የሕይወት ታሪክ
ለ70 ዓመታት በኩባ ይሖዋን ማገልገል
የተወለድኩት በ1947 ውብ በሆነችው የኩባ ደሴት ነው። ኩባ የምትገኘው በካሪቢያን ባሕርና በአትላንቲክ ውቅያኖስ መካከል ነው። ወላጆቼ ከእኔ በኋላ ሁለቱን ታናናሽ እህቶቼን ወለዱ። የምንኖረው በኤስመራልዳ መንደር ነበር።
በትንሿ መንደራችን ውስጥ ያለን ሕይወት ሰላማዊ ነበር። አክስቶቻችንን፣ አጎቶቻችንንና አያቶቻችንን ጨምሮ አንዳንድ ዘመዶቻችን የሚኖሩት በአቅራቢያችን ነው። የምንበላው አጥተን አናውቅም። በሕይወታችንም ደስተኞች ነበርን።
የአምስት ዓመት ልጅ እያለሁ ወላጆቼ ከዎልተን ጆንስ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመሩ። ዎልተን ቀናተኛ ወንጌላዊ ሲሆን ወደ እኛ መንደር የሚመጣው ለአሥር ሰዓት ገደማ በእግሩ ተጉዞ ነው። እሱ በመጣ ቁጥር ብዙዎቹ የቤተሰቤ አባላት በአያቶቼ ቤት ተሰብስበው ለሰዓታት ከእሱ ጋር ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ይወያያሉ። ወላጆቼ እንዲሁም አጎቴ ፔድሮ እና አክስቴ ኤላ የሚማሩትን ነገር ወደዱት፤ ብዙም ሳይቆይ ተጠምቀው የይሖዋ ምሥክሮች ሆኑ። አሁን ኤላ ዕድሜዋ ወደ 100 ዓመት እየተጠጋ ቢሆንም ኩባ ውስጥ በአቅኚነት እያገለገለች ነው።
በወቅቱ ኩባ ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች በነፃነት አምልኳቸውን ማከናወን ይችሉ ነበር። የምንታወቀው በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች የተሞላ ቦርሳ ይዘን ከቤት ወደ ቤት በማገልገል ነው። ደግሞም በእግራችን በጣም ብዙ እንጓዝ ነበር። በዚያ ‘አመቺ ጊዜ’ ይሖዋን ማገልገል በጣም ያስደስታል። በኋላ ግን “አስቸጋሪ ጊዜ” ተከተለ።—2 ጢሞ. 4:2
አስቸጋሪ ጊዜ መጣ
በዚያው ዓመት አባቴና አጎቴ በአንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ወደ ሌላኛው የደሴቲቱ ክፍል ተጓዙ። የሚያሳዝነው በዚያ ጉዞ ወቅት በጠጡት የተበከለ ውኃ የተነሳ ሁለቱም ታይፎይድ ያዛቸው። ከተመለሱ በኋላ አጎቴ ፀጉሩ ቢረግፍም በሕይወት ተረፈ። አባቴ ግን ሞተ። በወቅቱ ገና 32 ዓመቱ ነበር።
አባቴ ከሞተ በኋላ እናቴ እኛን ይዛ በሎምቢዮ መንደር ወደሚኖረው ወንድሟ ቤት ለመግባት ወሰነች። በዚህም ምክንያት፣ በጣም የምንወዳቸውን አያቶቻችንን ጨምሮ ከዘመዶቻችን ለመለየት ተገደድን። ሆኖም በቤተሰብ ደረጃ ይሖዋን ማገልገላችንን አላቆምንም።
ነሐሴ 26, 1957 በሎምቢዮ አቅራቢያ በሚገኝ ሰው ሠራሽ ሐይቅ ውስጥ ተጠመቅኩ። ያኔ አሥር ዓመቴ ነበር። ሆኖም ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በኩባ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ያልተጠበቀ ለውጥ አጋጠማቸው። በ1959 የኩባ መንግሥት ተገልብጦ በኮሚኒስት አገዛዝ ተተካ።
አዲሱ መንግሥት ለወታደራዊ አገልግሎት ትልቅ ቦታ ይሰጥ ነበር። ይህ ደግሞ ለይሖዋ ምሥክሮች አስቸጋሪ ሁኔታ ፈጠረባቸው። ምክንያቱም በመላው ዓለም ያሉ የይሖዋ ሕዝቦች በፖለቲካዊና በወታደራዊ ጉዳዮች ረገድ ገለልተኛ ናቸው። በዚህም የተነሳ ለረጅም ጊዜ የነበረንን የአምልኮ ነፃነት ደረጃ በደረጃ አጣን። ውሎ አድሮ መንግሥት በይሖዋ ምሥክሮች ላይ እገዳ ጣለ። በመቶዎች የሚቆጠሩ ታማኝ ወንድሞች እስር ቤት ገብተዋል። አንዳንዶቹ ብዙ ጊዜ ይደበደቡና ምግብ ይከለከሉ ነበር። አንዳንድ ጊዜ የሚቀርበው ምግብ በውስጡ ደም ነበረው፤ መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ እንዲህ ያለውን ምግብ መብላት እንደሌለብን ይናገራል።
አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢኖሩም ለአምልኮ መሰብሰባችንን ቀጠልን። (ዕብ. 10:25) በእርሻዎችና በሌሎች ቦታዎች ትላልቅ ስብሰባዎችንም እናደርግ ነበር። በአንድ ወቅት ትልቅ የበጎች ጉረኖ ያለው አንድ ወንድም ጉረኖው ውስጥ ትልቅ ስብሰባ እንድናደርግ ፈቀደልን። ከስብሰባው በፊት ጉረኖውን ማጽዳትም ሆነ በጎቹን ከዚያ ማውጣት አልቻልንም። እንደዚያም ሆኖ፣ እውነተኛ በጎችና ምሳሌያዊ በጎች አንድ ላይ ሆነን ስብሰባችንን አደረግን!—ሚክ. 2:12
በዚያ ዘመን መንፈሳዊ ምግብ እንዳይጎድልብን ተግተው ለሚሠሩት ወንድሞች ከፍተኛ አድናቆት ነበረን። ለምሳሌ የትላልቅ ስብሰባ ንግግሮች አስቀድመው በካሴት ተቀድተው በመላዋ አገሪቱ ይሰራጩ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ሁሉንም የስብሰባውን ንግግሮች ተዘጋጅተው የሚያቀርቡትና የሚቀዱት ሁለት ወንድሞች ብቻ ናቸው። ወንድሞች ንግግሮቹን የሚቀዱት ተደብቀው ስለሆነ አንዳንድ ጊዜ ዶሮ ሲጮኽ ወይም ሌሎች አስቂኝ ድምፆችን ከጀርባ እንሰማለን። ስብሰባውን የምናደርግበት ቦታ ኤሌክትሪክ ከሌለው ዲናሞ የተገጠመለትን የማይንቀሳቀስ ብስክሌት ፔዳል የሚመታ አንድ ወንድም ይመደባል። በዚህ መንገድ የካሴት ማጫወቻውን ለማሠራት የሚያስችል የኤሌክትሪክ ኃይል እናገኛለን። በሌሎች አገሮች የሚኖሩትን የእምነት አጋሮቻችንን ያህል የተመቻቸ ሁኔታ ወይም ብዙ የታተሙ ጽሑፎች ባይኖሩንም የሚያስፈልገንን መንፈሳዊ ምግብ አጥተን አናውቅም። ይሖዋን በአንድነት ማገልገል የሚያስገኘውን ደስታም ማጣጣም ችለናል።—ነህ. 8:10
አቅኚነትና ወላጅነት
አሥራ ስምንት ዓመት ሲሞላኝ በፍሎሪዳ ከተማ የዘወትር አቅኚ ሆኜ ማገልገል ጀመርኩ። ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ ደግሞ የግዛቱ ዋና ከተማ በሆነችው በካማግዌ ልዩ አቅኚ ሆኜ እንዳገለግል ተመደብኩ። ከኤሚሊያ ጋር የተዋወቅነው እዚያ ነው። ኤሚሊያ ከሳንቲያጎ ዴ ኩባ የመጣች ቆንጆ እህት ነች። ከእሷ ጋር መጠናናት ጀመርን፤ ከዚያም በአንድ ዓመት ውስጥ ተጋባን።
(በስተ ግራ) ለሽማግሌዎች የተዘጋጀ የመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት—ካማግዌ፣ ኩባ፣ 1966
(በስተ ቀኝ) በሠርጋችን ዕለት፣ 1967
በአገሪቱ ካሉት በርካታ የመንግሥት የስኳር ፋብሪካዎች በአንዱ ተቀጥሬ መሥራት ጀመርኩ። እኔና ኤሚሊያ በአቅኚነት መቀጠል ባንችልም በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች በተቻለ መጠን ብዙ ሰዓት ማሳለፍ እንፈልግ ነበር። ስለዚህ ከሌሊቱ 9 ሰዓት እስከ ረፋዱ 5 ሰዓት የሚሠራበትን ፈረቃ መረጥኩ። በሌሊት መነሳት ባያስደስተኝም ይህ የሥራ ፕሮግራም በአገልግሎት አዘውትሬ ለመካፈልና ከኤሚሊያ ጋር በሁሉም ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት አስችሎኛል።
በ1969 የመጀመሪያ ልጃችን ጉስታቮ ተወለደ። በዚያው ጊዜ አካባቢ በወረዳ ሥራ እንድንካፈል ተጋበዝን። በወቅቱ ኩባ ውስጥ ልጆች ያላቸው ወንድሞች የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆነው ማገልገላቸው የተለመደ ነገር ነበር። በሕይወታችን ውስጥ በጣም ደስተኛ የነበርንበትም ሆነ በሥራ የተወጠርንበት ዘመን ያ ነው። እኔና ኤሚሊያ በዚህ መንገድ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን የማገልገል አጋጣሚ ማግኘታችን በረከት እንደሆነ ይሰማናል። በወረዳ ሥራ በተካፈልንባቸው ቀጣይ ዓመታት ኦቤድ እና አብነር የተባሉ ሌሎች ልጆችን ወለድን፤ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ደግሞ ሴት ልጃችን ማሄሊ ተወለደች።
በወረዳ ሥራ ያሳለፍነውን ጊዜ መለስ ብዬ ሳስብ በጣም ደስ ይለኛል። ምክንያቱም ይሖዋ በኩባ ያሉትን ሕዝቦቹን እንዴት እንደባረካቸው አይቻለሁ። እኛም እሱን የሚወዱ ልጆችን ለማሳደግ ያደረግነውን ጥረት ባርኮልናል። በዚያ ዘመን በወረዳ ሥራ መካፈል ምን እንደሚመስል ጥቂት ልንገራችሁ።
በእገዳው ወቅት በወረዳ ሥራ መካፈል
በ60ዎቹና በ70ዎቹ በእገዳው ምክንያት መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ይበልጥ ከባድ እየሆነ መጣ። የስብሰባ አዳራሾቻችን ተዘጉ። ሚስዮናውያን ከአገሪቱ ተባረሩ። በርካታ ወጣት ወንድሞች ታሰሩ። በሃቫና የነበረው ቅርንጫፍ ቢሮም ተዘጋ።
በወረዳ ሥራ ስንካፈል፣ 1990ዎቹ
በእገዳው ምክንያት ጉባኤዎችን መጎብኘት የምንችለው ቅዳሜና እሁድ ብቻ ነበር። ስለዚህ አንድን ጉባኤ ቅዳሜና እሁድ ላይ ከጎበኘን በኋላ በቀጣዩ ቅዳሜና እሁድም ተመልሰን እንሄዳለን። በምንጓዝበት ጊዜ ብዙ ዕቃ አንይዝም። በተጨማሪም የፖሊሶችን ትኩረት ላለመሳብ ስንል ብዙውን ጊዜ የምንጓዘው በብስክሌት ነበር። ጉብኝቱ የሚካሄደው በሚስጥር ነው። ዘመዶቻችንን የምንጠይቅ መስለን ነው የምንሄደው። ይህን ማድረግ በጣም ቀላል ነበር። እንዲያውም ከወንድሞችና ከእህቶች ጋር ልክ እንደ ቤተሰብ ከመቀራረባችን የተነሳ የሄድነው ለወረዳ ሥራ መሆኑን እንዳንረሳ መጠንቀቅ ነበረብን። (ማር. 10:29, 30) ብዙ ጊዜ ፖሊሶች ይከታተሉንና በጥያቄ ያፋጥጡን ነበር። ማንነታችን ከታወቀ ቤታቸው ያስተናገዱን ወንድሞች ሊታሰሩ ይችላሉ። ስለዚህ በጣም መጠንቀቅ አስፈልጎናል።—ሮም 16:4
በዚያ ወቅት፣ በቁሳዊ ድሆች ቢሆኑም አስደናቂ ልግስና ከሚያሳዩ በርካታ ወንድሞችና እህቶች ጋር ተገናኝተናል። በአንዳንዶቹ አካባቢዎች ቢንቢዎች በጣም ያስቸግራሉ። ሆኖም የሚያስተናግዱን ወንድሞች ተመችቶን እንድናድር ሲሉ በቤቱ ያለውን ብቸኛ አጎበር ለእኛ ይሰጡናል። አንዳንዶቹ ደግሞ የሚበላ ነገር ባይኖራቸውም እኛን በእንግድነት ለመቀበል ፈቃደኞች ነበሩ። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ ከሚያስተናግዱን ወንድሞች ጋር አብረን የምንበላው ምግብ ከቤታችን ይዘን እንሄድ ነበር።
ጉባኤዎችን ስንጎበኝ ሁሉንም ልጆቻችንን ይዘን መሄድ አንችልም። ስለዚህ አንዱን ልጅ ብቻ ይዘን እንሄዳለን። እናቴና እህቴ ደግሞ የቀሩትን ልጆች ይንከባከቡልናል። ደግሞም ልጅ ይዘን መሄዳችን ጥበቃ ሆኖልናል። አንዳንድ ጊዜ ፖሊሶች ይፈትሹን ነበር። ግን ጽሑፎቻችንን ቆሻሻ ሽንት ጨርቅ የምናስቀምጥበት ቦርሳ ውስጥ እንደብቃቸዋለን። ፖሊሶቹ ደግሞ ያንን አይፈትሹም።
ኤሚሊያ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ባሳለፍናቸው ዓመታት ልጆቻችንን ለመንከባከብም ሆነ እኔን ለመደገፍ ላደረገችው ነገር ሁሉ ላመሰግናት እፈልጋለሁ። እኔም በስኳር ፋብሪካው ውስጥ የነበረኝን ሥራ ከወረዳ ሥራ ጋር ጎን ለጎን ማስኬድ ችያለሁ። እንዴት መሰላችሁ? አንዳንድ ጊዜ ቅዳሜና እሁድን ነፃ ለመሆን ስል በሳምንት አንዴ ወይም ሁለቴ ሁለት ፈረቃ እሠራለሁ። በኋላ ግን የሥራ ምድቤ ተቀይሮ የቡድን ኃላፊ ሆንኩ። ስለዚህ በሳምንት ሰባት ቀን መሥራት ይጠበቅብኝ ነበር። የሥራ ፕሮግራሙን መቀበል ግዴታዬ ነበር። ሆኖም ከቡድኔ አባላት ጋር በመነጋገር ለቅዳሜና ለእሁድ የሚበቃ ሥራ እስከሰጠኋቸው ድረስ ጉባኤዎችን በምጎበኝበት ጊዜ ሥራ ባልገባም ችግር እንደሌለው ተስማማን። እስከማውቀው ድረስ አለቆቼ ቅዳሜና እሁድ ሥራ እንደማልገባ አላስተዋሉም።
ለውጥን በደስታ ማስተናገድ
እገዳው ከተነሳ በኋላ ያደረግነው የመጀመሪያ ትልቅ ስብሰባ፣ 1994
በ1994 ኩባ ውስጥ ሥራውን በኃላፊነት ይመሩ የነበሩት ወንድሞች ሁሉም ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ሃቫና ውስጥ በሚደረግ አንድ ልዩ ስብሰባ ላይ እንዲገኙ ጋበዙ። በወቅቱ በአገሪቱ ውስጥ 80 ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ነበርን። ከዚያ ሁሉ ዓመት በኋላ መገናኘት በመቻላችን በጣም ደስ አለን! በስብሰባው ላይ መጀመሪያ ድርጅቱ ስላደረጋቸው አንዳንድ ማስተካከያዎች ተወያየን። ከዚያም አንድ አስደንጋጭ ማስታወቂያ ሰማን። ወንድሞች ስማችንን ለባለሥልጣናቱ ለመስጠት እንዳሰቡ ነገሩን። ግን ለምን?
ወንድሞች፣ በመንግሥትና በይሖዋ ምሥክሮች መካከል ያለውን ግንኙነት ማሻሻል ስለሚቻልበት መንገድ ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ሲወያዩ እንደቆዩ ነገሩን። ባለሥልጣናቱ የሁሉም የወረዳ የበላይ ተመልካቾች ስም እንዲሰጣቸው ጠይቀው ነበር። ሁላችንም ስማችን እንዲሰጥ ተስማማን። ከዚያ ጊዜ አንስቶ ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር የተደረጉት ውይይቶች ግሩም ውጤት አስገኝተዋል።
ውሎ አድሮ በነፃነት መሰብሰብና መስበክ ቻልን። ሆኖም እንደ ሃይማኖት ድርጅት ገና እውቅና አላገኘንም ነበር። በኋላ እንደተገነዘብነው፣ ለካስ ባለሥልጣናቱ የአንዳንዶቹን ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ስም ቀድሞውንም ያውቁ ነበር። የጠየቁት ማረጋገጫ ስለፈለጉ ነው።
መስከረም 1994 በድጋሚ ቅርንጫፍ ቢሮ እንድናቋቁም ፈቃድ ተሰጠን። ከ20 ዓመት በፊት እንጠቀምበት የነበረውን ያንኑ ሕንፃ በድጋሚ መጠቀም ቻልን።
ከዚያም በ1996 እኔና ኤሚሊያ አንድ ስልክ ተደወለልንና በቤቴል እንድናገለግል ግብዣ ቀረበልን። መጀመሪያ ላይ በጣም ደንግጬ ነበር። ራሴን ካረጋጋሁ በኋላ ለወንድሞች ገና ከቤት ያልወጡ ሁለት ልጆች እንዳሉኝና እነሱን ማሳደግ እንደሚጠበቅብኝ ነገርኳቸው። ወንድሞች በደግነት ሁኔታዬን ከግምት ካስገቡ በኋላ እንደዚያም ቢሆን ቤቴል እንድናገለግል እንደሚፈልጉ ነገሩኝ። እኛም ግብዣውን ተቀብለን በቤተሰብ ደረጃ ወደ ሃቫና ለመዛወር ዝግጅት ማድረግ ጀመርን።
(በስተ ግራ) ኤሚሊያ በኩባ ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ በልብስ ስፌት ክፍል ስትሠራ፣ የ2000ዎቹ መጀመሪያ
(በስተ ቀኝ) የትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሽ ውሰና፣ 2012
እውነቱን ለመናገር፣ መጀመሪያ ላይ የቤቴል አገልግሎት አስደሳች አልሆነልኝም። በወረዳ ሥራ በጣም ብዙ ዓመት ስላሳለፍኩ ልቤ ያለው እዚያ ነበር። ዴስክ ጋ ተቀምጬ መዋል ከበደኝ። ሆኖም አብረውኝ የሚያገለግሉት ቤቴላውያን፣ በተለይ ደግሞ ባለቤቴ ኤሚሊያ አመለካከቴን እንዳስተካክል ረዱኝ። በጊዜ ሂደት ደስታዬን መልሼ ማግኘት ቻልኩ። አሁን ቤቴል ውስጥ በደስታ እያገለገልኩ ነው።
(በስተ ግራ) ለክርስቲያን ባለትዳሮች የተዘጋጀው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት የምረቃ ፕሮግራም፣ 2013
(በስተ ቀኝ) የኩባ ቅርንጫፍ ኮሚቴ፣ 2013
ከሴት ልጃችንና ከባለቤቷ ጋር በወረዳ ስብሰባ ላይ
አሁን እኔና ኤሚሊያ ዕድሜያችን ገፍቷል። ሆኖም ባለፉት ዓመታት ከበርካታ ወንድሞችና እህቶች ጋር የመተዋወቅ እንዲሁም ከእነሱ ጋር አብረን ይሖዋን የማገልገል መብት በማግኘታችን በጣም ደስተኞች ነን። በተለይ ደግሞ ልጆቻችንና የልጅ ልጆቻችን ይሖዋን ሲያገለግሉ ማየት በጣም ያስደስተናል። አረጋዊው ሐዋርያ ዮሐንስ በተናገረው ሐሳብ እንስማማለን፤ እንዲህ ብሏል፦ “ልጆቼ በእውነት ውስጥ እየተመላለሱ መሆናቸውን ከመስማት የበለጠ ደስታ የለኝም።”—3 ዮሐ. 4
አሁን በቤቴል ማገልገል ከጀመርን 30 ዓመት ገደማ ሆኖናል። እኔና ኤሚሊያ በየዕለቱ ከእርጅናና ከካንሰር ጋር መታገል ቢያስፈልገንም አቅማችን በፈቀደ መጠን የተሰጠንን ሥራ ለማከናወን ጥረት እናደርጋለን። በይሖዋ አገልግሎት ባሳለፍናቸው ዓመታት አንዳንድ ተፈታታኝ ሁኔታዎች አጋጥመውናል። ሆኖም ‘ደስተኛውን አምላክ’ በኩባ ደሴት ለ70 ዓመት ያህል ማገልገል በመቻላችን በጣም ደስተኞች ነን!—1 ጢሞ. 1:11፤ መዝ. 97:1