ከሰኔ 29–ሐምሌ 5, 2026
መዝሙር 131 “አምላክ ያጣመረውን”
ከትዳር አጋራችሁ ጋር ያላችሁን ጓደኝነት አጠናክሩ
“ከወንድም ይበልጥ የሚቀርብ ጓደኛ አለ።”—ምሳሌ 18:24
ዓላማ
ትዳር የሚሰምረው ባልና ሚስት እርስ በርስ የሚዋደዱና ሁለቱም ይሖዋን የሚወዱ ከሆነ ነው።
1. ጥሩ ጓደኞች የይሖዋ ስጦታ ናቸው የምንለው ለምንድን ነው?
ጥሩ ጓደኞች የይሖዋ ስጦታ ናቸው። (ያዕ. 1:17) ለይሖዋም ለእኛም ፍቅር አላቸው። በደስታችንም በሐዘናችንም ከጎናችን ይሆናሉ። ምክር በሚያስፈልገን ጊዜም ትክክለኛውን ምክር በሐቀኝነት ይሰጡናል። እንዲሁም እምነት ልንጥልባቸው እንችላለን። እንዲህ ያሉት ጓደኞች “ልብን ደስ ያሰኛሉ”!—ምሳሌ 27:9
2. ባለትዳሮች ጓደኝነታቸውን ማጠናከራቸው አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ማቴዎስ 19:6)
2 ባልና ሚስት የቅርብ ጓደኛሞች መሆናቸው በጣም አስፈላጊ ነው። እንዲህ ያለው ጓደኝነት በራሱ የሚመጣ ነገር አይደለም፤ ሥራ ይጠይቃል። ባለትዳሮች ጓደኝነታቸውን ችላ ካሉት የብቸኝነት ስሜት ሊሰማቸው፣ ደስታ ሊርቃቸው፣ ይባስ ብሎም ብስጩ ሊሆኑ ይችላሉ። ጓደኝነታቸውን ከተንከባከቡት ግን በሁለት ሰዎች መካከል ሊኖር የሚችለውን እጅግ የቀረበ ወዳጅነት ማጣጣም ይችላሉ። (ማቴዎስ 19:6ን አንብብ።) በዚህ ርዕስ ውስጥ ባለትዳሮች ጓደኝነታቸውን እያጠናከሩ መሄድ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን። በቅድሚያ ግን ያላገቡ ክርስቲያኖች የዕድሜ ልክ ጓደኛ የሚሆናቸውን ሰው ማግኘት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ እንመልከት።
የዕድሜ ልክ ጓደኛ የሚሆን ሰው ማግኘት
3-4. ጥሩ የትዳር አጋር ለማግኘት ምን ይረዳናል? (ምሳሌ 18:22)
3 ማንኛውንም ትልቅ ውሳኔ ከማድረጋችን በፊት ጥቅሙንና ጉዳቱን በጥንቃቄ ማመዛዘን ያስፈልገናል። ምክንያቱም እንዲህ ያሉት ውሳኔዎች ውጤታቸው ዘላቂ ነው።
4 በሕይወታችን ውስጥ ልናደርጋቸው ከምንችላቸው በጣም ትልቅ ውሳኔዎች አንዱ የዕድሜ ልክ ጓደኛ ማለትም የትዳር አጋር መምረጥ ነው። የትዳር ዝግጅትን የመሠረተው ይሖዋ እንደመሆኑ መጠን የትዳር ጓደኛ ከመምረጣችን በፊት ከይሖዋ ምክር ለማግኘት መጣራችን ተገቢ ነው። ይሖዋ ለማግባት የሚያስቡ ክርስቲያኖች ተስማሚ የትዳር ጓደኛ እንዲያገኙ ይፈልጋል። ደግሞም ምንጊዜም የሚበጀንን ያውቃል። (ምሳሌ 18:22ን አንብብ፤ ኢሳ. 48:17, 18) በቃሉ ውስጥ ያሉት መሠረታዊ ሥርዓቶች ተስማሚ የትዳር አጋር ለማግኘት ይረዱናል።
5. የትዳር ጓደኛ መፈለግ ያለብን ከተጠመቁ ክርስቲያኖች መካከል መሆን ያለበት ለምንድን ነው?
5 ስንጠመቅ የይሖዋ ወዳጆች ሆነናል። (መዝ. 25:14) ስለዚህ ለማግባት እያሰባችሁ ከሆነ የትዳር ጓደኛ መምረጥ ያለባችሁ ከይሖዋ ወዳጆች መካከል ነው። (1 ቆሮ. 7:39) እንዲህ ካደረጋችሁ የትዳር ጓደኛችሁ ከይሖዋ ያገኛችሁት ስጦታ እንደሆነ መተማመን ትችላላችሁ፤ ከይሖዋ ወዳጆች መካከል የትዳር ጓደኛ መምረጣችሁ ለእሱ መሥፈርቶች አክብሮት እንዳላችሁ ያሳያል። (ምሳሌ 19:14) በተጨማሪም ከማያምን ሰው ጋር ‘አቻ ባልሆነ መንገድ መጠመድ’ ከሚያስከትላቸው መዘዞች ይጠብቃችኋል። (2 ቆሮ. 6:14) ከእምነት አጋሮቻችን መካከል የሚሆነኝ ሰው አላገኘሁም የሚል ሰበብ በማቅረብ ከማያምን ሰው ጋር መጠናናት መጀመር የሞኝነት ድርጊት ነው። በሌላ በኩል ደግሞ በኋላ ላይ እውነትን ሊቀበል ይችላል ብሎ በማሰብ እንዲህ ዓይነት ግንኙነት ውስጥ መግባት ተገቢ አይደለም።
6-7. በምትጠናኑበት ወቅት ለየትኞቹ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት ያስፈልጋችኋል?
6 እርግጥ ነው፣ አንድ ሰው ስለተጠመቀ ብቻ ተስማሚ የትዳር ጓደኛ ይሆናል ማለት አይደለም። ለትዳር ካሰባችሁት ሰው ጋር በተያያዘ በሰከነ መንፈስ የሚከተሉትን ጥያቄዎችa ለመመለስ ሞክሩ፦ ‘ከቤተሰቡ ጋር ያለው ግንኙነት ምን ይመስላል? አሳቢና ሰው አክባሪ ነው? ጓደኞቹ እነማን ናቸው? አለመግባባት ሲፈጠር ምን ያደርጋል? እኔ ያልኩት ካልሆነ ብሎ ድርቅ ይላል ወይስ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት እስካልተጣሰ ድረስ የራሱን አመለካከት ለመተው ፈቃደኛ ይሆናል? ለገንዘብ ያለው አመለካከትስ ምን ዓይነት ነው?’
7 በተጨማሪም ራሳችሁን እንዲህ ብላችሁ መጠየቅ ትችላላችሁ፦ ‘ጓደኛዬ ይሖዋን ከልቡ ይወደዋል? “አዲሱን ስብዕና” እየለበሰ ነው? ይሖዋን ይበልጥ እንዳገለግል ያበረታታኛል? መንፈሳዊ ግቦቻችን ተመሳሳይ ናቸው? እንዲሁ ጓደኛሞች ከመሆን ባለፈ የልብ ወዳጄ ላደርገው እችላለሁ?’ (ቆላ. 3:9, 10) እህቶች፣ ልታገቡት ያሰባችሁት ሰው ጥሩ ጓደኛ ብቻ ሳይሆን ጥሩ የቤተሰብ ራስም መሆን ይችላል? (1 ቆሮ. 11:3) ወንድሞች ደግሞ እንዲህ ብላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ፦ ‘ላገባት ያሰብኳት እህት እንከኖቼን ችላ ለራስነት ሥልጣኔ ለመገዛት ፈቃደኛ ነች?’ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ጊዜ ይጠይቃል። ስለዚህ በምትጠናኑበት ወቅት በደንብ ተዋወቁ።
8-9. በመጠናናት ላይ ያሉ ሰዎች ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ ምን ይረዳቸዋል? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
8 ጥሩ ውሳኔ ማድረግ የምትችሉት በምትጠናኑበት ወቅት ስለ ግለሰቡ ትክክለኛ ማንነት በሚገባ ለማወቅ ጥረት ካደረጋችሁ ነው። ሌሎች ሰዎች ስለ ጓደኛችሁ ምን ዓይነት አመለካከት እንዳላቸው ለማወቅ ሞክሩ። ስላተረፈው ስምና ስለ ባሕርያቱ ልትጠይቋቸው ትችላላችሁ። ለምሳሌ በትሕትናው፣ በደግነቱ ወይም በምክንያታዊነቱ የሚታወቅ ሰው ነው? በፍሬንች ጊያና የምትኖረው ሣራ፣ ዳንኤልን ከማግባቷ በፊት ስለ እሱ በደንብ ለማወቅ ጥረት አድርጋ ነበር። እንዲህ ብላለች፦ “ስለ ዳንኤል ብዙ ሰው አማክሬያለሁ፤ ከዳንኤል ጋር አብሮ የኖረና አብሮት በአቅኚነት ያገለገለ ወንድም፣ የዳንኤል ጉባኤ ሽማግሌ፣ ሁለታችንንም የሚያውቁ ጓደኞቻችን እንዲሁም ጉባኤው ውስጥ ያሉ እህቶች ስለ እሱ እንዲነግሩኝ ጠየቅኳቸው።” ሌላም ማድረግ የምትችሉት ነገር አለ። ከቀድሞ ሕይወቱ ወይም አሁን እያጋጠሙት ካሉት ነገሮች ጋር በተያያዘ ማወቅ ያለባችሁ ነገር ይኖር እንደሆነ ራሱን ግለሰቡን በደግነት ልትጠይቁት ትችላላችሁ። ምክንያቱም አንዳንድ ሁኔታዎች ወይም ልማዶች በኋላ ላይ በትዳራችሁ ውስጥ ከባድ ችግር ሊፈጥሩ ይችላሉ።
9 በጣም የከነከናችሁ ነገር ካለ ወይም የጎለመሱ ወዳጆቻችሁ ለትዳር ስላሰባችሁት ሰው በሐቀኝነት የነገሯችሁ አሳሳቢ ነገር ካለ ጉዳዩን ችላ ብላችሁ አትለፉት። ይህም ግንኙነቱን ልቀጥል ወይስ ላቋርጥ የሚለውን ለመወሰን ይረዳችኋል።b ከዚህ በመቀጠል ደግሞ ትኩረታችንን ባለትዳሮች ላይ እናደርጋለን።
ስትጠናኑ የግለሰቡን ትክክለኛ ማንነት ለማወቅ ጥረት አድርጉ (አንቀጽ 8-9ን ተመልከት)
አብራችሁ ጊዜ በማሳለፍ ጓደኝነታችሁን አጠናክሩ
10. ባልና ሚስት አብረው ጊዜ ማሳለፋቸው ጥሩ የሆነው ለምንድን ነው?
10 ባልና ሚስት አብረው ጊዜ ማሳለፋቸው ጓደኝነታቸውንና ትዳራቸውን ያጠናክረዋል። ምንም ያህል ሕይወታቸው በሥራ የተወጠረ ቢሆን ለዚህ ጊዜ ሊያጡ አይገባም። አብረው ጊዜ ማሳለፋቸው በዕለቱ ውስጥ ስላጋጠማቸው ነገር ለማውራት፣ የሆድ የሆዳቸውን ለመጨዋወት፣ ፍቅራቸውን ለመግለጽ፣ አንዳንዴም ዘና ለማለት ያስችላቸዋል።
11. በባልና በሚስት መካከል ያለው ጓደኝነት ምን አደጋ ሊያጋጥመው ይችላል?
11 የልብ ጓደኛሞች የሆኑ ባልና ሚስት መራራቅ አይፈልጉም። እርግጥ ነው፣ ለተወሰነ ጊዜ መራራቅ የሚጠይቅ ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። ሆኖም ለረጅም ጊዜ ተራርቆ መቆየት አደገኛ ነው። ለምሳሌ አንዳንዶች ለሥራ ወደ ሌላ አገር በመሄዳቸው ረዘም ላለ ጊዜ ከቤተሰባቸው ርቀው ለመቆየት ተገደዋል። እንዲህ ማድረጋቸው ገንዘብ ሊያስገኝላቸው ቢችልም ትዳራቸውን ለአደጋ ያጋልጠዋል።
12-13. (ሀ) አንዳንድ ክርስቲያን ባለትዳሮች አብረው ጊዜ ለማሳለፍ ምን አድርገዋል? (ሥዕሉንም ተመልከት።) (ለ) የትዳር ጓደኛችሁ በሕይወታችሁ ውስጥ ምን ዓይነት ቦታ ሊኖረው ይገባል? (“የትዳር ጓደኛችን በሕይወታችን ውስጥ ያለው ቦታ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)
12 አንዳንድ ባለትዳሮች አዘውትረው አብረው ጊዜ ለማሳለፍ ምን እንዳደረጉ እስቲ እንመልከት። በጉዋም የምትኖረው ሊያ እንዲህ ብላለች፦ “እኔና ባለቤቴ የተለያዩ ነገሮችን አብረን ማድረግ ያስደስተናል። በተቻለ መጠን ግብዣዎች ላይ ለየብቻችን አንገኝም።” በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖረው ሮክሳን ደግሞ እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “ጊዜያችን በጣም የተጣበበ ስለሆነ ለሌሎች አስፈላጊ ነገሮች እንደምናደርገው ሁሉ አብረን ጊዜ ለማሳለፍም ፕሮግራም ማውጣት እንዳለብን ተገንዝበናል።” (ከአሞጽ 3:3 ግርጌ ጋር አወዳድር።) በፈረንሳይ የሚኖረው ዴሚየን እንዲህ ብሏል፦ “ሚስቴ ማከናወን የምትወዳቸውን ነገሮች ለመማርና ለመውደድ ጥረት አደርጋለሁ፤ እሷም እንደዛው።” (ማቴ. 7:12) በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖረው ኬቲ ደግሞ “አንዳንድ ጊዜ ስልካችን ትኩረታችንን እንዳይሰርቀው ሌላ ቦታ እናስቀምጠዋለን” ብላለች።
13 ከሁሉ በላይ ደግሞ በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች አብራችሁ ተካፈሉ። በፈረንሳይ የምትኖረው ሚርያም እንዲህ ስትል ተናግራለች፦ “በየቀኑ ጠዋት ላይ መጽሐፍ ቅዱስ ካነበብን በኋላ በወደድነውና ልንሠራበት ባሰብነው ነጥብ ላይ እንወያያለን። በዚህ መልኩ አብረን የምናሳልፈውን ጊዜ በጣም እወደዋለሁ። እንዲሁም አብረን መጸለያችን ባለቤቴ ለይሖዋ ምን ያህል ፍቅር እንዳለው ለመስማት ስለሚያስችለኝ በጣም ደስ ይለኛል።” ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ኬቲ ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “በአገልግሎት ላይ ስንሆን የትዳር ጓደኛችን እምነቱን ሲገልጽ የመስማት አጋጣሚ እናገኛለን። ይህ ደግሞ እርስ በርስ ያቀራርበናል። አንዳችን ከሌላው ለመማርም ያስችለናል። እኔና ባለቤቴ በአገልግሎት አብረን የምናሳልፈውን ጊዜ በጣም እንወደዋለን።”—ምሳሌ 27:17
አዘውትራችሁ አብራችሁ ጊዜ በማሳለፍ ጓደኝነታችሁን አጠናክሩ (አንቀጽ 12-13ን ተመልከት)
ችግሮች በሚያጋጥሟችሁ ጊዜም ጥምረታችሁን አጠናክሩ
14-15. ባልና ሚስት በትዳራቸው ውስጥ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ለመወጣት የቻሉትን ያህል ጥረት ማድረግ ያለባቸው ለምንድን ነው? በምሳሌ አስረዳ።
14 ባለትዳሮች ሁለቱም ፍጹማን ስላልሆኑ በትዳራቸው ውስጥ ችግር ያጋጥማቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ባለትዳሮች ‘በሥጋቸው ላይ መከራ እንደሚደርስባቸው’ በግልጽ ይናገራል። (1 ቆሮ. 7:28) ይህ አገላለጽ በትዳር ውስጥ ብዙ ጊዜ የሚያጋጥሙ ችግሮችን የሚያመለክት ነው። ጥሩ የሚባሉ ትዳሮችም እንኳ ችግር ያጋጥማቸዋል። ታዲያ እነዚህን ችግሮች በጋራ መጋፈጥና ጥምረታቸውን ጠብቀው መኖር ያለባቸው ለምንድን ነው?
15 እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት። አንድ ጥንታዊ ሕንፃ ወይም የሥነ ጥበብ ሥራ ጉዳት ቢደርስበት ባለቤቶቹ እንዲጠገን ማድረጋቸው አይቀርም። ለእድሳቱ ብዙ ገንዘብ ሊያፈሱ ይችላሉ፤ ሥራውም ዓመታት ይወስድ ይሆናል። ታዲያ ይህን ሁሉ ዋጋ የሚከፍሉት ለምንድን ነው? ይህ ሕንፃ ወይም የሥነ ጥበብ ሥራ ለእነሱ ውድ ንብረት ስለሆነ ነው። በተመሳሳይም ሁሉም ትዳሮች ውድ ናቸው። ጉዳት የደረሰበትን ሕንፃ ማደስ እንደሚቻለው ሁሉ ከባድ ችግር ያጋጠመውን ትዳርም መታደግ ይቻላል። ይህን ማድረግ ጊዜና ጥረት የሚጠይቅ ቢሆንም ባልና ሚስቱ ትዳራቸውን ለማጠናከርና ሳይለያዩ ለመቀጠል ጥረት ሲያደርጉ ይሖዋ ይደሰታል። (ሚል. 2:16) በዚህ መንገድ ትዳራቸው ላይ መሥራታቸው አንዳቸው ለሌላቸው፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ ለይሖዋ ፍቅርና አክብሮት እንዳላቸው ያሳያል።
16. በ1 ቆሮንቶስ 13:4-8ሀ መሠረት ባለትዳሮች ከባድ ችግር ሲያጋጥማቸው ምን ሊረዳቸው ይችላል? (ሥዕሉንና “ጓደኝነታችሁን ለማጠናከር የሚረዱ ሐሳቦች” የሚለውንም ሣጥን ተመልከት።)
16 በትዳራችሁ ውስጥ ችግር ካጋጠማችሁ ለመለያየት አትቸኩሉ። (1 ቆሮ. 7:10, 11) ከዚህ ይልቅ ራሳችሁን እንዲህ ብላችሁ ጠይቁ፦ ‘ጓደኝነታችንን ለማጠናከር ማድረግ የምችለው ነገር አለ?’ በተጨማሪም በ1 ቆሮንቶስ 13:4-8ሀ ላይ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፍቅር የሚናገረውን ሐሳብ አሰላስሉበት። (ጥቅሱን አንብብ።) እዚያ ውስጥ ከተጠቀሱት ባሕርያት መካከል ማሻሻል የሚገባችሁ ባሕርይ ይኖር እንደሆነ ራሳችሁን ጠይቁ። ከትዳሩ መገላገል የምትችሉበትን መንገድ ከመፈለግ ይልቅ እርስ በርስ መቀራረብ የምትችሉበትን መንገድ ፈልጉ። ከዚህም ሌላ የትዳር ጓደኛችሁ ማድረግ ባለበት ነገር ላይ ከማተኮር ይልቅ ትዳሩን ለመታደግ እኔ ምን ማድረግ እችላለሁ በሚለው ላይ አተኩሩ። ይሖዋ እንዲረዳችሁ ጸልዩ። በጽሑፎቻችን እና በቪዲዮዎቻችን ላይ ምርምር አድርጉ። እንዲሁም ሽማግሌዎችና ሌሎች የጎለመሱ ክርስቲያኖች ምክር እንዲሰጧችሁ ጠይቁ። በትዳራችሁ ውስጥ ሦስተኛውና ጠንካራው ገመድ በሆነው በይሖዋ ታመኑ፤ እንዲህ ካደረጋችሁ ትዳራችሁ “ቶሎ አይበጠስም።”—መክ. 4:12
በትዳራችሁ ውስጥ ችግሮች በሚያጋጥሟችሁ ጊዜም ጥምረታችሁን አጠናክሩ (አንቀጽ 16ን ተመልከት)
17. ለማግባት እያሰቡ ያሉም ሆኑ ባለትዳሮች ደስተኛ መሆን የሚችሉት እንዴት ነው?
17 ይሖዋ ሁሉም አገልጋዮቹ ደስተኛ እንዲሆኑ ይፈልጋል፤ ይህም ለማግባት እያሰቡ ያሉትንና ባለትዳሮችን ይጨምራል። እንግዲያው ለማግባት እያሰባችሁ ከሆነ የዕድሜ ልክ ጓደኛ የሚሆናችሁን ሰው በጥበብ ምረጡ። ባለትዳሮች ከሆናችሁ ደግሞ ከትዳር አጋራችሁ ጋር ያላችሁን ጓደኝነት ማጠናከራችሁን ቀጥሉ። በትዳራችሁ ውስጥ የሚያጋጥሟችሁን ችግሮች ለመወጣት አብራችሁ ሥሩ። እንዲሁም ይሖዋ በሚሰጣችሁ እርዳታ ታመኑ። እንዲህ ካደረጋችሁ ከዕድሜ ልክ ጓደኛችሁ ጋር ‘ተደስታችሁ ትኖራላችሁ!’—መክ. 9:9
መዝሙር 132 አንድ ሆነናል
a ወንዶችም ሆኑ ሴቶች እነዚህን ጥያቄዎች መጠየቅ ይኖርባቸዋል።