ አስደሳች ሥራ በአዲሱ ዓለም ውስጥም በስፋት ይቀጥላል። እንግዲያው ለምናስተምራቸው ሰዎች ማሰባችንን፣ የአምላክን ቃል መጠቀማችንን እንዲሁም ጥናቶቻችን በይሖዋ ላይ እንዲያተኩሩ መርዳታችንን እንቀጥል። እንዲህ ካደረግን በአገልግሎት ላይ የማስተማር ችሎታችንን ማሻሻል እንችላለን።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

  • ለምናስተምራቸው ሰዎች እንደምናስብላቸው ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

  • የምናስተምራቸው ሰዎች በአምላክ ቃል ላይ እንዲያተኩሩ መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?

  • የምናስተምራቸው ሰዎች በይሖዋ ላይ እንዲያተኩሩ መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?

መዝሙር 65 ወደፊት ግፋ!

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2026)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2026 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ