ከሐምሌ 6-12, 2026
መዝሙር 98 ቅዱሳን መጻሕፍት በመንፈስ መሪነት የተጻፉ ናቸው
የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የሚጠቅሙን እንዴት ነው?
‘የማሰብ ችሎታችሁን ተጠቅማችሁ ቅዱስ አገልግሎት አቅርቡ።’—ሮም 12:1
ዓላማ
መሠረታዊ ሥርዓቶች ምንድን ናቸው? መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ነጥለን ማውጣት የምንችለውስ እንዴት ነው?
1-2. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው መቼ ነው? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ በዛሬው ጊዜም ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ጥንታዊ መጽሐፍ ነው። መጻፍ የጀመረው ከ3,500 ዓመታት ገደማ በፊት ሲሆን ተጽፎ የተጠናቀቀው ደግሞ ከ2,000 ዓመታት ገደማ በፊት ነው። ያም ቢሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው “የአምላክ ቃል” በዛሬው ጊዜም ሕያውና ኃይለኛ ነው። (ዕብ. 4:12፤ 2 ጢሞ. 3:16, 17) በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ዘመናዊ ዓለም ውስጥ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ለመቋቋም እንደረዳቸው ይናገራሉ።
2 ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ ጥንታዊ መጽሐፍ ከመሆኑ አንጻር በዘመናችን ጠቃሚ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው? ሁለት ዋና ዋና ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል። አንደኛ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት የመነጨው በጥበቡ ተወዳዳሪ ከሌለውና “ሕያው አምላክ” ከሆነው ከፈጣሪያችን ነው። (1 ጢሞ. 4:10፤ ሮም 16:26, 27) ሁለተኛ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ጊዜ የማይሽራቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶች ይዟል። እነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች ለየትኛውም ዘመንና ለየትኛውም ሁኔታ ይሠራሉ።
3. በዚህ ርዕስ ውስጥ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመልሳለን?
3 የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ምንድን ናቸው? በዛሬው ጊዜ በጣም የሚያስፈልጉን ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ነጥለን ማውጣት የምንችለውስ እንዴት ነው? ይህ ርዕስ እነዚህን ጥያቄዎች ይመልስልናል። በተጨማሪም የኢየሱስ ትምህርቶች መሠረታዊ ሥርዓቶች ያላቸውን ጥቅም የሚያሳዩት እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።
የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ምንድን ናቸው?
4. የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ምንድን ናቸው?
4 የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች መሠረታዊ እውነቶች ናቸው፤ የአምላክ ሕጎች የተመሠረቱት በእነዚህ እውነቶች ላይ ነው። አንዳንድ ጊዜ ሕጉ ራሱ መሠረታዊ ሥርዓት ሊሆን ይችላል። (ማቴ. 22:37) ሆኖም መሠረታዊ ሥርዓቶች ከቀጥተኛ ሕጎች ብልጫ አላቸው። ሕጎች ብዙውን ጊዜ የሚሠሩት ለተወሰነ ዘመን ወይም ለተወሰነ ሁኔታ ብቻ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ግን ለተለያዩ ሁኔታዎችና ለተለያዩ ዘመኖች ያገለግላሉ። (መዝ. 119:111) መሠረታዊ ሥርዓቶች ከሕግ በስተ ጀርባ ያሉ ምክንያቶች ሊባሉ ይችላሉ፤ እንዲሁም የይሖዋን አስተሳሰብ ይበልጥ ለመረዳት ያግዙናል። እያንዳንዱ የይሖዋ ሕግ ከበስተ ጀርባው መሠረታዊ ሥርዓት አለ። ሕጎች መቀየር ሊያስፈልጋቸው ይችላል፤ መሠረታዊ ሥርዓቶች ግን ዘመን አያልፍባቸውም።—ኢሳ. 40:8
5. በሕግና በመሠረታዊ ሥርዓት መካከል ያለውን ልዩነት በምሳሌ አስረዳ። (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)
5 በሕግና በመሠረታዊ ሥርዓት መካከል ያለውን ልዩነት ለመረዳት አንድ ምሳሌ እንመልከት። አንዲት እናት ለትንሽ ልጇ ‘ይሄን ምድጃ አትንካ’ ትለው ይሆናል። ይህ ትእዛዝ ወይም ሕግ ነው። ከዚህ ሕግ በስተ ጀርባ ያለው መሠረታዊ ሥርዓት ግን ‘ትኩስ ነገር አትንካ፤ አለዚያ ጉዳት ይደርስብሃል’ የሚል ነው። ይህ መሠረታዊ ሥርዓት የሚሠራው ለምድጃ ብቻ አይደለም። ከምጣድ፣ ከካውያ ወይም ከማንኛውም የሚያቃጥል ነገር ጋር በተያያዘም ይሠራል። በተጨማሪም ይህ መሠረታዊ ሥርዓት የሚሠራው እዚያ ቤት ውስጥ ላሉ ዕቃዎች ብቻ አይደለም። እርግጥ ነው፣ ልጁ እያደገ ሲሄድ ምድጃ መጠቀሙ አይቀርም። ያም ቢሆን፣ ምድጃውን በሚጠቀምበት ጊዜ እንዳያቃጥለው መጠንቀቅ ይኖርበታል። ስለዚህ ‘ይሄን ምድጃ አትንካ’ የሚለው ሕግ ሊቀየር ቢችልም ከበስተ ጀርባ ያለው መሠረታዊ ሥርዓት ግን አይቀየርም።
አንድ ሕግ ሊቀየር ቢችልም ከበስተ ጀርባው ያለው መሠረታዊ ሥርዓት ግን አይቀየርም (አንቀጽ 5ን ተመልከት)
የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች አስፈላጊ የሆኑት ለምንድን ነው?
6. (ሀ) ይሖዋ በቃሉ ውስጥ ምን ሰጥቶናል? (ለ) ይሖዋ እንደሚያከብረን ያሳየን እንዴት ነው?
6 ይሖዋ ስለሚወደን ከአደገኛ ሁኔታዎች እንድንጠበቅ የሚረዱ ቀጥተኛ ሕጎችን ሰጥቶናል። (ያዕ. 2:11) በተጨማሪም ከእነዚህ ሕጎች በስተ ጀርባ ያሉትን መሠረታዊ ሥርዓቶች እንድንገነዘብ ይረዳናል። በሕይወታችን ውስጥ ቀጥተኛ ሕግ ያልተሰጠባቸው ብዙ ሁኔታዎች ያጋጥሙናል። በዚህ ጊዜ ይሖዋ በቃሉ አማካኝነት ይመራናል። የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች በሕይወታችን ውስጥ ጥሩ ውሳኔዎችን እንድንወስንና ትክክል የሆነውን ነገር እንድናደርግ ይረዱናል። ይሖዋ መሠረታዊ ሥርዓቶችን የሰጠን መሆኑ እንደሚያከብረን ያሳያል፤ በተጨማሪም የራሳችንን ውሳኔ እንድናደርግ ነፃነት ሰጥቶናል፤ ይህም ለእሱና ለመሥፈርቶቹ ያለንን ፍቅር የምናሳይበት አጋጣሚ ይሰጠናል።—ገላ. 5:13
7. የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ያላቸውን ጥቅም የሚያሳይ ምሳሌ ጥቀስ። (ሥዕሉንም ተመልከት።)
7 የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የሚጠቅሙን እንዴት እንደሆነ ለመረዳት አንድ ምሳሌ እንመልከት። በአንዳንድ አገሮች ውስጥ ለአሽከርካሪዎች የተዘጋጁ የመንገድ ዳር ምልክቶች አሉ። አንዳንዶቹ ምልክቶች ቀጥተኛ መመሪያ የያዙ ናቸው። አሽከርካሪው በምን ያህል ፍጥነት መሄድ እንዳለበት ወይም እዚያ ቦታ ጋ ሲደርስ መቆም እንዳለበት የሚደነግጉ ሊሆኑ ይችላሉ። እነዚህን ምልክቶች መጣስ በሕግ ያስቀጣል። አንዳንዶቹ ምልክቶች ግን የማስጠንቀቂያ ምልክቶች ናቸው። መንገዱ አደገኛ ቁልቁለት እንደሆነ ወይም በአካባቢው ትምህርት ቤት እንዳለ የሚጠቁሙ ምልክቶች ሊሆኑ ይችላሉ። አንድ ጎበዝ ሹፌር እንዲህ ያሉ ምልክቶችን ሲያይ የማመዛዘን ችሎታውን በመጠቀም የጥንቃቄ እርምጃዎችን ይወስዳል። ለምሳሌ ዝናብ እየዘነበ ከሆነ ተጠንቅቆ ያሽከረክራል። በተመሳሳይም ክርስቲያኖች በአምላክ ቃል ውስጥ በግልጽ ከተከለከሉ ድርጊቶች ሙሉ በሙሉ ይርቃሉ፤ ይሁንና ከእነዚህ ብቻ ሳይሆን የአምላክን ሕግ ወደመጣስ ሊመራቸው ከሚችል ከማንኛውም አስተሳሰብም ሆነ ድርጊት መራቅ ይኖርባቸዋል። ይህ ደግሞ የማመዛዘን ችሎታ ይጠይቃል።
የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች በመንገድ ዳር ካሉ የማስጠንቀቂያ ምልክቶች ጋር ይመሳሰላሉ (አንቀጽ 7ን ተመልከት)
8. በሮም 12:1, 2 መሠረት የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ለማግኘት ጥረት ማድረጋችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?
8 የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ለማግኘት ጥረት ማድረግና በእነሱ መመራት የሚያስገኝልን ሌላም ጥቅም አለ። የይሖዋን አስተሳሰብ ማስተዋል እንድንችል ያሠለጥነናል። መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ ለሕይወታችን የሚጠቅሙ ትምህርቶችን ለማግኘት ጥረት እናደርጋለን። ይሖዋ እነዚህን ትምህርቶች በቃሉ ውስጥ ያካተተው ለምን እንደሆነ እንዲሁም ትምህርቶቹን በሥራ ላይ ማዋል የምንችለው እንዴት እንደሆነ ራሳችንን እንጠይቃለን። እንዲህ ስናደርግ ‘የማሰብ ችሎታችንን’ ተጠቅመን ይሖዋን ማገልገል የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንማራለን። “ጥሩ የሆነውን፣ ተቀባይነት ያለውንና ፍጹም የሆነውን የአምላክ ፈቃድ” መርምረን እናረጋግጣለን።—ሮም 12:1, 2ን አንብብ።a
9. በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች መመራታችን ሌላስ ምን ጥቅም ያስገኝልናል? (ዕብራውያን 5:13, 14)
9 በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች መመራታችን ጎልማሳ ክርስቲያኖች እንድንሆን ይረዳናል። በመሠረታዊ ሥርዓቶች ስንመራ ከይሖዋ ጋር ያለን ወዳጅነት ይጠናከራል። (ዕብራውያን 5:13, 14ን አንብብ።) ትናንሽ ልጆች በእያንዳንዱ ሁኔታ ውስጥ ምን ማድረግ እንዳለባቸው እንዲያውቁ ዝርዝር ሕግ ወይም መመሪያ ያስፈልጋቸዋል። እነዚህን ሕጎች የሚታዘዙት ደግሞ ቅጣት ፈርተው ብቻ ሊሆን ይችላል። ይሖዋ ግን እኛን የሚይዘን እንደ ትናንሽ ልጆች ሳይሆን እንደ ጎልማሳ ሰዎች ነው። ከፈቃዱ ጋር የሚስማማ ውሳኔ እንደምናደርግ ይተማመንብናል፤ እንዲህ ስናደርግ ደግሞ ልቡ እጅግ ይደሰታል።—መዝ. 147:11፤ ምሳሌ 23:15, 26፤ 27:11
የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ነጥለን ማውጣት የምንችለው እንዴት ነው?
10. የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ነጥለን ማውጣት የምንችለው እንዴት ነው?
10 መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ፣ ከምናነበው ነገር ትምህርት ለማግኘት ጥረት ካደረግን የይሖዋን አመለካከት ለማወቅ የሚያስችሉ መሠረታዊ ሥርዓቶችን እናገኛለን። መሠረታዊ ሥርዓቶችን ማግኘት የምንችልበት ሌላው መንገድ ደግሞ ከሕጎች በስተ ጀርባ ያለውን ምክንያት ለማወቅ ጥረት ማድረግ ነው። ከሕጎቹ በስተ ጀርባ ያለው ምክንያት በደንብ ሲገባን የይሖዋን አስተሳሰብ ይበልጥ መረዳት እንችላለን። ሆኖም የይሖዋን አስተሳሰብ ለመረዳት እሱ እንዲረዳን መጸለይ እንዲሁም የማመዛዘን ችሎታ ማዳበር ይኖርብናል። (ምሳሌ 2:10-12) እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎችን ራሳችንን መጠየቅ እንችላለን፦ ‘ይሖዋ ይህን ሕግ የሰጠው ለምንድን ነው? ይሖዋ ይህን ድርጊት የሚከለክል ከሆነ ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ስለሆኑ ሌሎች ድርጊቶችስ ምን ይሰማዋል? ከዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ምን ትምህርት አገኛለሁ? ትምህርቱን በሥራ ላይ ማዋል የምችለውስ እንዴት ነው?’ ከሕጎች በስተ ጀርባ ያለውን ምክንያት እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች የሚያስተላልፉትን ትምህርት ፈልገን ስናገኝ ከይሖዋ ፈቃድ ጋር የሚስማሙ ጥሩ ውሳኔዎችን ማድረግ እንችላለን።
11. ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ነጥለን ማውጣት የምንችልበትን መንገድ ያሳየን እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
11 ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ነጥለን ማውጣት የምንችለው እንዴት እንደሆነ አሳይቶናል። ሦስት ምሳሌዎችን እስቲ እንመልከት። በሦስቱም ምሳሌዎች ላይ ኢየሱስ በመጀመሪያ ሕጉን ከዚያም ከሕጉ በስተ ጀርባ ያለውን መሠረታዊ ሥርዓት ተናግሯል። ኢየሱስ በተናገረው ነገር ላይ ስናሰላስል እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች በዚህ ዘመናዊ ዓለም ውስጥ በሥራ ላይ ማዋል የምንችለው እንዴት እንደሆነ እናስተውላለን።
ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ ከአምላክ ሕጎች በስተ ጀርባ ያሉትን መሠረታዊ ሥርዓቶች ነጥለን ማውጣት የምንችልበትን መንገድ አሳይቶናል (አንቀጽ 11ን ተመልከት)
12. በማቴዎስ 5:21, 22 ላይ ከተጠቀሰው ሕግ በስተ ጀርባ ያለው አንዱ መሠረታዊ ሥርዓት ምንድን ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
12 ማቴዎስ 5:21, 22ን አንብብ። “አትግደል።” ከዚህ ሕግ በስተ ጀርባ ያለው አንዱ መሠረታዊ ሥርዓት ምንድን ነው? ይሖዋ ሌሎችን እንድንጠላ አይፈልግም፤ በድርጊታችን፣ በንግግራችን፣ ሌላው ቀርቶ በአስተሳሰባችንም እንኳ ጥላቻ ማሳየት የለብንም። ኢየሱስ ከተናገረው ነገር እንደምንረዳው፣ አንድ ሰው ነፍስ ባያጠፋም እንኳ ወንድሙን ከጠላ ከሕጉ በስተ ጀርባ ያለውን መሠረታዊ ሥርዓት ሊጥስ ይችላል። “በወንድሙ ላይ ተቆጥቶ ቁጣው የማይበርድለት” ከሆነ ወይም ወንድሙን ከተሳደበም ‘ተጠያቂ ይሆናል።’ ምክንያቱም ወደ ግድያ የሚያመሩት ስሜቶችና ድርጊቶች እነዚህ ናቸው።—1 ዮሐ. 3:15
13. በማቴዎስ 5:21, 22 ላይ የሚገኘውን መሠረታዊ ሥርዓት በሥራ ላይ ማዋል የምንችለው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
13 በማቴዎስ 5:21, 22 ላይ የሚገኘውን መሠረታዊ ሥርዓት በዛሬው ጊዜ ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ተቆጥተን ከመቆየት ወይም ቂም ከመያዝ መቆጠብ ይኖርብናል። (ዘሌ. 19:18፤ ኢዮብ 36:13) ለምን? ምክንያቱም እንዲህ ያለው ስሜት በልባችን ውስጥ ጥላቻ እንዲቀሰቀስ ሊያደርግ እንዲሁም ሌሎችን የሚጎዳ ነገር ወደመናገር ወይም ወደማድረግ ሊመራን ይችላል። (ምሳሌ 10:12) ይህም ሐሜትንና ስም ማጥፋትን ያካትታል። (ምሳሌ 20:19፤ 25:23) በኢየሱስ ዘመን መልእክት መላላኪያ አፕሊኬሽን፣ ማኅበራዊ ሚዲያ ወይም ኢንተርኔት አልነበረም። ሆኖም ኢየሱስ የተናገረው መሠረታዊ ሥርዓት ከእነዚህ ዘመናዊ መሣሪያዎች አጠቃቀም ጋር በተያያዘም ይሠራል። የጎለመሱ ክርስቲያኖች እነዚህን መሣሪያዎች በሚጠቀሙበት ጊዜ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው ይገነዘባሉ። በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ የሰዎችን ስም የሚያጠለሽ ነገር ከመናገር ወይም ከመጻፍ መቆጠብ ይኖርብናል።
(አንቀጽ 12-13ን ተመልከት)
14. በማቴዎስ 5:27, 28 ላይ ከተጠቀሰው ሕግ በስተ ጀርባ ያለው መሠረታዊ ሥርዓት ምንድን ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
14 ማቴዎስ 5:27, 28ን አንብብ። “አታመንዝር።” ከዚህ ሕግ በስተ ጀርባ ያለው መሠረታዊ ሥርዓት ምንድን ነው? ይሖዋ የፆታ ብልግናን ብቻ ሳይሆን ወደዚያ ሊመሩ የሚችሉ ሐሳቦችንም ይጠላል። ኢየሱስ አንድ ባለትዳር ከሚስቱ ውጭ ሌላን ሴት በፍትወት ስሜት የሚመለከት ከሆነ ኃጢአት እንደሚሆንበት ተናግሯል። ስለዚህ ምንም ያህል ከፍተኛ ጥረት ቢጠይቅብን ሥነ ምግባር የጎደላቸውን ሐሳቦች ከአእምሯችን ማስወገድ ይኖርብናል። (ማቴ. 5:29, 30) ይህ መሠረታዊ ሥርዓት ላላገቡ ክርስቲያኖችም ይሠራል።
15. በማቴዎስ 5:27, 28 ላይ የሚገኘውን መሠረታዊ ሥርዓት በዛሬው ጊዜ በሥራ ላይ ማዋል የምንችለው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
15 በማቴዎስ 5:27, 28 ላይ የሚገኘውን መሠረታዊ ሥርዓት በዛሬው ጊዜ ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? የብልግና ምኞቶችን ከአእምሯችን ማስወገድ ይኖርብናል። (2 ሳሙ. 11:2-4፤ ኢዮብ 31:1-3) ከዚህ አንጻር፣ የጎለመሱ ክርስቲያኖች ከማንኛውም ዓይነት ፖርኖግራፊ ይርቃሉ። ‘ድርጊቱን እስካልፈጸምኩት ድረስ ባየው ችግር የለውም’ ብለው ሰበብ አያቀርቡም። ወይም ደግሞ በዓለም ላይ እንዳሉ ሰዎች፣ አንዳንድ የፖርኖግራፊ ዓይነቶች የሌሎቹን ያህል የከፉ እንዳልሆኑ አድርገው አያስቡም። በኢየሱስ ዘመን የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች፣ ፊልሞች ወይም ፎቶግራፎች አልነበሩም። ሆኖም ኢየሱስ የተናገረው መሠረታዊ ሥርዓት ይሖዋ በእነዚህ ዘመናዊ መሣሪያዎች ላይ ስለሚታዩ ነገሮች ያለውን አመለካከት እንድናውቅ ይረዳናል። የብልግና ፎቶዎችን ወይም ቪዲዮዎችን ለሌሎች ብንልክ አሊያም ደግሞ እንዲህ ስላሉ ነገሮች በስልክ ወይም በጽሑፍ መልእክት አማካኝነት ብናወራ ይሖዋ በጣም እንደሚያዝንብን ያስገነዝበናል። ባለትዳሮች ይህን መሠረታዊ ሥርዓት በሥራ ላይ ማዋላቸው በትዳር አጋራቸው ላይ ክህደት እንዳይፈጽሙ ይረዳቸዋል። (ሚል. 2:15) በተጨማሪም ይህ መሠረታዊ ሥርዓት ያገቡም ሆኑ ያላገቡ ክርስቲያኖች ወደ ፆታ ብልግና የሚመራ ምንም ነገር ከማድረግ እንዲቆጠቡ ይረዳቸዋል።—ምሳሌ 5:3-14
(አንቀጽ 14-15ን ተመልከት)
16. በማቴዎስ 5:43, 44 ላይ ከተጠቀሰው ሕግ በስተ ጀርባ ያለው መሠረታዊ ሥርዓት ምንድን ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
16 ማቴዎስ 5:43, 44ን አንብብ። “ባልንጀራህን ውደድ።” ከዚህ ሕግ በስተ ጀርባ ያለው መሠረታዊ ሥርዓት ምንድን ነው? ይሖዋ ሁሉንም ሰው እንደ ባልንጀራችን እንድንቆጥርና እንድንወድ ይፈልጋል። የሚያሳዝነው በኢየሱስ ዘመን የነበሩት አይሁዳውያን ይህን ሕግ በተሳሳተ መንገድ ተረድተውት ነበር። የሚጠበቅባቸው ባልንጀሮቻቸውን እንዲወዱ ስለሆነ ጠላቶቻቸውን መጥላት እንደሚችሉ ተሰምቷቸዋል። ኢየሱስ ግን የሕጉ ዓላማ ይህ እንዳልሆነ ያውቅ ነበር። አፍቃሪ የሆነው አባቱ ዘር፣ ብሔር ሳንለይ ሁሉንም ሰው እንደ ባልንጀራችን እንድንቆጥር እንደሚፈልግ ያውቃል።—ማቴ. 5:45-48
17. በማቴዎስ 5:43, 44 ላይ የሚገኘውን መሠረታዊ ሥርዓት በሥራ ላይ ማዋላችን የሚጠቅመን እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
17 በማቴዎስ 5:43, 44 ላይ የሚገኘውን መሠረታዊ ሥርዓት በዛሬው ጊዜ ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ባልንጀራችንን የምንወድ ከሆነ በዓለም ላይ በሚካሄዱ ጦርነቶችና ግጭቶች አንካፈልም። (ኢሳ. 2:4፤ ሚክ. 4:3) ለባልንጀራችን ያለን ፍቅር ከእኛ የተለየ ዘር፣ ብሔር ወይም ሃይማኖት ላላቸው ሰዎች ደግነት ለማሳየት ያነሳሳናል። (ሥራ 10:34, 35) በተጨማሪም በእኛም ሆነ በምንወዳቸው ሰዎች ላይ በደል ያደረሱ ሰዎችን ይቅር እንድንል ይረዳናል።—ማቴ. 18:21, 22፤ ማር. 11:25፤ ሉቃስ 17:3, 4
(አንቀጽ 16-17ን ተመልከት)
በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ለመመራት ቁርጥ ውሳኔ አድርግ
18. (ሀ) ቁርጥ ውሳኔያችን ምን ሊሆን ይገባል? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?
18 ይሖዋ እንደ ትናንሽ ልጆች ሳይሆን እንደ ጎልማሳ ሰዎች የሚይዘን በመሆኑ ምንኛ አመስጋኞች ነን! በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ውሳኔዎችን ስናደርግ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በሥራ ላይ እንድናውል ይፈልጋል። (1 ቆሮ. 14:20) እነዚህን ውሳኔዎች በምናደርግበት ወቅት “የይሖዋ ፈቃድ ምን እንደሆነ [ለማስተዋል]” ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። (ኤፌ. 5:17) ከይሖዋ ፈቃድ ጋር የሚስማማ ውሳኔ ለማድረግ የሚረዳን ለእሱ ያለን ፍቅር ነው እንጂ ይቀጣናል የሚል ፍርሃት አይደለም። ይሖዋ በዚህ ረገድ የሚረዳን ሌላ ስጦታም ሰጥቶናል፤ እሱም ሕሊናችን ነው። በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ ስለዚህ ጉዳይ እንመለከታለን።
መዝሙር 95 ብርሃኑ እየደመቀ ነው
a ክርስቲያኖች የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በጥንቃቄ ማመዛዘን ይጠበቅባቸዋል። የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች እርስ በርስ ያላቸውን ተዛማጅነትም ሆነ ከምናደርገው ውሳኔ ጋር የሚገናኙት እንዴት እንደሆነ መረዳት ይኖርብናል። አምላክ የሰጠንን የማመዛዘን ችሎታ ተጠቅመን የይሖዋን ሞገስና በረከት የሚያስገኝ ሚዛናዊ ውሳኔ ማድረግ እንችላለን። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩ ከአይሁድ እምነት የመጡ ክርስቲያኖች ይህ ትልቅ ለውጥ ነበር። ምክንያቱም ሕይወታቸውን ሲመሩ የኖሩት በዘር በተላለፉላቸው ዝርዝር ደንቦች ነው።